መዝገበ ቅዱሳን
23.4K subscribers
1.95K photos
9 videos
6 files
26 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡

እንኳን አደረሳችሁ

ርክበ ካህናት

=>ይህቺ ዕለት በቤተ ክርስቲያን "ርክበ ካህናት" : "ዕለተ ጥብርያዶስ" በመባል ትታወቃለች:: "ዳግሚት ዕለተ አግብኦተ ግብር" የሚሏትም አሉ::

+ #ርክበ_ካህናት በቁሙ "የካህናት ኖሎት (እረኞች) መገናኘትን" የሚመለከት ቃል ነው:: #የክብር_ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በሁዋላ ለደቀ መዛሙርቱ በየጸጋቸው መጠን እየተገለጠ ያጽናናቸው ያጸናቸው : ያስተምራቸው : ይባርካቸውም ነበር::

+እስከ ዕርገቱ ባሉ 40 ቀናትም መጽሐፈ ኪዳንን : ትምሕርተ ኅቡዓትን : ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን አስተምሯቸዋል:: በልቡናቸውም አሳድርድሮባቸዋል::

+#ቅዱስ_መጽሐፍ እንደሚል ደግሞ ከዕርገቱ አስቀድሞ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ 3 ጊዜ በጉባኤ ተገልጧል::
1.የትንሳኤ (ዮሐ. 20:19)
2.የአግብኦተ ግብር {ዳግም ትንሳኤ} (ዮሐ. 20:26)
3.የጥብርያዶስ /ዛሬ/:: (ዮሐ. 21:1)

+በተረፈው ግን ለድንግል ማርያም ሁሉን ዕለታት መገለጡን አበው ያስተምራሉ::

+በዚህች ዕለት በቅዱስ ዼጥሮስ መሪነት ሐዋርያቱ ወደ ጥብርያዶስ ሔዱ:: አሶችን ሊያጠምዱም በብዙ ደከሙ:: ነገር ግን ጌታችን በረድኤት አብሯቸው አልነበረምና አንዳች አሣ በመረባቸው ሊገባ አልቻለም::

+ማጥመድ (አስተምሮ ከክህደት ወደ ሃይማኖት : ከኃጢአት ወደ ጽድቅ መመለስ) የሚቻለው በረድኤተ እግዚአብሔር እንጂ በእውቀት ብዛት ወይም በአንደበተ ርቱዕነት ብቻ አይደለምና::

+ሲነጋ ግን #መድኃኒታችን ወደ ቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱ መጣ:: በጥብርያዶስ ባሕር ዳርቻም ቆሞ ታያቸው:: ከሚወደው ደቀ መዝሙሩ #ቅዱስ_ዮሐንስ በቀር የለየው ግን አልነበረም::

+ቸሩ አባት "ልጆቼ! አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁ?" ሲል ጠየቀ:: "ጌታ ሆይ! የለም" አሉት:: "የለንም" ብሎ የሌለንን ነገር በጌታ ፊት ማመኑ እጅግ መልካም ነው:: ምክንያቱም ያጣነውን ነገር ያን ጊዜ ሊጠቁመን ቸርነቱ ብዙ ነውና::

+ያን ጊዜ ሐዋርያቱን መረባቸው በመርከብ ቀኝ እንዲጥሉ አዘዛቸው:: እነርሱም በደስታ ጣሉ:: በአግራሞት እስኪሞሉ ድረስ : መረባቸውም ሊቀደድ እስኪደርስ ድረስ 153 ዓሦች ተያዙላቸው::

+ያን ጊዜም የሚወደው ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ ዮሐንስ ምስጢር አወጣ:: ለቅዱስ ዼጥሮስ "#ጌታ እኮ ነው" አለው:: ሽማግሌው ቅዱስ ግን ራቁቱን ነበርና ወደ ባሕሩ ተወረወረ::

+ከአፍታ በሁዋላም ጌታችን ከሐዋርያቱ ጋር በድጋሚ (ለ2ኛ ጊዜ) ለምሳ ተቀመጠ:: ባርኮ ሰጥቶ : ልባቸውን ሊያጸና አብሯቸው በላ::
*በዚያች ሰዓት ቅዱስ ዼጥሮስን 3 ጊዜ "ትወደኛለህን?" ሲል ጠየቀው:: ቅዱሱ አረጋዊም እየደጋገመ "ለሊከ ተአምር ከመ አነ አፈቅረከ (እንድወድህ አንተ ታውቃለህ)" ሲል መለሰ::

+ጌታም በበጐች ሐዋርያት (ካህናት) : በጠቦቶች አርድእት (ዲያቆናት) : በአባግዕት 36ቱ ቅዱሳት አንስት (ምዕመናን ወምዕመናት) ላይ ሁሉ እረኛ እንዲሆን ሾመው::

+ቀጥሎም የሰማዕትነቱን ምስጢር ገልጦለት "ተከተለኝ" (ለጊዜው በእግር : በሁዋላ ግን በግብር ምሰለኝ) ብሎታል:: ወልደ ነጐድጉዋድ ወፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስም ሞትን እንደማይቀምስ እንዲሁ ተናግሮለታል::

+ይህች ዕለትም እነዚህ ሁሉ ተግባራት የተከናወኑባት ናትና በእጅጉ ትከበራለች:: አባቶቻችን ዻዻሳትም ከጌታና ከደቀ መዛሙርቱ አብነትን ነስተው በዚህች ቀን 2ኛውን ታላቅ ሲኖዶስ ያደርጋሉ:: መንፈስ ቅዱስ እየተራዳቸው ለቤተ ክርስቲያንና ለኛ ለልጆቿ የሚጠቅም መመሪያን ያወጣሉ ብለን እንጠብቃለን::

+በተለይ ደግሞ በአምናው ርክበ ካህናት ስለ #28ቱ_ኢትዮዽያውያን_ሰማዕታት የሚባለውን ሁሉ ተስፋ አድርገን ነበር:::: #ከከዋክብት_ሰማዕታት ጋር ዜናቸውን ለመደመር (ለመመስከር) እጅጉን ናፍቀንም ነበር:: ዘንድሮም አዲስ ነገር ካለ ብንሰማ ደስ ይለናል::

+በተረፈው ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን የወረራት የጠላትን ጦር የሚሰብር : ምክራቸውን የሚመክት : ክፋታቸውን የሚያኮላሽ ውሳኔ ከአባቶቻችን እንጠብቃለን:: መንጋው ባዝኗልና:: እረኝነት የተሰጣቸው አባቶቻችን እንዲነቁልንም ከተስፋ ጋር እንማጸናለን::

=>የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መንፈሱ ከአባቶቻችንና ከእኛ ከኃጥአኑ ጋር በረድኤት ይኑር::

ከበዓሉ በረከትም ያድለን !!

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>