TIKVAH-ETHIOPIA
1.43M subscribers
55.6K photos
1.39K videos
200 files
3.74K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#CentralEthiopia

ከሰሞኑን ለጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ (ጎጎት) በዞኑ እየደረሰ ነው ያለውን የመብት ጥሰት በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

ፓርቲው " የመብት ጥሰቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል " ብሏል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያም ይህን መግለጫ መነሻ በማድረግ በመንግሥት በኩል ምላሽ ይኖር እንደሆን ጠይቆ ምላሽ አግኝቷል።

ፓርቲው ምን አለ ?

- በጉራጌ ዞኖች እየተፈፀመ ያለው የመብት ጥሰት ተባብሶ ቀጥሏል።
- በምስራቅ መስቃን ወረዳ የታሰሩ ሰዎች ለወራት ፍትህ ሳያገኙ እየተጉላሉ ይገኛሉ።
- በወልቂጤ ከተማ የታሰሩ በርካታ ሰዎች ችሎት ቀርበው ፍትህ የማግኘት መሰረታዊ መብታቸው ተጥሶ ይገኛል።
- የታሰሩ ሰዎች ምቹ ባልሆኑ ቦታዎች ታጉረው ፍትህ የማግኘት መብታቸው ተነፍገዋል።
- በወልቂጤ ከተማ እና አካባቢው ግለሰቦች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በጨለማ ቤታቸው ተሰብሮ ብርበራ እና እስር ይፈፀምባቸዋል። የፓርቲአችን ከፍተኛ አመራሮች እና አባላትም የእስር እና ብርበራው ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ።
- ሰዎች በሚታሰሩበት ወቅት ከፍተኛ ድብደባ እየተፈፀመባቸው እንደሆነ ከታሳሪዎች ማረጋገጥ ችለናል።
- አዲሱ ክልል ከተመሰረተ ጀምሮ የጉራጌ አካባቢዎች በኢንሴኖ፣ በቆሴ፣ በጢያ እና በወልቂጤ አካባቢዎች የበርካታ ንፁኃን ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል።
- ላለፉት 2 ወራት መንግስታዊ እና ህዝባዊ አገልግሎቶች በስርአቱ እየተሰጡ አይደለም። ትምህርት ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በአብዛኛው መደበኛ ስራቸውን በአግባቡ መስጠት አልቻሉም።
- የህዝቡ በሰላም ወጥቶ የመንቀሳቀስ መብት ተገድቧል።
- አካባቢው አሁንም በወታደራዊ ኮማንድ ፖስት ስር ተቀፍድዶ ምንም አይነት የመብት ጥያቄ ማንሳት የማይቻልበት እስር ቤት ሆኗል።
- በአሁን ሰዓት ከ25 በላይ ወጣቶች በወልቂጤ ከተማ ከ17 በላይ ወጣቶች በቡታጀራ እና በኢንሴኖ ከተማ ያለ ፍትህ እስር ቤት ታጉረው ይገኛሉ።

ፓርቲው መንግሥት የመብት ጥያቄ የሚያቀነቅኑ፣ ህዝባዊ ውግንና ያላቸው ብሩህ ወጣቶችን እያሳደደ በአንፃሩ በገንዘብ እና በስልጣን የተገዙ ወጣቶችን ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ነው ሲል ባወጣው መግለጫ ከሷል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ መግለጫውን ተመልክቶ በዚህ ጉዳይ መንግሥት የሚለውን ለመስማት ጥረት አድርጓል።

በጉዳዩ ላይ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቃላቸውን የሰጡት የዞኑ ኮማንድ ፖስት ኃላፊ ኮሚሽነር ቦጋለ ካሊሬ ፤ እንዲህ ያለዉ ሀሳብ የዞኑን ብሎም የክልሉንና የሀገር ሰላም የማይፈልጉ አካላት ሀሳብ መሆኑን በመግለጽ አሁን ላይ የጸጥታ ኃይሉ ትኩረት ማህበረሰቡን ማወያየትና ሰላም ማስፈን መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ ፤ በህግ ጥላ ስር የሚገኙ አካላት ጉዳያቸዉ በፍርድቤት እየታዬና አላግባብ የተያዙ ሰዎችም እየተጣሩ መሆኑን በማንሳት #በዘረፋና በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረዉ የተያዙትም ክስ እንደተመሰረተባቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አሁን ላይ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተለያዩ ዉይይቶች እየተደረጉና ዞኑን ወደሰላምና የተለመደ ሰላማዊ ህይዎቱ እየተመለሰ መሆኑን አመላክተዋል።

@tikvahethiopia
#CentralEthiopia

ትላንትና እሁድ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣  በምሥራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ6 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

አደጋው ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ ይጓዝ የነበረ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪ 7 ሰዎችን ከጫነ " ባጃጅ " ጋር በመጋጨቱ ነው የደረሰው።

የ5ቱ ተጓዦች ሕይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ፤ በሁለቱ ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶ ነበር። ከባድ ጉዳት አጋጥሟቸው ወደ ሆስፒታል ከተላኩት መካከል አንደኛው ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ህይወቱ አልፏል።

@tikvahethiopia
#CentralEthiopia

የ11 ዓመት እድሜ ያላትን የገዛ ልጁን የደፈረው አባት 16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ተፈርዶበታል።

ድርጊቱ የተፈጸመው በማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል፣ በጉራጌ ዞን፣ ገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ነው።

ተከሳሽ ሙሂዲን ወራቄ ይባላል።

የግል ተበዳይ (ልጁ) ያለ እድሜዋ በአዲስ አበባ ከተማ በሰራተኝነት ተቀጥራ ትሰራ ነበር።

በኃላም ፤ በቤተሰቡ መበተን ምክንያት በብቸኝነት የሚኖረዉን አባቷ ለመደገፍ ወደ ከዊሶ ወደ ተባለው መንደር ትመለሳለች።

ተከሳሽ ጋብቻ እየመሰረተ ሲፈታ ከሶስት ጊዜ በላይ ትዳር መስርቶ ፍቺ የፈፀመ ሲሆን የደረሱ ልጆቹንም ድሮ የልጅ ልጅ ለማየት በቅቷልም ነዉ የተባለዉ።

" አባቴን ትቼ  የትም አልሄድም " ስትል ከወላጅ አባቷ መኖር የጀመረችዉ ታዳጊ በተደጋጋሚ በገዛ አባቷ ተደፍራለች።

አንድ ቀን በወላጅ አባቷ ጭካኔና የነዉረኝነት ባህሪ የደረሰባትን በደል ሁሉ ለወላጅ እናቷ ትናገራለች።

አንጀቷ የበገነው እናትም ወደ ወረዳዉ ሴቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት አቅንታ ሰዉየዉ ለፍርድ ይቀርብ ዘንድ እገዛ እንዲደረግልኝ ስትል አቤቱታ በማሰማቷ ክስ ሊመሰረት ችሏል።

የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ፍርድ ቤት ተከሳሽ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ጥፋተኛ በማለት በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡

መረጃው ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ነው የተገኘው።

Via @tikvahethmagazine
#CentralEthiopia

" እባካችሁ የሰራንበትን ፤ የላባችንን ክፍያ ስጡን " እያሉ ቀን በቀን የሚጮሁ ዜጎች ባሉባት ሀገር እዚህ ጋር ደግሞ ጭራሽ የመንግሥት ሰራተኛ ላልሆኑ ሰዎች በመቶ ሺዎች ብር ወጥቶ ተከፍሏል።

የመንግስት ሰራተኛ ላልሆኑ 19 ሰዎች  ደመወዝ ሲከፍሉ ተደርሶባቸው በሙስና ወንጀል የተከሰሱ 3 ግለሰቦች በጽኑ እስራት እና በገንዘብ መቀጮ መቀጣታቸው ተሰምቷል።

በተፈፀመው ወንጀል ተሳታፊ በመሆን ሳይቀጠሩ ደመወዝ ይከፈላቸው የነበሩ ተከሳሾችም በ3 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።

የሙስና ወንጀሉ የተፈጸመው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀድያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ ነው።

የሀድያ ዞን ዐቃቤ ህግ ህዳር 30/2016 ዓ.ም ለሀድያ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ፅፎ ባቀረበው ክስ ምን ይላል ?

1ኛ. ተከሳሽ አቶ ናትናኤል አምቢኮ በሻሾጎ ወረዳ የፋይናንስ ጽ/ቤት የክፍያ ኦፊሰር፤
2ኛ. ተከሳሽ ወ/ሮ አዳነች ጡምደሎ በሻሾጎ ወረዳ የፋይናንስ ጽ/ቤት የክፍያ ቡድን መሪ፤
3ኛ. ተከሳሽ አቶ ታምራት ኒኔ የሻሾጎ ወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ (በሌለበት የታየ)፤
4ኛ. ተከሳሽ አቶ ሲሳይ ቢያድጌ በወረዳው በመንግስት ሰራተኛነት ሳይቀጠር ደመወዝ ሲከፈለው የነበረ፤
5ኛ. አቶ ሰላሙ አበጀ በወረዳው በመንግስት ሰራተኛነት ሳይቀጠር ደመወዝ ሲከፈለው የነበረ ሲሆን፤

በሻሾጎ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ላልተቀጠሩ  መምህራን ሰራተኞች በቁጥር 19 ሰዎች ከ2015 ዓ/ም ጀምሮ እስከ መስከረም 2016 ዓ/ም ድረስ ከ5 ወር እስከ 11 ወራት ደወመዝ እንዲከፈላቸው አድርገዋል።

በዚህም በድምሩ 7 መቶ 30 ሺህ 2 መቶ 39 ብር በመንግስት እና ሕዝብ  ሀብት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ፤ ያላግባብ ስልጣንን በመገልገል ወንጀል ፈፅመዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

የሀድያ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ጉዳዩን ተከታትሏል።

ተከሳሾች የቀረቧቸው የመከላከያ ምስክሮች የዐቃቤ ህግን የሰውና የሰነድ ማስረጃ አስተባብለው ባለመገኘታቸው ፍ/ቤቱ በሙሉ ድምፅ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቶባቸዋል።

በዚሁም መሰረት ፦ 

1ኛ. ተከሳሽ አቶ ናትናኤል አምቢኮ በሻሾጎ ወረዳ የፋይናንስ ጽ/ቤት ፔሮል አዘጋጅ የክፍያ ኦፊሰር በ7 ዓመት ከ8 ወር ፅኑ እስራትና በ5 ሺህ ብር እንዲቀጣ።

2ኛ. ተከሳሽ ወ/ሮ አዳነች ጡምደሎ ኩሪሶ  በሻሾጎ ወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤት የክፍያ ሂሳብ ቡድን መሪ በ7 ዓመት ከ8 ወር ፅኑ እስራትና በ 5 ሺህ ብር እንድትቀጣ።

3ኛ. ተከሳሽ አቶ ታምራት ኒኔ የሻሾጎ ወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ የነበረ እጁን ለህግ አካላት ያልሰጠና በፖሊስ ታድኖ ሲያዝ የእስራት ጊዜውን የሚያጠናቅቅ ሆኖ (በሌለበት የተወሰነ) በ11 ዓመት ፅኑ እስራትና በ 10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ።

4ኛ. ተከሳሽ አቶ ሲሳይ ቢያድጌ በትምህርት ጽ/ቤት ሳይቀጠርና መምህር ሳይሆን ለ9 ወራት ደመወዝ ሲከፈለው የነበረ በ3 ዓመት ፅኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ።

5ኛ. ተከሳሽ አቶ ሰላሙ አበጀ ተባበል በወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ሳይቀጠርና መምህር ሳይሆን ለ 9 ወራት ደመወዝ ሲከፈለው የነበረ በ3 ዓመት ፅኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።

መረጃ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ነው የተገኘው።

#CentralEthiopia #Ethiopia

@tikvahethiopia