TIKVAH-ETHIOPIA
1.43M subscribers
55.6K photos
1.39K videos
200 files
3.74K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#update BBC-ቤንሻንጉል⬇️

በቤንሻንጉል ጉምዝ በተፈጠረ ግጭት ከ50 ሺህ ሰዎች በላይ #ሲፈናቀሉ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተሰማ።

መስከረም 16/2011 ዓ.ም የካማሼ ዞን አመራሮች ከምዕራብ ኦሮሚያ አስተዳደር ጥምር ኮሚቴ ጋር የነበራቸውን ስብሰባ አጠናቅቀው እየተመለሱ በነበሩ የዞን፣ የወረዳ አመራሮችና የፀጥታ ኃይሎች ላይ በተከፈተው ተኩስ የ4 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ በተወሰኑ ከኦሮሚያ ጋር በሚዋሰኑ ስፍራዎች በተከሰተ ግጭት ሰዎች #መሞታቸውን፣ መፈናቀላቸውን ቤቶች መቃጠላቸውን የቤንሻንጉል ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አበራ ባይታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተለይ በበሎይ ጅጋንፎይ ወረዳ ስር ሳይ ዳለቻ ቀበሌ ግጭት የነበረ ሲሆን በግጭቱም 75 ቤቶች ተቃጥለዋል ብለዋል። በዚሁ ወረዳ ጅጋንፎይ ቀበሌ በጭበጭ በምትባል አካባቢ ላይ ቤቶች መቃጠላቸውን ጠቅሰው ሌሎች ቀበሌዎችም ላይ ተመሳሳይ ግጭቶች መከሰሰታቸውን ተናግረዋል።

በበሎይ ጅጋንፎ ሶቤይ ከተማ ላይ በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በሶጌ ዙሪያ ባሉ ቀበሌዎች ልቢጋ፣ ሳይ ዳላቻ፣ ታንካራ ቀበሌዎች በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አስረድተዋል።

"በተንካራ 105 ቤቶች ተቃጥለዋል 3 ሰዎችም ህይወታቸው አልፏል" ያሉት መስተዳድሩ በበጭበጭ 1 ሰው መሞቱንና አንገርባጃ ቀበሌ 2 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አስረድተዋል። እንደ ክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገለፃ ወደ ኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ እና በስጋት ምክንያት ወደ ጫካ የገቡ ሰዎች ያሉ ሲሆን ቁጥራቸው ምን ያህል ነው የሚለውን ግን የተጠናቀረ መረጃ የለኝም በማለት ሳይናገሩ ቀርተዋል።

የተፈናቀሉት ሰዎች ከቤንሻንጉል ብቻ ሳይሆን ክልሉን ከሚያዋስኑት የኦሮሚያ ቀበሌዎችም እንደሆነ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ሳስጋ ወረዳ ዱራበሎ፣ ካምፕ፣ በሎበሬዳ፣ ስምንተኛ ከሚባሉት ቀበሌዎች በስጋት ምክንያት ወደ ነቀምትና በሎበሬዳ ወደሚገኙ ማዕከሎች #ተፈናቅለው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ የሆኑት አቶ ታከለ ቶሎሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በቤንሻንጉል ክልል የኦሮሚያ አዋሳኝ ቀበሌዎች በተከሰተው ግጭት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 12 ደርሷል። ከዚህ በተጨማሪም 14 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን እነዚህም በሳስጋ ወረዳ ጤና ጣቢያና በነቀምት ሆስፒታል ህክምና እያገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ ከሆነ ቀያቸውን ጥለው ወደ ኦሮሚያ የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ ደርሷል። እነዚህ ሰዎች የተፈናቀሉት ከበሎይ ጅጋንፎና ያሶ ሲሆን ከኦሮሚያ አዋሳኝ ወረዳዎች ደግሞ ሀሮ ሊሙ፣ ሶጌና ሳስጋ አካባቢዎች ነው።

አቶ ታከለ ጨምረውም ከእነዚህ አካባቢዎች የሚፈናቀሉ የኦሮሞ እና የአማራ ተወላጆችች ቁጥር በየእለቱ እየጨመረ መሆኑን ገልፀዋል። የተፈናቀሉት ሰዎች ሳስጋ ወረዳ፣ ነቀምት ከተማ፣ ሀሮ ሊሙ ወረዳና ጉቶ ጊዳ ወረዳ ውስጥ ኡኬ ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ ጨምረው አስረድተዋል።

በምሥራቅ ወለጋ የሀሮ ሊሙ ወረዳ ኮሙኑኬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ በበኩላቸው አቶ #ዱጋሳ_ጃለታ ከቤንሻንጉል ክልል 7 ቀበሌዎች 20 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን እስካሁን ባላቸው መረጃ በወረዳው ብቻ 5 ሰዎች ሞተዋል።

2 #ነፍሰጡር እናቶች መንገድ ላይ መውለዳቸውን የተናገሩት አቶ ዱጋሳ ህፃናት፣ እናቶችና አቅመ ደካሞች የመኪና መንገድ ባለመኖሩ የተነሳ ለመሸሽ አዳጋች እንደሆነባቸውም ጨምረው አስረድተዋል።

በቤንሻንጉል ክልል #ግጭት በተከሰተባቸው በበሎይ ጅጋንፎይ ወረዳ #ሦስት አካባቢዎች እንዲሁም በካማሼ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሰፍረው እንደሚገኙ የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በተለያየ ጊዜ ምርት በሚደርስበት አካባቢ በክፍፍል ወቅት በተደጋጋሚ ግጭቶች እንደሚነሱ ነገር ግን እነዚህን ወስዶ #ብሄር ተኮር ግጭት ነው ማለት እንደማይቻል አስረድተዋል።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ የሆኑት አቶ ታከለ ቶሎሳ በበኩላቸው እስካሁን ድረስ 40 ሰዎች ከቤንሽንጉል 5 ሰዎች ደግሞ ከኦሮሚያ #በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ለተፈናቀሉ ሰዎች የአካባቢው ማህበረሰብ #እርዳታ እያደረገላቸው መሆኑን ከመንግሥት ደግሞ አስፈላጊው ድጋፍ እየተጠበቀ እንደሆነ ተናግረዋል።

ምንጭ፦ BBC የአማርኛው አገልግሎት

@tsegabwolde @tikvahethiopia