ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
✞✞✞✝️ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ✝️ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✝️ሐምሌ ፲፪✝️

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱስ "ሚካኤል ሊቀ መላእክት"
የተአምር በዓልና ለሰማዕቱ "አባ ሖር" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" ተአምረ ቅዱስ ሚካኤል "*+

=>ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን በዚህች ዕለት የመላእክት
ሁሉ አለቃቸው: የቅዱሳንም ረዳታቸው የሆነው ደጉ
መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ንጉሡን ሕዝቅያስን ግሩም
በሆነ ተአምር ከከተማው #ኢየሩሳሌም ጋር ታድጐታል::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ከመድኃኒታችን #ክርስቶስ ልደት 700 ዓመታት በፊት
#ሕዝቅያስ የሚባል ንጉሥ በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር::
ደጋጉ #ዳዊትና #ሰሎሞን ካረፉ በሁዋላ የሕዝቅያስን
ያክል ቅን እና የእግዚአብሔር ሰው በእሥራኤል ላይ
አልነገሰም:: ንጉሡ ጣዖት አምልኮን ነቃቅሎ አጥፍቶ
ሕዝቡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ አድርጐም
ነበር::

+ነገር ግን ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት
የአሕዛብ (የአሦር) ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት::
ወደ አካባቢውም መጥቶ: ከቦ አስጨነቀው:: ሰናክሬም
በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር:: በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ
ከ185,000 በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ
እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት::

+"እገብርልሃለሁ:: የፈለግከውንም እሰጥሃለሁ:: ሃገሬን
ግን አታጥፋ:: ኢየሩሳሌምን አታቃጥል:: ሕዝቤንም
አትግደል" በሚል ለመነው:: እጅ መንሻ ግብሩንም
ከከተማዋ የተገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ ጭኖ ላከለት::

+ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን
ልመና ወደ ጐን ብሎ የእሥራኤልን አምላክ : ቅዱስ
ስሙንም ተገዳደረ:: ለሕዝቅያስም "ከእኔ እጅ የሚያድንህ
ማነው? ሕዝቡንም #እግዚአብሔር ያድናል ብለህ
አታታልላቸው" ሲል ላከበት:: ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ
የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ::

+መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ #ቅዱስ_ኢሳይያስ ልኮ እርሱ
ወደ ቤተ መቅደስ ገባ:: በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን
ቀድዶ ማቅ ለበሰ:: ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ
አለቀሰ:: በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰናክሬምን
መገዳደርና የሕዝቅያስን ልመና ሰምቷልና በኢሳይያስ
አንደበት እንዲሕ አለ:- "ስለ ባሪያየ ስለ #ዳዊት
ከተማዋን አድናታለሁ::"

+በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል
ከሰማያት በግርማ ወረደ:: ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር
ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው
ከአሕዛብ ሠራዊት 185 ሺ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ::
በለኪሶ የነበረው ሰናክሬም በጧት ቢነሳ ሠራዊቱ ሁሉ
ወደ አስከሬን ክምር ተቀይሯል::

+በድንጋጤ ወደ #ነነዌ ሒዶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሲገባ የራሱ
ልጆች (አድራማሌክና ሳራሳር) ገደሉት:: ትዕቢተኛው
ሰናክሬም ለአሕዛብ ሁሉ መዘባበቻ ሆነ:: ቅዱስ ሕዝቅያስ
ግን በፈጣሪው ታምኗልና ቅዱስ ሚካኤል ሞገስ ሆኖ
የዓለም ነገሥታት ሁሉ ፈሩት:: (1ነገ. 18:13, 19:1)

+*" ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት "*+

=>ዳግመኛ በዚህ ቀን #አባ_ሖር ሰማዕቱ ይታሠባል::

+ቅዱሱ:-

¤ስርያቆስ በምትባል የግብጽ አውራጃ ተወልዶ ያደገ:
¤ገና በልጅነቱ መንኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ:
¤ዘመነ ሰማዕታት በመጣ ጊዜም በመኮንኑ ፊት ቀርቦ
በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያመነ:
¤ከመኮንኑም ብዙ ስቃይ የደረሰበት:
¤ብዙ ተአምራትን በመስራቱ ያሰቃየው የነበረውን መኮንን
ወደ ክርስትና መልሶ ለሰማዕትነት ያበቃ አባት ነው::

+እርሱም የሰማዕትነትን ክብር በእጅጉ ሽቷታልና ወደ ሌላ
ሃገር ሒዶ በዚህች ቀን አንገቱን ተሰይፎ የክብርን አክሊል
ተቀዳጅቷል:: በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ያሳመናቸው 127
ወንዶችና 20 ሴቶችም አብረውት ተሰይፈዋል::

=>እግዚአብሔር በሊቀ መላእክት ክንፍ ሃገራችንን
ከአሕዛብ ስውር ጦር ይጠብቅልን:: ከሰማዕቱም በረከት
ያሳትፈን::

=>ሐምሌ 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሕዝቅያስ ንጉሥ
2.ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
3.ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት
4."147" ሰማዕታት (የአባ ሖር ማሕበር)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
3.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ድሜጥሮስ
5.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
6.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
7.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
8.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

=>+"+ እግዚአብሔር ይላል:- ስለ እኔም ስለ ባሪያየም
#ስለ_ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ::
በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ::
ከአሦራውያንም ሠፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ::
ማለዳም በተነሱ ጊዜ እነሆ ሁሉ በድኖች ነበሩ:: +"+
(1ነገ. 19:34)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://t.me/zikirekdusn
🌻††† እንኳን ለቅድስት ጾመ ፍልሠታ ለማርያም እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅድስት ጾመ ፍልሠታ ለማርያም †††

††† ቸር #እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠው ጸጋ አንዱ #ጾም ነው:: የሰው ልጅ ከፈጣሪው ክብር እንዲደረግለት ክፋትን መስራት የለበትም:: መልካም መሆንም ይጠበቅበታል:: ለዚህ ምንጮቹ ደግሞ ጾም: ጸሎትና ስግደት ናቸው:: ያለ እነዚህ ምግባራት መቼም ወደ #ጽድቅ መድረስ አይቻልም::

ይቅርና እኛ ክፉዎቹ የሰማይና የምድር ፈጣሪ: የክብር ሁሉ ባለቤት ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሥጋችንን በተዋሐደ ጊዜ የመጀመሪያ ሥራው ያደረገው ጾምን ነው:: ስለዚህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን 7 አጽዋማትን በጉባዔ ሠርታ: በአዋጅ እንዲጾሙ ታደርጋለች:: ከእነዚህም አንዱ ጾመ ፍልሠታ ነው::

"ፈለሠ" - ሔደ: ተጉዋዘ እንደ ማለት ሲሆን " #ፍልሠታ" ማለት የእመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያምን የዕርገት ጉዞ የሚያዘክር ቃል ነው:: #እመ_ብርሃን በዚህ ዓለም ለ64 ዓመታት ኑራ ካረፈች በሁዋላ ሥጋዋ እንደ እኛ አልፈረሰም::

ለጊዜው በዕጸ ሕይወት ሥር ቆይታ እንደ ልጇ ትንሳኤ ተነስታ ዐርጋለች:: እርሷ በሁሉ ነገሯ ቀዳሚና መሪ ናትና:: ጾመ ፍልሠታን የጀመሩት አበው #ሐዋርያት ሲሆኑ እንድትጾምም ሥርዓት የሠሩ ራሳቸው ናቸው:: ከ7ቱ አጽዋማትም እጅግ ተወዳጅና እየተናፈቀች የምትፈጸም ናት::

ካህናትና ምዕመናንም ጾሟን እንደየአቅማቸው ክብር በሚያሰጥ መንገድ ይፈጽሟታል::
*የቻሉ ወደ ገዳማት ሔደው ጥሬ እየቆረጠሙ: ውሃ እየተጐነጩ ክብርን ያገኛሉ::
*ሌሎቹ ደግሞ ባሉበት ደብር አካባቢ እያደሩ ሌሊት ሰዓታቱን: በነግህ ኪዳኑንና ውዳሴ ማርያም ትርጉዋሜውን: በሰርክ ደግሞ ቅዳሴውን ይሳተፋሉ::
*የኔ ብጤ ደካማ ደግሞ ጠዋት ማታ ወደ ደጇ እየተመላለሰ "አደራሽን ድንግል" ይላታል::

††† በእርሷ አምነን አፍረን አናውቅምና ነጋ መሸ ሳንል እንማጸናታለን::

††† #ጽንዕት_በድንግልና: #ሥርጉት_በቅድስና #እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን: ልበለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን:: <3
*ጾሙን የፍሬ: የትሩፋትና የበረከት ያድርግልን::*

††† ቅዱሳን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ †††

††† እጅግ የተወደዱ: ሞገስ የሞላላቸውና ፈጣሪያቸውን በክብር ገንዘው የቀበሩ አባቶች ናቸው::

††† ቅዱስ ዮሴፍ ዘአርማትያስ †††

††† ቅዱሱ በእሥራኤል ምድር ተወልዶ ያደገ: ኦሪትን የተማረ ባለጠጋ ሰው ነው:: የተማረ ደግ ሰው ነውና የክርስቶስን መምጣት በተስፋ ይጠብቅ ነበር:: ባገኘውም ጊዜ በአዳኝነቱ (በመሲህነቱ) አምኖ በስውር ተከታዩ ነበር::

††† ቅዱስ ኒቆዲሞስ †††

††† ወንጌል እንደሚነግረን ይህ ሰው የአይሁድ አለቃ: መምሕር: ዳኛ እና ሃብታም ሰው ነበር:: እነዚህ ሁሉ ማነቆዎች ግን እርሱን ከፈጣሪው ሊያስቀሩት አልቻሉም:: ሌሊት እየመጣ ከጌታችን እግር ይማር ዘንድም አድሎታል:: በመካከልም ከአይሁድ ጋር ብዙ ተጋጭቷል::

ሁለቱ አባቶች መድኃኒታችን ስለ እኛ ሲል ሞቶ ባለበት ሰዓት ላይ በእርሱ የደረሰ ይደርስብናል ሳይሉ በድፍረት ሥጋውን ከዺላጦስ ተካሠው ለመኑ:: እንባቸው በፊታቸው እየወረደ ከመስቀል አውርደው በዮሴፍ በፍታና በኒቆዲሞስ ሽቱ ገነዙት::

እንዲህ እያሉ:-
"ሙታንን የምታስነሳ ጌታ አንተ ሞትክን?! ደካሞችን የምታጸና ቸር አንተ ደከምክን?!"
*በዚያች ሰዓት ጐልጐታ አካባቢ ዝማሬ መላእክትን እየሰሙ የክብር ባለቤትን ቀብረውታል:: ጌታችንም ከተነሳ በሁዋላ በንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::

"እየሳማችሁ አክብራችሁ እንደ ገነዛችሁኝ እኔም በሰማይ በእንቁ ዙፋን ላይ አስቀምጣቹሃለሁ" ብሏቸዋል:: "አነ አብረክሙ ዲበ መንበረ ሶፎር" እንዲል:: ጻድቃን አበው ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በተረፈ ዘመናቸው ወንጌልን ሰብከው: ከአይሁድ መከራን ታግሰው: በበጐ ሽምግልና ዐርፈዋል::

††† ቅዱስ አቦሊ ሰማዕት †††

††† ቅዱስ አቦሊ የሰማዕታቱ #ቅዱስ_ዮስጦስና #ቅድስት_ታውክልያ ልጅ ሲሆን በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ያበራ የቤተ ክርስቲያን ዕንቁ ሰማዕት ነው:: የሚገርመኝ ሦስቱ የግማሹ ዓለም አስተዳዳሪዎች ነበሩ:: ዮስጦስ ንጉሥ: ታውክልያ ንግሥት: አቦሊ ደግሞ ልዑል ነው::

ነገር ግን ይህንን ክብራቸውን #በክርስቶስ ፍቅር ጐን: ሚዛን ላይ ቢያኖሩት በጣም ቀሎ ታያቸው:: 3ቱም ከዙፋናቸው ወርደው: ወገባቸውንም ታጥቀው: ባሮቻቸው በነበሩ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ብዙ ተንገላቱ:: መራራ ሞትንም ታገሱ::

በተለይ ቅዱስ አቦሊ ከአንጾኪያ ወደ ግብጽ (ብስጣ) ይዘው አምጥተው ክርስትናውን እንዲተው ያላደረጉት የለም:: በቁሙ ቆዳውን ገፈው: በቆዳው አቅማዳ ሰፍተው: ያንንም አሸክመው: የተገፈፈ አካሉን ጨውና ኮምጣጤ እየቀቡ አዙረውታል::

እርሱ ግን ጌታ በላከለት ድንቅ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ረዳትነት ሁሉን ችሎታል:: በዘመኑ ብዙ ተአምራትን የሠራ ሲሆን አንድ ጊዜ ቤት ተንዶ 16 ሰዎች ቢያልቁ የተገፈፈ ቆዳውን እየጣለባቸው ተነስተዋል:: በተአምራቱና በተጋድሎውም ብዙ ሺህ አሕዛብን ለክርስትና: ብሎም ለሰማዕትነት አብቅቷል::

እርሱም ከብዙ የመከራ ጊዜያት በሁዋላ በዚህች ቀን አንገቱን ተከልሏል:: ጌታችን "ዜናሕን የጻፈውን: ያነበበውንና የሰማውን ይቅር እለዋለሁ" ብሎ ቃል ኪዳንን ሰጥቶታል::

††† ፈጣሪ ከጻድቃንና ሰማዕታት በረከትን አይለይብን:: ወርሐ ነሐሴንም ለበረከት ይቀድስልን::

††† ነሐሴ 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በአተ ጾመ ፍልሠታ
2.አበው ሐዋርያት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
3.ቅዱስ አቦሊ ሰማዕት
4.ታላቁ ቅዱስ ዸላሞን ገዳማዊ
5.ቅድስት ሐና (የእመ ብርሃን እናት)
6.ቅድስት ሐና ነቢይት (ወለተ ፋኑኤል)
7.ደናግል ቅዱሳት (የንግስት ሶፍያ ልጆች)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

††† "የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ #ዮሴፍ የጌታ ኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ዺላጦስን ለመነ:: ዺላጦስም ፈቀደለት:: ስለዚህም መጥቶ የጌታ ኢየሱስን ሥጋ ወሰደ:: ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ #ጌታ_ኢየሱስ መጥቶ የነበረ #ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ:: የጌታ ኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት::" †††
(ዮሐ. 19:38)

††† "በጽዮን መለከትን ንፉ:: ጾምንም ቀድሱ:: ጉባዔውንም አውጁ:: ሕዝቡንም አከማቹ:: ማሕበሩንም ቀድሱ:: ሽማግሌዎችንም ሰብስቡ:: ሕጻናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ:: ሙሽራው ከእልፍኙ: ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ::" †††
(ኢዩ. 2:15)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://t.me/zikirekdusn
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ ታኅሳስ24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት: ቅዱስ አግናጥዮስ እና ቅድስት አስቴር ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ  ✞✞✞

+*" ቅዱስ  #‎ተክለ_ሃይማኖት  ሐዋርያዊ "*+

*ልደት*

=>መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ:  #‎ጸጋ_ዘአብ  ካህኑና  #‎እግዚእ_ኃረያ  ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::

+በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው  #‎ቅዱስ_ሚካኤል : ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል::

+አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት 24, በ1206 (1196) ሲሆን የተወለዱት ታሕሳስ 24, በ1207 (1197) ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::

*ዕድገት*

=>የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው " #‎ፍሥሃ_ጽዮን " ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት: ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁና ከወቅቱ ዻዻስ  #‎አባ_ጌርሎስ  ተቀብለዋል::

*መጠራት*

=>አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት  #‎ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ  አእላፍ መላእክት እያመሰገኑ በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::

+የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:

"ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በኋላሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::

*አገልግሎት*

=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ ( #‎ጽላልሽ ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያንጊዜ  #‎ኢትዮዽያ  2 መልክ ነበራት::

1.ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::

2.ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር::

+ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት  #‎ሐዲስ_ሐዋርያ  አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቁዋዮችን) አጥፍተዋል::

*ገዳማዊ ሕይወት*

=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል::

+እነዚህም በአቡነ  #‎በጸሎተ_ሚካኤል  ገዳም ለ12 ዓመታት: በአቡነ  #‎ኢየሱስ_ሞዐ_ዘሐይቅ  ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ  #‎ዮሐኒ  ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት አገልግለዋል::

+በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ  #‎ዞረሬ  ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::

*ስድስት ክንፍ*

=>ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ  #‎እሥራኤል  የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::

+የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት  #‎አባ_ሚካኤል  ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::

+ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
¤በቤተ መቅደስ ብስራቱን
¤በቤተ ልሔም ልደቱን
¤በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
¤በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
¤በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

+የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደሆነው  #‎ቀራንዮ  ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ  #‎እመቤታችን_ድንግል_ማርያም  ፈጥና ደርሳ ጻድቁን ወደሰማይ አሳረገቻቸው::

+በዚያም:-
¤የብርሃን ዐይን ተቀብለው
¤6 ክንፍ አብቅለው
¤የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
¤ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
¤ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
¤ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
¤"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

*ተአምራት*

=>የጻድቁ ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::

+ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::

*ዕረፍት*

=>ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው ነሐሴ 24, በ1306 (1296) ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10 ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::

=>የጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የቅድስናና የክብር ስሞች :-

1.ተክለ አብ: ተክለ ወልድ: ተክለ መንፈስ ቅዱስ
2.ፍስሐ ፅዮን
3.ሐዲስ ሐዋርያ
4.መምሕረ ትሩፋት
5.ካህነ ሠማይ
6.ምድራዊ መልዐክ
7.እለ ስድስቱ ክነፊሁ (ባለስድስት ክንፍ)
8.ጻድቅ ገዳማዊ
9.ትሩፈ ምግባር
10.ሰማዕት
11.የኢትዮዽያ መነኮሳት አለቃ
12.ፀሐይ ዘበፀጋ
13.የኢትዮዽያ ብርሃኑዋ
14.ብእሴ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ሰው)
15.መናኒ
16.ኤዺስ ቆዾስ (እጨጌ)

=>እነዚህ የአባታችን ስሞች እንደዘመኑ ሰው ለመሞጋገስ የወጡ ሳይሆኑ ሁሉም በትክክል ሥራዎቹንና ለቤተ ክርስቲያን የሆነላትን የሚያዘክሩ ናቸው:

+" ቅዱስ አግናጥዮስ "+

=>ይህ ቅዱስ ሰው ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የጠገበ በመሆኑ በመላው ዓለም ዝነኛ ነው:: እርሱ:-
*በክርስቶስ እጅ ተባርኩዋል
*ፈጣሪውን ፊት ለፊት አይቷል
*ሐዋርያትን አገልግሏል
*ከምሥጢር አባት ከዮሐንስ ወንጌላዊ እግር ተምሯል
*ስለ ክርስትና ለአንበሶች ተጥሎ በመገደሉ "ምጥው ለአንበሳ" ይባላል::
ከዚህም አስቀድሞ የከተማው ሰዎች የሚያመልኩትን ዘንዶ እርሱ እንደ ገደለው የአውኪስጦስ አገር ሰዎች ወደ ንጉሥ ከሰውት ነበርና ስለዚህ ንጉሥ ልኮ አስቀረበው።

ቅዱስ ቴዎድሮስም ወደ ንጉሡ በቀረበ ጊዜ ንጉሡን እንዲህ ብሎ ዘለፈው አንተ የክፉ ሥራ ሁሉ መገኛ የሆንክ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የክብር ባለቤትን ትተህ የረከሱ ጣዖታትን ያመለክ የኃጢአት ልጅ ሆይ ወዮልህ #እግዚአብሔርም ፈጥኖ መንግሥትህን ያጠፋታል።

በዚያን ጊዜም ንጉሡ ተቆጥቶ ከመሬት ላይ ጥለው ይገርፉት ዘንድ ወታደሮችን አዘዛቸው። ይህንንም አደረጉበት ደሙም እንደ ውኃ ፈሰሰ። እጆቹንና እግሮቹንም ከግንድ ጋር ቸነከሩት።

በሥቃይም ውስጥ ሳለ ከ #እግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል ወደርሱ ወረደ እንዲህም አለው ጽና እነሆ የገድልህ ፍጻሜ ቀርቦአል ሥጋህ በውስጡ በሚኖርበትም ቦታ ድንቆችና ተአምራቶች ይገለጣሉ እነሆ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠህ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ፣ ወይም በስምህ የተራበ ለሚያጠግብ፣ የተጠማውን ለሚያጠጣ፣ ወይም ለቤተክርስቲያንህ መባን መጻሕፍትንም ለሚሰጥ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስስለታለሁ። ገድልህንም የሚጽፈውን፣ ወይም የሚያነበውን፣ የሚሰማውን፣ ወይም የሚገዛውን እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ።

ከዚህም በኋላ ብዙዎች ከንጉሥ ሠራዊትና ከሕዝቡ ተሰብስበው በንጉሡ ላይ እንዲህ ብለው ጮኹበት አንተ ከሀዲ #እግዚአብሔር ያጥፋህ ከጠላቶቻችን ያዳነንን ኃያልና ጽኑዕ የሆነውን የከበረ ቴዎድሮስን ታሠቃየዋለህና ይህንንም ብለው በክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመኑ ያን ጊዜም ንጉሥ ተቆጥቶ ሁሉንም አስገደላቸው ሰማዕትም ሆኑ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ።

ከዚህም በኋላ ንጉሡ አዘዘ የብረት ዐልጋም አምጥተው ቅዱሱን በላዩ አስተኙት ከበታቹም እሳትን አነደዱ ቅዱስ ቴዎድሮስም እንዲህ ብሎ ጸለየ አቤቱ ፈጣሪዬ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ምድጃ እንደ አዳንካቸው አድነኝ። ወዲያውኑም ያ እሳት ጠፋ እንደ ንጋት ጊዜ ቊርም ሆነ።

ከሰማይም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ክብር ይግባውና ከ #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ኃይል የተሰጠህ ሆይ ጽና በርታ ያን ጊዜም ቅዱሱ ተነሥቶ በንጉሡ ፊት ቆመ እንዲህም አለው ክብር ይግባውና #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ አድኖኛልና አንተ ከሀዲ እፈር አለው። የንጉሡም የጭፍራ አለቃ ይህን በአየ ጊዜ ክቡር ቴዎድሮስ ከሚያመልከው ክብር ይግባውና ከ #ጌ_ ከኢየሱስ_ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም ብሎ ጮኸ ርሱንም ራሱን አስቆረጠውና በሰማዕትነት ሞተ።

ቅዱስ ቴዎድሮስንም ብዙ ከአሠቃየውና ማሠቃየቱ ከሰለቸው በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ ሥጋውንም እንዲአቃጥሉ አዘዘ። በ #ጌታችንም ፈቃድ ከእናቱ ደጅ ወስደው እራሱን ቆረጡ ከእርሱም ደም፣ ወተትም ፈሰሰ ታላቅ እሳትም አንድደው ሥጋውን በውስጡ ጨመሩ እሳቱም ከቶ አልነካውም። እናቱም ለወታደሮች ብዙ ወርቅ ሰጥታ ሥጋውን ወሰደች በአማሩ ልብሶችም ገነዘችው እስከ መከራው ፍጻሜም በቤቷ ውስጥ አኖረችው።

ከዚያ በኋላም አብያተ ክርስቲያናት ተሠሩለት ስብጥ በሚባል በአባቱ አገርም በተሠራች ገዳም ሥጋውን አኖሩ ከሥጋውም ድንቆችና ተአምራቶች ተደረጉ ታላቅ ፈውስም ሆነ።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_20 እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
#ሐምሌ_23

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ ሦስት በዚች ቀን #ቅድስት_መሪና ሰማዕት ሆነች፣ #ቅዱስ_ለንጊኖስ ሰማዕት ሆነ፣ የመናገሻ ገነተ ጽጌ #ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ቤተ_ክርስቲያን (አራዳ ጊዮርጊስ) #ቅዳሴ_ቤቱ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_መሪና

ሐምሌ ሃያ ሦስት በዚች ቀን ቅድስት መሪና ሰማዕት ሆነች። የዚችም ቅድስት የአባቷ ስም ዳኬዎስ ነበር እርሱም በአንጾኪያ ሀገር ለጣዖታት ካህናት አለቃ ነበር ያን ጊዜ ንጉሡም ከሀዲው ዳኬዎስ ነበር።

አምስት ዓመትም በሆናት ጊዜ እናቷ ሞተች አባቷም ከከተማ ውጭ ለምትኖር ሞግዚት ሰጣት እርሷም ክርስቲያናዊት ነበረች የ #ክርስቶስ የሆነ የሃይማኖት ትምህርትን ሁሉ አስተማረቻት። ዐሥራ አምስት ዓመትም በሆናት ጊዜ አባቷ ሞተ።

ከዚህም በኋላ ሰዎች የሰማዕታትን ተጋድሏቸውንና መከራቸውን ሲናገሩ ሰምታ የ #ጌታ_ክርስቶስ ፍቅር በልቧ አደረ በሰማዕትነት መሞትንም ፈልጋ ሔደች።

በዚያን ጊዜም ከሀዲ መኰንን ወደዚያች አገር ደረሰ እርሷንም አይቶ ወደርሱ አስመጣትና ከወዴት ነሽ አላት #ክብር_ይግባውና_ከጌታ_ኢየሱስ ሰዎች ወገን ነኝ ስሜም መሪና ነው አለችው። ደም ግባቷንና ላሕይዋንም አይቶ መታገሥ ተሳነው እሺ ትለው ዘንድ በብዙ ነገር አባበላት። እርሷ ግን ረገመችው የረከሱ አማልክቶቹንም ረገመች።

ያን ጊዜም በብረት ዘንጎች ይደበድቧት ዘንድ ደሟ እንደ ውኃ እስኪፈስ ሕዋሳቷን ይቆራርጡ ዘንድ አዘዘ። ያን ጊዜም ወደ ጌታ #እግዚአብሔር ጸለየች የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤልም መጥቶ አዳናት። ሁለተኛም ወደ ወህኒ ቤት ያስገቧት ዘንድ አዘዘ #ጌታችንም ወደ ሰማይ አውጥቶ የቅዱሳን ሰማዕታትንና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳይቶ ወደ ቦታዋ መለሳት። በማግሥቱም ሥጋዋን በመጋዝ እንዲሠነጥቁ ጐኖቿንም እንዲሰነጣጥቁና በእሥር ቤት እንዲጥሏት አዘዘ ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል መጥቶ አዳናት።

በወህኒ ቤቱ ውስጥም ቁማ ስትጸልይ እጅግ የሚያስፈራ ታላቅ ዘንዶ ወደ ርሷ መጣ በአየችውም ጊዜ ደነገጠች ሰውነቷ ሁሉ ተንቀጠቀጠ መናገርም ተሳናት። ያን ጊዜም እጆቿ በ #መስቀል ምልክት አምሳል እንደተዘረጉ በልቧም ስትጸልይ ወደርሷ ቀርቦ ዋጣት። ያን ጊዜም ሆዱ ተሠንጥቆ ያለ ጉዳት ወጣች #እግዚአብሔርንም አመሰገነችው።

ሁለተኛም በጥቁር ሰው አምሳል ሰይጣንን አየችው እጆቹም በጉልበቶቹ ላይ ተጨብጠው ነበር። ፊቷንም በ #መስቀል ምልክት አማትባ በራሱ ጠጉር ይዛ ደበደበችው። በእግሮቿም ረገጠችው ያን ጊዜም #ክብር_ይግባውና_የጌታ_ክርስቶስ #ዕፀ_መስቀል ተገለጠላት በላዩም ነጭ ርግብ ተቀምጣ እንዲህ ብላ አነጋገረቻት መሪና ሆይ የ #መንፈስ_ቅዱስን የጸጋ አረቦን ተቀብለሻልና ደስ ይበልሽ።

በማግሥቱም መኰንኑ ልብሷን አራቁተው ዘቅዝቀው ሰቅለው እንዲአቃጥሏት ደግሞም ውኃ ከአፈሉበት ጋን ውስጥ እንዲጨምሩዋት አዘዘ። በውስጡም ሁና ስትጸልይ ከሰማይ ርግብ መጣ በአፉም ውስጥ የወርቅ አክሊል ነበር ማሠሪያዋንም ፈትቶ በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ አጠመቃት #እግዚአብሔርንም እያመሰገነች ከውኃው ውስጥ ወጣች።

መኰንኑም እንደ ዳነች በአየ ጊዜ ራሷን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። ወደ ሰማዕትነቱ ቦታም በደረሰች ጊዜ ነፍሷን በፍቅር ይቀበል ዘንድ ወደ #ጌታችን ጸለየች። #ክብር_ይግባውና_ጌታችንም ተገለጠላት ስሟን ለሚጠራ መታሰቢያዋንም ለሚያደርግ ገድሏንም ለሚጽፍ ወይም ለሚያነበውና ለሚሰማው ኃጢአቱን እንዲአስተሠርይለት ለርሷም ርሱን እንዲሰጣት ቃል ኪዳን ሰጣት።

ከዚህም በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጡ ከእርሷም ብዙ ተአምር ተገለጠ ዕውራን አይተዋልና፣ ሐንካሶች በትክክል ሔደዋልና፣ ደንቆሮዎችም ሰምተዋልና፣ ዲዳዎችም ተናግረዋልና ቁጥር የሌላቸው ብዙ ሰዎችም #ክብር_ይግባውና_በጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት መሪና ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ለንጊኖስ_ሰማዕት

በዚችም ቀን ከቀጰዶቅያ አገር ለንጊኖስ ሰማዕት ሆነ። ይህም ቅዱስ ከጲላጦስ ጭፍሮች ውስጥ ነበር #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስለ ዓለም ደኅንነት መከራ እንዲቀበል የፈቀደበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ በእርሱ ላይ የፈለጉትን ያደርጉ ዘንድ ለዐመፀኞች ፈቅዶላቸው ነበር። ይህም ለንጊኖስ #ጌታን ይሰቅሉት ዘንድ ጲላጦስ ከአዘዛቸው ወታደሮች ውስጥ ነበር።

በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ #ጌታችንን የቀኝ ጐኑን ወጋው ከጐኑም ደምና ውኃ ፈሰሰ። ይህንንም አይቶ እጅግ አደነቀ ከዚህም በፊት ፀሐይ እንደጨለመ፣ ጨረቃ ደም እንደሆነ፣ ዐለቱም እንደተሠነጠቀ፣ ሙታንም እንደተነሡ አይቶ ነበር።

#ጌታችንም በተነሣ ጊዜ ስለ ትንሣኤው የሆነውን ሰምቶ ይህን ምሥጢር ይገልጽለት ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ። ሐዋርያው ጴጥሮስንም ላከለት እርሱም ነቢያት ስለ #ጌታችን፣ ስለ መከራው፣ ስለ መሰቀሉ፣ ስለ መሞቱ፣ ስለ መነሣቱ፣ ስለ ዕርገቱም ትንቢት እንደተናገሩ ነገረው። እርሱም ከቅድስት #ድንግል በሥጋ ተወልዶ ዓለምን ለማዳን የመጣ የሕያው #እግዚአብሔር ልጅ #ክርስቶስ እንደሆነ አስረዳው።

ያን ጊዜም በቅዱስ ጴጥሮስ ቃል አመነ የምድራዊ ንጉሥ አገልግሎትንም ትቶ ወደ ቀጰዶቅያ ሔደ በውስጧም ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ ስም እንደ ሐዋርያት ሰበከ።

አይሁድም በጠላትነት ተነሡበት በመሳፍንትም ዘንድ ከሰሱት በላዩም የሐሰት ምስክር አስነሡበት ስለዚህም ራሱን በሰይፍ አስቆረጡት የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ በአደዋ ጦርነት ጊዜ ለረዳቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ከድሉ ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ መሐል ከተማ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ቤተክርስቲያን አሠሩ ስሟንም ገነተ ጽጌ ብለው ሰየሟት የባረኳትም ሊቀ ጳጳሱ ግብፃዊው አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱስ ጊዮርጊስ ልመናው አማላጅነቱ ከእኛ ጋር ይሁን አሜን!!! ተአምረ ጊዮርጊስ ተአምር 17 ላይ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_23)
#ነሐሴ_12

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ #ቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #ቅዱስ_ቈስጠንጢኖስ ወደ ሮሜ ከተማ ገባ በሮሜ አገሮችም ሁሉ ላይ ነገሠ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሚካኤል_ሊቀ_መላእክት

ነሐሴ ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

በዚች ቀን #እግዚአብሔር ወደ ዕሌኒ ልጅ ወደ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ልኮታልና ለእርሱም ጠላቶቹን እስከ አሸነፋቸው መንግሥቱም እስከ ጸናች ድረስ ኃይልን ሰጠው የጣዖታትንም ቤት አፍርሶ አብያተ ክርስቲያናትን ሠራ። በጌጥም ሁሉ አስጌጣቸው።

ስለዚህም አባቶቻችን የቤተክርስቲያን መምህራን የከበረ የመላእክት አለቃ የሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን እናደርግ ዘንድ አዘዙን።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ በከበረ መልአክ አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ታላቁ_ንጉሥ_ቅዱስ_ቆስጠንጢኖስ

በዚህችም ቀን ቈስጠንጢኖስ ወደ ሮሜ ከተማ ገባ በሮሜ አገሮችም ሁሉ ላይ ነገሠ።

(ዜናውም መጋቢት ሃያ ስምንት ቀን ላይ ተጽፏል።)
የዚህ ቅዱስ የአባቱ ስም ቍንስጣ የእናቱ ስም ዕሌኒ ነው ቊንስጣም በራንጥያ ለሚባል አገር ንጉሥ ነው መክስምያኖስም በሮሜ በአንጾኪያና በግብጽ ላይ ነግሦ ነበር።

ይህም ቍስጣ አረማዊ ነበር ግን በጎ ሥራ ያለው እውነትን የሚወድ በልቡናውም ይቅርታና ርኃራኄን የተመላ ክፋት የሌለበት ነው። ወደሮሐ ከተማ በሔደ ጊዜ ዕሌኒን አይቶ ሚስት ልትሆነው አገባት እርሷም ክርስቲያናዊት ናት። ንጉሥ ቈስጠንጢኖስንም ፀንሳ ወለደችው ስሙንም ቈስጠንጢኖስ ብላ ጠራቸው ይህም ዝንጉርጒር ማለት ነው።

ከዚህም በኋላ ንጉሥ ቊንስጣ ዕሌኒን በዚያው ትቷት ወደ በራንጥያ ከተማ ተመለሰ። እርሷም ልጇን እያሳደገች በዚያው ኖረች የክርስትናን ትምህርት አስተማረችው ይቅርታንና ርኅራኄን በክርስቲያን ወገኖች ላይ እንዲያደርግ በልቡናው ትዘራበት ነበር። እርሷ ክርስቲያን ስትሆን የክርስትና ጥምቀትን ታጠምቀው ዘንድ አልደፈረችም መንፈሳዊ ዕውቀትን ሁሉ በማስተማር አሳደገችው ዳግመኛም ለመንግሥት ልጆች የሚገባውንም ሁሉ።

ከዚያም በኋላ ወደ አባቱ ሰደደችው አባቱም በአየው ጊዜ ደስ ተሰኘበት ዕውቀትን የተመላ ሁኖ ፈረስ በመጋለብም ብርቱና የጸና ሆኖ አግኝቶታልና በበታቹም መስፍን አድርጎ ሹሞ በመንግሥቱ ሥራ ላይ ሁሉ ሥልጣን ሰጠው።

ከሁለት ዓመትም በኋላ አባቱ አረፈ ቈስጠንጢኖስም መንግሥቱን ሁሉ ተረከበ የቀና ፍርድንም የሚፈርድ ሆነ ከእርሱ በፊት የነበሩ ነገሥታት የጫኑባቸውን ጽኑ አገዛዝ ከሰዎች ላይ አስወገደ። አሕዛብም ሁሉ ታዘዙለት ወደዱትም የአገዛዙ ቅንነትና የፍርዱ ትክክለኛነት በአገሮች ሁሉ እስቲሰማ ተገዙለት።

የሮሜ ሰዎች ታላላቆች መልእክትን ወደርሱ ላኩ ከከሀዲ መክስምያኖስ ጽኑ አገዛዝ እንዲያድናቸው እየለመኑ እርሱ አሠቃይቷቸው ነበርና። መልእክታቸውንም በአነበቡ ጊዜ ስለ ደረሰባቸው መከራ እጅግ አዘነ ያድናቸውም ዘንድ ምን እደሚያደርግ በዐደባባይ ተቀምጦ እያሰበ ሲያዝን እነሆ ከቀኑ በስድስት ሰዓት በቀትር ጊዜ ኅብሩ እንደ ከዋክብት የሆነ መስቀል ታየው በላዩም በዮናኒ ቋንቋ ኒኮስጣጣን የሚል ጹሑፍ አለ ትርጓሜውም በዚህ ጠላትህን ድል ታደርጋለህ ማለት ነው።

#መስቀሉም ብርሃን የፀሐይን ብርሃን ሲሸፍነው በአየ ጊዜ አደነቀ። በላዩ ስለተጻፈውም አስቦ ለጭፍሮቹ አለቆችና ለመንግሥቱ ታላላቅ ባለሥልጣኖች አሳያቸው። እነርሱም ቢሆኑ ይህ መስቀል ስለምን እንደተገለጠ አላወቁም።

በዚያችም ሌሊት የ #እግዚአብሔር መልአክ ለቈስጠንጢኖስ በራእይ ተገልጦ እንዲህ አለው በቀኑ እኩሌታ በቀትር በአየኸው በዚያ #መስቀል አምሳል ላንተ ምልክት አድርግ በርሱም ጠላትህን ድል ታደርጋለህ አለው። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ልቡ ጸና የወርቅ መስቀልም አሠርቶ በነገሠበት ዘውድ ላይ አደረገው መኳንንቱንና ወታደሮቹን ጭፍሮቹን ሁሉ #መስቀል ሠርተው በጦር መሣሪያቸው ላይ ያደርጉ ዘንድ አዘዛቸው እነርሱም እንዳዘዛቸው አደረጉ።

ይህም የሆነው በበራንጥያ በነገሠ በሰባተኛ ዓመቱ ነው። የሮሜን ሰዎች ከሥቃያቸው ሊያድናቸው ሠራዊቱን ሰብስቦ ተነሥቶ ወጣ። መክስምያኖስም ሰምቶ በታላቅ ወንዝ ላይም ታላቅ ድልድይ ሠርቶ ወደ ቈስጠንጢኖስም ተሻግሮ ከእርሱ ጋራ ተዋጋ።

#መስቀሉም ምልክት ቀድሞ በታየ ጊዜ የመክስምያኖስ ሠራዊት ድል ይሆኑ ነበር የቈስጠንጢኖስም ሠራዊት ከመክስምያኖስ ሰራዊት ብዙ ሰው ገደሉ። የቀሩትም ሸሽተው ሲሔዱ ከመክስምያኖስ ጋር ሊሻገሩና ወደ ሮሜ ሊገቡ ድልድይ ላይ ወጡ ድልድዩም ፈርሶ ፈርዖን ከሠራዊቱ ጋራ እንደ ሠጠመ እንዲሁ መክስምያኖስ ከሠራዊቱ ጋራ ሠጠመ።

ቈስጠንጢኖስም ወደ ሮሜ ከተማ ሲገባ የሮሜ ሰዎች ከካህናት ጋራ መብራቶች ይዘው በእንቍ የተሸለሙ አክሊሎችን ደፍተው እምቢልታ እየነፉ ተቀበሉት የተማሩ ሊቃውንትም የከበረ #መስቀልን ሲያመሰግኑት የሀገራችን መዳኛ ይሉት ነበር ለከበረ #መስቀልም ሰባት ቀን በዓል አደረጉ።

ቈስጠንጢኖስም ዳግመኛ በሮሜ ነገሠ ከሀዲዎች የሆኑ መክስምያኖስና ዲዮቅልጥያኖስ ስለ ክብር ባለቤት ስለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖት ያሠሩአቸውን እሥረኞች ሁሉንም ፈታቸው ደግሞ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ ብሎ ዓዋጅ አስነገረ።

ዳግመኛም ክርስቲያኖችን እንዲአከብሩአቸው እንጂ እንዳያዋርዱአቸው የጣዖታቱንም ገንዘብና ምድራቸውን ለካህናት እንዲሰጧቸው አዘዘ ክርስቲያኖች በአረማውያን ላይ እንዲሾሙ አደረገ። ዳግመኛም አባቶቻችን ሐዋርያት እንዳዘዙ ማንም ሰው በሰሙነ ሕማማት ሥራ እንዳይሠራ አዘዘ።

በነገሠ በሥስራ አንድ ዓመት በሮሜ ሊቀ ጳጳሳት በሶል ጴጥሮስ እጅ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ። ሠራዊቱም ሁሉ። ይህም የከበረ #መስቀል ከተገለጠለት በኋላ በአራት ዓመት ነው።

ከዚህ በኋላም በእርሱ ርዳታና ድል ያገኘበትን የሚያድን ስለ ሆነ ስለ #ጌታችን_መስቀል ትመረምር ዘንድ እናቱ ዕሌኒን ወደ ኢየሩሳሌም ላካት። እርሷም ዐመፀኞች አይሁድ ቀብረው ከደፈኑት ቦታ አወጣችው።

በዘመኑ ሃይማኖታቸው የቀና የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ጳጳሳት የአንድነት ስብሰባ በኒቅያ ስለ አርዮስ ተደረገ። ለክርስቲያኖች መመሪያ በበጎ አሠራር ክርስቲያናዊት ሥርዓት ተሰራች።

ከዚህም በኋላ በበራንጥያ ታላቅ ከተማ ሊሠራ አሰበ እንደ አሰበውም ታላቅ ከተማ ሠርቶ በስሙ ቍስጥንጥንያ ብሎ ጠራት። በውስጧም አምላክን በወለደች በ #እመቤታችን_በቅድስት_ድንግል_ማርያም ስም በአግያና በሶፍያም ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሠራ መንፈሳዊ በሆነ በመልካም ጌጥ ሁሉ አስጌጣት። በውስጥዋ ከሐዋርያት የብዙዎቹን ዓፅም ከሰማዕታትና ከቅዱሳን ጻድቃን ሥጋቸውን ስለሚሰበስብ።

የክብር ባለቤት #ጌታችንን ደስ አሰኝቶ መልካም ተጋድሎውን ከፈጸመ በኋላ በኒቆምድያ ከተማ ጥቂት ታሞ መጋቢት ሃያ ስምንት አረፈ።

ገንዘውም በወርቅ ሣጥን አድርገው ተሸክመው ወደ ቊስጥንጥንያ አደረሱት የጳጳሳት አለቆችና ካህናቱ ከሁሉ ሕዝብ ጋር ወጥተው ተቀበሉት በብዙ ጸሎት በመዘመርና በማኅሌት በምስጋና ወደ ከበሩ ሐዋርያት ቤተ መቅደስ አስገብተው በክብር አኖሩት።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_እና_መጋቢት_28)
#መስከረም_6

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ስድስት በዚች ቀን ታላቅ ነቢይ የአሞጽ ልጅ #ቅዱስ_ኢሳይያስ አረፈ፣ #የአቡነ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ ዐፅማቸው ከዋልድባ አብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ዕለት ነው፣ #ቅድስት_ሰብልትንያ በዲዮቀልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ሞተች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ነቢዩ_ኢሳይያስ

መስከረም ስድስት በዚች ቀን ታላቅ ነቢይ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ አረፈ። ይህም ነቢይ ለይሁዳ በነገሡ በአምስቱ ነገሥታት ዘመን አስተማረ ትንቢትም ተናገረ እሊህም አዝያን ኢዮአታም አካዝ ሕዝቅያስና ምናሴ ናቸው።

በአካዝ ዘመንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ። እነሆ ስለዚህ #እግዚአብሔር ምልክትን ይሰጣችኋል። እነሆ ድንግል ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም #አማኑኤል ትለዋለች። ትርጓሜውም #እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ አንድ ሆነ ማለት ነው።

እርሱም በኃጢአታቸው ከሚመጣባቸው ፍዳ ወገኖቹን የሚያድናቸው ወደ ሃይማኖቱም የሚአስገባቸው እንደሆነ የእስራኤልንም ልጆች መሥዋዕታቸውንና ክህነታቸውን እንደሚሽር ከሐዲስ ወገኖችም የሚያመሰግኑት ካህናትን እንደሚሾም ተናገረ።

የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምም ኢየሩሳሌምን ከቦ የስድብ ቃልን በክብር ባለቤት በ #እግዚአብሔር ላይ በተናገረ ጊዜ የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምን ያጠፋው ዘንድ #እግዚአብሔር እንዳለው ለሕዝቅያስ ትንቢትን ተናገረ።

በዚያች ሌሊትም #እግዚአብሔር የላከው የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል ወደ ሠናክሬም ሰፈር መጥቶ ከፋርስ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ አርበኞችን ገደለ። የለኪሶ ሰዎች ሲነጋ በተነሡ ጊዜ የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ሁሉ አዩ።

ሕዝቅያስም ታሞ ለሞት በተቃረበ ጊዜ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደርሱ መጥቶ #እግዚአብሔር ትሞታለህ እንጂ አትድንም ብሏልና ቤትህን አዘጋጅ አለው። ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ ወደ #እግዚአብሔር ለመነ ፈጽሞ ጽኑ ልቅሶንም አለቀሰ።

ይህን ከነገረው በኋላ የ #እግዚአብሔር ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኢሳይያስ መጣ ሒደህ ለሕዝቅያስ የአባትህ የዳዊት ፈጣሪ #እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰማሁ ዕንባህንም አየሁ። እነሆ በዘመንህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት ጨመርኩልህ አለ በለው።

ዳግመኛም ስለ እስራኤል መማረክና ከምርኮ ስለ መመለሳቸው ትንቢት ተናገረ የፈሳሽ ውኃን ምንጭ በማፍሰስ በእጆቹ ላይ #እግዚአብሔር ምልክትን ገለጠ።

ክብር ይግባውና ስለ #መድኃኒታችን_ክርስቶስ መከራ ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ። እርሱም በመከራው ጊዜ ነገርን አልተናገረም እንደ በግ ይታረድ ዘንድ መጣ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንደ ማይናገር እንዲሁ በመከራው ጊዜ አልተናገረም።

ከዚህም በኋላ ደግሞ በሕዝቅያስ ልጅ በንጉሥ ምናሴ ላይ ትንቢት ተናገር ጣዖትን ስለማቆሙና ስለማምለኩ ገሠጸው። ስለዚህም ንጉሥ ምናሴ ተቆጥቶ በዕንጨት መሰንጠቂያ መጋዝ በራሱና በእግሮቹ መካከል ሠነጠቀው ምስክርነቱንም በዚህ ፈጸመ።

ትንቢት እየተናገረ የኖረበትም ዘመን ሰብዓ ዓመት ከዚያም በላይ ይሆናል። እርሱም ያስተማረው ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት በዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሦስት ዓመት ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ነብይ ኢሳይያስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የዋልድባው የአቡነ ሳሙኤል ዐፅማቸው ከዋልድባ አብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ዕለት ነው፡፡ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ትውልዳቸው ከካህናቱ ወገን አክሱም ነው አባታቸው እስጢፋኖስ እናታቸው አመተ ማርያም ይባላሉ። ለመምህር ሰጥተዋቸው ሲማሩ አድገው በኋላም ወላጆቻቸው በሞት ሲለዩአቸው ደብረ በንኰል ገዳም ገብተው ሥርዓተ ምንኩስናን ከአበው እያጠኑ ለትልቁም ለትንሹም በትሕትና እየታዘዙ ውሃ እየቀዱ እንጨት እየሰበሩ በትኅርምት በጽሞና በጸሎት ይኖሩ ነበር።

ሰይጣን በውዳሴ ከንቱ ጾር ቢመጣባቸው ከማሕበረ መነኮሳቱ ተለይተው በተባሕትዎ ለመኖር ሽተው ወጥተው ሲሔዱ ተከዜ ደረሱ። ወንዙ ሞልቶ የማያሻግራቸው ቢሆን ውሃውን በትምህርተ #መስቀል ባርከው በአንድ እጃቸው መጽሐፍ በአንድ እጃቸው መብራት እንደያዙ ገብተው መብራቱ ሳይጠፋ መጽሐፉ ሳይበላሽ ተሻግረዋል። ዋልድባ ሲደርሱ #ጌታ እዚህ ተቀመጥ ስላላቸው ገዳም መሥርተው ሥርዓተ ምንኩስናን እያስተማሩ ተቀመጡ። ዛሬ በዋልድባ የሚያመሰግኑበት #ውዳሴ_ማርያም #ቅዳሴ_ማርያምን ከተከዜ ወዲህ ያመጡ እሳቸው ናቸው። ይህንን እየጸለዩ ሲሔዱ ክንድ ከስንዝር መሬት ለቀው ይታዩ ነበር። አንድ ቀንም ይህንን ጸሎት ደግመው ውኃውን ቢባርኩት ኅብስተ ሕይወት ሆነላቸው ከነደቀ መዛሙርቶቻቸው ተመግበውታል።

#እመቤታችንም የፍቅር መግለጫ ዕጣን፣ ወርቅ፣ እንቁ ሰጥታቸዋለች። ውዳሴዬን ከቅዳሴዬ አንድ አድርጎ የደገመውን አንተ ከገባህበት መካነ ሕይወት አስገባዋለሁ ብላ ቃልኪዳን ሰጥታቸዋለች። ጊዜ እረፍታቸው ሲደርስ #ጌታን በስብሐተ መላእክት ተገልጦ በስምህ የተማጸነውን በጎ የሰራውን፣ ዜና ገድልህን የጻፈውን፣ ያስጻፈውን፣ ያነበበ፣ የተማረ፣ ያስተማረ፣ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ምሬልሃለሁ። በዚህ ቦታ በዋልድባ የሚሰበሰቡ ልጆችህን ከእዳ ከፍዳ እሰውርልሃለሁ አላቸው። እንኪያስ ቦታዋን ባርክልኝ ብለው እንደ መሶብ አንስተው አስባርከዋታል #ጌታችንም እህል አይብቀልብሽ ኃጢአት አይሻገርብሽ ብሎ ቃል ኪዳን ገባላት ለገዳመ ዋሊ። አባታችን አቡነ ሳሙኤል በበዓታቸው ውስጥ ጸንተው ሲኖሩ ታህሣሥ 12 ቀን ያረፉ ሲሆን ዛሬ መስከረም 6 ግን ፍልሰተ አጽማቸው የተከናወነበት እለት ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሰብልትንያ

በዚህችም ቀን ቅድስት ሰብልትንያ በከ*ሀዲ ንጉሥ ዲዮቀልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ሞተች። ይችንም ቅድስት ዕድሜዋ ዘጠኝ ዓመት ሲሆን ከሀ*ድያን ያዙዋት እጆቿንና እግሮቿንም አሥረው ከሚነድ እሳት ውስጥ ጣሏት የክብር ንጉሥ በሆነ በ #እግዚአብሔርም ኃይል ከእሳት ዳነች።

ውኃን በተጠማች ጊዜ #እግዚአብሔርን ለምናው ውኃን አፈለቀላትና ጠጣች ክብር ምስጉን የሆነ #ጌታችንንም አመሰገነችው። ከዚህም በኋላ ነፍሷን በ #እግዚአብሔር እጅ አደራ ሰጥታ ራሷን ከእሳት ውስጥ ወረወረች ምስክርነቷንም ፈጸመች።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_6 እና #ከገድላት_አንደበት)
#መስከረም_9

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዘጠኝ በዚህች የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል በሮም አገር ፍሩምያ በምትባል ከተማ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ነው፣ #ቅዱስ_አባት_አባ_ቢሶራ በሰማዕትነት አረፈ፣ #ቅዱስ_ያሳይ_ንጉሥ እረፍቱ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሊቀ_መላእክት_ቅዱስ_ሚካኤል

መስከረም ዘጠኝ በዚህች ቀን በሮም አገር ፍሩምያ በምትባል ከተማ ለሆነው ተአምር መታሰቢያ ሆነ። ይህም እንዲህ ነው የሰማይ ሠራዊት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ በሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚታዩ ድንቆችና ተአምራቶች ምክንያት ዮናናውያን ሰዎች ሰይጣናዊ ቅናትን እንደ ቀኑ ከመቅናታቸውም ብዛት የተነሣ በዚያ አካባቢ የሚወርደውን የወንዝ ውኃ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊመልሱትና ከሚጠብቃት መጋቢዋ ጋር በውኃ ስጥመት ሊአጠፉአት ፈልገው መለሱት።

የሰማያውያን ሠራዊት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለቤተ ክርስቲያኑ መጋቢ ለናርጢኖስ ተገለጠለት ወደርሱም ቀርቦ ጽና አትፍራ አለው ይህንን ብሎ በእጁ ውስጥ ባለ በትር አለቱን መታው አለቱም ተሰንጥቆ እንደ በር ሆነ የዚያ ወንዝ ውኃም በውስጡ አልፎ ሔደ።

ይህንንም ያዩ ምስጉን #እግዚአብሔርን አመሰገኑት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልንም አከበሩት። ከዚያች ቀን እስከ ዛሬ የወንዙን ውኃ በዚያች በተሠነጠቀች አለት ውስጥ አልፎ ሲሔድ ያዩታል ወደ መላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ከቶ አይቀርብም።

#ለእግዚአብሔርም ምሽጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_አባ_ቢሶራ

በዚህችም ቀን መጺል የምትባል አገር ኤጲስቆጶስ ቅዱስ አባት አባ ቢሶራ በሰማዕትነት አረፈ።

ይህም ቅዱስ በግብጽ አገር #እግዚአብሔርን በምትወድ መጺል በምትባል ከተማ ኤጲስቆጶስ ሆነ። ዲዮቅልጥያኖስም ነግሦ ክርስቲያኖችን በሚያሠቃያቸው ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ክርስቶስ ስም ደሙን ያፈስ ዘንድ ይህ አባት ወደደ።

ሕዝቡንም ሀሉ ሰብስቦ በቤተ መቅደሱ ፊት በዐውደ ምሕረቱ አቆማቸው ሊጠብቁት የሚገባውን ለጽድቅ የሚያበቃቸውን ትእዛዝ ሁሉ አዘዛቸው። ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና በ #ክርስቶስ ስም ደሙን ማፍሰስ እንደሚሻ ነገራቸው ይህንንም በሰሙ ጊዜ ታላቆችም ታናሾችም በላዩ አለቀሱ።

የሙት ልጆች እንሆን ዘንድ የምትተወን ምን ያደርግልሃል እኛስ እንድትሔድ አንለቅህም አሉት ሊይዙትም ቃጡ ግን አልተቻላቸውም ተውትም እርሱም ወደ ክብር ባለቤት #ክርስቶስ አደራ አስጠበቃቸውና ሰላምታ ሰጥቷቸው ከእነርሱ ዘንድ ወጥቶ ተጓዘ። እነርሱም መሪር ልቅሶን እያለቀሱ ሸኙት።

ስማቸው ቢስኮስ ፊናቢክስ ቴዎድሮስ የሚባሉ ኤጲስቆጶሳት አብረውት ሔድ መኰንኑ ወደ አለበት አገርም ደርሰው የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመኑ። እርሱም መኰንኑ አሠቃያቸው ኤጲስቆጶሳትም እንደሆኑ አውቆ ሥቃያቸውን አበዛ እሊህ አባቶች ግን በታላቅ ትዕግሥት የጸኑ ናቸው። ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ ያጸናቸዋልና።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ የሕይወት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። የቅዱስ ቢሶራ ሥጋው ግን ንሲል በሚባል አገር እስከ ዛሬ ይኖራል።

#ለእግዚአብሔርም ምሽጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ያሳይ_ንጉሥ

በዚችም ቀን ተጋድሎውን በዛፍ ላይ ሆኖ የፈጸመ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘ ንጉሥ ያሳይ አረፈ።

በቀደመው ዘመን መንግስታቸውን ትተው ከመነኑ ነገሥታት አንዱ ቅዱስ ያሳይ ነው። ምናኔ በቁሙ ከባድ ነው። መንግስትን፣ ዙፋንን፣ ክብርን ትቶ መመነንን ደግሞ ከማድነቅ በቀር እንዲህ ብለው ሊገልጹት ይከብዳል።

ቅዱስ ያሳይም መንግስቱን ትቶ ልምላሜ ወደሌለበት ደረቅ በርሃ ሔደ። በዚያም ከአንዲት ዛፍ በቀር ምንም ነገር አላገኘም። በዚያች ደረቅ ዛፍ ላይ ወጥቶ ለዓመታት በጾምና በጸሎት ተጋደለ።

በዘመነ ተጋድሎው ከዛፏ አልወረደም ሰውም አይቶ አያውቅም። በመጨረሻም ስለ ቅድስናው ዛፏ ለምልማለች። እርሱም በዚህች ቀን ዐርፏል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም
በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_9_ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
#መስከረም_12

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥራ ሁለት መላእክት አለቃ #የቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #ጉባኤ_ኤፌሶን የቅዱሳን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ ሆነ

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሚካኤል_ሊቀ_መላእክት

መስከረም ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

በዚችም ቀን ክብር ይግባውና #እግዚአብሔር ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢይ ኢሳይያስ ላከው ይቅርም ብሎት ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስ ሒዶ #እግዚአብሔር ይቅር እንዳለውና ከደዌው እንዳዳነው በዕድሜውም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እንደ ጨመረለት ይነግረው ዘንድ አዘዘው። ንጉሱም ሚስት አግብቶ ምናሴን እስከወለደው ድረስ እንዲሁ ሆነ።

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ለንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገለት ተአምር፡-

ከጻድቁ ንጉሥ ከቅዱስ ዳዊት በኋላ በእስራኤል እንደ ሕዝቅያስ ያለ ሌላ ጻድቅ ንጉሥ አልተነሣም፡፡ ከሕዝቅያስ በኋላ የተነሡት ሁሉም ጣዖትን አምልከዋል፣ ለጣዖታቱም የሚሆን መሠዊያ ሠርተዋል፡፡ ንጉሡ ሕዝቅያስ በነገሠ ጊዜ ግን ጣዖታትን ሰባብሯቸዋል፣ የእስራኤል ልጆች ያመልኩት የነበረውን የነሐስ እባብ ቆራርጦታል፡፡ #እግዚአብሔርንም በማመኑ መንግሥቱ እጅግ ሰምሮለታል፡፡ #እግዚአብሔርም ያሳጣው በጎ ነገርም የለም፡፡

ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዘመን የፋርሱ ነጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ኢየሩሳሌምን ከበባት፡፡ ይህም ሰናክሬም በወቅቱ እንደ እርሱ ያለ ኃይለኛ የለም ነበርና ሁሉም የምድር ነገሥታት ይፈሩትና ይገዙለት ነበር፡፡ ሕዝቅያስም ከሰናክሬም ግርማና የጦሩ ብዛት የተነሣ ፈርቶ ኢየሩሳሌምን እንዳያጠፋት ብዙ ወርቅና ብር እጅ መንሻ ቢልክለትም ሰናክሬም ግን እጅ መንሻውን አልቀበልም ብሎ ኢየሩሳሌምን ያጠፋ ዘንድ ተነሣ፡፡ ለሕዝቅያስም ‹‹አምላካችሁ #እግዚአብሔር ከእኔ እጅ ሊያደናችሁ ከቶ አይችልም›› የሚል የስድብን ቃል ላከለት፡፡

ሁለተኛም በልዑል #እግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል ጽፎ ደብዳቤ ላከለት፡፡ ሕዝቅያስም ይህን ሲሰማ ወደ #እግዚአብሔር ቤት ገብቶ አለቀሰ፡፡ ልብሱንም ቀዶ ማቅ በመልበስ የሰናክሬምን ድፍረትና በኢየሩሳሌምና በሕዝቧ ላይ ሊያደርስ ያሰበውንም ጥፋት ወደ #እግዚአብሔር አሳሰበ፡፡ ቀጥሎም ሕዝቅያስ ሰናክሬም የተናገረውን ይነግሩት ዘንድ ስለ ሕዝቡም እንዲጸልይ ለነቢዩ ኢሳይያስ መልእክት ላከበት፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ #እግዚአብሔር አመለከተ፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ስለ ንጉሡ ለነቢዩ መልእክትን አመጣለት፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም የመጣለትን መልስ እንዲህ ብሎ ለሕዝቅያስ ላከለት፡- ‹‹ልብህን አጽና፣ አትፍራ፡፡ በዓለሙ ሁሉ እንደ እርሱ ያለ ያልተሰማ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥራ በሰናክሬም ላይ #እግዚአብሔር ይሠራል›› አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል#እግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ መጥቶ 185,000 (መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ) የፋርስ ሠራዊቶችን በአንድ ሌሊት ገደላቸው፡፡ 2ኛ ነገ 17፣19፡፡ የለኪሶ ሰዎችም ሲነጋ በተነሡ ጊዜ ምድሪቱን በእሬሳ ተሞልታ ስላገኟት በድንጋጤና በፍርሃት ከንጉሣ ጋር ሸሽተው ነነዌ አገር ገቡ፡፡

ንጉሡ ሰናክሬምም ወደ አምላኩ ወደ ጣዖቱ ቤት ገብቶ ሲጸልይ የገዛ ልጆቹ በሰይፍ መትተው ገደሉትና ወደ አራራት ኩበለሉ፡፡2ኛ ነገ ምዕራፍ 19፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስም ከሰናክሬም እጅ ያዳነውን #እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡

ከዚህም በኋላ ሕዝቅያስ ታሞ ለሞት በደረሰ ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ ‹‹ #እግዚአብሔር ‹ትሞታለህ እንጂ አትድንም› ብሎሃል›› አለው፡፡ ነገር ግን ሕዝቅያስ አሁንም ልብሱንም ቀዶ ማቅ በመልበስ ጸሎቱን ወደ #እግዚአብሔር አቀረበ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ቅዱስ ሚካኤል #እግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ መጥቶ ነቢዩ ኢሳይያስን ወደ ንጉሡ ሕዝቅያስ ሄዶ በዕድሜው ላይ 15 ዓመት እንደተጨመረለት እንዲነግረው ያዘዘው፡፡

መልአኩ እንዳዘዘው ነቢዩ ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስን " #እግዚአብሔር የአባትህ የዳዊት አምላክ ጸሎትህን ሰማሁ፣ ዕንባህንም አየሁ፣ እነሆ እኔ አድንሃለሁ፡፡ በዘመኖችህም 15 ዓመት ጨምሬልሃለሁ፡፡ ከፋርስ ንጉሥ እጅም አድንሃለሁ፡፡ ይህችን አገር ስለ እኔና ስለ ባለሟሌ ዳዊት አጽንቼ እጠብቃታለሁ›› ብሎሃል ብሎ የተላከውን ነገረው፡፡ ከዚህም በኃላ ንጉሥ ሕዝቅያስ የ #እግዚአብሔር ኃይል ስላደረበት የምድር ነገሥታት ሁሉ ፈርተውት እየተገዙለት እጅ መንሻን ያገቡለት ጀመር፡፡ ንጉሡም ዕድሜው ከተጨመረለት በኃላ ሚስት አግብቶ ምናሴን እስኪወልድ ድረስ ቆየ፡፡ በመንበረ መንግሥቱም 29 ዓመት ነግሦ ከኖረ በኋላ #እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም ዐረፈ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጉባኤ_ኤፌሶን

በዚችም ቀን ደግሞ በኤፌሶን ከተማ የቅዱሳን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ ሆነ ይህም ለታላላቆች ጉባኤያት ሦስተኛ ነው።

ስብሰባቸውም የተደረገው የታላቁ ቴዎዶስዮስ ልጅ አርቃድዮስ የወለደው ታናሹ ቴዎዶስዮስ በነገሠ በሃያ ዓመት ነው። የስብሰባቸውም ምክንያት የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በንስጥሮስ ነው። እርሱ ስቶ እንዲህ ብሏልና እመቤታችን #ድንግል_ማርያም አምላክን በሥጋ አልወለደችውም እርሷ ዕሩቅ ሰውን ወልዳ ከዚህ በኋላ በውስጡ የ #እግዚአብሔር ልጅ አደረበት ከሥጋ ጋር በመዋሐድ አንድ አልሆነም በፈቃድ አደረበት እንጂ። ስለዚህም ክርስቶስ ሁለት ጠባይ ሁለት ባህርይ አሉት የተረገመ የከ*ሐዲ ንስጥሮስ የከፋች ሃይማኖቱ ይቺ ናት።

ስለ እርሱም የተሰበሰቡ እሊህ አባቶች ከእርሱ ጋር ተከራከሩ ከቅድስት #ድንግል_ማርያም የተወለደው አምላክ እንደሆነ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ በአበሠራት ጊዜ ከተናገረው ቃል ምስክር አመጡ። እንዲህ የሚል #እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው ከአንቺ የሚወለደውም ጽኑዕ ከሀሊ ነው የልዑል #እግዚአብሔር ልጅም ይባላል ።

ዳግመኛም እነሆ #ድንግል በድንግልና ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች ብሎ በትንቢቱ ከተናገረው ከኢሳይያስ ቃል ሁለተኛም ከእሴይ ዘር ይተካል ከእርሱም ለአሕዛብ ተስፋቸው ይሆናል።

ዳግመኛም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ ገሠጸው መከረው ስለዚህም እንዲህ ሲል አስረዳው ክብር ይግባውና የ #ክርስቶስ የመለኮቱና የትስብእቱ ባሕርያት በመዋሐድ አንድ ከሆኑ በኋላ አይለያዩም አንድ ባሕርይ በመሆን ጸንተው ይኖራሉ እንዲህም አምነን ሰው የሆነ #እግዚአብሔር ቃል አንዲት ባሕርይ ነው እንላለን።

ከ*ሀዲ ንስጥሮስ ግን ከክፉ ሐሳቡ አልተመለሰም ከሹመቱም ሽረው እንደሚአሳድዱትም ነገሩት። እርሱ ግን የጉባኤውን አንድነት አልሰማም ስለዚህም ከሹመቱ ሽረው ረግ*መው ከቤተ ክርስቲያን ለይተው አሳደ*ዱት ወደ ላይኛውም ግብጽ ሒዶ በዚያ ምላሱ ተጎልጒሎ እንደ ውሻ እያለከለከ በክፉ አሟሟት ሞተ።

እሊህም ሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት አባቶች ሃይማኖትን አጸኑዋት በዚህም ጉባኤ ውስጥ እንዲህ ብለው ጻፉ እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያም ከእርሷ ሰው የሆነውን የ #እግዚአብሔርን አካላዊ ቃል በሥጋ ወለደችው።

ከዚህም በኋላ ሥርዓትን ሠርተው ሕግንም አርቅቀው በእጆቻቸው ጽፈው ለምእመናን ሰጡ። እኛም የሕይወትንና የድኅነትን መንገድ ይመራን ዘንድ #እግዚአብሔርን እንለምነው። ለእርሱም ክብር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
ሁለተኛም የራጉኤልን ልጅ ሣራን ያገባት ዘንድ ተናገረው #እግዚአብሔርም ይጠብቀዋልና እንዳይፈራ አጽናናው። ወደራጉኤል ቤትም በደረሱ ጊዜ ሣራ ተቀብላ ደስ አሰኘቻቸው ከዚህም በኋላ ጦቢያ ሣራን ወደዳት። እርሷንም ይሰጠው ዘንድ አባቷን ጠየቀው አባቷም ለሰባት ባሎች አጋብቷት ሰባቱም እንደሞቱ ነገረው ጦብያም የ #እግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን አለ።

ወደ ጫጉላ ቤትም በአገቧቸው ጊዜ ሩፋኤል የነገረውን ቃል አስታወሰ የዓሣውንም ጉበትና ልብ ከደቀቀ ዕጣን ጋር አጤሰ ያን ጊዜ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን ሸሸ መልአክ ሩፋኤልም ይዞ ለዘላለሙ አሠረው።

ጦቢያም ሚስቱን ሣራን ይዞ ደስ ብሎት ወደ አባቱ ቤት ተመለሰ አባትና እናቱም በደስታ ተቀበሉት የአባቱንም ዐይኖች በኳለ ጊዜ እንደ ጭጋግ ሁኖ ከዐይኖቹ ተገፈፈ ዐይኑን ዐሸ ወዲያውኑ ድኖ ልጁን አየ። ከዚህም በኋላ የከበረ መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ራሱን ገለጠላቸው ብዙ ነገርንም ነግሮአቸው ወደ ሰማይ ዐረገ።

ከዚህም በኋላ ከወገኖቹ ጋር ተድላ ደስታን አደረገ ክብር ይግባውና ስለ #ክርስቶስ መከራ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ እርሱ በኃጢአታችን ይገርፈናል ደግሞ እርሱ ይቅር ይለናል ሁለተኛም መከራህን የሚያስቡ የተመሰገኑ ናቸው ። እነርሱ ክብርህን በአዩ ጊዜ በአንተ ደስ ይላቸዋልና አለ።

ዳግመኛም ስለ ኢየሩሳሌም መታነፅ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ ኢየሩሳሌም ሰንፔር መረግድ በሚባል በከበረ ዕንቁ ትሠራለች ድልድልዋ፣ ቅጽርዋ፣ አደባባይዋ፣ ደጆቿም በከበረ ዕንቊ በጠራም ወርቅ ይሠራሉ አደባባይዋም ቢረሌ፣ አትራኮስ፣ ሶፎር በሚባል ዕንቁ ይሠራልና በመንገድዋ ሁሉ ሁሉም #እግዚአብሔርን አስቀድሞ የነበረ ወደፊትም የሚኖር እያሉ ያመሰግኑታል ደግሞም ከዓለማት ሁሉ ጽዮንን ከፍ ከፍ ያደረጋት #እግዚአብሔር ይመስገን ይላሉ።

ሁለተኛም የእስራኤል ምርኮኞች ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመለሱ ትንቢት ተናገረ ሁለተኛም ደግሞ ዮናስ ከነነዌ እንዲወጣ ልጁን ጦብያን አዘዘው። ዳግመኛም ልጁን እንዲህ አለው ልጄ ሆይ ምጽዋት እንደምታድንና እንደምታጸድቅ ተመልከት ይህን ተናግሮ በዐልጋው ላይ ሳለ በመቶ ኀምሳ ስምንት ዘመኑ አረፈ በክብርም ቀበሩት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ጦቢት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_አጋቶን_ባህታዊ

በዚህ ቀን ታላቁ አባት አባ አጋቶን አረፈ፡፡ ይህን ቅዱስ ታላቅ ጻድቅ ገዳማዊና የ #እግዚአብሔር ሰው ሲሆን አንደበቱን ከክፋት ይከለክል ዘንድ ለ30 ዓመታት ድንጋይ ጐርሶ ኖሯል። ይህንን ቅዱስ ሊቃውንት ሲገልጹት "ክምረ ክምር ጽድቁ እስከ አስተርአየ" ይሉታል። ትእግስቱ ደግነቱ አርምሞው ትሩፋቱ ከመነገር በላይ ነው። በነበረበት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም እንደ ኮከብ ያበራ ታላቅ አባት ነው።

ታላቁ ገዳማዊ አባት አጋቶን የታላቁ መቃርዮስ የመንፈስ ልጅ ነው። ገዳመ አስቄጥስ እልፍ አእላፍ ቅዱሳንን ስታፈራ ይህ አባት ቅድሚያውን ይይዛል። ምንም በብዛት የሚታወቀው በአርምሞው (በዝምታው) ቢሆንም ባለ ብዙ ትሩፋት አባት ነው። የሚገርመው የቀደሙ አባቶቻችን የፈለገውን ያህል መናኝ ቢሆኑም የሰው ጥገኛ መሆንን አይፈልጉም። "ሊሠራ የማይወድ አይብላ" የሚለውን መለኮታዊ ትዕዛዝ መሠረት አድርገው ከተጋድሎ በተረፈቻቸው ሰዓት ሥራ ይሠራሉ። አንዳንዶቹ እንደሚመስላቸው ምናኔ ሥራ መፍታት አይደለምና ሰሌን ዕንቅብ ሠፌድ የመሳሰለውን ይሠፋሉ። ታላቁ አባ አጋቶንም በአንደበቱ ድንጋይ ጐርሶ በእግሮቹ ቀጥ ብሎ ቆሞ እንቅቦችን ይሠፋ ነበር። ቅዱሱ የሰፋውን ወደ ገበያ ይወጣል በጠየቁትም ዋጋ ሽጦት አንዲት ቂጣ ይገዛል። የተረፈውን ገንዘብ ግን እዚያው ለነዳያን አካፍሎት ይመጣል እንጂ ወደ ገዳሙ አይመልሰውም።

አንድ ቀን እንደልማዱ የሠፋቸውን እንቅቦች ተሸክሞ ወደ ገበያ ሲሔድ መንገድ ላይ አንድ የኔ ቢጤ ወድቆ ያገኛል። እንደ ደረሰም ስመ #እግዚአብሔር ጠርቶ ይለምነዋል። አባ አጋቶን ከእንቅቦቹ ውጪ ምንም ነገር አልነበረውምና "እንቅቡን እንካ" አለው። ነዳዩ ግን ወይ የሚበላ ካልሆነም ገንዘብ እንደሚፈልግ ይነግረዋል። ወዲያው ደግሞ "የምትሠጠኝ ነገር ከሌለህ ለምን ወደ ገበያ ተሸክመህ አትወስደኝም?" አለው። የነዳዩ አካል እጅግ የቆሳሰለ በመሆኑ እንኩዋን ሊሸከሙት ሊያዩትም የሚከብድ ነበር። ጻድቁ ግን ደስ እያለው ያለማመንታት አንስቶ ተሸከመው። ከረጅም መንገድ በኋላ ከገበያ በመድረሳቸው አውርዶ ከጐኑ አስቀመጠው። ያ ነዳይ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ ቢለምንም የሚዘከረው አጣ። አባ አጋቶን አንዷን እንቅብ ሲሸጥ "ስጠኝ?" ይለዋል። ጻድቁም ይሠጠዋል። እንዲህ "ስጠኝ" እያለ የእንቅቦችን ዋጋ ያ ነዳይ ወሰደበት። አባ አጋቶን ግን ምንም ቂጣ ባይገዛም በሆነው ነገር አልተከፋምና ሊሔድ ሲነሳ ነዳዩ "ወደ ቦታየ ተሸክመህ መልሰኝ" አለው። አባቶቻችን ትእግስታቸው ጥግ የለውምና ጐንበስ ብሎ በፍቅር አንስቶት አዘሎት ሔደ። ካነሳበት ቦታ ላይ ሲደርሱ ይወርድለት ዘንድ ጻድቁ ቆመ። ነዳዩ ግን አልወርድም አለ። ትንሽ ቆይቶ ግን ለቀቀው ሊያየው ዞር ቢል መሬት ላይ የለም። ቀና ሲል ግን ያየውን ነገር ማመን አልቻለምና ደንግጦ በግንባሩ ተደፋ። ነዳይ መስሎ እንዲያ ሲፈትነው የነበረው ሊቀ መላእክት #ቅዱስ_ሚካኤል ነበርና ክንፎቹን ዘርግቶ በብርሃን ተከቦ በግርማ ታየው ከወደቀበትም አነሳው። "ወዳጄ አጋቶን ፍሬህ ትእግስትህ ደግነትህ ግሩም ነውና ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎት ተሰወረው፤ ጻድቁም በደስታ ወደ በዓቱ ሔደ። አባ አጋቶን ተረፈ ዘመኑን በአርምሞ ኑሮ ዐርፏል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_16)
#ጥቅምት_12

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት አስራ ሁለት በዚህች ዕለት ሊቀ መላእክት #ቅዱስ_ሚካኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ #ቅዱስ_ዳዊትን በሳኦል ፈንታ እንዲሾመው ለሳሙኤል የነገረበት እና በጎልያድ ላይ ኃይልን የሰጠበት እንዲሁም የወንጌላዊው #ቅዱስ_ማቴዎስ እና #የቅዱስ_ድሜጥሮስ የዕረፍት ቀን ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዳዊት_ልበ_አምላክ (የነገሠበት)

ጥቅምት ዐሥራ ሁለት በዚች ዕለት የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ የሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። በዚችም ቀን ወደ ነቢይ ሳሙኤል #እግዚአብሔር ልኮታልና የዳዊት አባት ወደሆነ በቤተ ልሔም ወደሚኖር ወደ እሴይ ቤት ይሔድ ዘንድ በቂስ ልጅ በሳኦልም ፈንታ ለእስራኤል ልጆች እንዲነግሥ ልጁ ዳዊትን ይቀባው ዘንድ አዘዘው።

ሳሙኤልም ወደ እሴይ ቤት ሔዶ ልጆችህን ሁሉንም አቅርብልኝ ብለው እሴይም ከዳዊት በቀር ሁሉንም አቀረባቸው እርሱ በእርሻ ውስጥ በጎችን ይጠብቅ ነበርና።

ሳሙኤልም የመንግሥት ቅባት ያለበትን ብልቃጥ በራሳቸው ላይ ከፍ ከፍ በአደረገ ጊዜ #እግዚአብሔር አልመረጣቸውም ። ሳሙኤልም እሴይን ልጆችህ እነዚህ ብቻ ናቸውን አለው ዕሴይም በጎች የሚጠብቅ አንድ ትንሽ ልጅ አለ አለው።

ሳሙኤልም ደግሞ ዕሴይን እሱ ሳይመጣ ምሳ አልበላምና ልከህ አስመጣው አለው። እሱም ልኮ አስመጣው መልኩም ቀይ ዐይኖቹም የተዋቡ አርአያውም ያማረ ነው #እግዚአብሔርም ሳሙኤልን ይህ ይበልጣቸዋልና ተነሥተህ ቅባው አለው። በዚያንም ጊዜ ሳሙኤል የመንግሥት ቅባት ያለበትን ቀንድ አምጥቶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው ከዚያችም ቀን ጀምሮ ለሁል ጊዜ የ #እግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ አደረበት በእስራኤል ልጆችም ላይ ነገሠ።

ደግሞ ሁለተኛ በዚች ቀን #እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ወደ ዳዊት ላከው ረዓይታይ ጎልያድን እስኪገድለውና የእስራኤልን ልጆች እስከሚያድናቸው ረድቶ ኃይልን ሰጠው።

ስለዚህም የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን እናደርግ ዘንድ የቤተክርስቲያን መምህራን አዘዙን።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያው_ቅዱስ_ማቴዎስ

#የጌታችን_አምላካችንና_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን አምላካዊ ትእዛዝ ተቀብለው ወንጌልን ለመላው ዓለም በማብሠር መምለክያነ ጣዖትን ወደ አሚነ #እግዚአብሔር፣ አሕዛብን ወደ ክርስትና ከመለሱ ቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ አንደኛው ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ አገሩ ናዝሬት፣ የዘር ሐረጉም ከይሳኮር ነገድ ሲኾን አባቱ እልፍዮስ (ዲቁ)፣ እናቱ ደግሞ ካሩትያስ ይባላሉ፡፡

ለደቀ መዝሙርነት ከመመረጡ በፊት ‹ሌዊ› ይባል ነበረ፤ ከተጠራ በኋላ ግን ‹ማቴዎስ› ተብሏል፡፡ ‹ማቴዎስ› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹ጸጋ #እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ስጦታ)› ማለት ሲኾን ስሙን ያወጣለትም #ጌታችን_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ነው፡፡ ለወንጌል አገልግሎት የተጠራውም በቅፍርናሆም ከተማ ከቀራጭነት ሥራ ላይ ነው /ማቴ. ፱፥፱-፲፫፤ ሉቃ. ፭፥፳፯-፴፪/፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ቍጥሩ ከ፲፪ቱ ሐዋርያት ሲኾን ከ፬ቱ ወንጌሎች አንደኛውን የጻፈው እርሱ በመኾኑ ‹ወንጌላዊ› እየተባለ ይጠራል፡፡ ወንጌሉን የጻፈውም ጌታችን ባረገ በ፰ኛው ዓመት መጨረሻ በ፵፩ /፵፪ ዓ.ም፣ ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በመጀመሪያው ዘመን በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው /ማቴ.፳፰፥፳/፡፡ ጽሕፈቱንም በፍልስጥኤም ጀምሮ በህንድ ፈጽሞታል፡፡

እንደ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ወንጌሉ በውስጡ ከ፻፶ በላይ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን ማካተቱ አይሁድን ለማሳመን የተጻፈ ለመኾኑ ማስረጃ ነው፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ከኦሪታዊ ይዘቱ አኳያ በመጀመሪያ ተቀመጠ እንጂ የተጻፈው ግን ከማርቆስ ወንጌል ቀጥሎ እንደኾነም መምህራን ይናገራሉ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በሀገረ ስብከቱ በፍልስጥኤም #ጌታችን ከፅንስ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ድረስ ያደረጋቸውን ተአምራት፣ ያስተማረውን ትምህርትና የሠራቸውን ትሩፋቶች ሲያስተምራቸው ብዙ አሕዛብ ከኦሪት ወደ ወንጌል፤ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመልሰዋል፡፡ ምእመናኑ ‹‹በቃል ያለ ይረሳል፤ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳልና ያስተማርኸንን ጻፍልን›› ብለውት፤ አንድም እንደ አባትነቱ ከራሱ አንቅቶ /አመንጭቶ/፤ አንድም አይሁድ ክርስቲያኖችን ‹‹ክርስቶስ ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም መኾኑን ሠፍራችሁ፣ ቈጥራችሁ አስረዱን›› ቢሏቸው ለማስረዳት የዕውቀት ማነስ ነበረባቸውና እርሱ ጽፎላቸዋል፡፡

ወንጌሉን ከጻፈ በኋላም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ አፓንጌ በሚባል አገር ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን በ #ክርስቶስ አሳምኗል፡፡ የማቴዎስን ወንጌል ወንጌላዊው /ሐዋርያው/ ዮሐንስ በእልአንሳን፣ በህንድና በኢየሩሳሌም አገሮች እየተረጐመ አስተምሮታል፡፡ የእርሱ ስብከት በመጽሐፍ ቅዱስ አለመጠቀሱም መላ ሕይወቱን ለ #ክርስቶስ አገልግሎት የሰጠ ሐዋርያ መኾኑን እንደሚያሳይ መምህራን ይመሰክራሉ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ‹‹ወልደ ዳዊት፣ ወልደ አብርሃም›› በማለት የ #ክርስቶስን ምድራዊ ልደት /ሰው መኾን/ ጽፏልና ከአራቱ የኪሩቤል ገጽ መካከል በአንደኛው በገጸ ሰብእ ይመሰላል፡፡ የኤፌሶን ወንዝ ፈለገ ሐሊብ ይባላል፤ ርስትነቱም ለሕፃናት ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም በዘር የሚወለዱ አበውን ልደት ጽፏልና፤ ዳግመኛም ሄሮድስ ስላስፈጃቸው ሕፃናት ተናግሯልና በኤፌሶን ወንዝ ይመሰላል፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልን አስተምሮ ብዙዎችን ወደ አሚነ #እግዚአብሔር ከመለሰ በኋላ #ጌታችን ወደ ካህናት አገር እንዲሔድና የካህን ልብስ ለብሶ፣ ፀጉሩንና ጺሙን ተላጭቶ፣ በቀኝ እጁ ዘንባባ ይዞ ወደ አገሩ ቅፅር እንዲገባ ስላዘዘው በደመና ተጭኖ ሔዶ ወደ ቤተ ጣዖታቱ ገብቶ በጸለየ ጊዜ መብረቅ የመሰለ ብርሃን ወረደ፡፡ የአምላክን ከሃሊነት ለመግለጥ በተከሠተው ርዕደ መሬትም የአገሩ ጣዖታት ኹሉ ወድቀው ተሰባበሩ፡፡ አርሚስ የሚባለው የጣዖቱ ካህንም ካየው አምላካዊ ብርሃንና ድንቅ ተአምር የተነሣ በ #ክርስቶስ አምኖ ከተጠመቀ በኋላ የቅዱስ ማቴዎስ ረድእ ኾኗል፡፡

ይህ ክሥተትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙዎችን በ #ክርስቶስ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል፡፡ ያማኞች ቍጥርም ፬ ሺሕ እንደ ነበረ በገድለ ሐዋርያት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በኋላ የንጉሡ ልጅ በሞተ ጊዜ ቅዱስ ማቴዎስ ወደ #እግዚአብሔር ጸልዮ ከሞት ቢያስነሣው ንጉሡ፣ ቤተሰቦቹና የአገሩ ሰዎች ኹሉ በ #ኢየሱስ_ክርስቶስ አምነው አጵሎን የተባለውን ጣዖት በእሳት አቃጥለው ቤተ ጣዖቱን የአምልኮተ #እግዚአብሔር መፈጸሚያ ሥፍራ አድርገውታል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም አርሚስን ኤጲስ ቆጶስ በማድረግ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾሞላቸዋል፡፡

በገድለ ሐዋርያት እንደ ተጠቀሰው ቅዱስ ማቴዎስ ከማረፉ በፊት በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል፤ በዚያም ሄሮድስ በግፍ በጨፈጨፋቸው ሕፃናት ክብረ በዓል #ጌታችን ወደ እነርሱ ሲመጣ፣ መላእክትም በዙሪያው ከበው ሲያመሰግኑት ያይ ነበር፡፡ ከዚያ ተመልሶም በየአገሩ እየዞረ ወንጌልን አስተምሯል፤ ካስተማረባቸው አገሮችም ፍልስጥኤም፣ ፋርስ፣ ባቢሎን፣ ኢትዮጵያና ዓረቢያ ይጠቀሳሉ፡፡ የማስተማር ተልእኮው የተከናወነውም በታንሿ እስያ ውስጥ ነው፡፡ ግሪካውያን አሕዛብ «አምላካችንን ሰደበብን» ብለው አሥረውት በነበረ ጊዜም ወኅኒ ቤት ኾኖ ይሰብክ ነበር፡፡