ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ጥቅምት_12

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት አስራ ሁለት በዚህች ዕለት ሊቀ መላእክት #ቅዱስ_ሚካኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ #ቅዱስ_ዳዊትን በሳኦል ፈንታ እንዲሾመው ለሳሙኤል የነገረበት እና በጎልያድ ላይ ኃይልን የሰጠበት እንዲሁም የወንጌላዊው #ቅዱስ_ማቴዎስ እና #የቅዱስ_ድሜጥሮስ የዕረፍት ቀን ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዳዊት_ልበ_አምላክ (የነገሠበት)

ጥቅምት ዐሥራ ሁለት በዚች ዕለት የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ የሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። በዚችም ቀን ወደ ነቢይ ሳሙኤል #እግዚአብሔር ልኮታልና የዳዊት አባት ወደሆነ በቤተ ልሔም ወደሚኖር ወደ እሴይ ቤት ይሔድ ዘንድ በቂስ ልጅ በሳኦልም ፈንታ ለእስራኤል ልጆች እንዲነግሥ ልጁ ዳዊትን ይቀባው ዘንድ አዘዘው።

ሳሙኤልም ወደ እሴይ ቤት ሔዶ ልጆችህን ሁሉንም አቅርብልኝ ብለው እሴይም ከዳዊት በቀር ሁሉንም አቀረባቸው እርሱ በእርሻ ውስጥ በጎችን ይጠብቅ ነበርና።

ሳሙኤልም የመንግሥት ቅባት ያለበትን ብልቃጥ በራሳቸው ላይ ከፍ ከፍ በአደረገ ጊዜ #እግዚአብሔር አልመረጣቸውም ። ሳሙኤልም እሴይን ልጆችህ እነዚህ ብቻ ናቸውን አለው ዕሴይም በጎች የሚጠብቅ አንድ ትንሽ ልጅ አለ አለው።

ሳሙኤልም ደግሞ ዕሴይን እሱ ሳይመጣ ምሳ አልበላምና ልከህ አስመጣው አለው። እሱም ልኮ አስመጣው መልኩም ቀይ ዐይኖቹም የተዋቡ አርአያውም ያማረ ነው #እግዚአብሔርም ሳሙኤልን ይህ ይበልጣቸዋልና ተነሥተህ ቅባው አለው። በዚያንም ጊዜ ሳሙኤል የመንግሥት ቅባት ያለበትን ቀንድ አምጥቶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው ከዚያችም ቀን ጀምሮ ለሁል ጊዜ የ #እግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ አደረበት በእስራኤል ልጆችም ላይ ነገሠ።

ደግሞ ሁለተኛ በዚች ቀን #እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ወደ ዳዊት ላከው ረዓይታይ ጎልያድን እስኪገድለውና የእስራኤልን ልጆች እስከሚያድናቸው ረድቶ ኃይልን ሰጠው።

ስለዚህም የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን እናደርግ ዘንድ የቤተክርስቲያን መምህራን አዘዙን።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያው_ቅዱስ_ማቴዎስ

#የጌታችን_አምላካችንና_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን አምላካዊ ትእዛዝ ተቀብለው ወንጌልን ለመላው ዓለም በማብሠር መምለክያነ ጣዖትን ወደ አሚነ #እግዚአብሔር፣ አሕዛብን ወደ ክርስትና ከመለሱ ቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ አንደኛው ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ አገሩ ናዝሬት፣ የዘር ሐረጉም ከይሳኮር ነገድ ሲኾን አባቱ እልፍዮስ (ዲቁ)፣ እናቱ ደግሞ ካሩትያስ ይባላሉ፡፡

ለደቀ መዝሙርነት ከመመረጡ በፊት ‹ሌዊ› ይባል ነበረ፤ ከተጠራ በኋላ ግን ‹ማቴዎስ› ተብሏል፡፡ ‹ማቴዎስ› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹ጸጋ #እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ስጦታ)› ማለት ሲኾን ስሙን ያወጣለትም #ጌታችን_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ነው፡፡ ለወንጌል አገልግሎት የተጠራውም በቅፍርናሆም ከተማ ከቀራጭነት ሥራ ላይ ነው /ማቴ. ፱፥፱-፲፫፤ ሉቃ. ፭፥፳፯-፴፪/፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ቍጥሩ ከ፲፪ቱ ሐዋርያት ሲኾን ከ፬ቱ ወንጌሎች አንደኛውን የጻፈው እርሱ በመኾኑ ‹ወንጌላዊ› እየተባለ ይጠራል፡፡ ወንጌሉን የጻፈውም ጌታችን ባረገ በ፰ኛው ዓመት መጨረሻ በ፵፩ /፵፪ ዓ.ም፣ ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በመጀመሪያው ዘመን በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው /ማቴ.፳፰፥፳/፡፡ ጽሕፈቱንም በፍልስጥኤም ጀምሮ በህንድ ፈጽሞታል፡፡

እንደ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ወንጌሉ በውስጡ ከ፻፶ በላይ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን ማካተቱ አይሁድን ለማሳመን የተጻፈ ለመኾኑ ማስረጃ ነው፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ከኦሪታዊ ይዘቱ አኳያ በመጀመሪያ ተቀመጠ እንጂ የተጻፈው ግን ከማርቆስ ወንጌል ቀጥሎ እንደኾነም መምህራን ይናገራሉ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በሀገረ ስብከቱ በፍልስጥኤም #ጌታችን ከፅንስ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ድረስ ያደረጋቸውን ተአምራት፣ ያስተማረውን ትምህርትና የሠራቸውን ትሩፋቶች ሲያስተምራቸው ብዙ አሕዛብ ከኦሪት ወደ ወንጌል፤ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመልሰዋል፡፡ ምእመናኑ ‹‹በቃል ያለ ይረሳል፤ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳልና ያስተማርኸንን ጻፍልን›› ብለውት፤ አንድም እንደ አባትነቱ ከራሱ አንቅቶ /አመንጭቶ/፤ አንድም አይሁድ ክርስቲያኖችን ‹‹ክርስቶስ ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም መኾኑን ሠፍራችሁ፣ ቈጥራችሁ አስረዱን›› ቢሏቸው ለማስረዳት የዕውቀት ማነስ ነበረባቸውና እርሱ ጽፎላቸዋል፡፡

ወንጌሉን ከጻፈ በኋላም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ አፓንጌ በሚባል አገር ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን በ #ክርስቶስ አሳምኗል፡፡ የማቴዎስን ወንጌል ወንጌላዊው /ሐዋርያው/ ዮሐንስ በእልአንሳን፣ በህንድና በኢየሩሳሌም አገሮች እየተረጐመ አስተምሮታል፡፡ የእርሱ ስብከት በመጽሐፍ ቅዱስ አለመጠቀሱም መላ ሕይወቱን ለ #ክርስቶስ አገልግሎት የሰጠ ሐዋርያ መኾኑን እንደሚያሳይ መምህራን ይመሰክራሉ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ‹‹ወልደ ዳዊት፣ ወልደ አብርሃም›› በማለት የ #ክርስቶስን ምድራዊ ልደት /ሰው መኾን/ ጽፏልና ከአራቱ የኪሩቤል ገጽ መካከል በአንደኛው በገጸ ሰብእ ይመሰላል፡፡ የኤፌሶን ወንዝ ፈለገ ሐሊብ ይባላል፤ ርስትነቱም ለሕፃናት ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም በዘር የሚወለዱ አበውን ልደት ጽፏልና፤ ዳግመኛም ሄሮድስ ስላስፈጃቸው ሕፃናት ተናግሯልና በኤፌሶን ወንዝ ይመሰላል፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልን አስተምሮ ብዙዎችን ወደ አሚነ #እግዚአብሔር ከመለሰ በኋላ #ጌታችን ወደ ካህናት አገር እንዲሔድና የካህን ልብስ ለብሶ፣ ፀጉሩንና ጺሙን ተላጭቶ፣ በቀኝ እጁ ዘንባባ ይዞ ወደ አገሩ ቅፅር እንዲገባ ስላዘዘው በደመና ተጭኖ ሔዶ ወደ ቤተ ጣዖታቱ ገብቶ በጸለየ ጊዜ መብረቅ የመሰለ ብርሃን ወረደ፡፡ የአምላክን ከሃሊነት ለመግለጥ በተከሠተው ርዕደ መሬትም የአገሩ ጣዖታት ኹሉ ወድቀው ተሰባበሩ፡፡ አርሚስ የሚባለው የጣዖቱ ካህንም ካየው አምላካዊ ብርሃንና ድንቅ ተአምር የተነሣ በ #ክርስቶስ አምኖ ከተጠመቀ በኋላ የቅዱስ ማቴዎስ ረድእ ኾኗል፡፡

ይህ ክሥተትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙዎችን በ #ክርስቶስ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል፡፡ ያማኞች ቍጥርም ፬ ሺሕ እንደ ነበረ በገድለ ሐዋርያት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በኋላ የንጉሡ ልጅ በሞተ ጊዜ ቅዱስ ማቴዎስ ወደ #እግዚአብሔር ጸልዮ ከሞት ቢያስነሣው ንጉሡ፣ ቤተሰቦቹና የአገሩ ሰዎች ኹሉ በ #ኢየሱስ_ክርስቶስ አምነው አጵሎን የተባለውን ጣዖት በእሳት አቃጥለው ቤተ ጣዖቱን የአምልኮተ #እግዚአብሔር መፈጸሚያ ሥፍራ አድርገውታል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም አርሚስን ኤጲስ ቆጶስ በማድረግ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾሞላቸዋል፡፡

በገድለ ሐዋርያት እንደ ተጠቀሰው ቅዱስ ማቴዎስ ከማረፉ በፊት በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል፤ በዚያም ሄሮድስ በግፍ በጨፈጨፋቸው ሕፃናት ክብረ በዓል #ጌታችን ወደ እነርሱ ሲመጣ፣ መላእክትም በዙሪያው ከበው ሲያመሰግኑት ያይ ነበር፡፡ ከዚያ ተመልሶም በየአገሩ እየዞረ ወንጌልን አስተምሯል፤ ካስተማረባቸው አገሮችም ፍልስጥኤም፣ ፋርስ፣ ባቢሎን፣ ኢትዮጵያና ዓረቢያ ይጠቀሳሉ፡፡ የማስተማር ተልእኮው የተከናወነውም በታንሿ እስያ ውስጥ ነው፡፡ ግሪካውያን አሕዛብ «አምላካችንን ሰደበብን» ብለው አሥረውት በነበረ ጊዜም ወኅኒ ቤት ኾኖ ይሰብክ ነበር፡፡