AddisWalta - AW
48.3K subscribers
44K photos
222 videos
20 files
16.9K links
This is Walta Media and Communication Corporate’s official Telegram channel.

For more updates please visit https://shorturl.at/ehosX https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
Download Telegram
ሻሸመኔ
#ከተሞቻችን

የምዕራብ አርሲ ዞን ዋና መቀመጫ የሆነችው የሻሸመኔ ከተማ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ አቅጣጫ 255 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን በ1913 እንደተቆረቆረች ይነገርላታል።

ከከተማዋ ስያሜ ጋር በተያያዘ እንደ አፈታሪክ የምትነሳ አንዲት "ሻሼ" የምትባል እንግዳ ተቀባይ ሴት በአካባቢው ትኖር እንደነበር እና የሻሼ ቤት ወይም በኦሮምኛ "መነ-ሻሼ" የሚለው የስፍራው ስያሜ በጊዜ ሂደት ተቀይሮ ሻሸመኔ እንደተባለ በታሪክ ይወሳል።

ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያላት የሻሸመኔ ከተማ ከባህር ጠለል በላይ 1937 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች።

ጀምበር የማይጠልቅባት የሻሸመኔ ከተማ የዞኑ ዋና የንግድ እና የትራንስፖርት ማዕከል ስትሆን ሐዋሳን ጨምሮ ወላይታ እና ዲላን የምታገናኝ ባለ5 በር ኮሪደር ከተማ ነች።

የተለያዩ ብሄረሰቦችን በጉያዋ ያቀፈችው ሻሸመኔ በ12 ወረዳ እና 4 ክፍለ ከተማዎች የተዋቀረች ስትሆን አቦስቶ፣ ጎፋ፣ አዋሾ፣ ኩዬራ እና አራዳ ከሰፈር ስያሜዎቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

ከበሀማስ፣ ከኮቤኮ፣ ከካሪቢያን እና ከጃማይካ የመጡ ዜጎች ለበርካታ ዓመታት ከትመው የሚኖሩባት ከተማ እንደሆነችም ይነገርላታል።

በከተማዋ ሻሸመኔ ሙዚየምና የተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሊድ ስታር ኢንተርናሽናል አካዳሚ፣ ሉሲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሚሊኒየም ሻሸመኔ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ እናት ኮሌጅ እና የሻሸመኔ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ይገኙበታል።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0tqnYZqVyqH8k4ni2NZqrG57kTBLcjgagtMR986bCEyGm6CVVHv7gsMjX8ct6TbNpl
#ከተሞቻችን
ዓዲግራት

በ14ኛው ክፍለ ዘመን እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ታሪካዊቷ የዓዲግራት ከተማ ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተሰሜን አቅጣጫ 1ሺሕ 38 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

የአመለሸጋ ሕዝብ መገኛ፣ የአብሮነት ማሳያና በእንግዳ አክባሪነቷ ተምሳሌት የሆነች ከተማ ናት፡፡

ከተማዋ ከባሕር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 457 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን ደጋማ የአየር ፀባይ አላት፡፡

ለከተማዋ ስያሜ የሆነውና "ዓዲግራት" የሚለው ቃል ትግርኛ ሲሆን ትርጓሜውም "የእርሻ መሬት ሀገር" እንደ ማለት ነው።

በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተገነባ የሚነገርለት "ደብረ ዳሞ" እና የ"ጉንዳ ጉንዶ" ገዳማት በዓዲግራት አካባቢ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው፡፡

የከተማዋ ተወላጆች ከየአሉበት ተሰባስበው ከወላጆቻቸው ጋር የመስቀል እና የአረፋ በዓላትን በድምቀት የሚያከበሩባት ከተማ ነች።

ሙሉውን ለማንበብ ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0AJQXDKAqaHh6RecyrUZ85bL8CvqapPPVVEJrhjcTUR4XzYDDCKNa1SBB5HEkEGQgl
ዲላ
#ከተሞቻችን

የአረንጓዴው ምድር የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ከተማና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የክላስተር ከተሞች አንዷ የሆነችው ዲላ ከመዲናችን አዲስ አበባ በደቡብ አቅጣጫ 365 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የሰላም እና የአብሮነት ተምሳሌት የሆነችው ዲላ ከተማ በ1904 ዓ.ም ገደማ በቀድሞ የሲዳማ ሀገር ገዥ ባራምባራስ ደቻ ኡዶ እንደተቆረቆረች ይነገራል። ምስረታዋም ከቀረጥ ኬላ መከፈት ጋር ተያይዞ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ቆላማ የአየር ንብረት ያላትና ነፋሻማዋ የዲላ ከተማ 1 ሺሕ 570 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ያላት ሲሆን ሜዳማ እና ተራራማ መልክዓ ምድራዊ ተፈጥሮ ተሸልማለች።

በሶስት ክፍለ ከተሞች እና በዘጠኝ ቀበሌዎች የተዋቀረችው ዲላ ከተማ የተለያዩ የሰፈር እና መንደር ስያሜዎችም አሏት፡፡ ከነዚህም ሁላ፣ ናገአ፣ ሻላዬ፣ ጎላ እና ዶምቦስኮ ይገኙበታል።

በአከባቢው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆነው ቡናን ጨምሮ እንሰት፣ ገብስና ስንዴ እንዲሁም ሌሎች ምርቶች ይመረታል፡፡ ዲላ በአትክልት እና ፍራፍሬ የምትታወቅ ሲሆን ማንጎ፣ ሙዝ፣ አቮካዶ እና ፖም ተጠቃሾች ናቸው።

ከከተማዋ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙትን የቱቱፈላ ትክል-ድንጋይ እና ጥንታዊው የጪጩ ገብርኤል ገዳምን ጨምሮ የዋሻ ላይ ስዕሎች፣ ፏፏቴዎች እንዲሁም የፍል ውሃን ለመጎብኘት ለሚመጡ ቱርስቶች ምቹ ማረፊያና መዳረሻም ናት የድላ ከተማ።

ከተማዋ የጌዴኦ ዘመን መለወጫ በዓል የሆነው "ደራሮ" በድምቀት የሚከበርባትም ከተማ ናት።
👇👇
https://shorturl.at/tzCOT
#ከተሞቻችን
ጅግጅጋ

የምስራቋ ፈርጥ፣ የብዙኃን መናህሪያ እና የእንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ምድር የሆነችው የጅግጅጋ ከተማ ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተምስራቅ አቅጣጫ 618 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

በአብዛኛው ሜዳማ ተፈጥሯዊ የመሬት ገፅታ የተጎናጸፈችው ይህች ከተማ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና መቀመጫ ናት፡፡

ከባህር ጠለል በላይ 1ሺሕ 609 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ጅግጅጋ ሞቃታማ የአየር ንብረት አላት፡፡ ከተማዋ በ1916 ዓ.ም በፊታውራሪ ተክለ ሐዋሪያት ተክለ ማርያም እንደተመሰረተች ይነገራል።

ጅግጅጋ የሚለው ቃል መነሻው ሕዝቡ የውሃ ጉድጓዶች ሲቆፍር ከተሰሙ የተለያዩ የ"ጂግ-ጂግ" ድምፆች መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብ "ላአ" ተብሎ ይጠራ እንደነበር እና ይህም በሶማሌ ቋንቋ "ማራኪ እይታ" ማለት እንደሆነ ይነገራል።

የካራማራ ሰንሰለታማ ተራራ ከጂግጂጋ ከተማ በ12 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ውብ እና አረንጓዴ መልከዓ ምድራዊ ተፈጥሮ ያለው ይህ ተራራ የካራማራ የድል ብስራት ህያው ምስክርም ጭምር ነው።

ጅግጅጋ በአራት ክፍለ ከተማ እና ሀያ ቀበሌዎች የተዋቀረች ስትሆን ክፍለ ከተማዎቿ ካራማርዳ፣ ዱዳሂዲ፣ ጋራብአሴ እና ቆርዴሬ ይባላሉ፡፡
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid02kXrPXbE7B9Zo2QiSZStaASibiaWH4tqHiUFMShGMcrqfnkZZ5YcUcwT7SffMBtP8l
ሆሣዕና
#ከተሞቻችን

ሆሣዕና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ክላስተር ከተሞች አንዷ ስትሆን የሀዲያ ዞን አስተዳደር ዋና መቀመጫም ናት፡፡ ከተማዋ ከአዲስ አበባ በደቡብ አቅጣጫ 230 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

ሆሳዕና ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 217 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝና ወይናደጋ የአየር ንብረት ያላት ሜዳማ እና ተዳፋታማ ተፍጥሯዊ የመሬት ገፅታን ተላብሳለች፡፡

በ1888 ዓ.ም እንደተቆረቆረች የምነገርላት ሆሳዕና የከተማዋ የቀድሞ መጠሪያ ዋቸሞ እንደነበርና ወደ ሆሳዕና የቀየሩት ራስ አባተ ቧያለው ሲሆኑ ተሹምው ወደ ስፍራው ባመሩበት ዕለት እየተከበረ የነበረውን የሆሳዕና በዓል ምክንያት በማድረግ እንደሆነም ይነገራል።

ሆሣዕና በስድስት ቀበሌዎች የተዋቀረች ከተማ ስትሆን ኬንተሪ፣ ገብረፃዲቅ፣ የአብስራ፣ ማሪያም፣ ሞቢል፣ ቁጭራ፣ አራዳ እና ካናል/መሳለሚያ በሚል የሚጠሩ የሰፈር ስያሜዎችም አሏት።

በከተማዋ የከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሆነውን ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ፣ ሆሣዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ ሆሳዕና መምህራን ኮሌጅ እንዲሁም ቅድስት ስላሴ፣ ዋቸሞ 1ኛ ደረጃ፣ አለሙ ወልደሀና 2ኛ ደረጃ እና ሌሎችም ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ።

ሆሣዕና ምቹ የሆቴል እና ቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚታይባት ከተማ ስትሆን ቪክትሪ፣ አዲላ፣ ዋኣኔ መላይ፣ ዎዜ ስታር፣ በረከት እና የመሳሰሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እና ሌሎች ይጠቀሳሉ።
👇👇
https://shorturl.at/ghpFR
ባህር ዳር
#ከተሞቻችን

በ13ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ባህር ዳር ከተማ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መቀመጫ ስትሆን የቀድሞ ስያሜዋም ባህር ዳር ጊዮርጊስ ይባል እንደነበር ታሪክ ይጠቅሳል።

አፄ ሰርጸ ድንግል “ታቦቱን የት እናኑረው” ተብለው በተጠየቁ ጊዜ "ባህሩ ዳር" ማለታቸውን ተከትሎ ከተማዋ ባህር ዳር በሚል ስያሜ መጠራት መጀመሯንም በአፈ ታሪክ ይነገራል።

ከአዲስ አበባ በሰሜን አቅጣጫ 565 ኪ.ሜ ርቀት እንዲሁም ከባህር 1 ሺሕ 801 ሜትር ከፍታ ላይ የከተመችው ባህር ዳር ወይናደጋ የአየር ፀባይ ያላት እና ውብ አረንጓዴ ተፈጥሮን የተለገሰች ከተማ ናት።

ባህርዳር በ6 ክፍለ ከተሞች፣ 3 የሳተላይት ከተሞች እና 11 የገጠር ቀበሌዎች የተዋቀረ የከተማ አስተዳደር ያላት ሲሆን ታዋቂ ከሆኑ የሰፈር ስያሜዎቿ መካከልም ሞቢል፣ አየርሜዳ፣ ዘንዘልማ፣ ጎርደም፣ ዓባይ ማዶ እና መሸንቲ ይገኙበታል።

በብዝኃ ህይወት ጥበቃ በዩኔስኮ የተመዘገበው እና እንደ ዳጋ እስጢፋኖስ፣ ክበራን ገብርኤል እና እንጦስ ኢየሱስን ያሉ 21 የሚደርሱ ጥንታዊ ገዳማትን በደሴት አቅፎ የያዘው ጣና በኢትዮጵያ ትልቁ ሀይቅ ሲሆን ጥቁር ዓባይን ከራሱ ሳይቀላቅል ለዘመናት ያሻገረ የከተማዋ ውበት ልዩ ተፈጥሯዊ መገለጫ ነው።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid02SFyq2X5GhK7wmJp5TAieRkoauPpJJA6tpXxso54GuFQie9QFHcT8WM3GAptwAK4Kl
ነቀምቴ
#ከተሞቻችን

ነቀምቴ በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና መቀመጫ ሆና በማገልገል ላይ የምትገኝ ለምለሟ የንግድ ከተማ ናት፡፡ ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተምዕራብ አቅጣጫ በ328 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

ከተማዋ በ1830 ዓ.ም በደጅ አዝማች ሞሮዳ በከሬ እንደተቆረቆረችም ይነገርላታል።

ደጋማ የአየር ንብረት ያላት የነቀምቴ ከተማ ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 88 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን ኮረብታማ እና ሜዳማ መልክዓ ምድራዊ ተፈጥሮንም ተላብሳለች።

የምዕራብ ኦሮሚያ ትልቋ ከተማ እንደሆነች የሚነገርላት ነቀምቴ አራት የመውጫ መግቢያ በሮች አሏት፡፡ እነዚህም በሮች ከተማዋን ከአዲስ አበባ፣ ከጅማ፣ ከአሶሳ እና ከባሕርዳር ጋር ያገናኛሉ።

በሰባት ክፍለ ከተሞች የተዋቀረችው ነቀምቴ በከተማዋ ብዙ የሰፈር ስያሜዎች አሏት፡፡ ከእነዚህም በኪጃማ፣ ቀሶ፣ ቦርድ፣ ሸዋበር፣ አጂፕ፣ ማሪያም እና ደርጌ ጥቂቶቹ ናቸው።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid027c3GVofwttjqpAkz9NoALCN9Mn62zDXzKGuHdJhVVv53eg8zswvQ9jPBbUrb5NfSl
ኮምቦልቻ
#ከተሞቻችን

የፍቅር፣ የደግነት እና የአብሮነት ከተማ የሆነችው ኮምቦልቻ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ ትገኛለች፡፡ ከተማዋ የቀድሞ ስያሜዋ "ቢራሮ" እንደነበረና በ1928 ዓ.ም በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ወቅት እንደተቆረቆረች ይነገራል፡፡

ኮምቦልቻ ከተማ በየጎፍ ተራራ የተከበበች ናት። በአካባቢው ገዝፎ የሚታየው እና አቀበት ከሆነው አንቻሮ ፊት ለፊት ተገትሮ የሚገኘው የጎፍ ተራራ ደግሞ ለበርካታ የዱር እንስሳት መኖሪያ የሆነ ጥብቅ ደን ያለበት ነው፡፡

ለከተማዋ የስም ስያሜ ሁለት መላ ምቶች የሚሰጡ ሲሆን አንደኛው "ኮምቦልሻ" ከሚል ኦሮምኛ ቃል ሆኖ ትርጓሜውም ነጭ ግራር የከበባት ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ "ካምቦሉቻ" የሚል የጣሊያንኛ ቃል ሆኖ ትርጓሜው መብራት ያለበት ሰፈር ማለት እንደሆነ ይገለጻል።

ከባህር ጠለል በላይ በ1 ሺሕ 857 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ኮምቦልቻ ከተማ ወይና ደጋ የአየር ንብረት አላት፡፡ በአብዛኛው ሜዳማ እና ተራራማ ተፈጥሯዊ የመሬት ገፅታንም ተላብሳለች።

ከአዲስ አበባ በ377 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ኮምቦልቻ ደረጃውን የጠበቀ አየር ማረፊያ እና ደረቅ ወደብ ያላት ሲሆን በክልሉ ከሚገኙ አራት የኢንዱስትሪ ከተሞችም አንዷ ናት።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid02AuberQEYp4r3maZYyz2NEL7BVBy92JrUmsA5UGDgtvwnVJ5x44y5oBnsBXcV85Y6l
ቢሾፍቱ
#ከተሞቻችን

የኢትዮ-ጅቡቲን የባቡር መስመር ዝርጋታ ተከትሎ በ1917 ዓ.ም እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ቢሾፍቱ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የምትገኝ ከተማ ስትሆን ከአዲስ አበባ በ47 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።

ከባህር ጠለል በላይ 1 ሺሕ 920 ሜትር አማካኝ ከፍታ እና ወይናደጋ የአየር ፀባይ ያላት ቢሾፍቱ ስያሜዋን ያገኘችው "ቢሻን ኦፍቱ" ከሚለው የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ትርጉሙም "ውሃ የሞላባት" ማለት ነው።

የረር፣ ባቦጋያ፣ ሀደው እና ኤባዩ በሚባሉ ተራሮች የተከበበችው ቢሾፍቱ ወደ ሰባት የሚደርሱ ሀይቆችን በውስጧ የያዘች ሲሆን ቢሾፍቱ፣ ባቦጋያ፣ ሆራ አርሰዴ፣ ኪሎሊ፣ ጨለለቃ፣ ኩሪፍቱ እና በልበላ ደግሞ ስያሜያቸው ነው።

ቢሾፍቱ በዘጠኝ የከተማ እና በአምስት የገጠር ቀበሌዎች የተዋቀረች ከተማ ስትሆን ታዋቂ ከሆኑ የሰፈር ስያሜዎቿ መካከል ሰርክል፣ 60 ማዞርያ፣ እጥቤ፣ ዝቋላ፣ ለምለም፣ ጌትሸት እና ሰንሻይን ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና ቢሮ የሚገኝባት ቢሾፍቱ በርካታ የሥልጠናና የምርምር ማዕከላት ያሏት ሲሆን የአየር ኃይል አካዳሚን ጨምሮ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምና ፋኩልቲ፣ ብሔራዊ የእንስሳት ሕክምና ኢንስቲትዩት እና ቢሾፍቱ የግብርና ምርምር ማዕከል በከተማዋ ይገኛሉ።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0YC1TzcR8iUcTeVk88wA95G6MU2uexkSCmyFFm8hR4VsfxrdteQjV9HeAcsh1KpdNl
ሽረ እንዳሥላሰ
#ከተሞቻችን

በ14ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በመንደርነት ተመስርታ በ1928 ዓ.ም ወደ አውራጃነት ያደገችው ሽረ በአሁን ሰዓት የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ክልል ፈርጥ ከተማ ስትሆን የታህታይ ቆራሮ ወረዳ አስተዳደር ማዕከል ነች።

ሽረ ከባህር ጠለል በላይ 1ሺሕ 953 ሜትር አማካኝ ከፍታ እና ወይና ደጋ የአየር ፀባይ ያላት በኮረብታማ መልከዓ ምድር የተከበበች ከተማ ስትሆን ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተሰሜን 1ሺሕ 87 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።

ከስያሜዋ ጋር በተያያዘ በጊዜው የነበረ ጀግና ኩናማዎችን አሸንፎ ከተማውን እንደተቆጣጠረ ለሕዝቡ ማሸነፉን ለመግለፅ በትግርኛ ቋንቋ "ስዒረ" ማለቱን ተከትሎ ሽረ ተብላ መጠራት እንደጀመረች በአፈታሪክ የሚነገር ሲሆን ጥንታዊቷ የቅድስት ስላሴ ገዳም ከከተማዋ ስም ጋር ተቀፅላ ሆና ትጠራለች።

በጣሊያናዊ መሀንዲስ ማስተር ፕላን የተሰራላት ሽረ ታዋቂ ከሆኑ የሰፈር ስያሜዎቿ መካከል ኣጓዱ፣ ተክልዬ(24)፣ ዲቦራ፣ እንዳ ጀርመን፣ ቀይ ለከፍ፣ ድልድል፣ መድየ እና ቄራ ተጠቃሾች ናቸው።

በከተማዋ አማካኝ ስፍራ ላይ ከሀገር ባለውለታ የጦር ጀነራሎች መካከል ስሙ በጉልህ የሚነሳው የሜጀር ጀነራል ሓይሎም አርአያ ሐውልት ይገኛል።

ሽረ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች የሚገኙባት ከተማ ስትሆን ከእነዚህም መካከል ገባር ሽረ፣ ቃሌም፣ አፍሪካ፣ ሀዳስ ኢንተርናሽናል እና ደጀና ሆቴሎች ተጠቃሽ ናቸው።
ተጨማሪውን ለማንበብ👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0w94my5XJ5kGCJWbx6A7qMRqJmqQ6YbqcFB4TyeA2g9VU7ZzE1CKaWehjjjLgTxbvl
ሀላባ ቁሊቶ
#ከተሞቻችን

ሀላባ ቁሊቶ ከተማ በ1896 አካባቢ እንደተመሰረተች ይነገርላታል፡፡ ስያሜዋን ያገኘችውም "ቁሊቶ" ከምትባል ጥበበኛ ሴት እንደሆነ ይገለጻል።

በአሁኑ ወቅት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ክላስተር ከተማ እና የሀላባ ዞን ዋና መቀመጫ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡

ከባህር ጠለል 1 ሺሕ 726 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው የሀላባ ቁሊቶ ከተማ ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያላት ስትሆን በአብዛኛው ሜዳማ የመሬት አቀማመጥን የተላበሰች ናት።

ሰላማዊ እና ለመኖር ምቹ የሆነች ይህች ውብ ከተማ ከአዲስ አበባ 247 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው፡፡

ከሰፈር ስያሜዎቿም 6 ኪሎ፣ ቆዳ፣ ፍርድ ቤት፣ ዛላ፣ ብላቴ፣ ቦነሻ ተራ፣ ጤና ጣቢያ እና አረብ ሰፈር ይገኙበታል።

ከሀላባ ቁሊቶ ከተማ በ1 ነጥብ 5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘውን ፋማ ፏፏቴን ጨምሮ በዙሪያዋ የተለያዩ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች ይገኙባታል፡፡ የጎብኚዎችን ቀልብ በመግዛት የሚታወቁ የአርቶ ፍል ውሀ እና የኑረላ አህመድ መካነ መቃብር ከከተማዋ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛሉ።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0yfxUknQ5J3XFkfnUdZwmFHKVsfj5f3crwNjsBeJW253XNK6PjFiht4Xa2mUXvMS6l
ደብረ ማርቆስ
#ከተሞቻችን

በ1845 ዓ.ም በደጃዝማች ተድላ ጓሉ እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ደብረ ማርቆስ በአማራ ክልል የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ስትሆን የቀድሞ ስያሜዋ "መንቆረር" ይባል እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።

በጊዜው የሀገሩ ገዥ የነበሩት ንጉስ ተክለ ሃይማኖት የመርቆሪዎስ ቤተክርስትያን በመብረቅ መመታቱን ተከትሎ በምትኩ ባሰሩት ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስትያን ከተማዋ እንድትሰየም ካወጁ በኃላ "ደብረ ማርቆስ" መባል እንደጀመረች ይነገራል።

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን አቅጣጫ በ300 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ደብረ ማርቆስ ከባህር ጠለል በላይ በ2 ሺሕ 446 ሜትር አማካኝ ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን ደጋማ የአየር ፀባይ አላት።

ወደ ሪጂኦ ፖሊታን ከተማነት ያደገችው ደብረ ማርቆስ ከታዋቂ የሰፈር ስያሜዎቿ መካከል ዲናሬ፣ አራት ብረት፣ 15ኛ ሻለቃ፣ ሆስፒታል፣ ስንዴ ጎም፣ ውትርን፣ ኪዳነ ምህረት፣ አብማ ማሪያም፣ ሰንተራ፣ ፒኮክ፣ ውሰታ፣ ድብዛ እና አምራቾች ተጠቃሽ ናቸው።

በደብረ ማርቆስ የደራሲ ሀዲስ አለማየሁ መታሰቢያ ሀውልት እና የንጉስ ተክለ ሃይማኖት ቤተ መንግስት የሚገኝ ሲሆን የመግቢያው በርም በልዩ ኪነ ህንፃ ጥበብ የተሰራና የከተማዋ መገለጫ የሆነ ልዩ ምልክት ነው።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0qsWAiFHhcaT2rdJtedY3EBosucZmczbuyF6zPhJz93hWEk6JvUGS1AoYLQXDAZkSl
ጎሬ
#ከተሞቻችን

ጎሬ በኦሮሚያ ክልል በኢሉአባቦራ ዞን የአለ ወረዳ ዋና ከተማ ናት፡፡ የጎሬ ከተማ ከሚያዝያ 1928 ዓ.ም እስከ ሕዳር 1929 ዓ.ም ድረስ 7 ወራት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና እንዳገለገለች ይገለጻል፡፡

ከተማዋ በ1874 ዓ.ም አካባቢ በራስ ቢትወደድ ተሰማ እንደተቆረቆረች ይነገርላታል፡፡

ከአዲስ አበባ 607 ኪ.ሜ የምትርቀው የጎሬ ከተማ 2 ሺሕ 85 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን ወይና ደጋ የአየር ፀባይ አላት፡፡ ዙሪያዋን በከበባት ውብ የተፈጥሮ ፀጋዎችም ትታወቃለች፡፡

አርመን፣ ግሪክ፣ እንግሊዝ፣ ሱዳን እና አረቦች ይኖሩባት የነበረችው ጎሬ በሀገራችን ቀደምት የአየር ማረፊያ የተገነባላት እንዲሁም የድንጋይ ንጣፍን ጨምሮ መሰል መሰረተ ልማቶች የነበሯት ናት። በወቅቱ በነበረው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ምክንያትም "የምዕራብ በር" የሚል ስያሜን አግኝታለች።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid02ZMBr3jM6J6EGhbjDavUCJqZzjGoPjaH5gdo1Jbm6aCjV2A8Grqh4ZtTPvQdGKT57l
አላማጣ
#ከተሞቻችን

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የጣሊያን ወረራን ተከትሎ የተመሰረተችው አላማጣ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የምትገኝ ከተማ ስትሆን ቀደምት ስያሜዋ "ጀሀን ኢራ" ይባል እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

"አላማጣ" ለሚለው የከተማዋ ስያሜ ሁለት መላምቶች ይቀርባሉ። አንደኛው "አላምጠህ ብላ" የሚል ከሁለት ወታደሮች ንግግር ከተወሰደ ሐረገ የመጣ ነው የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከረጅም ጊዜ በኃላ ዝናብ ያዩ አባት መገረማቸውን ሲገልፁ "አላህ መጣ" ማለታቸውን ተከትሎ እንደሆነ ይነገራል።

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን አቅጣጫ 595 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከራያ ቆቦ ቀጥላ የምትገኘው የአላማጣ ከተማ ከባህር ጠለል በላይ 1ሺሕ 564 ሜትር አማካኝ ከፍታ ሲኖራት ቆላማ የአየር ንብረት እና ሜዳማ መልከዓ ምድራዊ ተፈጥሮን ተላብሳለች።

አላማጣ ለንግድ እና ለመኖሪያ ምቹ ከመሆኗ የተነሳ ከከተማዋ አጎራባች ከሆኑ አካባቢዎች ማለትም ከኮረም፣ ከመኾኒ፣ ከራያ ቆቦ እና ሌሎችም ጋር ጠንካራ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አላት።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid027d4792oNNvwCgg1ZCeSoYe8teb74pAfuUhLkP5bxAxWzKxThbnGr2bXmmWE7Pkmal
ዳንግላ

#ከተሞቻችን

የዳንግላ ከተማ በአማራ ክልል በአዊ ብሄረሰብ ዞን የምትገኝ ከተማ ስትሆን ከ240 ዓመት በፊት እንደተቆረቆረች ይነገራል፡፡

በአፈ ታሪክ ከተማዋ ስያሜዋን ያገኘችው "ዳንግ" የተባለ የጠፋ ወንድማቸውን ፍለጋ ወደስፍራው ያቀኑ ሰዎች በሀገሬው ቋንቋ "ዳንግ እላ" ወይም ዳንግ የለም? ብለው መጠየቃቸውን ተከትሎ እንደሆነ ይገለጻል።

ዳንግላ ከመዲናችን አዲስ አበባ 478 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንዲሁም ከባህር ዳር 78 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 190 ሜትር ከፍታ ላይ ያለችው ዳንግላ . . . .

ሙሉውን ከማስፈንጠሪያው ያንብቡ
👇🏾👇🏾👇🏾👇🏾👇🏾👇🏾

https://tinyurl.com/6973e28x
ወራቤ
#ከተሞቻችን

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስምጥ ሸለቆ ከተሞች ውስጥ አንዷ የሆነችው ወራቤ የስልጤ ዞን ዋና ከተማ ስትሆን ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 172 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።

ከባሕር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 100 ሜትር ከፍታ እንዲሁም ወይናደጋ የአየር ፀባይ ያላት ወራቤ በ11 የቀበሌ መስተዳደር የተዋቀረችና 15 ሺሕ ሄክታር የቆዳ ስፋት ያላት ከተማ ናት።

በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ከነባሮቹ ሪያድ ሆቴል እና መኝታ እስከ ፋና ሆቴል፣ መሀሪ ሆቴል፣ ፖርክ ሆቴል፣ ሀያት ሆቴል እስከ አዳዲሶቹ አቶት ኢንተርናሽናል፣ ሀርመይን ኢንተርናሽናል ሆቴል እና ሌሎችም በውቢቷ ወራቤ ይገኛሉ።

ወራቤ በከተማዋ እና ዙሪያዋ በምታስተዳድራቸው ቀበሌዎች በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሏት ሲሆን ከነዚህም መካከል ዘፎ ፏፏቴ፣ ጉድሮ ደን፣ አልከሶ መስጅድ፣ አጌደሌ የተፈጥሮ ድልድይ፣ ገንቦ ዋሻ፣ ያኒ ፏፏቴ፣ ቡናር ሸለቆ እና ሌሎችም ይገኙበታል።

በከተማዋ የወራቤ ዩኒቨርሲቲ እና ወራቤ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ወራቤ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ፣ ሀይር ሀንዚ፣ ዘሞ ባቴ ሁለተኛ ደረጃ፣ አሊፍ፣ አርዲ አፀደ ህፃናት ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ።

ከተማዋ የተለያዩ ፋብሪካዎች፣ የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል እና የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መገኛ ነች።

በወራቤ ከተማ የስልጤ ባህላዊ ምግቦች የሚዘጋጁ ሲሆን ከነዚህም መካከል አተካኖ፣ ሱልሶ፣ ጎመን ክትፎ፣ አይብ በጎመን ተጠቃሽ ሲሆኑ ሻሜታ ከባህላዊ መጠጥ መካከል አንዱ ነው።

በዚህች ውብ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁ እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትዝታችሁን አጋሩን።
መልካም ሳምንት!

በአዲስዓለም ግደይ
አሰላ

#ከተሞቻችን

አሰላ በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምስራቅ የሀገራችን ክፍል የምትገኝ ስትሆን የአርሲ ዞን ዋና መቀመጫ ናት፡፡ በ1930 ዓ.ም አካባቢ እንደተመሰረተች የሚነገርላት አሰላ ከአዲስ አበባ 175 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

ከተማዋ ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 430 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ እና ደጋማ የአየር ፀባይን የተላበሰች ናት።

"አሰላ" የሚለው ቃል ከአርሲ ኦሮሞ ወገን ከሆነው የጎሳ . . . .

ዝርዝሩን ከማስፈንጠሪያው ያንብቡ
👇🏽👇🏽👇🏽

https://shorturl.at/Q0a1C
ቻግኒ
#ከተሞቻችን

ቻግኒ ከተማ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን ውስጥ ትገኛለች፡፡ ከተማዋ በ1842 ዓ.ም እንደተቆረቆረች ይነገራል፡፡ ቻግኒ የሚለው የከተማዋ ስያሜ የአገውኛ ቋንቋ ሲሆን "ቻ" ማለት ነገ የሚል ትርጉም ሲኖረው፣ "ኒ" ማለት ደግሞ ቤት ማለት ነው፡፡ በዚህም "የነገ ቤት" የሚል የአማርኛ ፍቺ አለው።

ከባህር ጠለል በላይ 1 ሺሕ 538 ሜትር ከፍታ ላይ የከተመችው ቻግኒ ከተማ ቆላማ የአየር ንብረት አላት፡፡ ከመዲናችን አዲስ አበባ 495 ኪ.ሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ቻግኒ ለኑሮ የምትመች ከተማ ናት፡፡

ከተማዋ በአምስት የከተማ እና የገጠር ቀበሌዎች የተዋቀረች ስትሆን ልዩ ልዩ የሰፈር ስያሜዎች አሏት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ቴክኒክ፣ ጂጂ፣ መድሀኒያለም፣ ቦሌ፣ አባሙሳ፣ ሽሮ ሜዳ የሚባሉ የሰፈር ስሞች ይጠቀሳሉ።

በቻግኒ ሕዳሴ ቻግኒ 2ኛ ደረጃ፣ መሰረት 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ፣ ቻግኒ 2ኛ ደረጃ፣ ሂባ አካዳሚ፣ ቻግኒ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ እና ሌሎች የትምህርት ተቋማት ይገኛሉ፡፡

ከቻግኒ ከተማ በደቡብ አቅጣጫ 1 ኪ.ሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው "ዶንዶር ፏፏቴ" ልዩ የከተማዋ ተፈጥሯዊ መስህብ ሥፍራ ነው።

ከ35 ሜትር ከፍታ ላይ ቁልቁል እየተወነጨፈ ከሚወርደው ፏፏቴ የሚወጣው የውሃው ጭስ ለቻግኒና ለአካባቢዋ ድንቅ የተፈጥሮ ውበትን አላብሶታል፡፡ በፏፏቴው ዙሪያም እዕዋፋትን ጨምሮ የተለያዩ የዱር እንስሳት ይገኛሉ፡፡

ቻግኒ የሀገር ባለውለታ የሆኑ ታላላቅ ሰዎችን፣ ሙዚቀኞችንና ጋዜጠኞችን ያፈራች ከተማ ነች።

በዚህች ውብ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁ እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትዝታችሁን አጋሩን።
       መልካም ሳምንት!

በአዲስዓለም ግደይ
ደብረ ታቦር
#ከተሞቻችን

በ1327 ዓ.ም በአፄ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግስት እንደተመሰረተች የሚነገርላት ደብረ ታቦር በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን የምትገኝ ከተማ ስትሆን "ጁራ" በሚል የቀድሞ ስያሜዋ ትታወቃለች።

የቀድሞ በጌ ምድር የአስተዳደር መቀመጫ እና በሁለት ነገስታት የኢትዮጰያ ዋና ከተማ ሆና ያገለገለች ታሪካዊ ከተማ ናት።

ስያሜዋን በተመለከተ ከተማው አሁን ያረፈበት ስፍራ እየሩሳሌም ከሚገኘው የታቦር ተራራ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ጋር መመሳሰሉን ተከትሎ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን "ደብረ" የሚለው ቃል ተራራን ሲወክል "ታቦር" ደግሞ ብርሃን የሚል ትርጓሜ አለው።

ደብረ ታቦር ከመዲናችን አዲስ አበባ 667 ኪ.ሜ የምትርቅ ሲሆን፣ ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 706 ሜትር ከፍታ እና ደጋማ የአየር ፀባይ ያላት ከተማ ናት።

ቆጨራ፣ መነሀሪያ፣ ፔርሙዳ፣ ሰኞ ገበያ፣ ወይብላ፣ ጎንደር በር፣ ቴክኒክ፣ ውሀ ልማት፣ ጀግኖች አንባ እና ሌሎችም በደብረ ታቦር ከተማ ውስጥ የሚገኙ ታዋቂ የሰፈር ስሞች ናቸው።

በከተማዋ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ደብረ ታቦር ሁለተኛ ደረጃ፣ ፈቀደ እዝጊ ኮሌጅ፣ ዳልሻ ቤዛዊት አለም ትምህርት ቤት፣ ጋፋት አንደኛ ደረጃ፣ ደብረታቦር ፖሊ ቴክኒክ እንዲሁም ሌሎች ይጠቀሳሉ።

ደብረ ታቦር የሀገራችን ዘመናዊ ኢንዱስትሪ አብዮት መሠረት የተጣለባት ከተማ ናት። ለዚህም ታሪካዊው የጋፋት ኢንጂነሪንግ ተጠቃሽ ሲሆን ይህም የሴባስቶፖል መድፍ የተሰራበት ስፍራ ነው…👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid02HJXJ9mKMkMPCAKUi5RAux7KrxAeV3k2YzwSD514viHiDBEMnTAAzZGQrNXkGirnkl
ወልቂጤ
#ከተሞቻችን

ከተመሠረተች ከ150 ዓመታት በላይ ያስቆጠረችው ወልቂጤ ከተማ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የምትገኝ ከተማ ስትሆን ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምዕራብ 155 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንዲሁም ከባህር ጠለል በላይ በ1 ሺሕ 910 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች፡፡

ወይናደጋ የአየር ንብረት ያላት ወልቂጤ ሜዳማ የመሬት አቀማመጥ ያላት ከተማም ናት።

የከተማዋ ጠቅላላ የቆዳ ስፋት 7 ሺሕ 260 ሄክታር ሲሆን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች፣ ከአራት በላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎችም የትምህርት ተቋማት በውስጧ ይገኛሉ።

የንግድ እንቅስቃሴ በሰፊው የሚካሄድባት የወልቂጤ ከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ እና ዘመናዊ ሆቴሎችም አሏት። ከእነዚህም መካከል ስራኖ፣ የጆካ፣ ኢንቲሳር፣ ባሮክ፣ ረድኤት እና ሌሎችም በጥቂቱ ተጠቃሽ ናቸው።

የህብረ ብሄራዊነት እና የአብሮነት ተምሳሌት የሆነችው ወልቂጤ ከተማ ሁሉም ነዋሪዎቿ ተዋደውና ተቻችለው የሚኖሩባት ድንቅ ከተማ ናት፡፡ ይህ ውብ የሆነችው ከተማ በስራ ወዳድነታቸውና እና በእንግዳ ተቀባይነት ባህላቸው የታወቁ ህዝቦች መገኛ ናት።

በዚህች ውብ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁ እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትዝታችሁን አጋሩን።
መልካም ሳምንት!

በአዲስዓለም ግደይ