ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#መስክረም_16

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም በአስራ ስድስት በዚህች ቀን #ከጌታችን_መቃብር_ላይ_ቤተክርስቲያን_የታነፀችበትና_የተቀደሰችበት ዕለት፣ ከንፍታሌም ነገድ የሆነ የገባኤል ልጅ #ጦቢት_ዕረፍት ነው፣ ተራ ነገርን እንዳይናገር ድንጋይ ጎርሶ የኖረ #አባ_አጋቶን_ባሕታዊ አረፈ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሕንጸታ_ለኢየሩሳሌም

መስከረም ዐሥራ ስድስት በዚች ቀን ከ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መቃብር ላይ ቤተ ክርስቲያን የታነፀችበትና የተቀደሰችበት ነው። ደግሞ በኢየሩሳሌም አገር ንግሥት ዕሌኒ የገለጠቻቸው የከበሩ ቦታዎች ሁሉ የተሠሩበትና የከበሩበት ሆነ።

ይህም እንዲህ ነው ልጇ ቁስጠንጢኖስ በነገሠ በሃያ ዓመት ቅዱሳን የሆኑ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶችን በኒቅያ ከተማ ከሰበሰበ በኋላ ቅድስት እናቱ ዕሌኒ እንዲህ አለችው ልጄ ሆይ እኔ ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም በመሔድ የክብር ንጉሥ የሆነ የ #ክርስቶስን ቅዱስ ዕፀ #መስቀል ፈልጌ አወጣ ዘንድ ለ #እግዚአብሔር ስዕለትን ተስያለሁ።

ቁስጠንጢኖስም ሰምቶ በዚህ ነገር ደስ አለው ከብዙ ሠራዊትም ጋር ብዙ ገንዘብ ሰጥቶ ላካት የከበሩ የግምጃ ልብሶችንም ሰጣት እርሷም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ ከከበሩ ቦታዎች ተባረከች። ከዚህም በኋላ ስለ ከበረና አዳኝ ስለ ሆነ ቅዱስ ዕፀ #መስቀል መረመረች በታላቅ ድካምና ችግር አገኘችውና ታላቅ ክብርን አከበረችው በታላቅ ምስጋናም አመሰገነችው።

ከዚህም በኋላ በጎልጎታ በቤተልሔምም ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በተወለደበት ዋሻ ደግሞ በጽርሐ ጽዮን የእመቤታችን #ማርያም ሥጋዋ በተቀበረበት በጌቴሴማኒ በደብረ ዘይትም በከበሩ ቦታዎች ሁሉ የቤተ መቅደስ መሠዊያ እንዲሠሩ አዘዘች። ዳግመኛም በዕንቁ በወርቅና በብር እንዲአስጌጧቸው አዘዘች።

በኢየሩሳሌምም ስሙ መቃርስ የሚባል ኤጲስቆጶስ አለ። እርሱም ንግሥት ዕሌኒን እንዲህ ብሎ መከራት ይህን እንዲህ አትሥሪ ከጥቂት ዘመናት በኋላ በዚህ አገር ሊነግሡ አሕዛብ ይመጣሉ። ሁሉን ይማርካሉ ቦታዎችንም ያፈርሳሉ ወርቁን፣ ብሩን፣ ዕንቁውን ይወስዳሉና ነገር ግን ጠንካራ የሆነ የማይናወጽና የማይፈርስ ጥሩ ሕንፃ ልታሠሪ ይገባል ከዚህ የሚተርፈውንም ለድኆችና ለችግረኞች ስጪአቸው አላት።

እርሷም የአባ መቃርስን ምክሩን ተቀብላ መኳንንቱ ሁሉ ለአባ መቃርስ በመታዘዝ በከበሩ ቦታዎች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲአንፁ አዘዘቻቸው።

ከዚህም በኋላ ንግሥት ዕሌኒ ወደ ልጅዋ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስ በተመለሰች ጊዜ በኢየሩሳሌም ያደረገችውን ሁሉ ነገረችው ሰምቶ እጅግ ደስ አለው እንደገና ሌላ ብዙ ገንዘብና ሕንፃውን ተቆጣጥረው የሚያሠሩ ሹሞችን ላከ ለሚገነቡና ለሕንፃው ሥራ ለሚአገለግሉ ሁሉ ደመወዛቸውን ሳያጓድሉ ሁል ጊዜ ወደ ማታ እንዲሰጧቸው ንጉሡ አዘዘ። ስለ ደመወዛቸው እንዳይጮኹና እንዳያዝኑ #እግዚአብሔርም ስለ ጩኸታቸው በእርሱ ላይ እንዳይቆጣ ይፈራልና።

ጻድቅ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስም በነገሠ በ፴ ዓመቱ የከበሩ ቦታዎች ሕንፃቸው በተፈጸመ ጊዜ ንዋየ ቅዱሳትን ዋጋቸው ብዙ ድንቅ የሆነ የከበሩ የግምጃ ልብሶችንም ላከ።

ደግሞም ወደ ቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ኤጲስቆጶሳቶቹን በመያዝ እንዲዘጋጅ እንዲሁም ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳትና ወደ እስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ አትናቴዎስ ኤጲስቆጶሳቶቹን በመያዝ ሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ኢየሩሳሌም ተሰብስበው በከበሩ ቦታዎች ውስጥ የተሠሩትን ወይም የታነፁትን አብያተ ክርስቲያናት እንዲያከብሩ።

ንጉሡም እንዳዘዘ ሁሉም ተሰበሰቡ እስከ መስከረም ወር ዐሥራ ስድስት ቀን ኑረው በዚች ቀን ሁሉንም አብያተ ክርስቲያናት መሠዊያቸውንም አከበሩአቸው የቁርባን ቅዳሴንም ቀድሰው ለምእመናን ሥጋውንና ደሙን አቀበሉ በዚችም ቀን ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታን ሆነ።

የከበረ #መስቀልንም በመሸከም በነዚያ በከበሩ ቦታዎች ዞሩ በውስጣቸውም ለ #እግዚአብሔር ሰገዱ አመሰገኑትም #መስቀሉንም አከበሩት ወደ ሀገሮቻቸውም በሰላም በፍቅር ተመልሰው ገቡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በ #መስቀሉ ኃይልም ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጦቢት_ነቢይ

በዚችም ቀን በፋርስ ንጉሥ አሜኔሶር እጅ ተማርኮ ወደ ነነዌ አገር የተወሰደ ከንፍታሌም ነገድ የገባኤል ልጅ ጦቢት አረፈ። ይህም ጻድቅ ጦቢት በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ዕውነትና ቅን በሆነ ሕግ ጸንቶ የሚኖር ነው ከወገኖቹም ጋር ከመማረኩ በፊት ለችግረኞች ብዙ ምጽዋትን ይሰጥ ነበር ብዙ ጊዜም የበጎቹን ጠጉርና ከእህሉ ዐሥራቱን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጣ ነበር ከገንዘቡም ከሦስት አንዱን ለድኆች የሚሰጥ ነው።

በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ሁሉም ክደው በዓልና ደማሊ ለሚባሉ ጣዖታት ይሠው ነበር ። ወገኖቹም ወደ ነነዌ በተማረኩ ጊዜ ሁሉም የአሕዛብን እህል በሉ እርሱ ግን ሰውነቱን ይጠብቅ ነበር የአሕዛብን መብል እንዳይበላ #እግዚአብሔርን ያስበው ነበርና።

በአንዲት ዕለትም በአደባባይ የወደቀ በድን አግኝተው ነገሩት ወዲያውኑ እህል ሳይቀምስ ተነሥቶ ሔደ ፀሐይም እስከሚገባ ወደ አንድ ቤት ውስጥ አስገብቶ አኖረው ፀሐይ ሲገባም ቆፍሮ ቀበረው በዚያች ሌሊትም እንደ ኃጢአተኛ ሁኖ በእድሞ ሥር ተኝቶ አደረ። በእድሞውም ላይ ወፎች መኖራቸውን ስለ አላወቀ ፊቱን ገልጦ ሳለ ኩሳቸውን ከዐይኖቹ ላይ ጣሉበት ዓይኖቹም ተቃጠሉ ከእሳቸውም ጢስ ወጣ ታወሩም ባለመድኃኒትም ሊያድነው አልቻለም።

በዚያንም ጊዜ ጦቢት ወደ #እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ለመነ አቤቱ በቸርነትህ አስበኝ ወደ ችግረኛነቴም ተመልከት ለመማረክና ለመዘረፍ በአደረግኸን በእኔና በአባቶቼ ኃጢአት ተበቅለህ አታጥፋኝ። አሁንም በፊትህ ደስ የሚያሰኝህን ነገር አድርግ ከመኖር ሞት ይሻለኛልና በሞት እሰናበት ዘንድ አፈርም እሆን ዘንድ ነፍሴን የሚቀበል መልአክን እዘዝ።

በዚያችም ዕለት የራጉኤል ልጅ ሣራን በጭኗ ያደረ ክፉ አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን ለሰባት ባሎች አጋብተዋት ወደርሷ ሲገቡ ሁሉንም ስለገደላቸው ስለዚህ የአባቷ አገልጋዮች ያሽሟጥጧት ነበርና ከሽሙጣቸው ያድናት ዘንድ እያለቀሰች ወደ #እግዚአብሔር ትለምን ነበር ጸሎቷና የጦቢት ጸሎትም በልዑል #እግዚአብሔር በጌትነቱ ልዕልና ፊት ተሰማ።

ጦቢትም በገባኤል ዘንድ አደራ ያስጠበቀውን የብሩን ነገር አሰበ ልጁ ጦብያንም ጠርቶ ሳልሞት በገባኤል ዘንድ አደራ ያስጠበቅሁትን ብር ትቀበል ዘንድ ከአንተ ጋራ የሚሔድ በደመወዝ የሚቀጠር አሽከር ፈልግ አለው።

ጦብያም አባቴ ሆይ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ ከዚህም በኋላ አሽከር ሊፈልግ ሔደ ቅዱስ ሩፋኤልንም አሽከር በሚሆን ሰው አምሳል አገኘው እርሱም ከጦብያ ጋር መጣ ስሙንም አዛሪያ ነኝ አለ ጦቢትም ላካቸው። ሲሔዱም በመሸ ጊዜ ወደ ጤግሮስ ወንዝ ደረሱ ጦብያም ገላውን ይታጠብ ዘንድ ወረደ። ታላቅ ዓሣም ሊውጠው ተወረወረ ሩፋኤልም ጦብያን ዓሣውን ያዘው አትፍራው እረደውና ጉበቱን፣ ልቡንና፣ አሞቱን ያዝ አለው እርሱም እንዳዘዘው አደረገ።

ጦብያም ቅዱስ ሩፋኤልን አንተ ወንድሜ አዛርያ ይህ የዓሣ ሐሞት ጉበቱና ልቡ ምን ይደረጋል አለው። አዛርያ የተባለ መልአክም እንዲህ ብሎ መለሰለት ጋኔን ያደረበት ሰው ወንድ ወይም ሴት ጉበቱንና ልቡን ከደቀቀ ዕጣን ጋራ ያጤሱለት እንደሆነ ጋኔን ይሸሻል ሐሞቱም ዐይኖቹ የታወሩ ሰውን ቢኩሉት ይድናል።
#መስከረም_18

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም አስራ ስምንት በዚህች ቀን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ #አቡነ_ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር፣ የደብረ ጽጋጉ #አቡነ_አኖሬዎስ፣ ሰማዕቱ #ቅዱስ_መርቆሬዎስ_ካልዕ#የአቡነ_ያዕቆብ_ግብፃዊ ዕረፍታቸው ነው። ዳግመኛም ይህች ዕለት ሐዋርያው #ቅዱስ_ቶማስ በሕንድ አገር ድንቅ ተአምር ያደረገባት ዕለት ናት፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኤዎስጣቴዎስ_ከፋሌ_ባህር

መስከረም ዐሥራ ስምንት በዚች ቀን ወንጌልን የሚሰብክ የሃይማኖት መምህር አባታችን ኤዎስጣቴዎስ አረፈ ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ክርስቶስ ሞዓ የእናቱ ስም ስነ ሕይወት ይባላል ሁለቱም ደጋጎች #እግዙአብሔርን የሚፈሩና በሕጉ ጸንተው የሚኖሩ ነበሩ።

ከዘህም በኋላ በከበረ መልአክ በቅዱስ ገብርኤል አብሣሪነት ይህን ቅዱስ ወለዱት ስሙን የጌታ ጥብቅ ብለው ሰየሙት ። በአደገም ጊዜ የዳዊትን መዝሙርና የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍትን አስተማሩት ።

ከዚህም በኋላ የእናቱ ወንድም አባ ዘካርያስ ወደአለበት የመነኰሳት ገዳም ወሰዱት ። አባ ዘካርያስም የ #እግዚአብሔርን ጸጋ እንዳደረችበት አውቆ የምንኩስናን ሥርዓት አስተምሮ የመላእክትን አስኬማ አለበሰው ። ከገድሉ ጽናት የተነሣ በገዳም ያሉ አረጋውያን እስኪያደንቁ ድረስ በጾም በጸሎት የተጠመደ ሆነ እርሱ በጥበብና በዕውቀት የጸና ነውና ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ዲቁና ተሾመ የዲያቆናት አለቃ እንደሆነ እስጢፋኖስም ለቤተ ክርስቲያን አገለገለ ።

ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከሚካኤልና ከገብርኤል ጋር ተገለጠለትና ሰላምታ ሰጠው በንፍሐትም #መንፈስ_ቅዱስን አሳደበረት እንዲህም አለው ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ ሆይ እኔ ከእናትህ ማሕፀን መረጥኩህ ያለ ፍርሀትና ድንጋፄ ወንጌልን ለብዙዎች ሕዝቦች ትሰብክ ዘንድ ከኢትዮጵያ እስከ አርማንያ ድረስ መምህር አደረግሁህ አንተን የሰማ እኔን ሰማ አንተን ያልሰማ እኔን አልሰማም #ጌታችንም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ በክብር ዐረገ ።

ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስም ወደ ጳጳስ ሒዶ ቅስና ተሾመ የወንጌልንም ሃይማኖት ይሰብክ ዘንድ ጀመረ ብዙ ሰዎች ወደ ርሱ እስቲሰበሰቡ ድረስ በእርሱም እጅ መንኩሰው ደቀ መዛሙርትን ሆኑት ከእርሳቸውም ታላቁ አባ አብሳዲ ነው ።

ብዙዎችንም የከፋች ሥራቸውን አስትቶ ከክህደታቸው መለሳቸው ትምህርቱም በሀገሩ ሁሉ ደረሰ በመላ ዘመኑም የሰንበታትና የበዓላት አከባበር የጸና ሁኖ ተሠራ ከሐዋርያትም ሕግና ሥርዓት ወደቀኝም ሆነ ወደ ግራ ሁሉም ፈቀቅ አላሉም ።

ወደ ኢየሩሳሌምም ሁለት ጊዜ ሔደ #እግዚአብሔርም በእጆቹ የዕውራንን ዐይኖች በማብራት አንካሶችንና ጎባጦችን በማቅናት አጋንንትን በማስወጣት ቁጥር የሌላቸው ተአምራትን አደረገ ።

ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ለመሔድ በአሰበ ጊዜ ልጆቹን ሰብስቦ የመነኰሳትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ከመናፍቃንም ጋር እንዳይቀላቀሉ አማፀናቸው ። ልጁ አብሳዲንም በእነርሱ ላይ ሾመውና ወደ ኢየሩሳሌም ሰንበትን እያከበረና የ #ክርስቶስን ሃይማኖት እያስተማረ ሔደ ። ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚንም ደርሶ ከእርሱ ቡራኬ ተቀበለ የሃይማኖትንም ነገር ተነጋገሩ ዳግመኛም ከከበሩ ቦታዎች በመሳለም በረከትን ተቀበለ በዮርዳኖስም ተጠመቀ ።

ከዚያም ወደ አርማንያ ሔደ ወደ ኢያሪኮ ባሕርም ሲደርስ በመርከባቸው ያሳፍሩት ዘንድ መርከበኞችን ለመናቸው በከለከሉትም ጊዜ ዓጽፉን በባሕሩ ላይ ዘረጋ በ #ቅድስት_ሥላሴ ስም በላዩ ባረከ ራሱንም በ #መስቀል ምልክት አማተበ እንደ መርከብም ሁኖለት በላዩ ተጫነ ሁለት መላእክትም ቀዛፊዎች #ጌታችንም እንደ ሊቀ ሐመር ሆኑለት ። ከባሕሩም ግርማ የተነሣ እንዳይፈሩ ልጆቹን አጽናናቸው ። ግን እንዲህ አላቸው ልጆቼ በልባችሁ ቂምንና ሽንገላን እንዳታኖሩ ተጠበቁ ለኔ ግን ከእናንተ አንዱ አንደ ሚጠፋ ይመስለኛል ይህን ሲናገር ልቡ የቂም የበቀል ማከማቻ ስለሆነ ወዲያውኑ አንዱ ከእነርሱ መካከል ሠጠመ ።

#እግዚአብሔርም ፈቃድ ባሕሩን ተሻግሮ ወደ አርማንያ ከተማ ደርሶ ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር ተገናኘ ሰገደለትም ከእርሱም ቡራኬን ተቀበለ ሊቀ ጳጳሱም በአየው ጊዜ ታላቅ ደስታን ደስ አለው በፍቅርም ተቀበለው ።

አባታችን ኤዎስጣቴዎስም ሁሉም በትመህርቱ አንድ እስከሆኑ ድረስ የአርማንያን ሰዎች ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው የሠሩትን ሥርዓት እያስተማራቸው ኖረ ።

ከዚህም በኋላ ዕረፍቱ ሲደርስ ክብር ይግባውና #ጌታችን ተገለጠለትና ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ገድሉንም ለሚጽፍ ቃል ኪዳንን ሰጠው ። በአረፈም ጊዜ ጳጳሳትና ካህናት በታላቅ ክብር ገንዘው በሰማዕቱ በቅዱስ መርምህናም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀበሩት ። ከሥጋውም ብዙ ተአምራት ተገለጡ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_አኖሬዎስ_ትልቁ

በዚችም ቀን የደብረ ጽጋግ መምህር አባ አኖሬዎስ አረፈ።

"አኖሬዎስ ትልቁ" መባላቸው "ትንሹ አኖሬዎስ" በሚል ስያሜ የተጠሩ ሌላ ጻድቅ አሉና ነው፡፡ ይኸውም ታላቁ አቡነ አኖሬዎስ አባታቸው ዘርዐ ሃይማኖት ወይም ዘርዐ አብርሃም እናታቸው ደግሞ ክርስቶስ ዘመዳ ይባላሉ፡፡ አቡነ አኖሬዎስ ታላቁ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ ሕፃን ሞዐ፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ አቡነ ዜና ማርቆስና አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋር እነዚህ ሁሉም የወንድማማቾች ልጆች ናቸው፡፡

እነኚህ ደጋግ ቅዱሳን በእናትም የእኅትማማቾች ልጆች ናቸው፡፡ ማለትም የአኖሬዎስ ታላቁ እናት ክርስቶስ ዘመዳ፣ የሕፃን ሞዐ እናት ትቤ ጽዮን፣ የንጉሡ የዐፄ ይኮኖ አምላክና የማርያም ዘመዳ እናት እምነ ጽዮን እኅትማማቾች ናቸው፡፡ እነዚህም ሦስቱ እኅትማማቾች (እምነ ጽዮን፣ ትቤ ጽዮንና ክርስቶስ ዘመዳ) መድኃኒነ እግዚእ የሚባል አንድ ወንድም አላቸው፡፡ እርሱም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት እናት የቅድስት እግዚእ ኀረያ አባት ነው፡፡ ማርያም ዘመዳም አቡነ ዜና ማርቆስንና ማርያም ክብራን ወልዳለች፡፡ ማርያም ክብራም ትንሹን አኖሬዎስን ወልዳለች፡፡ ታላቁ አቡነ አኖሬዎስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካረፉ በኋላ ወደ ትግራይ በመሄድ ፀዓዳ ዓንባ ከተባለ ቦታ ገዳም መሥርተዋል፡፡

ግብፃዊው አቡነ ያዕቆብ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የደብረ ሊባኖሱን እጨጌ አቡነ ፊልጶስን አስጠርተው ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት “ኢትዮጵያ በአንድ ጳጳስ መወሰን የለባትም፡፡ ስለዚህ ዐሥራ ሁለት አበው መርጠን ክርስትና ይስፋፋ” ብለው ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘሞረት፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋር፣ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘወረብ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፣ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘግድም፣ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመርሐ ቤቴ፣ አቡነ አድኃኒ ዘዳሞት፣ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል፣ አቡነ ኢዮስያስ ዘወጅ፣ አቡነ ዮሴፍ ዘእናርያን መርጠው ሀገረ ስብከት ተሰጥቷቸው ለሐዋርያዊ ተልእኮ ተሠማሩ፡፡ እነዚህ ዐሥራ ሁለቱን ንቡራነ ዕድ ለስብከተ ወንጌል በመላዋ አገሪቱ ሲሠማሩ ለአቡነ አኖሬዎስ እንደ ግብጦን የተባለ ቦታ ደረሳቸው፡፡ ይህም ቦታ ከግንደ በረት እስከ ባሌ ያለውን አገር ያካትታል፡፡ እርሳቸውም ሰባት ታቦታት ይዘው በመሄድ አብያተ ክርስቲያናት ተክለው ክርስትናን አስፋፍተዋል፡፡ በአካባቢው ስብከተ ወንጌልን ካስፋፉ በኋላ ባርጋባን የተባለ የአካባቢው ሰው ተአምራታቸውንና ትምህርታቸውን ተመልክቶ በጽጋጋ
#መስከረም_20

#ቅዱስ_አትናቴዎስ_ካልዕ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ በዚች ቀን ለሊቃነ ጳጳሳት ሃያ ስምንተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባት አትናቴዎስ አረፈ፣ በተጨማሪ በዚች ቀን#ቅድስት_ድንግል_መሊዳማ በሰማዕትነት ያዐረፈችበት፣ #የድንግል_አቴና#የፊና_የፊላ፣ የመነኰስ #አብርሃም_የታዴዎስ_የአቢናፍንዮስ#የጻድቁ_አርማንዮስ#የኢየሩሳሌም፣ ኤጲስቆጶሳት አለቃ ሰማዕት የሆነ #የስምዖን መታሰቢያቸው ነው።

#ቅዱስ_አትናቴዎስ_ካልዕ

ይህም አባት አስቀድሞ የእስክንድርያ አገር ቤተክርስቲያን መጋቢ ነበር ከእርሱም በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጴጥሮስ በአረፈ ጊዜ ይህን አባት ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ ሁሉም ኤጲስቆጶሳት መኳንንቱና ሊቃውንቱ ሕዝቡም በአንድ ምክር ተስማሙ በ #እግዚአብሔር ሕግ በመጽናት ያደረገው መልካም ተጋድሎውና ቅድስናው ስለርሱ ስለተነገረ መንፈስ ቅዱስም እንደ አደረበት ስለ ተረዱ ያለ ፈቃዱም ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።

ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና የ #ክርስቶስን መንጋዎች በምክሩ፣ በትምህርቱ፣ በጸሎቱ ከዲያብሎስ ተኵ*ላዎች በመልካም አጠባበቅ ጠበቃቸው እሊህም ሃይማኖትን የሚለውጡ መና*ፍቃን ናቸው።

በሊቀ ጵጵስናውም ፯ት ዓመት ኖረ #እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_20)
በዚችም ቀን ቅዱስ ቆጵርያኖስና ድንግሊቱ ዮስቴና በሰማዕትነት አረፉ። ይህም ቅዱስ ቆጵርያኖስ አስቀድሞ ከሀ*ዲና ሥራ*የኛ ነበር እርሱም ለሥራ*የኞች ሁሉ አለቃቸው ነው።

በሥራ*ዩም ሥራ ከመመካቱ ብዛት የተነሣ በሥ*ራይ የሚበልጠው ካለ ሊያይና ከዚያ ሊማር ከሌለ ግን በእነርሱ ላይ ሊመካባቸው ወደ አንጾኪያ አገር ሔደ።

ቆጵርያኖስም ወደ አንጾኪያ ከተማ በደረሰ ጊዜ ወሬው ተሰማ በአንጾኪያም ከተማ ከሀገር ታላላቆች ተወላጅ የሆነ አንድ ጐልማሳ አለ እርሱም ላህይዋ የሚያምር አንዲቷን ድንግል ብላቴና ተመኛት ወደ ቤተ ክርስቲያን በምትሔድ ጊዜ እያያት በእርሷ ፍቅር ልቡ እንደ እሳት ተቃጠለ በምንም በምን ሊአገኛት አልተቻለውም ገንዘብ በመስጠትም ቢሆን ወይም በማስፈራራት ወይም በሥ*ራይ ሥራ አልሆነለትም።

የቆጵርያኖስም ወሬው በተሰማ ጊዜ እርሱ ከሥራ*የኞች ሁሉ እንደሚበልጥ ስለርሱ ተነግሮአልና ያም ድንግል ዮስቴናን የተመኛት ጐልማሳ ወደ ቆጵርያኖስ ሒዶ በልቡ ያለውን ጉዳዩን ድንግሊቱን ዮስቴናን እንደተመኛትና እርሷን ማግኘት እንደተሳነው ነገረው ቆጵርያኖስም እኔ የልብህን ፍላጎት እፈጽምልሃለሁ አትዘን አለው።

ከዚያም በኋላ ያን ጊዜ ዮስቴናን ወደርሱ ያመጧት ዘንድ በሥራ*ዩ የአጋንንትን ሠራዊት ወደርሷ ላከ እነዚያም አጋንንት ወደርሷ በቀረቡ ጊዜ እርሷን መውሰድ አልቻሉም ከጸሎቷ የተነሣ ይቃጠላሉና እንዲህም ብዙ ጊዜ ላካቸው ግን ወደርሱ ሊያመጧት አልቻሉም ቆጵርያኖስም ሁሉንም አጋንንት ጠርቶ ድንግል ዮስቴናን ካላመጣችሁልኝ እኔ ከእናንተ ተለይቼ ክርስቲያን እሆናለሁ አላቸው።

ከዚህም በኋላ የሰይጣናት አለቃ ሊሸነግለው አሰበ አንዱንም ሰይጣን ከሰይጣናት ውስጥ በዮስቴና አምሳል ተመስሎ ለቆጵርያኖስ እንዲታየው አደረገ። ሰይጣኑም አለቃው እንዳዘዘው እንዲህ አድርጎ ተዘጋጀ እነሆ አሁን የዮስቴናን መምጣት ለቆጵርያኖስ ነገረው እርሱም እውነት መስሎት እጅግ ደስ አለው ሊቀበላትም ተነሣ። በእርሷ አርአያ የተመሰለውንም ምትሐት በአየ ጊዜ የሴቶች እመቤት ዮስቴና መምጣትሽ መልካም ሆነ አለ ይህንንም ስሟን በጠራ ጊዜ ያ በእርሷ አምሳል የተመሰለ ሰይጣን እንደ ጢስ ሁኖ ተበተነ።

በዚያንም ጊዜ የሽንገላው ምክንያት ምትሐ*ቱም ከንቱ እንደሆነ ቆጵርያኖስ አወቀ አስተዋለም በልቡም እንዲህ አለ። ስሟን በጠሩበት ቦታ እንደ ጢስ የሚበተኑ ከሆነ በፊቷ ሊቆሙ ሊሸነገሏትስ እንዴት ይቻላቸዋል ይህንንም ብሎ ወዲያውኑ የጥን*ቆላ መጻሕፍቶቹን አቃጠለ።

ከዚህም በኋላ ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን ተጠምቆ የምንኲስና ልብስን ለበሰ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ዲቁና ሾመው። ዳግመኛም ቅስና ሾመው በትሩፋት ሥራና በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ለሀገሩ ምዕራብ ለሆነች ቅርጣግና ለምትባል አገር ኤጲስቆጶስ ይሆን ዘንድ ተገባው ያን ጊዜም ቅድስት ዮስቴናን ወስዶ ለደናግል ገዳም እመ ምኔት አደረጋት።

በቅርጣግናም የቅዱሳን የአንድነት ስብሰባ በሆነ ጊዜ ከጉባኤው አባላት እርሱ አንዱ ነው።

ከብዙ ወራት በኋላም ከሀ*ዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ስለእነርሱ ሰማ ወደርሱም አስቀረባቸውና የክብር ባለቤት #ክርስቶስን ክደው ለጣዖቶቹ እንዲሰግዱ አዘዛቸው። ትእዛዙንም ባልሰሙ ጊዜ ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው ብዙ ሥቃይንም ከአሠቃያቸው በኋላ የቅዱስ ቆጵርያኖስንና የቅድስት ደንግል ዮስቴናን የሦስት ወንዶችንም ራሳቸውን አስቆረጠ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም_21 እና #ማኅበረ_ቅዱሳን_ድረገጽ)
#መስከረም_22

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ ሁለት በዚህች ቀን የፋርስ ንጉሥ የሳቦር ልጆች #የከበሩ_ኮቶሎስና_እኅቱ_አክሱ#የከበረ_ዮልዮስ በሰማዕትነት ያረፉበት መታሰቢቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኮቶሎስና_እኅቱ_ቅድስት_አክሱ

መስከረም ሃያ ሁለት በዚች ቀን የፋርስ ንጉሥ የሳቦር ልጆች የከበሩ ኮቶሎስና እኅቱ አክሱ በሰማዕትነት አረፉ።

ለቅዱስ ኮቶሎስም ጣጦስ የሚባል ክርስቲያን ወዳጅ አለው ይህም ንጉሥ ሳቦር እሳትን የሚያመልክ ነው ብዙዎች ምእመናንን ስለሚያሠቃያቸው ክብር ይግባውና የ #ክርስቶስን ስም ይጠራ ዘንድ በዚያ ወራት የደፈረ የለም።

ይህም ጣጦስ በአንዲት አገር ላይ ገዥ ነበር እርሱ ክርስቲያን እንደሆነ በንጉሡ ዘንድ ወነጀሉት። ንጉሡም ስለርሱ የተነገረው እውነት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያረጋግጥ ዘንድ ሌላውን መኰንን ወደርሱ ላከ። ሁለተኛም ክርስቲያንን ያገኘ እንደሆነ ጽኑዕ ሥቃይ እንዲያሠቃይ አዘዘው።

የንጉሥ ልጅ ኮቶሎስም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ወዳጁ ጣጦስ ወደአለባት ወደዚያች አገር ሔደ ያ መኰንንም በደረሰ ጊዜ ጣጦስን በንጉሥ እንደ ወነጀሉት እንዲሁ ክርስቲያን ሁኖ አገኘው በዚያን ጊዜም የእሳት ማንደጃ ሠርተው ጣጦስን እንዲአቃጥሉት አዘዘ ቅዱስ ጣጦስ ግን በ #መስቀል ምልክት በእሳቱ ላይ አማተበ እሳቱም የኋሊት ተመልሶ ጠፋ።

ኮቶሎስም ይህን ተአምር በአየ ጊዜ እጅግ አድንቆ ጣጦስን ወንድሜ ሆይ ይህን ሥራይ እንዴት ተማርክና አወቅህ አለው። ጣጦስም ይህ ከሥራይ አይደለም ክብር ይግባውና ከ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖት ይህ ድንቅ ተአምር እንጂ ብሎ መለሰለት።

ኮቶሎስም እኔ በ #ክርስቶስ የማምን ከሆንኩ እንደዚህ ልሠራ እችላለሁን? አለው ጣጦስም እንዲህ ብሎ መለሰለት በእርሱ ካመንክበት ከዚህ የሚበልጥ ተአምራት ታደርጋለህ።

በዚያንም ጊዜ ቅዱስ ኮቶሎስ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመነ በዚያን ጊዜም ነበልባሉ እጅግ ከፍ ከፍ እስከሚል እሳቱን አነደዱ ቅዱስ ኮቶሎስም ቀረብ ብሎ በእሳቱ ላይ በ #መስቀል ምልክት አማተበ እሳቱም ወደ ኋላ ዐሥራ ሁለት ክንድ ተመለሰና ጠፋ።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ወደ ንጉሥ ሳቦር ከመኰንኑ ከጣጦስና ከልጁ ከኮቶሎስ የሆነውን ሁሉ ጻፈ ንጉሡም ሰምቶ ጭፍራ ልኮ አስቀረባቸው የቅዱስ ጣጦስንም ራሱን በሰይፍ ቆረጠውና የሰማዕትነትን አክሊል ተቀበለ።

ልጁን ቅዱስ ኮቶሎስን ግን ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየውና ደግሞ እንዲአሠቃየው ለሌላ መኰንን ሰጠው እርሱም ብዙ ካሠቃየው በኋላ አሠረው። እኅቱም አክሱ ወደ እሥር ቤት ወደርሱ መጣች ወደ ቀድሞ ሥራው እንዲመለስ ትሸነግለው ዘንድ አባቷ ልኳታልና። እርሱ ግን እኅቱን ገሠጻት መከራት የቀናች ሃይማኖትንም አስተማራት ያን ጊዜም ከስኅተቷ ተመልሳ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመነች።

ከዚህም በኋላ ወንድሟ ቅዱስ ኮቶሎስ ወደ አንድ ቄስ ላካት እርሱም የክርስትና ጥምቀትን በሥውር አጠመቃት። ወደ አባትዋም ተመልሳ እንዲህ አለችው አባቴ ሆይ ለእኔና ለወንድሜ ለኮቶሎስ የሆነው ላንተ ቢደረግልህ ይሻልሃል ክብር ይግባውና ሰማይና ምድርን በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ ከፈጠረ ከ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለምና።

ይህንንም ነገር አባቷ ከእርሷ በሰማ ጊዜ በእርሷ ላይ እጅግ ተቆጥቶ ነፍሷን በ #እግዚአብሔር እጅ እስከ ሰጠች ድረስ ጽኑዕ ሥቃይን እንዲአሠቃዩአት አዘዘ በዚህም ምስክርነቷን ፈጽማ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለች።

ወንድሟን ቅዱስ ኮቶሎስን ግን በፈረሶች ጅራት ውስጥ አሥረው በተራራዎች ላይ አስሮጧቸው ሥጋውም ተቆራርጦ ተበተነ ነፍሱንም በፈጣሪው እጅ ሰጠ። የቀረ ሥጋውንም ወደ ሦስት ቆራርጠው የሰማይ ወፎች ይበሉት ዘንድ በተራራ ላይ ጣሉት በእንደዚህም ሁኔታ ምስክርነቱን ፈጽሞ የሕይወት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ወታደሮችም ሲመለሱ የሰማዕታትን ሥጋ ይወስዱ ዘንድ በሀገር አቅራቢያ ያሉ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን #እግዚአብሔር አዘዛቸው እነርሱም በሌሊት ሔደው የቅዱሳን ሰማዕታትን ሥጋቸውን ወስደው በታላቅ ክብር ገነዙአቸው እንደ በረዶም ነጭ ሁነው አግኝተዋቸዋልና። የመከራው ወራትም እስቲፈጸም ድረስ በመልካም ቦታ አኖሩአቸው።

ከዚያም በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ተሠርታላቸው የቅዱሳን ሥጋቸውን በዚያ አኖሩ ከሥጋቸውም ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮልዮስ_በሰማዕትነት

በዚችም ቀን የከበረ ዮልዮስ በሰማዕትነት ያረፈበት መታሰቢያው ነው። ይህም ቅዱስ አቅፋሐስ ከሚባል አገር ነው ክብር ይግባውና #ጌታችንም ስለ ቅዱሳን ሰማዕታት ለሥጋቸው እንዲአስብ ገድላቸውንም እንዲጽፍ ሥጋቸውንም ገንዞ እየአንዳንዱን ወደ ሀገራቸው እንዲልክ ያቆመው ነው።

#እግዚአብሔርም በመኳንንቱ ልብ መታወርን ስለ አመጣ ለሰማዕታት ይህን ያህል በጎ ሥራ ሲሠራ ምንም ነገር አይናገሩትም ስለ ጣዖት አምልኮም አያስገድዱትም ነበር። ጽሕፈትም የሚያውቁ ሦስት መቶ አገልጋዮች አሉት እነርሱም የሰማዕታትን ገድላቸውን እየተከታተሉ ይጽፋሉ።

በመሠቃየትም ሳሉ ሰማዕታትን ያገለግላቸዋል በቊስላቸውም ውስጥ መድኃኒት ያደርግላቸዋል ሰማዕታትም ይመርቁታል እንዲህ ብለውም ትንቢት ይናገሩለት ነበር። አንተም ክብር ይግባውና ስለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ደምህ ይፈስ ዘንድ አለህ ከቅዱሳን ሰማዕታትም ጋራ ትቈጠራለህ።

የከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ የግዛቱ ዘመን በተፈጸመ ጊዜ ዮልዮስን ከቅዱሳን ሰማዕታት ከቁጥራቸው አንድ ሊአደርገው ወዶ ቅዱሳን ሰማዕታትም ትንቢት እንደተናገሩለት በመኰንኑ ፊት ስለ ከበረ ስሙ ይታመን ዘንድ ለግብጽ አገር ደቡብ ወደሆነች ወደ ገምኑዲ ወደ መኰንኑ አርማንዮስ እንዲሔድ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አዘዘው።

ወዲያውኑ ተነሥቶ ሔደ ከዚያም ደርሶ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ታላቅ ሥቃይን ብዙ ጊዜ አሠቃየው #እግዚአብሔርም ያለ ጥፋት በጤና ያነሣው ነበር። ከዚህም በኋላ ምድር አፍዋን ከፍታ ጣዖታቱን ትውጣቸው ዘንድ ቅዱስ ዮልዮስ ክብር ይግባውና ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ ወዲያውኑ አፍዋን ከፍታ ሰብዓ ጣዖታትን መቶ ሠላሳ የሆኑ ካህናቶቻቸውን ዋጠቻቸው።

በዚያንም ጊዜ ቅዱስ ዮልዮስን አምጥተው ለአማልክት በግድ እንዲአሰግዱት መኰንኑ አዘዘ ጣዖታቱን ግን ከካህናቶቻቸው ጋር ጠፍተው አገኙአቸው በዚያ ያሉ ሕዝቦችም ይህን አይተው እጅግ አደነቁ። ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም አመኑ መኰንኑ አርማንዮስም ጣዖታቱ ከካህናቶቻቸው ጋር እንደ ጠፉ በአየ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመነ። ከቅዱስ ዮልዮስም ጋር ወደ አትሪብ ሔደው በመኰንኑ ፊት ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ታመኑ የአትሪብ መኰንን ግን ቅዱስ ዮልዮስን እጅግ ጭንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃየው ክብር ይግባውና #ጌታችንም ያለ ጥፋት ያነሣው ነበር።
#መስከረም_23

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ ሦስት በዚህች ዕለት የክርስቶስ ሙሽራው የሆነች #ቅድስት_ቴክላ መታሰቢያ በዓሏ ነው፤ ዳግመኛም #ቅዱሳን_አውናብዮስ_እና_እንድርያስ በሰማዕትነት አረፉ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ቴክላ_የክርስቶስ_ሙሽራው

መስከረም ሃያ ሦስት በዚህች ዕለት የ #ክርስቶስ ሙሽራው የሆነች ቅድስት ቴክላ የመታሰቢያ በዓሏ ነው፡፡

ይህችውም ቅድስት ለሐዋርያው ለቅዱስ ጳውሎስ ረድእ ሆና ያገለገለች ታላቅ ሐዋርያዊት እናት ናት፡፡ የመቄዶንያ ሀገር ባለጸጎች የነበሩት ወላጆቿ ጣዖት አምላኪ ነበሩና በሕጋቸውና በሥርዓታቸው አሳደጓት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደዚህች ሀገር ገብቶ ቅዱስ ወንጌልን ሰበከ፡፡ ቅድስት ቴክላም ትምህርቱን በሰማች ጊዜ በቤቷ ሆና ሳትበላና ሳትጠጣ 3 ቀን ቆየች፡፡ ከዚህም በኋላ ለሚጠብቃት ዘበኛዋ እንዳይናገርባት በማለት የወርቅ ወለባዋን ሰጠችውና ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሄደች፡፡ እርሱም በደስታ ተቀብሎ የ #ክርስቶስን ሃይማኖት አስተማራት፡፡ በማግሥቱም ቅድስት ቴክላን እናቷ ስትፈልጋት ከቅዱስ ጳውሎስ እግር ሥር አገኘቻት፡፡ ከዚያም ወደ መኰንኑ ዘንድ ሄዳ ልጇ ክርስቲያን መሆኗን በመናገር ከሰሰቻትና ለመኰንኑ አሳልፋ ሰጠቻት፡፡

መኰንኑም ሁለቱን ቅዱስ ጳውሎስንና ቅድስት ቴክላን እንዲያመጧቸው ወታደሮቹን ላከ፡፡ ካመጧቸውም በኋላ መጀመሪያ ቅዱስ ጳውሎስን ወደ እሳት ወረወሩት፡፡ ነገር ግን #እግዚአብሔር በተአምራት አዳነው፡፡ ቅድስት ቴክላን ግን ለሀገሩ ልጆች መቀጣጫ ትሆን ዘንድ መኰንኑ ሰውን ሁሉ ከሰበሰበ በኋላ ወደ እሳቱ እንዲወረውሯት አዘዘ፡፡ እርሷ ግን በ #መስቀል ሦስት ምልክት ካማተበች በኋላ በራሷ ፈቃድ ማንም ሳይነካት ዘላ ከእሳቱ ውስጥ ገባች፡፡ ነገር ግን በ #እግዚአብሔር ጥበቃ ልክ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ እርሷም ማንም ሳያያት ከእሳቱ ውስጥ ወጥታ ቅዱስ ጳውሎስ ካለበት ደረሰች፡፡ የራሷንም ጸጉር ቆርጣ በእርሱም ወገቧን ታጥቃ ቅዱስ ጳውሎስን ተከተለችው፡፡

መኰንኑም በሕይወት መኖሯን ሰምቶ ድጋሚ አስፈልጎ አስያዛትና ሃይማኖቷን እንድትለውጥ አስገደዳት፡፡ እሺ እንዳላለችው ባወቀ ጊዜ በተራቡ አንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ጨመራት ነገር ግን አንበሶቹ ሰግደው የእግሯን ትቢያ ሲልሱላት ተመለከተ፡፡ መኰንኑም ይህንን በተመለከተ ጊዜ እርሱና ወገኖቹም ሁሉ አምነው ተጠመቁና የ #ክርስቶስ መንጋዎች ሆኑ፡፡ ቅድስት ቴክላም የ #ጌታችንን ወንጌል በማስተማርና ቅዱስ ጳውሎስንም በማገልገል ብዙ ከተጋደለች በኋላ መስከረም 27 ቀን ዐርፋለች፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ቴክላ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አውናብዮስ_እና_እንድርያስ

ዳግመኛም በዚች ቀን ቅዱሳን ጻድቃን መነኰሳት አውናብዮስና እንድርያስ በሰማዕትነት አረፉ። እሊህ ቅዱሳንም ከልዳ ሀገር ከታላላቆቹ ተወላጆች ናቸው ከታናሽነታቸውም በአምላካዊ ምክር ተስማምተው በሶርያ ውስጥ ከሚገኙ ገዳማት ወዳንዱ ገዳም ሒደው መነኰሳት ሆኑ።

ከዚህም በኋላ ወደ ከበረ ወደ ተመሰገነ አባ መቃርስ ሔዱ ደቀ መዛሙርቱም ሁነው ታዘዙለት ምክሩንም በመቀበል በጾም በጸሎት በገድል ሁሉ ተጠምደው የሚኖሩ ሆኑ በእንዲህ ያለ ሥራም በዚያ ሦስት ዓመት ኖሩ በጎ የሆነ ተጋድሎአቸውና የአገልግሎታቸው ዜና በተሰማ ጊዜ አውናብዮስን መርጠው ኤጲስቆጶስነት፣ እንድርያስን ቅስና ሾሙአቸው በበጎ አጠባበቅም የ #ክርስቶስን መንጋዎች ጠበቋቸው።

ከዚህም በኋላ ሥጋቸውን ፈጽሞ እስከ አደከሙ ድረስ ተጋድሎአቸውንና አገልግሎታቸውን እጅግ አበዙ። ከሀ*ዲ ንጉሥ ዮልዮስም ስለእርሳቸው በሰማ ጊዜ ወታደሮች ልኮ ወደርሱ አስቀርቦ የክብር ባለቤት #ክርስቶስን ክደው ወደ ረከሰች አምልኮቱ እንዲገቡ አዘዛቸው ያን ጊዜ እርሱንና የረከሱ ጣዖ*ታቱን ረገሙ እርሱም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ወደ ብዙ ክፍልም ቆራርጦ ከፋፈላቸውና ነፍሳቸውን በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጡ። እያንዳንዳቸውም ሦስት ሦስት አክሊላትን ተቀበሉ አንዱ በገድል ስለ መጸመድና ስለ ምንኲስና ዋጋ፣ ሁለተኛው ስለ ክህነት አገልግሎት፣ ሦስተኛው ደማቸውን ስለ ማፍሰሳቸው ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_23)
#መስከረም_25

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ አምስት በዚች ቀን የከበረች #ቅድስት_በርባራ መታሰቢያዋ ነው፣ #ታላቁ_ነቢይ_ዮናስ እረፍቱ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ባርባራ (በርባራ) ሰማዕት

አንድ አምላክ በሚሆን በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም አሜን።
[ታኅሣሥ 8 የዕረፍት በዓሏ እና መስከረም 25 ተዓምር ያደረገችበት በዓሏ የሚከበረው ቃል ኪዳኗ ከድንገተኛ ሞት የሚጠብቀው የ #ቅድስት_በርባራ ድንቅ ታሪኳ፤ በቀደምት ኢትዮጵያውያን የቀረበላት ውዳሴና ዓለም ዐቀፍ ክብሯ]

የተቀበለችው ቃል ኪዳን ከድንገተኛ ሞት የሚጠብቀው በመላው ዓለም ከጥንት ጀምሮ የምትታወቀው ከ273-306 ዓ.ም የነበረችው ሰማዕቷ ቅድስት በርባራ Αγία Βαρβάρα, Great Martyr Barbara ከ305-311 በነገሠው በከሓዲው መክስምያኖስ (emperor Maximian) ዘመነ መንግሥት መስፍን የነበረው የዲዮስቆሮስ ልጅ ናት። እጅግ ውብ ስለነበረች ሰው እንዳያያት ጣዖት አምላኪ የነበረ አባቷ ለርሷም ለብቻዋ ሰገነት ያለው ማረፊያ ታላቅ ሕንፃ አሠርቶላት አንድ አረማዊ መምህር ብቻ ወደርሷ እንዲገባ አደረገ።

ያሠራላት ሰገነት ከፍ ያለ ስለነበር አበባዎችን ይልቁኑ በምሽት የሚያበሩትን ከዋክብት የምሽቱ አስደናቂ ግርማ እየተመለከተች መደነቅ ጀመረች። በዚህ ጊዜ እነዚህ የአባቷ ጣዖታት አስደናቂ ዓለማትን እንደማይፈጥሩ ተረዳች። በሕይወቷ የዓለማት ፈጣሪን ለማወቅና በድንግልና ሕይወት ለመኖር ወሰነች። ብዙ የጋብቻ ጥያቄን ውድቅ አደረገች። በዚህ ምክንያት አባቷ ውጪውን እንድትለምደው ከግቢ እንድትወጣ ፈቀደላት።

በዚህ ጊዜ ከክርስቲያን ሴቶች ጋር በመገናኘቷ ስለ ምስጢረ #ሥላሴ፣ የአምላክ ሰው የመሆን ምስጢርን አስረዷት። እውነተኛውን የድኅነት መንገድ በመረዳቷ ከእስክንድር ወደ ሄሊዎፓሊስ መጥቶ በነበረ ካህን በድብቅ ተጠመቀች።

በዚያ ወቅት አባቷ በመታጠቢያ ክፍሏ ላይ ደግሞ ኹለት መስኮቶችና ቅንጡ የሆነ መታጠቢያ እንዲሠሩላት ዐናጺዎችን አዘዘ፤ ርሷ ግን የ #ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት በማመኗና በመጠመቋ ምስጢረ #ሥላሴን አስባ ሦስተኛ መስኮትን እንዲጨምሩ ዳግመኛም አዳኝ የኾውን የ #መስቀሉን ምልክት በውሃ መታጠቢያው ላይ እንዲሠሩ ሐናጺዎችን አዘዘቻቸው፡፡

አባቷም ወደዚኽ ሕንጻ በገባ ጊዜ ልጁ ያሠራችውን አይቶ ዐናጺዎችን ሲጠይቃቸው፤ ይኽነን እንዲሠሩ ያዘዘቻቸው ልጁ መኾኗን ነገሩትን ርሱም “ለምን እንደዚኽ አደረግሽ” ብሎ ጠየቃት፡፡ “ወትቤሎ አእምር ወለቡ ኦ አቡየ እስመ በ #ሥሉስ ቅዱስ ይትፌጸም ኲሉ ግብር በእንተዝ አግበርኩ ሣልሲተ መስኮተ፤ ወዘንተኒ መስቀለ በአምሳለ ስቅለቱ ለ #መድኀኒነ_ኢየሱስ_ክርስቶስ” ይላል ርሷም “አባቴ ሆይ አስተውል፤ ልዩ ሦስት በኾነ በ #ሥላሴ ስም ሥራ ኹሉ ይፈጸማልና ስለዚኽ ሦስተኛ መስኮት አሠራኊ፤ ይኽም #መስቀል ዓለሙ ኹሉ በርሱ በዳነበት በ #መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ_መስቀል አምሳል ነው አንተም አባቴ ሆይ ከስሕተትኽ ተመልሰኽ የፈጠረኽን አምላክ አምልከው” በማለት ተናገረችው፡፡

አባቷም ከርሷ ይኽነን በሰማ ጊዜ በንዴት ሰይፉን መዝዞ በኋላዋ ሮጠ፤ ያን ጊዜ ሸሽታ በዐለት ውስጥ ገብታ ለጊዜው ብትሸሸግም በኋላ ግን ወደ አባቷ ተመለሰች፤ ርሱም እንድትሠቃይ ለሌላ መኰንን አሳልፎ ሰጣት፤ ርሱም እየገረፈ በጊዜው አሉ በተባሉ በታላላቅ ሥቃይን ቢያሠቃያትም የባሕርይ አምላክ #ክርስቶስን ግን አልካደችም፤ ከዚያም ብቻዋን ወደ ወህኒ ተጣለች፤ በዚያም ኾና “ #ጌታዬ አምላኬ ሆይ አትተወኝ” ብላ ጸለየች፤ በእኩለ ሌሊትም የእስር ቤቱን ደማቅ ብርሃን መላው፤ “ከአንቺ ጋር ነኝና አትፍሪ” የሚለውን የአምላክን ድምፅ ሰማች፤ ከዚያም #ጌታችን ቊስሎቿን ኹሉ ፈወሰላት፡፡

በነጋታው ቅድስት በርባራን በማርቲያኑስ ፊት አቆሟት፤ ኹሉም ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንደዳነችና ፊቷም እንደ ፀሓይ ጨረር ሲያንጸባርቅ ተመለከቱ፤ መኰንኑም “አማልክቶቻችን ስለፈወሱሽ የምስጋና መሥዋዕትን ሠዊ” አላት፤ ቅድስት በርባራም ለአገረ ገዢው “በ #ጌታዬ_በኢየሱስ_ክርስቶስ ነው የዳንኩት” አለችው፡፡ ማርቲያኑስም በቊጣ ኾኖ በአስከፊ ኹኔታ ቅድስት በርባራ እንድትሠቃይ አዘዘ፤ በዙሩያዋ ቆመው ይመለከቱ የነበሩ ሕዝቦች ርሷን ለመከላከል ምንም ቃል አልወጣቸውም፡፡

በዚያም የሂሊኦፓሊስ ነዋሪ ዮልያና የምትባል ሴት ነበረችና ቅድስት በርባራን ሲያሰቃይዋት አይታ ከርሷ ጋር በ #ክርስቶስ ስም መከራን ለመቀበል በመወሰን አብራት መከራ መቀበል ጀመረች። ሁለቱም ሰማዕታትን በምስማር ሰውነታቸውን እየወጉ ያሰቃይዋቸው ነበር። ለመዘባበት ዕርቃናቸውን በአደባባይ ሊወስዷቸው ቢሞክሩም በቅድስት በርባራ ጸሎት #ጌታ መልአኩን ልኮ በአስደናቂ መጎናጸፊያ ሰውነታቸውን ጋርዶታል።

በመጨረሻም ጨካኙ መኰንን ብዙ ዐይነት ሥቃይ ቢደርስባቸው እነዚኽ ቅዱሳት አንስት በ #ክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት እንደማይለውጡ ባየ ጊዜ አንገታቸው እንዲቈረጥ አዘዘ።

ከወታደሮቹ መኻከል አንዱ አንገታቸው ለመቊረጥ ሰይፉን መዘዘ፤ በአባቷ ወደ ተዘጋጀው ወደ መግደያው ስፍራ ይዟቸው ኼደ፤ ያን ጊዜ ቅድስት በርባራ እንዲኽ ብላ ጸለየች “ዘላለማዊ #እግዚአብሔር ሆይ ከእኔ ሞት በኋላ እኔንና መከራዬን ለሚያስቡ ኹሉ ሥጦታኽን ስጣቸው፤ ድንገተኛ ሕመምና ብርቱ (አስጨናቂ) ሞትን በእነርሱ ላይ ፈጽሞ አታምጣባቸው” አለች፡፡

ከዚያም የክብር ባለቤት #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መሻቷን ኹሉ እንደሚፈጽምላት ቃል ኪዳን ሲገባላት በሰጣት ቃል ኪዳን የሚታመኑ ኹሉ ድንገተኛ ሞት እንደማያገኛቸው ቃል ኪዳን ገባላት።

በመጨረሻም አባቷ የርሷንና የባልንጀራዋ የዮልያና አንገታቸው እንዲቈረጥ አዘዘና ታኅሣሥ 8, በ306 ዓ.ም. አንገታቸው ተቈርጦ የሰማዕትነት አክሊል ሲቀዳጁ፤ ቅድስት ዮልያናንም በኹለት ጡቶቿ በኩላብ ሰቅለው ሰይፈዋታል፡፡ በዚያን ጊዜ ከሰማይ መብረቅ ወርዶ አባቷንና ጓደኛው የኾነ መኰንን መርትያኖስን አቃጠላቸው፤ ከዚኽ የተነሣ በዓለም ባለው ሥዕሏ ላይ የመብረቅ ብልጭታ ይሣላል፡፡ ቅድስት በርባራም በዚህ ምክንያት በአማላጅነቷ ከጥንት ጀምሮ ባሉት ክርስቲያኖች ከመብረቅ አደጋና ከእሳት የምትጠብቅ እንደሆነች ይነገራል።

ያም በመታጠቢያ ቤት ውስጥ በ #መስቀል ምልክት ያሠራቸው መታጠቢያ ለታመመ ኹሉ ከርሱ በታጠበ ጊዜ የሚያድን ኾነ፤ ከዚኽም በኋላ የሰማዕታቱን ሥጋቸውን ወስደው ከከተማ ውጪ ባለች ቤተ ክርስቲያን ስሟ ገላልያ በሚባል ቦታ አኖሯቸው፤ ይኽ ሥጋቸውም በቅዱሳን ሰማዕታት በአቡቂርና በዮሐንስ በምስር አገር ባለ ቤተ ክርስቲያን ተቀመጠ፡፡

ይኽነን ተጋድሎዋን ለማዘከር በመላው ዓለም በሚሣለው ሥዕሏ ላይ ሦስት መስኮት ያለው ሰገነት፣ ዘንባባ፣ ጽዋ፣ መብረቅ፣ የሰማዕትነት አክሊል ይዛ ይታያል፡፡ በዐዲስ አበባ በምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ባሉት የግድግዳ ላይ ሥዕላት ላይ ቅድስት በርባራና ቅድስት ዮልያና ተሥለዋል። በዓለም ላይ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በስሟ የታነጹላት ሲኾን በሩሲያ ብዙዎች ቤተ ክርስቲያናት በስሟ ሲሠየሙላት አንደኛው በሞስኮ ከቅዱስ ባስልዮስ ካቴድራል አጠገብ ይገኛል::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ 8 በሚነበበው መዝገበ ቅዱሳን በሆነው ስንክሳር ላይ ቅድስት በርባራና ዮልያናን ታስባለች።
#ነቢዩ_ዮናስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“ዮናስ” ማለት “ርግብ” ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም እንደ ቅዱስ ጀሮም ትርጓሜ “ስቃይ” ተብሎም ይተረጐማል፡፡ ይኸውም ተልእኮውን የሚገልጥ ነው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ አድሮ እንደ ወጣ ኹሉ፥ የደቂቀ አዳምን ሕማም ለመሸከም መጥቶ የተሰቃየው #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ ስለዚኽ የነቢዩ ዮናስ እንዲኽ በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት መቆየት የ #ጌታችንን ሞትና ትንሣኤ በጥምቀት ተካፋዮች ለሚኾኑ ኹሉ በርግብ የተመሰለውን #መንፈስ_ቅዱስ እንደሚቀበሉና ለዚያ የተዘጋጁ እንዲኾኑ ማዘጋጀት ማለትም ማወጅ ነበር ማለት ነው /ማቴ.፲፪፡፴፱-፵/፡፡

ነቢዩ ዮናስ ነገዱ ከነገደ ይሳኮር ወገን ሲኾን አባቱ አማቴ እናቱም ሶና ይባላሉ፡፡ በአይሁድ ትውፊት እንደሚነገረው ደግሞ ዮናስ ነቢዩ ኤልያስ ከሞት ያስነሣው የሠራፕታዋ መበለት ልጅ ነው /፩ኛ ነገ.፲፰፡፲-፳፬/፡፡

ነቢዩ ዮናስ በአገልግሎት የነበረበት ዘመን በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ሲኾን መኖርያውም በገሊላ በጋትሔፈር ከተማ ነበረ /፪ኛ ነገ.፲፬፡፳፭/፡፡
ነቢዩ ዮናስ የሰሜናዊው ክፍል ማለትም የእስራኤል ነቢይ ነበር፡፡ ሲያገለግል የነበረውም ከ፰፻፳፭ እስከ ፯፻፹፬ ቅ.ል.ክ. ገደማ ነው፡፡ ከአሞጽም ጋር በዘመን ይገናኛሉ፡፡

ከእስራኤል ውጪ ወደ አሦራውያን ዋና ከተማ ወደ ነነዌ ኼዶ እንዲያስተምር በዚያ ዘመን ከነበሩት ነቢያት ብቸኛው ነው፡፡ ከዚኽም የተነሣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዮናስን “ነቢየ አሕዛብ” በማለት ይጠሩታል፡፡

ነነዌ➛ ይኽች ጥንታዊት ከተማ በጤግሮስ ወንዝ ዳር ከዛሬዋ የሞሱል ከተማ በተቃራኒ ከባግዳድ ሰሜን ምዕራብ ፫፻፶ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ነበረች፡፡ የመሠረታትም ናምሩድ ይባላል /ዘፍ.፲፡፲፩/፡፡ በኋላም ሰናክሬም የአሦር መንግሥት ዋና ከተማ አደረጋት /፪ኛ ነገ.፲፱፡፴፮/፡፡

የነነዌ ሕዝቦች መዠመሪያ ባቢሎናውያን ሲኾኑ /ዘፍ.፲፡፲፩/ አስታሮት (“የባሕር አምላክ”)የሚባል ጣዖትን ያመልኩ ነበር፡፡ ከተማይቱ በሃብቷና በውበቷ ትታወቅ ነበር፡፡ የአሦር ነገሥታትም በጦርነት የማረኳቸውን ሰዎች ያጉሩባት ስለ ነበረች “ባርያ” ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች የሚበዙባት ነበረች፡፡ ነገሥታቱ በጨካኝነታቸው፣ የብዙ ንጹሐን ዜጐችን ደም በከንቱ በማፍሰስ፣ በምርኮኞች ሞትና ስቃይ ደስ በመሰኘት እንደ መዝናኛም በመቊጠር ይታወቃሉ፡፡ ነቢዩ ናሆም “የደም ከተማ” ብሎ የጠራትም ከዚኹ የተነሣ ነው /ናሆ.፫፡፩/፡፡ ነቢዩ ዮናስ ይኽችን ከተማ ነበር ወደ ንስሐ እንዲጠራ በልዑል #እግዚአብሔር የተላከው፡፡
ነቢዩ ሶፎንያስ እንደምትጠፋ በተናገረው ትንቢት መሠረት /ሶፎ.፪፡፲፫/ በ፮፻፲፪ ቅ.ል.ክ. ላይ በባቢሎናውያን ፈርሳለች፡፡

#ትንቢተ_ዮናስ

ከብሉይ ኪዳን ኹለት መጻሕፍት ስለ አሕዛብ የሚናገሩ ናቸው፡፡ እነርሱም ትንቢተ አብድዩና ትንቢተ ዮናስ ናቸው፡፡ ትንቢተ አብድዩ ስለ ኤዶማውያን የሚናገር መጽሐፍ ሲኾን ትንቢተ ዮናስ ደግሞ ስለ ነነዌ ሰዎች ይናገራል፡፡ በትንቢተ አብድዩ አሮጌውና ደም አፍሳሹ ሰውነት (ኤዶማዊነት) ቀርቶ አዲሱና ጽዮናዊ (መንፈሳዊ) ሰው እንደሚመጣ በምሳሌ ይናገራል፡፡ በትንቢተ ዮናስ ደግሞ አሕዛብ አምነው በንስሐ እንደሚመለሱና #እግዚአብሔርም በአሕዛብ መካከል ቤተ ክርስቲያን እንደሚያቋቁም በኅብረ አምሳል ያስረዳል፡፡

አይሁዳውያን ብዙውን ጊዜ ነቢያትን ሲያሳድዱና ሲገድሉ እንደነበረ #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በዚኽ ምድር በተመላለሰበት ወራት ተናግሯል /ማቴ.፭፡፲፪፣ ፳፫፡፴፩/፡፡ ከዚኹ በተቃራኒ የነነዌ ሰዎች ማለትም አሕዛብ ግን የነቢዩ ዮናስን የአንድ ቀን ትምህርት ተቀብለው እውነተኛ ንስሐ ገብተዋል፡፡ ይኽ ደግሞ አሕዛብ #ክርስቶስን እንደሚቀበሉት፥ የገዛ ወገኖቹ የተባሉት አይሁድ ግን እንደሚክዱት የሚያስረዳ ነው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ወደ ነነዌ ላለመኼድ የኮበለለበት ምክንያትም ይኼው ነበር፡፡ ጀሮም የተባለ የጥንታዊቷ የላቲን ቤተ ክርስቲያን ሊቅ ትንቢተ ዮናስን በተረጐመበት መጽሐፉ ይኽን ሲያብራራ፡- “ነቢዩ ዮናስ የአሕዛብ በንስሐ መመለስ የአይሁድ ጥፋትን እንደሚያመለክት በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር፡፡ ስለዚኽ ወደ ነነዌ ላመኼድ የፈለገው አሕዛብን ጠልቶ አይደለም፤ የገዛ ወገኖቹ ጥፋት በትንቢት መነጽር አይቶ አልኼድም አለ እንጂ፡፡ ይኸውም ሊቀ ነቢያት ሙሴ በአንድ ስፍራ ላይ “ወዮ! እኒኽ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፤ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አኹን ይኽን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍኽ እባክህ ደምስሰኝ” እንዳለው ነው /ዘጸ.፴፪፡፴፪/፡፡ ሙሴ እንዲኽ ስለጸለየ እስራኤላውያን ከጥፋት ድነዋል፤ ሙሴም ከሕይወት መጽሐፍ አልተደመሰሰም፡፡ … ዳግመኛም ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ “ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በ #ክርስቶስ ኾኜ እውነትን እናገራለኹ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በ #መንፈስ_ቅዱስ ይመሰክርልኛል፡፡ በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ኾኑ ስለ ወንድሞቼ ከ #ክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድኾን እጸልይ ነበር” እንዳለው ነው /ሮሜ.፱፡፩-፪/፡፡… ነቢዩ ዮናስ እንግዲኽ ብቻውን ከነቢያት ተመርጦ ወደ እስራኤል ጠላቶች (ወደ አሦራውያን)፣ ጣዖትን ወደምታመልክና #እግዚአብሔር ወደማታውቅ አገር ኼዶ እንዲሰብክ መመረጡ በእጅጉ አሳዝኖታል” ይላል፡፡ ክብር ይግባውና #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም፡- “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚኽ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና” ብሏል /ማቴ.፲፪፡፵፩/፡፡

አሕዛብ አሚነ #ክርስቶስን እንደሚቀበሉና አይሁድ ከአሚነ #ክርስቶስ እንደሚወጡ የተረጋገጠው በነነዌ ሰዎች መመለስ ብቻ አይደለም፡፡ የመርከበኞቹና የመርከቢቱ አለቃ ባሳዩት እምነት፣ ፈሪሐ #እግዚአብሔርንና#እግዚአብሔር ባቀረቡት መሥዋዕትም ጭምር እንጂ፡፡ ቅዱስ ጀሮም ቅድም በጠቀስነው መጽሐፉ ላይ እንዲኽ ሲል ያክላል፡- “አይሁድ ፍርድን በራሳቸው ላይ ጨመሩ፤ አሕዛብ ግን እምነትን ገንዘብ አደረጉ፡፡ የነነዌ ሰዎች በንስሐ ወደ አምላካቸው ተመለሱ፤ የእስራኤል ሰዎች ግን ንስሐ ባለ መግባታቸውና በጠማማ መንገዳቸው ስለጸኑ ጠፉ፡፡ እስራኤል መጻሕፍትን ተሸክመው ቀሩ፤ የነነዌ ሰዎች (አሕዛብ) ግን የመጻሕፍቱን #ጌታ ተቀበሉት፡፡ እስራኤላውያን ነቢያት ነበሯቸው፤ የነነዌ ሰዎች (አሕዛብ) ግን የነቢያቱን ሐሳብና መልእክት ገንዘብ አደረጉ፡፡ የእስራኤል ሰዎች ፊደሉ ገደላቸው፤ መንፈስ ግን የነነዌን ሰዎች (አሕዛብን) አዳናቸው፡፡”

በአጠቃላይ መጽሐፉን በአራት ክፍል ከፍለን ማየት እንችላለን፡-
1, ምዕራፍ አንድን ስናነብ ነቢዩ ዮናስ ወደ ነነዌ ኼዶ እንዲያስተምር እንደታዘዘና ነቢዩም ወደ ኢዮጴ እንደ ኰበለለ፣ ከመከበኞች ጋር ተወዳጅቶ ከመርከብ ወጥቶ ሲቀመጥ ኃይለኛ ማዕበልና ሞገድ እንደተነሣ፣ ነቢዩ ዮናስ ወደ ማዕበሉ እስኪጣል ድረስም ማዕበሉ ጸጥ እንዳላለ እናነባለን፡፡ የባሕሩ ማዕበልና ሞገድ ጸጥ ያለው ነቢዩ ወደ ባሕሩ ሲጣል ነው፡፡ በኃጢአት ማዕበል የሚነዋወፀው የሕይወታችን ባሕርም ፀጥ ያለው ክብር ይግባውና #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የእኛን ባሕርይ ባሕርይ አድርጐ ሲመጣ ነው፡፡
#መስከረም_26

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ ስድስት በዚች ቀን #መጥምቁ_ዮሐንስ የተጸነሰበት፣ የዮስጦስ ልጅ #ቅዱስ_አቦሊ የስጋው ፍልሰት የሆነበት ቀን ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ_ጽንሰቱ

መስከረም ሃያ ስድስት በዚች ቀን #እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ገብርኤልን ወደ በራክዩ ልጅ ዘካርያስ ልኮት መጥምቁ ዮሐንስ ከእርሱ ስለ መወለዱ አበሠረው።

ስሙ የተመሰገነ #እግዚአብሔር ልጅን ይሰጠው ዘንድ አስቀድሞ ሁል ጊዜ በመጸለይ ወደ #እግዚአብሔር ይማልድ ነበር። ልጅ ያልወለደውን #እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ምድርን ምሉዋት ያለውን በረከት ያጣ ነው በማለት እስራኤል ይገዳደሩት ነበርና።

ልመናውንም ሰማ በቤተ መቅደስም ቁሞ ዕጣንን ሲያሳርግ መልአኩን ላከለት በከበረ ወንጌልም እንደተባለ መንገዱን ይጠርግ ዘንድ በንጉሥ #ክርስቶስ ፊት እንደሚሔድ የተነገረለት ታላቅ ነቢይ ዮሐንስ ከእርሱ መወለዱን አበሠረው።

ዘካርያስም የሰውነቱን መድከም የመውለጃውም ዘመን እንዳለፈና ፈጽሞ እንዳረጅ የሚስቱም እንዲሁ ዘመኗ እንዳለፈና ፈጽማ እንዳረጀች መካንም እንደሆነች ያውቃልና ስለዚህ ይህ ነገር እንዴት ይሆንልኛል እኔ ያረጀሁ ሽማግሌ ነኝ ሚስቴም እንዲሁ ዘመኗ አልፎ መካን ሁናለች ብሎ የ #እግዚአብሔርን መልአክ ተከራከረው።

መልአኩም እኔ ይህን ልነግርህ ከ #እግዚአብሔር ዘንድ ወዳንተ ተልኬ ነበር ልትጠራጠር ባልተገባህም ነበር አሁንም ይህ በጊዜው እስቲፈጸም ዲዳ ሁነህ መናገር ይሳንሃል ብሎ ገሠጸው። ዘካርያስም የወልደ #እግዚአብሔርን መንገድ የሚጠርግ ዮሐንስ እስከሚወለድበት ጊዜ ድረስ ዲዳ ሆነ።

በሚገረዝበትም ቀን የሕፃኑን አባት ዘካርያስን የሕፃኑን ስም ምን ብለው እንደሚሰይሙት ጠየቁት እርሱም ብራና ለምኖ ስሙ ዮሐንስ ነው ብሎ ጻፈ በዚያም ጊዜ አንደበቱ ተፈትቶ #እግዚአብሔርን አመሰገነው። ስለ ልጁ ዮሐንስም እርሱ የልዑል ነቢይ እንዲባል መንገዱንም ይጠርግ ዘንድ በ #እግዚአብሔር ፊት እንደሚሔድ ትንቢት ተናገረ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቦሊ

በዚችም ቀን የዮስጦስ ልጅ ቅዱስ አቦሊ የስጋው ፍልሰት ሆነ። ይህም ቅዱስ አቦሊ ከመንግሥት ልጆች ውስጥ ነበር ዐላውያንን ወግቶ በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስን ክብር ይግባውና #ክርስቶስን ክዶ አገኘው።

ያም አቦሊና አባቱ ዮስጦስ ሌሎችም የመንግሥት ልጆች ሁሉ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስን ሊያጠፉትና መንግሥትን ከእርሱ ሊወስዱ ችሎታ ሲኖራቸው የማታልፍ ሰማያዊት መንግሥትን አሰቡ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ አቦሊ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም አብዝቶ አባበለው። እንዲሁም አባቱ ዮስጦስንና የከበረች እናቱ ታውክልያን አባበላቸው እነርሱ ግን አልሰሙትም ልባቸው በመድኅን #ክርስቶስ ፍቅር ተነድፏልና።

ንጉሡም እነርሱን በዚያ ማሠቃየትን ፈራ ስለዚህም ከመልእክት ደብዳቤ ጋር ወደግብጽ ስሙ ኄርሜኔዎስ ወደሚባል የእስክንድርያ ገዥ ላካቸው በመልእክቱም እንዲህ አለው ዮስጦስና ሚስቱ ታውክልያ ልጃቸው አቦሊም ወደአንተ በሚደርሱ ጊዜ አባብላቸው አለዚያም እየአንዳንዳቸውን ለያያቸው።

በዚያችም ሌሊት ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ለዮስጦስና ለሚስቱ ታውክልያ ለልጃቸው አቦሊም ተገልጦላቸው አጽናናቸው ከእነርሱም የሚሆነውን ነገራቸው የጸና ቃል ኪዳንም ሰጣቸው።

ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስም በደረሱ ጊዜ ስለእነርሱ እጅግ አደነቀ እነርሱ መንግሥታቸውን ትተዋልና ክፋ ነገርንም ሊናገራቸው አልደፈረም ከምክራቸው ይመለሱ ዘንድ በለሰለሰ ቃል ሸነገላቸው እንጂ ነገር ግን አልሰሙትም።

ከዚህም በኋላ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ ለእየብቻቸው ለያያቸው ቅዱስ ዮስጦስን ወደ እንዴናው ከተማ ሚስቱን ታውክሊያን ፃ ወደ ሚባል አገር ልጃቸው አቦሊንም ብስጣ ወደ ሚባል አገር ሰደዳቸው ለእያንዳንዳቸውም የሚአገለግላቸው አንዳንድ አገልጋይ ሰጣቸው።

ቅዱስ አቦሊም ወደ ሀገር ብስጣ በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በመኰንኑ ፊት ታመነ። መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን በእሳት ቃጠሎና በመንኰራኵር አሰቃየው ሕዋሳቱንም ቆራርጦ ለአንበሶች ጣለው ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስም ከሥቃዩ ሁሉ አድኖ ያለ ጉዳት በጤና አነሣው።

ብዙዎች ሰዎችም ስቃዩንና ዳግመኛ መዳኑን በአዩ ጊዜ እጅግ አደነቁ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስም አምነው ሰማዕታት ሆኑ።

መኰንኑ ግን እጅግ ተቆጥቶ የቅዱስ አቦሊን ቆዳውን እንዲገፍፉትና ጨውና መጻጻን በማቅ አምጥጠው ቍስሉን እንዲያሹ አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉበት።

ከዚህም በኋላ ቆዳውን አሸክመው በከተማ ውስጥ ሁሉ አዞሩት ወደ #ጌታችንም እንዲህ ብሎ ጸለየ የሕያው #እግዚአብሔር ልጅ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ_ሆይ ርዳኝ ከዚህ ሥቃይም አድነኝ። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደርሱ መጣ ሁለመናውንም ዳስሶ አዳነው።

መኰንኑም በእርሱ ላይ የሚያደርገውን እስኪያስብ ከእሥር ቤት እንዲጨምሩት አዘዘ። ቅዱስ አቦሊም ቁሞ ጸለየ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #ጌታችን ተገለጠለትና የመረጥኩህ አቦሊ ሰላም ለአንተ ይሁን እኔም ከአንተ ጋር እኖራለሁ አለው #ጌታችንንም በአየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው ክብር ይግባውና #ለጌታችንም ሰገደለት።

ስሙ አብስኪሮን የሚባል አንድ ባለ ጸጋ ነበር የቤቱንም ግድግዳ አፍርሰው አዲስ ይሠሩለት ዘንድ ሠራተኞችን አመጣ ሥራቸውንም እስኪጨርሱ ከዚያ ይቆሙ ዘንድ ሁለቱን ልጆቹን አዘዛቸው።

ከግርግዳውም ላይ በወጡ ጊዜ ግርግዳው ተደርምሶ ዐሥራ ስድስት ሰዎችና ሁለቱ ልጆቹ ሞቱ። ባለጸጋውም የሆነውን በአየ ጊዜ ልብሱን ቀደደ ጩኾም አለቀሰ ወደ ቅዱስ አቦሊም ሒዶ ከእግሩ በታች ሰገደለት እንዲህም አለው ራራልኝ ሁለቱ ልጆቼ ሙተዋልና ከእነርሱም ጋራ ዐሥራ ስድስት ሰዎች ሞቱ። ከሞትም ብታሥነሣቸው እኔ በአምላክህ አምናለሁ።

ያን ጊዜም ቅዱስ አቦሊ ተነሣ እንዲህ ብሎ ጸለየ ስለ ቅዱስ ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ የመረጥከኝ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ በእኒህ በሞቱ ሰዎች ላይ ኃይልህን ግለጥ። እኒህ ሰዎች ሁሉ እንዲአምኑ ያለ አንተም ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ከሞት አንሣቸው። ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

ከዚህም በኋላ የተገፈፈ ቆዳውን ወስዶ በሞቱት ሰዎች ላይም ዘረጋውና በሕያው #እግዚአብሔር ልጅ በ #ጌታ_በኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ከሞት ተነሡ አለ። ወዲያውም ሁሉም ድነው ተነሡ በዚያ ያሉ ሕዝብም ይህን ድንቅ ሥራ በአዩ ጊዜ የክርስቲያን አምላክ የቅዱስ አቦሊም አምላክ #ኢየሱስ_ክርስቶስ አንድ ነው እኛም እናምንበታለን ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለምና እያሉ ጮኹ።

ባለ ጸጋው አብስኪሮንም መጥቶ ለቅዱስ አቦሊ እንዲህ እያለ ሰገደ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ክብር ይግባውና እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ዛሬ አወቅሁ እኔም አምንበታለሁ። ከቤተሰቦቹም ሁሉ ጋር አመኑ መኰንኑም አፈረ።
#ማኅሌተ_ጽጌ ፤ ምንጩ ትርጉሙና መልእክቱ (ክፍል አንድ)

በስመ #አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ኃይለ ቃልን ከትርጓሜ፣ ትርጓሜን ከምሥጢር እንዲሁም ደግሞ ምሥጢርን ከዜማ ጋር አስተባብረውና አስማምተው የሚደርሱ ሊቃውንት ባለቤት ናት፡፡ በ5ኛው መ.ክ.ዘመን የተነሣው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አምስቱን ጸዋትወ ዜማ ሲደርስ በ14ኛው መ.ክ.ዘመን የተነሣው አባ ጊዮርጊስ ደግሞ ሰዓታትን ደርሷል፡፡ በዚሁ ዘመን አባ ጊዮርጊስ ጋር ጥልቅ መንፈሳዊ ፍቅር የነበረው አባ ጽጌ ድንግል “ማኅሌተ ጽጌ” የተባለውን ድርሰት ደርሷል፡፡ ማኅሌተ ጽጌ ግጥማዊ አካሔድ ያለው ድንቅ ኢትዮጵያዊ ድርሰት ነው፡፡ ይህ ድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውለው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው የእመቤታችን የቅድስት #ድንግል_ማርያም የስደት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ሌሊት በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ መሰደድና መንከራተት እያሰቡ የሚደረስ ምሥጋናና ጸሎት ነው፡፡

በሀገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት /ዘመነ ጽጌ/ ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ዘመን #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ “ስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔርን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ እናንተንማ ይልቁን እንዴት እንግዲህ ምን እንበላለን ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ ...» /ማቴ.5፡28-33/ በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባን መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር እንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ምግብና ልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡ እንዲሁም ክቡር ዳዊት «ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ ሰብእሰ ከመ ሳዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ፤ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆን አስብ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነው እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና» /መዝ.1ዐ2፤14-16/ በማለት እንደ ተናገረው የሰው ሕይወት በሣር ይመሰላል፡፡ ሣር አድጐ አብቦ ከዚያ በኋላ ይደርቅና በነፋስ አማካኝነት ያ የረገፈው ሣር እየተነሣ የነበረበት ቦታ ስንኳ እስከማይታወቅ ድረስ ይሆናል፡፡ ሰውም ከአደገ በኋላ በሕማም ፀሐይነት ይደርቅና በሞተ ነፋስነት ይወሰዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መቃብር ሲወርድ የነበረበት ቦታ ይዘነጋል፡፡ ስለዚህ ዘመነ ጽጌ ሰው ዘመኑ እንደ አበባ በቶሎ የሚረግፍ መሆኑን በማሰብ ይህ ዘመን ሳያልፍ መልካም ሥራ ለመሥራት ትንሣኤ ኅሊና የሚነሣበት ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለዘመነ ጽጌ የሠራው ድጓም ይህንኑ የሰውን ዘመን አጭርነት የሕይወቱን ኢምንትነት በዚህ ሕላዌ የተፈጠረ ሰው በዚህ ዓለም ክፉ ሥራ መሥራት እንደሌለበት ሁልጊዜ በተዘክሮተ ሞት እንዲኖር የሚያስረዳ ነው፡፡

በዘመነ ጽጌ ቅዱስ ያሬድ ከደረሰው ድጓ በተጨማሪ ከላይ እንደተጠቀሰው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣ አባ ጽጌ ድንግል ከዚሁ ዘመን ጋር የተያያዘ ድርሰት ደርሷል፡፡ ይህ ድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ በአብዛኛው አምስት ስንኞች ያሉት ሲሆን ብዛቱም 15ዐ ያክል ነው፡፡ ይህም ድርሰት «ማኅሌተ ጽጌ» በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኘው ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያምንና ልጇን #መድኃኒታችንና_አምላካችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመሰለ የሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባ ሲመስል ልጇን በፍሬ እርሷን በፍሬ ሲመስል ደግሞ ልጇን በአበባ እየመሰለ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ «ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዓርግ ጽጌ እምጉንዱ፤ ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል» /ኢሳ.11፡1/ ብሎ ከእሴይ ዘር የምትገኘውን #እመቤታችንን በበትር ከርሷ የሚገኘውን #ክርስቶስን ደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመር እያንዳንዱን መልክዕ #እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬ በመመሰል የ #እግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር በታሪክ፣ በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅ በሆነና በተዋበ ሁኔታ አዋሕዶ ደርሶታል፡፡

#እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋን ሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስ ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው ለፍቅሯ ሲሳሳ ለነበረው ለአባ ጽጌ ድንግል ደግሞ ይህንን ማኅሌተ ጽጌን እንዲደርስ አድርጋዋለች፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ማኅሌተ ጽጌ በመልክዕ አደራረስ ሥርዓት የተደረሰ ሲሆን ይህንንም ለመመልከት እንዲያመች በሚከተሉት ክፍሎች ከፋፍሎ ማቅረብ ይቻላል፡፡

1, #ጸሎት

በዚህ አገባብ ጸሎት ስንል በተለየ ሁኔታ ጸሎትነቱ የጐላውን ለማየት እንጂ ድርሰቱ በሙሉ ጸሎት ነው፡፡ ሌሎቹንም እንዲሁ ታሪክ፣ ተግሳጽ፣ ምሥጢር ተብለው መከፈላቸው በበዛውና በጐላው ለመግለጽ ነው እንጂ ሁሉም በሁሉ አለ፡፡ በጸሎትነታቸው ጐልተው ከሚታዩት ውስጥ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡

1.1. አንብርኒ #ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፣
ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት፣
በእንተ ርስሐትየሰ ኢትመንንኒ ንግሥት፣
እስመ ወሀብኩ ንብረትየ ለፍቅርኪ ሞት፣
ዘአሰገርዎሙ ለሰማዕት በጽጌሁ ሕይወት፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን «የምእመናንንና የ #ክርስቶስን ነገር በምሥጢር በተናገረበት በመኃልይ መጽሐፉ «እንደ ማኅተም በልብህ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ» /መኃ.9፤6/ ይላል፡፡ ይኸውም የምእመናንንና የ #ክርስቶስን አንድነት የሚገልጽ ነው፡፡ «አንብርኒ #ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፤ ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት» ማለቱ #እመቤታችንን እንደ ማኅተም በልብሽ አኑሪኝ በማለት በእናትነትሽ፣ በአማላጅነትሽ አትርሽኝ ካለ በኋላ «በእንተ ርስሐትየሰ አትመንኒ ንግሥት» ይላል፡፡ ይኸም ማለት አትርሽኝ በልብሽ አኑሪኝ ብዬ የምለምንሽ አንቺ እንዳትረሽኝ የሚያደርግ መልካም ሥራ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሰውነቴ ክፋት ምክንያት በኃጢአቴና በወራዳነቴ ምክንያት እኔን ከማሰብ ከልቡናሽ አታውጪኝ በማለት #እመቤታችን በርኅሩኅ ልቧ «መሐር ወልድየ ወተዘከር ኪዳንየ» እያለች እንድታዘክረን የሚያሳስብ ጸሎት ነው፡፡

ሶበ አተቦ ለማይ በቅዳሴኪ እንዘ ይጼሊ፣
ረሰዮ ኅብስተ ጽጌ ሃይማኖት ሳሙኤል ዘሐቅለ ዋሊ፣
ምሕረተ ወፍትሐ ለተአምርኪ አኀሊ፣
ሥረዪ ኃጢአትየ ወእጸብየ አቅልሊ፣
እስመ ኩሉ ገቢረ ማርያም ትክሊ፡፡