ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
የምትሻ ነፍስ መልስ የምታገኝበት ግሩም መጽሐፍ ነው፡፡ በውስጡም በዘመነ ሐዲስ ስለሚቀርበው ቊርባን /፩/፣ ስለ ጋብቻ ምንነት /፪/፣ እንዲኹም ስለ አስራት አሰጣጥ /፫/ በጥልቀት ያስተምራል፡፡

መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1. ምዕራፍ አንድን ስናነብ፥ ምንም እንኳን #እግዚአብሔር አባታቸው መኾኑን ቢያውቁም፣ ምንም እንኳን #እግዚአብሔር #ጌታ እንደኾነ ቢረዱም በገቢር ግን የአባትነትም ኾነ እንደ ጌትነቱ የመፈራት ክብርን አለመስጠታቸው ይገልጣል፡፡ ነውረኛ የኾነ መሥዋዕትን በማቅረባቸው የ #እግዚአብሔርን ስም እንዴት እንደናቁት ያሳያል፡፡ በሌላ አገላለጽ የእምነትና የምግባር አንድነትን የሚያስረዳ እውነተኛና ተቀባይነት ያለው አምልኮ ምን እንደሚመስል የሚያረዳ ነው፡፡
2. ምዕራፍ ኹለትን ስንመለከት ደግሞ የካህናቱን ኢሞራላዊነት ይናገራል፡፡ በዚኽ ድርጊታቸውም የ (እግዚአብሔርን ኪዳን እንዴት እንዳፈረሱት ለበረከት የኾነውም እንደምን ለመርገም እንዳደረጉት ያስረዳል፡፡

3. ምዕራፍ ሦስትና አራት ላይ #እግዚአብሔር እንደሚመጣና ሕዝቡንም ኾነ ቤተ መቅደሱን እንደሚቀድስ ይናገራል፡፡ ምዕራፍ ሦስት ላይ በመዠመሪያ ምጽአቱ ላይ ክብር ይግባውና #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሕዝቡን (ቤተ መቅደሱን) በገዛ ደሙ ለመዋጀት እንደሚመጣና ሕዝቡም እርሱን ለመቀበል በገቢር እንዲመለሱ ሲጠይቅ በምዕራፍ አራት ላይ ደግሞ የጽድቅ ፀሐይ የተባለው #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ጨለማ የተባለውን ክፋት ከሰው ልጆች ለማራቅ እንደሚመጣ ይናገራል፡፡ በዚያ አንጻርም በሕያዋንና በሙታን ላይ ዳግም ለመፍረድ እንደሚመጣ ይገልጣል፡፡

እኛስ ከዚኽ ምን እንማራለን?
© #እግዚአብሔርን በከንፈራችን ሳይኾን በገቢር እንደምንወደው መግለጥ እንዳለብን፤ ንጹሕ መሥዋዕትም ይኸው እንደኾነ /፩/፤
© እንዲኽ ካልኾነ ግን ብንጦምም፣ ብንጽልይም፣ ብንመጸውትም፣ ቤተ ክርስቲያን ብንመላለስም፣ መባ ብናቀርብም መሥዋዕታችን ኹሉ ፋንድያ እንደኾነ /፪፡፫/፤
© ምንም ያኽል ኃጢአተኞች ብንኾንም ልንመለስ እንደሚገባን /፫፡፯/፤ እርሱም ከየትኛውም ዓይነት ኃጢአታችን እንደሚያነጻን፤ የእርሱ ገንዘብ እንደምንኾንና አንድ ሰው የሚያገለግለው ልጁን እንደሚምረው የሠራዊት #ጌታ_እግዚአብሔርም እንደሚምረን /፫፡፲፯/፤
© እንዲኽ ከተመለስን በኋላ የጽድቅ ፀሐይ #ክርስቶስ ላይጠልቅ በሕይወታችን ላይ አብርቶ እንደሚኖር እንማራለን፡፡

…ተመስጦ…
ቸርና ቅዱስ #እግዚአብሔር ሆይ! በሕይወታችን እጅግ ጐስቋሎች ኾነን ስምኽን ብናቃልለውም ደካሞች ነንና በከንፈራችን ብቻ ሳይኾን በገቢርም እንድናውቅኽ እንድናመልክኽም እርዳን፡፡ ሊቀ ካህናችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ! እውነተኛ ካህናት እንድንኾን እርዳን፡፡ አባቶቻችን ካህናት ቅዱስ ሥጋኽና ክቡር ደምኽን ለምእመናን ለኹላችንም ሲያቀብሉ እኛም በክህነታችን ቁራሽ ዳቦና ኩባያ ውኃ ለድኾች መስጠት እንድንለማመድ እርዳን፡፡ የጽድቅ ፀሐይ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ! ቅድስናኽ እኛን ቢቀድሰን እንጂ ኃጢታችን አንተን አያረክስኽምና በእኛ ዘንድ እደር፡፡ በኹለንተናችን ላይም አብራ፡፡ ጨለማን ከእኛ ዘንድ አስወግድልን፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን!!!
#ጳጒሜን_3

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጳጒሜን ሦስት በዚህች ዕለት የሰዎች ሁሉ ጸሎት የሚያርግባት #ርኅወተ_ሰማይ ትባላለች፣
የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ #ቅዱስ_ሩፋኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ ለእግዚአብሔር ልጅ ምሳሌው የሆነ #የካህኑ_መልከጼዴቅ መታሰቢያው ነው፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ መልካም ስም አጠራር ያለው #ቅዱስ_ዘርዐ_ያዕቆብ አረፈ፣ ሰንዱን ከሚባል አገር #ቅዱስ_ሰራጵዮን አረፈ፣ አቡነ ቀጸላ ጊዮርጊስ ዕረፍታቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ርኅወተ_ሰማይ

ጳጒሜን ሦስት በዚህች ዕለት የሰዎች ሁሉ ጸሎት የሚያርግባት፣ አራተኛው መጋቢ ኮከብ የሚያልፍባት፣ ለሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው ጸጋ በረከት የሚሰጥባት ዕለት ስለሆነች ርኅወተ ሰማይ (ሰማይ የሚከፈትባት) ቀን ትባላለች።

አሁን በሰማይ መዘጋት መከፈት ኑሮበት አይደለም። የሰው ልጆችን ልመና ቅዱሳን መላእክት ያለ ከልካይ የሚያሳርጉበት አንድም ቅዱስ ሩፋኤል የዓመቱን የጸሎት መዝገብ የሚከፍትበት ቀን ስለሆነ እንዲህ ተባለ እንጂ።

እመቤታችን #ድንግል_ማርያም ለአጼ ናዖድ እንደ ነገረቻቸው በዚህች ዕለት ሁሉም ቅዱሳን ስለሚታሰቡ፣ የ #እግዚአብሔር የምሕረት መዝገቡ ስለሚከፈት፣ ዕለቷን ክብርት ያሰኛታል። በቅዱስ ሩፋኤል አበጋዝነት (መሪነት) በዚህች ዕለት ለዓመት የሚበቃ ምሕረት ይገኛል።

ስለዚህም አባቶቻችን በዚህች ሌሊት ሦስት መቶ ስልሳ አምስት አቡነ ዘበሰማያትን ሲጸልዩ ያድራሉ። በሌላ ወገን ደግሞ የጌታ ዳግም ምጽዓቱ መታሰቢያ እንደ መሆኗ ትልቅ ትኩረትም ይሰጣታል። ቸሩ #ጌታችን ከተከፈተች ገነት ከተነጠፈች ዕረፍት ሁላችንንም ያድርሰን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሩፋኤል_ሊቀ_መላእክት

በዚህች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ የሩፋኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። እርሱም ከመላእክት አለቆች ሦስተኛ የሆነ ነው። ደግሞም ከእስክንድርያ ውጭ በደሴት የታነፀች ቤተ ክርስቲያኑ በከበረ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን በውስጧ ተአምር የተገለጸባት የከበረችበት ነው።

ይህም እንዲህ ነው ሀብታም ሴት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ መጥታ ሳለ ከእርሷ ጋርም ብዙ ሰው ነበረ። ከባሏም የወረሰችው ብዙ ገንዘብ አላት በሊቀ ጳጳሳቱ ቤት አንጻር ያለውን ኮረብታ አስቆፈረችው በጥቅምት ወር ዐሥራ ስምንት ቀን እንደጻፍን የወርቅ መዝገብ ተገለጠ።

በዚያም ወርቅ ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትን አነፀ ከእርሳቸውም አንዲቱ የመላእክት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ ሩፋኤል በስሙ የታነፀች ይህች ናት። ሥራዋንም በፈጸመ ጊዜ እንደዛሬው በዚች ቀን አከበራት።

ብዙ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጸች ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና። የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው። ወደ ክብር ባለቤት #እግዚአብሔርም በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ ያን ጊዜ ይህ የከበረ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በጦሩ ወግቶ እንዲህ አለው እግዚአብሔር አዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጽ ጸጥ ብለህ ቁም። አንበሪውም ጸጥ ብሎ ቆመ አልታወከም በውስጧም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆነ።

ይቺም ቤተ ክርስቲያን እስላሞች እስከተነሡበት ዘመን ኖረች ከዚህም በኋላ ሁለተኛ ያ አንበሪ ተናወጸ ደሴቲቱም በላይዋ ከሚኖሩ ብዙ ሕዝብ ጋራ ሠጠመች።

#ዳግመኛም የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ ጻድቅ ለሆነ ንጉሥ አኖሬዎስ ተናገረ። እንዲህም አለው ንጉሥ ሆይ እኛ ወዳንተ ልንመጣ በመርከብ እንደተሳፈርን ዕወቅ በጒዞ ላይ ሳለንም በቀዳሚት ሰንበት ቀን በደሴት ውስጥ ታናሽ ቤተ ክርስቲያን አየን ወደ ወደቡም ደርሰን በዕለተ እሑድ ሥጋውን ደሙን እንቀበል ዘንድ ወደርሷ ሔድን።

ለዚያች ቤተ ክርስቲያንም በጐኗ ታናሽ ገዳም አገኘን በውስጧም ወንድሞች መነኰሳት አሉ በክብር ባለቤት ጌታችንም ፈቃድ ወደ ርሳቸው ደረስን ። መነኰሳቱንም በቀደሙ አባቶች ዘመን የተጻፈ አሮጌ መጽሐፍ በእናንተ ዘንድ እንዳለ እጽናናበት ዘንድ እርሱን ሰጡኝ አልኳቸው። እንዲህም ብለው መለሱልኝ እኛ ትርጓሜያቸውን የማናውቀው መጻሕፍቶች በዕቃ ቤት አሉ። እኔም አያቸው ዘንድ ወደዚህ አምጡልኝ አልኳቸው። በአመጡአቸውም ጊዜ መረመርኳቸው #ጌታችንም በደቀ መዛሙርቱ ፊት ያደረጋቸውን ኃይሎችና ድንቆች ተአምራቶችን ስለ ሰማይና ምድርም ጥንተ ተፈጥሮ አገኘሁ።

ሁለተኛም ስመረምር ስለ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ሹመትና መዐርግ አባቶቻችን ንጹሐን ሐዋርያት የጻፉትን አገኘሁ ይኸውም #ጌታችን በደብረ ዘይት ከእሳቸው ጋራ እያለ የመለኮቱን ምሥጢር በገለጠላቸው ጊዜ። ሐዋርያትም እንዲህ ብለው እንደለመኑት #ጌታችንና ፈጣሪያችን ሆይ የከበረ የሩፋኤልን ክብሩን ታስረዳን ዘንድ እንለምንሃለን በየትኛው ዕለት በየትኛው ወር ሾምከው።

ከባልንጀሮቹ የመላእክት አለቆችም ትክክል ነውን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ዘንድ በዓለም ውስጥ ስለርሱ እንድናስተምር እርሱም በመከራቸው ጊዜ ይረዳቸው ዘንድ በአማላጅነቱም በአንተ ዘንድ ይቅርታን ያገኙ ዘንድ።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አዘዘና ከሦስተኛው ሰማይ ሦስቱ የመላእክት አለቆች ሚካኤል፣ ገብርኤልና ሩፋኤል መጡ በታላቅ ደስታም ለክብር ባለቤት ለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሰገዱ። #ጌታችንም ሩፋኤልን እንዲህ አለው የክብርህን ገናናነት የባልንጀሮችህንም ልዕልናቸውን እንዲያውቁ ለሐዋርያት ንገራቸው።

ያን ጊዜም ለ #ጌታችን ሰገደ ይነግራቸውም ዘንድ ጀመረ እንዲህም አላቸው ደገኛው የመላእክት አለቃ ሚካኤል ለሁሉም መላእክት አለቃቸው ነው ስሙም ይቅር ባይ ይባላል።

ሁለተኛም የመላእክት አለቃ ገብርኤል የስሙ ትርጓሜ አገልጋይም ጌታም የሆነ የዓለሙ ሁሉ እመቤት የሆነች አምላክን የወለደች ቅድስት #ድንግል_ማርያምን ያበሠራት ነው። የእኔም ስሜ ሩፋኤል ነው ይህም ደስ የሚያሰኝ ቸር መሐሪ ቅን የዋህ ማለት ነው እኔም ኃጢአተኞችን በ #እግዚአብሔር ዘንድ አልከሳቸውም ከኃጢአታቸው በንስሓ እስኪመለሱ ስለ ቅንነቴ በእነርሱ ላይ እታገሣለሁ እንጂ።

በሃያ ሦስቱ የመላእክት ነገድ ሠራዊት ላይ #እግዚአብሔር የሾመኝ እኔ ሩፋኤል ነኝ #እግዚአብሔር አብን ይቅር ባይ ልጁን አጽናኝና አዳኝ የሆነ #መንፈስ_ቅዱስን እናመሰግነው ዘንድ።

በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሺህ ዓመት ተድላ ደስታ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የክብር ጽዋን በሚሰጣቸው ጊዜ ለቅዱሳኖቹ በጎ ነገርን እንድሰጣቸው #እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ። ደግሞም በዚች ቀን ከዕፀ ሕይወት ዐጽቅ ወስጄ ለተመረጡ ክርስቲያኖች በእጄ እንድሰጣቸው #እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ።

የሰማያት መዛግብትም ከእጄ በታች ተጠብቀው የሚኖሩ እኔ ሩፋኤል ነኝ። እኔም #እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ እከፍታቸዋለሁ እዘጋቸዋለሁም።

በምድር ሰው ለባልንጀራው ስለ ስሜ በጎ ነገር ቢያደርግ እኔ በመከራው በችግሩ ረዳዋለሁ ወይም የሹመቴን ነገር የሚጽፍ ወይም ከቅዱሳን ጋራ ስሜን የሚያስብ ወይም በስሜ ለቊርባን የሚሆነውን የሚሰጥ ወይም በበዓሌ ቀን ምጽዋትን የሚሰጥ ይኸውም #እግዚአብሔር በሊቃነ መላእክት ክብር የሾመኝና ያከበረኝ ጳጕሚን ሦስት ቀን ነው። ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እስከማስገባው በብርሃን ሠረገላ እኔ እሸከመዋለሁ በምድር ላይ ከቶ እንደርሱ ያለ የማይገኝ መዐዛው እጅግ ጣፋጭ በሆነ ሽቱ ነፍሶቻቸው እርሱን በማሽተት ደስ እንዲላቸው አደርጋለሁ።
#ነቢዩ_አሞጽ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“አሞጽ” ማለት “ሽክም፣ ጭነት” ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በዚኽ ስም የሚጠሩ ሦስት ሰዎች ያሉ ሲኾን እነርሱም የነቢዩ ኢሳይያስ አባት /ኢሳ.፩፡፩/፣ የምናሴ ልጅ ንጉሥ አሞጽ /፪ኛ ነገ.፳፩፡፲፰/ እንዲኹም ለዛሬ የምናየውና ከደቂቀ ነቢያት አንዱ የኾነው ነቢዩ አሞጽ ናቸው፡፡

➛የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት እንደሚያስረዳው የነቢዩ አሞጽ አባት ቴና ሲባል እናቱ ደግሞ ሜስታ ትባላለች፡፡ ነገዱም ከነገደ ስምዖን ወገን ነው፡፡

📌ነቢዩ አሞጽ ከመጠራቱ በፊት የላም ጠባቂና የወርካ ለቃሚ ነበር፡፡ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅም አልነበረም፤ #እግዚአብሔር በጐችን ከመከተል ጠራው እንጂ /አሞ.፯፡፲፬-፲፭/፡፡ ምንም እንኳን ከግብርና የመጣ ቢኾንም ንግግር የማይችል፣ ያልተማረ፣ ድፍረት የሌለው ነቢይ አልነበረም፡፡

➛ነቢዩ አሞጽ ምንም እንኳን ከደቡባዊው መንግሥት ቢኾንም እንዲያስተምር የተላከው ለሰሜናዊው ክፍልም ጭምር ነበር፡፡
በራሱ መጽሐፍ እንደነገረን በዘመኑ የነበረው የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን ሲኾን በእስራኤል የነበረው ንጉሥ ደግሞ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ይባላል /አሞ.፩፡፩/፡፡ በነቢይነት ያገለገለውም ከ፯፻፹፯-፯፴፭ ቅ.ል.ክ. ላይ ነው፡፡

📌በነቢዩ አሞጽ ዙርያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ
➛ነቢዩ አሞጽ በሚያገለግልበት ወራት የይሁዳና የእስራኤል ኃጢአት ጣራ የነካበት ጊዜ ነበር፡፡ ከእኛ ዘመን ጋርም በእጅጉ ይመሳሰላል፡፡ አንባቢያን ይኽን ቀጥሎ ከተጠቀሰው ጋር ማነጻጸር ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳን በአንጻራዊ መልኩ ነቢዩ አሞጽ በነበረበት ወራት ሰላም የነገሠበት ቢኾንም ሕዝቡ ግን የ #እግዚአብሔር ሕግ ጥሏል፤ ትእዛዙን አይጠብቅም፡፡ ባለጸጐች የሚባሉት በሀብት ላይ ሀብት ጨምረው የሚኖሩ ቢኾኑም ድኾቹ ግን ከዕለት ወደ ዕለት ከድጡ ወደ ማጡ የሚኼዱ ነበሩ፡፡ ጻድቁን ስለ ብር፣ ችግረኛውን ስለ አንድ ጥንድ ጫማ የሸጡበት ጊዜ ነበር፡፡ የድኾችን ራስ በምድር ትቢያ ላይ ይረገጣል፤ የትሑታን መንገድ ይጣመማል፡፡ ቅዱሱን የ #እግዚአብሔር መንገድ ያረክሳሉ፡፡ አባትና ልጅ ለዝሙት ግብር ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፡፡ ጻድቁ በጽድቅ መንገድ ልኺድ ቢል ከእነርሱ ጋር ስላልተስማማ ያስጨንቁታል፡፡ እውነትን የሚናገር ሰው አምርረው ይጸየፉታል፡፡ #እግዚአብሔር  ነቢያቱን እየላከ ሐሳቡና ፈቃዱ ምን እንደኾነ ደጋግሞ ቢነግራቸውም አይመለሱም፡፡ ቅን ነገርን ማድረግ አያውቁም፡፡ ችጋረኛውን ይውጡታል፡፡ የአገሩን ድኻ ያጠፋሉ፡፡ ሚዛኑን አሳንሰው በሐሰት ይሸጣሉ፡፡ ንጹሕ እኽል ሳይኾን ግርዱን ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ድኻውን ይደበድቡታል፤ ይበድሉታል፤ ፍርድ ያጣምሙበታል፤ ያስጨንቁታል፤ ጉቦ ይቀበሉታል፡፡ በዚያም ላይ ቀረጥን ያበዙበታል፡፡ ለራሳቸው ግን ከተጠረበ ድንጋይ ቤቶችን ይሠራሉ፡፡ ያማሩ የወይን ቦታዎችን ይተክላሉ፡፡ ግፍንና ቅሚያን በአዳራሾቻቸው ያከማቻሉ፡፡ ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ይተኛሉ፡፡ በምንጣፋቸው ላይ ተደላድለው ይቀመጣሉ፡፡ አምጡ እንብላ እንጠጣ ይላሉ፡፡ ከበጐች መንጋ ጠቦቱን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ይበላሉ፡፡ በመሰንቆ ድምፅ ይንጫጫሉ (ይዘፍናሉ)፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ ካህናትና ነቢያት ለገንዘብ የሚሠሩ ነበሩ፡፡
በቅርብ ጊዜ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በአኹኑ ሰዓት የዓለማችን ሰማንያ ከመቶ ሃብትና ንብረት በሃያ ፐርሰንት ግለሰቦች ብቻ የተያዘ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ በዓለማችን ፍትሐዊ የኾነ የሃብት ክፍፍል የለም ማለት ነው፡፡ በአገራችን ያለውን ነባራዊ ኹኔታ ስናየውም ቢብስ እንጂ ከዚኹ አይሻልም፡፡ ነቢዩ አሞጽ በሚያገለግልበት ወራት የነበረው ኹናቴ ከአኹኑ ኹኔታ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል ያልነውም ከዚኽ ተነሥተን ነው፡፡
በሌላ መልኩ በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ምዕራፍ ፲፬ ከቁጥር ፳፫ እስከ ፍጻሜ ያለውን ኃይለ ቃል ስናነብ ኢዮርብዓም ወደ አምልኮ ጣዖት ማዘንበሉን እናነባለን፡፡
በሕዝቡ ዘንድ የነበረው የእምነትና የጸሎት ኹኔታ በእጅጉ የወደቀ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በዓላትን እንዲያከብሩ፣ የተቀደሰ ጉባዔ እንዲያደርጉ፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲኹም የእኽል የቊርባን እንዲያቀርቡ፣ በመሰንቆ እንዲያመሰገኑ የነገራቸውና ያዘዛቸው #እግዚአብሔር ራሱ ቢኾንም ነቢዩ ሆሴዕ፡- “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን ከሚቃጠለውም መሥዋዕት ይልቅ #እግዚአብሔርን ማወቅ እወዳለኹ” እንዳለ /ሆሴ.፮፡፮/ ግብራቸው እጅግ የከፋ ስለኾነ ይኽን ቢያቀርቡለትም አልተቀበላቸውም፡፡ “ዓመት በዓላችኹን ጠልቼዋለኹ፤ ተጸይፌውማለኹ፤ የተቀደሰውን ጉባዔአችሁ ደስ አያሰኘኝም፡፡ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችኹ የእኽሉን ቊርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ ለምስጋና መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም፡፡ የዝማሬኽንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆኽንም ዜማ አላደምጥም” ያላቸው ስለዚኹ ነው /አሞ.፭፡፳፩-፳፫/፡፡ መፍትሔውም #እግዚአብሔርን መፈለግ ብቻ መኾኑን ተናግሯል /አሞ.፭፡፬-፱/፡፡ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ መልካሙን እንዲፈልጉ፣ ይኽን ቢያደርጉም የሠራዊት ጌታ #እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንደሚኾን ተናግሯል /አሞ.፭፡፲፬-፲፭/፡፡

                 #ትንቢተ_አሞጽ

ከኋለኛው ዘመን ነቢያት የተናገረውን ትንቢት በመጻፍ የመዠመሪያው ነው፡፡ የአሞጽ ትንቢተ በአብዛኛው በእስራኤልና በአከባቢው ባሉ አገሮች ላይ የሚመጣውን ፍርድ ማስታወቅ ነው፡፡ ፵፩ ጊዜ “ #እግዚአብሔር እንዲኽ ይላል” እያለ መናገሩም ይኽንኑ ያስረዳል፡፡ የሚዠምረውም በአሕዛብ ላይ ማለትም በቂር፣ በኤዶም፣ በደማስቆ፣ በሶርያ፣ በቴማን፣ በጢሮስ፣ በሞዓብ ሊመጣ ያለውን ፍርድ በማስታወቅ ነው /አሞ.፩ ሙሉውን ያንብቡ/፡፡ ቀጥሎም በይሁዳና በእስራኤል ሊመጣ ያለውን ፍርድ ይናገራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከላይ ለመግለጥ እንደሞከርነው የሕዝቡ በግዴለሽነት መኖር ያመጣው መዘዝ ነው፡፡
ነቢዩ አሞጽ ክብር ይግባውና #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በተሰቀለበት ጊዜ ስለሚኾነው ተአምር ናግሯል፡፡ ሕዝብና አሕዛብ በክርስቶስ አንድ እንደሚኾኑ መናገሩም ቅዱሳን ሐዋርያት ጠቅሰዉታል /፱፡፲፩-፲፪፣ ሐዋ.፲፭፡፲፭-፲፰/፡፡

➛በአጠቃላይ መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1, ፍርድ በእስራኤል ጐረቤት አገሮች /፩:፩-፪፡፭/፤
2, ፍርድ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ /፪፡፮-፫፡፮/፤
3, ፍርድ በእስራኤል በደል ምክንያት /፫፡፩-፮፡፲፬/፤
4, ፍርድ በአምስት ዓይነት መንገድ /፯፡፩-፱፡፲/፤ በዚኽም መካከል የአሜስያስና የአሞጽ ታሪክ /፯፡፲-፲፯/፤
5, በፍጻሜው ዘመን ስላለው የእስራኤል ተስፋ /፱፡፲፩-ፍጻሜ/፡፡

የነቢዩ አሞጽ የመጨረሻው ዕረፍት
ስለ ነቢዩ አሞጽ የመጨረሻው ዕረፍት መረጃ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ግንቦት ፳፩ ላይ የሚነበበው ስንክሳርም ነቢዩ በዚያ ዕለት እንደሚታሰብ ከመናገር ውጪ ያለው ነገር የለም፡፡

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር!!
#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ እና #ነቢዩ_ኤልያስ

ቅዱስ ዮሐንስ በበርካታ መንገዶች ከነቢዩ ኤልያስ ጋር ተያይዟል፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መምጣትና መንገድ ጠራጊነት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
«እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የ #እግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ቴስቢያዊውን ኤልያስን እልክላችኋለሁ … እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል፡፡» /ሚል.4÷5-6/
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም የቅዱስ ዮሐንስን መወለድ ለአባቱ ለዘካርያስ በቤተ መቅደስ ሲያበሥረው እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
«… እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የከሐድያንንም ሐሳብ ወደ ጻድቃን ዕውቀት ይመልስ ዘንድ ሕዝብንም ለ #እግዚአብሔር የተዘጋጀ ያደርግ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል» /ሉቃ.1÷17/

በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ከመሲህ መምጣት በፊት የኤልያስን መምጣት ይጠብቁ ነበር፡፡ ለምሳሌ #ጌታችንን ደቀመዛሙርቱ «ጻፎች ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣ ዘንድ አለው ለምን ይላሉ?» ብለው ጠይቀውት ነበር፡፡ /ማቴ.17÷10፣ ማር.9÷11/
#ጌታችንም ኤልያስ ይመጣል ተብሎ የተነገረው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን እንዳስረዳቸው እነርሱም እንደተረዱ ቅዱስ ማቴዎስ ይነግረናል /ማቴ.17÷11-13/
«ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለችው «አዎን፤ ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ያቀናል፡፡ ነገር ግን እላችኋለሁ፡፡ ኤልያስ ፈጽሞ መጥቷል፤ የወደዱትንም አደረጉበት እንጂ አላወቁትም …» ከዚህም በኋላ ደቀመዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንደነገራቸው አወቁ፡፡»

ከአንድ ታላቅ እና ታዋቂ ሰው በኋላ የሚነሱ ደጋግ ሰዎችን በእዚያ በታላቁ ሰው ስም መጥራት በትንቢቶች ውስጥ የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ዳዊት እሥራኤላውያን የሚወዱትና ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ንጉሣቸው ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ካለፈ በኋላ #እግዚአብሔር ደጋግ ነገሥታትን እንደሚያስነሳላቸው ለእሥራኤል ተስፋ ሲሰጥ ዳዊትን አስነሳላችኋለሁ ይላቸው ነበር፡፡
«ባርያዬም ዳዊት በላያቸው ላይ ንጉሥ ይሆናል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል» /ሕዝ.37÷24/
«ለ #እግዚአብሔርም ለማስነሣላቸው ለንጉሣቸው ለዳዊትም ይገዛሉ» /ኤር.3ዐ ÷9/፡
አሁንም የተደረገው ይኸው ነው፡፡ አይሁድ ኤልያስን በጣም ይወዱትና ያከብሩት ነበር፡፡ አሁንም ድረስ ያሉ አይሁዳውያን የፋሲካን በዓል በሚያከብሩበት ዕለት ለማዕድ ሲቀመጡ «ለኤልያስ» ብለው አንድ ቦታ ይተዋሉ፤ የወይን ጠጅ የተሞላ ብርጭቆም ያስቀምጣሉ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ መምጣት «ኤልያስ ይመጣል» ተብሎ የተነገረው ለዚህ ነው፡፡ «እንደ ኤልያስ ያለ የኤልያስን ዓይነት ሥራ የሚሠራ ነቢይ ይወጣል» ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ለካህኑ ለዘካርያስ የተናገረው ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡ «…በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል…»

በእርግጥም ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን እና ነቢዩ ኤልያስን ብዙ የሚያመሳስሉአቸው ነገሮች አሉ፡፡
#አለባበሳቸው፡- የነቢዩ ኤልያስ አለባበስ በሁለተኛው መጽሐፈ ነገሥት እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፡፡ «እነርሱም ሰውየው ጠጉራም ነው፡፡ በወገቡም ጠፍር ታጥቆ ነበር አሉት፡፡ እርሱም ቴስብያዊው ኤልያስ ነው አለ» /2ኛነገ.1÷8/

#ትምህርታቸው፦ የሁለቱም ነቢያት ትምህርት ትኩረት የእስራኤል ሕዝብ ኃጢያታቸውን ትተው ወደ #እግዚአብሔር እንዲመለሱ ማድረግ ሲሆን፤ የሁለቱም ተግሳጽ የተሞላበት ነበር፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤልያስ «የ #እግዚአብሔር ከሆናችሁ የ #እግዚአብሔር ብቻ ሁኑ፤ የበአል /የጣኦት/ ከሆናችሁ የበአል /የጣኦት/ ብቻ ሁኑ» እያለ ጠንካራ ንግግሮች ይናገር ነበር፡፡

#ነገሥታትን መገሰጻቸው፡- ነቢዩ ኤልያስ ንጉሡን አክአብንና ንግሥቲቱ ኤልዛቤልን ናቡቴን ርስቱን ቀምተው በግፍ በማስገደላቸው ገስጿቸዋል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን አስመልክቶ ባስተማረው ትምህርት «በእርግጥም የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ትህርምት እጅግ የሚያስደንቅ ነበር፤ አይሁድንም በእርሱ ውስጥ ነቢዩ ኤልያሰን እንዲያዩ አድርጓቸዋል» ብሏል፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ ክብር እና መዓርጋት

ቅዱስ ዮሐንስ ክብሩ በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ የክብሩ ምስክሮችም #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ እና መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ናቸው፡፡
#ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ እንዲህ ሲል የመጥምቁን ክብር ተናግሯል፡፡
«ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጥታችኋል? ከነፋስ የተነሣ የሚወዛወዛውን ሸንበቆ ነው? ወይስ ምን ልታዩ መጥታችኋል ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን ነውን? እነሆ ቀጭን ልብስ የሚለብሱማ በነገሥታት ቤት አሉ? ምን ልታዩ መጥታችኋል ነቢይ ነውን? አዎን እርሱ ከነቢያት እጅግ ይበልጣል፤ እነሆ በፊትህ መንገድህን የሚጠርግ መልእክተኛዬን እልካለሁ ተብሎ ስለ እርሱ የተጻፈለት ይህ ነውና፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ ሴቶች ከወለዷቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም» /ማቴ.11÷7-11/
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም እንዲህ ሲል ክብሩን ተናግሮለታል፡- «እርሱ በ #እግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናል» /ሉቃ.1÷15/

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ «የቅዱስ ዮሐንስ ክብር እና ከፍ ከፍ ማለት ምንጮች ሁለት ናቸው፡፡» ይላሉ፡፡
1. በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ስለሆነ
ከመጥምቁ ዮሐንስ በፊት የ #እግዚአብሔር መንፈስ ወደ ብዙ ሰዎች መምጣቱ ተጽፏል፡፡ ለምሳሌ ያህልም
➛ሳሙኤል ሳኦልን ቀብቶ ባነገሠው ጊዜ «የ #እግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ወረደ» ተብሏል /1ኛሳሙ.10÷10/፡፡
➛ሳሙኤል ዳዊትን በንግሥና በቀባው ጊዜ «የ #እግዚአብሔር መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ መጣ» ተብሏል 1ኛ ሳሙ.16÷13፡፡
➛«የ #እግዚአብሔር መንፈስ ከሶምሶን ጋር ይሄድ ነበር» ተብሎም ተጽፏል /መሳ.13÷24/፡፡ ይሁን እንጂ የ #እግዚአብሔር መንፈስ «ሞልቶታል» የተባለ ግን ማንም አልነበረም፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ግን በ #መንፈስ_ቅዱስ የተሞላ ነበር፡፡ የከበረ እና ታላቅ በመሆኑ አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡
#መንፈስ_ቅዱስ የተሞላው ግን መቼ ነበር? በመንፈስ ቅዱስ የተሞላው ገና በማኅፀን ሳለ እናቱ ኤልሳቤጥ የእመቤታችንን የሰላምታ ድምፅ በሰማችበት ቅፅበት ነው፡፡
«ኤልሳቤጥም የ #ማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፤ ፅንሱ በማኅፀኗ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ መላባት» /ሉቃ.1÷14/
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል «ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል» ብሎ የተናገረው በዚህን ጊዜ ተፈጽሟል፡፡

2. ተጋድሎው
#መንፈስ_ቅዱስ ስጦታ በእኛ ሕይወት ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው እኛ በድርጊታችንና በተጋድሎአችን ስንጠብቀው፣ ስንንከባከበውና ስንሠራበት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ይህንን በሚገባ አድርጓል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ያደገው በበረሃ ውስጥ፣ በብሕትውና /በብቸኝነት/፣ የግመል ጠጉር እየለበሰ፣ አንበጣ እና የበረሃ ማር ብቻ እየተመገበ ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እንዲህ ብለዋል «እርሱ በበረሃው ውስጥ ጸሎትና ተመስጦን፣ ድፍረትን እና ፍርሃት አልባነትን፣ ጥንካሬን እና እምነትን ተምሯል፡፡ #እግዚአብሔር #እመቤታችንን አምላክን ፀንሣ ለመውለድ በቤተ መቅደስ እንዳዘጋጃት እርሱን ደግሞ ለመንገድ ጠራጊነት ተልእኮው በበረሃ አዘጋጅቶታል፤ እኛም የእነዚህ ነገሮች ባለቤት ለመሆን የብቸኝነትና የትህርምት ጊዜ የምናሳለፍበት የየራሳችን በረሃ ያስፈልገናል፡፡»

#ቅዱስ_ዮሐንስ መዓርጋት
#ነቢዩ_ኢሳይያስ

ኢሳይያስ የሚለው ስም በአይሁድ ማኅበረ ሰብ ውስጥ እጅግ የተለመደ ስም ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እንኳ ብያንስ ወደ ፯ የሚኾኑ ሰዎች በዚኽ ስም ተጠርተዋል፡፡
“ኢሳይያስ፣ የሻያ” ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ ሲኾን የስሙም ትርጓሜ “ #መድኃኒት” ማለት ነው፡፡ ሆሴዕ፣ ኢያሱ፣ ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት እንደኾነ መድኃኒት መባሉ ግን እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ ባጭር ታጥቆ፥ ጋሻ ነጥቆ፥ ዘገር ነቅንቆ አማሌቃውያንን አጥፍቶ እስራኤልን አድኖ፥ እንደ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሥጋዉን ቆርሶ፥ ደሙን አፍስሶ፥ ፲፫ቱን ሕማማተ መስቀል ታግሦ፥ አጋንንትን ድል ነስቶ ነፍሳትን አድኖ አይደለም፤ ተልእኮውን የሚገልጥ ነው እንጂ፡፡ በሌላ አገላለጽ ሊመጣ ያለው መሲሕ ማለትም #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በድንግልና ተፀንሶ፣ በድንግልና ተወልዶ፣ ቀስ በቀስ አድጎ፣ የደቂቀ አዳምን ሕማም ተሸክሞ አጠቃላይ የሰው ልጆችን በአስደናቂ መጐብኘትን ጐብኝቶ እንደሚያድናቸው ስለሚናገር “ኢሳይያስ - መድኃኒት” የሚል ስም ተሰጥቶታል፡፡

➛ተመሳሳይ ስም ካላቸው ከሌሎች ሰዎች ለመለየትም “የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ” ተብሎ ተጠርቷል /ኢሳ.፩፡፩/፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይኽ አሞጽ ነቢዩ እንዳልኾኑ ይስማማሉ፡፡ እናንቱም የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት እንደሚያስረዳው ሶፊያ ትባላለች፡፡

ኢሳይያስ ይኖር የነበረው በኢየሩሳሌም ነው፡፡ ኢሳይያስ ባለትዳርና የኹለት ልጆች አባት ነበር፡፡ ሚስቱም ነቢይት እንደነበረች መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል /ኢሳ.፰፡፫/፡፡ መተርጕማን እንደሚናገሩት፡- “የኢሳይያስ ሚስት ነቢይት መባሏ የባለቤቷን መንፈሳዊ ሕይወት፣ ተጋድሎውን ትጋራ ስለነበርና በተልእኮው ኹሉ ትረዳው ስለነበረ እንጂ ራዕይን የማየት ትንቢትንም የመናገር ጸጋ ተስጥቷት ስለነበረ አይደለም” ይላሉ፡፡ ኢሳይያስ ከባለቤቱ ኹለት ልጆችን ያፈራ ሲኾን የልጆቹ ስያሜም ትንቢት አዘል ትርጓሜን የቋጠረ ነው፡፡ ታላቁ ልጅ “ያሱብ” ይባላል፡፡ “ያሱብ” ማለትም “ቅሬታዎቹ ይመለሳሉ” ማለት ነው /ኢሳ.፯፡፫/፡፡ ታናሹ ልጅ ደግሞ “ማኄር ሻላል ሐሽ ባዥ” ይባላል፡፡ ይኸውም “ምርኮ ፈጠነ ብዝበዛም ቸኰለ” ማለት ነው /ኢሳ.፰፡፫/፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በቤተ ሰቡ በጣም ደስተኛ ነበር፡፡ ይመካባቸውም ነበር፡፡ “እነሆ፥ እኔና #እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት #ጌታ#እግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን” ማለቱም ይኽንን ያስረዳል /ኢሳ.፰፡፲፰/፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ በኢየሩሳሌም ሲኖር በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የቤተ መንግሥት አማካሪ ነበር፡፡ በራሱ መጽሐፍ እንደነገረንም በዘመኑ የነበሩ የይሁዳ ነገሥታት ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ ይባላሉ /ኢሳ.፩፡፩/፡፡ የነቢይነትን ሥራ የዠመረውም ወዳጁ ዖዝያን በሞተ በዓመቱ ነው፡፡ ይኸውም በ፯፻፵ ዓ.ዓ. አከባቢ ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ “ዖዝያንን ገስጽ” ሲባል ወዳጁ ስለኾነ ይሉኝታ ይዞት እምቢ ብሎ ነበር፡፡ ከዚኽም የተነሣ ከአፉ ላይ ለምፅ ወጣበት፡፡ ጌታም ተገልጦ፡- “የምትወደውና የምታከብረው ዖዝያን ሞተ፤ መንግሥቱም አለፈ፡፡ ሞት፣ ኅልፈት፣ በመንግሥቴም ሽረት የሌለብኝ እኔ አምላክኽ ብቻ ነኝ” አለው፡፡ ኢሳይያስ ይኽን ሲሰማ እጅግ ደነገጠ፡፡ ዳግመኛም #እግዚአብሔር፡- “ወደዚኽ ሕዝብ ማንን ልላክ?” አለው፡፡ ኢሳይያስም፡- “እኔ እሔድ ነበር፤ ግን በአፌ ለምፅ አለብኝ” ሲል መልአኩ በጉጠት አፉን ቀባውና ለምፁ ድኖለት ትንቢት ተናግሯል /ኢሳ.፮/፡፡

➛ነቢዩ ኢሳይያስ የነበረበት ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ግብረ ገብነታዊና ፖለቲካዊ ኹኔታ
ነቢዩ ኢሳይያስ በኢየሩሳሌም ሲኖር የቤተ መንግሥትም አማካሪ ኾኖ እንደማገልገሉ መጠን የነገሥታቱን ብዕል፣ ለመጓጓዣ የሚገለገሉባቸው ሠረገላዎች፣ ለማዕድ የሚጠቀሙባቸው ዕቃዎች፣ ሕዝቡን ንቀው የሚያዩበት ትዕቢታቸው፣ ከሚስቶቻቸው ጋር የሚያሳልፉት የቅንጦት ኑሮአቸውን ይመለከት ነበር፡፡ በየዕለቱ በሚዘጋጀው የእራት ግብዣ ልዑላኑ በከፍተኛ የወታደር፣ የሃይማኖትና የሲቪል አመራሮች ታጅበው የሚጠጡት ወይን፣ በመጨረሻም ሰክረው የሚያሳዩት አሳፋሪ ድርጊትን ያይ ነበር፡፡ ይኽ በእንዲኽ እንዳለ እነዚኽ ልዑላን ወደ ቤተ መቅደስ መጥተው የሚያቀርቡት የመሥዋዕት ብዛት፣ ከስግብግቦቹ የሃይማኖት መሪዎች የሚቀርብላቸው ውዳሴ ከንቱ፣ ከቤተ መቅደሱ መልስ በኋላ ደግሞ የሚያከናውኑትን አሕዛባዊ ግብር በአጽንዖት ይመለከት ነበር፡፡ ነቢዩ ሲመለከት የነበረው ይኽን የቤተ መንግሥቱና የቤተ ክህነቱ የቅንጦት ኑሮን ብቻ አይደለም፡፡ የመበለቶች፣ የወላጅ አልባ ሕፃናት፣ የድኾች፣ የችግረኞች ጩኸትም በነቢዩ ጆሮ ያስተጋባ ነበር፤ ወደ መንበረ ጸባዖትም ሲወጣ ያስተውል ነበር፡፡
➛ነቢዩ ራሱ “ራስ ኹሉ (የቤተ መንግሥቱ አመራር) ለሕመም ልብም ኹሉ (የቤተ ክህነቱ አመራር) ለድካም ኾኗል። ከእግር ጫማ አንሥቶ እስከ ራስ ድረስ (ከተራው ሕዝብ አንሥቶ እስከ አመራሩ ድረስ) ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም” ብሎ እንደገለጠው /ኢሳ.፩፡፭-፮/ የይሁዳ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት ከነ ተራው ሕዝቡ ተበላሽቶ ነበር፡፡ ኹሉም በ #እግዚአብሔር ታምኖ ሳይኾን በሰው ክንድ ተደግፎ ይሰባሰባል፤ ግዑዛን እንስሳት እንኳ የጌታቸውን ጋጣ ሲያውቁ ሰዎች ግን ፈጣሪያቸውን ረስተዋል፡፡ አለቆች በግብዝነት፣ ጉቦን በመውደድ፣ ለድኻ አደጉ ባለመፍረድ፣ የመበለቲቱን ሙግት ባለመስማት ይታወቃሉ /ኢሳ.፩፡፳፫/፡፡ አንባቢ ሆይ! አኹን ያለውን የቤተ ክህነታችንና የቤተ መንግሥት ኹናቴ ከዚኹ ጋር ያገናዝቡ!!!

#በነቢዩ ኢሳይያስ ጊዜ የነበረውን ፖለቲካዊ ትኩሳት ስንመለከትም፥ ነቢዩ አገልግሎቱን በዠመረበት ወራት በኹለት ኃያላን መንግሥታት ማለትም በግብጽና በአሦር መካከል ውጥረት ነግሦ ነበር፡፡ ወደ አገልግሎቱ ማብቂያ አከባቢ ደግሞ በአሦርና በባቢሎን መካከል የነበረው ፍጥጫ ጣራ የደረሰበት ወራት ነበር፡፡ የእነዚኽ ኃያላን መንግሥታት መፈክር፡- “Power is the truth - እውነት ማለት ሥልጣን ነው” የሚል ነበር፡፡ በእነዚኽ ኃያላን መንግሥታት መካከል የነበረው ፍጥጫ በእስራኤልና በይሁዳን እንዴት ጫና እንዳሳደረ ለመረዳትም ፪ኛ ነገሥት ከምዕራፍ ፲፭ እስከ ፲፯ ያለውን ክፍል ማንበብ በቂ ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለማየት ያኽልም፡-
#የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ምናሴ የአሦር ንጉሥ ለነበረው ለፎሐ መንግሥቱን ያጸናለት ዘንድ አንድ ሺሕ ሰቅል ብር ሰጥቶታል /፪ኛ ነገ.፲፭፡፲፱-፳/፡፡
➛የዖዝያን (ይሁዳ ንጉሥ) ንግሥና ማብቂያ አከባቢ ቴልጌልቴልፌልሶር የተባለ የአሦር ንጉሥ ፋቁሔ የተባለው የእስራኤል ንጉሥ ነግሦ ሳለ ሃገሪቱን ወርሮ ነበር /፪ኛ ነገ.፲፭፡፳፱/፡፡ በይሁዳ ላይ ነግሦ በነበረው በአካዝ ላይም ዘመቱበት፡፡ ኢሳይያስም የራሱን ልጆች ምልክት እያደረገ አካዝ በ #እግዚአብሔር እንዲታመን እንጂ እንዳይደነግጥ መከረው፡፡ አካዝ ግን ጠላቶቹን እንዲቋቋምለት ለማድረግ ለአሦር ንጉሥ ግብር ይልክለት ነበር /ኢሳ.፯፡፩-፲፯፣ ፪ኛ ዜና ፳፰፡፲፮-፳፩/፡፡
#ነቢዩ_ዮናስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“ዮናስ” ማለት “ርግብ” ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም እንደ ቅዱስ ጀሮም ትርጓሜ “ስቃይ” ተብሎም ይተረጐማል፡፡ ይኸውም ተልእኮውን የሚገልጥ ነው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ አድሮ እንደ ወጣ ኹሉ፥ የደቂቀ አዳምን ሕማም ለመሸከም መጥቶ የተሰቃየው #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ ስለዚኽ የነቢዩ ዮናስ እንዲኽ በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት መቆየት የ #ጌታችንን ሞትና ትንሣኤ በጥምቀት ተካፋዮች ለሚኾኑ ኹሉ በርግብ የተመሰለውን #መንፈስ_ቅዱስ እንደሚቀበሉና ለዚያ የተዘጋጁ እንዲኾኑ ማዘጋጀት ማለትም ማወጅ ነበር ማለት ነው /ማቴ.፲፪፡፴፱-፵/፡፡

ነቢዩ ዮናስ ነገዱ ከነገደ ይሳኮር ወገን ሲኾን አባቱ አማቴ እናቱም ሶና ይባላሉ፡፡ በአይሁድ ትውፊት እንደሚነገረው ደግሞ ዮናስ ነቢዩ ኤልያስ ከሞት ያስነሣው የሠራፕታዋ መበለት ልጅ ነው /፩ኛ ነገ.፲፰፡፲-፳፬/፡፡

ነቢዩ ዮናስ በአገልግሎት የነበረበት ዘመን በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ሲኾን መኖርያውም በገሊላ በጋትሔፈር ከተማ ነበረ /፪ኛ ነገ.፲፬፡፳፭/፡፡
ነቢዩ ዮናስ የሰሜናዊው ክፍል ማለትም የእስራኤል ነቢይ ነበር፡፡ ሲያገለግል የነበረውም ከ፰፻፳፭ እስከ ፯፻፹፬ ቅ.ል.ክ. ገደማ ነው፡፡ ከአሞጽም ጋር በዘመን ይገናኛሉ፡፡

ከእስራኤል ውጪ ወደ አሦራውያን ዋና ከተማ ወደ ነነዌ ኼዶ እንዲያስተምር በዚያ ዘመን ከነበሩት ነቢያት ብቸኛው ነው፡፡ ከዚኽም የተነሣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዮናስን “ነቢየ አሕዛብ” በማለት ይጠሩታል፡፡

ነነዌ➛ ይኽች ጥንታዊት ከተማ በጤግሮስ ወንዝ ዳር ከዛሬዋ የሞሱል ከተማ በተቃራኒ ከባግዳድ ሰሜን ምዕራብ ፫፻፶ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ነበረች፡፡ የመሠረታትም ናምሩድ ይባላል /ዘፍ.፲፡፲፩/፡፡ በኋላም ሰናክሬም የአሦር መንግሥት ዋና ከተማ አደረጋት /፪ኛ ነገ.፲፱፡፴፮/፡፡

የነነዌ ሕዝቦች መዠመሪያ ባቢሎናውያን ሲኾኑ /ዘፍ.፲፡፲፩/ አስታሮት (“የባሕር አምላክ”)የሚባል ጣዖትን ያመልኩ ነበር፡፡ ከተማይቱ በሃብቷና በውበቷ ትታወቅ ነበር፡፡ የአሦር ነገሥታትም በጦርነት የማረኳቸውን ሰዎች ያጉሩባት ስለ ነበረች “ባርያ” ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች የሚበዙባት ነበረች፡፡ ነገሥታቱ በጨካኝነታቸው፣ የብዙ ንጹሐን ዜጐችን ደም በከንቱ በማፍሰስ፣ በምርኮኞች ሞትና ስቃይ ደስ በመሰኘት እንደ መዝናኛም በመቊጠር ይታወቃሉ፡፡ ነቢዩ ናሆም “የደም ከተማ” ብሎ የጠራትም ከዚኹ የተነሣ ነው /ናሆ.፫፡፩/፡፡ ነቢዩ ዮናስ ይኽችን ከተማ ነበር ወደ ንስሐ እንዲጠራ በልዑል #እግዚአብሔር የተላከው፡፡
ነቢዩ ሶፎንያስ እንደምትጠፋ በተናገረው ትንቢት መሠረት /ሶፎ.፪፡፲፫/ በ፮፻፲፪ ቅ.ል.ክ. ላይ በባቢሎናውያን ፈርሳለች፡፡

#ትንቢተ_ዮናስ

ከብሉይ ኪዳን ኹለት መጻሕፍት ስለ አሕዛብ የሚናገሩ ናቸው፡፡ እነርሱም ትንቢተ አብድዩና ትንቢተ ዮናስ ናቸው፡፡ ትንቢተ አብድዩ ስለ ኤዶማውያን የሚናገር መጽሐፍ ሲኾን ትንቢተ ዮናስ ደግሞ ስለ ነነዌ ሰዎች ይናገራል፡፡ በትንቢተ አብድዩ አሮጌውና ደም አፍሳሹ ሰውነት (ኤዶማዊነት) ቀርቶ አዲሱና ጽዮናዊ (መንፈሳዊ) ሰው እንደሚመጣ በምሳሌ ይናገራል፡፡ በትንቢተ ዮናስ ደግሞ አሕዛብ አምነው በንስሐ እንደሚመለሱና #እግዚአብሔርም በአሕዛብ መካከል ቤተ ክርስቲያን እንደሚያቋቁም በኅብረ አምሳል ያስረዳል፡፡

አይሁዳውያን ብዙውን ጊዜ ነቢያትን ሲያሳድዱና ሲገድሉ እንደነበረ #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በዚኽ ምድር በተመላለሰበት ወራት ተናግሯል /ማቴ.፭፡፲፪፣ ፳፫፡፴፩/፡፡ ከዚኹ በተቃራኒ የነነዌ ሰዎች ማለትም አሕዛብ ግን የነቢዩ ዮናስን የአንድ ቀን ትምህርት ተቀብለው እውነተኛ ንስሐ ገብተዋል፡፡ ይኽ ደግሞ አሕዛብ #ክርስቶስን እንደሚቀበሉት፥ የገዛ ወገኖቹ የተባሉት አይሁድ ግን እንደሚክዱት የሚያስረዳ ነው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ወደ ነነዌ ላለመኼድ የኮበለለበት ምክንያትም ይኼው ነበር፡፡ ጀሮም የተባለ የጥንታዊቷ የላቲን ቤተ ክርስቲያን ሊቅ ትንቢተ ዮናስን በተረጐመበት መጽሐፉ ይኽን ሲያብራራ፡- “ነቢዩ ዮናስ የአሕዛብ በንስሐ መመለስ የአይሁድ ጥፋትን እንደሚያመለክት በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር፡፡ ስለዚኽ ወደ ነነዌ ላመኼድ የፈለገው አሕዛብን ጠልቶ አይደለም፤ የገዛ ወገኖቹ ጥፋት በትንቢት መነጽር አይቶ አልኼድም አለ እንጂ፡፡ ይኸውም ሊቀ ነቢያት ሙሴ በአንድ ስፍራ ላይ “ወዮ! እኒኽ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፤ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አኹን ይኽን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍኽ እባክህ ደምስሰኝ” እንዳለው ነው /ዘጸ.፴፪፡፴፪/፡፡ ሙሴ እንዲኽ ስለጸለየ እስራኤላውያን ከጥፋት ድነዋል፤ ሙሴም ከሕይወት መጽሐፍ አልተደመሰሰም፡፡ … ዳግመኛም ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ “ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በ #ክርስቶስ ኾኜ እውነትን እናገራለኹ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በ #መንፈስ_ቅዱስ ይመሰክርልኛል፡፡ በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ኾኑ ስለ ወንድሞቼ ከ #ክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድኾን እጸልይ ነበር” እንዳለው ነው /ሮሜ.፱፡፩-፪/፡፡… ነቢዩ ዮናስ እንግዲኽ ብቻውን ከነቢያት ተመርጦ ወደ እስራኤል ጠላቶች (ወደ አሦራውያን)፣ ጣዖትን ወደምታመልክና #እግዚአብሔር ወደማታውቅ አገር ኼዶ እንዲሰብክ መመረጡ በእጅጉ አሳዝኖታል” ይላል፡፡ ክብር ይግባውና #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም፡- “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚኽ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና” ብሏል /ማቴ.፲፪፡፵፩/፡፡

አሕዛብ አሚነ #ክርስቶስን እንደሚቀበሉና አይሁድ ከአሚነ #ክርስቶስ እንደሚወጡ የተረጋገጠው በነነዌ ሰዎች መመለስ ብቻ አይደለም፡፡ የመርከበኞቹና የመርከቢቱ አለቃ ባሳዩት እምነት፣ ፈሪሐ #እግዚአብሔርንና#እግዚአብሔር ባቀረቡት መሥዋዕትም ጭምር እንጂ፡፡ ቅዱስ ጀሮም ቅድም በጠቀስነው መጽሐፉ ላይ እንዲኽ ሲል ያክላል፡- “አይሁድ ፍርድን በራሳቸው ላይ ጨመሩ፤ አሕዛብ ግን እምነትን ገንዘብ አደረጉ፡፡ የነነዌ ሰዎች በንስሐ ወደ አምላካቸው ተመለሱ፤ የእስራኤል ሰዎች ግን ንስሐ ባለ መግባታቸውና በጠማማ መንገዳቸው ስለጸኑ ጠፉ፡፡ እስራኤል መጻሕፍትን ተሸክመው ቀሩ፤ የነነዌ ሰዎች (አሕዛብ) ግን የመጻሕፍቱን #ጌታ ተቀበሉት፡፡ እስራኤላውያን ነቢያት ነበሯቸው፤ የነነዌ ሰዎች (አሕዛብ) ግን የነቢያቱን ሐሳብና መልእክት ገንዘብ አደረጉ፡፡ የእስራኤል ሰዎች ፊደሉ ገደላቸው፤ መንፈስ ግን የነነዌን ሰዎች (አሕዛብን) አዳናቸው፡፡”

በአጠቃላይ መጽሐፉን በአራት ክፍል ከፍለን ማየት እንችላለን፡-
1, ምዕራፍ አንድን ስናነብ ነቢዩ ዮናስ ወደ ነነዌ ኼዶ እንዲያስተምር እንደታዘዘና ነቢዩም ወደ ኢዮጴ እንደ ኰበለለ፣ ከመከበኞች ጋር ተወዳጅቶ ከመርከብ ወጥቶ ሲቀመጥ ኃይለኛ ማዕበልና ሞገድ እንደተነሣ፣ ነቢዩ ዮናስ ወደ ማዕበሉ እስኪጣል ድረስም ማዕበሉ ጸጥ እንዳላለ እናነባለን፡፡ የባሕሩ ማዕበልና ሞገድ ጸጥ ያለው ነቢዩ ወደ ባሕሩ ሲጣል ነው፡፡ በኃጢአት ማዕበል የሚነዋወፀው የሕይወታችን ባሕርም ፀጥ ያለው ክብር ይግባውና #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የእኛን ባሕርይ ባሕርይ አድርጐ ሲመጣ ነው፡፡
2, ምዕራፍ ኹለትን ስናነብ ነቢዩ ዮናስ ወደ ባሕሩ ሲጣል ዓሣ አንበሪ እንደተቀበለውና በከርሡም ሦስት ሌሊትና ሦስት መዓልት እንደተሸከመው፤ ዮናስም በዚያ ኾኖ ያመሰግን እንደነበር እናነባለን፡፡ በዚኽም የዋኁ ዮናስ #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የእኛን ሞት ተሸክሞ ወደ #መስቀል እንደወጣና ከዚያም ሞታችንን ይገድል ዘንድ ወደ መቃብር እንደወረደ የሚያስረዳ ነው፡፡ የዮናስ ምስጋናም የቤተ ክርስቲያን ምስጋና ነው፡፡

3, ምዕራፍ ሦስትን ስናነብ ዓሣ አንበሪው ነቢዩ ዮናስን እንደተፋውና ወደ ነነዌ እንደኼደ የነነዌ ሰዎችም በዮናስ የንስሐ ጥሪ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንተመለሱ እናነባለን፡፡ እውነተኛው ዮናስ #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ አሕዛብን ወደ መንግሥቱ እንደሚጠራና ብዙዎች እንደሚያምኑበት ያመለክታል፡፡

4, ምዕራፍ አራትን ስናነብ ደግሞ ነነዌ እንደዳነችና #እግዚአብሔርም ዮናስን በአስደናቂ ጥበቡ የውስጥ ሰላሙን እንደመለሰለት እናነባለን፡፡ #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ደስ የተሰኘው ከልጆቹ ከሕዝብም (ከዮናስም) ከአሕዛብም (ከነነዌም) ዕርቅን ሲፈጽም ይቅርም ሲላቸው ነው፡፡

ከትንቢተ ዮናስ ምን እንማራለን?

➛ትንቢተ ዮናስ #እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅና የማይለካ ፍቅር የተገለጠበት መጽሐፍ ነው፡፡ በመጽሐፉ #እግዚአብሔር የእስራኤል ብቻ ሳይኾን የኹሉም አምላክ እንደኾነ ተገልጧል፡፡ የሕዝብም የአሕዛብም ሠራዒና መጋቢ እንደኾነና የኹሉም ድኅነትን እንደሚሻ ተመልክቷል፡፡
➛በመጽሐፉ የነቢዩን ድካም ተገልጧል፤ ይኸውም ነቢያት እንደኛ ሰዎች እንደነበሩና ድካም እንደነበረባቸው ግን ደግሞ #እግዚአብሔር በመለኮታዊ ጥበቡ ድካማቸውን ለታላቅ ተልእኮ እንደተጠቀመበት ተጽፏል፡፡
#እግዚአብሔር ከአእምሮ በላይ ጠቢብ እንደኾነ፣ ፈጣሪን አያውቁም ተብለው ለሚታሰቡ እንደ መርከበኞቹ ላሉ ሰዎች እንኳን የዕውቀት ብርሃንን እንደሚሰጣቸው ተገልጧል፡፡
#እግዚአብሔር ከጥበቡና ከጥልቅ ፍቅሩ የተነሣ ልጆቹን ለመገሠፅና ከእርሱ ጋር እንዲታረቁ ለማድረግ ግዑዛን ፍጥረታት እንኳን እንደሚጠቀም ተገልጧል፡፡ ለምሳሌ፡- መርከቢቱ ያናውፅ ዘንድ የተላከው ጽኑ ንፋስ፣ ዮናስን የዋጠው ዓሣ አንበሪ፣ ዮናስ ዋዕየ ፀሐይ እንዳይመታው የበቀለችው ቅል፣ ቅሊቱን እንዲበላ በማግሥቱ የታዘዘው ትል #እግዚአብሔር ከዮናስ ጋር ለመታረቅ የተጠቀመባቸው ፍጥረታት ናቸው፡፡ ዛሬስ #እግዚአብሔር በምን ዓይነት መንገድ እየጠራን ይኾን?

ለልዑል #እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!!
#ማኅሌተ_ጽጌ ፤ ምንጩ ትርጉሙና መልእክቱ (ክፍል አንድ)

በስመ #አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ኃይለ ቃልን ከትርጓሜ፣ ትርጓሜን ከምሥጢር እንዲሁም ደግሞ ምሥጢርን ከዜማ ጋር አስተባብረውና አስማምተው የሚደርሱ ሊቃውንት ባለቤት ናት፡፡ በ5ኛው መ.ክ.ዘመን የተነሣው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አምስቱን ጸዋትወ ዜማ ሲደርስ በ14ኛው መ.ክ.ዘመን የተነሣው አባ ጊዮርጊስ ደግሞ ሰዓታትን ደርሷል፡፡ በዚሁ ዘመን አባ ጊዮርጊስ ጋር ጥልቅ መንፈሳዊ ፍቅር የነበረው አባ ጽጌ ድንግል “ማኅሌተ ጽጌ” የተባለውን ድርሰት ደርሷል፡፡ ማኅሌተ ጽጌ ግጥማዊ አካሔድ ያለው ድንቅ ኢትዮጵያዊ ድርሰት ነው፡፡ ይህ ድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውለው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው የእመቤታችን የቅድስት #ድንግል_ማርያም የስደት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ሌሊት በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ መሰደድና መንከራተት እያሰቡ የሚደረስ ምሥጋናና ጸሎት ነው፡፡

በሀገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት /ዘመነ ጽጌ/ ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ዘመን #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ “ስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔርን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ እናንተንማ ይልቁን እንዴት እንግዲህ ምን እንበላለን ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ ...» /ማቴ.5፡28-33/ በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባን መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር እንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ምግብና ልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡ እንዲሁም ክቡር ዳዊት «ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ ሰብእሰ ከመ ሳዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ፤ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆን አስብ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነው እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና» /መዝ.1ዐ2፤14-16/ በማለት እንደ ተናገረው የሰው ሕይወት በሣር ይመሰላል፡፡ ሣር አድጐ አብቦ ከዚያ በኋላ ይደርቅና በነፋስ አማካኝነት ያ የረገፈው ሣር እየተነሣ የነበረበት ቦታ ስንኳ እስከማይታወቅ ድረስ ይሆናል፡፡ ሰውም ከአደገ በኋላ በሕማም ፀሐይነት ይደርቅና በሞተ ነፋስነት ይወሰዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መቃብር ሲወርድ የነበረበት ቦታ ይዘነጋል፡፡ ስለዚህ ዘመነ ጽጌ ሰው ዘመኑ እንደ አበባ በቶሎ የሚረግፍ መሆኑን በማሰብ ይህ ዘመን ሳያልፍ መልካም ሥራ ለመሥራት ትንሣኤ ኅሊና የሚነሣበት ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለዘመነ ጽጌ የሠራው ድጓም ይህንኑ የሰውን ዘመን አጭርነት የሕይወቱን ኢምንትነት በዚህ ሕላዌ የተፈጠረ ሰው በዚህ ዓለም ክፉ ሥራ መሥራት እንደሌለበት ሁልጊዜ በተዘክሮተ ሞት እንዲኖር የሚያስረዳ ነው፡፡

በዘመነ ጽጌ ቅዱስ ያሬድ ከደረሰው ድጓ በተጨማሪ ከላይ እንደተጠቀሰው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣ አባ ጽጌ ድንግል ከዚሁ ዘመን ጋር የተያያዘ ድርሰት ደርሷል፡፡ ይህ ድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ በአብዛኛው አምስት ስንኞች ያሉት ሲሆን ብዛቱም 15ዐ ያክል ነው፡፡ ይህም ድርሰት «ማኅሌተ ጽጌ» በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኘው ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያምንና ልጇን #መድኃኒታችንና_አምላካችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመሰለ የሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባ ሲመስል ልጇን በፍሬ እርሷን በፍሬ ሲመስል ደግሞ ልጇን በአበባ እየመሰለ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ «ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዓርግ ጽጌ እምጉንዱ፤ ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል» /ኢሳ.11፡1/ ብሎ ከእሴይ ዘር የምትገኘውን #እመቤታችንን በበትር ከርሷ የሚገኘውን #ክርስቶስን ደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመር እያንዳንዱን መልክዕ #እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬ በመመሰል የ #እግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር በታሪክ፣ በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅ በሆነና በተዋበ ሁኔታ አዋሕዶ ደርሶታል፡፡

#እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋን ሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስ ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው ለፍቅሯ ሲሳሳ ለነበረው ለአባ ጽጌ ድንግል ደግሞ ይህንን ማኅሌተ ጽጌን እንዲደርስ አድርጋዋለች፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ማኅሌተ ጽጌ በመልክዕ አደራረስ ሥርዓት የተደረሰ ሲሆን ይህንንም ለመመልከት እንዲያመች በሚከተሉት ክፍሎች ከፋፍሎ ማቅረብ ይቻላል፡፡

1, #ጸሎት

በዚህ አገባብ ጸሎት ስንል በተለየ ሁኔታ ጸሎትነቱ የጐላውን ለማየት እንጂ ድርሰቱ በሙሉ ጸሎት ነው፡፡ ሌሎቹንም እንዲሁ ታሪክ፣ ተግሳጽ፣ ምሥጢር ተብለው መከፈላቸው በበዛውና በጐላው ለመግለጽ ነው እንጂ ሁሉም በሁሉ አለ፡፡ በጸሎትነታቸው ጐልተው ከሚታዩት ውስጥ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡

1.1. አንብርኒ #ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፣
ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት፣
በእንተ ርስሐትየሰ ኢትመንንኒ ንግሥት፣
እስመ ወሀብኩ ንብረትየ ለፍቅርኪ ሞት፣
ዘአሰገርዎሙ ለሰማዕት በጽጌሁ ሕይወት፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን «የምእመናንንና የ #ክርስቶስን ነገር በምሥጢር በተናገረበት በመኃልይ መጽሐፉ «እንደ ማኅተም በልብህ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ» /መኃ.9፤6/ ይላል፡፡ ይኸውም የምእመናንንና የ #ክርስቶስን አንድነት የሚገልጽ ነው፡፡ «አንብርኒ #ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፤ ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት» ማለቱ #እመቤታችንን እንደ ማኅተም በልብሽ አኑሪኝ በማለት በእናትነትሽ፣ በአማላጅነትሽ አትርሽኝ ካለ በኋላ «በእንተ ርስሐትየሰ አትመንኒ ንግሥት» ይላል፡፡ ይኸም ማለት አትርሽኝ በልብሽ አኑሪኝ ብዬ የምለምንሽ አንቺ እንዳትረሽኝ የሚያደርግ መልካም ሥራ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሰውነቴ ክፋት ምክንያት በኃጢአቴና በወራዳነቴ ምክንያት እኔን ከማሰብ ከልቡናሽ አታውጪኝ በማለት #እመቤታችን በርኅሩኅ ልቧ «መሐር ወልድየ ወተዘከር ኪዳንየ» እያለች እንድታዘክረን የሚያሳስብ ጸሎት ነው፡፡

ሶበ አተቦ ለማይ በቅዳሴኪ እንዘ ይጼሊ፣
ረሰዮ ኅብስተ ጽጌ ሃይማኖት ሳሙኤል ዘሐቅለ ዋሊ፣
ምሕረተ ወፍትሐ ለተአምርኪ አኀሊ፣
ሥረዪ ኃጢአትየ ወእጸብየ አቅልሊ፣
እስመ ኩሉ ገቢረ ማርያም ትክሊ፡፡
እነዚህም ቅዱሳን ነገሥታት ትምህርተ ወንጌልን እየሰጡ በአክሱም ቤተ መንግሥታቸው ሳሉ ከዕለታት አንደኛው ቀን #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ በአክሱም ‹‹ማይ ኰኩሐ›› በሚባል ተራራ ላይ ቁሞ አብርሃ ወአጽብሓን ጠርቶ ‹‹በዚህች ቦታ ላይ ቤተ መቅደሴን አንጹልኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ቦታው ባህር ላይ ነው በየት እናንጽልህ?›› አሉት፡፡ #ጌታችንም በጥበቡ ከገነት ጥቂት አፈር አምጥቶ በባሕሩ ላይ ቢበትንበት ባሕሩ ደርቆ ሜዳ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ #ጌታችን ‹‹ቤተ መቅደሴን በዚህ ሥሩ›› ብሏቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ #ጌታችንም በቆመባት ዓለት ላይ የእግሩ ጫማ ቅርጽ እስከ አሁን ሳይጠፋ በግልጽ ይታያል፡፡ ቦታውም ከዚያ ወዲህ ‹‹መከየደ እግዚእ›› እየተባለ ይጠራል፡፡

አብርሃ ወአጽብሓ ከመንግሥት አስተዳደሩ ጋር ክርስትናንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በመላ ኢትዮጵያ በማዳረስ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል፡፡ ካህናትንና ዲያቆናትን ይዘው በመላ ኢትዮጵያ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ ሕዝቡን ሁሉ እያስተማሩ፣ ሃይማኖትን እያጸኑ፣ ሥርዓተ ጥምቀትን እያስፋፉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል፡፡ በሀገራችን በአራቱም አቅጣጫ ወንጌልን አስፋፍተው ሕግ ሠርተዋል፡፡ የከበሩ ቅዱሳን ነገሥት አብርሃ ወአጽብሓ በእንዲህ ዓይነት ግብር ጸንተው በመኖር #እግዚአብሔርንም ሰውንም አገልግለው ለሀገራችንም ብርሃን አብርተውላት ነው ያለፉት፡፡

ታላቁ አብርሃ በ364 ዓ.ም ጥቅምት 4 ቀን እሁድ ዕለት ዐረፉ፡፡ ከ13 ዓመት በኋላ ታናሹ አጽብሓ በ379 ዓ.ም ጥቅምት 4 ቀን ዐረፉ፡፡ ልደታቸውም ሆነ ሞታቸው አንድ ቀን ነው-የዕረፍታቸው ዓመቱ ይለያይ እንጂ፡፡ የተቀበሩበት ቦታም አንድ ነው፡፡ የንግሥና ስማቸው ኢዛናና ዛይዛና ይባላል፡፡

እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያው_ቅዱስ_ሐናንያ

በዚችም ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሐዋርያ ቅዱስ ሐናንያ በሰማዕትነት አረፈ ። ይህም ቅዱስ በሐዋርያት እጅ ለደማስቆ አገር ኤጲስቆጶስነት ተሾመ እርሱም ክብር ይግባውና #ጌታችን በደማስቆ ጐዳና ተገልጦለት ለወንጌል ትምህርት በጠራው ጊዜ ሐዋርያ ጳውሎስን ያጠመቀው እርሱ ነው ።
እርሱም አስቀድሞ ለግብሪል ወገኖች አስተማረ ብዙዎች በሽተኞችን አዳናቸው ብዙ ሰዎችንም ክብር ይግባውና ወደ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖት መለሳቸው ።

ከዚህም በኋላ ስሙ ሉቅያኖስ የሚባል መኰንን ያዘው በምድር ላይ ደሙ እንደውኃ እስከሚፈስ ድረስ ገረፈው ጐኖቹንም በብረት በትሮች ሠነጣጠቀ ደረቱንም በእሳት መብራቶች አቃጠለ ። ከዚህም በኋላ ከከተማ ውጭ አውጥተው በደንጊያ ይወግሩት ዘንድ አዘዘ በዚህም ነፍሱን በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጠ ።

እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ ሐናንያ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_በርተሎሜዎስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን አቡነ በርተሎሜዎስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ጻድቁ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ልጆች ውስጥ አንዱ ሲሆኑ ያመነኮሷቸውና የሾሟቸውም እርሳቸው ናቸው፡፡ የቆባ፣ የጠጠርና የኮረም ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሹመው በብዙ ድካም አገልግለዋል፡፡ ጻድቁ ደብረ ሊባኖስን የሚያጥኑበት ተራቸው በወርሃ ጳጉሜ ነበር፡፡

ወሎ ራያ ውስጥ ያለችውን ጥንታዊቷንና ባለታሪኳን ደብረ ዘመዳን የመሠረቷት ይህ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የሳላት የእመቤታችን ሥዕል ሁልጊዜ ሰዓታትና ማኅሌት በማይታጎልባት በዚህች ጥንታዊ ገዳም ውስጥ ትገኛለች፡፡ እጅግ በርካታ ቅርሶችም ይገኙባታል፡፡ በአካባቢዋም ዘብ ሆነው የሚጠብቋት በርካታ የዱር አራዊት ይገኛሉ፡፡ ጻድቁ በታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ ኖረው በሰላም ዐርፈዋል፡፡

#ስለ_አቡነ_በርቶሎሜዎስ_ዕረፍት፦ ... ከዚኽ በኋላ በዚያች ቀንና በዚያች ሰዓት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከክብርት እናቱ ከእመቤታችን ወላዲተ አምላክ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ወደ እርሱ መጥቶ ተገለጠለት። ያን ጊዜም መንፈሳዊ አባታችን አባ በርተሎሜዎስ ደንግጦ ወደቀ። እንደምውትም ኾነ። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግፎ አንሥቶ "ወዳጄ፤ የእናቴ የድንግል ማርያምም ወዳጅ በርተሎሜዎስ ሆይ እነሆ ገድልህ ፈጽመሃል። መላእክትህንም በመልካም ተጋድሎ ጨርሰሃል። ስለ ትሕትናህ መረጥሁህ። እነሆ በማይታበል ቃሌ ፍጹም ክብርን ሰጠኹህ። በጸሎትህ አምኖ መቃብርህ ያለበትን ገዳም የሚሳለም ራሱንም ስለ ስምህ ብሎ ዝቅ የአደረገውን ኹሉ ኃጢአቱን ይቅር ብሎ ደስታ የተመላች ገነትን አወርሰዋለሁ"።

"ዝክርህን የዘከረ፣ ስምህን የጠራ፣ መጽሐፈ ገድልህን የጻፈ፣ ይኽንን መጽሐፈ ገድልህንም የጸለየበት፣ በጆሮውም የሰማውን ኹሉ እኔ ስሙን ስምህ በተጻፈበት የወርቅ ዐምደ ሰሌዳ ውስጥ እጽፍለታለሁ። ዕጣንና ዘቢብ መብራት ቅብዐ ቅዱስንም ለቤተ ክርስቲያንህ የሚሰጥ እኔ በመንግሥተ ሰማያት ዋጋውን አላጎድልበትም። መቃብርህ ወደአለበት ወደ ዚኽ ገዳም የሄደ ወይም መቃብርህን የጠበቀውን እኔ የመቃብር ቦታዬ ወደ አለበት እንደሄደ ቆጥሬ ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ። በገዳምህ ምንኵስናን ተቀብሎ የመነኰሰውን ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ። አስኬማውንም አስኬማ መላእክት አደርግለታለሁ። በስምህ እንግዳን የሚቀበል ለባልንጀራውም በሚቻለው ኹሉ በጎ ለሚያደርግ ወደ ቀደመ በደሉ ካልተመለሰ በደሉን አላስብበትም። የተጠማን ለሚያጠጣ የተራበን ለሚያበላም በሺህ ዓመት የሚገለጥ የደስታ ሕወትን ደስ የሚያሰኝ ጽዋዐ ሕይወትን አጠጣዋለሁ"።

"መቃብርህ በአለበት ገዳም የሚቀበረው ኹሉ፤ ስንኳ የሚቀበረውን ተሸክሞው ወደ ገዳምህ የመጡትንም በደላቸውን አላስብባቸውም። ስምህን ጠርቶ በማናቸውም ነገር በጸሎትህ ታምኖ ቢኾን በገዳምህ በመኖር እስከ ዕለተ ሞቱ የአገለገለውን እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ። ወዳጄ በርተሎሜዎስ እነሆ የማይታበል ቃል ኪዳኔን ሰጠኹህ። ብርሕት ሀገርንም አወረስሁህ። አንተ ከወንድሞች መካከል ለአንዱም ስንኳ ገድልህን ሳትነግር በምሥጢር ሰውረህ ነበር፤ እኔ ግን የገድልህን ክብር በዓለም ዳርቻዎች ኹሉ ገልጬ በዐሥራ አምስቱ አህጉራተ ገነት በአምስቱ አህጉራተ መንግሥተ ሰማያትም እሾምሃለሁ"።

#ጌታችንና_አምላካችን_መድኃኒታችን_ኢየሱ_ከርስቶስ ለአባታችን አባ በርተሎሜዎስ ይኽንን ኹሉ ቃል ኪዳን ሰጥቶት በታላቅ ምስጋና ወደ ሰማያት ዐረገ። ከወልደ #እግዚአብሔር ክርስቶስ በተሰጠው በዚኽ ቃል ኪዳን ምክንያትም ሰው ሊድን ነውና አባ በርቶሎሜዎስ ስለተሰጠው ቃል ኪዳን እጅግ ተደሰተ። "ለአንተና ለአባትህ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል ለዘለዓለሙ አሜን በእውነት ይኹን ይደረግ" ብሎ በፈጣሪው በጌታችንና በአምላካችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ወድቆ ሰገደ።

አባታችን አባ በርቶሎሜዎስ ግን በከንቱ ምስጋና በሰው ዘንድ ተወድሶ እንዳይኾንበት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻ ተጋድሎውን ለማንም ቢኾን ሊገልጥ አልወደደም ነበር። እርሱ በትዕግሥትና በትሕትና ፍጹም ልቡናውም በፈሪሃ እግዚአብሔር የተመላ ነውና። እኔስ የገድሉን ነገር ለገዳማውያኑ እመሰክራለሁ፤ ከዕለተ ልደቱ እስከ ዕረፍቱም ከሃይማኖትና ከስብሐተ #እግዚአብሔር በቀር ከአንደበቱ የዚኽ ዓለም ነገር አልወጣም።
በዘመኑ ወደ ቅድስት ደብረ ዘመዳ ከገባ መቶ ዘጠና ዓመት ከዘጠኝ ወራት ኖረ። አስቀድሞ የነበረበት ግን አልታወቀም። ከዚኽ በኋላ ግን ዕለተ ዕረፍቱ እንደቀበረ በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ዐውቆ ልጆቹ ገዳማውያን መነኰሳትን ሰብስቦ " #እግዚአብሔር ለመረጠው ይገባልና ለዚኽ ገዳም ሹመት አትሽቀዳደሙ። ኃይለ እግዚአብሔር የአደረበት የቅድስናውና የትምህርቱ ነገር በዓለም ኹሉ የሚነገርለት ከእኔ በኋላ ታላቅ ጻድቅ ሰው መጥቶ በዚኽች ገዳም ይሾማል። ድንቅ ድንቅ ተአምራትም ይደረጋሉ፤ እናንተ ግን እርሱ የአዘዛችሁን ስሙ" ብሎ የገዳሟን ሥርዐት እንደ ቀድሞው አሳሰባቸው።

ከዚኽ በኋላም አባታችን አባ በርቶሎሜዎስ ትንሽ ታምሞ በወርኀ ጥቅምት በአራተኛው ቀን በሦስት ሰዓት ዐረፈ። ያን ጊዜም ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከእመቤታችን ከቅድስት #ድንግል_ማርያም ጋራ እልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክትንና ነቢያትን ሐዋርያትንም ጻድቃንንና ሰማዕታትን ኹላቸው ቅዱሳንንም በእየክብራቸውና በእየመዓርጋቸው በእየወገናቸውም አስከትሎ መጣ።

ቅዱሳን መላእክትና ሊቃነ መላክትም የ #እግዚአብሔር ሰው ንዑድ ክቡር ገዳማዊ ደግ ጻድቅ አባታችን አባ በርቶሎሜዎስን የብርሃን አክሊል አቀዳጁት። ከፀሐይ ሰባት እጅ የሚያበራ ልብሰ ብርሃንን አለበሱት። በመዝሙር ዳዊት በአንድ ቃል "የጻድቅ ሰው ዕረፍቱ በ #እግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው። የጻድቅ ዝክርም በዘለዓለም ይኖራል። ጻድቅስ እንደ ሊባኖስ በዝቶ ያፈራል። እሊኽም በቤተ #እግዚአብሔር የተተከሉ ናቸው"። ይኽንና የመሳሰለውንም ኹሉ እየዘመሩ ወደ ሰማያት አሳረጉት። #ጌታችንና_አምላካችን_መድኃኒታችንን_ኢየሱስ_ክርስቶስም "ንጽሕት ነፍስ ወደ ዕረፍትሽ ግቢ እኔ #እግዚአብሔር ረዳትሽ ነኝና። ከብዙ ፃማ ሥጋም (ደካማ) አሳርፌ ፍጹም ደስታ ወደአለበት ወስጄ በዘለዓለም በዚያ ትኖሪያለሽ" ብሎ የአባታችን የአባ በርቶሎሜዎስን ክብርት ነፍሱን ተቀበሎ ደስ አሰኛት።

የአባታችን አባ በርቶሎሜዎስ ገዳማውያን ደቀ መዛሙርትም ጽኑ ለቅሶን አለቀሱለት። በግምጃ ልብስም ገንዘው በታላቅ ክብር ወደ ቤተ መቅደስ አግብተው በበዐቱ ቀበሩት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_4
#የአብርሃ_ወአጽብሐ_ታሪክ_በገዳሙ_የታተመ #ከገድላት_አንደበት)