ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
አቡነ አብሳዲ ገዳማትንና ምንኵስናን ለማስፋፋት ብዙ የደከሙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ቀንና ሌሊት ሳያርፉ ምእመናን በማስተማር አባታቸው ኤዎስጣቴዎስ እንዳስተማሯቸው
ገዳማትንና ምንኵስናን በኤርትራና በኢትዮጵያ በማስፋፋት ለገዳማዊ ምናኔ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሐዋርያ ናችው፡፡ በመንፈስ የወለዷቸው በርካታ መነኵሳት ልጆቻቸው አማካኝነት በኢትዮጵያና በኤርትራ የተገደሙት ገዳማት ከ120 በላይ ናቸው፡፡

በልጆቻቸው አማካኝነት በኤርትራ ከተገደሙት ገዳማት ውስጥ፦ ደብረ ኮል አቡነ ብሩክ (መራጉዝ)፣ የአቡነ ዮናስ ገዳማት (ደብረ ድኹኻን ቆሓይን፣ ደብረ ጽጌ ትምዛእ፣ ደብረ ሣህል ዛይዶኮሎም)፣ ደብረ አቡነ ሙሴ (ማይ ጎርዞ)፣ ደብረ ሲና አቡነ ድምያኖስ፣ ምድሪ ወዲ ሰበራ፣ ደብረ ሐዋርያት አቡነ ሴት (ዓዲ ቂታ)፣ ደብረ ማርያም (ዓይላ) እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ እነኚህን እንደ ምሳሌ ጠቀስን እንጂ በኢትዮጵያም የአቡነ አብሳዲ ልጆች የመሠረቷቸው በርካታ ገዳማት አሉ፡፡

አባታችን የረጅም ዘመን ተጋድሏቸውን በፈጸሙ ጊዜ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ለኹለተኛ ጊዜ ተገልጦላቸው ‹‹በሰሜን ያለች ይኽችን ገዳም ባርኬልሃለውና ከልጆችህ ጋር በእርሷ ኑር›› ካላቸው በኋላ ቃልኪዳን ገብቶላቸው ተሰወረ፡፡ ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ይኽችም ለአባታችን የተሰጠቻቸው ገዳም ደበረማርያም (ደብረ ክሳሄ) ናት፡፡

ከዚኸም በኋለ ቅዱስ አባታችን አብሳዲ ደከመኝ ልረፍ ሳይሉ መላ ዘመናቸውን ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን ፈጽመው ከ #እግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ተቀብለው በ101 ዓመታቸው መስከረም 30 ቀን 1383 ዓ.ም ዐርፈው ቆሓይን በምትገኘው ገዳማቸው ደብረ ክሳሄ ደብረ ማርያም ገዳም ተቀበሩ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አብሳዲ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ገሪማ_ዘመደራ (#አባ_ይስሐቅ)

አቡነ ገሪማ የተወለዱት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሮም ውስጥ ነው። ወላጆቻቸው መስፍንያኖስ እና ሰፍንግያ #እግዚአብሔርን የሚወዱ የሮም ከተማ ንጉሥና ንግሥት ነበሩ። ልጅ በማጣታቸው #እመቤታችንን ለመኑ።

እመ ብርሃንም ደግ ፍሬ ሰጠቻቸው። ስሙን ይስሐቅ ብለው አሳደጉት። ገና በልጅነቱ አባቱ ድንገት በመሞቱ ይስሐቅ በዙፋኑ ተተክቶ ነገሠ። ለሰባት ዓመታት ሕዝቡን በፍትሕ እያስተዳደረ መጻሕፍትንም እያጠና ኑሯል።

አንድ ቀን ግን ከግብጽ በርሃ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው። ላኪው አባ ጰንጠሌዎን ሲሆኑ መልዕክቱ "ምድራዊ ንግሥና ምን ያደርግልሃል? ይልቁኑስ በሰማይ ለዘላለም እንድትነግሥ ወደ በርሃ ና!" የሚል ነበር።

ንጉሥ ይስሐቅ አላመነታም ሌሊት ተነስቶ ወደ ፈጣሪው ጸልዮ በለበሳት ልብስ ብቻ ዙፋኑን ጥሎ መነነ። ድንገት ግን ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ በቀኝ ክንፉ ነጥቆ ግብጽ አባ ጰንጠሌዎን በዓት ላይ አኖረው።

እርሳቸውም ተቀብለው ፍኖተ አበውን አስተምረው አመነኮሱትና ዘጠኝ ሁነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ብዙ ሲሰሩ አንዱና ታላቁ አባ ይስሐቅ (ገሪማ) ናቸው። ሰውነታቸውን በገድል ቀጥቅጠውት ቆዳና አጥንታቸው ተጣብቆ ነበር።

አንድ ቀን አባ ይስሐቅ በልቶ ቀደሰ ብለው ነግረዋቸው አባ ጰንጠሌዎን አዘኑ። ልምከር ብለው "ልጄ ይስሐቅ የሰማውብህ ነገር አለና ሰዎችን አርቅልኝ።" አሉ። አባ ይስሐቅ ግን "ሰዎች ብቻ አይደሉም፤ ዛፉም እንጨቱም ገለል ይበል።" ቢሉ የቤተ ክርስቲያኑ አጸድ አንድ ምዕራፍ (ሁለት መቶ ሜትር) ተጠራርጎ ሸሸ።

ይህንን የተመለከቱት አባ ጰንጠሌዎን "ወልድየ ይስሐቅ ገረምከኒ (ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ)።" አሏቸው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮም "አቡነ ገሪማ" ተብለው ቀሩ።

አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሲሔዱ እነዚያ የሸሹ ዛፍና ድንጋዮች "ገሪማ ለእኛም ግሩም ነህ።" እያሉ በዝማሬ ተከትለዋቸዋል። ይህም የተደረገው በዚህች ዕለት መስከረም ፴ ቀን ነው።

ጻድቁ ወንጌልንና ገዳማትን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል፦
፩. ስንዴ ጧት ዘርተውት በዘጠኝ ሰዓት ያፈራ ነበር። "በጽባሕ ይዘርዕ ወበሠርክ የአርር" እንዲል።
፪. ጧት የተከሉት ወይን በዘጠኝ ሰዓት ያፈራ ነበር።
፫. አንድ ቀን ምራቃቸው ቢወድቅ ጠበል ሆኖ ዛሬም አለ።
፬. ብዕራቸው ወድቃ አብባ አፍርታለች።
፭. አንድ ቀን ድርሳን እየደረሱ ሊመሽ በመሆኑ ፀሐይን አቁመዋታል።

ከእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ #ጌታችን ተገልጦ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ሰጣቸው። "ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገ እስከ አሥራ ሁለት ትውልድ እምርልሃለሁ። አንተ ግን ሞትን አትቀምስም።" ብሏቸው ተሰወረ። ያን ጊዜ መላእክቱ በሠረገላ ጭነው እየዘመሩ ብሔረ ሕያዋን አድርሰዋቸዋል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_30)