መዝገበ ቅዱሳን
22.8K subscribers
1.93K photos
9 videos
6 files
26 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
#መስከረም_28

መስከረም ሃያ ስምንት በዚች ቀን #ቅዱስ_አባዲርና እኅቱ #ቅድስት_ኢራኢ በሰማዕትነት አረፉ፣ የኬልቅዩስ ልጅ #ቅድስት_ሶስና አረፈች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባዲር_እና_እኅቱ_ኢራኢ

መስከረም ሃያ ስምንት በዚች ቀን ቅዱስ አባዲርና እኅቱ ኢራኢ በሰማዕትነት አረፉ። ይህም ቅዱስ ለአንጾኪያ መንግሥት የሠራዊት አለቃ ለሆነ ለፋሲለደስ የእኅቱ ልጅ ነው እርሱም በአባቱ መንግሥት የሠራዊት አለቃ ነበር በውስጡም የሚጸልይበት እልፍኝ አለው። ከሌሊቱም እኩሌታ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለትና እንዲህ አለው የሰማዕትነት አክሊልን ትቀበል ዘንድ እኅትህ ኢራኢን ይዘህ ወደ ግብጽ አገር ሒድ። ስለ ሥጋችሁም እንዲአስብ ሳሙኤል የሚባለውን አንድ ሰው እኔ አዛለሁ ከዚህም በኋላ ሰላምታ ሰጥቶት በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ።

እንዲሁ ለእኅቱ ኢራኢ ተገልጦላት እንዲህ አላት የወንድምሽን ቃሉን ስሚው ትእዛዙንም አትተላለፊ ከእንቅልፏም ነቅታ እጅግ ተንቀጠቀጠች ወደ ወንድሟም ሒዳ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተገለጠላትና እንደ ተናገራት አስረዳችው። እጅግም ደስ አላቸው ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስም ስለ ስሙ ወደ ግብጽ አገር ሒደው ደማቸውን ያፈሱ ዘንድ በዚህ ምክር ተስማሙ።

የቅዱስ አባዲር እናትም ይህን ነገር በአወቀች ጊዜ ልብሷን ቀዳ አለቀሰች ከባሮቿም ጋር ወደ ቅዱስ አባዲር መጥታ በሰማዕትነት እንዳይሞት ታምለው ጀመር እርሱም ስለ ሰማዕትነት ነገር ዲዮቅልጥያኖስን እንዳይናገረው ማለላት በዚያንም ጊዜ ከልቅሶዋ ታግሣ ጸጥ አለች።

ወደ ሌላ ቦታ ሒዶ በሰማዕትነት እንደሚሞት ግን አላሰበችም። ቅዱስ አባዲርም በየሌሊቱ ሁሉ እንዲህ የሚያደርግ ሆነ ልብሱንም ለውጦ ከቤቱ ይወጣል በወህኒ ቤት ላሉ እሥረኞችም ውኃ በመቅዳት ያጥባቸዋል እስከሚነጋም እንዲህ ያደርጋል በር የሚጠብቀውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው ይህን ለማንም አትናገር ይህንንም ሥራ ብትገልጥ እኔ ራስህን በሰይፍ እቆርጣለሁ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ አባዲር ተነሣ እኅቱን ኢራኢንም ይዞ ወደ ግብጽ አገር ሒዶ እስክንድርያ ደረሰ። ከወታደሮችም ያወቁት አሉ አንተ የሠራዊት አለቃ ጌታችን አባዲር አይደለህም እንዴ አሉት። እርሱም ፈገግ ብሎ ብዙዎች እንዲሁ ይሉኛል እኔ ግን እመስለው ይሆናል እንጂ እርሱን አይደለሁም አላቸው ከዚያም ወደ ሌላ ቦታ ሔደ። በዚያም እንደቀድሞው እርሱ አባዲር እንደ ሆነ ተናገሩት እርሱም አይደለሁም ይላቸው ነበር።

ከዚህም በኋላ ከእስክንድርያ ከተማ ወጥቶ ወደ ታላቋ የምስር ከተማ ሔደ በዚያም ከአባ አበከረዙን ጋር ተገናኝተው ከእርሱ ቡራኬ ተቀበሉ። ከዚያም ወደ እስሙናይን ደርሰው ከዲያቆን ሳሙኤል ጋር ተገናኙ በማግሥቱም ወደ እንጽና ከተማ ሔዱ በመኰንን አርያኖስም ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመኑ።

መኰንኑም ጽኑዕ ሥቃይን ሊአሠቃያቸው ጀመረ ቅዱስ አባዲርም በሥቃይ ውስጥ ያጸናቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ለመነ ያን ጊዜ ጌታችን የእርሱን ነፍስና የእኅቱን ነፍስ ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወስዶ ሰማዕታት የሚኖሩበትን የብርሃን ቤቶችን አሳያቸውና ከዚህም በኋላ ወደ ሥጋቸው መለሳቸው።

መኰንኑም ማሠቃየት በሰለቸ ጊዜ ራሳቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። ራሳቸውንም ከሚቆርጧቸው በፊት መኰንኑ አርያኖስ ቅዱስ አባዲርን እንዲህ አለው አንተ ማን እንደሆንክ ስምህም ማን እንደሆነ አንተም ከወዴት እንደሆንክ ትነግረኝ ዘንድ በፈጣሪህ አምልሃለሁ አለው።

ቅዱስ አባዲርም በነገርኩህ ጊዜ ራሳችንን እንዲቆርጡ ያዘዝከውን ትእዛዝ እንዳትለውጥ አንተም ማልልኝ አለው መኰንኑም ማለለት ያን ጊዜም የሠራዊት አለቃ እኔ አባዲር ነኝ አለው መኰንኑ አርያኖስም እንዲህ ብሎ ጮኸ ወዮልኝ ጌታዬ ሆይ በአንተ ፈንታ እኔ ልሞት ይገባኛል ይህን ሁሉ ጽኑ ሥቃይ እስከ አሠቃየሁህ ድረስ አንተ ጌታዬ እንደሆንክ እንዴት አላስረዳኸኝም ቅዱስ አባዲርም አንተም እንደኔ በሰማዕትነት ትሞት ዘንድ አለህና አትዘን አሁንም ምስክርነታችንን በፍጥነት ፈጽም ብሎ መለሰለት።

በዚያንም ጊዜ ራሳቸውን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አርያኖስ አዘዘና እርሱንና እኅቱ ኢራኢን ቆረጧቸው። ያማሩ ልብሶችንም ዘርግተው ገነዙአቸው ዲያቆን ሳሙኤልም የመከራው ወራት እስከሚያልፍ ወደ ቤቱ ወስዶ አኖራቸው ከዚያም በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ታነፀችላቸውና ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ ከእርሳቸውም ታላላቅ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።


✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሶስና

በዚችም ቀን የኬልቅዩስ ልጅ ቅድስት ሶስና አረፈች። ዜናዋም እንዲህ ነው ይችን ቅድስት ሶስናን በባቢሎን የሚኖር ስሙ ኢዮአቄም የሚባል አንድ ሰው አገባት እርሷ እጅግ መልከ መልካም የሆነች ፈጣሪ እግዚአብሔርንም የምትፈራው ነበረች።

እናትና አባቷም ደጋግ ነበሩ ለልጃቸውም ሙሴ የጻፋትን ኦሪት አስተምረዋት ነበር። ባሏ ኢዮአቄም ግን እጅግ ባለጸጋ ነበር በቤቱም አጠገብ የተክል ቦታ ነበረው ከሁሉ እርሱ ይከብር ነበርና አይሁድ ወደርሱ ይመጡ ነበር።

ኃጢአት ከባቢሎን አገር ሕዝቡን እንጠብቃቸዋለን ከሚሉ ከግብዞች ወገኖች እንደ ወጣች እግዚአብሔር ስለነርሱ የተናገረባቸው ግብዞች የሆኑ ሁለት መምህራን በዚያ ወራት ታዩ።

እነርሱም በኢዮአቄም ቤት የለመዱ የሚአገለግሉም ናቸው። የሚፈራረዱም ሁሉ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ ወደ ቤታቸው ከገቡ በኋላ ቀትር በሆነ ጊዜ ሶስና ወደ ባሏተክል ቦታ ገብታ በዚያ ትመላለስ ነበር።

ገብታ በተመላለሰች ጊዜ እነዚያ መምህራን ሁልጊዜ ያዩዋት ነበርና ተመኙዋት። ልቡናቸውንም ለወጡ ሰማይንም እንዳያዩ ዐይኖቻቸውን ግልብጥብጥ አደረጉ ሰማያዊ እግዚአብሔርን እንዳያስቡ እውነትኛ ሕግን አላሰቡም።

ሁለቱም ሁሉ ወደዷት ፈቃዳቸውን መናገር አፍረዋልና እርስበርሳቸው በልቡናቸው ያለውን ነገር አልተነጋገሩም ይደርሱባትም ዘንድ ይወዱ ነበር ያገኟትም ዘንድ ሁልጊዜ ይጠብቋታል።

አንዱም አንዱን የምሳ ጊዜ ነውና ወደ ቤታችን እንግባ አለው እየራሳቸውም ተለያይተው ሔዱ ። ተመልሰውም በጎዳና አንድነት ተገናኙ ሁለቱም ተያዩ ያን ጊዜም ፍላጎታቸውን ተነጋገሩ ብቻ ለብቻ እሷን የሚያገኙበትን ጊዜ ተቃጠሩ።

ከዚህም በኋላ በቀን ሲጠብቋት ሶስና ሁል ጊዜም ትገባ እንደነበር ከሁለቱ ደንገጡሮቿ ጋር ገባች አልቧታልና በተክል ውስጥ ትታጠብ ዘንድ ወደደች። ተሠውረው ከሚጠብቋት ከሁለቱ ረበናት በቀር በዚያ ማንም ማን አልነበረም።

ዘይትና ሽቱ አምጥተው ያጥቧት ዘንድ ልትታጠብ የተክሉንም ደጅ ይዘጉ ዘንድ ደንገጡሮቿን አዘዘቻቸው። እነርሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ የተክሉን ደጃፍ ዘግተው ያዘዘቻቸውን ያመጡ ዘንድ በስርጥ ጐዳና ወጡ የተሠወሩ እነዚያን ረበናት ግን አላዩአቸውም።

እነዚያ ደንገጡሮች ከወጡ በኋላ ሁለቱ ረበናት ተነሥተው ወደርሷ ሮጡ እነሆ የተክሉ ደጃፍ ተዘግቷል የሚያየን የለምና እንደርስብሽ ዘንድ እንወዳለንና እሺ በይን አሏት። ይህ ካልሆነ ካንቺ ጋር ሰውን እንዳገኘን ተናግረን እናጣላሻለን ስለዚህም ደንገጡሮችሽን ከአንቺ አሰወጥተሽ ሰደድሽ።
ሶስናም አለቀሰች በሁሉም ፈጽሞ ተጨነቅሁ ባደርገው እሞታለሁ ባላደርገውም አልድንም ከእጃቸው ማምለጥንም አልችልም በእግዚአብሔር ፊት ከምበድል ኃጢአት ሳልሠራ በእጃችሁ መውደቅ ይሻለኛል አለች።

ሶስና ቃሏን አሰምታ ጮኸች። እነዚያም ረበናት ከእርሷ ጋር ጮኹ አንዱ ሩጦ ሒዶ የተክሉን ደጃፍ ከፈተ በቤቷም ያሉ በተክል መካከል ጩኸትን ሰምተው ወጡ ምን እንደሆነ ያዩ ዘንድ በሥርጥ ጐዳናም ሮጡ።

እነዚህ ሁለቱ ረበናት ይህንን ነገር በተናገሩ ጊዜ በሶስና ላይ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ ተሰምቶ አያውቅም ነበርና ዘመዶቿና አሽከሮቿ እጅግ አፈሩ።

በማግሥቱም ሕዝቡ በባሏ በኢዮአቄም ዘንድ ተሰበሰቡ እነዚያም ሁለቱ ረበናት ሶስናን ያስገድሏት ዘንድ ከዓመፀኛ ልባቸው ጋራ መጡ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ያመጡአት ዘንድ ወደ ኢዮአቄም ሚስት ወደ ሶስና ላኩ ብለው አዘዙ ወደርሷም ላኩባት። እርሷም ከእናት ከአባቷ ከወገኖቿ ከዘመዶቿ ከሚያውቋትም ሁሉ ጋር መጣች።

ሶስና ግን እጅግ ደመ ግቡ ነበረች መልኳም ያማረ ነው። ዓመፀኞች የሆኑ እነዚያ ሁለቱ ረበናት መልኳን ለመጥገብ ይገልጧት ዘንድ አዘዙና ገለጧት። አባቷ፣ እናቷ፣ ቤተሰቦቿ፣ የሚያውቋትም ሁሉ አለቀሱላት። እነዚያም ሁለቱ መምህራን በሕዝቡ መካከል ተነሥተው እጆቻቸውን በራሷ ላይ አኖሩ። እርሷ ግን ልቡናዋ በእግዚአብሔር ታምኗልና እያለቀሰች ወደ ሰማይ ተመለከተች።

እነዚያም ረበናት ብቻችንን በተክል ውስጥ ስንመላለስ እርሷ ከሁለቱ ደንገጡሮቿ ጋር ገባች ደንገጡሮቿንም ልካቸዋለችና የተክሉን ደጃፍ ዘግተው ሔዱ ከዚያም በኋላ አንድ ጐልማሳ ከተሠወረበት መጥቶ አብሮዋት ተኛ። እኛ ግን በዚያ ተክል ዳርቻ ሁነን ኃጢአታቸውን አየን ወደነርሱም ሮጥን አንድነት ተኝተውም አገኘናቸው። እኛም እርሱን መያዝ ተሳነን እርሱ በርትቶብናልና አመለጠን የተክሉንም ደጃፍ ከፍቶ ወጣ። እርሷን ግን ይዘን ሰውዬው ማን እንደ ሆነ ጠየቅናት ግን አልነገረችንም ለዚህም ነገር ምስክሩ እኛ ነን አሉ።

የሕዝቡ መምህራንና መኳንንትም ነበሩና በአደባባይ የተሰበሰቡ ሰዎች ነገራቸውን አመኑላቸው ትሙት በቃ ብለውም ፈረዱባት። ሶስናም ቃሏን አሰምታ ጮኸች ዘለዓለም ጸንተህ የምትኖር የተሠወረውን የምታውቅ የሚደረገውን ሁሉ ሳይደረግ የምታውቅ ፈጣሪ ሆይ በሐሰት እንዳጣሉኝ አንተ ታውቃለህ እነዚህ መምህራን ክፉ ነገርን ባደረጉብኝ ገንዘብ የሠራሁት ኃጢአት ሳይኖር እነሆ እሞታለሁ አለች። እግዚአብሔርም ቃሏን ሰማ።

ይገድሏት ዘንድ ሲወስዷት እግዚአብሔር ስሙ ዳንኤል በሚባል ልጅ ላይ ልቡናን አነሣሣ እኔ ከዚች ሴት ደም ንጹሕ ነኝ ብሎ ቃሉን አሰምቶ ተናገረ። ሕዝቡም ሁሉ ወደርሱ ተመልሰው አንተ የምትናገረው ይህ ነገር ምንድን ነው አሉ።

ዳንኤልም በመካከላቸው ቁሞ አላዋቆች የምትሆኑ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሳትመረምሩና ነገሩን ሳትረዱ በእስራኤል ልጅ ላይ እንዲህ አድርጋችሁ እንደዚህ ያለ ፍርድን ትፈርዳላችሁን አለ እነዚህ መምህራን በሐሰት አጣልተዋታልና ወደ አደባባይ ተመለሱ አላቸው።

ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ ወደ አደባባይ ተመለሱ አለቆችም ዳንኤልን እግዚአብሔር አንተን አልቆሃልና በመካከላችን ተቀምጠህ ተናገር አሉት። ዳንኤልም እየራሳቸው አራርቃችሁ አቁሙአቸው እኔም ልመርምራቸው አላቸውና አንዱንም አንዱን አራርቀው አቆሟቸው።

ዳንኤልም ከእርሳቸው አንዱን ጠርቶ ከዚያ ሰው ጋር በምን ዕንጨት ሥር ሲነጋገሩ አየሃት አለው በኮክ ዕንጨት ሥር ሲነጋገሩ አየኋቸው አለ እርሱንም አርቆ ሁለተኛውን ሲነጋገሩ ያየህበት ዕንጨት ምንድን ነው አለው ሮማን ከሚባል ዕንጨት ሥር ነው አለ። ሕዝቡም ሁሉ ቃላቸውን አሰምተው በመጮህ ያመነችበት ሶስናን ያዳናት እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

ከቃላቸው የተነሣ ዳንኤል አስነቅፏቸዋልና ምስክርነታቸውንም ሐሰት አድርጎባቸዋልና በነዚያ በሁለቱ መምህራን ላይ በጠላትነት ተነሥተው ገደሏቸው።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም)
#መስከረም_29

መስከረም ሃያ ዘጠኝ በዚህችም ቀን #ከቅድስት_አርሴማና_ከእመምኔቷ_ከአጋታ ጋር ደናግላን በሰማዕትነት አረፉ፤ ዳግመኛም #የቅዱስ_ዮሐንስ_ነባቤ_መለኮት (ወንጌላዊው) እንደ ንስር መጥቆ "ቀዳሚሁ ቃል.." ( ዮሐ. ፩፥፩) ብሎ ወንጌሉን የጻፈበት ዕለት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሰማዕት_ቅድስት_አርሴማ

በዚችም ቀን ከቅድስት አርሴማና ከእመምኔቷ ከአጋታ ጋር ደናግል በሰማዕትነት አረፉ። ይህም እንዲህ ነው በከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን እርሱ መልኳ ውብ የሆነ ብላቴና ድንግል ሊአገባ ሽቶ በየሀገሩ ሁሉ ሒደው መርጠው ያመጡለት ዘንድ አሽከሮቹን አዘዘ።

ይችንም የሚመስላት የሌለ ቅድስት አርሴማን በሮሜ አገር በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ አገኙዋት። ሥዕሏንም ሥለው ለንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ላኩለት ንጉሡም ሥዕሏን በአየ ጊዜ እጅግ ደስ አለውና ለሠርግ እንዲመጡ ወደ መኳንንቱ ላከ።

እሊያ ደናግልም ይህን ነገር በአወቁ ጊዜ ይረዳቸው ዘንድ ድንግልናቸውንም ይጠብቅ ዘንድ አልቅሰው ወደ እግዚአብሔር ለመኑ። ከዚህም በኋላ ተነሥተው በሥውር ሸሹ የንጉሥ ድርጣድስ ግዛት ወደ ሆነ ወደ አርማንያ ሀገርም ደርሰው በአንድ ቦታ ተቀመጡ ከእርሳቸውም ጋር የተሰደዱ ቁጥራቸው ሰባ አምስት የሆነ ወንዶች፣ ሴቶችም ሠላሳ ዘጠኝ የሆኑ ከእርሳቸው ጋራ አሉ። ምግባቸውን አያገኙም ነበርና በታላቅ ችግር ውስጥ ኖሩ ከእነርሱም መብራት የምትሠራ አንዲት ሴት ነበረች ከእርሷም የእጅ ሥራ ከሚገኘው በየጥቂቱ ይመገባሉ።

ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም የከበረች አርሴማን በፈለጋት ጊዜ አላገኛትም ግን በአርማንያ አገር እንዳለች ስለርሷ ሰማ። ደግሞ ለአርማንያ ንጉሥ ለድርጣድስ ስለርሷ ከዲዮቅልጥያኖስ ሸሽታ እንደ መጣች የአርሴማን ሥራ ነገሩት እርሱም አንዱን የአርማንያ መኰንን ለእኔ ጠብቃት ወደ እኔም ላካት ብሎ አዘዘው።

ደናግሉም ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ ሌላ ቦታ ተሠወሩ ወደ ንጉሥም ወነጀሉአቸው ንጉሡም ቅዱስት አርሴማን በክብር አድርገው ያመጧት ዘንድ አዘዘ እርሷም ወደ እርሱ መምጣትን እምቢ በአለች ጊዜ እየጎተቱ ወስደው ወደርሱ አደረሷት።

የቅድስት አርሴማንም ላህይና ደም ግባቷን በአየ ጊዜ ድንግልናዋን ሊያረክስ ሽቶ እናቷ አጋታን አባብላ እሺ ታሰኝለት ዘንድ አዘዛት አጋታም ወደርሷ ሒዳ ልቧን አስጨከነች እንዲህም አለቻት። ዕወቂ ይህ ርኲስ አረሚ እንዳያረክስሽና ሰማያዊ ሙሽራሽን እንዳትተዪ እርሱም ክብር ይግባውና የእግዚአብሔር ልጅ ሕያው ክርስቶስ ነው።

ንጉሡም ይዞ ወደ እልፍኙ ሊአስገባት ከአደባባይ መካከል ተነሥቶ ድንግል አርሴማን ያዛት። በዚያንም ጊዜ በቅድስት አርሴማ ላይ የእግዚአብሔር ኃይል አደረባትና በምድር ላይ ጣለችው እርሱ ግን በጦርነት እጅግ የጸና አርበኛ ስለ ነበር በታናሽ ሴት ብላቴና ስለተሸነፈ ያን ጊዜ አፈረ። ራሷንም በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጧት ከዚህም በኋላ ደናግሉን ሁሉ ከእናታቸው አጋታ ጋር ይገድሏቸው ዘንድ አዘዘ።

አንዲት የታመመች ድንግል ነበረች በዐልጋዋ ላይም እንደተኛች ወደ ወታደሮች ጮኸች መጥተውም እንደ እኅቶቿ ራሷን ቆረጡ ሁሉም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ እነዚያንም ከሮሜ አገር አብረው የመጡ ወንዶችን ገደሏቸው ቁጥራቸውም ሰባ አምስት ናቸው ሥጋቸውም በተራራ ላይ የተጣለ ሁኖ ቀረ።

ሰማዕታትም ከተገደሉ በኋላ በንጉሡ ላይ ጋኔን ተጫነበት መልኩም ተለውጦ እንደ እርያ ሆነ። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ወደርሱ መጥቶ በላዩ ጸልዮ እስከ አዳነው ድረስ ስለዚህም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ። የቅዱሳን ሰማዕታትንም ሥጋቸውን ከተጣለበት ሰብስበው በአማረ ቦታ አኖሩአቸው ያማረች ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንም ተሠራችላቸው። ከእነርሱም ታላላቅ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_ወንጌላዊ_ነባቤ_መለኮት

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ እንደ ንስር መጥቆ "ቀዳሚሁ ቃል.." ( ዮሐ. ፩፥፩) ብሎ ወንጌሉን የጻፈበት ዕለት እንደሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፡- ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን ለመስበክ ዕጣ የደረሰው እስያ ስለነበር ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን አስከትሎ ሄደ፡፡ ይኽችውም ኤፌሶን በጥንቱ በታናሽ እስያ በዛሬው የቱርክ ግዛት ውስጥ ከተማ ናት፡፡ ዛሬ ኢያዞሎክ ተብላ የጥንት ታሪኳ ጠፍቷል፡፡ አስቀድሞ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ሰብኮባታል፡፡ ደቀ መዝሙሩን ቅዱስ ጢሞቴዎስንም በከተማዋ ላይ ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ እርሱም በግፍ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ቅዱስ ዮሐንስን እየረዳው በከተማዋ ብዙ አገልግሏል፡፡ በኋላ ግን በግፍ ገድለውታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ኤፌሶን ለመሄድ በመርከብ ሲሳፈር መርከቡ በማዕበል ተሰበረ፡፡ ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን መዕበሉ ወደ አንዲት ደሴት አደረሰው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በመርከቡ ስባሪ ተንጠልጥሎ በባሕሩ ማዕበል መካከል 40 ቀንና 40 ሌሊት ከኖረ በኋላ ማዕበሉ ተፍቶ አብሮኮሮስ ካለበት ደሴት አደረሰውና ተያይዘው ኤፌሶን ከተማ ገቡ፡፡ የከተማይቱም ሰዎች እጅግ ክፉዎች ስለነበሩ መጀመሪያ ላይ ቅዱስ ወንጌልን መስበክ አልቻሉም ነበር፡፡ እነርሱም እጅግ ክፉዎች መሆናቸውን ስላወቀ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ዕጣው ሲደርሰው በሀዘን አልቅሶ ነበር፡፡ አሁንም ከተማው በገቡ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ምክንያት በመፍጠር ሮምና ለምትባል ሴት የውሽባ ቤቷ እሳት አንዳጅ ሆኖ አብሮኮሮስም ዕቃ አጣቢ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ የቀጠረቻቸው ሴትም እጅግ ታሠቃያቸው ጀመር፡፡ ባሮቿ እንደሆኑ ተስማምተው ስለጻፉላት ትደበድባቸውም ነበር፡፡

እነርሱም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ እየኖሩ እያለ በአንዲት ዕለት የአገረ ገዥው ልጅ ለመታጠብ ወደ ውሽባው ቤት ገባ፡፡ በውሽባ ቤቱም የሰይጣን ኃይል ስለነበረበት የመኰንኑን ልጅ አንቆ ገደለው፡፡ የአገሪቱም ሰዎች ሁሉ ለሞተው የመኰንን ልጅ ሊያለቅሱ ሲሰበሰቡ ቅዱስ ዮሐንስም አብሮ ቆሞ ሲመለከት ሮምና መጥታ "በጌታዬ ልጅ ሞት ልትደሰት መጣህን" እያለች ረገመችው፡፡ እርሱም "አይዞሽ አትዘኚ" አላትና ወደ ሞተው ልጅ ቀርቦ በመስቀል ምልክት ካማተበበት በኋላ በፊቱ እፍ አለበት፡፡ የሞተውም ልጅ ድኖ ተነሣ፡፡ የሀገሪቱም ሰዎች እጅግ ደነገጡ፡፡ ሮምናም ደንግጣ "እግዚአብሔር የሚሉት አምላክ አንተ ነህን" ብላ ጠየቀችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም "በፍጹም እኔ አምላክ አይደለሁም፣ እኔ የእርሱ አገልጋዩና ሐዋርያው ነኝ እንጂ" አላት፡፡ ሮምናም ስለበደለቻቸው በደል ሁሉ መሪር ዕንባን እያለቀሰች ይቅር እንዲሏት ለመነቻቸው፡፡ እነርሱም አረጋጉዋት፡፡ ከሕዝቡም ውስጥ ብዙዎቹ በጌታችን አመኑ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ሌሎች ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን እየሰበከ ከጣዖት አገልጋዮች በቀር ሁሉንም አሳምኖ አጠመቃቸው፡፡ አገልጋዮችን ኤጲስቆጶሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ከሾመላቸው በኋላ ወደ ሌሎች አቅራቢያ አገሮች ሄደ፡፡

በመጨረሻም በከሃዲውና በጨካኙ በድምጥያኖስ ዘመን በጣዖት አምላኪዎች ተከሶ ለፍርድ ቀረበ፡፡ በፈላ ውኃ ካሠቃዩት በኋለ በፍጥሞ ደሴት አጋዙት፡፡ በዚያም ሳለ ራእዩን ተመልክቶ ጻፈው፡፡ ድምጥያኖስም ከተገደለ በኋላ ከግዞቱ ተመልሶ ሦስቱን መልእክታቱንና ቅዱስ ወንጌሉን ጽፏል፡፡ ጌታችንም አስቀድሞ ሞትን እንደማይቀምስ ለዮሐንስ ቃል ገብቶለት ነበርና (ዮሐ 21፡22) ጥር 4 ቀን እንደ ኤልያስና ሄኖክ ሞትን እንዳያይ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወስዶታል።
ጌታችን ለዮሐንስ ያልነገረው እርሱም ያላስተማረው ምሥጢር የለም፡፡ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር "በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ…" ብሎ የጌታችን ነገር ተመራምሮ ለመድረስ ሲል በመሀል መልአኩን በዮርዳኖስ ባሕር ላይ ሲሄድ አገኘው፡፡ መልአኩም የዮርዳኖስን ባሕር በእንቁላል ቅርፊት እየጨለፈ ወደ ውጭ ሲያፈስ ተመለከተው፡፡ ዮሐንስም ተገርሞ "ምን ማድረግህ ነው" አለው፡፡ መልአኩም "የዮርዳኖስን ባሕር ቀድቼ እየደፋሁ ልጨርሰው ነው" ሲለው ዮሐንስም መልሶ "ታዲያ በእንቁላል ስባሪ ነውን?" አለው፡፡ መልአኩም "አዎን" አለው፡፡ ዮሐንስም "በከንቱ ደከምክ" አለው፡፡ ይህን ጊዜ መልአኩም መልሶ "አንተስ እንጂ ደግሞ የአምላክን መገኘት፣ አኗኗሩንም ተመራምረህ በጥበብ ለማግኘት ብለህ 'በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ..' ብለህ ጀምረህ የለምን? አንተ ጌታን ተመራምረህ ካገኘህና ከደረስክበት እኔም የዮርዳኖስን ወንዝ በዚህ እንቁላል ቅርፊት ቀድቼ እጨርሰዋለሁ" አለው፡፡ ዮሐንስም ይህን ጊዜ ደንግጦ ዝቅ ብሎ "ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ…" ብሎ ሀሳቡን ለወጠና ሌላ ታሪክ ቀጠለ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ወክሎ እመቤታችንን በአደራ የተቀበለ እርሱም ለመቤታችን በአደራ የተሰጠ ሲሆን እመቤታችንን ከወሰዳት በኋላ ለ16 ዓመት እየተንከባከበ ጠብቋታል፡፡ እናቱም በሕፃንነቱ ስለሞተች እመቤታችን ናት እየተንከባከበች ያሳደገችው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በመልኩም ከጌታችን ጋር ይመሳል ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሥዕል የመሳል ተሰጥኦም ነበረው፡፡ ጌታችን በተሰቀለበት ዘመን የነበረው ጢባርዮስ ቄሳር ልጁ በሽተኛ ነበር፡፡ የጌታችንን የማዳን ሥራ እየሰማ እነ ጲላጦስም ስለጌታችን የሚጽፉለትን ይሰማ ስለነበር ልጁን ከጌታችን መቃብር ላይ እንዲያኖሩለት ላከው፡፡ ልጁም ፈጥኖ ተፈወሰለት፡፡ ጢባርዮስ ቄሳርም በልጁ መዳን ምክንያት የጌታችንን ውለታ ማስቀመጥ ፈልጎ የጌታችንን ሥዕሉን የሚሥልለትን ሲያጠያይቅ ዮሐንስን አገናኙት፡፡ ዮሐንስም ጌታችንን ልክ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ አድርጎ በመሣል ለጢባርዮስ ቄሳር ሰጠው፡፡ ሲሥለውም በመጀመሪያ ጌታችንን ልክ እንደተሰቀለ አድርጎ ራቁቱን ነበር የሳለው፡፡ ዮሐንስ የሳለው የጌታችን ሥዕልም አፍ አውጥቶ "በመጀመሪያ አይሁድ በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?" ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ "እንዴት አድርጌ ልሳልህ?" ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም "ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ" አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ከሳለው በኋላ ሥዕሉን ትኩር ብሎ ተመልክቶ ቢስመው ከንፈሩ አንድ ቀን ተኩል ያህል ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸውን የጌታችንን ስነ ስቅለት የሚያሳዩ ሥዕሎች መገኛቸው ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስ የሳለው ሥዕል ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፦
በሕይወቱና በኑሮው ሁሉ ጌታችንን ለመምሰል ይጥር ነበርና ጌታችንም እጅግ ይወደው ስለነበር "#ፍቁረ_እግዚእ" ተባለ፣ የታላቁ ያዕቆብ ታናሽ ወንድም ስለሆነና አባቱም ዘብድዮስ ስለሚባል "#ዮሐንስ_ወልደ_ዘብድዮስ" ተባለ፣ ለጌታችን ባለው ቅናትና ከወንድሙ ጋር ሆነው ባሳዩት የኃይል ሥራ እንዲሁም የጌታችንን አምላክነት በመግለጡ "#ወልደ_ነጎድጓድ" ተብሏል፣ ነገረ መለኮትን ከሌሎቹ በበለጠ ሁኔታ አስፍቶና አምልቶ በማስተማሩ "#ነባቤ_መነኮት ወይም #ታኦሎጎስ" ተብሏል፣ ኃላፊውንና መጻዒውን ጊዜ በራእዩ ስለገለጠ "#አቡቀለምሲስ" ተባለ፣ ይህም በግሪክኛ #ባለራእይ ማለት ነው፣ የጌታችንን መከራ መስቀሉን እያስታወሰ 70 ዘመን ሙሉ እያለቀሰ ስለኖረና ፊቱም በሀዘን ስለተቋጠረ "#ቁጹረ_ገጽ" ተብሏል፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም እና #ከገድላት_አንደበት)
#መስከረም_30

መስከረም ሠላሳ በዚህች ቀን #በአባ_አትናቴዎስ ላይ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ነው፣ #የቅዱስ_አባ_ሣሉሲ እና #የደብረ_ክሳሄው_አቡነ_አብሳዲ ዕረፍታቸው ነው። ዳግመኛም #አባ_ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አትናቴዎስ

መስከረም ሠላሳ በዚህች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በከበረና በተመሰገነ በአባ አትናቴዎስ ላይ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ሆነ።

ይህም ሁለተኛም ቁስጠንጢኖስ ወደ ረከሰች የአርዮስ ሃይማኖት በገባ ጊዜ የእስክንድርያውን ሊቀ ጳጳሳት አባ አትናቴዎስን አሳድዶ ከሀዲውን ጊዮርጊስን በእስክንድርያ መንበር ላይ ሾመው። የአርዮስንም ሃይማኖት እንዲአጠናክር የረከሰ የአርዮስን ሃይማኖት የማይቀበሉትን ግን ሁሉንም ይገድላቸው ዘንድ አዘዘው ብዙዎች ፈረሰኞች ጦረኞችን ለእርሱ ሰጥቶታልና። ስለዚህም ከእስክንድርያ ሰዎች ቁጥር የሌላቸውን ብዙዎች ምእመናንን ገደላቸው።

ቅዱስ አትናቴዎስም በተሰደደበት ስድስት ዓመት ኖረ። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔርን ልጅ የካደው ታናሹ ቁስጠንጢኖስ ወደአለበት ወደ ቁስጥንጥንያ ተነሥቶ ሔደ ንጉሡንም እንዲህ አለው ወደ ተሾምሁበት መንበሬ ትመልሰኝ እንደሆነ መልሰኝ ይህ ካልሆነ የምስክርነት አክሊልን እንድቀበል ግደለኝ።

ንጉሡም ይህን ነገር ከእርሱ በሰማ ጊዜ በታናሸ መርከብ አድርገው ያለ ቀዛፊና ያለ መብልና መጠጥ በባሕር ውስጥ እንዲተዉት አዘዘ ንጉሡም በስጥመት ወይም በረኃብና በጥም እንደሚሞትለት አስቦ ነበርና የቀናች ሃይማኖትንም ስለመለወጡ እንዳይዘልፈው ከእርሱ ያርፍ ዘንድ እንዲሁም ንጉሡ እንዳዘዘ በቅዱስ አትናቴዎስ ላይ አደረጉበት። ንጉሡም እንጀራና ውኃ ባይሰጠው ከሰማይ ለእርሱ የወረደ እንጀራ ስለርሱ የፈለቀ ውኃም አለው። የመርከብም ቀዛፊ ቢከለክለው እነሆ ዓለሙን ሁሉ በቃሉ የሚጠብቅ የሚመራ ከእርሱ ጋር ነበር። ስለዚህም ቅዱስ አትናቴዎስ በውስጧ የተቀመጠባት ያቺ መርከብ መላእክት እየቀዘፏት በጸጥታና በሰላም ተጓዘች በሦስተኛውም ቀን ከእስክንድርያ ወደብ ደረሰ።

የምእመናን ወገኖችም ደግ ጠባቂያቸው እንደ ደረሰ በሰሙ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው መብራቶችንም በመያዝ በምስጋና እየዘመሩ ሊቀበሉት ወጡ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገቡት። ከሀዲው ጊዮርጊስም ከወገኖቹ ጋር ወጥቶ ሔደ።

በዚያችም ቀን ቅዱስ አትናቴዎስ ለእግዚአብሔር ታላቅ በዓልን አከበረ የእስክንድርያም ሰዎች እስከ ዛሬ ድረስ ያከብሩ አታል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ሣሉሲ

በዚችም ቀን ቅዱስ አባ ሣሉሲ አረፈ። ይህም ቅዱስ መስጋድል ሲሆን ራሱን እንደ እብድ አደረገ እርሱም በሥውር ይጸልያል ይጾማልም በሰው ፊት ግን ምንም ምን አይጸልይም አይጾምም በየጥዋቱ ሁሉ የሚመገበውን የሣር ፍሬ አድርጎ በሰው ፊት ያላምጣል በምሽት ጊዜ ግን ከውንድሞች መነኰሳት ጋር ምንም ምን አይቀምስም።

አበ ምኔቱ አባ ይስሕቅና መነኰሳቱ ሁሉ ከሥራው የተነሣ ያደንቃሉ ይህንንም ልማዱን ሊአስጥሉት ይሻሉ ነገር ግን ልቡን እንዳያሳዝኑት ያስባሉ።

በአንዲትም ዕለት የገዳማቸው በዓል ሆነ አበ ምኔቱ አባ ይስሐቅም መነኰሳቱን እንዲህ አላቸው ቅዱስ ቁርባንን ከመቀበሉ በፊት እህልን እንዳይቀምስ አባ ሣሉሲን ጠብቁት። እነርሱም ጠበቁት የሚበላበትም ጊዜ ሲደርስ ከእነርሱ ሊለይ ወደደ መነኰሳቱም ከለከሉት እርሱም በረኃብ እንዳልሞትና በእናንተ ላይ በደል እንዳይሆንባችሁ ልቀቁኝ ብሎ ጮኸባቸው።

ባልተውትም ጊዜ በዚያን ወቅት ቆቡን ከራሱ ላይ አውልቆ እመቤቴ ማርያም ሆይ ከእሊህ መነኰሳት እጅ አድኝኝ ብሎ የቤተ ክርስቲያኑን ግድግዳ በቆቡ መታበት ሕንፃውም ተሠንጥቆለት በዚያ ወጥቶ ሔደ የግድግዳውም ግምብ ተመልሶ እንደቀድሞው ሆነ።

የተሰበሰቡትም ይህን ድንቅ ተአምር በአዩ ጊዜ ሦስት መቶ ጊዜ ኪርያላይሶን እያሉ ጮኹ በዚያንም ጊዜ ያቺን ቆብ ወድቃ አገኙአት በታላቅም ክብር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩዋት ድውያንንም በመፈወስ ከእርሷ ብዙ ተአምራት ተደረገ።

ሊቀ ጳጳሳቱም በሰማ ጊዜ ከእርሷ ሊባረክ ወዶ ያቺን ቆብ ሊወስዳት ፈለገ በየጊዜውም ሲወስዳት ወደቦታዋ ወደዚያ ገዳም ትመለሳለች እንዲህም ሦስት ጊዜ ሆነ ከዚህም በኋላ መውሰዱን ተወ።

ከብዙ ወራትም በኋላ እንደ ዛሬው ሁሉ በዚች ቀን አባ ሣሉሲ በዚሁ ገዳም በአረፈበት ቦታ ተገልጾ ተገኘ በክብርም ገንዘው ቀበሩት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_አብሳዲ_ዘደብረ_ማርያም (ክሳሄ)

አቡነ አብሳዲ አጽፋቸውን እንደጀልባ ተጠቅመው የኢያሪኮን ባሕር የተሻገሩት የታላቁ ጻድቅ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር ደቀ መዝሙር ናቸው፡፡ የደብረ ክሳሄው አቡነ አብሳዲ ገድላቸውን የፈጸሙት ኤርትራ ውስጥ ነው፡፡

አቡነ ኤዎስጣቴዎስን ጌታችን በቃሉ ጠርቶ ‹‹በላይህ ላይ ያለውን ቅዱስ መንፈስ በወዳጅህ በልጅህ አብሳዲ ላይ አሳድር፣ ሙሴ የራሱን መንፈስ በነዌ ልጅ በኢያሱ ላይ እንዳሳደረ፣ ኤልያስም በረድኡ በኤልሳዕ ላይ እንዳሳደረ›› አላቸው፡፡ ምክንያቱም ልጆቻቸውን ትተው ወደ ኢየሩሳሌም ከዚያም ወደ አርማንያ እንዲሔዱ ነግሯቸዋልና ነው፡፡ አባታችንም ልጃቸውን አቡነ አብሳዲን ሦስት ጊዜ ‹‹አብሳዲ አብሳዲ አብሳዲ›› ብለው ጠሩት፡፡ እርሱም አባቱን ‹‹አቤት ጌታዬ እነሆ ጠርተኸኛልና›› አለው፡፡ አባታችን ኤዎስጣቴዎስም ‹‹እነሆ በረከት ከሰማይ ለአንተ ተሰጠች፣ ይህችንም በረከት ብርንና ወርቅን የማይወዱ ራሳቸውንም ወደ ጠባብ በር ያስገቡ እንደ አንተ ካለ ጻድቃንና ከተመረጡት በቀር መቀበል የሚችል የለም፤ እነርሱም ሥጋቸውን አሳልፈው ለጻዕር ለጭንቅ የሰጡ ናቸው፤ ከተወለዱም ጀምሮ ጣፋጭ የሆኑ የምድር ምግቦችን ያልወደዱ ናቸው፣ ራሳቸውንም እንደምታልፍ ነፋስ ያደረጉ ናቸው፡፡›› አባታችን ኤዎስጣቴዎስም ይህንን ተናግረው በአብሳዲ ራስ ላይ እጃቸውን ጫኑ፡፡ ሙሴ በኢያሱ እንደጫነ፣ ያዕቆብም በይሁዳና በሌዊ ላይ እጁን ጭኖ ለመንግሥትና ለክህነት እንደባረካቸው ዮሴፍም ልጆቹን ኤፍሬምና ምናሴን ይባርካቸው ዘንድ ወደ አባቱ እስራኤል አምጥቷቸው እርሱም የተባረከና ቅዱስ ሕዝብ ያድርጋችሁ ብሎ እንደባረካቸው እንደዚሁም ሁሉ አባታችን ኤዎስጣቴዎስ ልጃቸውን አብሳዲን እንዲህ እያሉ ባረኩት፡- ‹‹የቀደሙ አባቶች በረከት፣ የነቢያትና የሐዋርያት በረከት፣ ድል የሚነሡ የሰማዕታት በረከትና በተጋድሎ የጸኑ የጻድቃን በረከት፣ የቅዱሳን መላእክት በረከት፣ ማኅበረ በኩር የተባሉ የሁሉም ቅዱሳን በረከት፣ አምላክን የወለደች የቅድስት ድንግል ማርያም በረከት፣ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ በረከት በአንተ ላይና በልጆችህ ላይ ይደር፤ መታሰቢያዬንና መታሰቢያህንም በሚያደርጉ ላይ ይደር ለዘለዓለሙ አሜን›› ብለው መባረክን ከባረኩት በኋላ አብሳዲን ግንባሩን ቀብተው አተሙት፡፡

አቡነ አብሳዲ ገዳማትንና ምንኵስናን ለማስፋፋት ብዙ የደከሙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ቀንና ሌሊት ሳያርፉ ምእመናን በማስተማር አባታቸው ኤዎስጣቴዎስ እንዳስተማሯቸው
ገዳማትንና ምንኵስናን በኤርትራና በኢትዮጵያ በማስፋፋት ለገዳማዊ ምናኔ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሐዋርያ ናችው፡፡ በመንፈስ የወለዷቸው በርካታ መነኵሳት ልጆቻቸው አማካኝነት በኢትዮጵያና በኤርትራ የተገደሙት ገዳማት ከ120 በላይ ናቸው፡፡
በልጆቻቸው አማካኝነት በኤርትራ ከተገደሙት ገዳማት ውስጥ፦ ደብረ ኮል አቡነ ብሩክ (መራጉዝ)፣ የአቡነ ዮናስ ገዳማት (ደብረ ድኹኻን ቆሓይን፣ ደብረ ጽጌ ትምዛእ፣ ደብረ ሣህል ዛይዶኮሎም)፣ ደብረ አቡነ ሙሴ (ማይ ጎርዞ)፣ ደብረ ሲና አቡነ ድምያኖስ፣ ምድሪ ወዲ ሰበራ፣ ደብረ ሐዋርያት አቡነ ሴት (ዓዲ ቂታ)፣ ደብረ ማርያም (ዓይላ) እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ እነኚህን እንደ ምሳሌ ጠቀስን እንጂ በኢትዮጵያም የአቡነ አብሳዲ ልጆች የመሠረቷቸው በርካታ ገዳማት አሉ፡፡

አባታችን የረጅም ዘመን ተጋድሏቸውን በፈጸሙ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኹለተኛ ጊዜ ተገልጦላቸው ‹‹በሰሜን ያለች ይኽችን ገዳም ባርኬልሃለውና ከልጆችህ ጋር በእርሷ
ኑር›› ካላቸው በኋላ ቃልኪዳን ገብቶላቸው ተሰወረ፡፡ ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ይኽችም ለአባታችን የተሰጠቻቸው ገዳም ደበረማርያም (ደብረ ክሳሄ) ናት፡፡

ከዚኸም በኋለ ቅዱስ አባታችን አብሳዲ ደከመኝ ልረፍ ሳይሉ መላ ዘመናቸውን ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን ፈጽመው ከእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ተቀብለው በ101 ዓመታቸው መስከረም 30 ቀን 1383 ዓ.ም ዐርፈው ቆሓይን በምትገኘው ገዳማቸው ደብረ ክሳሄ ደብረ ማርያም ገዳም ተቀበሩ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ገሪማ_ዘመደራ (#አባ_ይስሐቅ)

አቡነ ገሪማ የተወለዱት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሮም ውስጥ ነው። ወላጆቻቸው መስፍንያኖስ እና ሰፍንግያ እግዚአብሔርን የሚወዱ የሮም ከተማ ንጉሥና ንግሥት ነበሩ። ልጅ በማጣታቸው እመቤታችንን ለመኑ።

እመ ብርሃንም ደግ ፍሬ ሰጠቻቸው። ስሙን ይስሐቅ ብለው አሳደጉት። ገና በልጅነቱ አባቱ ድንገት በመሞቱ ይስሐቅ በዙፋኑ ተተክቶ ነገሠ። ለሰባት ዓመታት ሕዝቡን በፍትሕ እያስተዳደረ መጻሕፍትንም እያጠና ኑሯል።

አንድ ቀን ግን ከግብጽ በርሃ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው። ላኪው አባ ጰንጠሌዎን ሲሆኑ መልዕክቱ "ምድራዊ ንግሥና ምን ያደርግልሃል? ይልቁኑስ በሰማይ ለዘላለም እንድትነግሥ ወደ በርሃ ና!" የሚል ነበር።

ንጉሥ ይስሐቅ አላመነታም ሌሊት ተነስቶ ወደ ፈጣሪው ጸልዮ በለበሳት ልብስ ብቻ ዙፋኑን ጥሎ መነነ። ድንገት ግን ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ በቀኝ ክንፉ ነጥቆ ግብጽ አባ ጰንጠሌዎን በዓት ላይ አኖረው።

እርሳቸውም ተቀብለው ፍኖተ አበውን አስተምረው አመነኮሱትና ዘጠኝ ሁነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ብዙ ሲሰሩ አንዱና ታላቁ አባ ይስሐቅ (ገሪማ) ናቸው። ሰውነታቸውን በገድል ቀጥቅጠውት ቆዳና አጥንታቸው ተጣብቆ ነበር።

አንድ ቀን አባ ይስሐቅ በልቶ ቀደሰ ብለው ነግረዋቸው አባ ጰንጠሌዎን አዘኑ። ልምከር ብለው "ልጄ ይስሐቅ የሰማውብህ ነገር አለና ሰዎችን አርቅልኝ።" አሉ። አባ ይስሐቅ ግን "ሰዎች ብቻ አይደሉም፤ ዛፉም እንጨቱም ገለል ይበል።" ቢሉ የቤተ ክርስቲያኑ አጸድ አንድ ምዕራፍ (ሁለት መቶ ሜትር) ተጠራርጎ ሸሸ።

ይህንን የተመለከቱት አባ ጰንጠሌዎን "ወልድየ ይስሐቅ ገረምከኒ (ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ)።" አሏቸው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮም "አቡነ ገሪማ" ተብለው ቀሩ።

አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሲሔዱ እነዚያ የሸሹ ዛፍና ድንጋዮች "ገሪማ ለእኛም ግሩም ነህ።" እያሉ በዝማሬ ተከትለዋቸዋል። ይህም የተደረገው በዚህች ዕለት መስከረም ፴ ቀን ነው።

ጻድቁ ወንጌልንና ገዳማትን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል፦
፩. ስንዴ ጧት ዘርተውት በዘጠኝ ሰዓት ያፈራ ነበር። "በጽባሕ ይዘርዕ ወበሠርክ የአርር" እንዲል።
፪. ጧት የተከሉት ወይን በዘጠኝ ሰዓት ያፈራ ነበር።
፫. አንድ ቀን ምራቃቸው ቢወድቅ ጠበል ሆኖ ዛሬም አለ።
፬. ብዕራቸው ወድቃ አብባ አፍርታለች።
፭. አንድ ቀን ድርሳን እየደረሱ ሊመሽ በመሆኑ ፀሐይን አቁመዋታል።

ከእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ ጌታችን ተገልጦ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ሰጣቸው። "ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገ እስከ አሥራ ሁለት ትውልድ እምርልሃለሁ። አንተ ግን ሞትን አትቀምስም።" ብሏቸው ተሰወረ። ያን ጊዜ መላእክቱ በሠረገላ ጭነው እየዘመሩ ብሔረ ሕያዋን አድርሰዋቸዋል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም)
ማኅሌተ ጽጌ መስከረም 30
፩ ነግሥ ( ለኵልያቲክሙ)
ሰላም፡ ለኵልያቲክሙ፡ እለ፡ ዕሩያን፡ በአካል፤
ዓለመክሙ፡ ሥላሴ፡ አመ፡ ሐወፀ፣ ለሣህል፤
እምኔክሙ፡ አሐዱ፡ እግዚአብሔር፡ ቃል፤
ተፈጸመ፡ ተስፋ፡ አበው፡ በማርያም፡ ድንግል፤
ወበቀራንዮ፡ ተተክለ፡ መድኃኒት፡ መስቀል ፡፡

ዚቅ
ወኃይዝተ፡ ወንጌል፡ የዓውዳ፡ ለቤተክርስቲያን፤
እም፡ አርባዕቱ፡ አፍላጋት፤ እንተ፡ ትሰቀይ፡ ትእምርተ፡ ለለጽባሑ፤
እማቴዎስ፡ ልደቶ፡ ወእማርቆስ፡ መንክራቶ፤
እም፡ ሉቃስ፡ ዜናዊ፡ ተሰምዮ፡ ወእም፡ ዮሐንስ፡ በግዓ፤
ወዘንተ፡ ሰሚዓ፡ ትገብር፡ በዓለ፡ በፍግዓ።

፪ ጽጌ አስተርአየ
ጽጌ፡ አስተርአየ ፡ ሠሪጾ፡ እምዐጽሙ፤
ለዘአምኃኪ፡ ጽጌ፡ ለገብርኤል፡ ምስለ፡ ሰላሙ፤
ወበእንተዝ ፡ ማርያም ፡ ሶበ ፡ ሐወዘኒ ፡ ጣዕሙ፤
ለተአምርኪ ፡ አኀሊ፡ እሙ፤
ማኅሌተ፡ ጽጌ፡ ዘይሰመይ፡ ስሙ፡፡
ወረብ
መዓዛ፡ ጣዕሙ፡ ለተአምርኪ፡ ሶበ፡ ሶበ፡ ሐወዘኒ፤
ወበእንተዝ፡ ማርያም፡ አሐሊ፡ ለተአምርኪ፡፡

ዚቅ
ሃሌ፡ ሉያ፡ ሃሌ፡ ሃሌ፡ ሉያ፤
ናሁ፡ አስተርአየ፡ ጽጌ፤
መርዓቱኒ፡ ትቤ፡ ወልድ፡ እኁየ ፡ ይምዕዝ ፡ ከርቤ፤
ናሁ ፡ አስተርአየ ፡ ጽጌ፤
ዕንባቆም ፡ ነቢይ ፡ ግብረ፡ ምግባሩ፡ ለወልድ፡ አንከርኩ፡ ይቤ፤
ናሁ ፡ አስተርአየ፡ ጽጌ፤
ንጉሠ ፡ ሰላም፡ ክርስቶስ፤
ዓቢይ፡ ልዕልናከ፡ ወመንክር፡ ስብሐቲከ፡ ለዕረፍት፡ ሰንበተ ፡ ሠራዕከ፡፡

፫ እንዘ ተሐቅፊዮ
እንዘ ፡ ተሐቅፊዮ ፡ ለሕጻንኪ ፡ ጽጌ፡ ፀዓዳ ፡ ወቀይሕ፤
አመ ፡ ቤተ ፡ መቅደስ ፡ ቦእኪ ፡ በዕለተ ፡ ተአምር ፡ ወንጽሕ፤
ንዒ ፡ ርግብየ ፡ ትናዝዝኒ ፡ እምላህ፤
ወንዒ ፡ ሠናይትየ ፡ ምስለ ፡ ገብርኤል ፡ ፍሡሕ፤
ወሚካኤል ፡ ከማኪ ፡ ርኅሩኅ ፡፡
ወረብ
እንዘ፡ ተሐቅፊዮ፡ ለሕጻንኪ፡ ጽጌ፡ ፀዓዳ፡ ወቀይሕ፤
አመ፡ ቤተ፡ መቅደስ፡ ቦእኪ፡ በዕለተ፡ ተአምር፡ ወንጽሕ፤

ዚቅ
ንዒ፡ ርግብየ፡ ወንዒ፡ ሠናይትየ፤ እንተ፡ ሐዋርያት፡ ይሴብሑኪ፤
መላእክት፡ ይትለአኩኪ፤ ፃዒ፡ እምሊባኖስ፡ ሥነ፡ ሕይወት፡፡

፬ ሰዊተ ሥርናዩ
ሰዊተ፡ ሥርናዩ፡ ለታዴዎስ፡ ወለበርተሎሜዎስ፡ ወይኑ፤
እንተ፡ ጸገይኪ፡ አስካለ፡ በዕለተ፡ ተከለኪ፡ ዕደ፡ የማኑ፤
ማርያም፡ ለጴጥሮስ፡ ጽላሎቱ፡ ወለጳውሎስ፡ ሰበኑ፤
ብኪ፡ ምውታን፡ ሕያዋነ፡ ኮኑ፤
ወሐዋርያት፡ መላእክተ፡ በሰማይ፡ ኮነኑ፡፡

ወረብ
ማርያም፡ ለጴጥሮስ፡ ጽላሎቱ፡ ጽላሎቱ፡ ወለጳውሎስ፡ ሰበኑ፤
ወሐዋርያት፡ መላእክተ፡ መላእክተ፡ በሰማይ፡ ኮነኑ፡፡

ዚቅ
ኦ፡ መድኃኒት፡ ለነገሥት፤ ማኅበረ፡ ቅዱሳን፡ የዓውዱኪ፤
ነቢያት፡ የአኵቱኪ፡ ወሐዋርያት፡ ይዌድሱኪ፤
እስመ፡ ኪያኪ፡ ኃርየ፡ ለታዕካሁ፡ ከመ፡ ትኩኒዮ፡ ማኅደረ ፤
መላእክት፡ ይኬልሉኪ፡ ጻድቃን፡ ይባርኩኪ፡ አበው፡ ይገንዩ፡ ለኪ፤
እስመ፡ ኪያኪ፡ ኃርየ፡ ለታዕካሁ፡ ከመ፡ ትኩኒዮ፡ ማኅደረ፡፡

፭ ክበበ ጌራ ወርቅ
ክበበ፡ ጌራ ወርቅ፡ ጽሩይ ፡ እምዕንቈ ባሕርይ ፡ ዘየኃቱ፣
ዘተጽሕፈ ፡ ብኪ ፡ ትእምርተ ፡ ስሙ ፡ ወተዝካረ ፡ ሞቱ፣
አክሊለ ጽጌ ፡ ማርያም ፡ ለጊዮርጊስ ፡ ቀጸላ መንግሥቱ፣
አንቲ ፡ ኵሎ ፡ ታሰግዲ ፡ ሎቱ፣
ወለኪኒ ፡ ይሰግድ ፡ ውእቱ፡፡

ወረብ
ክበበ፡ ጌራ፡ ወርቅ፡ ጽሩይ፡ ዘየኃቱ፡ እምዕንቈ፡ ባሕርይ፤
ማርያም፡ አክሊለ፡ ጽጌ፡ ለጊዮርጊስ፡ ቀጸላ፡ መንግሥቱ፤

ዚቅ
ውድስት፡ አንቲ፡ በአፈ፡ ነቢያት፤ ወስብሕት፡ በሐዋርያት፤
አክሊለ፡ በረከቱ፡ ለጊዮርጊስ፤
ወትምክህተ፡ ቤቱ፡ ለእሥራኤል፡፡

፮ በስመ እግዚአብሔር (ሰቆቃወ ድንግል)
በስመ፡ እግዚአብሔር፡ ሥሉስ፡ ሕጸተ፡ ግጻዌ፡ ዘአልቦ፤
ሰቆቃወ፡ ድንግል፡ እጽሕፍ፡ በቀለመ፡ አንብዕ፡ ወአንጠብጥቦ፤
ወይሌ፡ ወላህ፡ ለይበል፡ ዘአንበቦ፤
ከማሃ፡ ኀዘን፡ ወተሰዶ፡ ሶበ፡ በኵለሄ፡ ረከቦ፤
ርእዮ፡ ለይብኪ፡ ዓይነ፡ ልብ፡ ዘቦ።

ወረብ
ከማሃ፡ ኀዘን(፪)፡ ወተሰዶ፡ ኀዘን፤
ርእዮ፡ ለይብኪ፡ ዓይነ፡ ልብ፡ ዘቦ፡ ዓይነ፡ ልብ።

ዚቅ
እወ፡ አማን፡ እምውሉደ፡ ሰብእ፡ አልቦ፤
ምንዳቤ፡ ወግፍዕ፡ ዘከማኪ፡ በውስተ፡ ኵሉ፡ ዘረከቦ።
++++++++++++++

መዝሙር
ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሃሌ ሉያ
ትዌድሶ፡ መርዓት፤ እንዘ፡ ትብል፡ ነዓ፡ ወልድ፡ እኁየ፡ ንፃእ፡ ኃቅለ፤
ትዌድሶ፡ መርዓት፤ ንርአይ፡ ለእመ፡ ጸገየ፡ ወይን፡ ወፈረየ፡ ሮማን፤
ትዌድሶ፡ መርዓት፤ አሠርገወ፡ ሰማየ፡ በከዋክብት፡ ወምድርኒ፡ በስነ፡ ጽጌያት፤
ትዌድሶ፡ መርዓት፤ እስመ፡ ውእቱ፡ ወልድ፡ ዋሕድ፡ እግዚአ፡ ለሰንበት፤
ትዌድሶ፡ መርዓት፡ ወትብሎ፤ ወልድ፡ እኁየ፡ ቃልከ፡ አዳም፡፡

አመላለስ
ትዌድሶ፡ መርዓት፡ ወትብሎ፤
ወልድ፡ እኁየ፡ ቃልከ፡ አዳም።

ሰላም
ናሁ፡ አስተርአየ፡ ጽጌ፤ መርዓቱኒ፡ ትቤ፡ ወልድ፡ እኁየ ፡ ይምዕዝ ፡ ከርቤ፤
ናሁ፡ አስተርአየ፡ ጽጌ፤ ዕንባቆም፡ ነቢይ፡ ግብረ፡ ምግባሩ፡ ለወልድ፡ አንከርኩ፡ ይቤ፤
ናሁ፡ አስተርአየ፡ ጽጌ፤ ንጉሠ፡ ሰላም፡ ክርስቶስ፤
ዓቢይ፡ ልዕልናከ፡ ወመንክር፡ ስብሐቲከ፡ ለዕረፍት፡ ሰንበተ ፡ ሠራዕከ፡፡
+++
#ጥቅምት_1

ጥቅምት አንድ በዚህችም ቀን #ቅድስት_አንስጣስያ በሰማዕትነት አረፈች፤ ዳግመኛም የማርታና የአልዓዛር እህት #የቅድስት_ማርያም_እንተ_ዕፍረት የእረፍቷ መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_አንስጣስያ_ሰማዕት

በዚህችም ቀን በጥቅምት አንድ ቅድስት አንስጣስያ በሰማዕትነት አረፈች። ይችም ቅድስት መስተጋድልት ከሮሜ አገር ናት ወላጆቿም ክርስቲያኖች ናቸው ጠቃሚ የሆነ ትምህርትን በማስተማር ክብር ባለው በመልካም ሥርዓት አሳደጓት።

በአደገችም ጊዜ ወላጆቿ ሊያጋቧት ፈለጉ እርሷ ግን ይህን ሥራ አልፈለገችም የምንኲስናን ልብስ መልበስ ፈለገች እንጂ፤ ከታናሽነቷም መንፈሳዊ ገድልን መረጠች።

ስለዚህም በሥውር ሒዳ በሮሜ ካሉ ገዳማት ወደ አንዱ ገዳም ገባች ታናሽ ስትሆንም የምንኲስና ልብስን በመልበስ በጾም በጸሎት በረኃብ በጽምዕ በመጠመድ የዚህን ዓለም ሐሳብ ሁሉ ከልቡናዋ ቆርጣ በመተው በመጋደል ሥጋዋን አደከመች።

በቀኑ ርዝመትም ሁሉ የምትጾም ሆነች በየሁለት ቀኖችም ታከፍላለች በጌታችን ጾም ግን ያለ ሰንበታት ቀን የምትመገበው የለም። በሰንበታትም የምትመገበው ከቀትር ጸሎት በኋላ ነው። በነዚያም በምንኲስናዋ ወራት በእሳት ያበሰሉትን ወጥ አልቀመሰችም።

በገዳሟ አቅራቢያም ሌላ የደናግል ገደም አለ የዚያ ደብር በዓልም በደረሰ ጊዜ እመ ምኔቷ በዓሉን ለማክበር ይቺን ቅድስት አንስጣስያን ከእኅቶቿ ደናግል ጋር አስክትላት በአንድነት ተጓዙ። ሲጓዙም የንጉሥ ዳኬዎስን ወታደሮች አየቻቸው። ከእርሳቸውም ጋር የታሠሩ ክርስቲያኖች አሉ ወታደሮቹም አሥረው በቁጣ ይጎትቷቸው ነበር። ልቧም በሃይማኖቷ ፍቅር ነደደና ያን ጊዜ እንዲህ ብላ ዘለፈቻቸው የእውነት ፈጣሪን የካዳችሁ ልባችሁ የደነዘዘ እግዚአብሔር በመልኩና በአምሳሉ በፈጠራቸውና ስለእነርሱም ነፍሱን ለሞት አሳልፎ በሰጠላቸው ላይ ለምን እንዲህ ትሠራላችሁ።

ይህንንም በአለቻቸው ጊዜ ወታደሮች ተቆጡ ይዘውም ወደ መኰንኑ አቀረቧት እርሱም እንዲህ ብሎ ጠየቃት በእውነት አንቺ የተሰቀለውን የምታመልኪው ክርስቲያን ነሽን? እርሷም ስለእኛ የተሰቀለውን ክብር ይግባውና እርሱን አመልከዋለሁ ብላ መለሰችለት።

በዚያን ጊዜም ጽኑ ሥቃይን አሠቃያት በሥጋዋም እሳትን ጨመረ ከዚህም በኋላ ዘቅዝቆ ሰቀላት ከበታቿም አጤሱባት ከሃይማኖቷም ባልተናወጸች ጊዜ ራሷን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። በዚህ በታላቅ ሥቃይም ውስጥ ሳለች ራሷን በሰይፍ ቆረጧት። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ማርያም_እንተ_ዕፍረት

ዳግመኛም በዚህች ዕለት የማርታና የአልዓዛር እህት ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት የእረፍቷ መታሰቢያ ነው።

በዘመነ ሐዋርያት በተመሳሳይ 'እንተ ዕፍረት' (ባለ ሽቱ) ተብለው የሚጠሩ 2 እናቶች ነበሩ:: ሁለቱም ስማቸው ማርያም ስለ ነበር ለመለየት እንዲያመች አንደኛዋን 'ማርያም ኃጥዕት (ከኃጢአት የተመለሰች) ሁለተኛዋን ደግሞ 'ማርያም እኅተ አልዓዛር በቢታንያ የነበረችው ብለው አበው ይጠሯቸዋል።

በሉቃስ ወንጌል ላይ የምትገኘው ከኃጢአት ሕይወት የተመለሰችው ስትሆን በዮሐ. 12:1 ላይ ያለችው የአልዓዛር እህት (ድንግሊቱ) ናት። ዛሬም የምናስባት ይህቺውን እናታችን ነው።

ቅድስት ማርያም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በሚያስተመርበት ዘመን በቢታንያ አካባቢ ትኖር የነበረች ድንግል ወጣት ናት። ወላጆች ባልነበረበት ቤት ውስጥ ታላቆቿ አልዓዛርና ማርታ አሳድገዋታል።

በቤተሰብ ደረጃ እንግዳን ይቀበሉ ነበርና ጌታችን ወደዳቸው። አልዓዛርን ከ72ቱ አርድእት: ማርያምና ማርታን ደግሞ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል። ወንድማቸው አልዓዛር በታመመ ጊዜ ወደ ጌታ ልከው ነበር።

ያለ ጊዜው የማይሠራ ጌታ ባይመጣ አልዓዛር ሞተ። በ4ኛው ቀን አምላክ ሲመጣ ቅድስት ማርያም በጌታ ፊት ሰግዳ "እግዚእየ ሶበሰ ኀሎከ ዝየ እምኢሞተ እኁየ" "አንተ በዚህ በኖርክስ ወንድሜ ባልሞተ ነበር" ብላ አለቀሰች። (ዮሐ.11)

ጌታም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አምላክነቱ አራርቶት አለቀሰ። ወዲያውም በስልጣነ ቃሉ አዞ አልዓዛርን አስነሳው። ከፋሲካ (ጌታ ከመሰቀሉ 6 ቀናት) በፊትም ቅዱሳኑ ለጌታ ግብር አገቡ። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ታደመላቸው። (ዮሐ.12፥1)

በዚያም አልዓዛር ከጌታ ጐን ሲቀመጥ ቅድስት ማርያም ከጌታ ሥር ተንበርክካ ናርዶስ የሚሉትን የ300 ዲናር ሽቱ በጌታ ላይ አፈሰሰች። መዓዛ መለኮቱና ሽቱው ሲገናኝ "መልዐ መዓዛሁ" እንዲል የሚመስጥ ሽታ ቤቱን ሞላው።

በወቅቱ ይሁዳ ቢቃወምም ጌታ ምላሹን ሰጥቶታል። ቅድስት ማርያምንም "ማርያምሰ ኃርየት መክፈልተ ሠናየ ዘኢየኃይድዋ" ብሎ አመስግኗታል። ያስመሰገናት ቁጭ ብላ በተመስጦ መማሯ ብቻ እንዳልሆነ አባ ሕርያቆስ መስከሯል።

ሲመክረንም "አርምሞንና ትዕግስትን እንደ ማርያም ገንዘብ እናድርግ" ብሎናል። (ቅዳሴ ማርያም) ቅድስት ማርያም በጌታችን ክርስቶስ በኅማሙ ጊዜ ሲቀብሩት ነበረች። ትንሳኤውንም ዐይታለች።

ከጌታ እርገት በኋላም መንፈስ ቅዱስን ተከትላ ለወንጌል አገልግሎት ተግታለች። ቅድስት እናታችን ማርያም እንተ ዕፍረት ዛሬ እንዳረፈች እናዘክራለን።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምትና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
#ጥቅምት_2

ጥቅምት ሁለት በዚች ቀን የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ሳዊሮስ ወደ ግብጽ አገር ተሰዶ የመጣበት፣ #የቅዱስ_አባ_ሕርያቆስ የልደቱና ዕረፍቱ መታሰቢያ ናት፣ የፈጠጋሩ #ቅዱስ_አቡነ_ማትያስ ዕረፍታቸው ነው፡።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሳዊሮስ

ጥቅምት ሁለት በዚች ቀን የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ሳዊሮስ ወደ ግብጽ አገር ተሰዶ መጣ ።

ይህም የሆነው በመናፍቁ ንጉሥ በዮስጥያኖስ ዘመን ነው እርሱም ንጉሡ በኬልቄዶን ሃይማኖት የሚያምን ነው ሚስቱ ንግሥት ግን ሃይማኖቷ የቀና ነው ቅዱስ አባ ሳዊሮስን ትወደዋለች ታከብረዋለችም ንጉሡም በሥውር ሊገድለው ይሻዋል።

ቅዱስ አባ ሳዊሮስንም በሥውር ይገድለው ዘንድ ንጉሥ እንደሚሻው ንግሥት በአወቀች ጊዜ ከአንጾኪያ አገር እንዲወጣና ነፍሱን እንዲአድን ወደ አባ ሳዊሮስ ላከች። እርሱ ግን መሸሽ አልፈለገም ለንግሥትም እንዲህ አላት እኔ ክብር ይግባውና ስለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሞት የተዘጋጀሁ ነኝ ንግሥቲቱም ብዙዎች ምእመናንም አብዝተው በለመኑት ጊዜ ከሀገር ወጣ ከእርሱም ጋር ከምእመናን አብረውት ወደ ግብጽ አገር የተሰደዱ አሉ።

ንጉሡም በፈለገው ጊዜ አላገኘውም ፈልገውም ወደርሱ ያመጡት ዘንድ ወታደሮቹን ላከ ክብር ይግባውና ጌታችን ስለ ሠወረው እነርሱም በቅርባቸው ሁኖ በመካከላቸው ሲጓዝ አላገኙትም። በአንድ ቦታም አብሮአቸው ሲያድር እርሱ እያያቸው እነዚያ የንጉሥ ጭፍሮች አያዩትም እርሱንም አጥተው ተመለሱ።

ወደ ግብጽ አገርም በደረሰ ጊዜ ከቦታ ወደቦታ ከደብር ወደ ደብር በሥውር የሚዘዋወር ሆነ እግዚአብሔርም በእጆቹ ላይ ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራትን አደረገ።

በአንዲት ቀንም ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረሰ በመጻተኛ መነኲሴ አምሳልም ወደ አባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያንም ገባ በዚያንም ጊዜ ቄሱ ዕጣንና ቁርባንን ሊአሳርግ ጀመረ እንደ ሥርዓቱም እየዞረ ዐጠነ። የሐዋርያትንም መጻሕፍት የጻፉአቸውን መልእክቶች የከበረ ወንጌልንም ከአነበቡ በኋላ እጆቹን ታጥቦ ማኅፈዱን በገለጠው ጊዜ በጻሕሉ ውስጥ የቊርባኑን ኅብስት አላገኘውም ደንግጦም አለቀሰ።

ከዚህም በኋላ ወደ ሕዝቡ ተመልሶ እንዲህ አላቸው ወንድሞቼ እነሆ የቊርባኑ ኅብስት ተሠውሮ በጻሕሉ ውስጥ አላገኘሁትምና ይህ የሆነ በእኔ ኃጢአት ወይም በእናንተ ኃጢአት እንደሆነ አላወቅሁም።

በዚያንም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት እንዲህ አለው ይህ የሆነ በኃጢአትህ ወይም በሕዝብ ኃጢአት አይደለም ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስ እያለ መሥዋዕትን ለማሳረግ በመድፈርህ ነው እንጂ ቄሱም መልአኩን ጌታዬ ሊቀ ጳጳሳት መኖሩን አላወቅሁም አለው አባ ሳዊሮስም ወደ ቆመበት ቦታ አመለከተው።

ቄሱም ወደ አባ ሳዊሮስ ሒዶ ከእግሩ በታች ሰገደ ቡራኬም ከእርሱ ተቀበለ። ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስም የጀመረውን የቅዳሴውን ሥርዓት እንዲፈጽም ቄሱን አዘዘው። እርሱንም በታላቅ ክብር ወደ ቤተ መቅደስ አስገቡት ከዚህም በኋላ ቄሱ ወደ መሠዊያው በወጣ ጊዜ የቁርባኑን ኅብስት በጻሕሉ ውስጥ አገኘው ካህናቱና ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

የቁርባኑንም ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ካህናቱና ሕዝቡም ሁሉ ከሊቀ ጳጰሳት አባ ሳዊሮስ ቡራኬ ተቀበሉ። ከዚያም ወጥቶ ወደ ሀገረ ስሐ ሔደ ስሙ ዶርታዎስ ከሚባል እግዚአብሔርን ከሚወድ ባለ ጸጋ ሰው ደርሶ ከእርሱ ዘንድ ተቀመጠ። ምእመናንንም እያስተማራቸውና በቀናች ሃይማኖት እያጸናቸው እስከሚአርፍባት እስከ የካቲት ወር ዐሥራ አራት ቀን ኖረ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሊቁ_ቅዱስ_አባ_ሕርያቆስ

ክርስቲያን ሆኖ እመቤታችንን የሚወድ ሰው ሁሉ ይህንን አባት ያውቀዋል። አባ ሕርያቆስ ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ ሲሆን አካባቢው ብህንሳ (ንሒሳ) ይባላል። ይህቺ ቦታ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ጨምሮ በርካታ ቅዱሳንን ያፈራች ናት።

አባ ሕርያቆስን በዚህ ዘመን ነበረ ተብሎ ትክክለኛውን ዓ/ም ለመናገር ይከብዳል። ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት መረዳት እንደሚቻለው ግን የነበረበት ዘመን 4ኛው ወይም 5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደ ሆነ መገመት ይቻላል።

ቅዱሱ በዘመኑ የተለየ ማንነት የነበረው ሰው ነው። ገና ከልጅነቱ እመ ብርሃንን የሚወዳት በመሆኑ ቅን የዋህና ገራገር ነበረ። መቼም እመቤታችን ይወዳል ሲባል እንደ ዘመኑ በአፍ ብቻ እንዳይመስለን። ቀንና ሌሊት ለፍቅሯ የሚተጋ ማዕበለ ፍቅሯ የሚያማታው ሰው ነበር እንጂ።

የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ስም ሲጠራ ምስጥ ብሎ ልቡናው ይሰወርበት ነበር ዘወትር የእርሷን ፍቅር ከማሰብ በቀር ሌላ ሥራ አልነበረውም። የልጅነት ጊዜው ሲያልፍም ድንግልንና ቸር ልጇን ያገለግል ዘንድ መነነ።

ዘመኑ ዘመነ ሊቃውንት እንደ መሆኑ ሁሉም ለትምሕርት ሲተጉ እርሱ ግን ለጸሎትና ለደግነት ብቻ ነበር የሚተጋው። ከትምሕርት ወገንም የሰሞን ጉዋዞችን አንዳንድ ቅዳሴያትንና የዳዊትን መዝሙር ተምሮ ነበር።

በተለይ ግን የዳዊትን መዝሙር እየጣፈጠው መላልሶ መላልሶ ያመሰግንበት ነበር። ከዳዊት መካከል ደግሞ መዝሙር 44ን ፈጽሞ ይወዳት ነበር። ይህቺ ጥቅስ የምትጀምረው "ጐስዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" ብላ ነው። የውስጧ ምሥጢርም ስለ ድንግል ማርያምና ስለ ክርስቶስ ነው።

አባ ሕርያቆስ ይህቺን መዝሙር በቃሉ አጥንቶ? ቁሞም ተቀምጦም ተኝቶም ተነስቶም ያለ ማቁዋረጥ ይላት ነበር። እየጣፈጠችው "ልቡናየ በጐ ነገርን አወጣ" እያለ ይዘምር ነበር። በወቅቱ ታዲያ የብህንሳ ኤዺስ ቆዾስ በማረፉ ምትክ ሲያፈላልጉ መንፈስ ቅዱስ አባ ሕርያቆስን መረጠ።

ምንም አለመማሩ ቢያሰጋችቸውም 'በጸሎቱ በደግነቱ ሃገር ይጠብቃል' ብለው ሾሙት ነገር ግን ምንም በሥልጣን የበላያቸው ቢሆን ተማርን የሚሉ ሰዎች ይጠሉት ይንቁትም ነበር። እርሱ ግን እንደ ጠሉኝ ልጥላቸው እንደ ናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅር ያገለግል ነበር።

አንድ ቀን ታዲያ መንገድ ይወጣል:: በበርሃ ብቻውን እየተራመደ "ጐሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" እያለ እየዘመረ ተመሥጦ ቢመጣበት መንገድ ሳተ። እርሱ በምስጋናው ሲደሰት እግሩ ግን ከገደል ጫፍ ደርሶ ነበር። ገደሉን ልብ አላለውም ነበርና ሳይታወቀው ወደ ገደሉ ውስጥ ተወረወረ።

በዚህ ጊዜ ደንግጦ ቢመለከት እጅግ ጥልቅ በሆነ ገደል ውስጥ ራሱን አገኘው። ነገር ግን አንድም አካሉ አልተነካም። ልብሱም አልቆሸሸም። ለራሱ ተገርሞ ዙሪያ ገባውን ሲመለከት እርሱ ቁጭ ያለበት ብርሃንን የተሞላ የልብስ ዘርፍ ነበር።

"እመ ብርሃን" ብሎ ሲጮህ የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነች እመቤታችን ከፊቱ ቁማ ታየችው። እመ አምላክን በገሃድ ቢያያት እንደ እንቦሳ ዘለለ።

የሚገርመው ደግሞ የተቀመጠበት የድንግል ማርያም የቀሚሷ ዘርፍ ነበር። እመቤታችን አነጋገረችው ባረከችው። ፍቅሯ ቢመስጠው ከሰው ሳይገናኝ ምግብም ሳይበላ እዚያው ገደሉ ውስጥ ለ1 ዓመት ያህል በተመስጦ ቆይቷል።

በሁዋላ እመ ብርሃን መጥታ ከገደሉ አውጥታ ወደ ሐገሩ መለሰችው። ከጥቂት ጊዜ በሁዋላም አንድ ፈተና ገጠመው። አንድ ቀን እመቤታችን በተወለደችበት ግንቦት 1 ቀን ቅዳሴ 'ማን ይቀድስ' ሲባል ሰዎቹ 'አባ ሕርያቆስ ይሁን' አሉ።

እርሱ ግን "እኔ አይቻለኝም እናንተ ሊቃውንት ቀድሱ" አላቸው። "አይሆንም"ብለው እርሱኑ አስገቡት። ይህንን ያደረጉት ለተንኮል ነበር። ልክ ወንጌል ተነቦ ፍሬ ቅዳሴ ሲመረጥ እርሱ "እግዚእን (የጌታ ቅዳሴን) ልቀድስ" ቢል እነርሱ "የሚቀደሰው የሊቅ ቅዳሴ ነው" አሉት።
ይህንን ያሉት እርሱ የሊቃውንቱን ቅዳሴ አያውቅምና በሰው ፊት እንዲዋረድ ነው። እንዲህም ብለው ባለመማሩ ተሳለቁበት። አባ ሕርያቆስ ግን እያዘነ ወደ መንበሩ ዞረ። ድንግልንም "እመቤቴ መናቄን መገፋቴን ተመልከች" አላት።

ወዲያው ግን ድንግል ማርያም ወርዳ ቀጸበችው (ጠራችው)። በዘርፋፋው ቀሚሷ ላይም ረቂቅ የሆነ ቅዳሴን አሳየችው። ደጉ ሰው ደስ ብሎት "ጐሥዐ ልብየ" ሲል 2ቱ እግሮቹ ከመሬት ከፍ አሉ። እርሱም "ወአነ አየድእ ቅዳሴሃ ለማርያም" ብሎ እስከ ኃዳፌ ነፍሱ ድረስ አደረሰው።

ሕዝቡና ካህናቱ በሆነው ነገር ሲደነቁ አንዳንዶቹ "ዝም ብሎ ነው የቀባጠረ" አሉ። ቅዱሱ ግን ቅዳሴ ማርያምን በብራና ጠርዞ በሕዝቡ መካከል ድውይ ፈወሰበት። እሳት ሳያቃጥለው: ውሃ ሳይደመስሰው ቀረ።

መጽሐፈ ቅዳሴው ሙትንም አስነስቷል። ከዚህች ሰዓት ጀምሮ በዘመኑ ቁጥር 1 ሊቅሙ ሆነ። ብዙ መጻሕፍትን ሲተረጉም አጠቃላይ ድርሰቶቹም እልፍ (10,000) ናቸው። ሊቁ እንዲህ በንጹሕ ተመላልሶ ዐርፏል። ይህቺ ቀን ለቅዱሱ የልደቱና ዕረፍቱ መታሰቢያ ናት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ማትያስ_ዘፈጠጋር

ዳግመኛም በዚህች ቀን የፈጠጋሩ አቡነ ማትያስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የበቁ፣ የነቁ፣ ምግባር ሃይማኖታቸው እንደፀሐይ ያበራ፣ ከተጋድሏቸውም ብዛት የተነሣ ከብቃት ደረጃ ላይ የደረሱ ቅዱሳን የሆኑ ደገኛ መምህራንን በማሰልጠን በአንብሮተ እድ ዓሥራ ሁለት ዓሥራ ሁለት አድርገው እየሾሙ ለስብከተ ወንጌል በመላ አገራችን ያሰራጯቸው ነበር፡፡ እነዚህም ንቡራነ እድ ከዋክብት በመላ አገራችን የወንጌልን ብርሃን ያበሩ ቅዱሳን ናቸው፡፡

በመጀመሪያ በተክለ ሃይማኖት በአንብሮተ እድ የሾሟቸው 12ቱ ከዋክብት የወረቡ አኖሬዎስ፣ የሞረቱ ዜና ማርቆስ፣ የጽላልሹ ታዴዎስ፣ የድምቤው ገብረ ክርስቶስ፣ የወገጉ ሳሙኤል፣ የእናርያው ዮሴፍ፣ የዳሞቱ አድኃኒ፣ የወጁ ኢሳይያስ፣ የመንዝ የመራቤቴውና የወለቃው መርቆሬዎስ፣ የመሐግሉ ቀውስጦስ፣ የፈጠጋሩ ማትያስ፣ የደዋሮው ተስፋ ሕፃን፣ የእንሳሮው ዳዊት፣ የዘልዓቱ ናታን ናቸው፡፡

የፈጠጋሩ ማትያስም አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሾሟቸው ከ12 ንቡራነ እድ ውስጥ አንዱ ሲሆኑ ቁጥራቸውም ሁለተኛ ናቸው፡፡ ደብረ ሊባኖስን ያጥኑ የነበረው በሰኔ ወር ሲሆን በገዳሙም 13ኛው አባት በመሆን በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ በሀገራችን ተዘዋውረው በትምህርታቸውና በተአምራታቸው ወንጌልን ሲሰብኩ ኖረው በሰላም ዐረፈዋል፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት እና #ከገድላት_አንደበት)
#ጥቅምት_3

ጥቅምት ሦስት በዚህች ቀን የኢትዮጵያዊው ቄርሎስ #አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ በዓለ ፅንሰቱ ነው፣ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት 51ኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባ_ስምዖን አረፈ፣ #የቅዱስ_ጊዮርጊስ_ሐዲስ የምስክርነቱ መታሰቢያ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞#✞✞✞✞✞

#አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ

ጥቅምት ሦስት በዚህች ዕለት ከመጽሐፈ ሰዓታት ውጭ እጅግ ብዙ ድርሰቶችን የደረሰ ፈላስፋም ጻዲቅም ደራሲም መናኝ ባሕታዊም የሆነ ድርሰቶቹንም ለቅዱሳን በነፋስ ጭኖ ይልክላቸው የነበረ የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ኩራት ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በዓለ ፅንሰቱ ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስ ነገረ ሃይማኖትን ጠንቅቆ የተረዳና የሚያስረዳ ስለነበር በዘመኑ የተነሡ የሃይማኖት ክርክሮች ሁሉ እርሱ ከሌለ አይሳኩም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በሸዋ በይፋት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ አይሁድ ነበሩ፡፡ ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጀምሮ ብዙ መምህራን ወደነዚህ ሕዝቦች እየተሠማሩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ክርስትና ለተመለሱት ቤተ እስራኤላውያን በእመቤታችን፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በአባ ኖብና በሰማዕቱ በጊጋር ስም አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተው ነበር፡፡ ሁለቱ የመጀመሪያዎቹ አሁንም አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ቤተ እስራኤላውያኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ክርስትና አልተመለሱም ነበር፡፡

ከእነዚህ አይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ “ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉ” ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ እዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡ የመጀመርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡- “እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ 'አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?” ብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣ እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ?” ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡

በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ ሊቃውንቱም “እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ” ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደረገ፡፡ በአልጋ ላይ ሆኖም በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ ነገሩት፡፡ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጥልናል “እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ ምኩራብ ዘራች ቤተ ክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኩራብ ፈተለችው ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? እግዚአብሔር አብ አይደለምን?” በዚህ ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ሌላው ያጋጠመው ክርክር ቢቱ ከተባለው ሰው ጋር ያደረገው ክርክር ነበር፡፡ ቢቱ “በምጽአት ጊዜ የሚመጣው ወልድ ብቻውን እንጂ አብና መንፈስ ቅዱስ አይመጡም” የሚል ኑፋቄ ማስተማር ጀምሮ ነበር፡፡ ቢቱ ከዚህ ኑፋቄው በተጨማሪ የጥንቆላ ሥራም ይሠራ ነበር፡፡ ቢቱ በጥንቆላ ሥራው የተነሣ በቤተ መንግሥቱ ተቀባይነት የነበረው ሰው እንደ ነበረ ገድሉ ይናገራል፡፡ ይህን መሰሉን ተግባር አጥብቆ የተዋጋው ዘርዐ ያዕቆብ እስኪመጣ ድረስ ነገሥታቱ ምንም ክርስቲያኖች ቢሆኑበዚህ መሰሉ ስንኩል ሕፀፅ ይዋጡ ነበር፡፡

ቢቱና አባ ጊዮርጊስ ወደ ንጉሥ ዳዊት ቀርበው በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጡ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ጳጳሱና ሊቃውንቱ ባሉበት እንዲነጋገሩ ስለ ወሰነ ጳጳሱ እንዲመጡ አዘዘ፡፡ በዚህ ጊዜ ተንኮለኛው ቢቱ ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ከተከራከረ እንደሚረታ ስላወቀ “ንጉሡ የአባቶቻችንን ሃይማኖት ክዷልና አትምጣ” የሚል ደብዳቤ በአባ ጊዮርጊስ ስም ጽፎ ጳጳሱን ሊጠሩ በሄዱት መልእክተኞች እጅ ላከ፡፡ ወድያውም ለዐፄ ዳዊት ይህንን ነገር አሳበቀ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ፈጣን መልእክተኞች ልኮ የፊተኞቹ መልእክተኞች እንዲመለሱ አደረገና ደብዳቤው ተነበበ፡፡ የቢቱ ተንኮል ያልገባው ንጉሥ ዳዊት ይህን ደብዳቤ ሲመለከት አባ ጊዮርጊስን በደም አበላ እስኪነከር ድረስ እንዲደበደብ አድርጎ ወደ እስር ቤት አስገባው፡፡ ዐፄ ዳዊት እስኪሞትና ልጁ ቴዎድሮስ እስኪነግሥ ድረስም በዚያ ቆየ፡፡ ቢቱ ግን በመልአክ ተቀስፎ ሞተ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ስምዖን

ዳግመኛም በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ኃምሣ አንደኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ስምዖን አረፈ።

ይህም አባት ከእስክንድርያ ከታላላቆች ተወላጅ የሆነ ወላጆቹም ሃይማኖታቸው የቀና ነው እርሱም ከታናሽነቱ የሃይማኖት ወተትን ጠጥቶ አደገ ስለዚህም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተማረ።

የምንኵስናንም ልብስ ሊለብስ በልቡ አስቦ ወደ አስቄጥስ ገዳም በመሔድ ከእርሱ አስቀድሞ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በአባ ያዕቆብ ገዳም መነኰሰ በየጊዜው በሚጨመር ተጋድሎም ሥጋውን እያደከመ አብዝቶ በመጋደል በእርሱ ዘንድ ኖረ።

ዳግማዊ አባ ማርቆስም ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ይህን አባ ስምዖንን ስለ በጎተጋድሎውና ስለ አገልግሎቱ ከአባ ያዕቆብ ዘንድ ወሰደው እያገለገለውም ከእርሱ ጋር ኖረ።

አባ ማርቆስም በአረፈ ጊዜ አባ ያዕቆብ ተሾመ ያን ጊዜም እያገለገለው ከአባ ያዕቆብ ጋር ኖረ። ከዚህም በኋላ አባ ያዕቆብ በአረፈ ጊዜ ብዙዎች ካህናትና ኤጲስቆጶሳት የሀገር ታላላቆች ሁሉም ይህን አባት አባ ስምዖንን መረጡት። ትሩፋቱንና የአማረ ሥራውን በእነዚህ በሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ በነበረበት ጊዜ ስለተመለከቱ አምላካዊ ፍቅር አነሣሥቷቸዋልና በወንጌላዊ ማርቆስ መንበር ላይ ይዘው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።

ከዚህም በኋላ በሹመቱ ጸንቶ መልካምን ጉዞ ተጓዘ እግዚአብሔርንም አገለገለው የሃይማኖትንም ሕግ በማስጠበቅ የክርስቶስን መንጋዎች ጠበቀ።

በሹመቱ ወራትም ቤተ ክርስቲያን በጸጥታና በሰላም ኖረች። ከዚህም በኋላ እግሮቹን በጽኑዕ ደዌ ታመመ ፈጣሪ እግዚአብሔርንም ከዚህ ደዌ ያሳርፈው ዘንድ ለመነው። ክብር ይግባውና ጌታችንም ልመናውን ተቀብሎ በሰላም በፍቅር አንድነት አሳረፈው የሹመቱ ወራትም አምስት ወር ከዐሥራ አምስት ቀን ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ሐዲስ (ሰማዕት)

ሰማዕቱ የተወለደው በምድረ ግብጽ አሕዛብ (ተንባላት) በሰለጠኑበት የመጀመሪያው ዘመን ነበር። በተለይ ተንባላቱ ግብፅና ሶርያን ከያዙ በኋላ ባልተጠበቀ ፍጥነት በኃይልም በሰውም ተደራጅተው ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ (ሊቀ ሰማዕታት አይደለም) የተወለደው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር።
እናቱ የተመሠከረላት ክርስቲያን ብትሆንም እንዳለመታደል አባቱ ተንባላታዊ (አሕዛብ) ነበር። ስሙንም መዛሕዝም ይሉታል። ሕጻኑ እንደተወለደ ያወጡለት ስም አሕዛባዊ ከመሆኑ ባለፈ በሰዓቱ መጠመቅ አልቻለም። የወቅቱ ሕግ ከወላጆቹ አንዱ አሕዛባዊ ከሆነና አጠምቃለሁ ቢባል የሚከተለው ሰይፍ ነበር። በዚሕ ምክንያት ሳይጠመቅ 7 ዓመት ሞላው።

እናቱ ግን ሕጻን ቢሆንም ፍቅረ ክርስትናን ታስተምረው ነበር። ባይጠመቅም ጸበሉን እመነቱን ትቀባው ነበር። ደብቃ ቅዳሴ ታሰማውም ነበር። አንድ ቀን ግን ሕጻናት ሲቆርቡ አይቶ ካልቆረብኩ ብሎ አለቀሰ። ምን ታድርገው? ወደ ውጪ አውጥታ ከአውሎግያ (የሰንበት በረከት) አበላችው። "ጌታዬ ልጄን እርዳው" አለች።

ልክ በአፉ ሲቀምሳት መዓዛ መንፈስ ቅዱስ አደረበትና ፍጹም ተደሰተ። ትንሽ ከፍ ሲል ለምን እንደማይጠመቅና እንደማይቆርብ እናቱን ጠየቃት። "ልጄ ሆይ! ይገድሉሃል" አለችው። ከዚህች ቀን ጀምሮ የሚጠመቅበትን ዘዴ ይፈልግ ጀመር።

አስቀድሞ ትምሕርተ ክርስትናን ተማረ። ለአካለ መጠን ሲደርስ አፈላልጐ ጠንካራ ክርስቲያን የሆነች ሴት አገባ። ጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ ሚስቱን ስለ መጠመቅ አማከራት። "ሌላ ሃገር ሒደህ ተጠመቅ" አለችው። ከግብፅ ተነስቶ ሶርያ ገባ። አባቶችን አፈላልጎ ተጠመቀ። ቀጥሎም መንገዱን ወደ ልዳ አደረገ።

ወደ ደብሩ ተጠግቶ አባቶችን "ስም አውጡልኝ" ቢላቸው መንፈስ ቅዱስ አናግሯቸው "ጊዮርጊስ" አሉት። እሱም ደስ እያለው ባጭር ታጥቆ የልዳውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገለግለው ገባ። ትንሽ ቆይቶ ሁከት መንፈሳዊ ተሰማው። ማለትም ስለ ሃይማኖቱ ደሙን ማፍሰስ ፈለገና ወደ ግብፅ ተመለሰ።

በዚያ ያሉ አሕዛብ በክርስትና ስም ልብስና ሞገስ ሲመለከቱት ተበሳጩ። ዕለቱኑ አሠሩት። ሌሊት እናቱና ሚስቱ መጥተው አሉት "አደራ! ፍቅረ ዓለም እንዳያታልልህ። ሰማዕት ብትሆን ላንተም ክብር ለእኛም ሞገስ ነው" ብለውም አጽናኑት። እንዲህ ያሉ እናትና ሚስት ማግኘትም ታላቅ እድል ነው::

ሐዲስ ጊዮርጊስም ጸና። ከዚያች ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ደበደቡት አካሉን ቆራረጡት ደሙንም መሬት ላይ አንጠፈጠፉት። በየመንገዱ እየጎተቱ ተሳለቁበት። እርሱ ግን ክርስቶስን ወዷልና ሁሉን ታገሰ። ሌሊት በሆነ ጊዜም ጌታችን ተገልጦ "ከሰማዕታት ተቆጠርህ" አለው።

በማግስቱ በአደባባይ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡት። ክፋታቸው የጸና ነውና ሥጋውን በእሳት አቃጠሉት። ወደ ባሕርም ጣሉት። እናቱ ከባሕር ስታወጣው ግን ምንም አላገኘውም ነበር። በዚሕች ቀን እናቱና ሚስቱ በክብር ቀብረውታል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት እና #መጽሐፈ_አርጋኖን_መግቢያ)
#ጥቅምት_4

ጥቅምት አራት በዚች ቀን #ቅዱስ_ባኮስ በሰማዕትነት አረፈ፣ #ቅዱሳን_ነገሥታት_አብርሃ_ወአጽብሓ ያረፉበትም ዕለት ነው፣ ሐዋርያው #ቅዱስ_ሐናንያ በሰማዕትነት ዐረፈ፣ #አቡነ_በርተሎሜዎስ ዕረፍታቸው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ባኮስ

ጥቅምት አራት በዚህች ቀን የቅዱስ ሰርጊስ ባልንጀራ ቅዱስ ባኮስ በከሀዲ ንጉሥ አንጥያኮስ እጅ በሰማዕትነት አረፈ።

ይህም እንዲህ ነው እሊህን ቅዱሳን ከሀዲው ንጉሥ መክስምያኖስ በያዛቸው ጊዜ እነርሱ ወታደሮች ነበሩና ትጥቃቸውን ቆርጦ ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው ከዚህም በኋላ ወደ ሶርያ አገር ወደ ንጉሥ አንጥያኮስ ሰደዳቸው። እርሱም ቅዱስ ሰርጊስን አሠረው ቅዱስ ባኮስን ግን ሰቅለው እንዲደበድቡት በአንገቱም ከባድ ደንጊያ አንጠልጥለው ከኤፍራጥስ ወንዝ ከባሕር እንዲጥሉት አዘዘ ንጉሡም እንደ አዘዘ እንዲሁ አደረጉ።

እግዚአብሔር ግን የቅዱስ ባኮስን ሥጋ ጠብቆ ወደ ወደብ አደረሰው በዚያ ወደብ አቅራቢያም በገድል ተጠምደው የሚኖሩ የአንደኛው ስሙ ማማ የሁለተኛው ባባ የሚባሉ ባሕታውያን አሉ። ለእሊህ ወንድሞችም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጠላቸውና ሒደው የቅዱስ ባኮስን ሥጋ ወደ በዓታቸው እንዲወስዱ አዘዛቸው።

በዚያንም ጊዜ መልአክ እንዳዘዛቸው ሔዱ የቅዱስ ባኮስንም ሥጋ አገኙ በአጠገቡም አንድ ቀንና አንድ ሌሊት ሲጠብቁት የነበሩ አንበሳና ተኵላ አሉ እነርሱም ከሰው ሥጋና ከእንስሳ በቀር የማይመገቡ ሲሆኑ ግን ከልዑል አምላክ ዘንድ ስለታዘዙ ነው። እሊያ ቅዱሳንም የቅዱስ ባኮስን ሥጋ ወሰዱ በታላቅ ክብር እያመሰገኑ እስከ በዓታቸውም አድርሰው በዚያ ቀበሩት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ነገሥታት_አብርሃ_ወአጽብሓ

ዳግመኛም በዚህ ቀን ቅዱሳን ነገሥታት አብርሃ ወአጽብሓ ያረፉበት ነው። አባታቸው ታዜር እናታቸው ሶፍያ (አህየዋ) ይባላሉ፡፡ መንትዮች የሆኑት እነዚህ ቅዱሳን የተወለዱት ጌታችን በተወለደባት ዕለት በታኅሣሥ 29 ቀን 312 ዓ.ም ነው፡፡ በታላቁ አባት በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን እየተማሩ አድገው በእሳቸው እጅ በ330 ዓ.ም መጋቢት 29 ቀን ተጠመቁ፡፡ በእነርሱም ጊዜ አማናዊው ጥምቀትና ቁርባን መጣልን፡፡ በሀገራችን 154 አብያተ ክርስቲያናትን ያሠሩ ሲሆን 44ቱ ፍልፍል ናቸው፡፡ በተለይም ገርዓልታ ያለው ቀመር ዓርባዕቱ እንስሳ ፍልፍል ቤተ መቅደስ በሩ በራሱ ጊዜ ይከፈታል ይዘጋል እንጂ ሰው አይከፍተውም አይዘጋውም፡፡

አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን በአክሱም ሲኖሩ ከሳምንቱ ቀናት ውስጥ ቅዳሜና እሁድ ብቻ የዛፍ ቅጠሎችን ከመመገብ በቀር ሌላ ምግብ ባለመመገብ በታላቅ ተጋድሎ ይኖሩ ነበር፤ አህልም አይቀምሱም፤ በየቀኑም አምስት ሺህ ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡ በእርሳቸውም የተጋድሎ ዘመን ደጋግ የሆኑ ቅዱሳን ነገሥታት አብርሃና አጽብሓ ነገሡ፡፡

ነገሥታቱም ሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃንን እጅግ በጣም ይወዷቸው ነበር፡፡ አባታችንም በእንዲህ ዓይነት ተጋድሎ ሲኖሩ ከዕለታት በአንደኛው ቀን የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክ ለአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ተገልጣላቸው ‹‹ዲቁናና ቅስናን መቀበል ይገባሃል፣ ለጵጵስና ተዘጋጅ፣ እግዚአብሔር ይህችን ከፍ ያለችውን ማዕረግ ሰጥተሃልና የልጄ ወዳጅ ሆይ በጸሎትህና በልመናህ በስብከትህም የኢትዮጵያ ሰዎች ሁሉ ይድናሉ፣ በእጅህ ጥምቀትንና ሥጋ ወደሙን ይቀበላሉ›› አለችው፡፡ ጌታችንም እንዲሁ ተገልጦላቸው ‹‹ወደ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አትናቴዎስ ሄደህ ከፍ ያችውን ማዕረግ ተቀብለህ የኢትዮጵያን ሰዎች አጥምቅልኝ፣ ነቢዩ ዳዊት ስለ እነርሱ ‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች› ብሎ ተናግሯልና›› አላቸው፡፡ ነገሥታቱ አብርሃንና አጽብሓ ነገረ ክርስቶስን እያሰቡ ስለ ጥምቀት ልጅነት ይጨነቁ ነበር፡፡ ከሊቀ ካህናቱም ጋር በዚህ ጉዳይ ሲጨዋወቱ ሊቀ ካህናቱ ስለ አቡነ ሰላማ ነገሯቸው፡፡ ነገሥታቱም አቡነ ሰላማን አስጠርተው ስለነገረ ክርስቶስ ምሥጢር እንዲያስረዷቸው ጠየቋቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ይወለዳል ካሉበት ጀምሮ የልደቱን፣ የትምህርቱን የጥምቀቱን፣ የስቅለቱን፣ የሞቱን፣ የትንሣኤውንና የእርገቱን ነገር ሌላውንም ሁሉ ተንትነው አስተማሯቸው፡፡ ሐዋርያትም በጌታ ተሾመው ዓለምን ዞረው ማስተማራቸውን እንዲሁ ተረኩላቸው፡፡ ነገሥታቱም ይህንን በሰሙ ጊዜ እጅግ ደስ ብሏቸው ፍሬምናጦስን ‹‹ወንድማችን ሆይ! ይህን ሥርዓት በሀገራችን እንድታስፋፋ›› አሏቸው፡፡ አባታችን ግን ‹‹ለዚህ የሚያበቃ ሥልጣን ያለው እንጂ ለእኔ አይቻለኝም›› አሉ፡፡ ነገሥታቱም ‹‹ይህን የሚችል ማነው?›› ብለው ቢጠይቋቸው ‹‹በእስክንድርያ ጳጳሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን የሚሾም አባት አለ አሏቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ነገሥቱ ወደ እስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቅዱስ አትናቴዎስ ደብዳቤ በመጻፍ ‹‹አባታችንና መምህራችን ሆይ! የምንጠይቅህን እሺ በጀ በለን ይኸውም ወደ ጽድቅ ጉዳና የሚመራንን ጳጳስ ሹምልን›› በማለት ብዙ ወርቅና ብር ገጸ በረከት አስይዘው ከብዙ ሊቃውንት ጋር ፍሬምናጦስን ወደ እስክንድርያ ላኳቸው፡፡

ከዚህም በኋላ አባታችን ከነገሥታቱ አብርሃና አጽብሓ ጋር ተማክረው ወደ እስክንድሪያ ሄደው በቅዱስ አትናቴዎስ እጅ በአገራችን ላይ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ታኅሳስ 18 ቀን ተሾሙ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ከሾሟቸውና ከመረቋቸው በኋላ ለአቡነ ሰላማና አብረውት ለነበሩ ሊቃውንት መጻሕፍተ ብሉያትን፣ መጻሕፍተ ሐዲሳትንና ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ታቦተ ማርያምን፣ ታቦተ ሚካኤልንና ታቦተ ገብርኤልን አስይዘው ለነገሥታቱም ደብዳቤ ጽፈው ከብዙ ገጸበረከት ጋር በታላቅ ክብር ሸኟቸው፡፡ ቅዱሳን የሚሆኑ ሁለቱ ነገሥታትም አቡነ ሰላማ ከእስክንድርያ ተሾመው መምጣቸውን በሰሙ ጊዜ ‹‹የኢትዮጵያ ሰዎች ሁላችሁ እስከ 40 ቀን ተሰብሰቡ›› ብለው አዋጅ አስነገሩ፡፡ አባታችንንም በደብረ ሲናም ሄደው አገኟቸውና ከዚያች ቀን ጀምሮ ሕዝቡም ሁሉ እስከ 40 ቀን ድረስ ተጠመቁ፡፡ በዚያችም ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያች በደብረ ሲና አገር ላይ ወረደና ሕዝቡን ሁሉ ባረኮ ተመልሶ ሲያርግ ከአባ ሰላማ በቀር ያየው አልነበረም፡፡ ወደ አክሱምም ሄደው ቅዱሳን ነገሥታቱም የአድባራት ሁሉ የበላይ የምትሆን የቅድስት ጽዮንን ቤተ ክርስቲያን በወርቅና በዕንቊ ሠሯትና አባ ሰላማ ባርከው ቀደሷት፡፡ ታቦተ ጽዮንም ከድንኳን ወጥታ ማንም ካህን ሳይሸከማት አብርሃና አጽብሓ ወዳሠሩላት ቤተ መቅደስ ራሷ በመንፈስ ቅዱስ ገብታ ተገኘች፡፡
አባታችን በእመቤታችንም በዓለ ዕረፍት ጥር 21 ቀን በውስጧ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀድሱ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በግራ በቀኝ እየተራዷቸው እርሳቸውም ከምድር ሦስት ክንድ ከፍ ብለው ሥርዓተ ቅዳሴውን ፈጽመው ለነገሥታቱና ለሕዝቡም ሁሉ አቆረቧቸው፡፡ የዚያን ዕለትም እጅግ ታላቅ በዓልን አደረጉ፡፡

እነዚህም ቅዱሳን ነገሥታት ትምህርተ ወንጌልን እየሰጡ በአክሱም ቤተ መንግሥታቸው ሳሉ ከዕለታት አንደኛው ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ በአክሱም ‹‹ማይ ኰኩሐ›› በሚባል ተራራ ላይ ቁሞ አብርሃ ወአጽብሓን ጠርቶ ‹‹በዚህች ቦታ ላይ ቤተ መቅደሴን አንጹልኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ቦታው ባህር ላይ ነው በየት እናንጽልህ?›› አሉት፡፡ ጌታችንም በጥበቡ ከገነት ጥቂት አፈር አምጥቶ በባሕሩ ላይ ቢበትንበት ባሕሩ ደርቆ ሜዳ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችን ‹‹ቤተ መቅደሴን
በዚህ ሥሩ›› ብሏቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ጌታችንም በቆመባት ዓለት ላይ የእግሩ ጫማ ቅርጽ እስከ አሁን ሳይጠፋ በግልጽ ይታያል፡፡ ቦታውም ከዚያ ወዲህ ‹‹መከየደ እግዚእ›› እየተባለ ይጠራል፡፡

አብርሃ ወአጽብሓ ከመንግሥት አስተዳደሩ ጋር ክርስትናንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በመላ ኢትዮጵያ በማዳረስ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል፡፡ ካህናትንና ዲያቆናትን ይዘው በመላ ኢትዮጵያ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ ሕዝቡን ሁሉ እያስተማሩ፣ ሃይማኖትን እያጸኑ፣ ሥርዓተ ጥምቀትን እያስፋፉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል፡፡ በሀገራችን በአራቱም አቅጣጫ ወንጌልን አስፋፍው ሕግ ሠርተዋል፡፡ የከበሩ ቅዱሳን ነገሥት አብርሃ ወአጽብሓ በእንዲህ ዓይነት ግብር ጸንተው በመኖር እግዚአብሔርንም ሰውንም አገልግለው ለሀገራችንም ብርሃን አብርተውላት ነው ያለፉት፡፡

ታላቁ አብርሃ በ364 ዓ.ም ጥቅምት 4 ቀን እሁድ ዕለት ዐረፉ፡፡ ከ13 ዓመት በኋላ ታናሹ አጽብሓ በ379 ዓ.ም ጥቅምት 4 ቀን ዐረፉ፡፡ ልደታቸውም ሆነ ሞታቸው አንድ ቀን ነው-የዕረፍታቸው ዓመቱ ይለያይ እንጂ፡፡ የተቀበሩበት ቦታም አንድ ነው፡፡ የንግሥና ስማቸው ኢዛናና ዛይዛና ይባላል፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያው_ቅዱስ_ሐናንያ

በዚችም ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሐዋርያ ቅዱስ ሐናንያ በሰማዕትነት አረፈ ። ይህም ቅዱስ በሐዋርያት እጅ ለደማስቆ አገር ኤጲስቆጶስነት ተሾመ እርሱም ክብር ይግባውና ጌታችን በደማስቆ ጐዳና ተገልጦለት ለወንጌል ትምህርት በጠራው ጊዜ ሐዋርያ ጳውሎስን ያጠመቀው እርሱ ነው ።

እርሱም አስቀድሞ ለግብሪል ወገኖች አስተማረ ብዙዎች በሽተኞችን አዳናቸው ብዙ ሰዎችንም ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት መለሳቸው ።

ከዚህም በኋላ ስሙ ሉቅያኖስ የሚባል መኰንን ያዘው በምድር ላይ ደሙ እንደውኃ እስከሚፈስ ድረስ ገረፈው ጐኖቹንም በብረት በትሮች ሠነጣጠቀ ደረቱንም በእሳት መብራቶች አቃጠለ ። ከዚህም በኋላ ከከተማ ውጭ አውጥተው በደንጊያ ይወግሩት ዘንድ አዘዘ በዚህም ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_በርተሎሜዎስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን አቡነ በርተሎሜዎስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ጻድቁ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ልጆች ውስጥ አንዱ ሲሆኑ ያመነኮሷቸውና የሾሟቸውም እርሳቸው ናቸው፡፡ የቆባ፣ የጠጠርና የኮረም ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሹመው በብዙ ድካም አገልግለዋል፡፡ ጻድቁ ደብረ ሊባኖስን የሚያጥኑበት ተራቸው በወርሃ ጳጉሜ ነበር፡፡

ወሎ ራያ ውስጥ ያለችውን ጥንታዊቷንና ባለታሪኳን ደብረ ዘመዳን የመሠረቷት ይህ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የሳላት የእመቤታችን ሥዕል ሁልጊዜ ሰዓታትና ማኅሌት በማይታጎልባት በዚህች ጥንታዊ ገዳም ውስጥ ትገኛለች፡፡ እጅግ በርካታ ቅርሶችም ይገኙባታል፡፡ በአካባቢዋም ዘብ ሆነው የሚጠብቋት በርካታ የዱር አራዊት ይገኛሉ፡፡ ጻድቁ በታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ ኖረው በሰላም ዐርፈዋል፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት
#የአብርሃ_ወአጽብሐ_ታሪክ_በገዳሙ_የታተመ
#ከገድላት_አንደበት
ሥርዓተ ማኅሌት ዘጥቅምት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ "ጥቅምት ፭"

የማንኛውም ወርኃ በዓልና ክብረ በዓል ሥርዓተ ማኅሌት መጀመሪያ (ሥርዓተ ነግሥ)
ስምዓኒ እግዚኦ ጸሎትየ፡ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፡ ወይብጻሕ ቅድሜከ ገአርየ፡ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፡ ወኢትሚጥ ገጸከ እምኔየ፡ በዕለተ ምንዳቤየ አጽምእ እዝነከ ኀቤየ፡ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፡ አመ ዕለተ እጼውአከ ፍጡነ ስምዓኒ፡ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፡ ለዓለም ወለዓለመ ዓለም፡ ሃሌ ሉያ ዘውእቱ ብሂል፡ ንወድሶ ለዘሃሎ እግዚአብሔር ልዑል፡ ስቡሕ ወውዱስ ዘሣረረ ኲሎ ዓለመ፡ በአሐቲ ቃል።

መልክአ ሥላሴ
ሰላም ለሕፅንክሙ ምርፋቀ ጻድቃን አግብርቲሁ፤ ማያተ ኢያሱ ሥላሴ እለ ትውኅዙ እምሕሊናሁ፤ እንዘ በአፍአሁ አንትሙ ወአንትሙ በውሣጤሁ፤ ኢነጸረ ኀበ ሐይመት ከመ አብርሃም አቡሁ፤ ወመስኮተ ነቢይ ዳንኤል ኢፈቀደ ያርኁ።

ዚቅ
በአፍአኒ አንትሙ፣ ወበውሣጤኒ አንትሙ፤ በገዳምኒ አንትሙ፤ ብርሃኑ ለዓለም (ለኢያሱ) አንትሙ።

መልክአ ሚካኤል
ሰላም ለሕፅንከ እንተ በዲቤሁ ሕቁፍ፤ ጸሎተ ቅዱሳን ውኩፍ፤ ሚካኤል ክቡር መስፍነ ትጉሃን አእላፍ፤ ለረዲኦትየ ከመ ዘይሠርር ዖፍ፤ እንዘ ትሠርር ነዓ በ፪ኤ አክናፍ።

ዚቅ
ከመ መዓዛ ቅዱሳን፤ ውስተ አብያተ ክርስቲያን፤ ይሰምዖሙ ጸሎቶሙ ለንጹሐን ከመ መዓዛ ቅዱሳን።

ነግሥ
ሰላም ለዝክረ ስምኪ ዘመንክር ጣዕሙ፤ ለወልድኪ አምሳለ ደሙ፤ መሠረተ ህይወት ማርያም ወጥንተ መድኃኒት ዘእምቀዲሙ፤ ኪያኪ ሠናይተ ዘፈጠረ ለቤዛ ዓለሙ፤ እግዚአብሔር ይትባረክ ወይትአኮት ስሙ።

ዚቅ
እስመ ርእየ ሕማማ ለዓመቱ፤ ወገብረ ኃይለ በመዝራዕቱ፤ መዝገቡ ለቃል ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ መድኃኒተ ሕዝብ፤ መዓዛሆሙ ለቅዱሳን።

መልክአ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
ሰላም ለዝክረ ስምከ ዘኆኅያቲሁ ቅሩጽ፤ ኀበ ዓምደ ብርሃን ጽዱል ወአኮ ዘዕፅ፤ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ኃያል ሠዋቄ ትንቱናን እምዳኅፅ፤ ለዝክረ ስምከ ሠናየ ዜና ወድምፅ፤ ትሴብሕ ኢትዮጵያ ወትዜምር ግብፅ።

ዚቅ
ኮከብ ብሩህ ዘሠረቀ እምአቅሌስያ፤ ቤተ ክርስቲያን ዘንሰምያ፤ ኮኖሙ አበ ለሰብአ ግብፅ ወኢትዮጵያ፤ አማን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያ።

ዓዲ (ወይም)
ዚቅ
ፃማ ቅዱሳን ዲቤሁ አዕረፈ፤ አፈዋተ ወንጌል ጸገየ ዘልፈ፤ አባ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሃይማኖተ ተአጽፈ፤ ኀበ ዓምደ ወርቅ ስሙ ተጽሕፈ።

ወረብ
ኮከብ ብሩህ ዘሠረቀ እምአቅሌስያ ቤተ ክርስቲያን ዘንሰምያ/፪/
ኮኖሙ አበ ለሰብአ ግብፅ ወኢትዮጵያ አማን በአማን ሐዋርያ/፪/

መልክአ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
ሰላም ለጒርኤከ ኅሩመ መብልዕ ዘኮነ፤ ወእስከ ስቴ ማይ መነነ፤ ሶበ ረድኤተከ ርእዩ ወኪዳነከ እሙነ፤ ይቤሉከ ኲሉ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አቡነ፤ በኪዳንከ አሥራተ ንሥአነ።

ወረብ
አሥራተ ንሥአነ አሥራተ ንሥአነ/፪/
ገብረ መንፈስ ቅዱስ አሥራተ ንሥአነ/፪/

ዚቅ
በመንግሥተ ሰማያት ይነግሥ ምስሌከ፤ ኃጥእ ዘገብረ ተዝካረከ፤ ወጸውዓ ስመከ እንዘ ይብል አምላከ ተካየድከ፤ በእንተዝ ንሥአነ ለሕዝብከ፤ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አሥራተ በኪዳንከ።

መልክአ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
ሰላም ለአዕጋሪከ እለ ኢሖራ በፍናዊሃ፤ ለዛቲ ዓለም ዘዕበድ ጥበባቲሃ፤ ለኢትዮጵያ ምድርነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያሃ፤ ውስተ ገፀ ኲሉ ደወላ ዜና ነገርከ በዝኃ፤ ወእስከ ጽንፋ ለምድር ነቢብከ በጽሐ።

ዚቅ
ዝንቱሰ ብእሲ መምህርነ፤ ዘተፈነወ ውስተ ምድርነ፤ ይክሥት ብርሃነ ይፈውስ ዱያነ፤ ሐዋርያ ዘኮነ ወተሰምዓ ዜናሁ፤ ውስተ ኲሉ ምድር።

ወረብ
ዝንቱሰ ገብረ ሕይወት ተፈነወ ውስተ ምድርነ/፪/
ይክሥት ብርሃነ ይፈውስ ዱያነ ሐዋርያ ሐዋርያ ዘኮነ/፪/

አንገርጋሪ
ኮከብ ብሩህ ዘሠረቀ እምአቅሌስያ፤ ቤተ ክርስቲያን ዘንሰምያ፤ ኮኖሙ አበ ለሰብአ ግብፅ ወኢትዮጵያ፤ አማን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያ።

አመላለስ
አማን በአማን/፬/
ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያ/፬/

እስመ ለዓለም
ንጉሥኪ ጽዮን አሠርገዋ ለምድር በጽጌያት፤ ወለሰማይኒ በከዋክብት፤ ውእቱ ክብሮሙ ለቅዱሳን፤ ብርሃኖሙ ለመሐይምናን፤ ዘየአምር እምቅድመ ሕሊና፤ ዘይኄሊ ልብ አርአየ ኃይሎ፤ በላዕሌነ ወጸገወነ ሠናይቶ።

አመላለስ
ዘይኄሊ ልብ አርአየ ኃይሎ/፪/
በላዕሌነ ወጸገወነ ሠናይቶ/፪

ወረብ
ንጉሥኪ ጽዮን አሠርገዋ ለምድር በጽጌያት አሠርገዋ ለምድር/፪/
"ውእቱ ክብሮሙ"/፪/ ለቅዱሳን/፪/

@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery