ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_2_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁷ ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤
⁸ በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤
⁹ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤
¹⁰ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን።
¹¹ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና።
¹² ስለዚህ ሞቱ በእኛ ሕይወቱም በእናንተ ይሠራል።
¹³ ነገር ግን፦ አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን፤
¹⁴ ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛን ደግሞ ከኢየሱስ ጋር እንዲያስነሣን ከእናንተም ጋር እንዲያቀርበን እናውቃለንና።
¹⁵ በብዙዎች በኩል የተትረፈረፈው ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን ያበዛ ዘንድ፥ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና።
¹⁶ ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል።
¹⁷-¹⁸ የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።
⁶ እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤
⁷ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።
⁸ በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤
⁹ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።
¹⁰ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል።
¹¹ ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ሁከቱም ከቀረ በኋላ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስመጥቶ መከራቸው፥ ተሰናብቶአቸውም ወደ መቄዶንያ ይሄድ ዘንድ ወጣ።
² ያንም አገር እያለፈ በብዙ ቃል ከመከራቸው በኋላ ወደ ግሪክ አገር መጣ።
³ በዚያም ሦስት ወር ተቀምጦ ወደ ሶርያ በመርከብ ሊሄድ ባሰበ ጊዜ፥ አይሁድ ሴራ ስላደረጉበት በመቄዶንያ አልፎ ይመለስ ዘንድ ቆረጠ።
⁴ የሸኙትም የቤርያው ሱሲጳጥሮስ ከተሰሎንቄ ሰዎችም አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ የደርቤኑም ጋይዮስና ጢሞቴዎስ የእስያ ሰዎችም ቲኪቆስ ጥሮፊሞስም ነበሩ፤
⁵ እነዚህም ወደ ፊታችን አልፈው በጢሮአዳ ቆዩን።
⁶ እኛ ግን ከቂጣ በዓል ቀን በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሥተን በአምስት ቀን ወደ ጢሮአዳ ወደ እነርሱ ደረስንና በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_2_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"በእግዚአብሔር ተወከልኩ እፎ ትብልዋ ለነፍስየ። አዐይል ውስተ አድባር ከመ ዖፍ። እስመ ናሁ ኀጥአን ወሰቁ ቀስቶሙ"። መዝ 10፥1-2።
"በእግዚአብሔር ታመንሁ፤ ነፍሴን፦ እንደ ወፍ ወደ ተራሮች ተቅበዝበዢ እንዴት ትሉአታላችሁ? ኃጢአተኞች እነሆ ቀስታቸውን ገትረዋልና፥ ፍላጻቸውንም በአውታር አዘጋጅተዋልና፥ ልበ ቅኖችን በስውር ይነድፉ ዘንድ"። መዝ 10፥1-2።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_2_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
¹¹ ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።
¹² ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።
¹³ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም።
¹⁴ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።
¹⁵ መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል።
¹⁶ መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።
¹⁷ እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
🌹የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ ሕርያቆስና የአቡነ ማትያስ የዕረፍት በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_3_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የተነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ኤፌሶን 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፥ ይህ የሚገባ ነውና።
²-³ መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት።
⁴ እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው።
⁵ ባሪያዎች ሆይ፥ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በልባችሁ ቅንነት በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤
⁶ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ።
⁷ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤
⁸ ባሪያ ቢሆን ወይም ጨዋ ሰው፥ እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና።
⁹ እናንተም ጌቶች ሆይ፥ ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፥ በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንዳያደላ ታውቃላችሁና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ራእይ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች።
² እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጨንቃ ጮኸች።
³ ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፥
⁴ ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ።
⁵ አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።
⁶ ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች።
⁷ በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥
⁸ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም።
⁹ ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።
¹⁰ ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።
¹¹ እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፥ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም።
¹² ስለዚህ፥ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፥ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ ነገር ግን አርባ ዓመት ሲሞላው ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ይጐበኝ ዘንድ በልቡ አሰበ።
²⁴ አንዱም ሲበደል አይቶ ረዳው፥ የግብፅን ሰውም መትቶ ለተገፋው ተበቀለ።
²⁵ ወንድሞቹም እግዚአብሔር በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያስተውሉ ይመስለው ነበር፥ እነርሱ ግን አላስተዋሉም።
²⁶ በማግሥቱም እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኛቸው፥ ሊያስታርቃቸውም ወዶ፦ ሰዎች ሆይ፥ እናንተስ ወንድማማች ናችሁ፤ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትበዳደላላችሁ? አላቸው።
²⁷ ያም ባልንጀራውን የሚበድል ግን፦ አንተን በእኛ ላይ ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው?
²⁸ ወይስ ትናንትና የግብፁን ሰው እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትወዳለህን? ብሎ ገፋው።
²⁹ ሙሴም ከዚህ ነገር የተነሣ ሸሽቶ በምድያም አገር መጻተኛ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ልጆች ወለደ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_3_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የተነበበው_የተዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ። ሰብእሰ ከመ ሣዕር መዋዕሊሁ። ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ"። መዝ.102፥14-15።
"ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ። ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል"፤ መዝ.102፥14-15።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_3_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል፦ አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት።
¹⁷ እርሱም፦ ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ።
¹⁸ እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤
¹⁹ ነፍሴንም፦ አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ።
²⁰ እግዚአብሔር ግን፦ አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው።
²¹ ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።
²² ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ።
²³ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና።
²⁴ ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም፥ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፥ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ እናንተስ ከወፎች እንዴት ትበልጣላችሁ?
²⁵ ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?
²⁶ እንግዲህ ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለ ምን በሌላ ትጨነቃላችሁ?
²⁷ አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም።
²⁸ እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?
²⁹ እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፥ አታወላውሉም፤
³⁰ ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል።
³¹ ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 
🌹የተቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_ማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የጽንሰት በዓል፣ የሁለተኛ ሳምንት የማኅሌተ ጽጌና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ማኅሌተ_ጽጌ፤ ምንጩ ትርጉሙና መልእክቱ (ክፍል ሁለት)

በስመ #አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

የቀጠለ…

2, #ታሪክ

በብሉይና በሐዲስ ኪዳን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙትን ድርጊቶች እያነሣ የሚሔድና በዚያውም ከታሪኩ ጋር አብሮ ጸሎትና ምሥጢር የያዘ ነው፡፡ ታሪክን ከሚያነሡት መካከል የሚከተሉትን ለአብነት መመልከት ይቻላል፡፡

2.1. «እስከ መነነቶ ሜልኮል ቅድመ ታቦተ ሕግ ከመ ዘፈነ፣
ንጉሠ እስራኤል ኪያኪ ዘጸገየ ስነ፣
ቅድመ ገጸ ሥዕልኪ ድንግል እዘፍን አነ
ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐተኪ ቁርባነ፣
በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ፡፡

ዳዊት ታቦተ ጽዮንን ከአቢዳራ ቤት ወደ ከተማው ባስመጣ ጊዜ በሙሉ ኃይሉ በ #እግዚአብሔር ታቦት ፊት ሲዘምር ሜልኮል ተመልክታ በልብዋ ናቀችው፡፡ በዚህም ምክንያት #እግዚአብሔር ስላዘነባት ልጅ ሳትወልድ ሞታለች፡፡ ሳሙ.6፡12-23፡፡ ደራሲውም ይህንን ታሪክ ካስታወሰ በኋላ «ቅድመ ገጸ ሥዕልኪ ድንግል እዘፍን አነ - ዳዊት ለ #እመቤታችን ምሳሌ በሆነች በታቦተ ጽዮን ፊት እንደዘመረ እኔም በሥዕልሽ ፊት ላንቺ እዘምራለሁ»፤ «ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐትኪ ቁርባነ በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ ሜልኮል፡- በዳዊት ይቀርብ የነበረውን የታቦተ ጽዮንን ምስጋና በመናቋ እንደተረገመች ያንቺንም ተአምርሽንና ምስጋናሽን የሚንቅ ሁሉ በሰውና በመላእክት አፍ የተረገመ ይሁን» የሚል ነው፡፡ ሜልኮል የምሳሌዋን የታቦተ ጽዮንን ምሥጋና በመናቋ ከተረገመች ዛሬ የአማናዊቷን ታቦተ ጽዮን የ #እመቤታችንን ምሥጋና የሚንቁና ምሥጋና የሚያቀርቡትን የሚነቅፉ ሰዎች ምን ያኽል የተረገሙ ይሆኑ? እነዚህም «በድፍረትና በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ» /መዝ.3ዐ÷18/ ባለው ርግማን የተረገሙ ናቸው፡፡

2.2. እንበይነ አውሎጊስ ለዳንኤል አመ አርአዮ ስቅለተ፣
ከመ እገሪሁ ሰዓምኪ ወሰአልኪዮ ምሕረተ፣
ለተአምረ ሣህል ወልድኪ በእንተ ፍቅረ ሰብእ ዘሞተ፣
እንዘ ታዘክሪዮ ድንግል ይምሐረኒ ሊተ፣
ከናፍሪሁ ጽጌ አንኂ ስዕመተ፡፡

አውሎጊስ የሚባል የወፍጮ ድንጋይ እየጠረበ በመሸጥ ከዚያ በሚያገኘው ትንሽ ገቢ የሚተዳደር ደኃ ሰው ነበር፡፡ የሚያገኘውንም ገንዘብ ለራሱ ትንሽ ለዕለት ኑሮው ካስቀረበ በኋላ ከርሱ የባሰባቸው ችግረኞችን እየረዳ ይኖር ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በዚህ ግብር ሳለ አባ ዳንኤል የሚባል ባሕታዊ ያየዋል፡፡ ይህም ባሕታዊ አውሎጊስ በዚህ በድህነት ኑሮው እንደዚህ ድሆችን የሚረዳ ከሆነ ብዙ ገንዘብማ ቢያገኝ ምን ያክል ብዙ ሰው በረዳና መልካም ሥራ በሠራ ነበር» ብሎ #እግዚአብሔር ለዚህ ሰው ብዙ ሀብት እንዲሰጠው ሱባኤ ያዘ፡፡ #እግዚአብሔርም ሀብት ለዚህ ሰው /ለአውሎጊስ/ እንደማይጠቅመው ቢነግረውም አባ ዳንኤል በራሱ ሀሳብ ብቻ በመጓዝ ሀብቱን እንዲሰጠው አጥብቆ ስለተማፀነ እንደለመነው ሊያደርግለት ጸሎቱን ተቀበለ፡፡ ከዚህ በኋላ አውሎጊስ እንደልማዱ ድንጋይ ሲቆፍር በማሰሮ የተቀበረ ወርቅ አገኘ፡፡ ወርቁን ወስዶ ለንጉሡ ሰጠ፡፡ ንጉሡ ወርቅ ሲያገኝ ለራሱ ሳያደርግ ለንጉሥ የሚያመጣ ሰው ምን ያክል ታማኝ ቢሆን ነው ብሎ በዚያው በቤተ መንግሥቱ እንደራሴ አድርጎ ሾመው፡፡ አውሎጊስ ከተሾመ በኋላ አጃቢው ክብሩና ሀብቱ ሲበዛ ትሩፋት መጨመሩ ቀርቶ የቀደመ ሥራውንም ተወ፡፡ ለተበደለ የማይፈርድ ባለጉዳይ የሚያጉላላ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ዳንኤል በሕልም #እግዚአብሔር ሲቆጣውና ሲፈርድበት አየ፡፡ የማይገባ ልመና ለምኖ አውሎጊስን የቀደመ ትሩፋቱን እንዲተውና አሁን እንዲበድል ምክንያት ሆኗልና፡፡ አባ ዳንኤል በደሉ ገብቶት ከ #ሥዕለ_ማርያም ሥር ወድቆ ተማፅኖ #እመቤታችን ልጇን ተማጽና ይቅር አስባለችው፡፡
አባ ዳንኤል በሕልም ያየው ነገር ስለከበደው ምናልባት አውሎጊስ ድሀ በድሎ ፍርድ አጓድሎ እንደሆነ ብሎ ሊያየው ቢሄድ እርሱንም የማያናግረው ሆነ፡፡ «ስለ ሰው ፍቅር የሞተ ልጅሽን ስለ አባ ዳንኤል ለምነሽ እንዳስማርሽው እኔንም ይቅር እንዲለኝ የጽጌ ልጅሽን ምሕረት ለምኝልኝ» በማለት እኛንም ባላወቅነው እየገባንና እየፈረድን ለሚመጣብን ቅጣት እንድታስምረን የሚያመለክት ነው፡፡

2.3. ኦ ረዳኢተ ድኩማን ዘይረድአኪ ኢትኃሥሢ፣
እምንበረ ላዕክኪ በምዕር ከመ ገፍታዕኪዮ ለወራሲ፣
ለገፍትዖ ፀርየ ድንግል ኃይለ ጽጌኪ ልበሲ፣
እንዘ ይሣለቅ ተአምረኪ ወሐሰተ ይሬሲ፣
መፍትውኑ ከመ ይህየው ከይሲ፡፡

#እመቤታችንን ተአምር አሰባስቦ የጻፈው ቅዱስ ደቅስዮስ ነው፡፡ #እመቤታችንም ለዚህ ውለታው ሌላ ሰው የማይቀመጥበት ሰማያዊ ወንበር እና ሌላ ሰው የማይለብሰው አጽፍ ሰጥታዋለች፡፡ ከደቅስዮስ ዕረፍት በኋላ በእርሱ ቦታ የተሾመው ኤጲስ ቆጶስ በዚህ መንበር ለመቀመጥና አጽፉን ለመልበስ ሲል «ተው ይህ ለደቅስዮስ ብቻ የተሰጠ ነው» ቢሉት «እኔም እንደርሱ ኤጲስ ቆጶስ ነኝ ከእርሱ በምን አንሳለሁ?» በማለት ከወንበሩ ሲቀመጥ ወዲያው ሞቷል፡፡ ከላይ የተጻፈው ድርሰትም የሚያስረዳው ይህንን ነው፡፡ «ድኩማንን፣ ችግረኞችን የምትረጅ አንቺ ግን ረዳት የማትሽ ሆይ ከወዳጅሽ ከደቅስዮስ ወንበር ላይ በትዕቢትና በድፍረት የተቀመጠውን እንደተቀበልሽው የእኔንም ጠላቶች አጋንንትን እኩያት ኃጣውእን ለማስወገድ የጽጌሽን ማለት የልጅሽን ኃይል ይዘሽ ተነሽ» በማለት ለወዳጆቿ የምትቆም #እመቤታችን ከጠላታችን እንድትታደገን ከታሪኩ አንጻር የቀረበ ጸሎት ነው፡፡

2.4. «በጌጋየ አዳም ወሔዋን ሱራፌል ዘአጸዋ፣
እንበለ ጽጌኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ፣
ተፈሥሒ ድንግል መያጢተ አዳም እምጼዋ፣
በተአምርኪ ውስተ ምድረ ጽጌ አቲዋ
ከመ ጣዕዋ አንፈርዓፀት ጼዋ፡፡

አዳምና ሔዋን ባጠፉት ጥፋት ከገነት ተባረው ወደ ምድረ ፋይድ እንዲወርዱ ተፈርዶባቸው ገነትን ሱራፌል መልአክ በምትገለባበጥ የእሳት ሰይፍ ይጠብቅ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀት ገነትን «እንበለ ጽጌከ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ፤ ያለ አንቺ ጽጌ ያለ #ክርስቶስ በሱራፌል ስትጠበቅ የነበረችውን ገነት ሊከፍታት የቻለ ማንም ፍጥረት የለም» ዘፍ.3፡24፡፡ ካንቺ በተገኘ በ #ክርስቶስ ወደ ቀደመ ክብሯና ቦታዋ የተመለሰች ሔዋን የእናቱን ጡት ጠብቶ ደስ እንደሚሰኝ እንደሚዘል እንቦሳ ደስ ተሰኘች፡፡ በአጠቃላይ ይህ የሚያስረዳው ያለ #ክርስቶስ ሰው መሆንና በ #መስቀል ተሰቅሎ ቤዛ መሆን ማንም የገነትን በር ሊከፍት እንደማይችል ሲሆን የተዘጋውን የገነት በር የከፈተና የሰው ልጅ ያጣውን የልጅነት ጸጋ የመለሰ #ክርስቶስ ደግሞ ከ #እመቤታችን የተገኘ መሆኑን ነው፡፡ #እግዚአብሔር በኢሳይያስ አንደበት «መድኃኒቴም አይዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ» ኢሳ.46÷13፡፡ እንዳለ የተዋረደው የሰው ልጅ የከበረበትና የዳነበት መድኃኒት #ኢየሱስ_ክርስቶስ የተገኘው ጽዮን ከተባለች ከእመቤታችን ከቅድስት #ድንግል_ማርያም ነው፡፡ ይህንን መድኃኒት ለዓለሙ ያበረከተች እርሷ ናት፡፡

3. #ተግሣጽ

አባ ጽጌ ድንግል ይህንን ማኅሌተ ጽጌ ሲደርስ ለ #መስቀልና#እመቤታችን ክብርና ስግደት አይገባም የሚሉ ደቂቀ እስጢፋ የሚባሉ መናፍቃን ተነሥተው ነበር፡፡ በዘመኑ የነበሩት ንጉሥ አፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጉባኤ አሠርተው አከራክረው መናፍቃኑ ተረትተዋል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌ ውስጥ እነዚህን የ #እመቤታችንን ተአምርና ክብር በመግለጽ መናፍቃንን በመገሰጽ በዚህ የተግሣጽ ድርሰታቸው አስተምረዋል፡፡ ለምሳሌ የተወሰኑትን እንመልከት፦
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_6_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጢሞቴዎስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ ብቻዋንም ኖራ በእውነት ባልቴት የምትሆን በእግዚአብሔር ተስፋ ታደርጋለች፥ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤
⁶ ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት።
⁷ ያለ ነቀፋ እንዲሆኑ ይህን ደግሞ እዘዝ።
⁸ ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።
⁹ ባልቴት በመዝገብ ብትጻፍ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት እንዳያንስ፥ የአንድም ባል ሚስት የነበረች እንድትሆን ያስፈልጋል፤
¹⁰ ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፥ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።
¹⁰ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል።
¹¹ ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።
¹² እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ።
¹³ ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
¹⁴ በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 17
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁰ እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤
³¹ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።
³² የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን፦ ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት።
³³ እንዲሁም ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጣ።
³⁴ አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ፤ ከእነርሱ ደግሞ በአርዮስፋጎስ ያለው የፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዮስ ደማሪስ የሚሉአትም አንዲት ሴት ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_6_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
   "እበውእ ቤተከ ምስለ መባእየ። ወእሁብ ብጽዓትየ ዘነበብኩ በአፉየ። ዘእቤ በከናፍርየ አመ ምንዳቤየ"። መዝ 65፥13-14
“ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ በመከራዬ ጊዜ በአፌ የተናገርሁትን ከንፈሮቼም ያሉትን ስእለቴን ለአንተ እፈጽማለሁ።” መዝ 65፥13-14 ወይም መዝ.112÷8
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_6_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³² ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤
³³ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።
³⁴ በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።
³⁵ ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤
³⁶ ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል።
³⁷ ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤
³⁸ መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።
³⁹ ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።
⁴⁰ እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።
⁴¹ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።
⁴² ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም። ወይም👉 ሉቃ.2÷36-39
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️  🌹
የሚቀደው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_የማርያም ነው። መልካም የነቢይት ቅድስት ሐና፣ የአባ ጰንጠሌዎን፣ የቅዱስ ዲዮናስዮስ፣ የቅዱስ ሄኖስ የዕረፍታቸው በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን። 🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_14

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ዐሥራ አራት በዚች ቀን ታላቁና የከበረው አባታችን #አቡነ_አረጋዊ ተሰወሩ፣ የቊስጥንጥንያ ንጉሥ የቴዎዶስዮስ ልጅ #ቅዱስ_ገብረ_ክርስቶስ አረፈ፣ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የሆነ አንዱ #ቅዱስ_ሐዋርያ_ፊልጶስ አረፈ፣ ከሮሜ ሀገር የሆነ የከበረ የእግዚአብሔር ሰው #ሙሽራው_ቅዱስ_ሙሴ አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጻድቁ_አቡነ_አረጋዊ

ጥቅምት ዐሥራ አራት በዚህች ቀን ታላቁና የከበረው አባታችን አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል) የተሰወሩበት ነው።

እኚህ አባት ከ9 ቅዱሳን አባቶች አንዱ ሲሆኑ
አባታቸው ይስሐቅ የሮም ንጉስ ነበሩ፡፡ እናታቸው ንግስት እደና ይባሉ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ስማቸው ዘሚካኤል ነው፡፡ ጥበብ መንፈሳ ሲማሩ አድገው ወደ እስክንድርያ ገዳም ገቡ፡፡ አበምኔቱ አባ ጳኩሚስ በፈቃደ #እግዚአብሔር የመጡ መሆናቸውን አውቀው መዓረገ ምንኩስና ሰጥተዋቸዋል፡፡

የንጉሳዊ የቅንጦት ኑሮ ንቀው ትተው ገዳም ገብተው በምንኩስና ተወስነዋል፡፡ አባታችን በተጋድሏቸውም ከአባ እንጦንስ፣ ከአባ ጳውሊ እና ከአባ መቃርስ ቀጥሎ በአራተኛ ማዕረግ አበ መነኮሳት ሆነው ተመርጠዋል።

በገዳመ ዳውናስ 7 ዓመት ከቆዩ በኋላ ወደ ሮም ተመልሰው ሲያስተምሩ የሀገራችን ኢትዮጵያን ዜና ሰምተው ለመምጣት በ480 ዓ.ም ከአባ ፍሬምናጦስ በኋላ መንገድ ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም በክንፉ ተሸክሞ አክሱም አድርሷቸዋል፡፡

ተመልሰውም ሄደው ስለ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መስክረዋል፡፡ ሐዋርያ ሳይላክላት በሃይማኖት በምግባር ጸንታ ትኖራለች ብለው ለሰባቱ ዘመዶቻቸው አበው መነኮሳት ነገሯቸው፡፡ ስምንቱም ጓዛቸውን ጠቅልለው በሮም ነግሶ የነበሩ ይስሐቅን (አባ ገሪማን) ጨምረው ንጉስ አልአሜዳ በነገሰ በአምስተኛ ዓመት ማለትም በ480 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ዘጠኝ ሆነው መጥተዋል፡፡

አባ አረጋዊ እናታቸው ቅድስት እድናን ደቀ መዝሙራቸውን ማትያስን አስከትለው እግረ መንገዳቸውን እያስተማሩና ድውያንን እየፈወሱ ደብረ ዳሞ ደረሰዋል፡፡

ከእግረ ደብር ሆነው አሁን ይህን ተራራ በምን ልወጣው እችላለሁ እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ በንግግሩ ሐሰት የሌለበት አምላካችን በነቢዩ ዳዊት ላይ አድሮ በመዝሙር 90/91፥11-16 ላይ “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። እንዳለው የታዘዘ ዘንዶ መጥቶ ስደሳ ክንድ በሚያህል ጅራቱ ጠምጥሞ ቅዱስ ሚካኤል ሰይፈ እሳት ይዞ እየጠበቃቸው ከተራራው አናት አድርሷቸዋል፡፡

ወዲያው ሃሌ ሉያ ለ #አብ ሃሌ ሉያ ለ #ወልድ ሃሌ ሉያ ለ #መንፈስ_ቅዱስ ብለው አመስግነዋል፡፡ ቦታውም ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሏል፡፡ በዚያ ዕለት ግማሽ ህብስት በልተው ጠገቡ፤ ከዚያ በኋላ ግን ምድራዊ ሕብስት አልተመገቡም፡፡ በሰንበተ ክርስታያን ከቅዳሴ በኋላ ሕብስተ ሰማያዊ እያመጡላቸው ይመገቡ ነበር እንጂ፡፡ ኋላም ዜና ጽድቃቸውን ሰምተው ከስድስት ሺህ ያላነሱ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበውላቸዋል፡፡

ዘጠና ዘጠኝ አመት ሲሞላቸው ጌታ በመንፈቀ ሌሊት ተገልጾ ምድራዊ መንግስትህን ትተህ ስላገለገልከኝ ህልፈት ሽረት የሌለባት ሰማያዊ መንግስቴን አወርሰሃለሁ ብሎ ቃልኪዳን ሰጣቸው፡፡ በስምህ የተማጸነውን እስከ አስራ አምስት ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ አንተም ከሞት ገጽ ትሰወራለህ ብሎ ተስፋቸውን ነገራቸው፡፡ እሳቸው መነኮሳቱን ሰብስበው ከእንግዲህ በሥጋ አታዩኝም ብለው ነግረዋቸው አበምኔት ሾመውላቸው በዚህች ዕለት በዚያው በደብረ ዳሞ ተራራ በስተምስራቅ አቅጣጫ ተሰውረዋል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ገብረ_ክርስቶስ

በዚህችም ቀን ዳግመኛ የቊስጥንጥንያ ንጉሥ የቴዎዶስዮስ ልጅ የቅዱስ ገብረ ክርስቶስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። ይህም ቴዎዶስዮስ #እግዚአብሔርን የሚፈራ ነው ሚስቱም በጎ የምትሠራ #እግዚአብሔርንም የምትፈራ ናት ስሟም መርኬዛ ነው። እነርሱም ልጅ ስለሌላቸው ያዝኑ ነበር ወደ ኢየሩሳሌምም ሒደው ስእለትን ተሳሉ ቸር መሐሪ ወደሆነ #እግዚአብሔርም ለመኑ እርሱም ልመናቸውን ተቀበሎ ይህን ያማረ ልጅ ሰጣቸው ስሙንም አብደልመሲህ ብለው ሰየሙት ትርጓሜውም ገብረ ክርስቶስ ማለት ነው ። የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ የሥጋዊንም ትምህርት አስተማሩት ።

አድጎ በጕለመሰም ጊዜ የሮሜውን ንጉሥ ልጅ አጭተው እንደ ሥርዓቱ አጋቡት ከሌሊቱ እኩሌታም በሆነ ጊዜ ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ ተነሥቶ ወደሙሽራዪቱ ገባ እጅዋንም ይዞ ከእርስዋ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ ። ከዚያም የሃይማኖት ጸሎት በአንድ አምላክ እናምናለን የሚለውን እስከ መጨረሻ ጸለየ የተሞሸረበትንም ልብስ ከላዩ አውልቆ የግምጃ ልብስን ለበሰ ወደ ሙሽሪቷም ሒዶ ራስዋን ሳማት እንዲህም እያለ ተሰናበታት #እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይኑር ከሰይጣን ሥራ ሁሉ ያድንሽ ። እርሷም አልቅሳ ጌታዬ ወዴት ትሔዳለህ ለማንስ ትተወኛለህ አለችው እርሱም በ #እግዚአብሔር ዘንድ እተውሻለሁ እኔም #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስን ልከተለው እሔዳለሁ የአባቴ መንግሥት አላፊ ነውና አንቺም መሐላሽን አስቢ አላት ያን ጊዜ መሐላዋን አስባ ዝም አለች ።

ለሠርጉም የታደሙት ሁሉ እንደተኙ በሌሊት ወጥቶ ሔደ ወደ ባሕርም ዳርቻ ደርሶ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞችን አገኘ የዓመት መንገድ ወደሚሆን አርማንያም እስከሚደርስ ከእነርሱ ጋር ተጓዘ ።

ነግቶ ወደ ሠርጉ አዳራሽ አባትና እናቱ በገቡ ጊዜ ሙሽራውን ልጃቸውን አላገኙትም ሙሽሪትንም ልጃችን ወዴት አለ ብለው ጠየቋት እርሷም እንዲህ አለቻቸው ። በሌሊት ወደ እኔ ገባ መሐላን አማለኝ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ ራሴንም ስሞኝ ከእኔ ዘንድ ወጣ እኔም እያለቀስኩ ብቻዬን አደርኩ ነገርዋንም ሰምተው ወድቀው በመጮህ ታላቅ ልቅሶን አለቀሱ ።

በዚያችም ጊዜ በሀገሮች ውስጥ ሁሉ ልጁን ገብረ ክርስቶስን ይፈልጉት ዘንድ ንጉሡ አምስት መቶ አገልጋዮቹን ላከ ለድኆችና ለምስኪኖችም ምጽዋት አድርገው የሚሰጥዋቸውን ብዙ ገንዘብን ሰጣቸው ።

ገብረ ክርስቶስ ግን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል #ማርያም ስም በአርማንም አገር በተሠራች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ደጅ የሚኖር ሆነ ። አባቱ የላካቸውም ሁለቱ አገልጋዮች ከዚያ ደርሰው ስለርሱ መረመሩ ግን ወሬውን ማግኘት ተሳናቸው ለድኆችም ምጽዋትን ሰጡ እርሱም ከድኆችም ጋር ምጽዋትን ተቀበለ ።

በዚያም ዐሥራ አምስት ዓመት ከኖረ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያም ለአንድ ቄስ ተገለጸችለት ቦታውንም አመልክታ እንዲህ አለችው ። የ #እግዚአብሔር ሰው ገብረ ክርስቶስን ይዘህ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስገባው ከውጭ አትተወው ቄሱም #እመቤታችን እዳዘዘችው አደረገ ።

ከዚህም በኋላ የተመሰገነ ገብረ ክርስቶስ በሌሊት ተነሣ ከ #እመቤታችንም ሥዕል ፊት ቁም ጸለየ እንዲህም አላት እመቤቴ ሆይ የተሠወረ ሥራዬን አንቺ ለምን ገለጥሽ አሁንም ወደሚሻለኝ ምሪኝ ይህንንም ብሎ የ #እመቤታችንን ሥዕሏን ተሳልሞ በሌሊት ወጥቶ ወደ ባሕሩ ወደብ ደረሰ ወደሌላ ሀገርም ሊሔድ ወዶ በመርከብ ተሳፈረ። ግን በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ከአባቱ አገር ደረሰ የአባቱና የእናቱም ባሮች እየናቁትና እየሰደቡት በአባቱ ደጅ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ ።
#ጥቅምት_15

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ዐሥራ አምስት በዚች ቀን #ቅዱሳን_ሐዋርያት ዓለምን በእጣ ለ12 የተካፋፈሉበት እና ከኒቆምድያ አገር #ቅዱስ_ቢላሞን በሰማዕትነት ያረፈበት ቀን ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#12ቱ_ቅዱሳን_ሐዋርያት

ጥቅምት ዐሥራ አምስት በዚች ቀን ቅዱሳን ሐዋርያት ዓለምን በእጣ ለ12 የተካፋፈሉበት ዕለት ነው። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከ #እመቤታችን በቀር ከቅዱሳን ሐዋርያት የሚበልጥ አልተነሳም። "ሐዋርያ" ማለት "ፍንው፣ ልዑክ፣ የተላከ፣ የጽድቅ መንገደኛ" እንደ ማለት ነው። በምሥጢሩ ግን "ባለሟል" ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል።

ይህስ እንደምን ነው ቢሉ:-

የፍጥረታት ሁሉ ጌታ የክብር ባለቤት #መድኃኔዓለም ከድንግል #ማርያም ተወልዶ፣ አድጐ፣ ተጠምቆ፣ ጾሞ ከገዳመ ቆረንቶስ ሲመለስ ቀዳሚ ሥራው ያደረገው ደቀ መዛሙርቱን መጥራት ነበር::

ከተከተሉት የ5 ገበያ ሕዝብ መካከል "ወሐረየ እምሰብአ ዚአሁ አሠርተ ወክልኤተ ሐዋርያተ" እንዲል በመጀመሪያ 12ቱን ሐዋርያት መረጠ። እሊህም:- #ዼጥሮስ የተባለ ስምኦን፣ #እንድርያስ (ወንድሙ)፣ #ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ፣ #ዮሐንስ (ወንድሙ)፣ #ፊልዾስ#በርተሎሜዎስ#ቶማስ#ማቴዎስ#ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ፣ #ታዴዎስ (ልብድዮስ)፣ #ናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን) እና #ማትያስ (በይሁዳ የተተካው) ናቸው። (ማቴ. 10፥1)

እነዚህን 12 አርድእቱን ከጠራ በሁዋላ ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ከዋለበት ሲማሩ ይውሉ ነበር። ሌሊት ደግሞ ምሥጢር ሲያስተረጉሙ ያድሩ ነበር።

#ጌታ እንደሚገባ ካስተማራቸው በሁዋላ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ሾማቸው። ለዓለም እረኞች የእርሱም ባለሟሎች ሆኑ። እጅግ ብዙ መከራ እንደሚገጥማቸው ነገራቸው። (ማቴ.10፥16, ዮሐ.16፥33) በዚያው ልክ ክብራቸውንም አከለላቸው። (ማቴ. 19፥28) ሥልጣንም "በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል።" (ማቴ. 18፥18) "ይቅር ያላችኋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል፤ ያላላችኋቸው ግን አይቀርላቸውም።" (ዮሐ.20፥23) ብሎ ሰጣቸው።

የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ (ማቴ. 16፥19)፣ እረኝነትን (ዮሐ. 21፥15) ተቀበሉ። #ጌታ በንጹሕ አንደበቱ ሐዋርያቱን እጅግ ሲያከብራቸው "ጨው፣ የዓለም ብርሃናት" (ማቴ. 5፥13) አላቸው። ወንድሞቹም ተባሉ። (ዮሐ.7፥5) ከዚህም በሚበልጥ በሌላ ክብር አከበራቸው።

ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ በ #ጌታ ሕማማት ጊዜ ገና ነበሩና አንዳንዶቹ ፈርተው ተበተኑ። ተመልሰው ግን በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩ ሰንብተው የ #ጌታን ትንሳኤ ተመለከቱ። እጆቹን፣ እግሮቹንም ዳስሰው ሐሴትን አደረጉ።

ለ40 ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትምሕርተ ኅቡዓት፣ ሌላም በፍጡር አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢራትን ተምረው #ጌታ ሊቀ ጵጵስናን ሹሟቸው ዐረገ።

ለ10 ቀናት በ #እመብርሃን ሥር ተጠልለው ሲጸልዩና በአንድ ልብ ሲተጉ ሰንብተው #መንፈስ_ቅዱስ ወረደላቸው። በአንዴም ከፍርሃት ወደ ድፍረት ተመልሰው ፍጹማን ብርሃናውያን ሆኑ። 71 ልሳናትን ነስተው በአንዲት ስብከት ብቻ 3ሺ ነፍሳትን ማረኩ። (ሐዋ.2፥41)

ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እየተመላለሱ አስተምረው ብዙ እሥራኤላውያንን ወደ ክርስትና ማርከዋል። ከዚህ በኋላ ግን እንደ ትውፊቱ በዚህች ቀን ዓለምን በእጣ ለ12 ተካፈሏት።

ይህ ሲሆን #መንፈስ_ቅዱስ አብሯቸው ነበርና ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው አሕጉረ ስብከቶች ደረሷቸው። እነርሱም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አስከትለው ለታላቁ መንፈሳዊ ዘመቻ ወረዱ።

በሔዱበት ቦታም ከተኩላ፣ ከአንበሳና ከነምር ጋር ታገሉ። በጸጋቸውም አራዊትን (ክፉ ሰዎችን) ወደ በግነት መልሰው ለ #ክርስቶስ አስረከቡ። በየሃገሩ እየሰበኩ ድውያንን ፈወሱ፣ ለምጻሞችን አነጹ፣ እውራንን አበሩ፣ አንካሶችን አረቱ፣ ጐባጦችን አቀኑ፣ ሙታንንም አስነሱ፣ እልፍ አእላፍ አሕዛብንም ወደ መንጋው ቀላቀሉ።

ስለዚህ ፈንታም ብዙዎቹ በእሳት ተቃጠሉ፣ ቆዳቸው ተገፈፈ፣ በምጣድ ተጠበሱ፣ ደማቸው በምድር ላይ ፈሰሰ፣ ከአንድ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር ሁሉም ይህችን ዓለም በሰማዕትነት ተሰናበቱ። ጨው ሆነው አጣፍጠዋልና ብርሃንም ሆነው አብርተዋልና እናከብራቸዋለን። "አባቶቻችን፣ መምሕሮቻችን፣ ጌቶቻችንና ሊቆቻችን" እንላቸዋለን።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቢላሞን

ዳግመኛም በዚች ቀን ከኒቆምድያ አገር ቅዱስ ቢላሞን በሰማዕትነት አረፈ።

የዚህም ቅዱስ አባቱ ጣዖት አምላኪ ነው እናቱ ግን ክርስቲያን ናት ጥበብንም አስተማሩት ከዚህም በኋላ ስሙ አርማላስ ከሚባል ቄስ ጋር ተገናኘ። እርሱም ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን የቀናች ሃይማኖት አስተማረው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቀው ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ታምራትን የማድረግ ሀብትን #እግዚአብሔር እስከ ሰጠው ድረስ በጾም በጸሎት ታላቅ ገድልን ተጋደለ።

በአንዲት ቀንም ለዓይኖቹ መድኃኒትን እንዲአደርግለት አንድ ዕውር ሰው ወደርሱ መጣ ቅዱስ ቢላሞንም በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም እያለ በዕውሩ ዐይኖች ላይ የ #መስቀልን ምልክት አደረገ ያን ጊዜ ዐይኖቹ ድነው አየባቸው ጤነኛም ሆነ።

ንጉሥም ዐይኖቹ የተገለጡለትን የዚያን ዕውር ዜና በሰማ ጊዜ ወደርሱ አስቀረበውና ዐይኖችህን ማን አዳነህ ብሎ ጠየቀው እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት ቅዱስ ቢላሞን ፈወሰኝ እርሱ እጁን በዐይኖቼ ላይ አድርጎ በስመ #አብ #ወወልድ #ወመንፈስ_ቅዱስ እያለ በ #መስቀል ምልክት አማተበብኝ ያን ጊዜ አየሁ ይህንንም ብሎ እኔ ክርስቲያን ነኝ እያለ በንጉሡ ፊት በግልጽ ጮኸ። ንጉሡም ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡት የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ከዚህም በኋላ ወታደር ልኮ ቅዱስ ቢላሞንን አስቀረበው ስለ ሃይማኖቱም በጠየቀው ጊዜ እርሱም ክርስቲያን ነኝ ብሎ በፊቱ ታመነ ንጉሡም ብዙ ሽንገላን በመሸንገል አባበለው። ብዙ ቃል ኪዳንም ገባለት ባልሰማውም ጊዜ በእርሱ ላይ ተቆጥቶ ድምፁን ከፍ አድርጎ ካልሰማኸኝ እኔ ጽኑ ሥቃይን አሠቃይሃለሁ አለው። ቅዱስ ቢላሞንም እኔ ከሥቃይህ የተነሣ ፈርቼ ሃይማኖቴን ለውጬ ፈጣሪዬን አልክድም አለው።

ከዚያችም ቀን ጀምሮ በብዙ አይነት ሥቃይ በብዙ ቀኖች ውስጥ ማሠቃየትን ጀመረ። በግርፋት በስቃላትም በባሕር ስጥመትም ወደ እሳት በመወርወርም የሚያሠቃይበት ጊዜ አለ።

በዚህም ሥቃይ ውስጥ ሳለ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በአጠመቀው ቄስ በአርሜላዎስ አምሳል ተገልጾለት እንዲህ የሚል የደስታ ቃል አሰማው። የመረጥኩህ ቢላሞን ሆይ ደስ ይበልህ እኔ ሰማያዊ መንግሥትን አዘጋጅቼልሃለሁና።

የንጉሡ ጭፍሮችም ይህን የደስታ ቃል ሰሙ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም አምነው እነርሱ በሕያው #እግዚአብሔር ልጅ #ክርስቶስ የአመኑ መሆናቸውን በንጉሡ ፊት ገለጡ በዚያንም ጊዜ ራሳቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ ንጉሡ አዘዘ። ቅዱስ ቢላሞንንም እንዲቆርጡት አዘዘ ከእሊህ ጭፍሮች ጋርም እንዲህ ገድሉን ፈጸመ ቁጥራቸውም መቶ ኀምሣ ስምንት ነው የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
#ጥቅምት_16

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ዐሥራ ስድስት በዚች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_ያቃቱ አረፈ፣ ኢትዮጵያውያን የህኑ የጻድቁ አቡነ ሀብተማርያም እረድዕ የነበሩት #አቡነ_ኢያሱ_ዘጀር_ሥላሴ በዓለ ዕረፍታቸው ነው፣ ለአርባ ስምንት ዓመታት ከሰው ጋር ሳይነጋገሩ በዝምታ ብቻቸው ለኖሩ #ነብር_ሰባት_ዓመት_ውሃ_ሲቀዳላቸው ሲያገለግላቸው የነበሩ ታላቁ አባት #አቡነ_አሮን_ዘአርምሞ ዕረፍታቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ያቃቱ

ጥቅምት ዐሥራ ስድስት በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ዘጠነኛ የሆነ ቅዱስ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ያቃቱ አረፈ።

ከርሱ በፊት የነበረ አባ ብንያሚን በአረፈ ጊዜ ይህን አባት መርጠው በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በዘመኑም ብዙ ችግር ደርሶበታል ስሙ ቴዎዶስዮስ የሚባል አንድ መለካዊ ሰው ነበረ እርሱም ወደ ደማስቆ ንጉሥ ወደ ዘይድ ሒዶ ብዙ እጅ መንሻ ሰጥቶ ለእስክንድርያ አገረ ገዥ ሁኖ ተሾመ።

ይህንንም አባት አባ ያቃቱን ሊአስጨንቀው ጀመረ በየዓመቱ ግብር ሰባት ሺህ የወርቅ ዲናር ከእርሱ እስከተቀበለ ድረስ #እግዚአብሔርም እስከ አጠፋው ድረስ ይህን አባት እንዲህ አሠቃየው።

በዘመኑም የብዙዎች ቅዱሳን አባቶች አባት የሆነ የአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃዋ ተፈጸመ።

በአንዲት ሌሊትም ከ #እግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዚህ አባት ተገለጸለት ፍዩም በሚባል አገር በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ዮሐንስ የሚባል ጻድቅ ሰው መነኰስ እንዳለ ነገረው። ሕዝብን በማስተማርና በመምከርም ይረዳው ዘንድ መልእክተኞችን ልኮ እንዲአስመጣውም አዘዘው ሁለተኛም ከእርሱ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት እንደሚሆን ገለጠለት።

በዚያንም ጊዜ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣው ሥራውንም ሁሉ አስረከበው ይህንንም አባት ከብዙ ድካም የሚያሳርፈው ሆነ በሹመቱ ወንበር ዐሥራ ዘጠኝ ዓመት ኑሮ ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ኢያሱ_ዘጀር_ሥላሴ

አቡነ ኢያሱ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሰሜን ሸዋ የተነሡ ሲሆን ምንኵስናቸውን ከደብረ ሊባኖሱ ከዕጨጌ አቡነ መርሐ ክርስቶስ እንደተቀበሉ ታሪካቸው ያስረዳል። ትውልዳቸው አምሐራ ሳይንት ሲሆን መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር #ቅድስት_ሥላሴ ገዳምን የመሠረቱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው።

እርሳቸው የመሠረቱት ጀር #ቅድስት_ሥላሴ ገዳም በግራኝ ወረራ ሳይወድም ስለቀረ ጥንታዊነቱን እንደጠበቀ ስለሚገኝና ታላቅ የበረከት ቦታ የቅዱሳን መናኸሪያ ስለሆነ ብዙዎች ነገሥታት ገዳሙን እየሔዱ ተሳልመው በረከት አግኝተውበታል። የአቡነ ኢያሱን ገድላቸውን ከአቡነ ሀብተ ማርያም ገድል ጋር ጣልያናዊው ራይኔሪ በሀገሩ ሮም እንዳተመው ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ጽፈዋል። (0s valdo Raineri, Atti di Habta Māryam (†1497) e.di Iyasu (†1508), Santi Monaci Etiopici, Roma 1990 (Or ChrA 235), 165-265.)

የጻድቁ በዓለ ዕረፍታቸው ጥቅምት 16 በገዳሙ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲሆን ስለ ጻድቁ ገድል በዝርዝር ተጽፎ አላገኘንም፣ ይልቁንም አቡነ ኢያሱ ስለገደሙት ታላቁ ጀር #ቅድስት_ሥላሴ ገዳም ነው በብዛት የሚነገረው።

አቡነ ኢያሱ ጀር ስላሴ ከመምጣታቸውም በፊት አስቀድመው በአቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም፣ በደብረ ሊባኖስ እና በሌሎችም ገዳማት እየተዘዋወሩ በተጋድሎ ሲቀመጡ ‹‹ቦታኸ ይኸ አይደለም›› ተብለው በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ነው ወደ ጀር ሥላሴ የመጡት። ወደ ቦታው ከመምጣታቸው በፊት አካባቢው ባእድ አምልኮ የተስፋፋበት ነበር፣ ነገር ግን ጻድቁ ሕዝቡን ክርስትናን አስተምረው ወደ አምልኮተ #እግዚአብሔር መልሰውታል። የምንኵስናን መሠረት ጥለውበታል። የአቡነ ኢያሱ የዕረፍታቸው ቦታ ደብረ ሊባኖስ ቢሆንም መታሰቢያቸው በመራቤቴ በሚገኘው አስደናቂ ገዳማቸው ይታሰባል። በገዳሙ በክብረ በዓሉ ወቅት ታቦት አይወጣም፣ ከበሮ አይመታም። ምክያቱም ፍጹም የጸሎት የጽሞና ቦታ ስለሆነ ነው።

መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር #ቅድስት_ሥላሴ አቡነ ኢያሱ ገዳም በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ እጅግ አስደናቂ ሲሆን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በደንቢ ግራርጌ ቀበሌ ጀር በሚባል ስፍራ የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው። ገዳሙ ከአዲስ አበባ 137 ኪ.ሜ ከደብረ ብርሃን 91 ኪ.ሜ ከለሚ ከተማ 4 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ከጥንት ጀምሮ ስዉር ገዳም ሆኖ የቆየ ነው። ገዳሙ በ1495 ዓ.ም በዐፄ ናኦድ ዘመነ መንግሥት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ጻዲቁ አቡነ ኢያሱ ወደዚህ ቦታ መጥተው መሥርተውታል። በጅረት ታጂቦ ስለሚገኝ ነው ጀር ሥላሴ የተባለው። የክብር ባለቤት #ጌታችን_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በራእይ አስመልክቶ ከመሠረታቸው ገዳማት አንዱ ነው። አቡነ ኢያሱም በገዳሙ በሚገኘው አንድ ትልቅ ዋርካ ሥር ቆመው ይጸልዩ እንደነበር አባቶች ያስረዳሉ። አሁንም ድረስ ዋርካው በሥፍራው ላይ ሕያው ማስረጃ ሆኖ ይገኛል።

ገዳሙ ከአቡነ ኢያሱ ዕረፍት ከዘመናት በኋላ በግራኝ አህመድ ወረራ ጥቃት ደርሶበት መነኰሳቱም ተበታትነው ለ247 ዓመት ጠፍ ሆኖ ከቆየ በኋላ በ1747 ዓ.ም አቡነ ዮሴፍ የተባሉት ጻድቅ በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ከአምባሰል ተነሥተው መጥተው ገደሉን ቦርቡረው ቅኔ ማሕሌት፣ ቅድስትና ቅዱሳንን ያሟላ ቤተ መቅደስ በማነጽ ዳግም ገዳሙን በማቅናት የቀደመውን የአባቶችን ታሪክ ማስቀጠል ችለዋል። በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት ቅርሶቹና ነዋየ ቅዱሳቱ አደጋ እንዳይደርስባቸው አባቶች ሰብስበው በስውር ከቀበሩ ከረጅም ጊዜ በኋላ የቀበሩበት ቦታ ጠፍቶባቸው ነበር ነገር ግን የወንዙ ውኃ አቅጣጫውን ቀይሮ ሽቅብ ፈስሶ ቅርሶቹ ያሉበትን ቦታ አመላክቷል።

መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር #ቅድስት_ሥላሴ አቡነ ኢያሱ ገዳም የበርካታ መናንያን አበው በኣት ከመሆኑም ባሻገር የወንዶች ብቻ ገዳም ሲሆን መናንያኑ ከአራዊት ጋር ተስማምተው የሚኖሩበት ነው። ዙሪያው በገደል የተከበበ ሲሆን ወደ ገዳሙ ለመውረድ የዕንጨት መሰላልን ተጠቅሞ መጓዝ ግድ ይላል። ወደ ገዳሙ መግቢያ የሚያስወርደው መሰላል ደቡብ ወሎ ከሚገኘው ከታላቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም መግቢያ ጋር ይመሳሰላል። የመሰላሉ ርዝመት ከ15 ሜትር በላይ ይሆናል።

ገዳሙ ከ #እግዚአብሔር ጋር በሱባዔ ለመገናኘት ፍጹም ጸጥታ የሰፈነበት ከመሆኑም በላይ ረድኤተ #እግዚአብሔር ያለበት ቅዱስ ቦታ ነው። ዋሻው የሚከፈተው ዐቢይ ጾም ላይ እና በ #እመቤታችን የፍልሰታ ጾም ወቅት ነው። በዋሻው ውስጥ ሱባዔ የሚያዘው በደረቅ ሽምብራ ቆሎ እና በአንድ ኩባያ በሶ ብቻ ነው። አባቶች በኣት ዘግተው ጾመ ፍልሰታን፣ ጾመ ነቢያትን፣ ጾመ ሐዋሪያትን በይበልጥ በምነና ሕይወት የሚያሳልፉበት የበረከት ገዳም ነው።
በጀር #ሥላሴ የሚገኘው ታሪካዊ ታላቅ ተራራ በልበሊት ኢየሱስን ግራኝ አሕመድ ሲያቃጥል ሁለት በወርቅ የታነጹ አብያተ ክርስቲያናት በፍቃደ #እግዚአብሔር እንደሰወረ አባቶች ይናገራሉ። ይኸም ጥንታዊና ታሪካዊ ተራራ አሁንም በቦታው የሚገኝ ሲሆን በዋሻው ውስጥ የክብር ባለቤት #ጌታችን በስደቱ ወራት ከእናቱ ድንግል #ማርያም፣ ከዮሴፍና ከሰለሜ ጋር ለጥቂት ጊዜ የተቀመጠበት ሲሆን አቡነ ዜና ማርቆስና አቡነ ተክለ ሃይማኖትም በምነና የተጋደሉበት ታላቅ ዋሻ ነው። ዋሻው እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ውስጥ ለውስጥ የሚያስኬድ ሲሆን በውስጡ ከ40 በላይ አብያተ ክርስቲያናት እንደተሰወሩበት አባቶች ይናገራሉ።

በግራኝ አሕመድ ወረራ ወቅት የግራኝ ሠራዊት አብያተ ክርስቲያናቱን እናጠፋለን ብለው ሲመጡ በተኣምራት ሰምጠው እንደጠፉ አባቶች ያስረዳሉ። አዛዦቹንም በዋሻ ውስጥ የሚገኙት ወፍ የሚያህሉ ተርቦች ነድፈው ጨርሰዋቸዋል። እነዚያ ተርቦች አሁንም ድረስ በገዳሙ ውስጥ ያልተፈቀደ ነገር ሲደረግ በመናደፍና በመከልከል ዋሻውን የሚጠብቁ ሲሆኑ አንዱ ተርብ ከነደፈ ሕይወት ሊያጠፋ እንደሚችል የገዳሙ አባቶች ይናገራሉ። ከዚኸም በላይ ዋሻው በነብርም ይጠበቃል።

ገዳሙ ባለብዙ ቃልኪዳን ሲሆን ብዙ ስውራን አበው ዛሬም የሚኖሩበት ትንቢታቸው የማይነጥብ ብዙ ግሁሳን የከተሙበት ነው። ስውራኑ አበው ዛሬም #እግዚአብሔር ለፈቀደለት ሰው ይገለጣሉ። ደገኞቹ የኢትዮጵያ ቀደምት ነገሥታት የገዳሙን ክብር በመረዳት ቦታው ድረስ በመሔድ በረከት ይቀበሉ ነበር። ዳግማዊ ምኒሊክ ለጀር #ሥላሴ ገዳምና ለገዳማውያኑ አለኝታ ስለነበሩ በገዳሙ የታሪክ መዝገብ ስማቸው ዘወትር ይነሳል። ግርማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ቦታውን ይንከባከቡት የነበረ ሲሆን ለገዳሙ መርጃ የሚሆን አዲስ አበባ ላይ የሚከራይ ቤት አሠርተው በኪራዩ ገቢ ገዳሙ እንዲጠቀም አድርገው ነበር። በአካልም ገዳሙ ድረስ በመሔድ በረከትን ይቀበሉ ነበር።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_አሮን_ዘአርምም

መጽሐፍ አሮን ዘከትሞ ወዘአርምሞ ይላችዋል። የትውልድ ሀገራቸው ትግራይ ተንቤን ነው። ለ48 ዓመታት ከሰው ጋር ምንም ሳይነጋገሩ በዝምታ ብቻ የኖሩ ታላቅ አባት ሲሆኑ ቀዳማዊ ዘኢትዮጵያ ከተባሉት የመጀመርያዎቹ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው። ቤተ መቅደስ ገብተው ሲያጥኑ ርግብ ዕጣን ታመጣላቸው ነበር። ምግባር ቱሩፋታቸው እጅግ ያማረው እኚህ አባት በዘመናቸው ድርቅ በሆነ ጊዜ የእህል እጦት ሆኖ ሕዝቡን ሰብስበው እግዚኦታ ካደረሱ በኋላ የሀገሩን ሁሉ ጎተራ በተአምራት በእህል ሞልተው አትረፍርፈውታል። በዚህም አስገራሚ ተአምራቸው ሕዝቡንም ከችግርና ከርሃብ አድነውታል።

አቡነ መድኃኒነ እግዚአ ዘደብረ በንኰል አህያቸውን የበላባቸውን አንበሳ በአህያው ምትክ ሰባት ዓመት ውኃ እንዳስቀዱት ሁሉ አቡነ አሮንም ነብርን ሰባት ዓመት ውኃ እያስቀዱ እንዲያገለግላቸው አድርገውታል። ሌሎች የዱር አራዊትም ያገለግሏቸው ነበር። በአንድ ወቅት በሀገሩ ድርቅ ሆኖ ሰው ግማሹ ተሰዶ ግማሹ ደክሞ ስለነበር ጻድቁ ግን የዱር አራዊትን ጠርተው ሠራተኛ አድርገው በማዘዝ ጥንቸልን ውኃ በማስቀዳት፣ ጅብን ጭቃ በማስረገጥ፣ አንበሳን በአናጺነት እንዲሠራ፣ ነብርን ደግሞ አቀባይ በማድረግ እያዘዙ በማሠራት በ #እመቤታችን ስም እጅግ አስደናቂ ቤተ ክርስቲያን መስከረም 10 ቀን ሠርተዋል። የአቡነ አሮን ዘአርምሞ የአንድነት ገዳማቸው ትግራይ ሽሬ ውስጥ ይገኛል።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_16ና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ኤፌሶን 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ።
¹⁴-¹⁵ እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤
¹⁶ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤
¹⁷ የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።
¹⁸ በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤
¹⁹ ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤
¹¹ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤
¹² የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።
¹³ በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው?
¹⁴ ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥
¹⁵ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።
¹⁶ በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ።
¹⁷ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋልና።
¹⁸ ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁸ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
²⁹-³⁰ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።
³¹ ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
   "ኪያከ ተወከሉ አበዊነ። ተወከሉከኒ ወአድኀንኮሙ። ኀቤከ ጸርሑ ወድኅኑ"። መዝ 21፥4-5።
"አባቶቻችን አንተን ተማመኑ፥ ተማመኑ አንተም አዳንሃቸው። ወደ አንተ ጮኹ አመለጡም፥ አንተንም ተማመኑ አላፈሩም"። መዝ 21፥4-5።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_16_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤
² አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ፦
³ በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
⁴ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና።
⁵ የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና።
⁶ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።
⁷ የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና።
⁸ ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።
⁹ የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።
¹⁰ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
¹¹ ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።
¹² ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።
¹³ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም።
¹⁴ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️  🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም አባ ያቃቱ የዕረፍት በዓል፣ የአቡነ ኢያሱና የአቡነ አሮን የዕረፍታቸው በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_21

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ አንድ በዚህችም ቀን #እመቤታችን_ተአምራትን_አድርጋ_ሐዋርያው_ማትያስን ከእሥራት ቤት ያወጣችበት፣ #የነቢይ_ኢዩኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ፣ የማርታና የማርያም ወንድም #የቅዱስ_አልዓዛር ሥጋው ከቆጵሮስ አገር የፈለሰበት፣ የቅዱስ አባት #አባ_ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም እረፍት ነው፣ ታላቁ ጻድቅ #አቡነ_አላኒቆስ ዕረፍታቸው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#እመቤታችን_ለሐዋርያው_ቅዱስ_ማትያስ_ያደረገችለት_ተአምር

በዚህችም ቀን እመቤታችን #ማርያም ተአምራትን አድርጋ ደቀ መዝሙር ማትያስን ከእሥራት ቤት አዳነችው።

የከበሩ ቅዱሳን ወንጌልን በዓለም ዞረው ይሰብኩ ዘንድ ዕጣ ሲጣጣሉ ለቅዱስ ማትያስ ዕጣ የደረሰው ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ነበር፡፡ ይህችም ሀገር እስኩቴስ የተባለች ሩሲያ እንደሆነች የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ቅዱስ ማትያስም እነዚህ ሰውን የሚበሉ ሰዎች አገራቸው እንደደረሰ ዐይኑን አውልቀው አሠሩት፡፡ ምግባቸውም የመጻተኛ ሰው ሥጋ ነው፡፡ በልማዳቸው መሠረት መጻተኛን ሰው ገና እንደያዙት ዐይኖቹን ዐውልቀው በእሥር ቤት ያኖሩታል፡፡ እስከ 30 ቀንም ድረስ ሳር እያበሉ ያስቀምጡትና በ30ኛው ቀን አውጥተው አርደው ይበሉታል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስንም በልማዳቸው መሠረት ዐይኖቹን አውልቀው አሠሩት፡፡ ሐዋርያውም በእሥር ቤት ሆኖ በዚያ ላይ ዐይኖቹን ታውሮ ሳለ በጭንቅ ወደ #ጌታችንና ወደ #እመቤታችን ይለምን ነበር፡፡ ነገር ግን እመብርሃንና ልጇ #መድኃኔዓለም 30ኛው ቀን ሳይፈጸም ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስን ወደ እርሱ ላኩለት፡፡ ቅዱስ ማትያስም ዐይኑን ፈወሱለትና ማየት ቻለ፡፡

እንድርያስም በተዘጋው በር በተአምራት ገብቶ አሥርቤቱ ውስጥ ያሉ እሥረኞችን በስውር አውጥቶ ከከተማው ውጭ ካስቀመጣቸው በኋላ ሁለቱ ሐዋርያት ተመልሰው ሰውን ለሚበሉት ሰዎች ተገለጡላቸው፡፡ እነርሱም ይዘው በአንገታቸው ገመድ አግብተው ለ3 ቀን በሀገራቸው ጎዳናዎች ላይ ሁሉ ጎተቱዋቸው፡፡ ሁለቱም ሐዋርያት በጸሎታቸው ከእሥር ቤቱ ምሰሶ ሥር ውኃ አፈለቁና ውኃው ሀገራቸውን ሁሉ እስኪያጥለቀልቅና ሰዎቹንም እስከ አንገታቸው ድረስ እስከሚደርስ ሞላ፡፡ ሁሉም በተጨነቁ ጊዜ ሁለቱ ሐዋርያት በፊታቸው ተገለጡና ‹‹በጌታችን እመኑ ትድናላችሁ›› በማለት ወንጌልን ሰብከውላቸው አሳመኗቸው፡፡ ምሥጢራትንም ሁሉ ገለጡላቸው፡፡ ደግሞም የአራዊት ጠባይን ከሰዎቹ ያርቅላቸው ዘንድ ወደ #ጌታችንና ወደ ተወደደች እናቱ ከጸለዩ በኋላ በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም አጠመቋቸው፡፡ ያ የአውሬነት ጠባያቸውም ጠፍቶላቸው የዋህ፣ ቅንና ሩኅሩኆቸ ሆኑ፡፡ ሐዋርያትም ሃይማኖትን እያስተማሯቸው 30 ቀን አብረዋቸው ከተቀመጡ በኋላ አገልጋይ ኤጲስ ቆጶሳትን፣ ካህናትንና ዲያቆናትን ሾመውላቸው ወደ ሌላ ሀገር ሄዱ፡፡

ለሐዋርያት ሞገሳቸው ጣዕመ ስብከታቸው የኾነች ክብርት #እመቤታችን ለእኛም ትለመነን!

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኢዩኤል_ነቢይ

ዳግመኛም በዚህችም ቀን የነቢይ ኢዩኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። ይህም የእስራኤልን ልጆች የሚያስተምርና የሚገሥጻቸው ነበር ስለ #ክርስቶስም በኢየሩሳሌም መኖርና ማስተማር ትንቢት ተናገረ። ደግሞም ስለ መከራው በሐዋርያትና በሰባ ሁለቱ አርድእት በሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ላይ የ #መንፈስ_ቅዱስን መውረድ እንዲህ ሲል ተናገረ።

ከዚህ በኋላ በሥጋዊ በደማዊ ሰው ሁሉ ከመንፈሴ አሳድርበታለሁ ሴቶች ልጆቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ ትንቢትን ይናገራሉ አለቆቻችሁ ሕልምን ያልማሉ ጎልማሶቻችሁም ራእይን ያያሉ። ሁለተኛም እንዲህ አለ ያን ጊዜ ከተራራው ማር ከኮረብታውም ወተት ይፈሳል በቤተ #እግዚአብሔር አጠገብ ካሉ ከይሁዳ አገሮች ሁሉ ምንጩ ከላይ ወደታች ይፈሳል።

ሙታን በሚነሡ ጊዜ ስለሚሆነው የፍርድ ሰዓት እንዲህ አለ ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ የከዋክብትም ብርሃናቸው ይጠፋል። የትንቢቱንም ወራት አድርሶ #እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በነብዩ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አልዓዛር የማርታና የማርያም ወንድም

በዚችም ቀን ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው የቅዱስ አልዓዛር ሥጋው ከቆጵሮስ አገር የፈለሰበት ሆነ።

ከክርስቲያን ነገሥታትም አንዱ ሥጋው በቆጵሮስ እንዳለ በሰማ ጊዜ ከቆጵሮስ ደሴት ወደ ቊስጥንጥንያ አፈለሰው። ሊአፈልሱትም በወደዱ ጊዜ በከበረ የደንጊያ ሣጥን ውስጥ ሁኖ በምድር ውስጥ ተቀብሮ አገኙት በላዩም እንዲህ የሚል ጽሑፍ ነበረ ይህ በመቃብር ውስጥ አራት ቀን ከኖረ በኋላ ከሙታን ለይቶ ላስነሣው ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ወዳጁ የሆነ የቅዱስ አልዓዛር ሥጋ ነው።

ይህንንም በአዩ ጊዜ ደስ ተሰኙበት ተሸክመውም ወደ ቊስጥንጥንያ አገር ወሰዱት ካህናቱም ሁሉ ወጥተው በታላቅ ክብር በመዘመርና በማመስገን ተቀበሉት በአማረ ቦታም አኖሩት በዚችም ቀን በዓልን አደረጉለት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አልዓዛር ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_ዘኢየሩሳሌም

በዚህችም ቀን ለከበረች አገር ኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት የሆነ ቅዱስ አባት አባ ዮሐንስ #እግዚአብሔርን በሚወድ የንጉሥ ሰይፈ አርዕድ ደግሞ ቈስጠንጢኖስ ለሚባል ልጁ በሆነ በንጉሣችን በዳዊት ዘመን አረፈ።

ይህም ቅዱስ ከምስር አገር ታላላቆች #እግዚአብሔርን የሚፈሩ የክርስቲያኖች አባቶች ልጅ ነው። የዲቁና መዓረግንም ለመሾም እስከ ተገባው ድረስ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማሩ በበጎ አስተዳደግ አሳደጉት። ከዚህም በኋላ በዲቁናው ሹመት አገልግሎቱን በአሳመረ ጊዜ የቅስና መዓረግ የሚገባው ሁኖ ቅስና ተሾመ።

በጾም በጸሎት #እግዚአብሔርንም በመፍራት የተጠመደ ሁኖ ድኆችንና ችግረኞችን የሚወዳቸው የሚረዳቸው ሆነ ያን ጊዜ የሐዋርያት የሆነች የጵጵስና ሹመት የምትገባው ሁና በከበረች አገር በኢየሩሳሌም በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ ሕዝቡንም በፈሪሀ #እግዚአብሔርና በትሕትና የሚያስተምራቸው ሆነ።

እነርሱም ስለ ቅድስናው እጅግ የሚወዱት ሆኑ መልኩና የአንደበቱ አገላለጥ እንደ #እግዚአብሔር መልአክ ያማረ ነበር። በሹመቱም ጥቂት ዘመናት ከኖረ በኋላ ከመንበረ ሢመቱ እስከ አራቀው ድረስ በላዩ ሰይጣን ምክንያትን አመጣ።

ይህም እንዲህ ነው በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአባ ማርቆስ ዘመን በግዛቱ ውስጥ ያሉ እስላሞች ስለ ዐመፁበት የኢትዮጵያ ንጉሥ ፈጅቷቸው ነበርና ስለዚህ በግዛቱ ውስጥ በሚኖሩ እስላሞች ላይ ክፉ እንዳያደርግ ለኢትዮጵያ ንጉሥ መልእክት እንዲልክ ሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስን የምስር ንጉሥ አዘዘው።

አባ ማርቆስም ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥ ስለሚላኩ ሰዎች ከመኳንንቱ ከኤጲስ ቆጶሳቱና ከሀገር ታላላቆች ሽማግሌዎች ጋር ተማክሮ እሊህን ብሩሀን ከዋክብት የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስን የምስር ኤጲስቆጶስ አባ ሳዊሮስን በእውቀታቸው በአስተዋይነታቸውና በቅድስናቸው መረጡአቸው ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥም ይሔዱ ዘንድ ግድ አሏቸው።