ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
800 subscribers
3.46K photos
104 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
#መጋቢት_14

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ዐሥራ አራት በዚህችም ቀን #ቅዱስ_ቶማስ ሐዋርያ በአንዲት ሴት ላይ ተአምራትን አደረገ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #የቅዱስ_ቄርሎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ፣ ከአረጋውያን ፍጹማን መነኰሳት ውስጥ አንዱ #ቅዱስ_አባ_ባጥል አረፈ፣ #ቅዱስ_አባት_አባ_ሲኖዳ በሰማዕትነት አረፈ፣ የከበሩ #ቅዱሳን_አጋንዮስ_አውንድርዮስና_ብንድዮስ በሰማዕትነት አረፉ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቶማስ_ሐዋርያ

መጋቢት ዐሥራ አራት በዚህችም ቀን ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ ሰባት ዓመት ያህል የጋኔን ግንኙነት በአስቸገራት በአንዲት ሴት ላይ ተአምራትን አደረገ። ሐዋርያ ቶማስንም የችው ጊዜ የክርስቶስ ሐዋርያው ሆይ እጅግ ከሚያሠቃየኝ ጠላት አድነኝ ብላ ወደርሱ ጮኸች።

እርሱም በምን ምክንያት አገኘሽ አላት እርሷም ከመታጠቢያ ከውሽባ ቤት ስወጣ እንደ ሰው ድው ድው እያደረገ በመታወክ መጣ ድምጡም ሰላላና ቀጪን ነው በሴትና በወንድ ሥራ ሁሉ ነይ እርስበርሳችን አንድ እንሁን አለኝ በተኛሁም ጊዜ በሌሊት መጥቶ ከእኔ ጋራ አንድ ሆነ ብሸሽም አይተወኝም መጥቶ ያሠቃየኛል እንጂ እኔም ከጸሎትህ የተነሣ አጋንንት እንደሚንቀጠቀጡ አውቃለሁና ጸልይልኝ አድነኝም አለችው።

ሐዋርያ ቶማስም ሰምቶ ጸለየ ጋኔኑንም ከእርሷ እንዲወጣ አዘዘው ያንጊዜም በእሳትና በጢስ አምሳል ከሴቲቱ ላይ ወጥቶ ተበተነ ከዚህ በኃላ በክርስቶስ መስቀል በላይዋ አማተበ ሥጋውንና ደሙንም አቀበላት ወደ ዘመዶቿም አሰናበታት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#የቅዱስ_ቄርሎስ

በዚህች ቀን በእስክንድርያ ለተሾሙ አባቶች ሰባ አምስተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የቅዱስ ቄርሎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። እርሱም በምግባሩ ፍጹም ዐዋቂ ሆነ ሀገሩም ፍዩም ይባላል በእርሷም ቅስና ተሹሞባት ነበር።

ከዚያም ለቆ ወደ አባ ፊቅጦር ገዳም ደረሰ እርሱም ከምስር ከተማ ውጭ የኢትዮጵያውያን ዐዘቅት የዐባይ ግድብ በአለበት ነው። በዚያም ታላቅ ገድልን እየተጋደለ ብዙ ዘመናትን ኖረ። ብዙ መጻሕፍትንም ተምሮ ትርጓሜያቸውንና ምሥጢራቸውን ጠንቅቆ ዐወቀ።

አሸናፊ ወደሚባለውም ንጉሥ አደባባይ ቀርቦ የእስላሞች ታላላቅ ሊቃውንቶቻቸውና ከምሁራኖቻቸው ውስጥ መምህሮቻቸው ተከራከሩት። ጠቃሚ የሆነ ዕውቀት የተመላበትን መልስ አገኙ የሚጠይቁትንም ሁሉ በመልካም አመላለስ ነገራቸው።

ከዚህ በኃላ የዕውቀቱና የቅድስናው ዜና በተሰማ ጊዜ ያለ ፈቃዱ ይዘው በእስክንድርያ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት መንጋውንም ጠበቀ በጸሎትና በቅዳሴ ያገለግሉ ዘንድ ለካህናት ሥርዓትንና መመሪያን ሠራ። ይህም አባት በሊቀ ጵጵስናው ሰባት ዓመታት ከዘጠኝ ወር ከዐሥር ቀኖች ኖረ። ከቀኑም በሦስት ሰዓት አረፈ በምስክርነት አደባባይም ተቀበረ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ባጥል

በዚህችም ዕለት ከአረጋውያን ፍጹማን መነኰሳት ውስጥ አንዱ አባ ባጥል አረፈ። ይህም ቅዱስ ሰው አባ ዮሐኒ የተባለ አበምኔት በመነኰሳት ላይ ነገረ ሠሪን እንደ ሚቀበል በሰማ ጊዜ በዓቱን ትቶ ወደ እስክንድርያ መጥቶ የሴት አዳሪዎችንና የአመንዝራዎችን ሁሉ ስማቸውን ጻፈ።

ከኪራይ ሠራተኞችም ጋራ ሲሠራ ይውላል። ደመወዙን በተቀበለ ጊዜ የሽንብራ ቂጣ ግዝቶ ይበላል የቀረውንም ገንዘብ ይዞ ወደ አንዲቱ ሒዶ ይሰጣታል በዚች ቀን ከአንቺ ጋራ አድራለሁና ራስሽን ለእኔ አዘጋጂ ይላታል። ከኃጢአትም ሊጠብቃት ከእርስዋ ዘንድ ያድራል ሌሊቱን ሁሉ ተነሥቶ ሲጸልይና ሲሰግድ እግዚአብሔርንም ሲለምን ያድራል ሲነጋም ሥራውን ለማንም እንዳትገልጥ አምሏት ወደ ተግባሩ ይሔዳል።

በየዕለቱም ወደ አመንዝራዎቹ እየሔደ እንዲህ ያደርግ ነበር አንዲቱም ሴት ምሥጢሩን ገለጠች ጋኔንም ይዞ አሳበዳት። ሰዎችም ስለዚህ ክፉ ሽማግሌ ክፉ ሥራ የለበትም ብላ ዋሽታለችና እግዚአብሔር መልካም አደረገባት ተባባሉ። እርሷም እንዳናመነዝር ገንዘብ በመስጠት ከኃጢአት ይጠብቀናል እንጂ ነውር የለበትም ብላ ነበርና።

የቀሩት አመንዝራዎች በእርሷ ላይ የሆነውን በአዩ ጊዜ ደነገጡ እንደርሷም እንዳያብዱ እውነቷን ነው ማለትን ፈሩ። እርሱም ይችስ በእገሌ ዕለት ትጠብቀኛለች ይል ጀመረ ሰዎችም ሁሉ ያሙት ጀመር እርሱም እንደ ሰው ሁሉ ሥጋ የለኝምን ወይስ እግዚአብሔር መነኰሳትን ተቆጥቶ በፍትወት ተቃጥለው እንዲሞቱ ትቷቸዋልን አላቸው።

እነርሱም ልብስህን ለውጠህ ሚስት አግባ ይህ ይሻልሃልና አሉት። እርሱም አዎን ብወድ በሚስቴ እጠነቀቃለሁ በዚህም በክፉ አኗኗር እኖራለሁ እናንተ ግን ከእኔ ዘንድ ሒዱ ምን ትሻላችሁ በእኔ ላይ እግዚአብሔር ፈራጆች አድርጓችኃልን ይልቁንስ እናንተ እንዳይፈረድባችሁ ለራሳችሁ አስቡ ፈራጅ አንድ ነውና ዕለቲቱም አንዲት ናትና አላቸው ይህም ቅዱስ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አገኘ በሰው ዘንድ ግን የተናቀ ሁኖ ኖረ።

ከእርሱ ጥቅም የአገኙ አመንዝራዎችም ዝሙታቸውን ተው። ከእርሳቸውም ሕራዊ ጋብቻ ተጋብቶ የኖረ አለ ወደ ገዳምም ገብቶ መንኵሶ በጾም በጸሎት ተወስኖ የኖረ አለ። በአንዲት ዕለትም ከአንዲት አመንዝራ ቤት ሲወጣ ያቺን ሴት አስቀድሞ የለመዳት አንድ ሰው አገኘውና ይህ ሽማግሌ እስከ መቼ ድረስ በዚህ በክፉ ሥራ ይኖራል ብሎ ፊቱን በጥፊመታው።

ከዚህም በኃላ በአንዲት ቀን በበዓቱ ውስጥ ሰግዶ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጥቶ በቤቱም መድረክ የዚች አገር ሰዎች ጊዜው ሳይደርስ በማንም ላይ አትፍረዱ እንዳይፈረድባችሁ የሚልም ጽሑፍ ተጽፎ ተገኘ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_አባ_ሲኖዳ

በዚህችም ቀን ደግሞ ቅዱስ አባት አባ ሲኖዳ በሰማዕትነት አረፈ። እርሱም በግብጽ አገር ከብሕንሳ ከተማ ነው ወደ መክስምያኖስም ክርስቲያናዊ ሲኖዳ አማልክትን የማያመልክ ነው ብለው ነገር ሠሩበት። እርሱም አስቀርቦ ስለ ሃይማኖቱ ጠየቀው በንጉሡም ፊት በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ እርሱም ዕውነተኛ አምላክ እንደ ሆነም መሰከረ፡፡ መክስምያኖስም ይህን የከበረ አባ ሲኖዳን በምድር ላይ ዘርግተው በበትሮች እንዲደበድቡት አዘዘ። ዐጥንቶቹ እስቲሠነጠቁ ደሙም በምድር ላይ እንደ ውኃ እስቲፈስ እንዲሁ አደረጉበት።

ከዚህም በኃላ እግሩን ይዘው ጎትተው ወስደው ሽታው በሚከረፋ በጨለማ ወህኒ ቤት ጣሉት የእግዚአብሔርም መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ተገለጠለት። ቊስሎቹንም አድኖ ጤነኛ አደረገው አበረታውም በርታ አትፍራ ስለ መከራህም የክብር አክሊል ተዘጋጅቶልሃልና ደግሞም በጽኑዕ ሥቃይ ትሠቃይ ዘንድ አለህ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ እኔም ከአንተ ጋራ እኖራለሁ አለው ከዚያም ከእርሱ ተሠወረ።

በነጋ ጊዜም የነገሥታትን ትእዛዝ የሚተላለፍ ያንን ዐመፀኛ ሒዳችሁ እዩት ሙቶም ከሆነ ለውሾች ጣሉት ብሎ መክስምያኖስ ወታደሮቹን አዘዘ። ወደርሱም በደረሱ ጊዜ ቁሞ ሲጸልይ አግኝተውት ያለምንም ጥፋት ጤነኛ እንደሆነና በሥጋውም ውስጥ የሕማም ምልክት እንደሌለ እርሱም ከቶ ምንም ሥቃይ እንዳላገኘው እንደ ጤነኛና ደስ እንዳለው ሰው ተግቶ እንደሚጸልይ ስለርሱ ለንጉሡ ነገሩት።

ንጉሡም ወደርሱ አስመጣው ከሕይወቱም የተነሣ አደነቀ ልብሶቹንም አስወልቆ ያለጉዳት ጤነኛ እንደሆነ ሥጋውን አየ ደንግጦም ይህ ያየሁት ሥራይ ታላቅ ነው አለ። ከዚያም ዘቅዝቀው ሰቅለው ከበታቹ እሳትን እንዲአነዱ አዘዘ ይህንንም አደረጉበት ደግሞ በመንኰራኩር አሠቃዩት በአለንጋዎችም አብዝተው ገረፉት ደበደቡትም።
††† እንኳን ለቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ
ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††
#ቅዱስ_ኤስድሮስ †††

††† ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው:: ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ: ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል:: ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው::

ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል:: የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው::
"አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም:: ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት::" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው::

እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ!

በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ:: ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም::

እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ:: የሚረግሟችሁን መርቁ:: ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ::" ብሎናልና:: (ማቴ. 5:44) ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል::

በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል:: የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና::

ቤተ ክርስቲያናችን ኢትዮዽያዊውን የጐንደር ዘመን ሊቅ ጨምሮ በዚህ ስም የምትዘክራቸው አያሌ ቅዱሳንና ሊቃውንት አሏት::

ዛሬ የምናከብረው ሰማዕቱ ቅዱስ ኤስድሮስ በዘመነ ሰማዕታት የነበረ: ቅዱስ ፃና የሚባል ደግ ጉዋደኛ የነበረው: ሁለቱንም እናቶቻቸው እንደሚገባ ያሳደጉዋቸው የ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያኖች ነበሩ::

በወጣትነት ዘመናቸው በድንግልና: ቅዱስ ፃና የሠራዊት አለቃ: ቅዱስ ኤስድሮስ ደግሞ የልብስ ዝግጅት ባለሙያ ነበሩ:: ከሚያገኙት ገቢ ለዕለት ጉርስ ብቻ እያስቀሩ ለነዳያን ይመጸውቱ ነበር::
በመከራ ዘመን (ዘመነ-ሰማዕታት) ቅዱሳኑ ያላቸውን ሁሉ ለነዳያን አካፍለው በክርስቶስ ስም መሞትን መርጠዋል::

በዚህች ቀንም አስቀድሞ ቅዱስ ኤስድሮስ አንገቱን ተሰይፎ የክብርን አክሊል ተቀዳጅቷል::

††† ፈጣሪ ከሰማዕቱ ክብር ያድለን::

††† መጋቢት 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


1.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት

††† ወርሐዊ በዓላት

1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ

††† "የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ:: ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ: ፀሐይ: ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ . . . አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ: ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ::
ሰባኪው:- "ከንቱ: ከንቱ: ሁሉ ከንቱ ነው" ይላል::"  †††
(መክ. 1፥1-9)

††† "ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል:: እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ:: ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ:: ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ::"  †††
(1ዼጥ. 4፥7)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለቅዱሳኑ የአስከናፍር ቤተሰብ ዓመታዊ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ
ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††
#ቅዱስ_አስከናፍር †††

††† ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት አስከናፍር የሚባል ደግ ክርስቲያን ማርታ የምትባል በሃይማኖትና ምግባር የምትመስለውን ሴት አግብቶ ይኖር ነበር:: እንደ ሕጉና ሥርዓቱ በሥጋ ወደሙ ተወሥነው እንግዳ ቢቀበሉ: ነዳያንን ቢያበሉ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ አርቃድዮስና ዮሐንስ የሚባሉ ልጆችን ሰጣቸው::

አስከናፍርና ማርታ ልጆቻቸውን ጥበብ መንፈሳዊን (ቃለ እግዚአብሔርን) አስቀድመው አስተምረው : ሥጋዊ ጥበብን እንዲማሩላቸው ቢልኩዋቸው መንገድ ላይ መርከብ ተሰብሮባቸው ብዙዎቹ ሲሞቱ ወንድማማቾች ግን የመርከብ ስባሪ ወደተለያየ ቦታ አድርሷቸዋል::

አርቃድዮስና ዮሐንስ "ወደ ዓለም አንመለስም" ብለው መነኑ:: ወላጆቻቸው የሆነውን ሰምተው በጭንቅ ሃዘንና ለቅሶ ለብዙ ጊዜ ኑረዋል:: ከዘመናት በሁዋላ ግን የልጆቻቸውን መኖር በራዕይ የተረዱት አስከናፍርና ማርታ ሃብት ንብረታቸውን ለነዳያን አካፍለው ወደ በርሃ መንነው ሔደዋል::

ጥበበኛ እግዚአብሔር አራቱንም አገናኝቷቸው ለብዙ ዓመታት በአንድ ገዳም ውስጥ ተጋድለዋል::
በዚሕች ዕለትም አራቱም ወደ ሰማያዊው ሠርግ ተጠርተዋል::

††† ቸር አምላክ ከቅዱሱ ቤተሰብ በረከት ይክፈለን::

††† መጋቢት 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


1.ቅዱስ አስከናፍር : ሚስቱ ማርታ : ልጆቹ አርቃድዮስና ዮሐንስ
2.ቅዱስ አርስጥቦሎስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት-የቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዝሙር)
3.ሰባቱ ቅዱሳን ሰማዕታት (ከተለያየ ቦታ ተሰብስበው በክርስቶስ ስም የሞቱ)

††† ወርሐዊ በዓላት

1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

††† "እንግዲህ ወንዶች በሥፍራ ሁሉ አለ ቁጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ:: እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ:: እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ: ወይም በዕንቁ: ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ::" †††
(1ጢሞ. 2፥8)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from 🕊ኢዮአታም🕊
#ቅዱስ_አርስጥቦሎስ_ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት-የቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዝሙር)
#አትርሳ!

አንድ ሰው ወደ ቤተ መንግሥት አንዲት ሴተኛ አዳሪን ይዞ መጥቶ በንጉሡ ፊትም ሩካቤ ቢፈጽም፣ ወይም ቢሰክር፣ ወይም ይህን የመሰለ ሌላ ተግባር ቢፈጽም የቅጣት ቅጣት ይደርስበታል፡፡

አሁን ራሳችንን ጥያቄ እንጠይቅ፡፡ እግዚአብሔር የሰማይም የምድርም ንጉሥ ነው ወይስ አይደለም? ነው! የምናደርገውን ማንኛውም ድርጊት ይመለከታል ወይስ አይመለከትም? ኧረ ይመለከታል!
ታዲያ በምድራዊ ንጉሥ ፊት ከላይ የጠቀስናቸውን ነውሮች ደፍሮ የፈጸመ ሰው ጽኑ ቅጣት የሚቀጣ ከኾነ እንደዚህ ያሉ ተግባራትን በእግዚአብሔር ፊት ለማከናወን የምንደፍረው ለምንድን ነው? ምድራዊው ንጉሥ ቢቀጣ ምድራዊ ቅጣትን ነው፡፡ ሰማያዊው ንጉሥ ሲቀጣ ግን ሰማያዊ ቅጣት እንደ ኾነ አናውቅምን? ...

ሰው ሆይ! እያንዳንዷን ድርጊትህ የሚመለከት የሰማይም የምድርም ንጉሥ እንዳለ በፍጹም አትርሳ፡፡

(#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ- አምስቱ የንስሐ መንገዶች እና ሌሎች - ገጽ 119)
† እንኳን ለታላቁ ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ዳንኤል ዓመታዊ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ
ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††
#ቅዱስ_ዳንኤል †††

††† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ጴጥ. 1:10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

††† ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት: አራቱ ዐበይት ነቢያት: አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ::

††† "አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት" ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ
*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ
*አብርሃም
*ይስሐቅ
*ያዕቆብ
*ሙሴና
*ሳሙኤል ናቸው::

††† "አራቱ ዐበይት ነቢያት"
*ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
*ቅዱስ ኤርምያስ
*ቅዱስ ሕዝቅኤልና
*ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

††† "አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት"
*ቅዱስ ሆሴዕ
*አሞጽ
*ሚክያስ
*ዮናስ
*ናሆም
*አብድዩ
*ሶፎንያስ
*ሐጌ
*ኢዩኤል
*ዕንባቆም
*ዘካርያስና
*ሚልክያስ ናቸው::

††† "ካልአን ነቢያት" ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስና
*ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው::

††† ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል)ና
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::

††† በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት):
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::
ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳንኤል ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ600 ዓመታት አካባቢ ከይሁዳ ነገሥታት ዘር ተወለደ:: ገና በሕፃንነቱ ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ : ሕዝቡን ማርኮ ወደ ባቢሎን ሲያወርዳቸው አብሮ ወርዷል::

ከሕፃንነቱ ጀምሮ በአምላኩ ፍቅር የታሠረ : ከሦስቱ ጓደኞቹ (አናንያ : አዛርያና ሚሳኤል) ጋር ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር:: በዘመኑ እንደርሱ ያለ መተርጉመ-ሕልም አልተገኘምና ለወገኖቹ ሞገሳቸው ነበር::

ኃይለኛውን ንጉሥ ናቡከደነጾርን ጨምሮ የባቢሎንና ፋርስ ነገሥታት ያከብሩት : ይወዱትም ነበር::

ቅዱስ ዳንኤል በጥበብና በሃይማኖት የአሕዛብን አማልክት ድል ነስቷል:: አሕዛብ በተንኮል ወደ አናብስት ጉድጓድ ውስጥ ቢያስጥሉት እግዚአብሔር የአናብስቱን አፍ ዘግቷል:: ዕንባቆምንም አምጥቶ መግቦታል::

ቅዱስ ዳንኤል የብሉይ ኪዳኑ "አቡቀለምሲስ" ይባላል:: ስለ ጌታችን የማዳን ሥራና ስለ ዳግም ምጽዐቱ በግልጥ ተናግሯል:: ሐረገ ትንቢቱም 12 ምዕራፍ ነው:: የዘመኑ አይሁድ ክርስቶስ ገና አልተወለደም ለማለት ዳንኤልን ጠልተውታል::

ታላቁ ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ዳንኤል እስራኤል ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ አብሯቸው አልመጣም:: ከ70 ዓመታት በላይ በጸጋ ትንቢት ኑሮ እዛው ባቢሎን ውስጥ አርፏል::

††† ፈጣሪ ከበረከቱ ለሁላችን ያድለን::

††† በዚህች ቀን ክፉዎች አይሁድ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይገድሉ ዘንድ በቤተ ቀያፋ መከሩ::

††† እርሱ ቸሩ አምላክ ከክፉ መካሪዎች ይሠውረን::

††† መጋቢት 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


1.ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳንኤል (የስሙ ትርጓሜ- እግዚአብሔር ፈራጅ ነው ማለት ነው::)

††† ወርኀዊ በዓላት

1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.አባ ሳሙኤል
6.አባ ስምዖን
7.አባ ገብርኤል

††† "የዚያን ጊዜም ንጉሡ አዘዘ:: ዳንኤልንም አምጥተው በአንበሶች ጉድጓድ ጣሉት . . . ድንጋይም አምጥተው በጉድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙት . . . በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሳ . . . ወደ ዳንኤል በቀረበ ጊዜ በኀዘን ቃል ጠራው . . . ዳንኤልም ንጉሡን . . . በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና . . . አምላኬ መልዐኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ:: አንዳችም አልጐዱኝም አለው . . . ዳንኤልም ከጉድጓድ ወጣ:: በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም::" ††† (ዳን. ፮፥፲፮-፳፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from 🕊ኢዮአታም🕊
የምታዩት ቦታ #ሱሳ (Susa) የሚባል ሲሆን የታላቁ ነቢይ #ቅዱስ_ዳንኤል መቃብር እንደ ሆነ ይታመናል:: የሚገኘው ደግሞ #ኢራን (Iran) ውስጥ ነው:: የነቢዩ ዕረፍት ምሥጢር ነው::

<< ምናልባት ግን ሊቁ በመልክአ ኢየሱስ "ለኩርናዕከ" ላይ:-
"ኢየሱስ ክርስቶስ ሞገሰ ዳንኤል ነቢየ ሱሳ" (የሱሳ ነቢይ የዳንኤል ሞገሱ አንተ ኢየሱስ ክርስቶስ ነህ) ያለው ይህንን ሊነግረን ይሆን? >>

<< መድኃኒታችን ከታላቁ ነቢይ በረከቱን ያሳትፈን !! >>
††† እንኳን ለዘመነ ሐጋይ (በጋ) የመጨረሻ ዕለትና ለሐዋርያው ቅዱስ አንሲፎሮስ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ
ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አምላካችን እግዚአብሔር ሁሉን ስነ ፍጥረት የፈጠረ ለሰው ልጆች ጥቅም ነው:: ጌታ አዝማናትን : ወሮችን : ሳምንታትን : ቀኖችንና ሰዓታትን ፈጥሮ : ወስኖ ሰጥቶናል:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት እንደ መሆኗ ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ይፈፀማል::

በራሷ የዘመን ቀመር ስሌት መሠረትም አንድ ዓመት በአራት ወቅቶች ይከፈላል:: አባታችን ሊቁ ቅዱስ ያሬድም እነዚህን ወቅቶች መሠረት አድርጎ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::

እነዚሕ አዝማናት (ወቅቶች):-
1.ዘመነ ክረምት (ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25)
2.ዘመነ መፀው (ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25)
3.ዘመነ ሐጋይ (ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25)
4.ዘመነ ፀደይ (ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25) መሆናቸው ይታወቃል::

ዘመነ ሐጋይ (በጋን) የባረከ አምላክ ዘመነ ፀደይ (መከርን) እንዲባርክልን : የንስሐ ጊዜም እንዲያደርግልን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን::

††† #ቅዱስ_አንሲፎሮስ †††

††† በዚህች ዕለት ጌታችንን በሃገረ ናይን የተከተለ : ከዋለበት ውሎ : ካደረበት ያደረ : ከሰባ ሁለቱ አርድእት የተቆጠረ ሐዋርያው ቅዱስ አንሲፎሮስ አርፏል::

††† ዳግመኛ በዚህ ዕለት አይሁድ ለመጨረሻ ጊዜ ጌታችንን ሊገድሉት ተስማሙ:: ይሁዳም በ30 ብር ይሸጠው ዘንድ ከአይሁድ ጋር ተዋዋለ::

††† የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታውና ምሕረቱ ከሁላችን ጋር ይሁን::

††† መጋቢት 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


1.ቅዱስ አንሲፎሮስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)

††† ወርኀዊ በዓላት

1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

††† "ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ: ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዘመናትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን:: እርሱም . . . ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ::" †††
(ዕብ. ፩፥፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለታላቁ ክርስቲያናዊ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ
ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††
#ቅዱስ_ቆስጠንጢኖስ †††

††† ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ለቤተ ክርስቲያን የፈፀመውን መልካም ተግባር ያሕል መሥራት የቻለ ንጉሥ በሐዲስ ኪዳን የለም:: ጻድቁ ንጉሥ ከቅድስት እናቱ እሌኒና ከአረማዊ አባቱ ቁንስጣ በበራንጥያ ተወለደ::

ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የመከራ ጊዜ) ወይም የሰማዕታት ዘመን በመሆኑ ክርስቲያኖች በግፍ የሚጨፈጨፉበት ወቅት ነበር:: ክርስቲያኖችን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት በተደረገው የ40 ዓመታት ዘመቻ አብያተ መቃድስና መጻሕፍት ተቃጠሉ:: ብዙዎቹ በየበርሃው ተሰደዱ:: ሚሊየኖች በግፍ አለቁ::

የዚሕን ዘመን መከራ በውል ያልተረዳ ሰው ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ሊያከብር አይችልም:: ምክንያቱም ይህን የመከራ ዘመን በፈቃደ እግዚአብሔር አስቁሞ : ቀርነ ሃይማኖት የቆመው : ብዙ ሥርዓት የተሠራው : ቤተ ክርስቲያንም ያበራችው በዘመኑ ነውና::

ቅዱሱ ንጉሥ ለሁሉም ነቢያት : ሐዋርያትና ሰማዕታት አብያተ ክርስቲያናትን ራሱ በመሠረታት በቁስጥንጥንያ አንጿል:: በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን በሰላም ኖራለት : በኃይለ መስቀሉ ጠላት ጠፍቶለት ኑሮ በዚህች ቀን አርፏል:: "ቆስጠንጢኖስ" ማለት "ሐመልማል" ማለት ነው::

††† ዳግመኛ በዚሕ ቀን የዓለማት ፈጣሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በሆነው ሞቱ በመቃብር ውስጥ አድሯል::

††† ጌትነት ያለው አምላካችን በይቅርታው ይጐብኘን:: መልካም መሪንም ይስጠን::

††† መጋቢት 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ (ጻድቅ ንጉሥ)
2.ቅድስት እሌኒ ንግስት

††† ወርኀዊ በዓላት

1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)

††† "እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ: ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር: ልመናና ጸሎት: ምልጃም: ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ: ስለ ነገሥታትና መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ:: ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው::" †††
(፩ጢሞ. ፪፥፩-፬)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ከተባረከ ወር ሚያዝያ እና ከሰማዕቱ አባታችን ቅዱስ ክርስቶፎሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††
#ቅዱስ_ክርስቶፎሮስ †††

††† ክርስቶፎሮስ ትርጉሙ "ለባሴ ክርስቶስ" እንደ መሆኑ በሐዋርያት ዘመን የነበሩ ብዙ ቅዱሳን በዚህ ስም ይጠሩ ነበር:: ከነዚህ አንዱ ቅዱስ ክርስቶፎሮስ ሃገሩ በላዕተ ሰብእ (ሰውን የሚበሉ) ውስጥ ነበር::

ይህች ሃገር አሁን የት እንዳለች በውል ባይታወቅም የቅዱስ ማትያስ ሃገረ ስብከት በመሆኗ አውሮፓና እስያ ድንበር አካባቢ እንደሆነች ይገመታል::

የአካባቢው ሰዎች ከሰው ሥጋ ውጪ እህልን አይቀምሱም ነበር:: ቅዱስ ማትያስ በነርሱ ያደረውን ርኩስ መንፈስ አስወጥቶ አሳምኗቸዋል::

ከሃገሩ ሰዎችም አንዳንዱ ገጻተ ከለባት (የውሻ መልክ ያላቸው) ነበሩ:: ክርስቶፎሮስም ከነርሱ አንዱ ነበር:: በክርስቶስ አምኖ ከተጠመቀ በሁዋላ በስብከቱ ብዙዎችን አሳምኖ : ስለ ሃይማኖትም ብዙ ጸዋትወ መከራ ተቀብሎ በዚህች ቀን በሰማዕትነት አርፏል::

††† ከሰማዕቱ በረከት አምላኩ ያድለን::

††† ሚያዝያ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


1.ቅዱስ ክርስቶፎሮስ (ሐዋርያና ሰማዕት)
2.አባ ስምዖን ዘሃገረ ሐሊባ
3.ቅዱስ መላልኤል (የያሬድ አባት - ከአዳም 5ኛ ትውልድ)
4.እግዚአብሔር ፀሐይን : ጨረቃን : ከዋክብትን ፈጠረ

††† ወርኀዊ በዓላት

1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
4.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
5.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
6.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
7.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

††† "ስለዚሕ ወንድሞቼ ሆይ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ:: ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ:: በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ:: የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? . . . እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን:: ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና::" †††
(1ቆሮ. 10፥14-18)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
#ሚያዝያ_2

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ ሁለት በዚህችም ቀን የቃይናን ልጅ #የቅዱስ_መላልኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ ፊቱ እንደ ውሻ የሆነ #ቅዱስ_ክርስቶፎሮስ በሰማዕትነት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መላልኤል

ሚያዝያ ሁለት በዚህችም ቀን የቃይናን ልጅ የመላልኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ መላልኤልም መቶ ስልሳ አምስት ዓመት ኖረ ያሬድንም ወለደው።

መላልኤልም ያሬድን ከወለደው በኃላ ሰባት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። የመላልኤልም መላ ዘመኑ ሁሉ ስምንት መቶ ዘጠና አምስት ዓመት ነው። ቅዱስ መላልኤልም ሚያዝያ ሁለት ቀን በእሑድ ዕለት ሞተ በማከማቻም ውስጥ ቀበሩት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ክርስቶፎሮስ (ሐዋርያና ሰማዕት)

በዚችም ቀን ፊቱ እንደ ውሻ የሆነ ቅዱስ ክርስትፎሮስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ ሰውን ይበሉ ከነበሩ ሰዎች ሀገር ነው በጦርነትም ማረኩት አባቱም በሐዋርያ ማትያስ እጅ ያመነ ነው። በማረኩትም ጊዜ ቋንቋቸውን አያውቅም ነበር የክብር ባለቤት ወደሆነ እግዚአብሔርም ማለደ ቋንቋቸውንም ገልጦለት እንደርሳቸው ተነሰገረ የክርስቲያን ወገኖችን የሚያሠቃዩአቸውንም ገሠጻቸው የጦር ሠራዊቱንም የሚመራ መኰንን ጽንዕ ግርፋትን ገረፈው። ቅዱስ ክርትፎሮስም መኰንኑን የጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዙ ኃይሌን ባትይዘኝና ባታስታግሠኝ አንተና ሠራዊትህ ከእኔ እጅ ባልዳናችሁ ነበር አለው።

መኰንኑም ስለ ርሱ ወደ ንጉሥ ላከ ከእርሱ የሆነውንም ነገረው። ንጉሡም ወደ ርሱ እንዲያመጡት ሁለት መቶ ወታደሮችን ላከለት እርሱም ያለ መፍራት ያለ ማፈግፈግ አብሮአቸው ሔደ። በእጁ በትር ነበረች በላይዋ በጸለየ ጊዜ በቀለችና አበበች። እነዚያ ወታደሮች ተርበው የሚበሉት እንጀራ በአጡ ጊዜ ቅዱስ ክርስትፎሮስ ጸለየ በእነርሱ ዘንድ እንጀራ በዝቶ ተትረፈረፈ እጅግም አድንቀው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። አባ ጳውሎስ እጅ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቁ።

ወደ ንጉሡም ፊት በደረሱ ጊዜ ንጉስ ዳኬዎስ ሊያስፈራውና ሊሸነግለው ጀመረ ደግሞ እጅግ መልከ መልካም የሆኑ ሁለት አመንዝራ ሴቶችን ወደርሱ ሰደደ እነርሳቸው እንደሚያስቱትና በኀጢአት እንደሚጥሉት አስቧልና። እርሱ ግን ገሠጻቸው አስተማራቸውም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በደማቸው ምስክር ሁኑ። እንዲሁም እነዚያ ሁለት መቶ ወታደሮች በንጉሡ ፊት በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ራሶቻቸውንም በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነትንም በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

ቅዱስ ክርስትፎሮስም ንጉሡን አንተ የሰይጣንን ሥራ የምትቀበል ማደሪያው የሆንክ ብሎ ዘለፈው ንጉሡም ተቆጥቶ በትልቅ ብረት ምጣድ ውስጥ እንዲጨምሩትና ከበታቹ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ። እንዲሁም አደረጉበት ነገር ግን ከጉዳት እንዳሰቡት ምንም የደረሰበት የለም። ጤነኛ ሆኖ ሰዎችን አስተማራቸው እንጂ። እጅግም አድንቀው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። ቅድሱንም ከእርሷ ሊአወጡት ወደዚያች ብረት ምጣድ ቀረቡ ንጉሡም አንገቶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘ የሕይወት አክሊልንም ተቀበሉ። ከዚያም በኃላ ታላቅ ደንጊያ በአንገቱ አንጠልጥለው ከጥልቅ ጉደረጓድ እንዲጨምሩት ንጉሡ አዘዘ በጨመሩትም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በጤንነት አወጣው። ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ አንገቱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ ንጉሡ አዘዘ። ቅዱሱም በእግዚአብሔር መንግስት የድል አድራጊነትን አክሊል ተቀዳጀ፡፡

ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ)
#ሰሙነ_ሕማማት

ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ሰሙነ ሕማማት የጾመ ሁዳዴ የመጨረሻው ሳምንት፤ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም የሚታሰብበት፤ ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ የሚያዜሙበት፤ ግብረ ሕማማት በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍ የሚያነቡበትና የሚሰሙበት፤ በነግህ፣ በሠልስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት /ዘጠኝ /ሰዓት፣ በሰርክ /በዐስራ አንድ/ ሰዓት እየመላለሱ የሚሰግዱበትና የሚጸለዩበት ልዩ ሳምንት ነው ከሆሳዕና ማግስት እስከ ትንሣኤ ።

በዚህ ሳምንት በተለይ ካህናት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራና ስቃይ እንዲሁም የሰው ልጅ ፭ ሺ ፭ መቶ ዘመን በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከርም ጭምር ነው። የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራና ሕማም በጽኑ እንድናስበው ያስተማሩን ሐዋርያት ናቸው። ለእነርሱም የነገራቸው ደግሞ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ሰሙነ ሕማማት የጌታችንን ሕማማት ከማሰብ ጋር በየዕለቱ በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የምናስታውስበት ሳምንት ነው፦

#ሰኞ
#መርገመ_በለስ_የተፈጸመበት_ሰኞ_ይባላል
በዚህ ዕለት ጌታችን ከቢታኒያ ሲወጣ ተራበ ቅጠል ያለባትን በለስ ተመልክቶ ወደ በለሲቱ ቢቀርብ ከቅጠል በቀር ምንም ነገር ባለማግኘቱ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ምንም ካንቺ ፍሬ አይበላ” ማር ፲፩፥፲፬ በማለት ስለረገማት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል።

#አንጽሖተ_ቤተ_መቅደስ_ይባላል፡-
ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሄዶ በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እና የሚለውጡትን “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” ማቴ ፳፩፥፲፫ በማለት ከቤተመቅደስ ገርፎ አስወጥቷቸዋልና።

#ማክሰኞ
#የጥያቄ_ቀን_ይባላል
ሰኞ ዕለት በቤተመቅደስ ሲሸጡ እና ሲለውጡ የነበሩትን ሁሉ እየገረፈ በማባረሩ ምክንያት ለሰው ልጅ ሹመትንና ስልጣንን የሰጠ ጌታ “በምን ስልጣን ይህንን ታደርጋለህ?” ማቴ ፳፩፥ ፳፫ ተብሎ በፈሪሳውያን ተጠይቋልና የጥያቄ ቀን ይባላል።

#የትምህርት_ቀን_ይባላል፡-
በዚህ ዕለት በቤተመቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረም የትምህርት ቀን ይባላል። ሉቃ ፳፩ ፥፳፰ ፣ ማር ፲፪፥፪።

#ረቡዕ
#ምክረ_አይሁድ_ይባላል
ረቡዕ እለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል። ወቅቱ የፋሲካን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በመሆኑ እና ብዙ ህዝብም ጌታን ይከተለው ስለነበር ሁከት እንዳይነሳ ስጋት ነበራቸው ። ነገር ግን ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ስለነገራቸው ሉቃ ፳፪፥፩-፮ ጭንቀታቸው ተወግዶ በጌታ መያዝ ተስማምተዋል።

#የመልካም_መዓዛ_ቀንም_ይባላል፡-
ጌታችን በዚህ ዕለት በለምጻሙ በስምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት/ባለሽቶዋ ማርያም/ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ የአልባጥሮስ ሽቱ አምጥታ በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው ማቴ ፳፮፥፮-፯ የመዓዛ ቀን ይባላል።

#የእንባ_ቀን_ይባላል፡-
ባለሽቱዋ ሴት (ማርያም እንተ እፍረት) ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት እየለመነች በእግሩ ስር ተደፍታ በእንባዋ እግሩን አርሳለችና ማር ፲፬፥፱ የእንባ ቀን ይባላል።

#ሐሙስ
#ጸሎተ_ሐሙስ_ይባላል
ጌታችን ለአይሁድ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲጸልይ በማደሩ ማቴ ፳፮፥፴፮ ጸሎተ ሐሙስ ይባላል።ጌታችን የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ ያጠበበት ዕለት በመሆኑም ዮሐ ፲፫፥፫-፲፩ ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል።

#የምስጢር_ቀን_ይባላል፡-
ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ የቅዱስ ቁርባን ምስጢር ማቴ፳፮፥፳፮-፳፱ በዚህ ዕለት ተፈጽሟልና የምስጢር ቀን ይባላል።

#የሐዲስ_ኪዳን_ሐሙስ_ይባላል፡-
መሥዋዕተ ኦሪት /በእንስሳት ደም የሚቀርብ መሥዋዕት/ቀርቶ ለአለም ድኅነት ራሱን ያቀረበበት ቀን በመሆኑ ሉቃ ፳፪፥፳ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል።

#የነጻነት_ሐሙስ_ይባላል፡-
ለኃጢአትና ለዲያቢሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱን እንዲሁም የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነም ዮሐ ፲፭፥ ፲፭ የነጻነት ሐሙስ ይባላል።

#ዓርብ
#የስቅለት_ዓርብ_ይባላል
ጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለበት ዕለት ነውና ማቴ ፳፯፥፴፭ የስቅለት ዓርብ ይባላል።

#መልካሙ_ዓርብ_ይባላል፡-
ከጌታ ስቅለት በፊት በተለይም በሮማውያን ህግ የወንጀለኛ መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምሕረት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያቢሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በሞቱ መልካሙን ሕይወት ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ይባላል።

#ቅዳሜ
#ቀዳም_ስዑር_ትባላለች
ይህች እለት ከድሮ በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረች ቅዳሜ ይባላል።

#ለምለም_ቅዳሜ_ይባላል፡-
ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት በመሆኑም ለምለም ቅዳሜ ይባላል። ምዕመናንም ይህንን ለምለም ቀጤማ እስከ ትንሣኤ ለሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል።

#ቅዱስ_ቅዳሜ_ይባላል፡-
ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ያረፈበት ቀን ሲሆን በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ስራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን ሲያስቀራት በዚያ የነበሩትን ነፍሳት የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል።

(ስምዐ ጽድቅ  መጋቢት ፳፻፪ ዓ.ም)