ጌታችን በተግባር እንዳስተማረን መንፈሳዊ ሕይወት በትንሹ ተጀምሮ ከዚያ ቀስ በቀስ እያደገና እየጠነከረ የሚሄድ እንጂ በአንድ ጊዜ ተጀምሮ በቅጽበት ፍጹም የሚሆንበት አይደለም፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትን ከተለያየ ሁኔታና ሕይወት ከጠራቸው በኋላ ወዲያውኑ ዕለቱን ወደ ፍፁምነት ደረጃ አልደረሱም፡፡ ብዙ ድክመቶች ነበሩቸው። እርሱ ስለ ሰማያዊ መንግስት ሲነግራቸው ስለ ምድራዊ መንግስት የሚጠይቁበት ጊዜ ነበር።የሚነገራቸውን ባለማስተዋላቸው፣ ለእርሱ የቀኑና የተቆረቆሩ ምስሎአቸው እሳት ከሰማይ ወርዶ እርሱን ያልተቀበሉትን ሰዎች እንዲያጠፋቸው በመጠየቃቸው፣ ስለ ሞቱና መከራው ሲነግራቸው “አትሙትብን” በማለታቸው ÷ ስለ እምነት ማነስ ሁሉ ብዙ ጊዜ ተገሥጸዋል፡፡ እነርሱም ከዚህ የተነሳ “ጌታ ሆይ እምነት ጨምርልን” እስከማለት ደርሰዋል ። ጌታችንም ብዙ ጊዜ ይገስጻቸውና ስሕተታቸውን እንዲያስተካክሉ በአባትነቱ ይመክራቸው ነበር፤ ሦስት ዓመት ከእርሱ ጋር ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ በቃልም በተግባርም ተምረው እንኳ ፍጹማን መሆን አልቻሉም ነበር። ጌታችን በሰጣቸው ተስፋ መሰረት መንፈስ ቅዱስን ሲቀበሉ ነበር ፍጹማን የሆኑት። እንግዲህ ሐዋርያት በእንዲህ ዓይነት ሂደትና ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፉ ከሆነ ወደ ፍጹምነት ደረጃ መድረስ በአንድ በኩል በራስ ጥረት በዋናነትም በእግዚአብሔር ቸርነት በሂደትና ቀስ በቀስ እንጂ በአንድ ጊዜ በቅጽበት የሚሆን ነገር አይደለም ማለት ነው፡፡ በክርስትና የሕይወት ጉዞ ውስጥ የሕይወትን አካሄድ÷ ስልትና ዘዴ ማወቅ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የጉዞውን ርዝመትና ጠባይ እንዲሁም በሂደቱ ውስጥ ያሉና ሊገጥሙ የሚችሉ ነገሮችን አስቀድሞ ሳያውቁ የሚጀመር ጉዞ መሰናሎች ሲገጥሙት የመውደቅ ዕድሉ የሠፋ ነው፡፡ ከዚህም አንዱ የአካሄድን ፍጥነት መወሰን ነው፡፡ አንዳንዶች ክርስትና በተወሰነ ጊዜ ተሰርቶ ማለቅ እንዳለበት የሥራ ዕቅድ (ፕሮጀክት) ወዲያውኑ እንደ ጀመሩ አካሄዳቸው የጥድፊያና የችኮላ ይሆናል፡፡ ሰውነቱ ጾምን በሚገባ ሳይለማመድ እስከ ማታ ድረስ በመጾም ይጀምራል። «የክርስቶስ ክቡር ደም በፈሰሰባት ምድር በጫማ አልሄድም» እስከ ማለት ይደርሳል፡፡ ይህን ዓለም በሙሉ የመጸየፍና የምናኔ ነገር ብቻ ይታሰበዋል። ሌሎች ሰዎች ኀጢአተኞችና ደካሞች ሆነው ይታዩታል። አንዳንዶች ሥራቸውን እስከ መተው ደርሰው በየገዳማት መዞርን ብቻ ስራዬ ብለው ይይዛሉ:፡ በአጠቃላይ ነገሮችን ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን አድርገው ይይዟቸዋል፡፡ በየቦታው በመዞር ብቻ በረከትና ጽድቅ የሚገኝ ይመስለዋል። ከትምህርት ቤት ወደ ትምህርት ቤት እየተዘዋወረ መምህር ሲያማርጥና የተመቸ ሁኔታን ሲፈልግ አንድ ቁም ነገር ሳይማር ጊዜውን የሚያጠፋውን ተማሪ አበዉ ’እግረ ተማሪ’ ይሉታል፡፡ዛፍ እንኳን ፍሬ የሚያፈራው ከተተከለበት ቦታ ሲኖር ነው:: ነገር ግን በየጊዜው እየተነቀለ የሚተከል ከሆነ ወይ ይደርቃል፤ ባይደርቅ እንኳ ፍሬ ማፍራት አይችልም።ጊዜውን በዙረት ብቻ የሚጨርስ ሰውም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም፡፡ ቢያፈራም እንኳ በአንድ ቀን በቅላ በአንድ ቀን አብባ በአንድ ቀን ታፈራለች እንደምትባለው ዕፀ ከንቱ÷ ፍሬው ምትሐታዊ ይሆንና ከመታየቱ ወዲያውኑ ይረግፋል። በእንዲህ ያለ ሕይወት የሚጓዙ ሰዎች የማይመች አካሄድ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ይህ ዓይነት ሕይወት ብዙ ችግሮችን ሊያስከትል የሚችል አስቸጋሪ አካሄድ ነው፡፡
....................
ክርስትና የክርስቶስ ፍቅር እንደ ተረዳውና እንዳከበረው መጠን ከውስጥ በሚመነጭ ፍቅር የሚመሠረት እንጂ በተጽዕኖ ከውጭ የሚጫን ሸክም አይደለም። ሐዋርያው «የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል» አለ እንጂ ሌላ ማንም ያስገድደናል አላለም። በሰዎች ላይ ከባድና እስቸጋሪ ሸክም የሚጭኑ ጸሐፍትንና ፈሪሳውያንን ጌታችን እንዲህ በማለት ገሥጾአቸዋል « ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው እንኳ ሊነኩት አይወዱም»:: ማቴ 23÷4። እንዲህ በሌሎች ላይ መጫን ገድልና ትሩፋት መስሎ የሚታያቸው ሰዎች ሁሉን ከሚያውቅና ሁሉን በጊዜው ከሚያደርግ ጌታ ጋር ያሉትን ቅዱሳን ሐዋርያትን የግድ፥ እንዲጸሙ ለማደረግ ወደ ጌታችን ቀርበው: « እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጾመው ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጸሙት ስለ ምንድነው?» እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ለጾም ከራሱ ከባለቤቱ የበለጠ ተቆርቋሪዎች በመምሰል በሌሎች ላይ ለመወሰን ቀረቡ፡፡ ማቴ.9÷14። አባቶቻችን ሐዋርያትንም እንጀራ ሲበሉ፡ “እጃቸውን አይታጠቡም በሰንበት ቀን እሸት ቆርጠው በሉ» ወዘተርፈ እያሉ ይከሷቸውና ይነቅፏቸው ነበር:: ጌታችን ከሰው የሚፈልገው ግን ከባድና አስጨናቂ የሆኑ ነገሮችን አይደለም፤ « እናንተ ደካሞች፥ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፉችኀለሁ… ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና» በማለት የእርሱ ቀንበር ቀላልና የማይጎረብጥ መሆኑን ነገረን። የተለያዩ ሰዎች መጥተው ምን አናድርግ?» እያሉ በጠየቁት ጊዜ ዮሐንስ መጥምቅ የነገራቸዉ በዚያው በአቅማቸው ሊሠሩት የሚችሉትን እንጂ ከባድ የሆኑ ነገሮችን አላዘዛቸውም ሉቃ.3፥10-14:: ምክንያቱም ገና በመንፈስ ያላደጉ ስለነበሩ ከበድ ያለ ነገር ቢነግራቸው አይችሉትምና፡፡ ጌታችንም፦ «ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና በማለት ለሁሉም በሚቻልና በማይከብድ ሁኔታ አዘዘ ማቴ.7÷1። ሌሎች ለእኛ ሊያደርጉልን የምንወደውን ነገር እኛም ያንን ለሌሎች ማድረግ እንችላለንና። ሌሎች እንዲያደርጉልን ከምንፈልገው ነገር እኛ ለሌሎች ማድረግ የማንችለው ካለ ከሌሎች የምንፈልገው እኛ የማንችለውን ነው ማለት ነው። እኛ የማንችለውን ከሌሎች መጠበቅ ደግሞ ተገቢ አይደለም፡ እንዲሁም ራሳችን ከሌሎች የምንፈልገውን ጠንቅቀን እንደ ምናውቅ ሁሉ ሌሎች ከእኛ የሚፈልጉትንም በእኛው ፍላጎት አንጻር በቀላሉ ማወቅ እንችላለን፡ ስለዚህ ይህን ማወቅም ሆነ መፈጸም ከባድ አይደለም።
...................
ወደ ክርስትና የገቡት አይሁዶች እንኳ ኦሪታዊ ልማዳቸው አልተዋቸው ብሎ ከቤተ አሕዛብ እያመኑ ወደ ክርስትና የሚመጡትን አማንያን «ያንኑ የኦሪቱን ሕግና የሙሴን ትእዛዛት በሙሉ ሊጠብቁ ይገባል» እያሉ ስላስቸገሩ በዚህ ምክንያት የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ በኢየሩሳሌም ተደርጓል። በዚህ ጉባኤም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ «እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን እግዚአብሔርን አሁን ስለምን ትፈታተናላችሁ?» በማለት የጉባኤ መግቢያ ሐሳብ ተናገረ። ከዚያም ቅዱሳን ሐዋርያት ከተወያዩ በኋላ፦ ለጣዖት ከተሰዋ ከደምም ፥ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና ክዚህ ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ» ሲሉ በአንድነት ወሰኑ። የሐዋ. 15፥29።
#ዲያቆን_ያረጋል_አበጋዝ
#በየጥቂቱ_ማደግ
ሐመር መስከረም/ጥቅምት ፲፱፻፺፰ ዓ.ም