የጊንር ጽጌ ተዋህዶ ሰ/ት ቤት
304 subscribers
886 photos
16 videos
12 files
19 links
ይህ ቻናል ዓላማውን የሰንበት ት/ ቤቱን ጠቃሚ መረጃዎች እና መልእክት ማስተላለፍ አድርጎ ጥር 19/2012ዓም ሌሊት 6:50 ላይ ተከፈተ፡፡
Download Telegram
#መልክአ_ሕማማት፤ (የ፯ቱ ጊዜያት ጸሎት)
*መልክአ ሕማማት ማለት ስለ ጌታችን መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ ሕማም፥ መከራ፥ ስቃይ፥ የሚናገር መጽሐፍ ሲሆን፤ ደራሲው ታላቁ ሊቅና የደብረ ባሕርይ ጋሥጫ መምህር #አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋሥጫ_ ነው፡፡
*መልክአ ሕማማት በባለ 3ት መስመር አርኬ የተደረሰ ግጥማዊ ድርሰት ሲሆን፤ የተደረሰውም በ7ቱ የጸሎት ጊዜያት አንጻር በመሆኑ ‹‹#ጸሎት_ዘሰባዐቱ_ጊዜያት›› በሚል መጠሪያም ይጠራል፡፡ የእያንዳንዱ ጊዜ ድርሰትም በዋነኛነት 3ት ክፍሎችን የያዘ ነው፤ እነርሱም፤
1ኛ) ስብሐተ እግዝእትነ ማርያም /የእመቤታችን ምስጋና/
2ኛ) ስበሐተ ኢየሱስ ክርስቶስ /የኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና/
3ኛ) ስብሐተ ሥሉስ ቅዱስ /የሥሉስ ቅዱስ ምስጋና/
**በ7ቱ ጊዜያት ጸሎት ማድረስ እንደሚገባን ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 118 ላይ ‹‹ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ ይላል››፤ አባቶቻችን ሐዋርያትም ይህንኑ ደንግገዋል፡፡ /ዲድስቅልያ 37፣ ቀሌምንጦስ 1ና 7፣ አቡሊዲስ 25ኛና 27ኛ፣ ባስልዮስ 28ኛ አንቀጽ፣ ፍትሐ ነገሥት ገጽ 21/፡፡
፠ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ መልክአ ሕማማትን ሲደርስም በ7ቱ የጸሎት ጊዜያት የተፈጸሙትን ድጊቶች ከ3ቱ የየጊዜያቱ የድርሰቱ ክፍሎች ምስጋና (የማርያም፣ የጌታ፣ የሥሉስ ቅዱስ ምስጋና) ጋር እያመሠጠረና እያራቀቀ፥ እያስዋበና ምሥጢር እያመጣ፤ እንደ ወርቅ እያንከባለለ፥ እንደ ሸማ እየጠቀለለ፥ በግጥም እያስጌጠ፥ በቃላት እየሰደረ፥ በዜማ እያሸበረቀ፥ መንፈስን እየመሰጠ፤ ነው የደረሰው፡፡
#የ7ቱ_የጸሎት_ጊዜያት_የሚባሉትም
፠1ኛ) መንፈቀ ሌሊት(ሌሊት 6 ሰዐት)፤ ጌታችን የተወለደበት፥ የተጠመቀበት፥ የተነሣበትና ዳግመኛ የሚመጣበት ፥ … ሰዐት ነው፡፡
፠2ኛ) ነግህ (ማለዳ፥ ጧት)፤ ጨለማን አርቆ ብርሃንን የሚያመጣበት፥ አባታችን ቅዱስ አዳም የተፈጠረበት፥ መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ በጲላጦስ አደባባይ ፊት ቁሞ የተመረመረበት፥ …. ሰዐት ነው፡፡
፠3ኛ) ሠለስት (ጠዋት ሦስት ሰዐት)፤ እናታችን ሔዋን የተፈጠረችበት፥ ነቢዩ ዳንኤል ጸሎት ያደረሰበት፥ እመቤታችን ከቅዱስ ገብርኤል ብሥራትን ሰምታ የጸነሰችበት፥ መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ ለኛ ሲል በጲላጦስ አደባባይ የተገረፈበት፥ ….. ሰዐት ነው፡፡
፠4ኛ) ቀትር (6 ሰዐት)፤ አጋንንት የሚሰለጥኑበት ሰዐት ስለሆነ እንዳይሰለጥኑብን፥ አዳም ዕፀ በለስን በልቶ የሳተበት ስለሆነ እንዳንስት እንጸልያለን፡፡ በተጨማሪም ነቢዩ ሄኖክ ቤተ መቅደስን ያጠነበት፥ መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ ለኛ ሲል በመስቀል ላይ የተሰቀለበት፥ ….. ሰዐት ነው፡፡
፠5ኛ) ተስዓት (ዘጠኝ ሰዐት)፤ ቅዱስ ጴጥሮስና ዮሐንስ ለጸሎት ወደ ቤተ መቅደስ የወጡበት፥ መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው የለየበት፥ ….. ሰዐት ነው፡፡
፠6ኛ) ሠርክ (ዐሥራ አንድ ሰዐት)፤ ነቢዩ ኤልያስ መሥዋዕት የሰዋበት፥ ዕዝራ ጸሎትን ያቀረበበት፥ ሕዝቅያስ ጸልዮ ፀሐይን ወደ ዐሥር ደረጃዎች የመለሰበት፥ መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ ወደ በፈቃዱ ወደ አዲስ መቃብር የወረደበት፥ …… ሰዐት ነው፡፡
፠7ኛ) ንዋም (የመኝታ ሰዐት)፤ መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ በጌቴሴማኒ የጸሎትን ሥርዐት ያስተማረበት ፥ እንዲሁም ሌሊቱን በመላእክት ጥበቃ ከርኵሳን አጋንንት እንዲጠብቀን የምንጸለይበት …… ሰዐት ነው፡፡
#ለቡ(ልዩ ማስታወሻ)!! ይህ ታላቅ ጸሎት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስር ባሉ በሁሉም ገዳማትና አድባራት በሰሙነ ሕማማት የሚደርስ ሲሆን፤ በአንዳንድ ትላልቅ ገዳማት (እንደ ዋልድባ፣ ማኅበረ ሥላሴ፣ ደብረ ባሕርይ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ወደብረ ጎል አቡነ በጸሎተ ሚካኤል) ያሉ መነኰሳትና መናንያን ግን ከዓመት እስከ ዓመት ጸሎቱን በዜማ /በንባብ/ ያደርሱታል፡፡
/በቀጨኔ ደ.ሰላም መድኀኔዓለምና ደ.ት.ቅ.ገብርኤል ቤ.ክ ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ፤ ትምሕርት ዋና ክፍል ፥ ንዑስ ክፍል /ሕትመት እና ሚዲያ/ የተዘጋጀ ::
#share
Contact: https://t.me/finotehiwot1927
.Facebook...
https://www.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
.YouTube... https://www.youtube.com/channel/UCWVKGH0mSJl47u44uopEb2w,
.Telegram...
https://t.me/medihanaelem
http://tiktok.com/@finotehiwot
www.finotehiwotsundayschool.com
YouTube https://www.youtube.com/channel/UCWVKGH0mSJl47u44uopEb2w
Telegram https://t.me/medihanaelem