ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
802 subscribers
3.46K photos
104 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለሐዋርያው #ቅዱስ_ታዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ #ቅዱስ_ታዴዎስ_ሐዋርያ +"+

=>#ቅዱሳን_ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በ3 ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል::

¤እንደ #ዮሐንስ_ወንጌላዊ ያሉት በ20ዎቹ ውስጥ:
¤#ቅዱስ_ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በ30ና በ40ዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን
¤እነ #ቅዱስ_ዼጥሮስ ደግሞ በ50ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ:: ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም: ከጐልማሶችም ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው::

+ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ #ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች) #ስምዖን እና #ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል::

+ቅዱሱ ጌታችን ተከትሎ:
¤ከ12ቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ:
¤3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታ እግር ተምሮ:
¤በዕርገቱ ተባርኮ:
¤በበዓለ ሃምሳም 71 ልሳናትን ተቀብሎ:
¤#ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል::

+ቅዱስ ታዴዎስ አንድ ቀን ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር ወደ አንዲት ሃገር ይገባሉ:: ታዲያ ለቀናት ያለ ምግብ ወንጌልን ሲሰብኩ ቆይተው ነበርና ደጐቹ ሐዋርያት ራባቸው:: ወደ ከተማዋ ሳይገቡ አንድ ሽማግሌ ሲያርስ አይተው ሰላምታን ሰጡትና "እባክህ እርቦናልና አብላን" አሉት:: እርሱም ምንም ወገኑ ከአሕዛብ ቢሆነ አሳዝነውት በሬዎቹን ሳይፈታ እየሮጠ ሄደ::

+ያን ጊዜ ቅዱስ ታዴዎስ ሊቀ ሐዋርያትን "እርሱ እስኪመጣ ለምን አናርስም" አለው:: 2ቱ ተነስተው ታዴዎስ ሞፈር: ዼጥሮስ ደግሞ ስንዴውን ያዘ:: ቅዱሳኑ እየዘሩ ያረሱት ሰውየው ምግብ ይዞ እስኪመጣ አድጐ: አፍርቶ: እሸት ሆኖ ቆየው::

+ገበሬው የተደረገውን ተአምራት ባየ ጊዜ ደነገጠ:: ሊያመልካቸውም ወደደ:: እነርሱ ግን "እኛ የልዑል ባሮች ነን" ብለው በክርስቶስ ማመንን አስተማሩት:: "ልከተላችሁ" ቢላቸው "የለም! ከእሸቱ ይዘህ ወደ ከተማ ግባና ራት አዘጋጅልን:: እኛ እንመጣለን" አሉት::

+እርሱ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሕዛብ ነገሩን ተረዱ:: ተሠብሥበውም "እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እሳትም ሰይፍም አይበግራቸውም" ብለው ወደ ከተማ እንዳይገቡ ከበሩ ላይ ራቁቷን የሆነች ዘማ አቆሙ::

+ቅዱስ ታዴዎስ ገና ከርቀት ስላያት ቀና ብሎ #ቅዱስ_ሚካኤልን "እርዳን" አለው:: ሊቀ መላእክትም ድንገት ወርዶ ዘማዋን ሴት በጸጉሯ በዓየር ላይ ሰቀላት:: በከተማዋ ያሉ አሕዛብም ይህንና ሌሎች ተአምራትን አይተው ሁሉም በጌታችን አምነው ተጠመቁ:: ለሐዋርያቱም ሰገዱላቸው::

+አንድ ቀን ግን አንድ ጐረምሳ ባለ ጠጋ ቅዱስ ታዴዎስ "ሀብት ንብረታችሁን መጽውቱ" ሲል ሰምቶት ዘሎ የሐዋርያውን ጉሮሮ አንቆ ከሞት አድርሶት ነበር:: ያን ጊዜ "ጌታየ! ለካ ሀብታም ከሚጸድቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ያልክ ለዚህ ነው!" ብሏል:: ባለ ጠጋው "እንዴት ይሆናል?" ቢለው መርፌ አሠርቶ ግመሉን ከነ ባለቤቱ በሰው ሁሉ ፊት 3 ጊዜ አሳልፎታል::

+ያም ማለት ጌታችን እንዳለው "በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል::" (ማር. 10:23) በዚህ ምክንያትም ያ ክፉ ባለ ጸጋ ወደ ልቡናው ተመልሶ ከቅዱስ ታዴዎስ እግር ሥር ወደቀ:: ሐዋርያውም አለው "ሀብትህን ለነዳያን ስጥ:: ይህንንም በትር እንካና እየዞርክ ወንጌለ መንግስትን ስበክ::" ባለ ጸጋውም የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ በክብር ዐርፏል::

+ቅዱሳኑ ታዴዎስና ዼጥሮስ ግን በሃገሪቱ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸው: ካህናትን ሹመው: ያቺን በዓየር ላይ የሰቀሏትን ዘማም የተባረከች መበለት አድርገው: በሌሎች አሕጉራት ወንጌልን ለማዳረስ ወጥተዋል::

+ቅዱስ ታዴዎስም እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል:: ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል:: ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በሁዋላም በዚህች ቀን ዐርፏል::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

=>+"+ ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን "ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል!" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ:: ጌታ ኢየሱስም ደግሞ መልሶ "ልጆች ሆይ! በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ #እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው! ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል" አላቸው:: +"+ (ማር. 10:23-28)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
††† እንኳን ለዓምደ ሃይማኖት ቅዱስ ቄርሎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ †††

††† ቅዱስ ቄርሎስን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን " #ዓምደ_ሃይማኖት- የሃይማኖት ምሰሶ" ይሉታል:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

ሊቁ የተወለደው በእስክንድርያ (ግብጽ) በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: እናቱ የወቅቱ ፓትርያርክ #ቅዱስ_ቴዎፍሎስ እህቱ ነበረችና አጎቱ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ወስዶ አሳድጐታል:: ገና በልጅነቱ ወደ #አባ_ሰራብዮን ገዳም ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል:: በጾም: በጸሎትና በትሕትና የታሸ ነውና ሲማር አንድ ጊዜ ካነበበው በሕሊናው ተስሎ ይቀር ነበር::

ቅዱስ ቴዎፍሎስ "ምዕመናንን አስተምርልኝ" ብሎ ወደ ከተማ አመጣው:: #መንፈስ_ቅዱስ አድሮበታልና ሲያስተምር ወይ ደግሞ መጻሕፍትን ሲያነብ ከምዕመናን ወገን ስንኩዋን የሚያወራና የሚንቀሳቀስ ቀርቶ የሚቀመጥም አልነበረም:: ጣዕመ ስብከቱም ብዙዎችን ለወጠ::

ከዚያም በ412 ዓ/ም አጎቱ የነበረው ፓትርያርክ አባ ቴዎፍሎስ ሲያርፍ ዻዻሳትና ሊቃውንት በአንድነት ቅዱስ ቄርሎስን መረጡ:: የእስክንድርያም 24ኛ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሾመ:: በዘመኑ #ቤተ_ክርስቲያን አበራች:: በቅድስናው: በሊቅነቱ: በስብከቱ: በድርሰቶቹና በትጋቱ በፍጹም አገለገላት::

በወቅቱ ስመ ክፉ መናፍቅ ንስጥሮስ ተነስቶ የእስያ አብያተ ክርስቲያናትን አወካቸው:: ትምሕርቱ ክርስቶስን "2 አካል: ባሕርይ ነው" (ሎቱ ስብሐት!) የሚል ነበር:: በእውነት እንየው ከተባለ ግን ጠቡና ጥላቻው ከድንግል ማርያም ጋር ነበር:: ምክንያቱም ጌታችንን ወደ 2 የከፈለው #እመቤታችንን የአምላክ እናት አይደለሽም ለማለት ነው:: (ላቲ ስብሐት!)

ነገሩን #ቅዱስ_ቄርሎስ በሰማ ጊዜ ወዳለበት ሒዶ ቢመክረውም ንስጥሮስ ሊሰማ አልፈለገም:: በዚህ ምክንያት በትንሹ ቴዎዶስዮስ (የቁስጥንጥንያ ንጉሥ) ትዕዛዝ በኤፌሶን ታላቅ ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሆነ:: ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው የተቀደሰ ጉባዔ ነው:: በ431 ዓ/ም #በኤፌሶን ከተማ የመናፍቃኑን ጥርቅም ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና 200 #ቅዱሳን_ሊቃውንት ተገኙ::

የሚገባው ጸሎትና ሱባዔ ከተፈጸመ በሁዋላ ጉባዔው ተጀመረ:: አፈ ጉባዔው ሊቀ ማሕበር ማር (ቅዱስ) ቄርሎስ ነበርና በጉባዔ ፊት ንስጥሮስን ተከራክሮ ረታው:: ምላሽም አሳጣው:: ከቅዱሳት መጻሕፍት #ክርስቶስ አንድ ባሕርይ መሆኑን: #ድንግል_ማርያምም #ወላዲተ_አምላክ መሆኗን እየጠቀሰ: በምሳሌም እያሳየ አስረዳ::

የሰይጣን ማደሪያ ንስጥሮስ ግን እንቢ: አላምንም በማለቱ ተወግዞ ተለየ:: ቅዱሳን ሊቃውንቱም በቅዱስ ቄርሎስ አርቃቂነት 12 አንቀጾችን አዘጋጅተው ወደ ዓለም ሁሉ ላኩ:: እሊህ አንቀጾች ዛሬም በሊቃውንቱ እጅ አሉ:: ይነበባሉ: ይተረጎማሉ::

††† ከእነዚህም አንዱ ድንግል ማርያም " #ታኦዶኮስ(የእግዚአብሔር እናቱ) ናት" የሚል ነው:: እመቤታችንን:-
¤የአምላክ እናት:
¤ዘላለማዊት ድንግል:
¤ፍጽምት:
¤ንጽሕትና አማላጅ ብሎ ማመን ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃ በጐ ሃይማኖት ነውና::

ጉባዔው ከተጠናቀቀ በሁዋላ ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ጠርቶ "በድንግል ማርያም እመን:: እርሷ ከልጇ ታስታርቅሃለች" ቢለው በድጋሚ "እንቢ" አለው:: ያን ጊዜ ሊቁ "ለአምላክ እናት ያልታዘዘ ምላስህ ላንተም አይታዘዝህ" ብሎ ረገመው:: ወዲያው ምላሱ ተጐልጉሎ ወጥቶ ደረቱ ላይ ወደቀ::

እንደ ውሻ እየተዝረከረከ ሒዶ ከወዳጆቹ ጋር ቁሞ ሳለ መሬት ተከፍታ ውጣዋለች::
ቅዱስ ቄርሎስ ግን ለ32 ዘመናት በመንበሩ ላይ አገልግሎ: ፍሬ ትሩፋት አፍርቶ: ብዙ ድርሰቶችንም ደርሶ በ444 ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፏል:: ከድርሰቶቹም ቅዳሴው: ድርሳነ ቄርሎስና ተረፈ ቄርሎስ ይጠቀሳሉ::

††† ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቶቻችን ጸሎት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን:: ከሊቁም በረከቱን ይክፈለን::

††† ሐምሌ 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)
2.ቅዱስ ክልስቲያኖስ ዘሮሜ (ታላቅ ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት)
3.አባ ሉቅያስ ኤዺስ ቆዾስ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል

††† "የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ:: የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው:: ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ: እስከ ዘለዓለምም ያው ነው:: ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምሕርት አትወሰዱ:: ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም:: በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና::" †††
(ዕብ. 13:7)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለጻድቅ #አባ_ኅልያን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ አባ ኅልያን ገዳማዊ ✞✞✞

=>ጻድቁ ተወልዶ ያደገው ዐይነ ፀሐይ በምትባል የቀድሞ የግብፅ ክፍለ ሃገር ሲሆን ወላጆቹ ዲስጣና ካልሞና ይባላሉ:: እነርሱ መልካም ክርስቲያኖች ነበሩና ገና በልጅነት ይህንኑ አጥብቀው አስተምረውታል:: ቅዱሱ #ኅልያን ጾምን: ጸሎትን ብቻ ያይደለ በሥጋዊ ሙያውም የተመሰገነ አንጥረኛ ነበር::

+በወዙ በላቡ ሠርቶ ያገኘው ሃብት ነበረው:: በተለይ ወርቅና ብር እየሠራ ይተዳደር: ከገቢውም ነዳያንን ያስብ ነበር:: እንዲህ ባለ ግብር ሳለ አንድ ቀን ፈተና መጣበት:: አንዲት ዐረባዊት ሴት መጥታ የጀሮ ጌጥ (ጉትቻ) እንዲሠራላት ትጠይቀውና እርሱም ከወርቅ ይሠራላታል:: የጀሮ ጌጡን ከሰጣት በሁዋላ ግን "ዋጋውን አልሠጥህም" ትለዋለች::

+እርሱም "ምነው እህቴ! የደከምኩበትን ለምን አትከፍይኝም?" ሲላት ገላዋን አጋልጣ "ሴትነቴን ልስጥህ" ብላ ለዝሙት ጠየቀችው:: ድንግሉ ኅልያን ከአነጋገሯና ከድርጊቷ የተነሳ በጣም ደነገጠ:: ከፊቷ ላይ አማትቦ: ገስጿት ወደ ቤቱ ሔደ:: ሙሉ ሌሊት ሲያዝን አደረ:: ሊነጋጋ ሲል በልቡ ወሰነ:: ይሕችን ዓለም ሊተዋትም ቆረጠ::

+በወጣት ጉልበቱ ደክሞ ያፈራው ሃብቱ: ንብረቱ: ቤቱ: መሬቱ: ወርቁ: ብሩ አላሳሳውም:: ነዳያንን ሁሉ ወደ ቤቱ ጠርቶ ሙሉ ንብረቱን አካፈላቸው:: የተረፈችው የለበሳት ልብስ ብቻ ነበረችና ፈጽሞ ደስ እያለው ከተማውን ጥሎ ወደ በርሃ ተሰደደ:: ልቡናን የሚመረምር ጌታ ሊመራው ወዷልና 3 #ቅዱሳን ስውራንን ሰደደለት::

+ሦስቱም የብርሃን አክሊል ደፍተው: የብርሃን ካባ ላንቃ ለብሰው: የብርሃን ዘንግ ይዘው ተገለጡለት:: እየመሩም ወስደው በግራና በቀኝ ውሃ ከሚፈስባት: ደኗ ለዐይን ደስ ከምታሰኝ ዱር አደረሱት:: አካባቢው እንኩዋን ሰው እንስሳትም አልነበሩበትም:: 3ቱ ቅዱሳን ከቦታዋ እንደ ገቡ በላዩዋ ላይ ዕንቁ ያለባት የብርሃን ዘንግ ሰጥተውት "ወደ ፈጣሪ እንስገድ" አሉት::

+ሰግዶ ቀና ሲል ግን 3ቱም በአካባቢው አልነበሩም:: ተሠውረዋልና:: #አባ_ኅልያን ከቅዱሳኑ በመለየቱ ፈጽሞ አለቀሰ::

+ተጋድሎውን ግን በጾምና በጸሎት: በስግደትም አጠነከረ:: ቅዱሱ የሚመገበው: የሚለብሰውም ቅጠል ነበር:: በእርሱ ዘንድ ሌሊት የሚባል አልነበረም:: ምክንያቱም ያቺ ዘንግ ሲመሽ ግሩም የሆነ ብርሃን ታወጣ ነበርና ነው::

+መንገድ መሔድ በፈለገ ጊዜም ትመራው: ጐዳናውንም ታሳጥርለት ነበር:: እንዲህ ባለ ግብር ለበርካታ ዓመታት ከሰው ተለይቶ ኖረ:: አጋንንት በተለያየ መንገድ ፈተኑት:: ግን አልቻሉትም:: አቅም ሲያጥራቸው ወደ ከተማ ሔደው: በሰው አርአያ ሽፍቶችን አናግረው ሊያስገድሉት ሞከሩ:: ነገር ግን ከፊት ለፊት እያዩት ሽፍቶቹ ሲራመዱ ቢውሉም ሊደርሱበት አልቻሉም::

+#እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ መንገዱን ያረዝምባቸው ነበር:: በሁዋላ ግን ሽፍቶቹ በድካምና በውሃ ጥም ሊያልቁ ሆነ:: ጻድቁ ምንም እርሱን ለመግደል ቢመጡም አዘነላቸው:: ባሕሩን ያለ ታንኩዋ እየረገጠ ደረሰላቸው:: ከዱር ፍሬ አብልቶ: ንጹሕ ውሃም አጠጥቶ ሸኛቸው::

+እድሜው እየገፋ ሲሔድ አንድ ቀን እነዛ በፊት የተሠወሩ 3 ቅዱሳን እንደ ገና ተገለጡለት:: በደስታ ሲጨዋወቱ አድረው ሲነጋ አባ ኅልያን ወደ ምሥራቅ ሰግዶ ዐረፈ:: 3ቱ ቅዱሳንም ሥጋውን ገንዘው በበዓቱ ቀበሩት:: ዜና ሕይወቱንም ጽፈው አስቀመጡትና እንደ ገና ተሠወሩ::

=>የቅዱሳን አምላክ ለእኛም የአባቶችን ረድኤት ይላክልን:: ከጻድቁም በረከትን ይክፈለን::

=>ሐምሌ 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አባ ኅልያን ገዳማዊ
2.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት (ዘሐምስቱ አሕጉር)
3.ቅዱስ ታውድሮስ ሰማዕት
4.ሰማዕታት ሉክዮስና ድግናንዮስ (በንስሃ ለክብር የበቁ የጦር አለቆች)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮዽያዊ)
3."318ቱ" ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮዽያዊ)
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

=>+"+ ጌታ ኢየሱስም "አትግደል: አታመንዝር: አትስረቅ: በሐሰት አትመስክር: አባትህንና እናትህን አክብር: ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ" አለው:: ጐበዙም "ይህንማ ሁሉ ከሕጻንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ:: ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው?" አለው:: ጌታ ኢየሱስም "ፍጹም ልትሆን ብትወድ ሒድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ:: መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ:: መጥተህም ተከተለኝ" አለው:: +"+ (ማቴ. 19:18)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
††† እንኳን ለቅዱሳን አበው አባ መቃርስ: ቅዱስ አብርሃም እና ቅዱስ ፊንሐስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ታላቁ ቅዱስ መቃርስ †††

††† ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ( #መቃሬ) "ጽድቅ እንደ መቃርስ" የተባለለት: የመነኮሳት ሁሉ አለቃ: ከ80 ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ: በግብፅ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ: ከ50,000 በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው::

በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብፅ ወደ እስያ በርሃ ከጉዋደኛው #ቅዱስ_መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል:: በዚያ ለ2 ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በሁዋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነንጉሳቸው አጥምቀዋል::

በተሰደዱባት ሃገርም #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) #እመቤታችንን: #ቅዱሳን_ሐዋርያትን: #አዕላፍ_መላእክትን: በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን #ዳዊትን: #ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን: #ማርቆስን: #ዼጥሮስን: #ዻውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል:: በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::

ታላቁ ቅዱስ መቃርስና መቃርዮስ ከ2 ዓመታት ስደትና መከራ በሁዋላ ስደት በወጡባት በዚችው ዕለት መልዐኩ ኪሩብ በክንፉ ተሸክሞ ወደ ግብፅ መልሷቸዋል:: በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከ50,000 በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል::

ይህች ዕለት ለአባታችን መቃሪ በዓለ ፍልሠቱ ናት:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በሁዋላ ከክቡር ሥጋው ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ (የሳስዊር) ሰዎች ሊወስዱት ፈለጉ:: #ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ ያደገባት ወላጆቹ (አብርሃምና ሣራ) የኖሩባት ቦታ ናት::
የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው::

በምድረ ግብጽ: በተለይም በገዳመ #አስቄጥስ የአባ መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር:: መሥረቅ ኃጢአት ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር: አንድም ለበረከት (በረከትን ሲሹ) አደረጉት::

ወደ ሳስዊርም ወስደው: ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም አንጸው በክብር አኖሩት:: በዚያም ለመቶዎች ዓመታት ተቀመጠ:: በ7ኛው መቶ ክ/ዘመን ግን ተንባላት (እስላሞች) መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ:: በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ:: በሌላ ቦታም እንደ ገና በስሙ #ቤተ_ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት::

በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ:: #አባ_ሚካኤል ሊቀ ዻዻሳት በነበረበት ዘመን: ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሰውነታቸው ታወከ::

ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው አልቻለም:: ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና:: ሕዝቡና ሃገረ ገዢው የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላቹሃለን" ብለው ሰይፍ: ዱላ: ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው::

መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ:: መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም #ታላቁ_መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራዕይ ተቆጣው:: በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ::

ሕዝቡም በዝማሬና በማኅሌት: ከብዙ እንባ ጋር ሸኟቸው:: ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ ተደረገ:: #ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው በክብር አኑረውታል:: ይህ የተደረገው በዚህች ዕለት ነው::

††† አባታችን ቅዱስ አብርሃም †††

††† የሃይማኖት-የደግነት-የምጽዋት-የፍቅር አባት የሆነው #አብርሃም ደጉ በዚህች ቀን ይታሠባል:: በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የአብርሃም አባቱ ታራ ጣዖትን ይጠርብና ይሸጥ ነበር:: ሽጦ ገንዘብ የሚያመጣለት ደግሞ ልጁ አብርሃም ነበር::

በዚያ ወራት አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ፍለጋ ገብቶ ነበር:: አንድ ቀን ጣዖቱን ሊሸጥ ወደ ገበያ እየሔደ የተሸከመውን እንጨት ይመራመረው ገባ:: "አሁን ይሔ ምኑ ነው አምላክ!" እያለም ያደንቅ ገባ:: መንገድ ላይም ደክሞት ካረፈበት "ለምን አልጠይቀውም" በሚል አናገረው::

"እርቦኛል አብላኝ" አለው:: መልስ የለም:: "እሺ አጠጣኝ" አለው:: አሁንም ያው ነው:: "ባይሆን እሺ አጫውተኝ" አለው:: ጣዖቱ ተራ እንጨት ነውና መልሱ ዝምታ ነበር:: ከዚያ ተነስቶ ወደ ገበያው ሲደርስ "ዐይን እያለው የማያይ: ጆሮ እያለው የማይሰማ አምላክ የሚገዛ" እያለ ይጮህ ጀመር::

ይህን ሲሰሙ አንዳንዶቹ "የታራ ልጅ አብዶ" ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ "እሱ ያቀለለውን ማን ይገዛዋል" ብለውት ሔደዋል:: ከገበያ ሲመለስም ጣዖቱን ተመልክቶ አብርሃም እንዲህ አለ:: "አንተ ቀድሞውን በዕለተ ሠሉስ የተፈጠርክ ዕፅ ነህ" ብሎ ሰባበረው::

ወደ ቤቱ ሲመለስም ሁሉንም ጣዖታት ሠባበራቸው:: ይህ የተደረገው ከ2,000 ዓመታት በፊት በዚህች ቀን ነው:: የመንግሥተ ሰማያት አበጋዝ: የእግዚአብሔር ወዳጅ አባታችን አብርሃም በመጨረሻው በውሃ: በነፋስ: በእሳትና በፀሐይ ተመራምሮ ፈጣሪውን አግኝቷል::

††† ቅዱስ ፊንሐስ ካህን †††

††† ካህኑ ፊንሐስ የብሉይ ኪዳን ዘመን አገልጋይ: ከነገደ #ሌዊ: የሊቀ ካህናቱ የአሮን የልጅ ልጅ ነው:: አባቱም ሊቀ ካህናቱ #አልዓዛር ነው:: ፊንሐስ #እሥራኤል ከግብጽ ሲወጡ ሕጻን የነበረ ሲሆን አድጐ በመጀመሪያ ካህን: አባቱ አልዓዛርና አያቱ #አሮን ሲያርፉ ደግሞ ሊቀ ካህንነትን ተሹሟል::

አንድ ቀን በጠንቅ-ዋዩ በበለዓም ክፉ ምክር እሥራኤላውያን ከሞዐብ ሴቶች ጋር በኃጢአት በመሳተፋቸው #እግዚአብሔር ተቆጥቶ ነበር:: ያጠፋቸው ዘንድም መቅሰፍት ተጀምሮ ሳለ ፊንሐስ ወንድና ሴት: በደብተራ ኦሪቱ አንጻር የማይገባውን ሲሠሩ አያቸው::

ለፈጣሪው ቀንቶ በአንድ ጦር ሁለቱንም በአንድ ላይ ጥሏቸዋል:: ያን ጊዜ ጌታ "አስተንፈስካ ለነፍስየ" ብሎታል:: መቅሰፍቱም ተከልክሏል:: በዚህም ምክንያት ካህኑ ፊንሐስ የ300 ዓመት ዕድሜ ተጨምሮለት: እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል:: (ዘኁ. 25:7, መዝ. 105:30)

††† ለአበው ቅዱሳን የተለመነ አምላክ ለእኛም ይለመነን:: ክብራቸውንም በእኛ ላይ ይሳልብን::

††† ነሐሴ 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (4ኛ ቀን)
2.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ፍልሠቱ)
3.አባታችን ቅዱስ አብርሃም (ጣዖቱን የሰበረበት)
4.ቅዱስ ፊንሐስ ካህን (ወልደ አልዓዛር)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
4.አቡነ ሥነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

††† "እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ:- 'በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ:: እያበዛሁም አበዛሃለሁ' ብሎ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለ:: እንዲሁም እርሱ ከታገሠ በሁዋላ ተስፋውን አገኘ::" †††
(ዕብ. 6:13)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
†††✝️🌻 እንኳን ለቅዱሳት አንስት ኄራኒ ሰማዕት: ንግሥተ ሳባ እና ንግሥት ዕሌኒ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††✝️🌻

†††✝️🌻 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††✝️🌻

††† ✝️🌻ቅድስት ኄራኒ ሐዋርያዊት ሰማዕት †††✝️🌻

††† ይህቺ ቅድስት ወጣት መልክ ከደም ግባት: ምግባር ከሃይማኖት: ስም ከመልካምነት የተባበረላት ሰማዕት ናት:: #ኄራኒ ማለት "ሰላማዊት: የተወደደች" ማለት ነው:: አንድም በጥሬው "ሰላምና ፍቅር" ማለት ነው::

ቅድስት ኄራኒ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን በታናሽ እስያ የንጉሥ #ሉክያኖስ ልጅ ናት:: ከተወለደች ጀምሮ ስለ ክርስትና ሰምታ አታውቅም:: ምክንያቱም አባቷ ጣዖት አምላኪ ከመሆኑ ባለፈ ክርስቲያኖችን ይቀጣ ስለ ነበር ነው::

ልጁን ማንም እንዳያገኛት ሲል ንጉሡ ለቅድስት ኄራኒ ቤተ መንግስት ሠራላት:: ማንም እንዳይገባ በዙሪያው 12 አጥር አጠረበት:: ጣዖቶቹን እንድታጥን አገልጋዮችንም ሾመላት::

ምናልባት አጥር ሰውን ሊከለክለው ይችላል:: #እግዚአብሔር ግን እግዚአብሔር ነውና ምንም አይከለክለውም:: ጌታ ደግሞ ይህቺን ወጣት ለወንጌል አገልግሎት ይፈልጋታል:: አንድ ቀን አባቷ: ልጁ ምሑር እንድትሆንለት አለ የተባለ ሽማግሌ ፈላስፋ ቀጠረላት::

ጥበበ እግዚአብሔር ማለት ይሔ ነው:: አባቷ ይሕ ሽማግሌ ማንን እንደሚያመልክ አልተረዳም:: አረጋዊው እጅግ የተዋጣለት ክርስቲያን ነው:: ግን ማንም አያውቅበትም:: አረጋዊው ቅድስት ኄራኒን ዝም ብሎ ሊሰብካት አልወደደም::

መጀመሪያ በስነ ምግባር አነጻት:: ቀጥሎ ግን "ጌታ ሆይ! ጐዳናህን ምራት" እያለ ይጸልይላት ገባ:: ጌታችን ልመናውን ሰምቶታልና ቅድስቷ አንድ ቀን ግሩም ራዕይን አየች::

እርሷ ለማዕድ ተቀምጣ ሳለ: የምሥራቅና የምዕራብ መስኮቶቿም ተከፍተው ሳሉ: በምሥራቁ መስኮት ነጭ ርግብ በአፏ የወይራ ዝንጣፊ (ቆጽለ ዘይት) ይዛ ገባችና ማዕዷ ላይ አኑራው ሔደች:: እርሷን ተከትሎ ደግሞ ንስር በአፉ አክሊል ይዞ ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ሔደ::

በ3ኛው ግን ቁራ: እባብ በአፉ ይዞ በምዕራቡ መስኮት ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ወጣ:: ቅድስት ኄራኒ ያየችው ራዕይ ቢጨንቃት ሽማግሌ መምሕሯን "ተርጉምልኝ" አለችው::

እርሱም "ልጄ ሆይ! ለዘመናት ስጠብቀው የነበረ ምኞቴን ነው ጌታ ያሳየሽ:: የሕልምሽ ትርጉም እንዲህ ነው:- ነጭ ርግብ የመንፈስ ቅዱስ (የሃይማኖት) ምሳሌ ናት:: የወይራ ዝንጣፊው ደግሞ #ማሕተመ_ጥምቀት( #ሜሮን) ነው:: ቁራ የክፉ ነገሥታት ምሳሌ ሲሆን እባብ የመከራ ምሳሌ ነው::

ንስር ድል የመንሳት ምልክት ሲሆን አክሊል ደግሞ የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው:: ልጄ! ክርስቲያን ሆነሽ የሚደርስብሽን ሁሉ ጌታ አሳይቶሻል" ብሎ ተርጉሞላት ተሰናበታት::

እርሷም ወደ ምሥራቅ ዙራ ጸለየች:- "የማላውቅህ አምላክ ሆይ! ወደ እውነትህ ምራኝ" ስትል ለመነች:: በዚያች ሰዓት የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ አጽናናት:: የሚያጠምቃትም እንደሚልክላት ነገራት::

በዚያን ጊዜ አባቷ ገብቶ "ልጄ! ከመሣፍንቱ ላንዱ ልድርሽ ስለሆነ ምን ትያለሽ?" አላት:: "3 ቀን ስጠኝ" አለችውና ሰጣት:: ወደ ጣዖቶቹ ዕለቱኑ ወርዳ "ላግባ ወይስ ይቅርብኝ?" አለቻቸው:: ከቀድሞም በወርቅ የተለበጡ ድንጋዮች ናቸውና ዝም አሉ:: በሙሉ ቀጥቅጣ ሰባብራቸው ተመለሰች::

በዘመኑ #ቅዱሳን_ሐዋርያት(በተለይ እነ #ቅዱስ_ዻውሎስ) በሕይወተ ሥጋ ነበሩና ከቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቤቷ እንደ ተዘጋ ገባ:: ክርስትናን ከጥንቱ እስከ ተፍጻሜቱ አስተምሮ አጠመቃት::

በ3ኛው ቀን አባቷ "ምን መከርሽ?" ቢላት "የእኔ ምክር #መርዓተ_ክርስቶስ(ሰማያዊ ሙሽራ) መሆን ነው" አለችው:: አባቷ ደነገጠ:: እጅግ ስለ ተናደደ ወደ አደባባይ አውጥቶ: አስሮ መሬት ላይ ጣላትና በመቶ የሚቆጠሩ ፈረሶች እንዲረግጧት አደረገ::

በወቅቱ ሰው የሚጠብቀው የአካሏን ቁርጥራጭ ነበር:: ነገር ግን ጌታ ከእርሷ ጋር ነበርና ልብሷ እንኩዋ ጭቃ አልነካም:: አባቷ ንጉሥ ሉክያኖስና ሠራዊቱ ያዩትን ማመን አልቻሉም:: ሁሉም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው "ከክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም" አሉ:: ቅድስት ኄራኒ ምንም ሳትናገር ይህንን ሁሉ ሰው ማረከች::

ወዲያውም ንጉሡ መልእክተኛ ልኮ: የቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዝሙርን አስጠርቶ: ከነ ቤተሰቦቹ ተጠመቀ:: የዚህን ዓለም ክብር ንቆም ንግሥናውን ተወ:: የጸሎት ሰውም ሆነ:: የቅድስት ኄራኒ ተጋድሎ ግን ቀጠለ::

በአካባቢው የነበረ ንጉሥ መጥቶ የአባቷን መንግስት ቀማ:: እርሷንም እጅግ አሰቃያት:: እርሱ አልፎ አርማንዮስ የሚባል ንጉሥ እንዲሁ አሰቃያት:: እርሱም አለፈ:: ከእርሱ ቀጥሎ የመጣው ንጉሥ ብዙ መከራዎችን በእርሷ ላይ አደረሰ:: በጦርም ጐኗን ወግቶ ገደላት::

ከጥቂት ሰዓታት በሁዋላ ግን ልክ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ተነስታ ጠራችው:: በጣም ደንግጦ "አምላክሽ አምላኬ ነው" ሲል አመነ:: ከ30,000 በላይ ሠራዊቱን ይዞም ተጠመቀ::

ቅድስት ኄራኒ በቀረ ሕይወቷ በስብከተ ወንጌል እስያን አድርሳለች:: ጌታ አብርቶላት: እርሷም አብርታ: እልፍ ፍሬን አፍርታ: በዚህች ቀን ዐርፋለች:: የሐዋርያትንም: የሰማዕታትንም አክሊል ተቀዳጅታለች::

†††✝️🌻 ንግሥተ ሳባ †††✝️🌻

††† ይሕቺ ኢትዮዽያዊት ከ3 ሺ ዘመናት በፊት የነበረች ደግ እናት ናት:: በሥጋዊ ደረጃ ከታንዛንያ እስከ #የመን ያስተዳደረች ስመ ጥር ንግሥት ስትሆን በመንፈሳዊው ደረጃ ደግሞ እግዚአብሔር የቀባውን ሰው ፍለጋ ወደ #ኢየሩሳሌም ተጉዛለች::

ከዚያውም አምልኮተ እግዚአብሔርን ከሥርዓተ ኦሪት ጋር አምጥታለች:: ድንግልናዋን ለታላቁ #ንጉሥ_ሰሎሞን ሰጥታ #ምኒልክን ወልዳለች:: ይህቺ ንግሥት በጌታችን (በፈጣሪ) አንደበትም ተመስግናለች:: (ማቴ. 12:42) በስምም " #ሳባ: #አዜብና #ማክዳ ተብላ ትታወቃለች:: ዛሬ ዕለተ ልደቷ ነው::

††† ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት †††

††† ይሕቺ ቅድስት የቅዱስ #ቆስጠንጢኖስ እናቱ: የመስቀሉ ወዳጅ: የቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የሆነች ክብርት እናት ናት:: ይህቺም ቅድስት የተወለደቺው በዚሁ ዕለት ነው::

††† የቅዱሳት እናቶቻችን አምላክ እህት እናቶቻችንን ከክፋትም: ከጥፋትም: ይሠውርልን:: ለሃገርም: ለሃይማኖትም የሚጠቅሙ ሴቶችንም ጌታ አይንሳን:: በረከታቸውም ይደርብን::

††† ነሐሴ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (6ኛ ቀን)
2.ቅድስት ኄራኒ ሐዋርያዊት (ሰማዕት)
3.ቡርክት ንግሥተ ሳባ (ልደቷ)
4.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት (ልደቷ)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ
2.አበው ጎርጎርዮሳት
3.አቡነ ምዕመነ ድንግል
4.አቡነ አምደ ሥላሴ
5.አባ አሮን ሶርያዊ
6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

††† " #ንግሥተ_አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስታ ትፈርድበታለች:: የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና:: እነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ::" †††
(ማቴ. 12:42)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
#ደግ እና #ጻድቅ #ንጉሥ አፄ #ዘርዓያዕቆብ ካረፉ ዛሬ (ጳጒሜን 3) 555ዓመት ሞላቸው፡፡

✞ ሃይማኖታቸው የቀናው ንጉሥና የእመቤቴ ወዳጅ ከ1426 - 1460 በቆየ መሪነታቸው፡-

✿ለቤተ ክርስቲያንና ለሃገር ብዙ ሆነዋል፡፡
✿ኢትዮጵያን ዳግም ወደ ልዕልናዋ መልሰዋል ፡፡
✿ሃይማኖት ይቀናና ይሠፋ ዘንድ ተግተዋል፡፡
✿ከ11 ያላነሱ መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡ (መጽሐፈ ብርሃንን ፡ ምዕላድን ፡ መልክዐ ማርያምን ፡ መልክዐ ጊዮርጊስን ጨምሮ)
✿ብዙ መጻሕፍትን ከውጪ ቋንቋ አስተርጉመዋል፡፡
✿የሃይማኖት ጉባኤያትንም አድርገዋል ፡፡

✞ በዚህ ሁሉ መሐል ግን ስለሃገርና ቤተ ክርስቲያን ልዕልና ሲሉ የወሰዷቸውን መንግስታዊ ርምጃዎችን እየጠቀሱ ሊያቃልሏቸው የሚሞክሩ ዘመን የወለዳቸው ጸሐፍት አሉ፡፡

✞ ስለእነዚህ ሰዎች የምለው የለኝም ፡፡ "አቤቱ ፍረድልን" ከማለት በቀር፡፡

✞ ትልቁ ችግር ግን ሁሉን ነገር በሥጋዊ ልቦና ለመመርመር መሞከሩ ይመስለኛል፡፡

✞ ቤተ ክርስቲያን ግን ክብራቸውን፡-
✿በገድለ #ተክለሃይማኖት
✿በገድለ አቡነ #ተክለሐዋርያት
✿በገድለ አቡነ #ፊልጶስ ዘደብረ ቢዘን
✿በገድለ አቡነ #መብዓጽዮን
✿በድርሳነ #ኪዳነምሕረት እና
✿በመጽሐፈ #ስንክሳር . . . ትመሰክራለች፡፡

✞ የበለጠውን ምስክርነት የሚሻና ፡ ቅን ልቡና ያለው ሰው ካለ ደግሞ ወደ #ጻድቃኔማርያም ሔዶ እውነቱን ሊረዳ ይቻለዋል፡፡
"#የዘርዓያዕቆብ #እመቤት" ሲሏት #እመብርሃን ትሰማለችና፡፡

አምላከ #ቅዱሳን ከጻድቁ ንጉሥ በረከት ያሳትፈን፡፡
እንኩዋን ለታላቁ #ነቢይና_ሰማዕት_ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ

=>ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: #ቅዱስ_ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "#ዘካርያስ ካህኑና #ቅድስት_ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

¤የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!

¤እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::

¤ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

¤ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል #እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

¤የአምላክ እናቱ ስትደርስና "#ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ #ሰብአ_ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

¤እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና #ስምዖን ወርደው ቀበሯት::

¤ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ #ድንግል_ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

¤ከዚህ በሁዋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::

¤ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ #መንፈስ_ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::

¤ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ:: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::

¤"እንቢ ጌታዬ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "#መጥምቀ_መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::

¤በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)

¤ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት #ደብረ_ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: #ቅዱሳን_ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት::

¤ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ሥልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ሚያዚያ 15 ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::

<<¤ አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ (የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች) ¤>>
1.ነቢይ
2.ሐዋርያ
3.ሰማዕት
4.ጻድቅ
5.ካሕን
6.ባሕታዊ/ገዳማዊ
7.መጥምቀ መለኮት
8.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
9.ድንግል
10.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
11.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
12.መምሕር ወመገሥጽ
13.ዘየዐቢ እምኵሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

=>ጌታችን #መድኃኔ_ዓለም የመጥምቁ ዮሐንስን ምትረት አስቦ ይቅር ይበለን:: ጸጋውን: በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን::

=>መስከረም 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)
2.ቅዱስ ዳስያ ሰማዕት
3.ቅዱስ ዲዲሞስ ሰማዕት
4.ቅድስት መሪና

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

=>+"+ #ጌታ_ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ #ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ . . . ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችሁአለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን . . . እውነት እላቹሃለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም . . . ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ:: ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው #ኤልያስ ይሕ ነው::
የሚሰማ ጀሮ ያለው ይስማ:: +"+ (ማቴ. 11:7-15)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

ምንጭ:- ዝክረ ቅዱሳን

🕊👉 @zekidanemeheret
ታኦዶኮስ (ወላዲተ እግዚአብሔር)

በ431 (424) ዓ/ም በዚህች ቀን (መስከረም 12) #በኤፌሶን የተሰበሰቡት 200ው #ቅዱሳን #ሊቃውንት እና ሊቀ ማኅበር #ማር #ቄርሎስ ዓምደ ሃይማኖት እንዲህ ሲሉ ሃይማኖታቸውን ገልጠዋል፡፡

""  ንሕነሰ ነአምን ከመ ድንግል ቅድስት ኮነት ታኦዶክስ፡፡ ዝ ብሒል ወላዲተ እግዚአብሔር ቃል፡፡ ""
(እኛስ ቅድስት ድንግል ማርያም ታኦዶኮስ እንደሆነች እናምናለን፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ቃል እናቱ ማለት ነው፡፡)

ከመዝ ናአምን (እንዲህ እናስተምራለን) ፡ ወከመዝ ንትአመን (እንዲሁም እናምናለን)፡፡

ንስጥሮሳውያንን (ፀረ ማርያሞችን) ግን እናወግዛለን፡፡

✿የወላዲተ አምላክ ማርያም ጣዕመ ፍቅሯ ፡ ዝክረ ውዳሴዋ በዝቶ ይደርብን፡፡✿
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ✞✞✞

✞✞✞ እንኳን ለአበው
#ቅዱሳን_ኤዎስጣቴዎስ_አኖሬዎስና_ማር_ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

†  🕊  አቡነ_ኤዎስጣቴዎስ_ረባን    🕊   †

=>ሐዋርያዊው ጻድቅ ኢትዮዽያዊ (ኤርትራዊ) ሲሆኑ በዓለም ደረጃ የሚታወቅ አገልግሎት ያላቸው አባት ናቸው:: በመካከለኛው ዘመን የኢትዮዽያ ታሪክ የኤዎስጣቴዎስንና የተክለ ሃይማኖትን ያህል ስሙ የጐላ ጻድቅ አይገኝም::

+ጻድቁ በ1265 ዓ/ም አካባቢ እንደ ተወለዱ ሲታመን ወላጆቻቸው #ክርስቶስ_ሞዐ እና #ሥነ_ሕይወት ይባላሉ:: የጻድቁ የመጀመሪያ ስም #ማዕቀበ_እግዚእ (ለጌታ የተጠበቀ) ነው:: ኤዎስጣቴዎስ የተባሉ በኋላ ነው::

+ገና ከልጅነታቸው መንፈሰ እግዚአብሔር አድሮባቸዋልና ለዚህ ዓለም ግድ አልነበራቸውም:: ከመምህር ዘንድ ገብተው: ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምረው: ዲቁናን ተቀብለው ያገለግሉ ገቡ:: በዲቁና አገልግሎታቸው ስሉጥ በመሆናቸውም የዘመኑ አበው 'ዳግማዊ እስጢፋኖስ' እያሉ ይጠሯቸው ነበር::

+ከዚያ በወጣትነት እድሜአቸው ምናኔን መርጠው: ጾምና ጸሎትን ከስግደት ጋር አዘወተሩ:: እንዲህ ባለ ሕይወት ሳሉ አንድ ቀን ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዘንድ መጣ::

+በዘባነ ኪሩብ: በግርማው ቢያዩት ደነገጡ:: ጌታ ግን "ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ! ገና ከእናትህ ማሕጸን መርጬሃለሁ:: ከኢትዮዽያ እስከ አርማንያም ሐዋርያ ትሆን ዘንድ ሹሜሃለሁ:: 'ዘኪያከ ሰምዐ: ኪያየ ሰምዐ . . . አንተን የሰማ እኔን ሰማ: አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ አለ" ብሏቸው ባርኩዋቸው ዐረገ::

+ጻድቁ ፈጣሪያቸውን ስለ ስጦታው እያመሰገኑ ቅስናን ተቀብለው ስብከትን ጀመሩ:: ስም አጠራራቸውም ፈጥኖ በሃገሪቱ ተሰማ:: በየቦታው እየዞሩ ያላመነውን አሳምነው እያጠመቁ: ያመነውን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እያጸኑ: ሕይወተ ገዳምን እያስፋፉ ኖሩ::

+አሁን ኤርትራ ውስጥ የሚገኘውንና እርሳቸው የመሠረቱትን ገዳም ጨምሮ ለገዳማዊ ሕይወት መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል:: በገዳማቸውም አባ አብሳዲን ጨምሮ በርካታ አርድእትን አስተምረዋል: አፍርተዋል::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በተለይ የሚታወቁት #ቀዳሚት_ሰንበት እንዳትናቅ (እንድትከበር) ባደረጉት ጥረት ነው:: ደግሞም ተሳክቶላቸዋል:: ቅርብ ጊዜ ከምናየው የድፍረት ሥራ በቀር በሃገራችን 2ቱም ሰንበቶች ክቡር ናቸው::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ 2 ጊዜ በእግራቸው ተጉዘዋል:: መሔዳቸው ግን ለመሳለም ብቻ አይደለም:: ይልቁኑ የወንጌል ዘርን እየዘሩ: ፍሬውንም እየለቀሙ እንጂ:: እርሳቸው መቼም ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ቸል አይሉምና::

+በመጨረሻ ሕይወታቸውም በገዳማቸው ላይ ደቀ መዝሙራቸውን አባ አብሳዲን ሹመው ለአዲስ ጉዞ ተነሱ:: እኩሎች ልጆቻቸውን በገዳማቸው ትተው እኩሎችን አስከትለው ጉዞ ወደ አርማንያ ተደረገ::

+በመንገድም ወደ ባሕረ #ኢያሪኮ ሲደርሱ የሚሻገሩበት መርከብ አጡ:: ድንቅ አባት ናቸውና በእምነት አጽፋቸውን (ኩታቸውን) አውልቀው ባሕሩ ላይ ጣሉት:: በላዩ ላይም በትእምርተ መስቀል አማትበው ተቀመጡበት::

+ደቀ መዛሙርቶቻቸውም ባሕሩ ላይ በተነጠፈው ኩታ ላይ ከበው ተቀመጡ:: ከሰማይም ጌታችን ወርዶ በመካከላቸው ቆመ:: #ሚካኤል በቀኝ #ገብርኤልም በግራ ቆሙ:: ጻድቁ ደግሞ ልጆቻቸውን ያስተምሯቸው: ይተረጉሙላቸው ገቡ::

+በመካከል ግን አንዱ (የማነ ብርሃን ይሉታል በቅኔ ቤት) በመጠራጠሩ እርሱ የተቀመጠባት ብቻ ተቀዳ ሰጠመ:: በሁዋላ ግን ጻድቁ ተመልሰው አውጥተው: ከሞት አስነስተውታል:: በዚህም ምክንያት 'ዘአደወ ባሕረ-ማዕበልን የተሻገረ' ይባላሉ::

+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በአርማንያ ለዘመናት ሰብከው: ሕይወተ ገዳምን አስፋፍተው: ብዙ ተአምራትን ሠርተው: በተወለዱ በ80 ዓመታቸው: በ1345 ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: በብዙ ዝማሬ በመቅደሰ #መርምሕናም ተቀብረዋል:: ዛሬ #በኢትዮዽያ: #ኤርትራ: #ግብጽና #አርማንያ ይከብራሉ::

†   🕊   አቡነ_አኖሬዎስ_ጻድቅ    🕊   †

=>እኒህ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ 'ታላቁ አኖሬዎስ' ይባላሉ:: በዚህ ስም ከሚጠሩ አባቶች ዋነኛው እኒህ ናቸው:: ተወልደው ያደጉት #ሙገር አካባቢ ሲሆን ዘመኑም 14ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው::ወላጆቻቸውም #ሰላማ እና #ክርስቶስ_ዘመዳ ይባላሉ::

+ጻድቁ ከአቡነ #ተክለ_ሃይማኖት ደቀ መዛሙርት አንዱ ናቸው:: በወንጌል ትምህርት ከመሞላታቸው ባሻገር ፍጹም መናኝ ስለ ነበሩ እጅግ ደፋር ነበሩ:: የትኛውንም ስሕተት ፊት ለፊት ይናገሩም ነበር::

+አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲያርፉ ጌታ "በአንተ ፈንታ አኖሬዎስ ቀሪ ጣዖት አምልኮን ያጠፋል" ብሎ ነግሯቸው ነበር:: ይኸውም አልቀረ ጻድቁ ከ12ቱ ንቡራነ እድ እንደ አንዱ በተመረጡ ጊዜ በደቡቡ የሃገራችን አካባቢ ክርስትናን አስፋፍተዋል::

+#ደብረ_ጽጋጋ ገዳምንም የመሠረቱ እርሳቸው ናቸው:: ዛሬ '#ኑራ_ሑሴን' እየተባለ ታሪኩ ጠልሽቶ የሚነገርለት ዋሻ የጻድቁ በዓት ነው:: አቡነ አኖሬዎስ 2ቱን ነገሥታት (#ዓምደ_ጽዮንንና #ሰይፈ_አርእድን) በመገሰጻቸው ብዙ ፈተና ደርሶባቸዋል:: ጻድቁ ብዙ ፍሬ አፍርተው በዚህ ቀን ዐርፈዋል::

†   🕊   ማር_ያዕቆብ_ግብጻዊ    🕊   †

=>በግብጽ ገዳማት ውስጥ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ተነስተው ካበሩ ቅዱሳን አንዱ ማር ያዕቆብ ነው:: ቅዱሱ ከተባረከ ቤተሰብ ተወልዶ: በሥርዓቱ አድጐ ገና በልጅነቱ ከመምህሩ ጋር መንኗል:: ከገድሉ ጽናት የተነሳ ሰይጣን በግልጽ ይፈታተነው ነበር::

+በተለይ ለ7 ዓመታት ያህል ይደበድበው መሬት ላይ ይጐትተው በጥፊ ይመታው ነበር:: እርሱ ግን በጸሎቱ መብረቅ አውርዶ አባርሮታል:: በበርሃው ምንም የሚበላ ነገር ባለ መኖሩ የዱር እንስሳትን ወተት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይጠጣ ነበር::

+ቅዱሱ ሰማዕት ለመሆን ሞክሮም ነበር:: ማር ያዕቆብ ገድሉና ተአምራቱ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ስሙ ከፍ ከፍ ብሏል:: እስኪ ጊዜውና እድሉ ካለዎት #መጽሐፈ_ስንክሳር ላይ የተጻፈውን ገድሉን እንዲያነቡ ልጋብዝዎት:: ጻድቁ ያረፈው በዚሁ ዕለት ነው::

=>አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹ ካሉበት ጉባኤ እንደ ምሕረቱ ታላቅነት ያድርሰን:: በረከታቸውንም ይሙላልን::

=>መስከረም 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
2.አቡነ አኖሬዎስ ዓቢይ
3.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
4.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
5.ቅድስት እሌኒ ንግሠት
6.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
7.ቅዱስ መርቆሬዎስ ካልዕ (ሰማዕት)
8.ቅዱስ ቶማስ ሰማዕት
9.ቅዱስ ኤፍሬም ሰማዕት
10.አባ ፊልሞስ
11.ቅዱስ ሰልሖን ሰማዕት
12.ቅዱስ አክሳኤልስ ሰማዕት
13.ቅዱስ ይስሐቅ ሰማዕት
14.ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀሲስ
15.ቅዱስ ነኪጣ ሰማዕት
16.አባ ፊላታውዎስ መንክራዊ
17.አባ ኖብ ባሕታዊ
18.አባ አትናቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት
19."60" ሰማዕታት (ማሕበረ ቅዱስ አቦሊ)

=>ወርሐዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)

+ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም #ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም . . . መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ:: + (ማቴ. 5፥13-16)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
#ቅድስት #ደብረ #ቢዘን (ኤርትራ)

#እመቤታችን በስደቷ ጊዜ ያረፈችበት፡፡
#በመካከለኛው_ዘመን እጅጉን ታዋቂ የነበረና የታላላቁ #ቅዱሳን #አባ_ፊልጶስ ፡  #አባ_ዮሐንስ እና #አባ_ናርዶስ ገዳም ነው፡፡

ዛሬ ደግሞ የታላቁ አባ ዮሐንስ ዓመታዊ በዓላቸው ነው፡፡

ከቅዱሱ ገዳምና ከሐዋርያዊው #ጻድቅ በረከት ይክፈለን፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡

=>+"+ እንኳን ለአበው "
ቅዱሳን አባ አብርሃም ወአባ ገዐርጊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+*"
#ቅዱሳን_አብርሃም_ወገዐርጊ "*+

+*" ተጋድሎተ ቅዱሳን "*+

=>ቅዱሳኑን የመሰሉ አባቶች "መስተጋድላን" ይባላሉ በግዕዙ:: ለሃይማኖታቸው እስከ ደም ጠብታና እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ መጋደላቸውን የሚያሳይ ነው:: መጋደል ጐዳናው ብዙ ዓይነት ነው::

+ከራሱ ጋር የሚጋደል አለ:: ከዓለም ጋር የሚጋደልም አለ:: የቅዱሳኑ ተጋድሎ ግን በዋነኝነት ከ2 አካላት ጋር ነው:: በመጀመሪያ ፍትወታት እኩያትን (ኃጣውዕን) ከሚያመጡ አጋንንት ጋር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ "ሃይማኖታችሁን ካዱ: ለጣዖትም ስገዱ" ከሚሉ ከሃድያን ጋር የሚደረግ ትግል ነው::

+በተለይ 2ኛው እስከ ሞት የሚያደርስ ውሳኔን ይጠይቃል:: የዚህን ቅዱስ ሕይወት ለመረዳት ግን አንድ ነገርን ልብ እንድትሉልኝ እፈልጋለሁ::

+ያለንበት ዘመን ክርስትና በራድ (ቀዝቃዛ) በመሆኑ የቀደሙ አባቶች የጸና ተጋድሎ አንዳንዴ ግራ ሲያጋባን ተመልክቻለሁ:: ቅዱሳኑ ሁሌም አንድ ነገርን እያሰቡ ይኖራሉ:: ይኼውም በዘመኑ በርካቶቻችን የረሳነው: ወይም ማስታወስ የማንፈልገው ነገር ይመስላል::

+ሰማያዊው አምላክ ከዙፋኑ ወርዶ በተዋሐደው ሥጋ በቃል ሊገለጽ የማይችል መከራን ስለ እኛ ተቀብሏል:: ክርስትና ማለት ቀራንዮን በልብ ውስጥ መሳል ነው:: ፍቅረ መስቀሉን: የጌታንም ውለታ የሚያስብ ማንኛውም ሰው: የትኛውም ዓይነት መከራ ቢመጣበት አይታወክም::

+ቅዱሳኑም የፍቅራቸውና የትእግስታቸው ምሥጢር ይኼው ነው:: ጌታችን "የሚወደኝ ቢኖር የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ" (ማቴ. 16:18) እንዳለው ቅዱሳኑ ይህንን ቃል በቃል ሲፈጽሙት እነሆ እንመለከታለን::

+*" ገዳማዊ ሕይወት "*+

=>ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::

+ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::

+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::

+ከጌታ ዕርገት በሁዋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል::

+ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ80 ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::

+ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በሁዋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኩዋሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ::

+እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል::

+አባ እንጦንስ አባ መቃርስን: አባ መቃርስ አባ ዮሐንስን ወልደዋል:: አባ ዮሐንስም የታላቁ ገዳመ አስቄጥስ አበ ምኔት ሆነው በጸጋ አገልግለዋል:: አስቄጥስ በምድረ ግብጽ የሚገኝ: በስፋቱና ብዙ ቅዱሳንን በማፍራቱ ተወዳዳሪ የሌለው የዓለማችን ቁጥር አንድ ገዳም ነው::

+ሕይወተ ምንኩስናም ወደ መላው ዓለም የተስፋፋ በዚህ ገዳም መናንያን አማካኝነት ነው:: በዚህ ገዳም ላይ የሚሾሙ አበው ደግሞ በብዛት መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸውና አባታቸውን ቅዱስ መቃርስ ታላቁን የመሰሉ ናቸውና ኃላፊነቱ እጅግ ከባድ ነው::

+በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብጽ ተወልደው ያደጉት አባ ዮሐንስ ከመነኑባት ዕለት ጀምረው በፍጹም ተጸምዶና ተጋድሎ ለፈጣሪያቸው ስለ ተገዙ የታላቁ ገዳም አበ ምኔት ሊሆኑ ተገባቸው::

+በአበ ምኔትነት ዘመናቸውም መንጋውን ይጠብቁ ዘንድ ብዙ ደከሙ:: በተለይ ቅዱስ ቃሉን ያስተምሩ ዘንድ ተጉ:: ሕይወተ መላእክትንም ያሳዩ ዘንድ በቃል ብቻ ያይደለ በተግባር ሆነው : ከመንፈሳዊ አብራካቸው ብዙ ቅዱሳንን ወለዱ::

+ከዋክብቱ አባ ገዐርጊ: አባ አብርሃም: አባ ሚናስ: አባ ዘካርያስ . . . የአባ ዮሐንስ ፍሬዎች ናቸውና:: ጻድቁ በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል:: ከዕረፍታቸው በሁዋላ እንኩዋ መግነዛቸውና የልብሳቸው እራፊ ብዙ ድውያንን ፈውሷል::

+*" #ቅዱሳን_አብርሃም_ወገዐርጊ "*+

=>እነዚህ 2 ቅዱሳን በግብጽ በርሃ ያበሩ የቅዱሱ አባ ዮሐንስ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቹ ናቸው:: አስቀድሞ ወደ በርሃ የወጣ አባ አብርሃም ሲሆን እርሱም በምድረ ግብጽ የተባረኩ ሰዎች ልጅ ነው::

+ወላጆቹ በፈቃደ እግዚአብሔር እርሱን ከወለዱ በሁዋላ ብዙ በጐነትን አሳይተዋል:: ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የችግርና የረሃብ ጊዜ) ነበርና ሃብታቸውን በምጽዋት ጨርሰዋል:: የሚገርመው የቅዱሱ አባት "ነዳያን እየተራቡ ዝም አልልም" ብሎ እየተበደረ ያበላቸው ነበር::

+እርሱ ባረፈ ጊዜም የተባረከች ሚስቱ መልካምን እየሠራች ብዙ ተፈትናለች:: ለባርነት ተማርካ እስክትሔድ ድረስም ታግሣለች:: ቅዱሱን ልጇን አብርሃምንም እንደሚገባ አሳድጋ "ሚስት ላጋባህ" አለችው::

+እርሱ ግን "እናቴ ሆይ! እኔ ይህንን ዓለም አልፈልገውም" ሲል መለሰላት:: ይህንን ስትሰማም ሐሴትን አድርጋ አብርሃምን ወደ በርሃ ሸኘችው:: አባ አብርሃምም ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሔዶ በደብረ አባ መቃርስ መነኮሰ:: ተጋድሎንም በዚያው ጀመረ::

+ሲጾም: ሲጸልይ: ሲጋደልም ዘመናት አለፉ:: በዚህ ጊዜም ታላቁ አባ ገዓርጊ ከዓለም ወደ በርሃ መጥቶ መነኮሰ:: የአባ ዮሐንስ የመንፈስ ልጆች ውስጥም እንደ አንዱ ተቆጠረ:: አባ ገዐርጊን የተመለከተው አባ አብርሃምም ስለ ወደደው አብረው መኖር ጀመሩ::

+2ቱ ቅዱሳንም "በግቢግ" በምትባል በዓታቸው በፍቅር ለፈጣሪያቸው ሲገዙ ዘመናት አለፉ:: በነዚህ ዘመናትም በርካታ ቅዱሳን ከመንፈሳዊ አብራካቸው አፈሩ ከቅድስናቸው ብዛትም ከሰንበት በቀር እህልን አይቀምሱም ነበር::

+የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አንድ ቀን ከዓለት በተወቀረች በዓታቸው ውስጥ በጸሎት ላይ ሳሉ ወረደላቸው:: የበዓታቸውን ዓለት ሰንጥቆ ሲገባ ታላቅ ግርማና ብርሃን አካባቢውን ዋጠው:: ቅዱሳኑም ለመድኃኒታችን ተደፍተው ሰገዱ::

+እርሱ አነጋግሯቸው: ባርኩዋቸው ዐርጉዋል:: ለምልክትም በዓታቸው እንደ ተሰነጠቀ ቀርቷል:: ዘወትርም በዕለተ ሰንበት ይገለጥላቸው ነበር:: ቅዱሳን አባ ገዐርጊና አባ አብርሃም በርካታ ተአምራትን ሲሠሩ ኑረዋል::
እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አቡነ ዘርዓ ቡሩክ እና 7ቱ ደቂቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

#አቡነ_ዘርዓ_ቡሩክ

=>ሃገራችን ኢትዮዽያ:-
*ብሉይ ከሐዲስ ያልጐደለባት
*በክርስቶስና በድንግል እናቱ ኪደተ እግር የተቀደሰች
*የቅዱሳን መጠጊያ እና
*ብዙ ቅዱሳንን ከእቅፏ ያፈራች ስለ ሆነች የተባረከች ሃገር ትባላለች::

+ሁሉም የሃገራችን ክፍሎች ቅዱሳንን አፍርተዋል:: በምሥራቅም: በምዕራብም: በሰሜንም: በደቡብም ያሉ አካባቢዎች ሁሉ የቅዱሳን ቤቶች ናቸው:: ቅዱሳንን በብዛት ካፈሩ አካባቢዎች አንዱ ደግሞ ምድረ ጐጃም ነው::

+በጐጃም አካባቢ ከተነሱ ቅዱሳን ደግሞ አንዱና ስመ ጥሩ ጻድቅ አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ናቸው:: አቡነ ዘርዓ ቡሩክ በብዙ ጐዳና የተለዩ አባት ናቸው:: ለመጥቀስ ያህል እንኩዋ:-

1.በታሪክ ዓለምን ከበው የያዙ 2ቱ ግሩማን አራዊት (ብሔሞትና ሌዋታንን) ጥርስ ቆጥረው: ብዙ ምሥጢራትንም ተመልክተው ተመልሰዋል:: (በነገራችሁ ላይ ይህ ጉዳይ ዛሬም ድረስ ሳይንሱ በብዙ ድካም ያልደረሰበት ነው)
2.ጻድቁ በልደታቸው ጊዜ ዓይነ ስውራንን አብርተዋል:: ለራሳቸው ግን ይህን የግፍ ዓለም ላለማየት ጸልየው ዓይናቸው እንዲጠፋ አድርገዋል::
3.መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል ቅዱስ ኢያሱ በገባኦን ፀሐይን አቁሟል:: ዘርዓ ቡሩክ ግን በጥበበ እግዚአብሔር ፀሐይን ለ5 ዓመት አቁመዋል::
4.ጻድቁ ከንጽሕናቸው ብዛት 12 ክንፍ (መንፈሳዊ ክንፍ) ተሰጥቷቸው ነበር:: ከዚህ በተረፈም በጾም: በጸሎት: በትርምትና በስብከተ ወንጌል ፍጹም ጽሙድ ነበሩ::

+ጻድቁ የተወለዱት በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን እዚያው ጐጃም ውስጥ ሲሆን አባታቸው ደመ ክርስቶስ: እናታቸው ደግሞ ማርያም ሞገሳ ይባላሉ:: ወላጆች በልጅ እጦት ተማለው ይህን የተቀደሰ ፍሬ አገኙ:: "ጸጋ ኢየሱስ" ብለውታል:: ከኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥቷቸዋልና::

+ቀጥሎ የወለዱትንም "ተስፋ ኢየሱስ" ብለውታል:: ይህም የጻድቁ ታናሽ ወንድም ነው:: በሒደት ግን የጸጋ ኢየሱስ ስም በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ ዘርዓ ቡሩክነት ተቀይሯል:: ጻድቁን ስመ ጥር ካደረጉዋቸው ሥራዎቻቸው መካከል በአፄ ሱስንዮስ ዘመን የሠሩት ቅድሚያውን ይወስዳል::

+ነገሩ እንዲህ ነው:: በ1598 ዓ/ም በኢትዮዽያ ላይ የነገሡት አፄ ሱስንዮስ ዼጥሮስ ፓኤዝ (ፔድሮ ፓኤዝ) ከሚባል ፈረንጅ መናፍቅ ጋር በፈጠሩት ወዳጅነት ሃይማኖታቸውን ለወጡ:: ካቶሊክ (ሮማዊ)ም ሆኑ::

+በሁዋላም አልፎንሱ ሜንዴዝ የሚሉት እሾህ መጥቶ ሁሉም የኢትዮዽያ ሕዝብ መናፍቅ እንዲሆን ከንጉሡ ጋር መከረ:: ለጊዜው በቤተ መንግስቱ አካባቢ የነበሩ መሣፍንት ተቀላቀሉ:: እየቆየ ግን ዜናው በመላ ሃገሪቱ ተሰማ::

+በተለይ በ1611 በተዋሕዶ አማኞችና በመናፍቁ ንጉሥ መካከል ነገሩ ተካሮ ዻዻሱ አቡነ ስምዖን ጠዳ ላይ መገደላቸው ተሰማ:: በዚህ ጊዜ ገበሬው ከእርሻው: ሴቷ ከማዕድ ቤት: ካህኑ ከመቅደሱ: ነጋዴው ከገበያው እየወጡ ስለ ቀናችው ሃይማኖት ደማቸውን አፈሰሱ::

+በበዓት የተወሰኑ በሺህ የሚቆጠሩ ቅዱሳንም ወጥተው ተሰየፉ:: በዚህ ጊዜም የግሺው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ዳዊታቸውን አንግበው ለሰማዕትነት ሔዱ:: ዓባይ ወንዝ ላይ ሲደርሱ ዳዊታቸውን ወደ ወንዙ ውስጥ ጣሉት::

+ተሻግረውም ከንጉሡ አደባባይ ደንቀዝ ደረሱ:: በጊዜውም ልክ እንደነ ፍቅርተ ክርስቶስና ወለተ ዼጥሮስ እርሳቸውም መከራ ደረሰባቸው:: ንጉሡም ሳይገደሉ እንዲታሠሩ አደረገ:: በጨለማ እስር ቤትም 5 ዓመታትን ሲያሳልፉ ትኩስ ምግብን ያመጡላቸው ነበር::

+እርሳቸው ግን ምግባቸው ሰማያዊ ነበርና አልነኩትም:: ከ5 ዓመት በሁዋላም ያ ሁሉ ምግብ በተአምራት በትኩስነቱ እየጨሰ ተገኝቷል:: ዘርዓ ቡሩክም ከእሥር ተፈትተዋል::
+እግዚአብሔርም በከሐዲው ንጉሥ ላይ ፈርዶ ፋሲል ነግሷል: ሃይማኖት ተመልሷል:: ጻድቁም በዓባይ ወንዝ ላይ የጣሉት ዳዊታቸውን ሳይርስ አግኝተውታል::

+ጐጃም ሲደርሱም ሰይጣን እርሳቸውን መስሎ ሲያስት ስላገኙት ወደ ጥልቁ አስጥመውታል:: በተረፈ ዘመናቸው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ብዙ ተጋድለው ጥር 13 ቀን ዐርፈዋል:: ታኅሳስ 13 ቀን ልደታቸው ነው::

<< ድንቅ ሠሪ አባት ናቸውና ዛሬም በግሺ ብዙ ተአምራት ይደረጋሉ >>

+" #ቅዱሳን_7ቱ_ደቂቅ "+

=>እነዚህ 7 ቅዱሳን ከዘመነ ሰማዕታት እስከ ዘመነ ጻድቃን የተዘረጋ ታሪክ አላቸው:: 7ቱም ባልንጀሮች ሲሆኑ በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን በኤፌሶን ተወልደው አድገዋል:: ክርስትናን ተምረውም በወጣትነታቸው የንጉሥ ጭፍሮች ሁነዋል:: የተቀጠሩትም የቤተ መንግስቱን ግምጃ ቤት ለመጠበቅ ነው::

+በሥራቸውም ሆነ በጠባያቸው ደጐች ነበሩና ንጉሡ ዳኬዎስም: ሕዝቡም ይወዷቸው ነበር:: እነርሱ ግን በጉብዝና ወራት ፈጣሪን ማሰብን መርጠው በፍቅር: በጸሎትና በምጽዋት ይተጉ ነበር:: ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ ግን ጭንቅ መከራ መጣ::

+ንጉሡ ዳኬዎስ ክርስትናውን ትቶ ጣዖት አምላኪ ሆነ:: አዋጅም አስነገረ:: አዋጁም "ክርስቶስን ያልካደ: ለጣዖትም ያልሰገደ: ሃብት ንብረቱ ለዘረፋ: እጅ እግሩ ለእስር: ደረቱ ለጦር: አንገቱ ለሰይፍ: ቤቱም ለእሳት ይሰጣል" የሚል ነበር:: በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ::

+የበርካቶቹም ደማቸው ፈሰሰ:: ኤፌሶን የግፍና የአመጻ ከተማ ሆነች:: የመከራ ጽዋው ጊዜውን ጠብቆ ወደ 7ቱ ወጣቶች ዘንድ ደረሰ:: ንጉሡ እነሱንም አስጠርቶ "ለጣዖት ስገዱ" አላቸው:: እነርሱ ግን የአምላካቸውን ፍቅር በዋዛ የሚቀይሩ አልነበሩምና "እንቢ" አሉት::

+ንጉሡ ምንም ክፉና አውሬ ቢሆንም ይወዳቸዋል:: ሊገድላቸው አልፈለገምና አሳሰራቸው:: ከቀናት በሁዋላ አስጠርቶ ሊያታልላቸው ሞከረ:: ግን አልተሳካለትም:: በዚያ ወራት ጦርነት ይበዛ ነበርና ግዛት ለማስፋትም ቢሉ ለማስገበር ዳኬዎስ ወጣ::

+ከመውጣቱ በፊት ግን 7ቱን አስጠርቶ "አሁን ከእስር ፈትቻቹሃለሁ:: ከጦርነት እስክመለስ ከልባችሁ ጋር ምከሩ:: ካልሆነ ሞት ይጠብቃቹሃል" ብሏቸው ነበር የወጣው:: ቅዱሳኑ ንጉሡ እንደ ወጣ ተቀምጠው መከሩ:: ውሳኔንም አስተላለፉ::

+ዓለምን ንቀው: ሃብት ንብረታቸውን መጽውተው: ትንሽ ሳንቲም ብቻም ይዘው በድብቅ ወጡ:: አንድ ወታደር (በጐች አሉት) ይከተላቸው ነበርና የት እንደ ገቡ ተመለከተ:: ቅዱሳኑ ዘወትር በመዓልትና በሌሊት በበዓታቸው ውስጥ ይተጉ ነበር:: ከእነሱም አንዱ በተራ እየወጣ ቂጣ ይገዛ ነበር::

+አንድ ቀን ግን ከእነሱ አንዱ ራት ሊገዛ ሲወጣ ንጉሡ መመለሱን ሰማ:: ወደ በዓቱ ተመልሶ ለወንድሞቹ ነገራቸው:: ከዚያች ቀን በሁዋላ 7ቱም አልወጡም:: በዓታቸውን ዘግተው ሲጸልዩ ደክሟቸው ተኙ:: ከዚያች ቀን በሁዋላ ግን አልነቁም::

+ያ የበጐች ባለቤት (ወታደር) ለብዙ ቀናት አለመውጣታቸውን ሲመለከት "ሙተዋል" ብሎ አዘነ:: በድብቅ ክርስቶስን ያመልከው ነበርና:: እርሱ የቅዱሳኑን ተጋድሎ በድንጋይ ሰሌዳ ላይ ጽፎ ወደ በዓታቸው ውስጥ ጣለው::

+ትልቅ ድንጋይም አምጥቶ ገጠመው:: እነዚህ ቅዱሳን ተኝተዋልና አልነቁም:: ቀናት: ወራት: ዓመታት ተዋልደው ለ372 ዓመት ተኙ:: አንድ ቀን አንድ እረኛ ለሥራ ፈልጐት ድንጋዩን ፈነቀለው:: በዚህ ጊዜ ቅዱሳኑ ነቁ::

+በወቅቱ መልካቸው የወጣት ነው:: እድሜአቸው ግን 400 ሊሞላ ትንሽ ቀርቶት ነበር:: ልክ እንደ አቤሜሌክ ብዙ መተኛታቸው አልታወቃቸውምና ከመካከላቸው አንዱ የራት ዳቦ ሊገዛ ቢወጣ ግራ ተጋባ:: ኤፌሶን የማያውቃት ሌላ ሃገር ሆነችበት:: ከተማዋ ዘምናለች::
#መጋቢት_14

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ዐሥራ አራት በዚህችም ቀን #ቅዱስ_ቶማስ ሐዋርያ በአንዲት ሴት ላይ ተአምራትን አደረገ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #የቅዱስ_ቄርሎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ፣ ከአረጋውያን ፍጹማን መነኰሳት ውስጥ አንዱ #ቅዱስ_አባ_ባጥል አረፈ፣ #ቅዱስ_አባት_አባ_ሲኖዳ በሰማዕትነት አረፈ፣ የከበሩ #ቅዱሳን_አጋንዮስ_አውንድርዮስና_ብንድዮስ በሰማዕትነት አረፉ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቶማስ_ሐዋርያ

መጋቢት ዐሥራ አራት በዚህችም ቀን ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ ሰባት ዓመት ያህል የጋኔን ግንኙነት በአስቸገራት በአንዲት ሴት ላይ ተአምራትን አደረገ። ሐዋርያ ቶማስንም የችው ጊዜ የክርስቶስ ሐዋርያው ሆይ እጅግ ከሚያሠቃየኝ ጠላት አድነኝ ብላ ወደርሱ ጮኸች።

እርሱም በምን ምክንያት አገኘሽ አላት እርሷም ከመታጠቢያ ከውሽባ ቤት ስወጣ እንደ ሰው ድው ድው እያደረገ በመታወክ መጣ ድምጡም ሰላላና ቀጪን ነው በሴትና በወንድ ሥራ ሁሉ ነይ እርስበርሳችን አንድ እንሁን አለኝ በተኛሁም ጊዜ በሌሊት መጥቶ ከእኔ ጋራ አንድ ሆነ ብሸሽም አይተወኝም መጥቶ ያሠቃየኛል እንጂ እኔም ከጸሎትህ የተነሣ አጋንንት እንደሚንቀጠቀጡ አውቃለሁና ጸልይልኝ አድነኝም አለችው።

ሐዋርያ ቶማስም ሰምቶ ጸለየ ጋኔኑንም ከእርሷ እንዲወጣ አዘዘው ያንጊዜም በእሳትና በጢስ አምሳል ከሴቲቱ ላይ ወጥቶ ተበተነ ከዚህ በኃላ በክርስቶስ መስቀል በላይዋ አማተበ ሥጋውንና ደሙንም አቀበላት ወደ ዘመዶቿም አሰናበታት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#የቅዱስ_ቄርሎስ

በዚህች ቀን በእስክንድርያ ለተሾሙ አባቶች ሰባ አምስተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የቅዱስ ቄርሎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። እርሱም በምግባሩ ፍጹም ዐዋቂ ሆነ ሀገሩም ፍዩም ይባላል በእርሷም ቅስና ተሹሞባት ነበር።

ከዚያም ለቆ ወደ አባ ፊቅጦር ገዳም ደረሰ እርሱም ከምስር ከተማ ውጭ የኢትዮጵያውያን ዐዘቅት የዐባይ ግድብ በአለበት ነው። በዚያም ታላቅ ገድልን እየተጋደለ ብዙ ዘመናትን ኖረ። ብዙ መጻሕፍትንም ተምሮ ትርጓሜያቸውንና ምሥጢራቸውን ጠንቅቆ ዐወቀ።

አሸናፊ ወደሚባለውም ንጉሥ አደባባይ ቀርቦ የእስላሞች ታላላቅ ሊቃውንቶቻቸውና ከምሁራኖቻቸው ውስጥ መምህሮቻቸው ተከራከሩት። ጠቃሚ የሆነ ዕውቀት የተመላበትን መልስ አገኙ የሚጠይቁትንም ሁሉ በመልካም አመላለስ ነገራቸው።

ከዚህ በኃላ የዕውቀቱና የቅድስናው ዜና በተሰማ ጊዜ ያለ ፈቃዱ ይዘው በእስክንድርያ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት መንጋውንም ጠበቀ በጸሎትና በቅዳሴ ያገለግሉ ዘንድ ለካህናት ሥርዓትንና መመሪያን ሠራ። ይህም አባት በሊቀ ጵጵስናው ሰባት ዓመታት ከዘጠኝ ወር ከዐሥር ቀኖች ኖረ። ከቀኑም በሦስት ሰዓት አረፈ በምስክርነት አደባባይም ተቀበረ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ባጥል

በዚህችም ዕለት ከአረጋውያን ፍጹማን መነኰሳት ውስጥ አንዱ አባ ባጥል አረፈ። ይህም ቅዱስ ሰው አባ ዮሐኒ የተባለ አበምኔት በመነኰሳት ላይ ነገረ ሠሪን እንደ ሚቀበል በሰማ ጊዜ በዓቱን ትቶ ወደ እስክንድርያ መጥቶ የሴት አዳሪዎችንና የአመንዝራዎችን ሁሉ ስማቸውን ጻፈ።

ከኪራይ ሠራተኞችም ጋራ ሲሠራ ይውላል። ደመወዙን በተቀበለ ጊዜ የሽንብራ ቂጣ ግዝቶ ይበላል የቀረውንም ገንዘብ ይዞ ወደ አንዲቱ ሒዶ ይሰጣታል በዚች ቀን ከአንቺ ጋራ አድራለሁና ራስሽን ለእኔ አዘጋጂ ይላታል። ከኃጢአትም ሊጠብቃት ከእርስዋ ዘንድ ያድራል ሌሊቱን ሁሉ ተነሥቶ ሲጸልይና ሲሰግድ እግዚአብሔርንም ሲለምን ያድራል ሲነጋም ሥራውን ለማንም እንዳትገልጥ አምሏት ወደ ተግባሩ ይሔዳል።

በየዕለቱም ወደ አመንዝራዎቹ እየሔደ እንዲህ ያደርግ ነበር አንዲቱም ሴት ምሥጢሩን ገለጠች ጋኔንም ይዞ አሳበዳት። ሰዎችም ስለዚህ ክፉ ሽማግሌ ክፉ ሥራ የለበትም ብላ ዋሽታለችና እግዚአብሔር መልካም አደረገባት ተባባሉ። እርሷም እንዳናመነዝር ገንዘብ በመስጠት ከኃጢአት ይጠብቀናል እንጂ ነውር የለበትም ብላ ነበርና።

የቀሩት አመንዝራዎች በእርሷ ላይ የሆነውን በአዩ ጊዜ ደነገጡ እንደርሷም እንዳያብዱ እውነቷን ነው ማለትን ፈሩ። እርሱም ይችስ በእገሌ ዕለት ትጠብቀኛለች ይል ጀመረ ሰዎችም ሁሉ ያሙት ጀመር እርሱም እንደ ሰው ሁሉ ሥጋ የለኝምን ወይስ እግዚአብሔር መነኰሳትን ተቆጥቶ በፍትወት ተቃጥለው እንዲሞቱ ትቷቸዋልን አላቸው።

እነርሱም ልብስህን ለውጠህ ሚስት አግባ ይህ ይሻልሃልና አሉት። እርሱም አዎን ብወድ በሚስቴ እጠነቀቃለሁ በዚህም በክፉ አኗኗር እኖራለሁ እናንተ ግን ከእኔ ዘንድ ሒዱ ምን ትሻላችሁ በእኔ ላይ እግዚአብሔር ፈራጆች አድርጓችኃልን ይልቁንስ እናንተ እንዳይፈረድባችሁ ለራሳችሁ አስቡ ፈራጅ አንድ ነውና ዕለቲቱም አንዲት ናትና አላቸው ይህም ቅዱስ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አገኘ በሰው ዘንድ ግን የተናቀ ሁኖ ኖረ።

ከእርሱ ጥቅም የአገኙ አመንዝራዎችም ዝሙታቸውን ተው። ከእርሳቸውም ሕራዊ ጋብቻ ተጋብቶ የኖረ አለ ወደ ገዳምም ገብቶ መንኵሶ በጾም በጸሎት ተወስኖ የኖረ አለ። በአንዲት ዕለትም ከአንዲት አመንዝራ ቤት ሲወጣ ያቺን ሴት አስቀድሞ የለመዳት አንድ ሰው አገኘውና ይህ ሽማግሌ እስከ መቼ ድረስ በዚህ በክፉ ሥራ ይኖራል ብሎ ፊቱን በጥፊመታው።

ከዚህም በኃላ በአንዲት ቀን በበዓቱ ውስጥ ሰግዶ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጥቶ በቤቱም መድረክ የዚች አገር ሰዎች ጊዜው ሳይደርስ በማንም ላይ አትፍረዱ እንዳይፈረድባችሁ የሚልም ጽሑፍ ተጽፎ ተገኘ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_አባ_ሲኖዳ

በዚህችም ቀን ደግሞ ቅዱስ አባት አባ ሲኖዳ በሰማዕትነት አረፈ። እርሱም በግብጽ አገር ከብሕንሳ ከተማ ነው ወደ መክስምያኖስም ክርስቲያናዊ ሲኖዳ አማልክትን የማያመልክ ነው ብለው ነገር ሠሩበት። እርሱም አስቀርቦ ስለ ሃይማኖቱ ጠየቀው በንጉሡም ፊት በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ እርሱም ዕውነተኛ አምላክ እንደ ሆነም መሰከረ፡፡ መክስምያኖስም ይህን የከበረ አባ ሲኖዳን በምድር ላይ ዘርግተው በበትሮች እንዲደበድቡት አዘዘ። ዐጥንቶቹ እስቲሠነጠቁ ደሙም በምድር ላይ እንደ ውኃ እስቲፈስ እንዲሁ አደረጉበት።

ከዚህም በኃላ እግሩን ይዘው ጎትተው ወስደው ሽታው በሚከረፋ በጨለማ ወህኒ ቤት ጣሉት የእግዚአብሔርም መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ተገለጠለት። ቊስሎቹንም አድኖ ጤነኛ አደረገው አበረታውም በርታ አትፍራ ስለ መከራህም የክብር አክሊል ተዘጋጅቶልሃልና ደግሞም በጽኑዕ ሥቃይ ትሠቃይ ዘንድ አለህ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ እኔም ከአንተ ጋራ እኖራለሁ አለው ከዚያም ከእርሱ ተሠወረ።

በነጋ ጊዜም የነገሥታትን ትእዛዝ የሚተላለፍ ያንን ዐመፀኛ ሒዳችሁ እዩት ሙቶም ከሆነ ለውሾች ጣሉት ብሎ መክስምያኖስ ወታደሮቹን አዘዘ። ወደርሱም በደረሱ ጊዜ ቁሞ ሲጸልይ አግኝተውት ያለምንም ጥፋት ጤነኛ እንደሆነና በሥጋውም ውስጥ የሕማም ምልክት እንደሌለ እርሱም ከቶ ምንም ሥቃይ እንዳላገኘው እንደ ጤነኛና ደስ እንዳለው ሰው ተግቶ እንደሚጸልይ ስለርሱ ለንጉሡ ነገሩት።

ንጉሡም ወደርሱ አስመጣው ከሕይወቱም የተነሣ አደነቀ ልብሶቹንም አስወልቆ ያለጉዳት ጤነኛ እንደሆነ ሥጋውን አየ ደንግጦም ይህ ያየሁት ሥራይ ታላቅ ነው አለ። ከዚያም ዘቅዝቀው ሰቅለው ከበታቹ እሳትን እንዲአነዱ አዘዘ ይህንንም አደረጉበት ደግሞ በመንኰራኩር አሠቃዩት በአለንጋዎችም አብዝተው ገረፉት ደበደቡትም።
ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ቆርጠው ለውሾች እንዲጥሉት አዘዘ ውሾች ግን ፈጽሞ አልቀረቡትም ሌሊትም ሲሆን ምእመናን መጥተው ሥጋውን ወሰዱ በአዳዲሶች ልብሶችና በጣፋጭ ሽቶዎች ገነዙት በሣጥንም አድርገው ቀበሩት።ከሥጋውም ብዙዎች አስደናቂዎች ተአምራቶች ተደረጉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አጋንዮስ_አውንድርዮስና_ብንድዮስ

በዚህችም ቀን ደግም የከበሩ አጋንዮስ አውንድርዮስና ብንድዮስ በሰማዕትነት አረፉ። እሊህም ቅዱሳን ከአባቶቻቸው ጀምሮ ክርስቲያኖች ናቸው አምላካዊ ትምህርትንም ሁሉየተማሩ ናቸው።

በእግዚአብሔርም ሕግ ጸንተው ሲኖሩ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አርሞስ መርጦ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ ሾማቸው ግን በታወቁ ቦታዎች ላይ አይደለም በብዙዎች አገሮች ውስጥ እንዲሰብኩ ላካቸው እንጂ። በሀገሮችም ያሉ ከሀዲያን ያዙአቸው ያለርኀራኄም አብዝተው ገረፉአቸው በደንጊያም ወገሩአቸው ነፍሳቸውንም በጌታችን እጅ ሰጡ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)