መዝገበ ቅዱሳን
20.7K subscribers
1.92K photos
9 videos
6 files
24 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለሐዋርያው "ቅዱስ እንድርያስ" እና "ለቅዱሳኑ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳቸሁ ✞✞✞

=>መሐሪ #እግዚአብሔር ኃጢአታችሁ በዛ : ሰውነታችሁ ከፋ ሳይል በአባታዊ ርሕራሔው ጠብቆ ይሔው ወርኀ ሐምሌን በሰላም አስፈጸመን:: አይመስለንም እንጂ በእነዚህ 30 ቀናት ሚሊየኖች አንቀላፍተዋል:: ሚሊየኖች በደዌ ዳኝነት ተይዘዋል:: በርካቶቹም ከሃይማኖታቸው ወጥተዋል::

+ታዲያ እኛ ይህ ሁሉ ያልደረሰብን በጐ ስለሆንን አይደለም:: ይልቁኑ ቸርነቱ በእኛ ላይ ስለበዛ ብቻ ነው እንጂ:: አሁንም በሰላም ከአዲሱ ዘመን እንዲያደርሰን ልንማጸነው ይገባል::

=>በዚህች ዕለት ደግሞ እነዚህን ቅዱሳን እናከብራለን:-

+*" ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ "*+

=>ቅዱሱ ሐዋርያ ተወልዶ ያደገው #በቤተ_ሳይዳ አካባቢ ሲሆን የሊቀ ሐዋርያት #ቅዱስ_ዼጥሮስ ትንሽ ወንድም ነው:: አባቱም #ዮና ይባላል:: ገና ከልጅነቱ ጀምሮ አሣ ማጥመድን ከትልቅ ወንድሙ ተምሯል:: እድሜው ከፍ ባለ ጊዜ ኦሪትን ተምሮ የመጥምቁ #ቅዱስ_ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆኗል::

+ከእርሱም እያገለገለ ለ6 ወራት ተምሯል:: በወቅቱ ከወንጌላዊው (ወልደ ዘብዴዎስ) #ዮሐንስ ጋር ቅርብ ባልንጀራም ነበር:: ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ያን ድንቅ #ምሥጢረ_ሥላሴ ከተመለከቱትም አንዱ ነው::

+ጌታ ከጾም (ከገዳመ ቆረንቶስ) በተመለሰ ጊዜ እንድርያስ #መንፈስ_ቅዱስ አነሳስቶት ተከትሎታል:: መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ "ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያዐትት ኃጢአተ ዓለም - የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ" ማለቱን ሰምቶ ቅዱስ እንድርያስ ጌታን ተከተለ::

+በዚህም የመጀመሪያው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመባል በቃ:: (ዮሐ. 1:47) ሊቁ #ማር_ገላውዴዎስም እመቤታችንን ሲያመሰግናት
"ለሐዋርያ #እንድርያስ ቀዳማዊ ማርያም ሃይማኖቱ::
ለመጀመሪያው ሐዋርያ ለእንድርያስ ሃይማኖቱ ማርያም አንቺ ነሽ::" ብሏል:: (#መልክዐ_ስዕል)

+ቅዱሱ ሐዋርያ ስሉጥ (ፈጣን) አገልጋይ እንደ ነበርም ወንጌል ይነግረናል:: (ዮሐ. 6:5) ለ3 ዓመታት ከ3 ወት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ : በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሎ : ምን ሃገረ ስብከቱ #ልዳ ብትሆን ብዙ አሕጉረ ዓለምን ሰብኩዋል::

+ይህች ቀን ሐዋርያው ከጌታ ጋር በመርከብ ውስጥ የተነጋገረባትና ቅዱስ ማትያስን ሰውን ከሚበሉ ሰዎች እጅ ያዳነባት ናት:: ቅዱስ እንድርያስ 30 ቀናት የሚፈጅ የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ከአርድእቱ ጋር ወደ ወደብ ቢሔድም መርከበኞች ሁሉ አናሳፍርም በማለታቸው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣት መርከበኛ መስሎ ሐዋርያውንና አርድእቱን የሠላሳውን ቀን መንገድ በሰዓታት ልዩነት እንዲጨርሱ አድርጉዋል::

+ቅዱስ እንድርያስም ፍጡር (እንዲሁ ሰው) መስሎት ለጌታችን ስለ ጌታችን ሰብኮለታል:: መርቆታልም:: መርከበኛው ጌታችን መሆኑን ሲያውቅም ደንግጦ አልቅሷል::

"ሶበ አእመረ ኪያሁ ወጠየቀ አምሳሎ::
ዘተናገርኩ በድፍረት ምስሌከ ኩሎ::
ሥረይ ሊተ ጌጋይየ ወኅድግ ይቤሎ::" እንዲል::

+"ማረኝ?" ብሎታል:: ጌታችንም "አይዞህ እኔ ካንተ ጋር ነኝ" ብሎታል:: ቅዱሱ ሐዋርያ ለወንጌል አገልግሎት ተግቶ ያረፈው ታሕሳስ 4 ቀን ነው::

+*" ቅዱስ ዻውሎስ መናኒ "*+

=>ይህ ቅዱስ መላ ሕይወቱ ድንቅ ነው:: በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ሲሆን የተባረከች ሚስት እና 2 ቡሩካን ልጆች የነበሩት አባት ነው:: #ቅዱስ_ዻውሎስ የነዳያን አባት : እጅግ ባለ ጸጋ : ቤተሰቡን የቀደሰና ባለ ሞገስ ሰውም ነው::

+ታዲያ ምጽዋት ወዳጅ ነውና ሲመጸውት : ሲመጸውት ሃብቱ አለቀ:: አሁንም መመጽወቱን አላቆመምና ቤቱ : ንብረቱ አልቆ ከነ ቤተሰቡ ነዳያን ሆኑ:: እርሱ ግን ያለ ምጽዋት ማደር አይችልምና አንድ ሃሳብ መጣለት:: ሚስቱንና ልጆቹን መሸጥ እንዳለበት ወሰነ::

+እነርሱ እንደ መሪያቸው ፍጹማን ናቸውና በደስታ ሃሳቡን ተቀበሉት:: መጀመሪያ ትልቁ ልጅ ተሸጠ:: ገንዘቡ ግን አሁንም በምጽዋት አለቀ:: ቀጥሎ ትንሹ ልጅ ተሸጠ:: አሁንም በምጽዋት አለቀ:: 3ኛ ደግ ሚስት ተሸጠችና እርሱም ተመጸወተ::

+በመጨረሻ ቅዱስ ዻውሎስ ራሱንም ሽጦ መጸወተና ይህ ድንቅ ሥራ ተጠናቀቀ:: ( ነገሩ ግራ እንዳያጋባን "ተሸጡ" ስንል ለአሕዛብ ወይም ለሌላ ሰው አይደለም:: 4ቱም የተሸጡት ለገዳማት ሲሆን ገዥዎቹ አበ ምኔቶቹ ናቸው:: ) ቅዱስ ዻውሎስ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መትቶ ምጽዋትንም : ገዳማዊ ሕይወትንም አትርፏል::

+በሁዋላ ወደ ተሸጠበት ገዳም ገብቶ እንዲህ ብሎ ጮኸ:- "ጌታ ሆይ! የሰጠኸኝን ሁሉ ላንተ መልሼ ይሔው መጥቻለሁ::" ጌታም ከሰማይ መለሰለት:- "ወዳጄ ሆይ! ባንተ ደስ ብሎኛል:: ተቀብዬሃለሁ" አለው:: 4ቱም #ቅዱሳን በንጹሕ ተጋድሎ ኑረው በዚህች ቀን ዐርፈው የማታልፈውን ርስት ወርሰዋል::

+*" ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላዕክት "*+

=>ከታላላቅ ሊቃናት አንዱ የሆነው #ቅዱስ_ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም:: የመላእክት መዓርግ ሲነገር #ሚካኤል : #ገብርኤል : #ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው::

+በ3ቱ ሰማያት ካሉት 9ኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ (#የሥልጣናት) መሪ (አለቃ) ነው:: መልአኩ እጅግ ርሕሩሕ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው:: #ለኖኅ መርከብርን ያሳራው : ከጥፋት ውሃም ያዳነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው::

+በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው:: #ቅዱስ_ሱርያል በሌላ ስሙ "#እሥራልዩ" ይባላል:: "የእሥራኤል ረዳት" እንደ ማለት:: ዛሬ ደግሞ የሊቀ መልአኩ ቅዳሴ ቤቱ ነው::

+*" ቅዱሳን መርቆሬዎስና ኤፍሬም "*+

=>እነዚህ ወጣቶች በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበሩ ሲሆን ከተወለዱባት #ገሊላ ወደ ግብጽ (#ገዳመ_አስቄጥስ) በምናኔ መጥተዋል:: ለ20 ዓመታትም በክህነት አገልግሎትና በተጋድሎ ኑረዋል::

+አንድ ቀን መናፍቃን (አርዮሳውያን) በወታደር ተከበው መጥተው በገዳሙ እንቀድሳለን አሉ:: የራሳቸውን መስዋዕት መንበሩ ላይም አኖሩ:: ከዛ ያሉ አበው አዘኑ:: ወጣቶቹ መርቆሬዎስና ኤፍሬም ግን ለአምላካቸው ቀኑ::

+ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው መናፍቃኑን "በክርስቶስ አምላክነት የማያምን በዚህ መቅደስ ውስጥ አይሰዋም" ብለው በድፍረት የመናፍቃንን መስዋዕት ወደ ውጪ በተኑት:: በዚያች ሰዓት መናፍቃኑ 2ቱን ቅዱሳን ወደ መሬት ጥለው ደበደቧቸው:: ረገጧቸው:: የቅዱሳኑ አጥንቶችም ተሰባበሩ:: በመጨረሻ በስቃዩ ብዛት 2ቱም በአንድነት ዐረፉ::

=>የእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን አምላክ ተረፈ ዘመኑን የንስሃ : የፍቅርና የአንድነት ያድርግልን:: ከወዳጆቹም በረከትን ያድለን::

=>ሐምሌ 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ዻውሎስ መናኒ (ከቤተሰቡ ጋር)
3.ቅዱስ ሱርያል (እሥራልዩ) ሊቀ መላእክት
4.ቅዱሳን መርቆሬዎስና ኤፍሬም (ሰማዕታት)
5.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት (ፍልሠቱ)
6.እናታችን ማርያም ክብራ ኢትዮዽያዊት (የዐፄ ናዖድ ሚስት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
2.አባ ሣሉሲ ክቡር
3.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
4.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
5.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ መስከረም ፳፫ (23) ❖

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱሳን #ጻድቃን_ወሰማዕት
#አውናብዮስና_እንድርያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል
በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ #ቅዱሳን_አበው_አውናብዮስ_ወእንድርያስ +"+

=>4ኛው መቶ ክ/ዘ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዘመነ
ከዋክብት ይባላል:: ምናልባትም በዓለም ላይ ላለፌት
1,500 ዓመታት ያንን ዘመን መልሶ ማየት አልተቻለም::

*ያ ዘመን ብዙ #ሰማዕታት ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #ሊቃውንት ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #ጻድቃን ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #ደናግል ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #መነኮሳት ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #ባህታውያን (ግኁሳን) ነበሩበት::

+ዘመኑ #ዘመነ_ብርሃን ነው:: እልፍ አእላፍ ቅዱሳን
በዚህ ዘመን አብርተዋልና:: ጠላት ሰይጣንን ከቦታው
አሳድደው አስጨንቀውታል:: በዚህ ዘመነ ብርሃን ከወደ
ምሥራቅ ካበሩ ከዋክብት መካከል ደግሞ በዚህ ዕለት
አባቶቻችን ቅዱሳን አውናብዮስና እንድርያስን
እናዘክራለን::

+ቅዱሳኑ ባለ ብዙ ሃብት ነበሩ:: ከሰማዕታት: ከጻድቃን:
ከደናግል: ከሊቃውንቱም አሉበት:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

¤በተጠቀሰው ዘመን በቅዱስ #ጊዮርጊስ ሃገር በልዳ
ከከበሩ ወገኖች ተወልደዋል::

+የቅዱሳኑ ወላጆች ክርስቲያኖች: በዚያውም ላይ ባለ
ሥልጣኖችና ሃብታሞች ነበር:: ልጆቻቸውን
(አውናብዮስንና እንድርያስን) ሥጋዊውንም:
መንፈሳዊውንም ትምሕርት አስተምረዋቸዋል:: ወጣት
በሆኑ ጊዜ ወላጆቻቸው የዚህን ዓለም ነገር
ሲያስቡላቸው: እነሱ ግን የተሻለውን እድል ያስቡ ነበር::

+ዘወትር ገድላተ ቅዱሳንን ያነቡ: ዜና አበውን ይሰሙ
ነበርና ይመንኑ ዘንድ ልቡናቸው አወካቸው:: በአንዲት
ሌሊት ግን በመንፈስ ቅዱስ አጋዘዥነት ወስነው:
ከሃገራቸው #ልዳ ወጥተው ወደ ገዳም ሔዱ::

+ክብር ለቅዱሳኑ #አባ_ሮማኖስና #አባ_በርሶማ ይሁንና
በወቅቱ በሶርያ ምድር ገዳማዊ ሕይወት ተስፋፍቶ: ብዙ
አድባራት በበርሃ ውስጥ ነበሩ:: 2ቱ ቅዱሳንም በአንዱ
ገዳም ውስጥ ገብተው አገለገሉ::

+ተጋድሏቸውን እያበረቱ እስከ ምንኩስና ደረጃም ደረሱ::
ተጋድሏቸው በጾም: በጸሎትና በትእግስት ብቻ
አይደለም:: በትሕትና በፍቅር በደግነትና በመታዘዝም
ጭምር ነበር እንጂ::

+የምንኩስናና የገዳማዊ ሕይወት ጠላት 'ፍቅረ ዓለምና
ፍትወት እንስሳዊት' ናቸው:: አንድ ሰው ከዚህ ዓለም
ቁሳቁስ ሳይርቅ መናኝ መሆን አይችልም:: ቅዱሳኑ ግን
በመንኖ ጥሪት ይህችን ዓለም ከነኮተቷ ናቁዋት:
አቃለሏት::

+የሥጋ ፈቃዳቸውን ያጠፉ ዘንድ ሰውነታቸውን በጾምና
በጸሎት: ዕረፍትም በማሳጣት ቀጧት:: #እግዚአብሔር
ደግሞ ስለዚህ ፈንታ ጸጋውን አበዛላቸው:: ቅዱሳኑ
በሶርያ ገዳማት ለዘመናት ከተጋደሉ በሁዋላ ወደ ግብጽ
ለመውረድ ወሰኑ:: ምክንያታቸው ደግሞ:-

1ኛ.ከውዳሴ ከንቱ ለመራቅ
2ኛ.ከቅዱሳን አበው ለመባረክ እና
3ኛ.ለተሻለ ተጋድሎ ለመብቃት ነበር:: እየጸለዩ
እያመሰገኑም ግብጽ: ቀጥሎም ገዳመ አስቄጥስ ደረሱ::

+ታላቁ #ርዕሰ_መነኮሳት_አባ_መቃርስን ፊት ለፊት
ቢያገኙት ደስ አላቸው:: ሐሴትንም አደረጉ::
እግዚአብሕርን በማደሪያዎቹ ማግኘት ይቻላልና:: የታላቁ
ቅዱስ ደቀ መዝሙር ሆነው: በድንግልና ተጠብቀው:
በተጋድሎ በርትተው በቦታው ለ3 ዓመታት ቆዩ::

+እግዚአብሔር ደግሞ ለሌላ አገልግሎት ፈልጐአቸው
ነበርና በዚያ ሰሞን በከተማ የነበሩ ሊቃውንት ወደ ገዳም
መጡ:: ገዳማውያንንም ዻዻስ ስላረፈብን "የምንሾመው
መልካም እረኛን ስጡን" አሏቸው::

+ገዳማውያኑ ሱባኤ ገብተው ቢጠይቁ መንፈስ ቅዱስ
ቅዱስ አውናብዮስን መረጠ:: አበውም ቅዱሱን ዽዽስና
ሲሾሙት ወንድሙን እንድርያስን ረዳት አደረጉት:: 2ቱ ቅዱሳን ከበርሃ ወደ
ከተማ መውጣታቸውን ተከትሎ ተጋድሏቸውን ለማበርታት
ወሰኑ::

+ምክንያቱም ለአንድ ገዳማዊ ከተማ ውስጥ ከመኖር
በላይ ፈተና የለምና:: ቅዱሳኑ ቀን ቀን ድውያንን
ሲጠይቁ: ሙታንን ሲቀብሩ: ሕዝቡን ሲያስተምሩ:
ሥጋውን ደሙን ሲያቀብሉ ውለው ሌሊት ይጋደላሉ::

+ለፈቃደ ሥጋቸው ሳያደሉ እንዲህ ባለ ቅድስና ኖረው
ደግሞ ሌላ ፈተና መጣ:: የከተማው ሃገረ ገዢ አረማዊ
በመሆኑ "ለጣዖት ስገዱ: ክርስቶስን ካዱ" ይል ጀመር::
ቅዱሳኑ ሕዝቡን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም
ሊያስተምሩ ወደዋልና መኮንኑን "ተው! ተሳስተሃል"
አሉት::

+በዚህ ምክንያትም ብዙ ስቃይ ገጠማቸው::
በመጨረሻም በዚህች ዕለት ሰማዕት ሆነዋል:: ጌታም
ስለ ድንግልናዊ ሕይወታቸው: ስለ ወንጌል
አገልግሎታቸውና ስለ ሰማዕትነታቸው 3 አክሊላትን
አቀዳጅቷቸዋል::

=>አምላከ አበው ቸርነቱን ይላክልን:: የቅዱሳኑን
በረከትም ያሳድርብን::

=>መስከረም 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን
በዓላት=
1.ቅዱሳን ጻድቃን አውናብዮስ ወእንድርያስ (ሰማዕታት)
2.ቅዱስ ጐርጐርዮስ መንክራዊ
3.ቅድስት ቴክላ ድንግል
4.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሰማዕት

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እሥራኤል)
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
6.አባ ሳሙኤል
7.አባ ስምዖን
8.አባ ገብርኤል

=>+"+ በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ
ማን ነው? ነገር ግን ስለ #ጽድቅ እንኩዋ መከራን
ብትቀበሉ #ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ:
አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን
በልባችሁ ቀድሱት:: +"+ (1ዼጥ.3:13)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
@petroswepawulos