ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
ፈዛዛ የሚወዱትን ደጋጎች የሚያደርጉ ሰዎች ይመጣሉ፡፡

በመጨረሻው ዘመን ኃጥአን በጻድቃን ይመሰላሉ፣ ጻድቃንን ኃጢአተኞች ያደርጓቸዋል፡፡ በዚያን ዘመን እውነተኛዎቹ መምህራን አይሾሙም፣ ኃጢአተኞች መማለጃ ሰጥተው ወሬ እያቀበሉ ይሾማሉ፣ እንደ እባብ ክፉ ነገርን ለማድረግ ፍላፃቸውን ያሾሉ ደጋግ ሰዎችን በነገር ያጠፏቸው ዘንድ በእውነት ንጹሕ የሆኑትን ሰዎች አመፅን በተመላ አንደበታቸው ሹመትን ከመውደድ የተነሣ በቅናት ያጠፏቸዋል፡፡ በዚያን ዘመን መጻሕፍትን የሚያውቁ አይሾሙም፣ ነገርን የሚያመላልሱና የአገሮችን ቋንቋ የሚያውቁ ከመኳንንትና ከነገሥታት ዘንድ ሔደው ነገርን የሚሠሩ ሰውን የሚያጣሉ በአመፅ ሹመትን የሚያገኙ ብቻቸውን ይሾማሉ እንጂ ደጋጎች አይሾሙም፡፡ በሚመረጡበትም ጊዜ ከአባታቸው ከሰይጣን ጋር ሆነው ‹እገሌ መጻሕፍትን ያውቃል፣ የአገሮችን ቋንቋ የሚያውቅ ይሾም› ይላሉ፡፡ ያንጊዜም አመፅ ይበዛል፣ ፍቅርም ትጎድላለች፡፡ ከእኔ በኋላ የሚሆነውን እነሆ ነገርኳችሁ ይህንንም አውቃችሁ በልቡናችሁ ያዙ፡፡››
#ጌታችን ለአቡነ ፊሊጶስ የገባላቸው ልዩ ቃልኪዳን፡- ‹‹ገድልህንና ስለ እኔ የታገስካቸውን መከራዎችህን የጻፈውን ከሁላቸው ከቅዱሳንና ከሰማዕታት ጋር በሰማያዊት ኢየሩሳሌም በወርቀ ቀለም ለዘለዓለሙ ስሙን እጽፍልሃለሁ፡፡ ሥጋህ ከተቀበረበት ቦታ ይቅርታዬንና ቸርነቴን አደርጋለሁ፡፡ መቃብርህ የበረከት ቦታ ትሆናለች፡፡››

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ጻድቃን_እንድራኒቆስና_አትናስያ

በዚህች ቀን# ክርስቶስን የሚወዱ የእንድራኒቆስና የሚስቱ የአትናስያ መታሰቢያቸው ነው። እነርሱም ከአንጾኪያ ከተማ ነበሩ። በወርቅና በብርም የከበሩ ባለጸጎች ነበሩ ከገንዘባቸውም ለድኆችና ለችግረኞች ይሰጡ ነበር።

ከዚህም በኃላ አንድ ወንድ ልጅና አንዲት ሴት ልጅን ወለዱ ወንዱን ዮሐንስ ሴቲቱንም ማርያም ብለው ሰየሟቸው ልጆችም አደጉ እንዲራኒቅስና ሚስቱም እንግዳ በመቀበል ለድኆችና ለምስኪኖች በመመጽወት በጎ ሥራን አበዙ እነርሱም መገናኘትን ትተው ሰውነታቸውን በንጽሕና ጠበቁ።

ልጆቻቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆናቸው ጊዜ የሆድ ዝማ በሽታ ታመው በአንዲት ቀንም ሞቱ እንዲራኒቆስም አይቶ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ ሥዕል ፊት ራሱን ጥሎ እንዲህ ብሎ አለቀሰ ከእናቴ ማሕፀን ራቁቴን ወጣሁ ወደ #እግዚአብሔርም ራቁቴን እሔዳለሁ እርሱም ሰጠ እርሱም ወሰደ የ #እግዚአብሔር የጌትነቱ ስም የተባረከ ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

እናታቸውም ለሞት እስከምትደርስ እጅግ አዘነች ልጆቿ ወደ ተቀበሩበት ወደ ዐፀደ ቤተ ክርስቲያን ሔደች ከኀዘንዋም ብዛት የተነሳ አንቀላፋች በእንቅልፏም ውስጥ በልጆችሽ ሞተ አታልቅሺ እነርሱ ግን በሰማያት ደስ እያላቸው ናቸው እያለ በመነኰስ አምሳል ሲነግራት አየች። ይህንንም ሰምታ ሒዳ ለባሏ ነገረችው።

ከዚህም በኃላ ይህን ዓለም ይተዉ ዘንድ ተስማሙ ገንዘባቸውንም ሁሉ ምንም ሳያስቀሩ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጡ በሌሊትም ወጥተው ወደ እስክንድርያ ከተማ ደረሱ ሚስቱንም በዚያ ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ በአባ ዳንኤል ዘንድ መነኰሰ። ከዚያም ተመልሶ ሚስቱ አትናስያን ወደ ሴቶች ደናግል ገዳም ወሰዳት በዚያም ተዋት።

ከዐሥራ ሁለት ዓመትም በኃላ እንድራኒቆስ ከቅዱሳት መካናት ይባረክ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ አባ ዳንኤልን ለመነው ፈቀደለትም በ #መድኃኒታችንም ቸርነት ሚስቱ አትናስያ በወንድ አምሳል በጉዞ ላይ ተገናኘችው ሚስቱ እንደሆነችም አለወቀም እርሷ ግን አወቀችው ነገር ግን ሚስቱ እንደሆነች አልገለጠችለትም።

ወደ ቅዱሳት መካናትም በደረሱ ጊዜ ሥራቸውን ፈጽመው ወደ አባ ዳንኤል በአንድነት ተመለሱ። አባ ዳንኤልም ሚስቱ እንደሆነች በ #መንፈስ_ቅዱስ አውቆ እንድራኒቆስን ባልንጀራ ካደረግኸው ከዚህ መነኰስ ጋራ በአንድ ቦታ ኑሩ እርሱ ቅዱስ ነውና አለው። ዐሥራ ሁለት ዓመትም በአንድነት ኖሩ ማንም የአወቀ አልነበረም።

አባ ዳንኤልም ይጎበኛቸውና ስለ ነፍሳቸው ጥቅም ያስተምራቸው ነበር። ከዚህም በኃላ አትናስያ በታመመች ጊዜ ለእንድራኒቆስ አባታችንን አባ ዳንኤልን ጥራልኝ አለችው ሒዶም ለአባ ዳንኤል እንዲህ ብሎ ነገረው ባልንጀራዬ ታሞ ለመሞት ተቃርቧልና ትጎበኘው ዘንድ ና። በደረሰም ጊዜ በታላቅ ሕመም ላይ አገኛት እርሷም ታቆርበኝ ዘንድ እሻለሁ አለችው ያን ጊዜም ተፋጠነና ሥጋውንና ደሙን አቀበላት ከዚህም በኃላ አረፈች በሚገንዟትም ጊዜ ሴት እንደሆነች አገኙ ዳግመኛም ታሪኳንና ለባሏ ያወራቻቸውን ምልክቶች አገኙ።

እንድራኒቆስም በአነበበ ጊዜ እርሷ ሚስቱ እንደሆነች አወቀ ደንግጦም ልቡ ተሠወረ ፊቱንም እየጻፈ ጮኸ ያለቅስ ጀመረ።ከጥቂት ቀን በኃላም ታመመ አረጋውያንም መጥተው በረከቱን ተቀበሉ ሥጋውንና ደሙንም ተቀበሉ በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ_28 እና #ከገድላት_አንደበት)
#ሐምሌ_30

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሐምሌ ሠላሳ በዚች ቀን ቅዱሳን የገሊላ ሰዎች #ቅዱሳን_መርቆሬዎስና_ኤፍሬም በሰማዕትነት አረፈ፣ ክብርንና ብልጽግናን ንቆ የተወ #ቅዱስ_ጳውሎስ_መናኒ አረፈ፣ #ቅዱስ_ሐዋርያ እንድርያስ ተአምራትን አደረገ፣ የንጉሥ ናዖድ ሚስት #ንግሥት_ማርያም_ክብራ አረፈች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_መርቆሬዎስና_ኤፍሬም (ሰማዕታት)

ሐምሌ ሠላሳ በዚች ቀን ቅዱሳን የገሊላ ሰዎች መርቆሬዎስና ኤፍሬም በሰማዕትነት አረፈ። እሊህም ከአክሚም ከተማ የመጡ የሚዋደዱ በ #መንፈስ_ቅዱስ ወንድማሞች በሥጋም ዘመዳሞች ነበሩ መንፈሳዊ ስምምነትንም ተስማምተው በላይኛው ግብጽ ካሉ ገዳማት በአንዱ ገዳም መነኰሱ በጾም በጸሎትና በስግደት እየተጋደሉ በገዳሙ ውስጥ ሃያ ዓመት ያህል ኖሩ።

ከዚህም በኃላ ጠላት ሰይጣን በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ከአርዮሳውያን ችግርን በአመጣ ጊዜ አርዮሳውያኑ በአርዮሳዊ ንጉሥ ትእዛዝ መሥዋዕትን ሊሠው ወደ ኦርቶዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገቡ ቀንተው ወደ ቤተ ክርስቲያን ገቡና አርዮሳውያን ያኖሩትን መሥዋዕት በተኑት።

እንዲህም አሏቸው በ #ሥሉስ_ቅዱስ ስም ያልተጠመቀ መሥዋዕትን ያሳርግ ዘንድ አይገባውም። ያን ጊዜም አርዮሳውያን ይዘው ደበደቧቸው ታላቅ ግርፋትንም ገረፏቸው ዐጥንቶቻቸውም እስኪሰበሩ ድረስ በምድር ላይ ጥለው ረገጧቸው ነፍሶቻቸውንም በ #እግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጡ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ ምእመናንም መጥተው ሥጋቸውን ወሰዱ በአማሩ ልብሶችም ገንዘው በመልካም ቦታ አኖርዋቸው ከእነሱም ለበሽተኞች ታላቅ ፈውስ ሆነ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእኒህ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዻውሎስ_መናኒ

በዚህችም ቀን ክብርንና ብልጽግናን ንቆ የተወ ጳውሎስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ባለጸጋ ነበር። ደግ የሆነች ሚስትና የተባረኩ ልጆችም ነበሩት። መነኮስ ሊሆን ወደደ ሚስቱንና ልጆቹንም ጠርቶ እነሆ ክብር ይግባውና ስለ #ክርስቶስ ፍቅር እሸጣችሁ ዘንድ ወደድኩ አላቸው እነርሱም አሳዳሪያቸን ነህና የወደድከውን አድርግ አሉት።

ከዚህም በኋላ ገንዘቡን ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለችግረኞች በተነ ሚስቱንም ወደ ደናግል ገዳም ወሰዳት እመምኔቷንም ጠራትና እንዲህ አላት ለገዳምሽ አገልጋይ ትሆን ዘንድ ሚስቴን ልሸጥልሽ እወዳለሁ እርሷም እሺ አለችው የመሸጫዋንም ደብዳቤ ጻፈ የሺያጭዋን ዋጋ ተቀብሎ ለድኆች ሰጠ ልጆቹንም ወደ አበ ምኔቱ ወስዶ እንደ እናታቸው ሸጣቸው ለአበ ምኔቱም አሳልፎ ሰጣቸው።

ከዚህም በኃላ ወደ ሌላ ቦታ ሔደ ራሱንም ለገዳሙ አለቃ ሸጠ አለቃውንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ብቻዬን ልገባ እሻለሁ አለው በገባም ጊዜ በሩን በላዩ ዘጋ። እጆቹንም ዘርግቶ ቆመ በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብሎ ጮኸ አቤቱ በፍጹም ልቡናዬ ወዳንተ እንደ መጣሁ አንተ ታውቃለህ።

ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ሀሳብህን ሁሉ አውቅሁ በፍጹም ልቤም ተቀበልኩህ። ከዚህም በኃላ መነኮስ አስጨናቂ የሆኑ የገዳሙን ሥራዎች ሁሉ እንደ ባሪያ እየሠራ ኖረ ራሱንም ከሁሉ እጅግ አዋረደ ነገር ግን ስለ መዋረዱ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ አደረገው። ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ ከዚህም በኃላ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_እንድርያስ_ሐዋርያ

በዚችም ቀን ቅዱስ ሐዋርያ እንድርያስ ተአምራትን አደረገ። እንድርያስ በጽርዕ አገር እያለ #ክብር_ይግባውና_ጌታችን_ኢየሱስ ተገልጦ እንዲህ አለው ማትያስን ከእሥር ቤት ታወጣው ዘንድ ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ሒድ የዚያች አገር ሰዎች ከሦስት ቀን በኃላ ሊበሉት ያወጡታልና ።

እንድርያስም ጌታችንን እንዲህ አለው የቀረው ሦስት ቀን ከሆነ እንዴት እደርሳለሁ ነገር ግን ፈጥኖ የሚያወጣውን ከመላእክት አንድ ላክ እንጂ።

#ጌታችንም ለእንድርያስ እንዲህ ብሎ መለሰለት ስማ ሀገሪቱን ወደዚህ ነዪ ከልዃት በውስጧ ከሚኖሩ ሁሉ ጋር ትመጣለች አንተና ደቀ መዘሙሮችህ ግን ጠዋት በሆነ ጊዜ ተነሥታችሁ ወደ ባሕር ሒዱ የተዘጋጀ መርከብንም ታገኛላችሁ እርሱም ያደርስሃል ይህንንም ብሎ ከእርሱ ዘንድ በክብር ዐረገ። በነጋ ጊዜም እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተነሥቶ ወደ ወደብ ደረሰ ጥሩ መርከብንም አየ #ጌታችንንም በሊቀ ሐመር አምሳል አየው #ጌታችን እንደሆነ አላወቀም ሊቀ ሐመር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን አለው #ጌታም#እግዚእብሔር ሰላም ይደርብህ አለው እንደርያስም ደግሞ በዚህ መርከብ ወዴት ትሔዳለህ አለው ሰውን ወደ ሚበሉ ሰዎች አገር እሔዳለሁ አለው እንድርያስም ሊቀ ሐመሩን ወንድሜ ሆይ ከአንተ ጋር ትጭነኝ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው ሊቀ ሐመሩም እሺ ብሎ ወደ መርከቡ አወጣቸው። በባሕሩ ላይም ሲጓዙ #ጌታችን እንድርያስን እንዲህ ብሎ ጠየቀው #ጌታህ ምን ኃይል አደረገ እንድርያስም #ጌታችን ከአደረጋቸው ተአምራቶች ሊነግረው ጀመረ #ጌታችን እንደሆነ አላወቀም ነበርና።

ከዚህም በኋላ ሊቀ ሐመሩ እነደሚአንቀላፋ ሰው ሆነ ያንጊዜም እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተኛ በዚያን ጊዜም #ጌታችን እንድርያስንና ሁለቱን አርድእቱን ይሸክሙአቸው ዘንድ መላእክትን አዘዛቸውና ወስደው በባሕሩ ዳርቻ አኖሩዋቸው። እንድርያስም ከእነቅልፍ በነቃ ጊዜ መረከብን አላገኘም እጅግም አደገቀ ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አላቸው ልጆቼ ሆይ በመርከብ ውስጥ ከ #ጌታችን ጋር ነበርን ግን አላወቅንም።

ከዚህም በኋላ እንድርያስ ተነስቶ ጸለየ ክብር ይግባውና #ጌታችንም በመልካም ጎልማሳ አምሳል ተገለጸለት እንዲህም አለው ወዳጄ እንድርያስ አትፍራ እኔ ይህን አድርጌአለሁና አንተ በሦስት ቀን አልደርስም ብለህ ነበር ስለዚህ በፍጥረት ሁሉ ላይ ኃይል እንዳለኝ የሚሳነኝም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ እንግድህም ወደ ከተማው ገብተህ ማትያስን ከእሥር ቤት አውጣው ከእርሱ ጋር ያሉትንም ሁሉ።

ከዚህም በኋላ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተነሥቶ ወደ ከተማ ገባ ማትያስ ወዳለበትም እስር ቤት ሔደ። በደረሰም ግዜ የወህኒ ቤቱ ደጀ ራስዋ ተከፈተች በገባ ጊዜም ማትያስን ተቀምጦ ሲዘምር አገኘው እርስ በርሳቸውም ሰላምታ ተሳጣጡ እንድርያስም ማትያስን ከሁለት ቀን ቡኋላ አውጥተው እንደ እንስሳ አርደው ይበሉኛል አልክ አንተ በ #ጌታችን ዘንድ ያየናትን ያቺን ምሥጥር ረሰሃትን በምንናገረት ጊዜ ሰማይና ምድርን ይናወጣሉ አለው። ማትያስም ወንድሜ ሆይ እንሆ ይህን አወቅሁ ነገር ግን በዚች ከተማ ውስጥ ሥራዬን እንድፈጽም የ #ጌታችን ፍቃድ እንደ ሆነ እኔ እናገራሎህ እርሱ ራሱ እንሆ እኔ እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ ብሏልና ወደ ዝህም እሥር ቤት በጨመሩኝ ጊዜ ክብር ይግባውና #ጌታችንን ጠራሁት እርሱም ሃያ ሰባት ቀን ሲፈጸም ወንድምህ እንድርያስን ወዳንተ እልከዋሎህ እርሱም ከእሥር ቤት ያወጣሃል ከአንተ ጋራ ያሉትን ሁሉ ያወጣችዋል ብሎ ገለጠልኝ እንሆም ደርሰሃል የምትሠራውን አስተውል አለው።

እንድርያስም ወደ እስረኞች በተመለከተ ጊዜ እንደ እንስሳ ሥር ሲበሉ አይቶ አዘነ አለቀሰም ሰይጣንንም ከሠራዊቱ ጋር አሥረው ከዝህ በኃላ አንድርያስና ማትያስ ተነሥተው ወደ #እግዚአብሔር ማለዱ እጆቻቸውንም በእሥረኞች ሁሉ ላይ ጫኑ አእምሮአቸውም ተመለሰ ከከተማው ውጭ ወጥተው በዝያ በአንድነት እንድቀመጡ አዘዙአቸው።
#ነሐሴ_1

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተባረከው #የነሐሴ_ወር_የቀኑ_ሰዓት_ዐሥራ_ሦስት ነው ከዚህም በኋላ ይጎድላል።
ነሐሴ አንድ በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናቷ #የቅድስት_ሐና መታሰቢያዋ ነው፣ የዮስጦስ ልጅ #ቅዱስ_አቦሊ በሰማዕትነት አረፈ፣ የከበሩ ሰዎች #ቅዱሳን_የዮሴፍና_የኒቆዲሞስ መታሰቢያቸው ነው፣ በተጨማሪም በዚህች ቀን የፋኑኤል ልጅ የነብይት #ሐና፣ የንግሥት ሶፍያ ልጆች የቅዱሳት ደናግል መታሰቢያቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሐና (የእመ ብርሃን እናት)

ነሐሴ አንድ በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናቷ የሐና መታሰቢያዋ ነው። ይህችም ቅድስት ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት (ጣ ጠብቆ ይነበብ) ልጁ ናት። ለማጣትም ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱም ስሟ ማርያም ናት ሁለተኛዋም ስሟ ሶፍያ ሦስተኛዪቱም ስሟ ሐና ናት ታላቂቱ ማርያምም ለባል ተድራ አዋላጅ የሆነች ሰሎሜን ወለደቻት እርሷም #መድኃኒታችንን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ በስደቷም ወራት ከአረጋዊ ዮሴፍ ጋር እመቤታችንን #ድንግል_ማርያምን ያገለገለቻት ናት።

ሶፍያም ለባል ተድራ ለመጥመቁ ዮሐንስ እናቱ የሆነች ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደቻት። ይችንም ቅድስት ሐናን ከይሁዳ ነገድ ለሆነ ጻድቅ ስሙ ኢያቄም ለሚባል አጋቧት። (ሰሎሜና ኤልሳቤጥ ለቅድስት ሐና የእኅትማማች ልጆች ናቸው።)

ቅድስት ሐና ኢያቄምን አግብታ ስትኖር የቴክታና እና የጴጥሪቃ ምክነት በዘር ወርዶ መክና በመኖሯ የዐይኗ ማረፊያ የልቧ ተስፋ የሚሆን ልጅ እንዲስጣት ፈጣሪዋን ስትማጸን ኖራለች።

የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ አምላክ ልመናዋን ሰምቶ ሐምሌ ፴ ራእይ አየች። ራእዩንም ከባሏ ከኢያቄም ጋር ተወያየተው ምንጣፍ ለይተው ሱባኤ ገቡ።

ከአንድ ሱባኤ በኋላ ነሐሴ ፯ ቀን #ጌታ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እንደሚወልዱ አበሠራቸው። ከዚያም እመቤታችን ጸንሳ ልዩ ልዩ ተአምራትን አድርጋለች። ሳምናስን ከሞት አስነስታለች። በርሴባን ዐይኗን አብርታለች። ከዚያም በአይሁድ ተንኮልና አሳዳጅነት ወደ ሊባኖስ ተራራ ተሰዳ #ድንግል_ማርያምን ወልዳለች። በመውለዷም ሕዳሴ አካል አግኝታ ከኖረች በኋላ ዐርፋለች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሐናና ኢያቄም ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቦሊ

በዚህችም ቀን የዮስጦስ ልጅ ቅዱስ አቦሊ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ አቦሊ ከመንግሥት ልጆች ውስጥ ነበር ዐላውያንን ወግቶ በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስን ክብር ይግባውና #ክርስቶስን ክዶ አገኘው።

ያም አቦሊና አባቱ ዮስጦስ ሌሎችም የመንግሥት ልጆች ሁሉ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስን ሊያጠፉትና መንግሥትን ከእርሱ ሊወስዱ ችሎታ ሲኖራቸው የማታልፍ ሰማያዊት መንግሥትን አሰቡ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ አቦሊ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም አብዝቶ አባበለው። እንዲሁም አባቱ ዮስጦስንና የከበረች እናቱ ታውክልያን አባበላቸው እነርሱ ግን አልሰሙትም ልባቸው በ #መድኅን_ክርስቶስ ፍቅር ተነድፏልና። ንጉሡም እነርሱን በዚያ ማሠቃየትን ፈራ ስለዚህም ከመልእክት ደብዳቤ ጋር ወደግብጽ ስሙ ኄርሜኔዎስ ወደሚባል የእስክንድርያ ገዥ ላካቸው በመልእክቱም እንዲህ አለው ዮስጦስና ሚስቱ ታውክልያ ልጃቸው አቦሊም ወደአንተ በሚደርሱ ጊዜ አባብላቸው አለዚያም እየአንዳንዳቸውን ለያያቸው።

በዚያችም ሌሊት ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ለዮስጦስና ለሚስቱ ታውክልያ ለልጃቸው አቦሊም ተገልጦላቸው አጽናናቸው ከእነርሱም የሚሆነውን ነገራቸው የጸና ቃል ኪዳንም ሰጣቸው።

ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስም በደረሱ ጊዜ ስለእነርሱ እጅግ አደነቀ እነርሱ መንግሥታቸውን ትተዋልና ክፋ ነገርንም ሊናገራቸው አልደፈረም ከምክራቸው ይመለሱ ዘንድ በለሰለሰ ቃል ሸነገላቸው እንጂ ነገር ግን አልሰሙትም።

ከዚህም በኋላ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ ለእየብቻቸው ለያያቸው ቅዱስ ዮስጦስን ወደ እንዴናው ከተማ ሚስቱን ታውክሊያን ፃ ወደ ሚባል አገር ልጃቸው አቦሊንም ብስጣ ወደ ሚባል አገር ሰደዳቸው ለእያንዳንዳቸውም የሚአገለግላቸው አንዳንድ አገልጋይ ሰጣቸው። ቅዱስ አቦሊም ወደ ሀገር ብስጣ በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በመኰንኑ ፊት ታመነ። መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን በእሳት ቃጠሎና በመንኰራኵር አሰቃየው ሕዋሳቱንም ቆራርጦ ለአንበሶች ጣለው ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ከሥቃዩ ሁሉ አድኖ ያለ ጉዳት በጤና አነሣው።

ብዙዎች ሰዎችም ስቃዩንና ዳግመኛ መዳኑን በአዩ ጊዜ እጅግ አደነቁ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በአምላካችን_በመድኃኒታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስም አምነው ሰማዕታት ሆኑ።

መኰንኑ ግን እጅግ ተቆጥቶ የቅዱስ አቦሊን ቆዳውን እንዲገፍፉትና ጨውና መጻጻን በማቅ አምጥጠው ቍስሉን እንዲያሹ አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉበት።

ከዚህም በኋላ ቆዳውን አሸክመው በከተማ ውስጥ ሁሉ አዞሩት ወደ #ጌታችንም እንዲህ ብሎ ጸለየ የሕያው #እግዚአብሔር_ልጅ_ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ ርዳኝ ከዚህ ሥቃይም አድነኝ። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደርሱ መጣ ሁለመናውንም ዳስሶ አዳነው።

መኰንኑም በእርሱ ላይ የሚያደርገውን እስኪያስብ ከእሥር ቤት እንዲጨምሩት አዘዘ። ቅዱስ አቦሊም ቁሞ ጸለየ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #ጌታችን ተገለጠለትና የመረጥኩህ አቦሊ ሰላም ለአንተ ይሁን እኔም ከአንተ ጋር እኖራለሁ አለው #ጌታችንንም በአየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው ክብር ይግባውና ለ #ጌታችንም ሰገደለት።

ስሙ አብስኪሮን የሚባል አንድ ባለ ጸጋ ነበር የቤቱንም ግድግዳ አፍርሰው አዲስ ይሠሩለት ዘንድ ሠራተኞችን አመጣ ሥራቸውንም እስኪጨርሱ ከዚያ ይቆሙ ዘንድ ሁለቱን ልጆቹን አዘዛቸው።

ከግርግዳውም ላይ በወጡ ጊዜ ግርግዳው ተደርምሶ ዐሥራ ስድስት ሰዎችና ሁለቱ ልጆቹ ሞቱ። ባለጸጋውም የሆነውን በአየ ጊዜ ልብሱን ቀደደ ጩኾም አለቀሰ ወደ ቅዱስ አቦሊም ሒዶ ከእግሩ በታች ሰገደለት እንዲህም አለው ራራልኝ ሁለቱ ልጆቼ ሙተዋልና ከእነርሱም ጋራ ዐሥራ ስድስት ሰዎች ሞቱ። ከሞትም ብታሥነሣቸው እኔ በአምላክህ አምናለሁ።

ያን ጊዜም ቅዱስ አቦሊ ተነሣ እንዲህ ብሎ ጸለየ ስለ ቅዱስ ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ የመረጥከኝ #ጌታዬ_አምላኬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ በእኒህ በሞቱ ሰዎች ላይ ኃይልህን ግለጥ። እኒህ ሰዎች ሁሉ እንዲአምኑ ያለ አንተም ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ከሞት አንሣቸው። ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

ከዚህም በኋላ የተገፈፈ ቆዳውን ወስዶ በሞቱት ሰዎች ላይም ዘረጋውና በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሞት ተነሡ አለ። ወዲያውም ሁሉም ድነው ተነሡ በዚያ ያሉ ሕዝብም ይህን ድንቅ ሥራ በአዩ ጊዜ የክርስቲያን አምላክ የቅዱስ አቦሊም አምላክ #ኢየሱስ_ክርስቶስ አንድ ነው እኛም እናምንበታለን ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለምና እያሉ ጮኹ።

ባለ ጸጋው አብስኪሮንም መጥቶ ለቅዱስ አቦሊ እንዲህ እያለ ሰገደ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ክብር ይግባውና እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ዛሬ አወቅሁ እኔም አምንበታለሁ። ከቤተሰቦቹም ሁሉ ጋር አመኑ መኰንኑም አፈረ።
#ነሐሴ_10

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥር በዚህች ቀን የታላቁ ጻድቅና ገዳማዊ #አባ_ዓቢየ_እግዚእ ዓመታዊ የተአምር በዓል ነው፣ #ቅዱስ_መጥራ በሰማዕትነት ሞተ፣ #ቅዱስ_ሐርስጥፎሮስ በሰማዕትነት ሞተ፣ የከበሩ #ቅዱሳን_ቢካቦስና_ዮሐንስ በሰማዕትነት ሞቱ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ዓቢየ_እግዚእ_ኢትዮዽያዊ

ነሐሴ ዐሥር በዚህች ቀን የታላቁ ጻድቅና ገዳማዊ አባ ዓቢየ እግዚእ ዓመታዊ የተአምር በዓል ነው። አባ ዓቢየ እግዚእ የተወለዱት በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ትግራይ ተንቤን (መረታ) ውስጥ ነው። የተባረኩ ወላጆቻቸው ያፍቅረነ እግዚእ እና ጽርሐ ቅድሳት ይባላሉ። አጥምቀው "ዓቢየ እግዚእ" ሲሉ ስም ያወጡላቸው የወቅቱ ጳጳስ ሰላማ መተርጉመ መጻሕፍት ናቸው። ትርጉሙም 'በጌታ ዘንድ ታላቅ ሰው' ማለት ነው።

ዓቢየ እግዚእ በሕፃንነታቸው ሌሊት ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጸልዩ አድረው ቀን ቀን እየተማሩ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ። ገና በወጣትነታቸው ወደ ታላቁ መነኮስ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ (ደብረ በንኮል) ሔደው መንኩሰዋል።

በገዳሙ በጾም በጸሎትና በስግደት ተወስነው ከኖሩ በኋላ ወደ ዋልድባ ሔደው የተሰወረች ቤተ ክርስቲያን አግኝተዋል። በጊዜው በአርባ ቀን አንዲት ቅጠል ብቻ ለቁመተ ሥጋ ይበሉ ነበር።

ከዚያም ወደ ሃገራቸው ተንቤን ተመልሰው ዛሬም ድረስ ድንቅ ሆኖ የሚታየውን ገዳም መሥርተው ብዙ መናንያንን አፍርተዋል። ዓቢየ እግዚእ ገዳማዊና ጻድቅ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያዊ አባትም ነበሩ። ከትግራይ እስከ ደንቢያ ደግሞ ሃገረ ስብከታቸው ነው።

አንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርትን አስከትለው ለስብከት ሲንቀሳቀሱ ተከዜ ወንዝ አካባቢ ደረሱ። ቀኑ ነሐሴ ዐሥር ነውና ተከዜ እስከ ገደፉ ሞልቶ ለሦስት ቀናት ባለመጉደሉ ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች ሲያለቅሱ ደረሱ። ጻድቁ በአካባቢው የነበሩት ኢ-አማንያን (አሕዛብ) ቢሆኑም ራርተዋልና "አምላከ ሙሴ" ብለው ጸልየው ወደ ጥልቁ ውስጥ ገቡ።

ቅዱስ ሚካኤል አብሯቸው ነበርና ተከዜ ግራና ቀኝ ተከፍሎ መሃሉ የብስ ሆነ። ይሕን ድንቅ ያዩ ከዘጠኝ መቶ አርባ በላይ አሕዛብም አምነው በጻድቁ እጅ ተጠምቀዋል። ይሕም ዘወትር ነሐሴ ዐሥር ቀን በቤተ ክርስቲያናቸው (ጐንደር) ይከበራል።

ከዚያም እያስተማሩ ጐንደር ደረሱ። ያኔ ጐንደር በቀሃና አንገረብ ወንዞች የታጠረች አንዲት መንደር ነበረች። ጻድቁ ቀን ቀን እየሰበኩ ማታ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናቸው የታነጸበት ሥፍራ ላይ ሲጸልዩ ያድሩ ነበር።

በዚያ ዘመን ጐንደር ውስጥ ጅብ እባብና መሠል አራዊት ገብተው ሕዝቡን ጨረሱት። ይሕንን የተመለከቱት አባ ዓቢየ እግዚእ ወደ እግዚአብሔር አለቀሱ። በፍጹም ልባቸውም ስለ ሕዝቡ ለመኑ። የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ወደ ጻድቁ ቀርቦ "በስምሕ የተማጸኑ በቃል ኪዳንህ ያመኑ: በምድር አራዊት አይሠለጥኑባቸውም። በሰማይም እሳትን አያዩም። ጐንደርንም አራዊት ገብተው ሰውን አይጐዱም።" ብሏቸው አርጓል።

አባ ዓቢየ እግዚእ በገዳማቸው ተንቤን ለብዙ ዘመናት በቅድስና ኑረው ሦስት ሙታንን አስነስተው ብዙ ድውያንን ፈውሰው ብሔረ ብጹዓንን ጎብኝተው የድኅነት ቃል ኪዳንም ተቀብለው በመቶ አርባ ዓመታቸው ግንቦት ዐሥራ ዘጠኝ ቀን አርፈዋል። የጻድቁ ክብር ለሁሉ ነውና እናስባቸው።

ይህች ዕለት ባሕረ ተከዜን ከፍለው ሕዝቡን ያሻገሩባት አሕዛብንም ያጠመቁባት ናትና በገዳማቸው ጐንደር ውስጥ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያናቸውም ይከበራል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መጥራ

በዚህች ቀን በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በቅዱስ ዲሜጥሮስ ዘመንና በከሀዲው ንጉሥ በዳኬዎስ ዘመነ መንግሥት ቅዱስ መጥራ በሰማዕትነት ሞተ።

ይህም ቅዱስ የክብር ባለቤት #ክርስቶስን ክደው ለጣዖት መስገድን የሚያዝ የንጉሡን ደብዳቤ በሰማ ጊዜ ይህ ቅዱስ ወዲያውኑ ሒዶ ከወርቅ የተሠራ የአጵሎንን ክንድ ሰረቀ በየጥቂቱም ሰባብሮና ቆራርጦ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጣቸው።

የጣዖቱም አገልጋዮች ክንዱ ተቆርጦ አጵሎንን በአገኙት ጊዜ ስለርሱ ብዙዎችን ሰዎች ያዟቸው። በዚያንም ጊዜ ወደ መኰንኑ ቀርቦ ክርስቲያን እንደሆነ በፊቱ ታመነ ሁለተኛም የአጵሎንን የወርቅ ክንድ የወሰድኩ እኔ ነኝ ለድኆችና ለችግረኞችም ሰጠኃ ኋቸው አለው።

መኰንኑም በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ አስጨናቂ የሆነ ታላቅ ሥቃይንም አሠቃየው ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ጨመሩት #እግዚአብሔርም አዳነው ያለ ጥፋትም በጤና አወጣው።

ከዚህም በኋላ እጆቹንና እግሮቹን ቆረጡ ብዙ ደም ከአፍንጫው ወደ ምድር እስከ ሚወርድ ዘቅዝቀው በዕንጨት ላይ ሰቀሉት።

በዚያንም ጊዜ የ #እግዚአብሔር መልአክ ወርዶ ቅዱስ መጥራንን ፈታው ከተሰቀለበትም አውርዶ በመዳሠሥ አዳነው። አንድ ዕውር ሰውም መጣ ከአፍንጫው ከወረደውም ደም ወስዶ ዐይኖቹን ቀባ ወዲያውኑ አየ። መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀዳጀ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ መጥራ ጸሎት ይማረን በረከቱም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሐርስጥፎሮስ

በዚህችም ቀን ዳግመኛ በከሀዲ መክስምያኖስ እጅ ቅዱስ ሐርስጥፎሮስ በሰማዕትነት ሞተ። በንጉሥ መክስምያኖስ ፊት በአቆሙት ጊዜ ለአማልክት ሠዋ አለው። የከበረ ሐርስጥፎሮስም እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔ #እግዚአብሔር_ኢየሱስ_ክርስቶስን አመልከዋለሁ ለእርሱም እሠዋለሁ። ንጉሡም ተቆጥቶ ሥጋው ተቆራርጦ በምድር ላይ እስቲወድቅ በበትር ይደበድቡት ዘንድ አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት።

ከዚህም በኋላ ወደ ወህኒ ቤት ጣሉት በላህያቸውም እንዲአስቱት ሁለት ሴቶችን ንጉሡ ወደርሱ ላከ ቅዱሱ ግን የ #ክርስቶስን ሃይማኖት አስተማራቸው የዛሬ የሆነ የዚህንም ዓለም ኃላፊነት አስገነዘባቸው ወደ መክስምያኖስም በተመለሱ ጊዜ እንዴት አደረጋችሁ አላቸው።

እነርሱም እንዲህ አሉት በከበረ ሐርስጥፎሮስ አምላክ የክብር ባለቤት በሆነ በ #ክርስቶስ እኛ እናምናለን ንጉሡም ሰምቶ አንዲቱን በዕንጨት ላይ ሰቅለው እንዲአቃጥሏት ሁለተኛዋን በአንገቷ ደንጊያ አንጠልጥለው ቊልቊል እንዲሰቅሏት አዘዘና ምስክርነታቸውን እንዲህ ፈጸሙ።

ከዚህም በኋላ ዕንጨቶችን ሰብስበው በማንደጃው ውስጥ አድርገው አነደዱ የከበረ ሐርስጥፎሮስን እጅና እግሩ እንደ ታሠረ ከውስጡ ጨመሩት ያን ጊዜም በስመ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ አለ እሳቱ ከቶ ምንም አልነካውም። ሕዝቡም ይህን አይተው የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ዐሥር ሺህ ያህል ሰዎች አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።

ሁለተኛም የብረት ሠሌዳዎችን በእሳት አግለው አመጡ ቅዱሱንም በላያቸው በአስተኙት ጊዜ ምንም ምን የነካው የለም። ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው በክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃያ ሺህ አንድ መቶ ሰዎችና አርባ ሕፃናት አምነው ምስክር ሁነው ሞቱ።

ንጉሥ መክስምያኖስም አይቶ እጅግ ተቆጣ የቅዱስ ሐርስጥፎሮስንም ራስ በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። ከንጉሡም ዘንድ በወጣ ጊዜ ጸሎትን አደረገ ፊቱንም በ #መስቀል ምልክት አማተበ ከዚህም በኋላ ምስክርነቱን ፈጸመ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሐርስጥፎስ እና በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ቢካቦስና_ዮሐንስ

በዚህችም ቀን እስሙናይን ከሚባል አገር የከበሩ ቢካቦስና ዮሐንስ ሌሎችም ከእሳቸው ጋራ በሰማዕትነት ሞቱ። ይህም ቅዱስ ቢካቦስ ክርስቲያን ሲሆን በሥውር ወታደር ሆነ። አንጥያኮስ ለሚባል መኰንንም ስለ ዮሐንስና ስለ ኤጲስቆጶስ አባ አክሎግ ከተርሴስ አገር ስለ ናሕር ስለ አባ ፊልጶስም እነርሱ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ነገር ሠሩባቸው።

መኰንኑም እነርሱን አቅርቦ እናንት ክርስቲያኖች ናችሁን አላቸው እኛ በእውነት ክርስቲያን ነን በሕያው #እግዚአብሔር ልጅ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ እናምናለን አሉት። መኰንኑም ይህን ነገር ትታችሁ ለአማልክት ሠዉ አላቸው።

ቅዱሳኑም እንዲህ ብለው መለሱለት እኛስ ለረከሱና ለተናቁ አማልክት አንሠዋም ሰማይና ምድርን ከፈጠረ ከ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በቀር። መኰንኑም ሰምቶ እጅግ ተቆጣ ምስክርነታቸውንም እስከፈጸሙ ድረስ አሠቃያቸው።

ቅዱስ ቢካቦስን ግን ከአሠቃየው በኋላ አሠረውና ከመንኰራኲር ውስጥ ጨመረው ዘቅዝቆም ሰቀለው ሕዋሳቱንም ቆራረጠው #ጌታችንም ያስታግሠውና ያበረታው ነበር ያለ ጉዳትም ጤናማ አድርጎ አስነሳው።

ከዚህም በኋላ በርሙን ወደሚባል አገር ከብዙዎች ሰማዕታት ጋራ ላከው በመርከብም ውስጥ እህልና ውኃ ሳይቀምሱ ሃያ ስድስት ቀኖች ኖሩ። በርሙን ወደሚባል አገርም በደረሱ ጊዜ ጽኑ ሥቃይን አሠቃይተው በምሳር ቆረጡት የምስክርነቱንም ተጋድሎ ፈጸመ በመንግሥተ ሰማያትም አክሊልን ተቀበለ።

ከሀገረ በርሙን ሹማምንቶችም አንድ ባለ ጸጋ ሰው መጥቶ የቅዱስ ቢካቦስን ሥጋ ወስዶ በአማሩ ልብሶች ገነዘው ወደ አገሩ እስሙናይንም ላከው። በመከራውም ወራት ቊጥር የሌላቸው ብዙዎች ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ ከእርሱም ጋራ የተገደሉ ዘጠና አምስት ሰዎች ናቸው።

ከዚህም በኋላ ለቅዱሱ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለት ሥጋውን በውስጧ አኖሩ ከእርሱም ብዙ ድንቅ ተአምር ተገለጠ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_10 እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
#ነሐሴ_14

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በእስክንድርያ ሀገር ድንቅ ተአምርን አደረገ፣ #የአባ_ስምዖንና የወዳጁ #የአባ_የዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ፣ #ቅዱስ_ባስሊቆስ በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መስቀለ_ክርስቶስ

ነሐሴ ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በእስክንድርያ ሀገር ድንቅ ተአምርን አደረገ። ስለርሱም ከአይሁድ ብዙዎች አምነው በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአባ ቴዎፍሎስ እጅ ተጠመቁ እርሱም ለቅዱስ ቄርሎስ የእናቱ ወንድም ነው። ይህም እንዲህ ነው በእስክንድርያ አገር ስሙ ፈለስኪኖስ የሚባል አይሁዳዊ ባለጸጋ ሰው ይኖር ነበር እርሱም እንደ አባቶቹ የኦሪትን ሕግ የሚጠብቅና #እግዚአብሔርን የሚፈራ ነው።

ዳግመኛም ሙያተኛዎች ሁለት ድኃዎች ክርስቲያኖች አሉ በአንደኛውም ላይ ሰይጣን የስድብ መንፈስ አሳድሮበት ጓደኛውን ወንድሜ ሆይ #ክርስቶስን ለምን እናመልከዋለን እኛ ዶኆች ነን ይህ #ክርስቶስን የማያመልክ አይሁዳዊ ፈለስኪኖስ ግን እጅግ ባለጸጋ ነው አለው።

ጓደኛውም እንዲህ ብሎ መለሰለት ዕወቅ አስተውል የዚህ ዓለም ገንዘብ ከ #እግዚአብሔር የሆነ አይደለም ምንም አይጠቅምም ጥቅም ቢኖረው ጣዖትን ለሚያመልኩ ለአመንዝራዎች ለነፍሰ ገዳዮች ለዐመፀኞች ሁሉ ባልሰጣቸውም ነበር።

አስተውል የከበሩ ነቢያት ድኆች ችግረኞችም እንደነበሩ ሐዋርያትም እንደርሳቸው ችግረኞች እንደነበሩ። #ጌታችንም ድኆችን ወንድሞቼ ይላቸው እንደነበረ። ሰይጣን ግን የጓደኛውን ምክር እንዲቀበል ምንም ምን አልተወውም ሃይማኖቱን ምንም ምን አልተወውም ሃይማኖቱን ለውጦ ነፍሱን እስከማጥፋት ድረስ አነሣሣው ቀሰቀሰው እንጂ።

ከዚህም በኋላ ወደ ፈለስኪኖስ ሒዶ በአንተ ዘንድ እንዳገለግል ተቀበለኝ አለው። ፈለስኪኖስም እንዲህ ብሎ መለሰለት በሃይማኖቴ የማታምን አንተ ልታገለግለኝ አይገባም ከቤተ ሰቦቼም ጋራ የማትተባበር ልቀበልህ አይገባኝም። ሁለተኛም ይህ ጐስቋላ ወዳንተ ተቀበለኝ እኔም ወደ ሃይማኖትህ እገባለሁ ያዘዝከኝንም ሁሉ አደርጋለሁ አለው።

አይሁዳዊው ባለጸጋም ከመምህሬ ጋር እስከምማከር ጥቂት ታገሠኝ ብሎ ከዚያም ወደ መምህሩ ሒዶ ድኃው ክርስቲያናዊ ያለውን ሁሉ ነገረው መምህሩም #ክርስቶስን የሚክድ ከሆነ ግረዘውና ተቀበለው አለው።

አይሁዳዊውም ተመልሶ መምህሩ የነገረውን ለዚያ ድኃ ነገረው ያም ምስኪን የምታዙኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ። ከዚህም በኋላ ወደ ምኵራባቸው ወሰደው የምኵራቡም አለቃ በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ጠየቀው። ንጉሥህ #ክርስቶስን ክደህ አይሁዳዊ ትሆናለህን እርሱም አዎን እክደዋለሁ አለ።

የምኵራቡም አለቃ #መስቀል ሠርተው በላዩ የ #ክርስቶስን ሥዕል እንዲአደርጉ መጻጻንም የተመላች ሰፍነግ በዘንግ ላይ አሥረው ከጦር ጋራ እንዲሰጡት አዘዘ ከዚያም ከተሰቀለው ላይ ምራቅህን ትፋ መጻጻውንም አቅርብለት #ክርስቶስ ሆይ ወጋሁህ እያልህ ውጋው አሉት።

ሁሉንም እንዳዘዙት አድርጎ በወጋው ጊዜ ብዙ ውኃና ደም ፈሰሰ ለረጂም ጊዜም በምድር እየፈሰሰ ነበር በዚያን ጊዜም ያ ከሀዲ ደርቆ እንደ ደንጊያ ሆነ። በአይሁድ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሀት ወደቀባቸው በእውነት የአብርሃም ፈጣሪ ስለእኛ ተሰቅሏል እኛም ዓለምን ለማዳን የመጣ የሕያው #እግዚአብሔር ልጅ እርሱ እንደሆነ አመንበት እያሉ ጮኹ።

ከዚህም በኋላ አለቃቸው ከዚያ ደም ወስዶ የአንድ ዕውር ዐይኖችን አስነካው ወዲያውኑ አየ ሁሉም አመኑ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ ሒደው የሆነውን ሁሉ ነገሩት። ሊቀ ጳጳሳቱም ከካህናቱ ሁሉ ጋራ ተነሣ አባ ቄርሎስ ከእርሱ ጋራ አለ። ወደ አይሁድ ምኵራብም ሒዶ ውኃና ደም ከእርሱ ሲፈስ #መስቀሉን አገኘው ከዚያም ደም ወስዶ በግንባሩ ላይ ቀብቶ በረከትን ተቀበለ ሕዝቡንም ሁሉ ግንባራቸውን በመቀባት ባረካቸው።

ያንንም #መስቀል አክብረው ተሸክመው እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው ያኖሩት ዘንድ አዘዘ። ደም የፈሰሰበትንም ምድር አፈሩን አስጠርጎ ለበረከትና ለበሽተኞች ፈውስ ሊሆን በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኖረው።

ከዚህም በኋላ ፈለስኪኖስ ከቤተ ሰቦቹ ሁሉ ጋራ ሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስን ተከተለው ከአይሁድም ብዙዎቹ የቀደሙ አባቶቻቸው በሰቀሉት የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም አጥምቋቸው ከእርሱ ጋራ አንድ አደረጋቸው ሥጋውንና ደሙንም አቀበላቸው። ከዚህም በኋላ ለዘላለሙ ክብር ምስጉን የሆነ #እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደየቤታቸው ገቡ። እኛንም ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን በ #መስቀሉ ኃይል ያድነን አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አባ_ስምዖንና_አባ_ዮሐንስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የአባ ስምዖንና የወዳጁ የዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ። እሊህ ቅዱሳንም በአማኒው ዮስጦንስ ዘመን መንግሥት የነበሩ ናቸው እሊህም ወንድሞች የከበሩ ክርስቲያን ናቸው።

ከዚህ በኋላ ለከበረ #መስቀል በዓል ቅዱሳት መካናትን ሊሳለሙ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዱ ሥራቸውንም አከናውነው ወደ አገራቸው ሲመለሱ በፈረሶቻቸው ተቀምጠው ወደ ኢያሪኮ ቀረቡ።

ዮሐንስም በዮርዳኖስ በረሀ ያለውን የመነኰሳቱን ገዳም አይቶ ወንድሙ ስምዖንን ወንድሜ ሆይ በእሊህ ገዳማት እኮ የ #እግዚአብሔር መላእክት ይኖራሉ አለው ዮሐንስም ከእርሳቸው ጋራ ከሆን አወን ልናያቸው እንችላለን አለው።

ከዚያም ከፈረሶቻቸውን ወርደው ለሰዎቻቸው ሰጥተው እስከምናገኛችሁ በየጥቂቱ ተጓዙ ብለው እንደሚጸዳዱ መስለው ወደ ዱር ገቡ።

የዮርዳኖስንም ጐዳና ተጒዘው ከሰዎቻቸው በራቁ ጊዜ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ ጸሎት እናድርግ ከእኛም አንዳንችን ወደ መነኰሳቱ ገዳም በምታደርስ ጐዳና ቁመን ዕጣ እንጣጣል #እግዚአብሔር ከፈቀደ ዕጣችን ወደ ወጣበት እንሔዳለን።

ከዚህም በኋላ ስምዖን በዮርዳኖስ ጐዳና ቆመ ዮሐንስም ወደ ሀገራቸው በሚወስድ ጐዳና ላይ ቆመ ዕጣውንም በአወጡበት ጊዜ ዮርዳኖስ ጐዳና ላይ ወጣ እጅግም ደስ አላቸውና ስለ ደስታቸው ብዛት እርስ በእርሳቸው ተያይዘው ተሳሳሙ።

አንዱም አንዱ ወደኋላ እንዳይመለስ ስለጓደኛው ይጠራጠርና ይፈራ ነበር አንዱም ሁለተኛውን ይመክረውና ለበጎ ሥራ ያተጋው ነበር።

ዮሐንስ ስለ ስምዖን ይፈራ ነበር ስለ ወለላጆቹ ፍቅር አንዳይመለስ ስምዖንም ስለ ዮሐንስ ይፈራ ነበር እርሱ በዚያ ወራት መልከ መልካም የሆነች ሚስት አግብቶ ነበርና።

ከዚህም በኋላ ወደ #እግዚአብሔር ጸለዩ እንዲህም አሉ በውስጧ እንመነኵስ ዘንድ ለኛ የተመረጠች ገዳም ደጃፍዋ ክፍት ሆኖ ብናገኝ ምለክት ይሆናል።

የገዳሙም አለቃ ኒቆን የሚሉት በተሩፋት ፍጹም የሆነ ድንቆች ተአምራትን የሚያደርግ ሀብተ ትንቢት የተሰጠጠው ሲሆን በዚያች ሌሊት በጎቼ ይገቡ ዘንድ የገዳሙን በር ክፈተት የሚለውን ራእይ አየ።

ወደርሱም በደረሱ ጊዜ የ #ክርስቶስ በጎች ሆይ መምጣታችሁ መልካም ነው አላቸውና ከ #እግዚአብሔር ዘንድ እንደ ተላኩ ሰዎች አድርጎ ተቀበላቸው።

ከዚህም በኋላ አበ ምኔቱን የምንኵስናን ልብስ ያለብሳቸው ዘንድ ለመኑት እነርሱ በቆቡ ላይ የብርሃን አክሊል አድርጎ መላእክትም ከበውት አንዱን መነኰስ አይተዋልና ስለዚህም ፈጥነው ይመነኵሱ ዘንድ ተጉ።
#ነሐሴ_20

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ በዚች ቀን መጻሕፍትን የተረጐመ #አባ_ሰላማ አረፈ፣ በከሀዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ዘመን የነበሩ ከኤፌሶን ሀገር #ቅዱሳን_ሰባቱ_ደቂቅ አረፉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሰላማ_ካልዕ (#መተርጉም)

ነሐሴ ሃያ በዚች ቀን መጻሕፍትን የተረጐመ አባ ሰላማ አረፈ።

እኒህ ታላቅ ደግ ሰው የነበሩት በሃገራችን ኢትዮዽያ ከ1340 እስከ 1380 ዓ/ም ነው:: በትውልድ ግብጻዊ ቢሆኑም ለኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ውለታን ውለዋል:: በዘመኑ ዻዻስ ሁነው ቢመጡም እንደ ሌሎቹ ዻዻሳት በቤተ መንግስት አካባቢ ሥራ ፈትተው መቀመጥን አልፈለጉም::

ወዲያው እንደ መጡ የግዕዝ ልሳንን ልቅም አድርገው ተማሩ:: ቀጥለው ኢትዮዽያውያን ሊቃውንትን ሰብስበው ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተረጉሙ ገቡ:: አሥራው መጻሕፍትን (81ዱን) ጨምሮ ብዙ መሠረታዊ መጻሕፍትን መተርጐም ችለዋል::

ይህም ሥራ አድካሚ በመሆኑ ከ30 ዓመታት በላይ ጊዜን ወስዷል:: ከተረጐሟቸው መጻሕፍትም፦ #ስንክሳር#ግብረ_ሕማማት#ላሃ_ማርያም#ፊልክስዩስ(መጽሐፈ መነኮሳት)፣ #መጽሐፈ_ግንዘት፣ድርሳን ዘቅዱስ #ያዕቆብ_ዘሥሩግ. . . ይጠቀሳሉ::

አቡነ ሰላማ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸውና በገዳማዊ ሕይወታቸው ይታወቁ ነበር:: በተጨማሪም በየቦታው እየዞሩ ይናዝዙ: ያጠምቁም ነበር:: በወቅቱ ልክ እንደ ስማቸው ሰላም እንዲሰፍን ይተጉ ነበር:: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን እያስታረቁ ለቤተ ክርስቲያን በአንድነት እንዲቆሙ አድርገዋል::

ጻድቁ አቡነ ፊልዾስን ጨምሮ ቅዱሳንን ገንዘውም ቀብረዋል:: በቀደመ ስማቸው #አባ_ፊቅጦር የሚባሉት ካልዕ (2ኛው) ሰላማ በ1380 ዓ/ም ከ40 ዓመታት ትጋት በኋላ ዐርፈዋል:: ሲጠሩም:- #መተርጉም (መጻሕፍትን የተረጐሙ)፣ #ብርሃነ_አዜብ(የኢትዮዽያ ብርሃን)፣ #መጋቤ_ሃይማኖት ተብለው ነው::

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ሰባቱ_ደቂቅ

በዚህችም ቀን በከሀዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ዘመን የነበሩ ከኤፌሶን ሀገር ሰባቱ ደቂቅ አረፉ። እሊህም ሰባቱ ደቂቅ ከንጉሥ ዳኬዎስ ጭፍሮች ውስጥ በመዛግብቱ ላይ የሾማቸው ነበሩ። አምልኮ ጣዖትንም በአወጀ ጊዜ ጣዖትን በማምለክ ሥራ አልተሳተፉም። እሊህንም ቅዱሳን በንጉሥ ዘንድ ወነጀሏቸው ይዞም አሠራቸው።

ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ለመሔድ በፈለገ ጊዜ እስከ ሚመለስ ድረስ ፈትቶ ለቀቃቸው ምናልባት ከምክራቸው ቢመለሱ ብሎ በልቡ አስቦ። ከዚህም በኋላ እሊህ ቅዱሳን ለረከሱ ጣዖታት እንዳይሰግዱ የጭፍራነት ሥራቸውን ትተው በተራራ ውስጥ ወደአለ ዋሻ ሒደው በዚያ ተሠወሩ።

የዋሻውን አፍ ዘጉ ከእሳቸውም ጋራ በንጉሥ ዳኬዎስ ስም የተቀረጸ ብር ነበር። ከእርሳቸውም አንዱም አንዱ በየተራቸው ወጥቶ ምግባቸውን ገዝቶ ወደእሳቸው ይመለስ ነበር። ዳኬዎስም ከሔደበት እንደተመለሰ በሰሙ ጊዜ የዋሻውን ደጃፍ ዘግተው ተኙ።

የእሊህንም ቦታቸውን የሚያውቅ አማኒ የሆነ ከጭፍሮች ውስጥ አንድ ሰው ነበረ ወደ ከተማ ሲወጡ ያገኛቸው ዘንድ ጠበቃቸው ባልመጡም ጊዜ ተነሥቶ ወደ ዋሻቸው ሔደ። ዋሻዋንም ከውስጥ እንደ ዘጓት ሁና አገኛት እነርሱም በረሀብ የሞቱ መሰለው ታላቅም የደንጊያ ሠሌዳ አምጥቶ ከእሳቸው የሆነውን ገድላቸውን ጽፎ በቀዳዳ ወደ ዋሻው ውስጥ አስገባው።እሊህም ቅዱሳን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዘመናት አንቀላፉ ዳኬዎስም ሙቶ እስከ ቴዎዶስዮስ ብዙ ነገሥታት ነገሡ።

በዚህም ምእመን ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዎች ተነሥተው ብዙዎች ተከተሏቸው። በዚያንም ጊዜ እሊህን ቅዱሳን ሰባቱን ደቂቅ እግዚአብሔር አነቃቸው ትንሣኤ ሙታን መኖሩን ግልጽ ያደርግ ዘንድ።

ከዚህም በኋላ ከእርሳቸው አንዱ ምግባቸውን ሊገዛ የከሀዲ ዳኪዎስንም ወሬ ይሰማ ዘንድ ብር ይዞ ወጣ ወደ ከተማም በገባ ጊዜ የከተማዋ ሁኔታ ተለወጠበት። በከተማውም በር መስቀሎችን አየ በየቅጽሮቿም የክብር ባለቤት የሆነ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ስሙን ያለ መፍራት ሲጠሩ ሰማ አንዱንም ሰው ይች አገር ኤፌሶን አይደለችምን ብሎ ጠየቀ እርሱም አዎን ናት አለው።

ያንንም ብር አውጥቶ ለባለ ሱቁ ሰጠው ምግባቸውን ይሸጥለት ዘንድ ባለ ሱቁም ያን ብር ተመለከተው የንጉሥ ዳኬዎስም ስም ተቀርጾበት አገኘውና ያንን ሰው ይዞ በአንተ ዘንድ የተሸሸገ መዝገብ አለ ይህ ምልክት ከአንተ ተገኝቷልና አለው።

እንዲህም ሲጣሉ ወደእርሳቸው ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ እንዲህም ብለው ጠየቁት አንተ ከወዴት ነህ ከዚች አገር ነኝ አላቸው።ማንን ታውቃለህ አሉት እርሱም ዕገሌንና ዕገሌን አላቸው ከዘመን ብዛት የተነሣ የጠራቸውን ሰዎች የሚያውቃቸው የለም።ስለዚህም በእርሱ ላይ ተቆጥተው ወደ ዳኞችና ወደ ኤጲስቆጶስ አባ ቴዎድሮስ ወደ ንጉሥ ቴዎዶስዮስም አቀረቡት።

ንጉሡና ኤጲስቆጶሱም ከአንተ የሆነውን እውነቱን ንገረን ከወዴት አገር ነህ አሉት። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው እኛ ሰባታችን የከሀዲ ንጉሥ ዳኬዎስ ጭፍሮች ነን እርሱም ወጥቶ ወደ ሌላ አገር በሔደ ጊዜ ከአንዷ ዋሻ ውስጥ ገብተን የዋሻዋን በር ዘግተን ተኛን። እነሆ ስንነቃ የምንመገበውን ምግብ እገዛ ዘንድ ላኩኝ።

ንጉሡና ኤጲስቆጶሱ በሰሙ ጊዜ ተነሥተው ወደዚያ ዋሻ ከእርሱ ጋራ ሔዱ ከእርሳቸውም ጋራ ብዙ ሕዝቦች አሉ ቅዱሳኑንም ተቀምጠው አገኙአቸው። የዘመኑም ቁጥር በውስጡ የተጻፈበትን በከሀዲው ንጉሥ በዳኬዎስ ዘመን የሆነውን ሠሌዳውን ወድቆ አገኙት ዘመኑም ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት እንደሆነ ታወቀ።

ንጉሡና ኤጲስቆጶሱ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉትም ይህን ድንቅ ሥራ አይተው ትንሣኤ ሙታን እንዳለ አመኑ። እሊህ ሰባቱ ደቂቅንም በጠየቋቸው ጊዜ ከእርሳቸው የሆነውን ሁሉ ነገሩአቸው።

ከዚህም በኋላ ተመልሰው ተኙ። ነፍሳቸውንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ። ንጉሥም የወርቅ ሣጥን ሠራላቸው በሐር ልብሶችም ገንዘው በመልካም ቦታ አኖሩዋቸው። ከሥጋቸውም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።

ስማቸውም:- መክሲማኖስ፣ ታሙኪሮስ፣ መርዳዲሞስ፣ ዮሐንስ፣ ቈስጠንጢኖስ፣ አዝሚና ዲዮናስዮ ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የእሊህም ቅዱሳን በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን!

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_20 እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
#ነሐሴ_26

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ ስድስት በዚህች ቀን ለአብርሃም ሚስት ለተመሰገነች #ቅድስት_ሣራ መታሰቢያዋ ነው፣ የከበረ #አባ_ሞይስስና_እኅቱ_ሣራ በሰማዕትነት ሞቱ፣ የከበሩ መነኰሳት #ቅዱሳን_አጋቦስና_ቴክላ በሰማዕትነት ሞቱ፣ የከበሩ አባቶቻችን #አቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ እና #አቡነ_ሀብተ_ማርያም የተፀነሱበት ዕለት ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሣራ

ነሐሴ ሃያ ስድስት በዚህች ቀን ለአብርሃም ሚስት ለተመሰገነች ሣራ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶች አዘዙ።

ይቺንም ክብርተ ማሕፀን የሆነች ጡቶቿም የተባረኩ ክብርት ሣራን የጌራራ ንጉሥ አቤሜሌክ ባል እንዳላት ሳያውቅ በወሰዳት ጊዜ እንዳይቀርባት #እግዚአብሔር ገሠጸው በደዌም ቀሠፈው ባሏ አብርሃምም በጸለየለት ጊዜ ከደዌው ተፈወሰ ከዚህም በኋላ ከብዙ ገንዘብ ጋራ ወደ ባሏ መለሳት።

ከዚህም በኋላ #እግዚአብሔር በሦስትነቱ ተገልጦ ወደ ቤቷ እንግድነት በመጣ ጊዜ ለአብርሃምም የይስሐቅን መወለድ በነገረው ጊዜ ሣራም በድንኳኑ ውስጥ ሳቀች እንዲህ ስትል እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል።

#እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው ሣራን ለብቻዋ ምን አሳቃት እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል እኔም አሁን አርጅቻለሁ ብላ በውኑ ለ #እግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን። ከዚህም በኋላ ሣራ ፀንሳ #እግዚአብሔር ባለው ወራት በርጅናዋ ለአብርሃም ወንድ ልጅን ወለደች።

ይስሐቅም በአደገ ጊዜ ልጅዋ ይስሐቅን ከእስማኤል ጋራ ሲጫወት አየችው። አብርሃምንም ሣራ እንዲህ አለችው ይቺን ባሪያ ከነልጅዋ አባራት የባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋራ አይወርስምና። ይህም ነገር ለአብርሃም ስለ ልጁ እስማኤል እጅግ ጭንቅ ሆነበት።

#እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው የዚህ ልጅ የዚችም ባሪያ ነገር በፊትህ ጭንቅ አይሁንብህ የምትልህን ሁሉ ሣራን ስማት ከይስሐቅ ዘር ይተካልሃልና።

ይህም ነገር ታላቅ ምሥጢር አለው የተመሰገነ ጳውሎስ ቅድስት ሣራን የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ አድርጓታልና። ከዚህም በኋላ በበጎ እርጅና በአረፈች ጊዜ ከኬጢያዊ ኤሞር ልጆች በገዛው ቦታ ቀበራት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ሞይስስና_እህቱ_ሣራ

በዚህች ቀን የከበረ አባ ሞይስስና እኅቱ ሣራ በሰማዕትነት ሞቱ። የእሊህም ቅዱሳን ወላጆቻቸው ደጎች እጅግም ባለጸጎች ናቸው። የከበረ ሞይስስ ወላጆቹ ከአረፉ በኋላ እኅቱ ሣራን ሊአጋባትና ወላጆቹ የተዉትን ገንዘብም ሊሰጣት እርሱም ወደ ገዳም ሒዶ ሊመነኵስ አሰበ።

ይህን አሳቡንም በነገራት ጊዜ እንዲህ ብላ መለሰችለት እኔን ልታጋባኝ ከወደድክ አስቀድሞ አንተ አግባ አርሱም እንዲህ አላት እኔ ብዙ ኃጢአት ሠርቻለሁ ስለዚህ ኃጢአቴን ለመደምሰስ እመነኵስ ዘንድ እሻለሁ ማግባት አይቻለኝም የነፍሴን መዳኛ አስባለሁ እንጂ ።

ሁለተኛም እንዲህ ብላ መለሰችለት አንተ ነፍስህን ስታድን እኔን በዓለም ወጥመድ ውስጥ እንዴት ትጥለኛለህ። እርሱም እንዲህ አላት ምንኵስና ከፈለግሽ ስለ ራስሽ የምታውቂ አንቺ ነሽ እኔም የወደድሺውን አደርግልሻለሁ።

እንዲህም አለችው ለነፍስህ የምታደርገውን ለኔም እንዲሁ አድርግ እኛ ሁለታችን ከአንድ ባሕርይ ከአንድ አባት ከአንዲት እናት የተገኘን ነንና የልቧንም ቆራጥነት አይቶ ወዲያውኑ ከእርሷ ጋራ ተነሣ ገንዘባቸውንም ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በተኑ።

ከዚህም በኋላ እኅቱ ሣራን ወሰዳት ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ ወዳለ የደናግል ገዳም ውስጥ አስገባት እርሱም ከወንዶች ገዳም ገብቶ በዚያ ተጋድሎን ተጋደለ። እንዲሁ እኅቱም ጽኑዕ በሆነ ገድል ተጠምዳ እየተጋደለች ሁለቱም ሳይገናኙ ዐሥር ዓመት ኖሩ።

በሊቀ ጳጳሳት አባ ድሜጥሮስ የሹመት ዘመን ሳዊርያኖስ የሚባል ከሀዲ ተነሥቶ የክርስቲያንን ወገኖች ማሠቃየት ጀመረ። ከመነኰሳት ገዳማትም ብዙዎች በሰማዕትነት ሞቱ። አባ ሞይስስም ተነሣ ሊሰናበታትም ወደ እኅቱ ሣራ ላከ በሰማዕትነት መሞት እንደሚሻም ነገራት።

ሣራ እኅቱም በሰማች ጊዜ ወዲያውኑ ተነሣች ሒዳ በሰማዕትነት ትሞት ዘንድ እንድታሰናብታት እመ ምኔቷን ለመነቻት እመ ምኔቷም ጸለየለችላት ሰላምታም ሰጥታ አሰናበተቻት እርሷም ደናግሉን ሁሉ ተሰናበተቻቸው።

ከዚህም በኋላ ወደ ወንድሟ ሔደች በጐዳናም አገኘችውና እርስ በርሳቸው ሰላም ተባባሉ ወደ እስክንድርያ ከተማም ገብተው በመኰንኑ ፊት ቁመው በክብር ባለቤት በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመኑ መኰንኑም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ከዚህም በኋላ ራሳቸውን በሰይፍ አስቆረጠ። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#መነኰሳት_አጋቦስና_እህቱ_ቅድስት_ቴክላ

በዚህችም ቀን የከበሩ መነኰሳት አጋቦስና ቴክላ በሰማዕትነት ሞቱ። እሊህም ቅዱሳን በከሀዲው ሉልያኖስ ዘመን መከራ በመቀበል ተጋደሉ ። ከመኳንንቶቹም አንዱ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ። ሥቃያቸውም በአሰለቸው ጊዜ ለአንበሶች ጣላቸውና ገድላቸውን ፈጽመው የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ

በዚህች ቀን አባታቻን አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የተፀነሱበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱሱ አባት ሀገራቸው ጎንደር ክፍለ ሀገር ስማዳ ወረዳ ሲና ዳኅና በሚባል ቦታ ነሐሴ 26 ቀን ተፀንሰው ግንቦት 26 ቀን 1210 ዓ.ም ከአባታቸው ዘክርስቶስና ከእናታቸው እግዚእ ክብራ ተወለዱ። የተወለዱትም በቅዱስ ነአኲቶ ለአብ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የቆብ አባት ሲሆኑ ታላቁን ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገዳም የቆረቆሩ ደገኛ አባት ናቸው፡፡

ዕድሜያቸው 30 ዓመት እስከሚደርስ ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ትምህርተ ሃይማኖትንና ግብረ ገብን ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በ1240 ዓ.ም ይህንን ዓለም በመተው ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገቡ፡፡ በደብረ ዳሞ ገዳም መነኰሳቱን እየረዱ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያጠኑ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየገለበጡ ለሰባት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደብረ ዳሞ 3ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ዮሐኒ እጅ ምንኩስናን በ1247 ዓ.ም ተቀበሉ፡፡

አንድ ቀን ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደርሳቸው መጥቶ ‹‹የስምህ መክበርያ ወደሆነው ሐይቅ ወደ ተባለው ሥፍራ ሂድ›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ቦታውን እንዴት ዐውቀዋለሁ?›› በማለት መልአኩን ቢጠይቁት ‹‹ተነሥ! ጉዞህን ጀምር ቦታውን እኔ አሳይሃለሁ›› አላቸው፡፡ አባ ኢየሱስ ሞዓ በመልአኩ እንደታዘዙት ከበዓታቸው ተነሥተው ተከተሉት፡፡ የብዙ ወራት መንገድ የሆነውን ጐዳናም በስድስት ሰዓት አደረሳቸው፡፡ በዚያን ወቅት ከሐይቅ ገዳም በስተ ሰሜን ወደነበረው ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ፡፡ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ከመግባታቸው በፊት ለ6 ወራት ያህል በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ያገለግሉበት በነበረው ቤተ ክርስቲያን ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፡፡ በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው ለነበሩ አበውም ማታ ማታ አንድ ብርሃን ወደ ሐይቁ ሲገባ ጠዋት ጠዋትም ሲወጣ ይታያቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን በገዳሙ አባቶች ልመናና በልዑል #እግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ ሐይቅ ገዳም ገብተው አበምኔት ሆኑ፡፡
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_30_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³² እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና።
³³ እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥
³⁴ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ።
³⁵ ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤
³⁶ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤
³⁷ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤
³⁸ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።
³⁹-⁴⁰ እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ይሁዳ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤
¹⁸ እነርሱ፦ በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና።
¹⁹ እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው።
²⁰ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥
²¹ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።
²² አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥
²³ አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ።
²⁴ ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው
²⁵ ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።
¹³ በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም።
¹⁴ እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_30_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"መንክር ተላህያ ለባሕር። መንክርሰ እግዚአብሔር በአርያሙ። ስምዐ ዚአከ እሙን፡ፈድፋደ"። መዝ 92፥4-5 ወይም መዝ 100፥6-7።
"ከብዙ ውኆች ድምፅ ከባሕርም ታላቅ ሞገድ ይልቅ እግዚአብሔር በከፍታው ድንቅ ነው። ምስክርህ እጅግ የታመነ ነው፤ አቤቱ፥ እስከ ረጅም ዘመን ድረስ ለቤትህ ቅድስና ይገባል"። መዝ 92፥4-5
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_30_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 24
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤
¹⁴ ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር።
¹⁵ ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤
¹⁶ ነገር ግን እንዳያውቁት ዓይናቸው ተይዞ ነበር።
¹⁷ እርሱም፦ እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው? አላቸው።
¹⁸ ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ፦ አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው።
¹⁹ እርሱም፦ ይህ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፤
²⁰ እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው።
²¹ እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው።
²² ደግሞም ከእኛ ውስጥ ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤
²³ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ፦ ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን ሲሉ መጥተው ነበር።
²⁴ ከእኛም ጋር ከነበሩት ወደ መቃብር ሄደው ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፥ እርሱን ግን አላዩትም።
²⁵ እርሱም፦ እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤
²⁶ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው።
²⁷ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው።
²⁸ ወደሚሄዱበትም መንደር ቀረቡ፥ እርሱም ሩቅ የሚሄድ መሰላቸው።
²⁹ እነርሱ፦ ከእኛ ጋር እደር፥ ማታ ቀርቦአልና ቀኑም ሊመሽ ጀምሮአል ብለው ግድ አሉት፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ።
³⁰ ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፥ ቈርሶም ሰጣቸው፤
³¹ ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ።
³² እርስ በርሳቸውም፦ በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን? ተባባሉ።

ወይም

ማርቆስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ።
²-³ እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ፥
⁴ ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ።
⁵ የይሁዳም አገር ሁሉ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፥ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።
⁶ ዮሐንስም የግመል ጠጉር ለብሶ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ አንበጣና የበረሀ ማርም ይበላ ነበር።
⁷ ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል።
⁸ እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱሳን_ሐዋርያት_ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢዩ ቅዱስ ሚልክያስ የዕረፍት በዓልና የሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ የመታሰቢያ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጳጒሜ_2_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ቲቶ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእግዚአብሔር ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ፤ ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ፥
³ በዘመኑም ጊዜ፥ መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ፥ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ፤
⁴ በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጄ ለሚሆን ለቲቶ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።
⁵ ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፥ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፥ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ፤
⁶ የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሚሆን፥ የሚያምኑም ልጆች ያሉት፥ ስለ መዳራትም ወይም ስለ አለመታዘዝ የማይከሰስ ማንም ቢኖር፥ ሹመው።
⁷ ኤጲስ ቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥
⁸ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤
⁹ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና።
¹⁰ የማይታዘዙና ከንቱ የሚናገሩ የሚያታልሉ ይልቁንም ከተገረዙት ወገን የሚሆኑ ብዙ ናቸውና፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁷ አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።
⁸ እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ።
⁹ ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።
¹⁰ የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።
¹¹-¹² ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤
¹³ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³¹ ከጸለዩም በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፥ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ።
³² ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፥ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም።
³³ ሐዋርያትም የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸው።
³⁴ በመካከላቸው አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረምና፤ መሬት ወይም ቤት ያላቸው ሁሉ እየሸጡ የተሸጠውን ዋጋ ያመጡ ነበርና፥
³⁵ በሐዋርያትም እግር አጠገብ ያኖሩ ነበር፤ ማናቸውም እንደሚፈልግ መጠን ለእያንዳንዱ ያካፍሉት ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጳጒሜ_2_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር። ምክር ሠናይት ለኵሉ ዘይገብራ። ወስብሐቲሁኒ ይነብር ለዓለም"። መዝ 110፥10።
“የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥ ለሚያደርጓትም ሁሉ ደኅና ማስተዋል አላቸው፤ ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።” መዝ 110፥10።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጳጒሜ_2_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎቹን ሰብዓ ሾመ፥ ሁለት ሁለትም አድርጎ እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ በፊቱ ላካቸው።
² አላቸውም፦ መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።
³ ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ።
⁴ ኮረጆም ከረጢትም ጫማም አትያዙ፤ በመንገድም ለማንም እጅ አትንሡ።
⁵ ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ፦ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ።
⁶ በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል።
⁷ በዚያም ቤት ከእነርሱ ዘንድ ካለው እየበላችሁና እየጠጣችሁ ተቀመጡ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና። ከቤት ወደ ቤት አትተላለፉ።
⁸ ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሉአችሁ፥ ያቀረቡላችሁን ብሉ፤
⁹ በእርስዋም ያሉትን ድውዮችን ፈውሱና፦ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች በሉአቸው።
¹⁰ ነገር ግን ወደምትገቡባት ከተማ ሁሉ ባይቀበሉአችሁ፥ ወደ አደባባይዋ ወጥታችሁ፦
¹¹ ከከተማችሁ የተጣበቀብንን ትቢያ እንኳን እናራግፍላችኋለን፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን እወቁ በሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱሳን_ሐዋርያት_ቅዳሴ ነው። መልካም የሐዋርያው የቅዱስ ቲቶ የዕረፍት በዓልና የጾም፣ የጸሎትና የምሕላ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️