ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
853 subscribers
3.46K photos
103 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
††† እንኳን ለካህኑ ሰማዕት ቅዱስ አልዓዛር እና ለቅዱሳን ቤተሰቡ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አልዓዛር ካህን †††

††† ይህ ቅዱስ #የብሉይ_ኪዳን_ሰማዕታት ተብለው ከሚታወቁት ዋነኛው ነው:: የነበረበት ዘመንም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሲሆን " #ዓመተ_መቃብያን/ #ዘመነ_ካህናት" ይባላል::

በወቅቱ ሰሎሜ የምትባል ደግ ሴት አግብቶ ይኖር የነበረው ቅዱስ አልዓዛር በኢየሩሳሌም ተወዳጅ ነበር:: ሐረገ ትውልዱ ከአሮን ወገን ነውና በክህነቱ ተግቶ ያገለግል ነበር:: በዚያ ላይ ሊቀ ካህንነትን በመመረጡ ሕዝቡን ይሠራ: ያስተምር: ያስተዳድር ነበር::

ቅዱስ አልዓዛር ከተባረከች ሚስቱ ሰሎሜ 7 ወንዶች ልጆችን አፍርቷል:: እነርሱንም በሥርዓት አሳድጐ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጐ ነበር:: በዚያው ዘመን በኢየሩሳሌም አካባቢ የሚኖሩ 3 እኩያን (ክፉ) ካህናት ነበሩ::

እነዚሁም ሕዝቡን ከማስቸገር: ፈጣሪን ከማሳዘን ቦዝነው አያውቁም ነበር:: የክፋታቸው መጨረሻ ግን የገዛ ሃገራቸውን ማጥፋት ሆነ:: ነገሩ እንዲህ ነው:- 3ቱም ተመካክረው የአልዓዛርን የሊቀ ካህንነት ቦታ ሊቀሙ ወስነው ወደ እርሱ ሔዱና እንዲህ አሉት::

"ሹመት በተርታ: ሥጋ በገበታ" ሲሆን ያምራልና እኛ በተራችን በወንበሩ ላይ እንቀመጥ::"
እርሱ ግን "ሕዝቡን ጠይቃችሁ ተሾሙ" አላቸው:: እነርሱም ሕዝቡን ጠርተው "ሹመት ይገባናል" ቢሏቸው ሕዝቡ መልሶ "አልዓዛርን የሾመው እግዚአብሔር ነውና እናንተም ከፈጣሪ ጠይቃችሁ ተሾሙ" አሏቸው::

በዚህ ጊዜ 3ቱ እኩያን ተቆጡ:: ምክንያቱም እግዚአብሔር እንደ ማይሰጣቸው ያውቃሉና:: ወዲያው ግን 3ቱም ከአካባቢው ጠፉ:: ከኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ጨካኙ የግሪክ ንጉሥ አንጥያኮስ ሔዱ::

አንጥያኮስ ማለት "ቀኝ ዐይናችሁን ገብሩልኝ" የሚል ንጉሥ ነው:: እርሱን " #ኢየሩሳሌም ባለቤት የላትምና ሒደህ ውረራት" አሉት:: "አጥሩ ጥብቅ ነው:: በምን እገባለሁ?" ቢላቸው "እኛ በመላ እናስገባሃለን" አሉት:: እርሱም 240,000 ሠራዊት አስከትቶ ወረደ::

እነርሱ ቀድመው ወደ ኢየሩሳሌም ገብተው ያስወሩ ጀመር:: "እናንተ ሹመት ብትነሱንም እኛ ግን አንጥያኮስን ያህል ንጉሥ በእሥራኤል አምላክ አሳምነን መጣን" እያሉ ይሰብኩ ገቡ:: ቅዱስ አልዓዛር "አትስሟቸው:: በዚያም ላይ አሕዛብ የተቀደሰውን ምድር መርገጥ የለባቸውም" ብሎ ነበር::

ነገር ግን አንዳንድ ችኩሎች አይጠፉምና ፈጥነው የከተማዋን በር ከፈቱት:: ሠራዊቱን ደብቆ ትንሽ ራሱን የቆመ የመሰለው አንጥያኮስ በምክንያት: በክፋትና በመላ ሁሉን ሠራዊቱን አስገባ:: የሚገርመው በጊዜው የከተማዋ ሕዝብ 12 እልፍ (120,000) ሲሆን ንጉሡ ያስገባው ሠራዊት ግን 24 እልፍ (240,000) ሆኖ ተገኘ::

ወዲያው አንጥያኮስ ሕዝቡን ሰበሰበና አልዓዛርን ለብቻው ጠርቶ ተናገረው:: "አንተ አምላክህን እንደምትወድ ሰምቻለሁ:: አንተ የበጉን መሥዋዕት በልተህ: #ለሥዕለ_ኪሩብ ሰግደህ: ሕዝቡን ግን እሪያ (አሳማ) እንዲበላና ለፀሐይ እንዲሰግድ አድርግልኝ" አለው::

ቅዱስ አልዓዛር መለሰለት:- "እግዚአብሔር የሾመኝኮ በጐ ሃይማኖትን ላስተምር እንጂ ለክፋት አይደለም:: ለሕዝቤ የክፋት አብነት ፈጽሞ አልሆንም" አለው:: ያን ጊዜ ንጉሡ በቅዱሱ ላይ ተቆጣ:: "የምልህን ካላደረግህ ብዙ ግፍ ይደርስብሃል" ቢለው ቅዱሱ መልሶ "የፈለግኸውን አድርግ" አለው::

በዚያን ጊዜ ንጉሡ የቅዱሱን ሚስትና 7 ልጆች እንዲያመጡለት አዘዘ:: ቅዱሱ እያየ ከፊቱ ላይ 7ቱንም ልጆቹን በሰይፍ አስመታቸውና 7ቱም ወደቁ:: ለአንድ አባት ይህ የመጨረሻው መራራ ፈተና ነው:: #አልዓዛር ግን ምን አንጀቱ በኀዘን ቢቃጠልም ከልጆቹ ለእግዚአብሔር አድልቷልና ቻለው ታገሠው::

በዚህ ለውጥ እንዳልመጣ ያየው ንጉሡ ሌላ ፍርድ ተናገረ:: ቅዱሱንና ሚስቱን ( #ሰሎሜን) በፈትል ጠቅልለው በሠም ነከሯቸው:: (ጧፍ እንደሚሠራበት መንገድ ማለት ነው:: )

አሁንም ግን ከአምልኮታቸው ፈቀቅ ባለማለታቸው ትልቅ ብረት ምጣድ ተጥዶ: 2ቱም ከነነፍሳቸው እንዲቃጠሉ ተደረገ:: ቀጥሎም ሕዝቡን እንዲፈጁ አዋጅ ወጣ:: በከተማዋ ከነበረው ሕዝብ 40,000 ያህሉ ተገደሉ::

40,000 ያህሉ ሲማረኩ 40,000 ያህሉን ደግሞ #ይሁዳ የሚባል አርበኛ በር ሰብሮ ይዟቸው ሸሸ:: "እንሾማለን: እንሸለማለን" ብለው ሕዝባቸውን ያስፈጁ እነዚያ ካህናትም #እግዚአብሔር ፈርዶባቸው እነርሱም ተገደሉ:: ቅዱሱ የአልዓዛር ቤተሰብ ግን የክብርን አክሊል አግኝተዋል::

††† #የእሥራኤል_አምላክ ቸሩ እግዚአብሔር እንዲህ ካለው መከራ በኪነ ጥበቡ ይሰውረን:: ከቅዱሳኑ በረከትም አይለየን::

††† ነሐሴ 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አልዓዛር ካህን (ሰማዕት)
2.ቅድስት ሰሎሜ ሰማዕት (ሚስቱ)
3."7ቱ" ቅዱሳን ሰማዕታት (ልጆቹ)
4.ቅዱስ አሞን ሰማዕት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

††† "አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ::
የቅድስናህንም #መቅደስ አረከሱ::
#ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት::
የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች መብል አደረጉ::
የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት::
ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውሃ አፈሰሱ::
የሚቀብራቸውም አጡ::" †††
(መዝ. 78:1)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††