ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ነሐሴ_14

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በእስክንድርያ ሀገር ድንቅ ተአምርን አደረገ፣ #የአባ_ስምዖንና የወዳጁ #የአባ_የዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ፣ #ቅዱስ_ባስሊቆስ በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መስቀለ_ክርስቶስ

ነሐሴ ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በእስክንድርያ ሀገር ድንቅ ተአምርን አደረገ። ስለርሱም ከአይሁድ ብዙዎች አምነው በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአባ ቴዎፍሎስ እጅ ተጠመቁ እርሱም ለቅዱስ ቄርሎስ የእናቱ ወንድም ነው። ይህም እንዲህ ነው በእስክንድርያ አገር ስሙ ፈለስኪኖስ የሚባል አይሁዳዊ ባለጸጋ ሰው ይኖር ነበር እርሱም እንደ አባቶቹ የኦሪትን ሕግ የሚጠብቅና #እግዚአብሔርን የሚፈራ ነው።

ዳግመኛም ሙያተኛዎች ሁለት ድኃዎች ክርስቲያኖች አሉ በአንደኛውም ላይ ሰይጣን የስድብ መንፈስ አሳድሮበት ጓደኛውን ወንድሜ ሆይ #ክርስቶስን ለምን እናመልከዋለን እኛ ዶኆች ነን ይህ #ክርስቶስን የማያመልክ አይሁዳዊ ፈለስኪኖስ ግን እጅግ ባለጸጋ ነው አለው።

ጓደኛውም እንዲህ ብሎ መለሰለት ዕወቅ አስተውል የዚህ ዓለም ገንዘብ ከ #እግዚአብሔር የሆነ አይደለም ምንም አይጠቅምም ጥቅም ቢኖረው ጣዖትን ለሚያመልኩ ለአመንዝራዎች ለነፍሰ ገዳዮች ለዐመፀኞች ሁሉ ባልሰጣቸውም ነበር።

አስተውል የከበሩ ነቢያት ድኆች ችግረኞችም እንደነበሩ ሐዋርያትም እንደርሳቸው ችግረኞች እንደነበሩ። #ጌታችንም ድኆችን ወንድሞቼ ይላቸው እንደነበረ። ሰይጣን ግን የጓደኛውን ምክር እንዲቀበል ምንም ምን አልተወውም ሃይማኖቱን ምንም ምን አልተወውም ሃይማኖቱን ለውጦ ነፍሱን እስከማጥፋት ድረስ አነሣሣው ቀሰቀሰው እንጂ።

ከዚህም በኋላ ወደ ፈለስኪኖስ ሒዶ በአንተ ዘንድ እንዳገለግል ተቀበለኝ አለው። ፈለስኪኖስም እንዲህ ብሎ መለሰለት በሃይማኖቴ የማታምን አንተ ልታገለግለኝ አይገባም ከቤተ ሰቦቼም ጋራ የማትተባበር ልቀበልህ አይገባኝም። ሁለተኛም ይህ ጐስቋላ ወዳንተ ተቀበለኝ እኔም ወደ ሃይማኖትህ እገባለሁ ያዘዝከኝንም ሁሉ አደርጋለሁ አለው።

አይሁዳዊው ባለጸጋም ከመምህሬ ጋር እስከምማከር ጥቂት ታገሠኝ ብሎ ከዚያም ወደ መምህሩ ሒዶ ድኃው ክርስቲያናዊ ያለውን ሁሉ ነገረው መምህሩም #ክርስቶስን የሚክድ ከሆነ ግረዘውና ተቀበለው አለው።

አይሁዳዊውም ተመልሶ መምህሩ የነገረውን ለዚያ ድኃ ነገረው ያም ምስኪን የምታዙኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ። ከዚህም በኋላ ወደ ምኵራባቸው ወሰደው የምኵራቡም አለቃ በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ጠየቀው። ንጉሥህ #ክርስቶስን ክደህ አይሁዳዊ ትሆናለህን እርሱም አዎን እክደዋለሁ አለ።

የምኵራቡም አለቃ #መስቀል ሠርተው በላዩ የ #ክርስቶስን ሥዕል እንዲአደርጉ መጻጻንም የተመላች ሰፍነግ በዘንግ ላይ አሥረው ከጦር ጋራ እንዲሰጡት አዘዘ ከዚያም ከተሰቀለው ላይ ምራቅህን ትፋ መጻጻውንም አቅርብለት #ክርስቶስ ሆይ ወጋሁህ እያልህ ውጋው አሉት።

ሁሉንም እንዳዘዙት አድርጎ በወጋው ጊዜ ብዙ ውኃና ደም ፈሰሰ ለረጂም ጊዜም በምድር እየፈሰሰ ነበር በዚያን ጊዜም ያ ከሀዲ ደርቆ እንደ ደንጊያ ሆነ። በአይሁድ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሀት ወደቀባቸው በእውነት የአብርሃም ፈጣሪ ስለእኛ ተሰቅሏል እኛም ዓለምን ለማዳን የመጣ የሕያው #እግዚአብሔር ልጅ እርሱ እንደሆነ አመንበት እያሉ ጮኹ።

ከዚህም በኋላ አለቃቸው ከዚያ ደም ወስዶ የአንድ ዕውር ዐይኖችን አስነካው ወዲያውኑ አየ ሁሉም አመኑ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ ሒደው የሆነውን ሁሉ ነገሩት። ሊቀ ጳጳሳቱም ከካህናቱ ሁሉ ጋራ ተነሣ አባ ቄርሎስ ከእርሱ ጋራ አለ። ወደ አይሁድ ምኵራብም ሒዶ ውኃና ደም ከእርሱ ሲፈስ #መስቀሉን አገኘው ከዚያም ደም ወስዶ በግንባሩ ላይ ቀብቶ በረከትን ተቀበለ ሕዝቡንም ሁሉ ግንባራቸውን በመቀባት ባረካቸው።

ያንንም #መስቀል አክብረው ተሸክመው እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው ያኖሩት ዘንድ አዘዘ። ደም የፈሰሰበትንም ምድር አፈሩን አስጠርጎ ለበረከትና ለበሽተኞች ፈውስ ሊሆን በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኖረው።

ከዚህም በኋላ ፈለስኪኖስ ከቤተ ሰቦቹ ሁሉ ጋራ ሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስን ተከተለው ከአይሁድም ብዙዎቹ የቀደሙ አባቶቻቸው በሰቀሉት የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም አጥምቋቸው ከእርሱ ጋራ አንድ አደረጋቸው ሥጋውንና ደሙንም አቀበላቸው። ከዚህም በኋላ ለዘላለሙ ክብር ምስጉን የሆነ #እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደየቤታቸው ገቡ። እኛንም ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን በ #መስቀሉ ኃይል ያድነን አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አባ_ስምዖንና_አባ_ዮሐንስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የአባ ስምዖንና የወዳጁ የዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ። እሊህ ቅዱሳንም በአማኒው ዮስጦንስ ዘመን መንግሥት የነበሩ ናቸው እሊህም ወንድሞች የከበሩ ክርስቲያን ናቸው።

ከዚህ በኋላ ለከበረ #መስቀል በዓል ቅዱሳት መካናትን ሊሳለሙ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዱ ሥራቸውንም አከናውነው ወደ አገራቸው ሲመለሱ በፈረሶቻቸው ተቀምጠው ወደ ኢያሪኮ ቀረቡ።

ዮሐንስም በዮርዳኖስ በረሀ ያለውን የመነኰሳቱን ገዳም አይቶ ወንድሙ ስምዖንን ወንድሜ ሆይ በእሊህ ገዳማት እኮ የ #እግዚአብሔር መላእክት ይኖራሉ አለው ዮሐንስም ከእርሳቸው ጋራ ከሆን አወን ልናያቸው እንችላለን አለው።

ከዚያም ከፈረሶቻቸውን ወርደው ለሰዎቻቸው ሰጥተው እስከምናገኛችሁ በየጥቂቱ ተጓዙ ብለው እንደሚጸዳዱ መስለው ወደ ዱር ገቡ።

የዮርዳኖስንም ጐዳና ተጒዘው ከሰዎቻቸው በራቁ ጊዜ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ ጸሎት እናድርግ ከእኛም አንዳንችን ወደ መነኰሳቱ ገዳም በምታደርስ ጐዳና ቁመን ዕጣ እንጣጣል #እግዚአብሔር ከፈቀደ ዕጣችን ወደ ወጣበት እንሔዳለን።

ከዚህም በኋላ ስምዖን በዮርዳኖስ ጐዳና ቆመ ዮሐንስም ወደ ሀገራቸው በሚወስድ ጐዳና ላይ ቆመ ዕጣውንም በአወጡበት ጊዜ ዮርዳኖስ ጐዳና ላይ ወጣ እጅግም ደስ አላቸውና ስለ ደስታቸው ብዛት እርስ በእርሳቸው ተያይዘው ተሳሳሙ።

አንዱም አንዱ ወደኋላ እንዳይመለስ ስለጓደኛው ይጠራጠርና ይፈራ ነበር አንዱም ሁለተኛውን ይመክረውና ለበጎ ሥራ ያተጋው ነበር።

ዮሐንስ ስለ ስምዖን ይፈራ ነበር ስለ ወለላጆቹ ፍቅር አንዳይመለስ ስምዖንም ስለ ዮሐንስ ይፈራ ነበር እርሱ በዚያ ወራት መልከ መልካም የሆነች ሚስት አግብቶ ነበርና።

ከዚህም በኋላ ወደ #እግዚአብሔር ጸለዩ እንዲህም አሉ በውስጧ እንመነኵስ ዘንድ ለኛ የተመረጠች ገዳም ደጃፍዋ ክፍት ሆኖ ብናገኝ ምለክት ይሆናል።

የገዳሙም አለቃ ኒቆን የሚሉት በተሩፋት ፍጹም የሆነ ድንቆች ተአምራትን የሚያደርግ ሀብተ ትንቢት የተሰጠጠው ሲሆን በዚያች ሌሊት በጎቼ ይገቡ ዘንድ የገዳሙን በር ክፈተት የሚለውን ራእይ አየ።

ወደርሱም በደረሱ ጊዜ የ #ክርስቶስ በጎች ሆይ መምጣታችሁ መልካም ነው አላቸውና ከ #እግዚአብሔር ዘንድ እንደ ተላኩ ሰዎች አድርጎ ተቀበላቸው።

ከዚህም በኋላ አበ ምኔቱን የምንኵስናን ልብስ ያለብሳቸው ዘንድ ለመኑት እነርሱ በቆቡ ላይ የብርሃን አክሊል አድርጎ መላእክትም ከበውት አንዱን መነኰስ አይተዋልና ስለዚህም ፈጥነው ይመነኵሱ ዘንድ ተጉ።
ከዚያም በማግስቱ አበ ምኔቱ የምንኲስናን ልብስ አለበሳቸው በቀን እንደሚተያዩ በሌሊትም እርስበርሳቸው የሚተያዩ እስቲሆኑ በፊታቸው ላይ የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን በራ ሁለተኛም በዚህ መነኵስ ላይ እንደሰዩ በራሶቻቸው ላይ የብርሃን አክሊል አዩ።

ከዚህም በኋላ ከመነኰሳቱ መካከል ተለይተው ወደ በረሀ ይገቡ ዘንድ ኀሳብ መጣባቸው። በዚያችም ሌሊት ብርሃንን የለበሰ ሰው ለአበ ምኔቱ ተገልጾ የ #ክርስቶስ በጎች እንዲወጡ የገዳሙን በር ክፈት አለው በነቃም ጊዜ ወደ በሩ ሒዶ ተከፍቶ አግኝቶት እያዘነና እየተከዘ ሳለ ሊወጡ ፈለገው እሊህ ቅዱሳን መጡ በፊታቸውም በትረ መንግስትን አየ።

በአያቸውም ጊዜ ደስ ብሎት ተገናኛቸው እነርሱም በልባቸው ያሰቡትን ነግረውት እንዲጸልይላቸው ለመኑት ለረጅም ጊዜም አለቀሰ ከዚህም በኋላ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ በቀኙና በግራው አቆማቸው እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ ጸሎት አድርጎ ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቃቸው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር አደራ አስጠበቃቸው። ከዚያም በፍቅር አሰናበታቸው።

ከዚህም በኋላ አርጋኖን ወደ ምባል ወንዝ ሔዱ በዚያም አንድ ገዳማዊ በዚያን ወራት ያረፈ በውስጡ የኖረበትን በዓት አገኙ በውስጡም ያ ሽማግሌ ገዳማዊ ሲመገበው የነበረ ለምግባቸው የሚያስፈልጋቸውን የእህል ፍሬዎችን አገኙ ምግባቸውን በአዘጋጀላቸው በ #እግዚአብሔርም እጅግ ደስ አላቸው።

በድንግያ ውርወራ ርቀት መጠን አንዱ ከሁለተኛው የተራራቁ ሁነው ሰፊ በሆነ ተጋድሎ ቡዙ ዘመናት ኖሩ። ሰይጣንም ቡዙ ጊዜ ይፈታተናቸው ነበር ግን አባታቸው ቅዱስ ኒቅዮስ በራእይ ወደ እሳቸው መጥቶ ስለ እነርሱ ይጸልያል ተኝተውም ሳሉ የዳዊትን መዝሙር ያስተምራችዋል በነቁም ጊዜ ያስተማራቸውን ሁሉ በትክክል ያነቡታል እጅግም ደስ ይላቸዋል።

አምላካዊ ራእይም ተሰጣቸው ተአምራትንም ያደርጋሉ በዚያችም በረሀ የክብር ባለቤት በሆነ በ #ክርስቶስ ኃይል ሰይጣንን ድል እስከ አደረጉት ድረስ የቀኑን ሐሩር የሌሊቱን ቊር ታግሠው ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነሩ።

ከዚህም በኋላ ስምዖን ወንድሙ ዮሐንስ እንዲህ አለው በዚህ በረሀ በመኖራችን ምን እንጠቃማለን ና ወደ አለም ወጥተን ሌሎችን እንጥቀማቸው እናድናቸውም ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አለው ወንድሜ ሆይ ይህ ኀሳብ ከሰይጣን ቅናት የተነሣ ይመስለኛል።

ስምዖን እንዲህ አለው ከሰይጣን አይደለም በዓለም ላይ እንድዘበትበት #እግዚአብሔር አዞኛልና ነገር ግን ና እንጸልይ ያን ጊዜም በአንድነት ጸለዩ ልብሳቸውንም እስከ አራሱት ድረስ እርስበርሳቸው ተቃቅፈው አለቀሱ። ከዚህም በኋላ ስምዖን እስከሚሞትባት ቀን ሥራውን ይሠውርለት ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር እየጸለየ ጎዳናውን ተጓዘ።

ወደ ዓለምም ገብቶ ራሱን እንደ እብድ አደረገ እብዶችንም የፈወሰበት ጊዜ አለ እሳትን በእጁ የሚጨብጥበትም ጊዜ አለ። ከዚህም በኋላ ከከተማው በር የሞተ ውሻ አግኝቶ በመታጠቂያውም አሥሮ እየጐተተ እንደሚጫወት ሆነ ሰዎች እስከሚሰድቡትና እስከሚጸፉት ድረስ።

በአንዲት ቀን እሑድ ከቅዳሴ በፊት የኮክ ፍሬ ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ መቅረዞችንም ሰበረ። ሴቶችንም መትቶ ከእርሳቸው ጋራ እንደሚተኛ ጐተታቸው ባሎቻቸውም ደበደቡት።

ዕረፍቱም ሲቀርብ የ #እግዚአብሔር መልአክ የእርሱንም የወንድሙ የዮሐንስንም የዕረፍታቸውን ጊዜ ነገረው ወደ ወይን ሐረግ ሥር ገብቶ ከወንድሙ ዮሐንስ ጋራ ነፍሱን በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጠ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ባስሊቆስ

በዚህችም ቀን ቅዱስ ባስሊቆስ በሰማዕትነት ሞተ። በእሥር ቤትም እርሱ ሳለ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገልጦለት እንዲህ አለው የምስክርነትህ ፍጻሜ ደርሷልና ሒደህ ዘመዶችህን ተሰናበታቸው።

ከዚህም በኋላ ወታደሮችን ከእርሱ ጋራ ወደ ቤቱ ይሔዱ ዘንድ ለመናቸው ሒደውም ወደ ቤቱ ገቡ እናቱንና ዘመዶቹንም ተሰናበታቸው። በማግሥቱም የከበረ ባስሊቆስን ወደ ፍርድ ሸንጎ አቀረቡትና በሁለት ምሰሶዎች መካከልም አሥረው ሲደበድቡት ዋሉ በእግሮቹም ችንካሮችን አደረጉበት ደሙም በምድር ላይ ፈሰሰ ያየው ሁሉ አለቀሰለት።

ከዚህም በኋላ ከደረቀ ዕንጨት ላይ አሠሩት ዕንጨቱም በቀለና ቅርንጫፍና ቅጠሎችን አወጣ። ሰዎችም የልብሱን ጫፍ ለመንካት የሚጋፉ ሆኑ በበሽተኞችና በዚህ ዕንጨት ላይ ያደረገውን ተአምር አይተዋልና።

ከዚህም በኋላ ዋርሲኖስ ወደሚባል አገር በመርከብ ወሰዱት ወታደሮችም እንዳትሞት እህልን ብላ አሉት እርሱም እኔ ከሰማያዊ መብል የጠገብኩ ነኝ ምድራዊ መብልን አልመርጥም አላቸው።

ወደ መኰንኑም በአቀረቡት ጊዜ ለአማልክት መሥዋዕትን አቅርብ አለው የከበረ በባስሊቆስም እኔ አንድ ለሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የምስጋና መሥዋዕትን አቀርባለሁ አለው።

ሁለተኛም ወደ ጣዖታቱ ቤት እንዲአስገቡት አዘዘ እርሱም ቁሞ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ ያን ጊዜ እሳት ወርዶ ጣዖታቱን አቃጠላቸው መኰንኑም ፈርቶ ሸሽቶ ወደውጭ ወጣ። ቁጣንም ተመልቶ ይገድሉት ዘንድ ያ መኰንን አዘዘ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ባስሊቆስ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ መከራውን ይሳተፍ ዘንድ ስለ አደለውም አመሰገነው።

ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት ብዙዎችም መላእክት ነፍሱን ሲያሳርጓት አዩዋት #ጌታችን_ኢየሱስም ወዳጄ ባስሊቆስ ወደ እኔ ና እኔ የምዋሽ አይደለሁም ተስፋ ያስደረግሁህን እፈጽምልሃለሁ ብሎ ጠራው። እንዲህም ተጋድሎውን ፈጸመ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_14)