ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
4.83K subscribers
726 photos
5 videos
13 files
235 links
የዲ.ን ሄኖክ ሀይሌን ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ሰኔ_24

#ቅዱስ_ሙሴ_ጸሊም_ኢትዮጵያዊው

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሰኔ ሃያ አራት በዚች ቀን አባ ሙሴ ጸሊም በሰማዕትነት ሞተ። ሰዎች ከገድሉ የተነሣ ይህን ቅዱስ ያደንቁታል እርሱ አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍቷት ነበረና እርሱ በሥጋው ጠንካራ በሥራውም ኃይለኛ ነበር ይበላና ይጠጣ ይቀማና ያመነዝር ነበር ይገድልም ነበር ማንም ሊቋቋመው አይችልም ነበር።

አንድ በግ በአንድ ጊዜ ጨርሶ እንደሚበላና አንድ ፊቀን ወይን ጠጅ እንደሚጠጣ ስለ እርሱ ተነግሮአል። እርሱም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይ ነበረ ብዙ ጊዜም ወደ ፀሐይ እያንጋጠጠ ፀሐይ ሆይ አንተ አምላክ ከሆንክ አነጋግረኝ ይል ነበር ደግሞም በልቡ የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ ይል ነበር።

ከዚህም በኋላ በአስቄጥስ ገዳም ያሉ መነኰሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል ያዩታልም እያሉ ሲነጋገሩ ሰዎችን ሰማቸው። ያን ጊዜም ተነሣ ሰይፉንም ታጥቆ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ በደረሰም ጊዜ አባ ኤስድሮስን አገኘው። አባ ኤስድሮስም ፈራው ሙሴ ጸሊምም እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ አለው። አባ ኤስድሮስም ወደ አባ መቃርስ ወስዶ አገናኘው።

እርሱም ተቀብሎ ሃይማኖትን አስተማረው እንዲህም አለው ታግሠህ የማስተምርህን ከጠበቅህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ። ከዚህም በኋላ የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ አመነኰሰው ከብዙዎች ገድለኞች ቅዱሳን ይልቅ ብዙና ጽኑዕ ገድልን መጋደል ጀመረ።

ሰይጣንም ቀድሞ ሲሠራው በነበረ በመብሉና በመጠጡ በዝሙቱም ይዋጋው ነበረ እርሱም በራሱ ላይ የሚደርስበትን ሁሉ ለአባ ኤስድሮስ ይነግረው ነበር እርሱም አጽናንቶ ሊሠራው የሚገባውን ያስተምረው ነበር።

ከገድሉ ብዛትም የተነሣ አረጋውያን መነኰሳት በሚተኙ ጊዜ ቤቶቻቸውን በመዞር ውኃ መቅጃዎችን ወስዶ ውኃ መልቶ በየቤታቸው ደጃፍ ያኖር ነበር። ውኃው ከእነርሱ ሩቅ ነበረና እንዲህም እያደረገ በመጋደል ለብዙ ዘመናት ኖረ።

ሰይጣንም በእርሱ ቀንቶ በእግሩ ውስጥ አስጨናቂ የሆነ አመታትን መታው ተኝቶም እየተጨነቀ ብዙ ቀን ታመመ። ከዚህም በኋላ የመታውና የሚፈታተነው ሰይጣን እንደሆነ ዐውቆ ሥጋው በእሳት ተለብልቦ እንደ ደረቀ ዕንጨት እስቲሆን ድረስ ተጋድሎውንና አገልግሎቱን አበዛ። እግዚአብሔርም ትዕግስቱን አይቶ ከደዌው ፈወሰው የሰይጣንንም ጦር ከእርሱ አራቀለት የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ አደረበት ወደርሱም አምስት መቶ ወንድሞች መነኰሳት ተሰበሰቡ በእነርሱም ላይ አበ ምኔት ሆነ።

ከዚህ በኋላ ቅስና ሊሾሙት መረጡት በቤተ መቅደስም በሊቀ ጳጳሳቱ ዘንድ በአቆሙት ጊዜ ሊቀ ጳጳሳቱም አልፈቀደም ነበር አረጋውያኑንም ይህን ጠቋራ ለምን አመጣችሁት ከዚህ አውጡት አላቸው እርሱም መልክህ የከፋ ጠቋራ ሆይ መልካም አደረጉብህ በማለት ራሱን እየገሠጸ ወጣ ከዚህ በኋላ ዳግመኛ ሊቀ ጳጳሳቱ ጠራውና እጁን በላዩ ጭኖ ቅስና ሾመው እንዲህም አለው ሙሴ ሆይ እነሆ በውስጥም በውጭም ሁለመናህ ነጭ ሆነ።

በአንዲትም ዕለት ቅዱሳን አረጋውያን ወደርሱ መጡ በእርሱም ዘንድ ውኃ አልነበረም እርሱም ከበዓቱ ብዙ ጊዜ ወጣ ገባ ይል ነበር ከዚህ በኋላም ብዙ ዝናም ዘንሞ ጕድጓዶችን ሁሉ ሞላ። አረጋውያንም ለምን ብዙ ጊዜ ወጣ ገባ ትል ነበር ብለው ጠየቁት እርሱም እግዚአብሔርን ውኃ ካልሰጠኸኝ ቅዱሳን አገልጋዮችህን ምን አጠጣቸዋለሁ እለው ነበር በቸርነቱም ዝናምን ልኮልን ውኃን አገኘን አላቸው።

በአንዲትም ዕለት አባ ሙሴ ከአረጋውያን ጋራ ወደ አባ መቃርስ ሔደ አባ መቃርስም የሰማዕትነት አክሊል ያለው ከእናንተ ውስጥ አንዱን እነሆ አያለሁ አላቸው አባ ሙሴም አባቴ ሆይ ምናልባት እኔ እሆናለሁ በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደል ዘንድ አለው የሚል ጽሑፍ አለና ብሎ መለሰ።

ከዚህም በኋላ የበርበር ሰዎች መጡ አባ ሙሴም ከእርሱ ጋራ ያሉትን መነኰሳት እነሆ የበርበር ሰዎች ደረሱ መሸሽ የሚፈልግ ይሽሽ አላቸው እነርሱም አባታችን አንተስ አትሸሽምን አሉት እርሱም በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደላል ስለሚለው የእግዚአብሔር ቃል እነሆ ያቺን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠብቃት ኖሬአለሁ አላቸው።

ወዲያውኑም የበርበር ሰዎች ገብተው በሰይፍ ገደሉት መሸሽ ስለ አልፈለጉ ከእርሱ ጋራ ሰባት መነኰሳትም ተገደሉ አንዱ ግን ከምንጣፍ ውስጥ ተሠወረ የእግዚአብሔርንም መልአክ አየ በእጁም አክሊል ነበር እርሱም ቆሞ ይጠብቅ ነበር። ይህንንም በአየ ጊዜ ከተሠወረበት ወጣ የበርበር ሰዎችም ገደሉት የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበለ።

ወንድሞች ሆይ ከሀዲና ነፍሰ ገዳይ ቀማኛና ዘማዊ የነበረውን ለውጣ ደግ አባት መምህርና የሚያጽናና ለመነኰሳትም ሥርዓትን የሠራ ካህን እንዳደረገችው በሁሉም አብያተ ክርስቲያን ስሙ እንዲጠራ እንዳደረገችው የንስሐን ኃይሏን ተመልከቱ። ሥጋውም በአስቄጥስ ገዳም ደርምስ በተባለ ቦታ ለዘላለም ይኖራል ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ይታያሉ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሰኔ_24)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ከዘመነ ጸደይ ወደ ዘመነ ክረምት መሸጋገሪያ ለሆነችው ዕለትና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

=>ስንዱ እመቤት ቤተ ክርስቲያን (ሃገራችን) ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ትጠቀማለች:: እሊሕም ዘመናት መጸው (ጽጌ): ሐጋይ (በጋ): ጸደይ (በልግ)ና ክረምት ናቸው:: ዘመናቱ ወቅቶችን ከመለየትና ማሳወቅ ባሻገር የእኛ ሕይወትም ምሳሌዎች ናቸውና ልብ ልንላቸው ይገባል::

+በተለይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና "ሽሽታችሁ (ስደታችሁ) በክረምትና በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ" ብሎናልና (ማቴ. 24:20) ልንጸልይ ይገባናል:: በዘመነ ክረምት ቅጠል እንጂ ፍሬ የለበትምና ፍሬ ምግባር ሣናፈራ ሞት እንዳይመጣ: አንድም ክረምት የዝናብና የጭቃ ጊዜ በመሆኑ እንኩዋንስ ለስደት ለኑሮም አይመችምና እንደ ሊቃውንት እንዲህ ብለን እንጸልይ:-

"በዝንቱ ክረምት በመዋዕሊነ:
እንበለ ፍሬ እንዘ በቆጽል ኀሎነ:
ናስተበቁዐከ እግዚኦ ኢይኩን ጉያነ::"
(ክረምት በተባለ በእኛ እድሜ:
ፍሬ ሳናፈራ በቅጠል /ያለ መልካም ሥራ/ ሳለን:
አቤቱ ጌታ ሆይ ስደትን አታምጣብን)

=>ቸሩ አምላካችን ከዘመነ መጸው በሰላም ያድርሰን:: ተረፈ ዘመኑንም የንስሃ: የፍሬና የበረከት ያድርግልን::

=>በዚሕች ዕለት እነዚህ ቅዱሳን ይከበራሉ:-

+" ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ "+

+በዘመነ ሐዋርያት ይሁዳ ተብለው ይጠሩ ከነበሩት አንዱ የሆነው ቅዱሱ የአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ልጅ ሲሆን እናቱ ማርያም ትባል ነበር:: እናቱ ስትሞትበት ተጎድቶ የነበረ ቢሆንም ገና በልጅነቱ ድንግል ማርያም አግኝታው በፍጹም ጸጋ አሳድጋዋለች:: አስተዳደጉም ከጌታችን ጋር በአንድ ቤት ነበር::
ጌታችን እርሱንና ወንድሞቹን (ያዕቆብና ስምዖንን) ከ72ቱ አርድእት ቆጥሯቸዋል:: ቅዱስ ይሁዳ ወንጌል ላይ ከጌታችን ጋር መነጋገሩን ዮሐንስ ወንጌላዊ መዝግቧል:: (ዮሐ. 14:22)

+ቅዱስ ይሁዳ ከጌታችን እግር 3 ዓመት ተምሮ: መንፈስ ቅዱስንም ተቀብሎ ብዙ አሕጉራትን ዙሯል:: አይሁድንም አረማውያንንም ወደ ክርስቶስ ይመልስ ዘንድ ብዙ ድካምና ስቃይን በአኮቴት ተቀብሏል:: አንዲት አጭር (ባለ አንድ ምዕራፍ) መልእክትም ጽፏል:: አጭር ትምሰል እንጂ ምሥጢሯ እጅግ የሠፋ ነው:: ቅዱስ ይሁዳን በዚህች ቀን አረማውያን ገድለውት በሐዋርያነቱ ላይ የሰማዕትነትን ካባ ደርቧል::

+" ቅዱሳን ዺላጦስና አብሮቅላ "+

=>ብዙዎቻችን መስፍኑን ዺላጦስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታችን እንዳይሰቀል ከአይሁድ ጋር ሲከራከር እናውቀዋለን:: የጌታችን ሞቱ በፈቃዱ ነበርና አይሁድ እንቢ ሲሉት የክርስቶስን ንጽሕና መስክሮ: እጁንም ታጥቦ ሰጥቷቸዋል:: የዺላጦስ ታሪክ ግን እዚህ ላይ አያበቃም::

+ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በሁዋላ ትንሳኤውን በራዕይ ገልጦለት አይሁድን ተከራክሯቸዋል:: ውሸታም ወታደሮችንም ቀጥቷል:: በመጨረሻ ግን በሮም ቄሳር ተጠርቶ ከእሥራኤል እስከ ሮም ድረስ ሰብኮ በሮም አደባባይ አንገቱ ተሠይፏል::

+ቅድስት እናታችን አብሮቅላም የዺላጦስ ሚስት ስትሆን ቁጥሯ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ነው:: ጌታችንን ተከትላ: ቤቷን ለሐዋርያት አስረክባ: ቤተ ክርስቲያንንም በዘመኗ አገልግላ ዐርፏለች:: ዛሬ ሁለቱም ቅዱሳን ይታሠባሉ::

=>ጌታችን ከሐዋርያው ይሁዳ: ከዺላጦስና አብሮቅላም ጸጋ በረከትን ያድለን::

=>ሰኔ 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
2.ሰማዕቱ ዺላጦስ መስፍን
3.ቅድስት አብሮቅላ (ሚስቱ)
4.አባ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት
5.የጸደይ መውጫ / የክረምትመግቢያ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ /አባ ቡላ/
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

=>+"+ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ: የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ በእግዚአብሔር አብ ተወደው: ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ:
ምሕረትና ሰላም: ፍቅርም ይብዛላችሁ::
ወዳጆች ሆይ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኩዋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ:: +"+ (ይሁዳ. 1:1)

✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል:: አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://t.me/zikirekdusn
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለሐዋርያው #ቅዱስ_ታዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ #ቅዱስ_ታዴዎስ_ሐዋርያ +"+

=>#ቅዱሳን_ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በ3 ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል::

¤እንደ #ዮሐንስ_ወንጌላዊ ያሉት በ20ዎቹ ውስጥ:
¤#ቅዱስ_ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በ30ና በ40ዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን
¤እነ #ቅዱስ_ዼጥሮስ ደግሞ በ50ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ:: ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም: ከጐልማሶችም ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው::

+ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ #ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች) #ስምዖን እና #ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል::

+ቅዱሱ ጌታችን ተከትሎ:
¤ከ12ቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ:
¤3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታ እግር ተምሮ:
¤በዕርገቱ ተባርኮ:
¤በበዓለ ሃምሳም 71 ልሳናትን ተቀብሎ:
¤#ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል::

+ቅዱስ ታዴዎስ አንድ ቀን ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር ወደ አንዲት ሃገር ይገባሉ:: ታዲያ ለቀናት ያለ ምግብ ወንጌልን ሲሰብኩ ቆይተው ነበርና ደጐቹ ሐዋርያት ራባቸው:: ወደ ከተማዋ ሳይገቡ አንድ ሽማግሌ ሲያርስ አይተው ሰላምታን ሰጡትና "እባክህ እርቦናልና አብላን" አሉት:: እርሱም ምንም ወገኑ ከአሕዛብ ቢሆነ አሳዝነውት በሬዎቹን ሳይፈታ እየሮጠ ሄደ::

+ያን ጊዜ ቅዱስ ታዴዎስ ሊቀ ሐዋርያትን "እርሱ እስኪመጣ ለምን አናርስም" አለው:: 2ቱ ተነስተው ታዴዎስ ሞፈር: ዼጥሮስ ደግሞ ስንዴውን ያዘ:: ቅዱሳኑ እየዘሩ ያረሱት ሰውየው ምግብ ይዞ እስኪመጣ አድጐ: አፍርቶ: እሸት ሆኖ ቆየው::

+ገበሬው የተደረገውን ተአምራት ባየ ጊዜ ደነገጠ:: ሊያመልካቸውም ወደደ:: እነርሱ ግን "እኛ የልዑል ባሮች ነን" ብለው በክርስቶስ ማመንን አስተማሩት:: "ልከተላችሁ" ቢላቸው "የለም! ከእሸቱ ይዘህ ወደ ከተማ ግባና ራት አዘጋጅልን:: እኛ እንመጣለን" አሉት::

+እርሱ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሕዛብ ነገሩን ተረዱ:: ተሠብሥበውም "እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እሳትም ሰይፍም አይበግራቸውም" ብለው ወደ ከተማ እንዳይገቡ ከበሩ ላይ ራቁቷን የሆነች ዘማ አቆሙ::

+ቅዱስ ታዴዎስ ገና ከርቀት ስላያት ቀና ብሎ #ቅዱስ_ሚካኤልን "እርዳን" አለው:: ሊቀ መላእክትም ድንገት ወርዶ ዘማዋን ሴት በጸጉሯ በዓየር ላይ ሰቀላት:: በከተማዋ ያሉ አሕዛብም ይህንና ሌሎች ተአምራትን አይተው ሁሉም በጌታችን አምነው ተጠመቁ:: ለሐዋርያቱም ሰገዱላቸው::

+አንድ ቀን ግን አንድ ጐረምሳ ባለ ጠጋ ቅዱስ ታዴዎስ "ሀብት ንብረታችሁን መጽውቱ" ሲል ሰምቶት ዘሎ የሐዋርያውን ጉሮሮ አንቆ ከሞት አድርሶት ነበር:: ያን ጊዜ "ጌታየ! ለካ ሀብታም ከሚጸድቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ያልክ ለዚህ ነው!" ብሏል:: ባለ ጠጋው "እንዴት ይሆናል?" ቢለው መርፌ አሠርቶ ግመሉን ከነ ባለቤቱ በሰው ሁሉ ፊት 3 ጊዜ አሳልፎታል::

+ያም ማለት ጌታችን እንዳለው "በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል::" (ማር. 10:23) በዚህ ምክንያትም ያ ክፉ ባለ ጸጋ ወደ ልቡናው ተመልሶ ከቅዱስ ታዴዎስ እግር ሥር ወደቀ:: ሐዋርያውም አለው "ሀብትህን ለነዳያን ስጥ:: ይህንንም በትር እንካና እየዞርክ ወንጌለ መንግስትን ስበክ::" ባለ ጸጋውም የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ በክብር ዐርፏል::

+ቅዱሳኑ ታዴዎስና ዼጥሮስ ግን በሃገሪቱ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸው: ካህናትን ሹመው: ያቺን በዓየር ላይ የሰቀሏትን ዘማም የተባረከች መበለት አድርገው: በሌሎች አሕጉራት ወንጌልን ለማዳረስ ወጥተዋል::

+ቅዱስ ታዴዎስም እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል:: ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል:: ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በሁዋላም በዚህች ቀን ዐርፏል::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

=>+"+ ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን "ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል!" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ:: ጌታ ኢየሱስም ደግሞ መልሶ "ልጆች ሆይ! በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ #እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው! ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል" አላቸው:: +"+ (ማር. 10:23-28)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://t.me/zikirekdusn
††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ መርቄሎስ እና ለነቢዩ ቅዱስ ዕዝራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ †††

††† ቅዱሱ በነገድ እሥራኤላዊ የሆነ የመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን ሰው ነው:: ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ሲያስተምር በምሥጢሩና በተአምራቱ ተማርኮ ተከትሎታል:: ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ይሆን ዘንድ አድሎታል:: ከጌታችን ሕማማትና ስቅለት በፊትም ድውያንን መፈወስና አጋንንትን ማስወጣት ከቻሉ አርድእትም አንዱ ነው::

ቅዱስ መርቄሎስ በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለወንጌል አገልግሎት ተሰማርቷል:: በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሰላሳ አራት ዓመታት በማገልገሉ ሐዋርያት ስሙን "ጳውሎስ" ብለውታል:: ጳውሎስ ማለት ብርሃን ማለት ነውና:: ልክ ሳውል "ጳውሎስ" እንደተባለው ማለት ነው::

ስሙ የግብር (በሥራ የሚገኝ) ስም ነው:: በዚህም ምክንያት ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን የምትጠራው "ጳውሎስ የተባለው መርቄሎስ" እያለች ነው::

ቅዱስ መርቄሎስ በ60ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በሮም ይሰብክ ነበር:: ኔሮን ቄሳር ሊቀ ሐዋርያትን ዘቅዝቆ ሲሰቅለው የተመለከተና ይህንኑ የጻፈ እርሱ ነበር:: ወታደሮቹ ቅዱስ ጴጥሮስን ገድለውት ሲሔዱ ቅዱስ መርቄሎስ እያነባ ቀርቦ: ችንካሮችንም ነቅሎ: ሊቀ ሐዋርያትን ከተሰቀለበት አወረደው::

በፍጥነት ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ አምጥቶ በቅዱስ ጴጥሮስ ሥጋ ላይ አፈሰሰና በፍቅርና በክብር ሊገንዘው ጀመረ:: በዚህ ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት አይኑን ግልጥ አድርጎ መርቄሎስን ተመለከተውና አለው:- "ልጄ! ምነው ለእኔ ይህንን ያሕል ሽቱ አባከንክ?" አለውና ተምልሶ ዐረፈ::

ቅዱስ መርቄሎስም እግዚአብሔርን እያመሰገነ በንጹሕ በፍታ ገንዞ እርሱ በሚያውቀው ቦታ ሠወረው:: ሊቀ ሐዋርያትን በመገነዙ የክብር ክብር ተሰጥቶታል::

ቅዱሱ አሁንም ስብከተ ወንጌልን ቀጠለ:: ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን እርሱም ተይዞ በኔሮን ፊት ቀረበ:: ኔሮን ቄሳር ቅዱስ መርቄሎስን ጠየቀው:: "እንዴት ባለ አሟሟት ልግደልህ? እንደ መምህርሕ ጴጥሮስ ወይስ ሌላ የምትፈልገው ዓይነት አሟሟት አለህ?"

ቅዱስ መርቄሎስ መለሰለት:- "የትኛውም ዓይነት ሞት እኔን አያስፈራኝም:: የምፈልገው ወደ ጌታዬ ቶሎ መሔድ ብቻ ነው::" አለው:: ንጉሡ ኔሮንም ዘቅዝቃችሁ ስቀሉት አላቸው:: ወታደሮቹም በዚህች ዕለት እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለውታል::

††† ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ †††

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ500 ዓመት አካባቢ የነበረ
¤እሥራኤል ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ መጻሕፍት ተቃጥለው ጠፍተው ነበርና ስለ እነሱ አብዝቶ የለመነ
¤ጥበብን ሽቷልና እግዚአብሔር ቅዱስ ዑራኤልን የላከለት
¤በሊቀ መላእክት እጅም ጽዋዐ ልቡናን የጠጣ
¤ብዙ ምሥጢራት የተገለጡለት
¤ለአርባ ቀናት ምግብ ሳይበላ አገልጋዮቹ የጠፉ መጻሕፍትን እየነገራቸው የጻፉለት
¤መጽሐፈ ዕዝራ የተሰኘ መጽሐፍን ያዘጋጀና
¤በብሉይ ኪዳን ከነበሩ ዐበይት ነቢያተ ጽድቅ አንዱ የሆነ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነው::

††† ስለ ቅድስናውም ሞትን አልቀመሰም:: በዚህች ዕለት ቅዱሳን መላእክት ብሔረ ሕያዋን ውስጥ አስገብተውታል::

††† እግዚአብሔር ከሐዋርያውና ከነቢዩ በረከትን አይንሳን::

††† ሐምሌ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
2.ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ
3.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
4.ቅድስት ቴዎዳስያ ሰማዕት
5.ቅድስት ንስተሮኒን ዘኢየሩሳሌም

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል

††† "እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን: ሁለተኛም ነቢያትን: ሦስተኛም አስተማሪዎችን: ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን: ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ: እርዳታንም: አገዛዝንም: የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጓል:: ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? . . . ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ::" †††
(፩ቆሮ. ፲፪፥፳፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
እግዝእትየ፦

መዝገበ #በረከት
መዝገበ #ቅድሳት
መዝገበ #ንጽሕ
መዝገበ #ርህራሄ
መዝገበ #የዋሃት

✞ባርክኒ በእዴኪ፤ በከመ ባረኪዮ #ለኤፍሬም ፍቁርኪ፤ በበረከተ ወልድኪ ወአቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ፡፡

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል:: አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://t.me/zikirekdusn
††† እንኳን ለታላቁ ሊቅና አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ †††

††† እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው ንጽቢን በምትባል የሶርያ ግዛት ውስጥ በ298 / 306 ዓ/ም ነው:: ወላጆቹ በክርስቶስ የማያምኑ አላውያን ነበሩ:: (ምንም አንዳንድ ምንጮች ክርስቲያኖች ነበሩ ቢሉም)

ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ንጽቢን ጵጵስናን የተሾመ ቅዱስ ያዕቆብ የሚባል ታላቅ ሰው ነበር:: የሰማዕትነት: የሐዋርያነት: የጻድቅነትና የሊቅነት ግብር ያለው አባት ነው:: ታዲያ ቅዱስ ኤፍሬም ይሔ አባት ሁሌ ሲያስተምር ይሰማው ነበርና በስብከቱ ተማርኮ ደቀ መዝሙሩ ለመሆን በቃ::

ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱስ ያዕቆብ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ሙሉ የወጣትነት ጊዜውን ያሳለፈው በትምሕርት ነው:: የሚገርመው መምሕሩ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍጹም ልቡ የሚወድና ጠርቷት የማይጠግብ አባት ነውና ለልጁ ለቅዱስ ኤፍሬም ይሕንኑ አጥብቆ አስተምሮታል::

ቅዱስ ኤፍሬም ክርስትናን ሲመረምር የእመቤታችን ፍቅር ይበዛለት ጀመር:: ምክንያቱም እመ ብርሃንን ሳይወዱ ክርስትና የለምና:: እንደ እርሱ የሚወዳት የለም እስኪባል ድረስ ያገለግላት: ይገዛላትም ገባ::

እንዲህ እንደ ዛሬ የድንግል ማርያም ምስጋና በአንደበት እንጂ በመጽሐፍ አይገኝም ነበር:: እርሱ ግን ከወንጌለ ሉቃስ በስድስተኛው ወርን (ይዌድስዋን) እና ጸሎተ ማርያምን(ታዐብዮን) አውጥቶ በየዕለቱ በዕድሜዋ ልክ ስልሳ አራት ስልሳ አራት ጊዜ ያመሰግናት ነበር::

በእንዲህ ያለ ግብር እያለ አርዮስ በመካዱ እርሱን ለማውገዝና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማጽናት በ317 (325) ዓ.ም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በኒቅያ ሲሰበሰቡ አንዱ መምሕረ ኤፍሬም ቅዱስ ያዕቆብ ነበር:: በዚህ ምክንያት ቅዱስ ኤፍሬም ከሊቃውንቱ ትምሕርትና በረከትን አግኝቷል::

ከጉባዔ መልስ መንገድ ላይ በራዕይ የብርሃን ምሰሶ አይቶ "ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?" ብሎ ቢጠይቅ "ይሕማ ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ነው::" አለው:: እርሱም መምሕሩን ቅዱስ ያዕቆብን ተሰናብቶ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ (ቂሣርያ) ወረደ:: ተገናኝተውም በአንድ ሌሊት ቋንቋ ተገልጦላቸው ሲጨዋወቱ አድረዋል::

በቦታው ብዙ ተአምራት ተደርጓል:: ቅዱስ ኤፍሬም ከታላቁ ባስልዮስ ከተማረ በኋላ ሃገረ ስብከት ተሰጥቶት ያስተምር ጀመር:: ሁል ጊዜ ታዲያ ጸሎቱ ይሔው ነበር:: "እመቤቴ ሆይ! ምስጋናሽ እንደ ሰማይ ከዋክብት: እንደ ባሕር አሽዋ በዝቶልኝ: እንደ እንጀራ ተመግቤው: እንደ ውኃ ጠጥቼው: እንደ ልብስም ተጐናጽፌው" እያለ ይመኝ ነበር::

አፍጣኒተ ረድኤት: ፈጻሚተ ፈቃድ እመ ብርሃንም በገሃድ ተገልጻ የልቡን ፈቃድ ፈጸመችለት:: ዛሬ ጸጋ በረከት የምናገኝበትን ውዳሴ ማርያምን ደረሰላት:: ሲደርስላትም እርሷ አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላ ወርዳ: በፊቱም ተቀምጣ ሲሆን እርሱ ደግሞ ባጭር ታጥቆ: በፊቷ ቆሞ: በመንፈስ ቅዱስም ተቃኝቶ ነው::

ውዳሴዋን በሰባት ቀናት ከደረሰላት በኋላ በብርሃን መስቀል ባርካው: ሊቀ ሊቃውንትም እንዲሆን ምሥጢር ገልጣለት ዐረገች:: ከዚህ በኋላ በምሥጢር ባሕር ውስጥ ዋኝቶ አሥራ አራት ሺህ ድርሰቶችንም ደርሷል:: ዛሬ ሶርያ ውስጥ የምንሰማውን ዜማም የደረሰው ይህ ቅዱስ ነው::

እንዲያውም አንድ ቀን የምሥጢር ማዕበል ቢያማታው "አሃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ" ብሎ ጸልዩዋል:: (የጸጋህን ማዕበል ያዝልኝ) እንደ ማለት ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በመጨረሻ ሕይወቱ ተክሪት በምትባል ሃገር ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሟል::

በጣፋጭ ስብከቱ ብዙዎችን ካለማመን መልሷል:: የምዕመናንንም ሕይወት አጣፍጧል:: ለመናፍቃንና ለአርዮሳውያን ግን የማይጋፉት ግድግዳ ሆኖባቸው ኑሯል:: በዘመኑም ብዙ ተጋድሎ አፍርቷል:: ተአምራትንም ሠርቷል:: በተወለደ በስልሳ ሰባት ዓመቱ በ365 (373) ዓ.ም ዐርፎ ተቀብሯል::

††† ቅዱሱ ለሶርያ ብቻ ሳይሆን እመቤታችንን ለምንወድ የዓለም ክርስቲያኖች ሁሉ ሞገሳችን ሆኗል:: ስለዚህም እንዲህ እያልን እንጠራዋለን:-
1.ቅዱስ ኤፍሬም
2.ማሪ ኤፍሬም
3.አፈ በረከት ኤፍሬም
4.ሊቀ ሊቃውንት ኤፍሬም
5.ጥዑመ ልሳን ኤፍሬም
6.አበ ምዕመናን ኤፍሬም
7.ርቱዐ ሃይማኖት ኤፍሬም . . . አባታችን አንተ ነህ::

††† ጽንዕት በድንግልና: ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ለቅዱስ ኤፍሬም የሰጠሽውን ጸጋውን: ክብሩን: አእምሮውን: ለብዎውን በልቡናችን ሳይብን: አሳድሪብን . . . አሜን::

††† ጴጥሮስ ወጳውሎስ †††

††† ዳግመኛ በዚህ ቀን ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ይታሠባሉ::

ቅዱሳኑ ሶርያ አካባቢ ውስጥ ወደምትገኝ አንዲት ሃገር ገብተው ሕዝቡን ከንጉሣቸው ጰራግሞስ ጋር አሳምነው አጥምቀዋል:: ነገር ግን እነርሱ ሲወጡ ሰይጣን አስቶት አጥፊ ሰው ወደ መሆን ተመልሶ ንጉሡ ሐዋርያትን አሰቃይቷቸዋል::

ስለ ቅዱሳኑ ግን ፈረሶቹ ሰግደው: በሰው አንደበት ቅድስናቸውን መስክረዋል:: በመጨረሻም ንጉሡን ከነ ሕዝቡና ሠራዊቱ በዓየር ላይ ሰቅለው ንስሐ ሰጥተውታል:: በእነዚህ ተአምራትም ሁሉም አምነው ለከተማዋና ለሕዝቡ ድኅነት ተደርጓል::

††† ከአባቶቻችን አበው ሐዋርያት በረከት ይክፈለን::

††† ሐምሌ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
2.ብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስ ወጳውሎስ
3.አባ ሓርዮንና ደቀ መዛሙርቱ (ሰማዕታት)
4.አባ ፍሬምናጦስ መስተጋድል

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ሰማዕት
3.ቅድስት እንባ መሪና
4.ቅድስት ክርስጢና

††† "ለምኑ ይሰጣችሁማል:: ፈልጉ ታገኙማላችሁ:: መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል:: የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና:: የሚፈልገውም ያገኛል:: መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል::" †††
(ማቴ. ፯፥፯)

††† "የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" †††
(መዝ. ፴፯፥፴)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል:: አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://t.me/zikirekdusn
የደብረ ታቦር መዝሙራት

በደብር በደብረ ታቦር
በደብር በደብረ ታቦር (2)
ታቦር ወአርሞንኤም (4)
ትርጉም፦  በታቦር ተራራ የነበረ አርሞንኤምና ታቦር

በደብር በደብረ ታቦር
በደብር በደብረ ታቦር (2)
ሰባሕኩከ በደብር (4)
ትርጉም፦ በታቦር ተራራ አመሰገንኩህ

በስመ  ዚአከ
በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ ዮም (2)
ታቦር ወአርሞንኤም (4)
ትርጉም፦ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ዛሬ ደስ ይላቸዋል

አሐደ ለከ
አሐደ ለከ ወአሐደ ለሙሴ (2)
ወአሐደ ለኤልያስ ንግበር ማኅደረ (4)
ትርጉም፦ አንዱንም ላንተ አንዱንም ለሙሴ (2)
    አንዱንም ለኤልያስ እንስራ ዳስ (4)

ደብረ ታቦር አብርሂ
ደብረ ታቦር አብርሂ ኢየሩሳሌም (2)
 ብርሃንኪ (5) እግዚአብሔር (2)
ትርጉም፦ ብርሃንሽ እግዚአብሔር ነውና የታቦር ተራራ በኢየሩሳሌም አብሪ

ደብር ርጉእ
ደብር ርጉእ ወደብር ጥሉል (2) ለምንት ይትነሥኡ ርጉአን አድባር (2)
ደብር ዘሠምሮ እግዚአብሔር የኀድር ውስቴቶ እግዚአብሔር (2)
ትርጉም፦ የጸኑ ተራሮች ለምን ይነሣሉ? እግዚአብሔር ይህን ተራራ ያድርበት ዘንድ ወደደው በእውነት እግዚአብሔር ያድርበታል።

ወተወለጠ
ወተወለጠ ራእዩ በቅድሜሆሙ ራእዩ በቅድሜሆሙ (2)
ወአልባሲሁኒ ኮነ ፀዓዳ ከመ በረድ (2)
ትርጉም፦ መልኩ በፊታቸው ተለወጠ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ

ወይቤ ሠመርክዎ
ወይቤ ሠመርክዎ (2)
ወይቤ ሎቱ ስምዕዎ(4)
ትርጉም፦ ወደድከው እርሱንም ስማው አለ