ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ነሐሴ_18

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ስምንት በዚህች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_እለእስክንድሮስ አረፈ፣ የከበረና የተመሰገነ ሐዋርያ #ቅዱስ_እንድራኒቆስ መታሰቢያው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_እለእስክንድሮስ

ነሐሴ ዐሥራ ስምንት በዚህች ቀን ቁጥሩ ከአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስ አረፈ። ይህም አባት ከአርዮስ ወገኖች ብዙ ችግር ደርሶበታል እርሱ ከወገኖቹ ጋር ሁኖ አርዮስን አውግዞ ከቤተክርስቲያን አሳዶት ነበርና።

በታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ዘመን በኒቅያ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶች ሊቃውንት አርዮስን በጉባኤ አውግዘው ከቤተ ክርስቲያን ለይተው በአሳደዱት ጊዜ ወደ ንጉሡ ቈስጠንጢኖስ ጓደኞቹን ይዞ ገብቶ በእለእስክንድሮስና በአትናቴዎስ ላይ ነገር ሠራ ሁለተኛም እለእስክንድሮስ ከካህናቱ ጋር ይቀበለው ዘንድ እንዲያዝለት ንጉሡን ለመነው።

ንጉሡም ልመናውን ተቀብሎ መልእክተኞችን ልኮ አባት እለእስክንድሮስን አስመጥቶ እንዲህ አለው "አትናቴዎስ ትእዛዛችንን በመተላለፍ አርዮስን አልቀበልም ብሏል፤ እኛም አንተን እንዳከበርንህ አንተ ታውቃለህ አሁንም ትእዛዛችንን አትተላለፍ አርዮስንም ከውግዘቱ ፈትተህ ልባችንን ደስ አሰኝ" አለው ።

ቅዱስ እለእስክንድሮስም ለንጉሥ እንዲህ ብሎ መለሰለት "አርዮስን እኮን ቤተክርስቲያን አልተቀበለችውም። ልዩ ሦስትነትን አያመልክምና" ንጉሡም "አይደለም እርሱ በ #ሥሉስ_ቅዱስ ያምናል እንጂ" አለው ቅዱስ እለእስክንድሮስም " #ወልድ በመለኮቱ ከ #አብ#መንፈስ_ቅዱስ ጋራ ትክክል እንደሆነ የሚያምን ከሆነ በእጁ ይጻፍ" ብሎ መለሰለት።

ንጉሥም አርዮስን አስቀርቦ "ትክክለኛ ሃይማኖትህን ጻፍ" አለው አርዮስም በልቡ ሳያምን ' #ወልድ#አብ ጋራ በመለኮቱ ትክክል ነው' ብሎ ጻፈ በሐሰትም የከበረ ወንጌልን ይዞ ማለ። ንጉሡም ቅዱስ እለእስክንድሮስን "አሁን በአርዮስ ላይ ምክንያት አልቀረህም ትክክለኛ ሃይማኖቱን ጽፎአልና በከበረ ወንጌልም ምሎአልና" አለው ።

አባ እለእስክንድሮስም ንጉሡን እንዲህ አለው "በአባትህ በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እጅ የተጻፈ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ አባቶች በእጆቻቸው የጻፉትን እርሱንና ወገኖቹን ከቤተ ክርስቲያን እንዳሳደዷቸው የአርዮስን ክህደቱንና ውግዘቱን አትናቴዎስ አንብቦታል። ነገር ግን አንድ ሱባዔ በእኔ ላይ ታገሥ በዚህ ሱባዔ በአርዮስ ላይ አንዳች ነገር ካልደረሰ ይህ ካልሆነ ሃይማኖቱ መሐላውም እውነት ነው እኔም ተቀብዬ ከካህናቱ ጋር እቀላቅለዋለሁ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም ከእሳቸው ጋራ አንድ ይሆናል።"

ንጉሡም አባት እለእስክንድሮስን እንዲህ አለው "እወቅ እኔ ስምንቱን ቀኖች እታገሥሃለሁ አርዮስን ካልተቀበልከው በአንተ ላይ የፈለግሁትን አደርጋለሁ።" ከዚህም በኋላ ከንጉሡ ዘንድ ወጥቶ ወደ ማደሪያው ሔደ ቤተክርስቲያንን ከአርዮስ መርዝ ያድናት ዘንድ በዚያ ሱባዔ እየጾመና እየጸለየ ወደ #እግዚአብሔር ሲለምን ሰነበተ።

ከዚያም ሱባዔ በኋላ አርዮስ መልካም ልብስን ለበሰ ወደ ቤተክርስቲያንም ገብቶ በመሠዊያው ፊት ከካህናቱ ጋራ ተቀመጠ። ከዚህም በኋላ አባ እለእስክንድሮስ እያዘነና እየተከዘ ገባ ከኀዘኑም ብዛት የተነሣ የሚሠራውን አላወቀም የቅዳሴውንም ሥርዓት ሊጀምር ቆመ። ያን ጊዜ የአርዮስ ሆዱ ተበጠበጠና ወጥቼ ልመለስ አለ ይህንንም ብሎ ወደ መጸዳጃ ቦታ ወጣ። ሊጸዳዳም በተቀመጠ ጊዜ አንጀቱና የሆድ ዕቃው ሁሉ ወጣ በዚያውም ላይ ሞተ።

በዘገየም ጊዜ ሊፈልጉት ወጡ በመጸዳጃውም ቦታ ሬሳውን ወድቆ አገኙት። ለዚህም ለአባት እለእስክንድሮስ ነገሩት እርሱም አደነቀ የከበረች ቤተክርስቲያኑን ያልጣላት ምስጉን የሆነ #ክርስቶስንም አመሰገነው።

ንጉሡም በሰማ ጊዜ አደነቀ ከሀዲ አርዮስም በሐሰት እንደማለና በሽንገላ እንደጻፈ አወቀ። የዚህንም አባት የእለእስክንድሮስን ቅድስናውን ዕውነተኛነቱ ሃይማኖቱም የቀናች መሆኗን የአርዮስንም ሐሰተኛነቱንና ከሀዲነቱን ተረዳ።

አንድ የሆነ #አብ_ወልድ_መንፈስ_ቅዱስንም አመሰገነው መለኮታቸውም አንድ እንደሆነ ታመነ።

ይህም አባት በበጎ ሥራ ጸንቶ ኖረ ለምለም ወደ ሆነ እርጅናም ደርሶ ወደ ወደደው #ክርስቶስ ሔደ የሕይወት አክሊልንም አገኘ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_እንድራኒቆስ

በዚህችም ቀን የከበረና የተመሰገነ ሐዋርያ እንድራኒቆስ መታሰቢያው ነው። ይህንንም ሐዋርያ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መረጠው። እርሱም የ #እግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩ ጌታ ከመከራው በፊት ከላካቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የተቆጠረ ነው።

በጽርሐ ጽዮንም #መንፈ_ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋራ የ #መንፈስ_ቅዱስን ስጦታ ተቀብሎ በብዙ አገሮች ውስጥ ሰበከ። በኒውብያ አገር ላይም ሐዋርያት በአንብሮተ እድ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት በውስጧም ሰበከ በጨለማ በድንቁርና የሚኖሩ ብዙዎች አረማውያንንም የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖት አስገባቸው።

ከዚህም በኋላ ሐዋርያ ዮልዮስን ወሰደው በአንድነትም በብዙ አገሮች ዙረው አስተማሩ። ብዙ ሰዎችንም አጠመቁ ተአምራትንም በማድረግ ከሰዎች ላይ አጋንንትን አባረሩ። ብዙዎች በሽተኞችንም ፈወሱአቸው የጣዖታትንም ቤቶች አፍርሰው የክብር ባለቤት የሆነ የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናትን አነፁ። አገልገሎታቸውንም በፈጸሙ ጊዜ #ጌታችን ከድካም ወደ ዕረፍት ከኀዘንም ወደ ደስታ ሊወስዳቸው ወደደ።

ከዚህ በኋላ ሐዋርያ እንድራኒቆስ ታመመና ግንቦት ሃያ ሁለት ቀን አረፈ ቅዱስ ዮልዮስም ገንዞ በመቃብር አኖረው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_18 ና_ዘወርኀ_ግንቦት_22)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_18_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ፊልጵስዩስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው።
² ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ።
³ እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና።
⁴ እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ።
⁵ በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
² እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።
³ ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን።
⁴ አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።
⁵ ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤
⁶ በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።
⁷ ወንድሞች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረቻችሁ አሮጌ ትእዛዝ እንጂ የምጽፍላችሁ አዲስ ትእዛዝ አይደለችም፤ አሮጌይቱ ትእዛዝ የሰማችኋት ቃል ናት።
⁸ ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል።
⁹ በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ።
¹⁰ ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤
¹¹ ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና።
¹² ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
¹³ አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
¹⁴ አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ።
¹⁵-¹⁶ ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።
¹⁷ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።
¹⁸ ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።
¹⁹ ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁸ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
²⁹-³⁰ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።
³¹ ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_18_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ዘዐበያ ለበረከት ወትርኅቅ እምኔሁ። ወለብሳ ለመርገም ከመ ልብስ ወቦአ ከመ ማይ ውስተ አማዑቱ። መዝ.108÷17-18
"መርገምን ወደደ ወደ እርሱም መጣች፤ በረከትንም አልመረጠም ከእርሱም ራቀች።
መርገምን እንደ ልብስ ለበሳት፥ እንደ ውኃም ወደ አንጀቱ፥ እንደ ቅባትም ወደ አጥንቱ ገባች"። መዝ.108÷17-18
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_18_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 15
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶ አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ፤ ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ።
⁷ እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ፦
⁸ ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤
⁹ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።
¹⁰ ሕዝቡንም ጠርቶ፦ ስሙ አስተውሉም፤
¹¹ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው አላቸው።
¹² በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው፦ ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ አወቅህን? አሉት።
¹³ እርሱ ግን መልሶ፦ የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል።
¹⁴ ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ አለ።
¹⁵ ጴጥሮስም መልሶ፦ ምሳሌውን ተርጕምልን አለው።
¹⁶ ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ እናንተ ደግሞ እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን?
¹⁷ ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን?
¹⁸ ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው።
¹⁹ ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና።
²⁰ ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፥ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የ #ማርያም ቅዳሴ ወይም የ #ሠለስቱ_ምእት ቅዳሴ ነው። መልካም የታላቁ ሐዋርያ የሊቀ ጳጳስ የ #እለእስክንድሮስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️