ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ነሐሴ_16

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች #የእመቤታችን_ድንግል_ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ፣ የሰማዕታት አለቃ #የቅዱስ_ጊዮርጊስ ሥጋው የፈለሰበት ነው፣ #ቅዱስ_ጊጋር በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ዕርገተ_ማርያም

ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን #ድንግል_ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ ። ከዕረፍቷም በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር ።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ ተገለጠላቸው እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው ። ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድስተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደአለባት ገነት በ መንፈስ_ቅዱስ ተነጠቀ ።

የክብር ባለቤት #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስን የእመቤታችን #ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው። የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው ። እነርሱም የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ #እግዚአብሔር አዞሻል አሏት ። ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን #ማርያም ሥጋዋ ወጣ ።

የክብር ባለቤት #ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ ። ያን ጊዜም በገነት ያሉ ዕፀዋት ሁሉም አዘነበሉ መላእክት የመላእክት አለቆች ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት ።

አባቷ ዳዊትም ንግሥት እመቤታችን ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች እያለ በበገና አመሰገናት ። በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኋላ በልጁዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች ።

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ከሰማይ ወረደ ሐዋርያትን ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያም ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው ። እርሱም እንደ አየ እንደ ሰማ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንደ አሳረጓት ነገራቸው ።

ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ ። ከዚህም በኋላ እያዘኑ ሳሉ እነሆ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገለጠላቸውና የፍቅር አንድነት ልጆች ሰላም ይሁንላችሁ ስለ እናቴ #ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ ። እነሆ እኔ እርሷን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል አላቸው ይህንንም ብሎ ከእርሳቸው ዘንድ ወደ ሰማያት ዐረገ ።

ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴም ወር በባተ ቀን ለሐዋርያት ዮሐንስ እንዲህ አላቸው አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሰየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባዔ በመጾም የክብር ባለቤት #ጌታችንን_ኢየሱስ_ክርስቶስን እንለምነው በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን ።

በዚያን ጊዜም ዮሐንስ እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ የነሐሴ ወር እንደ ዛሬ ዐሥራ ስድስተኛ ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው ። በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ ተነሥታ እመቤታችን #ማርያምን አዩዋት። እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን እያንዳንዳቸውን ባረከቻቸው በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው።

የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዒ ካህን ሆነ ። እስጢፋኖስም አዘጋጀ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ ። ሁሉም ሐዋርያት በመሠዊያው ዙሪያ ቆሙ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ።

#ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው ። ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን #ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት።

በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው ። መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚች ቀን ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ ። የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውት ቸርነቴ ትገናኘዋለች ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው።

እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያምም ክብር ይግባውና #ጌታችንን እንዲህ አለችው ልጄ ሆይ እነሆ በዐይኖቻቸው አዩ በጆሮቻቸውም ሰሙ በእጆቻቸውም ያዙ ሌሎችም ታላላቅ ደንቆች ሥራዎችን አዩ ። እመቤታችንም ይህን ስትናገር #ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ ።

የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል እርሷ ስለእኛ ወደ ተወደደ ልጅዋ ሁልጊዜ ትማልዳለችና ።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በቅድስት #ድንግል_ማርያም አማላጅነት ይማረን ። በረከቷም ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከአባ ማትያስ ከሁሉም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት ጋራ ሐዋርያት ከሰበሰቧት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሁላችን ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#የቅዱስ_ጊዮርጊስ_ፍልሰተ_አጽሙ

በዚህችም ዕለት የሰማዕታት አለቃ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥጋው ከፋርስ አገር ወደ አገሩ ልዳ በክብር የፈለሰበት ነው። የሥጋውም ፍልሰት ከእመቤታችን #ድንግል_ማርያም የሥጋ ፍልሰት ጋር አንድ ሆኗል ስለዚህም እርሷን መውደዱን የሚያወቁ ሥዕሉን ከሥዕሏ አጠገብ ይሥላሉ በስሙ ለሚማፀኑ የድኅነት ወደብ ይሆን ዘንድ።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በኃያሉ ተጋዳይ በቅዱስ ጊዮርጊስም ጸሎት በእኛ ላይ ምህረት ይቅርታ ቸርነት ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጊጋር_ሰማዕት

በዚህችም ቀን የሶሪያ መስፍን ጊጋር በሰማዕትነት ሞተ። ሰማዕት የሆነበትም ምክንያት #ጌታችን ከእመቤታችን ከእናቱ ከ #ድንግል_ማርያም ጋራ በተሰደደ ጊዜ በሊባኖስ ተራራ ሳለ ኄሮድስ ሰምቶ ከበው ይዘው ይገድሏቸው ዘንድ ጭፍሮቹን ላከ ጊጋርም ጭፍሮች እንዳገኟቸው አሸሻቸው።

ስለዚህም ኄሮድስ ተቆጣ ጊጋርንም ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው ሕዋሳቱንም ሁሉ ቆራረጠ። ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገልጦለት ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ገድሉንም ለሚጽፍ ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት በሦስት አክሊሎችም ተጋረደ ሦስት አክሊላትን ተቀዳጀ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአማላጅነቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_16)
#ጥቅምት_3

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሦስት በዚህች ቀን የኢትዮጵያዊው ቄርሎስ #አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ በዓለ ፅንሰቱ ነው፣ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት 51ኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባ_ስምዖን አረፈ፣ #የቅዱስ_ጊዮርጊስ_ሐዲስ የምስክርነቱ መታሰቢያ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞#✞✞✞✞✞

#አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ

ጥቅምት ሦስት በዚህች ዕለት ከመጽሐፈ ሰዓታት ውጭ እጅግ ብዙ ድርሰቶችን የደረሰ ፈላስፋም ጻዲቅም ደራሲም መናኝ ባሕታዊም የሆነ ድርሰቶቹንም ለቅዱሳን በነፋስ ጭኖ ይልክላቸው የነበረ የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ኩራት ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በዓለ ፅንሰቱ ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስ ነገረ ሃይማኖትን ጠንቅቆ የተረዳና የሚያስረዳ ስለነበር በዘመኑ የተነሡ የሃይማኖት ክርክሮች ሁሉ እርሱ ከሌለ አይሳኩም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በሸዋ በይፋት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ አይሁድ ነበሩ፡፡ ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጀምሮ ብዙ መምህራን ወደነዚህ ሕዝቦች እየተሠማሩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ክርስትና ለተመለሱት ቤተ እስራኤላውያን በእመቤታችን፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በአባ ኖብና በሰማዕቱ በጊጋር ስም አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተው ነበር፡፡ ሁለቱ የመጀመሪያዎቹ አሁንም አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ቤተ እስራኤላውያኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ክርስትና አልተመለሱም ነበር፡፡

ከእነዚህ አይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ “ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉ” ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ እዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡ የመጀመርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡- “እናንተ የ#እግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ #ክርስቶስ እውነት የ #እግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ 'አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?” ብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣ እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ?” ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡

በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ ሊቃውንቱም “እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ” ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደረገ፡፡ በአልጋ ላይ ሆኖም በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ ነገሩት፡፡ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጥልናል “እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ ምኩራብ ዘራች ቤተ ክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኩራብ ፈተለችው ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? #እግዚአብሔር_አብ አይደለምን?” በዚህ ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ሌላው ያጋጠመው ክርክር ቢቱ ከተባለው ሰው ጋር ያደረገው ክርክር ነበር፡፡ ቢቱ “በምጽአት ጊዜ የሚመጣው #ወልድ ብቻውን እንጂ #አብና #መንፈስ_ቅዱስ አይመጡም” የሚል ኑፋቄ ማስተማር ጀምሮ ነበር፡፡ ቢቱ ከዚህ ኑፋቄው በተጨማሪ የጥንቆላ ሥራም ይሠራ ነበር፡፡ ቢቱ በጥንቆላ ሥራው የተነሣ በቤተ መንግሥቱ ተቀባይነት የነበረው ሰው እንደ ነበረ ገድሉ ይናገራል፡፡ ይህን መሰሉን ተግባር አጥብቆ የተዋጋው ዘርዐ ያዕቆብ እስኪመጣ ድረስ ነገሥታቱ ምንም ክርስቲያኖች ቢሆኑበዚህ መሰሉ ስንኩል ሕፀፅ ይዋጡ ነበር፡፡

ቢቱና አባ ጊዮርጊስ ወደ ንጉሥ ዳዊት ቀርበው በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጡ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ጳጳሱና ሊቃውንቱ ባሉበት እንዲነጋገሩ ስለ ወሰነ ጳጳሱ እንዲመጡ አዘዘ፡፡ በዚህ ጊዜ ተንኮለኛው ቢቱ ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ከተከራከረ እንደሚረታ ስላወቀ “ንጉሡ የአባቶቻችንን ሃይማኖት ክዷልና አትምጣ” የሚል ደብዳቤ በአባ ጊዮርጊስ ስም ጽፎ ጳጳሱን ሊጠሩ በሄዱት መልእክተኞች እጅ ላከ፡፡ ወድያውም ለዐፄ ዳዊት ይህንን ነገር አሳበቀ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ፈጣን መልእክተኞች ልኮ የፊተኞቹ መልእክተኞች እንዲመለሱ አደረገና ደብዳቤው ተነበበ፡፡ የቢቱ ተንኮል ያልገባው ንጉሥ ዳዊት ይህን ደብዳቤ ሲመለከት አባ ጊዮርጊስን በደም አበላ እስኪነከር ድረስ እንዲደበደብ አድርጎ ወደ እስር ቤት አስገባው፡፡ ዐፄ ዳዊት እስኪሞትና ልጁ ቴዎድሮስ እስኪነግሥ ድረስም በዚያ ቆየ፡፡ ቢቱ ግን በመልአክ ተቀስፎ ሞተ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን በረከታቸው ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ስምዖን

ዳግመኛም በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ኃምሣ አንደኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ስምዖን አረፈ።

ይህም አባት ከእስክንድርያ ከታላላቆች ተወላጅ የሆነ ወላጆቹም ሃይማኖታቸው የቀና ነው እርሱም ከታናሽነቱ የሃይማኖት ወተትን ጠጥቶ አደገ ስለዚህም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተማረ።

የምንኵስናንም ልብስ ሊለብስ በልቡ አስቦ ወደ አስቄጥስ ገዳም በመሔድ ከእርሱ አስቀድሞ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በአባ ያዕቆብ ገዳም መነኰሰ በየጊዜው በሚጨመር ተጋድሎም ሥጋውን እያደከመ አብዝቶ በመጋደል በእርሱ ዘንድ ኖረ።

ዳግማዊ አባ ማርቆስም ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ይህን አባ ስምዖንን ስለ በጎተጋድሎውና ስለ አገልግሎቱ ከአባ ያዕቆብ ዘንድ ወሰደው እያገለገለውም ከእርሱ ጋር ኖረ።

አባ ማርቆስም በአረፈ ጊዜ አባ ያዕቆብ ተሾመ ያን ጊዜም እያገለገለው ከአባ ያዕቆብ ጋር ኖረ። ከዚህም በኋላ አባ ያዕቆብ በአረፈ ጊዜ ብዙዎች ካህናትና ኤጲስቆጶሳት የሀገር ታላላቆች ሁሉም ይህን አባት አባ ስምዖንን መረጡት። ትሩፋቱንና የአማረ ሥራውን በእነዚህ በሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ በነበረበት ጊዜ ስለተመለከቱ አምላካዊ ፍቅር አነሣሥቷቸዋልና በወንጌላዊ ማርቆስ መንበር ላይ ይዘው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።

ከዚህም በኋላ በሹመቱ ጸንቶ መልካምን ጉዞ ተጓዘ #እግዚአብሔርንም አገለገለው የሃይማኖትንም ሕግ በማስጠበቅ የ #ክርስቶስን መንጋዎች ጠበቀ።

በሹመቱ ወራትም ቤተ ክርስቲያን በጸጥታና በሰላም ኖረች። ከዚህም በኋላ እግሮቹን በጽኑዕ ደዌ ታመመ ፈጣሪ #እግዚአብሔርንም ከዚህ ደዌ ያሳርፈው ዘንድ ለመነው። ክብር ይግባውና #ጌታችንም ልመናውን ተቀብሎ በሰላም በፍቅር አንድነት አሳረፈው የሹመቱ ወራትም አምስት ወር ከዐሥራ አምስት ቀን ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን በረከታቸው ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ሐዲስ (ሰማዕት)