ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
813 subscribers
3.46K photos
104 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
#መጋቢት_21

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ሃያ አንድ በዚችም ዕለት የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከሙታን ለይቶ ወደ አስንሳው ወደ #አልዓዛር ቤት ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ የሔደበት ነው፣ ተአምረኛው አባት #አባ_ሊባኖስ_ዘመጣዕ ዓለምን ፍጹም በመናቅ የመነኑበት ነው፣ የማቱሳላ ልጅ #ጻድቁ_ላሜህ መታሰቢያው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቤተሰብ (አልዓዛር፣ ማርያና ማርታ)

መጋቢት ሃያ አንድ በዚችም ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ለይቶ ወደ አስንሳው ወደ አልዓዛር ቤት ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ሔደ በዚያም ምሳ አዘጋጂለት ማርታም ምግብ በማቅረብ ታገለግላቸው ነበር።

ሁለተኛዋ ማርያም ግን እግሮቹን ሽቱ እየቀባች በጸጕሩዋ ታሸው ነበር። ጌታችንም አመሰገናት እርሷ ከመቀበሪያዬ ጠብቃዋለች በማለት ስለ ቅርብ ሞቱ አመለከተ።

ዳግመኛም ድኆች ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉ እኔ ግን ከእናንተ ጋራ አልኖርም አለ በዚህም ተሰቅሎ የሚሞትበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ዳግመኛም በዚችም ቀን አልዓዛርን ሊገሉት የካህናት አለቆች ተማከሩ ገናና ስለሆነች ምልክት በእርሱ ምክንያት ብዙዎች በጌታችን የሚያምኑ ሁነዋልና።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሊባኖስ_ዘመጣዕ

በዚችም ዕለት ከዐለት ላይ ውኃ እያፈለቁ ድውያንን የሚፈውሱት ተአምረኛውና አባት አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ ዓለምን ፍጹም በመናቅ መንነዋል፡፡ እርሳቸውም የአባታችን የተክለ ሃይማኖት ገዳም ‹‹ደብረ ሊባኖስ›› በስማቸው የተሰየመላቸው ናቸው፡፡ አባ ሊባኖስ አባታቸው አብርሃም እናታቸው ንግሥት ይባላሉ፡፡ እነርሱም በወርቅና በብር እጅግ የበለጸጉ ሮማዊ ናቸው፡፡ ልጃቸውን አባ ሊባኖስን በሃይማኖት በምግባር ኮትኩተው ካሳደጓቸው በኋላ ዕድሜያቸው ሲደርስ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ያጋቧቸው ዘንድ ከቁስጥንጥንያ አገር ሚስት ባመጡለት ጊዜ እርሱ ግን ፈጽሞ እምቢ አለ፡፡ ወደጫጉላቤትም መግባትን እምቢ አለ፡፡ በዚህም ጊዜ ነቢዩ ሳሙኤልን እንደጠራው አባታችንንም እግዚአብሔር ሦስት ጊዜ በስማቸው ጠራቸውና ‹‹ከአባትህ ተለይ አንተ የመንግሥተ ሰማያት ሙሽራ ነህ እንጂ የዚህ ምድራዊ ዓለም ሙሽራ አይደለህም›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ወዴት እሄዳለሁ? ምንስ ላድርግ?›› ባሉ ጊዜ ወዲያው የታዘዘ መልአክ በሌሊት መጥቶ ከአባታቸው ቤት አውጥቶ ታላቁ አባት አባ ጳኩሚስ ዘንድ አደረሳቸው፡፡ ታላቁ አባት አባ ጳኩሚስም ለአባ ሊባኖስ በዓት በመስጠት ገዳመ ሥርዓትን፣ አስኬማ መላእክትን፣ ቅናተ ዮሐንስን አስተምረዋቸው አመነኮሷቸውና ከ8ቱ ቅዱሳን ጋር እንዲገናኙ አደረጓቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ያ ከአባታቸው ቤት ወስዶ አባ ጳኩሚስ ገዳም ያደረሳቸው ያ መልአክ ድጋሚ ተገለጠላቸውና ‹‹ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ሂድና ተጋድለህን በዚያ ፈጽም ዝናህ በስፋት ይነገራል፣ ለብዙዎችም አባት ትሆናቸዋለህ›› አላቸው፡፡ ቀጥሎም ራሱ መልአኩ ወደ ኢትዮጵያ አመጣቸውና በአክሱም ተቀመጡ፡፡ በዚያም ብዙ ከተጋደሉ በኋላ ወደ ሸዋ መጡና ወንጌልን ዞረው አስተምረው ብዙ ድውያንን ፈውሰው ከዓመታት ቆይታ በኋላ ተመልሰው አክሱም ሄዱ፡፡ በአክሱምም 7 የተለያዩ ጸበሎችን ከድንጋይ ላይ በተአምራት አፍልቀው ድውያንን ፈውሰው ዕውራንን አበሩ፡፡ በዓታቸውንም ከአክሱም ጽዮን ፊት ለፊት አድርገው ሲኖሩ ከዕለታት በአንደኛው ቀን አባታችን በተአምራት ከጭንጫ ካፈለቁት ጸበል ‹‹ተራ ውሃ ነው›› ብላ አንዲት ሴት ልጇን አዝላ ልትቀዳ መጣች፡፡ ወዲውም ከቦታው ስትደርስ አድጧት ወደቀችና ልጇም አምልጥጧት ልቡን ድንጋይ መቶት ሞተ፡፡ ሴትዮዋም ስትጮህ አባ ሊባኖስ ፈጥነው ወጡና በልጁ ላይ ጸልየው በመስቀል ምልክት አማትበው ከሞት አስነሥተውታል፡፡ ሕፃኑ ልጅ ከሞት እንደተነሣ ‹‹አምላከ አባ ሊባኖስ›› ብሎ አመሰገነ፡፡

ይህንንም ደግ ሥራቸውንና ተአምራታቸውን ያዩ አንዳንድ እኩይ ካህናት በቅናት ተመልተው ‹‹ምትሃት ነው የሚያሳየው›› ብለው በጻድቁ ላይ ሕዝቡን አሳደሙባቸው፡፡ አባታችንም ካህናቱን ለመምከር ቢሞክሩም አላስቀምጥ አሏቸው፡፡ ይልቁንም ጦር ጦራቸውን ይዘው አሳደዷቸው፡፡ አባታችንም በዚህ እጅግ አዝነው ከአክሱም ተነሥተው ደርቃ ወደምትባል ቦታ ሄዱ፡፡ በዚያም በጾም በጸሎት እየተጋደሉ ሲኖሩ በእነዚያ በጠሏቸውና በክፋት በተነሡባቸው ካህናት አገር ግን ለ3 ዓመት ምንም ዝናብ ሳይዘንብ ቀረ፡፡ አባታችን በተሰደዱባት በደርቃ አገር ግን ብዙ ዝናብ ይዘንብ ነበር፡፡ አባታችን በዚያችም አገር እንደልማዳቸው ከዐለት ላይ ውኃ አፍልቀው በውኃው ብዙ ድውያንን ፈውሰውበታል፡፡ በዚያም ትልቅ በዓት መሥርተው በተጋድሎ ሲኖሩ በክፉ የተነሡባቸው እኩይ የሆኑ ካህናት መጥተው ‹‹አባታችን በከንቱ አምተንሃል በድለንሃልና ይቅር በለን፣ በድርቅ ማለቃችን ነውና ዝናብም እንዲዘንብልን ጸልይን›› ብለው ከእግራቸው ሥር ወደቁ፡፡ አባታችንም ይቅር ብለው ከፈጣሪ አማለዷቸው፡፡ ዝናቡም ወዲያው ዘነበላቸውና በአገሪቱ ጥጋብ ሆነ፡፡

ከዚህም በኋላ አባታችን አስቀድመው ወዳዩአት ወደ ሸዋ ምድር ግራርያ መጡና በዓታቸውን በአሰቦት ጫካ አደረጉ፡፡ ነገር ግን መልአኩ ተገልጦላቸው ‹‹ሊባኖስ ሆይ! ከዚህ ቦታ የአንተ መኖሪያ አይደለም፣ በዚህ ቦታ ላይ እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያገናኝ የሚያስታርቅ ታላቅ ጻድቅ ይወጣበታልና ይህ ቦታ የእርሱ ርስት ነው፣ የብዙ መነኮሳትም መንደር ይሆናል ነገር ግን የቦታው ስም በአንተ ስም ይጠራልሃል›› አላቸው፡፡ በኋላ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ተወልደው በዓታቸውን በዚያ ቦታ ላይ ሲያጸኑ ቦታው ግን ‹‹ደብረ ሊባኖስ›› ተብሎ በመጀመሪያው አባት ስም ተሰየመ፡፡ መልአኩም በሌሊት እየመራ ወደ አክሱም ወሰዳቸው፡፡ ከዚያም ‹‹ታሪክ ወደምትሠራበት ዕጣ ክፍልህ ወደሆነው ቦታ አደርስሃለሁ›› አላቸውና ወደ ኤርትራ አካለ ጉዛይ አውራጃ ልዩ ስሙ መጣዕ ወደተባለው ቦታ ወሰዳቸው፡፡ በዚያም አባታችን ድውያንን እየፈወሱ፣ ለምፃሞችን እያዳኑ፣ ሙታንን እያስነሡ ብዙ ተአምራትን እያደረጉ ወንጌልን እየሰበኩ ‹‹ሊባኖስ ዘመጣዕ›› የሚባለውን ትልቁን ገዳማቸውን መሠረቱ፡፡ በወቅቱ የነበረው ዐፄ ገብረ መስቀልም የመጀመሪያውን ቤተ ክርስቲያን አሠራላቸው፡፡

ቅዱስ ላሊበላ 23 ዓመት ሙሉ ካነጻቸው እጅግ ድንቅ 11 ቤተ መቅደሶች ውስጥ አንደኛውን በአባ ሊባኖስ ስም ሰይሞላቸዋል፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል ያሠራላቸው ሌላኛው ገዳማቸው ትግራይ ተንቤን ውስጥ ይገኛል፡፡ እጅግ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ የሚታወቁት አባታችን እንደ ተስዓቱ ቅዱሳን ከሮም በመምጣት በሀገራችን ላይ ብርሃንን አብርተዋል፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጻድቁ_ላሜህ

በዚችም ዕለት የማቱሳላ ልጅ የላሜህ መታሰቢያው ነው። እርሱም አንድ መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኑሮ ኖኀን ወለደው ከወለደውም በኋላ አምስት መቶ ስልሳ አምስት አመት ኖረ።

በድምር ሰባት መቶ አርባ ሰባት ዓመት ኖረ። እግዚአብሔርንም አገልግሎት በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት እና #ከገድላት_አንደበት)
እንኳን ለቅዱሳን "ሕጻናተ ቤተ ልሔም" እና "አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" #ሕጻናተ_ቤተ_ልሔም "*+

=>በሮሙ ቄሣር በአውግስጦስ ዘመን ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ አዋጅ ወጥቷልና እመ ብርሃን ማርያም ከቅዱሳኑ ዘመዶቿ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ወደ አባቷ ዳዊት ከተማ ወደ ቤተ ልሔም ሔደች::

+በዚያም ሳሉ የምትወልድበት ጊዜ ቢደርስ በፍጹም ድንግልና እንደ ጸነሰችው ሁሉ በፍጹም ድንግልና ወለደችው:: (ኢሳ. 7:14, ሕዝ. 44:1) ተፈትሖም አላገኛትም:: ልማደ አንስትም አልጐበኛትም:: ምጥም አልነበረባትም::

+በጊዜውም በምሥራቅ የፋርስ: የባቢሎንና የሳባ ነገሥት አስቀድሞ ከበለዓም: በሁዋላም ከዠረደሸት በተረዱት መሠረት ኮከቡን በማየታቸው ታጥቀው ተነሱ::

+ከምሥራቅ አፍሪቃና ከእስያም በተመሳሳይ ኮከቡን በማየታቸው 12 ነገሥታት በየግላቸው 10 10 ሺህ ሠራዊትን እየያዙ ድንግልንና ንጉሥ ልጇን ፍለጋ ወጡ::

+12ቱ ነገሥታት ከነ ሠራዊታቸው ሲሔዱ ስንቃቸው በማለቁ 9 ነገሥታት ተስፋ ቆርጠው ተመለሱ:: 3ቱ ግን በፍጹም ጥብዓት ከ30ሺ ሠራዊት ጋር በኮከብ እየተመሩ ኢየሩሳሌም ደረሱ::

+እነዚህም መሊኩ የኢትዮዽያ (የሳባ ንጉሥ ተወራጅ): በዲዳስፋና መኑሲያ (ማንቱሲማር) ደግሞ የፋርስና የባቢሎን ነገሥታት ናቸው:: ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱም ሔሮድስና ሠራዊቱ ታወኩ::

+እነርሱ ግን የቤተ ልሔምን ዜና ከጠየቁ በሁዋላ በጐል ድንግል ማርያምን: ክርስቶስን: ዮሴፍና ሰሎሜን አገኙ:: ለ2 ዓመታት እነርሱን ፍለጋ ደክመዋል: ተንከራተዋልና ደስታቸው ወሰን አጣ::

+በእመቤታችንና በልጇ ፊት በደስታ ዘለሉ:: "አንፈርዓጹ ሰብአ ሰገል" እንዲል:: ወርቁን: እጣኑንና ከርቤውንም ገብረው በግንባራቸው በፊቱ ሰገዱ:: 3 ጊዜ እየወጡ እየገቡ ቢመለከቱት በኪነ ጥበቡ አንዴ እንደ ሕጻን: በ2ኛው እንደ ወጣት: በ3ኛው እንደ አረጋዊ ሆኖ ታይቷቸው ፈጽመው አድንቀዋል::

+ወደ ሃገራቸው ሲመለሱም "ወአስነቀቶሙ ሕብስተ ሰገም" እንዲል የገብስ ዳቦ ጋግራ ድንግል ሰጠቻቸው:: እነርሱም ይህንን እየተመገቡ የ2 ዓመቱን መንገድ በ40 ቀን ሲጨርሱት ዳቦው ግን ያ ሁሉ ሺህ ሰው ተመግቦት አላለቀም:: ተአምራትንም ሠርቷል::

+ሰብአ ሰገል ቅዱስ መልአክ እንደ ነገራቸው በሔሮድስ ዘንድ ሳይሆን በሌላ ጐዳና ተጉዘው ሃገራቸውን መግባታቸውን ንጉሡ ሰማ:: እንደ ዘበቱበት ሲያውቅም የሚያደርገው ጠፍቶበት ወደ ቤቱ ገባ::

+በሕሊናው የሚመላለሰውም አንድ ነገር ብቻ ነበር:: የአይሁድ ንጉሥ የተባለውን (እርሱስ የሰማይና የምድር ሁሉ ንጉሥ ነው) እንዴት ሊያጠፋው እንደሚችል ያስብ ነበር:: በዚያች ሰዓትም ሰይጣን በሰው ተመስሎ ወደ እርሱ ቀረበ::

+ሕጻኑን እንዴት ሊገድለው እንደሚችል ነግሮት: በዓለም ታይቶ የማይታወቀውን ጭካኔ አስተማረው:: ርጉም ሔሮድስም ሠራዊቱን ጠርቶ "አዋጅ ንገሩልኝ" አላቸው::

+እነርሱም "በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ: በይሁዳም የምትገኙ እናቶች:- አውግስጦስ ቄሣር ሕጻናትን በማርና በወተት አሳድገህ ለሹመት አብቃልኝ: ለእናቶቻቸውም ወርቅና ብር ስጥልኝ ስላለ 2 ዓመትና ከዚያ በታች የሆናቸውን ሕጻናት ሁሉ አምጡ" እያሉ አዋጁን ነገሩ::

+የቤተ ልሔምና የአካባቢዋ እናቶችም ያላቸው አንድም: ሁለትም እየያዙ: የሌላቸው ደግሞ እየተዋሱ ወደ ሔሮድስ ዘንድ ይዘዋቸው መጡ:: ያን ጊዜ አውሬው ሔሮድስ እናቶችን በአንድ ቦታ እንዲታጐሩ አድርጐ ሕጻናቱን በወታደሮቹ አሳፍሶ ወደ ተራራ አወጣቸው::

+በሥፍራውም ተወዳዳሪ በሌለው ጭካኔ 1,200 ወታደሮቹን አሰልፎ ሕጻናቱን አሳረዳቸው:: ሰይፍ የበላቸው የቤተ ልሔም ሕጻናት ቁጥርም 144,000 ሆነ::

+የሕጻናቱ ደም ከተራራው እንደ ጐርፍ ወረደ:: የእናቶች የጡት ወተትም በመሬት ላይ ይፈስ ነበርና ተቀላቀለ:: የቤተ ልሔም እናቶች አንጀታቸው በእጥፉ ተቆረጠ:: ታላቅ ሰቆቃም አካቢውን ሞላው:: ዋይታም ሆነ::

+ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ እንዳለው ነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ:: "ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች:: የሉምና መጽናናት አልቻለችም" (ማቴ. 2:18, ኤር. 31:15)

+ሰይጣን ግን አላማው እንዳልተሳካና ድንግልና አምላክ ልጇ መሸሻቸውን ሲያውቅ ይህንኑ ለሔሮድስ ሹክ አለው:: ስለዚህም ንግሥተ አርያም ድንግል ማርያምና ወልደ አምላክ ልጇ በስደት ለ3 ዓመት ከ6 ወር ተንገላቱ::

+እንደ ገናም ክፉ ሰዎች መጥተው ለሔሮድስ አሉት:- "አንተ የምትሻው በዘካርያስ ቤት አለና ግደለው::"
ሔሮድስም ወታደሮቹን ልኮ: ሕጻኑን ቅዱስ ዮሐንስን ቢያጣው ደጉን ነቢይ: አረጋዊ ዘካርያስን በቤተ መቅደስ መካከል ገድሎታል::

+በጊዜው የሚፈርድ እግዚአብሔርም ስለ ሕጻናቱ ደም ተበቅሎ ሔሮድስን አጠፋው:: ወደ እመቀ እመቃትም አወረደው:: 144 ሺው ንጹሐን ሕጻናት ግን ስልጣነ ሰማይ ተሰጣቸው:: ከእነርሱ በቀር ማንም በማያውቀው ምሥጢርና ዜማ ፈጣሪያቸውን ይሠልሱትና ይቀድሱት ዘንድም አደላቸው:: (ራዕ. 14:1)

+አባ ሕርያቆስ በሐዳፌ ነፍስ ድርሰቱ "ያስምዓነ ቃለ መሰናቁት ዘሕጻናት-የሕጻናትን የመሰንቆ ድምጽ ያሰማን" እንዳለ:: (ቅዳሴ ማርያም)

+እነዚህ 144 ሺህ ንጹሐን ሕጻናት ዛሬ በሰማይ ለምዕመናን ምሕረትን: ለጨካኞች ፍርድን ይለምናሉ:: በፍርድ ቀንም በጌታ ፊት በክብር ቅንዋቶቹን ይዘው ይመጣሉ::

<< ክብራቸው ታላቅ ነውና ለቅዱሳን ሕጻናት ምስጋና ይሁን !! >>

+*" #አባ_ሊባኖስ_ዘመጣዕ "*+

=>በሃገራችን እጅግ ዝነኛ ከሆኑ ቅዱሳን አንዱ አባ ሊባኖስ ናቸው:: እርሳቸው እንደ ተስዓቱ (ዘጠኙ) ቅዱሳንና አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሁሉ ከውጪ ሃገር የመጡ ናቸው::

+የነበሩበት ዘመንም 5ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻና 6ኛው መቶ ክ/ዘመን ውስጥ ነው:: ጻድቁ አባ ሊባኖስን "አባ መጣዕ" እያሉ መጥራት የተለመደ ነው:: "መጣዕ" ማለት ኤርትራ ውስጥ የሚገኝና ጻድቁ በተጋድሏቸው የቀደሱት ቦታ ነው:: ጥንተ ታሪካቸውስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+አባ ሊባኖስ ትውልዳቸው ከሮም ታላላቅ ሰዎች ነው:: አባታቸው አብርሃም: እናታቸው ደግሞ ንግሥት ይባላሉ:: በብሥራተ መልአክ ተጸንሰው ስለ ተወለዱ ስማቸውም በዚያው "ሊባኖስ" ተብሏል::

+"ሊባኖስ" እመ ብርሃን የተወለደችበት ቅዱስ ሥፍራ ሲሆን በጥሬ ትርጉሙ "ደጋ" ማለት ነው:: ምሥጢራዊ ትርጉሙ ግን ለጻድቅነት ያገለግላል:: አባ ሊባኖስ በሃገራቸው ሮም ከወላጆቻቸው ጋር አድገው ለአካለ መጠን ሲደርሱ ከወደ ቁስጥንጥንያ ሸጋ ብላቴና አጭተው አጋቧቸው::

+ወጣቱ አባ ሊባኖስ ግን ማታ "ወደ ጫጉላ አልገባም" ብለው እንቢ አሉ:: ለዚያች ሌሊት ብቻ ከአባታቸው ጋር እንዲያድሩ ተፈቀደላቸው:: መጻሕፍትን የተማሩ ነበሩና በሌሊት ምን እንደሚያደርጉ ሲያወጡ: ሲያወርዱ ቅዱስ መልአክ ከሰማይ ወርዶ 3 ጊዜ "ሊባኖስ" ብሎ ጠራቸው::

+"እነሆኝ ጌታየ!" ቢሉት ከአባታቸው ጐን ነጥሎ እያጫወተ ሳይታወቃቸው ከሮም ግብጽ (ገዳመ ዳውናስ) አደረሳቸው::

+በጊዜው ታላቁ ኮከብ ቅዱስ ዻኩሚስ ነበር:: አባ ሊባኖስን አስተምሮ አመነኮሳቸው: በዓትም ለየላቸው:: በዚያ ለተወሰነ ጊዜ እንደቆዩም ቅዱሱ መልአክ መጥቶ "ለዘለዓለም መጠሪያህ በዚያ ነውና ወደ ኢትዮዽያ ሒድ" አላቸው::