ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ሚያዝያ_5
#አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ_ስም
ሚያዝያ አምስት በዚች ቀን የካህኑ የቡዝ ልጅ ታላቅ #ነቢዩ_ቅዱስ_ሕዝቅኤል አረፈ፣ የኢትዮጵያ ብርሃኗ #ማኅሌታዊው_ቅዱስ_ያሬድ የተወለደበት ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሕዝቅኤል_ነቢይ

ሚያዝያ አምስት በዚች ቀን የካህኑ የቡዝ ልጅ ታላቅ ነቢይ ሕዝቅኤል አረፈ። ይህም ካህንም ነቢይም ሆኖ ናቡከደነጾር የእስራኤልን ልጆች በማረካቸው ጊዜ ወደ ባቢሎን ተማርኮ ሔደ።

በባቢሎን አገርም ሳለ የትንቢት መንፈስ በላዩ አደረ በትንቢቱ ውስጥ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከከበረች ድንግል እመቤታችን ማርያም ስለ መወለዱና ከወለደችውም በኃላ በድንግልና ጸንታ ስለ መኖርዋ ተናገረ።

እንዲህም ብሎ ትንቢት ተናገረ እኔ ወደ ምሥራቅ ስመለከት የተዘጋች ደጅ አየሁ። ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች አትከፈትም የሚገባባትም የለም። የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር እንደተዘጋች ይገባባታልና ከእርሱ በቀር የሚገባም የሚወጣም የለም አለኝ።

ሁለተኛም ስለ ክርስትና ጥምቀት በንጹሕ ውኃ እረጫችኃለሁ ከኃጢአታችሁም ትነጻላችሁ ከርኲሰታችሁም ሁሉ። አዲስ ልብን እሰጣችኃላሁ አዲስ ዕውቀትንም አሳድርባችኃለሁ ድንቊርና ያለበትንም ልብ ከሰውነታችሁ አርቄ ዕውቀት ያለውን ልብ እሰጣችኃለሁ መንፈስ ቅዱስንም ተቀብለው የእግዚአብሔር ልጆች እንደሚሆኑ ተናገረ።

ሕዝቡንም ማስተማር ስለ መተዋቸው ካህናትን ሲገሠጽ ካላስተማራችኃቸውና ካላነቃችኃቸው የሰዎችን ነፍስ እግዚአብሔር ከእናንተ ይፈልጋል አላቸው።

ደግሞ ስለ ሥጋ መነሣት በሕይወት ለመኖርም ቢሆን ወይም በሥቃይ አስቀድሞ እንደነበሩት በድኖች ተነሥተው ከነፍሶቻቸው ጋራ አንድ ሊሆኑ አላቸው ብሎ ተናገረ። ለሚያነባቸው የሚጠቅሙ ብዙዎች ትምቢቶችን ተናገረ።

እግዚአብሔርም በእጆቹ ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶችን ገለጠ። የእስራኤል ልጆች በባቢሎን ሳሉ ጣዖት ባመለኩ ጊዜ ገሠጻቸው። ስለዚህም አለቆቻቸው በጠላትነት በላዩ ተነሥተው ገደሉት ይህም ሁሉ ትንቢቱ የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ሰው ከመሆኑ በፊት ነው። የትንቢቱም ዘመን ሃያ ዓመት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ያሬድ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የኢትዮጵያ ብርሃኗ ማኅሌታዊው ቅዱስ ያሬድ የተወለደበት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከእናቱ ቅድስት ክርስቲና (ታውክልያ) ከአባቱ ከቅዱስ አብዩድ (ይስሐቅ) በአክሱም በ505ዓ.ም ሚያዝያ 5 ቀን ተወለደ። አባቱ የአክሱም ጽዮን ቄሰ ገበዝ ነበር። በዚያን ጊዜ የብሉያትና የሐዲሳት መምህራንና ተማሪዎች የሚገኙት አክሱም ጽዮን ነውና የአኵሱም ቤተ ቀጢን (ቤተ ጉባኤ) መምህር የነበረው የእናቱ ወንድም አጎቱ መምህር ጌዴዎን ይባል ነበር።

ቅዱስ ያሬድ የሰባት ዓመት ብላቴና በኾነ ጊዜ አባቱ ስለ ሞተ ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት በዚያ ዘመን አጠራር ለጌታው ዐደረ። ጌታውም የዐፄ ገብረ መስቀል ቢትወድድ አዛዥ ዜና ገብርኤል ይባላል። ያሬድን ዐቅሙ ለጉልበት ሥራ እንዳነሰ አይቶት "አንተ ልጅ ጋሻ ቢያስይዙህ አትችል፤ ሾተል ቢያሸክሙህ አይሆንልህ ለምን ከዚህ መጣህ?" ብሎ መለሰለት። ከዚያ በኋላ ከአጎቱ ዘንድ ሔደ። መምህሩም "ከዚህ የመጣህበት ምክንያት ምንድ ነው?" አለው። እርሱም "መጽሐፍት እማራለኹ ብዬ ነው የመጣኹት" አለው። መምህር ጌድዎንም ዐቅሙንና ዕውቀቱን በመገመት ለተማሪዎች "በሉ ፊደል አስቆጥሩት" አላቸውና ትምህርቱን ጀመረ። ኾኖም ቃለ እግዚአብሔርን የመቀበል ችሎታው ደካማ ስለነበር አብረው የሚማሩትም ሕፃናት "ሰነፍ ያሬድ ዕንጨት ስበር ውሃ ቅዳ" እያሉ አፌዙበት፤ ቀለዱበት። አጎቱ ጌዴዎንም ከትምህርቱ ድክመት የተነሣ በጨንገር (በአለንጋ) ቢገርፈው ሕፃኑ ያሬድም በዚህ ተበሳጭቶና ተስፋ ቆርጦ ከአክሱም ከተማ ወጥቶ ወደ እናቱ መንደር ወደ መደባይ ወለል ደረሰ። ለጥሙ ከምንጭ ውሃ ጠጥቶ ለድካሙ ከዛፋ ጥላ አረፈ። በምን ምክንያት ከጓደኞቹ በታች እንደኾነ ሲያስብና ሲያሰላስል ሲያዝንና ሲተክዝ ከቆየ በኋላ እግዚአብሔር አንድ የሚያጽናና ምልክት አሳየው። ይኸውም አንድ ትል የዛፏን ፍሬ ለመመገብ ፈልጎ ወደ ላይ እየወጣና እየወደቀ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በሰባተኛው ጊዜ ወደ ዛፋ ወጥቶ ፍሬዋን ሲመገብ ተመለከተ ተማሪ ያሬድም ከዚህ ትል ትዕግሥትን፣ ጽናትን፣ ጥረትን፣ ስኬትን ትምህርት ወስዶ እኔም እኮ ተስፋ ሳይቆርጥ ብዙ ጥረት ካደረግኹ እግዚአብሔር ያሳካልኛል ብሎ በተስፋ ተጽናንቶ እንደገና ወደ መምህሩ በመመለስ ትምህርቱን ለመቀጠል ወሰነ። ወደ መደባይ ያደረገው የነበረውን ጉዞ ሠርዞ ወደ አክሱም ከተማ ወደ መምህሩ ጌድዬን ጉባኤ ቤት ተመለሰ። በመጸጸት አጎቱን "አባቴ ስለተቆጣኸኝና ስለገረፍከኝ ተበሳጭቼ ሔጄ ነበር ፤ ነገር ግን በመንገድ ላይ እግዚአብሔር ስላስተማረኝ ተጸጽቼ መጥቻለኹ። ከእንግዲህስ ወዲህ እየተቆጣኽና እየገሠጽህ አስተምረኝ" ሲል አሳቡን ሳይደብቅ ገለጸለት።

አጎቱም ያሬድ ተጸጽቶ በመመለሱ በጣም ተደስቶ ዐይነ ልቡናውን ያበራለት ዘንድ ፈጣሪውን እያለቀሰ በለመነለት ጊዜ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ለያሬድ ዕውቀትን ገለጸለት። የያሬድ ኅሊናው ተከፍቶለት መዝሙረ ዳዊትን፣ ውዳሴ ማርያምን፣ መሓልየ ነቢያት፣ መሐልየ ሰሎሞንን፣ መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን ንባባቸውን እስከ አገባባቸው አወቀ።

ቅዱስ ያሬድ ቅዱሳት መጻሕፍትን በቃሉ ይዞ ሲያስተምር ሳለ የትምህርቱን ጥራት፣ የሃይማኖት ጽናት፣ ደግነቱንና ትዕግስቱን፣ ትሕትናውና ተልኮውን በመምህሩና በካህናቱ ተመስክሮለት የአክሱም ጳጳሱ አባ ዮሐንስ ሢመተ ዲቁና ሾመው። ቅዱስ ያሬድ የታላቋ የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን አጋልጋይ ዲያቆን ኾነ።

ትምህርቱን በስፋት ስለቀጠለበት የመጻሕፍት ብሉያትና ሐዲሳት፣የመጻሕፍት ሊቃውንት ትርጓሜ ሊቅ ኾነ። ቅዱስ ያሬድም ለመንፈሳዊ አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ከዘጠኙ ቅዱሳን ጋራ በቤተ ቀንጢን ጉባኤ ቤት ይውል ስለነበር ገዳማዊ ሕይወት ከእነርሱ በመማር እንደ እነ አቡነ አረጋዊ፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጰንጠሌዎን በድንግልና ተወስኖ በንጽሕና ሲያገለግል ቆይቷል።

ለቅዱስ ያሬድ ሰማያዊ ዜማ መገለጽ፦ ኅዳር5 ቀን 527ዓ.ም ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት እግዚአብሔር ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን (መላእክት በአዕዋፍ ተመስለው) እርሱ ወዳለበት ላከለት። እነርሱም ያሬድ ባለበት ቦታ አንጻር በአየር ላይ ረብበው በግእዝ ቋንቋ "ብፁዕ ያሬድ ብፅዕት ከርሥ እንተ ጾረተከ ወብፁዕት አጥባት እለ ሐፀናከ (የተመሰገንክና የተባረክ ያሬድ ሆይ፤ አንተን የተሸከመች ማሕፀን የተመሰገነች ናት፤ አንተን ያሳደጉ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው") ብለው አወደሱት። ቅዱስ ያሬድም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ወደ ሰማይ አንጋጦ ሦስቱን አዕዋፍ አየና "እናንተ በሰው አንደበት የምትናገሩ ከወዴት መጣችኹ" አላቸው። ከሦስቱ አዕዋፍ አንዷም "ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ማሕሌትን ሰምተኽ እንድታዜም የተመረጥኽ መኾኑን እነግርህና እናበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልከን መጥተናል" አለችው። ከዚያም ቅዱሳን መላእክት በዜማ ወደሚያመሰግኑባት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በአካል ተነጠቀ።
#ነቢይ_ወሰማዕት_ቅዱስ_ኤርምያስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

“ኤርምያስ” ማለት “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ያደርጋል” ማለት ነው፡፡ ከአራቱ ዓበይት ነቢያት አንዱ ሲኾን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን አባቱ “ኬልቅያስ” ይባላል፡፡ እናቱ ደግሞ “ማርታ” እንደምትባል የቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ትውፊት ያስረዳል፡፡ አገሩ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ካለው ከተማ ከ“ዓናቶት” ነው፤ ትውልዱም ከካህናት ወገን እንደነበረ ተጽፏል /ኤር.፩፡፩/፡፡

#ነቢዩ_ኤርምያስ ለነቢይነት የተለየው ከእናቱ ማኅፀን ዠምሮ ነው /ኤር.፩፡፮/፡፡ ይኸውም እንደ ነቢዩ ሳሙኤል፤ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ማለት ነው፡፡ አንድም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “በእናቴ ማኅፀን ሳለኹ የለየኝ …” እንዳለው ነው /ገላ. ፩፡፲፭/፡፡
#ነቢዩ_ኤርምያስ ለእስራኤል ብቻ ሳይኾን ለአሕዛብም ጭምር ነቢይ እንዲኾን በተጠራ ጊዜ ደንግጧል፤ “ሕፃን አንድም ሕፃነ አእምሮ ነኝና ወዮልኝ” በማለትም አመንትቷል፡፡ በዃላ ግን እግዚአብሔር፡- “እስራኤልና አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፣ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ትመልሳቸዋለኽና ሕፃን ነኝ አንድም ሕፃነ አእምሮ ነኝ አትበል” ተብሎ በተሰጠው ተስፋ መሠረት በረታ፡፡

#በነቢዩ_ዘመን በይሁዳ ነግሠው የነበሩት ነገሥታት አምስት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-
1, ባዕድ አምልኮን ለማስወገድ፣ የእግዚአብሔርን ቤትና አምልኮ ለማሳደስ ብዙ የደከመው፣ በመሞቱም ነቢዩ ያለቀሰለት /፪ኛ ዜና ፴፬-፴፭/ ኢዮስያስ፤
2, በነገሠ በ፫ኛው ወር የግብጽ ንጉሥ አስሮ የወሰደው የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአክስ (ሰሎም) /፪ኛ ዜና ፴፮፡፩-፬፣ ኤር.፳፪፡፲-፲፪/፤
3, ፈርዖን ኒካዑ በወንድሙ በኢዮአክስ ምትክ በይሁዳ ያነገሠው፣ አስቀድሞ ለግብጽ በኋላም ለባቢሎን የተገዛው /፪ኛ ዜና ፴፮፡፬-፰/፣ በ፲፩ የንግሥና ዘመኑ እጅግ ክፉ የነበረው /ኤር.፳፪፡፲፫-፲፱/፣ የእግዚአብሔርን ቃል በመናቅ ኤርምያስን የተቃወመው መጽሐፉንም ያቃጠለበት /ኤር.፴፮/ ኢዮአቄም፤
4, ከአባቱ ከኢዮአቄም በኋላ በኢየሩሳሌም ለሦስት ወራት የነገሠ፣ በ፭፻፺፯ ከክ.ል.በ. ላይ ከቤተሰቦቹና ከአለቆቹ በጠቅላላ ከዐሥር ሺሕ ሰዎች ጋር ወደ ባቢሎን ተማርኮ የሔደው /፪ኛ ነገ.፳፬፡፰-፲፯፣ ኤር.፳፪፡፳፬-፴/ ዮአኪን (ኢኮንያን)፤
5, ከኢዮስያስ ልጆች ሦስተኛ የኾነው፣ የወንድሙ ልጅ ዮአኪን በተማረከ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከ፭፻፺፯-፭፻፹፯ ከክ.ል.በ. በይሁዳ ያነገሠው፣ ከነቢዩ ኤርምያስ ምክር ላይጠቀምበት ምክርን ይጠይቅ የነበረው፣ በክፋቱ የጸና፣ ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ባቢሎን ተወስዶ የተመለሰው /ኤር.፶፩፡፶፱/፣ በኋላ ላይ በግብጽ ተማምኖ ባቢሎን ንጉሥ ላይ ያመፀው፣ ከዓመት ተመንፈቅ በኋላ ተይዞ የተማረከና ዕዉር ኾኖ በግዞት ቤት ሳለ የሞተው ሴዴቅያስ ናቸው፡፡

#ነቢዩ_ኤርምያስ የነበረበት ነባራዊ ኹኔታ....

#ነቢዩ_ኤርምያስ አገልግሎቱን የዠመረው የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ (ከ፮፻፵-፮፻፱ ከክ.ል.በ.) በነገሠ በ፲፫ኛው ዓመት ላይ ነበር፡፡ ይኸውም በ፮፻፳፮ ከክ.ል.በ. መኾኑ ነው፡፡ ይኽ ዓመት ደግሞ እጅግ በጣም ወሳኝ የኾነ ወቅት ነበር፡፡ በአንድ በኵል ንጉሥ ኢዮስያስ ባዕድ አምልኮን ለማስወገድ፣ የ #እግዚአብሔርን ቤትና አምልኮ ለማሳደስ ከዠመረ አንድ ዓመት ኾኖታል፡፡ በሌላ በኵል ደግሞ ባቢሎናውያን ከአሦር አገዛዝ ነፃ ለመውጣት አንድ ዓመት ይቀራቸው ነበር፡፡ ስለዚኽ ነቢዩ ኤርምያስ አገልግሎቱን የዠመረው በቤተ ክህነቱም በፖለቲካውም ወሳኝ ኩነቶች የሚፈጸሙበት ሰዓት ላይ ነበር ማለት ነው፡፡ ከዚኹ ጋር በተያያዘ የሰሜኑ ክፍል ሕዝብ ወደ ሶርያ ተማርኮ ከፈለሰ ገና ፻ ዓመቱ ነው (የተማረኩት በ፯፻፳፪ ከክ.ል.በ. መኾኑ ከዚኽ በፊት መነጋገራችን ያስታውሱ)፡፡
የሕዝቡን ግብረ ገብነት ስንመለከት ደግሞ፥ #በቤተ_መቅደስ ሔደው መሥዋዕት ስላቀረቡ ብቻ #እግዚአብሔርን ከልባቸው ያመለኩት ይመስላቸው ነበር፡፡ #እግዚአብሔር ግን ከመሥዋዕት ይልቅ #ልብን ነው የሚፈልገው፡፡ ይኸውም ሊቁ #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ፡- “እግዚአብሔር ከወርቃማ ምሥዋዕት ይልቅ ወርቃማ ነፍሳትን ይሻል” እንዳለው ነው፡፡ #ነቢዩ_ኤርምስያስ ይኽን የግብዝነት ምልልሳቸውን እንዲያስተካክሉ ነገራቸው፡፡ መፃተኛውን፣ ድኻ አደጉን፣ መበለቲቱን እየበደሉ እልፍ ጊዜ መሥዋዕት ማቅረባቸው ቤተ መቅደሱን የወንበዴዎች ዋሻ ማድረግ እንደኾነ አሳሰባቸው /ኤር.፯፡፰-፲/፡፡ ካልተመለሱ ግን እነርሱ በባዕድ ንጉሥ እንደሚማረኩ፥ ቤተ መቅደሱም እንደሚፈርስ በቤተ መቅደሱ በር ኾኖ በመጮኽ በግልጽ ነገራቸው /ኤር.፯፡፬/፡፡ ሕዝቡና ካህናቱ ግን አላመኑትም፡፡ ይባስ ብለዉም
#መቱት /ኤር.፳፡፪/፤
#በእግር ግንድ ያዙት፤
#በጭቃ ጕድጓድ ጣሉት፤
#ኹለት ጊዜ አሰሩት /ኤር.፴፯፡፲፫-፳፩/፤ #አብዷል አሉት /ኤር.፳፱፡፳፮/፡፡
ተወዳጆች ሆይ! እኛስ? እኛስ መፃተኛውን አልበደልንምን? ድኻ አደጉን አላንከራተትንምን? መበለቲቱን አላስከፋታንምን? ይኽን እንድናስተካክልስ እግዚአብሔር ስንት ጊዜ ተናገረን? ታድያ ቤተ መቅደሱ ሰውነታችን እስኪፈርስ ድረስ እየጠበቅን ነው? ወይስ እንደ ነቢዩ ቃል ተመልሰናል? እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ድረስ የጠበቀን ከኀጢአታችን ጋር ተስማምቶ ሳይኾን የንስሐ ጊዜ ሲሰጠን ነው፡፡

#ነቢዩ_ኤርምያስ ልዩ ባሕርያት👇

1, በ #መጽሐፍ_ቅዱስ ውስጥ ስለ ደረሰበት መከራ እንደ ኤርምያስ ያለቀሰ ሰው የለም፡፡ በስነ መለኮት ምሁራን ዘንድ፡- “ #አልቃሻው_ነቢይ” እየተባለ መጠራቱም ይኽን ባሕርዩን የሚያመለክት ነው፡፡ ሰቆቃወ ኤርምያስ ማንበብም ይኽን ሐሳብ ግልጽ ያደርግልናል፡፡

2, የ #ጸሎት_ነቢይ ነው፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ከሌሎች ነቢያት ለየት የሚያደርገው ሌላኛው ነጥብ ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገረው በጸሎት መኾኑ ነው፡፡ ትንቢቱን፣ ራዕዩን የሚገለጽለት ሲጸልይ ነው፡፡ ሲከፋው የሚያወያየው ወዳጅ ሚስት የለውም፤ አላገባምና፡፡ ልጅም የለውም፡፡ ስለዚኽ ሲከፋው፣ የወንድሞቹን ስቃይ ሲያይ፣ ቤተ መቅዱስን መፍረስ ሲመለከት ያለቅሳል፡፡ #እግዚአብሔርም ያናግሯል፡፡

3, #ነቢዩ ምንም እንኳን ኢየሩሳሌምንና ሕዝቡን ቢወድም /ኤር.፰፡፲፰-፱፡፩/፣ ፲፫፡፲፯/ መማረካቸው እንደማይቀር ሊነግራቸው ተገድዷል፡፡ ከዚኽም በላይ፡- “ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ስጡ፤ ተገዙም፤ ምርኮኞችም እስከ ፸ ዓመት ድረስ አይመለሱም” ብሎ የተገለጠለትን የ #እግዚአብሔርን ቃል ስለተናገረ ተጠላ፡፡ ብዙዎችም ሊገድሉት አሰቡ /ኤር.፲፩፡፳፩፣ ፳፮፡፲፩፣ ፴፮፡፲፮፣ ፴፰፡፮-፲/፡፡ #ተመታ /ኤር.፳፡፪/፤ #በእግር ግንድ ተያዘ ፤ #በጭቃ ጕድጓድ ተጣለ፤ #ኹለት ጊዜ ታሰረ /ኤር.፴፯፡፲፫-፳፩/፤ #አብዷል ተባለ /ኤር.፳፱፡፳፮/፡፡ ስለዚኽ ነቢዩ በራሱ መጽሐፍ ላይ ስለ ራሱና ስለደረሰበት መከራ ብዙ ስለ ጻፈ ከሌሎች ነቢያት ይልቅ ጠባዩና ኹኔታው ተገልጿል፡፡

4, ከዚኹ ኹሉ ጋር ለሕዝቡ ምልክት እንዲኾን ሚስት እንዳያገባ፣ ወደ ግብዣ ወይም ወደ ልቅሶ እንዳይሔድ ተከልክሏል /ኤር.፲፮/......።

#ትንቢተ_ኤርምያስ
#ነቢዩ_ኤርምያስ ትንቢቱን የተናገረው ከላይ በገለጽናቸው አምስት የይሁዳ ነገሥታት ዘመን ነው፡፡ እግዚአብሔር ኤርምስያስን በጠራው ጊዜ፡- “የይሁዳ ሕዝብ እኔን ትተው ሌሎች አማልክትን ስላመለኩ ከሰሜን ጠላት አስነሣባቸዋለኹ” ብሎ ነገረው /ኤር.፩፡፲፫-፲፮/፡፡ ኤርምያስም ሕይወታቸው ወደ ኾነው #እግዚአብሔር እንዲመለሱ ያለማቋረጥ ለ፳፫ ዓመታት ይጠራቸው ነበር፤ እነርሱ ግን አልሰሙትም /ኤር.፳፭፡፫-፯/፡፡ በዚያም፥ በተጠራ በ፳፫ኛው ዓመት ከሰሜን የሚመጣባቸው ንጉሥ ናቡከደነፆር በባቢሎን ነገሠ /ኤር.፳፭፡፩/፡፡ እርሱም በይሁዳ ላይ ብቻ ሳይኾን በብዙ ሕዝቦች ላይ እንደሚመጣ፣ እስከ ፸ ዓመትም ድረስ እነዚኽ ሕዝቦች ለባቢሎን እንደሚገዙ ተነበየ /ኤር.፳፭፡፰-፲፩/፡፡ ከዚኽም በኋላ ባቢሎን እንደሚወድቅ ገለጠ /ኤር.፳፭፡፲፪-፲፬/፡፡ ይኽን ከባድ የፍርድ መልእክት ለመናገር የበቃው በአምላኩ ኃይል እንጂ በራሱ ችሎታ አልነበረም /ኤር.፩፡፮-፲/፡፡ በእነዚኽም ፳፫ ዓመታት የተናገረው ትንቢት ኹሉ ተጽፎ ሲነበብለት ንጉሥ ኢየአቄም ጽሑፉን ቆራርጦ አቃጠለው፤ #ኤርምያስ ግን እንደገና በ #ባሮክ እጅ አስጻፈው /ኤር.፴፮/፡፡

ተወዳጆች ሆይ! እኛስ ስንት ጊዜ ተመለሱ ተብለን ይኾን? ስንት ጊዜስ የእግዚአብሔርን ቃል ችላ ብለን ተኝተን ይኾን? እስኪ ኹላችንም የየራሳችንን እንመልከት!!!

ሴዴቅያስ ከነገሠ ጊዜ ዠምሮ #ኤርምያስ፥ ሴዴቅያስን፡- “ለባቢሎን ንጉሥ ተገዙ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ ኢየሩሳሌምም አትጠፋም” ይለው ነበር /ኤር.፳፯፡፲፪-፲፯/፡፡ ሴዴቅያስ ግን በግብጽ ስለተማመነ /ኤር.፴፯፡፫-፲/፣ ደግሞም ስላመካኘ /ኤር.፴፰፡፲፱/ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ አልሰጠም፡፡ ከዚኽም የተነሣ በእርሱና በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ፍርድ የባሰ ኾነ /ኤር.፴፱፡፩-፲፣ ፪ኛ ዜና ፴፮፡፲፩-፳፩/፡፡

#ነቢዩ_ኤርምያስ የፍርድን መልእክት ብቻ የተናገረ አይደለም፤ ጨምሮም የተስፋ ቃልን ተናግሯል፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከምርኮ እንደሚመልስ፣ ኢየሩሳሌም ታድሳ “#እግዚአብሔር ጽድቃችን” እንደምትባል /ኤር.፴፫፡፲፮/፣ #እግዚአብሔርም ከሕዝቡ ጋር አዲስ ኪዳንን እንደሚያደርግ፣ ከዳዊት ዘር የኾነው ንጉሥ ነግሦ፣ ስሙ “ #እግዚአብሔር ጽድቃችን” እንደሚባል ተንብዮአል /ኤር.፳፫፡፩-፮፣ ፴-፴፫/፡፡

የ#ትንቢተ ኤርምስያስ ዋና መልእክት፡-

#እግዚአብሔር_ታላቅና_ቅዱስ ስለኾነ ሕዝቡ ከክፋት ተመልሰው በፍጹም ልብ እንጂ በሐሰት እንዳያመልኩት ማስገንዘብ ነው፡፡ ይኸውም፡- “ወምስለ ኵሉ ኢተመይጠት ኀቤየ ኅሥርተ ይሁዳ እኅታ በኵሉ ልባ - አታላይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ ብፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም” /ኤር.፫፡፲/፤ ካህናቱና ነቢያቱ እግዚአብሔርን ስለመፍራት፣ በቅንነትም ስለመኖር ሳይኾን ሕዝቡን፡- “የ #እግዚአብሔር_ቤት እዚኽ ነው፤ እናንተም ሕዝቡ ናችሁ፤ አይዞአችሁ፤ ምንም አይደርስባችሁም” እያሉ ማታለላቸው /ኤር.፯፡፫-፲፩፣ ፲፬፡፲፫-፲፰፣ ፳፫፡፱-፵/ ለዚኹ ምስክር ነው፡፡ #እግዚአብሔር ግን የሚያየው ደጋግመን እንደተናገርነው #ልብን ነው፤ በፍጹም ልባቸው እግዚአብሔርን የሚፈልጉትም ያገኙታል፡፡

#መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1, የነቢዩ መጠራት (፩)፤
2, ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ የሚል ጥሪና የማስጠንቀቂያ መልእክቶች (፪-፳)፤
3, ዮአኪን ከተማረከ በኋላ ለነገሥታት፣ ለሕዝቡና ለምርኮኞች የተሰጡ መልእክቶች (፳፩-፳፱፣ ፴፭-፴፮፣ ፵፭)፤
4, የኢየሩሳሌም ልማትና የአዲስ ኪዳን ተስፋ (፴-፴፫)፤
5, የኢየሩሳሌም መከበብና ውድቀት (፴፬፣ ፴፯-፴፱)፤
6, ኤርምያስ በይሁዳ ከቀሩት አይሁድ ጋር መኖሩ (፵-፵፪)፤
7, የኤርምያስ በግብጽ መኖር (፵፫-፵፬)፤
8, በአሕዛብ ላይ የተነገሩ ትንቢቶች (፵፮-፶፩)
9, ተጨማሪ የታሪክ ክፍል ፣ የኢየሩሳሌም መውደቅ (፶፪)፡፡

#ሰቆቃወ_ኤርምያስ

#ሰቆቃ ማለት ሙሾ፣ ለቅሶ ማለት ነው፡፡ መጽሐፉ በዚኽ ስያሜ እንዲጠራ የኾነበት ዋና ምክንያትም ኢየሩሳሌም በጠላት እጅ ወድቃ፣ ቤተ መቅደሷና አጥሮቿ በጠላት ፈራርሳ፣ እናቶች ልጆቻቸው በረሃብ አልቀው በማየት ዝም እስከማለት የደረሱበት ረሃብና ጥም ጸንቶባቸው፣ ካህናትና ነቢያት መገደላቸውን አይቶ የጻፈው ስለኾነ ነው፡፡ መጽሐፉ አምስት ምዕራፎችን የያዘ ሲኾን በውስጡ ከለቅሶው በተጨማሪ የእግዚአብሔር ቊጣና ቅጣት እንዲኹም ስለ ተስፋ ድኅነት በስፋት ተገልጾበታል፡፡

#ተረፈ_ኤርምያስ

የሰቆቃወ ኤርምያስ ቀጣይ ክፍል ነው፡፡ መጽሐፉ ስለ ጣዖት አምልኮ ከንቱነት በስፋት ስለሚያትት “አርአያ መጽሐፍ ዘኤርምያስ - ኤርምያስ ፊት የጻፈውን መጽሐፍ የሚመስል መጽሐፍ፤ አንድም የጣዖትን መልክ ለይቶ ለይቶ የሚያሳይ መጽሐፍ” ተብሎ ይጠራል፡፡

#መጽሐፈ_ባሮክ

የዚኽ መጽሐፍ ጸሐፊ የነቢዩ ኤርምያስ ታማኝ ወዳጅ፣ ደቀ መዝሙርና ጸሐፊ የነበረው ባሮክ ነው /ኤር.፴፮፡፩-፴፪/፡፡ ምንም እንኳን ጸሐፊው ባሮክ ቢኾንም በይዘቱና እግዚአብሔር ለነቢዩ ኤርምያስ የገለጠለት በመኾኑ ከትንቢተ ኤርምያስ ጋር በመደመር አንድ ኾኖ ይቈጠራል፡፡ መጽሐፉ፥ ባሮክ በተማረከበት አገር በባቢሎን ሳለ ለኢየሩሳሌም ኗሪዎች ጽፎ የላከላቸው ነው፡፡ በውስጡም በምርኮ ስላሉት የአይሁድ ኑሮ፣ ስለ ኃጢአት ኑዛዜ ንስሐና ጸሎት እንዲኹም ለአይሁድ የቀረቡ ልዩ ልዩ ምክሮችን ይዟል፡፡

#ተረፈ_ባሮክ

ይኽ መጽሐፍ የመጽሐፈ ባሮክ ቀጣይ ጽሑፍ ሲኾን እግዚአብሔር ለባሮክ፣ ለአቤሜሌክና ለኤርምያስ የተናገረው ቃል ሲኾን እስራኤላውያንን በባቢሎን በምርኮ በነበሩበት ዘመን እንዴት ጠብቆ እንዳሳለፋቸውና በኤርምያስ መሪነት ምርኮኞቹ ወደ ኢየሩሳሌም እንዴት እንደተመለሱ የሚተርክ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ከላይ ለመግለጥ እንደሞከርነው እግዚአብሔር ለነቢዩ ኤርምያስ የገለጠለትና በባሮክ እጅ የተጻፈ ነው፡፡ ለዚኽም ምስክራችን፥ #ወንጌላዊው_ማቴዎስ፡- “በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥ ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት የሚል ተፈጸመ” ብሎ የተናገረው ቃል በዚኹ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ መኾኑ ነው /ማቴ.፳፯፡፱-፲/፡፡ ቃሉም ቃል በቃል እንዲኽ ይላል፡- “ኤርምያስም ጳስኮርን እንዲኽ አለው፡- እናንተስ በዘመናችሁ ኹሉ ከአባቶቻችሁና ከእናንተ በኋላ ከሚመጡ ልጆቻችሁ ጋር ጽድቅን ትቃረኗታላችሁ፡፡ እነርሱስ ከአባቶቻችሁ ይልቅ እጅግ የተናቀች ኀጢአትን ሠሩ፡፡ እነርሱም ዋጋ የማይገኝለትን ይሸጡታል፤ ሕማማትን የሚያስወግደውን እንዲታመም ያደርጉታል፤ ኀጢአትን የሚያስተሰርየውንም ይፈርዱበታል፡፡ የእስራኤል ልጆች የተስማሙበትን የክብሩን ዋጋ ሠላሳ ብር ይቀበላሉ፤ ያንም ብር ለሸክላ ሠሪ ቦታ አድርገው ይሰጡታል፡፡ እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ እንዲኹ እናገራለኹ፡፡ ስለዚኽ ንጹሕ ደምን ፈርደው አፍስሰዋልና ፍርድና ጥፋት በእነርሱ ላይ፥ ከእነርሱም በኋላ በልጆቻቸው ላይ ይወርድባቸዋል” /ተረ.ባሮ.፩፡፩-፭/፡፡

#የነቢዩ_የመጨረሻ_ዕረፍት
#ነሐሴ_22

#ነቢዩ_ሚክያስ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ሁለት በዚህች ቀን ታላቅ ነቢይ የሞራት ልጅ ሚክያስ አረፈ። ይህም ነቢይ በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ትንቢት በመናገር አስተማረ።

ስለ #ጌታችን መውረድም እንዲህ አለ። እነሆ #እግዚአብሔር ከልዑል መንበሩ ወደዚህ ዓለም ይወርዳል ።

ሁለተኛም ስለ ልደቱ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ የኤፍራታ ዕጣ የምትሆኚ አንቺም ቤተ ልሔም የእስራኤል ነገሥታት ከነገሡባቸው አገሮች አታንሺም ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና ።

ስለ ምኵራብ መቅረት፣ ስለ ቤተክርስቲያን በዓለም ሁሉ መታነፅ ትንቢት ተናግሯል። ዳግመኛም ስለ ሕገ ወንጌል መሠራት ሕግ ከጽዮን የ #እግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣል አለ። የትንቢቱም ወራት ሲፈጸም ወደ በጎ ሽምግልና ደርሶ ወደ ወደደው #እግዚአብሔር ሔደ።

የትንቢቱም ዘመን ከ #ጌታችን መምጣት በፊት በስምንት መቶ ዓመት ነው። ማርታ በምትባልም ቦታ ተቀበረ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ነሐሴ)
#ነሐሴ_30

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሠላሳ በዚች ቀን ከዐሥራ ስድስቱ ነቢያት አንዱ #ታላቅ_ነቢይ_ሚልክያስ ያረፈበት እና ጌታ ባሕር ውስጥ #ለሐዋርያ_እንድርያስ በሊቀ ሐመር አምሳል ተገልጦ ድንቅ ተአምር ያደረገለት ቀን ነው፣ የእናታችን #ቅድስት_ዜና_ማርያም የእረፍቷ መታሰቢያ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ነቢዩ_ሚልክያስ

ነሐሴ ሠላሳ በዚች ቀን ከዐሥራ ስድስቱ ነቢያት አንዱ ታላቅ ነቢይ ሚልክያስ አረፈ። ይህም ነቢይ የእስራኤል ልጆች ከተሰደዱበት ከባቢሎን ሀገር በተመለሱ ጊዜ የ #እግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፋቸው ገሥጿቸዋል።

ሁለተኛም ነቋር ስለሆነ መሥዋዕት ስለ አሥራትና በኵራት ገሥጿቸዋል። በዚህ ነቢይ አንደበት #እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሯልና ርኅራኄ አድርጋችሁ ምጽዋትን መጽውቱ፣ ዐሥራቴንና በኵራቴንም አስገቡና እስቲ ፈትኑኝ እኔ ከሰማይ ዝናሙን ባላወርድላችሁ በረከትንም አስቲበቃችሁ ባልጨምርላችሁ የምድራችሁንም ፍሬ ነቀዝና መሰክ እንዳይበሉት እከለክላለሁ።

ዳግመኛም ከክብር ባለቤት #መድኃኒታችን_ክርስቶስ አስቀድሞ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ መምጣቱ ስለ ነቢዩ ኤልያስም ተናገረ። ደግሞ ስለ አይሁድ የሥርዓተ ክህነት ፍጻሜ ተናገረ በአሕዛብም አገር ውስጥ ለ #እግዚአብሔር የሚቀበላቸውን መሥዋዕት የሚያሳርጉ ዕውነተኞች ንጹሐን ካህናት እንዳሉ ገለጠላቸው።

በበጎ ተጋድሎውም #እግዚአብሔርን ከአገለገለ በኋላ ከዚህ ዓለም በመፍለስ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ነብይ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያው_ቅዱስ_እንድርያስ

በዚችም ቀን #ጌታችን በባሕር ውስጥ ለሐዋርያ እንድርያስ በሊቀ ሐመር አምሳል ተገልጦ ድንቅ ተአምር አደረገለት።

እንድርያስም #ጌታችንን በመርከብህ አሳፍረን ነገር ግን የምንከፍልህ የመርከብ ዋጋ የለንም አለው። በሊቀ ሐመር የተመሰለ #ጌታችንም ስለምን የላችሁም አለው እንድርያስም በከረጢታችን ወርቅን፣ ብርን እንዳንይዝ ስለአዘዘን ነው አለው። #ጌታችንም እንዲህ ከሆነ ወደ መርከቤ ወጥታችሁ ተሳፈሩ አላቸው ያንጊዜም ወደ መርከብ ወጥተው ተሳፈሩ።

ከዚህም በኋላ #ጌታችን እንድርያስንና ደቀ መዛሙርቱን ከባሕሩ ማዕበል የተነሣ መታገሥ እንድትችሉ ተነሥታችሁ እንጀራ ብሉ አለ። እንድርያስም አድንቆ እንዲህ አለው በመንግሥተ ሰማያት የሕይወት እንጀራ #እግዚአብሔር ይስጥህ። ደቀ መዛሙርቱ ግን በባሕር ላይ ጉዞ ስለአልለመዱ ከባሕሩ ማዕበል ፍርሀት የተነሣ መብላት መነጋገርም ተሳናቸው ።

#ጌታችንም እንድርያስን ደቀ መዛሙርትህን ወደ ምድር እንዲወርዱ እዘዛቸው ሲፈሩ አያቸዋለሁና ይህ ካልሆነ እንዳይፈሩ አንተ የ #ኢየሱስ ደቀ መዝሙሩ ከሆንክ ጣዕም ባለው ቃል አስተምራቸው እነሆ ከየብስ ርቀናልና አለው። #ጌታችንም መርከቡን መቅዘፍ ጀመረ እንድርያስም ማስተማርና ማጽናናት ያዘ በልቡም ጸለየ ያን ጊዜም ከባድ እንቅልፍን አንቀላፉ ስለተኙለትም እንድርያስ ደስ አለው።

እንድርያስም ወደ #ጌታችን ተመልሶ እንዲህ አለው ዐሥራ አራት ጊዜ በባሕር ላይ ጒዞ አድርጌአለሁ እንዳንተ የሚቀዝፍ አላገኘሁም። #ጌታም መልሶ እንዲህ አለው እኛስ በባሕር ላይ ስንጓዝ ሁል ጊዜ እንቸገራለን። ነገር ግን አንተ የክብር ባለቤት የ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደሆንክ ባሕር ስለአወቀችህ ማዕበሏን በአንተ ላይ አላነሣችም እንድርያስም በታላቅ ቃል እንዲህ ብሎ ጮኸ። የክብር ባለቤት #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመሰግንሃለሁ ከሚያከብርህ ሰው ጋር ተገናኝቼ ተነጋግሬአለሁና።

ከዚህም በኋላ #ጌታችን እንድርያስን እንዲህ አለው አንተ የ #ክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ ነህና ንገረኝ። አይሁድ የ #እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ስለምን አላመኑም የሠራውን ብዙ ድንቅ ተአምርን ሰምተናልና አለው። እንድርያስም እንዲህ አለው አዎን ወንድሜ እርሱ የ #እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ገልጦልናል አንካሶችንም በትክክል እንዲሔዱ አድርጓልና፣ ደንቆሮዎችንም አሰምቷልና፣ ዲዳዎችንም አናግሮአልና፣ ለምጻሞችንም አንጽቷልና፣ ውኃውንም ወይን አድርጓልና፣ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣን አንሥቶ ያዘ ሕዝቡንም በመስክ ሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ ሣሩም እንጀራ እስቲለብስ ድረስ በልተው ጠገቡ የተረፈውንም በብዙ ቅርጫቶች አነሣን ይህም ሁሉ ሲሆን አላመኑም።

#ጌታ_ኢየሱስም እንዲህ አለው ይህን ያደረገ በግልጥ ነው ወይስ በሥውር። እንድርያስም እንዲህ አለው ይህንስ በግልጥ ነው ያደረገ በሥውር ያደረገውም አለ ግን የምትፈትነኝ መሰለኝ #ጌታችንም እንዲህ አለው ወንድሜ ሆይ ልቤን ደስ ስለሚላት ነውና ንገረኝ።

እንድርያስም እንዲህ አለው ልጄ ሆይ በጎ ሥራህን ሀሉ #እግዚአብሔር ይፈጽምልህ አሁንም ስማ #ጌታችን ያደረገውን ተአምር እኛ ዐሥራ ሁለታችን ሐዋርያቶቹ ከእርሱ ጋራ ስንጓዝ ከሊቃነ ካህናትና ከሕዝቡ ብዙዎች አሉ። ወደ ምኵራብም ደረስን #ጌታችንም እንዲህ አለ በሰማይ ባሉ በኪሩቤልና በሱራፌል አምሳል በምድር ላይ ሰው የሠራትን ይቺን የተቀረጸች ሥዕል ታያላችሁን።

ከዚህም በኋላ ወደሥዕሊቱ ተመልሶ ብልህ ሰው የተጠበበብሽ የሰማያውያን መልክን ያደረግሽ አንቺን እላለሁ ከቦታሽ ተነቅለሽ ውረጂ የካህናት አለቆችንም ወቀሻቸው እኔም ዕሩቅ ብእሲ ወይም #እግዚአብሔር እንደሆንኩ መስክሪ አላት። ወዲያውኑ ከቦታዋ ተነቅላ ወረደች እንደሰውም በመናገር እንዲህ አለች እናንተ የደነቆራችሁ አይሁድ የራሳችሁ መደንቆር ያልበቃችሁ ሌሎችንም ለማደንቆር የምትሹ ለድኅነታችሁ ሰው የሆነ #እግዚአብሔርን እንዴት ዕሩቅ ብእሲ ትሉታላችሁ አስቀድሞ ሰውን የፈጠረው በንፍሐት ልጅነትንም የሰጠው ይህ ነው።

አብርሃምን የተናገረው፣ ይስሐቅንም ከመታረድ ያዳነው፣ ያዕቆብንም ወደ አገሩ ያስገባው ይህ ነው ለሚፈሩት በረከትን የሚሰጥ ለማይታዘዙለት ቅጣትን የሚያዘጋጅ ይህ ነው ።

እውነት እነግራችኋላሁ እናንተ ስለምትክዱት ሕጉንና ሥርዓቱንም ትለውጣላችሁና ስለዚህ እነሆ መስዋዕታችሁ ይሻራል ምኵራቦቻችሁም በዋሕድ ወልደ #እግዚአብሔር ስም አብያተ ክርስቲያናት ይሆናሉ። ይህንንና የሚመስለውን ተናግራ ዝም አለች።

እኛም የካህናት አለቆችን መልሰን እንዲህ አልናቸው እነሆ ቅርጺቱ ሥዕል ተናግራ ወቀሰቻችሁ ታምኑ ዘንድ ይገባችኋል። የካህናት አለቆችና አይሁድም እንዲህ አሉን ይህ የሚያናግረው በሥራይ ነው አብርሃምን በወዴት አገኘው ከሞተ ዘመኑ ብዙ ነውና።

#ጌታ_ኢየሱስም ወደ ቅርጺቱ መለስ ብሎ እንዲህ አላት አብርሃምን እንዳነጋገርኩት አላመኑምና ሔደሽ እንዲህ በይው። አስቀድሞ አዳምን የፈጠረው፣ አንተንም ወዳጁ ያደረገህ፣ አንተ ልጆችህ ይስሐቅና ያዕቆብን ይዘህ ተነሥ ከመቃብርም ወጥተህ ወደዚህ ኑ የካህናት አለቆችን ትወቅሱአቸው ዘንድ እኔ የማውቃችሁና የተነጋገርኳችሁ መሆኔን አስረዷቸው። ቅርጺቱም ሥዕል ይህን ሰምታ እያየናት ሔደች ወደ አብርሃምም መቃብር ደርሳ በውጭ ቁማ ጠራቻቸው። ወዲያውኑ ከሦስቱ አርእስተ አበው ጋር ዐሥራ ሁለቱ ወጡ ከእኛ ውስጥ ወደ ማን ነው የተላክሽ አሏት። ቅርጺቱም እንዲህ ብላ መለሰች ወደ ሦስቱ የአባቶች አለቆች ነው እናንተ ግን እስከ ትንሣኤ ሙታን ድረስ ተኙ ያን ጊዜም ወደ መቃብራቸው ተመለሱ።
#ነቢዩ_ሚልክያስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

“ሚልክያስ” ማለት “መልአክ፣ ሐዋርያ፣ መልእክተኛ” ማለት ነው፡፡ ጥር ፰ ቀን የሚነበበው ስንክሳር እንደሚያስረዳው ነቢዩ ሚልክያስ የተወለደው ሕዝቡ ከፄዋዌ (ከምርኮ) ከተመለሱ በኋላ ነው፡፡ ከሕፃንነቱ አንሥቶም የ #እግዚአብሔርን መንገድ የሚወድ ነበር፡፡ ሕዝቡም ይኽን አካኼዱን አይተው እጅግ ያከብሩት ነበር፡፡ ይኽን መልካምነቱንም አይተው “ከ #እግዚአብሔር የተላከ ነው” ሲሉ ስሙን ሚልክያስ ብለው ጠሩት፡፡

ነቢዩ ሚልክያስ ከጸሐፍት ነቢያት የመጨረሻው ነቢይ ነው፡፡ ከሐጌና ከዘካርያስ በኋላም በነቢይነት አገልግሏል፡፡ ከ፬፻፶-፬፻ ቅ.ል.ክ. ላይ እንደነበረም ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ዕዝራና ነህሚያ ቤተ አይሁድን በሚስተካክሉበት ጊዜ ሚልክያስም ተባባሪያቸው ነበር፡፡

➛በነቢዩ ዙረያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ

➛በምርኮ የነበሩት አይሁድ በ፭፻፴፰ ቅ.ል.ክ. ላይ ከምርኮ ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚችሉ ሲነገራቸው ከኹለት ቡድን ተከፍለዋል፡፡ አንደኛውና የሚበዛው ቡድን ወደ ተስፋይቱ ምድር መመለስን ያልወደደና በባቢሎን አገር በሀብትና ንብረት የተደራጀ ነው፡፡ ይኼ ቡድን ምንም እንኳን በባዕድ አገር የሚኖር ቢኾንም ባርነቱ የተመቸው ይኽንንም ዓለም የወደደ ነው፡፡ ይኼ ቡድን #እግዚአብሔር ለአባቶቹ የገባውን ቃል ኪዳን ለመካፈል ያልፈለገ ቡድን ነው፡፡ በሕገ ኦሪቱ መሠረት #እግዚአብሔርን እያመለከ ለመኖር ያልፈቀደ ቡድን ነው፡፡

➛ኹለተኛውና የሚያንሰው ቡድን ደግሞ ወደ ተስፋይቱ ምድር የተመለሰው ነው፡፡ ይኼ ቡድን ከምርኮ ሲመጣ የኢሩሳሌምን አጥር፣ ቤተ መቅደሱን ለመሥራት፤ እንዲኹም የቀድሞውን አምልኮተ #እግዚአብሔር ለመመለስ ነበር፡፡ ነገር ግን ከእነዚኽም መካከል ቤታቸውን ለመሸላለም “የ #እግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ዘመን ገና ነው” የሚሉ ነበሩ፡፡ አኹንም ከእነዚኽ ከተመለሱት ቅሪቶች መካከል ምንም እንኳን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ቢያከናውኑም አካኼዳቸው ግን ከልብ አልነበረም፡፡ መሥዋዕታቸው የቃየን መሥዋዕት ነበር፡፡ ሲዠምር “የ #እግዚአብሔር ማዕድ አስናዋሪ ነው” ይላሉ፡፡ በፊቱ የተዘጋጀ እኽሉም “አባር የመታው እንክርዳድ ነው” ይላሉ፡፡ እነርሱም ለመሥዋዕት ዕውሩን አንካሳውን እንስሳ ያመጣሉ /፩፡፰/፡፡

#ነቢዩ_ሚልክያስ የተላከበት ምክንያትም ይኽን አካኼዳቸውን እንዲያስተካክሉ ለማሳሰብ ነበር፡፡
#ነቢዩ_ሚልክያስ በነገሥታቱ ዘመን እንደነበረው ዓይነት ስብከት አልሰበከም፤ የባዕድ አምለኮ ዐፀዶችን እንዲያፈርሱም አልተናገረም፡፡ ልክ እንደ ዕዝራ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አላሳሰባቸውም፤ ልክ እንደ ነህምያም የኢየሩሳሌምን አጥር ቅጥር እንዲሠሩ አላሳሰባቸውም፡፡ ወደ ውሳጣዊ ሕይወታቸው ዘልቆ በቅድስና ከ #እግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንዲኖራቸው አሳሰባቸው እንጂ፡፡ #እግዚአብሔር በእውነትና በመንፈስ የሚያመልኩት አምላክ ነውና ከምንም በፊት ውሳጣዊ ማንነታቸውን ወደ አገራቸው ወደ ሰማይ እንዲመልሱ፣ የነፍሳቸው የኢየሩሳሌምን አጥር ቅጥር እንዲሠሩ ነበር ያሳሰባቸው፡፡

#ትንቢተ_ሚልክያስ

ትንቢተ ሚልክያስ እጅግ መሳጭና የ #እግዚአብሔር ፍቅር እንደምን ጥልቅ እንደኾነ የምናነብበት መጽሐፍ ነው፡፡ #እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በሙሉ ያለማዳለት ይወዳል፡፡ #እግዚአብሔር ሲወድ አንዱን በመጥላት ሌላውንም በመውደድ አይደለም፡፡ ያለ ማዳላት ኹላችንም ይወደናል እንጂ፡፡ ሰዎች በ #እግዚአብሔር ዘንድ የተጠሉ የሚኾኑት ከራሳቸው ክፋት የተነሣ ነው፡፡ ሕጉንና ትእዛዙን ሳያከብሩ ሲቀሩ #እግዚአብሔር አይቀበላቸውም፡፡ አፍአዊ በኾነ አምልኮ #እግዚአብሔርን መቅረብ ወደ ሕይወትም መጋበዝ አይቻልምና እነዚኽ ሰዎች በ #እግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነት የሌላቸው ይኾናሉ፡፡ በትንቢተ ሚልክያስ የምናገኘው አንዱ አንኳር ነጥብ ይኸው ነው /፩፡፪-፭/፡፡

ነቢዩ ሚልክያስም ለዚኹ ኹሉ ችግር መፍትሔው አንድና አንድ ብቻ እንደኾነ ይሰብካል፤ ይኽ ከ #እግዚአብሔር የተቀበለውንም መልእክት ለሕዝቡ ያስተላልፋል፡፡ “ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለኹ ይላል የሠራዊት #ጌታ_እግዚአብሔር” በማለት /፫፡፯/፡፡ ይኽ ለሰው ኹሉ የተከፈተ በር ነው፡፡ የእኛ ደንዳናነት ካልኾነ በስተቀር ይኽን የድኅነት በር መዝጋት የሚችል አካል የለም፡፡ እንኳንስ ፍጡር ይቅርና #እግዚአብሔርም ቢኾን ስለማይችል ሳይኾን ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ይኽን በር በማንም ሰው ፊት አይዘጋውም፡፡ #እግዚአብሔርስ እርሱ እንዳይገባ የዘጋንበትን በር እንድንከፍትለት ያንኳኳል እንጂ አይዘጋውም፡፡ “ወድጃችኋለኹ ይላል የሠራዊት ጌታ #እግዚአብሔር” /፩፡፪/፡፡

ትንቢተ ሚልክያስን ገና ማንበብ ስንዠምር ከምርኮ የተመለሰው ሕዝብ አንድን ነገር ጠብቆ እንደመጣ እንገነዘባለን፡፡ ሕዝቡ አፍአዊ የኾነ በረከትን ሽቶ እንደ ነበር እንረዳለን፡፡ ከዚኽ በፊት ነቢያቱ ስለ መሲሑ የተናገሩት ኹሉ በጊዜአቸው የሚፈጸም መስሎአቸው እንደ ነበር እናስተውላለን፡፡ የዳዊት ድንኳን እንደገና በዘመናቸው እንደምትሠራ፥ ፈርሶና ተዳክሞ የነበረው መንግሥታቸውም እንደገና አንሰራርቶ በዓለም ላይ ገናና መንግሥት እንደሚኾን ገምተው እንደ ነበር እንረዳለን፡፡ እነርሱ እንዳሰቡት አፍአዊ የኾነ ነገር ሳይፈጸም ሲቀር ግን ግርምት ይዞአቸው #እግዚአብሔርን፡- “በምን ወደድኸን?” እንዳሉት እናነባለን /፩፡፪/፡፡ እንዲኽ ዓይነት የግርምትና የመደነቅ ንግግርም በብዙ ቦታ ላይ ሲናገሩት እናገኛቸዋለን፡፡ “ስምኽን ያቃለልነው በምንድነው?” /፩፡፮/፤ “ያረከስንኽ በምንድነው?” /፩፡፯/፤ “ያታከትነው በምንድነው?” /፪፡፲፯/፤ “የምንመለሰው በምንድነው?” /፫፡፯/፤ “የሰረቅንኽ በምንድነው?” /፫፡፰/፤ “በአንተ ላይ ድፍረት የተናገርነው በምንድነው?” /፫፡፲፫/፤ “ትእዛዙንስ በመጠበቅ በሠራዊት #ጌታ#እግዚአብሔር ፊት ኀዘንተኞች ኾነን በመኼድ ምን ይረባናል?” /፫፡፲፬/ እንዲል፡፡ #እግዚአብሔር ግን እነዚኽ ሰዎች ምድራዊውን ሳይኾን ሰማያዊውን፣ ጊዜአዊውን ሳይኾን ዘለዓለማዊውን፣ አፍአዊውን ሳይኾን ውሳጣዊውን፣ ብልና ዝገት የሚያገኘውን ሳይኾን በሰማያዊው መዝገብ የተቀመጠውን እንዲሹ ይጠራቸዋል፡፡ ነውረኛ መሥዋዕትን እያቀረቡ #እግዚአብሔርን ከመሸንገል ተመልሰው /፩፡፲፬/፣ የግፍ ሥራቸውን በልብስ መክደንን ትተው /፪፡፲፮/፣ “ክፉን የሚያደርግ ኹሉ በ #እግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው” ፥ እንዲኹም “የፍርድ አምላክ ወዴት አለ?” /፪፡፲፯/፣ “የሚታበዩትን ሰዎች ብፁዐን እንላቸዋለን” እያሉ /፫፡፲፭/ እግዚአብሔርን ከመፈታተን ተመልሰው ስሙን እንዲፈሩና የክፋት በረዶአቸው በጽድቅ ፀሐዩ እንዲቀልጥላቸው፥ በሕይወትም እንዲኖሩ ይጠራቸዋል /፬/።

በአጠቃላይ መጽሐፉ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ፥ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር፥ … የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ከቅዱሳን ኹሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቀቱም ምን ያኽል መኾኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የ #ክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ …” እንዳለው /ኤፌ.፫፡፲፮-፲፱/ #እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር እንደምን ጥልቅ እንደኾነ፣ የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ የሚከፍት የተትረፈረፈው የ #እግዚአብሔር ጸጋ ለሰው ልጆች እንደምን ብዙ እንደኾነ፣ ከአፍአ ሳይኾን ከልቡ የተመለሰ ሰው ምን እንደሚያገኝ የሚያስረዳ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡ ድኅነትን
#ጳጒሜን_5

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጳጒሜን አምስት በዚህች ቀን #የአባ_በርሱማ#የነቢዩ_አሞጽ እና #የአባ_ያዕቆብ_ዘምስር የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_በርሱማ

ጳጒሜን አምስት በዚህች ቀን የከበረ አባት ከልብስ ተራቁቶ የሚኖር የብርቱ ልጅ አባ በርሱማ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ በምስር አገር እጅግ ባለጸጎች ነበሩ እነርሱም #እግዚአብሔርን የሚፈሩ መጻተኞችንም በፍቅር የሚቀበሏቸው በ #እግዚአብሔርም በሕጉ ሁሉ ጸንተው የሚኖሩ ናቸው።

ይህን ቡሩክ በርሱማን በወለዱት ጊዜ በፈሪሀ #እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትንም ሁሉ በማስተማር አሳደጉት። ከዚህም በኋላ ወላጆቹ አረፉ የእናቱም ወንድም ወላጆቹ የተውለትን ገንዘብ ሁሉንም ወሰደ አባ በርሱማም አባትና እናቱ የተውለትን ገንዘብ የእናቱ ወንድም እንደ ወሰደ አይቶ የዓለምን ኃላፊነት አሰበ። እንዲህም አለ መድኃኒታችን ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ይጣላት ስለእኔም ሰውነቱን የጣላት ያገኛታል ብሏል።

ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን በሰጠ ነበር። የሰው ልጅ በአባቱ ጌትነት ከመላእክቶቹ ጋር ይመጣ ዘንድ አለውና ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ይከፍለዋል።

ይህንንም ብሎ ከዓለም ወጣ በበጋ ቃጠሎ፣ በክረምት ቅዝቃዜ ልብስ ሳይለብስ በአምስት ኮረብታዎች ላይ ኖረ። ወገቡንም በማቅ መታጠቂያ ይታጠቃል በልቡም እንዲህ ይላል በርሱማ ሆይ በሚያስፈራ ዕውነተኛ ፈራጅ ፊት ትቆም ዘንድ አለህ እኮን። ሁልጊዜም በጾም በጸሎት በስግደት በቀንና በሌሊት ይተጋ ነበር። በሚመገቡም ጊዜ በውኃ የራሰ ደረቅ ቂጣ ይመገባል ቆዳውም ከአጥንቱ ጋር ተጣበቀ።

ከዚያም ቦታ ሊሸሽ ወደደ ከንቱ የሆነ የሰውን ምስጋና ፈርቷልና በምስር ወዳለት የቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሰ በዚያም በጾም በጸሎት በስጊድ እየተጋደለ ሃያ አምስት ዓመት ኖረ።

በዚያችም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በዋሻ ውስጥ ታላቅ ዘንዶ አለ ዘንዶውንም ከመፍራት የተነሣ ሰው መብራትን ማብራት የማይችል ነው።

#እግዚአብሔርም የዚህን ቅዱስ የአባ በርሱማን ደግነቱን ሊገልጥና በእጆቹም ድንቆች ተአምራትን ለማድረግ በወደደ ጊዜ አባ በርሱማ ወደዚያች ዋሻ ገባ ወደ #እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ጸለየ የሕያው #እግዚአብሔር ልጅ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ እባቡን ጊንጡን እንረግጥ ዘንድ በጠላት ኃይል ላይ ሁሉ ሥልጣንን የሰጠኸን አንተ ነህ። አሁንም በዚች ዋሻ ውስጥ በሚኖር ከይሲ ላይ ታሠለጥነኝ ዘንድ እለምንሃለሁ ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

ከዚህም በኋላ ራሱን በመስቀል ምልክት አማተበ እንዲህም እያለ ዘመረ በተኲላና በእባብ ላይ ትጫማለህ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። ከዚህም በኋላ ያንን ዘንዶ በእጁ ይዞ እንዲህ አለው ከእንግዲህ ገራም ሁን ታጠፋ ዘንድ ሥልጣን አይኑርህ ኃይልም ቢሆን በማንም ላይ ከሰው ወገን በአንዱ ላይ ክፉ ሥራ አታደርግ የሚሉህን ሰምተህ የምትታዘዝ ሁን እንጂ በዚያን ጊዜም አንበሶች ለነቢዩ ዳንኤል እንደተገዙ ያ ዘንዶ ከአባ በርሱማ እግሮች በታች ተገዢ ሆነ።

ከዚህም በኋላ አባ በርሱማ በመራብ በመጠማት ተጋድሎውን ጨመረ በየሁለት ቀን፣ በየሦስት ቀን፣ በየሰባት ቀን እያከፈለ ብርሃን በላዩ እስቲወጣ ያለ ማቋረጥ የሚጾም ሆነ። ለጸሎት በሚቆም ጊዜ ከይሲው ከርሱ ይርቃል በሚቀመጥም ጊዜ ሲጠራው ወደርሱ ይመጣል።

በዚችም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የውኃ ጒድጓድ አለች ወደርሷ በመውረድ ሁል ጊዜ ከማታ እስከ ንጋት ከውስጧ ገብቶ ያድራል በክረምትም በበጋም እንደዚህ ያደርጋል መላዋን ሌሊትም በውስጥዋ እየጸለየ ያድራል።

የሚመገበውም የደረቀና የሻገተ ቂጣ ሲሆን የሚጠጣውም የከረፋ ውኃ ነው። የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን አዘውትሮ ያነባል ይልቁንም የዳዊትን መዝሙር አባቶችም ሥጋቸውን ለማድከም ያደረጓቸውን ትኀርምቶች በማንበብ ስለዚህ ትኀርምትን ንጽሕናን ወደደ ለሰዎችም እንዲህ እያለ ጠቃሚ ሥራዎችን ያስተምራል ያለ ልብ ንጽሕና በቀር አንዱ እንኳን የ #እግዚአብሔር መንግሥት ማየት አይችልም ኃጢአት ሁሉ ከንስሓ በኋላ ይሠረያልና።

ለክርስቲያን ወገኖችም እንዲህ ያስተምራቸዋል ከ #እግዚአብሔርም ተአምራት የማድረግ ሀብት ተሰጠው ከገድሉም ለሰው የገለጥነው ጥቂቱን ነው።

የዚህም አባት አርአያው የሚያምር መልኩም በብርሃን ያሸበረቀ ገጽታው ደስ የሚል ነው። ጥሪት በማጣቱም ደስ ይልዋልና። ከዓለማዊ ልብስ የተራቆተ ዓለምን ከማግኘትም የራቀ ነው። ቀድሞ ከቤቱ ከወጣ ጀምሮ የቀይ ግምጃ ጨርቅ በማገልደም ሥጋውን ይሸፍናል በክረምትም በበጋም የቀን ሐሩርን የሌሊት ቊርን ይታገሣል በጐኑና በምድር መካከል ምንጣፍ አላደረገም ወደ ሕይወት አገር ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት የሚያደርስ ተጋድሎን እንደዚህ ተጋደለ።

ከክፉዎች ሰዎችና ከክፉዎች አጋንንት ብዙ ጊዜ ኀዘን ፈተና አግኝቶታል ከዚህም ሁሉ ጋር በዚህ ጭንቅ በሆነ ሥራ የረዳው #እግዘሐአብሔርን ፈጽሞ ያመሰግነዋል። ይህንን በጎ የገድል ጒዞ በተጓዘ ጊዜ ሰዎች ዜናውን ሰሙ ሽማግሎችም ጐልማሶችም ከእነርሱ በጽነት የተሰነካከለ ወይም ከጠላት ሰይጣን ፈተና ያገኘው ወይም የመንፈስ ደዌ ያገኘው ሁሉ መሪና አጽናኝ ይሆናቸው ዘንድ ተመኝተውት ፈለጉት ከእርሱ ፈውስ ያገኙ ዘንድ መጡ።

ይህ የከበረ አባ በርሱማ በዚህ የጽና ተጋድሎ ሠላሳ ዓመታትን በፈጸመ ጊዜ #እግዚአብሔርንም አገልግሎ ከዚህ በኋላ ጳጒሜን አምስት በዚች ቀን በሺህ ሠላሳ ሦስት ዓመተ ሰማዕታት በሰላም በፍቅር አንድነት አረፈ።

ከዚህ አስቀድሞ ደቀ መዝሙሩ ቀሲስ ዮሐንስ በልቡ እንዲህ አለ ከአባታችን በርሱማ በኋላ እንግዲህ ስዎችን ማን ያጽናናቸዋል። ደቀ መዝሙሩ ያሰበውን በመንፈስ ቅዱስ አውቆ በንጹሕ አንደበቱ እንዲህ ብሎ መለሰለት። ልጄ ዮሐንስ ሆይ የቶባል ልጅ አባ በርሱማ ብሎ ስሜን የሚጠራኝን ሁሉ ከእሳቸው እንደማልርቅ ዕወቅ እኔ እነሆኝ ብዬ የክብር ባለቤት ከሆነ ከ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ዘንድ የሚሻውን ሁሉ እፈጽምለታለሁ።

ከዚህም በኋላ ወደ ግራው ተመልክቶ እነሆ ፈለጉብን ተመራመሩን ከክፋ ሥራ ምንም ምን በእኛ ላይ አላገኙም አለ።

ከዚህም በኋላ ደግሞ ደቀ መዝሙሩ አብርሃምን ቢላዋ ወይም መቊረጭት ስጠኝ አለው መቁረጫውንም ተቀብሎ ምላሱን ቆርጦ ጣላትና #እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው የሚያስፈራኝ ምንድነው የሚለውን መዝሙር እስከ መጨረሻው ይዘምር ጀመር።

ከዚህም በኋላ አዳኝ በሆነ #መስቀል ምልክት ፊቱን አማተበ ነፍሱንም በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጠ ብርሃናውያን መላእክትም የከበረች ንጽሕት ነፍሱን ተድላ ደስታ ወደ ሚገኝባት ገነት አሳረጓት።

መነኰሳቱም ከበግ ጸጒር በተሠራ ንጽሕ በሆነ በነጭ ባና ገነዙት ተሸክመውም ወስደው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት። ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰማንያኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ መጣ ከእርሱ ጋርም ኤጲስቆጶሳት ቀሳውስትና ዲያቆናት የምስር አገር ታላላቆችና ብዙ የክርስቲያን ወገኖች በአንድነት ሁነው በመዘመርና በማመስገን በታላቅ ክብር ሥጋውን ገንዘው ቀበሩት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ሰው በአባ በርሱማ በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ነቢዩ_አሞጽ
#ነቢዩ_አሞጽ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“አሞጽ” ማለት “ሽክም፣ ጭነት” ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በዚኽ ስም የሚጠሩ ሦስት ሰዎች ያሉ ሲኾን እነርሱም የነቢዩ ኢሳይያስ አባት /ኢሳ.፩፡፩/፣ የምናሴ ልጅ ንጉሥ አሞጽ /፪ኛ ነገ.፳፩፡፲፰/ እንዲኹም ለዛሬ የምናየውና ከደቂቀ ነቢያት አንዱ የኾነው ነቢዩ አሞጽ ናቸው፡፡

➛የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት እንደሚያስረዳው የነቢዩ አሞጽ አባት ቴና ሲባል እናቱ ደግሞ ሜስታ ትባላለች፡፡ ነገዱም ከነገደ ስምዖን ወገን ነው፡፡

📌ነቢዩ አሞጽ ከመጠራቱ በፊት የላም ጠባቂና የወርካ ለቃሚ ነበር፡፡ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅም አልነበረም፤ #እግዚአብሔር በጐችን ከመከተል ጠራው እንጂ /አሞ.፯፡፲፬-፲፭/፡፡ ምንም እንኳን ከግብርና የመጣ ቢኾንም ንግግር የማይችል፣ ያልተማረ፣ ድፍረት የሌለው ነቢይ አልነበረም፡፡

ነቢዩ አሞጽ ምንም እንኳን ከደቡባዊው መንግሥት ቢኾንም እንዲያስተምር የተላከው ለሰሜናዊው ክፍልም ጭምር ነበር፡፡
በራሱ መጽሐፍ እንደነገረን በዘመኑ የነበረው የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን ሲኾን በእስራኤል የነበረው ንጉሥ ደግሞ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ይባላል /አሞ.፩፡፩/፡፡ በነቢይነት ያገለገለውም ከ፯፻፹፯-፯፴፭ ቅ.ል.ክ. ላይ ነው፡፡

📌በነቢዩ አሞጽ ዙርያ የነበረው ነባራዊ ኹኔታ
ነቢዩ አሞጽ በሚያገለግልበት ወራት የይሁዳና የእስራኤል ኃጢአት ጣራ የነካበት ጊዜ ነበር፡፡ ከእኛ ዘመን ጋርም በእጅጉ ይመሳሰላል፡፡ አንባቢያን ይኽን ቀጥሎ ከተጠቀሰው ጋር ማነጻጸር ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳን በአንጻራዊ መልኩ ነቢዩ አሞጽ በነበረበት ወራት ሰላም የነገሠበት ቢኾንም ሕዝቡ ግን የ #እግዚአብሔር ሕግ ጥሏል፤ ትእዛዙን አይጠብቅም፡፡ ባለጸጐች የሚባሉት በሀብት ላይ ሀብት ጨምረው የሚኖሩ ቢኾኑም ድኾቹ ግን ከዕለት ወደ ዕለት ከድጡ ወደ ማጡ የሚኼዱ ነበሩ፡፡ ጻድቁን ስለ ብር፣ ችግረኛውን ስለ አንድ ጥንድ ጫማ የሸጡበት ጊዜ ነበር፡፡ የድኾችን ራስ በምድር ትቢያ ላይ ይረገጣል፤ የትሑታን መንገድ ይጣመማል፡፡ ቅዱሱን የ #እግዚአብሔር መንገድ ያረክሳሉ፡፡ አባትና ልጅ ለዝሙት ግብር ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፡፡ ጻድቁ በጽድቅ መንገድ ልኺድ ቢል ከእነርሱ ጋር ስላልተስማማ ያስጨንቁታል፡፡ እውነትን የሚናገር ሰው አምርረው ይጸየፉታል፡፡ #እግዚአብሔር  ነቢያቱን እየላከ ሐሳቡና ፈቃዱ ምን እንደኾነ ደጋግሞ ቢነግራቸውም አይመለሱም፡፡ ቅን ነገርን ማድረግ አያውቁም፡፡ ችጋረኛውን ይውጡታል፡፡ የአገሩን ድኻ ያጠፋሉ፡፡ ሚዛኑን አሳንሰው በሐሰት ይሸጣሉ፡፡ ንጹሕ እኽል ሳይኾን ግርዱን ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ድኻውን ይደበድቡታል፤ ይበድሉታል፤ ፍርድ ያጣምሙበታል፤ ያስጨንቁታል፤ ጉቦ ይቀበሉታል፡፡ በዚያም ላይ ቀረጥን ያበዙበታል፡፡ ለራሳቸው ግን ከተጠረበ ድንጋይ ቤቶችን ይሠራሉ፡፡ ያማሩ የወይን ቦታዎችን ይተክላሉ፡፡ ግፍንና ቅሚያን በአዳራሾቻቸው ያከማቻሉ፡፡ ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ይተኛሉ፡፡ በምንጣፋቸው ላይ ተደላድለው ይቀመጣሉ፡፡ አምጡ እንብላ እንጠጣ ይላሉ፡፡ ከበጐች መንጋ ጠቦቱን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ይበላሉ፡፡ በመሰንቆ ድምፅ ይንጫጫሉ (ይዘፍናሉ)፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ ካህናትና ነቢያት ለገንዘብ የሚሠሩ ነበሩ፡፡
በቅርብ ጊዜ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በአኹኑ ሰዓት የዓለማችን ሰማንያ ከመቶ ሃብትና ንብረት በሃያ ፐርሰንት ግለሰቦች ብቻ የተያዘ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ በዓለማችን ፍትሐዊ የኾነ የሃብት ክፍፍል የለም ማለት ነው፡፡ በአገራችን ያለውን ነባራዊ ኹኔታ ስናየውም ቢብስ እንጂ ከዚኹ አይሻልም፡፡ ነቢዩ አሞጽ በሚያገለግልበት ወራት የነበረው ኹናቴ ከአኹኑ ኹኔታ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል ያልነውም ከዚኽ ተነሥተን ነው፡፡
በሌላ መልኩ በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ምዕራፍ ፲፬ ከቁጥር ፳፫ እስከ ፍጻሜ ያለውን ኃይለ ቃል ስናነብ ኢዮርብዓም ወደ አምልኮ ጣዖት ማዘንበሉን እናነባለን፡፡
በሕዝቡ ዘንድ የነበረው የእምነትና የጸሎት ኹኔታ በእጅጉ የወደቀ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በዓላትን እንዲያከብሩ፣ የተቀደሰ ጉባዔ እንዲያደርጉ፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲኹም የእኽል የቊርባን እንዲያቀርቡ፣ በመሰንቆ እንዲያመሰገኑ የነገራቸውና ያዘዛቸው #እግዚአብሔር ራሱ ቢኾንም ነቢዩ ሆሴዕ፡- “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን ከሚቃጠለውም መሥዋዕት ይልቅ #እግዚአብሔርን ማወቅ እወዳለኹ” እንዳለ /ሆሴ.፮፡፮/ ግብራቸው እጅግ የከፋ ስለኾነ ይኽን ቢያቀርቡለትም አልተቀበላቸውም፡፡ “ዓመት በዓላችኹን ጠልቼዋለኹ፤ ተጸይፌውማለኹ፤ የተቀደሰውን ጉባዔአችሁ ደስ አያሰኘኝም፡፡ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችኹ የእኽሉን ቊርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ ለምስጋና መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም፡፡ የዝማሬኽንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆኽንም ዜማ አላደምጥም” ያላቸው ስለዚኹ ነው /አሞ.፭፡፳፩-፳፫/፡፡ መፍትሔውም #እግዚአብሔርን መፈለግ ብቻ መኾኑን ተናግሯል /አሞ.፭፡፬-፱/፡፡ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ መልካሙን እንዲፈልጉ፣ ይኽን ቢያደርጉም የሠራዊት ጌታ #እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንደሚኾን ተናግሯል /አሞ.፭፡፲፬-፲፭/፡፡

                 #ትንቢተ_አሞጽ

ከኋለኛው ዘመን ነቢያት የተናገረውን ትንቢት በመጻፍ የመዠመሪያው ነው፡፡ የአሞጽ ትንቢተ በአብዛኛው በእስራኤልና በአከባቢው ባሉ አገሮች ላይ የሚመጣውን ፍርድ ማስታወቅ ነው፡፡ ፵፩ ጊዜ “ #እግዚአብሔር እንዲኽ ይላል” እያለ መናገሩም ይኽንኑ ያስረዳል፡፡ የሚዠምረውም በአሕዛብ ላይ ማለትም በቂር፣ በኤዶም፣ በደማስቆ፣ በሶርያ፣ በቴማን፣ በጢሮስ፣ በሞዓብ ሊመጣ ያለውን ፍርድ በማስታወቅ ነው /አሞ.፩ ሙሉውን ያንብቡ/፡፡ ቀጥሎም በይሁዳና በእስራኤል ሊመጣ ያለውን ፍርድ ይናገራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከላይ ለመግለጥ እንደሞከርነው የሕዝቡ በግዴለሽነት መኖር ያመጣው መዘዝ ነው፡፡
ነቢዩ አሞጽ ክብር ይግባውና #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በተሰቀለበት ጊዜ ስለሚኾነው ተአምር ናግሯል፡፡ ሕዝብና አሕዛብ በክርስቶስ አንድ እንደሚኾኑ መናገሩም ቅዱሳን ሐዋርያት ጠቅሰዉታል /፱፡፲፩-፲፪፣ ሐዋ.፲፭፡፲፭-፲፰/፡፡

➛በአጠቃላይ መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1, ፍርድ በእስራኤል ጐረቤት አገሮች /፩:፩-፪፡፭/፤
2, ፍርድ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ /፪፡፮-፫፡፮/፤
3, ፍርድ በእስራኤል በደል ምክንያት /፫፡፩-፮፡፲፬/፤
4, ፍርድ በአምስት ዓይነት መንገድ /፯፡፩-፱፡፲/፤ በዚኽም መካከል የአሜስያስና የአሞጽ ታሪክ /፯፡፲-፲፯/፤
5, በፍጻሜው ዘመን ስላለው የእስራኤል ተስፋ /፱፡፲፩-ፍጻሜ/፡፡

የነቢዩ አሞጽ የመጨረሻው ዕረፍት
ስለ ነቢዩ አሞጽ የመጨረሻው ዕረፍት መረጃ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ግንቦት ፳፩ ላይ የሚነበበው ስንክሳርም ነቢዩ በዚያ ዕለት እንደሚታሰብ ከመናገር ውጪ ያለው ነገር የለም፡፡

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር!!
#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ እና #ነቢዩ_ኤልያስ

ቅዱስ ዮሐንስ በበርካታ መንገዶች ከነቢዩ ኤልያስ ጋር ተያይዟል፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መምጣትና መንገድ ጠራጊነት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
«እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የ #እግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ቴስቢያዊውን ኤልያስን እልክላችኋለሁ … እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል፡፡» /ሚል.4÷5-6/
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም የቅዱስ ዮሐንስን መወለድ ለአባቱ ለዘካርያስ በቤተ መቅደስ ሲያበሥረው እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
«… እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የከሐድያንንም ሐሳብ ወደ ጻድቃን ዕውቀት ይመልስ ዘንድ ሕዝብንም ለ #እግዚአብሔር የተዘጋጀ ያደርግ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል» /ሉቃ.1÷17/

በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ከመሲህ መምጣት በፊት የኤልያስን መምጣት ይጠብቁ ነበር፡፡ ለምሳሌ #ጌታችንን ደቀመዛሙርቱ «ጻፎች ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣ ዘንድ አለው ለምን ይላሉ?» ብለው ጠይቀውት ነበር፡፡ /ማቴ.17÷10፣ ማር.9÷11/
#ጌታችንም ኤልያስ ይመጣል ተብሎ የተነገረው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን እንዳስረዳቸው እነርሱም እንደተረዱ ቅዱስ ማቴዎስ ይነግረናል /ማቴ.17÷11-13/
«ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለችው «አዎን፤ ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ያቀናል፡፡ ነገር ግን እላችኋለሁ፡፡ ኤልያስ ፈጽሞ መጥቷል፤ የወደዱትንም አደረጉበት እንጂ አላወቁትም …» ከዚህም በኋላ ደቀመዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንደነገራቸው አወቁ፡፡»

ከአንድ ታላቅ እና ታዋቂ ሰው በኋላ የሚነሱ ደጋግ ሰዎችን በእዚያ በታላቁ ሰው ስም መጥራት በትንቢቶች ውስጥ የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ዳዊት እሥራኤላውያን የሚወዱትና ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ንጉሣቸው ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ካለፈ በኋላ #እግዚአብሔር ደጋግ ነገሥታትን እንደሚያስነሳላቸው ለእሥራኤል ተስፋ ሲሰጥ ዳዊትን አስነሳላችኋለሁ ይላቸው ነበር፡፡
«ባርያዬም ዳዊት በላያቸው ላይ ንጉሥ ይሆናል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል» /ሕዝ.37÷24/
«ለ #እግዚአብሔርም ለማስነሣላቸው ለንጉሣቸው ለዳዊትም ይገዛሉ» /ኤር.3ዐ ÷9/፡
አሁንም የተደረገው ይኸው ነው፡፡ አይሁድ ኤልያስን በጣም ይወዱትና ያከብሩት ነበር፡፡ አሁንም ድረስ ያሉ አይሁዳውያን የፋሲካን በዓል በሚያከብሩበት ዕለት ለማዕድ ሲቀመጡ «ለኤልያስ» ብለው አንድ ቦታ ይተዋሉ፤ የወይን ጠጅ የተሞላ ብርጭቆም ያስቀምጣሉ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ መምጣት «ኤልያስ ይመጣል» ተብሎ የተነገረው ለዚህ ነው፡፡ «እንደ ኤልያስ ያለ የኤልያስን ዓይነት ሥራ የሚሠራ ነቢይ ይወጣል» ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ለካህኑ ለዘካርያስ የተናገረው ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡ «…በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል…»

በእርግጥም ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን እና ነቢዩ ኤልያስን ብዙ የሚያመሳስሉአቸው ነገሮች አሉ፡፡
#አለባበሳቸው፡- የነቢዩ ኤልያስ አለባበስ በሁለተኛው መጽሐፈ ነገሥት እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፡፡ «እነርሱም ሰውየው ጠጉራም ነው፡፡ በወገቡም ጠፍር ታጥቆ ነበር አሉት፡፡ እርሱም ቴስብያዊው ኤልያስ ነው አለ» /2ኛነገ.1÷8/

#ትምህርታቸው፦ የሁለቱም ነቢያት ትምህርት ትኩረት የእስራኤል ሕዝብ ኃጢያታቸውን ትተው ወደ #እግዚአብሔር እንዲመለሱ ማድረግ ሲሆን፤ የሁለቱም ተግሳጽ የተሞላበት ነበር፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤልያስ «የ #እግዚአብሔር ከሆናችሁ የ #እግዚአብሔር ብቻ ሁኑ፤ የበአል /የጣኦት/ ከሆናችሁ የበአል /የጣኦት/ ብቻ ሁኑ» እያለ ጠንካራ ንግግሮች ይናገር ነበር፡፡

#ነገሥታትን መገሰጻቸው፡- ነቢዩ ኤልያስ ንጉሡን አክአብንና ንግሥቲቱ ኤልዛቤልን ናቡቴን ርስቱን ቀምተው በግፍ በማስገደላቸው ገስጿቸዋል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን አስመልክቶ ባስተማረው ትምህርት «በእርግጥም የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ትህርምት እጅግ የሚያስደንቅ ነበር፤ አይሁድንም በእርሱ ውስጥ ነቢዩ ኤልያሰን እንዲያዩ አድርጓቸዋል» ብሏል፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ ክብር እና መዓርጋት

ቅዱስ ዮሐንስ ክብሩ በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ የክብሩ ምስክሮችም #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ እና መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ናቸው፡፡
#ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ እንዲህ ሲል የመጥምቁን ክብር ተናግሯል፡፡
«ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጥታችኋል? ከነፋስ የተነሣ የሚወዛወዛውን ሸንበቆ ነው? ወይስ ምን ልታዩ መጥታችኋል ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን ነውን? እነሆ ቀጭን ልብስ የሚለብሱማ በነገሥታት ቤት አሉ? ምን ልታዩ መጥታችኋል ነቢይ ነውን? አዎን እርሱ ከነቢያት እጅግ ይበልጣል፤ እነሆ በፊትህ መንገድህን የሚጠርግ መልእክተኛዬን እልካለሁ ተብሎ ስለ እርሱ የተጻፈለት ይህ ነውና፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ ሴቶች ከወለዷቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም» /ማቴ.11÷7-11/
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም እንዲህ ሲል ክብሩን ተናግሮለታል፡- «እርሱ በ #እግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናል» /ሉቃ.1÷15/

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ «የቅዱስ ዮሐንስ ክብር እና ከፍ ከፍ ማለት ምንጮች ሁለት ናቸው፡፡» ይላሉ፡፡
1. በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ስለሆነ
ከመጥምቁ ዮሐንስ በፊት የ #እግዚአብሔር መንፈስ ወደ ብዙ ሰዎች መምጣቱ ተጽፏል፡፡ ለምሳሌ ያህልም
➛ሳሙኤል ሳኦልን ቀብቶ ባነገሠው ጊዜ «የ #እግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ወረደ» ተብሏል /1ኛሳሙ.10÷10/፡፡
➛ሳሙኤል ዳዊትን በንግሥና በቀባው ጊዜ «የ #እግዚአብሔር መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ መጣ» ተብሏል 1ኛ ሳሙ.16÷13፡፡
➛«የ #እግዚአብሔር መንፈስ ከሶምሶን ጋር ይሄድ ነበር» ተብሎም ተጽፏል /መሳ.13÷24/፡፡ ይሁን እንጂ የ #እግዚአብሔር መንፈስ «ሞልቶታል» የተባለ ግን ማንም አልነበረም፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ግን በ #መንፈስ_ቅዱስ የተሞላ ነበር፡፡ የከበረ እና ታላቅ በመሆኑ አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡
#መንፈስ_ቅዱስ የተሞላው ግን መቼ ነበር? በመንፈስ ቅዱስ የተሞላው ገና በማኅፀን ሳለ እናቱ ኤልሳቤጥ የእመቤታችንን የሰላምታ ድምፅ በሰማችበት ቅፅበት ነው፡፡
«ኤልሳቤጥም የ #ማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፤ ፅንሱ በማኅፀኗ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ መላባት» /ሉቃ.1÷14/
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል «ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል» ብሎ የተናገረው በዚህን ጊዜ ተፈጽሟል፡፡

2. ተጋድሎው
#መንፈስ_ቅዱስ ስጦታ በእኛ ሕይወት ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው እኛ በድርጊታችንና በተጋድሎአችን ስንጠብቀው፣ ስንንከባከበውና ስንሠራበት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ይህንን በሚገባ አድርጓል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ያደገው በበረሃ ውስጥ፣ በብሕትውና /በብቸኝነት/፣ የግመል ጠጉር እየለበሰ፣ አንበጣ እና የበረሃ ማር ብቻ እየተመገበ ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እንዲህ ብለዋል «እርሱ በበረሃው ውስጥ ጸሎትና ተመስጦን፣ ድፍረትን እና ፍርሃት አልባነትን፣ ጥንካሬን እና እምነትን ተምሯል፡፡ #እግዚአብሔር #እመቤታችንን አምላክን ፀንሣ ለመውለድ በቤተ መቅደስ እንዳዘጋጃት እርሱን ደግሞ ለመንገድ ጠራጊነት ተልእኮው በበረሃ አዘጋጅቶታል፤ እኛም የእነዚህ ነገሮች ባለቤት ለመሆን የብቸኝነትና የትህርምት ጊዜ የምናሳለፍበት የየራሳችን በረሃ ያስፈልገናል፡፡»

#ቅዱስ_ዮሐንስ መዓርጋት
#መስከረም_4

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም አራት በዚህች ቀን #ወንጌላዊው_ቅዱስ_ዮሐንስ ልደቱ ነው፣ የድባው #አቡነ_ሙሴ እረፍታቸው ነው፣ #ነቢዩ_ኢያሱ_ወልደ_ነዌ አረፈ፣ #አባ_መቃርስ_ሊቀ_ዻዻሳት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_ወንጌላዊ

መስከረም አራት በዚህች ዕለት ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ከእናቱ ማርያም ባውፍልያ ከአባቱ ዘበዴዎስ የተወለደበት ዕለት እንደሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን ለመስበክ ዕጣ የደረሰው እስያ ስለነበር ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን አስከትሎ ሄደ፡፡ ይኽችውም ኤፌሶን በጥንቱ በታናሽ እስያ በዛሬው የቱርክ ግዛት ውስጥ ከተማ ናት፡፡ ዛሬ ኢያዞሎክ ተብላ የጥንት ታሪኳ ጠፍቷል፡፡ አስቀድሞ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ሰብኮባታል፡፡ ደቀ መዝሙሩን ቅዱስ ጢሞቴዎስንም በከተማዋ ላይ ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ እርሱም በግፍ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ቅዱስ ዮሐንስን እየረዳው በከተማዋ ብዙ አገልግሏል፡፡ በኋላ ግን በግፍ ገድለውታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ኤፌሶን ለመሄድ በመርከብ ሲሳፈር መርከቡ በማዕበል ተሰበረ፡፡ ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን መዕበሉ ወደ አንዲት ደሴት አደረሰው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በመርከቡ ስባሪ ተንጠልጥሎ በባሕሩ ማዕበል መካከል 40 ቀንና 40 ሌሊት ከኖረ በኋላ ማዕበሉ ተፍቶ አብሮኮሮስ ካለበት ደሴት አደረሰውና ተያይዘው ኤፌሶን ከተማ ገቡ፡፡ የከተማይቱም ሰዎች እጅግ ክፉዎች ስለነበሩ መጀመሪያ ላይ ቅዱስ ወንጌልን መስበክ አልቻሉም ነበር፡፡ እነርሱም እጅግ ክፉዎች መሆናቸውን ስላወቀ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ዕጣው ሲደርሰው በሀዘን አልቅሶ ነበር፡፡ አሁንም ከተማው በገቡ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ምክንያት በመፍጠር ሮምና ለምትባል ሴት የውሽባ ቤቷ እሳት አንዳጅ ሆኖ አብሮኮሮስም ዕቃ አጣቢ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ የቀጠረቻቸው ሴትም እጅግ ታሠቃያቸው ጀመር፡፡ ባሮቿ እንደሆኑ ተስማምተው ስለጻፉላት ትደበድባቸውም ነበር፡፡

እነርሱም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ እየኖሩ እያለ በአንዲት ዕለት የአገረ ገዥው ልጅ ለመታጠብ ወደ ውሽባው ቤት ገባ፡፡ በውሽባ ቤቱም የሰይጣን ኃይል ስለነበረበት የመኰንኑን ልጅ አንቆ ገደለው፡፡ የአገሪቱም ሰዎች ሁሉ ለሞተው የመኰንን ልጅ ሊያለቅሱ ሲሰበሰቡ ቅዱስ ዮሐንስም አብሮ ቆሞ ሲመለከት ሮምና መጥታ "በጌታዬ ልጅ ሞት ልትደሰት መጣህን" እያለች ረገመችው፡፡ እርሱም "አይዞሽ አትዘኚ" አላትና ወደ ሞተው ልጅ ቀርቦ በመስቀል ምልክት ካማተበበት በኋላ በፊቱ እፍ አለበት፡፡ የሞተውም ልጅ ድኖ ተነሣ፡፡ የሀገሪቱም ሰዎች እጅግ ደነገጡ፡፡ ሮምናም ደንግጣ " #እግዚአብሔር የሚሉት አምላክ አንተ ነህን" ብላ ጠየቀችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም "በፍጹም እኔ አምላክ አይደለሁም፣ እኔ የእርሱ አገልጋዩና ሐዋርያው ነኝ እንጂ" አላት፡፡ ሮምናም ስለበደለቻቸው በደል ሁሉ መሪር ዕንባን እያለቀሰች ይቅር እንዲሏት ለመነቻቸው፡፡ እነርሱም አረጋጉዋት፡፡ ከሕዝቡም ውስጥ ብዙዎቹ በ #ጌታችን አመኑ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ሌሎች ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን እየሰበከ ከጣዖት አገልጋዮች በቀር ሁሉንም አሳምኖ አጠመቃቸው፡፡ አገልጋዮችን ኤጲስቆጶሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ከሾመላቸው በኋላ ወደ ሌሎች አቅራቢያ አገሮች ሄደ፡፡

በመጨረሻም በከሃዲውና በጨካኙ በድምጥያኖስ ዘመን በጣዖት አምላኪዎች ተከሶ ለፍርድ ቀረበ፡፡ በፈላ ውኃ ካሠቃዩት በኋለ በፍጥሞ ደሴት አጋዙት፡፡ በዚያም ሳለ ራእዩን ተመልክቶ ጻፈው፡፡ ድምጥያኖስም ከተገደለ በኋላ ከግዞቱ ተመልሶ ሦስቱን መልእክታቱንና ቅዱስ ወንጌሉን ጽፏል፡፡ #ጌታችንም አስቀድሞ ሞትን እንደማይቀምስ ለዮሐንስ ቃል ገብቶለት ነበርና (ዮሐ 21፡22) ጥር 4 ቀን እንደ ኤልያስና ሄኖክ ሞትን እንዳያይ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወስዶታል።

#ጌታችን ለዮሐንስ ያልነገረው እርሱም ያላስተማረው ምሥጢር የለም፡፡ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር "በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በ #እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ…" ብሎ የ #ጌታችን ነገር ተመራምሮ ለመድረስ ሲል በመሀል መልአኩን በዮርዳኖስ ባሕር ላይ ሲሄድ አገኘው፡፡ መልአኩም የዮርዳኖስን ባሕር በእንቁላል ቅርፊት እየጨለፈ ወደ ውጭ ሲያፈስ ተመለከተው፡፡ ዮሐንስም ተገርሞ "ምን ማድረግህ ነው" አለው፡፡ መልአኩም "የዮርዳኖስን ባሕር ቀድቼ እየደፋሁ ልጨርሰው ነው" ሲለው ዮሐንስም መልሶ "ታዲያ በእንቁላል ስባሪ ነውን?" አለው፡፡ መልአኩም "አዎን" አለው፡፡ ዮሐንስም "በከንቱ ደከምክ" አለው፡፡ ይህን ጊዜ መልአኩም መልሶ "አንተስ እንጂ ደግሞ የአምላክን መገኘት፣ አኗኗሩንም ተመራምረህ በጥበብ ለማግኘት ብለህ 'በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በ #እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ..' ብለህ ጀምረህ የለምን? አንተ #ጌታን ተመራምረህ ካገኘህና ከደረስክበት እኔም የዮርዳኖስን ወንዝ በዚህ እንቁላል ቅርፊት ቀድቼ እጨርሰዋለሁ" አለው፡፡ ዮሐንስም ይህን ጊዜ ደንግጦ ዝቅ ብሎ "ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ…" ብሎ ሀሳቡን ለወጠና ሌላ ታሪክ ቀጠለ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ #ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ወክሎ #እመቤታችንን በአደራ የተቀበለ እርሱም ለእመቤታችን በአደራ የተሰጠ ሲሆን #እመቤታችንን ከወሰዳት በኋላ ለ16 ዓመት እየተንከባከበ ጠብቋታል፡፡ እናቱም በሕፃንነቱ ስለሞተች #እመቤታችን ናት እየተንከባከበች ያሳደገችው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በመልኩም ከ #ጌታችን ጋር ይመሳል ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሥዕል የመሳል ተሰጥኦም ነበረው፡፡ #ጌታችን በተሰቀለበት ዘመን የነበረው ጢባርዮስ ቄሳር ልጁ በሽተኛ ነበር፡፡ የ #ጌታችንን የማዳን ሥራ እየሰማ እነ ጲላጦስም ስለ #ጌታችን የሚጽፉለትን ይሰማ ስለነበር ልጁን ከ #ጌታችን መቃብር ላይ እንዲያኖሩለት ላከው፡፡ ልጁም ፈጥኖ ተፈወሰለት፡፡ ጢባርዮስ ቄሳርም በልጁ መዳን ምክንያት የ #ጌታችንን ውለታ ማስቀመጥ ፈልጎ የ #ጌታችንን ሥዕሉን የሚሥልለትን ሲያጠያይቅ ዮሐንስን አገናኙት፡፡ ዮሐንስም #ጌታችንን ልክ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ አድርጎ በመሣል ለጢባርዮስ ቄሳር ሰጠው፡፡ ሲሥለውም በመጀመሪያ #ጌታችንን ልክ እንደተሰቀለ አድርጎ ራቁቱን ነበር የሳለው፡፡ ዮሐንስ የሳለው የ #ጌታችን ሥዕልም አፍ አውጥቶ "በመጀመሪያ አይሁድ በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?" ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ "እንዴት አድርጌ ልሳልህ?" ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም "ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ" አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ከሳለው በኋላ ሥዕሉን ትኩር ብሎ ተመልክቶ ቢስመው ከንፈሩ አንድ ቀን ተኩል ያህል ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸውን የ #ጌታችንን ስነ ስቅለት የሚያሳዩ ሥዕሎች መገኛቸው ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስ የሳለው ሥዕል ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፦
#መስከረም_6

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ስድስት በዚች ቀን ታላቅ ነቢይ የአሞጽ ልጅ #ቅዱስ_ኢሳይያስ አረፈ፣ #የአቡነ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ ዐፅማቸው ከዋልድባ አብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ዕለት ነው፣ #ቅድስት_ሰብልትንያ በዲዮቀልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ሞተች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ነቢዩ_ኢሳይያስ

መስከረም ስድስት በዚች ቀን ታላቅ ነቢይ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ አረፈ። ይህም ነቢይ ለይሁዳ በነገሡ በአምስቱ ነገሥታት ዘመን አስተማረ ትንቢትም ተናገረ እሊህም አዝያን ኢዮአታም አካዝ ሕዝቅያስና ምናሴ ናቸው።

በአካዝ ዘመንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ። እነሆ ስለዚህ #እግዚአብሔር ምልክትን ይሰጣችኋል። እነሆ ድንግል ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም #አማኑኤል ትለዋለች። ትርጓሜውም #እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ አንድ ሆነ ማለት ነው።

እርሱም በኃጢአታቸው ከሚመጣባቸው ፍዳ ወገኖቹን የሚያድናቸው ወደ ሃይማኖቱም የሚአስገባቸው እንደሆነ የእስራኤልንም ልጆች መሥዋዕታቸውንና ክህነታቸውን እንደሚሽር ከሐዲስ ወገኖችም የሚያመሰግኑት ካህናትን እንደሚሾም ተናገረ።

የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምም ኢየሩሳሌምን ከቦ የስድብ ቃልን በክብር ባለቤት በ #እግዚአብሔር ላይ በተናገረ ጊዜ የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምን ያጠፋው ዘንድ #እግዚአብሔር እንዳለው ለሕዝቅያስ ትንቢትን ተናገረ።

በዚያች ሌሊትም #እግዚአብሔር የላከው የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል ወደ ሠናክሬም ሰፈር መጥቶ ከፋርስ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ አርበኞችን ገደለ። የለኪሶ ሰዎች ሲነጋ በተነሡ ጊዜ የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ሁሉ አዩ።

ሕዝቅያስም ታሞ ለሞት በተቃረበ ጊዜ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደርሱ መጥቶ #እግዚአብሔር ትሞታለህ እንጂ አትድንም ብሏልና ቤትህን አዘጋጅ አለው። ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ ወደ #እግዚአብሔር ለመነ ፈጽሞ ጽኑ ልቅሶንም አለቀሰ።

ይህን ከነገረው በኋላ የ #እግዚአብሔር ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኢሳይያስ መጣ ሒደህ ለሕዝቅያስ የአባትህ የዳዊት ፈጣሪ #እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰማሁ ዕንባህንም አየሁ። እነሆ በዘመንህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት ጨመርኩልህ አለ በለው።

ዳግመኛም ስለ እስራኤል መማረክና ከምርኮ ስለ መመለሳቸው ትንቢት ተናገረ የፈሳሽ ውኃን ምንጭ በማፍሰስ በእጆቹ ላይ #እግዚአብሔር ምልክትን ገለጠ።

ክብር ይግባውና ስለ #መድኃኒታችን_ክርስቶስ መከራ ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ። እርሱም በመከራው ጊዜ ነገርን አልተናገረም እንደ በግ ይታረድ ዘንድ መጣ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንደ ማይናገር እንዲሁ በመከራው ጊዜ አልተናገረም።

ከዚህም በኋላ ደግሞ በሕዝቅያስ ልጅ በንጉሥ ምናሴ ላይ ትንቢት ተናገር ጣዖትን ስለማቆሙና ስለማምለኩ ገሠጸው። ስለዚህም ንጉሥ ምናሴ ተቆጥቶ በዕንጨት መሰንጠቂያ መጋዝ በራሱና በእግሮቹ መካከል ሠነጠቀው ምስክርነቱንም በዚህ ፈጸመ።

ትንቢት እየተናገረ የኖረበትም ዘመን ሰብዓ ዓመት ከዚያም በላይ ይሆናል። እርሱም ያስተማረው ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት በዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሦስት ዓመት ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ነብይ ኢሳይያስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የዋልድባው የአቡነ ሳሙኤል ዐፅማቸው ከዋልድባ አብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ዕለት ነው፡፡ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ትውልዳቸው ከካህናቱ ወገን አክሱም ነው አባታቸው እስጢፋኖስ እናታቸው አመተ ማርያም ይባላሉ። ለመምህር ሰጥተዋቸው ሲማሩ አድገው በኋላም ወላጆቻቸው በሞት ሲለዩአቸው ደብረ በንኰል ገዳም ገብተው ሥርዓተ ምንኩስናን ከአበው እያጠኑ ለትልቁም ለትንሹም በትሕትና እየታዘዙ ውሃ እየቀዱ እንጨት እየሰበሩ በትኅርምት በጽሞና በጸሎት ይኖሩ ነበር።

ሰይጣን በውዳሴ ከንቱ ጾር ቢመጣባቸው ከማሕበረ መነኮሳቱ ተለይተው በተባሕትዎ ለመኖር ሽተው ወጥተው ሲሔዱ ተከዜ ደረሱ። ወንዙ ሞልቶ የማያሻግራቸው ቢሆን ውሃውን በትምህርተ #መስቀል ባርከው በአንድ እጃቸው መጽሐፍ በአንድ እጃቸው መብራት እንደያዙ ገብተው መብራቱ ሳይጠፋ መጽሐፉ ሳይበላሽ ተሻግረዋል። ዋልድባ ሲደርሱ #ጌታ እዚህ ተቀመጥ ስላላቸው ገዳም መሥርተው ሥርዓተ ምንኩስናን እያስተማሩ ተቀመጡ። ዛሬ በዋልድባ የሚያመሰግኑበት #ውዳሴ_ማርያም #ቅዳሴ_ማርያምን ከተከዜ ወዲህ ያመጡ እሳቸው ናቸው። ይህንን እየጸለዩ ሲሔዱ ክንድ ከስንዝር መሬት ለቀው ይታዩ ነበር። አንድ ቀንም ይህንን ጸሎት ደግመው ውኃውን ቢባርኩት ኅብስተ ሕይወት ሆነላቸው ከነደቀ መዛሙርቶቻቸው ተመግበውታል።

#እመቤታችንም የፍቅር መግለጫ ዕጣን፣ ወርቅ፣ እንቁ ሰጥታቸዋለች። ውዳሴዬን ከቅዳሴዬ አንድ አድርጎ የደገመውን አንተ ከገባህበት መካነ ሕይወት አስገባዋለሁ ብላ ቃልኪዳን ሰጥታቸዋለች። ጊዜ እረፍታቸው ሲደርስ #ጌታን በስብሐተ መላእክት ተገልጦ በስምህ የተማጸነውን በጎ የሰራውን፣ ዜና ገድልህን የጻፈውን፣ ያስጻፈውን፣ ያነበበ፣ የተማረ፣ ያስተማረ፣ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ምሬልሃለሁ። በዚህ ቦታ በዋልድባ የሚሰበሰቡ ልጆችህን ከእዳ ከፍዳ እሰውርልሃለሁ አላቸው። እንኪያስ ቦታዋን ባርክልኝ ብለው እንደ መሶብ አንስተው አስባርከዋታል #ጌታችንም እህል አይብቀልብሽ ኃጢአት አይሻገርብሽ ብሎ ቃል ኪዳን ገባላት ለገዳመ ዋሊ። አባታችን አቡነ ሳሙኤል በበዓታቸው ውስጥ ጸንተው ሲኖሩ ታህሣሥ 12 ቀን ያረፉ ሲሆን ዛሬ መስከረም 6 ግን ፍልሰተ አጽማቸው የተከናወነበት እለት ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሰብልትንያ

በዚህችም ቀን ቅድስት ሰብልትንያ በከ*ሀዲ ንጉሥ ዲዮቀልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ሞተች። ይችንም ቅድስት ዕድሜዋ ዘጠኝ ዓመት ሲሆን ከሀ*ድያን ያዙዋት እጆቿንና እግሮቿንም አሥረው ከሚነድ እሳት ውስጥ ጣሏት የክብር ንጉሥ በሆነ በ #እግዚአብሔርም ኃይል ከእሳት ዳነች።

ውኃን በተጠማች ጊዜ #እግዚአብሔርን ለምናው ውኃን አፈለቀላትና ጠጣች ክብር ምስጉን የሆነ #ጌታችንንም አመሰገነችው። ከዚህም በኋላ ነፍሷን በ #እግዚአብሔር እጅ አደራ ሰጥታ ራሷን ከእሳት ውስጥ ወረወረች ምስክርነቷንም ፈጸመች።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_6 እና #ከገድላት_አንደበት)