ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ጥቅምት_21

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ አንድ በዚህችም ቀን #እመቤታችን_ተአምራትን_አድርጋ_ሐዋርያው_ማትያስን ከእሥራት ቤት ያወጣችበት፣ #የነቢይ_ኢዩኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ፣ የማርታና የማርያም ወንድም #የቅዱስ_አልዓዛር ሥጋው ከቆጵሮስ አገር የፈለሰበት፣ የቅዱስ አባት #አባ_ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም እረፍት ነው፣ ታላቁ ጻድቅ #አቡነ_አላኒቆስ ዕረፍታቸው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#እመቤታችን_ለሐዋርያው_ቅዱስ_ማትያስ_ያደረገችለት_ተአምር

በዚህችም ቀን እመቤታችን #ማርያም ተአምራትን አድርጋ ደቀ መዝሙር ማትያስን ከእሥራት ቤት አዳነችው።

የከበሩ ቅዱሳን ወንጌልን በዓለም ዞረው ይሰብኩ ዘንድ ዕጣ ሲጣጣሉ ለቅዱስ ማትያስ ዕጣ የደረሰው ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ነበር፡፡ ይህችም ሀገር እስኩቴስ የተባለች ሩሲያ እንደሆነች የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ቅዱስ ማትያስም እነዚህ ሰውን የሚበሉ ሰዎች አገራቸው እንደደረሰ ዐይኑን አውልቀው አሠሩት፡፡ ምግባቸውም የመጻተኛ ሰው ሥጋ ነው፡፡ በልማዳቸው መሠረት መጻተኛን ሰው ገና እንደያዙት ዐይኖቹን ዐውልቀው በእሥር ቤት ያኖሩታል፡፡ እስከ 30 ቀንም ድረስ ሳር እያበሉ ያስቀምጡትና በ30ኛው ቀን አውጥተው አርደው ይበሉታል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስንም በልማዳቸው መሠረት ዐይኖቹን አውልቀው አሠሩት፡፡ ሐዋርያውም በእሥር ቤት ሆኖ በዚያ ላይ ዐይኖቹን ታውሮ ሳለ በጭንቅ ወደ #ጌታችንና ወደ #እመቤታችን ይለምን ነበር፡፡ ነገር ግን እመብርሃንና ልጇ #መድኃኔዓለም 30ኛው ቀን ሳይፈጸም ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስን ወደ እርሱ ላኩለት፡፡ ቅዱስ ማትያስም ዐይኑን ፈወሱለትና ማየት ቻለ፡፡

እንድርያስም በተዘጋው በር በተአምራት ገብቶ አሥርቤቱ ውስጥ ያሉ እሥረኞችን በስውር አውጥቶ ከከተማው ውጭ ካስቀመጣቸው በኋላ ሁለቱ ሐዋርያት ተመልሰው ሰውን ለሚበሉት ሰዎች ተገለጡላቸው፡፡ እነርሱም ይዘው በአንገታቸው ገመድ አግብተው ለ3 ቀን በሀገራቸው ጎዳናዎች ላይ ሁሉ ጎተቱዋቸው፡፡ ሁለቱም ሐዋርያት በጸሎታቸው ከእሥር ቤቱ ምሰሶ ሥር ውኃ አፈለቁና ውኃው ሀገራቸውን ሁሉ እስኪያጥለቀልቅና ሰዎቹንም እስከ አንገታቸው ድረስ እስከሚደርስ ሞላ፡፡ ሁሉም በተጨነቁ ጊዜ ሁለቱ ሐዋርያት በፊታቸው ተገለጡና ‹‹በጌታችን እመኑ ትድናላችሁ›› በማለት ወንጌልን ሰብከውላቸው አሳመኗቸው፡፡ ምሥጢራትንም ሁሉ ገለጡላቸው፡፡ ደግሞም የአራዊት ጠባይን ከሰዎቹ ያርቅላቸው ዘንድ ወደ #ጌታችንና ወደ ተወደደች እናቱ ከጸለዩ በኋላ በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም አጠመቋቸው፡፡ ያ የአውሬነት ጠባያቸውም ጠፍቶላቸው የዋህ፣ ቅንና ሩኅሩኆቸ ሆኑ፡፡ ሐዋርያትም ሃይማኖትን እያስተማሯቸው 30 ቀን አብረዋቸው ከተቀመጡ በኋላ አገልጋይ ኤጲስ ቆጶሳትን፣ ካህናትንና ዲያቆናትን ሾመውላቸው ወደ ሌላ ሀገር ሄዱ፡፡

ለሐዋርያት ሞገሳቸው ጣዕመ ስብከታቸው የኾነች ክብርት #እመቤታችን ለእኛም ትለመነን!

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኢዩኤል_ነቢይ

ዳግመኛም በዚህችም ቀን የነቢይ ኢዩኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። ይህም የእስራኤልን ልጆች የሚያስተምርና የሚገሥጻቸው ነበር ስለ #ክርስቶስም በኢየሩሳሌም መኖርና ማስተማር ትንቢት ተናገረ። ደግሞም ስለ መከራው በሐዋርያትና በሰባ ሁለቱ አርድእት በሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ላይ የ #መንፈስ_ቅዱስን መውረድ እንዲህ ሲል ተናገረ።

ከዚህ በኋላ በሥጋዊ በደማዊ ሰው ሁሉ ከመንፈሴ አሳድርበታለሁ ሴቶች ልጆቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ ትንቢትን ይናገራሉ አለቆቻችሁ ሕልምን ያልማሉ ጎልማሶቻችሁም ራእይን ያያሉ። ሁለተኛም እንዲህ አለ ያን ጊዜ ከተራራው ማር ከኮረብታውም ወተት ይፈሳል በቤተ #እግዚአብሔር አጠገብ ካሉ ከይሁዳ አገሮች ሁሉ ምንጩ ከላይ ወደታች ይፈሳል።

ሙታን በሚነሡ ጊዜ ስለሚሆነው የፍርድ ሰዓት እንዲህ አለ ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ የከዋክብትም ብርሃናቸው ይጠፋል። የትንቢቱንም ወራት አድርሶ #እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በነብዩ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አልዓዛር የማርታና የማርያም ወንድም

በዚችም ቀን ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው የቅዱስ አልዓዛር ሥጋው ከቆጵሮስ አገር የፈለሰበት ሆነ።

ከክርስቲያን ነገሥታትም አንዱ ሥጋው በቆጵሮስ እንዳለ በሰማ ጊዜ ከቆጵሮስ ደሴት ወደ ቊስጥንጥንያ አፈለሰው። ሊአፈልሱትም በወደዱ ጊዜ በከበረ የደንጊያ ሣጥን ውስጥ ሁኖ በምድር ውስጥ ተቀብሮ አገኙት በላዩም እንዲህ የሚል ጽሑፍ ነበረ ይህ በመቃብር ውስጥ አራት ቀን ከኖረ በኋላ ከሙታን ለይቶ ላስነሣው ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ወዳጁ የሆነ የቅዱስ አልዓዛር ሥጋ ነው።

ይህንንም በአዩ ጊዜ ደስ ተሰኙበት ተሸክመውም ወደ ቊስጥንጥንያ አገር ወሰዱት ካህናቱም ሁሉ ወጥተው በታላቅ ክብር በመዘመርና በማመስገን ተቀበሉት በአማረ ቦታም አኖሩት በዚችም ቀን በዓልን አደረጉለት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አልዓዛር ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_ዘኢየሩሳሌም

በዚህችም ቀን ለከበረች አገር ኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት የሆነ ቅዱስ አባት አባ ዮሐንስ #እግዚአብሔርን በሚወድ የንጉሥ ሰይፈ አርዕድ ደግሞ ቈስጠንጢኖስ ለሚባል ልጁ በሆነ በንጉሣችን በዳዊት ዘመን አረፈ።

ይህም ቅዱስ ከምስር አገር ታላላቆች #እግዚአብሔርን የሚፈሩ የክርስቲያኖች አባቶች ልጅ ነው። የዲቁና መዓረግንም ለመሾም እስከ ተገባው ድረስ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማሩ በበጎ አስተዳደግ አሳደጉት። ከዚህም በኋላ በዲቁናው ሹመት አገልግሎቱን በአሳመረ ጊዜ የቅስና መዓረግ የሚገባው ሁኖ ቅስና ተሾመ።

በጾም በጸሎት #እግዚአብሔርንም በመፍራት የተጠመደ ሁኖ ድኆችንና ችግረኞችን የሚወዳቸው የሚረዳቸው ሆነ ያን ጊዜ የሐዋርያት የሆነች የጵጵስና ሹመት የምትገባው ሁና በከበረች አገር በኢየሩሳሌም በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ ሕዝቡንም በፈሪሀ #እግዚአብሔርና በትሕትና የሚያስተምራቸው ሆነ።

እነርሱም ስለ ቅድስናው እጅግ የሚወዱት ሆኑ መልኩና የአንደበቱ አገላለጥ እንደ #እግዚአብሔር መልአክ ያማረ ነበር። በሹመቱም ጥቂት ዘመናት ከኖረ በኋላ ከመንበረ ሢመቱ እስከ አራቀው ድረስ በላዩ ሰይጣን ምክንያትን አመጣ።

ይህም እንዲህ ነው በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአባ ማርቆስ ዘመን በግዛቱ ውስጥ ያሉ እስላሞች ስለ ዐመፁበት የኢትዮጵያ ንጉሥ ፈጅቷቸው ነበርና ስለዚህ በግዛቱ ውስጥ በሚኖሩ እስላሞች ላይ ክፉ እንዳያደርግ ለኢትዮጵያ ንጉሥ መልእክት እንዲልክ ሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስን የምስር ንጉሥ አዘዘው።

አባ ማርቆስም ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥ ስለሚላኩ ሰዎች ከመኳንንቱ ከኤጲስ ቆጶሳቱና ከሀገር ታላላቆች ሽማግሌዎች ጋር ተማክሮ እሊህን ብሩሀን ከዋክብት የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስን የምስር ኤጲስቆጶስ አባ ሳዊሮስን በእውቀታቸው በአስተዋይነታቸውና በቅድስናቸው መረጡአቸው ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥም ይሔዱ ዘንድ ግድ አሏቸው።
🌹 "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌹

         🌹 #ጥቅምት ፳፩ (21) ቀን።

🌹 እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ መሰቀልህን በቅዱሳት መጻሕፍት ሰማሁ ይኽን በዐይኔ አሳየኝ በማለት #መድኃኔዓለምን_ለጠየቁት_እሱም ለገለጸላቸው፤ የንጉሡን መልዕክተኞች ከንጉሡ ቤት እንገናኝ በማለት መልዕክተኞቹ ዘጠኝ ቀን ተጉዘው ሲደርሱ እሳቸው ቀድመዋቸው ንጉሡ ቤት ለተገኙት #አቡነ_ዐሥራ_ወልድ_ለዕረፍታቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

                              
🌹 #አቡነ_ዐሥራተ_ወልድ፦ በዳሞት አውራጃ ልዩ ስሟ እነሴ በምትባል ቦታ በዐፄ ሠርጸ ድንግል ዘመነ መንግሥት በ1584 ዓ.ም ተወለዱ። አባታቸው ፃማ ክርስቶስ እናታቸው ጽጌ ማርያም ይባላሉ። ኹለቱም በሕገ #እግዚአብሔር ጽንተው የሚኖሩ በሃይማኖት በምግባር የተመሰገኑ በተጋድሎ በትሩፋት የታወቁ ክርስቲያኖች ነበሩ ነገር ግን ልጅ ስላልነበራቸው እንደ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ሁልጊዜ #እግዚአብሔርን በጸሎት ይጠይቁ ነበር አምላክን የወለደች ክብርት #እመቤታችንንም ይማጸኗት ነበር።

🌹 ኹለቱም #እግዚአብሔርን የሚፈሩ በምድራዊ ሀብትም የበለጸጉ ነበሩ፤ ለድኖችና ለምስኪኖች አብዝተው ይመጸውቱ ስለነበር ከጾማቸው በኋላ ያለ ድኖችና ምስኪኖች ብቻቸውን አይመገቡም ነበር። #እግዚአብሔርም ጸሎት ልመናቸውን ተቀብሎ የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ወደደ። ከዕለታትም በአንደኛው ቀን የ #እግዚአብሔር ሰው ለጽጌ ማርያም ታይቶ "ዝናው በአራቱ ማዕዘን ኹሉ የሚደርስ በሕይወተ ሥጋ እያለ የብዙ ሰዎችን ነፍስ በጸሎቱ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ የሚያወጣ ወደ ሰማይም ወጥቶ የ #ሥላሴን ምሥጢር የሚያይ የተባረከ ልጅን ትወልጂ ዘንድ አለሽና ደስ ይበልሽ" በማለት ካበሠራት በኋላ አቡነ ዐሥራተ ወልድ ሰኔ ሃያ ቀን ተወለዱ።

🌹 ጻድቁም በተወለዱ በስምንተኛ ቀናቸው "ለ #አብ ምስጋና ይገባል ለ #ወልድ ምስጋና ይገባል ለ #መንፈስ_ቅዱስ ምስጋና ይገባል" ብለው ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል። እስከ ዐሥራ ኹለት ዓመታቸውም ድረስ ውኃ በመቅዳት ዕንጨት በመስበር ወላጆቻቸውን ካገለገሉ በኋላ ወላጆቻቸው ወደ ታላቁ ጻድቅ ወደ አቡነ ተጠምቀ መድኅን ዘንድ ወስደው እንዲያስተምሩላቸው አደራ ብለው ሰጧቸው።

🌹 አቡነ ተጠምቀ መድኅንም ዐሥራተ ወልድን ተቀብለው የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ኹሉ አስተማሯቸው። በሚማሩበትም ጊዜ #መንፈስ_ቅዱስ በአፋቸው ያቀብላቸው ስለነበር አስቀድመው የተማሩ ይመስሉ ነበር። በሦስት ዓመትም ውስጥ መጻሕፍተ ብሉያትን መጻሕፍተ ሐዲሳትን መጻሕፍተ መነኰሳትን፣አዋልድ መጻሕፍትንም ኹሉ ከነትርጓሜያቸው ከአቡነ ተጠምቀ መድኅን ተምረው #እግዚአብሔርም ከሐሰት መጻሕፍት ከሟርት ከጥንቆላ መጻሕፍት በቀር ያልገለጠላቸው የመጻሕፍት ምሥጢር የለም። የመላእክትንና የቅዱስ ያሬድንም ዜማ ገለጠላቸው።

🌹 ከዚኽም በኋላ አቡነ ዐሥራተ ወልድ ለመመንኰስ ወላጆቻቸውን አስፈቅደው ከመምህራን ጋር ወደ ታላቁ ገዳም ወደ ደብረ ዳሞ ሔደው በዚያም መነኰሳቱን እያገለገሉ ለ25 ዓመታት ያህል በተጋድሎ ከኖሩ በኋላ በዐፄ ፋሲል ዘመን መንግሥት በ40 ዓመታቸው በ1624 ዓም መንኰሱ። ከሊቀ ጳጳሱ ከአቡነ ሚካኤልም እጅ የቅስና ማዕረግ ተቀበሉ። ከዚኽም በኋላ ከመምህራቸው ከአቡነ ተጠምተ መድኅን ጋር ወደ ጋሾላና ጉሓን ገዳማት ሔደው ተጋድሏቸውን ጨምረው መጾም መጸለይን አበዙ። ወደ ተራራ ሔደው ዳዊት ሲያነቡ ያድራሉ፣ ምሥራቅም ዙረው እምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ፤ ወደ ምዕራብም ዙረው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ፤ ወደ ሰሜንም ዙረው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ ወደ ደቡብም ዙረው እምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ፤ እንዲህም እያደረጉ በየዕለቱ ኹለት ሺህ ይሰግዱ ነበር። ላባቸው እንደ ውኃ ፈስሶ ምድርን እስኪያርስ ድረስ ይሰግዳሉ፤ የቆሙበትም ምድር እንደ ጉድጓድ ይጎደጉዳል። እንደዚህ ባለ ታላቅ ተጋድሎ ጸንተው ብዙ ዘመን ኖሩ። የ #ጌታችንንም ዐርባ ጾም ምንም ሳይቀምሱ ዐርባውን ቀን ይጾሙ ነበር።

🌹 ከዚኸም በኋላ አቡነ ዐሥራት ወልድ ጃባ በሚባለው ቦታ ዐሥራ አንድ ዓመት በተጋድሎ ኖሩ። አባታችን ያከብሯት የነበረች ቅዱስ ሉቃስ የሣላት የክብርት #እመቤታችን ሥዕል በዚያ ነበረችና እርሷም ድንቅ ድንቅ ተኣምራትን ታደርግላቸው ነበር። ጃባ በምትባል ቦታም ዘወትር ታነጋግራቸው ነበር። በአንደኛውም ሌሊት ተኝተው ሳሉ አምላክን በድንግልና የወለደች ክብርት #እመቤታችን ተገልጣላቸው "ልጄ ወዳጅ ዐሥራተ ወልድ ሆይ! በጸሎትና በልመናህ የጃባ ሰዎች ኹሉ ይድናሉ፣ በቃልህ #ክርስቶስን አምነው በእጅህ #ቅዱስ_ሥጋውንና #ክቡር_ደሙን ይቀበላሉ" አለቻቸው።

🌹 ከዚኽም በኋላ የታዘዘ የ #እግዚአብሔር መልአክ ለኹለቱም ቅዱሳን ተገልጦላቸው አቡነ ተጠምቀ መድኅንን ወደ ጋዝጌ እና ወደ መተከል ሔደው የከበረች ወንጌልን እንዲያስተምሩ ሲያዛቸው አቡነ ዐሥራተ ወልድን ደግሞ ወደ ጫራ ምድር ሔደው በዚያ ወንጌልን ይሰብኩ ዘንድ አዘዛቸው። ኹለቱም ቅዱሳን እርስ በርሳቸው በመንፈሳዊ ሰላምታ እጅ ተነሣሥተው ለሐዋርያዊ አገልግሎት ተለያይተው ወደታዘዙባቸው ቦታዎች ሔዱ። አባታችን ዐሥራተ ወልድም እየጸለዩ ስምንት ዓመት ከስድስት ወር በርበር በምትባል በረሓ ውስጥ ሳሉ በአራቱም ማዕዝናት እየተዘዋወሩ በምሥራቅ አንድ ሽህ በምዕራብ አንድ ሺህ በሰሜን አንድ ሺህ በደቡብ አንድ ሺህ ጊዜ ይስግዱ ጀመር የክብር ባለቤት #ጌታችን_አምላካችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም በዚህ ጊዜ ተገልጦላቸው "ወዳጀ ዐሥራተ ወልድ ሆይ! ለምን ሥጋህን እንደዚህ አደከምህ" አላቸው አባታችንም " #ጌታ ሆይ! ኃይላቸውን በስግደት ቀንና ሌሊት በመትጋት የሚያደክሙ በመንግሥትህ አይደሰቱምን በዓለም የደከመ ለዘለዓለም ይድናል ጻድቃን ዳግመኛም በብዙ ድካምና መከራ ወደ #እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል" እንዳለ በማለት መለሱ። #ጌታችን_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ "ድካምህ በከንቱ አትቀርም በሰማያውያን መላእክት በተባረኩ ጻድቃን ድል በነሱ ሰማዕታት ንጹሐን በሚሆኑ ደናግል በፍጹማን መነኰሳት ፊት የድካምህን ዋጋ እሰጥሃለሁ። እንግዲህ ከዛሬ ጀምረህ ወደ አዘዝኩህ ቦታ ሒድ፤ "መንግሥተ ሰማያትም ቀርባለች" እያልህ የመንግሥትን ወንጌል አስተምር፣ ኃይሌ ከአንተ ጋር ይኖራልና" ብሎ አዘዛቸው።

🌹 #ጌታችን ይህን ሲነግራቸው አውሎ ነፋስ መጥቶ ጉርብ ወደ ምትባለው ዋሻ ወስዶ አደረሳቸው። በሥራ የሚኖሩ የሀገሩ ሰዎችም የአባታችን ዐሥራተ ወልድን መምጣት ሰምተው ተቆጥተው በአባታችን ላይ በጠላትነት ተነሡባቸው፣ ጋሻቸውንና ጦራቸውን ይዘው የመጡ ቢሆንም አባታችን ግን የከበረች የ #ክርስቶስን ወንጌል አስተምረው አሳምነው አጠመቋቸው። የጫራንም ሕዝብ አምስት ዓመት ካስተማሯቸው በኋላ ዳግመኛ የሻሽናን ሕዝብ ያስተምሯቸው ዘንድ የ #እግዚአብሔር መልአክ እየመራው ሻሽና አደረሳቸው። አባታችን በዚያም የሀገሩን ሕዝብ አስተምረው አጠመቁ።
🌹 የጎንደር ንጉሥ ጻድቁ ዮሐንስ የአባታችን ዐሥራተ ወልድን ቅድስናና ገድል በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ ያመጧቸው ዘንድ መልእክተኞችን ላከ፤ መልእክተኞችም አባታችንን በሻሽና አገኟቸው፤ አባታችን ግን መልእክተኞቹን "ልጆቼ እኔ ኃጢአተኛ ስሆን ከጎንደር እስከ ሻሽና ንጉሡ ምን ብሎ ላካችሁ?" አሏቸው። ይኸንንም ተናግረው የንጉሥን ጭፍራ "ወደ እናንተ እስክመለስ ድረስ ከዚኸ ጠብቁ" ብለው ወደ ንጉሡ ዘንድ ከመሔዳቸው በፊት ወደ ጸሎት ቤት ገብተው ከዳዊት መዝሙር ጸለዩ። ጸሎታቸውንም ከፈጸሙ በኋላ አባታችን ወደ እነርሱ ተመልሰው "እኔ ሽማግሌ ሰው ነኝ ወደ ጎንደር ለመሔድ አልችልም" አሏቸው። እነርሱም "አባታችን ሆይ! አንተ ከእኛ ጋር ካልሔድህ ተመልሰን አንሔድም" አሉ። አባታችንም እጅግ አዝነው "ልጆቼ ሒዱ እኛ እርሰ በእርሳችን በንጉሡ ቤት እንገናኘለን አሏቸውና ተመልስው ሔዱ ተመልስው ከሔዱ በኋላ ወደ ንጉሡ ቤት ቢደርሱ አባታችንን ከንጉሡ ጋር ተቀምጠው አገኟቸው።

🌹 የንጉሡ መልእክተኞችም ለንጉሡ "እኛ ከሻሽና ከተነሣን እስከዚህ ዘጠኝ ቀናችን ነው ይኽ አባት የሚያስደንቅ ተአምር እያደረገ በየት አለፈን?" ብለው እጅግ ተገረሙ። ንጉሡም ይኽን ድንቅ ተኣምር በስማ ጊዜ ከአባታችን እግር ሥር ሰገደ አቡነ ዐሥራተ ወልድንም "አባቴ ሆይ አስተምረህ ላሳመንኽውና ለአጠመቅኽው ሕዝብ ታቦትን ወስደህ ቤተክርስቲያን ሥራ ከታቦታትም የወደዱኻውን ምረጥ"። በማለት ጠየቃቸው። ብፁዕ አባታችን ዐሥራተ ወልድም "በጣም የምወዳት እንደ ምግብ የምመገባት እንደ መጠጥ የምጠጣት እንደ ልብስ የምለብሳት፣ እንደ ምርጉዝ የምደገፋት በፍቅሯ የምረካባት የ #ኪዳነ_ምሕረት ታቦት ናትና እርሷን እወዳታለሁ" ብለው መረጡ፤ ንጉሡም ቃላቸውን ሰምቶ ታላቅ ደስታ ተደሰተ ፈቀደላቸውም።

🌹 ከዚኽም በኋላ አቡነ ዐሥራተ ወልድ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው በዚያ " #ጌታየ ሆይ መሰቀልህን በቅዱሳት መጻሕፍት ሰማሁ ይኽን በዐይኔ አሳየኝ" እያሉ አንድ ዓመት ቆመው ጸለዩ። የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ለአባታችን ተገለጠላቸውና መጀመሪያ አይሁድ እንዴት እንደሰቀሉት የእሾኽ አክሊልን እንደአቀዳጁት፣ ጎኑን በጦር እንደተወጋ አሳያቸው። አቡነ ዐሥራተ ወልድም የ #ጌታችንን ስቅለት በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ደንግጠው ወደቁ።

🌹 በዚያን ጊዜም #ጌታችን ወደ እርሳቸው መጥቶ "ልታይ የማትችለውን ዕለተ ዐርብ ለምን ለመንከኝ? እንግዲህ ተነሣና ወደ ሀገርህ ተመለስ የሰበሰብሃቸው መንጋዎችህ አንተን በማጣታቸው ተበትነዋልና" አላቸው። ከዚኽም በኋላ #ጌታችን ታላቅ የምሕረት ቃልኪዳን ገብቶላቸው በክብር ዐረገ። አባታችን ዐሥራተ ወልድም ከገዳማቸው ወጥተው ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው አንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ በትንሣኤ ዕለት #ቅዱስ_ሥጋውንና #ክቡር_ደሙን ተቀብለው በ #መንፈስ_ቅዱስ ኃይል ተመስጠው ካህናት ጸሎተ ቅዳሴውን ሳይጨርሱ ገዳማቸው ዙርዙር ኪዳነ ምሕረት ደረሱ።

🌹 ከዚኽም በኋላ አባታችን ጉርብ በምትባል ዋሻ ውስጥ በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ሠርቶላቸው መቶ ዐሥር ዓመት ከኖሩና #ጌታችንም ታላቅ የምሕረት ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ የጥቅምት ወር በባተ በሃያ አንድ ቀን ከዚኽ ዓለም ድካም በሰላም ዐርፈዋል። ከአባታችን ከአቡነ ዐሥራተ ወልድ #እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!።

ምንጭ፦ ከእንተ ቅዱሳን ኅሩያን መጽሐፍ የተወስደ።
   
#ጥቅምት_22

#ቅዱስ_ሉቃስ_ወንጌላዊ
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ሁለት በዚህች ቀን ብልህ ጥበበኛ የሆነ ቅዱስ ወንጌላዊ ሉቃስ በሰማዕትነት አረፈ።

በሀገረ አንጾኪያ ከአሕዛብ ወገን የተለወደው አይሁዳዊው ሉቃስ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የተቆጠረ ባለ መድኃኒትና ወንጌልን የጻፈ ቅዱስ ሐዋርያ ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በወንጌል ትርጓሜያቸው ስሙ ‹ዓቃቤ ሥራይ› ወይም ‹ባለ መድኃኒት› የሚል ትርጉም በውስጡ የያዘ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በላቲን ቋንቋ ‹ሉካስ› ማለት ‹ብርሃናማ፣ ብርሃን የያዘ› ማለት ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ደግሞ ብልህና ጥበበኛ በማለት ይገልጸዋል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ የሚመሰለው በገጸ ላህም ነው፡፡ ‹‹ፍሪዳ አምጡና እረዱ፤ ከእርሱ ጋር እየበላን ደስ ይበለን›› እያለ ምሳሌውን ይጽፋልና፡፡ (ሉቃ.፲፭፥፳፫) በጤግሮስም ወንዝ ይመሰላል፤ ጤግሮስ ፈለገ መዓር ወይም የመዓር ወንዝ ነው፤ ርስትነቱም ጸዊረ ነገር (ምሥጢር መሸከም) የሚቻላቸው ሰዎች ርስት ነው፡፡

ቅዱስ ሉቃስ በአቴና ሀገር በእስክንድሪያ ሕክምናን አጥንቷል፤ የሥነ ሥዕልም ችሎታ ነበረው፤ ይህን የሥዕል ችሎታውንም በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ መጻሕፍቱ ላይ በሥዕላዊ መልክ ገልጾታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደሚናገረው እመቤታችን #ቅድስት_ድንግል_ማርያም ልጇን አቅፋ (ምስለ ፍቁር ወልዳ) ለመጀመርያ ጊዜ የሣለው እርሱ ነው፡፡ ሥዕሎቹም በኢትዮጵያ በተድባባ ማርያም፣ በደብረ ዘመዶ፣ በዋሸራና በጀብላ ይገኛሉ፡፡ ተመሳሳዩም በስፔን ቅድስት #ማርያም ካቴድራል እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት ምስጋናው ‹‹ከወንጌላውያን አንዱ የሆነው ጠቢቡ ሉቃስ ለሣላት ሥዕልሽ ሰላምታ ይገባል›› በማለት አመስግኗል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከመረጠው በኋላ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር በመሆን አገልግሏል፡፡ ቀድሞ ዓቃቤ ሥራይ ዘሥጋ (ሥጋዊ ሐኪም) ቢሆንም በኋላ ግን ዓቃቤ ሥራይ ዘነፍስ (መንፈሳዊ ሐኪም) እንደሆነ ሊቃውንቱ ይናገራሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እርሱ ሲመሰክር ‹‹የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል›› በማለት ገልጦታል፡፡ (ቆላ.፬፥፲፬) ቅዱስ ሉቃስ ተንሣኢ (ፈጣን) እየተባለም የሚጠራው ለስብከተ ወንጌል ስለሚፋጠን ነበር፤ በወንጌሉም አጻጻፍ ላይ ስለ ሕመማቸውና ድኅነት ስለሚያገኙበት ሁኔታ ገልጦ ጽፏል፤ ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑት ታሪኮች የደጉ ሳሚራዊና ደም ይፈሳት ስለነበረችው ሴት ናቸው፡፡ (ሉቃ.፲፥፴‐፴፭፤፰፥፵፫) ሐዋርያው መበሥር ወይም ብሥራት ነጋሪ እየተባለም ይጠራል፤ ይህም ብሥራተ መልአክን ጽፏልና ነው፡፡ (ሉቃ.፩፥፩)

የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል የተጻፈው በሀገር አኪይያ (ሮም) በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ነው፤ የሉቃስ ወንጌል ‹የአሕዛብ ወንጌል›፣ ‹ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ›፣ ‹ሰባኬ ጸሎት›፣ ወንጌለ አንስት ተብሎም ይጠራል፡፡

፩. ‹የአሕዛብ ወንጌል› እየተባለ የሚጠራው ወንጌሉ የተጻፈው ለአሕዛብ በመሆኑ ነው፡፡

፪. ሰባኬ #መንፈስ_ቅዱስ የሚባለው ስለ #መንፈስ_ቅዱስ ደጋግሞ ስለሚናገር ነው፡፡

፫. ሰባኬ ጸሎት የተባለው ከሌሎች ወንጌላት የበለጠ ደጋግሞ የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያምን ጸሎት ጽፏልና ነው፡፡

፬. ወንጌለ አንስት የሚባለው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያም፣ ስለ ቅድስት ኤልሳቤጥ፣ ስለ ማርያም እንተ እፍረት፣ ስለ ናይን እና ወዘተ በስፋት ስለሚናገር ነው፡፡

ወንጌሉን ከመጻፉ አስቀድሞም ቅዱስ ሉቃስ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ትርጓሜ ወንጌል ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በአንጾኪያ ሀገር ቅዱስ ጳውሎስን ካገኘው በኋላም ሊቀ ሐዋርያው ሰማዕት እስከሆነበት ድረስ አገልግሎታል፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ጋርም በነበረበት ጊዜም መቄዶንያ የምትባል ሀገር ከፍሎ እንዲስተምር እንደሰጠው በወንጌል ትርጓሜ ተገልዿል፡፡ ቅዱስ ሉቃስም በዚያ ሀገር ከ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መፀነስ ጀምሮ፣ መዋዕለ ስብከቱን፣ የሠራውን ትሩፋትና ገቢረ ተአምሩን በሙሉ ለአሕዛቡ በነገራቸው ጊዜ ከኃጢያት ወደ ጽድቅ፣ ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮ #እግዚአብሔር ተመለሰው በማመን የክርስትና ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ ለስብከት በሚጓዝበትም ወቅት ትምህርት ባልተዳረሰባቸው ስፍራ ሲያስተምር አንድ ታዖፊላ የተባለ የእስክንድርያ መኮንን ስብከቱን አድምጦ በማመን ‹ዜና ሐዋርያትን› (ገድለ ሐዋርያትን) እንዲጽፍለት በጠየቀው መሠረት ጽፎለታል፡፡ በዚህም ቅዱስ ሉቃስ የጻፋቸው መጻሕፍት ከወንጌሉና ከሐዋርያት ሥራ ጋር ሦስት ናቸው፡፡

ቅዱስ ሉቃስ የሕይወት ታሪኩ እንደሚገለጸው በድንግልና የኖረ ሐዋርያ ነው፤ ሐዋርያዊ አገልግሎቱንም የፈጸመው በአብዛኛው በግሪክ ነበር፡፡ ሐዋርያቱ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ካረፉ በኋላም በሮም ሀገር ማስተምር ቀጠለ፤ በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ ለምእመናን መልእክትን ይጽፍ ነበር፤ ስለዚህም ጣዖት አምላኪዎች ከአይሁድ ጋር በመስማማት በአንድ ምክር ሆነው በንጉሥ ኔሮን ፊት በመቆም ስለ ሐዋርያው ሉቃስ እንዲህ ብለው ተናገሩ፤ ‹‹ይህ ሉቃስ በሥራይ ብዙ ሰዎችን ወደ ትምህርቱ አስገባቸው፡፡›› ንጉሥ ኔሮንም ወደ ፍርድ ዐደባባይ ሉቃስን እንዲያቀርቡት ባዘዘ ጊዜ ሐዋርያው ሉቃስ ዕረፍቱ እንደ ደረሰ በ #መንፈስ_ቅዱስ ዐውቆ ወደ ባሕር ዳርቻ ሄደ፡፡ በዚያም ዓሣ የሚያጠምድ አንድ ሽማግሌ ሰው አግኝቶ መጻሕፍቱንና ደብዳቤዎችን እንደሰጠውና ‹‹ወደ #እግዚአብሔር መንገድ መርተው ያደርሱሀልና እነዚህን መጻሕፍት ጠብቃቸው›› በማለት እንደገነገረው መጽሐፈ ስንክሳር ይጠቅሳል፡፡

ከዚህም በኋላ በንጉሥ ኔሮን ፊትም ቀርቦ በቆመ ጊዜ ንጉሡ ‹‹በሥራይህ ሕዝቡን የምታስት እስከ መቼ ነው?›› ብሎ ጠየቀው፤ ቅዱስ ሉቃስም ‹‹እኔ ለሕያው #እግዚአብሔር ልጅ ለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም›› ብሎ መለሰለት፡፡ ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው፤ ‹‹እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይህች እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ በቆረጡትም ጊዜ ‹‹ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ ዕወቅ፤ ነገር ግን የ #ጌታዬና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት፤ ከዚህም በኋላ ለያት፤ በዚያም የነበሩ አደነቁ፤ የሠራዊቱም አለቃና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ፤ ቁጥራቸውም ዐራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ፡፡ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ በማዘዙ ቆረጡአቸው፤ የምስክርነት አክሊልም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ያረፈው በ፹፬ ዓመቱ ነው፡፡

ከዚህም በኋላ ሥጋውን በማቅ አይበት ውስጥ አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት፤ በአማረ ቦታም አኖሩት፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ አማላጅነት፣ ተረዳኢነትና በረከት አይለየን፤ አሜን!

(ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_22)
#ጥቅምት_24

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ አራት በዚህች ዕለት #የቅድስት_ጸበለ_ማርያም መታሰቢያዋ ነው፣ መስተጋድል መነኰስ #ቅዱስ_አባ_አብላርዮስ ያረፈበት ቀን ነው፣ የመፍቀሬ ነዳያን #አባ_ዘግሩም ዓመታዊ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ጸበለ_ማርያም

በዚህች ዕለት ታስባ የምትውለውንና #ጌታችን በደሃ ሰው ተመስሎ ተገልጦ ቁራሽ እንጀራ የለመናትን በኋላም በጀርባዋ አዝላ የሸኘችው ቅድስት ጸበለ ማርያም እረፍቷ መስከረም ፲፰ ቀን ነውና ጥር ፲፰ ቀንም በዓል ነው። እርሷም በጎኗ ተኝታ የማታውቅ፣ በ #ጌታችን ፵ ጾም ወራት ከሰንበት በቀር ምንም የማትቀምስ፣ ነብሮች የእግሯን ትቢያ ይልሱላት የነበረች ታላቅ ኢትዮጵያዊት ቅድስት ናት። ይኽችውም ከነቢያት፣ ከሐዋርያትና ከሰማዕታት ዕድል የተሰጣት እናት ናት፡፡ ከደናግል መነኮሳትም ዕድል ተሰጣት መነኩሲትም ድንግልም ናትና፡፡

እናታችን ቅድስት ጸበለ ማርያም፡- ቅድስት ጸበለ ማርያም ትውልዷ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ቀሐ አካባቢ ነው፡፡ ወላጆቿ አባቷ እንድርያስና እናቷ መስቀል ክብራ ፈሪሃ #እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እያስተማሩ በሃይማኖት በምግባር ኮትኮተው አሳደጓት፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ተከስተ ብርሃን የተባለ ደገኛ ባሕታዊ ወደ አባቷ ቤት መጥቶ ባደረበት #መንፈስ_ቅዱስ ኀይል የቅድስት ጸበለ ማርያምን ጸጋ አወቀ፡፡ ለወላጆቿም "ይኽቺ ልጅ ወደፊት ነፍሳት የሚድኑባት የከበረች ትሆናለች" ብሎ በእርሷ ላይ ትንቢት ተናገረ፡፡

ቅድስት ጸበለ ማርያም ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ ወላጆቿ በጋብቻ ሕግ እንድትወሰን ፈለጉ፡፡ ነገር ግን ቅድስት ጸበለ ማርያም "ቅዱስ ጳውሎስ ለ #እግዚአብሔር አጭቶኛልና ፈጣሪዬን በድንግልና ለማገልገል ተስያለሁ" በማለት ተቃወመቻቸው፡፡ ወደ አንድ ደገኛ ባሕታዊም ዘንድ ሄዳ በጸሎቱ ከዚህ ነገር እንዲያድናት ተማጸነችው፡፡ እርሱም ፈቃደ #እግዚአብሔርን በጸሎት ከጠየቀላት በኋላ ማድረግ የሚገባትንና ወደፊት የሚገጥማትን ሁሉ ነገራት፡፡ እርሷም ለዕጣን እንዲሆን ጌጧን ሁሉ አውጥታ ሸጠችና "መሥዋዕቴን አሳርግልኝ" ብላ ለባሕታዊው ሰጠችው፡፡ እርሱም ከጸለየላት በኋላ የጸሎቱን ምላሽ ነገራት፡፡

ወለጆቿም ያለፈቃዷ በሕግ ቢያጋቧትም ቅድስት ጸበለ ማርያም ግን በሌሊት ማንም ሳያያት ከጫጉላ ቤት ወጥታ ሄዳ በልዳው ፀሐይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ወደተሠራች ቤተክርስቲያን ሄዳ እያለቀሰች ጸሎት አደረገች፡፡ #እመቤታችንም ከሚካኤል ወገብርኤል እንዲሁም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተገለጠችላትና እንዲጠብቋት ነገረቻቸው፡፡ ቤተሰቦቿም እንዳያዝኑባት ፈርታ ተመልሳ ወደ ባሏ ዘንድ ብትገባም ባሏ በግብር እንዳያውቃት መላእክቱ ይጠብቋት ነበር፡፡ ባሏንም ሰውነቷ እንደእሳት ያቃጥለው ነበር፡፡ እርሱም አእምሮውን ከሳተ ከ3 ቀን በኋላ ሲነቃ የደረሰበትን ለቤተ ዘመዶቹ ባስረዳቸው ጊዜ "ከገዳም የመጣች ከሆነች ለእኛ ልትሆን አይገባም" አሉና አስጊጠውና ሸልመው መልሰው ወደ ቤተሰቦቿ ላኳት፡፡

አባቷም ዳግመኛ ወደ ባሏ እንድትመለስ በማስገደድ ብዙ አሰቃቂ ግርፋት ቢገርፋትም በተአምራት ምንም እንዳላገኛት ሆነች፡፡ ከዚኽም በኋላ ወጥታ ወደ ምድረ በዳ ሄደች፡፡ ወደ ገዳምም ሄዳ ዋሻ ውስጥ ገብታ ስትጸልይ አድራ አረፍ ስትል ነብር መጥቶ የእግሯን ትቢያ ይልሳት ነበር፡፡ ከዚያም ወጥታ ንህበት ወደሚባል ሀገር መጥታ ቶማስ ከሚባል መነኩሴ ጋር በታላቅ ተጋድሎ ኖረች፡፡ ቆማ ስትጸልይ እንባዋ መሬቱን ያርስ ነበር ነገር ግን ሰው እንዳያውቅባት አፈር በላዩ ትጨምርበታለች፡፡ በአንድ ዕለትም በቤተክርስቲያን ቆማ ስትጸልይ በሁለቱ ማዕዘን የተቀበሩ ምውታን ሲጮኹ ሰማቻቸው፣ እነርሱ ግን በሲኦል ነበሩ፡፡ ጩኸታቸውንም በሰማች ጊዜ በእንባዋ ላይ እንባን በጸሎቷም ላይ ጸሎትን ጨምራ ስለ እነርሱ ለመነች፡፡ ስለእነርሱም ሱባኤ ያዘች፡፡ በባሕርይው ቸርና ይቅርባይ የሆነ ልዑል #እግዚአብሔርም ጸሎቷን ሰምቶ እነዚያን ነፍሳት ማረላት፡፡

ቅድስት ጸበለ ማርያም በምግባርና በትሩፋት በጾም በጸሎት ጸንታ ከኖረች በኋላ የምንኩስና ቀንበርን ትሸከም (በምናኔ ትኖር) ዘንድ በብሕትውና ወደሚኖረው ታላቁ አባት ወደ አቡነ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ ዘንድ ሄደች፡፡ እርሱም ማኅሌተ ጽጌን ከአባ ጽጌ ድንግል ጋር የደረሰው ነው፡፡

አቡነ ገብረ ማርያምም ካስተማራትና በኋላ አመነኮሳትና ስሟን "ጸበለ ማርያም" ብሎ ሰየማት፡፡ ከዚኽም በኋላ ተጋድሎዋን እጅግ በማብዛት ትሕርምትን ገንዘብ አደረገች፡፡ ከዕንጨት ፍሬዎች ውጭ የማትመገብ ሆነች፡፡ በተቀደሰችው የ #ጌታችን ፵ ጾም ወራት ግን ከሰንበት በቀር እርሱንም ፈጽሞ አትቀምስም፣ እስከ ፋሲካም ድረስ ከበዓቷ ስለማትወጣ ማንም አያያትም ነበር፡፡ ከመነኮሰችም ጊዜ ጀምሮ በጎኗ ተኝታ አታውቅም፡፡ ባመማት ጊዜም ተቀምጣ ታንቀላፋ ነበር፡፡ በውርጭ ቅዝቃዜ መከራን እየተቀበለች በባሕር ውስጥም ቆማ እየጸለየች ታድራለች፡፡ በስግደቷም በቀን እስከ 8 እልፍ ትሰግድ ነበር፡፡ ከወንድሟ ቶማስም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ተማረች፡፡ የዮሐንስን ወንጌልና የራእዩን መጽሐፍ ዘወትር በማንበብ ትጸልያለች፡፡ የ #እመቤታችን በዓል በሆነ ጊዜ አርጋኖን ውዳሴዋን በቀን ሦስት ጊዜ ታነባለች፣ አንቀጸ ብርሃንንም በየሰባቱ ጊዜ ትጸልያለች፡፡ የዳዊትንም መዝሙር በፈጸመች ጊዜ የ #ጌታችንን መከራ ግርፋት እያሰበች ራሷን ሺህ ጊዜ ትገርፋለች፡፡ ዳግመኛም አገዛዛቸው መልካም ይሆን ዘንድ ስለ ጳጳሱና ስለ ንጉሡ አንድ አንድ ሺህ ጊዜ፣ ስለ መነኮሳትም ሺህ ጊዜ፣ ስለኃጥአንም ሺህ ጊዜ ራሷን ትገርፋለች፡፡ ዳግመኛም ነጭ ዕጣን በእጇ ይዛ ሰባት ቀን እስኪሆን ድረስ ዕንባዋን ታፈስበታለች፣ ያም ነጭ ዕጣን ከዕንባዋ ብዛት የተነሣ ጥቁር ይሆናል፡፡ በዓል በሚሆንበት በሰባተኛው ቀን አስቀድማ ዐውቃ በመሠዊያ ያሳርገው ዘንድ ያን ዕጣን ለቄሱ ትሰጠዋለች፡፡ #እግዚአብሔርም እንደሱራፌል የጽናሕ መዐዛና እንደኪሩቤል ዕጣን ሽታ አድርጎ ከቄሱ እጅ ሲቀበል በግልጽ ታያለች፡፡

ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ቅድስት ጸበለ ማርያም እየጸለየች ሳለ የክብር ባለቤት #ጌታችን_አምላካችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በቆሰለ ችግረኛ ደሃ ሰው ተመስሎ ለቅድስት ጸበለ ማርያም ተገልጦ ወደ እርሷ በመምጣት ቁራሽ እንጀራ ለመናት፡፡ እርሷም ፈጥና ይዛ መጥታ ሰጠችው። እንጀራውንም ተቀብሎ ሲያበቃ "በመንገድ ብዛት ደክሜአለሁና በጀርባሽ አዝለሽ ትሸኚኝ ዘንድ እወዳለሁ" አላት፡፡ እርሷም ለድሆች አዛኝ ናትና አዝላው የድንጋይ መወርወሪያ ያህል እንደወሰደችው ቁስሉ ይድን ጀመር፡፡ ወዲያውም ቁስሉ ድኖ ምንም እንዳላገኘው ፍጹም ደህነኛ ሰው ሆነ፡፡ ያንጊዜም ፊቱ እንደፀሐይ አበራ፣ ሁለንተናውም ተለወጠ፡፡ የክብር ባለቤት #ጌታችን ከጀርባዋ ወርዶ በፊት ለፊቷ ቆመና "የከበርሽ አገልጋዬ ጸበለ ማርያም ሆይ! ምን እንዳድርግልሽ ትወጃለሽ?" አላት፡፡ እርሷም ከድንጋጤዋ የተነሣ እንደበድን ሆና መሬት ላይ ወደቀች፡፡ #ጌታችንም አበረታትና እጇን ይዞ አነሣትና "የልብሽን መሻት ለምኚኝ" አላት፡፡ እርሷም "አምላኬ ሆይ! በፊትህስ ሞገስ ካገኘሁ በሲኦል ያሉ ነፍሳትን ይቅር በላቸው" አለችው፡፡ በዚኽም ምክንያት በ #ጌታችን ቸርነትና በእርሷም አማላጅነት ብዙ ነፍሳት ከሲኦል ወጡ፡፡ #ጌታችንም ሰላምታ ሰጥቷት በክብር ዐረገ፡፡
ዳግመኛም #ጌታችን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ሦስት በትሮችን ሰጥቷት በእነርሱ እየተመረኮዘች እስከሲኦል ድረስ ትሄድና ነፍሳትን ታወጣና ታስምር እንደነበር ራሷ ተናገረች፡፡ ዳግመኛም ስትናገር "ሰማያውያን ብዙ ስሞች አወጡልኝ፣ 'የወይን ፍሬ' እያሉ ይጠሩኛል፣ 'የበረከት ፍሬ' የሚሉኝም አሉ፣ 'የገነት ፍሬም' ይሉኛል" አለች፡፡ ዳግመኛም ከልዑል ዘንድ ብዙ ጸጋዎች እንደተሰጣት በሕይወት ሳለች ለአንደ ደገኛ ቄስ ነገረችው፡፡

ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አምላክን በድንግልና የወለደች ክብርት #እመቤታችን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ተገለጠችላትና "ስሜን የተሸከምሽ ጸበለ ማርያም ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን" አለቻት፡፡ #እመቤታችንም ብዙ ምሥጢርን ከነገረቻት በኋላ ጡቶቿንም አጠባቻትና በጸጋ የከበረች አደረገቻት፡፡ በስሟም ብዙ ተአምራትን የምታደርግ ሆነች፡፡

ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም ከነቢያት፣ ከሐዋርያትና ከሰማዕታት ዕድል የተሰጣት እናት ናት፡፡ እንደነቢያት የሚመጣውን ሁሉ እንዳለፈ አድርጋ ትናገራለች፡፡ ዳግመኛም የትምህርታቸውን ፍለጋ ስለተከተለችና ለሕጋቸው ስለተገዛች ከሐዋርያት ጋር ዕድል ተሰጣት፡፡ ሦስተኛ ግድ ሳይሏት በፈቃዷ ስለተቀበለቻቸው ግርፋቶቿና ስላገኛት መከራ የሰማዕታት ዕድል ተሰጣት፡፡ ከደናግል መነኮሳትም ዕድል ተሰጣት መነኩሲትም ድንግልም ናትና፡፡ ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም መልካም የሆነውን ተጋድሎዋን ከፈጸመችና #ጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን ከገባላት በኋላ በሰላም ዐርፋለች፡፡ እንደ ንግሥት ዕሌኒም የሞቷን #መስቀል ተሸክማ ተጠብቆላት ወዳለ ተስፋዋ በክብር ሄደች፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ጸበለ ማርያም ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_አብላርዮስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን መስተጋድል መነኰስ አባ አብላርዮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ጋዛ ከሚባል አገር ነው ወላጀቹም አረማውያን ናቸው የዮናናውያንንም ትምህርታቸውንና ፍልስፍናቸውን አስተማሩት ሰውነቱ ለጥበብ ማደሪያዋ እስከሆነ ድረስ በዕውቀቱ ከጓደኞቹ በላይ ሆነ።

ከዚህም በኋላ ከሀገሩ የሌለ መልካም የሆነ ጥበብን ከውጭ አገር መማርን ወዶ ተነሥቶ ወደ እስክንድርያ ሀገር ሔደ መምህራንም ሁሉ ከሚኖሩበት ቦታ ገብቶ ከእሳቸው ዘንድ ብዙ ትምህርትን ተማረ በዚያንም ጊዜ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ለመማር ተነሣሥቶ ቸኰለ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት ብዙዎቹን አነበበ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስም ይተረጕምለትና ያስረዳው ነበር።

ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አምኖ የክርስትናን ጥምቀት ተጠመቀ ከዚያም መንኵሶ በምንኵስና ሕግ ጸንቶ ገድልን ተጋደለ ወደ አባ እንጦንዮስም ሔዶ መንፈሳዊ የሆነ የትሩፋትን ሥራ እየተማረ በእርሱ ዘንድ ብዙ ወራት ኖረ።

ወላጆቹም እንደሞቱ በሰማ ጊዜ ሒዶ የተዉለትን ገንዘባቸውን ሁሉንም ወስዶ ለድኆችና ለችግረኞች መጸወተ ከዚህም በኋላ ከሶርያ ገዳማት ወደ አንዱ ገዳም ገባ በዚያም በጾም በጸሎት በስግደት በመትጋት ፍጹም ገድልን ተጋደለ በየሰባት ቀን እስቲመገብ ድረስ ምግቡም የዱር ሣር ነበር።

#እግዚአብሔርም ሀብተ ትንቢትን ሰጥቶት ልቡናው ብሩህ ሆነ ድንቆች ተአምራትንም የሚያደርግ ሆነ ኤጲፋንዮስንም ያመነኰሰውና ለደሴተ ቆጵሮስም ኤጲስቆጶስ እንደሚሆን ትንቢት የተናገረለት እርሱ ነው።

የዚህም አባት መላ ዕድሜው ሰማንያ ዓመት ነው ከክርስትናውና ከምንኵስናው በፊት ዐሥራ ሰባት ዓመት በምንኵስናም ስልሳ ሦስት ዓመት ነው ክብር ይግባውና #እግዚአብሔርንም ካገለገለ በኋላ በሰላም አረፈ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም አመስግኖታል ሁለተኛም ቅዱስ ባስልዮስ በመጻሕፍቱ አመስግኖታል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#መፍቀሬ_ነዳያን_አባ_ዘግሩም

ዳግመኛም በዚህች ቀን የመፍቀሬ ነዳያን አባ ዘግሩም ዓመታዊ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡ አባታቸው ገርዜነ ጸጋ የተባለ ደገኛ ካህን ሲሆን እናታቸው ደግሞ ነፍስተ እግዚእ ትባላለች፡፡ እነዚህም ደገኛ ክርስቲያኖች በ #እግዚአብሔር ሕግ ጸንተው ብዙ ዘመን ሲኖሩ የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ #እግዚአብሔርን ይለመኑት ነበር፡፡ ልዑል #እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ የተባረከ ልጅ እንደሚወልዱ አበሰራቸው፡፡ አባ አብርሃምም በመልአኩ ብሥራት ግንቦት ሃያ አራት ቀን በተወለዱ ጊዜ ወላጆቻቸው ብርሃነ መስቀል ብለው ጠሩት፡፡ በኋላ የተጠራበት ስመ ጥምቀቱ ግን ማኅፀንተ ሚካኤል ነው፡፡ ወላጆቹም በመንፈሳዊ አስተዳደግ ስላሳደጉት ከልደቱ ጀምሮ ጸጋ #እግዚአብሔር አደረበት፡፡ በ #መንፈስ_ቅዱስ አደገ፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያንም መሄድን አላስታጎለም፡፡ እንደ ነቢዩ ሳሙኤል ከታናሽነቱ ጀምሮ በ #እግዚአብሔር ቤት አድጓልና፡፡

አድጎ ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን፣ መጻሕፍተ ነቢያትን፣ መዝሙረ ዳዊትን ይማር ዘንድ አባቱ ለመምህር ሰጠው፡፡ ሕፃኑም በትምህርቱ አስተዋይ ሆነ፡፡ ሳያቋርጥ ሁልጊዜ ከመምህሩ መረዳትን ያበዛ ነበር፡፡ በ #መንፈስ_ቅዱስም ኃይል የጸና ሆነ፡፡ ዲቁናም ከተሾመ፡፡

ከዚህም በኋላ እናቱና አባቱ ያለ ፈቃዱ ሚስት ያጩለት ዘንድ ወደዱ፡፡ በመጽሐፍ ‹‹የልጅ ልጅህን ታያለህ፣ አንተ ብፁዕ ነህ፣ መልካምም ይሆንልሃል›› የሚል በመጽሐፍ ተጽፏልና፡፡ ስለዚህም ያጋቡት ዘንድ አቻኮሉት፤ እርሱ ግን ዓለመን ፍጹም ንቆ በምንኩስና በተጋድሎ መኖርን ወደደ፡፡

ለምንኩስናም ስሙ አባ ክርስቶስ ይባርከነ ወደተባለ አንድ መነኩሴ ወዳለበት ገዳም ሲሄድ በመንገድ መደራ በተባለች ቦታ በታላቅ ገዳም ውስጥ ከእንግዶች ጋር አደረ፤ በሌሊት በነቃ ጊዜ አንድ ድኃ በዚያች ቤት ውስጥ አገኘ፤ የድኃውን ልብስ ወስዶ የእርሱን ልብስ ሰጥቶተ በሌሊት ወጥቶ መንገዱን ሔደ፡፡ በነጋም ጊዜ ያ ድኃ ያደረገለትን ለሰዎቹ ተናገረ፡፡ ‹‹በእንግዳ ማደሪያ ከእኔ ጋር አብሮ ያደረ አንድ ሰው እኔ የለበስሁትን ልብስ ወስዶ የእርሱን መልካም ልብስ ተወልኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹… የ #እግዚአብሔር ሰው ነውና መልካም ሥራ አደረገልህ አንተ ግን ሔደህ ስለ እርሱ ጸልይለት›› አሉት፡፡

አባ አብርሃም ግን ከአባ ክርስቶስ ይባርከነ ከቀድሞ ቤቱ በደረሰ ጊዜ በዚያም አላገኘውም፤ ውኃ ከሌለበት፤ ፀጥታ ከሰፈነበት ምድረ በዳም ሔደ፡፡ የፀሐይ ወቅት ነበረና በዚያ ሲመላለስ ሳለ ውኃ ጥም ያዘው፡፡ ያን ጊዜም በገዳሙ ውስጥ ባዶ ወጭት አገኘና በፊቱ አስቀምጦ ወደ #እግዚአብሔር በጸለየ ጊዜ ወዲያው ብዙ ዝናም ዘነመ፤ በወጭቷም አጠራቀመና እስኪበቃው ድረስ ከእርሷ ጠጣ፡፡ ከዚያም አባታችን ክርስቶስ ይባርከነን አገኘውና ሊያደርግ የሚፈልጋቸውን ምሥጢሩን ሁሉ ነገረው፡፡ የ #እግዚአብሔር መልአክ መጥቶ አባታችንን ‹‹…በደመና ተጭነህ ወደ ዳሞት አገር ሂድ›› አለው፤ አባታችንም በደመና ተጭኖ ፍራጽ ከተባለ ገዳም ደረሰ፤ በዚያም ምድርን ባረኮ ውሃ አፈለቀ፤ መልአኩም ወደ ቀኝህ ተመልከት አለው፡፡ ወደ ቀኙ ሲያይ ዐደልን ብርሃን ከቧት ተመለከተ፤ ዕፅዋትም ጭፍቅ ያሉ ነበሩ፤ አባ ዘግሩምም ይህች ቦታየ ናት አለ፤ የጻሕናንን ምድር እየባረከም ይሄድ ዘንድ ወደደ፡፡ ብዙ ውሃ አፈለቀ፤ ዐደልም ደረሰ፤ በዚያም ውሃ አፈለቀ፤ አባታችን ዘግሩም ወደ ውስጧ ገባ በዚያም ተቀመጠ፣ የገዳሙ አራዊትም በዚህ ተደሰቱ፡፡ ሙሴ ጽላትን እንደተቀበለ ሁሉ ጥቅምት ሃያ አራት ቀን የ
#እግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ አመጥቶ የብርሃን #መስቀልና#መድኃኔዓለምን ታቦት ሰጠው፡፡ ዳግመኛም የ #እግዚአብሔር መልአክ የተዘጋጀ ኅብስትና የተቀዳ ጽዋን፤ ለመሥዋዕት የሚሆነውንም ሁሉ ሰጠው፤ አባታችንም ከካህናት ጋር በዚያች ቤተ ክርስቲያን ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሰጣቸው፡፡

በቤተ ክርስቲያን አጠገብ አንዲት የዋንዛ ዛፍ ነበረች፤ ሕዝቡም ይሰበሰቡባትና በሥሯ ተቀምጠው ክፉ ሥራ ይሠሩ ነበር፤ አባታችንም ‹‹ለምን እንዲህ የማይገባ ሥራ ትሠራላችሁ? ሲላቸው እነርሱ ግን አልሰሙም፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችንም ያቺን ዛፍ ‹‹ከበታችሽ ካሉት ሕዝብ ጋር ተነሥተሽ ሒጂ›› ብሎ በቃሉ አዘዛት፡፡ ያን ጊዜም ያች ዛፍ ከሕዝቡ ጋር ተነሥታ የሁለት ጦር ውርወራ ያህል ሔደች፡፡ #ጌታችን በቅዱስ ወንጌሉ ‹‹የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ቢኖራችሁና ይችን ሾላ ተነስተሽ ወደዚህ ነይ ብትሏት ትመጣለች፤ ይህን ተራራ ከዚህ ሂድ ብትሉት ይሄዳል›› እንዳለ አባታችን አባ ዘግሩምም ይህንን አደረጉ፡፡

ከአባታችን ይባረኩ፤ እጅ ይነሡም ዘንድ አርባ አራት ቅዱሳን በደመና ተጭነው አባታችን ካለበት ቦታ ወደ ዐደል መጡ፡፡ ሶምሶን ከአህያ መንጋጋ፤ ሙሴ ከዐለት ውሃ እንዳፈለቁ ሁሉ ለሚያስፈልጋቸው ነገር ይጠቀሙበት ዘንድ አባታችንም በጸሎቱ በአንድ ጊዜ አርባ አራት የውሃ ምንጮችን አፍልቆ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ይህን አይተው አደነቁ፤ ስምህ ዘግሩም ይሁን አሉት፤ ስለዚህም አባታችን አባ ዘግሩም ተባለ፤ ምንጮቹም ድውያንንና ሕሙማንን የሚፈውሱ ሆኑ፡፡

ዳግመኛም ለአባታችን የሚገለገልበት አንድ አህያ ነበረው፤ የሚጭነው ሰው ሳይከተለው ለሁለት ቀናት ሔዶ ወደ ጫነው ሰው ቤት ይመለስ ነበር፤ የአገሩ ሰዎችም ይህን አይተው ያላቸውን ሁሉ ይጭኑትና ብቻውን ሔዶ ወደ አባታችን ይመለስ ነበር፡፡

የአቡነ ብርሃነ መስቀልን ተአምራቱን ዜናውን በሰማ ጊዜ ከንጉሡ ባለሟሎች አንዱ መጣ፡፡ ሌላም በቤቱ አጠገብ የሚኖር አንድ ሰው መጣና ‹‹ጨው ጭኜ ወደ ገበያ እወስድበት ዘንድ አህያህን ስጠኝ›› ብሎ ለመነው፡፡ የተቸገሩትን ለመርዳት የሚልከው አንድ አህያ ነበረውና አባ አብርሃምም ‹‹የጨው መጠን ምን ያህል ነው?›› አለው፡፡ ያ ሰውም ‹‹በሰቅል ስሳ ይሆናል›› አለው፡፡ አባታችን አብርሃምም ‹‹ውሰደው ከተናገርኸው በላይ ግን አትጫነው›› አለው፡፡ ሰውየውም አህያውን ወስዶ አባታችን እንዳለው ጫነው፤ ለአባታችን ያልነገረውን በቤቱ የተረፈውን ግን ያ ሰውና ወንድሙ ተሸከሙት፡፡ እነርሱም ተካፍለው ተሸክመው መንገዳቸውን እየሄዱ ሳለ ከአገር ብዙ በራቁ ጊዜ ወንድሙን ‹‹ና አህያውን እንጫነውና እንደፈቀድነው እንሒድ የሚያየን የለምና›› አለው፡፡ በዚሀመ ምክራቸው መሠረት ተሸክመውት የነበረውነ በአህያው ላይ ጫኑት፡፡ ነገረ ግን አህያው መንቀሳቀስን ፈጽሞ እምቢ አለ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም፤ ሲገፉትና ሲደበድቡት ብዙ ደከሙ፤ እንዲህ እያደረጉ ሳሉ አንድ አገልጋይ የንጉሥ መልእክት ይዞ መጣ፡፡ እኒህን ስሕተተኞችም አገኛቸውና ‹‹ጌቶቼ ለምን ትደክማላችሁ?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ይህ አህያ አልሄድም አለን›› አሉት፤ የንጉሡ መልእክተኛም #መንፈስ_ቅዱስ አነሳሳውና ከፊታቸው ቆመና ‹‹የዚህ ነገር ምክንያቱ ምንድን ነው?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ይህን አህያ ከአንድ #መንፈስ_ቅዱስ ካደረበት ቀሲስ አመጣነው፤ በዚህ ቀሲስ ቃል ላይ በጨመርን ጊዜ መሔድን እምቢ አለን›› በማለት የሠሩትን ነገሩት፡፡ ‹‹እስኪ የጨመራችሁትን ቀንሱለት›› አላቸው፤ ቀነሱለትና ያን ጊዜ አህያው ተነሥቶ እነርሱም ወደሚፈልጉበት ቦታ ሔዱ፡፡ ይህንንም ሁለት ጊዜ ሦስት ጊዜ ደጋግመው አደረጉ እምቢም አላቸው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የቅዱሱን ቃል በመተላለፋቸው እንደሆነ አወቁ፤ ያም የንጉሡ አገልጋይ ተደንቆ ‹‹ኑ ይህ ቅዱስ ካለበት አድርሱኝ›› አላቸው፡፡ አባታችን ካለበት ቦታም ደርሶ ከእርሱ ዘንድ ተባረከ፡፡

ያም አህያውን የወሰደው ሰው ከአቡነ ብርሃነ መስቀል እግር ሥር ተንበርክኮ ‹‹በፊትህ በድያለሁና ቃልህንም አሳብያለሁና አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ፤ አህያውም መሄድን እምቢ አለ፤ የጨመርንበትን ሸክም በቀነስንለት ጊዜ ግን ይሄዳል›› አለው፡፡ ዳግመኛም ‹‹…እኔ ግን እንደ እኔ አይነት ሰው ነህ መስሎኝ ቃልህን አፈረስሁ፤ አንተ ግን በፍቅርህ ገመድ ሳብኸኝ›› አለው፡፡ አባታችን ብርሃነ መስቀልም ‹‹ለምን ሐሰት ተናገርህ? መጽሐፍ ‹ሐሰት የኀጢአት መጀመሪያ ናት፤ ሐሰተኞችም የ #እግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም› ይል የለምን?›› በማለት ከመከረው በኋላ በሰላም ወደቤቱ እንዲሔድ ነገረው፡፡

ያም ሰው ከአቡነ ብርሃነ መስቀል ዘንድ ወጥቶ መንገዱን ሔደ፤ ያ የንጉሡ መልእክተኛም አብርሃም ከተባለ ከአቡነ ዘግሩም ዘንድ ተባርኮ ወጣ፤ የቤተ ክርስቲያኗንም አሠራር አይቶ የአባታችን የአብርሃምን ተአምር አደነቀ፤ የንጉሡን ትእዛዝ ይፈጽም ዘንድም መንገዱን ሄደ፡፡ ከብዙ ቀናት በኋላ ያ መልእክተኛ ከንጉሡ ዘንድ ደረሰ፤ ስመ መንግሥቱ ቆስጠንጢኖስ ለተባለ የ #እግዚአብሔር ወዳጅ ለሆነ ለንጉሥ ዳዊት ነገሩን ነገረው፡፡ ‹‹ጻድቅ ንጹሕ የሆነ ቀሲስ አለ፤ በዚህ ዘመን በመንግሥትህ ሀገር ሁሉ እንደርሱ ያለ ሰው የለም፤ ሥራው ሁሉ እንደቀደሙት አባቶች ነውና›› አለው፡፡

በዐይኑ ያየውን፤ በጆሮው የሰማውን ሁሉ ስለሠራት ቤተ ክርስቲያንም ነገረው፤ ንጉሡም ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ በልቡ ተደሰተ፤ በመንፈሱም ሐሴትን አደረገ፤ #እግዚአብሔርንም አመሰገነው፤ እንዲህም አለ፡- ‹‹በዘመነ መንግሥቴ የተሰወረውን የሚያውቅ፤ ተአምራትን የሚያደርግ እንዲህ ያለ ጻድቅ ሰውን የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ #እግዚአብሔር ስሙ ይክበር፡፡ አባቴ ቤተ ክርስቲያን ማነጽ በፈለግህ ጊዜ ወደ እኔ ለምን አልላክህም ብሎ ላከበት፤ እኔ ከደቀ መዛሙርትህ እንደ አንዱ አይደለሁምን በረከትህን በተቀበልሁ ነበር አለ፡፡ በዚህ የመንግሥት ዙፋን ላይ ያለሁ በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ነው እንጂ በራሴ ፈቃድ ይመስልሃልን በእስረኞች መካከል ሳለሁ ከእስረኞች መካከልም ተኝቼ ሳለ ከዚያ አውጥቶ በአባቶቼ በሰይፈ አርዕድና በዐምደ ጽዮን ዙፋን ላይ አስቀመጠኝ፡፡ አንተ ግን በኀጢአቴ አትናቀኝ፤ ለቤተ ክርስቲያን የምትፈልገውን ይህን ገንዘብ ውሰድ፡፡›› ዳግመኛም ለአባታችን ልብስ ላከለት፤ ሚስቱም እንዲሁ ላከች ‹‹በጸሎትህ አትርሳን›› አሉት፡፡

ከዚህም በኋላ ይመነኩስ ዘንድ ወደደ፤ የመላእክትና የቅዱሳን ልብስ የምትሆን የምንኩስና ልብስን ያለብሰው ዘንድ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ረድእ ወደ ሆነው ወደ አባ ብሶይ መጣ፡፡ ወደ እርሱ ደርሶ ሥርዐተ ምንኩስና ከፈጸመለት በኋላ አባታችን አብርሃም ‹‹የቀድሞ ስሜን ተውልኝ›› አለው፤ አባ ብሶይም ‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን ስም እንደ ለወጠላቸው ስምህን እለውጣለሁ እንጂ አይሆንም›› አለው፡፡ ‹‹ስምህንም አብርሃም፣ ጳውሎስ፣ ዮሐንስ ከሚሉት መካከል ዕጣ በማጣጣል እሰይምሃለሁ›› አለው፡፡

ሦስት ጊዜም ዕጣ ጣሉ፤ አብርሃም የሚለውም ስም ወጣ፤ ይህ ነገር ከ #እግዚአብሔር እንደሆነ አወቀ፡፡ ከታናሽነቱ ጀምሮ የአብርሃም ምግባር የሆነውን እንግዳ መቀበልን፣ እግር ማጠብንና የተራበውን ማብላት ጀመረ፤ ስለዚህ አብርሃም መባል ተገባው፡፡ ‹‹ከታናሽነቴ ጀምሮ የአብርሃምን ሃይማኖት እንደወደድሁ፣ እንግዳ በመቀበል እንደ ኖርሁ ይህን ስም የሰጠኝ #እግዚአብሔር ይመስገን›› አለ፡፡ መንኩሶ በፈቃዱ አብርሃም ተብሎ ተጠርቷልና በብዙ ገድልና በትሕርምት በዚያች ቦታ ኖረ፡፡
የነዳያን ፍቅር በልቡ ውስጥ አለ፤ ሁል ጊዜ ስለ ምግባቸውና ስለ ልብሳቸው ያስብ ነበር፤ ለሚያስፈልጋቸው ነገርም ገንዘብ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ለድኆች ልብሱን ያካፍላል፤ ለእነርሱም ሰጥቶ እርሱ ራቁቱን ይቆማል፤ ልጆቹም ይመጣሉ፤ ‹‹ልብስህ ወዴት ነው?›› ይሉት ነበር፤ እርሱም ‹‹ሌቦች በማያገኙበት ቦታ አለ›› ይላቸው ነበር፡፡ ልጆቹ ግን ሥራውን አያውቁም ነበር፤ ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንበት ሁሉን ይሠውር ነበር፤ አይገልጥላቸውም ነበር፤ ድኃ ባየ ጊዜ አጽፉን ይሰጥ ነበር፤ አጽፉን ይቅርና ምንም ልብስ አያስቀርም ነበር፡፡

አንድ ቀን አንድ ድኃ መጥቶ ስለ #እግዚአብሔር ስም ምግብና ልብስ ለመነው፡፡ አባታችን ያን ድኃ ባየው ጊዜ አጽፉን ሰጠው፤ ዳግመኛ አንድ ድኃ መጣ፤ በቤቱም የሚሰጠውን አጣ፤ መጠምጠሚያውን አውርዶ እርሷንም ለድኃው ሰጠውና በቤቱ ተቀመጠ፡፡ አንድ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ መጥቶ ራቁቱን አገኘውና ተቆጣበት፤ ‹‹ክቡር አባቴ ሆይ! ለምን እንዲህ ትሆናለህ? አለው፡፡ ‹‹ለምትበላውና ለምትለብሰው ሳታስቀር ያለ አቅምህ ለምን ምጽዋት ትሰጣለህ? ልብስህንና መጎናጸፊያህን ሰጥተህ አንተ ራቁትህን ትሆናለህ፡፡›› አባታችንም ‹‹ልጄ ሆይ! ፈጽሞ ስለሚያረጅና ስለሚጠፋ የዚህ ዓለም ልብስ ፈንታ የብርሃን መጎናጸፊያ የሚያለብሰኝ አምላኬ አለልኝ›› አለ፤ ልጆቹም ሌላም ልብስ አምጥተው አለበሱ፡፡ ‹‹ይህንም እንደ ቀደመው አታድርግ›› አሉት፤ እርሱ ግን ስለ ድኆችና ስለ ችግረኞች ፍቅር ብዙ ጊዜ ምጽዋት ያደርግ ነበር፤ ቅብዓት በሰውነት፣ ውሃ በአንጀት እንዲገባ የነዳያን ፍቅር ወደ ልቡ ገባ፡፡

የነዳያንን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ከልቡ ደስታ የተነሣ ለመነሣት ይፈልጋል፤ ከማእድ ላይ ቢሆንም እንኳን ድምፃቸውን ከሰማ እጁን ወደ ማእድ አያወርድም ነበር፤ ይሰጣል እንጂ ምንም ነገር አያተርፍም ነበር፡፡ ነዳያን ግን ዘወትር ጩኸትና ልመናን አያቋርጡም ነበር፤ አባታችን ስለ ምግባቸውና ስለ ልብሳቸው እንደሚያስብ አውቀው ከቤቱ አይርቁም ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ወደ አንዲት ታላቅ ሀገር ሔዶ ከዚያ ደረሰ፤ በሰንበት ምሽት ለእሑድ አጥቢያ ከዚያ አደረ፤ ሥርዓተ ቁርባን ከተፈጸመ በኋላ ደቀ መዝሙሩን ‹‹ልጄ የምንበላው ነገር አለህ ወይስ የለህም?›› አለው፤ ያ ደቀ መዝሙርም ‹‹አባቴ አዎን አለኝ›› አለው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ያያቸውን ታላላቅ መነኮሳት ሰበሰበ፤ ቁጥራቸውም ዐራት መምህራን ነበሩ፡፡ የተዘጋጀ ምግብና ጠላ ያን ጊዜ እነርሱም ከቤታቸው እንጀራ አመጡ፤ ሁለት ያመጣ አለ፤ ሦስትም ያመጣ አለ፤ ሁላቸውም እንደ አቅማቸው አመጡ፤ አባታችንም ጸሎት ያደርግ ዘንድ ተነሣ፤ ባረከላቸውም፡፡

ደቀ መዝሙሩንም ‹‹ጠላውን አምጣው›› አለው፤ ሁለት መነኮሳትም እንሥራውን አመጡት፤ ከመካከላቸው አንዱን ጠጣ አለው፤ ቀምሶም ለአባታችን ሰጠው፤ ጣዕሙ ደስ ባሰኘው ጊዜ አባታችን ከሩቅ ሀገር የመጡ የተራቡ ሰዎች ከቤቱ ደጃፍ እንዳሉ አወቀ፡፡ መነኮሳቱንም ‹‹አባቶቼ፣ ወንድሞቼና ልጆቼ ፈቃዳችሁ ከሆነስ ለ #ክርስቶስ እንሰጠው ዘንድ ለነዳያንና ለችግረኞች እንስጣቸው›› አላቸው፡፡

በቤተ ክርስቲያን የተሰበሰቡ ወንድሞች መነኮሳት፣ ክቡራን ካህናት፣ ዲያቆናትና ሕዝቡ የ #መንፈስ_ቅዱስ ማደሪያ የሆነ፣ በወንጌል ወተት ያደገ፣ የ #እግዚአብሔር ሰው የሆነ የአባታችንን ትሕትና፣ ትሩፋትና ቅድስና ባዩ ጊዜ አዘኑበት፡፡ ምንም ቃል አልመለሱለትም፤ በቦታቸው ወይም በቤታቸው አልነበሩምና፤ በልባቸው ‹‹እኛስ ከሩቅ ሀገር የመጣን አይደለምን?›› አሉ፡፡ እነርሱ ግን ከዚያው ይኖሩ ነበር፤ አባታችን ግን ነዳያንን ሰብስቦ ያንን ምግብ ሰጣቸው፡፡

ወደ ቤቱ ተጠርተው የመጡ እነዚያ መነኮሳትም አንዲት ቃል አልተናገሩም፤ ነገር ግን በልባቸው ተቆጡ፤ በጣምም አዘኑ፤ አባታችን ግን ደቀ መዛሙርቱን ሌላ ማእድ ያቀርቡ ዘንድ አዘዘ፤ ከመንገድ ስንቅ ይመገቡ ነበርና ጥቂት አመጡ፡፡ ገና ሳይቀምሱም ከሕዝብ አንዱ ‹‹አባቴ ሆይ! ጸልይልኝ፤ ይህን ጥቂት በረከትም ተቀበል›› ብሎ ብዙ ጠላ ላከ፤ እነዚህ መነኮሳት ግን ይህን ባዩ ጊዜ ፈጽመው ተደነቁ፤ ፈጽመው ፈሩ፤ ተንቀጠቀጡም፡፡ አባታችንም ተነሥቶ ለ #ክርስቶስ ሰጠሁት፤ ለተራቡትም አስቀደምሁ፤ ለድኆች የሚሰጥ ለ #እግዚአብሔር ያበድራል የሚል ተጽፏልና አላቸው፡፡

እነዚህ መነኮሳትም ‹‹አባታችን መምህራችን ሆይ! ይቅር በለን አንተ ብዙ ሐዘንን ታውቃለህና፤ እኛ ስለሆዳችንና ስለልብሳችን አዘንን፤ አንተ ግን እንደ ጌታህ #ክርስቶስ የድኆችና የችግረኞች ወዳጅ ነህና›› አሉት፡፡ ‹‹አላወቅንምና አባታችን ይቅር በለን፤ አንተ ፈቃደ #እግዚአብሔርን ትፈጽማለህ፤ እርሱም ልመናህን ይሰማልና›› አሉት፡፡ ‹‹እንዲሰጥህ አላወቅንም፤ ነገር ግን ጎተራህን ሁሉ እንደሚሞላልህ ሰምተን ነበር፤ የተዘጋጀ ምግብንም እንዳወረደልህ ሰምተን ረሳን፤ አሁንም አባታችን ይቅር በለን፤ ባንተ ላይ ተቆጥተን ነበር፤ #እግዚአብሔር ከአንተ ጋር እንደሆነ አላወቅንም፤ አንተ ግን አስቀድመህ ለተራቡት ሰጠህ፤ ቀጥሎም ከአምላክህ በረከት ለእኛ ለመብላት ለተዘጋጀን ሰጠኸን›› አሉት፡፡ አባታችን ዘግሩምም ‹‹ወንድሞቼና ልጆቼ ይህን የማደርገው ለሰው ልታይ ብዬ አይደለም፤ ለትምክህትም አይደለም፤ #እግዚአብሔር የሰጠኝ ሀብት ነው እንጂ›› አላቸው፡፡ ‹‹እኔ እሰጣለሁ፤ እርሱም የሚያስፈልገኝን ነገር አላሳጣኝም›› አላቸው፤ እነርሱም ከእርሱ ተባረኩ፤ ከዚህም በኋላ ታላላቅ ተአምራትና ድንቅ ነገርን የሚያደርግ የ #እግዚአብሔርን ገናናነት ተነጋገሩ፡፡

ከዕለታት አንድ ቀንም አባ ዘግሩም ቆሞ ሳለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ወደ እርሱ መጣ፤ ቅድስት የሆነች የጎኑን መወጋትና ቁስሎቹን ሁሉ አሳየው፡፡ በደሙ መፍሰስም ተደሰተ፤ ሰግዶም እንዲህ አለ፤ ‹‹#ጌታየ የሚፈሰውን ደምህን እዳስስ ዘንድ ፍቀድልኝ›› አለው፤ #ጌታችንም ቅዱስ የሆነ ደሙን ይዳስስ ዘንድ ፈቀደለት፤ እንደ ቅዱስ ቶማስም ጎኑን ዳሰሰ፤ ቅዱስ ቶማስስ ደቀ መዛሙርቱን ስላላመነ ነበር፤ ይህ አባታችን ግን #ጌታችን ‹‹ሳያዩኝ የሚያምኑኝ ብፁዓን ናቸው›› ብሎ እንደተናገረው ሳያይ ያመነ ነው፡፡ ይህ አባታችን ግን ሳያይ አመነ፤ በቅዱስ ደሙ መፍሰስም ደስ አለው፤ ወንድሞቼ ሆይ ለአባታችን የተሰጠውን ጸጋ ተመልከቱ፤ የ #መድኃኒታችንን ቁስሎች ዳስሷልና፤ ለድኆች የማዘን ፍሬው ይህ ነው፤ ‹‹ለድኆች የሚራራ ለ #እግዚአብሔር ያበድራል›› ተብሏልና፡፡

ለሰው ልጅ የሚሰጥ ታላቅ ጸጋን አገኘ፤ ከሀገሮች ሲመለስም ወደ ደብረ ጽዮን ለመሄድ ግባ ከተባለ ታላቅ ወንዝ ደረሰ፤ ከፈሳሹ ብዛት የተነሣ ስትበረታታ አገኛት፡፡ ብዙ ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ የሚያደርጉትንም አጡ፤ ብፁዕ አባታችን ግን ከወንዙ ዳር ቆመ፤ በምርጉዙም በባሕሩ ላይ አማተበ፤ ያን ጊዜ ወንዙ ወዲያና ወዲህ ተከፈለ፤ በዚያ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ተሻገሩ፡፡ ነቢዩ ሙሴ የኤርትራን ባሕር በከፈላት ሕዝቡንም በመራ ጊዜ እንደ ተሻገሩ ሁሉ ተሻግረዋልና #እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ይህም አባታችን ባሕርን በየብስ አሻገራቸው፤ ከዚህ በኋላ በሰላም ወደ ቤቱ ደረሰ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ገድለ_ቅድስት_ጸበለ_ማርያም#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_24 እና #ከገድላት_አንደበት)
#ጥቅምት_25

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ አምስት በዚህች ቀን #ቅዱስ_አቡነ_አቢብ (አባ ቡላ) አረፈ፣ የመላእክት አምሳል የሆነ #አባ_እብሎይ አረፈ፣ የከበረ #ቅዱስ_ዮልዮስ_ሰማዕት ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው፣ የደብረ ሊባኖሱ #አባ_ሕፃን_ሞዐ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቡነ_አቢብ (አባ ቡላ)

ጥቅምት ሃያ አምስት በዚህች ቀን ታላቅና ክብር የሆነ አቢብ የተባለ መስተጋድል አባ ቡላ አረፈ።

የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አብርሃም የእናቱም ስም ሐሪክ ነው እነርሱም ከሮሜ አገር ሉፊ ከሚባል አውራጃ ናቸው በዘመናቸውም ከሀዲው ንጉሥ መክስምያኖስ በክርስቲያን ወገኖች ላይ መከራ ስለ አመጣ ስደት ሁኖ ነበርና እነርሱም በስደት ብዙ ዘመን ኖሩ።

ልጅንም በአጡ ጊዜ የተባረከ ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ በጾም በጸሎት ተወስነው ወደ #እግዚአብሔር ለመኑ የ #እግዚአብሔርም መልአክ በሕልም ተገለጠላቸውና ፍሬ የመላበትን ዘለላ ሰጣቸው።

ይህም ቅዱስ በተፀነሰ ጊዜ በቤታቸው አጠገብ ታላቅ ዛፍ በቀለ በቅጠሉም ላይ በሮማይስጥ ቋንቋ ቡላ የ #እግዚአብሔር አገልጋይ በጽዮንም አድሮ የሚኖር የያዕቆብ ፈጣሪ ያከበረው የሚል ጽሑፍ ነበረበት።

በተወለደም ጊዜ ክርስትና ሳያስነሡ ዓመት ሙሉ አኖሩት እመቤታችን #ማርያምም ለሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ለሰለባስትርዮስ ተገልጣ ወደ አብርሃም ቤት ሒዶ ሕፃኑን እንዲአጠምቀው አዘዘችው እርሱም ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው ስሙንም ቡላ ብሎ ሰየመው እናትና አባቱም ሳይነግሩት ቡላ ስለ ሰየመው አደነቁ ዕፁብ ዕፁብ አሉ።

ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱ በጸለየ ጊዜ የቊርባን ኅብስትና ወይን የተመላ ጽዋ ከሰማይ ወረደ እርሱም ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ከሕፃኑ ጋር አቀበላቸው በዚያንም ጊዜ ሕፃኑ የአንድ ዓመት ልጅ ሲሆን በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከ #ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ #አብ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከ #አብ#መንፈስ_ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ #ወልድ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው በባሕርይ በህልውና በመለኮት በ #አብ#ወልድ ጋር አንድ የሆነ #መንፈስ_ቅዱስ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው ብሎ ተናገረ።

ከጥቂት ዘመንም በኋላ አባትና እናቱ ኅዳር ሰባት ቀን ሙተው ሕፃኑ ብቻውን ቀረ።

ሕፃኑም ዐሥር ዓመት በሆነው ጊዜ ለጣዖት መስገድን የሚያዝ ከሀዲ መኰንን መጣ ቅዱስ ቡላም በሰማ ጊዜ ወደ መኰንኑ ሒዶ የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ መኰንኑም በአካል ታናሽነቱን አይቶ እጅግ አደነቀ በዚያንም ጊዜ በችንካር እንዲቸነክሩት ሥጋውንም እንዲሠነጣጥቁት ቆዳውንም ከዐጥንቱ እንዲገፉ እጆቹንና እግሮቹንም በመጋዝ እንዲቆርጡ ጀርባውንም እንዲገርፉ በሾተሎችና በጦሮች መካከል አድርገው ከመንኰርኵር ውስጥ እንዲጨምሩት ዳግመኛም በመንገድ ላይ እንዲጐትቱት አዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም መጥቶ አዳነው ያለ ጉዳትም ጤነኛ አደረገው።

ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ መኰንን ሒዶ እርሱንና የረከሱ ጣዖቶቹን ረገመ መኰንኑም ተቆጥቶ በሚያዝያ ወር ዐሥራ ስምንት ቀን ራሱን በሰይፍ ቆረጠው ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወርዶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው ወደ አንድ ገዳምም ወስዶ የምንኲስና ልብስንና አስኬማን በ #መስቀልም ምልክት አለበሰው። እንዲህም አለው ከቅዱሳን ጻድቃን አንድነት ትሆን ዘንድ #እግዚአብሔር አዝዞሃል።

ያን ጊዜም ቅዱስ አባ ቡላ ከደረቅ ተራራ ላይ ወጣ ያለ ማቋረጥም በውስጧ እየተጋደለ ኖረ። የ #ጌታችን_የኢየሱስ_ክርስቶስን መከራውንና ስቅለቱን በአሰበ ጊዜ ከረጅም ዕንጨት ላይ በመውጣት ራሱን ወደታች ሁል ጊዜ ይወረውር ነበር።

በአንዲትም ቀን ከዛፍ ላይ በተወረወረ ጊዜ ሰይጣን ሊገድለው ስለ በረታበት ሞተ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #መድኃኒታችን ከሞት አነሣውና እንዲህ አለው ከእንግዲህ ስምህ ቡላ አይሁን አቢብ ይባል እንጂ የብዙዎች አባት ትሆናለህና።

እርሱም የ #ክርስቶስን ፍቅር እጅግ ጨመረ ፊቱንም እየጸፋ ሥጋውን በየጥቂቱ እየቆረጠ ጀርባውንም ሰባት መቶ ጊዜ እየገረፈ ኖረ #ጌታችንም ይፈውሰው ነበር በየእሑድም ቀን ከቅድስት ድንግል እመቤታችን #ማርያም እንደተወለደ በሌሎች ቀኖችም እንደተያዘና ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበለ ሁኖ ይገለጽለት ነበር።

ስለዚህም ሳይበላ ሳይጠጣ አርባ ሁለት ዓመት ኖረ ዳግመኛም ናላው ፈስሶ እስቲአልቅ ዐሥራ ሁለት ወር በራሱ ተተክሎ ኖረ። በአንዲትም ቀን የ #ጌታችንን መከራ በአሰበ ጊዜ ሰይፉን በአንጻሩ ተከለ ከዕንጨት ላይም ወጥቶ በላዩ ወድቆ ሞተ ቅድስት ድንግል እመቤታችን #ማርያምም ከአእላፍ መላእክት ጋር መጥታ የእኔና የልጄ ወዳጅ ሰላምታ ይድረስህ አለችው ። ከበድኑም ቃል ወጥቶ የሰማይና የምድር ንግሥት #እመቤቴ ሰላምታ ይገባሻል አላት እርሷም በከበሩ እጆቿ ዳሥሣ ከሞት አስነሣቸው።

ዕድሜውንም ፈጽሞ ከዚህ ዓለም የሚወጣበት ጊዜ ሲደርስ ክብር ይግባውና #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በእጁ ልዩ የሆኑ አክሊሎችን የሚያበሩ ልብሶችንም ይዞ ተገለጠለት ወዳጄ አቢብ ሆይ በማያልቅ ተድላ ደስታ ደስ አሰኝህ ዘንድ ወደእኔ ና ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ እኔ ኃጢአቱን አስተሠርይለት ዘንደ በራሴ ማልኩልህ ወይም ለተራቆተ የሚያለብሰውን ለተራበም የሚያጠግበውን ለተጠማ የሚያጠጣውን የገድልህን መጽሐፍም የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውንና የሚሰማውን በጸሎትህም የሚታመኑትን ሁሉ እስከ ዐሥር ትውልድ እምራቸዋለሁ ይህንም ብሎ አፉን ሳመው በደረቱም ላይ አድርጎ ወደአየር አወጣው የመላእክትንም ምስጋና በሰማች ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ገባች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አቡነ አቢብ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_እብሎይ

ዳግመኛም በዚህችም ቀን ደግሞ አክሚም ከሚባል አገር የመላእክት አምሳል የሆነ አባ እብሎይ አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አሞኒ የእናቱ ስም ሙስያ ነው ሁለቱም በ #እግዚአብሔር ፊት ጻድቃን የሆኑ በሕጉ ጸንተው የሚኖሩ ድኆችንና መጻተኞችን የሚወዱ የሚረዱ ናቸው።

ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም ሙስያም ዕንጨት የያዘ ብርሃናዊ ሰው በቤቷ ውስጥ ሲተክለውና ወዲያውኑ ለምልሞ አብቦ ሲያፈራ ያ ብርሃናዊው ሰውም ከዚህ ፍሬ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል ሲላት እርሷም ከፍሬው ወስዳ ስትበላና በአፏ ውስጥ ጣፋጭ ሲሆንላት በልቧም ፍሬ ይሆንልኝ ይሆን ስትል ራእይን አየች።

ከእንቅልፏም በነቃች ጊዜ ራእይን እንዳየች ለባሏ ነገረችው እርሱም እርሷ እንዳየችው ያለ ማየቱን ነገራት #እግዚአብሔርንም አብዝተው አመሰገኑት ትሩፋትንና ተጋድሎን በመጨመር በየሁለት ቀን የሚጾሙ ሆኑ ምግባቸውም እንጀራና ጨው ነው።

ይህን ቅዱስ እብሎይን በፀነሰችው ጊዜ እናቱ በገድል ወንዶችን እስከምታሸንፍ ድረስ በየሌሊቱ ሁሉ አንድ ሽህ ስግደትን ትሰግዳለች ሕፃኑን እስከ ወለደችው ድረስ ዘጠኝ ወር ያህል እንዲህ ስትጋደል ኖረች።

በወለዱትም ጊዜ እብሎይ ብለው ሰየሙት በጐለመሰም ጊዜ የምንኩስናን ልብስ ሊለብስ ወደደ ምክንያትም እስቲያገኝ እንዲህ ኖረ አቢብ የሚባል ወዳጅ ነበረውና እርሱ በሌሊት ወሰደው ከላዕላይ ግብጽ በሚገኙ ገዳማት በአንዱ ገዳም ውስጥ መነኰሰ በገድልም በመጠመድ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ።
ከጥቂት ወራትም በኋላ በጥቅምት ወር ሃያ አምስት ቀን አባ አቢብ አረፈ ያን ጊዜ አባ እብሎይ አብሎግ ወደሚባል ገዳም ሔደ ወደርሱም ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ እርሱም በበጎ አምልኮ #እግዚአብሔርን መፍራትን የሚያስተምራቸው ሆነ።

ቅዱስ አቢብም በአረፈበት ቀን መታሰቢያውን ሲያደርጉ ይህ ቅዱስ አባ አብሎይ ወንድሞች ሆይ በአባ አቢብ ስም ዛሬ ጸሎትን የሚጸልየውን ኃጢአቱን #እግዚአብሔር ያስተሰርይለታል በዕረፍትህ መታሰቢያ ቀን የአባ አቢብ ፈጣሪ ሆይ ኃጢአቴን ሁሉ ተውልኝ ብሎ አንዲት ጸሎትን የሚጸልየውን ሁሉ እኔ ኃጢአቱን እተውለታለሁ ሲል ቃል ኪዳን ሰጥቶታልና አላቸው።

በዚያችም ሰዓት ከመነኰሳት አንዱ አረፈ እነርሱም ሊገንዙት በዚያ ቁመው ሳሉ አባ እብሎይ ስለ ተናገረው ቃል ከመነኰሳት አንዱ ተጠራጠረ በዚያንም ጊዜ ያ የሞተው ተነሥቶ ይናገር ዘንድ ጀመረ አባ እብሎይ ስለተናገረው ቃል ለምን ትጠራጠራላችሁ ለአባታችን አቢብ በመታሰቢያው ቀን በዚህ ቃል ኪዳን #እግዚአብሔር ሰጥቶናልና አላቸው ። ይህንንም ብሎ ተመልሶ አረፈ መነኰሳቱም አደነቁ ምስጉን #እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።

ይህ አባ እብሎይም ብዙ ዘመናት ኖረ ልጆቹ መነኰሳትም በዙ ብዙ ገዳማትም ተሠሩለት። የኖረበትም ዘመኑ በታላቁ አባ መቃርስ ዘመን ነው የአባ እብሎይንም የትሩፋቱን ዜና አባ መቃርስ በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ተሰኘበት እርሱን እያጽናና እያረጋጋ መነኰሳት ልጆቹንም #እግዚአብሔር የሚወደውን በመሥራት ያጸናቸው ዘንድ መልእክትን ጻፈለት።

ይህንንም በአስቄጥስ ገዳም ሁኖ አባ መቃርስ ሲጽፍ አባ እብሎይ በላዕላይ ግብጽ ሳለ በ #መንፈስ_ቅዱስ አውቆ በዙሪያው ያሉትን መነኰሳት እንዲህ አላቸው። እነሆ ማጽናናትን የተመላች መልእክትን አባ መቃርስ ጻፈልን። ከዚህም በኋላ ከአባ መቃርስ ዘንድ የተላኩትን መነኰሳት ሁሉ ወጥተው በደስታ ተቀብለው አስገቧቸው መልእክቱንም በመነኮሳቱ ሁሉ ፊት አነበቡ በታላቅ ደስታም ደስ አላቸው።

ይህም አባ እብሎይ ወደ አባ አሞንዮስ የሔደ ከእርሱ ዘንድም የምትኖረውን ስሟ የዋሂት የተባለችውን የተቀደሰች ሴት ያየ ነው። ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው ወዶ በየካቲት ወር በአምስተኛው ቀን አረፈ እኛ ግን የአባ እብሎይን ዜና ከወዳጁ ከአባ አቢብ ጋር ጻፍን።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አባ እብሎይ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮልዮስ_ሰማዕት

በዚህችም ቀን ዳግመኛ አቅፋሐስ ከሚባል አገር ሰማዕት ለሆነ ለቅዱስ ዮልዮስ ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው።

ይህም ቅዱስ ዮልዮስ በሀገረ ጥዋ በሰማዕትነት በአረፈ ጊዜ በገድሉ እንደተጻፈ ዲዮቅልጥያኖስ ከጠፋ በኋላ ጻድቅ ሰው ቈስጠንጢኖስ ሳይጠመቅ ነገሠላቸው በጥቂት ወራትም የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ የቤተ ክርስቲያንም ሥልጣን ከፍ ከፍ አለ ከሀድያን ነገሥታት ለገደሏቸው ንጹሐን ሰማዕታት በስማቸው አብያተ ክርስቲያናት ታነፁ።

ስለ ቅዱሳን ሰማዕታትም ስለ ሥጋቸው እንዲአስብ ገንዞ በመሸከም ወደ አገራቸው እንዲአደርሳቸው ከአገልጋዮቹም ጋር ገድላቸውን እንዲጽፍ #እግዚአብሔር እንደአቆመውና እንደጠበቀው ከዚህም እርሱ ራሱ በሰማዕትነት እንዴት እንደ ሞተ የቅዱስ ዮልዮስን ዜና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በሰማ ጊዜ ስለበጎ ተጋድሎው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ቅዱስ ዮልዮስን አመሰገነው ።

ስለዚህም ለቅዱስ ዮልዮስ ያማረች ቤተ ክርስቲያን በግብጽ አገር ሠርተው ሥጋውን በውስጧ ያኖሩ ዘንድ ንጉሡ ወደ ግብጽ አገር ብዙ ገንዘብ ላከ በዚያንም ጊዜ ንጉሡ እንዳዘዘ አነፁለት ። የቅዱስ ዮልዮስንም ሥጋ አፍልሰው በውስጧ አኖሩት ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስም ከኤጲስቆጶሳቱ ጋር አከበራት እንደዛሬዪቱም ቀን በዓል አከበረባት ከሥጋውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ዮልዮስ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሕጻን_ሞዐ_ዘደብረ_ሊባኖስ

በዚህችም ቀን የደብረ ሊባኖሱ አባ ሕፃን ሞዐ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ነው። በአባታቸው አርከሌድስ እናታቸው ትቤ ጽዮን ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ጥር 25 ነው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ እና ከእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የሥጋ ዝምድና አላቸው፡፡ ይኸውም አባታቸው አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ወንድማማቾቸ ናቸው፡፡ አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ሌሎች ሌሎች አራት ወንድሞች አሏቸው፡፡

እነርሱም እንድርያስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ቀሲስ ዮናስ እና ቀሲስ ዮሐንስ ናቸው፡፡ አርከሌድስ ሕፃን ሞዐን ይወልዳል፣ ጸጋ ዘአብ ተክለ ሃይማኖትን ይወልዳል፣ እንድርያስ ሳሙኤል ዘወገግን፣ ዘርዐ አብርሃም ታላቁ አኖሬዎዮስን፣ ቀሲስ ዮናስ ገላውዲዮስንና የፈጠጋሩን ማትያስን፣ እና ቀሲስ ዮሐንስ ዜናማርቆስን ይወልዳሉ፡፡ እነዚህ የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን በእናታቸውም ወገን ቢሆን እንዲሁ በዝምድና የተቆራኙ ናቸው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ በሌላኛው ስማቸው ሕፃን ዘደብረ በግዕ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ ይኸውም የደብረ በግዕን ገዳም የመሠረቱት እርሳቸው ስለሆኑ ነው፡፡

ከ47ቱ የሀገራችን ቀደምት ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በመንዝና በተጉለት የሚገኙ ታላላቅ ገዳማትን አብዛኞቹን የመሠረቷቸው አቡነ ሕፃን ሞዐ ናቸው፡፡ ጻድቁ በክፉዎች ወሬና ሴራ ምክንያት ከበሬ ጋር ተጠምደው ሰማዕትነት የተቀበሉ አባት ናቸው፡፡ ከበሬ ጋር ሲታረሱ ውለው በእጅጉ ከደከማቸው በኋላ በኃይል የተነፈሱባት ምድሪቱ ዛሬም ድረስ ልክ እንደሰው የሚሞቅ ትንፋሽ ታወጣለች፡፡ ያም በጻድቁ እስትንፋስ አምሳል ከመሬት ውስጥ የሚወጣው እስትንፋስ ለአስም በሽታ መድኃኒት ሆኖ ብዙዎችን እየፈወሰ ነው፡፡

ገዳማቸው ከደብረ ብርሃን ከተማ በእግር የ2 ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይኸውም ከወንይዬ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አጠገብ ነው፡፡ ጻድቁ ጥር 25 ቀን ልደታቸው፣ ጥቅምት 25 ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ዕለት ሲሆን ሐምሌ 25 ደግሞ ዕረፍታቸው ነው፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_25 እና #ከገደላት_አንደበት)