TIKVAH-ETHIOPIA
1.41M subscribers
55K photos
1.37K videos
199 files
3.67K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ኮሬ #ዳርባማናና

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ዳርባ ማናና ወረዳ 2 ወጣቶች መገደላቸውን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከአከባቢው ነዋሪዎች ለማወቅ ችሏል።

አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የቀድሞ አማሮ ልዩ ወረዳ ባለሥልጣን ደግሞ ፤ ወጣቶቹ የተገደሉት ሲጠፉ የነበሩ መከላከያ ሠራዊትን ለማስመለጥ ሞክራችኋል ተብለው እንደሆነ ተናግረዋል።

በመንግስት የፀጥታ ኃይል የተገደለው አንደኛው ወጣት ሳሙኤል ሰለሞን እንደሚባልና ይኸው ወጣት ቀጥታ ሞተር ሳይክል ላይ እንደነበር ተመቶ እንደተገደለ ገልጸዋል።

ሌላኛው አቡለ ጸጋዬ የተባለ ወጣት ጉጂ ቦሬ ወደ ተባለ ካምፕ ከተወሰደ ከቀናት በኃላ ስቃይ ተፈፅሞበት መገደሉን ገልጸዋል።

ቃላቸውን የሰጡ አንድ የአካባቢው ነዋሪ  በበኩላቸው ፦

* ከመከላከያ ሲኮበልሉ የነበሩ አባሎችን ሲፈልጉ የነበሩ የመንግሥት ሠራዊቶች ሁለት በሞተር ሲጓዙ የነበሩ ወጣቶችን ኮሬ ዞን ሸሮ ቀበሌ ሙራ ማንቻ የሚባል ቦታ ምሽት አራት ሰዓት ላይ እንዳገኟቸው ገልጸዋል።

* አንዱ ከጸጥታ ኃይሎቹ በተተኮሰ ጥይት ወዲያው እንደሞተ ፣ ሌላኛውን ደግሞ ለማምለጥ ሲሞክር ይዘውት ወደ ሌላ ቦታ ወስደውት እንደነበር ፤ በኃላም እሁድ 7 ሰዓት ላይ እንደተረሸነ መስማታቸውን ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተፈጸመ ስለተባለው ግድያ ምን ምላሽ እንዳላቸው የኮሬ ዞን ምክትል ፖሊስ አዛዥ አቶ ሲዳሞ ማደቦን ጠይቋል።

ምክትል ፖሊስ አዛዡ  ፤ " በዚህ ነገር ላይ እኔ መግለጫ መስጠት አልችልም፣ ምክንያቱም ወጣቶች በሆነውም ባልሆነውም ቅሬታ ሊያቀርቡ ይችላሉ። መንግሥት እንደ መንግሥት እርምጃ ሊወስድ ይችላል " ብለዋል።

አክለውም፣ " የምሰጠው ነገር ከሕግ ጋር ሊጋጭ ስለሚችል ተነጋግረን ነው መረጃ የምንሰጠው " ሲሉ አክለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ጥያቄ ለዞኑ ፓሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አራርሶ ነጋሽ አቅርቧል።

ሁለት ወጣቶች በጸጥታ ኃይል ለምን እንደተገደሉ ሲጠየቁ ከአሥር ደቂቃ በኋላ እንዲደወል ቀጠሮ ቢሰጡም በቀጠሮው ሰዓት በድጋሚ ሲደወል ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆኑም።

በተጨማሪ፦ " እባክዎ ስልክዎን ያንሱና ምላሽ በመስጠት ኃላፊነትዎን ይወጡ። የወከሉት ሕዝብ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እየተተኮሰበት እየተገደለ እንደሆነ እየገለፀልን ነው ፤ በዚህ ጉዳይም ከ10 ደቂቃ በኋላ ደውሉ ብለው ነበር " ተብሎ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ለተላከላቸው የጽሑፍ መልዕክትም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ከዚህ ባለፈ ፦

- የኮሬ ዞን ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ አየለ ስልክ ባላማንሳታቸው፣

- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህ "ስብሰባ ላይ ነኝ" በማለታቸውና በድጋሚ ሲድልወልም ስልክ ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ለማካተት አልቻልንም።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) የክልሉ ቅርንጫፍ በበኩሉ፣ ስለሁለቱ ወጣቶች እስካሁን መረጃ ባይደርሰውም በዞኑ ባለው የጸጥታ ችግር ነዋሪዎች እየተደበደቡ መሆኑን ከዚህ በፊትም እንደተከታተለ አስረድቷል።

ዘገባው በአ/አ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው።

@tikvahethiopia
#ኮሬ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፤ በኮሬ ዞን በተፈጸመ ጥቃት 3 ታዳጊ ልጆችን ጨምሮ 4 ሰዎች ተገደሉ።

ጥቃቱ የተፈጸመው ትላንት በጎርካ ወረዳ ፤ " ቆቦ ቀበሌ " ነው ተብሏል።

የኮሬ ዞን አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ፥ ለንጹሐን አርሶ አደሮች ሞት ምክንያት ለሆነው ጥቃት " በምዕራብ ጉጂ ዞን ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ እና ፀረ-ሰላም " ሲል የጠራቸውን አካላት ተጠያቂ አድርጓል።

እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ገለጻ ጥቃት ከደረሰባቸው ነዋሪዎች መካከል አንድ የ14 ዓመት ታዳጊ የሚገኝበት ሲሆን ሁለቱ ደግሞ እድሜያቸው ከ17 እስከ 19 ባለው ውስጥ ይገመታል።

አንድ ነዋሪ ፤ ታጣቂዎቹ ቀደም ብለው ማታ ላይ ገብተው ቦታ ይዘው እንደነበርና 7 ክላሽ የታጠቁ ሰዎች እንደሆኑ ገልጸዋል።

" ሟቾቹ ከብት ሊያግዱ ይዘው እየሄዱ እያለ፤ ከብት የሚታገድበት ቆላ የሚባል ቦታ ሲደርሱ እዚያ ጋር ነው ተኩስ የጀመሩት " ሲሉ አስረድተዋል።

ታጣቂዎቹ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ አራቱ ታዳጊዎች እያገዱ የነበሯቸውን ከብቶች ለመውሰድ ቢሞክሩም ተኩሱን ሰምተው በመጡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲመለሱ ተደርገዋል።

የዞኑ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ፥ የኮሬ ሕዝብ በሚያዝያ ወር ብቻ ብዙ ሞቶችን ማስተናገዱን ገልጿል።

ምን ያህል የሚለውን በቁጥር አልገለጸም።

ነዋሪዎች ግን ከመጋቢት ወር ጀምሮ ቢያንስ አራት ጊዜ በተፈጸሙ ጥቃቶች ነዋሪዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

መረጃው የቢቢሲ አማርኛ አገልግሎት ነው።

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
“ ባለፈው ሳምንት ብቻ 7 ሰዎች ናቸው የተገደሉት ” - ነዋሪዎች በኮሬ ዞን ፤ #በታጣቂዎች አማካኝነት ንጹሃን ላይ የሚደርስ ጥቃት በእርቀ ሰላም ተፈቶ ቆሞ የነበረ ቢሆንም ከ4 ወራት ወዲህ በማገርሸቱ የንጹሐን ግድያ፣ የንብረት ዘረፋ እየተፈጸመ መሆኑን የዞኑ ባለስልጣትና ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል። መንግሥት መፍትሄ እንዲሰጥም ተጠይቋል። ባለስልጣናቱና ነዋሪዎቹ ለድርጊቱ  የ " ኦነግ…
#ኮሬ

° " የንጹሀን ሞት ይቁም፤ገዳዮች ለፍትህ ይቅረቡልን !! " - የዳኖ ቀበሌ ነዋሪዎች

° " በግጭቱ ሁለት ሰዎች ሲጎዱ የአንደኛው ህይዎቱ አልፏል " - የኮሬ ዞን የሰላምና ጸጥታ ሀላፊዉ ተፈራ ቦንዶሮ

በኮሬ ዞን ፤ ዳኖ ቀበሌ ከትናንት ጀምሮ የደረሰ በቆሎ ታጥቀው በመጡ አካላት በመጨፍጨፉ ምክንያት በተነሳው ግጭት የሰው ህይወት አልፏል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ይህ ድርጊት ታጥቀው ከምዕራብ ጉጂ ዞን ጋላናና ሱሮ ባርጉዳ ወረዳ ቀበሌያት ወደ ኮሬ ዞን ዘልቀው በገቡ አካላት ነው የተፈጸመው ብለዋል።

እነዚሁ ታጣቂዎች " ከዚህ ቀደምም ከብቶች ሲነዱብን አርሶአደሮች ሲገደሉብን ቆይተዋል " ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህ አመት ብቻ #ከ20_በላይ ሰዎች መሞታቸውን አስረድተዋል።

በመሆኑም " እነዚህን አካላት መንግስት አስታግሶ ለህግ / ለፍትህ ያቅርብልን ፤ የንጹሀን ሞት ይቁም ፤ ሰሚ በማጣታችን እሄዉ ዛሬም ግጭቱ ቀጥሏል " ብለዋል።

በአካባቢው ያለዉ ተኩስም የታጠቁ አካላትን ወሰን አልፈዉና ወደመንደሩ ተጠግተዉ የጀመሩት ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ ቃላቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡት የኮሬ ዞን የሰላምና ጸጥታ ሀላፊዉ ተፈራ ቦንዶሮ ፥ (ቃላቸውን በሰጡበት ሰዓት / ከሰዓት ) አካባቢው ላይ ከባድ ተኩስ እንደነበር ገልጸዋል።

ግጭቱን ለማርገብ ርብርብ ላይ በመሆናቸዉ ምላሽ ለመስጠት አይመችም ቢሉም ቆይተዉ የተብራራ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከምዕራብ ጉጂ ዞን የመጡ ታጣቂ ሀይሎች አካባቢው በመመንጠርና የበቆሎ ማሳዎችን በመጨፍጨፋቸው ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል።

በግጭቱ አንድ ሰው #ሲሞት ፤ አንድ ሰው ቆስሏል ብለወል።

ግጭቱን በቀሰቀሱት በኩል የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የሚያዉቁት ነገር እንደሌለ ገልጸው አሁን ላይ አካባቢዉ መረጋጋቱን ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም ምን ታስቧል ? ሲል ጠይቋል።

እሳቸውም ፤ ከአካባቢው በተወሰነ ርቀት ላይ የሀገር መከላከያ ሀይሎች እንደሚኖሩና ከሚቆጣጠሩት ቦታ በተጨማሪ የታጠቁ ሀይሎች የሚመጡበትን መንገድ እንዲቆጣጠሩ ለመነጋገር ማሰባቸዉን ገልጸዉ ይህ ግን በመከላከያው ፈቃድና የስምሪት ሁኔታ የሚወሰን ነው ብለዋል።

ግጭቱ ያለበት የኮሬና ጉጂ ማህበረሰብ መሀከል በአካባቢዉ ባህል መሰረት የእርቅ ስርዓት በተደጋጋሚ ቢካሄድም ዕርቁ ውጤታማ ሳይሆን መቅረቱን ለማወቅ ችለናል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ፤ በምዕራብ ጉጂ ዞን በኩል ምላሽ ለማግኘት ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካም ፤ ከዚህ ቀደምም ሙከራ ቢደረግም ምላሽ ሰጪ አልተገኘም። አሁንም ምላሽ አለኝ የሚል ምላሹን መስጠት ይችላል።

#TikvahEthiopiaFamilyHawassa

@tikvahethiopia