TIKVAH-ETHIOPIA
1.44M subscribers
55.9K photos
1.4K videos
202 files
3.77K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
የአግ 7 ወቅታዊ መግለጫ⬇️

አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ ዛሬ በመከሄድ ላይ ያለዉ የለዉጥ እንቅስቃሴ የለዉጥ ሂደቱ ቀጥተኛ ባለቤት የሆነዉን የኢትዮጵያን #ህዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት የናፈቀዉን መላዉን የአለም ህዝብ ያስደመመ ለዉጥ ነዉ። ይህ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ከተጠናወተን የባዶ ድምር የመጠፋፋት ፖለቲካ አላቆን ልዪነቶቻችንን በሰለጠነ መንገድ ማስወገድ ወደምንችልበት የፖለቲካ ስርአት የሚወስደን የለዉጥ ሂደት ባለፉት ጥቂት ወራት በብዙ ውጣዉረዶች ዉስጥ የተጓዘ ቢሆንም አጀማመሩ የሚያበረታታና ተስፋ የሰነቀ ነዉ።

ባለፉት ሁለትና ሦስት ወራት ዉስጥ በግልጽ እንደተመለከትነዉ የዚህ ለዉጥ ደጋፊ የሆኑና ለዉጡን ወደፊት ለማራመድ የሚፈልጉ የሰብዓዊ መብት ታጋዮች፥ ታዋቂ ግለሰቦች፥ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሀይማኖት አባቶች ለብዙ አመታት በስደት ከኖሩባቸዉ አገሮች ወደ
እናት አገራቸዉ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ከእነዚህ ወደ አገራቸዉ ከተመለሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ዉስጥ አንዱ አርበኞች ግንቦት 7 ነዉ።

አርበኞች ግንቦት 7 ገና ከምስረታዉ ጀምሮ ካራመዳቸዉና ዛሬም በግምባር ቀደም ከሚያራምዳቸዉ መርሆዎች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚመሰረተዉ የፖለቲካ ስርአት በዜግነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርአት መሆን አለበት የሚል ጠንካራ መርህ ነዉ።

የዜግነት ፖለቲካ ደግሞ የራሱ መብትና ነጻነት እንዲከበር የሚፈልገዉን ያክል እሱም የሌሎችን መብትና ነጻነት ማክበር እንዳለበት የሚያውቅና የሚረዳ ዜጋ መኖርን የግድ ይላል። አርበኞች ግንቦት 7 ኢትዮጵያ ዉስጥ መገንባት አለበት ብሎ ለአመታት የታገለለት ዲሞክራሲያዊ ስርአት ከሚፈልጋቸዉ ቅድመ ሁኔታዎች ዉስጥ አንዱና ትልቁ የፖለቲካ አካሄዳቸዉ ከማይጥመንና በሃሳብ ከምንለያያቸዉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ወይም የወል ስብሰቦች ጋር ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር መቻልን ነዉ። የማይስማማንን እና የምንቃወመዉን የፖለቲካ አቋም ሠላማዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድ የማንችል ከሆነ #ዲሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት ቀርቶ ስለ ዲሞክራሲ ማሰብም አንችልም።

ባለፈዉ እሁድ ጳጉሜ 4 ቀን 2010 ዓም በዉጭ አገሮች ለረጂም አመታት ይንቀሳቀሱ የነበሩት የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ከፍተኛ አመራር አባላት ወደ አገራቸዉ ሲመለሱ የአዲስ አበባና አካባቢዉ ነዋሪ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ የኔ ነዉ ብሎ የሚያምንበትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ እያውለበለበ በደስታና በሆታ ከፍተኛ አቀባበል አድርጎላቸዋል።

አገር ውስጥ ሆነው በነጻነት ትግል ለማካሄድ እንዳይችሉ የተገፉ ሌሎችም የፖለቲካ ድርጅቶች ባለፉት ሶስት ወራት ዉስጥ ወደ አገራቸዉ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፥ አሁንም በመመለስ ላይ ናቸዉ። እነዚህ ወደ አገራቸዉ የሚመለሱ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እናራምዳለን ብለዉ የታገሉለትን የፖለቲካ ፕሮግራምና የኤኮኖሚ ፖሊሲ አምኖ የተቀበለ አባልና ደጋፊ አላቸዉ። የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች የንቅናቄዉ አመራር አባላት ከዉጭ አገሮች ሲገቡ #ያሰኛቸዉን አርማና መፈክር ይዘዉ ወጥተዉ አንደተቀብሏቸዉ ሁሉ አሁን በመግባት ላይ ያሉና ወደፊትም ወደ አገራቸዉ የሚገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላትና ደጋፊዎች ያሰኛቸዉን አርማና መፈክር አንግበዉ መሪዎቻቸዉን የመቀበል ሙሉ #መብት ሊኖራቸዉ ይገባል ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 በጽኑ ያምናል። ንቅናቄው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በጽናት እየታገለ ያለው ዜጎች ድጋፋቸውንም ሆነ ተቃውሟቸውን #በነጻነት መግለጽ የሚችሉበት ሥርአት በአገራችን እንዲሰፍን ነዉ እንጂ አንዱ የሌላውን መብት በጉልበትና በሀይል መጨፍለቅ እንዲችል አይደለም።

ከሰሞኑ በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መሪዎች ወደ አገራቸዉ ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች በጎዳናዎች ላይ የሰቀሉትን የድርጅታቸውን ባንዲራ እናወርዳለን በሚሉና መውረድ የለበትም በሚሉ ሀይሎች መካከል የተነሳዉ አግባብ የለሽ #ግጭት ንቅናቄያችን የሚታገልለትን የዲሞክራሲ መርህ #የሚጻረር ተግባር ከመሆኑም በላይ በአገራችን የፈነጠቀውን የመቻቻል ፖለቲካ ከጅምሩ የሚያደበዝዝ በመሆኑ አርበኞች ግንቦት 7 ድርጊቱን በጽኑ #እያወገዘ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ የንቅናቄያችን አባላትና #ደጋፊዎች ቢኖሩ ከዚህ አይነቱ ትርጉም የለሽና ፀረ-ዲሞክራሲ የሆነ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ #እንዲታቀቡ ያሳስባል።

አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ የፖለቲካ ልዩነቶችን ማስተናገድ የሚችል የፖለቲካ ስርአት እንገነባለን ስንል የተለያዩ የፖለቲካ ሀይሎች በፖለቲካ አስተሳስብና በርዕዮተ አለም ቢለያዩም በልዩነቶቻቸዉ ላይ ተከባብረዉና የህዝብን ዳኝነት ተቀብለዉ መኖር አለባቸዉ ማለት ነዉ።

ስለሆነም ከሰሞኑ በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በታዩ ሽኩቻዎች ላይ በሁለቱም ጎራዎች የተሳተፉ ሀይሎች ሁሉ እንደ ማህበረሰብ አንድ ላይ ከሚያጠፋን የፖለቲካ አካሄድ ተላቅቀዉ እንደ አንድ አገር ህዝብ ጎን ለጎን አብሮ የሚያቆመንን የፖለቲካ ስርአት በጋራ መገንባት የሚያስችለንን ሁኔታ ፈጥረን የጋራ አገራችንን በጋራ እንድንገነባ አርበኞች ግንቦት 7 አገራዊ የአደራ ጥሪ ያስተላልፋል።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለአለም ትኑር!!!

የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ
@tsegabwolde @tikvahethiopia