መዝገበ ቅዱሳን
24.2K subscribers
1.97K photos
9 videos
6 files
26 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
#ነሐሴ_20

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ በዚች ቀን መጻሕፍትን የተረጐመ #አባ_ሰላማ አረፈ፣ በከሀዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ዘመን የነበሩ ከኤፌሶን ሀገር #ቅዱሳን_ሰባቱ_ደቂቅ አረፉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሰላማ_ካልዕ (#መተርጉም)

ነሐሴ ሃያ በዚች ቀን መጻሕፍትን የተረጐመ አባ ሰላማ አረፈ።

እኒህ ታላቅ ደግ ሰው የነበሩት በሃገራችን ኢትዮዽያ ከ1340 እስከ 1380 ዓ/ም ነው:: በትውልድ ግብጻዊ ቢሆኑም ለኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ውለታን ውለዋል:: በዘመኑ ዻዻስ ሁነው ቢመጡም እንደ ሌሎቹ ዻዻሳት በቤተ መንግስት አካባቢ ሥራ ፈትተው መቀመጥን አልፈለጉም::

ወዲያው እንደ መጡ የግዕዝ ልሳንን ልቅም አድርገው ተማሩ:: ቀጥለው ኢትዮዽያውያን ሊቃውንትን ሰብስበው ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተረጉሙ ገቡ:: አሥራው መጻሕፍትን (81ዱን) ጨምሮ ብዙ መሠረታዊ መጻሕፍትን መተርጐም ችለዋል::

ይህም ሥራ አድካሚ በመሆኑ ከ30 ዓመታት በላይ ጊዜን ወስዷል:: ከተረጐሟቸው መጻሕፍትም፦ #ስንክሳር#ግብረ_ሕማማት#ላሃ_ማርያም#ፊልክስዩስ(መጽሐፈ መነኮሳት)፣ #መጽሐፈ_ግንዘት፣ድርሳን ዘቅዱስ #ያዕቆብ_ዘሥሩግ. . . ይጠቀሳሉ::

አቡነ ሰላማ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸውና በገዳማዊ ሕይወታቸው ይታወቁ ነበር:: በተጨማሪም በየቦታው እየዞሩ ይናዝዙ: ያጠምቁም ነበር:: በወቅቱ ልክ እንደ ስማቸው ሰላም እንዲሰፍን ይተጉ ነበር:: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን እያስታረቁ ለቤተ ክርስቲያን በአንድነት እንዲቆሙ አድርገዋል::

ጻድቁ አቡነ ፊልዾስን ጨምሮ ቅዱሳንን ገንዘውም ቀብረዋል:: በቀደመ ስማቸው #አባ_ፊቅጦር የሚባሉት ካልዕ (2ኛው) ሰላማ በ1380 ዓ/ም ከ40 ዓመታት ትጋት በኋላ ዐርፈዋል:: ሲጠሩም:- #መተርጉም (መጻሕፍትን የተረጐሙ)፣ #ብርሃነ_አዜብ(የኢትዮዽያ ብርሃን)፣ #መጋቤ_ሃይማኖት ተብለው ነው::

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ሰባቱ_ደቂቅ

በዚህችም ቀን በከሀዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ዘመን የነበሩ ከኤፌሶን ሀገር ሰባቱ ደቂቅ አረፉ። እሊህም ሰባቱ ደቂቅ ከንጉሥ ዳኬዎስ ጭፍሮች ውስጥ በመዛግብቱ ላይ የሾማቸው ነበሩ። አምልኮ ጣዖትንም በአወጀ ጊዜ ጣዖትን በማምለክ ሥራ አልተሳተፉም። እሊህንም ቅዱሳን በንጉሥ ዘንድ ወነጀሏቸው ይዞም አሠራቸው።

ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ለመሔድ በፈለገ ጊዜ እስከ ሚመለስ ድረስ ፈትቶ ለቀቃቸው ምናልባት ከምክራቸው ቢመለሱ ብሎ በልቡ አስቦ። ከዚህም በኋላ እሊህ ቅዱሳን ለረከሱ ጣዖታት እንዳይሰግዱ የጭፍራነት ሥራቸውን ትተው በተራራ ውስጥ ወደአለ ዋሻ ሒደው በዚያ ተሠወሩ።

የዋሻውን አፍ ዘጉ ከእሳቸውም ጋራ በንጉሥ ዳኬዎስ ስም የተቀረጸ ብር ነበር። ከእርሳቸውም አንዱም አንዱ በየተራቸው ወጥቶ ምግባቸውን ገዝቶ ወደእሳቸው ይመለስ ነበር። ዳኬዎስም ከሔደበት እንደተመለሰ በሰሙ ጊዜ የዋሻውን ደጃፍ ዘግተው ተኙ።

የእሊህንም ቦታቸውን የሚያውቅ አማኒ የሆነ ከጭፍሮች ውስጥ አንድ ሰው ነበረ ወደ ከተማ ሲወጡ ያገኛቸው ዘንድ ጠበቃቸው ባልመጡም ጊዜ ተነሥቶ ወደ ዋሻቸው ሔደ። ዋሻዋንም ከውስጥ እንደ ዘጓት ሁና አገኛት እነርሱም በረሀብ የሞቱ መሰለው ታላቅም የደንጊያ ሠሌዳ አምጥቶ ከእሳቸው የሆነውን ገድላቸውን ጽፎ በቀዳዳ ወደ ዋሻው ውስጥ አስገባው።እሊህም ቅዱሳን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዘመናት አንቀላፉ ዳኬዎስም ሙቶ እስከ ቴዎዶስዮስ ብዙ ነገሥታት ነገሡ።

በዚህም ምእመን ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዎች ተነሥተው ብዙዎች ተከተሏቸው። በዚያንም ጊዜ እሊህን ቅዱሳን ሰባቱን ደቂቅ እግዚአብሔር አነቃቸው ትንሣኤ ሙታን መኖሩን ግልጽ ያደርግ ዘንድ።

ከዚህም በኋላ ከእርሳቸው አንዱ ምግባቸውን ሊገዛ የከሀዲ ዳኪዎስንም ወሬ ይሰማ ዘንድ ብር ይዞ ወጣ ወደ ከተማም በገባ ጊዜ የከተማዋ ሁኔታ ተለወጠበት። በከተማውም በር መስቀሎችን አየ በየቅጽሮቿም የክብር ባለቤት የሆነ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ስሙን ያለ መፍራት ሲጠሩ ሰማ አንዱንም ሰው ይች አገር ኤፌሶን አይደለችምን ብሎ ጠየቀ እርሱም አዎን ናት አለው።

ያንንም ብር አውጥቶ ለባለ ሱቁ ሰጠው ምግባቸውን ይሸጥለት ዘንድ ባለ ሱቁም ያን ብር ተመለከተው የንጉሥ ዳኬዎስም ስም ተቀርጾበት አገኘውና ያንን ሰው ይዞ በአንተ ዘንድ የተሸሸገ መዝገብ አለ ይህ ምልክት ከአንተ ተገኝቷልና አለው።

እንዲህም ሲጣሉ ወደእርሳቸው ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ እንዲህም ብለው ጠየቁት አንተ ከወዴት ነህ ከዚች አገር ነኝ አላቸው።ማንን ታውቃለህ አሉት እርሱም ዕገሌንና ዕገሌን አላቸው ከዘመን ብዛት የተነሣ የጠራቸውን ሰዎች የሚያውቃቸው የለም።ስለዚህም በእርሱ ላይ ተቆጥተው ወደ ዳኞችና ወደ ኤጲስቆጶስ አባ ቴዎድሮስ ወደ ንጉሥ ቴዎዶስዮስም አቀረቡት።

ንጉሡና ኤጲስቆጶሱም ከአንተ የሆነውን እውነቱን ንገረን ከወዴት አገር ነህ አሉት። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው እኛ ሰባታችን የከሀዲ ንጉሥ ዳኬዎስ ጭፍሮች ነን እርሱም ወጥቶ ወደ ሌላ አገር በሔደ ጊዜ ከአንዷ ዋሻ ውስጥ ገብተን የዋሻዋን በር ዘግተን ተኛን። እነሆ ስንነቃ የምንመገበውን ምግብ እገዛ ዘንድ ላኩኝ።

ንጉሡና ኤጲስቆጶሱ በሰሙ ጊዜ ተነሥተው ወደዚያ ዋሻ ከእርሱ ጋራ ሔዱ ከእርሳቸውም ጋራ ብዙ ሕዝቦች አሉ ቅዱሳኑንም ተቀምጠው አገኙአቸው። የዘመኑም ቁጥር በውስጡ የተጻፈበትን በከሀዲው ንጉሥ በዳኬዎስ ዘመን የሆነውን ሠሌዳውን ወድቆ አገኙት ዘመኑም ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት እንደሆነ ታወቀ።

ንጉሡና ኤጲስቆጶሱ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉትም ይህን ድንቅ ሥራ አይተው ትንሣኤ ሙታን እንዳለ አመኑ። እሊህ ሰባቱ ደቂቅንም በጠየቋቸው ጊዜ ከእርሳቸው የሆነውን ሁሉ ነገሩአቸው።

ከዚህም በኋላ ተመልሰው ተኙ። ነፍሳቸውንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ። ንጉሥም የወርቅ ሣጥን ሠራላቸው በሐር ልብሶችም ገንዘው በመልካም ቦታ አኖሩዋቸው። ከሥጋቸውም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።

ስማቸውም:- መክሲማኖስ፣ ታሙኪሮስ፣ መርዳዲሞስ፣ ዮሐንስ፣ ቈስጠንጢኖስ፣ አዝሚና ዲዮናስዮ ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የእሊህም ቅዱሳን በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን!

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
#መስከረም_24

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ አራት ኢትዮጵያዊቷ #ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ ወደ ደብረ ሊባኖስ የገባችበት፣ ከላይኛው ግብጽ የሆነ ቅዱስ አባት #መነኰስ_ጎርጎርዮስ ያረፈበት እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመረጣቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ለአንዱ #ሐዋርያ_አድሊጦስ የምስክርነቱ መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ

መስከረም ሃያ አራት ኢትዮጵያዊቷ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ወደ ደብረ ሊባኖስ የገባችበት ነው። ቅድስት እናት ክርስቶስ ሠምራ ቅንነቷ፣ ደግነቷና ቅድስናዋ እጅግ የበዛ ነው። አንድ ቀን ግን ገና በትዳር ውስጥ እያለች ከአገልጋዮቿ አንዷን ትጠራትና ታዛታለች። ያቺ አገልጋይ ግን የታዘዘችውን ጀሮ ዳባ ልበስ ብላ ሳትታዘዛት ትቀራለች።

ደጋግማ ብትነግራትም ልትሰማት አልቻለችም። ያን ጊዜ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ልትገስጻት ብላ ጠጠር ብትወረውርባት ያች አገልጋይ ወድቃ ሞተችባት። ቅድስቲቱ እጅግ ደንግጣ አለቀሰች። የምታደርገውንም አጣች።

ወዲያው ግን ፈጠን ብላ: ወገቧን ታጥቃ ትጸልይ ጀመረች። "ጌታየ ሆይ! ከሞት አስነሳልኝና ዓለምን ትቼ በቀሪ ዘመኔ አንተን አገልለግልሃለሁ" ብላ ፈጣሪን በብዙ እንባ ተማጸነችው:: ያን ጊዜም አገልጋዩዋ ከሞት ተነሳችላት።

ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ጊዜን አላጠፋችም። ልጆቿን በቤት ትታ ሃብትን ብረቷን ንቃ አንድ ልጇን አዝላ ቤቷን እንደ ተከፈተ ትታው ወደ ገዳም ወጣች። በዚህ ዕለትም (መስከረም 24 ቀን) ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገባች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጎርጎርዮስ_ዘላዕላይ_ግብጽ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ከላይኛው ግብጽ የሆነ ቅዱስ አባት መነኰስ ጎርጎርዮስ አረፈ ። የዚህም የቅዱስና የተመሰገነ ጎርጎርዮስ ወላጆቹ ደጎች ናቸው በዚህ ዓለም ገንዘብም እጅግ ባለጸጎች ነበሩ ይህን ልጃቸውን ጎርጎርዮስንም በበጎ አስተዳደግ አሳደጉት ። መንፈሳዊ የሆነ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን ሁሉ ሥጋዊም የሆነ ጥበብንና ቋንቋን አስተማሩት ።

ከዚህም በኋላ የሀገራቸው ኤጲስቆጶስ ወደ ሆነ ወደ አባ ይስሐቅ ወሰዱት እርሱም እጁን በላዩ ጭኖ አናጒንስጢስነት ሾመው ።

ከዚህም በኋላ ወላጆቹ ሊአጋቡት አሰቡ እርሱ ግን ይህን ሥራ አልወደደም ሁለተኛም ወደ ጳጳስ ወስደውት ፍጹም ዲቁናን ተሾመ ወደ አባ ጳኲሚስም አዘውትሮ በመሔድ ከእርሱ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚማር ሆነ ከወላጆቹም ብዙ ገንዘብን ወስዶ ወደ አባ ጳኲሚስ አቅርቦ በገዳማቱ ለሚሠሩ ሕንፃዎች ሥራ ያደርግለት ዘንድ ብዙ ልመናን ለመነው እርሱም ተሳትፎ እንዲሆንለት ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ለመነኰሳት ቤት መሥሪያ አደረገለት ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዓለምን ትቶ ጥሪቱንና ገንዘቡን ሁሉ ንቆ በመተው ወደ ቅዱስ አባ ጳኲሚስም ሒዶ የምንኲስና ልብስን ለብሶ በጾም በጸሎት በመትጋት በመስገድ ከትሕትና፣ ከቅንነት፣ ከፍቅር ጋር ይጋደል ጀመረ አርአያነቱንና ምሳሌነቱን በአዩ ጊዜ ከእርሱ ፈሪሀ እግዚአብሔርን ተምረው አመንዝራዎች የከፋ ሥራቸውን እስከ ተውና ንስሐም ገብተው ንጹሐንም እስከ ሆኑ ድረስ ተጋደሉ ። ከአባ ጳኲሚስም ዘንድ ዐሥራ ሦስት ዓመት ኖረ ።

አባ መቃርስም ወደ አባ ጳኲሚስ በመጣ ጊዜ ሰውነቱን በማድከም ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ ጥቂት ቀኖች ኖረ ከዚያም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሊመለስ ወደደ አባ ጳኲሚስም ከአባ መቃርስ ጋር እንዲሔድ አባ ጎርጎርዮስን አዘዘው እርሱም አብሮ ሔደ በእርሱም ዘንድ ብዙ ዘመናት ኖረ ።

ከዚህም በኋላ በዋሻ ብቻውን ይኖር ዘንድ እንዲአሰናብተው የከበረ አባ መቃርስን ለመነው እርሱም እንደ ወደድክ አድርግ አለው ። ያን ጊዜ ወደ ተራራ ሒዶ ታናሽ ዋሻ ቆርቁሮ በውስጧ ሰባት ዓመት ኖረ አባ መቃርስም በየዓመቱ ሁለት ጊዜ መጥቶ ይጎበኘዋል አንደኛ ለከበረ የልደት በዓል ሁለተኛ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተነሣባት በትንሣኤ በዓል ቀን ከርሱ ጋርም ሥጋውንና ደሙን ተቀብሎ ወደ ቦታው ይመለሳል ። አባ መቃርስም ስለ ሥራው ሁሉ ይጠይቀዋል እርሱም የሚያየውንና በእርሱ የሆነውን ሁሉ ይገልጽለታል አባ መቃርስም ሊሠራው የሚገባውን የምንኲስና ሥራን ይሠራ ዘንድ ያዘዋል ።

በተጋድሎም ውስጥ ሃያ ሁለት ዓመታት ሲፈጽሙለት ከዚህ የድካም ዓለም ያሳርፈው ዘንድ እግዚአብሔር ፈቅዶ መልአኩን ላከለት እርሱም ከሦስት ቀን በኋላ ከዚህ ከኀላፊው ዓለም ወጥተህ ወደ ዘላለም ሕይወት ትገባለህ አለው ።

አባ ጎርጎርዮስም በአስቄጥስ ገዳም ያሉ አረጋውያንን አስጠራቸውና ተሳለማቸው በጸሎታቸውም እንዲአስቡት ለመናቸው እነርሱም ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲአስባቸው ለመኑት ከሦስት ቀንም በኋላ አርፎ ወደ ዘላለም ሕይወት ገባ ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያ_አድሊጦስ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)

በዚህችም ቀን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመረጣቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ለአንዱ ሐዋርያ አድሊጦስ የምስክርነቱ መታሰቢያ ነው ። ይህም ሐዋርያ ትውልዱ ከአቴና አገር ከታላላቆቿና ከምሁራኖቿ ነው እርሱም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ አገለገለውም ።

አጽናኝ የሆነ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በሃምሳኛው ቀን ከተቀበለ በኋላ ወደ ብዙዎች አገሮች ሒዶ ሕይወት የሆነ ወንጌልን ሰበከ መግኒን ወደሚባልም አገር ደርሶ በውስጧ የከበረ ወንጌልን ሰበከ የብዙዎችንም ልቦና ብሩህ አድርጎላቸው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ። የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ሕይወት የሆኑ የወንጌልንም ትእዛዞች አስተምሮ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው ።

ከዚህም በኋላ ከእሳቸው ዘንድ ወጥቶ ወደ አቴና አገር ተመለሰ በውስጧም የከበረ ወንጌልን አስተማረ በዚያን ጊዜም በደንጊያ ወገሩት ጽኑዕ የሆነ ሥቃይንም አሠቃዩት ። ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ወረወሩትና በዚያ ተጋድሎውንና ምስክርነቱን ፈጽሞ የሕይወት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረምና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
አሁንም ስለ እግዚአብሔር ብለህ ስለ ቀናች ሃይማኖትም በድካም ከእኛ ጋር አንድ በመሆን ስለእኛ ወደ ግብጽ ሊቀ ጳጰሳት ወደ ቅዱስ ፊላታዎስ ጳጳስ ይልክልን ዘንድ ከራስህ ደብዳቤ እንድትጽፍለት እለምንሃለሁ የሚል ነበር ።

በዚያንም ጊዜ የኖባ ንጉሥ ጊዮርጊስ ለኢትዮጵያ አገር ጳጳስን ይሾምላቸው ዘንድ የልመና ደብዳቤ ወደ አባ ፊላታዎስ ጻፈ ይህ ቅዱስ ፊላታዎስም ልመናውን ተቀብሎ ከአስቄጥስ ገዳም ስሙ ዳንኤል የሚባል አንድ ጻድቅ መነኰስ አስመጣ እርሱን ጵጵስና ሹሞ ወደ ኢትዮጵያ አገር ላከው ወደ እነሱም በደረሰ ጊዜ የኢትዮጵያ ሰዎች በታላቅ ደስታ ተቀበሉት ። በዚህም አባት ፊላታዎስ ዘመን ብዙ ተአምራት ተገልጠዋል በሰላምም አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል እና በቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
በዚህችም ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ቆዝሞስ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃምሳ አራተኛ ነው። ይህም አባት ብዙ መከራና ኀዘን ደረሰበት በዘመኑም በክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ላይ መከራና ችግር ደረሰባቸው በእነዚያም ወራት የክርስቲያን ወገኖችና አይሁዳውያን ልብሳቸውን በሰማያዊ ቀለም እንዲያቀልሙት እንጂ ነጭ ልብስ እንዳይለብሱ የእስላሞች ንጉሥ ጋዕፊር አዝዞ ነበርና።

በዚህም አባት ዘመን ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራት ተገለጡ በአስቄጥስ ገዳም በቅዱስ ሳዊሮስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ነበረች ጐኗም ተገልጦ ከእርሷ ብዙ ደም ፈሰሰ በግብጽ አገር ከአሉ ከሌሎች ሥዕሎችም ከዐይኖቻቸው ብዙ ዕንባ ፈሰሰ ይህም የሆነው በሊቀ ጳጳሳቱና በክርስቲያን ወገኖች ላይ ስለ ደረሰው መከራ እንደ ሆነ በመራቀቅ የሚያስተውሉ አወቁ።

ከዚህም በኋላ ስለእነዚያ የከፉ ወራቶች ፈንታ በጎ የሆኑ ወራቶችን እግዚአብሔር ሰጠው ሁል ጊዜም ምእመናንን የሚያስተምራቸውና የሚያጽናናቸው በቀናች ሃይማኖትም የሚያበረታታቸው ሆነ ። በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበርም ላይ ሰባት ዓመት ከአምስት ወር ከኖረ በኋላ በአምስት መቶ ሰባ አምስት ዓመተ ሰማዕታት ኅዳር ሃያ አንድ ቀን አረፈ ይንሶር በሚባል ዋሻውም ተቀበረ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_ዘአስዩጥ

በዚችም ቀን ደግሞ የብርሌ የብርጭቆ ሠሪዎች ልጅ የሆነ ከአስዮጥ አገር ቅዱስ አባት አባ ዮሐንስ አረፈ ። ይህንንም ቅዱስ በወለዱት ጊዜ በበጎ ተግሣጽ አሳድገውታል የጥርብ ሥራንም አስተማሩት ከጥቂት ዘመናትም በኋላ አባቱና እናቱ አረፉ። ያን ጊዜ ወደ ቅዱስ አባ ኢስድሮስና ወደ አባ ባይሞን ዘንድ ሒዶ መነኰሰ በጾምና በጸሎት በገድል ሁሉ ተጠምዶ ተጋደለ ዜናውም በራቁ ገዳማት ሁሉ ተሰማ ።

ከዚህም በኋላ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጠለት ወደ ሀገሩ ሒዶ ወገኖቹን የጽድቅን ጎዳና ይመራቸው ዘንድ አዘዘው። ቅዱስ ቊርባንንም ሳይቀበል ከበዓቱ የማይወጣ ሆነ። በአንዲት ዕለትም ሁለት ቅዱሳን አረጋውያን አባ አብዢልና አባ ብሶይ ወደርሱ መጡ ገና ወደርሱ ሳይቀርቡ ከሩቅ ሳሉ ስማቸውን በመጥራት ሳያውቃቸው አባቶቼ ለመምጣታችሁ ሰላምታ ይገባል ብሎ ተናገረ እጅግም አደነቁት አባ ሲኖዳም ከግብጽ አገር እየመጣ ብዙ ጊዜ ይጎበኘው ነበር።

የከዳተኞችም ጠብ በግብጽ አገር ላይ በተነሣ ጊዜ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ የላከው የጦር መኰንን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መጣ። በጸሎቱም ይራዳው ዘንድ ለመነው ቅዱስ ዮሐንስም መስቀሉን አንሥቶ መኰንኑን አይዞህ አትዘን አንተ ጠላቶችህን ድል ታደርጋለህና አለው እንደ ቃሉም ሆነ።

ዳግመኛም በንጉሥ ቴዎዶስዮስ ላይ ጠላት በተነሣበት ጊዜ ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ላከ እርሱም አትዘን አንተ ጠላትህን ታሸንፋለህ አለው ያን ጊዜም ጠላቶቹን አሸነፈ ።

ከዚህም በኋላ በእነዚያ ወራት ንጉሥ ቴዊዶስዮስ የርኲሰትን ሥራ ስለ ሠሩ የአስዮጥን ሰዎች እንዲገድሏቸው ሀገራቸውንም እንዲአጠፉ አዘዘ። ንጉሡም የላከው መኰንን ሳይደርስ የእግዚአብሔር መልአክ ይህን ነገር ለአባ ዮሐንስ አሳወቀው የሀገርም ሰዎች የንጉሡን ትእዛዝ በሰሙ ጊዜ ወደ አባ ዮሐንስ ገዳም ወጥተው ስለ መጥፋታቸው በፊቱ አለቀሱ አባ ዮሐንስም አትጨነቁ አይዟችሁ እግዚአብሔር ያድናችኋልና አላቸው።

መኰንኑም በመጣ ጊዜ ከእርሱ በረከትን ይቀበል ዘንድ ወደ አባ ዮሐንስ ደረሰ አባ ዮሐንስም ንጉሡ ያዘዘውን ሁሉ ነገረው መኰንኑም ሰምቶ ደነገጠ ለቅድስናውም ተገዢ ሆነ ለመኰንኑም ርኩስ መንፈስ ያደረበት የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረው ያድንለት ዘንድ ቅዱስ ዮሐንስን ለመነው በዚያንም ጊዜ ዘይትን ቀብቶ አዳነው።

ከዚህም በኋላ የአስዩጥ ሰዎችን መገደላቸውን እንዲተው ወደ ንጉሥ ይጽፍለት ዘንድ መኰንኑን አባ ዮሐንስ ለመነው መኰንኑም ጽፎ ለአባ ዮሐንስ ሰጠው አባ ዮሐንስም ተቀብሎ ወደ ዋሻው ገባ ወደ ጌታችንም ጸለየ ብርህት ደመናም መጣች ተሸክማም ወደ ንጉሡ አደረሰችው ያን ጊዜም ንጉሥ ከማዕድ ላይ ነበረ ያንንም ደብዳቤ ከወደላይ ጣለለት ንጉሡም አንሥቶ በአነበበው ጊዜ ከመኰንኑ የተጻፈ እንደሆነ በመካከላቸው በአለ ምልክት ተጽፎ አገኘው የተጻፈውም ቃል ስለ አባ ዮሐንስ ልመና ሀገሪቱን ማጥፋትን እንዲተው የሚል ነበር ቀና ባለ ጊዜም ደመና አየ ንጉሡም አደነቀ።

ከዚህም በኋላ ሀገሪቱን ማጥፋትን ስለ አባ ዮሐንስ ይተው ዘንድ መልሱን ለመኰንኑ ንጉሡ ጽፎ ደብዳቤዋን ወደ ደመናው ወረወራት የተሰበሰቡትም እያዩ እጅ ተቀበለችውና ወደ ደመናው ገባች ወዲያውኑ አባ ዮሐንስ በዚያች ደመና ወደበዓቱ ተመለሰና በማግሥቱ ያቺን ደብዳቤ ለመኰንኑ ሰጠው በላይዋም የንጉሡ ፊርማውና ማኅተሙ አለ በአያትና በአነበባት ጊዜ ደነገጠ አደነቀም ስለ ሀገሪቱ ድኅነትም እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደአገሩ ተመለሰ።

የንጉሥ ዘመድ የሆነች የከበረች ሴት ዜናውን በሰማች ጊዜ ከደዌዋ ይፈውሳት ዘንድ ወደርሱ መጣች በጸሎቱም ተፈወሰች። ከዚህም በኋላ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ በሞተ ጊዜ መናፍቁ መርቅያን ነገሠ ። ቅዱስ አባ ዲዮስቆሮስንም አሠቃየው ። የቀናች ሃይማኖትን ስለመለወጡ አባ ዮሐንስ እየዘለፈና እየረገመው ወደ ርሱ ደብዳቤ ላከ ከጥቂት ወራትም በኋላ እግዚአብሔር ቀሠፈው።

ለእርሱም ዕድሜው መቶ ሃያ አምስት ዓመት ሲሆነው ዕረፍቱ እንደ ደረሰ አወቀ እየጸለየም ግምባሩን ምድር አስነክቶ ሰገደ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ ከመቃብሩም ቁጥር የሌላቸው ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራት ተገለጡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በጸሎቷ የሚገኝ በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋር ይኑር። በቅዱሳኑም ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
ዳግመኛም ለጣዖታት መስገድን እሺ ይለው ዘንድ ቅዱስ ጢሞቴዎስን ማባበል ጀመረ እምቢ ባለውም ጊዜ የነዳጅ ድፍድፍ ሥጋውን ቀብተው ከእሳት ማንደጃ ውስጥ እንዲጨምሩት አዘዘ በጨመሩትም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ከዚህ ቃጠሎ አዳነው ።

ከዚህም በኋላ ሁለተኛ ወደ ወህኒ ቤት መለሱት ተአምራትንም የሚያደርግ ሆነ በአንዲት ዕለትም በዚያ ሲጸልይ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ መጥቶ ቃል ኪዳንን ገባለት ሰላምታንም ሰጠው።

በማግሥቱም ከእሥር ቤት አውጥተው ወደ በንሑር ከተማ ወስደው ቅድስት ራሱን ቆረጡ ያን ጊዜ ንውጽውጽታ ሆነ አየርም መላእክትን ተመላች አማንያን ሰዎችም መጥተው ሥጋውን ወስደው በመልካም አገናነዝ ገንዘው ቀበሩት። የመከራውም ዘመን በአለፈ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ሠሩለት ሰኔ ሃያ ሰባት ቀንም አከበርዋት ሥጋውንም በውስጥዋ አኖሩ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር#ከገድላት_አንደበት እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
በዳግመኛውም ዓመት ያቺ ባሕር ተገልጣ እንደ ልማዳቸው ገቡ ሕፃኑንም በሕይወት ሁኖ በቅዱስ ቀሌምንጦስ የሥጋ ሣጥን ዘንድ ቁሞ አገኙት በዚህ ባሕር ውስጥ አኗኗርህ እንዴት ነበር ምን ትበላ ነበር የባሕር አራዊትስ እንዴት አልበሉህም ብለው ጠየቁት። እርሱም ቅዱስ ቀሌምንጦስ ያበላኝ ነበር እግዚአብሔርም በባሕር ካሉ አራዊት ይጠብቀኝ ነበር ብሎ መለሰ ሰምተውም እጅግ አደነቁ በቅዱሳኑና ስለ ከበረ ስሙ ደማቸውን በአፈሰሱ ሰማዕታት የሚመሰገን ምስጉን እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
✞ ይህ ታላቅ መልአክ በ1ኛ ነገ. 19፥5-18 በምናገኘው ታሪክ ላይ ነብዩ ኤልያስን ከተኛበት እየቀሰቀሰ እንጎቻን ብላ ሲለው የነበረው መልአክ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል ነው፡፡

✞ ሌላው የአዳም 7ኛ ትውልድ የሆነው ሞትን ሳያይ የተሰወረው ሄኖክ እንዲህ ሲል ጠቅሶታል "አራተኛውም የዘላለም ሕይወትን የሚወርሱ ሰዎች ተስፋ ሊሆን ንሰሐ በሚገቡ ሰዎች ላይ የተሾመው ፋኑኤል ነው" መ.ሄኖክ 10፥15

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ዜና_ማርቆስ_ጻድቅ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ዕረፍታቸው ነው።

አባ ዜና ማርቆስ በሃገራችን በተለይ በደቡብ ምድረ ጉራጌ ስመ ጥር ሐዋርያዊ ጻድቅ ናቸው። ምድረ ሽዋ ደግሞ እርሳቸውን ጨምሮ የብዙ ቅዱሳን መፍለቂያ ናትና ክብር ይገባታል። ነቢየ ጽድቅ ዳዊት "ትውልደ ጻድቃን ይትባረኩ" "የጻድቃን (የቅኖች) ትውልድ ይባረካል" (መዝ.111) ያለው ነገር በምድረ ዞረሬ (ጽላልሽ) ተፈጽሟል።

ሦስት ወንድማማች የተባረኩ ካህናት በስፍራው ነበሩ። ስማቸው ጸጋ ዘአብ፣ እንድርያስና ዮሐንስ ይባላል። ከእነዚህ መካከልም ጸጋ ዘአብ እግዚእ ኃረያን አግብቶ ኮከበ ከዋክብት ተክለሃይማኖትን ሲወልድ፤ ካህኑ ዮሐንስ ደግሞ ዲቦራ የምትባል ደግ ሴት አግብቶ ዜና ማርቆስን ወልዷል።

የአቡነ ዜና ማርቆስ ጽንሰታቸው ሚያዝያ 30 በብሥራተ ማርቆስ ወንጌላዊ ሲሆን ልደታቸው ደግሞ ኅዳር 24 ቀን በበዓለ ሱራፌል ካህናተ ሰማይ ነው። ዘመኑም 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው።

ዜና ማርቆስ በተወለዱ በ40 ቀናቸው አጐታቸው ቀሲስ እንድርያስ (የ72 ዓመት ሽማግሌ ናቸው) ሊያጠምቁ ቀረቡ። ሕጻኑ ዜና ማርቆስ ግን ከእናታቸው እቅፍ ወርደው 3 ጊዜ "እሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ" እያሉ ቢሰግዱ የመጠመቂያው ገንዳ ውኃ ፈላ። ይህንን የተመለከቱት ካህኑ ደንግጠው ወጥተው ሲሮጡ ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት ተገልጦ "አትፍራ! ይልቁኑ ከጠበሉ ራስህን ተቀባ" አላቸው። እንዳላቸው ቢያደርጉ ራሰ በራ ነበሩና ጸጉር በቀለላቸው።

ሕጻኑ ዜና ማርቆስ ግን 5 ዓመት ሲሞላቸው ወደ ጉባኤ ቤት ገብተው በአጭር ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ። ዲቁናን ተቀብለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱም ሽፍቶች አግኝተው በትራቸውን ቀምተው አንገላተው ሰደዋቸዋል። ወዲያው ግን ያቺ በትር እባብ ሁና ሽፍቶችን አጥፍታቸዋለች።

ጻድቁ ለቤተሰብ እየታዘዙ፣ ንጽሕናቸውንም እየጠበቁ ኑረው 30 ዓመት ሲሞላቸው ወላጆቻቸው ግድ ብለው ማርያም ክብራ ለምትባል ወጣት አጯቸው። እሳቸው ግን በሠርጉ ሌሊት ከጫጉላ ቤት ጠፍተው በርሃ ገቡ። ከዚያም በቅዱስ መልአክ መሪነት ሃገረ ምሑር ደረሱ። በቦታውም ጣዖትን ሰባብረው፣ ተአምራትንም አድርገው ሕዝቡን ወደ ክርስትና መለሱ።

መስፍኑ አውጊት ግን ተፈታተናቸው። አሠራቸው። አሥራባቸው(በረሀብ ቀጣቸው)። በጦር እወጋለሁ ሲል ግን መሬት ተከፍታ ከነ ተከታዮቹ ውጣዋለች። ከ5 ዓመታት በኋላ ግን ማልደው ከሰጠመበት አውጥተው አጥምቀውታል። ቀጥለውም ምድረ ጉራጌ ወርደው ሕዝቡን አሳምነው አጥምቀዋል።

የአዳልን ሕዝብና ንጉሡን አብደልማልን አስተምረው ያጠመቁም እርሳቸው ናቸው። ድል አሰግድ የሚባለውን መስፍንም ያሳምኑ ዘንድ ጠንቋዮቹን ድል አድርገው አጥፍተዋል።

ጻድቁ ዜና ማርቆስ ከዚህ ሐዋርያዊ ሥራቸው በተጨማሪ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምንኩስናን ከተቀበሉባት ቀን ጀምረው በጾም፣ በጸሎትና በሰጊድ ኑረዋል። ፀሐይን በምድረ ጉራጌ እስከ ማቆም ደርሰውም ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል።

አእላፍ ደቀ መዛሙርትን ሲያፈሩ 200 አንበሶች በቀኝ፣ 200 ነብሮች በግራ ይከተሏቸው ነበር። ደብረ ብሥራትን ጨምሮም ገዳማትን አንጸዋል። በመጨረሻም የምሕረት ቃል ኪዳንን ከፈጣሪ ዘንድ ተቀብለው ታኅሣሥ ሦስት ቀን በ140 ዓመታቸው ዐርፈዋል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ይማረን፤ በመልአኩ እና በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
የዚህም አባት ተአምራቶቹ ብዙ ናቸው ተነግሮ አያልቅም በአንዲትም ቀን በበረሀ ውስጥ ሲጓዝ ጅብ ልብሶቹን በጥርሶቻ ይዛ ሳበችውና በሠንጣቃ ገደል ውስጥ የወደቁ ልጆቿን አሳየችው በአወጣላትም ጊዜ ሰገደችለት እግሮቹንም ላሰች።

ከዚህም በኋላ ዕረፍቱ ሲቀርብ በታኅሣሥ ሦስት ቀን ወደ ሠርግ እንደሚጠራው ራእይን አየ ይኸውም የቅዱሳን አባቶች የአባ እንጦንስ፣ የአባ መቃርስ፣ የአባ ጳኪሚስ፣ የአባ ቴዎድሮስ፣ የአባ ሙሴ ጸሊም፣ የአባ ሲኖዳ የአንድነት ተድላ ደስታ ወዳለበት ነው። እነርሱም በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ከእኛ ጋር ትኖር ዘንድ ወደእኛ መምጣትህ መልካም ነው አሉት ብዙ አትክልቶችና ዙፋኖች ወዳሉት ታላቅ አዳራሽም ደጅ አደረሱት ማቴዎስ ይገባ ዘንድ የአዳራሹን ደጆች ክፈቱ የሚልንም ቃል ሰማ ከዚህም በኋላ በዚሁ ወር በሰባት አረፈ ሦስት አክሊላትንም ተቀበለ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን በጻድቅ በነቢያት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታህሣሥና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
በዚያንም ወራት የከሀዲው ልዮን ልጅ ቁስጠንጢኖስ ተነሥቶ በአምላክ ፈቃድ ስለተሣሉ ሥዕሎች ጸብ በማንሣት አብያተ ክርስቲያናትን አወከ ይህም አባ ዮሐንስ የቤተክርስቲያን ሹመት ሳይኖረው በቀናች ሃይማኖት እያጸናቸው በአምላክ ፈቃድ ለተሣሉ ሥዕሎችም ስግደት እንደሚገባ መስክር ከቅዱሳት መጽሕፍት እያመጣ የሚጽፍና ወደ ምእመናን ሁሉ የሚልክ ሆነ ።

ከሀዲው ቈስጠንጢኖስም በሰማ ጊዜ ጥርሱን አፋጨ በዮሐንስ ብርዕ አምሳል የሚጽፍ ጸሐፊንም ፈልጎ በዮሐንስ ብርዕ አምሳያ እንዲህ ብሎ አጻፈ ከአንተ ዘንድ ያለ ዮሐንስ ከአንተ ጋር ተዋግቼ አገርህን እማርክ ዘንድ ይህን ደብዳቤ ጽፎ ላከልኝ ብሎ በወንጀል ለደማስቆ ገዥ ላከለት በሰማ ጊዜም እውነት ስለ መሰለው የሚጽፍባት ቀኝ እጁን ቆረጠው ።

አባ ዮሐንስም የተቆረጠች እጁን ይዞ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ሒዶ በብዙ ዕንባ እንዲህ ብሎ ለመናት እመቤቴ ሆይ ለሥዕልሽ መስገድ ስለሚገባ በተጣለሁ ጊዜ አይደለምን ይህ መቆረጥ የደረሰብኝ አሁንም በቸርነትሽ ፈውሺኝ አንቺ በሥራው ላይ ሁሉ ችሎታ አለሽና ይህንንም ብሎ ጥቂት አንቀላፋ ። በእንቅልፉም ሳለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገለጸችለትና እጁን እንደ ቀድሞው መለሰችለት በነቃም ጊዜ ድና አገኛት እግዚአብሔርንም አመሰገነው ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምንም አመሰገናት ።

ከዚህም በኋላ ወደ ገዳም ሒዶ መነኰሰ አበ ምኔቱም የምንኩስናን ሥርዓት ያስተምረው ዘንድ ለአንድ ሽማግሌ መንፈሳዊ አባት ሰጠው ሽማግሌውም ልጄ ዮሐንስ ሆይ አፍአዊት ከሆነች ትምርትህ ምንም ምን አታድርግ ግን ዝምታን ተማር አለው ከትሕትናውም ብዛት የተነሣ ሰይጣንን ድል ነሣው ።

ከዕለታትም በአንዲቷ ከመነኰሳቱ አንዱ ሽማግሌ ሞተ መነኰሳቱም ስለ ወንድማቸው ሙሾ እንዲአወጣለት አባ ዮሐንስን ለመኑት አባ ዮሐንስም ከሽማግሌው መምህሬ ትእዛዝ የተነሣ እኔ እፈራለሁ አላቸው ለማንም አይገለጥም አሉት ምልጃንም በአበዙበት ጊዜ ለሚሰማት ሁሉ የምታሳዝን ሙሾ ደረሰ መምህሩም አውቆ በእርሱ ላይ ተቆጣ ከበዓቱም አባረረው እርሱም አባ ዮሐንስ ወደ አረጋውያን ሁሉ ተማጠነ ሽማግሌውንም ይቅርታ እንዲአደርግ ግድ በአሉት ጊዜ የመነኰሳቱን የመፀዳጃ ቤት የጠረገ እንደሆነ እምረዋለሁ አለ አባ ዮሐንስም ሰምቶ መንፈሳዊ መምህሩ እንዳዘዘው አደረገ እርሱም ቅንነቱንና ትሩፋቱን አይቶ በደስታ ተቀብሎ ወደ ማደሪያው አስገባው ።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም አረጋዊ መምህሩን ድርሳናትን መድረስን እንዳይከለክለው አዘዘችው ከዚህም በኋላ ብዙ ድርሳናት ደረሰ የኢየሩሳሌሙም ሊቀ ጳጳሳት ቅስና ሾመው በአምላክ ፈቃድ ስለ ተሣሉ ሥዕሎች ክብር ስለ ቀናች ሃይማኖትም ነገሥታቱንና መኳንንቱን ሲዘልፋቸው ኖረ ወደ ሽምግልናም በደረሰ ጊዜ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ተክለ_አልፋ_ዘደብረ_ድማሕ

በዚህችም ቀን የደብረ ድማሕ ገዳም አበምኔት ቅዱስ አባት ተክለ አልፋ አረፈ። ዳግመኛም በክርስቶስ የሚታመን የገብረ ማርያም ዕረፍቱ ነው እርሱም የሰማዕታትንና የጻድቃንን በየዕረፍታቸው ቀን ለየአንዳንዱ ርኁባንን በማጥገብ የተራቆቱትን በማልበስ መታሰቢያቸውን የሚያደርግ ነው ።

እንዲህም ባለ ሥራ ላይ እያለ ያንጊዜ እስላሞች ወደ ሸዋ አገር መጡ እርሱም ያማሩ ልብሶችን ለብሶ ወደ ቤተክርስቲያን ሔዶ ገብቶ ጸሎትን ጸለየ ሲጸልይም እስላሞች ወደርሱ መጥተው ራሱን በሰይፍ ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ#ከገድላት_አንደበት እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
#ታኅሣሥ_16

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ዐስራ ስድስት በዚች ቀን የእስራኤል መሳፍንት አንዱ #ቅዱስ_ጌዴዎን_ኃያል ዐረፈ፣ #የሙሴ_እኅት_ማርያም መታሰቢያዋ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጌዴዎን_ኃያል

ታኅሣሥ ዐስራ ስድስት በዚች ቀን የእስራኤል መሳፍንት አንዱ ጌዴዎን ዐረፈ፡፡ ይህም ከነገደ ምናሴ የሆነ የአባቱ ስም ዮአስ ይባላል ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ተገለጠለትና ለእስራኤል ሾመው። የጠዖታትንም መሠዊያ እነሰዲያፈርስ ዛፎችንም እንዲቆርጥ አዘዘው መሠዊያም ለእግዚአብሔር ሠርቶ በዚያ በሰበረው ዕንጨት እንዲሠዋ አዘዘው ሁሉንም እንዳዘዘው አደረገ። እግዚአብሔር የላከው መልአክም ተመለከተው "እስራኤልን ከምድያም እጅ ታድናቸዋለህና ከሠራዊትህ ጋር ሒድ እነሆ ላክሁህ" አለው።

ጌዴዎንም "አድናቸዋለሁ እንዳልክ እስራኤልን በእጄ ታድናቸው እንደሆነ እነሆ እኔ በአደባባይ የተባዘተ ፀምርን እዘረጋለሁ ጠል በምድር ላይ ሳይወርድ በፀምሩ ላይ ብቻ ቢወርድ አድናቸዋለሁ እንዳል እስራኤልን በእጄ እንድታድ ናቸው ያን ጊዜ አውቃለሁ" አለ እንዳለውም ሆነ። ጌዴዎንም በማግሥቱ ማልዶ ሒዶ ያንን ጨመቀው ከዚያ ፀምር አንድ መንቀል ሙሉ ውኃ ወጣ።

ጌዴዎን እግዚአብሔርን "በቊጣህ አትቆጣኝ ዳግመኛ አንድ ጊዜ ልናገር በፀምር ላይ ብቻ ሳይወርድ ጠል በምድር ሁሉ ላይ ይውረድ" አለው። እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት እንዳለው አደረገ። ፀምሩ ብቻ ደረቅ ሁኖ ጠል በምድር ሁሉ ላይ ወረደ። ጌዴዎንንም የእግዚአብሔር መንፈስ ረድኤት አጸናው ነጋሪትንም መታ አብያዜርም በኋላው ሁኖ ደነፋ ወደ ነገደ ምናሴር፣ ወደ ነገደ ዛብሎን፣ ወደ ነገደ ንፍታሌምም መልክተኞችን ላከ ወጥተውም ተቀበሏቸው። ጌዴዎንም ከርሱ ጋር ያሉ ወገኖቹም ሁሉ ሔዱ አሮኤድ በሚባል አገርም ሰፈሩ የመሰድያምና የአማሌቅ ሠራዊትም በእንበሬም ቆላ መሠዊያ ቀኝ ሰፈሩ።

እግዚአብሔርም ጌዴዎንን "እጃችን አዳነችን ብለው እንዳመኩብኝ የምድያምን ሰዎች በእጃቸው መጣል እንደማልችል ካንተ ጋር ያሉ ሕዝብ ብዙ ናቸው" እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው "ከእናንተ የሚፈራ የመመደነግጥ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይመለስ" ብለህ ለሕዝቡ ንገራቸው። ሕዝቡም ከገለዓድ ተመለሱ ከሕዝቡም ሁለት እልፍ ከሁለት ሽህ ተመልሰው እልፍ ሰዎች ቀሩ።

እግዚአብሔር ጌዴዎንን "ገና ብዙ ሕዝብ አሉ ወደ ውኃ አውርደህ በዚያ ፈትናቸው እኔ ይሒዱ የምልህ ሰዎች እነርሳቸው ካንተ ጋር ይሒዱ" አለው ሕዝቡንም ወደ ውኃ አወረዳቸው። እግዚአብሔር ጌዴዎንን "ውሻ በምላሱ ጠለፍ ጠለፍ አድርጎ እንዲጠጣ ከውኃው ጠለፍ ጠለፍ አድርጎ የሚጠጣውን ሁሉ ለብቻው አቁመው ውኃን ይጠጣ ዘንድ በጉልበቱ የተንበረከከውንም ሁሉ ለብቻው አቁመው" አለው። በምላሳቸው ጠለፍ ጠለፍ አድርገው የጠጡ ሰዎች ቊጥራቸው ሦስት መቶ ሆነ የቀሩት ሕዝብ ግን ውኃን ይጠጡ ዘንድ በጉልበታቸው ተንበረከኩ።

እግዚአብሔርም ጌዴዎንን "እንደዚህ በእጃቸው ውኃን በጠጡት በእነዚህ ሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ የምድያምን ሰዎች ወደ ቤታቸው ይመለሱ" አለው። በዚያችም ሌሊት እሊህ ሦስት መቶ ሰዎች መለከትን ነፉ "ይህ የእግዚአብሔር ኃይልና የጌዴዎን ጦር ነው" ብለው ጮኹ። የምድያምም ሰዎች የመለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔር በልባቸው ፍርሀትን አሳድሮባቸው ደንግጠው ሸሹ እግዚአብሔርም ያንዱን ሰይፍ ወዳንዱ ወደ ጓደኛው መለሰ በሠራዊቶቻቸው ሁሉ እርስበርስ መተላለቅ ሆነ መኳንንቶቻቸውን ኄሬብንና ዜብን ነገሥቶቻቸው ዛብሄልንና ስልማናንም ገደሏቸው ከምድያምም ሠራዊት ፈረሰኞችና ጦረኞችን አንድ መቶ ሁለት ሽህ ገደሉ።

ከዚህም በኋላ የምድያም ሰዎች በእስራኤል ፊት ተዋረዱ ዳግመኛም ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም በጌዴዎንም ዘመን ምድር አርባ ዘመን ዐረፈች። ከዚህም በኋላ በዚች ቀን ታኅሣሥ16 በሰላም በፍቅር ዐረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ማርያም_እህተ_ሙሴ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የሙሴ እኅት ማርያም መታሰቢያዋ ነው፡፡ ይህች እናት የሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴና የሊቀ ካህናቱ ቅዱስ አሮን ትልቅ እህት ስትሆን ወላጆቿ እንበረምና ዮካብድ ይባላሉ:: እሥራኤል ከግብጽ ባርነት እንዲወጡ የእርሷን ያህል አስተዋጽኦ ያደረገች ሴት የለችም::

ከመነሻውም ቅዱስ ሙሴን የጠበቀች: በሕግ በሥርዓት እንዲያድግ ከእናቱ ጋር ያገናኘች: ወገኖቿ ከግብጽ ሲወጡም ሴቶችን የመራች እናት ናት:: ወንድሞቿን ሙሴንና አሮንንም ታገለገላቸው ነበር:: በተለይ እግዚአብሔር ባሕረ ኤርትራን የብስ ሲያደርጋት ከበሮን አንስታ "ንሴብሖ ለእግዚአብሔር" ብላ ፈጣሪዋን አመስግናለች:: (ዘጸ. 15:20)

አንድ ጊዜም "ኢትዮዽያዊቷን ሲፓራን ለምን አገባህ" በሚል ስለ ተናገረችው እግዚአብሔር ተቆጥቶ በለምጽ መቷታል:: (ዘኁ. 12:1) ቆይቶም በቅዱሱ ምልጃ ምሯታል:: ማርያም በመንገድ ሳሉ: ወደ ርስት ሳይደርሱ ዐርፋ ተቀብራለች:: (ዘኁ. 20:1)

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)