ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
5.85K subscribers
1.06K photos
7 videos
37 files
247 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
🌻††† እንኳን ለቅድስት ጾመ ፍልሠታ ለማርያም እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅድስት ጾመ ፍልሠታ ለማርያም †††

††† ቸር #እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠው ጸጋ አንዱ #ጾም ነው:: የሰው ልጅ ከፈጣሪው ክብር እንዲደረግለት ክፋትን መስራት የለበትም:: መልካም መሆንም ይጠበቅበታል:: ለዚህ ምንጮቹ ደግሞ ጾም: ጸሎትና ስግደት ናቸው:: ያለ እነዚህ ምግባራት መቼም ወደ #ጽድቅ መድረስ አይቻልም::

ይቅርና እኛ ክፉዎቹ የሰማይና የምድር ፈጣሪ: የክብር ሁሉ ባለቤት ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሥጋችንን በተዋሐደ ጊዜ የመጀመሪያ ሥራው ያደረገው ጾምን ነው:: ስለዚህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን 7 አጽዋማትን በጉባዔ ሠርታ: በአዋጅ እንዲጾሙ ታደርጋለች:: ከእነዚህም አንዱ ጾመ ፍልሠታ ነው::

"ፈለሠ" - ሔደ: ተጉዋዘ እንደ ማለት ሲሆን " #ፍልሠታ" ማለት የእመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያምን የዕርገት ጉዞ የሚያዘክር ቃል ነው:: #እመ_ብርሃን በዚህ ዓለም ለ64 ዓመታት ኑራ ካረፈች በሁዋላ ሥጋዋ እንደ እኛ አልፈረሰም::

ለጊዜው በዕጸ ሕይወት ሥር ቆይታ እንደ ልጇ ትንሳኤ ተነስታ ዐርጋለች:: እርሷ በሁሉ ነገሯ ቀዳሚና መሪ ናትና:: ጾመ ፍልሠታን የጀመሩት አበው #ሐዋርያት ሲሆኑ እንድትጾምም ሥርዓት የሠሩ ራሳቸው ናቸው:: ከ7ቱ አጽዋማትም እጅግ ተወዳጅና እየተናፈቀች የምትፈጸም ናት::

ካህናትና ምዕመናንም ጾሟን እንደየአቅማቸው ክብር በሚያሰጥ መንገድ ይፈጽሟታል::
*የቻሉ ወደ ገዳማት ሔደው ጥሬ እየቆረጠሙ: ውሃ እየተጐነጩ ክብርን ያገኛሉ::
*ሌሎቹ ደግሞ ባሉበት ደብር አካባቢ እያደሩ ሌሊት ሰዓታቱን: በነግህ ኪዳኑንና ውዳሴ ማርያም ትርጉዋሜውን: በሰርክ ደግሞ ቅዳሴውን ይሳተፋሉ::
*የኔ ብጤ ደካማ ደግሞ ጠዋት ማታ ወደ ደጇ እየተመላለሰ "አደራሽን ድንግል" ይላታል::

††† በእርሷ አምነን አፍረን አናውቅምና ነጋ መሸ ሳንል እንማጸናታለን::

††† #ጽንዕት_በድንግልና: #ሥርጉት_በቅድስና #እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን: ልበለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን:: <3
*ጾሙን የፍሬ: የትሩፋትና የበረከት ያድርግልን::*

††† ቅዱሳን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ †††

††† እጅግ የተወደዱ: ሞገስ የሞላላቸውና ፈጣሪያቸውን በክብር ገንዘው የቀበሩ አባቶች ናቸው::

††† ቅዱስ ዮሴፍ ዘአርማትያስ †††

††† ቅዱሱ በእሥራኤል ምድር ተወልዶ ያደገ: ኦሪትን የተማረ ባለጠጋ ሰው ነው:: የተማረ ደግ ሰው ነውና የክርስቶስን መምጣት በተስፋ ይጠብቅ ነበር:: ባገኘውም ጊዜ በአዳኝነቱ (በመሲህነቱ) አምኖ በስውር ተከታዩ ነበር::

††† ቅዱስ ኒቆዲሞስ †††

††† ወንጌል እንደሚነግረን ይህ ሰው የአይሁድ አለቃ: መምሕር: ዳኛ እና ሃብታም ሰው ነበር:: እነዚህ ሁሉ ማነቆዎች ግን እርሱን ከፈጣሪው ሊያስቀሩት አልቻሉም:: ሌሊት እየመጣ ከጌታችን እግር ይማር ዘንድም አድሎታል:: በመካከልም ከአይሁድ ጋር ብዙ ተጋጭቷል::

ሁለቱ አባቶች መድኃኒታችን ስለ እኛ ሲል ሞቶ ባለበት ሰዓት ላይ በእርሱ የደረሰ ይደርስብናል ሳይሉ በድፍረት ሥጋውን ከዺላጦስ ተካሠው ለመኑ:: እንባቸው በፊታቸው እየወረደ ከመስቀል አውርደው በዮሴፍ በፍታና በኒቆዲሞስ ሽቱ ገነዙት::

እንዲህ እያሉ:-
"ሙታንን የምታስነሳ ጌታ አንተ ሞትክን?! ደካሞችን የምታጸና ቸር አንተ ደከምክን?!"
*በዚያች ሰዓት ጐልጐታ አካባቢ ዝማሬ መላእክትን እየሰሙ የክብር ባለቤትን ቀብረውታል:: ጌታችንም ከተነሳ በሁዋላ በንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::

"እየሳማችሁ አክብራችሁ እንደ ገነዛችሁኝ እኔም በሰማይ በእንቁ ዙፋን ላይ አስቀምጣቹሃለሁ" ብሏቸዋል:: "አነ አብረክሙ ዲበ መንበረ ሶፎር" እንዲል:: ጻድቃን አበው ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በተረፈ ዘመናቸው ወንጌልን ሰብከው: ከአይሁድ መከራን ታግሰው: በበጐ ሽምግልና ዐርፈዋል::

††† ቅዱስ አቦሊ ሰማዕት †††

††† ቅዱስ አቦሊ የሰማዕታቱ #ቅዱስ_ዮስጦስና #ቅድስት_ታውክልያ ልጅ ሲሆን በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ያበራ የቤተ ክርስቲያን ዕንቁ ሰማዕት ነው:: የሚገርመኝ ሦስቱ የግማሹ ዓለም አስተዳዳሪዎች ነበሩ:: ዮስጦስ ንጉሥ: ታውክልያ ንግሥት: አቦሊ ደግሞ ልዑል ነው::

ነገር ግን ይህንን ክብራቸውን #በክርስቶስ ፍቅር ጐን: ሚዛን ላይ ቢያኖሩት በጣም ቀሎ ታያቸው:: 3ቱም ከዙፋናቸው ወርደው: ወገባቸውንም ታጥቀው: ባሮቻቸው በነበሩ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ብዙ ተንገላቱ:: መራራ ሞትንም ታገሱ::

በተለይ ቅዱስ አቦሊ ከአንጾኪያ ወደ ግብጽ (ብስጣ) ይዘው አምጥተው ክርስትናውን እንዲተው ያላደረጉት የለም:: በቁሙ ቆዳውን ገፈው: በቆዳው አቅማዳ ሰፍተው: ያንንም አሸክመው: የተገፈፈ አካሉን ጨውና ኮምጣጤ እየቀቡ አዙረውታል::

እርሱ ግን ጌታ በላከለት ድንቅ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ረዳትነት ሁሉን ችሎታል:: በዘመኑ ብዙ ተአምራትን የሠራ ሲሆን አንድ ጊዜ ቤት ተንዶ 16 ሰዎች ቢያልቁ የተገፈፈ ቆዳውን እየጣለባቸው ተነስተዋል:: በተአምራቱና በተጋድሎውም ብዙ ሺህ አሕዛብን ለክርስትና: ብሎም ለሰማዕትነት አብቅቷል::

እርሱም ከብዙ የመከራ ጊዜያት በሁዋላ በዚህች ቀን አንገቱን ተከልሏል:: ጌታችን "ዜናሕን የጻፈውን: ያነበበውንና የሰማውን ይቅር እለዋለሁ" ብሎ ቃል ኪዳንን ሰጥቶታል::

††† ፈጣሪ ከጻድቃንና ሰማዕታት በረከትን አይለይብን:: ወርሐ ነሐሴንም ለበረከት ይቀድስልን::

††† ነሐሴ 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በአተ ጾመ ፍልሠታ
2.አበው ሐዋርያት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
3.ቅዱስ አቦሊ ሰማዕት
4.ታላቁ ቅዱስ ዸላሞን ገዳማዊ
5.ቅድስት ሐና (የእመ ብርሃን እናት)
6.ቅድስት ሐና ነቢይት (ወለተ ፋኑኤል)
7.ደናግል ቅዱሳት (የንግስት ሶፍያ ልጆች)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

††† "የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ #ዮሴፍ የጌታ ኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ዺላጦስን ለመነ:: ዺላጦስም ፈቀደለት:: ስለዚህም መጥቶ የጌታ ኢየሱስን ሥጋ ወሰደ:: ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ #ጌታ_ኢየሱስ መጥቶ የነበረ #ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ:: የጌታ ኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት::" †††
(ዮሐ. 19:38)

††† "በጽዮን መለከትን ንፉ:: ጾምንም ቀድሱ:: ጉባዔውንም አውጁ:: ሕዝቡንም አከማቹ:: ማሕበሩንም ቀድሱ:: ሽማግሌዎችንም ሰብስቡ:: ሕጻናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ:: ሙሽራው ከእልፍኙ: ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ::" †††
(ኢዩ. 2:15)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://t.me/zikirekdusn
#ሐምሌ_20

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ በዚህች ቀን #እመቤታችን_ድንግል_ማርያም ከተወለደች በኋላ በሰማንያ ቀን ከርግብ ገላግልቶች ጋራ ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው፣ ታላቅና ክቡር የሆነው የሠራዊት አለቃ #ቅዱስ_ቴዎድሮስ በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#በዓታ_ለእግዝእትነ_ማርያም

ሐምሌ ሃያ በዚህች ቀን እመቤታችን #ድንግል_ማርያም ከተወለደች በኋላ በሰማንያ ቀን ከርግብ ገላግልቶች ጋራ ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው፣

ለስም አጠራሯ ክብር ይሁንና እመ ብርሃን #ድንግል_ማርያም በዚህች ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ገብታለች:: በዓሉ ከሰላሳ ሦስቱ የእመቤታችን በዓላት እንደ አንዱ አይቆጠርም:: ምክንያቱም ቅዱሳን ሊቃውንት በዓታ ከበዓታ ጋር ይስማማል ብለው የታኅሣሥ ሦስትን በዓል ከሰላሳ ሦስቱ ደምረውታል::

#እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ የገባችው ሁለት ጊዜ ሲሆን:-

1.ዛሬ የምናከብረውና በተወለደች በሰማንያ ቀኗ የገባችበት ነው:: (ከግንቦት 1 ጀምረን እናስላው 80 ቀን ይመጣል::)

ኦሪት እንዳዘዘው ቅዱሳን ኢያቄምና ሐና ንጽሕት ሕፃን #ድንግል_ማርያምን ታቅፈው የርግብ ልጆች (ግልገሎች) ዋኖስም ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሒደዋል::

ካህናቱ ዘካርያስና ስምዖን ወጥተው በደስታ ተቀብለዋቸዋል:: እመቤታችን ለወላጆቿ ማኅጸን የከፈተች በኩር ናትና በእግዚአብሔር ፊት አቅርበዋታል::

2.ከሦስት ዓመታት በኋላ እንደ ስዕለታቸው ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው #ለእግዚአብሔር ሰጥተዋት ተመልሰዋል::

#እግዚአብሔር ዛሬ ያልቃል ነገ ይደቃል የማይባለውን የድንግል እናቱን ፍቅር አብዝቶ ያድለን:: በረከቷም በእኛ ላይ ጸንቶ ይኑር::

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቴዎድሮስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ታላቅና ክቡር የሆነው የሠራዊት አለቃ ቅዱስ ቴዎድሮስ በሰማዕትነት ሞተ። የዚህ ቅዱስ አባት ስሙ ዮሐንስ ይባል ነበር። እርሱም ከላይኛው ግብጽ ሰጥብ ከምትባል መንደር ነበር። ወደ አንጾኪያ ከተማም ከሠራዊቱ ጋራ ወሰዱትና በዚያ ኖረ ከዚያች ከተማ መኳንንቶችም ያንዱን ልጅ አገባ እርሷም ጣዖትን ታመልክ ነበር። ባሏ ዮሐንስ የሚያመልከውን ግን አታውቅም ነበር።

ከዚህም በኋላ ይህን ቅዱስ ቴዎድሮስን በወለዱት ጊዜ እናቱ ወደ ጣዖቷ አቅርባ አምልኮትዋን ልታስተምረው ፈለገች አባቱ ግን አስተወው ስለዚህም ተቆጥታ ባሏ ዮሐንስን አባረረችው ሕፃኑ ቴዎድሮስም በእናቱ ዘንድ ቀረ።

አባቱ ዮሐንስም ልጁ ቴዎድሮስን ወደ እውነተኛ መንገድ ይመራው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ይጸልይና ይማልድ ነበር። ሕፃኑ ቴዎድሮስም በአደገ ጊዜ ጥበብን ተማረ ጌታችንም ልቡን ብሩህ አደረገለት ስሙ አውላኪስ ወደሚባል ኤጲስቆጶስም ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ። እናቱም ታላቅ ኅዘንን አዘነች።

ከዚህም በኋላ ስለ አባቱ በሕይወት እንዳለ ወይም እንደሌለ ጠየቀ ከአገልጋዮቹም አንዱ የአባቱን ሥራ በሥውር ነገረው። ቅዱስ ቴዎድሮስም ጐለመሰ እጅግም ብርቱ ሆነ ንጉሡም የሠራዊት አለቃ አድርጎ ሾመው።

የፋርስ ሰዎችንም ሊወጋቸው በወጣ ጊዜ ይህ ቅዱስ ቴዎድሮስ በረታ የፋርስ ንጉሥንም ልጅ ይዞ ማረከው ከእርሱም ጋር ምሥራቃዊው ቴዎድሮስ ነበር የፋርስንም ሠራዊት አሳደዱአቸው።

ከጥቂት ወራቶች በኋላም የፋርስና የበርበር ስዎች በሮማውያን ላይ ተነሡ። ብዙ ከተሞችንም አጠፉ ዲዮቅልጥያኖስም በሰማ ጊዜ እጅግ ፈራ ቴዎድሮስንም ጠርቶ ምን እናድርግ ሠራዊትህን ሁሉ የጦር መሣሪያህንም ሁሉ ይዘህ ወደ ሰልፍ ውጣ አለው።

ቅዱስ ቴዎድሮስም እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ የጦር መሣሪያህን ወስደህ ለአሽከሮችህ ስጣቸው እኔ ክብር ይግባውና በፈጣሪዬ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ርዳታ እተማመናለሁና የጦር መሣሪያ አልሻም እኔም ብቻዬን ወደ ጦርነቱ እሔዳለሁ ከወታደሮችም አንድ እንኳ ከእኔ ጋራ አልወስድም። በእጄ ውስጥ ያለ ይህ ጦር የተቀመጥኩበትም ፈረስ ይበቃኛል ከእኔ ጋራ የሚወጣ ፈጣሪዬ እርሱ ይረዳኛልና። ንጉሡም እነሆ ጠላቶቻችን ወደእኛ ቀርበዋልና የወደድከውን አድርግ አለው።

በማግሥቱም ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደ ሰልፍ ወጣ ንጉሡም የበርበርን ሰዎች ትወጋቸው ዘንድ ምን ኃይል አለህ እነርሱ ብዙ ወገኖች ናቸውና አለው። ቅዱሱም ለንጉሡ እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ ከሠራዊትህ ጋራ በዚህ ቁም እኔም ወደ እነርሱ ብቻዬን እሔዳለሁ በነርሱም ላይ የሚደርሰውን ታያለህ። እኔ በ #እግዚአብሔር ኃይል እንደማጠፋቸው አውቃለሁና። ከእነርሱም አንዱ እንኳ ወደቤቱ አይመለስም። ንጉሡም አደነቀ ከእርሱ ጋር ያሉትም አደነቁ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደ ጦርነቱ ብቻውን ሔደ ንጉሡንም ከእርሱ ሩቅ በሆነ ቦታ ተወው። ወደ በርበር ሰዎችም ደርሶ ትዋጋላችሁን ወይስ በሰላም ወደ አገራችሁ ትመለሳላችሁ አላቸው። እነርሱም ከአንተ በቀር ለሰልፍ የመጣ አናይምና ከማን ጋር እንዋጋለን አሉት እርሱም ማንም ከእኔ ጋር እንዲመጣ አልሻም። እኔ ብቻዬን በ #ፈጣሪዬ ኃይል አጠፋችኋለሁ አላቸው።

ምናልባት ውሻ ልታባርር መጥተህ ይሆናል ከፈቀድህ ግን ወደ አንተ ይመጣ ዘንድ ከእኛ ውስጥ አንዱን ምረጥና ሁለታችሁ ተጋጠሙ አሉት።

ያን ጊዜ ቅዱስ ቴዎድሮስ ከፈረሱ ላይ ወረደና ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ እንዲህ እያለ ጸለየ ጣዖታትን እስከ አጠፋቸውና የባቢሎንን ከተማ ዘንዶ እስከ ገደለው ድረስ ነቢዩ ዳንኤልን ያጸናኸው ጌታዬ አምላኬ ሆይ እንዲሁም ዛሬ ከእኔ ጋራ ሁን በረድኤትህም አጽናኝ #አብ_ወልድ_መንፈስ_ቅዱስ ሆይ ምስጋና ይገባሀል ለዘላለሙ አሜን።

ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ጦሩን አንሥቶ በላዩ በመስቀል ምልክት አማተበ በፈረሱ ላይም ተቀምጦ በበርበር ሰዎች ላይ እንዲህ እያለ ጮኸ እንዋጋ ዘንድ ወደኔ ኑ ክብር ይግባውና ለ #እግዚአብሔር_ኢየሱስ_ክርስቶስ እኔ ባሪያው ነኝ እንዲህም እያለ በመካከላቸው ገብቶ የበርበርን ሰዎች አጠፋቸው ከእነርሱም ፈረሰኛንም ሆነ እግረኛን ምንም አላስቀረም የመኳንንቶቻቸውንም ቸብቸቦ ቆርጦ ወደ ንጉሡ አቀረበ። ንጉሡም ተቀበለው ሠራዊቱም ሁሉ ሰገዱለት። የአንጾኪያም ከተማ ሰዎች ሁሉም ወጥተው የበርበርን አገር ማረኩ።

አውኪስጦስ በሚባል አገርም ሰዎች የሚያመልኩት ታላቅ ዘንዶ ነበረ ይበላቸውም ዘንድ በየዕለቱ ሁለት ሁለት ሰዎችን ይሰጡት ነበር ሁለት ልጆችም ያሏት አንዲት ክርስቲያናዊት መበለት ነበረች። እንዲበላቸውም ልጆችዋን ወሰደው ለዘንዶው አቀረቧቸው።

በዚያን ጊዜም ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደዚያ አገር ደረሰ ያች መበለትም በፊቱ ቆመች ልጆቿን ወስደው እንዲበላቸው ለዘንዶው እንዳቀረቧቸው በእርሷ ላይ የሆነውን ሁሉ አልቅሳ ነገረችው።

ክርስቲያን እንደሆነችም ባወቀ ጊዜ በልቡ ይችን ሴት በድለዋታል #እግዚአብሔርም ይበቀልላታል አለ። ወዲያውኑም ከፈረሱ ወረደና ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ጸለየ። ከዚህም በኋላ ወደ ዘንዶው ቀረበ የከተማው ሰዎችም ሁሉ ወደርሱ ይመለከቱ ነበር። በጦሩም ወግቶ ያንን ዘንዶ ገደለው። ርዝመቱም ሃያ አራት ክንድ ሆነ የመበለቷንም ልጆች አዳናቸው።

ከዚህም በኋላ አባቱን ይፈልገው ዘንድ ወደ ላይኛው ግብጽ ሔደ አባቱንም አገኘው አባቱም ልጁ እንደሆነ በምልክቶቹ አወቀው ቅዱሱም አባቱ እስከ አረፈ ድረስ በዚያ ኖረ።

ከዚህም በኋላ ወደ አንጾኪያ ከተማ ተመለሰ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስንም ክብር ይግባውና #ክርስቶስን እንደካደና ጣዖትን እንደአመለከ ክርስቲያኖችንም ሲአሠቃያቸው አገኘው።
በዚያ ወራትም የግብጽ ንጉሥ አብዶ አልዓዚዝ ወደ እስክንድርያ ከተማ መጣ ይህ አባት ሊቀ ጳጳሳት ስምዖንም ሊቀበለው ወጣ ንጉሡም በሊቀ ጳጳሳቱ ፊት ላይ የደዌ ምልክት አይቶ መሳፍንቶቹን መልኩ እንዲህ እስኪለወጥ ድረስ ሊቀ ጳጳሳቱ ምን ደረሰበት ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም ክፉዎች ካህናት በእርሱ ላይ እንዳደረጉበት መርዝንም እንዳበሉት ነገሩት ንጉሡም ተቆጣ ካህናቱንና መሠርያኑንም በእሳት እንዲአቃጥሏቸው አዘዘ ያን ጊዜም ይህ አባት ከንጉሡ እግር በታች ወድቆ ይምራቸው ዘንድ እያለቀሰ ለመነው ንጉሡም አይደለም እንደሚገባቸው ያቃጥሏቸው እንጂ አለው። ይህም አባት ስለእኔ አንተ ከአቃጠልካቸው ለእኔ ክህነትና ሊቀ ጵጵስና አይገባኝም አለው። ንጉሡም ሰምቶ ከየዋህነቱና ከርኅራኄው የተነሣ አደነቀ እነዚያን ካህናትና መሠርዮች ከእስክንድርያ እንዲያሳድዷቸው አዘዘ።

ንጉሡም ይህን አባት እጅግ ወደደው አከበረውም እንደወደደም አብያተ ክርስቲያናትን ገዳማትን ይሠራ ዘንድ ፈቀደለት። እርሱም በምስር ሰሜን አልዋህ በሚባል አገር አብያተ ክርስቲያን ሠራ በሹመቱም ዘመን ሌሎች ብዙዎችን ሠራ።

ካደረጋቸው ተአምራቶቹ ሌላው ይህ ነው ሚናስ የሚባል አንድ ቄስ ነበረ ሙቶ ከተገነዘ በኋላ በዚህ አባት ጸሎት ተነሣ። የመነሣቱ ምክንያትም እንዲህ ነበር ይህ አባት ስምዖን በመላው አብያተ ክርስቲያናት ንብረት ንዋየ ቅድሳትና አልባሳት ላይ መጋቢ አድርጎ ይጠብቅ ዘንድ ቄሱን ሾመው። ሁልጊዜም የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ በቤትህ ውስጥ አታኑር እያለ ያዝዘው ነበር።

ከዚህም በኋላ ድንገተኛ ደዌ አገኘውና አንደበቱና ጒረሮው ተጣጋ። ሊቀ ጳጳሳቱም ሰምቶ እጅግ አዘነ ስለ አቢያተ ክርስቲያናትም ንብረት ያንን ቄስ ከሞት ያድነው ዘንድ በዚያች ሌሊት እግዚአብሔርን እየለመነ መላዋን ሌሊት ለጸሎት ተጋ።

መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ያ ቄስ ለመሞት እንደተቃረበ ይህ አባት ሰምዖን ሰማ ስለ አቢያተ ክርስቲያናት ነብረት ይጠይቃት ዘንድ አዝዞ ወደ ቄሱ ሚስት ረዳቱን ላከ።

ወደ ቄሱ ቤትም በቀረበ ጊዜ ሰዎች እያለቀሱለት ጩኸታቸውን ሰማ በገባ ጊዜም ሙቶ ልብሰ ተክህኖ መጐናጸፊያ ሲያለብሱት በዐልጋ ላይም ሲያስተኙት ብዙዎችም በዙሪያው ሲያለቅሱ አገኛቸው ያም ረዳቱ የቄሱን በድን ሊሳለም ዘንበል አለ። ያን ጊዜም ያ የሞተው ቄስ ተነሥቶ አቀፈውና የክቡር አባ ስምዖን ፈጣሪ እግዚአብሔር ሕያው ነው አለው። ረዳቱም በርታ አትፍራ አለው። ቄሱም በጌታው በአባ ስምዖን ጸሎት አዎ በእውነት ጸናሁ እግዚአብሔር ሕይወትን ሰጥቶ ከሞት አስነሥቶኛልና አለ።

ያን ጊዜም ያ ረዳት ስለ መሞቱ ደንግጠው የነበሩትን ካህናት እነሆ ቄሱ ከሞት ተነሥቷል ብሎ ጠራቸው። ካህናቱና ሕዝቡም ወደርሱ በቀረቡ ጊዜ ቄሱ እንዲህ አላቸው እኔ ሙቼ እንደነበረ ዕወቁ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ዙፋን ፊት አቆሙኝ ከአባት ሐዋርያ ማርቆስ እስከ አባ ይስሐቅ ያሉትን ሁሉንም የጳጳሳት አለቆች ክብር ይግባውና በክርስቶስ ዙፋን ፊት ቁመው አየኋቸው እኔንም ከወንድማችን ከሊቀ ጳጳሳት ስምዖን የአብያተ ክርስቲያናትን ንብረት ለምን ሸሸግህ ብለው ገሠጹኝ። ያን ጊዜም ጌታ ክርስቶስ ይቺን ነፍስ በውጭ ወዳለ ጨለማ ውሰዱአት ብሎ አዘዘ።

ሊወስዱኝም በጐተቱኝ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ዙፋን ፊት የጳጳሳት አለቆች ሰገዱ እንዲህ እያሉም ማለዱ ይህን ሰው አንድ ጊዜ ማረው ንብረታቸውን ስለሚጠብቅላቸው አብያተ ክርስቲያናት ብሎ ወንድማችን ስምዖን ስለ እርሱ እነሆ ቁሞ ይጸልያልና። ጌታችንም ልመናቸውን ተቀብሎ ነፍሴን ወደ ሥጋዬ መለሰ እንዲህም አለኝ እነሆ ስለ ምርጦቼና ስለ ወንድማቸው ስለ ሊቀ ጳጳሳት ስምዖን ማርኩህ አንተም የአብያተ ክርስቲያናትንም ንብረት ግለጥለት። አለዚያ ግን ወደዚህ እመልስሃለሁ የእነዚህንም ልመናቸውን ስለአንተ ሁለተኛ አልቀበልም።

በዚያ የነበሩም ሰዎች ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ኀዘናቸውም ወደ ደስታ ተለወጠ ይህም ቄስ ይህን ተአምር ለሁሉ እየተናገረ ብዙ ዘመናት ኖረ።

ይህም አባት ስምዖን በበዐቱ ውስጥ በገድል የተጸመደ ሁኖ ኖረ መንጋዎቹንም ያስተምራቸው፣ ይገሥጻቸውና በቀናች ሃይማኖትም ያጸናቸው ነበር። ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ዘዮሐንስ_ጻድቅ_ዘክብራን_ገብርኤል (ኢትዮዽያዊ)

ዳግመኛም በዚህች ቀን ጣና ክብራን ገብርኤል ገዳምን የመሠረቱት አቡነ ዘዮሐንስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ይኸውም አባቱ ዘካርያስና እናቱ ሶፍያ #እግዚአብሔርን በማመን የተመሰገኑ ምግባር ሃይማኖታቸው የቀና ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የሀገር ሰዎችም መክረው ዘካርያስን በእነርሱ ላይ ጌታና ገዥ አደረጉት፡፡ እርሱም በጥሩ አገዛዝ በፍቅር ገዛቸው፡፡ እነርሱም እንደ አሽከሮች ሆኑት፣ እርሱም እስከ አማራ ጠረፍ ድረስ ለሸዋ ሰዎች እንደ ቸር እረኛ ሆናቸው፡፡ ዘካርያስና ሚስቱ ሶፍያም በጎ ሥራን ሁሉ አላቋጡም፡፡ ምጽዋትን መስጠትን፣ ከገንዘባቸውም ከፍለው ለ #እግዚአብሔር አሥራት መስጠትን አላቋረጡም፡፡ የተቸገሩትን፣ የተራቡትንና የተጠሙትን ሁሉ ያበላሉ፣ ያጠጣሉ፡፡ ይህንንም ሲሄዱም ሲመለሱም ሁልጊዜ ያደርጋሉ፡፡

#ጌታችንን_የኢየሱስ_ክርስቶስንና የቅድስት #ድንግል_ማርያምን፣ የ #ጻድቃንና#ሰማዕታን መታሰቢያም ያድርጋሉ፡፡ ልጅም አልነበራቸውምና ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ይማፀኑ ነበር፡፡ ሶፍያም ጠዋት ማታ እንዲህ እያለች ትጸልይ ነበር፡- ‹መካን ለነበረች ለሐና ልጅ እንደሰጠኻት፣ ለአብርሃም ሚስት ለሣራም፣ ለጸጋ ዘአብ ሚስት እግዚእ ኀረያም እንደሰጠኻቸው አቤቱ እንደ እነርሱ አንተን ደስ የሚያሰኝህን ልጅ ስጠኝ› እያለች #እመቤታችንንም እየተማፀነች ታለቅስ ነበር፡፡ #እግዚአብሔርም መጥምቁ ዮሐንስን የመሰለ ልጅ ‹አባ ዘዮሐንስ› የተባለ ቅዱስ ልጅ ሰጣቸው፡፡ እሱም በሸዋ፣ በመራቤቴ እስከ አማራ ጠረፍ ድረስ የሚያበራ መብራት ሆነ፡፡››

በኋላም በጣና ሐይቅ ላይ የሚገኘውን ‹‹ክብራን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን›› የመሠረቱት እኚህ አባ ዘዮሐንስ የተባሉ ጻዲቅ ናቸው፡፡

ለአባ ዘዮሐንስ በጌታ ዘንድ ታዘው ነቢዩ ኤልያስና ዮሐንስ በእኩለ ሌሊት ተገልጠውላቸው አስኬማና ቆብ ሰጥተዋቸዋል፡፡ #እመቤታችንም ተገልጣላቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው እንዲመነኩሱ ነግራቸው ኤልያስና ዮሐንስ እየመሩ ከቦታው አድርሰዋቸዋል፡፡ ሰባት ዓመትም በዚያ ሲያገለግሉ ኖሩ፡፡ ስግደታቸውም ሁልጊዜ ስምንት ሺህ ነበር፡፡ ጌታም በደብሊባኖስ ሲያጥኑ ተገልጦላቸው ስምህ ‹‹ዘዮሐንስ ይሁን›› ብሎ ትልቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ ደመናም ተሸክማ ወስዳ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም አድርሳቸው በዚያም ከቆዩ በኋላ ደመናዋ መልሳ ወደ ሸዋ አምጥታቸዋለች፡፡ በትግራይ ለራሳቸው መጠለያ ሲሠሩ የ #ጌታ ፈቃድ አልነበረምና ከባድ የሆድ ሕመም መጣባቸው፡፡ ደመናዋም ደራ ሮቢት አደረሰቻቸው፡፡ በዚያም እንደደረሱ ገብርኤልና መስቀል ክብራ በሚባሉ #እግዚአብሔርን በሚወዱ ደጋግ ባለትዳሮች ቤት ዕረፍት አደረጉ፤ ለሰባት ቀናትም በዚያ ቆዩ፡፡ ከዚያም መልአኩ ተገልጦ ወደ ደሴቷ እንዲሄዱና እርሷም ዕጣ ክፍላቸው እንደሆነች ነገራቸው፡፡
#ነሐሴ_1

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተባረከው #የነሐሴ_ወር_የቀኑ_ሰዓት_ዐሥራ_ሦስት ነው ከዚህም በኋላ ይጎድላል።
ነሐሴ አንድ በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናቷ #የቅድስት_ሐና መታሰቢያዋ ነው፣ የዮስጦስ ልጅ #ቅዱስ_አቦሊ በሰማዕትነት አረፈ፣ የከበሩ ሰዎች #ቅዱሳን_የዮሴፍና_የኒቆዲሞስ መታሰቢያቸው ነው፣ በተጨማሪም በዚህች ቀን የፋኑኤል ልጅ የነብይት #ሐና፣ የንግሥት ሶፍያ ልጆች የቅዱሳት ደናግል መታሰቢያቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሐና (የእመ ብርሃን እናት)

ነሐሴ አንድ በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናቷ የሐና መታሰቢያዋ ነው። ይህችም ቅድስት ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት (ጣ ጠብቆ ይነበብ) ልጁ ናት። ለማጣትም ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱም ስሟ ማርያም ናት ሁለተኛዋም ስሟ ሶፍያ ሦስተኛዪቱም ስሟ ሐና ናት ታላቂቱ ማርያምም ለባል ተድራ አዋላጅ የሆነች ሰሎሜን ወለደቻት እርሷም #መድኃኒታችንን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ በስደቷም ወራት ከአረጋዊ ዮሴፍ ጋር እመቤታችንን #ድንግል_ማርያምን ያገለገለቻት ናት።

ሶፍያም ለባል ተድራ ለመጥመቁ ዮሐንስ እናቱ የሆነች ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደቻት። ይችንም ቅድስት ሐናን ከይሁዳ ነገድ ለሆነ ጻድቅ ስሙ ኢያቄም ለሚባል አጋቧት። (ሰሎሜና ኤልሳቤጥ ለቅድስት ሐና የእኅትማማች ልጆች ናቸው።)

ቅድስት ሐና ኢያቄምን አግብታ ስትኖር የቴክታና እና የጴጥሪቃ ምክነት በዘር ወርዶ መክና በመኖሯ የዐይኗ ማረፊያ የልቧ ተስፋ የሚሆን ልጅ እንዲስጣት ፈጣሪዋን ስትማጸን ኖራለች።

የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ አምላክ ልመናዋን ሰምቶ ሐምሌ ፴ ራእይ አየች። ራእዩንም ከባሏ ከኢያቄም ጋር ተወያየተው ምንጣፍ ለይተው ሱባኤ ገቡ።

ከአንድ ሱባኤ በኋላ ነሐሴ ፯ ቀን #ጌታ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እንደሚወልዱ አበሠራቸው። ከዚያም እመቤታችን ጸንሳ ልዩ ልዩ ተአምራትን አድርጋለች። ሳምናስን ከሞት አስነስታለች። በርሴባን ዐይኗን አብርታለች። ከዚያም በአይሁድ ተንኮልና አሳዳጅነት ወደ ሊባኖስ ተራራ ተሰዳ #ድንግል_ማርያምን ወልዳለች። በመውለዷም ሕዳሴ አካል አግኝታ ከኖረች በኋላ ዐርፋለች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሐናና ኢያቄም ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቦሊ

በዚህችም ቀን የዮስጦስ ልጅ ቅዱስ አቦሊ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ አቦሊ ከመንግሥት ልጆች ውስጥ ነበር ዐላውያንን ወግቶ በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስን ክብር ይግባውና #ክርስቶስን ክዶ አገኘው።

ያም አቦሊና አባቱ ዮስጦስ ሌሎችም የመንግሥት ልጆች ሁሉ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስን ሊያጠፉትና መንግሥትን ከእርሱ ሊወስዱ ችሎታ ሲኖራቸው የማታልፍ ሰማያዊት መንግሥትን አሰቡ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ አቦሊ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም አብዝቶ አባበለው። እንዲሁም አባቱ ዮስጦስንና የከበረች እናቱ ታውክልያን አባበላቸው እነርሱ ግን አልሰሙትም ልባቸው በ #መድኅን_ክርስቶስ ፍቅር ተነድፏልና። ንጉሡም እነርሱን በዚያ ማሠቃየትን ፈራ ስለዚህም ከመልእክት ደብዳቤ ጋር ወደግብጽ ስሙ ኄርሜኔዎስ ወደሚባል የእስክንድርያ ገዥ ላካቸው በመልእክቱም እንዲህ አለው ዮስጦስና ሚስቱ ታውክልያ ልጃቸው አቦሊም ወደአንተ በሚደርሱ ጊዜ አባብላቸው አለዚያም እየአንዳንዳቸውን ለያያቸው።

በዚያችም ሌሊት ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ለዮስጦስና ለሚስቱ ታውክልያ ለልጃቸው አቦሊም ተገልጦላቸው አጽናናቸው ከእነርሱም የሚሆነውን ነገራቸው የጸና ቃል ኪዳንም ሰጣቸው።

ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስም በደረሱ ጊዜ ስለእነርሱ እጅግ አደነቀ እነርሱ መንግሥታቸውን ትተዋልና ክፋ ነገርንም ሊናገራቸው አልደፈረም ከምክራቸው ይመለሱ ዘንድ በለሰለሰ ቃል ሸነገላቸው እንጂ ነገር ግን አልሰሙትም።

ከዚህም በኋላ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ ለእየብቻቸው ለያያቸው ቅዱስ ዮስጦስን ወደ እንዴናው ከተማ ሚስቱን ታውክሊያን ፃ ወደ ሚባል አገር ልጃቸው አቦሊንም ብስጣ ወደ ሚባል አገር ሰደዳቸው ለእያንዳንዳቸውም የሚአገለግላቸው አንዳንድ አገልጋይ ሰጣቸው። ቅዱስ አቦሊም ወደ ሀገር ብስጣ በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በመኰንኑ ፊት ታመነ። መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን በእሳት ቃጠሎና በመንኰራኵር አሰቃየው ሕዋሳቱንም ቆራርጦ ለአንበሶች ጣለው ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ከሥቃዩ ሁሉ አድኖ ያለ ጉዳት በጤና አነሣው።

ብዙዎች ሰዎችም ስቃዩንና ዳግመኛ መዳኑን በአዩ ጊዜ እጅግ አደነቁ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በአምላካችን_በመድኃኒታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስም አምነው ሰማዕታት ሆኑ።

መኰንኑ ግን እጅግ ተቆጥቶ የቅዱስ አቦሊን ቆዳውን እንዲገፍፉትና ጨውና መጻጻን በማቅ አምጥጠው ቍስሉን እንዲያሹ አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉበት።

ከዚህም በኋላ ቆዳውን አሸክመው በከተማ ውስጥ ሁሉ አዞሩት ወደ #ጌታችንም እንዲህ ብሎ ጸለየ የሕያው #እግዚአብሔር_ልጅ_ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ ርዳኝ ከዚህ ሥቃይም አድነኝ። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደርሱ መጣ ሁለመናውንም ዳስሶ አዳነው።

መኰንኑም በእርሱ ላይ የሚያደርገውን እስኪያስብ ከእሥር ቤት እንዲጨምሩት አዘዘ። ቅዱስ አቦሊም ቁሞ ጸለየ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #ጌታችን ተገለጠለትና የመረጥኩህ አቦሊ ሰላም ለአንተ ይሁን እኔም ከአንተ ጋር እኖራለሁ አለው #ጌታችንንም በአየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው ክብር ይግባውና ለ #ጌታችንም ሰገደለት።

ስሙ አብስኪሮን የሚባል አንድ ባለ ጸጋ ነበር የቤቱንም ግድግዳ አፍርሰው አዲስ ይሠሩለት ዘንድ ሠራተኞችን አመጣ ሥራቸውንም እስኪጨርሱ ከዚያ ይቆሙ ዘንድ ሁለቱን ልጆቹን አዘዛቸው።

ከግርግዳውም ላይ በወጡ ጊዜ ግርግዳው ተደርምሶ ዐሥራ ስድስት ሰዎችና ሁለቱ ልጆቹ ሞቱ። ባለጸጋውም የሆነውን በአየ ጊዜ ልብሱን ቀደደ ጩኾም አለቀሰ ወደ ቅዱስ አቦሊም ሒዶ ከእግሩ በታች ሰገደለት እንዲህም አለው ራራልኝ ሁለቱ ልጆቼ ሙተዋልና ከእነርሱም ጋራ ዐሥራ ስድስት ሰዎች ሞቱ። ከሞትም ብታሥነሣቸው እኔ በአምላክህ አምናለሁ።

ያን ጊዜም ቅዱስ አቦሊ ተነሣ እንዲህ ብሎ ጸለየ ስለ ቅዱስ ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ የመረጥከኝ #ጌታዬ_አምላኬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ በእኒህ በሞቱ ሰዎች ላይ ኃይልህን ግለጥ። እኒህ ሰዎች ሁሉ እንዲአምኑ ያለ አንተም ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ከሞት አንሣቸው። ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

ከዚህም በኋላ የተገፈፈ ቆዳውን ወስዶ በሞቱት ሰዎች ላይም ዘረጋውና በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሞት ተነሡ አለ። ወዲያውም ሁሉም ድነው ተነሡ በዚያ ያሉ ሕዝብም ይህን ድንቅ ሥራ በአዩ ጊዜ የክርስቲያን አምላክ የቅዱስ አቦሊም አምላክ #ኢየሱስ_ክርስቶስ አንድ ነው እኛም እናምንበታለን ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለምና እያሉ ጮኹ።

ባለ ጸጋው አብስኪሮንም መጥቶ ለቅዱስ አቦሊ እንዲህ እያለ ሰገደ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ክብር ይግባውና እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ዛሬ አወቅሁ እኔም አምንበታለሁ። ከቤተሰቦቹም ሁሉ ጋር አመኑ መኰንኑም አፈረ።
#ጳጒሜን_3

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጳጒሜን ሦስት በዚህች ዕለት የሰዎች ሁሉ ጸሎት የሚያርግባት #ርኅወተ_ሰማይ ትባላለች፣
የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ #ቅዱስ_ሩፋኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ ለእግዚአብሔር ልጅ ምሳሌው የሆነ #የካህኑ_መልከጼዴቅ መታሰቢያው ነው፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ መልካም ስም አጠራር ያለው #ቅዱስ_ዘርዐ_ያዕቆብ አረፈ፣ ሰንዱን ከሚባል አገር #ቅዱስ_ሰራጵዮን አረፈ፣ አቡነ ቀጸላ ጊዮርጊስ ዕረፍታቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ርኅወተ_ሰማይ

ጳጒሜን ሦስት በዚህች ዕለት የሰዎች ሁሉ ጸሎት የሚያርግባት፣ አራተኛው መጋቢ ኮከብ የሚያልፍባት፣ ለሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው ጸጋ በረከት የሚሰጥባት ዕለት ስለሆነች ርኅወተ ሰማይ (ሰማይ የሚከፈትባት) ቀን ትባላለች።

አሁን በሰማይ መዘጋት መከፈት ኑሮበት አይደለም። የሰው ልጆችን ልመና ቅዱሳን መላእክት ያለ ከልካይ የሚያሳርጉበት አንድም ቅዱስ ሩፋኤል የዓመቱን የጸሎት መዝገብ የሚከፍትበት ቀን ስለሆነ እንዲህ ተባለ እንጂ።

እመቤታችን #ድንግል_ማርያም ለአጼ ናዖድ እንደ ነገረቻቸው በዚህች ዕለት ሁሉም ቅዱሳን ስለሚታሰቡ፣ የ #እግዚአብሔር የምሕረት መዝገቡ ስለሚከፈት፣ ዕለቷን ክብርት ያሰኛታል። በቅዱስ ሩፋኤል አበጋዝነት (መሪነት) በዚህች ዕለት ለዓመት የሚበቃ ምሕረት ይገኛል።

ስለዚህም አባቶቻችን በዚህች ሌሊት ሦስት መቶ ስልሳ አምስት አቡነ ዘበሰማያትን ሲጸልዩ ያድራሉ። በሌላ ወገን ደግሞ የጌታ ዳግም ምጽዓቱ መታሰቢያ እንደ መሆኗ ትልቅ ትኩረትም ይሰጣታል። ቸሩ #ጌታችን ከተከፈተች ገነት ከተነጠፈች ዕረፍት ሁላችንንም ያድርሰን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሩፋኤል_ሊቀ_መላእክት

በዚህች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ የሩፋኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። እርሱም ከመላእክት አለቆች ሦስተኛ የሆነ ነው። ደግሞም ከእስክንድርያ ውጭ በደሴት የታነፀች ቤተ ክርስቲያኑ በከበረ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን በውስጧ ተአምር የተገለጸባት የከበረችበት ነው።

ይህም እንዲህ ነው ሀብታም ሴት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ መጥታ ሳለ ከእርሷ ጋርም ብዙ ሰው ነበረ። ከባሏም የወረሰችው ብዙ ገንዘብ አላት በሊቀ ጳጳሳቱ ቤት አንጻር ያለውን ኮረብታ አስቆፈረችው በጥቅምት ወር ዐሥራ ስምንት ቀን እንደጻፍን የወርቅ መዝገብ ተገለጠ።

በዚያም ወርቅ ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትን አነፀ ከእርሳቸውም አንዲቱ የመላእክት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ ሩፋኤል በስሙ የታነፀች ይህች ናት። ሥራዋንም በፈጸመ ጊዜ እንደዛሬው በዚች ቀን አከበራት።

ብዙ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጸች ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና። የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው። ወደ ክብር ባለቤት #እግዚአብሔርም በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ ያን ጊዜ ይህ የከበረ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በጦሩ ወግቶ እንዲህ አለው እግዚአብሔር አዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጽ ጸጥ ብለህ ቁም። አንበሪውም ጸጥ ብሎ ቆመ አልታወከም በውስጧም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆነ።

ይቺም ቤተ ክርስቲያን እስላሞች እስከተነሡበት ዘመን ኖረች ከዚህም በኋላ ሁለተኛ ያ አንበሪ ተናወጸ ደሴቲቱም በላይዋ ከሚኖሩ ብዙ ሕዝብ ጋራ ሠጠመች።

#ዳግመኛም የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ ጻድቅ ለሆነ ንጉሥ አኖሬዎስ ተናገረ። እንዲህም አለው ንጉሥ ሆይ እኛ ወዳንተ ልንመጣ በመርከብ እንደተሳፈርን ዕወቅ በጒዞ ላይ ሳለንም በቀዳሚት ሰንበት ቀን በደሴት ውስጥ ታናሽ ቤተ ክርስቲያን አየን ወደ ወደቡም ደርሰን በዕለተ እሑድ ሥጋውን ደሙን እንቀበል ዘንድ ወደርሷ ሔድን።

ለዚያች ቤተ ክርስቲያንም በጐኗ ታናሽ ገዳም አገኘን በውስጧም ወንድሞች መነኰሳት አሉ በክብር ባለቤት ጌታችንም ፈቃድ ወደ ርሳቸው ደረስን ። መነኰሳቱንም በቀደሙ አባቶች ዘመን የተጻፈ አሮጌ መጽሐፍ በእናንተ ዘንድ እንዳለ እጽናናበት ዘንድ እርሱን ሰጡኝ አልኳቸው። እንዲህም ብለው መለሱልኝ እኛ ትርጓሜያቸውን የማናውቀው መጻሕፍቶች በዕቃ ቤት አሉ። እኔም አያቸው ዘንድ ወደዚህ አምጡልኝ አልኳቸው። በአመጡአቸውም ጊዜ መረመርኳቸው #ጌታችንም በደቀ መዛሙርቱ ፊት ያደረጋቸውን ኃይሎችና ድንቆች ተአምራቶችን ስለ ሰማይና ምድርም ጥንተ ተፈጥሮ አገኘሁ።

ሁለተኛም ስመረምር ስለ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ሹመትና መዐርግ አባቶቻችን ንጹሐን ሐዋርያት የጻፉትን አገኘሁ ይኸውም #ጌታችን በደብረ ዘይት ከእሳቸው ጋራ እያለ የመለኮቱን ምሥጢር በገለጠላቸው ጊዜ። ሐዋርያትም እንዲህ ብለው እንደለመኑት #ጌታችንና ፈጣሪያችን ሆይ የከበረ የሩፋኤልን ክብሩን ታስረዳን ዘንድ እንለምንሃለን በየትኛው ዕለት በየትኛው ወር ሾምከው።

ከባልንጀሮቹ የመላእክት አለቆችም ትክክል ነውን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ዘንድ በዓለም ውስጥ ስለርሱ እንድናስተምር እርሱም በመከራቸው ጊዜ ይረዳቸው ዘንድ በአማላጅነቱም በአንተ ዘንድ ይቅርታን ያገኙ ዘንድ።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አዘዘና ከሦስተኛው ሰማይ ሦስቱ የመላእክት አለቆች ሚካኤል፣ ገብርኤልና ሩፋኤል መጡ በታላቅ ደስታም ለክብር ባለቤት ለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሰገዱ። #ጌታችንም ሩፋኤልን እንዲህ አለው የክብርህን ገናናነት የባልንጀሮችህንም ልዕልናቸውን እንዲያውቁ ለሐዋርያት ንገራቸው።

ያን ጊዜም ለ #ጌታችን ሰገደ ይነግራቸውም ዘንድ ጀመረ እንዲህም አላቸው ደገኛው የመላእክት አለቃ ሚካኤል ለሁሉም መላእክት አለቃቸው ነው ስሙም ይቅር ባይ ይባላል።

ሁለተኛም የመላእክት አለቃ ገብርኤል የስሙ ትርጓሜ አገልጋይም ጌታም የሆነ የዓለሙ ሁሉ እመቤት የሆነች አምላክን የወለደች ቅድስት #ድንግል_ማርያምን ያበሠራት ነው። የእኔም ስሜ ሩፋኤል ነው ይህም ደስ የሚያሰኝ ቸር መሐሪ ቅን የዋህ ማለት ነው እኔም ኃጢአተኞችን በ #እግዚአብሔር ዘንድ አልከሳቸውም ከኃጢአታቸው በንስሓ እስኪመለሱ ስለ ቅንነቴ በእነርሱ ላይ እታገሣለሁ እንጂ።

በሃያ ሦስቱ የመላእክት ነገድ ሠራዊት ላይ #እግዚአብሔር የሾመኝ እኔ ሩፋኤል ነኝ #እግዚአብሔር አብን ይቅር ባይ ልጁን አጽናኝና አዳኝ የሆነ #መንፈስ_ቅዱስን እናመሰግነው ዘንድ።

በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሺህ ዓመት ተድላ ደስታ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የክብር ጽዋን በሚሰጣቸው ጊዜ ለቅዱሳኖቹ በጎ ነገርን እንድሰጣቸው #እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ። ደግሞም በዚች ቀን ከዕፀ ሕይወት ዐጽቅ ወስጄ ለተመረጡ ክርስቲያኖች በእጄ እንድሰጣቸው #እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ።

የሰማያት መዛግብትም ከእጄ በታች ተጠብቀው የሚኖሩ እኔ ሩፋኤል ነኝ። እኔም #እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ እከፍታቸዋለሁ እዘጋቸዋለሁም።

በምድር ሰው ለባልንጀራው ስለ ስሜ በጎ ነገር ቢያደርግ እኔ በመከራው በችግሩ ረዳዋለሁ ወይም የሹመቴን ነገር የሚጽፍ ወይም ከቅዱሳን ጋራ ስሜን የሚያስብ ወይም በስሜ ለቊርባን የሚሆነውን የሚሰጥ ወይም በበዓሌ ቀን ምጽዋትን የሚሰጥ ይኸውም #እግዚአብሔር በሊቃነ መላእክት ክብር የሾመኝና ያከበረኝ ጳጕሚን ሦስት ቀን ነው። ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እስከማስገባው በብርሃን ሠረገላ እኔ እሸከመዋለሁ በምድር ላይ ከቶ እንደርሱ ያለ የማይገኝ መዐዛው እጅግ ጣፋጭ በሆነ ሽቱ ነፍሶቻቸው እርሱን በማሽተት ደስ እንዲላቸው አደርጋለሁ።
#መስከረም_10

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥር በዚች ቀን #ጼዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ተአምር ተገለጠ፣ የሜራሪ ልጅ #ቅድስት_ዮዲት እረፍቷ ነው፣ የከበረች #ቅድስት_መጥሮንያ በሰማዕትነት አረፈች፣ #ንግስት_ሳባ እረፍቷ፣ #ተቀጸል_ጽጌ #አጼ_መስቀል ይከበራል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጼዴንያ

መስከረም ዐሥር በዚህች ቀን ጼዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የ ድንግል_ማርያም ተአምር ተገለጠ።

ይቺንም ሥዕል የሣላት ወንጌላዊ ሉቃስ ነው ይባላል። ወደ ጼዴንያ አገርም የመጣችበት ምክንያት አንዲት ስሟ ማርታ የሚባል መበለት ሴት ነበረችና ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች ናት። አምላክን የወለደች እምቤታችን #ድንግል_ማርያምንም እጅግ ትወዳት ነበር። በሚቻላትም ሁሉ ታገለግላታለች።

በአንዲት ቀንም ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል መነኩሴ ከእርሷ ዘንድ እንግድነት አደረ በመልካም አቀባበልም ተቀበለችው በማግሥቱም ስተሸኘው አባት ሆይ የምትሔደው ወዴት ነው አለችው። እርሱም በከበሩ ቦታዎች ውስጥ ልሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም እሔዳለሁ አላት እርሷም ከእኔ ገንዘብ ወስደህ የእመቤታችን #ማርያምን ሥዕል ግዛልኝና በመመለሻህ ጊዜ አምጣልኝ አለችው። እርሱም በራሴ ገንዘብ ገዝቼ አመጣልሻለሁ አላት።

ከዚህም በኋላ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከቅዱሳት መካናት ተባረከና ሥዕሏን ሳይገዛ ወደ ጎዳናው ተመለሰ። ያን ጊዜም ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰማ ወደ ገቢያም ተመልሶ ላሕይዋና መልኳ ያማረና የተወደደ የሆነ የእመቤታችን #ማርያምን ሥዕል አግኝቶ ገዛት በሐርና በንጹሕ ልብስም ጠቀለላት።

በጎዳናውም እየተጓዘ ሳለ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ወንበዴዎች ተነሡበት ሊሸሽም ወደደ ከዚያቺም ሥዕል መንገድህን ሒድ የሚል ቃል ወጣ የተከተለውም ሳይኖር መንገዱን ተጓዘ። ሁለተኛም ነጥቆ ሊበላው አንበሳ ተነሣበት ያን ጊዜም ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረው።

አባ ቴዎድሮስም ይህን ሁሉ ድንቅ ተአምር ባየ ጊዜ ያቺን ሥዕል ወደ አገሩ ሊወስዳት ወደደ ግዛልኝ ላለችው መበለት ይሰጣት ዘንድ አልፈለገም።

ከዚህም በኃላ በመርከብ ተሳፍሮ በሌላ አቅጣጫ ሲጓዝ ታላቅ ነፋስ ተነሣበት ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያም ወሰደው ከመርከቡም ወርዶ ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ሔደ ማንነቱንም አልገለጠላትም እርሷም አላወቀችውም።

በማግሥቱም ተሠውሮ ወጥቶ ወደ አገሩ ሊሔድ በፈለገ ጊዜ የቅጽሩን ደጃፍ አጥቶ ሲያጥመሰምስ ዋለ በመሸ ጊዜም ወደ ማደሪያው ተመለሰ። ያቺም መበለት በአየችው ጊዜ ታደንቃለች እንዲህም ሁኖ እስከ ሦስት ቀን ኖረ በመሸ ጊዜ በሩን ያየዋል ነግቶ መሔድን ሲሻ የበሩ መንገድ ይሠወረዋል። ያቺም መበለት ያዝ አድርጋ አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን ስትቅበዘበዝ አይሀለሁና ምን ሆነህ ነው አለችው።

ከዚህም በኋላ ከዚያች ሥዕል የሆነውን ሁሉ ነገራት ራሱንም ገለጠላት። ያቺንም ሥዕል ሰጣት ተቀብላም የተጠቀለለችበትን ልብስ ፈታች ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች። ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የዚያን መነኩሴ እጆቹንና እግሮቹን ሳመች።

ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር የምትቀመጥበትን አዘጋጅታ አኖረቻት ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት በቀንና በሌሊትም የሚበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች ከመቅረዞችም ውጭ የሐር መጋረጃን ጋረደች። ከሥዕሊቱ በታችም ከሥዕሊቱ እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች ያም መነኩስ እስከሚሞትበት ቀን ድረስ የእመቤታችንን #ድንግል_ማርያምን ሥዕል እያገለገለ ኖረ።

የሀገሩም ሊቀ ጳጳሳት የዚያችን ሥዕል ዜና በሰማ ጊዜ ከኤጲስቆጶሳትና ከካህናት ከሕዝቡም ሁሉ ጋር መጣ በሠሌዳውም ውስጥ በአዩዋት ጊዜ ሥጋ የለበሰች ሁና አገኙዋት ከዚህ ከአምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ ከዚህም ቅባት ቀድተው ለበረከት በተካፈሉ ጊዜ ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ ይመላል።

ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜ ንውጽውጽታ ሆኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ በዚያች አገር ትኖራለች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእናቱ በእመቤታችን በ #ድንግል_ማርያም ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ዮዲት

ዳግመኛም በዚህች ቀን ባሏ ምናሴ ሞቶባት፣ ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም፣ በቀኖና፣ በትኅርምት፣ በኀዘን፣ በጸሎት ተወስና የምትኖር የሜራሪ ልጅ ቅድስት ዮዲት አረፈች።

ቅድስት ዮዲት ከከሀዲው ሆሎፎርኒስ እጅ በጥበቧ እስራኤልን ያዳነቻቸው ጥበበኛ የከበረች፣ በ #እግዚአብሔር ኃይል ራሱን እስከ ቆረጠች ድረስ በልቧ ተራቀቀች ወገኖቿንም ያዳነች ናት።

ነገሩም እንዲህ ነው፦ ለፋርስ ንጉሥ ለናቡከደነፆር የጦር አበጋዝ የነበረው ሆሎፎርኒስ ፈቃድ ተሰጥቶት እስራኤልን ለመውረር ሲመጣ በሠራዊቱ (ዮዲ2፣2-7) የእሥራኤል ልጆችም ሆሎፎርኒስ የአሕዛብን አገር እንዳጠፋና ንብረታቸውን እንደዘረፈ ሰምተው ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስና ሰለ ንዋያተ ቅድሳት መርከሰ ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው ከቤተ መቅደሱ በር ወድቀው አለቀሱ።(ዮዲ4፡2-15) ሆሎፎርኒስ ግን የሚጠጡትን ምንጫቸውን በመያዙ ፣ የእሥራኤል ልጆች በውኃ ጥም ከመቸገርና ከመሞት ይልቅ እጃቸውን ለጠላት ለመስጠት ወሰኑ፡፡ ነገር ግን ዖዝያን የአባቶቻቸው አምላክ መልስ እስኪሰጣቸውና ቸርነቱን እስኪመልስላቸው መከራውን በትዕግሥት እንዲቀበሉ ስለመከራቸው ጸኑ፡፡ ዮዲ 7፥10-32)

በዚህ ጊዜ ዮዲት ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትቢያ ነስንሳ፣ ሱባዔ ገባች! አምላክም ሕዝቡን የሚያድንበትን ዕውቀትና ጥበብ ግብር በገባች በሦስተኛ ቀን ገለጸላት፡፡(ዮዲ8፡2) ከዚያም “ወዴት ትሔጃለሽ አትበሉኝ አምላክ እሥራኤል ይከተልሽ ብሉኝ” ብላ የኀዘን ልብሷን ጣለች፡፡ ሰውነቷን ታጠበችና ሽቱ ተቀባች ባሏ በሕይወት ሳለ የምትለብሰውን የክት ልብሷን ለበሰች፣ የጠላት ሰዎች ሁሉ እስኪወዷት ድረስ ፈጽማ አጊጣ ሄደች፡፡ (ዮዲ.10፥2-3) እነርሱም ለእኔ ትገባለች ለእኔ ትገባለች እያሉ ተሻሙባት፡፡ የንጉሥ ጃንደረባ ጋይ የሚባል ይህችስ ለጌታዬ ትገባለች አለ፣ ለምን እንደመጣች ጠይቀዋት ለመልካም ነገር እንደመጣች ሲረዱ ከጦር አበጋዙ አደረሷት፡፡ (ዮዲ10፥12-22)

በአንዲትም ዕለት ሆሎፎርኒስ የአሽከሮች የምሣ ግብዣ አድርጎ ሲያበላ ሲያጠጣ ያችን ዕብራዊት ጥሩ ብሎ አስጠርቶ ከፊቱ አስቀምጦ ሲበላ አብዝቶ ሲጠጣ ውሎ ሰከረ፡፡(ዮዲ12፥1-20) ከዚያም አሽከሮችን ከሁሉ አስወጥቶ ድንኳኑን ቆልፎ እንደተኛ ከባድ እንቅልፍ ያዘው ዮዲትም ከፀለየች በኋላ ከራስጌው ያለውን ሰይፍ አንስታ የራስ ጠጉሩን ይዛ አንገቱን ቆርጣ በድኑን ከመሬት ጥላ ቸብቸቦውን በአቁማዳ ቋጥራ ለብላቴናዋ አሸክማ ግንዱን በታች ገልብጣ ዙፋኑን በላይ አድርጋ ወደ ሃገሯ ተመለሰች፡፡ (ዮዲ13፥1-10) ሕዝበ እሥራኤል በዚህ ድርጊቷ እጅግ ተደነቁ፣ ጠላታቸውን በእጃቸው የጣለላቸውን #እግዚአብሔር አምላካቸውንም አመሰገኑ፡፡ በኋላም የሆሎፎርኒስን ራስ በተራራው ላይ ሰቅለው መዋጋት ጀመሩ፡፡ እስከ ዮርዳኖስም እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡