TIKVAH-ETHIOPIA
1.4M subscribers
54.8K photos
1.37K videos
198 files
3.65K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
ጉብኝቱ ተሰረዘ‼️

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ከሰሞኑ የኬንያውን ፕሬዝዳንት ዑሁሩ ኬንያታን በኢትዮጵያ ተቀብለው አነጋግረው በኋላም አብረው ወደ ኤርትራ ለጉብኝት ሄደው ነበር፡፡ #በኤርትራ በነበራቸው ቆይታ የሦስትዮሽ ግንኙነትን፣ ቀጠናዊ ውሕደትንና ሰላምን ከመጠበቅ አንጻር መወያዬታቸው የሚታወስ ነው፡፡ በኤርትራ የተለያዩ አካባቢዎችንም በጋራ ጎብኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይና የኤርትራው ፕሬዝዳንት #ኢሳይያስ_አፈወርቂ በጋራ ወደ ደቡብ ሱዳን ጁባ ለይፋዊ ጉብኝት ማቅናታቸው የሚታወስ ነው፡፡ በጁባ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ጋር በሁለትዮሽና በሦስትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተሰምቷል፡፡

በመካከሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ወደ #ሱዳን ሪፐብሊክ ሊሄዱ እንደነበርና ድንገት ጉብኝታቸው እንደተሰረዘ ‹ሱዳን ትሪቡን› ዘግቧል፡፡

እንደ ዘገባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ሰኞ ሱዳን #ካርቱም ተጠብቀው ነበር፤ ነገር ግን በዝርዝር ባልተገለጸ ምክንያት ጉብኝቱ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል፡፡ ሱዳን ትሪቡን እንደገመተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈ-ወርቂ በአንድ አውሮፕላን ስለነበሩና ኢሳያስ ካርቱም ማረፍ #ስላልፈለጉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ የካርቱም ጉብኝት ሳይሰረዝ አልቀረም ብሏል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ሱዳን ‹‹የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎችን እየደገፈ ነው›› በሚል ቅሬታ ድንበሯን ዘግታ ነበር፤ ፕሬዝዳንት ኢሳያስም ሱዳንን ከሌሎች ዐረብ ሀገራት ጋር ‹‹በመንግሥቴ ላይ ያሴራሉ›› ሲሉ ሲከሱ ነበር፡፡

ይሁን እንጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በጀመሩት ጥረት የኤርትራና ኢትዮጵያ እንዲሁም የኤርትራና ሌሎች ሀገራት ግንኙነት መሻሻል እያሳዬ ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት የኤርትራና ሶማሊያ፣ የኤርትራና ጅቡቲ እንዲሁም የኤርትራና ሱዳን ግንኙነቶች መሻሻል እያሳዩ ነው፡፡ ፕሬዝዳንት አልበሽርም ከወር በፊት የኤርትራ ድንበራቸውን መክፈታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ነገር ግን አልበሽር እስካሁን የኤርትራ ኤምባሲያቸውን ሥራ አላስጀመሩም፤ በዚህ ልባቸው ያልተፈታው ኢሳያስ ካርቱም ማረፉን በጅ አለማለታቸው ነው የተጠረጠረው፡፡

በእርግጥ ሱዳን ትሪቡን ይህን አላለም እንጅ የሱዳን ወቅታዊ አለመረጋጋትም ለጉብኝቱ መሠረዝ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ለወራት የቀጠለው የሱዳን አለመረጋጋት አልበሽር ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንዲያውጁና የፌዴራልና የግዛት መንግሥታዊ መዋቅራቸውን እንዲበትኑ፣ የፓርቲ ስልጣናቸውንም እንዲያጡ አድርጓልና፡፡

Via AMMA
@tsegabwolde @tikvahethiopia
#ካርቱም

በትናንትናው ዕለት ሱዳናውያን ወጣቶች በካርቱም ጎዳናዎች ላይ #የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ ታይተዋል፡፡ ወጣቶቹ ይህን ያደረጉት በሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች መካከል በተደረሰው ወሳኝ ስምምነት ሂደት ኢትዮጵያ ለተጫወተችው ቁልፍ ሚና አድናቆታቸውን ለመግለፅ ነው፡፡ ወጣቶቹ በሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ስልጣን ለመጋራት በተፈረመው ገንቢ ስምምነት የተሰማቸውን ታላቅ ደስታም ገልፀዋል፡፡

ምንጭ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
@tsegabwolde @tikvahethiopia
#ካርቱም

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) የሚመሩት ልዑክ ካርቱም ገብቷል፡፡ በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማኅበራዊ ገጹ እንዳስነበበው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ልዑክ ዛሬ ወደ ሱዳን ያቀናው በሱዳን የሽግግር መንግሥትን በይፋ ለመመሥረት በሚከናወነው ሥነ-ሥርዓት ለመታደም ነው፡፡

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሐሰን ኦማር አልበሽር መንግሥት የሦስት አስርት ዓመታት ቆይታው በሕዝባዊ ተቃውሞ ተናግቶ ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሲመሠረት ሱዳን ወደ ቀውስ እንደምትገባ ብዙዎች ገምተው ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕብረት ባደረጉት ተከታታይ ጥረት ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱና ሲቪል የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በዚህም #ሱዳን ወደ #መረጋጋት እንደምትገባ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ የሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ ላይ ለመገኘትም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) የሚመሩት ልዑክ ዛሬ ጠዋት ካርቱም ገብቷል፤ ደማቅ አቀባበልም ተደርጎለታል፡፡

Via #AMMA
@tsegabwolde @tikvahethiopia
#ካርቱም

የሱዳን ሲቪል አስተዳደር የሚሰረትበት ስምምነት የፊርማ ሥነ-ሥርዓት እየተካሔደ ይገኛል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት በሰነዱ ላይ ፈርመዋል።

Via #EsheteBekele
@tsegabwolde @tikvahethiopia
#ካርቱም

የሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች እና የተቃዋሚ መሪዎች ስልጣን #ለመጋራት የሚያስችላቸውን ስምምነት በይፋ ተፈራራሙ። ስምምነቱ በሲቪል የሚመራ የሽግግር መንግስት ለመመስረት መንገድ ይጠርጋል ተብሎለታል። በስምምነት ስነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የደቡብ ሱዳን አቻቸው ሳልቫ ኪር ተገኝተዋል።

Via #DW
@tsegabwolde @tikvahethiopia
ፎቶ ፦ የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤሕነን) ታጣቂ ቡድን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረሙና ወደ ሀገር መግባቱ ዛሬ ክልሉ አሳውቋል።

የቤሕነን ታጣቂ ቡድን እና የቤኒሻንጉሙዝ ክልል መንግሥት የሰላም ስምምነት ላይ የደረሱት በሱዳን #ካርቱም መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዚህም ቡድኑ የሰላም አማራጮችን በመከተል ወደ ክልሉ ተመልሷል ተብሏል።

በሰላም ስምምነቱ መሠረት የቡድኑ አባላት ትጥቃቸውን ፍትተው ተሃድሶ በመውሰድ በክልሉ የሰላም እና የልማት ሥራዎች ላይ እንደሚሰማሩ ክልሉ ገልጿል።

(የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሚኒኬሽን)

@tikvahethiopia