TIKVAH-ETHIOPIA
1.41M subscribers
55K photos
1.37K videos
199 files
3.67K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ደመወዝ

• " ደመወዝ በሰዓቱ እየተከፈለን ባለመሆኑ ቤተሰብ ለማስተዳደር አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሰናል " - ሰራተኞች

• " በዚህ ወር ለሰራተኛ ደመወዝ ለመክፈል 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ ቢሆንም አሁን ላይ 8 ሚሊየን ብር ብቻ ነው የተገኘው " - ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ት ቤት

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በሚገኘው የካፋ ዞን ፤ ጌሻ ወረዳ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ በአግባቡ እየተከፈላቸው እንዳልሆነ ገልፀዋል።

ሰራተኞቹ ፤ የወርሃዊ ደመወዝ በአግባቡ አለመከፈሉ ለችግር እየዳረጋቸው መሆኑን አመልክተዋል ፤ በዚህ ሳቢያ ህይወታቸውን ለመግፋት ፈተና እንደሆነባቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ጠቁመዋል።

የወረዳው ኮሚኒኬሽን በበኩሉ ፤ በየወሩ በተደጋጋሚ ደምወዝ በአግባቡ ባለመከፈሉ ምክንያት የመንግስት ሰራተኞች #ለአላስፈላጊ_ወጪዎች እና #ችግሮች መዳረጋቸውን እንደገለፁ አሳውቋል። ገልጿል።

" በተያዘው የበጀት አመት አንድም ቀን ደመወዝ በጊዜው ተከፉሎ አያውቅም " ያሉት ሰራተኞቹ " ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል " ብለዋል።

የመንግስት ሰራተኞቹ ያለፈው የህዳር ወር ደመወዝ እስከ ትላንት ታህሳስ 12 ቀን ድረስ እንዳልተከፈላቸዉ ገልፀው " ቤተሰብ ለማስተዳደር አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሰናል " ብለዋል።

" ቀጣይም የሚከበረውን #የገናን_በዓል ለማክበር ደመወዝ በወቅቱ የማይገባ ከሆነ ለከፋ ችግር ልንዳረግ እንችላለን " ሲሉ ስጋታቸውን ጠቁመዋል። ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ዘላቂ መፍትሔ እንዲያበጅለትም ቅሬታ አቅራቢዎች ጠይቀዋል።

የጌሻ ወረዳ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ፅህፈት ቤት ፤ " የሰራተኞችን ቁጥር ታሳቢ ያላደረገ በጀት ከዞኑ መለቀቁ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ነው " ሲል አሳውቋል።

የጽ/ቤቱ ኃላፊ የሆኑት አቶ ታደሰ ቆጭቶ ፤ " ችግሩ ከዞን የሚለቀቀው ደመወዝ ሰራተኛውን ያመጣጠነ አለመሆኑ ነዉ " ያሉ ሲሆን በተለይም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ ደመወዝ እየተለቀቀ እንዳልሆነና በዚህ ወር ለሰራተኛ ደመወዝ ለመክፈል 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ ቢሆንም አሁን ላይ 8 ሚሊየን ብር ብቻ ማግኘት እንደተቻለ ተናግረዋል።

ኃላፊው "አሁን ላይ ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታትና ከመማር ማስተማር ጋር ተያይዞ መስተጓጐል እንዳይፈጠር ለመምህራን ብቻ ደመወዝ መክፈል ተችሏል " ያሉ ሲሆን " የሌሎችን ሰራተኞች ችግር ለመፍታት ከሚመለከተው አካላት ጋር እየተወያየን ነው " ብለዋል።

በሌላ በኩል በተመሳሳይ በዞኑ በ " ገዋታ ወረዳ " ያሉ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ የቲክቫህ ቤተሰብ አባላት ባለፉት በርካታ ወራት ደመወዝ በአግባቡ እየገባላቸው እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

የባለፈው ህዳር ወር ደመወዝም እስካሁን እንዳልገባ ገልፀው ፤ " ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሩ ከመፈታት ይልቅ እየተባባሰ ነው የሄደው፤ ለምን ይህ ይሆናል ? ብለን ስንጠይቅ የተለያየ ምክንያት ነው የሚሰጠን " ብለዋል።

ዛሬ በስልክ ያነጋገርነው የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል የሆነ አንድ መምህር ባለፉት በርካታ ወራት ለአንድም ቀን ደመወዝ በአግባቡ እየገባ እንዳልሆነና በዚህ ምክንያት የትምህርት ስርዓቱ ላይ መስተጓጎል እንደተፈጠረ አመልክቷል።

መምህሩ ፤ " ለበርካታ ወራት በሰዓቱ ደመወዝ ገብቶ አያውቅም ፤ ግፋ ቢል 15 ቀን 13 ቀን ወስዶ ነው እየገባ ያለው። የዚህ ጉዳይ ምክንያት ምንድነው ተብለው ሲጠየቁ ከፋይናንስ በጀት ተቀንሶ እየገባ መሆኑና ለሴክተር ሰራተኞች / ለመምህራን ማዳረስ እንደማይቻል ተብሎ ነው እየተነገረ ያለው። ለዚህ መፍትሄ አጥተን ነበር እንደአጋጣሚ ዛሬ ለመምህራን ደመወዝ እየገባ እንደሆነ እየተነገረ ነው ገና የህዳር ወር ፤ በዚህ ደመወዝ በአግባቡ አለመከፈሉ ምክንያት ትምህርትም ተስተጓግሎ ነበር ፤ እስከዚህ ድረስ ነው የችግሩ ስፋት " ብለዋል።

እኚሁ መምህር ፤ ዛሬ ሀሙስ ታህሳስ 13 የህዳር ወር ደመወዝ እየገባ እንደሆነ የሰሙት የመምህራንን ብቻ እንደሆነ ለሴክተር ሰራተኞች ገና መፍትሄ እየተፈላለገ ስለመሆኑ እንደሰሙ ገልፀዋል።

በወረዳው ደመወዝ በአግባቡ አለመግባት ሰራተኛውን ለችግር እና ለተለያዩ ወጪዎች እየዳረገው መሆኑ ተገልጿል ፤ ችግሩ እጅግ አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚፈልግም መልዕክታቸውን የላኩ ሰራተኞች አስገንዝበዋል።

@tikvahethiopia