ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
858 subscribers
3.46K photos
103 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
#መጋቢት_4

መጋቢት አራት በዚች ቀን የአይሁድ ተሳታፊዎች ስለሚባሉ ክፉዎች ሰዎች በአሞር ደሴት #የአንድነት_ስብሰባ ሆነ፣ የከበረና የተመሰገነ #መኰንን_ሐኑልዮስ በሰማዕትነት ሞተ፣ ኢትዮጵያዊቷ ጻድቅ #ቅድስት_ሐይመተ_ሥላሴ ዕረፍቷ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#የቅዱሳን_ሊቃውንት_ጉባዔ

መጋቢት አራት በዚች ቀን የአይሁድ ተሳታፊዎች ስለሚባሉ ክፉዎች ሰዎች በአሞር ደሴት የአንድነት ስብሰባ ሆነ። እነርሱ የከበረ የፋሲካን በዓል በኔሳን ወር ማለት በሚያዝያ አሥራ አራት ቀን ከአይሁድ ጋር ያከብሩ ነበርና።

ሰኞ ቢሆን ማክሰኞም ቢሆን ወይም ረብዕ ወይም ሐሙስ ወይም በዓርብ ቀን ወይም በቅዳሜ ሰንበት ከአይሁድ ጋር ያከብሩ ነበርና የደሴታቸውም ኤጲስቆጶስ አወገዛቸው ግን አለተመለሱም።

ስለዚህም ወደ ሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ድምትራጥዮስ ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ ሰረባሞን ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ ድሜጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌሙ ኤጲስቆጶስ ወደ አባ ሲማኮስ መልእክትን ላከ። የእነዚህንም ሰዎች ስሕተታቸውን ነገራቸው።

አራቱ ሊቃነ ጳጳሳት ከእነርሱ እየአንዳንዳቸው የከበረ የፋሲካ በዓልን በእሑድ ቀን ካልሆነ በቀር ከአይሁድ በዓልም በኋላ ካልሆነ በቀር አታድርጉ የሚል መልእክትን ላኩ። ይህንም ትእዛዝ የሚተላለፈውን ከምእመናን እንዲለይ አወገዙ።

በዚህም ጉባኤ አሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳት ተሰበሰቡ። እነዚያንም ሕግ ለዋጮች አቅርበው የሊቃነ ጳጳሳቱን መልእክቶቻቸውን በፊታቸው አነበቡ ከእነርሱም ከከፋች ምክራቸው የተመለሱ አሉ። በስሕተታቸውም ጸንተው የቀሩ አሉ። ረግመውና አውግዘውም ከምእመናን ለዪአቸው።
አባቶቻቸን ቅዱሳን ሐዋርያትም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣባትን ዕለተ ፋሲካን ያለ እሑድ ቀን የሚያከብር እርሱ በበዓላቸው ከአይሁድ ጋራ ተሳታፊ ነውና ከምእመናን ይለይ ብለው እንዳዘዙ እንዲሁ የፋሲካ በዓል በዕለተ እሑድ እንዲከበርና ሕጉም ጸንቶና ተወስኖ እንዲኖር ተሠራ።

እግዚአብሔር ከሰይጣን ስሕተት ይጠብቀን። በተጋድሎአቸውና በትሩፋታቸው ደስ ባሰኙት በቅዱሳን ጸሎትም ከወጥመዶቹና ከሽንገላውም ያድነን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ _ሐኑልዮስ_መኰንን

በዚህችም ቀን የከበረና የተመሰገነ መኰንን ሐኑልዮስ ከጵንፍልያ አውራጃ ብርግያ በምትባል ከተማ በሰማዕትነት ሞተ።ይህንንም ቅዱስ ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ መውደዱና እርሱንም ስለ ማምለኩ ከዲዮቅልጥያኖስ ተልኮ የመጣ ብርይንኮስ የተባለ መኰንን ያዘው።

በመኰንኑም ፊት በቆመ ጊዜ ምስጋና ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት ከፍ ከፍ ባሉ ቃላት አብራርቶ ገለጠ ።ብዙ ምስጋናዎችንም ለእግዚአብሔር አቀረበ የረከሱ ጣዖታትንም ረገማቸው።

መኰንኑም በዕንጨት መስቀል ላይ ይሰቅሉት ዘንድ አዘዘ ስለ ከበረ ስሙም ምስክር ይሆን ዘንድ ስል አደለው ምስጋና ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰገነው። ከዚያም ምስጋና ይግባውና በእግዚአብሔር እጅ ነፍሱን ሰጠ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሐይመተ_ሥላሴ

በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊቷ ጻድቅ በዝዋይ ደብረ ጽዮን ሐይቅ ውስጥ ገብታ ለአምስት ዓመት የጸለየች ታላቋ እናት ቅድስት ሐይመተ ሥላሴ ዕረፍቷ ነው፡፡ የትውልድ ሀገሯ ጎጃም ደብረ ጽላሎ ነው፡፡ ብዙ እናቶች በጣና ደሴት ውስጥ እየገቡ እንደጸለዩ ሁሉ እሷም ወደ ዝዋይ ሄዳ በዝዋይ ደብረ ጽዮን ሐይቅ ውስጥ ገብታ አምስት ዓመት ከባሕሩ ላይ የጸለየች ቅድስት እናት ናት፡፡ በታዘዘ መልአክ መሪነት ከሐይቁ ውስጥ ከወጣች በኋላ በገዳሙ ውስጥ ዐሥራ ዘጠኝ ዓመት ቆማ ጸልያለች፡፡

በመልአኩ መሪነት ወደ ቡልጋ ሄዳ በዚያም ዐሥራ አምስት ዓመት በታላቅ ተጋድሎ ኖራለች፡፡ ሰውነቷም እጅግ ከስቶ ሥጋዋ አልቆ ይታይ ነበር፡፡ በመጨረሻም መልአኩ ተገልጦ ጊዜ ዕረፍቷን ከነገራት በኋላ ወዲያው መጋቢት 4 ቀን በሰላም ስታርፍ ሦስት አክሊላት ወርደውላታል፡፡ ቅድስት ሐይመተ ሥላሴን ስንክሳሩም "የጽድቅ ኮከብ" እያለ ይጠቅሳታል፡፡ ቅዱስ ገድሏ በደብረ በግዕ ይገኛል፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት እና #ከገድላት_አንደበት)
እርሷም ከሞቱ በኃላ የሰዎች በድኖች አፈርም ከሆኑ ተነስተው ይሰቃያሉን ብላ መለሰችለት። አዎን አላት። ለዚህ ለምትነግረኝ ነገር ምልክቱ ምንድነው እግዚአብሄር ለሙሴ በሰጠው ኦሪት አልተፃፈ አባቶቻችንም ይህን አላመኑም አለችው። እርሱም በፍርድ ቀን ሙታን እንደ ሚነሱ ስለ ኃጥአንም ስቃይ ስለፃድቃንም ተድላ ደስታ በኦሪት መፅሀፍና በሀዲስ ኪዳን መፅሀፍ ተፅፎ እንዳለ ገለጠላት።

ትምህርቱና ተግሳፁ በልቧ አደረ በፍርድ ቀንም ሙታን እንደሚነሱ አመነች እንዲህም አለችው ከዚህ ከረከሰ ስራ ብመለስ እግዚአብሔር ይቀበለኛልን። አባ ግርማኖስም ወደ አለም እንደመጣና ተሰቅሎ ደሙን በማፍሰስ ኃጢአታችንን እንዳራቀልን በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካመንሽ ስለዚህ የነፃችና የፀናች ንስሃ ይሆንልሻል የክርስታና ጥምቀትንም ተጠመቂ እግዚአብሔርም ይቀበልሻል አስቀድመሽ ከሰራሽው ኀጢአት ምንም ምን አያስብብሽም ከእናትሽ ማህፀን እንደተወለደሽበት ቀን ትሆኛለሽ እንጂ።

የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቀናች ሀይማኖት ደጆችም ይከፈቱልሻል አላት።ያንጊዜም የክርስትና ጥምቀትን ያጠምቃት ዘንድ ለመነችው እርሱም ወደ በአልበክ ከተማ ኤጲስቆጶስ ወስዶ አደረሳት እርሷም በኤጲስቆጶሱ ፊት በልዩ ሶስትነት በመድሃኒታችን ክርስቶስም ሰው በመሆኑና ሞቶ በመነሳቱ አመነች።

ኤጲስቆጶሱም ተነስቶ በውኃው ላይ ፀልዮ አጠመቃት እግዚአብሔርም አይነ ልቡናዋን ገልጦላት ብሩህ መልአክ ወደ ውኃው ሲስባት ሌሎች መላእክትም ስለ እርሷ ፈፅሞ ደስ ሲላቸው ተመለከተች።

ከዚህም በኃላ ገፃችው የሚያስደነግጥ ጥቋቊሮችን አየች ከእርሳቸውም አንዱ መልኩ የከፋ ሲጎትታት እርሱም በርሷ ላይ ይቆጣ ነበር። ይህንንም ራእይ በአየች ጊዜ የክርስትና ሀይማኖት ፍቅር በልቧ ተጨመረ ኃጢአት በመስራት የሰበሰበችውን ገንዘቧን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጠች ከደናግል ገዳማትም ወደ አንዱ ገዳም ገብታ የምንኲስና ልብስ ለብሳ ፍፁም የሆነ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለች። ከአጋንንት ጋር ተዋጋች።

ሰይጣንም አስቀድሞ ከእርሷ ጋር ሲያመነዝሩ ከነበሩ በአንዱ ሰው ልብ አደረ ወደ መኰንኑ ሄዶ ነገር ሰራባት መኰንኑም ወደርሱ እንዲያቀርቧት አዘዘ። በደረሰችም ጊዜ ከደጅ ቆመች በሞተው በመኰንኑ ልጅ ለይ ታላቅ ጩኸትና ልቅሶ አየች ገብታም ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመፀለይ ማለደች የሞተውን የአገር ገዥውንም ልጅ ከሞት አስነሳቸው። መኰንኑም ይህን ድንቅ ተአምር በአየ ጊዜ እጅግ አደነቀ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በእርሷ ምክንያት ፍፁም የፀና እምነት አመነ።

ከእርሱ በኃላም ስለ እርሱ ስሙ ዲዮጎኖስ የሚባል ሌላ አገረ ገዢ ተሾመ ።የዚችንም ድንግል ዝናዋን ሰምቶ ወደርሱ አስመጣት ።እርሷም በአደባባይ ውስጥ አይኑ አንድ አይና የሆነ ጎልማሳ አየች ፀለየችና በመስቀል ምልክት በአይኑ ላይ አማተበች ያንጌዜም አይኑ ተገልጦ አየ፡፡ ያደረገችውን ይህን ድንቅ ስራ አይቶ ድንግሊቱን ወደ ቦታዋ መለሳት። ከእርሱም በኃላ ደግሞ ሌላ ስሙ በከኒቶስ የሚባል አገር ገዢ ተሾመ እርሱም ዝናዋን ሰምቶ ይቺን ቅድስት አውዶክስያን ወደርሱ አስመጣት ሊያሰቃያት ፈልጎ።

እርሷም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እድሏን ከሰማእታት ጋራ ይሰጣት ዘንድ ለመነችው እግዚአብሔርም ልመናዋን ተቀበለ። ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ መኰንኑ አዘዘ በመንግስተ ሰማያትም የሰማእትነት አክሊል ተቀበለች

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
#መጋቢት_9

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ዘጠኝ በዚህች ቀን ተጋዳይ የሆነ ጽኑዕ አባት #ቅዱስ_ኩትን አረፈ፣ የከበረ #ቅዱስ_እንድርያኖስና_ሚስቱ_አውሳብዮስና_አርማ በሰማዕትነት አረፉ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኩትን_ሐዋርያ

መጋቢት ዘጠኝ በዚህች ቀን ተጋዳይ የሆነ ጽኑዕ አባት ኩትን አረፈ። እርሱም በሶርያ አገር ስሟ በንጣንዮስ ከምትባል ቦታ የሚኖር ነው። አባቶቹም ከዋክብትን ያመልኩ ነበር የአባቱ ስም ንስጣር የእናቱም ስም ቴዎድራ ይባላል።

በአደገ ጊዜም ወላጆች ሊአጋቡት ፈለጉ እርሱ ግን አልወደደም ግድ ብለው ያለውዴታው ሚስትን አጋቡት ሊገናኛትም አልፈለገም ስለ ሥጋ ድካም ወይም ስለ ጽድቅ ሳይሆን የሥጋ ፍትወትን ስለሚጠላት ነው እንጂ። ደናግልም እንደሆኑ ሁለቱ ሁሉ ከሚስቱ ጋራ በአንድነት ኖረ።

አምላክ ሆይ ወደ ዕውቀትህ ምራኝ በማለት ጸሎትና ምልጃን ያዘወትር ነበር። ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ለቆርኔሌዎስ እንደተገለጠ ተገልጦ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን አስተማረው ከሐዋርያትም ወደ አንዱ ሔዶ የክርስትና ጥምቀትን እንዲጠመቅ አዘዘው።

የሐዋርያት የስብከታቸው ወራት ነበረና ሒዶ ተጠመቀ የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ሁሉ ሕጉን ሥርዓቱንም ሁሉ ተማረ መለኮታዊ ምሥጢርንም ተቀበለ። በየቀኑ ሁሉ የሐዋርያ ጳውሎስን ትምህርት ይሰማ ነበር የጽድቅን ሥራ መሥራትና ንጽሕና ለበጎ ሥራ መጠመድ ትጋት ቅንነት የዋህነት ጾም ጸሎት ሰጊድ በላዩ ተጨመረ። በእነዚህ ሁሉ የሚተጋ ሆነ እግዚአብሔርም አስደናቂ ተአምራቶችን እንዲአደርግ በርኲሳን አጋንንት ላይ ሥልጣንን ሰጠው።

በሚያደርገው ተአምራትም ወላጆቹን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደማመን ስቦ አስገባቸው ደግሞ ሚስቱንና ወላጆቿን አስገባቸው።

ከከሀድያን አንዱ ለሰይጣን ሊሠዋ ወደ ጣዖቱ ቤት በገባ ጊዜ ቅዱስ ኩትን አውቆ በሰይጣን ላይ ጮኸ እርሱ ሰይጣን እንጂ አምላክ እንዳልሆነ በሰው ፊት ያምን ዘንድ አዘዘው። ሰይጣንም እንዳዘዘው ራሱን ገለጠ በዚያ የነበሩ ሁሉም የቅዱስ ኩትን አምላክ አንድ እርሱ ብቻ ነው እያሉ ጮኹ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቁ።

ከዚህ በኋላ ከቀላውዴዎስ ቄሣር የተላከ መኰንን የቅዱስ ኩትንን ዜናውን በሰማ ጊዜ ወታደር ልኮ አስቀረበው ስለ ሥራውም ጠየቀው እርሱም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ መኰንኑም ጽኑ ግርፋት ገርፈው እንዲአሥሩት አዘዘ ይህንንም አደረጉበት።

የአገር ሰዎችም ቅዱስ ኩትንን አሠቃይተው እንዳሠሩት በሰሙ ጊዜ ሁሉም ወደርሱ ተራወጡ መኰንኑንም ሊገሉት ወደዱ መኰንኑም ሸሸ። ቅዱስ ኩትንንም ከማሠሪያው ፈትተው ከደሙም አጥበው ተሸክመው ወደቤቱ ወሰዱት ከዚያም በኋላ ብዙ ዘመናት ኑሮ የወደደውን እግዚአብሔርን አገልግሎ ደስ አሰኝቶ በፍቅር አንድነት አረፈ። ከዕረፍቱም በኋላ ቤቱን ቤተ ክርስቲያን አድርገው ሥጋውን በውስጥዋ አኖሩ ጌታችንም ከሥጋው ብዙዎች ታላላቅ ተአምራቶችን አሳየ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_እንድርያኖስ

በዚህች ቀን የከበረ እንድርያኖስና ሚስቱ አውሳብዮስና አርማ ሌሎች አርባ ሰዎችም በሰማዕትነት አረፉ።

እሊህንም ምርጦች ለረከሰ ከወርቅና ከብር ለተሠራ ጣዖት ማምለክን እምቢ ስላሉ የክብር ባለቤት ለሆነ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለስሙ ዐላውያን ጽኑ የሆነ ሥቃይን አሰቃዩአቸው።

ከዚህም በኋላ ራሶቻቸውን በሰይፍ ቆረጡ የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
#መጋቢት_10

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት አስር በዚች እለት የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት #ቅዱስ_መስቀል የተገለጠበትና የተገኘበት ነው፣ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ታላቁን ዲማ ጊዮርጊስን የመሠረቱ #የአቡነ_ተከስተ_ብርሃን የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዕፀመስቀል

መጋቢት አስር በዚች እለት የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችንና መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የተገለጠበትና የተገኘበት ነው። የዚህም የከበረ ዕፀ መስቀል መገለጡና መገኘቱ ሁለት ጊዜ ሆኗል።መጀመሪያ የፃድቁ ንጉስ የቆስጠንጢኖስ እናት በሆነች በንግስት ዕሌኒ እጅ ነው።

«እርሷ ለእግዚአብሄር ተስላ ነበርና ልጇ ቆስጠንጢኖስ ወደ ክርስቲያን ሀይማኖት ቢገባ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ መስቀሉን እስከ አገኘችው ድረስ ልትፈልግው በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ልታንፃቸው ነው።

ከዚህ በኃላ ልጇ አምኖ የክርስትና ጥምቀትን በተጠበቀ ጊዜ እሌኒ ቅድስት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች ከእረሷ ጋርም ብዙ ሰራዊት ነበር ደርሳም ስለ ከበረ መስቀል መረመረች የሚያስረዳት አላገኘችም የአይሁድ ወገን የሆነ አንድ ሽማግሌ ሰው አስራ በርሀብና በጥማት አስጨነቀችው።
በተጨነቀም ጊዜ ለንግስት እሌኒ የጉልጎታን ኮረብታ አስጠርጊ ብሎ ነገራት እርሷም ይጠርጉ ዘንድ አይሁድን አዘዘቻቸው።

ቤቱን የሚጠርግ ሰው ሁሉ ጥራጊውን በውስጡ የከበረ መስቀል በአለበት በጌታችን መቃብር ላይ እንዲጥል አይሁድ አስቀድመው አዝዘው ነበርና ንግስት እሌኒ እስከ ደረሰችበት ጊዜ ከሁለት መቶ አመት በላይ ጥራጊያቸውን ሲጥሉበት ኖሩ ኮረብታም ሆነ። አይሁድም በጠረጉ ጊዜ ሶስት መስቀሎች ተገለጡ የክብር ባለቤት ክርስቶስ የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ አላወቁም። የሞተ ሰውም አግኝተው አመጡ።

አንዱንም መስቀል አምጥተው በሞተው ሰው ላይ አኖሩት አልተነሳም ደግሞ ሌላውን መስቀል አምጥተው በሙቱ ላይ አኖሩ አሁንም አልተነሳም ከዚህም በኃላ ሶስተኛውን መስቀል አምጥተው በሙቱ ላይ አደረጉት ያንጊዜ የሞተው ሰው ተነሳ እሌኒም የክርስቶስ መስቀል እንደሆነ አውቃ ሰገደችለት የክርስቲያንም ወገኖች ሁሉ ሰገዱለት።

ለልጅዋ የላከችው ይህ መስቀል ነው የሚል በሌላ መፅሀፍ ይገኛል የቀረው ግን ግንዱ በውስጡ ተተክሎበት የነበረው ከእርሱም እኩሌታውን ከቅንዋቱ ጋራ ወደ ልጅዋ የላከችው ነው።

ከዚህም በኃላ ስራአታቸውና የህንፃቸው ነገር በመስከረም ወር በአስራ ሰባት ተፅፎ የሚገኝ አብያተ ክርስቲያናትንና የከበሩ ቦታዎችን አነፀች። ሁለተኛው በሮሙ ንጉስ በህርቃል ዘመን የሆነው ሲሆን የፋርስ ሰዎች በግብፅ አገር ሳሉ ወደ አገራቸው ሊመለሱ ወደዱ። ከሹማምንቶቻቸው አንዱ የጦር መኰንን ተነጥሎ ወደ ኢየሩሳሌም አልፎ ደረሰ ወደ ከበረ መስቀል ቤተ ክርስቲያንም ገባ። መስቀሉም በላዮ በተተከለበት ግንድ ፊት ታላቅ ብርሀን ሲበራ አይቶ ሊያነሳው እጁን ዘረጋ። እሳትም ወጥታ እጁን አቃጠለችው።

ከክርስቲያን በቀር ማንም ሊነካው እንደማይችል የመስቀልን የክብሩን ነገር ሰዎች ነገሩት። ሁለት ዲያቆናትንም ይዞ የከበረ መስቀልን እንዲሸከሙ አዘዛቸወወ ከኢየሩሳሌምም ብዙ ሰዎችን ማርኮ ወደ አገሩ ተመለሰ።

የፋርስ ሰዎች ኢየሩሳሌምን እንዳጠፏት ብዙዎች ሰዎችንም እነድ ማረኩና የከበረ የክርስቶስንም መስቀሉን እንደ ወስዱ የሮም ንጉስ ህርቃል በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ። ስለርሱም እንዲፆሙ ምእመናንን አዝዞ ወደፋርስ ዘምቶ ወጋቸው ብዙዎችንም ገደላቸው የከበረ እፀ መስቀልንም እየፈለገ በሀገራቸው ሁሉ ዞረ ግን አላገኘውም።

ያ ዲያቆናቱና መስቀሉን የወሰደ መኰንን ከቦታዎች በቤቱ አነፃር ባለ በአንድ ቦታ ላይ ወስዷቸው ጥልቅ ጉድጓድእንዲቆፍሩ አዝዞ በዚያ የከበረ መስቀልን አስቀበረ እነዚያንም ዲያቆናት ገደላቸው።

ነገር ግን ያ መኰንን የማረካት የካህናት ወገን የሆነች በእርሱ ቤት የምትኖር አንዲት ብላቴና ነበረች። እርሷም የከበረ መስቀልን ሲያስቀብርና ሁለቱን ዲያቆናት ሲገድላቸው በቤቱ ውስጥ ሁና በመስኮት ትመለከት ነበር ወደ ንጉስ ሀርቃልም ሂዳ መኰንኑ ያደረገውን ሁሉ ነገረችው።

ይህንንም ንጉስ ሰምቶ እጅግ ደስ አለው ያቺ ብላቴናም መራችው ከእርሱም ጋራ ብዙ ሰራዊት ሆኖ ኤጲስቆጶሳትና ካህናትም ነበሩ ።ወደ ቦታውም እስከምታደርሳቸው ያቺን ልጅ ተከተሏት ቅፍረውም የከበረ እፀ መስቀልን አገኙት ከአዘቅቱም አወጡት ንጉሱና ሰራዊቱም ሰገዱለት።

በልብሰ መንግስቱም አጐናፀፈው ታላቀወ ክብርንም አከበረው እጅግም ደስ አለው ከሰራዊቱ ጋር። የዚህም መስቀል ሁለተኛ የተገለጠበትና የተገኘበት በዚች ቀን በመጋቢት አስር ነው፡፡ ከዚህ በኃላ ንጉሱ የከበረ እፀ መስቀልን ተሸክሞ ወደ ቁስጥንጥንያ ከተማ ወሰደው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ተከስተ_ብርሃን

በዚህች ቀን ለኢትዮጵያ ጻድቅ ታላቁን ዲማ ጊዮርጊስን የመሠረቱ አቡነ ተከስተ ብርሃን ዘደብረ ድማኅ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው፡፡ ጻድቁ አባታቸው መልከ ጼድቅ እና እናታቸው ድል በኢየሱስ ይባላሉ፡፡ አባ ተከስተ ብርሃን ከዲማ ዋሻ በመነሳት እየተዘዋወሩ ወንጌልን አስተምረዋል። ከዕለታት አንድ ቀን ከጎጃም አውራጃ ይኸውም እነብሴ በሚገኘው ነድ አጹራ ማርያም በሚባለው ቦታ ያሉ ሰዎች የእጃቸውን ተዓምራት የቃላቸውን ትምህርት ሰምተው ከማመናቸው የተነሳ በአንድ ቀን ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ህዝብ በማጥመቃቸውና ቀኑ መሽቶ ስለነበረ ብርሃን ስለወረደላቸው አባ ተከስተ ብርሃን የሚል ስም ሰጥቷቸዋል፤ የቀድሞ ስማቸው አባ በኪሞስ ነበርና።

አባ ተከስተ ብርሃን እንዲህ ባለ መንፈሳዊ አግልግሎት ደብረ ድማኅንና እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ ኖረዉ በበአታቸው በዲማ በመቀመጥ ለ15 ዓመታት ለገዳሙ መምህር በመሆን ገዳሙን አጠናክረዋል። አባታችንም የሴትና የወንድ ገዳም አቋቁመው ሴቶችን በምሥራቅ ወንዶችን በምዕራብ መኖሪያቸው አድርገው በአንድ በር እየገቡ በአንድ አዳራሽ እየተሰበሰቡ እንደማዕረጋቸው በቆብና በአስኬማ እየተቀመጡ ሰርከ ህብስታቸው እንዲመገቡ አድርገው ከቆዩ በኋላ መጋቢት 10 ቀን ዐርፈው በዋሻው ውስጥ ተቀብረዋል። በስማቸው በፈለቀ ጠበል በሽተኞች በተለይ በመውለድ የሚሰቃዩት ይፈወሳሉ። ከአቡነ ተከስተ ብርሃን ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

የመድኃኒታችን የመስቀሉ በረከት ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት እና #ገድለ_ቅዱሳን)
ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ቆርጠው ለውሾች እንዲጥሉት አዘዘ ውሾች ግን ፈጽሞ አልቀረቡትም ሌሊትም ሲሆን ምእመናን መጥተው ሥጋውን ወሰዱ በአዳዲሶች ልብሶችና በጣፋጭ ሽቶዎች ገነዙት በሣጥንም አድርገው ቀበሩት።ከሥጋውም ብዙዎች አስደናቂዎች ተአምራቶች ተደረጉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አጋንዮስ_አውንድርዮስና_ብንድዮስ

በዚህችም ቀን ደግም የከበሩ አጋንዮስ አውንድርዮስና ብንድዮስ በሰማዕትነት አረፉ። እሊህም ቅዱሳን ከአባቶቻቸው ጀምሮ ክርስቲያኖች ናቸው አምላካዊ ትምህርትንም ሁሉየተማሩ ናቸው።

በእግዚአብሔርም ሕግ ጸንተው ሲኖሩ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አርሞስ መርጦ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ ሾማቸው ግን በታወቁ ቦታዎች ላይ አይደለም በብዙዎች አገሮች ውስጥ እንዲሰብኩ ላካቸው እንጂ። በሀገሮችም ያሉ ከሀዲያን ያዙአቸው ያለርኀራኄም አብዝተው ገረፉአቸው በደንጊያም ወገሩአቸው ነፍሳቸውንም በጌታችን እጅ ሰጡ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
#መጋቢት_15

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ዐሥራ አምስት በዚች ቀን የከበረች ተጋዳይ መነኰሳዪት #ቅድስት_ሣራ አረፈች፣ #ቅዱስ_ሰለፍኮስ በሰማዕትነት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#መነኰሳዪት_ቅድስት_ሣራ

መጋቢት ዐሥራ አምስት በዚች ቀን የከበረች ተጋዳይ መነኰሳዪት ሣራ አረፈች። ይቺም ቅድስት ከላይኛው ግብጽ ናት ወላጆቿም የክብር ባለቤት ክርስቶስን የሚያመልኩ ክርስቲያን ናቸው። እጅግም ባለጸጎች ነበሩ ነገር ግን ከእርስዋ በቀር ልጆች የሏቸውም በመልካም አስተዳደግም አሳደጓት ለክርስቲያን የሚገባ ትምህርትን ሁሉ አስተማሩዋት ደግሞም ጽሕፈትን አስተማሩዋት ሁልጊዜም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ታነባለች ይልቁንም የመነኰሳትን ዜና ታነብ ነበር።

መጻሕፍትንም አዘውትራ ስለምታነብ የምንኲስና ልብስ ለመልበስ ፈለገች በላይኛው ግብጽ ከሚገኙ ገዳማትም ወደ አንዱ ገዳም ሒዳ ገባች ብዙ ዘመናትም ደናግልን እያገለገለች ኖረች።

ከዚህም በኋላ የምንኲስና ልብስን ለበሰች ሰይጣንን ድል እስከ አደረገችው ድረስ ሰይጣን የሚያመጣውን ሥጋዊ ፍትወት እየታገለች ዐሥራ ሦስት ዓመት ኖረች። ንጽሕናን ከመውደዷ ጽናት በተሸነፈ ጊዜ በትዕቢት ሊጥላት ወዶ በቤት መዛነቢያ ልትጸልይ ቁማ ሳለች ተገልጦ ሣራ ሆይ ሰይጣንን ድል አድርገሽዋልና ደስ ይበልሽ አላት እርሷም መልሳ እኔ ደካማ ሴት ነኝ ከክብር ባለቤት ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ድል አድርጌ ላበረው አልችልም አለችው።

ይህችም ቅድስት አብረዋት ላሉ ደናግል ጥቅም ያላቸውን ብዙ ትምህርቶችን ታስተምራቸው ነበር እንዲህም ትላቸዋለች ከቀን ብዛት ጠላት እንዳያስተኝ እኔ እንደምሞት አስቀድሜ ሳላስብ እግሬን ከአንዱ መወጣጫ ደረጃ ወደ ሁለተኛም አውጥቼ አላኖራትም።

ዳግመኛም ለሰው ርኅራኄ ማድረግ በተሻለው ነበር ይህንንም በሚያደርግ ጊዜ የኋላ ኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ ይኖራል በዜና አረጋውያን መነኰሳት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈ ሌሎች ብዙ ቃሎችንም ተናግራለች።

ታላቅ ተጋድሎም እየተጋደለች በዓቷም በባሕር ዳርቻ ሁኖ ሰባት ዓመት ኖረች አንዲት ቀን እንኳ ከሰው አንዱም አላያትም እርሷ ግን ሁሉን ታይ ነበር። ሸምግላ እስከ ሰማንያ ዓመት በደረሰች ጊዜ ከዚህ ዓለም የሕይወት ማሠሪያ ተፈትታ የዘላለም ተድላ ደስታ ወደሚገኝበት ሔደች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሰለፍኮስ

በዚችም ቀን ዳግመኛ የቅድስት አስጠራጦኒቃ እጮኛዋ ቅዱስ ሰለፍኮስ በሰማዕትነት አረፈ።

የዚህን ቅዱስ ዜና ክርስቲያን እንደሆነ ከሀዲ ንጉሥ በሰማ ጊዜ ያመጡት ዘንድ አዘዘ ወደርሱም ሲቀርብ የአስጠራጦኒቃ እጮኛዋ ሰለፍኮስ የተባልክ አንተ ነህን አለው አዎን ነኝ አለ። ዳግመኛም ማንን ታመልካለህ አለው እርሱም እኔ የክብር ባለቤት የሆነ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አመልከዋለሁ ብሎ መለሰ። ንጉሡም መርዝ ያላቸው እባቦች ወዳሉበት እንዲጨምሩት አዘዘ እግዚአብሔርም አዳነው።

ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡት አዝዞ ቆረጡት በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
#መጋቢት_16

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

#አባ_ሚካኤል_ሊቀ_ዻዻሳት

መጋቢት ዓሥራ ስድስት በዚች ቀን በእስክንድርያ ከተሾሙ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ሰባተኛ የሆነ የእስክብድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት አባ ሚካኤል አረፈ። ይህም አባት በአስቄጥስ በአባ መቃርስ ገዳም መንኲሶ በገደል ተጸምዶ ኖረ ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎድሮስ በአረፈ ጊዜ በላዩ የትንቢት መንፈስ ያደረበት አንድ ጻድቅ ሰው እስከ ሚአስረዳቸው ድረስ ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ አድርገው ለዚች ሹመት ስለሚሻል ሲመክሩና ሲመረምሩ ብዙ ቀኖች ኖሩ።

ከዚህም በኋላ ያ ሰው እኔ በአባ መቃርስ ገዳም በነበርኩ ጊዜ ስጸልይ የሊቀ ጵጵስና ሹመት ለሚካኤል ይገባዋል ለዚች ሹመት የሚሻል እሱ ነውና የሚል ቃልን ከሰማይ ሰማሁ አላቸው፡፡ ሁሉም ስለ ትሩፋቱ ተናገሩ ስለ እርሱም ተስማምተው ከገዳሙ ወደ እስክንድርያ ሊያመጡት ከመስር ገዥ ዘንድ ደብዳቤ አጽፈው ያዙ።

ሊያመጡትም ሲሔዱ ስለ ገዳሙ አገልግሎት ከሽማግሎች መነኰሳት ራር ወደ ጋዛ ከተማ ሲመጣ በመንገድ አገኙት ይዘውም አሠሩት። ወስደውም በመስከረም ወር በዐሥራ ሰባት ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ያቺም ዕለት በጌታ ደም የከበረ መስቀል በዓሉ የሚከበርባት ናት።

ይህም የሆነው ከዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በኋላ የሐሚድ ልጅ እልሲድ በሚገዛበት ዘመን ነው። በሹመቱ ወራትም መርዋን አልጋዲን ነገሠ። የእስክንድርያም አገር ሰዎች ከጥቂት ካፊያ በቀር ብዙ ዝናብ ሳይዘንብላቸው ብዙ ዓመታት ኖሩ። በዚያች እርሱ በተሾ መባት ቀን በሁለተኛውም በሦስተኛውም ብዙ ዝናብ ዘንቦላቸው እጅግ ደስ አላቸው።

በዚህም አባት ዘመን በክርስቲያን ወገኖች ላይ ታላቅ መከራ ደረሰ ከምእመናንም ብዙዎች ሸሹ የክብር ባለቤት ክርስቶስንም የካዱት ሰዎች ቁጥራቸው ሃያ አራት ሺህ ሆነ። ለዚህ ነገር ምክንያት የሆነውን ከእርሱ እግዚአብሔር እስከአጠፋው ድረስ ይህ አባት ስለዚህ በታላቅ ኀዘን ውስጥ ነበር።

ዳግመኛም በዚህ አባት ዘመን ለመለካውያን ቆዝሞስ ሊቀ ጵጵስና ተሹሞ ሳለ የክብር ባለቤት ስለሆነ ስለ ክርስቶስ ተዋሕዶ ከዚህ አባት ከአባ ሚካኤል ጋራ ተከራክሮ ይህ አባት አባ ሚካኤል እንዳስረዳው አመነ።

እንዲህም ብሎ በእጁ ጻፈ የክብር ባለቤት ክርስቶስ ከተዋሕዶ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት ቄርሎስ እንደተናገረ የመለኮቱና የትስብእቱ አንድ ባሕርይ በመሆን ጸንቶ ይኖራል ሲል ኤጲስቆጶሳቱም እንዲሁ ከተዋሕዶ በኋላ ስለ ክርስቶስ የተለያዩ ሁለት ባሕርያት ሁለት ገጻት አሉት ይሉ ዘንድ የሚገባ አይደለም ሲሉ ጻፉ።

ሐዋርያትም በሰበሰቧት በከበረች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአንድነት ጸንተው ሊኖሩ ተስማሙ። ከዚህም በኋላ ከእስክንድርያ ሰዎች መለካዊ የሆነ ስሙ አንስጣስዮስ የሚባል ሰው በላያችው ጥፋትን አመጣ እርሱ ኤጲስቆጶስነት እንዲሾሙት ሽቶ አልሾሙትምና ስለዚህ ወደ እስላሞች ንጉሥ ሒዶ በአባ ሚካኤል ነገር ሠራበት ከዐመፀኞች ነገሥታትም ብዙ መከራ ደረሰበት። ጽኑዕ የሆነ ሥቃይም አሠቃዩት ብዙ ግርፋትም ገረፈው ለረጂም ጊዜ በእግር ብረት አሠሩት። አንገቱንም በሰይፍ ሊቆርጡ ወደ መኰንኑ አቅርበውት ነበር ስለ መንጋዎቹም ጥበቃ እግዚአብሔር አዳነው።

ዳግመኛም በመርዋን አልጋዲ ዘመነ መንግሥት የሙሴ ልጅ በሆነ በንጉሥ አገልጋይ አደባባይ በታላቅ ሥቃይ አሠቃዩት። መኰንኑም ገንዘብ እንዲሰጠው ሽቶ ሊቀ ጳጳሳቱን አባ ሚካኤልን አሠረው ሰዎችም መጥተው ዋስ ሁነው አወጡት። ምጽዋትም ጠይቆ ለመኰንኑ ብዙ ገንዘብ አምጥቶ እንዲሰጠው ወደ ላይኛው ግብጽ ወሰዱት።

ይህ አባትም ወደ ላይኛው ግብጽ በሔደ ጊዜ በዚያ ብዙ ተአምራትን አድርጎ የክብር ባለቤት ክርስቶስን የካዱትን ምእመናን ብዙዎቹን ወደቀናች ሃይማኖት መልሶ አስገባቸው።

የኢትዮጵያ ንጉሥም ይህን አባት የእስላሞች መኳንንት እንዳሠቃዩት በሰማ ጊዜ ፍጹም ኀዘንንም አዘነ። መንፈሳዊ ቅናትንም ቀንቶ ወደ ግብጽ አገር ዘምቶ ከላይኛው ግብጽ ደረሰ፡፡ ከርሱ ጋርም መቶ ሺህ ፈረሰኞች አርበኞች መቶ ሺህ በበቅሎ የተቀመጡ አሁንም በግመል የተቀመጡ መቶ ሺህ አርበኞች ወታደሮች ነበሩ ብዙ አገሮችንም አጠፉ ብዙዎችንም ማረካቸው።

የግብጽ ንጉሥም ይህ ሁሉ የሆነው ስለ ሊቀ ጳጳሳቱ ስለ አባ ሚካኤል እንደሆነ ዐውቆ ከእሥራቱ ፈጥኖ ፈታው ታላቅ ክብርንም አከበረው እንዲሁም የክርስቲያንን ወገኖች ሁሉ እጅግ አከበራቸው።

ከዚህም በኋላ ለኢትዮጵያ ንጉሥ ደብዳቤ ጽፎ ይልክ ዘንድ ወደ አገሩም እንዲመለስ ያዝዘው ዘንድ የግብጽ ንጉሥ ይህን አባት አባ ሚካኤልን ለመነው። ይህም አባት ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥ እርሱንና መኳንንቱን መሳፍንቱንና ሠራዊቱን እየባረከና እየመረቀ ደብዳቤ ጽፎ ላከ ።እንዲህም አለው እነሆ በአንተ ምክንያት ከእሥራትና ከዽቃይ ሁሉ እግዚአብሔር አድኖናልና አሁን ወደ አገርህ በሰላም በፍቅር ተመለስ ስለ እኔና ስለ ክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ስለ ደከምክ መልካም ዋጋህን እግዚአብሔር በመንግሥተ ሰማያት ይስጥህ።

የኢትዮጵያ ንጉሥም የዚህን አባት የሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤልን ደብዳቤ በአነበበ ጊዜ ፈጥኖ ተነሥቶ ወደ አገሩ በሰላም በፍቅር አንድነት ተመለሰ።

አባ ቆዝሞስና ወገኖቹም ከሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋራ በተስማሙ ጊዜ አባ ቆዝሞስ በውዴታው ለምስር ኤጲስቆጶስ ሁኖ ተሹሞ ከዚህ አባት ከአባ ሚካኤል ስልጣን በታች ሆነ። ይህም አባት መልካም ተጋድሎውን በፈጸመ ጊዜ ወደ ወደደው እግዚአብሔር ሔደ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የቅዱሱም አማልጅነቱ በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ይሁን አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
ከዕረፍታቸው በኋላ የተደረጉ በርካታ ታላላቅ ተአምራት አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ እርሳቸው ካረፉ ከትንሽ ቀናት በኋላ በመቃብራቸው ላይ ዘይት ፈለቀ፡፡ ከዚያም በእንጨት በተሰራ መቅጃ እየተቀዳ ወደ ትልቅ መጠራቀምያ ገብቶ ለቤተ መቅደስ መብራት በ12 ተቅዋም ተደርጎ ከዓመት እስከ ዓመት ይበራ ጀመር፡፡ ከተጠራቀመ ዘይቱም ለታመሙ ይቀቡትና ከተለያዩ ሕመሞች ይድናሉ፡ ያዕ 5:14፡፡ ዳግመኛም ኤርትራ በሚገኙት በሌሎቹ በአባታችን ደብር ውስጥ ከብዙ ጊዜ በኋላ በደብረ ሣህል ደብራቸውና በደብረ ጽጌ ፈለቀ፡፡ ቅብዓ ኑጉም ለታመሙ ፈውስ እየሰጠ ለቤተ መቅደስም መብራት ሆነ፡፡

ዳግመኛም ከተደረጉት ተአምራት ውስጥ አንዱ እንደ ቤተክርስቲያን ሕግጋት ጻድቁ ካረፉ በኋላ ለጸሎትና ለኑዛዜ ሰዎች ተሰብስቦው እህል እና ውሃ ተዘጋጅቶ በነበረበት ሰዓት "በዚ ቀን ሁሉ ሰው ተገኝቶ ያለሥጋ ዋልን›› ሲሉ ሦስት የተለያዩ ሚዳቆዎች በአቡነ ዮናስ ጸሎት ድንገት መጥተው በሰዎቹ መሐል ተገኙ፡፡ ሰዎቹም ሚዳቆዎቹን አረደው በሉ፡፡

ጻድቁ በስማቸው የተገደሙ ገዳማት (ደብረ ድኁኃንበ-ቆሓይን፣ ደብረ ጽጌ ትምዛእ፣ ደብረ ጽዮን ዓዲ ወሰኽ፣ ደብረ ጸሪቅ ትግራይ፣ እና ደብረ ሣህል ዓረዛ) ይባላሉ፡፡

አቡነ ዮናስ ያረፉት መጋቢት 17 ቀን ሲሆን ይህ ወቅት ታላቁ ዐቢይ ጾም የሚውልበት ስለሆነ በዓለ ዕረፍታቸውን ጥር 21 ቀን እንዲያከብሩ ለልጆቻቸው አስቀድመው ነግረዋቸዋል፡፡ በመሆኑም በዚሁ ዕለት ጥር 21 ቀን በሁሉም ገዳማቸው ውስጥ በታላቅ ክብረ በዓል ታስበው ውለዋል፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት እና #ከገድላት_አንደበት)
#መጋቢት_19

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ዐሥራ ዘጠኝ በዚች እለት #ሐዋርያ_አርስጥቦሎስ ሐዋርያ አረፈ፣ #ቅዱስ_አስከናፍርና የሚስቱ ማርታ የልጆቹ አርቃድዮስና ዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ፣ #የሰባቱ_ሰማዕታት መታሰቢያቸው ሆነ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አርስጦቦሎስ_ሐዋርያ

መጋቢት ዐሥራ ዘጠኝ በዚች እለት የሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር አርስጥቦሎስ ሐዋርያ አረፈ። እርሱም ጌታችን ከመረጣቸውና ከመከራው በፊት እንዲሰብኩ ከላካቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የተቆጠረ ነው።

በሃምሳኛው ቀን በዓልም መንፈስ ቅዱስ በላዮ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋራ ጸጋንና ኃይልን ተመልቶ ሕይወት በሚገኝበት በወንጌል ትምህርት ሐዋርያትን ተከትሎ በመሔድ አገለገላቸው።

ብዙዎችንም ወደ ድኀነት መንገድ መልሶ የክብር ባለቤት ወደ ሆነ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት አስገባቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጥምቆ የአምላክን ሕግና ትእዛዝ ከማስጠበቁ የተነሣ ነፍሳቸውን አዳነ።

አባቶቻችን ሐዋርያትም ይህን ቅዱስ አብራጣብያስ በሚባል አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት። ወደርሷም ሒዶ በውስጥዋ ወንጌልን ሰበከ ብዙዎቹንም በቀናች ሃይማኖት እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሳቸው።

በፊታቸውም ድንቆች ተአምራትን በማድረግ በሃይማኖት አጸናቸው ነገር ግን ከአይሁድና ከዮናናውያን ብዙ መከራ ደረሰበት።

ብዙ ጊዜም ወደ ፈረጆች አደባባይ ወስደው በደንጊያ ወገሩት ጌታችንም ከመከራው ሁሉ ጠብቆ አዳ ነው መልካም ተጋድሎውንም በፈጸመ ጊዜ በሰላም በፍቅር አረፈ። እነሆ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ሐዋርያ ጳውሎስ አስታውሶታል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አስከናፍር

በዚህችም ቀን ደግሞ ቅዱስ አስከናፍርና የሚስቱ ማርታ የልጆቹ አርቃድዮስና ዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ። ይህም አስከናፍር ብዙ ገንዘብ ያለው ባለጠጋ ነው ለእግዚአብሔርም ሕግ የሚጠነቀቅ ነበር ልጆቹንም መንፈሳዊ ምክርና ተግሣጽ በማስተማር አሳደጋቸው።

በአደጉም ጊዜ የጥበብንና የተግሣጽን ትምህርት እንዲማሩ ተይሩት ወደምትባል አገር ሰደዳቸውና ትምህርታቸውን በፈጸሙ ጊዜ ሊድራቸውና በሰርጋቸው ደስ ሊለው ሽቶ ያመጡአቸው ዘንድ ላከ በመርከብም ሁነው ሲመጡ ማዕበል ተነሥቶ መርከቡ ተሰበረ። እግዚአብሔርም ከስጥመት አድኖ በየብስ አወጣቸው ዮሐንስ የተባለውን በአንድ ቦታ ማዕበሉ አውጥቶ ጣለው።

ዮሐንስም ተስፋ በቆረጠ ጊዜ ወደ ቅዱሳን ገዳም ሒዶ መነኰሰ። ስለ ወንድሙ ስለአርቃድዮስም እንደሞተ ተጠራጥሮ በጸም በጸሎትና በስግደትም ሥጋውን አደከመ። አርቃድዮስም ወደ ዮርዳኖስ ገዳም ገብቶ ከአንድ ቅዱስ አረጋዊ ሰው ዘንድ መንኲሶ እየተጋደለ ሦስት ዓመት ኖረ።

አስከናፍር ግን ልጆቹ በማዕበል እንደሰጠሙ በሰማ ጊዜ ከሚስቱ ጋራ ማቅ ለብሰው አመድ አንጥፈው እያለቀሱ ተቀመጡ። በአንዲት ሌሊትም አስከናፍር በሕልሙ ልጁ ዮሐንስን በራሱ ላይ ከዕንቊ የተሠራ አክሊል ተቀዳጅቶ መስቀል ይዞ አየው።

አርቃድዮስንም በኮከብ አምሳል የሆነ አክሊል በራሱ ላይ ደፍቶ አየ ከእንቅልፉም ነቅቶ ለሚስቱ ያየውን ነገራት። ከዚያም በኋላ በየአድባራቱና በየገዳማቱ የልጆቻችንን ወሬ እንመረምር ዘንድ ተነሺ እንሒድ አላትና ወደ ዮርዳኖስ ሒደው ከመጥምቁ ዮሐንስ ገዳም ደረሱ።

ልጃቸውን አርቃዴዎስን ያመነኰሰውን አረጋዊ አባትን አገኙት ችግራቸውን ነገሩት እርሱም የክርስቶስ ወዳጆች አትዘኑ ወደ ቤተ መቅደስ ስትመለሱ ልጆቻችሁን በሕይወት ታገኛላችሁ አላቸው ደስ እያላቸውም ተመለሱ።

ዮሐንስም በመስቀል በዓል ሊሳለም መጣ አረጋዊውም ጠርቶ ከአርቃድዮስ ከወንድሙ አገናኘው ተያይዘውም አለቀሱ። ደግሞ አስከናፍርን ከሚስቱ ጋራ ጠርቶ ከልጆቻቸው ጋራ አገናኛቸውና በላያቸው ወድቀው እየሳሟቸው አለቀሱ።

ከዚህ በኋላ ከዚያ አረጋዊ ዘንድ የምንኲስና ልብስ ለበሱ ሚስቱን ማርታንም ከሴቶች ገዳም አስገባት አገልጋዮችንም ነፃ አውጥቶ አሰናበተ። ገንዘቡንም ለድኆችና ለችግረኞች በተነ ከገዳምም ገብቶ በጾም በጸሎት ተወሰነ እንዲሁም የተባረኩ ልጆቹ በገደል በትሩፋት የተጠመዱ ሁነው ኖሩ ጌታችንንም ደስ አሰኙት በፍቅር አንድነትም አረፉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሰባቱ_ቅዱሳን_ሰማዕታት

በዚህችም ቀን ደግሞ የሰባቱ ሰማዕታት መታሰቢያቸው ሆነ፡፡ እንርሱም የግብጽ ሰው እለእስክንድሮስና እስክንድሮስ ከጋዛ መንደር አጋብዮስ ከቡንጥስ ከተማ ኒሞላስ ከጠራልብስ ዲዮናስዮስ ሮሜሎስና ተላስዮስ ከግብጽ አውራጃዎች የሆኑ ናቸው።

እነርሱም በመንፈሳዊ ፍቅር ጸንተው ስለ ሃይማኖት ምስክሮች ሊሆኑ ተስማሙ። በፍልስጥዔም ውስጥ ወደ አለው ቂሣርያ ደርሰው በመኰንኑ ፍት ቆሙ።

በከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማመናቸውን ገለጡ መኰንኑም በጽኑዕ ሥቃይ አሠቃይቶ ገደላቸው። የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
ዐሥራ አምስት ዓመት በሆናት ጊዜ እናትና አባቷ ምን ያከሣሻል አሏት እርሷም እኔስ ኃጢአቴን ይቅር ይለኝ ዘንድ የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እጸልያለሁ አለቻቸው። አባቷም በሰማ ጊዜ ወደ ጢባርዮስ ሒዶ የልጁን ሥራ ነገረው እርሱም ወታደሮች ልኮ ወደ ርሱ አስመጣት። ለጣዖትም እንድትሰግድ መኰንኑ አባበላት እምቢ በአለችም ጊዜ ወደ ወህኒ ቤት አስገቧት እናቷም ክርስቲያናዊት ናት እየመጣች በክብር ባለቤት በክርስቶስ እምነት ታበረታታት ነበር።

ከዚህ በኋላ የብረት የሆነ የሰሌዳ ክርታስ ይሠሩላት ዘንድ በእሳትም አግለው ክንዶቿ ከወገቦቿ ጋራ አንድ እስቲሆኑ እንዲአጣብቋት አዘዘ ይህንንም በአደረጉባት ጊዜ ያንን የብረት ክርታስ ሰብራ በደኅና ወጣች ሕዝቡም ይህን አይተው በክብር ባለቤት በክርስቶስ አራት ሺህ ሰባት መቶ ያህል አምነው በሰማዕትነት ሞቱ የሰማዕታትንም አክሊል ተቀበሉ።

ሁለተኛም ደግመው ከእሥር ቤት አስገቧት ጥፍሮች ያሉት የብረት በሬ ሠሩላት ሆዷን ያስወጓት ዘንድ ሊሰቅሏትም ወደርሷ አቀረቡት ይህንንም በአደረጉባት ጊዜ በጌታ ኃይል በሬው ወዲያና ወዲህ ተከፈለ ሕዝቡም ይህን በአዩ ጊዜ በክብር ባለቤት በጌታችን ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አምስት ያህል ሰው አምነው በሰማዕትነት አረፉ።

ከዚህም በኋላ መርዝን ከተመሉ እባቦች ጉድጓድ ውስጥ ጨመሩዋት በጸለየችም ጊዜ እንደ ትቢያ ሆኑ። ሁለተኛም አራት ሰዎች የሚሸከሙትን ከባድ ደንጊያ አምጥተው በአንገቷ ላይ ሰቀሉ በጸለየችም ጊዜ ደንጊያው ወደ ሦስት ተከፈለ። ብዙዎች አረማውያንም በክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት አረፉ።

ለቅድስቲቱ ግን የብረት ምንቸት አዘጋጁላት በውስጡ የፈላ እርሳስ በላይዋ ያፈሱባት ዘንድ በነኩት ጊዜ በላያቸው ተሰብሮ የሚያሠቃዩአትን ገደላቸው። ንጉሡም አይቶ ተቆጣ ራሷንም በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ።

ምስክርነቷን ከምትፈጸምበት ቦታም በደረሰች ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች አስጠራጢኒቃ ሆይ አንቺ ብፅዕት ነሽ ስምሽ በሕይወት መጽሐፍ ተጽፏልና የሚል ቃል መጣላት ከዚያም በኋላ በሰይፍ ተቆረጠች።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
#መጋቢት_21

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ሃያ አንድ በዚችም ዕለት የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከሙታን ለይቶ ወደ አስንሳው ወደ #አልዓዛር ቤት ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ የሔደበት ነው፣ ተአምረኛው አባት #አባ_ሊባኖስ_ዘመጣዕ ዓለምን ፍጹም በመናቅ የመነኑበት ነው፣ የማቱሳላ ልጅ #ጻድቁ_ላሜህ መታሰቢያው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቤተሰብ (አልዓዛር፣ ማርያና ማርታ)

መጋቢት ሃያ አንድ በዚችም ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ለይቶ ወደ አስንሳው ወደ አልዓዛር ቤት ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ሔደ በዚያም ምሳ አዘጋጂለት ማርታም ምግብ በማቅረብ ታገለግላቸው ነበር።

ሁለተኛዋ ማርያም ግን እግሮቹን ሽቱ እየቀባች በጸጕሩዋ ታሸው ነበር። ጌታችንም አመሰገናት እርሷ ከመቀበሪያዬ ጠብቃዋለች በማለት ስለ ቅርብ ሞቱ አመለከተ።

ዳግመኛም ድኆች ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉ እኔ ግን ከእናንተ ጋራ አልኖርም አለ በዚህም ተሰቅሎ የሚሞትበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ዳግመኛም በዚችም ቀን አልዓዛርን ሊገሉት የካህናት አለቆች ተማከሩ ገናና ስለሆነች ምልክት በእርሱ ምክንያት ብዙዎች በጌታችን የሚያምኑ ሁነዋልና።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሊባኖስ_ዘመጣዕ

በዚችም ዕለት ከዐለት ላይ ውኃ እያፈለቁ ድውያንን የሚፈውሱት ተአምረኛውና አባት አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ ዓለምን ፍጹም በመናቅ መንነዋል፡፡ እርሳቸውም የአባታችን የተክለ ሃይማኖት ገዳም ‹‹ደብረ ሊባኖስ›› በስማቸው የተሰየመላቸው ናቸው፡፡ አባ ሊባኖስ አባታቸው አብርሃም እናታቸው ንግሥት ይባላሉ፡፡ እነርሱም በወርቅና በብር እጅግ የበለጸጉ ሮማዊ ናቸው፡፡ ልጃቸውን አባ ሊባኖስን በሃይማኖት በምግባር ኮትኩተው ካሳደጓቸው በኋላ ዕድሜያቸው ሲደርስ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ያጋቧቸው ዘንድ ከቁስጥንጥንያ አገር ሚስት ባመጡለት ጊዜ እርሱ ግን ፈጽሞ እምቢ አለ፡፡ ወደጫጉላቤትም መግባትን እምቢ አለ፡፡ በዚህም ጊዜ ነቢዩ ሳሙኤልን እንደጠራው አባታችንንም እግዚአብሔር ሦስት ጊዜ በስማቸው ጠራቸውና ‹‹ከአባትህ ተለይ አንተ የመንግሥተ ሰማያት ሙሽራ ነህ እንጂ የዚህ ምድራዊ ዓለም ሙሽራ አይደለህም›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ወዴት እሄዳለሁ? ምንስ ላድርግ?›› ባሉ ጊዜ ወዲያው የታዘዘ መልአክ በሌሊት መጥቶ ከአባታቸው ቤት አውጥቶ ታላቁ አባት አባ ጳኩሚስ ዘንድ አደረሳቸው፡፡ ታላቁ አባት አባ ጳኩሚስም ለአባ ሊባኖስ በዓት በመስጠት ገዳመ ሥርዓትን፣ አስኬማ መላእክትን፣ ቅናተ ዮሐንስን አስተምረዋቸው አመነኮሷቸውና ከ8ቱ ቅዱሳን ጋር እንዲገናኙ አደረጓቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ያ ከአባታቸው ቤት ወስዶ አባ ጳኩሚስ ገዳም ያደረሳቸው ያ መልአክ ድጋሚ ተገለጠላቸውና ‹‹ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ሂድና ተጋድለህን በዚያ ፈጽም ዝናህ በስፋት ይነገራል፣ ለብዙዎችም አባት ትሆናቸዋለህ›› አላቸው፡፡ ቀጥሎም ራሱ መልአኩ ወደ ኢትዮጵያ አመጣቸውና በአክሱም ተቀመጡ፡፡ በዚያም ብዙ ከተጋደሉ በኋላ ወደ ሸዋ መጡና ወንጌልን ዞረው አስተምረው ብዙ ድውያንን ፈውሰው ከዓመታት ቆይታ በኋላ ተመልሰው አክሱም ሄዱ፡፡ በአክሱምም 7 የተለያዩ ጸበሎችን ከድንጋይ ላይ በተአምራት አፍልቀው ድውያንን ፈውሰው ዕውራንን አበሩ፡፡ በዓታቸውንም ከአክሱም ጽዮን ፊት ለፊት አድርገው ሲኖሩ ከዕለታት በአንደኛው ቀን አባታችን በተአምራት ከጭንጫ ካፈለቁት ጸበል ‹‹ተራ ውሃ ነው›› ብላ አንዲት ሴት ልጇን አዝላ ልትቀዳ መጣች፡፡ ወዲውም ከቦታው ስትደርስ አድጧት ወደቀችና ልጇም አምልጥጧት ልቡን ድንጋይ መቶት ሞተ፡፡ ሴትዮዋም ስትጮህ አባ ሊባኖስ ፈጥነው ወጡና በልጁ ላይ ጸልየው በመስቀል ምልክት አማትበው ከሞት አስነሥተውታል፡፡ ሕፃኑ ልጅ ከሞት እንደተነሣ ‹‹አምላከ አባ ሊባኖስ›› ብሎ አመሰገነ፡፡

ይህንንም ደግ ሥራቸውንና ተአምራታቸውን ያዩ አንዳንድ እኩይ ካህናት በቅናት ተመልተው ‹‹ምትሃት ነው የሚያሳየው›› ብለው በጻድቁ ላይ ሕዝቡን አሳደሙባቸው፡፡ አባታችንም ካህናቱን ለመምከር ቢሞክሩም አላስቀምጥ አሏቸው፡፡ ይልቁንም ጦር ጦራቸውን ይዘው አሳደዷቸው፡፡ አባታችንም በዚህ እጅግ አዝነው ከአክሱም ተነሥተው ደርቃ ወደምትባል ቦታ ሄዱ፡፡ በዚያም በጾም በጸሎት እየተጋደሉ ሲኖሩ በእነዚያ በጠሏቸውና በክፋት በተነሡባቸው ካህናት አገር ግን ለ3 ዓመት ምንም ዝናብ ሳይዘንብ ቀረ፡፡ አባታችን በተሰደዱባት በደርቃ አገር ግን ብዙ ዝናብ ይዘንብ ነበር፡፡ አባታችን በዚያችም አገር እንደልማዳቸው ከዐለት ላይ ውኃ አፍልቀው በውኃው ብዙ ድውያንን ፈውሰውበታል፡፡ በዚያም ትልቅ በዓት መሥርተው በተጋድሎ ሲኖሩ በክፉ የተነሡባቸው እኩይ የሆኑ ካህናት መጥተው ‹‹አባታችን በከንቱ አምተንሃል በድለንሃልና ይቅር በለን፣ በድርቅ ማለቃችን ነውና ዝናብም እንዲዘንብልን ጸልይን›› ብለው ከእግራቸው ሥር ወደቁ፡፡ አባታችንም ይቅር ብለው ከፈጣሪ አማለዷቸው፡፡ ዝናቡም ወዲያው ዘነበላቸውና በአገሪቱ ጥጋብ ሆነ፡፡

ከዚህም በኋላ አባታችን አስቀድመው ወዳዩአት ወደ ሸዋ ምድር ግራርያ መጡና በዓታቸውን በአሰቦት ጫካ አደረጉ፡፡ ነገር ግን መልአኩ ተገልጦላቸው ‹‹ሊባኖስ ሆይ! ከዚህ ቦታ የአንተ መኖሪያ አይደለም፣ በዚህ ቦታ ላይ እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያገናኝ የሚያስታርቅ ታላቅ ጻድቅ ይወጣበታልና ይህ ቦታ የእርሱ ርስት ነው፣ የብዙ መነኮሳትም መንደር ይሆናል ነገር ግን የቦታው ስም በአንተ ስም ይጠራልሃል›› አላቸው፡፡ በኋላ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ተወልደው በዓታቸውን በዚያ ቦታ ላይ ሲያጸኑ ቦታው ግን ‹‹ደብረ ሊባኖስ›› ተብሎ በመጀመሪያው አባት ስም ተሰየመ፡፡ መልአኩም በሌሊት እየመራ ወደ አክሱም ወሰዳቸው፡፡ ከዚያም ‹‹ታሪክ ወደምትሠራበት ዕጣ ክፍልህ ወደሆነው ቦታ አደርስሃለሁ›› አላቸውና ወደ ኤርትራ አካለ ጉዛይ አውራጃ ልዩ ስሙ መጣዕ ወደተባለው ቦታ ወሰዳቸው፡፡ በዚያም አባታችን ድውያንን እየፈወሱ፣ ለምፃሞችን እያዳኑ፣ ሙታንን እያስነሡ ብዙ ተአምራትን እያደረጉ ወንጌልን እየሰበኩ ‹‹ሊባኖስ ዘመጣዕ›› የሚባለውን ትልቁን ገዳማቸውን መሠረቱ፡፡ በወቅቱ የነበረው ዐፄ ገብረ መስቀልም የመጀመሪያውን ቤተ ክርስቲያን አሠራላቸው፡፡

ቅዱስ ላሊበላ 23 ዓመት ሙሉ ካነጻቸው እጅግ ድንቅ 11 ቤተ መቅደሶች ውስጥ አንደኛውን በአባ ሊባኖስ ስም ሰይሞላቸዋል፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል ያሠራላቸው ሌላኛው ገዳማቸው ትግራይ ተንቤን ውስጥ ይገኛል፡፡ እጅግ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ የሚታወቁት አባታችን እንደ ተስዓቱ ቅዱሳን ከሮም በመምጣት በሀገራችን ላይ ብርሃንን አብርተዋል፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጻድቁ_ላሜህ

በዚችም ዕለት የማቱሳላ ልጅ የላሜህ መታሰቢያው ነው። እርሱም አንድ መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኑሮ ኖኀን ወለደው ከወለደውም በኋላ አምስት መቶ ስልሳ አምስት አመት ኖረ።

በድምር ሰባት መቶ አርባ ሰባት ዓመት ኖረ። እግዚአብሔርንም አገልግሎት በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት እና #ከገድላት_አንደበት)
ታላቁ ቴዎዶስዮስም በነገሠ ጊዜ ስለ መቅዶንዮስ ስለ ሰባልዮስና ስለ አቡሊናርዮስ በቊስጥንጥንያ መቶ ሃምሳ ኤጲስቆጶሳትን በአንድነት ሰበሰበ። ይህም አባት በጉባኤው ውስጥ አንዱ እርሱ ነበር መናፍቃንም መመለስን እንቢ በአሉ ጊዜ ከወገኖቹ ጋር ረገማቸው አውግዞም ለያቸው።

ሃይማኖትን ያቀኑ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ በሠሩት በጸሎተ ሃይማኖት ላይ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም ከሚለው ቀጥሎ እንዲህ የሚል ጨመረ። "የባሕርይ ገዢ በሚሆን በሚያድን በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን። ከአብ የተገኘ ከአብ ከወልድ ጋር እንስገድለት እናመሰግነውም በነቢያት አድሮ የተናገረ።

ሐዋርያት ሰብስበው አንድ በአደረጓት ከሁሉ በላይ በምትሆን ክብርት ንጽሕት ጽንዕት ልዩ በምትሆን በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።ኃጢአት በሚሠረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን። የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን የሚመጣውንም የዘላለም ሕይውት።"

ከዚህም በኋላ ይህ አባት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ። ሁለተኛም ስለ ጸሎተ ሃይማኖትና ስለ ትርጓሜው ሌላ በውስጡ ዐሥራ ስምንት ያህል ድርሳን ያለው መጽሐፍ ደረሰ። እርሱም ጥበብን እውቀትን ሁሉ የተመላ እጅግ የሚጠቅም ነው። በጵጵስናውም መንበር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከኖረ በኋላ በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
ሰላማን በአቃሊት ቅበረኝ ብለዋቸው በቃሬዛ አድርጎ ከጌርጌሳ ወደ አቃሊት ወሰዷቸው፤ እዚያም ሐምሌ 28 ቀን በሰላም ዐረፉ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰባት አክሊላት አቀዳጅቷቸዋል፡፡ዐፅማቸውም ከተቀበረ ከ140 ዓመት በኋላ በመጋቢት 23 ቀን ወደ ደብረ ሊባኖስ በክብር መጥቶ ዐርፏል፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት እና #ከገድላት_አንደበት)
#መጋቢት_25

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

#ሐዋርያ_አንሲፎሮስ

መጋቢት ሃያ አምስት በዚች ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የከበረና የተመሰገነ ሐዋርያ አንሲፎሮስ አረፈ።

ይህም ከእስራኤል ልጆች ከቢንያም ነገድ ነው ወላጆቹም የኦሪትን ሕግ የሚጠብቁ ናቸው እርሱም ሥራዎቹን በአየ ጊዜ ትምህርቶቹንም በሰማ ጊዜ ጌታችንን ተከተለው።

ድንቅ የሆኑ ተአምራቶችን እየተመለከተ ጥቂት ቀን ተቀመጠ ጌታችንም በሀገረ ናይን የመበለቲቱን ልጅ በአስነሣው ጊዜ ከዚያ ነበረ። ይህን አይቶ ወዲያውኑ አመነ ሌላ ምልክት አልሻም ብልጭ ብልጭ ሲል የነበረ የአይሁድ የሕግ ፋና ትቶ ወደ ዕውነተኛ ፀሐይ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርቦ ደቀ መዝሙሩ ሆነው እንጂ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከዐረገ በኋላ በጽዮን አዳራሽ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋራ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብሎ ሐዋርያትንም በመከተል በብዙ አገሮች ውስጥ አስተማረ።

ሐዋርያትም በሀገረ አቴና ኤጲስቆጶስ አድርገው ሾሙት በውስጥዋም ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን አሳመነ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው በትምህርቱና በምክሩ ዕውቀት እንዲአድርባቸው አደረጋቸው በትምህርቱም ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ፈወሳቸው።

ተጋድሎውንም በፈጸመ ጊዜ በሰላም አረፈ በድል አድራጊነትም የክብር አክሊል ተቀበለ።

መላ ዘመኑ ሰባ ዓመት ነው በአይሁድ ሕግ ሃያ ዘጠኝ ዓመት በክርስትና ሕግ አርባ አንድ ዓመት ኖረ። እነሆ የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስም በመልእክቶቹ አስታውሶታል ሰላምታም አቅርቦለታል።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
#መጋቢት_26

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ሃያ ስድስት በዚህች ዕለት #የክብር_ባለቤት_ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ፣ የሐዲስ ኪዳንንም የቊርባን ሥርዓት አሳያቸው፣ የከበረችና የተመሰገነች #ድንግሊቱ_ኢዮጰራቅስያ አረፈች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ምሴተ_ሐሙስ

መጋቢት ሃያ ስድስት በዚህች ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ እንዲህም አላቸው። እናንተም ለባልንጀሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉ።

ደግሞ የሐዲስ ኪዳንን የቊርባን ሥርዓት አሳያቸው። አሁንም በዚች ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችንን ለአይሁድ ይሁዳ አሳልፎ ሰጠው።

ነቢያት ትንቢት እንደተናገሩ የሽያጩን ዋጋ ሠላሳ ብር ተቀበለ። ይቅርታው ቸርነቱ ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋር ለዘላለሙ ይኑር አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ኢዮዸራቅስያ

በዚህች ቀን የከበረችና የተመሰገነች ድንግሊቱ ኢዮጰራቅስያ አረፈች። ይችም የተቀደሰች ብላቴና የንጉሥ አኖሬዎስ ዘመዱ ለሆነ በሮሜ ከተማ ከቤተ መንግሥት የአንድ ታላቅ መኰንን ልጅ ናት።

የሚሞትበትም ቀን በደረሰ ጊዜ እርሷን ልጁን ለንጉሥ አኖሬዎስ ይጠብቃት ዘንድ አደራ ሰጠው። አባቷም ካረፈ በኋላ ለአንድ ታላቅ መኰንን ልጅ ንጉሥ አኖሬዎስ አጫት።

በዚያም ወራት እናቷ የመሬቷን ግብር ልትቀበል በሏ የተወላትን የአትክልት ቦታዎቿም ያፈሩትን ይችንም ቅድስት ብላቴናዋን ከእርሷ ጋር ወሰደቻት። ዕድሜዋ ዘጠኝ ዓመት ሁኖ ሳለ አስከትላት ወደ ግብጽ ሔደች።

ወደ ግብጽ አገርም በደረሱ ጊዜ ሥራቸውን እስከሚፈጽሙ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ኖሩ። በዚያ ገዳም ውስጥ የሚኖሩ ደናግል ለገድል የተጸመዱ ናቸው። የሥጋ መብልን ቅባትም ቢሆን ጣፋጭ ፍሬዎችንም ምንም ምን አይበሉም ወይንም ቢሆን ከቶ አይቀምሱም ያለ ምንጣፍም በምድር ላይ ይተኛሉ።

ኢዮጰራቅስያም በዚያ ገዳም ውስጥ መኖርን ወደደች ገዳሙን ከምታገለግል መጋቢዋ ጋር ተፋቅራለችና። መጋቢዋም አንቺ ከዚህ ገዳም ወጥተሽ ተመልሰሽ እጮኛሽን ላትፈልጊ ቃል ግቢልኝ አለቻት ኢዮጰራቅስያም በዚህ ነገር ቃል ገባችላት።

እናቷ ሥራዋን በፈጸመች ጊዜ ወደ አገርዋ ልትመለስ ወደደች ልጅዋ ግን እኔ የዚህን የኃላፊውን ዓለም ሙሽርነት ስለማልሻ ራሴን ለክብር ባለቤት ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰማያዊ ሙሽራ ሰጥቻለሁ ብላ ከእርሷ ጋር መመለስን አይሆንም አለች።

ብላቴናዋ ከእርሷ ጋር እንደማትመለስ በተረዳች ጊዜ ገንዘቧን ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች መጽውታ ከልጁዋ ጋር በዚያ ገዳም ብዙ ዘመን ኑራ ከዚያ በኋላ አረፈችና በዚያው ቀበርዋት።

ንጉሥ አኖሬዎስም የኢዮጰራቅስያ እናቷ እንደሞተች ሰምቶ ለአጫት ያጋባት ዘንድ ኢዮጰራቅስያን እንዲአመጧት መልእክተኞችን ላከ። ቅድስቲቱም ንጉሥ ሆይ እወቅ የክብር ባለቤት ለሆነ ለሰማያዊ ሙሽራ ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ራሴን ሰጥቻከሁና ቃል ኪዳኔን መተላለፍ አይቻለኝም ብላ ወደ ንጉሡ ላከች።

ንጉሥ አኖሬዎስም መልእክቷን በሰማ ጊዜ አደነቀ ስለርስዋም አለቀሰ እርስዋ በዕድሜዋ ታናሽ ብላቴና ናትና። ይህች የከበረች ኢዮጰራቅስያ ግን ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለች ለመንፈሳዊ ሥራ እጅግ የተጠመደች ሆነች በየሁለት ቀን ሁለት ሁለት ቀን እያከፈለች መጾም ከዚያም በየሦስት ቀን ሦስት ሦስት ቀን ትጾም ጀመር ከዚያም በየሰባት ቀን ሰባት ሰባት ቀን የምትጾም ሆነች።

በተለየች በከበረች አርባ ጾም ምንም ምን የምትበላ አልሆነችም። ሰይጣንም በእርሷ ላይ ቀንቶ አስጨናቂ በሆነ አመታት እግርዋን መታት ብዙ ቀኖችም በሕማም ኖረች ከዚያም እግዚአብሔር ራርቶላት ከደዌዋ አዳናት በሽተኞችንም ታድናቸው ዘንድ በሽተኞችን የምትፈውስበትን ሀብት ሰጣት።

ለእመ ምኔቷና ለእኀቶቿ ደናግል በመታዘዝ ታገለግላቸው ነበር በእኀቶች ደናግል ሁሉ ዘንድ የተወደደች ናት። በአንዲት ዕለትም እመ ምኔቷ አክሊላትንና አዳራሾችን እንደ አዘጋጁ ራእይን አየች እርሷም እያደነቀች ከልጆቼ ለማን ይሆን ይህ የሚገባት ስትል እሊህ አክሊላትና አዳራሾች የተዘጋጁላት ለልጅሽ ለኢዮጰራቅስያ ነው እርሷም ወዲህ ትመጣለች አሏት።

ይህንንም ራእይ ለደናግሎች ነገረቻቸው እግዚአብሔርም ከዚህ ዓለም መከራ ሊያሳርፋት እስከ ወደደበት ቀን ለኢዮጰራቅስያ እንዳይነግሩዋት አዘዘቻቸው።

ከዚህ በኋላ በሆድ ዝማ ሕማም ጥቂት ታመመች ሁሉም ደናግል ከእመ ምኔቷ ጋር ወደ እርሷ ተሰበሰቡ ያቺ ቃል ኪዳን ያስገባቻት የምትወዳት መጋቢዋም መጣች በእግዚአብሔርም ዘንድ እንድታስባቸው ለመንዋት እርሷም በጸሎታቸው እንዲአስቧት ለመነቻቸው ከዚያም አረፈች ።

የተቀደሰችና የተከበረች እርሷን እኅታቸውን አጥተዋታልና ደናግሉ እጅግ አዝነው አለቀሱ። ከዚህም በኋላ የምትወዳት የገዳሙ መጋቢ የነበረች አረፈች ከእርስዋም በኋላ እመ ምኔቷ ጥቂት ቀን ታመመች ደናግሎችንም ሰብስባ በላያችሁ የምትሾሙትን እመ መኔት ምረጡ ስለ እኔ ኢዮጰራቅስያ ለምናለችና እኔ ወደ ጌታዬ ኢየሱስ እሔዳለሁ አሁን ግን ደጁን በላዬ ዘግታችሁ ሔዱ አለቻቸው እነርሱም እነዳዘዘቻቸው አደረጉ። በማግሥቱም ማለድ ብለው ሲደርሱ አርፋ አገኟት፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
ከዚህም በኋላ የከበረ አባ መቃርስ ተመልሶ ከእርሱ አስቀድሞ በዚያ በረሀ ውስጥ ሰው እንዳለ ያይ ዘንድ ወደ በረሀው ውስጥ ዘልቆ ገባ። ዕራቁታቸውን የሆኑ ሁለት ሰዎችን አይቶ ፈራ የሰይጣን ምትሐት መስሎታልና እልቦት ቦሪቦን ብሎ ጸለየ ይህም አቡነ ዘበሰማያት ማለት ነው እነርሱም በስሙ ጠርተው መቃሪ ሆይ አትፍራ አሉት እርሱም በበረሀ የሚኖሩ ቅዱሳን እንደሆኑ አውቆ ወደ እርሳቸው ቀርቦ እጅ ነሣቸው። እነሱም በዓለም ስላሉ ሰዎች ስለ ሥራቸውም ጠየቁት እርሱም በቸርነቱ እግዚአብሔር በሁሉም ላይ አለ ብሎ መለሰላቸው።

እርሱም ደግሞ የክረምት ቅዝቃዜ ይቀዘቅዛቸው እንደሆነ የበጋውም ትኩሳት ያልባቸው እንደሆነ ጠየቃቸው። እነርሱም በዚህ በረሀ እግዚአብሔር አርባ ዓመት ጠብቆናል የክረምት ቅዝቃዜ ሳይቀዘቅዘን የበጋ ትኩሳት ሳያልበን ኖርን ብለው መለሱለት ደግሞ እንደናንተ መሆን እንዴት እችላለሁ አላቸው።

እነርሱም ወደ በዓትህ ተመልሰህ ስለ ኃጢአትህ አልቅስ አንተም እንደእኛ ትሆናለህ አሉት ከእነርሱም በረከትን ተቀብሎ ወደቦታው ተመለሰ።

በእርሱ ዘንድ መነኰሳት በበዙ ጊዜ ጕድጓድ ቆፍረው መታጠቢያ ሠሩለት ሊታጠብ በወረደ ጊዜ ሊገድሉት ሰይጣናት በላዩ አፈረሱት መነኰሳትም መጥተው አወጡት።

እግዚአብሔርም ከዚህ አለም መከራ ሊያሳርፈው በወደደ ጊዜ ሁልጊዜ የሚጐበኘውን ኪሩብን ወደርሱ ላከ። እርሱም እኔ ወደ አንተ መጥቼ እወስድሃለሁና ተዘጋጅ አለው ከዚያ በኋላ አባ እንጦንስንና የቅዱሳንን አንድነት ማኅበር ሰማያውያን የሆኑ የመላእክትንም ሠራዊት በእግዚአብሔር እጅ ነፍሱን እስከ ሰጠ ድረስ ያይ ነበር።

መላ የዕድሜው ዘመን ዘጠና ሰባት ሆነ። የቅዱስ መቃርስ ነፍስ ወደ ሰማይ ስታርግ እንዳየ በዚህ ነገር ደቀ መዝሙሩ አባ በብኑዳ ምስክር ሆነ ሰይጣናትን እንደሰማቸው እየተከተሉ መቃሪ ሆይ አሸነፍከን አሸነፍከን እያሉ ሲጮኹ እስከ ዛሬ ገና ነኝ አላቸው ወደ ገነትም ሲገባ መቃሪ ሆይ አሸነፍከን ብለው በታላቅ ድምፅ ጮኹ የክብር ባለቤት ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመስገን ስሙም ይባረክ ከእጃችሁ ያዳነኝ አላቸው ብሎ መስክሮአል።

የሥጋው ፍልሰትም እንዲህ ሆነ እርሱ በሕይወት ሳለ ሥጋውን እንዳይሠውሩ ልጆቹን አዞአቸው ነበር የሀገሩ የሳሱይርም ሰዎች መጥተው ለደቀ መዝሙሩ ለዮሐንስ ገንዘብ ሰጡ።

ይህንንም ስለ ገንዘቡ ፍቅር ይመክረውና ይገሥጸው የነበረ ገንዘብ ከመውደድ ተጠበቅ የሚለው ነው። እርሱም መርቶ የቅዱስ አባ መቃርስን ሥጋ አሳያቸው ወደሀገራቸው ሳሱይር ወሰዱት እስከ ዓረብ መንግሥት መቶ ስልሳ ዘመን በዚያ ኖረ ደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ግን ገንዘብ ስለመውደዱ ዝልጉስ ሆነ።

ከዚህም በኋላ ልጆቹ መነኰሳት ወደ ሀገሩ ወደ ሳሱይር ሔዱ የከበረ አባት የአባ መቃርስን ሥጋ ሊወስዱ ፈለጉ የአገር ሰዎችም ከመኰንኑ ጋር ተነሥተው ከለከሉአቸው በዚያቺም ሌሊት የከበረ አባ መቃሪ ለመኰንኑ ተገልጦ ተወኝ ከልጆቼ ጋራ ልሒድ አለው። መኰንኑም መነኰሳቱን ጠርቶ የአባታቸውን ሥጋ ተሸክመው ይወስዱ ዘንድ ፈቀደላቸው።

በዚያን ጊዜም ተሸከመው አክብረው ወሰዱት በብዙ ምስጋና በመዘመርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ነሐሴ ዐሥራ ዘጠኝ ቀን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከእርሱም ታላላቅ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ። ማለድ ብለው ሲደርሱ አርፋ አገኟት፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ንጉሥ_ሰማዕት_ገላውዴዎስ

በዚህችም ቀን የኢትዮጵያ ንጉሥ ሰማዕት ገላውዲዎስ አንገቱን የተቆረጠበት ቀን ነው። ይህ ቅዱስም በተግሣጽ በምክር በፈሪሀ እግዚአብሔር አደገ አባቱ ንጉሥ ልብነ ድንግል ሃይማኖቱ የቀና ነበርና በዘመኑም የእስላም ወገን የሆነ ስሙ ግራኝ የሚባል ተነሥቶ አብያተ ክርስቲያናትን አጠፋ።

ከንጉሥ ልብነ ድንግል ጋር ጦርነት ገጠመ ንጉሡም ወግቶ መመለስ ቢሳነው አርበኞች ሠራዊትን እስከሚሰበስብ ከእርሱ ሸሸ በስደትም እያለ በድንገት ታሞ ሞተ።

ይህም አመፀኛ የኢትዮጵያን ሀገሮች እያጠፋ ዐሥራ አምስት ዓመት ያህል ኖረ። ከኢትዮጵያም ሕዝቦች የሚበዙትን ማርኮ ከቀናች ሃይማኖት አውጥቶ የእርሱ ሃይማኖት ተከታዮች አደረጋቸው በመመካትም እንዲህ አለ። ሀገሮችን ሁሉ ግዛቶቼ ስለ አደረግኋቸው ከእንግዲህ የሚቃወመኝ የለም።

ከዙህ በኋላ እግዚአበሔር ይህን ቅዱስ ገላውዴዎስን አስነሣ ከግራኝ ታላላቅ መኳንቶቹ ጋር ጦርነት ገጠማቸው ድልም አድርጎ አሳደዳቸው።

ግራኝም በሰማ ጊዜ ተቆጣ ከቱርክ አርበኞች ጋርና ከአእላፍ ፈረሰኞች ጋር መጥቶ ንጉሡን ገጠመው ጌታችንም ግራኝን በንጉሥ ገላውዴዎስ እጅ ጣለው ገደለውም። ግራኝን በመፍራት የተበተኑ ሁሉ ከተማረኩበትም ሁሉ ተመለሱ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናትም ተመልሰው ታነፁ የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስ ሃይማኖት ተቃናች።

ከዚህም በኋላ ከእስላሞች ወገን አንዱ ከብዙ አርበኞች ሠራዊት ጋር መጣ በመድኃኒታችን የስቅለት በዓል ከጥቂት ሰዎች ጋራ ተቀምጦ ሳለ በድንገት ንጉሡን ተገናኘው ሰዎቹም የጦር መኰንኖች እስቲሰበሰቡ ፈቀቅ እንበል አሉት።

እርሱ ግን የክርስቲያኖችን መማረክና የአብየተ ክርስቲያናትን መፍረስ አላይም ብሎ እምቢ አለ እንዲህም እያለ ወደ ውጊያው መካከል ገብቶ በርትቶ ሲዋጋ የኋላ ኋላ እስላሞች ሁሉም ከበቡት።

ተረባረቡበትም በጐራዴም ጨፈጨፉት በብዙ ጦሮችም ወጉት ከፈረሱም ጣሉት የከበረች አንገቱንም ቆረጡት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት እና #ከገድላት_አንደበት)
#መጋቢት_28

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

#ጻድቅ_ንጉስ_ቈስጠንጢኖስ

መጋቢት ሃያ ስምንት በዚች ቀን ጻድቅ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ አረፈ። የዚህ ቅዱስ የአባቱ ስም ቍንስጣ የእናቱ ስም ዕሌኒ ነው ቊንስጣም በራንጥያ ለሚባል አገር ንጉሥ ነው መክስምያኖስም በሮሜ በአንጾኪያና በግብጽ ላይ ነግሦ ነበር።

ይህም ቍስጣ አረማዊ ነበር ግን በጎ ሥራ ያለው እውነትን የሚወድ በልቡናውም ይቅርታና ርኃራኄን የተመላ ክፋት የሌለበት ነው። ወደ ሮሐ ከተማ በሔደ ጊዜ ዕሌኒን አይቶ ሚስት ልትሆነው አገባት እርሷም ክርስቲያናዊት ናት። ንጉሥ ቈስጠንጢኖስንም ፀንሳ ወለደችው ስሙንም ቈስጠንጢኖስ ብላ ጠራቸው ይህም ዝንጉርጒር ማለት ነው።

ከዚህም በኋላ ንጉሥ ቊንስጣ ዕሌኒን በዚያው ትቷት ወደ በራንጥያ ከተማ ተመለሰ። እርሷም ልጇን እያሳደገች በዚያው ኖረች የክርስትናን ትምህርት አስተማረችው ይቅርታንና ርኅራኄን በክርስቲያን ወገኖች ላይ እንዲያደርግ በልቡናው ትዘራበት ነበር። እርሷ ክርስቲያን ስትሆን የክርስትና ጥምቀትን ታጠምቀው ዘንድ አልደፈረችም መንፈሳዊ ዕውቀትን ሁሉ በማስተማር አሳደገችው ዳግመኛም ለመንግሥት ልጆች የሚገባውንም ሁሉ።

ከዚያም በኋላ ወደ አባቱ ሰደደችው አባቱም በአየው ጊዜ ደስ ተሰኘበት ዕውቀትን የተመላ ሁኖ ፈረስ በመጋለብም ብርቱና የጸና ሆኖ አግኝቶታልና በበታቹም መስፍን አድርጎ ሹሞ በመንግሥቱ ሥራ ላይ ሁሉ ሥልጣን ሰጠው።

ከሁለት ዓመትም በኋላ አባቱ አረፈ ቈስጠንጢኖስም መንግሥቱን ሁሉ ተረከበ የቀና ፍርድንም የሚፈርድ ሆነ ከእርሱ በፊት የነበሩ ነገሥታት የጫኑባቸውን ጽኑ አገዛዝ ከሰዎች ላይ አስወገደ። አሕዛብም ሁሉ ታዘዙለት ወደዱትም የአገዛዙ ቅንነትና የፍርዱ ትክክለኛነት በአገሮች ሁሉ እስቲሰማ ተገዙለት።

የሮሜ ሰዎች ታላላቆች መልእክትን ወደርሱ ላኩ ከከሀዲ መክስምያኖስ ጽኑ አገዛዝ እንዲያድናቸው እየለመኑ እርሱ አሠቃይቷቸው ነበርና። ነመልእክታቸውንም በአነበቡ ጊዜ ስለ ደረሰባቸው መከራ እጅግ አዘነ ያድናቸውም ዘንድ ምን እደሚያደርግ በዐደባባይ ተቀምጦ እያሰበ ሲያዝን እነሆ ከቀኑ በስድስት ሰዓት በቀትር ጊዜ ኅብሩ እንደ ከዋክብት የሆነ መስቀል ታየው በላዩም በዮናኒ ቋንቋ ኒኮስጣጣን የሚል ጹሑፍ አለ ትርጓሜውም በዚህ ጠላትህን ድል ታደርጋለህ ማለት ነው።

የመስቀሉም ብርሃን የፀሐይን ብርሃን ሲሸፍነው በአየ ጊዜ አደነቀ። በላዩ ስለተጻፈውም አስቦ ለጭፍሮቹ አለቆችና ለመንግሥቱ ታላላቅ ባለሥልጣኖች አሳያቸው። እነርሱም ቢሆኑ ይህ መስቀል ስለምን እንደተገለጠ አላወቁም።

በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ለቈስጠንጢኖስ በራእይ ተገልጦ እንዲህ አለው በቀኑ እኩሌታ በቀትር በአየኸው በዚያ መስቀል አምሳል ላንተ ምልክት አድርግ በርሱም ጠላትህን ድል ታደርጋለህ አለው። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ልቡ ጸና የወርቅ መስቀልም አሠርቶ በነገሠበት ዘውድ ላይ አደረገው መኳንንቱንና ወታደሮቹን ጭፍሮቹን ሁሉ መስቀል ሠርተው በጦር መሣሪያቸው ላይ ያደርጉ ዘንድ አዘዛቸው እነርሱም እንዳዘዛቸው አደረጉ።

ይህም የሆነው በበራንጥያ በነገሠ በሰባተኛ ዓመቱ ነው። የሮሜን ሰዎች ከሥቃያቸው ሊያድናቸው ሠራዊቱን ሰብስቦ ተነሥቶ ወጣ። መክስምያኖስም ሰምቶ በታላቅ ወንዝ ላይም ታላቅ ድልድይ ሠርቶ ወደ ቈስጠንጢኖስም ተሻግሮ ከእርሱ ጋራ ተዋጋ።

የመስቀሉም ምልክት ቀድሞ በታየ ጊዜ የመክስምያኖስ ሠራዊት ድል ይሆኑ ነበር የቈስጠንጢኖስም ሠራዊት ከመክስምያኖስ ሰራዊት ብዙ ሰው ገደሉ። የቀሩትም ሸሽተው ሲሔዱ ከመክስምያኖስ ጋር ሊሻገሩና ወደ ሮሜ ሊገቡ ድልድይ ላይ ወጡ ድልድዩም ፈርሶ ፈርዖን ከሠራዊቱ ጋራ እንደ ሠጠመ እንዲሁ መክስምያኖስ ከሠራዊቱ ጋራ ሠጠመ።

ቈስጠንጢኖስም ወደ ሮሜ ከተማ ሲገባ የሮሜ ሰዎች ከካህናት ጋራ መብራቶች ይዘው በእንቍ የተሸለሙ አክሊሎችን ደፍተው እምቢልታ እየነፉ ተቀበሉት የተማሩ ሊቃውንትም የከበረ መስቀልን ሲያመሰግኑት የሀገራችን መዳኛ ይሉት ነበር ለከበረ መስቀልም ሰባት ቀን በዓል አደረጉ።

ቈስጠንጢኖስም ዳግመኛ በሮሜ ነገሠ ከሀዲዎች የሆኑ መክስምያኖስና ዲዮቅልጥያኖስ ስለ ክብር ባለቤት ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት ያሠሩአቸውን እሥረኞች ሁሉንም ፈታቸው ደግሞ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ ብሎ ዓዋጅ አስነገረ።

ዳግመኛም ክርስቲያኖችን እንዲአከብሩአቸው እንጂ እንዳያዋርዱአቸው የጣዖታቱንም ገንዘብና ምድራቸውን ለካህናት እንዲሰጧቸው አዘዘ ክርስቲያኖች በአረማውያን ላይ እንዲሾሙ አደረገ። ዳግመኛም አባቶቻችን ሐዋርያት እንዳዘዙ ማንም ሰው በሰሙነ ሕማማት ሥራ እንዳይሠራ አዘዘ።

በነገሠ በሥስራ አንድ ዓመት በሮሜ ሊቀ ጳጳሳት በሶል ጴጥሮስ እጅ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ። ሠራዊቱም ሁሉ። ይህም የከበረ መስቀል ከተገለጠለት በኋላ በአራት ዓመት ነው።

ከዚህ በኋላም በእርሱ ርዳታና ድል ያገኘበትን የሚያድን ስለ ሆነ ስለ ጌታችን መስቀል ትመረምር ዘንድ እናቱ ዕሌኒን ወደ ኢየሩሳሌም ላካት። እርሷም ዐመፀኞች አይሁድ ቀብረው ከደፈኑት ቦታ አወጣችው።

በዘመኑ ሃይማኖታቸው የቀና የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ጳጳሳት የአንድነት ስብሰባ በኒቅያ ስለ አርዮስ ተደረገ። ለክርስቲያኖች መመሪያ በበጎ አሠራር ክርስቲያናዊት ሥርዓት ተሰራች።

ከዚህም በኋላ በበራንጥያ ታላቅ ከተማ ሊሠራ አሰበ እንደ አሰበውም ታላቅ ከተማ ሠርቶ በስሙ ቍስጥንጥንያ ብሎ ጠራት። በውስጧም አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በአግያና በሶፍያም ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሠራ መንፈሳዊ በሆነ በመልካም ጌጥ ሁሉ አስጌጣት። በውስጥዋ ከሐዋርያት የብዙዎቹን ዓፅም ከሰማዕታትና ከቅዱሳን ጻድቃን ሥጋቸውን ስለሚሰበስብ።

የክብር ባለቤት ጌታችንን ደስ አሰኝቶ መልካም ተጋድሎውን ከፈጸመ በኋላ በኒቆምድያ ከተማ ጥቂት ታሞ አረፈ። ገንዘውም በወርቅ ሣጥን አድርገው ተሸክመው ወደ ቊስጥንጥንያ አደረሱት የጳጳሳት አለቆችና ካህናቱ ከሁሉ ሕዝብ ጋር ወጥተው ተቀበሉት በብዙ ጸሎት በመዘመርና በማኅሌት በምስጋና ወደ ከበሩ ሐዋርያት ቤተ መቅደስ አስገብተው በክብር አኖሩት።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
ምሕረትንና ርኅራኄን የተመላች እመቤቴ የብርሃን እናት ድንግል ማርያም ይህን ስትናገረኝ እነሆ በእጃቸው የጦር መሣሪያ የያዙ ኃይለኞች ሰዎችን የተሞሉ መርከቦችን በቅርብ አየኋቸው እጅግም ፈራሁ እመቤቴ ማርያምም ተሠወረችኝ። ነገር ግን ከደመና ውስጥ ጳውሎስ ሆይ ሰዎችን አጥምቅ ማጥመቅንም አታቋርጥ የሚለኝን ቃል እሰማ ነበር። እኔም በታላቅ ቃል ፈጣሪዬ ሆይ ይህን የባሕር ውኃ ለእሊህ ለተጣሉ በጎች ሰይጣንም ለማረካቸው ጥምቀትን አድርገው ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በዚህ ባህር ጥምቀት እሊህን ሰዎች በሦስትነትህ ስሞች የልጅነትን ክብር የሚቀበሉ አድርጋቸው በማለት አሰምቼ ተናገርኩ።

እንዲህም ይህን እያልኩ ከባሕሩ ውኃ ዘግኜ ሰዎች በአሉባቸው መርከቦች በላያቸው ረጨሁት የሰዎቹም ቁጥራቸው አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ነው። እኔ ወደአለሁበት የባሕር ዳር በደረሱ ጊዜ ከመርከባቸው ወጥተው ፈለጉኝ እኔም እመቤቴ የብርሃን እናት እንዳዘዘችኝ በፊታቸው ቆምኩ በረድኤቷ ተማምኛለሁና አልፈራሁም። በአዩኝም ጊዜ ሁሉም በፊቴ ሰገዱ በአንድ ቃልም ቅዱስ ጳውሎስ ሆይ ፍቅር አንድነት ለአንተ ይሁን ወደአንተ ከመድረሳችን በፊት በመርከቦች ውስጥ እያለን እኛ ያየነውን አየህን አሉኝ።

እኔም አዲስ የተወለዳችሁ ልጆች ሆይ ምን አያችሁ አልኋቸው የሰማይ ደጆች ተከፍተው የቀኝ እጅ እንደ እሳት ነበልባል ተዘርግታ አየን ደግሞ የፊቷ ብርሃን ከፀሐይ ሰባት እጅ የሚበራ ሴት አየን። እርሷም ከደመና በታች የምትረጨውን ውኃ ተቀብላ በላያችን ትረጨዋለች ትስመናለች ታቅፈናለችም። በራሲቻችንም ላይ የብርሃን አክሊሎችን ታደርጋለች አሉኝ። ይህንንም በሰማሁ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለኝ በስሙ በምንሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዳለ ተረዳሁ።

ከዚህም በኋላ ሌሎች መርከቦች መጡ ኃይለኞች ሰዎችን ከጦር መሣሪያ ጋር የተመሉ ናቸው እንዲህም እያሉ ዛቱበኝ። አንተ ሥራየኛ ጥበበኞች ሕርምስና በለንዮስ ታምራት የሚያደርጉባቸው የጠልሰም መጻሕፍቶች ከእኛ ጋራ እንዳሉ ዕወቅ በማለት እኔም ቸር ፈጣሪዬ ሆይ የቀደሙትን በጎች ይቅር እንዳልካቸውና በውስጣቸው ኃይልህን እንደገለጥክ ለእነዚህም እንዲሁ ኃይልህን ግለጥ ይቅርም በላቸው አልኩ።

ከዚያም በኋላ ከባሕሩ ውኃ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥምቀትን ይሁናችሁ አልኩ ወዲያውኑ መርከቦች ከባሕሩ ዳር ደረሱ። ሁሉም ሰዎች ከመርከብ ወጥተው በፊቴ ሰገዱ የቸር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሆይ እናመሰግንሃለን አሉኝ።

ይህንንም ድንቅ ተአምር ከቀደሙት ባልንጀሮቻቸው ጋራ ተነጋገሩ ዜናዬም በዚያች አገር ንጉሥ ዘንድ ተሰማ እርሱም ከሰራዊቱ ጋር ተነሳ በመርከቦችም ተጭነው ወደእኔ መጡ። እኔም ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አቅንቼ የፈጣሪዬን ስም ጠራሁ ባሕርዋንም በመስቀል ምልክት አማተብኩባት። እንዲህም አልኳት አንቺ ባሕር በእግዚአብሔር ልጅ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ትከፈዪ ዘንድ አዝሻለሁ ምድሩም ይገለጥ መርከቦችም በየብስ ውስጥ ይቁሙ።

ነገሬንም ሳልጨርስ ባሕርዋ ተከፈለች በውስጥዋም ዐሥራ ሦስት ጎዳናዎች ተገለጡ መርከቦቹም ውኃ በሌለው ምድር ላይ ቆሙ ይህንንም አይተው ሰይፎቻቸውን መዘዙ ዕንጨቶችም ሆነው አገኙአቸው እኔም ከሕህሩ ውኃ ዘግኜ በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እያልኩ በላያቸው ረጨሁ። በዚያን ጊዜ እሊያ መርከቦች ነፋስ ተሸክሟቸው ያለ ውኃ ከምድር ከፍ ከፍ ብለው ተጓዙ ሰዎችም ከውስጣቸው ወጥተው ወደእኔ መጥተው ሰገዱ። ከእነሱም የቀደሙ ሰዎች ሰላምታ እንዳቀረቡልኝ ንጉሡም ከሀገር ሰዎች ሁሉ ጋር በፊቴ ሰገደ።

ከዚያም በኋላ ከእርሳቸው ጋር ወሰዱኝ ወደ ከተማውም በደረቅ ያለ መርከብ ገባን በምኵራባቸውም ውስጥ በጽጌ ረዳ አክሊል ጣዖቶቻቸው ተከልለው የሥንዴ እሸትም እንደ መስዋዕት ሆኖ ተጥሎ አየሁ ይህንንም አይቼ እጅግ አዘንኩ።

የአገር ሰዎችም ክብር መምህር ሆይ በዚች ዕለት ለአማልክት በዓል የምናደርግበት እንደ ነበረ ዕወቅ አሁን አንተ ለማን ታዝናለህ ለአብ እንድርገውን ወይም በወልድ ስም ወይም በመንፈስ ቅዱስ ስም በስማቸው ያጠመቅከን ስለሆነ አሉኝ። እኔም እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ የሚገባቸውን ሃይማኖትን አስተማርኳቸው መጻሕፍትንም በእጄ ጻፍኩላቸው።

በአማላጅነቷ ከርኵስ ሰይጣን ተገዥነት ስለዳኑ ያንን በዓል የብርሃን እናት በሆነች በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም እንዲያደርጉት አዘዝኋቸው ዕለቱም የእግዚአብሔርን ልጅ እንደምትፀንሰውና በሥጋ እንደመትወልደው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ያበሠረበት ስለሆነ።

እኔም አምላካዊ ትምርትን አስተማርኳቸው በቀናች ሃይማኖትም እንዲጸኑ አደረግኋቸው ውኃው በተከፈለበትም ላይ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም ታላቅ ቤተ ክርስቲያን እንዲሰሩ አዘዝኳቸው። በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድንቆች የሆኑ ብዙ ተአምራቶችንም አደረኩላቸው ከዚያ በኋላ ከእነርሱ ዘንድ ወጥቼ መጣሁ።

ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ቆርጠው ለውሾች እንዲጥሉት አዘዘ ውሾች ግን ፈጽሞ አልቀረቡትም ሌሊትም ሲሆን ምእመናን መጥተው ሥጋውን ወሰዱ በአዳዲሶች ልብሶችና በጣፋጭ ሽቶዎች ገነዙት በሣጥንም አድርገው ቀበሩት።ከሥጋውም ብዙዎች አስደናቂዎች ተአምራቶች ተደረጉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አጋንዮስ_አውንድርዮስና_ብንድዮስ

በዚህችም ቀን ደግም የከበሩ አጋንዮስ አውንድርዮስና ብንድዮስ በሰማዕትነት አረፉ። እሊህም ቅዱሳን ከአባቶቻቸው ጀምሮ ክርስቲያኖች ናቸው አምላካዊ ትምህርትንም ሁሉየተማሩ ናቸው።

በእግዚአብሔርም ሕግ ጸንተው ሲኖሩ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አርሞስ መርጦ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ ሾማቸው ግን በታወቁ ቦታዎች ላይ አይደለም በብዙዎች አገሮች ውስጥ እንዲሰብኩ ላካቸው እንጂ። በሀገሮችም ያሉ ከሀዲያን ያዙአቸው ያለርኀራኄም አብዝተው ገረፉአቸው በደንጊያም ወገሩአቸው ነፍሳቸውንም በጌታችን እጅ ሰጡ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
Forwarded from ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ (🕊Dawit🕊)
ምሕረትንና ርኅራኄን የተመላች እመቤቴ የብርሃን እናት ድንግል ማርያም ይህን ስትናገረኝ እነሆ በእጃቸው የጦር መሣሪያ የያዙ ኃይለኞች ሰዎችን የተሞሉ መርከቦችን በቅርብ አየኋቸው እጅግም ፈራሁ እመቤቴ ማርያምም ተሠወረችኝ። ነገር ግን ከደመና ውስጥ ጳውሎስ ሆይ ሰዎችን አጥምቅ ማጥመቅንም አታቋርጥ የሚለኝን ቃል እሰማ ነበር። እኔም በታላቅ ቃል ፈጣሪዬ ሆይ ይህን የባሕር ውኃ ለእሊህ ለተጣሉ በጎች ሰይጣንም ለማረካቸው ጥምቀትን አድርገው ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በዚህ ባህር ጥምቀት እሊህን ሰዎች በሦስትነትህ ስሞች የልጅነትን ክብር የሚቀበሉ አድርጋቸው በማለት አሰምቼ ተናገርኩ።

እንዲህም ይህን እያልኩ ከባሕሩ ውኃ ዘግኜ ሰዎች በአሉባቸው መርከቦች በላያቸው ረጨሁት የሰዎቹም ቁጥራቸው አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ነው። እኔ ወደአለሁበት የባሕር ዳር በደረሱ ጊዜ ከመርከባቸው ወጥተው ፈለጉኝ እኔም እመቤቴ የብርሃን እናት እንዳዘዘችኝ በፊታቸው ቆምኩ በረድኤቷ ተማምኛለሁና አልፈራሁም። በአዩኝም ጊዜ ሁሉም በፊቴ ሰገዱ በአንድ ቃልም ቅዱስ ጳውሎስ ሆይ ፍቅር አንድነት ለአንተ ይሁን ወደአንተ ከመድረሳችን በፊት በመርከቦች ውስጥ እያለን እኛ ያየነውን አየህን አሉኝ።

እኔም አዲስ የተወለዳችሁ ልጆች ሆይ ምን አያችሁ አልኋቸው የሰማይ ደጆች ተከፍተው የቀኝ እጅ እንደ እሳት ነበልባል ተዘርግታ አየን ደግሞ የፊቷ ብርሃን ከፀሐይ ሰባት እጅ የሚበራ ሴት አየን። እርሷም ከደመና በታች የምትረጨውን ውኃ ተቀብላ በላያችን ትረጨዋለች ትስመናለች ታቅፈናለችም። በራሲቻችንም ላይ የብርሃን አክሊሎችን ታደርጋለች አሉኝ። ይህንንም በሰማሁ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለኝ በስሙ በምንሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዳለ ተረዳሁ።

ከዚህም በኋላ ሌሎች መርከቦች መጡ ኃይለኞች ሰዎችን ከጦር መሣሪያ ጋር የተመሉ ናቸው እንዲህም እያሉ ዛቱበኝ። አንተ ሥራየኛ ጥበበኞች ሕርምስና በለንዮስ ታምራት የሚያደርጉባቸው የጠልሰም መጻሕፍቶች ከእኛ ጋራ እንዳሉ ዕወቅ በማለት እኔም ቸር ፈጣሪዬ ሆይ የቀደሙትን በጎች ይቅር እንዳልካቸውና በውስጣቸው ኃይልህን እንደገለጥክ ለእነዚህም እንዲሁ ኃይልህን ግለጥ ይቅርም በላቸው አልኩ።

ከዚያም በኋላ ከባሕሩ ውኃ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥምቀትን ይሁናችሁ አልኩ ወዲያውኑ መርከቦች ከባሕሩ ዳር ደረሱ። ሁሉም ሰዎች ከመርከብ ወጥተው በፊቴ ሰገዱ የቸር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሆይ እናመሰግንሃለን አሉኝ።

ይህንንም ድንቅ ተአምር ከቀደሙት ባልንጀሮቻቸው ጋራ ተነጋገሩ ዜናዬም በዚያች አገር ንጉሥ ዘንድ ተሰማ እርሱም ከሰራዊቱ ጋር ተነሳ በመርከቦችም ተጭነው ወደእኔ መጡ። እኔም ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አቅንቼ የፈጣሪዬን ስም ጠራሁ ባሕርዋንም በመስቀል ምልክት አማተብኩባት። እንዲህም አልኳት አንቺ ባሕር በእግዚአብሔር ልጅ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ትከፈዪ ዘንድ አዝሻለሁ ምድሩም ይገለጥ መርከቦችም በየብስ ውስጥ ይቁሙ።

ነገሬንም ሳልጨርስ ባሕርዋ ተከፈለች በውስጥዋም ዐሥራ ሦስት ጎዳናዎች ተገለጡ መርከቦቹም ውኃ በሌለው ምድር ላይ ቆሙ ይህንንም አይተው ሰይፎቻቸውን መዘዙ ዕንጨቶችም ሆነው አገኙአቸው እኔም ከሕህሩ ውኃ ዘግኜ በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እያልኩ በላያቸው ረጨሁ። በዚያን ጊዜ እሊያ መርከቦች ነፋስ ተሸክሟቸው ያለ ውኃ ከምድር ከፍ ከፍ ብለው ተጓዙ ሰዎችም ከውስጣቸው ወጥተው ወደእኔ መጥተው ሰገዱ። ከእነሱም የቀደሙ ሰዎች ሰላምታ እንዳቀረቡልኝ ንጉሡም ከሀገር ሰዎች ሁሉ ጋር በፊቴ ሰገደ።

ከዚያም በኋላ ከእርሳቸው ጋር ወሰዱኝ ወደ ከተማውም በደረቅ ያለ መርከብ ገባን በምኵራባቸውም ውስጥ በጽጌ ረዳ አክሊል ጣዖቶቻቸው ተከልለው የሥንዴ እሸትም እንደ መስዋዕት ሆኖ ተጥሎ አየሁ ይህንንም አይቼ እጅግ አዘንኩ።

የአገር ሰዎችም ክብር መምህር ሆይ በዚች ዕለት ለአማልክት በዓል የምናደርግበት እንደ ነበረ ዕወቅ አሁን አንተ ለማን ታዝናለህ ለአብ እንድርገውን ወይም በወልድ ስም ወይም በመንፈስ ቅዱስ ስም በስማቸው ያጠመቅከን ስለሆነ አሉኝ። እኔም እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ የሚገባቸውን ሃይማኖትን አስተማርኳቸው መጻሕፍትንም በእጄ ጻፍኩላቸው።

በአማላጅነቷ ከርኵስ ሰይጣን ተገዥነት ስለዳኑ ያንን በዓል የብርሃን እናት በሆነች በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም እንዲያደርጉት አዘዝኋቸው ዕለቱም የእግዚአብሔርን ልጅ እንደምትፀንሰውና በሥጋ እንደመትወልደው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ያበሠረበት ስለሆነ።

እኔም አምላካዊ ትምርትን አስተማርኳቸው በቀናች ሃይማኖትም እንዲጸኑ አደረግኋቸው ውኃው በተከፈለበትም ላይ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም ታላቅ ቤተ ክርስቲያን እንዲሰሩ አዘዝኳቸው። በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድንቆች የሆኑ ብዙ ተአምራቶችንም አደረኩላቸው ከዚያ በኋላ ከእነርሱ ዘንድ ወጥቼ መጣሁ።

ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)