ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ጳጒሜን_3

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጳጒሜን ሦስት በዚህች ዕለት የሰዎች ሁሉ ጸሎት የሚያርግባት #ርኅወተ_ሰማይ ትባላለች፣
የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ #ቅዱስ_ሩፋኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ ለእግዚአብሔር ልጅ ምሳሌው የሆነ #የካህኑ_መልከጼዴቅ መታሰቢያው ነው፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ መልካም ስም አጠራር ያለው #ቅዱስ_ዘርዐ_ያዕቆብ አረፈ፣ ሰንዱን ከሚባል አገር #ቅዱስ_ሰራጵዮን አረፈ፣ አቡነ ቀጸላ ጊዮርጊስ ዕረፍታቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ርኅወተ_ሰማይ

ጳጒሜን ሦስት በዚህች ዕለት የሰዎች ሁሉ ጸሎት የሚያርግባት፣ አራተኛው መጋቢ ኮከብ የሚያልፍባት፣ ለሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው ጸጋ በረከት የሚሰጥባት ዕለት ስለሆነች ርኅወተ ሰማይ (ሰማይ የሚከፈትባት) ቀን ትባላለች።

አሁን በሰማይ መዘጋት መከፈት ኑሮበት አይደለም። የሰው ልጆችን ልመና ቅዱሳን መላእክት ያለ ከልካይ የሚያሳርጉበት አንድም ቅዱስ ሩፋኤል የዓመቱን የጸሎት መዝገብ የሚከፍትበት ቀን ስለሆነ እንዲህ ተባለ እንጂ።

እመቤታችን #ድንግል_ማርያም ለአጼ ናዖድ እንደ ነገረቻቸው በዚህች ዕለት ሁሉም ቅዱሳን ስለሚታሰቡ፣ የ #እግዚአብሔር የምሕረት መዝገቡ ስለሚከፈት፣ ዕለቷን ክብርት ያሰኛታል። በቅዱስ ሩፋኤል አበጋዝነት (መሪነት) በዚህች ዕለት ለዓመት የሚበቃ ምሕረት ይገኛል።

ስለዚህም አባቶቻችን በዚህች ሌሊት ሦስት መቶ ስልሳ አምስት አቡነ ዘበሰማያትን ሲጸልዩ ያድራሉ። በሌላ ወገን ደግሞ የጌታ ዳግም ምጽዓቱ መታሰቢያ እንደ መሆኗ ትልቅ ትኩረትም ይሰጣታል። ቸሩ #ጌታችን ከተከፈተች ገነት ከተነጠፈች ዕረፍት ሁላችንንም ያድርሰን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሩፋኤል_ሊቀ_መላእክት

በዚህች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ የሩፋኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። እርሱም ከመላእክት አለቆች ሦስተኛ የሆነ ነው። ደግሞም ከእስክንድርያ ውጭ በደሴት የታነፀች ቤተ ክርስቲያኑ በከበረ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን በውስጧ ተአምር የተገለጸባት የከበረችበት ነው።

ይህም እንዲህ ነው ሀብታም ሴት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ መጥታ ሳለ ከእርሷ ጋርም ብዙ ሰው ነበረ። ከባሏም የወረሰችው ብዙ ገንዘብ አላት በሊቀ ጳጳሳቱ ቤት አንጻር ያለውን ኮረብታ አስቆፈረችው በጥቅምት ወር ዐሥራ ስምንት ቀን እንደጻፍን የወርቅ መዝገብ ተገለጠ።

በዚያም ወርቅ ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትን አነፀ ከእርሳቸውም አንዲቱ የመላእክት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ ሩፋኤል በስሙ የታነፀች ይህች ናት። ሥራዋንም በፈጸመ ጊዜ እንደዛሬው በዚች ቀን አከበራት።

ብዙ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጸች ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና። የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው። ወደ ክብር ባለቤት #እግዚአብሔርም በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ ያን ጊዜ ይህ የከበረ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በጦሩ ወግቶ እንዲህ አለው እግዚአብሔር አዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጽ ጸጥ ብለህ ቁም። አንበሪውም ጸጥ ብሎ ቆመ አልታወከም በውስጧም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆነ።

ይቺም ቤተ ክርስቲያን እስላሞች እስከተነሡበት ዘመን ኖረች ከዚህም በኋላ ሁለተኛ ያ አንበሪ ተናወጸ ደሴቲቱም በላይዋ ከሚኖሩ ብዙ ሕዝብ ጋራ ሠጠመች።

#ዳግመኛም የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ ጻድቅ ለሆነ ንጉሥ አኖሬዎስ ተናገረ። እንዲህም አለው ንጉሥ ሆይ እኛ ወዳንተ ልንመጣ በመርከብ እንደተሳፈርን ዕወቅ በጒዞ ላይ ሳለንም በቀዳሚት ሰንበት ቀን በደሴት ውስጥ ታናሽ ቤተ ክርስቲያን አየን ወደ ወደቡም ደርሰን በዕለተ እሑድ ሥጋውን ደሙን እንቀበል ዘንድ ወደርሷ ሔድን።

ለዚያች ቤተ ክርስቲያንም በጐኗ ታናሽ ገዳም አገኘን በውስጧም ወንድሞች መነኰሳት አሉ በክብር ባለቤት ጌታችንም ፈቃድ ወደ ርሳቸው ደረስን ። መነኰሳቱንም በቀደሙ አባቶች ዘመን የተጻፈ አሮጌ መጽሐፍ በእናንተ ዘንድ እንዳለ እጽናናበት ዘንድ እርሱን ሰጡኝ አልኳቸው። እንዲህም ብለው መለሱልኝ እኛ ትርጓሜያቸውን የማናውቀው መጻሕፍቶች በዕቃ ቤት አሉ። እኔም አያቸው ዘንድ ወደዚህ አምጡልኝ አልኳቸው። በአመጡአቸውም ጊዜ መረመርኳቸው #ጌታችንም በደቀ መዛሙርቱ ፊት ያደረጋቸውን ኃይሎችና ድንቆች ተአምራቶችን ስለ ሰማይና ምድርም ጥንተ ተፈጥሮ አገኘሁ።

ሁለተኛም ስመረምር ስለ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ሹመትና መዐርግ አባቶቻችን ንጹሐን ሐዋርያት የጻፉትን አገኘሁ ይኸውም #ጌታችን በደብረ ዘይት ከእሳቸው ጋራ እያለ የመለኮቱን ምሥጢር በገለጠላቸው ጊዜ። ሐዋርያትም እንዲህ ብለው እንደለመኑት #ጌታችንና ፈጣሪያችን ሆይ የከበረ የሩፋኤልን ክብሩን ታስረዳን ዘንድ እንለምንሃለን በየትኛው ዕለት በየትኛው ወር ሾምከው።

ከባልንጀሮቹ የመላእክት አለቆችም ትክክል ነውን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ዘንድ በዓለም ውስጥ ስለርሱ እንድናስተምር እርሱም በመከራቸው ጊዜ ይረዳቸው ዘንድ በአማላጅነቱም በአንተ ዘንድ ይቅርታን ያገኙ ዘንድ።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አዘዘና ከሦስተኛው ሰማይ ሦስቱ የመላእክት አለቆች ሚካኤል፣ ገብርኤልና ሩፋኤል መጡ በታላቅ ደስታም ለክብር ባለቤት ለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሰገዱ። #ጌታችንም ሩፋኤልን እንዲህ አለው የክብርህን ገናናነት የባልንጀሮችህንም ልዕልናቸውን እንዲያውቁ ለሐዋርያት ንገራቸው።

ያን ጊዜም ለ #ጌታችን ሰገደ ይነግራቸውም ዘንድ ጀመረ እንዲህም አላቸው ደገኛው የመላእክት አለቃ ሚካኤል ለሁሉም መላእክት አለቃቸው ነው ስሙም ይቅር ባይ ይባላል።

ሁለተኛም የመላእክት አለቃ ገብርኤል የስሙ ትርጓሜ አገልጋይም ጌታም የሆነ የዓለሙ ሁሉ እመቤት የሆነች አምላክን የወለደች ቅድስት #ድንግል_ማርያምን ያበሠራት ነው። የእኔም ስሜ ሩፋኤል ነው ይህም ደስ የሚያሰኝ ቸር መሐሪ ቅን የዋህ ማለት ነው እኔም ኃጢአተኞችን በ #እግዚአብሔር ዘንድ አልከሳቸውም ከኃጢአታቸው በንስሓ እስኪመለሱ ስለ ቅንነቴ በእነርሱ ላይ እታገሣለሁ እንጂ።

በሃያ ሦስቱ የመላእክት ነገድ ሠራዊት ላይ #እግዚአብሔር የሾመኝ እኔ ሩፋኤል ነኝ #እግዚአብሔር አብን ይቅር ባይ ልጁን አጽናኝና አዳኝ የሆነ #መንፈስ_ቅዱስን እናመሰግነው ዘንድ።

በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሺህ ዓመት ተድላ ደስታ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የክብር ጽዋን በሚሰጣቸው ጊዜ ለቅዱሳኖቹ በጎ ነገርን እንድሰጣቸው #እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ። ደግሞም በዚች ቀን ከዕፀ ሕይወት ዐጽቅ ወስጄ ለተመረጡ ክርስቲያኖች በእጄ እንድሰጣቸው #እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ።

የሰማያት መዛግብትም ከእጄ በታች ተጠብቀው የሚኖሩ እኔ ሩፋኤል ነኝ። እኔም #እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ እከፍታቸዋለሁ እዘጋቸዋለሁም።

በምድር ሰው ለባልንጀራው ስለ ስሜ በጎ ነገር ቢያደርግ እኔ በመከራው በችግሩ ረዳዋለሁ ወይም የሹመቴን ነገር የሚጽፍ ወይም ከቅዱሳን ጋራ ስሜን የሚያስብ ወይም በስሜ ለቊርባን የሚሆነውን የሚሰጥ ወይም በበዓሌ ቀን ምጽዋትን የሚሰጥ ይኸውም #እግዚአብሔር በሊቃነ መላእክት ክብር የሾመኝና ያከበረኝ ጳጕሚን ሦስት ቀን ነው። ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እስከማስገባው በብርሃን ሠረገላ እኔ እሸከመዋለሁ በምድር ላይ ከቶ እንደርሱ ያለ የማይገኝ መዐዛው እጅግ ጣፋጭ በሆነ ሽቱ ነፍሶቻቸው እርሱን በማሽተት ደስ እንዲላቸው አደርጋለሁ።