መዝገበ ቅዱሳን
20.7K subscribers
1.92K photos
9 videos
6 files
24 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
#ነሐሴ_13

ነሐሴ ዐሥራ ሦስት #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠበት ዕለት ነው፣ #የቅዱስ_ሙሴ_ሊቀ_ነቢያት ልደቱ ነው፣ ተጋዳይ #አባ_ጋልዩን አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ደብረ_ታቦር

ነሐሴ ዐሥራ ሦስት በዚች ቀን ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅና ክቡር በዓል ነው።

በዚች ቀን መድኃኒታችን ሦስቱን ደቀ መዛሙርቶቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ላይ አወጣቸው። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ። ስለ እነርሱም ጌታችን የሰው ልጅ በጌትነቱ ሲመጣ እስከሚያዩት ድረስ በዚህ ከቆሙት መካከል ሞትን የማይቀምሱት አሉ አለ።

ሰዎች ሁሉ እርሱ ለሙሴ ጌታውና ከሞት ያስነሣው እንደሆነ ለኤልያስም ፈጣሪው እንደሆነና ካሳረገበትም ያወረደው እርሱ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ እነሆ ከጌታ ከኢየሱስ ጋራ እየተነጋገሩ ሙሴና ኤልያስ ወደርሱ መጡ።
ስለዚህም ጴጥሮስ ጌታችንን እንዲህ አለው አቤቱ በዚህ ትኖር ዘንድ ትወዳለህን ሦስት ሰቀላዎችንም አንድ ላንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ እንሠራ ዘንድ።

በዚህም ቃል የደካማነትና የትሕትና ምልክት አለበት። ደካማነት የተባለ ጴጥሮስ ጌታችን ከሰማይ የወረደበትን ሥራ ትቶ በተራራ ላይ ይኖር ዘንድና ራሱን የሚሠውርበትን ቤት ይሠራለት ዘንድ የተናገረው ነው። ትሕትና ያልነውም ጴጥሮስ ለራሱና ለባልንጀሮቹ ሐዋርያት ቤት ይሠራ ዘንድ ስለ አላሰበ ነው። ራሱንና ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን እንደ ባሮች ነቢያትን ደግሞ እንደ ጌቶች አድርጎ አስቧልና።

ሰለ ሐዋርያትም የእውቀት ማነስ አታድንቅ በዚያን ጊዜ ፍጹማን አልሆኑምና። እንዲህም በሚልበት ጊዜ ጌታችን በሰው እጅ የተሠራ ማደሪያን የማይሻ መሆኑን ለጴጥሮስ ያሳየው ዘንድ እነሆ ደመና ጋረዳቸው።

የጌታችንን ጌትነቱን የሚገልጽ በሐዋርያትም ልቡና እምነትን የሚያጸና እንዲህ የሚል ቃል ከደመና ውስጥ መጣ። ይህ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው እርሱንም ስሙት።

ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋራ ሲነጋገሩ ተሰሙ ስለ ርሱ መምጣት የተናገሩትን ትንቢታቸውንም በቸርነቱ አረጋገጠ። ወደ ተራራ ላይ በመውጣቱም ነቢያትና ሐዋርያት ደስ አላቸው።

ሁለተኛም የአብን ቃል በሰሙ ጊዜ ከእነርሱ ሥውር የነበረ የወልድ ዋሕድን በእውነት ሰው መሆን በዚያን ጊዜ ተረዱ ያን ጊዜ የጌትነቱ ክብር ተገልጦአልና። ሐዋርያትም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የሆነ እርሱ ሙሴን ከመቃብር ያስነሣው ኤልያስንም ያሳረገው አውርዶም ያመጣው እርሱ እንደሆነ አወቁ። ከእርሱ በቀር ማንም ማን የሙሴን መቃብር የሚያውቅ የለምና ከዐሳረገው ከእርሱ በቀር ማንም ማን ኤልያስ ያለበትን የሚያውቅ የለምና። በሰማይና በምድር ሥልጣን ካለው ከሁሉ ጌታ በቀር ሙታንን አድኖ ሊአስነሣቸው ማንም አይችልም።

ደብረ ታቦርም የቤተ ክርስቲያን አምሳል ሆነች ከብሉይና ከሐዲስ በውስጧ ሰብስባለችና። የአብንም ቃል በሰሙ ጊዜ በግምባራቸው ፍግም ብለው በምድር ላይ ወደቁ እንደ ሙታንም ሆኑ። ከዓለም አስቀድሞ ከእርሱ ጋራ በህልውና እንዳለ ለልጁ አብ ምስክርን ሆነ ወዲያውኑ ሙሴ ወደ መቃብሩ ኤልያስም ወደ ቦታው ተመለሱ።

ሐዋርያትንም በአነቃቸው ጊዜ ከብቻው ጌታችን በቀር ማንንም አላገኙም። ከባሕርያችን የተዋሐደና ሥጋችንን የለበሰ ፍጹም አምላክ እንደሆነ በዚህ ሐዋርያት አስተማሩ።

እንግዲህ እናስተውል ሰው ካልሆነ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታቸንን ድንግል ማርያምን በአበሠራት ጊዜ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው እንዴት አላት። አምላክ ካልሆነስ ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም እንዴት አላት። ሰው ካልሆነ በበረት እንዴት አስተኙት። አምላክስ ካልሆነ መላእክት ከሰማይ ወርደው ለእግዚአብሔር በሰማያት ምስጋና በምድርም ሰላም ለሰውም ግዕዛኑ ሊሰጠው እያሉ እንዴት አመሰገኑ።

ሰው ካልሆነ ዮሐንስ በውኃ እንዴት አጠመቀው አምላክስ ካልሆነ አልዓዛርን ከመቃብር እንዴት ሊያስነሣው ቻለ። ይህ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው እንድ ልጅ አካላዊ ቃል እግዚአብሔር እርሱ ያለ መለወጥ ያለ መለየት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው እንደሆነ እናምንበታለን። እርሱም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ሁል ጊዜ አንድ ህላዌ ነው ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሙሴ_ሊቀ_ነቢያት

በዚችም ቀን የቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት ልደቱ ነው።

ዓለም በተፈጠረ በ3,600 ዓመት እሥራኤል በረሃብ ምክንያት ያዕቆብ ወደ ምድረ ግብፅ ወረደ:: በዚያም ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ለ215 ዓመታት ተከብረው ለ215 ዓመታት ደግሞ በባርነት በድምሩ ለ430 ዓመታት በምድረ ግብፅ ኑረዋል። በባርነት ዘመናቸውም 'ራምሴና ጋምሴ' የሚባሉ 2 ከተሞችን (ዛሬ ፒራሚዶች የምንላቸውን) በደም ገንብተዋል። ግፋቸው እየበዛ ሲሔድ ግን ጩኸታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ። ያድናቸውም ዘንድ አንድ ቅዱስ ሰው እንዲወለድ አደረገ። ይኽም ሰው ሙሴ ይባላል።

ወላጆቹ መታመናቸውን በፈጣሪያቸው ያደረጉ ዮካብድና እንበረም ሲሆኑ ከሌዊ ነገድ ናቸው፡፡ ከሙሴ ውጪም አሮንና ማርያምን ወልደዋል። ቅዱስ ሙሴ በተወለደበት ወራት ወንድ የእሥራኤል ሕጻናት ይገደሉ ነበር። ጌታ ግን በገዳዮቹ ልቡና ርሕራሔን አምጥቶ አትርፎታል።

በተወለደ በ3 ወሩ ወንዝ ላይ ጥለውት ተርሙት (የፈርኦን ልጅ) ወስዳ በቤተ መንግስት አሳድጋዋለች:: ሙሴ ያለችውም እርሷ ናት። 'ዕጓለ ማይ (ከውሃ የተገኘ) ለማለት ነው። ወላጆቹ ያወጡለት ስም ግን 'ምልክአም' ይባላል። ገና ሲወለድ ፊቱ እንደ መልአክ ያበራ ነበርና።

ቅዱስ ሙሴ 5 ዓመት በሆነው ጊዜ ፈርኦንን በጥፊ በመማታቱ ለፍርድ ቀርቦ እሳትን በመብላቱ አንደበቱ ኮልታፋ ሆኖ ቀርቷል። እናቱ ዮካብድ ሞግዚት ሆና ስላሳደገችው 40 ዓመት በሆነው ጊዜ የፈርኦንን ቤት ምቾትና የንጉሥ ልጅ መባልን ናቀ። ቅዱስ ዻውሎስ እንደሚለው በአሕዛብ ቤት ካለ ምቾት ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን ሊቀበል ወዷልና። (ዕብ. 11÷24)

አንድ ቀንም ለዕብራዊ ወገኑ ተበቅሎ ግብጻዊውን ገድሎት ወደ ምድያም ሸሸ። በዚያም ለ40 ዓመታት የካህኑን ዮቶርን በጐች እየጠበቀ ኢትዮዽያዊቱን ሲፓራን አግብቶ ኖረ። ልጆንም አፈራ። 80 ዓመት በሞላው ጊዜ እግዚአብሔር በደብረ ሲና ተናገረው። ሕዝቡንም ከባርነት ቀንበር እንዲታደግ ላከው፡፡ ሙሴም ከወንድሙ ጋር ግብጻውያንን በ9 መቅሰፍት በ10ኛ ሞተ በኩር መታ። እሥራኤልንም ነጻ አወጣ፡፡

ሊቀ ነቢያት የሠራቸው ሥራዎች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም፦ እርሱ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ ሕዝቡን በደረቅ አሻግሯል፣ ግብጻውያንን ከነሠረገሎቻቸው በባሕር ውስጥ አስጥሟል፣ ለሕዝቡ መና ከደመና አውርዷል፣ ውሃን ከጨንጫ (ከዓለት) ላይ አፍልቁዋል፣ በብርሃን ምሰሶ መርቷቸዋል፣ በ7 ደመና ጋርዷቸዋል፣ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ድል ነስቶላቸዋል፣ ቅዱስ ሙሴ ለ40 ዓመታት ሕዝቡን ሲመራ ከእግዚአብሔር ጋር ለ570 ጊዜ ተነጋግሯል።

ከጸጋው ብዛትም ፊቱ ብርሃን ስለ ነበር ሰዎች እርሱን ማየት አይችሉም ነበር። ታቦተ ጽዮንንና 10ሩ ቃላትን ተቀብሎ ጽላቱ ቢሰበሩ ራሱ ሠርቶ በጌታ እጅ ቃላቱ ተጽፈውለታል፡፡ ቅዱስ ክቡር ታላቅ ጻድቅ ነቢይና ደግ ሰው ቅዱስ ሙሴ በ120 ዓመቱ ዐርፎ በደብረ ናባው ሊቃነ መላእክት ቅዱሳን ሚካኤል ገብርኤልና ሳቁኤል ቀብረውታል። መቃብሩንም ሠውረዋል። (ይሁዳ 1÷9)

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ጋልዮን_መስተጋድል....
#አባ_ጋልዮን_መስተጋድል (ነሐሴ 13)

በዚችም ቀን ዳግመኛ ተጋዳይ አባ ጋልዩን አረፈ። ይህም በቀንና በሌሊት ለጸሎት የማይታክት ተጋዳይ ሆነ ጐልማሳ ሁኖ ሳለ ከመነኰሰም ጀምሮ እስከ ሸመገለ ድረስ ከበአቱ ቅጽር ውጭ አልወጣም ከማኅበር ጸሎት ጊዜ በቀር ከመነኰሳቱ ማንም አያየውም።

ሰይጣናትም ተጋድሎውን በአዩ ጊዜ መነኰሳትን ተመስለው ወደርሱ በመንፈቀ ሌሊት ገብተው እንዲህ አሉት። እኛ ተሠውረን የምንኖር ገዳማውያን ነን ከእኛ አንዱ በሞት ስለተለየ ከእኛ ጋራ ልንወስድህ ወደን ወዳንተ መጣን ለእርሱም ቃላቸው እውነት መስሎት ልብስና ሲሳይ ወደማይገኝበት ጠፍ ወደ ሆነ ተራራ ላይ እስከ አደረሱት ድረስ አብሮአቸው ሔደ።

ሲጠቃቀሱበትም በአየ ጊዜ ሰይጣናት መሆናቸውን አውቆ በላያቸው በመስቀል ምልክት በአማተበ ጊዜ ተበተኑ። በሚመለስም ጊዜ በወዲያም በወዲህም መንገድ አጣ የክብር ባለቤት ወደሆነ ጌታችን ጸለየ ከዚህ በኋላ ከአንዱ ገዳም ወደ አንዱ ገዳም የሚዘዋወሩ ከአባ ሲኖዳ ገዳም የሆኑ መነኰሳት ተገለጹለት። እነርሱም የዳዊትን መዝሙር ያነቡ ነበር ስለ ሥራው ጠየቁት በእርሱ ላይ የደረሰውን ሁሉ በነገራቸው ጊዜ ከእርሳቸው ጋራ ወስደውት በፀሐይ የበሰለ ዓሣ እየተመገበ ከእሳቸው ጋራ አንዲት ዓመት ሙሉ ኖረ።

ያመነኰሰው መምህሩ አባ ይስሐቅም ወሬውን በአጣ ጊዜ ፊቱን ያሳየው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። አባ ጋልዮንም በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ወደ ርሱ መጣ አባ ይስሐቅም በአየው ጊዜ በእርሱ ደስ አለው ወዴት ነበርክ አለው እርሱም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ነገረው።

ከዚህም በኃላ የሚያርፍበት ጊዜ ደርሶ በሰላም አረፈ መነኰሳቱም በክብር ቀበሩት።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
#አባ_ጋልዮን_መስተጋድል