#ነሐሴ_2
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሁለት በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር #ቅድስት_አትናስያ አረፈች፣ ከነገሥታት ወገን የሆነች #ቅድስት_ኢዮጰራቅስያ አረፈች፣ በተጨማሪ በዚች ቀን #ዲያቆናዊት_ኢዮኤልያና ዕረፍት፣ #ሰማዕቱ_ደሚናና ሰማዕታት የሆኑ ወንድሞቹ መታሰቢያቸው ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅድስት_አትናስያ_ቡርክት
ነሐሴ ሁለት በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር ቅድስት አትናስያ አረፈች።
የዚችም ቅድስት ወላጆቿ ባለጸጎች ነበሩ እነርሱም በሞቱ ጊዜ ቤቷን ለእንግዳ ማደሪያ ታደርግ ዘንድ በጎ ኃሳብ አሰበች ወደርሷም የሚመጡትን እንግዶች ሁሉ ትቀበላቸው ነበር። በገዳም ለሚኖሩ መነኰሳትም የሚያስፈልጓቸውን ትሰጣቸው ነበር ስለ በጎ ሥራዋም ይወዷት ነበር።
ከዚህም በኋላ ግብራቸው የከፋ ክፉዎች ሰዎች ወደርሷ ተሰብስበው ኃሳቧን ወደ ኃጢአት ሥራ መለሱትና ኃጢአትን አብዝታ ትሠራ ጀመር። በአስቄጥስ ገዳም በሚኖሩ አረጋውያን ቅዱሳን ዘንድም ወሬዋ ተሰማ ስለእርሷም እጅግ አዘኑ አባ ዮሐንስ ሐጺርንም ጠርተው ስለርሷ የሆነውን ነገሩት አስቀድማም ከእነርሱ ጋራ በጎ ስለ ሠራች ወደ እርስዋ ይሔድ ዘንድ ነፍስዋንም ለማዳን ይወድ ዘንድ ለመኑት።
እርሱም ትእዛዛቸውን ተቀበለ በጸሎታቸውም እንዲረዱት ለመናቸው ያን ጊዜም አባ ዮሐንስ ሐጺር ተነሥቶ ሔደ አትናስያ ወዳለችበት ቦታ ደረሰ ለበረኛዋም ለእመቤትሽ ስለእኔ ንገሪ አላት። በነገረቻትም ጊዜ ለረከሰ ሥራ እንደሚፈልጓት ሰዎች ሁሉ የመጣ መሰላትና አጊጣ በዐልጋዋ ላይ ሁና ጠራችው። ወደርሷም ገባ እርሱም እንዲህ እያለ ይዘምር ነበር በሞት ጥላ ውስጥ ብሔድም እንኳ ክፉን አልፈራውም አንተ ከእኔ ጋራ ነህና።
ከእርሷ ጋራም አስቀመጠችው ያን ጊዜም ራሱን ዘንበል አድርጎ አለቀሰ ለምን ታለቅሳለህ አለችው እርሱም ሰይጣናትን በላይሽ ሲጫወቱ አየኋቸው ክብር ይግባውና #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስን ለምን አሳዘንሺው የቀድሞ በጎ ሥራሽን ትተሽ ወደ ጥፋት ሥራ ተመልሰሻልና አላት።
ቃሉንም ሰምታ ደነገጠችና ተንቀጠቀጠች ምን ይሻለኛል አለችው ንስሐ ግቢ አላት እርሷም #እግዚአብሔር ይቀበለኛልን አለችው እርሱም አዎን አላት እርሷም ወደምትሔድበት ከአንተ ጋራ ውሰደኝ አለችው እርሱም ነዪ ተከተይኝ አላት።
ያን ጊዜም ፈጥና ተነሥታ በኋላው ተከተለችው ከገንዘቧም ምንም ምን አልያዘችም። በመሸም ጊዜ ለማደር ወደ ጫካ ውስጥ ገቡ በዚያም ለእርስዋ ቦታ አዘጋጅቶ እስኪነጋ በዚህ አረፍ ብለሽ ተኚ እኔም ወደዚያ እሆናለሁ አላት። ይህንንም ብሎ ከእርሷ ጥቂት ተገልሎ እየጸለየ ብቻውን ተቀመጠ።
በሌሊቱ እኩሌታም ሊጸልይ ተነሣ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ አየ የ #እግዚአብሔርም መላእክት የከበረች ነፍስን ተሸክመው ሲወጡ አይቶ አደነቀ። በነጋም ጊዜ ወደ ርሷ ሔደ ሙታም አገኛት እጅግም አዘነ ስለ ርሷም ያስረዳው ዘንድ እየሰገደ ወደ #እግዚአብሔር ለመነ።
ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ከቤቷ በወጣች ጊዜ #እግዚአብሔር ንስሓዋን ተቀብሎ ኃጢአትሽ ተሠረየልሽ ብሎአታል። ከዚህም በኋላ ሒዶ ለአረጋውያን የሆነውን ሁሉ ነገራቸው እነርሱም እርሱ እንዳያት ማየታቸውን ነገሩት የኃጢአተኛን ወደ ንስሐ መመለሱን እንጂ ሞቱን የማይሻ #እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅድስት_ኢዮዸራቅስያ_ድንግል
በዚህችም ቀን ከነገሥታት ወገን የሆነች ቅድስት ኢዮጰራቅስያ አረፈች። የእርስዋም የአባቷ ስም ኢጣጎኖስ ነው የንጉሥም አማካሪ ነበር የእናቷም ስም ኢዮጰራቅስያ ነው እነርሱም ደጎች ነበሩ ጾምና ጸሎትንም ወደ #እግዚአብሔር የሚያቀርቡ ነበሩ። ይችንም ቅድስት በወለዷት ጊዜ በእናቷ ስም ኢዮጰራቅስያ ብለዉ ጠሩዋት።
ከጥቂት ጊዜ በኋላም አባቷ አረፈ ዕድሜዋም ስድስት ዓመት በሆነ ጊዜ እናቷ ወደ ደናግል ገዳም ከእርሷ ጋር ወሰደቻት ይህችም ቅድስት ደናግሉ ሲያገለግሉ አይታ ስለ ምን እንዲህ ደክማችሁ ትሠራላችሁ አለቻቸው እነርሱም ክብር ይግባውና ስለ #ክርስቶስ ነው ብለው መለሱላት ወደ ዲያቆናዊትም ሒዳ ያመነኲሷት ዘንድ ለመነች እነርሱም ለእናቷ ነገሩዋት እናቷም ለዲያቆናዊተዋ ሰጠቻት በደናግሉም ሁሉ ዘንድ አደራ ሰጠቻት ከጥቂትም ቀኖች በኋላ እናቷ አረፈችና ቀበሩዋት።
ከዚህም በኋላ ቅድስት ኢዮጰራቅስያ የምንኲስና ልብስን ለበሰች በጾም በጸሎትና በሰጊድ ተጋድሎ ጀመረች በየሰባት ቀንም ትጾም ነበር ሰይጠንም በእርሷ ላይ ቀንቶ ሊፈትናት ጀመረ ወደ ውኃ ውስጥ እርስዋን የሚጥልበት ጊዜ ነበር እንጨትም ስትፈልጥ በምሳር የሚአቊስልበት ጊዜ ነበር። የፈላ ውኃም በላይዋ የሚያፈሰበት ጊዜ ነበር ነገር ግን ምንም ምን የጐዳት የለም።
ለደነግሎችም ስታገለግል ብዙ ዘመናት ኖረች ምንም አትታክትም ነበር በምድርም ላይ አትተኛም መላዋን ሌሊት ቁማ በጸሎት ታድር ነበር እንጂ ከገድሏ ጽናትም የተነሣ ደናግሉ እስከሚያደንቁ ድረስ አርባ ቀን ቁማ ትፈጽም ነበር።
ከዚህም በኋላ #ጌታችን በሽተኞችን በማዳን አጋንንትን በማስወጣት የዕውሮችን ዐይን በመግለጥ የአንካሶችንም እግር በማስተካከል ድንቆችንና ተአምራቶችን በእጆቿ ገለጠ።
ዲያቆናዊት ኢዮኤልያም ለኢዮጰራቅስያ መጸሐፍትንና የምንኵስናንም ሥርዓት አስተማረቻት በሥራም ሁሉ ትሳተፋት ነበር እጅግም ይፋቀሩ ነበር እርሷም ሰማያዊ ሙሽራ ወደአለበት የመንግሥት አዳራሽ የማያልቅ ተድላ ደስታም ወደአለበት ኢዮጵራቅስያን ሲያወጧት ራእይን አየች።
በነቃችም ጊዜ ለደናግል ነገረቻቸው ወደርሷ ሲሔዱም በትኩሳት በሽታ ታማ አገኟት ስለእነርሱም እንድትጸልይ ለመኑዋት እርሷም ደግሞ በጸሎታቸው እንዲአስቧት ለመነቻቸው ያን ጊዜም ጸሎት አድርጋ መረቀቻቸውና በሰላም አረፈች በእናቷም መቃብር ውስጥ ቀበሩዋት።
ወዳጅዋ ኢዮኤልያም ወደ መቃብርዋ ሒዳ ጸለየችና በሦስተኛው ቀን አረፈች ከእርሷም ጋር ተቀበረች።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_2)