መዝገበ ቅዱሳን
24.2K subscribers
1.97K photos
9 videos
6 files
26 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
ከዚህም በኋላ ወደ ሕዝብ መካከል ወጣ እያለቀሰ ጸለየ እንዲህም አለ አቤቱ በጌትነትህ ክብር ፊት የረከሰች እፌን እንዴት እገልጣለሁ በኃጢአት ብዛት የጠቆረ ፊቴንስ እንዴት ቀና አደርጋለሁ ነገር ግን እንደ ይቅርታህ ገናናነት እንደ ቸርነትህም ብዛት ሕዝብህን ይቅር በል አንተ መሐሪና ይቅር ባይ ነህና በዚያንም ጊዜ ብዙ ዝናም ወረደ እርሱም ጸሎቱንና ንስሓውን እግዚአብሔር እንደ ተቀበለው ኃጢአቱንም እንደ ተወለት አወቀ።

ከዚህም በኋላ አስቀድሞ እንደሚሠራው ተግቶ መጸለዩንና መሰገዱን አላጐደለም ነፍሱንም ዳግመኛ በኃጢአት ውስጥ እንዳትወድቂ ተጠበቂ በማለት ይገሥጻት ነበር ከዚህም በኋላ ዕድሜውን አድርሶ እግዚአብሔርንም አገልገሎ በሰላም አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ዕብሎይ_ገዳማዊ (የባሕታውያን አለቃ)

በዚህችም ዕለት የባሕታውያን አለቃ ኑሮው የመላእክትን ኑሮ የሚመስል ከትሩፋቱም የሃይማኖት ፍሬ የተገኘ የከበረ አባት ዕብሎይ አረፈ።

ቅዱስ አትናቴዎስም ከተሰደደበት በተመለሰ ጊዜ ወደ ቂሣርያ ኤጲስቆጶስ ወደ አባ ባስልዮስ ዘንድ መጥቶ ሁለቱም በአቡቂር ቤተ ክርስቲያን አደሩ በግብጽ ገዳማት ስለሚኖሩ ቅዱሳን እርስ በርሳቸው ሊነጋገሩ ጀመሩ አባት ሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስ አባ ጳኵሚስ አለ ብሎ ተናገረ አባ ባስልዮስም አባ እንጦንዮስና አባ አሞኒ አሉ አለ በእንዲህ ያለ ነገርም ከእርሳቸው የሚልቀውን ሊረዱ ሽተው ሳሉ የካቲት አምስት ቀን በመንፈቀ ሌሊት አባ አትናቴዎስ ራዕይን አየ።

እስከ ሰማይ የምትደርስ ታላቅ ዛፍ ነበረች ቅርንጫፎቿም እስከ ባሕር ደርሰዋል ብዙ ሰዎችም ከቅርንጫፎቿ በታች ተጠልለዋል በመካከሏም ታቦት መሠዊያ አለ ከዚህም ራእይ የተነሣ እየተደነቀ ሳለ እነሆ የመላእክት አለቃ የከበረ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ ይህን ያየኸውን ከባስልዮስ ጋር ተነጋገር እኔም እገልጥላችኋለሁ አለው።

እንዲህ ብሎ ተረጐመላቸው ያየሃት ዛፍ በግብጽ አውራጃዎች ውስጥ የሚሠራ ገዳም ነው ቅርንጫፎቿም መነኰሳት ናቸው መሠዊያውም መላእክት የሚጐበኙት የእግዚአብሔር ማደሪያ ይህ ርኵሳን መናፍስትን የሚሽር የሐዋርያት አለቃ የጴጥሮስ አምሳል የሆነ አባ ዕብሎይ ነው።

በእስክንድርያ የሚኖር አንድ የመቶ አለቃ የአባ ዕብሎይን ዜና ሰምቶ በረከቱን ይቀበል ዘንድ ወደ አባ ዕብሎይ እንዲልከው ሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስን ማለደው። እርሱም ከሰባት መነኰሳት ጋር ሰደደው እነርሱም አባ ኤስድሮስ፣ አባ ዮሐንስ፣ አባ ብሶይ፣ አባ አሞኒ፣ አባ ፊቅጦር፣ አባ አግሮኒኮስና አባ ካሉናስ ናቸው። በደረሱም ጊዜ አባ ዕብሎይ በደስታ ተቀበላቸው ከመነኰሳቱም ጋር የመጣው የመቶ አለቃ አንዲቷ ዐይኑ የታወረች ናት አባ ዕብሎይን በተሣለመው ጊዜ ዐይኑ ተከፈተች እርሱም በዓለም የሚያበራ ኮከብ ብሎ ተናገረ።

ዳግመኛም አባ ዕብሎይን ለመነው እንዲህም አለው ሚስቴ በለምጽ ደዌ ትጨነቃለች እርሷም በአስኬማህ የተማጸነች ናት እኔ ያገኘሁት ጸጋህ ለርሷም ይድረሳት። አባ ዕብሎይም በክብር ባለቤትም ጌታችን ስም ፈውስ ይሁንላት አለ ይህም ቃል ከአፉ እንደወጣ ድና ጤንነትን አገኘች።

በአንዲትም ዕለት አባ ዕብሎይ ከመነኰሳት መካከል ቁሞ ቤተ ክርስቲያን የምትሠራበትን ያስገነዝበን ዘንድ መድኃኒታችን ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይመጣልና አንዱም አንዱ ከእናንተ አይሒድ ከዚህ ይኑር እንጂ አላቸው።

ያን ጊዜም በዚያ ቦታ ብርሃን ወጣ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከከበሩ ደቀ መዛሙርቱና ከመላእክቶቹ ጋር መጣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕንፃዋ የሚመሠረትበትንም አሳያቸው።

እርሱም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ ፍቅርንም ያጸኑ ዘንድ ልጆቹን ይመክራቸው ነበር እየመከራቸውም ፊቱ ተለውጦ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ፊት ሆነ ሁለመናውም እንደሚነድ እሳት ሆነ እነርሱም ፈሩ። እርሱም ልጆቼ አትፍሩ እነሆ እኔ እሰናበታችኋለሁ አላቸው። ይህንንም ብሎ ነፍሱ ተመሠጠች በጎ መዓዛም ሸተተ ወዲያውኑ ዐይኑ ተገለጠና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ርዳኝ ነፍሴንም ወዳንተ ተቀበል አለ ይህንንም ብሎ አረፈ። የቀረውም ዜናው በጥቅምት ሃያ አምስት ቀን ተጽፎአል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት)
እግዚአብሔርም የአንዲት አይሁዳዊት ሴት ልቡናዋን ገለጠላት እርሷም በውስጥዋ ሽንገላና ቅናት ጠብ የሌለባት ናት የኦሪትንም ሕግ የምትጠብቅ ነበረች እርሷም ይህን ብርሃን አይታ ይህ ሰው እውነተኛ ነው አለች። ያን ጊዜም በላይዋ ብርሃን ወረደ እንዲህ ብላ ጮኸች እኔ በቅዱስ አጋቦስ ፈጣሪ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነ በጌታ ኢየሱስ የማምን ክርስቲያን ነኝ እግዚአብሔርንም ከፍ ከፍ እያደረገች ስታመሰግነው በደንጊያ ወገሩዋት ነፍሷንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ዘካርያስ

በዚህችም ቀን በምግባር ፍጹም የሆነ ተጋድሎውም የበዛ አባ ዘካርያስ አረፈ፡፡ እርሱንም ነፍሱ ከሥጋው በምትለይ ጊዜ አባ ሙሴ ወንድሜ ሆይ ምን ታያለህ አለው እርሱም ለእኔስ ዝምታ ይሻለኛል አለ ነፍሱም ስትወጣ አባ ኤስድሮስ ሰማይ ተከፍቶ አየ ልጄ ዘካርያስ ሆይ የመንግሥተ ሰማያት በር ተከፍቶልሃልና ደስ ይበልህ አለው በእንዲህም ያለ ሁኔታ አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት እና #መጋቤ_ሐዲስ_ሮዳስ)
እብሎይ ግን የቀድሞ ጸሎቱን አላቋረጠም እንዲህም እያለ እኔ ክፉ ባሪያ በየሰባቱ ሰባ ጊዜ በደልኩ ቸር ጌታ ሆይ መሐሪ አባት ሆይ ይቅር በለኝ የማይበድል ባሪያ የማይምር ጌታ የለምና። በዚችም ዕለት እስከ ሌሊቱ እኩሌታ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አደሩ እርሷም እሑድ ናት:: በዚያችም ጊዜ ከፊተኛው የሚበልጥ የሽቱ መዓዛ ሸተተ ገዳማዊውም ወንድሜ ዕብሎይ ና በውኃ ታጠብ ደስ ይበልህም በዚች ሰዓት ከተቀበልከው መከራ ታርፋለህና አለው:: በዚያንም ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለሁለቱም ቍርባኑን አቀበላቸው አባ ዕብሎይም አረፈ መላእክትም ነፍሱን ተሸክመው እስከ አርያም በረሩ።

ያ ገዳማዊም እኔ ሽማግሌ ነኝ ሥጋውን መሸከም አልችል የምቆፍርበትም የሌለኝ ምን አደርጋለሁ ብሎ የሚያስብ ሆነ በዚያንም ጊዜ ሁለት አንበሶች መጥተው ለሥጋው ሰገዱ መቃብሩንም ቆፍረው ሥጋውን እንደ ሰው ተሸክመው ወስደው ቀበሩት ገዳማዊውንም እጅ ነሱት እርሱም ባረካቸውና በሰላም ሔዱ።

ከዚህም በኋላ ያ ገዳማዊ የሚቀብረኝ አገኝ ይሆን ብሎ አሰበ ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ አትዘን ሥጋህን እኔ አስቀብራለሁ ያለ ሦስት ቀንም አልቀረህም ወዳንተም ሦስት ሰዎችን እልካለሁ የበግ ጠባቂው የአባ እብሎይን ገድል ንገራቸው እነርሱም ለሌሎች ይንገሩ ከእግዚአብሔር ምሕረት ተስፋ እንዳይቆርጡ በኃጢአት ለወደቁ አለኝታ ይሆን ዘንድ።

በማግሥቱም ሦስት ሰዎች መጡ እርሱም የበግ ጠባቂውን የአባ ዕብሎይን ተጋድሎ ነገራቸው እነርሱም እጅግ አድንቀው ጻፉት ከገዳማዊውም ዘንድ እስከ ሦስት ቀን ተቀመጡ ከዚህም በኋላ ገዳማዊው ተነሥቶ ጸለየ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ እነዚያ ሁለት አንበሶችም መጡ መቃብርንም ቆፍረው እንደ ሰው ወስደው ቀበሩትና ከእነዚያ ሦስት ሰዎች ጋር ተጓዙ ወደ አስቄጥስ ወደ አባ መቃርስ ገዳም እስከሚአደርሷቸው መርተው ወሰዱአቸው ሰዎቹም የሆነውን ሁሉ ለመነኰሳቱ ነገሩአቸው። እነርሱም እጅግ አደነቁ የበግ አርቢው የአባ ዕብሎይን ገድል ጻፉ ሁል ጊዜም በእሑድ ዕለት የሚያነቡት ሆኑ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_አሞኒ

በዚህችም እለት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጻድቃን አቡነ አሞኒ የተወለዱበት በዓልና ለልጃቸው አቡነ ዮሐኒም መታሰቢያቸው ነው፡፡ አባታችን የካቲት5 ቀን አክሱም ውስጥ ሲወለዱ ሰይጣናት የወላጆታቸውን ቤት ከበው በማየታቸው እንደተወለዱ በእጃቸው ቢያመለክቱ በአንድ ጊዜ 60 ሰይጣናት ተሸንፈው እንጢስ በነው ጠፍተዋል። አሞኒ ማለት አሸናፊ ማለት ነው። አባ አሞኒ የራስ ፀጉራቸው ልብስ መጎናጸፊያ ሆኖቸው የኖሩ ታላቅና ቀደምት አባት ናቸው።

በደመና ተጭነው ኢየሩሳሌም ደብረ ዘይት ድረስ በመሄድ ከአባ ዕብሎይ ጋር ተገናኝተው ብዙ ምሥጢርን አውርተዋል። አባ ዮሐኒንያ ሳደጉት አስተምረው ያሳደጓቸው አባ አሞኒ ናቸው፡፡ የእናቱን ጡት ፈጽሞ ጠብቶ የማያውቀውን የመንፈስ ቅዱስ ልጃቸውን አባ ዮሐኒን እሳቸው እያጫወቱት የታዘዘ አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው ቶራ (ሰሳ) እያጠባችው ነው ያደገው፡፡

አባ አሞኒ ልጃቸው አባ ዮሐኒ አድጎ 12 ዓመት ሲሆነው ከዚህም በኋላ ዲቁና ሊያሾሙትና አክሱም ጽዮን ወስደው ሊያስባርኩት ቤተ ካህናት ከተባለው ቦታ ይዘውት ሲሄዱ ልዩ ስሙ ሲሂታ ከሚባለው ቦታ ሲደርሱ ከወገባቸው በላይ እራቁታቸውን የሆኑ እንስራ የተሸከሙ ዐሥር ሴቶች አገኙ፡፡ አባ ዮሐኒም አባታቸውን "አባቴ እነዚህ ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ጽጉራቸው የረዘመ ምንድን ናቸው? እንደ እኛ የሆኑ መስህታን የሚባሉት እነዚህ ናቸውን?" አሏቸው፡፡ አባ አሞኒም "አይደሉም ልጄ ዝም ብለህ ሂድ" አሏቸው፡፡ በኋላ ግን ትዝ ሲላቸው "በዱር እንስሳት ያሳደኩት ልጄ ወንድና ሴት ለይቶ ሲያውቅ በዚያው ሊሳሳት አይደልምን?" ብለው በማሰብ ዲቁናና ክህነቱ ይቅርበት ብለው ተመልሰው ወደ በዓታቸው ይዘውት ገቡ፡፡ ከዚህም በኋላ አባ አበይዶ ወደ አባ አሞኒ መጣና እሳቸውን ከአባ ዮሐኒ ጋር እያገለገሏቸው ተቀመጡ፡፡ ዮሐኒ እየጻፈ አበይዶ የሚጻፍበትን ቆዳ እያዘጋጁ ሦስቱም በአንድነት በተጋድሎ መቀመጥ ጀመሩ፡፡

አባ ዮሐኒ ሃያ ዓመት አባ አሞኒ ደግሞ አርባ ዓመት በሆናቸው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸውና "አሞኒ ሆይ ከእንግዲህስ እግዚአብሔር ወደኔ ና ብሎሃል" አላቸው። እሳቸውም ልጆቻቸውን አባ ዮሐኒንና አባ አበይዶን ጠርተው "በሉ እንግዲህ እኔ ወደ እግዚአብሔር መሄዴ ነውና ጸልዩልኝ" አሏቸው፡፡ ከማረፋቸውም በፊት አባ ዮሐኒን ለብቻቸው ጠርተው "አንተ አባ ዮሐኒ ካሁን በፊት ሲሂታ ላይ ያየሃቸው ሴቶች ናቸው፣ አዳምንም ከገነት ያስወጡ ናቸው፡፡ ወደፊትም እንደ እነርሱ ያለ የደረሰብህ እንደሆነ ካለህበት ገደል ተወርውረህ ውደቅመ በባሕር ውስጥ ጥለቅ" ብለው ነግረዋቸው ዕለት ኅዳር5 ቀን በሰላም ዐረፉና ወደ ጠራቸው እግዚአብሔር ሄዱ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት እና #መዝገበ_ቅዱሳን)
#የካቲት_6

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የካቲት ስድስት በዚህች ቀን ሊቀ ጳጳሳት የከበረ #አባት_ቅዱስ_አቡሊዲስ ሥጋው ከባሕር የወጣበት ነው፣ ጌታን ሽቱ ለቀባችው #ቅድስት_ማርያም_እንተ_ዕፍረት የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው፣ የከበሩ #አቡቂርና_ዮሐንስ_ሦስት_ደናግልም_ከእናታቸው_ከአትናስያ ጋር በሰማዕትነት ሞቱ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_አቡሊዲስ

የካቲት ስድስት በዚህች ቀን የዓለሙ ሁሉ መምህር የሆነ የሮሜ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት አቡሊዲስ ሥጋው ከባሕር የወጣበት ነው።

ይህም የከበረ በእውቀቱም ፍጹም የሆነ ሰው ነው ከአባት አውክዮስም በኋላ ለሮም ሀገር ሊቀ ጳጳሳት ይሆን ዘንድ መንፈስቅዱስ መረጠው ይህም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ከላድያኑ በተሾመባት በመጀመሪያ ዓመት ነው ሕዝቡንም ከአረማውያን ጠባይ የሚጠብቃቸው የሚያስተምራቸውና በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት የሞያጸናቸው ሆነ።

በከሀዲውም ንጉሥ በከላድያኖስ ዘንድ ዜናው ተሰማ ይህንንም የከበረ አቡሊዲስን ይዞ በብዙ ግርፋትና ድብደባ አሠቃየው ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ በእግሮቹ ውስጥ ታላቅ ደንጊያ አሥሮ ከጥልቅ ባሕር የካቲት አምስት ቀን አሰጠመው። ማግሥትም ሲሆን የካቲት ስድስት በዛሬዋ ቀን የዚህ አባት ሥጋው በውኃ ላይ ተንሳፎ ተገኘ ደንጊያውም በእግሮቹ ውስጥ እንደታሠረ ነበር አንድ ምእመን ሰው ወስዶ በርሱ ዘንድ አኖረው በከበሩ ልብሶችም ገንዞ ሠወረው። ወሬውም በሮሜ አገሮች ሁሉ ተሰማ ንጉሡም ሊአቃጥለው ፈልጎት ነበር ግን አላገኘውም ያ ሰው ሠውሮታልና።

ይህም የከበረ አባት ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ ድርሳናትን ደርሶአል ከእርሳቸውም ስለ አካላዊ ቃል ሰው መሆንና ከኃጢአት በቀር በሥራው ሁሉ አንድ ባሕርይ ሰለ መሆኑ የደረሰው አለ። ዳግመኛም እግዚአብሔር የሚወደውን ስለ መሥራት የደረሳቸው ተግሣጻትና ትምህርቶች አሉ ስለ ቤተ ክርስቲያንም ሕግ ሠላሳ ስምንት መመሪያዎችን ሠርቷል እሊህም በሁሉ አብያተ ክርስቲያን ይገኛሉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ማርያም_እንተ_ዕፍረት

በዚህችም ቀን ጌታን ሽቱ ለቀባችው ማርያም የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው። ይችም ቅድስት አስቀድማ ኑሮዋን በዝሙት ያሳለፈች ኃጢአተኛ ነበረች። እርሷም ጐልማሶችን ወደርሷ ትማርካቸው ዘንድ በየራሱ በሆነ ሽልማትና ጌጥ ትሸለም ነበር።

በአንዲትም ዕለት እንደ ልማድዋ ተሸልማ አጊጣ ሽቱም ተቀብታ ፊቷን በመስታዋት ተመለከተች የጉንጯ ቅላትና ደም ግባቷ የዓይኗም ወገግታና ጥራት ማማሩን አይታ እያደነቀች አንድ ሰዓት ያህል ቆየች ከዚህም በኋላ በጎ ኀሳብ በላይዋ መጣ ሞትንና የዚህን ዓለም ማለፍ አሰበች።

የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስም ኃጢአተኞችን እንደሚቀበልና ኃጢኣትንም እንደሚአስተሰርይ ሰምታ ገንዘቧን ወስዳ የአልባስጥሮስን ሽቱ ገዝታ በስምዖን ዘለምጽ ቤት ለምሳ ተቀምጦ ሳለ ወደ ጌታችን ሔደች።

ከእግሩ በታችም ሰግዳ ያንን ሽቱ ቀባችው እግሮቹን በዕንባዋ አጠበችውና በራስዋ ጠጉር ወለወለችው ጌታችንም የፍቅርዋን ጽናት አይቶ ኃጢኣቷን በደሏን ተወላት የመንግሥት ወንጌልም በሚሰበክበት ይህን ያደረገችውን እንዲአስቡ አዘዘ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_አትናስያና_3ቱ_ሰማዕታት_ልጆቿ

በዚህችም ዕለት የከበሩ አቡቂርና ዮሐንስ ሦስት ደናግልም ከእናታቸው ከአትናስያ ጋር በሰማዕትነት ሞቱ። የእሊህም ስማቸው ቴዎድራ ትርጓሜው የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ሁለተኛዋ ቴዎፍና ትርጓሜውም የእግዚአብሔር ሃይማኖት ሦስተኛይቱም ቴዎዶክስያ ትርጓሜውም የእግዚአብሔር ምስጋና የእናታቸውም አትናስያ ትርጓሜው ሕይወት የሆነ ነው።

ይህም የከበረ አቡቂር ከታናሽነቱ በገድል ተጠምዶ የሚኖር መነኰስ ነው የከበረ ዮሐንስ ግን ከንጉሥ ሠራዊት ውስጥ ወታደር ነበር የእነርሱም ሀገራቸው እስክንድርያ ሲሆን የሚኖሩት በአንጾኪያ ነው በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም ፊት ቁመው ከእሊህ ደናግል ከእናታቸው ከአትናስያም ጋር በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ። እርሱም ከወዴት እንደሆኑ ጠየቀ ከእስክንድርያ አገር እንደሆኑ በተረዳ ጊዜ ወደዚያ ይወስዷቸው ዘንድ አዘዘ።

ወደ እስክንድርያ በደረሱ ጊዜ በመኰንኑ ፊት ቁመው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ መኰንኑም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ማሠቃየትንም በደከመ ጊዜ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የከበረች አትናስያም ደናግል ልጆቿን በከበረ ስሙ ምስክር ሁነው ከሞቱ ለሰማያዊ ሙሽራ ክርስቶስ እነርሱ ሙሽሮቹ እንደሚሆኑ በማስረዳት ታጸናቸውና ታስታግሣቸው ነበር እንዲሁም የከበረ አቡቂር በከበረች ሐዋርያዊት ቴክላ ላይ የደረሰውን መከራ ይገልጥላቸውና ያጸናቸው ነበር።

ወታደሮችም ለባለ ሰይፍ በማከታተል አንዲቱን ከአንዲቱ በኋላ የሚያቀርቡ ሆኑ ከዚያም እናታቸውን የከበሩ አቡቂርና ዮሐንስንም ቆረጡ መኰንኑም ሥጋቸውን ለአራዊትና ለአዕዋፍ ይጥሉ ዘንድ አዘዘ ምእመናንም ሥጋቸውን በሥውር ወሰዱ በክብርም ገነዙአቸው የመከራውም ዘመን እስቲያልፍ በሣጥን አድርገው ሠወሩአቸው።

ከዚህም በኋላ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶላቸው ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ ከእርሳቸውም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት)
ይህም አባት ቴዎድሮስ በገድል የተጠመደ ሆነ መልኩም የሚያምር ነው በሰውነቱም ላይ ከውስጥ ማቅ በመልበስ በላዩ የብረት ልብስ መንቈር ይለብስ ነበር በቅንነቱና በትሕትናው ፍጹም ሆነ። በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ተመርጦ በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ። የክርስቶስንም መንጋዎች በበጎ አጠባበቅ ጠበቀ ሁልጊዜ መጻሕፍትን በማንበብ ያስተምራቸው ነበር ይልቁንም በሰንበትና በበዓላት ቀን።

የሹመቱም ዘመን ጸጥታና ሰላም ነበረ ቤተ ክርስቲያንም በሰላም ኖረች በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበርም ላይ ዐሥራ አንድ ዓመት ተኩል ከኖረ በኋላ በሰላም አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_አብዱልማዎስ_ገዳማዊ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ገዳማዊው ጻድቁ አብዱልማዎስ አረፉ። ጻድቁ ግብጻዊ ሲሆኑ በበርሃ ሰው ሳያዩ ለ70 ዓመታት በቅድስና ኑረዋል:: በጊዜውም እግዚአብሔር አባ አብዱልማዎስን ወደ አባ ዕብሎይ ልኳቸው ነበር:: ሁለቱ ተገናኝተው አብረው ለ3 ቀናት ሲቆዩ ቅዱስ መልአክ እየተገለጸ አጽናንቷቸዋል:: ከሥውራን ማኅበርም ተቀላቅለው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለዋል::

አባ ዕብሎይ ሲያርፍ አንበሶች እያገዟቸው ቀብረዋቸዋል:: እርሳቸውም "እኔን የሚቀብረኝ ስጠኝ" ብለው ጸልየው ነበርና 3 ገዳማውያን መጥተውላቸዋል:: የካቲት 5 ቀን አባ ዕብሎይን ገንዘው ቀብረው በ3ኛው ቀን አርፈዋል::

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
በዚህች ዕለት በትሩፋቱ ፍጹም የሆነ ታላቅ አረጋዊ የገዳመ ሲሐቱ ኤልያስ አረፈ። የሚያረጋጋው በትሩፋቱ ፍጹም የሆነ አረጋዊ መነኵሴ እንዲልኩለት በመለመን ጻድቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ወደ ገዳመ ሲሐት በላከ ጊዜ ይህን በትሩፋቱ ፍጹም የሆነ ኤልያስን ላኩለት ስለርሱም እንዲህ ብለው ጻፉ "ንጉሥ ሆይ እነሆ በሥራው ኤልያስን የሚመስል ኤልያስ የሚባል ጻድቅ ሰው ልከንልሃል።"

ወደ ንጉሥም በደረሰ ጊዜ ንጉሥ እንዲህ አለው አንተ በገድልህ ነቢይ ኤልያስን እንደምትመስል መነኰሳቱ ስለአንተ ወደእኔ ልከዋል። አረጋዊውም በየውሀትና በትሕትና እንዲህ አለ ፦ "ጻድቅ ንጉሥ ሆይ ይቅርታ አድርግልኝ ሰው ሁሉ በጠባዩና በሥራው ይታወቃል የኤልያስም ገድሉ እንዲህ ነው ስለ ደግነቱ ምግቡን ቊራዎች ያመጡለት ነበር እኔ ግን ምግቤን በፀሐይ ውስጥ ባሰጣው ቊራ ይዞት ይሔዳል" ንጉሡም ሰምቶ ከቃሉ ጣዕም የተነሣ አደነቀ።

ዳግመኛም አባቴ ሆይ ለምን እግዚአብሔር ልጅ አልሰጠኝም አለው አረጋዊውም በምድር ላይ ሃይማኖት የሚከፋፈልበት ዘመን ይመጣል ከመናፍቃን ጋር አንድ እንዳይሆን ስለዚህ እግዚአብሔር ልጅን አልሰጠህም አለው።

ንጉሡም ብዙ ገንዘብን ሊሰጠው ወደደ እርሱ ግን አልተቀበለም። ወደ በአቱም እስከተመለሰ ድረስ እህል እንዳልቀመሰ ስለርሱ ተነገረ በሰላምም አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት)
በሶርያ አገርም አስተማረ በፊታቸው ተአምራትን በአደረገ ጊዜ በትምህርቱ ብዙዎች አመኑ። ዳግመኛም ወደ ታናሹ ቴዎዶስዮስ ንጉሥ ሒዶ በቀናች ሃይማኖት አጸናው ንጉሡም ብዙ ገንዘብን ሰጠው እርሱ ምንም ምን አልወሰደም በአንጾኪያም አገር በኤጲስቆጶሳቱ ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዲኖረው ንጉሥ ጻፈለትና ኀቲም ቀለበቱን ሰጠው።

በከሀዲው ንስጥሮስ ምክንያት ሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት በኤፌሶን ከተማ በተሰበሰቡ ጊዜ ከእሳቸው ጋር ይህ ቅዱስ አለ። ከእርሳቸውም ጋር ንስጡርን አወገዘው ዳግመኛም በአንጾኪያ አገር ያሉ መኳንንት መሳፍንት ሹማምንት ሁሉም ይታዘዙለት ዘንድ ንጉሥ ደብዳቤን ጻፈለት እርሱም በጎ ሥራ እንዲሠሩ በሃይማኖት እንዲጸኑ የሚያዝዝ ደብዳቤ በመጻፍ በንጉሥ ኀቲም ቀለበት እያተመ ለሀገሮች ሁሉ የሚልክ ሆነ።

ክፋዎች ሰዎችም ጠሉት በንጉሥም ዘንድ ነገር ሠሩበት እንዲህም አሉት እነሆ አባ በርሱማ እንደ ዓለም ሰው ሁኖ ይበላል ይጠጣል መልካም ልብስንም ይለብሳል ንጉሥም ሰለ አባ በርሱማ የተነገረውን ያረጋግጥ ዘንድ ከባለሟሎቹ አንዱን ላከ።

የንጉሡም ባለሟል ወደ አባ በርሱማ በደረሰ ጊዜ በእርሱ ላይ ከተነገረው ምንም ምን ያገኘው የለም ከዚህም በኋላ ወደ ንጉሥ ወሰደው ንጉሥም ቀድሞ ከሚያውቀው ከመንፈሳዊ ሥራው ልውጥ ሆኖ ያገኘው ነገር የለም ንጉሡም ታላቅ ክብርን አከበረው ወደ ቦታውም መለሰው።

መናፍቁ ንጉሥ መርቅያንም የኬልቄዶንን ጉባኤ በሰበሰበ ጊዜ የንጉሥ አማካሪዎች አባ በርሱማን እንዳያስመጣ ንጉሡን መከሩት እንደማይፈራና እንደማያፍር ለሰው ፊትም እንደማያዳላ ተከራክሮ ረትቶ እንደሚያሳፍራቸውም ስለሚያውቁ ነው።

አንዱን ክርስቶስን ወደ ሁለት የከፋፈሉበት ይህ ጉባኤ በተፈጸመ ጊዜ የከበረ አባ በርሱማ ተጣላቸው ነቀፋቸው ቃላቸውንም በመሻር አወገዛቸው እነርሱም ወደ ንጉሥ ወንጅለው በጽሑፍ ከሰሱት ንጉሡም ልኮ ወደርሱ አስቀረበው ግን በላዩ ስለ አደረ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ ሊቃወመው አልቻለም በሊቁ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላይ ሰለ አደረገችው ክፋት ንግሥቲቱን ረገማት ከጥቂት ቀንም በቀር አልኖረችም በክፉ አሟሟትም ሞተች።

ከዚህም በኋላ መናፍቃን የሚቃወሙት ሆኑ ምእመናን እንዳይታዘዙለት ወደ ሀገሮች ሁሉ ጽፈው የሚልኩ ሆኑ እነርሱ ግን አልተቀበሏቸውም ለእርሱ መታዘዛቸውንም አልተዉም። ዳግመኛም በጐዳና ሸምቀው ይገድሉት ዘንድ ሁለት መቶ መናፍቃን ሰዎች ከመናፍቃን ኤጴስቆጶሳት ጋር ተስማምተው ወደ እርሳቸው እንዲመጣና በአንድነት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚሔዱ ሁነው ላኩበት መጥቶም አብሮ በተጓዘ ጊዜ ደንጊያዎችን አንሥተው ጣሉበት ደንጊያዎቻቸውም ወደ ራሳቸው የሚመለሱ ሆኑ በፍርሃትም ከእርሱ ሸሹ።

እግዚአብሔርም ከዚህ ዓለም እሥረኛነት ሊአወጣው በወደደ ጊዜ መልአኩን ወደርሱ ልኮ ከአራት ቀን በኋላ ከዓለም እንደሚፈልስ ነገረው በዚያንም ጊዜ በዙሪያው ወዳሉ አገሮች ምእመናንን ያጽናናቸው ዘንድ ረድኡን ላከው እርሱም ሲዞር የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራስ ወደምትኖርበት ቦታ ደረሰና የከበረች የቅዱስ ዮሐንስን ራስ እጅ ነሣት ስለ ከሀዲው ስለ ንጉሥ መርቅያን በማልቀስ ለመነ። እንዲህ የሚልም ቃል ከመጥምቁ ዮሐንስ ራስ ወጣ አባ በርሱማ ወደ እግዚአብሔር ስለ ከሰሰው ያ መርቅያን ሙቷልና አትፍራ። የከበረ አባ በርሱማ ረድኡን ባረከውና በሰላም አረፈ።

ከበአቱም ደጃፍ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን መሰሶ ተተክሎ ታየ። ምእመናንም ሁሉ ከሩቅ አይተው ወደርሱ መጡ አርፎም አገኙት። ከሥጋውም ተባረኩ በላዩም አለቀሱ ከእርሱም ስለመለየታቸው እጅግ አዘኑ እንደሚገባም አየዘመሩና እያመሰገኑ ገንዘው በመቃብር አኖሩት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጳውሎስ_ሶርያዊ

በዚህችም ዕለት የከበረ ሶርያዊ ጳውሎስ በሰማዕትነት ሞተ፡፡ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ የሶርያ ሰዎችና በእስክንድርያ ከተማ የሚኖሩ ነጋዴዎች ናቸው ከዚህም በኋላ በእስሙናይን ከተማ የሚኖሩ ሆኑ።

ወላጆቹም ሲሞቱ ብዙ ገንዘብ ተዉለት ከዚህም በኋላ ከሀድያን ነገሥታትና መኳንንት በክርስቶስ የሚያምኑ ምእመናንን እንደሚያሠቃዩአቸውና እንደሚገድሏቸው ሰማ በዚያንም ጊዜ ተነሥቶ ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች በተነ። ከዚህም በኋላ የወደደውን መንገድ ይመራው ዘንድ ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየ ጌታችንም መልአኩን ሱርያልን ላከ እርሱም በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም የሚደርስበትን ሥቃይ ሁሉ ነገረው እነሆ ከአንተ ጋር እንድኖር እንዳጽናናህም እግዚአብሔር አዞኛልና አትፍራ አለው።

በዚያንም ጊዜ ተነሥቶ ወደ እንዴናው ከተማ ሔደ በመኰንኑም ፊት ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ልብሱን አራቁተው ይገርፉት ዘንድ አዘዘ።

ይህንንም አደረጉበት ከዚህም በኋላ በጐኖቹ ውስጥ መብራቶችን አስገብተው ለበለቡት እሳት ግን አልነካችውም መኰንኑም ለጣዖት እንዲሰግድ ብዙ ገንዘብ አመጣለት የተመሰገነ ጳውሎስም ወላጆቼ ሲሞቱ ዐሥራ ሰባት የወርቅ መክሊት ትተውልኝ ነበር። ስለ ክብር ባለቤት ክርስቶስ ፍቅር ትቼ ለድኆች መጸወትኩት ወደዚህ ወደተናቀ ገንዘብህ እንዴት እመለሳለሁ አለው።

መኰንኑም ሰምቶ ብረቶችን በእሳት አግለው በአፉና በጆሮዎቹ እንዲጨምሩ አዘዘ ይህንንም አደረጉበት ሱርያል መልአክም ወርዶ ዳሠሠውና አዳነው ሁለተኛም እባቦችን በላዩ ሰደዱ አልነኩትም ምላሱንም ቆረጡ ጌታችንም አዳነው።

መኰንኑም ወደ እስክንድርያ ከተማ በሚሔድ ጊዜ ከእርሱ ጋር ወሰደው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመርከብ ውስጥ ተገለጠለትና አጽናናው የዚህም ቅዱስ ኤሲ የሚባል ወዳጅ አለው እኅቱ ቴክላም። ጌታችንም ሥጋው ከሥጋቸው ነፍሱ ከነፍሳቸው ጋር እንደሚሆን ነገረው ያን ጊዜ እሊህ ቅዱሳን በእስክንድርያ ከተማ በእሥር ቤት ነበሩ የከበረ ጳውሎስም ወደርሳቸው በደረሰ ጊዜ እርስበርሳቸው ተሳሳሙ በመገናኘታቸውም ነፍሳቸው ደስ ብሏት እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

መኰንኑም ወደ እንዴናው ከተማ በሚመለስ ጊዜ የቅዱስ ጳውሎስን ራስ ቆርጠው ሥጋውን ከጥልቅ ባሕር ወረወሩ የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ ምእመናንም ሥጋውን በሥውር ወስደው በአማሩ ልብሶች ገነዙት በእነርሱም ዘንድ አኖሩት ከእርሱም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት እና #ከገድላት_አንደበት)
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት እና #ገድለ_ሐዋርያት)
#የካቲት_11

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የካቲት ዐሥራ አንድ በዚች ቀን የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት #ቅዱስ_በላትያኖስ በሰማዕትነት ሞተ፣ ተጋዳዩ ባለ አንበሳው #ቅዱስ_አውሎግ አረፈ፣ የአባ ስልዋኖስ ረድእ #ቅዱስ_አባ_በትራ አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#በላትያኖስ_ሰማዕት

የካቲት ዐሥራ አንድ በዚህች ቀን የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት በላትያኖስ በሰማዕትነት ሞተ።

ይህም ቅዱስ ብልህና አዋቂ የሆነ ታላቅ ተጋድሎን የሚጋደል ነው በሮሜ ሀገርም ሊቀ ጵጵስና ተሹሞ በቅዱስ ጴጥሮስ ወንበር ላይ ዐሥራ ሁለት ዓመት በሰላም ኖረ። ሕዝቡን የቀናች ሃይማኖትን እያስተማራቸው ሳለ መኰንኑ ፊሊጶስ በንጉሥ ቀላውዴዎስ ላይ ተነሥቶ በገደለው ጊዜ በርሱ ፈንታ ነገሠ በምእመናንም ላይ ታላቅ መከራን አመጣ በዚህ በንጉሥ ዳኬዎስ እጅ ብዙዎች በሰማዕትነት ሞቱ።

በዘመኑም ሰባት ሰዎች ከእርሱ ሸሹ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት ተኝተው ነቁ እርሱም በኤፌሶን ከተማ መስጊድ ሠርቶ በውስጡ ጣዖታትን አኖረ ሰዎችን ሁሉ ለጣዖታት እንዲሠዉ አስገደዳቸው ለጣዖታት ያልሠዉትንም ገደላቸው።

ይህ የከበረ በላትያኖስም የጣዖታት አምልኮን እንደሚቃወም ሕዝቡም በክብር ባለቤት በክርስቶስ ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ እንደሚያስተምር ንጉሥ በሰማ ጊዜ ወደ ሮሜ አገር ልኮ ወደ ኤፌሶን ከተማ አስመጣውና ለጣዖታት እንዲሠዋ ለመነው።

እርሱ ግን ቃሉን አልሰማም ተሣለቀበት አማልክቶቹንም ረገመ እንጂ። ንጉሡም ተቆጣ አንዲት ዓመት ያህልም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ በሰይፍ ራሱን ቆረጠው የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_አውሎግ_አንበሳዊ

በዚህችም ዕለት ተጋዳዩ ባለ አንበሳው አውሎግ አረፈ፡፡ የዚህ ቅዱስ ወላጆች ከሀገረ ንጽቢን የሆኑ በበጎ ሥራ ፍጹማን በወርቅና በብርም የበለጸጉ ናቸው። ለልጃቸውም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ አስተማሩት ከጥቂት ቀኖች በኋላ ወላጆቹ ብዙ ገንዘብን ትተውለት ሞቱ።

በአንዲትም ዕለት አውሎግ ያለህን ገንዘብህን ሁሉ ሽጠህ ለድኆች ሰጥተህ መከራ መስቀልህን ተሸክመህ ና ተከተለኝ የሚለውን የከበረ የወንጌልን ቃል አሰበና ወዲያውኑ ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች በትኖ ወደ አባ አውሎጊን ሔደ እርሱም በደስታ ተቀበለው።

ስለ ርሱ እንዲህ የሚለውን ራእይ አይቶ ነበር እነሆ ወዳንተ ጐልማሳ ይመጣል ተቀበለውና ከሚያገለግሉ መነኰሳት ጋር ቀላቅለው እየፈተነውም ሦስት ዓመት ያህል ኖረ ፍጹም የሆነ ቅድስናውንም በአየ ጊዜ የምንኵስናን ልብስ የመላእክትንም አስኬማ አለበሰው።

ከሰንበትም እስከ ሰንበት እየጾመ በብዙ ተጋድሎ ኖረ ምግቡም እንጀራና ጨው ነበረ በቀንና በሌሊትም ሰባት መቶ ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን ከስግደት ጋር ይጸልያል በዚህም ተጋድሎ አርባ ዓመት ኖረ።

ከዚህም በኋላ ያሰናብተው ዘንድ መምህሩ አባ አውሎጊንን ማለደውና ወደ በረሀ ሔደ ከአንዲት ታናሽ ዋሻ ውስጥም ገብቶ እየተጋደለ ኃምሳ ዓመት ኖረ። ለፍላጎቱም የሚያገለግሉት ሁለት አንበሶችን እግዚአብሔር ሰጠው በአንዲትም ዕለት ታመመ አንበሶቹንም እጠጣ ዘንድ የሞቀ ውኃ እሻለሁ አላቸው። አንዱ አንበሳም ወደ ተራራ ሒዶ እረኛ አግኝቶ ወደ አባ አውሎግ አመጣው በአየውም ጊዜ ሰገደለትና አባቴ ሆይ ምን ትሻለህ አለው። እርሱም የሞቀ ውኃ ታጠጣኝ ዘንድ እሻለሁ አለው እንዳለውም አደረገለት ከዚህም በኋላ አንበሳው እረኛውን ወደቦታው መለሰው።

ያም እረኛ ለእግሩ ተረከዝ ዓለሙ ሁሉ መጠኑ የማይሆን ጻድቅ ሰውን አገኘሁ ብሎ ለሰው ሁሉ ተናገረ በሰሙ ጊዜም ሰዎች ሁሉ ወደርሱ ተሰበሰቡ በሽተኞችንም ሁሉ አመጡለትና ፈወሳቸው።

በዚያ ወራትም መምህሩ አባ አውሎጊን ጣዖትን የሚያመልኩ የፋርስ ሰዎችን ወደ ቀናች ሃይማኖት ለመመለስ ወደ ፋርስ ሀገር ሊሔድ ፈለገ ዳግመኛም ልጁ አውሎግን ከእርሱ ጋር ሊወስደው ወደርሱ መልእክተኛ ሊልክ ሽቶ ሳለ መንፈስ ቅዱስ አንበሳውን አስገነዘበውና አጽፉንና ወንጌሉን አንሥቶ ተሸከመ። አባ አውሎግንም ጕዞን አመለከተው ተነሥቶም አንበሳውን ተከትሎ ወደ መምህር አውሎጊን ደረሰ እርሱም በደስታ ተቀበለው።

ሲጓዙም ከጤግሮስ ወንዝ ደረሱ ውኃውም ተከፍሎላቸው ተሻገሩ ወደ ሀገሩም ውስጥ በደረሱ ጊዜ አስተማሩአቸው ወደ ቀናች ሃይማኖትም መለሷቸውና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው።

በአንዲትም ዕለት ደግሞ ቅዱሳን በተራቡ ጊዜ ምግባቸውን ይፈልጉላቸው ዘንድ አባ አውሎግ አንበሶችን አዘዘ ሒደውም እንጀራ በአህያ ላይ ጭኖ የሚጓዝ ሽማግሌ አገኙ ሕፃንም ከእንጀራው ጋር አለ ።

አህያውንም ወደ ቅዱሳን አመጡት ከድንጋጤም የተነሣ ብላቴናው ሞተ ቅዱሳንም ጸልየው ሕፃኑ ድኖ ተነሣ ቅዱሳንም ተመገቡ አንበሶችም አህያውን ከእንጀራውና ከሕፃኑ ጋር ወደ ሽማግሌው መለሱት። ከዚህም በኋላ አባ አውሎግ ወደ በዓቱ ተመለሰና ጥቂት ታሞ አረፈ በታላቅ ክብርም ተቀበረ እነዚያ አንበሶችም መቃብሩን እየጠበቁ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖሩ ከዚያም በኋላ ወደ ዱር ገቡ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_በትራ

በዚህችም ቀን የአባ ስልዋኖስ ረድእ አባ በትራ አረፈ። ይህም ቅዱስ በደብረ ሲና ካለች በዓቱ በነበረ ጊዜ ትርኅምትን ይጠብቅ ነበር በራትም ጊዜ ለሥጋው የሚያሻውን ይመገባል።

ፈርኑ በሚባል አገር ላይ ኤጲስቆጶስ በአደረጉት ጊዜ ትርኅምትን በማብዛት ሰውነቱን እጅግ አደከመ ደቀ መዛሙርቱም አባታችን ሆይ በገዳም በበኣትህ በነበርክ ጊዜ ትርኅምትን እንዲህ አላበዛህም ነበር አሉት ይህም አባት እንዲህ አላቸው "ያን ጊዜ በገዳም በችግር ውስጥ ነበርኩ ዛሬ ግን ከብዙዎች መካከል በአንድነት አለሁ የምሻውም ሁሉ ብዙ አለኝ ነገር ግን ሥጋዬን ቀጥቼ ብገዛው ይሻላል እንዲህም እየተጋደለ ኖረ ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት)
#የካቲት_12

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የካቲት ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ወደ ረዓይታዊ ወደ ሶምሶን ተልኮ ኃይልን ሰጥቶት ጠላቶቹን ድል እንዲያደርግ የተራዳበት መታሰቢያ ነው፣ ተጋዳይ የሆነ የከበረ አባት #አባ_ገላስዮስ አረፈ፣ ታላቁ አባት #አቡነ_ሠርጸ_ጴጥሮስ አረፉ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#የመላእክት_አለቃ_ቅዱስ_ሚካኤል

የካቲት ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሚካኤል ወደ ረዓይታዊ ወደ ሶምሶን ተልኮ ኃይልን ሰጥቶት ጠላቶቹን ድል እንዲያደርግ የተራዳበት መታሰቢያ ነው።

በዚች ዕለት የከበረ ሚካኤልን እግዚአብሔር ወደ ረዓይታዊ ወደ ሶምሶን ላከው የፍልስዔም ሰዎች ሊገድሉት በጠላትነት በተነሡበት ጊዜ ድል እስከ አደረጋቸውና እስከ ገደላቸው ድረስ ረዳው ኃይልንም ሰጥቶ በአህያ መንጋጋ ከእርሳቸው አንድ ሺህ ሰዎችን ገደለ። ተጠምቶም ለሞት በተቃረበ ጊዜ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ተገለጠለትና አጸናው እግዚአብሔር ከአህያ መንጋጋ አጥንት ውኃን አፈለቀለትና ጠጥቶ ዳነ።

ዳግመኛም ከሚስቱ ጋር ተስማምተው ዐይኖቹን አሳወሩ የራሱንም ጠጉር ላጩ አሠሩትም ከዚህም በኋላ ለጣዖቶቻቸው በዓልን በአዘጋጁ ጊዜ ሶምሶንን ወደ ጣዖቶቻቸው ቤት ወሰዱት በዚያም ሦስት ሽህ ያህል ሰዎች ተሰብስበው ነበር የከበረ ሚካኤልም ተገለጠለትና ኃይልን መላው የዚያንም ቤት ምሰሶዎች ነቀላቸው ቤቱም በላያቸው ወድቆ ከእርሱ ጋር ሁሉንም ገደላቸው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ገላስዮስ_ገዳማዊ

በዚህችም ቀን ተጋዳይ የሆነ የከበረ አባት አባ ገላስዮስ አረፈ። የዚህ ቅዱስ ወላጆቹ አግዚአብሔርን የሚፈሩ ምእመናን ናቸው ጥበብንና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማሩትና ዲቁና ተሾመ።

ከታናሽነቱም ጀምሮ ይህን ዓለም ንቆ ተወ የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስንም ቀንበር በመሸከም በምንኵስና ሆኖ በትጋት እየጾመ እየጸለየና እየሰገደ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ እግዚአብሔርም መርጦት በአስቄጥስ ገዳም ባሉ መነኰሳት ላይ ቅስና ተሾመ።

ተጋድሎውንና አገልግሎቱን እየፈጸመ ሳለ ለአባ ጳኵሚስ እንደ ተገለጠ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና መነኰሳትን ሰብስቦ ፈሪሀ እግዚአብሔርን የምንኵስናንም ሕግ ያስተምራቸው ዘንድ አዘዘው በዚያንም ጊዜ ብዙዎች መነኰሳትን ሰበሰበ መንፈሳዊ የሆነ የአንድነት ማኅበራዊ ኑሮንም ሠራላቸው እርሱ በመካከላቸው እንደ መምህር አልሆነም ከእርሳቸው እንደሚያንስ አገልጋይ እንጂ።

ይህም አባት የዚህን ዓለም ጥሪት ሁሉ ንቆ የተወ ሆነ እጅግም የዋህና ቸር ሆነ ከብሉይና ከሐዲስ መጻሕፍቶችም የተሰበሰበ አንድ ታላቅ መጽሐፍን አጻፈ ለማጻፊያውም ዋጋ ዐሥራ ስምንት የወርቅ ዲናር አወጣ ከርሱ ሊጠቀሙ በሚፈልጉ ጊዜ መነኰሳቱ እንዲያነቡት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአትሮንስ ላይ አኖረው።

አንድ መጻተኛ ሰውም አረጋዊ አባ ገላስዮስን ሊጎበኝ በገባ ጊዜ ያንን መጽሐፍ አየውና አማረው በጭልታም ከዚያ ሰርቆት ወጣ ወደ ከተማ ውስጥም በገባ ጊዜ ሊሸጠው ወደደ አንድ ሰውም ዋጋው ምን ያህል ነው አለው እርሱም ዐሥራ ሰባት የወርቅ ዲናር ስጠኝ አለው። ያ የሚገዛውም ሰው ያልከውን እሰጥሃለሁ ነገር ግን ለወዳጄ እስካሳየው ታገሠኝ አለው ያሳየውም ዘንድ ሰጠው የሚገዛው ሰው ግን ወደ አባ ገላስዮስ ወሰደውና ተመልከትልኝ መልካም ከሆነ እገዛዋለሁ አለው አባ ገላስዮስም ያመጣውን ሰው ከአንተ ምን ያህል ፈለገ አለው ዐሥራ ሰባት የወርቅ ዲናር አለው ቅዱስ ገላስዮስም መጽሐፉ መልካም ነው ዋጋውም ቀላል ነው ግዛው ብሎ መለሰለት።

ወደ ሌባውም በተመለሰ ጊዜ አባ ገላስዮስ የነገረውን ሠውሮ ለአባ ገላስዮስ አሳየሁት እርሱም ዋጋው በዝቷል አለኝ አለው ሌባውም ያ ሽማግሌ ሌላ የተናገረህ ነገር የለምን አለው አዎን የለም አለው። ሌባውም እንግዲህ እኔ አልሸጠውም ብሎ ወደ አባ ገላስዮስ ሒዶ ከእግሩ በታች ወድቆ ለመነው ሰይጣን አስቶኛልና ይቅር በለኝ መጽሐፍህንም ውሰድ አለው የከበረ ገላስዮስም እኔ መጽሐፉን መውሰድ አልሻም አለው። ሌባውም በፊቱ እያለቀሰና እየሰገደ ብዙ ለመነው በብዙ ድካምም መጽሐፉን ተቀበለው ማንም ያወቀ የለም። እግዚአብሔርም ትንቢት የመናገርን ሀብት ሰጥቶት ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ።

በአንዲትም ዕለት ለገዳሙ መነኰሳት ዓሣ አመጡ ባለ ወጡ ዓሣውን አብስሎ በቤት ውስጥ አኑሮ አንዱን ብላቴና ጠባቂ አድርጎ ወደ ሥራው ሔደ ብላቴናውም ከዚያ ዓሣ በላ። ባለ ወጡ በመጣ ጊዜ ተበልቶ አገኘውና በብላቴናው ላይ ተቆጥቶ አረጋውያን አባቶች ሳይባርኩት እንዴት ደፍረህ በላህ አለው የቊጣ መንፈስም በልቡ አደረና ብላቴናውን ረገጠው ወዲያውኑ ሞተ እንደሞተም አይቶ ደነገጠ ታላቅ ፍርሀትንም ፈራ ሒዶ ለአባ ገላስዮስ የሆነውን ሁሉ ነገረው እርሱም ወስደህ ከቤተ መቅደሱ ፊት አስተኛው አለው ሰውየውም እንዳዘዘው አደረገ።

ወደ ማታ ጊዜም አረጋውያን መነኰሳት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰብስበው የማታውን ጸሎት አድርሰው ወጡ አረጋዊ አባ ገላስዮስም በወጣ ጊዜ የሞተው ብላቴና ተነሥቶ በኋላው ተከተለው ከመነኰሳትም ማንም አላወቀም እርሱም የገደለውን ባለ ወጥ ለማንም እንዳይናገር አዘዘው።

የተመሰገነ አባ ገላስዮስም ያማረ ትሩፋቱንና ተጋድሎውን ፈጽሞ አድርሶ እግዚአብሔርንም አገልግሎ ይህንንም በጎ መታሰቢያ ትቶ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም የሚለይበት ሲደርስ በሰላም አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሠርጸ_ጴጥሮስ

ዳግመኛም በዚህች እለት ታላቁ አባት አቡነ ሠርጸ ጴጥሮስ አረፉ፡፡ የትውልድ አገራቸው ሸዋ ደብረ ጽላልሽ ሲሆን በሕፃንነታቸው ወደ ወሎ ሄደው ሐይቅ እስጢፋኖስ ገብተው ብዙ ተጋድለዋል፡፡ከተጋድሎአቸውም በኋላ በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ እጅ መነኰሱ፡፡ በገዳሙ ብዙ ካገለገሉ በኋላ በመልአክ ትእዛዝ ወደ ጎጃም ሲሄዱ ዓባይን የተሻገሩት አጽፋቸውን አንጥፈው እርሱን እንደ ጀልባ ተጠቅመው ነው፡፡

ጻድቁ ታላቋን ተድባበ ማርያምን ለ41ዓመት አጥነዋል፡፡ የንጉሡ ልጅ ሞቶ ሊቀብሩት ሲወስዱት የአቡነ ሠርጸ፡ጴጥሮስ ጥላቸው ቢያርፍበት ከሞት አፈፍ ብሎ ተነሥቶ ድኖ "አምላከ አቡነ ሠርጸ ጴጥሮስ" ብሎ ፈጣሪውን አመስግኗል፡፡ ጻድቁ ሲያርፉም መቋሚያቸው አፍ አውጥታ ተናግራለች፤ ርዕደተ መቃብራቸው ሲፈጸምም እንባ አፍስሳ አልቅሳላቸዋልች፡፡ ይህቺ ተአምረኛ መቋሚያቸው ዛሬም ጎጃም ውስጥ መካነ መቃብራቸው ባለበት በደብረ ወርቅ ገዳም ትገኛለች፡፡ ጻድቁ ደብረ ወርቅ ገዳምን እንደ መሶብ አንሥተው አስባርከዋታል፡፡ አቡነ ሠርፀ ጴጥሮስ የካቲት12 ቀን ያረፉ ሲሆን ዐፅማቸውም በታላቋ ደብረ ወርቅ ይገኛል፡፡ ከሰማይ የወረደላቸው የወርቅ መስቀላቸውም በዚያው ይገኛል፡፡

ጸበላቸው እጅግ ፈዋሽና ኃይለኛ ከመሆኑም በላይ በሰውነት ውስጥ የሚገኝ በሽታንና አጋንንትን የሚያስወጣበት መንገድ ለየት ያለው፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት እና #ከገድላት_አንደበት)