ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ነሐሴ_1

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተባረከው #የነሐሴ_ወር_የቀኑ_ሰዓት_ዐሥራ_ሦስት ነው ከዚህም በኋላ ይጎድላል።
ነሐሴ አንድ በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናቷ #የቅድስት_ሐና መታሰቢያዋ ነው፣ የዮስጦስ ልጅ #ቅዱስ_አቦሊ በሰማዕትነት አረፈ፣ የከበሩ ሰዎች #ቅዱሳን_የዮሴፍና_የኒቆዲሞስ መታሰቢያቸው ነው፣ በተጨማሪም በዚህች ቀን የፋኑኤል ልጅ የነብይት #ሐና፣ የንግሥት ሶፍያ ልጆች የቅዱሳት ደናግል መታሰቢያቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሐና (የእመ ብርሃን እናት)

ነሐሴ አንድ በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናቷ የሐና መታሰቢያዋ ነው። ይህችም ቅድስት ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት (ጣ ጠብቆ ይነበብ) ልጁ ናት። ለማጣትም ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱም ስሟ ማርያም ናት ሁለተኛዋም ስሟ ሶፍያ ሦስተኛዪቱም ስሟ ሐና ናት ታላቂቱ ማርያምም ለባል ተድራ አዋላጅ የሆነች ሰሎሜን ወለደቻት እርሷም #መድኃኒታችንን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ በስደቷም ወራት ከአረጋዊ ዮሴፍ ጋር እመቤታችንን #ድንግል_ማርያምን ያገለገለቻት ናት።

ሶፍያም ለባል ተድራ ለመጥመቁ ዮሐንስ እናቱ የሆነች ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደቻት። ይችንም ቅድስት ሐናን ከይሁዳ ነገድ ለሆነ ጻድቅ ስሙ ኢያቄም ለሚባል አጋቧት። (ሰሎሜና ኤልሳቤጥ ለቅድስት ሐና የእኅትማማች ልጆች ናቸው።)

ቅድስት ሐና ኢያቄምን አግብታ ስትኖር የቴክታና እና የጴጥሪቃ ምክነት በዘር ወርዶ መክና በመኖሯ የዐይኗ ማረፊያ የልቧ ተስፋ የሚሆን ልጅ እንዲስጣት ፈጣሪዋን ስትማጸን ኖራለች።

የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ አምላክ ልመናዋን ሰምቶ ሐምሌ ፴ ራእይ አየች። ራእዩንም ከባሏ ከኢያቄም ጋር ተወያየተው ምንጣፍ ለይተው ሱባኤ ገቡ።

ከአንድ ሱባኤ በኋላ ነሐሴ ፯ ቀን #ጌታ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እንደሚወልዱ አበሠራቸው። ከዚያም እመቤታችን ጸንሳ ልዩ ልዩ ተአምራትን አድርጋለች። ሳምናስን ከሞት አስነስታለች። በርሴባን ዐይኗን አብርታለች። ከዚያም በአይሁድ ተንኮልና አሳዳጅነት ወደ ሊባኖስ ተራራ ተሰዳ #ድንግል_ማርያምን ወልዳለች። በመውለዷም ሕዳሴ አካል አግኝታ ከኖረች በኋላ ዐርፋለች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሐናና ኢያቄም ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቦሊ

በዚህችም ቀን የዮስጦስ ልጅ ቅዱስ አቦሊ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ አቦሊ ከመንግሥት ልጆች ውስጥ ነበር ዐላውያንን ወግቶ በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስን ክብር ይግባውና #ክርስቶስን ክዶ አገኘው።

ያም አቦሊና አባቱ ዮስጦስ ሌሎችም የመንግሥት ልጆች ሁሉ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስን ሊያጠፉትና መንግሥትን ከእርሱ ሊወስዱ ችሎታ ሲኖራቸው የማታልፍ ሰማያዊት መንግሥትን አሰቡ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ አቦሊ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም አብዝቶ አባበለው። እንዲሁም አባቱ ዮስጦስንና የከበረች እናቱ ታውክልያን አባበላቸው እነርሱ ግን አልሰሙትም ልባቸው በ #መድኅን_ክርስቶስ ፍቅር ተነድፏልና። ንጉሡም እነርሱን በዚያ ማሠቃየትን ፈራ ስለዚህም ከመልእክት ደብዳቤ ጋር ወደግብጽ ስሙ ኄርሜኔዎስ ወደሚባል የእስክንድርያ ገዥ ላካቸው በመልእክቱም እንዲህ አለው ዮስጦስና ሚስቱ ታውክልያ ልጃቸው አቦሊም ወደአንተ በሚደርሱ ጊዜ አባብላቸው አለዚያም እየአንዳንዳቸውን ለያያቸው።

በዚያችም ሌሊት ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ለዮስጦስና ለሚስቱ ታውክልያ ለልጃቸው አቦሊም ተገልጦላቸው አጽናናቸው ከእነርሱም የሚሆነውን ነገራቸው የጸና ቃል ኪዳንም ሰጣቸው።

ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስም በደረሱ ጊዜ ስለእነርሱ እጅግ አደነቀ እነርሱ መንግሥታቸውን ትተዋልና ክፋ ነገርንም ሊናገራቸው አልደፈረም ከምክራቸው ይመለሱ ዘንድ በለሰለሰ ቃል ሸነገላቸው እንጂ ነገር ግን አልሰሙትም።

ከዚህም በኋላ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ ለእየብቻቸው ለያያቸው ቅዱስ ዮስጦስን ወደ እንዴናው ከተማ ሚስቱን ታውክሊያን ፃ ወደ ሚባል አገር ልጃቸው አቦሊንም ብስጣ ወደ ሚባል አገር ሰደዳቸው ለእያንዳንዳቸውም የሚአገለግላቸው አንዳንድ አገልጋይ ሰጣቸው። ቅዱስ አቦሊም ወደ ሀገር ብስጣ በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በመኰንኑ ፊት ታመነ። መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን በእሳት ቃጠሎና በመንኰራኵር አሰቃየው ሕዋሳቱንም ቆራርጦ ለአንበሶች ጣለው ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ከሥቃዩ ሁሉ አድኖ ያለ ጉዳት በጤና አነሣው።

ብዙዎች ሰዎችም ስቃዩንና ዳግመኛ መዳኑን በአዩ ጊዜ እጅግ አደነቁ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በአምላካችን_በመድኃኒታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስም አምነው ሰማዕታት ሆኑ።

መኰንኑ ግን እጅግ ተቆጥቶ የቅዱስ አቦሊን ቆዳውን እንዲገፍፉትና ጨውና መጻጻን በማቅ አምጥጠው ቍስሉን እንዲያሹ አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉበት።

ከዚህም በኋላ ቆዳውን አሸክመው በከተማ ውስጥ ሁሉ አዞሩት ወደ #ጌታችንም እንዲህ ብሎ ጸለየ የሕያው #እግዚአብሔር_ልጅ_ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ ርዳኝ ከዚህ ሥቃይም አድነኝ። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደርሱ መጣ ሁለመናውንም ዳስሶ አዳነው።

መኰንኑም በእርሱ ላይ የሚያደርገውን እስኪያስብ ከእሥር ቤት እንዲጨምሩት አዘዘ። ቅዱስ አቦሊም ቁሞ ጸለየ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #ጌታችን ተገለጠለትና የመረጥኩህ አቦሊ ሰላም ለአንተ ይሁን እኔም ከአንተ ጋር እኖራለሁ አለው #ጌታችንንም በአየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው ክብር ይግባውና ለ #ጌታችንም ሰገደለት።

ስሙ አብስኪሮን የሚባል አንድ ባለ ጸጋ ነበር የቤቱንም ግድግዳ አፍርሰው አዲስ ይሠሩለት ዘንድ ሠራተኞችን አመጣ ሥራቸውንም እስኪጨርሱ ከዚያ ይቆሙ ዘንድ ሁለቱን ልጆቹን አዘዛቸው።

ከግርግዳውም ላይ በወጡ ጊዜ ግርግዳው ተደርምሶ ዐሥራ ስድስት ሰዎችና ሁለቱ ልጆቹ ሞቱ። ባለጸጋውም የሆነውን በአየ ጊዜ ልብሱን ቀደደ ጩኾም አለቀሰ ወደ ቅዱስ አቦሊም ሒዶ ከእግሩ በታች ሰገደለት እንዲህም አለው ራራልኝ ሁለቱ ልጆቼ ሙተዋልና ከእነርሱም ጋራ ዐሥራ ስድስት ሰዎች ሞቱ። ከሞትም ብታሥነሣቸው እኔ በአምላክህ አምናለሁ።

ያን ጊዜም ቅዱስ አቦሊ ተነሣ እንዲህ ብሎ ጸለየ ስለ ቅዱስ ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ የመረጥከኝ #ጌታዬ_አምላኬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ በእኒህ በሞቱ ሰዎች ላይ ኃይልህን ግለጥ። እኒህ ሰዎች ሁሉ እንዲአምኑ ያለ አንተም ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ከሞት አንሣቸው። ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

ከዚህም በኋላ የተገፈፈ ቆዳውን ወስዶ በሞቱት ሰዎች ላይም ዘረጋውና በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሞት ተነሡ አለ። ወዲያውም ሁሉም ድነው ተነሡ በዚያ ያሉ ሕዝብም ይህን ድንቅ ሥራ በአዩ ጊዜ የክርስቲያን አምላክ የቅዱስ አቦሊም አምላክ #ኢየሱስ_ክርስቶስ አንድ ነው እኛም እናምንበታለን ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለምና እያሉ ጮኹ።

ባለ ጸጋው አብስኪሮንም መጥቶ ለቅዱስ አቦሊ እንዲህ እያለ ሰገደ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ክብር ይግባውና እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ዛሬ አወቅሁ እኔም አምንበታለሁ። ከቤተሰቦቹም ሁሉ ጋር አመኑ መኰንኑም አፈረ።
ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ለቅዱስ አቦሊ ተገለጠለት እንዲህም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው። በመከራ ውስጥ ያለ ሰው በስምህ ርዳታ ቢለምን እኔ እሰማዋለሁ ልመናውን ፍላጎቱንም እፈጽምለታለሁ። በስምህ ቤተ ክርስቲያን ለሠራም እኔ በሰማያት ብርሃናዊ ማደሪያ ቤት እሠራለታለሁ የገድልህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውን ወይም የሚሰማውን እኔ በኪሩቤል ክንፎች ላይ ስሙን እጽፉለሁ በአብርሃም በይስሐቅና በያዕቆብ እቅፍም አሳርፈዋለሁ ተድላ ደስታ ካለባት ከገነት ፍሬዎችም እመግበዋለሁ።

ብዙ ኃጢአትን ሠርቶ የበደለውንም በስምህ ወደኔ እየለመነ ንስሐ ቢገባ በደሉን ሁሉ ይቅር እለዋለሁ። ከጻድቃንም ጋርም እቈጥረዋለሁ ሰላሜም ካንተ ጋራ ይሁን ይህንንም ብሎ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ።

መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ የከበረች ራሱን ቆረጡት የሕይወት አክሊልንም ተቀበለ። ሥጋውም ከምስር ከተማ ውጭ ሕንቅ በሚባል ገዳም ይኖራል ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ መስተጋድል ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አበው_ሐዋርያት_ዮሴፍና_ኒቆዲሞስ

በዚህችም ቀን ለአምላካዊት ምሥጢር አገልጋዮች ሊሆኑ የተገባቸው የከበሩ ሰዎች የዮሴፍና የኒቆዲሞስ መታሰቢያቸውን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶች አዘዙ።

በፈቃዱ መከራ ተቀብሎ ስለ ደኅንነታችን በሞተ ጊዜ የደኅንነታችንንም ምሥጢር በፈጸመ ጊዜ የሕያው #እግዚአብሔርን ልጅ የ #መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን ሥጋ እነርሱ ከ #መስቀል ላይ አውርደዋልና። የአይሁድም መገርመም ከጲላጦስ ዘንድ የ #መድኃኒታችንን ሥጋ እስከ ለመኑ ድረስ አላስፈራቸውም።

ጲላጦስም በፈቀደላቸው ጊዜ የእጆቹንና የእግሮቹን ችንካሮች ነቅለው ከ #መስቀል አውርደው በትክሻቸው ተሸከሙት ሲገንዙትም እንዲህ የሚል ቃል ከበድኑ ሰሙ። #ቅዱስ_እግዚአብሔር #ቅዱስ_ኃያል #ቅዱስ_ሕያው_የማይሞት#ቅድስት_ድንግል_ማርያም የተወለደ አቤቱ ይቅር በለን።

#ቅዱስ_እግዚአብሔር #ቅዱስ_ኃያል #ቅዱስ_ሕያው_የማይሞት በዮርዳኖስ የተጠመቀ በእንጨት #መስቀልም የተሰቀለ አቤቱ ይቅር በለን። #ቅዱስ_እግዚአብሔር #ቅዱስ_ኃያል #ቅዱስ_ሕያው_የማይሞት በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሣ በክብር ወደ ሰማያት ያረገ በአባቱም ቀኝ የተቀመጠ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ የሚመጣ አቤቱ ይቅር በለን።

#አብ ምስጋና ይገባል ለ #ወልድ ምስጋና ይገባል ለ #መንፈስ_ቅዱስ ምስጋና ይገባል ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን አሜን ይሁን ይሁን። ልዩ ሦስት ሕያው #እግዚአብሔር ይቅር በለን።

ይህንንም በሰሙ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖታቸው ጸናች። ዮሴፍም በፍታ ኒቆዲሞስም ሽቶዎችን አምጥተው #ጌታችንን ገነዙት በአዲስ መቃብር ውስጥም ቀበሩት።

ይህ ዮሴፍም ለሰማዕታት መጀመሪያ ለእስጢፋኖስ ዘመድ ለሆነው ለቀለዮጳ ወንድሙ ለኒቆዲሞስ ዘመዱ ነው ኒቆዲሞስም የአይሁድ አለቃ ፈሪሳዊ ነበር እርሱም ወደ #ጌታ_ኢየሱስ አስቀድሞ በሌሊት የሔደና ከ #እግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣ ያመነ ነበር። #ጌታችንም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው ወደ #እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንደማይችል የነገረው ነው።

ይህ ኒቆዲሞስም የ #ጌታችንን ቃል በሚአቃልሉ ጊዜ አይሁድን ይገሥጻቸው ነበር። ከተነሣ በኋላም በኢማሁስ መንገድ ሲሔድ #ጌታችን_ኢየሱስ የተገናኛቸው እሊህ ኒቆዲሞስና ቀለዮጳ ናቸው። እነርሱም ሳያውቁት በእርሱ ላይ የሆነውን ሁሉ ነገሩት። እርሱም ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ነቢያት ትንቢት እንደ ተናገሩ አስተማራቸው።

ከዘህም በኋላ እርሱ መሆኑን ባወቁት ጊዜ ተሠወራቸው እነርሱም ተመልሰው ለደቀ መዛሙርቱ ነገሩ። ክብር ይግባውና የ #ጌታችንን ሥጋ ስለ ቀበረ ሊገድሉት ፈልገው አይሁድ ዮሴፍን በወህኒ ቤት አሠሩት። የወህኒ ቤቱም በር በሊቃነ ካህናቱና በጲላጦስ ማኅተም ተቆልፎ ሳለ #ጌታችን በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጦ ዮሴፍ ወደ አለበት ገባ ከእርሱ ጋርም እልፍ አእላፋት መላእክት ነበሩ። ሱራፌልም በዙሪያው ቁመው በፊቱ ያጥናሉ በቀኝ በኩል ተሰቅሎ የነበረ ወንበዴውም ብሩህ ልብስ ለብሶ በቀኝ ቁሞአል ባለሟልነትን በልዑል ፊት አግኝቶአልና ስለ ኃጢአተኞች ይማልድ ነበር።

የወህኒ ቤት ጠባቂዎችም በአዩ ጊዜ ደነገጡ ፈርተውም መንቀጥቀጥ ያዛቸው #ጌታችንም ዮሴፍን ጠርቶ እንዲህ አለው ከአይሁድ ግርማ የተነሣ አትፍራ ከማሠሪያህ ልፈታሕ እኔ መጣሁ አንተ መከራዬን የተሳተፍከኝ የናዝሬቱ #ኢየሱስ እኔ ነኝ እኔ #ጌታህና የዓለሙ ሁሉ #ጌታ እንደሆንሁ ፈጽመህ ታውቅ ዘንድ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን የተወጋ ጐኔንም እይ።

ከዚያም ዮሴፍን ነጥቆ ወደ አገሩ አርማትያስ ወሰደው። የወህኒ ቤቱ ጠባቂዎችም ሔደው #ጌታችን ያደረገውን ሁሉ ዮሴፍንም ይዞ ከእርሱ ጋር እንደወሰደው ለካህናት አለቆች ነገሩ። የካህናት አለቆችም በሔዱ ጊዜ የወህኒ ቤቱ በር ተቆልፎ አገኙ እሽጉም አልተለወጠም ነበር። እሊህ ቅዱሳንም ከሐዋርያት ጋር ወንጌልን እየሰበኩ ኖሩ ብዙ መከራም አገኛቸው። ከዚህም በኋላ በሰላም አረፉ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሐና_ነቢዪት

በዚህም ዕለት ከአሴር ወገን የሆነች የፋኑኤል ልጅ ነቢዪት ሐና አረፈች፡፡ የእርሷም ዘመኗ አልፎ ነበር በድንግልና ከኖረች በኋላ ከባሏ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች። ሰማንያ አራት ዓመት ፈት ሁና ኖረች በጾምና በጸሎትም እያገለገለች ቀንም ሌትም ከምኲራብ አትወጣም ነበር።

ጌታችን ኢየሱስን ከተወለደ በኋላ በአርባ ቀን ወደ ቤተ መቅደስ በአስገቡት ጊዜ በዚያን ሰዓት ተነሥታ አመነች እግዚአብሔርንም አመሰገነችው። የኢየሩሳሌምን ድኅነት ተስፋ ለሚያደርጉ ሁሉ ስለርሱ ነገረች። ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈች።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_1)
#ነሐሴ_29

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን ከእመቤታችን ከቅድስት #ድንግል_ማርያም መድኃኒታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ በሥጋ ለመወለዱ መታሰቢያ በዓል ሆነ ለእርሱም ምስጋና ክብር ይሁን ለዘላለሙ አሜን፣ #የአባ_ዮሐንስ_ሐጺር ወደ አስቄጥስ ገዳም የሥጋው ፍልሰት ሆነ፣ #ቅዱስ_አትናቴዎስ #ገርሲሞስና_ቴዎዶጦስ ከሚባሉ ሁለት አገልጋዮቹ ጋር በሰማዕትነት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ዮሐንስ_ሐጺር

ነሐሴ ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን የአባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ አስቄጥስ ገዳም የሥጋው ፍልሰት ሆነ። ይህም የአባ እንጦንዮስ በሆነ በቊልዝም ገዳም ከአረፈ በኋላ ነው። ለእስክንድርያ አባ ዮሐንስ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ስምንተኛ የሆነ ነው። እርሱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ የከበሩ መነኰሳትም እንዲህ አሉት የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ በዚህ በቤተ ክርስቲያኑ ቢሆን እኛም ሥጋው በአለበት ለፈጣሪያችን #እግዚአብሔር እንሰግድ ዘንድ እንሻ ነበር።

ያን ጊዜ የ #እግዚአብሔር ቸርነት አነሣሣችውና ስሙ ቆዝሞስ ለሚባል ለአንድ አበ ምኔት መልእክትን ጻፈ ከእርሱም ጋር የቊልዝም አገር የሆነ አረጋዊ አለ በደረሱም ጊዜ በዚያን ሰዓት ሥጋውን መውሰድ አልተቻላቸውም። የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ የኬልቄዶንን ጉባኤ በተቀበሉ መለካውያን ዘንድ ይጠበቅ ስለነበረ ነገር ግን ቦታውን አወቁ ተረዱ ወደ ቦታቸውም ተመልሰው ሃይማኖታቸው የቀና ምእመናን ሰዎችን አገኙ እነርሱም በዚያች አገር የሚኖሩ ናቸው ስለርሱ የመጡበትን ነገሩአቸው።

ከጥቂት ቀኖች በኋላም ከታላላቅ ዐረቦች ወገን ለቊልዝም አገር መኰንን ተሾመ እርሱም ለኤጲስቆጶስ አባ ሚካኤል ወዳጁ ነው ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስም ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ ወደ ኤጲስቆጶሱ መልእክትን ጻፈ። በመልእክቱም የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ ከከሐድያን መለካውያን እጅ እስከ አፈለሱት ድረስ መልእክተኞች አእሩግ መነኰሳትን ምክንያት ፈልጎ እንዲረዳቸው በማሳሰብ አዘዘው።

ኤጲስቆጶሱም በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለው ሒዶም ወዳጁ ለሆነ ለመኰንኑ ጸሐፊ ነገረው። ጸሐፊውም ለመኰንኑ ነገረው። እነሆ መኰንኑም ከመነኰሳቱ ጋራ ሔደ ጸሐፊውም መነኰሳቱ ወደዚያ ቦታ እንዲገቡ ምክንያት እንዴት እናገኛለን አለ። መኰንኑም በልብሶቻቸው ላይ የዓረቦችን ልብሶች ያልብሱአቸውና ከእኔ ጋራ ወደዚያ ቦታ ይምጡ አለ እንዲሁም እንዳላቸው አደረጉ።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ሔደ ከእርሱም ጋራ ብዙ ፈረሰኞች ሰዎች ብዙ ሕዝብም የአስቄጥስ ገዳም የከበሩ አረጋውያን አሉ ወደቊልዝም ገዳምም ደረሱ። መኰንኑም በዚያ የሚኖራውን የመለካውያን ኤጲስቆጶስ እንዲህ ብሎ አዘዘው ያንተን ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስወጣቸው በዚች ሌሊት እኔ በውስጧ አድራለሁና ያ መለካዊም መኰንኑ እንዳዘዘው አደረገ።

መነኰሳቱም እንስሶቻቸውን ከከተማ ውጭ አዘጋጅተው በሌሊት ወደዚያ ገብተው የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ ይዘው ወደ ምስር ደረሱ ከዚያም ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረሱ የአባ መቃርስ ገዳም መነኰሳትም መስቀሎችን፣ ወንጌሎችን፣ ማዕጠንቶችንና መብራቶችን በመያዝ እየዘመሩና እያመሰገኑ ተቀበሏቸው ወደ አባት መቃርስ ሥጋም አቀረቡትና ከእርሱ ተባረኩ በላዩም ብዙ ሽቱዎችን ነሰነሱ የቊርባን ቅዳሴንም ቀደሱ የከበረ ወንጌልም በሚነበብ ጊዜ ታላቅ ድንቅ ተአምር ተገለጠ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለመናዋ በሰማያዊ ብርሃን በራች። ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ በጎ መዓዛ ሸተተ ታላቅ ደስታም ሆነ በዚያም ቦታ ሰባት ቀን ኖረ።

ከዚህም በኋላ ወደ ራሱ ቤተ ክርስቲያን ተሸክመው ወሰዱት ዕብራውያንም በ #እግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እያሉ #መድኃኒታችንን እንደተቀበሉት ልጆቹ መነኰሳት ተቀበሉትና ወደ ቦታው አኖሩት ከእርሱም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።

ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስ በወጣ ጊዜ ወደ አባ ዮሐንስ ሐጺር ቤተ ክርስቲያን ገባ። ከእርሱም ጋር ብዙዎች ኤጲስቆጶሳትና የእስክንድርያ አገር ታላላቆች ከግብጽ አገር ሁሉ አሉ። የአባ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ የተጠቀለለበትን ሰሌን ገልጦ ከእርሱ ተባረከ መሪር ልቅሶንም አለቀሰ ያን ጊዜ ሥጋው ሲገለጥ መብረቅና ነጐድጓድ ሆነ። በቤተ ክርስቲያኑም ውስጥ ያሉት ሁሉም ደንግጠው ወደቁ ሊቀ ጳጳሳቱም ሰሌኑን መልሶ በፍጥነት ሥጋውን ጠቀለለ በሽብሸባ እየዘመሩና እያመሰገኑ እንደቀድሞው ሸፈነው።

ከዚህም በኋላ ዳግመኛ እንዲህ እያሉ ሊያመሰግኑ ጀመሩ ፈጣን ደመና ሁነህ የ #መንፈስ_ቅዱስን ዝናም የተሸከምክ ሠለስቱ ደቂቅ ወዳሉበት ወደ ባቢሎን የሔድክ በላይህ በአደረ በ #መንፈስ_ቅዱስ ኃይል ወደ እስከንድርያ አገር የተመለስክ ሁለተኛም ወደ ቊልዝም የሔድክ የጣዖታትን ቤቶች አፍርሰህ ሃይማኖትን የሰበክ በሽተኞችን የፈወስክ አጋንንትን ያስወጣህ ወደርስትህም የተመለስክ አንተ የበረከት ማደሪያ ነህና። የአባ ዮሐንስ ሐጺር የሥጋው ፍልሰት ከንጹሐን ሰማዕታት ዘመን በአምስት መቶ ሃያ ዓመት ሆነ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አትናቴዎስ_ሰማዕት

በዚህችም ቀን ኤጲስቆጶስ አትናቴዎስ በሰማዕትነት ሞተ ከእርሱም ጋር ስማቸው ገርሲሞስና ቴዎዶጦስ የሚባል ሁለት አገልጋዮች በሰማዕትነት አረፉ።

ይህንንም ቅዱስ አትናቴዎስን የእንጦኒቆስን የጭፍራ አለቃውን ልጅ እርሱ እንዳጠመቃት በንጉሥ ዘንድ ወነጀሉትና ንጉሥ አርስያኖስ ያዘው እርሱም ክርስቲያን እንደሆነ ታመነ ብዙ ሥቃይንም አሠቃየው።

በሃይማኖቱም ጸና እንጂ ሃይማኖቱን ባልካደ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ እንዲሁም እሊህን ሁለቱን አገልጋዮች ገርሲሞስንና ቴዎዶጦስን በግርፋትና በስቅላት ከቀጣቸው በኋላ ራሶቻቸውን በሰይፍ አስቆረጠ ሦስቱም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

አማንያን ሰዎችም መጡ ለወታደሮችም ገንዘብ ሰጥተው የቅዱሳኑን ሥጋቸውን ወሰዱ በአማሩ ልብሶችም ገንዘው በሣጥን ውስጥ አኖሩአቸው ከሥጋቸውም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_29)
#ጳጒሜን_2

#ቅዱስ_ቲቶ_ሐዋርያ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጳጒሜን ሁለት በዚህች ቀን ሐዋርያ ጳውሎስ መልእክት የጻፈለት የከበረ ሐዋርያ ቲቶ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ትውልዱ ቀርጤስ ከሚባል አገር ነው። እርሱም ለዮናናውያን ወገን ለሆነ ለአገረ ገዥው እኅት ልጅዋ ነው።

ከታናሽነቱም የዮናናውያንን ትምህርትና ፍልስፍና ተምሮ እጅግ አዋቂ ሆነ በጠባዩም ቅን ሥራው ያማረ ለድኆችና ለችግረኞች መራራት የሚወድ ነው። ከሌሊቶችም በአንዲቱ ቲቶ ሆይ ስለ ነፍስህ ድህነት ተጋደል ይህ ዓለም አይጠቅምህምና የሚለውን በሕልሙ አየ። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ደነገጠ ምን እንደሚሠራም አላወቀም።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት የ #መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ትምህርት በተሰማ ጊዜ ብዙዎች ሰዎችም ተአምራቱን እርስበርሳቸው ተነጋገሩ የአክራጥስ መኰንንም ሰምቶ አደነቀ ዕውነት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ወይም የሥራይ እንደሆነ ሊያውቅ ሽቶ የሚልከው ብልህ ሰው ፈለገ የእኅቱንም ልጅ ቲቶንን መረጠው ከእርሱ የሚሻል የለምና። ሲልከውም ታላቅና ጥልቅ የሆነ ምርመራ እንዲመረምር አዘዘው።

ቲቶም ከይሁዳ ምድር በደረሰ ጊዜ የ #መድኃኒታችንን ድንቆች የሆኑ ተአምራቶቹን አየ ሕይወትነት ያላቸው ትምህርቶቹንም ሰማ። ከዮናናውያንም በትምህርታቸውና በሥራቸው መካከል ታላቅ የሆነ መራራቅን አግኝቶ የዮናናውያን ሃይማኖታቸው የቀናች እንዳልሆነች ለይቶ ዐወቀ።

ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት በ #ጌታችን_ኢየሱስ አመነ፤ ደቀ መዝሙሩም ሁኖ ተከተለው። ወደ እናቱ ወንድም ወደ አገረ ገዥውም መልእክትን ላከ የክብር ባለቤት #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ የሚያስተምረውና የሚሠራው ዕውነት እንደሆነ ነገረው።

#ጌታችንም ከሰባ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ውስጥ የተቆጠረ አደረገው ከዕርገቱም በኋላ ከሐዋርያት ጋር የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብሎ ከእሳቸው ጋር በሀገሮች ሁሉ ዙሮ አስተማረ። #ጌታችንም ጳውሎስን ጠርቶ ሐዋርያው በአደረገው ጊዜ ያን ጊዜ ሐዋርያ ጳውሎስን ተከተለው በብዙ አገሮችም ወንጌልን ሰበከ።

የከበረ ጳውሎስም በሮሜ ከተማ ምስክር ሆኖ ከሞተ በኋላ ቅዱስ ቲቶ ወደ ሀገረ አክራጥስ ተመለሰ ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው በዙሪያቸው ላሉ አገሮችም እንዲሁ አደረገ።

ከዚህም በኋላ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ ወደደው #እግዚአብሔር ሔደ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ቲቶ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጳጒሜን_2)
የነዳያን ፍቅር በልቡ ውስጥ አለ፤ ሁል ጊዜ ስለ ምግባቸውና ስለ ልብሳቸው ያስብ ነበር፤ ለሚያስፈልጋቸው ነገርም ገንዘብ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ለድኆች ልብሱን ያካፍላል፤ ለእነርሱም ሰጥቶ እርሱ ራቁቱን ይቆማል፤ ልጆቹም ይመጣሉ፤ ‹‹ልብስህ ወዴት ነው?›› ይሉት ነበር፤ እርሱም ‹‹ሌቦች በማያገኙበት ቦታ አለ›› ይላቸው ነበር፡፡ ልጆቹ ግን ሥራውን አያውቁም ነበር፤ ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንበት ሁሉን ይሠውር ነበር፤ አይገልጥላቸውም ነበር፤ ድኃ ባየ ጊዜ አጽፉን ይሰጥ ነበር፤ አጽፉን ይቅርና ምንም ልብስ አያስቀርም ነበር፡፡

አንድ ቀን አንድ ድኃ መጥቶ ስለ #እግዚአብሔር ስም ምግብና ልብስ ለመነው፡፡ አባታችን ያን ድኃ ባየው ጊዜ አጽፉን ሰጠው፤ ዳግመኛ አንድ ድኃ መጣ፤ በቤቱም የሚሰጠውን አጣ፤ መጠምጠሚያውን አውርዶ እርሷንም ለድኃው ሰጠውና በቤቱ ተቀመጠ፡፡ አንድ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ መጥቶ ራቁቱን አገኘውና ተቆጣበት፤ ‹‹ክቡር አባቴ ሆይ! ለምን እንዲህ ትሆናለህ? አለው፡፡ ‹‹ለምትበላውና ለምትለብሰው ሳታስቀር ያለ አቅምህ ለምን ምጽዋት ትሰጣለህ? ልብስህንና መጎናጸፊያህን ሰጥተህ አንተ ራቁትህን ትሆናለህ፡፡›› አባታችንም ‹‹ልጄ ሆይ! ፈጽሞ ስለሚያረጅና ስለሚጠፋ የዚህ ዓለም ልብስ ፈንታ የብርሃን መጎናጸፊያ የሚያለብሰኝ አምላኬ አለልኝ›› አለ፤ ልጆቹም ሌላም ልብስ አምጥተው አለበሱ፡፡ ‹‹ይህንም እንደ ቀደመው አታድርግ›› አሉት፤ እርሱ ግን ስለ ድኆችና ስለ ችግረኞች ፍቅር ብዙ ጊዜ ምጽዋት ያደርግ ነበር፤ ቅብዓት በሰውነት፣ ውሃ በአንጀት እንዲገባ የነዳያን ፍቅር ወደ ልቡ ገባ፡፡

የነዳያንን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ከልቡ ደስታ የተነሣ ለመነሣት ይፈልጋል፤ ከማእድ ላይ ቢሆንም እንኳን ድምፃቸውን ከሰማ እጁን ወደ ማእድ አያወርድም ነበር፤ ይሰጣል እንጂ ምንም ነገር አያተርፍም ነበር፡፡ ነዳያን ግን ዘወትር ጩኸትና ልመናን አያቋርጡም ነበር፤ አባታችን ስለ ምግባቸውና ስለ ልብሳቸው እንደሚያስብ አውቀው ከቤቱ አይርቁም ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ወደ አንዲት ታላቅ ሀገር ሔዶ ከዚያ ደረሰ፤ በሰንበት ምሽት ለእሑድ አጥቢያ ከዚያ አደረ፤ ሥርዓተ ቁርባን ከተፈጸመ በኋላ ደቀ መዝሙሩን ‹‹ልጄ የምንበላው ነገር አለህ ወይስ የለህም?›› አለው፤ ያ ደቀ መዝሙርም ‹‹አባቴ አዎን አለኝ›› አለው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ያያቸውን ታላላቅ መነኮሳት ሰበሰበ፤ ቁጥራቸውም ዐራት መምህራን ነበሩ፡፡ የተዘጋጀ ምግብና ጠላ ያን ጊዜ እነርሱም ከቤታቸው እንጀራ አመጡ፤ ሁለት ያመጣ አለ፤ ሦስትም ያመጣ አለ፤ ሁላቸውም እንደ አቅማቸው አመጡ፤ አባታችንም ጸሎት ያደርግ ዘንድ ተነሣ፤ ባረከላቸውም፡፡

ደቀ መዝሙሩንም ‹‹ጠላውን አምጣው›› አለው፤ ሁለት መነኮሳትም እንሥራውን አመጡት፤ ከመካከላቸው አንዱን ጠጣ አለው፤ ቀምሶም ለአባታችን ሰጠው፤ ጣዕሙ ደስ ባሰኘው ጊዜ አባታችን ከሩቅ ሀገር የመጡ የተራቡ ሰዎች ከቤቱ ደጃፍ እንዳሉ አወቀ፡፡ መነኮሳቱንም ‹‹አባቶቼ፣ ወንድሞቼና ልጆቼ ፈቃዳችሁ ከሆነስ ለ #ክርስቶስ እንሰጠው ዘንድ ለነዳያንና ለችግረኞች እንስጣቸው›› አላቸው፡፡

በቤተ ክርስቲያን የተሰበሰቡ ወንድሞች መነኮሳት፣ ክቡራን ካህናት፣ ዲያቆናትና ሕዝቡ የ #መንፈስ_ቅዱስ ማደሪያ የሆነ፣ በወንጌል ወተት ያደገ፣ የ #እግዚአብሔር ሰው የሆነ የአባታችንን ትሕትና፣ ትሩፋትና ቅድስና ባዩ ጊዜ አዘኑበት፡፡ ምንም ቃል አልመለሱለትም፤ በቦታቸው ወይም በቤታቸው አልነበሩምና፤ በልባቸው ‹‹እኛስ ከሩቅ ሀገር የመጣን አይደለምን?›› አሉ፡፡ እነርሱ ግን ከዚያው ይኖሩ ነበር፤ አባታችን ግን ነዳያንን ሰብስቦ ያንን ምግብ ሰጣቸው፡፡

ወደ ቤቱ ተጠርተው የመጡ እነዚያ መነኮሳትም አንዲት ቃል አልተናገሩም፤ ነገር ግን በልባቸው ተቆጡ፤ በጣምም አዘኑ፤ አባታችን ግን ደቀ መዛሙርቱን ሌላ ማእድ ያቀርቡ ዘንድ አዘዘ፤ ከመንገድ ስንቅ ይመገቡ ነበርና ጥቂት አመጡ፡፡ ገና ሳይቀምሱም ከሕዝብ አንዱ ‹‹አባቴ ሆይ! ጸልይልኝ፤ ይህን ጥቂት በረከትም ተቀበል›› ብሎ ብዙ ጠላ ላከ፤ እነዚህ መነኮሳት ግን ይህን ባዩ ጊዜ ፈጽመው ተደነቁ፤ ፈጽመው ፈሩ፤ ተንቀጠቀጡም፡፡ አባታችንም ተነሥቶ ለ #ክርስቶስ ሰጠሁት፤ ለተራቡትም አስቀደምሁ፤ ለድኆች የሚሰጥ ለ #እግዚአብሔር ያበድራል የሚል ተጽፏልና አላቸው፡፡

እነዚህ መነኮሳትም ‹‹አባታችን መምህራችን ሆይ! ይቅር በለን አንተ ብዙ ሐዘንን ታውቃለህና፤ እኛ ስለሆዳችንና ስለልብሳችን አዘንን፤ አንተ ግን እንደ ጌታህ #ክርስቶስ የድኆችና የችግረኞች ወዳጅ ነህና›› አሉት፡፡ ‹‹አላወቅንምና አባታችን ይቅር በለን፤ አንተ ፈቃደ #እግዚአብሔርን ትፈጽማለህ፤ እርሱም ልመናህን ይሰማልና›› አሉት፡፡ ‹‹እንዲሰጥህ አላወቅንም፤ ነገር ግን ጎተራህን ሁሉ እንደሚሞላልህ ሰምተን ነበር፤ የተዘጋጀ ምግብንም እንዳወረደልህ ሰምተን ረሳን፤ አሁንም አባታችን ይቅር በለን፤ ባንተ ላይ ተቆጥተን ነበር፤ #እግዚአብሔር ከአንተ ጋር እንደሆነ አላወቅንም፤ አንተ ግን አስቀድመህ ለተራቡት ሰጠህ፤ ቀጥሎም ከአምላክህ በረከት ለእኛ ለመብላት ለተዘጋጀን ሰጠኸን›› አሉት፡፡ አባታችን ዘግሩምም ‹‹ወንድሞቼና ልጆቼ ይህን የማደርገው ለሰው ልታይ ብዬ አይደለም፤ ለትምክህትም አይደለም፤ #እግዚአብሔር የሰጠኝ ሀብት ነው እንጂ›› አላቸው፡፡ ‹‹እኔ እሰጣለሁ፤ እርሱም የሚያስፈልገኝን ነገር አላሳጣኝም›› አላቸው፤ እነርሱም ከእርሱ ተባረኩ፤ ከዚህም በኋላ ታላላቅ ተአምራትና ድንቅ ነገርን የሚያደርግ የ #እግዚአብሔርን ገናናነት ተነጋገሩ፡፡

ከዕለታት አንድ ቀንም አባ ዘግሩም ቆሞ ሳለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ወደ እርሱ መጣ፤ ቅድስት የሆነች የጎኑን መወጋትና ቁስሎቹን ሁሉ አሳየው፡፡ በደሙ መፍሰስም ተደሰተ፤ ሰግዶም እንዲህ አለ፤ ‹‹#ጌታየ የሚፈሰውን ደምህን እዳስስ ዘንድ ፍቀድልኝ›› አለው፤ #ጌታችንም ቅዱስ የሆነ ደሙን ይዳስስ ዘንድ ፈቀደለት፤ እንደ ቅዱስ ቶማስም ጎኑን ዳሰሰ፤ ቅዱስ ቶማስስ ደቀ መዛሙርቱን ስላላመነ ነበር፤ ይህ አባታችን ግን #ጌታችን ‹‹ሳያዩኝ የሚያምኑኝ ብፁዓን ናቸው›› ብሎ እንደተናገረው ሳያይ ያመነ ነው፡፡ ይህ አባታችን ግን ሳያይ አመነ፤ በቅዱስ ደሙ መፍሰስም ደስ አለው፤ ወንድሞቼ ሆይ ለአባታችን የተሰጠውን ጸጋ ተመልከቱ፤ የ #መድኃኒታችንን ቁስሎች ዳስሷልና፤ ለድኆች የማዘን ፍሬው ይህ ነው፤ ‹‹ለድኆች የሚራራ ለ #እግዚአብሔር ያበድራል›› ተብሏልና፡፡

ለሰው ልጅ የሚሰጥ ታላቅ ጸጋን አገኘ፤ ከሀገሮች ሲመለስም ወደ ደብረ ጽዮን ለመሄድ ግባ ከተባለ ታላቅ ወንዝ ደረሰ፤ ከፈሳሹ ብዛት የተነሣ ስትበረታታ አገኛት፡፡ ብዙ ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ የሚያደርጉትንም አጡ፤ ብፁዕ አባታችን ግን ከወንዙ ዳር ቆመ፤ በምርጉዙም በባሕሩ ላይ አማተበ፤ ያን ጊዜ ወንዙ ወዲያና ወዲህ ተከፈለ፤ በዚያ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ተሻገሩ፡፡ ነቢዩ ሙሴ የኤርትራን ባሕር በከፈላት ሕዝቡንም በመራ ጊዜ እንደ ተሻገሩ ሁሉ ተሻግረዋልና #እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ይህም አባታችን ባሕርን በየብስ አሻገራቸው፤ ከዚህ በኋላ በሰላም ወደ ቤቱ ደረሰ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ገድለ_ቅድስት_ጸበለ_ማርያም#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_24 እና #ከገድላት_አንደበት)