ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ጳጒሜን_1

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተባረከ የጳጒሜን ወር ባተ። በዚህች ቀን ጳጒሜን አንድ #ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ የታሰረበት፣ የወንጌላዊ የቅዱስ #ዮሐንስ ረድእ #የዑቲኮስ_ሐዋርያና #ቀሲስ_አባ_ብሶይ የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ

ጳጒሜን አንድ ቀን በዚህች ዕለት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ወደ እሥር ቤት ገብቷል። ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ ንጉሡ ሔሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሔሮድያዳን በማግባቱና በመሰል ክፋቶቹ ቅዱስ ዮሐንስ ይገስጸው ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ "መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ" "ፊት አይቶ የማያዳላ" ነውና ገሰጸው።

ሔሮድስ ቅዱሱን ይፈራው ያከብረውም ነበር። በኋላ ግን ፈቃደ ሥጋው ስላየለበት በተለይ ደግሞ ከሰባት ቀናት በኋላ ልደቱን ሲያከብር እንዳይረብሸው በመስጋት በዚህች ቀን በወታደሮቹ አስይዞ እሥር ቤት ውስጥ
ጥሎታል። ለሰባት ቀናት በጨለማ ውስጥ አሥሮ መስከረም 2 ቀን አስቆርጦታል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዑቲኮስ_ሐዋርያ

በዚህች ቀን የወንጌላዊ ዮሐንስ ረድእ ሐዋርያና ሰማዕት የከበረ ዑቲኮስ አረፈ ።

ይህም ቅዱስ ወንጌላዊ ዮሐንስን ሲያገለግለውና ሲታዘዘው ኖረ። ከዚያም ከሐዋርያ ጳውሎስ ጋራ ሔደ እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም እንዲሰብክ አዘዘው በአረማውያንና በዮናናውያንም መካከል ሰበከ። የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስንም ወደማወቅ ብዙዎችን መለሳቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው።

የጣዖታት ቤቶችን አፍርሶ አብያተ ክርስቲያናትን ሠራ። ከከሀድያንም ብዙ መከራ ደረሰበት መታሠርና ብዙ ቀኖች ግርፋቶችን በመቀበል፤ የ #እግዚአብሔርም መልአክ ወደ እሥር ቤት ከምግብ ጋር መጥቶ ይመግበዋል።

ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ጣሉት እሳቱም ከቶ አልነካውም ሁለተኛም ለአንበሶች ጣሉት እነርሱም እንደ በጎች ሆኑለት። ከዚህም በኋላ ወደቍስጥንጥንያ ሀገር ሔደ። ሲሔድም የ #እግዚአብሔር መልአክ ይመራውና ያጸናናው ነበር ተጋድሎውንም ፈጽሞ በበጎ ሽምግልና ወደ እግዚአብሔር ሔደ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቀሲስ_ብሶይ_ሰማዕት

በዚችም ቀን የአባ ሖር ወንድም ቀሲስ ብሶይ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ ከአንፆኪያ አገር ክብር ካላቸው ወገኖች ውስጥ ነው ስለ ዕውቀቱና ስለ ሃይማኖቱ ጽናት ቅስና ተሾመ።

ወንድሙ አባ ሖርና እናቱ ወደ ግብጽ አገር ሔደው በሰማዕትነት ከሞቱ በኋላ እርሱም ተነሥቶ ወደ እስክንድርያ ሥጋቸውን ያይ ዘንድ ሔደ። ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች ሰጠ ከሦስት እንጀራና ከሚመረጐዛት ከአንዲት የሰኔል በትር በቀር ምንም አልያዘም ነበር።

ወደ እስክንድርያ አገርም በደረሰ ጊዜ የዘመዶቹ በድን ወዳለበት ሰዎች መርተው አደረሱት የእናቱንና የወንድሙንም ሥጋ በአየ ጊዜ ከእርሳቸው ስለ መለየቱ መሪር ልቅሶን አለቀሰ። ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ሒዶ በፊቱ ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ።

ለመኰንኑም የአባ ሖር ወንድም እንደሆነ ነገሩት መኰንኑም ታላቅ የደንጊያ ምሰሶ በሆዱ ላይ እንዲአቆሙበት አዘዘ ይህንንም በአደረጉበት ጊዜ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጠ።

ከዚህም በኋላ ደግሞ ሥጋውን ከወንድሙና ከእናቱ ሥጋ ደግሞ ቍጥራቸው ሰማንያ ስምንት ከሆነ ከሌሎች ሰማዕታት ሥጋ ጋር በአንድነት ያቃጥሉ ዘንድ መኰንኑ አዘዘ ወደ እሳት በጨመሩአቸውም ጊዜ ከቶ እሳቱ አልነካቸውም።

ምዕመናን ሰዎችም መጥተው የከበሩ የአባ ሖርንና የወንድሙ የአባ ብሶይን የእናታቸውንም ሥጋ ወሰዱ። ሀገሯ ዲብቅያ የሚባል የቅድስት ዳሞንንም ሥጋ፣ ሀገሩ በረሞን የሚባል የቅዱስ ቢማኮስንም ሥጋ፣ ጡልያ ከሚባል አገር የመጣ የውርሱኑፋን ሥጋም፣ አብስላሲ ወደሚባል አገር እስከሚያደርሷቸው በመርከብ ጫኗቸው። የስደቱ ወራት እስከሚፈጸም አክብረው ወስደው በመልካም ቦታ አኖሩዋቸው።

ከዚህም በኋላ አብያተ ክርስቲያን ተሠርቶላቸው ሥጋቸውን በውስጣቸው አኖሩ ከእርሳቸውም ተአምራት ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆኑ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእኒህ ቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጳጉሜን_1#ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)