TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.3K photos
1.42K videos
206 files
3.94K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
" በየሶሻል ሚዲያ የሚፈጸም ስም ማጥፋት በህግ እንጅ በሶሻል ሚዲያ መልስ መስጠት አያስፈልግም " - የሰላምና ጸጥታ ቢሮ

የሀዋሳ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ፥ ያለ ማስረጃ በየተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የከተማዋን ስም እያጠፉ ያሉ አካላትን ጉዳይ በህግ እየተከታተልኩ ነው አለ።

ይህን ያለው ከሰሞኑን ' ቲክቶክ ' እና ' ዩትዩብ ' ላይ የከተማዋን ሁኔታ የሚገልጽ የወጣቶች ንግግር ከተሰራጨ በኃላ ነው።

ወጣቶቹ ከተማይቱ ለደህንነት የምታሰጋ ፣ እግታም የሚፈጸምባት እንደሆነ በመግለጽ ዜጎች ወደ ሀዋሳ እንዳይሄዱ ጥሪ ሲያቀርቡ ይደመጣል።

ይህንን ተከትሎ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቃሉን የሰጠው የሀዋሳ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ፤ " ጉዳዩን በህግ አግባብ  እየተከታተልነዉ ነዉ " ብሏል።

" በየሶሻል ሚዲያ የሚፈጸም ስም ማጥፋት በህግ እንጅ በሶሻል ሚዲያ መልስ መስጠት አያስፈልግም " ሲል አመልክቷል።

" በእኛ በኩል እንዲህ ያለን የስም ማጥፋት አይተን ባናልፈውም ነዋሪው እና ሀዋሳን የጎበኙ እንግዶች ራሳቸዉ ምን አይነት አስተማማኝ ደህንነት እንዳለ ምላሽ ቢሰጡበት የተሻለ ነዉ " ሲል አክሏል።

ቢሮው ፥ " አሁን ላይ በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞች ሀያ አራት ሰአት ሰዉ በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችልባት ከተማ ሀዋሳ መሆኗን ላረጋግጥላችሁ እዉዳለሁ " ብሏል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታችንን መስጠት እንፈልጋለን ያሉ ወጣቶች ደግሞ ተጎዳው የሚል ማንኛውም ዜጋ በማስረጃ ለፍትህ አካል ማመልከት ይቻላል ብለዋል።

" እኛ እስከምናውቀው ድረስ ከተማይቱ የምታስፈራ ከተማ አይደለችንም ፤ ሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ከተሞች ደህንነት ያለባት ናት ፤ በዚህ ደረጃ ስም ማጥፋት እና መግለጽ ፍጹም ያልተገባ ነው " ሲሉ ተናግረዋል።

#TikvahEthiopiaHawassa

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#ደመወዝ #ደቡብኢትዮጵያ ° " ...ድርጊቱ የደመወዝ ቅሸባ ነው ሊባል የሚችለው ፤ እንዲህ አይነት የደመወዝ አከፋፈል ሰምተንም አናውቅ " - ሰራተኞች ° " ከእኛ #የሚወርደው የበጀት ሀብት እኮ የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ ለመክፈል የሚያስችል ነው " - የክልል ፋይናንስ ቢሮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የመንግስት ሰራተኞች " የደመወዝ ይከፈለን " ጥያቄ በብርቱ ከተነሳባቸው አካባቢዎች አንዱና ዋነኛው…
#SouthEthiopia

° " የግንቦት ወር ደመወዝ እስከ ዛሬ አልወሰዱም " - የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር

° " ተቸግረን ያዘገየነውን የመምህራን ደመወዝ ከሰኞ ጀምረን ክፍያ እንፈጽማለን " - የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያሉ መምህራን ከደመውዝ ጋር በተያያዘ ያቀርቡ የነበሩትን ተደጋጋሚ ጥያቄ ስናቀብላችሁ እንደነበር ይታወሳል።

በተደጋጋሚ ይነሱ የነበሩ የደመውዝ ጥያቄዎች አሁን ላይ በተወሰነ መልኩ ምላሽ ቢያገኙም አሁንም ጥያቄያቸው ያለተመለሰላቸው የመንግስት ሰራተኞች በተለይ በወላይታ ዞን ያሉ መምህራን ችግር ላይ መሆናቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

በተጨማሪ የደቡብ ኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝደንት አቶ አማኑኤል ጳዉሎስ ፥ " በወላይታ ዞን ሆብቻ ወረዳ የግንቦት ወር ደመወዝ እስከ ዛሬ አልወሰዱም " ብለዋል።

ሌሎች 2 ወረዳዎች ማለትም ቦሎሶ ሶሬ እና ካዎ ኮይሻ 50% ብቻ መውሰዳቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

" የመምህራን ችግር መባባሱን ተከትሎ ከዞኑ ባለስልጣናት ጋር ልንነጋገር ቀጠሮ ይዘናል " ያሉት አቶ አማኑኤል " ችግሩ በቶሎ መቀረፍ አለበት " ሲሉ አሳስበዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጎበዜ ጎዳና ፤ ችግሩ የተፈጠረዉ ክልሉ ለማዳበሪያ ውዝፍ እዳ የሰጠዉ ትኩረት የካሽ እጥረት በመፍጠሩ መሆኑን ገልጸዉ ይህ ችግር አሁን ላይ መፈታቱን ገልጸዋል።

" የዘገየውን የመምህራን ክፍያ በጣም ባጠረ ሁኔታ ለመክፈል ገንዘብ ጠይቀን ተፈቅዶልናል " ያሉት ኃላፊው " ከተቻለ ሰኞ ጀምረን መክፈል እንጀምራለን " ብለዋል።

መምህራንም ከችግራቸዉ ይወጣሉ ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

#TikvahEthiopiaHawassa

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
" ፍርዱ ለሚዲያ 16 ዓመት ከተባለ በኃላ ወደ 10 ዓመት ዝቅ እንዳለ ሰምቻለሁ " - ጸጋ በላቸው " ጉዳዩ ለቢሮዉም ሆነ ለኔ አዲስ ነው " - ወ/ሮ ወይንሸት ብርሀኑ በሀዋሳ ከተማ የዳሽን ባንክ ሰራተኛ ከሆነችዉ ጸጋ በላቸዉ ጋር በተያያዘ በጠለፋና አስገድዶ መድፈር ወንጀል ተከሶ  የነበረው ኮንስታብል የኃላመብራት ወ/ማርያም " ለብዙዎች አስተማሪ ይሆናል " በተባለ መልኩ የ16 አመት ጽኑ እስራት…
#Update

" ውሳኔዉ መስተካከሉ አስደስቶኛል ጥንካሬም ሆኖኛል " - ጸጋ በላቸዉ

" የይግባኝ ዉሳኔዉን ተከትሎ ፍርዱ ወደ 10  መቀነሱ ልክ አልነበረም " - የክልሉ ዋና ዐቃቤ ህግ


• ግለሰቡ በ14 ዓመት ከ6 ወር እስራት እንዲቀጣ ተፈርዷል።

በሀዋሳ ፥ የዳሽን ባንክ ሰራተኛዋን ጸጋ በላቸዉ ላይ የጠለፋ ወንጀል የፈጸመዉ የጸጥታ አባሉ ምክትል አስር አለቃ የኋላመብራቱ  ወልደማርያም የጠየቀው ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቶ ፍርዱ ከ16 አመት ወደ 10 መውረዱ ተሰምቶ ነበር።

በወቅቱ በዉሳኔዉ ያዘነችዉ ተበዳይ ጸጋ በላቸዉ ቅሬታ ውስጥ መግባቷን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ያሳለፈዉ ውሳኔ አግባብ አለመሆኑንና ቅጣቱ በጣም እንዳሳመማት ገልጻ  ቅሬታ ማቅረቧን መዘገባችን ይታወሳል።

ይህን የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሳኔ በመቃወም ይግባኝ የጠየቀዉ የክልሉ ዐቃቤ ህግ ቅጣቱ መውረዱ ከህግ አንጻር አግባብ አይደለም ብሎ በመከራከር የቅጣት ማቅለያውን ውድቅ በማድረግ ቅጣቱ ተስተካክሎ የ14 አመት ከ6 ወር ውሳኔ ተሰጥቷል።

በዚህ የፍርድ ሂደት አስተያየቷን በመልእክት ያጋራችን ወይዘሪት ጸጋ በላቸዉ በፍርዱ መስተካከል  ደስታ እንደተሰማትና ይህም  ጥንካሬ  እንደሚሰጣት ገልጻልናለች።

" እንደኔ አይነት ጉዳት የደረሰባችሁ እህቶች ሁሉ ወደህግ በመሄድ መጠየቅን አትፍሩ " የምትለው ጸጋ ፥ ከመጀመሪያውም በህግ ላይ እምነት እንደነበራት ተናግራለች።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አስተያየታቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡት የሲዳማ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ኃላፊው አቶ ማቶ ማሩ ፥ " ምንም እንኳን ሚዲያዎች ለዚህ ኬዝ የሰጡት ትኩረት ጉዳዩን ታዋቂ ቢያደርገውም ክልሉ ለሴት ልጅ ጥቃት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ በርካታ ጠንካራ ውሳኔዎች ተላልፈዋል " ሲሉ ገልጸዋል።

" ይህ የጸጋ በላቸዉ ኬዝ ማህበረሰቡን ያስተምራል ለተጎጅዋም ፍትህ ይሰጣል ብለን ስንከታተለዉ የነበረ ጉዳይ ከመሆኑ በላይ ድርጊቱን የፈጸመዉ ግለሰብ ማህበረሰብ ይጠብቃል ተብሎ ኃላፊነት የተሰጠዉ በመሆኑ ትኩረት ሰጥተነው ነበር " ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ ማቶ ከወራት በፊት የተሰጠውን የይግባኝ ውሳኔ ህጋዊ ድጋፍ የለውም ብሎ በመቃወም የክልሉ ዐቃቤ ህግ ፍርዱ እንዲስተካከል የጣረው ለዚህ ነበር  ብለዋል።

ቅጣቱ ከ10 ወደ 14 አመት መስተካከሉን ገልጸው " እንደክልል በዚህ አመት ብቻ ከ256 በላይ ሴቶችንና ህጻናትን የተመለከተ ኬዝ በትኩረት ይዘን እየሰራንበት ነው በተወሰኑት ላይም አስተማሪና  ጠንካራ ውሳኔዎች እየተሰጡ ነው " ሲሉ ገልጸዋል።

#TikvahEthiopiaHawassa

@tikvahethiopia