ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
853 subscribers
3.46K photos
103 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
††† መስከረም 3 ቀን የሚከበሩ የቅዱሳን በዓላት †††

††† እንኳን ለጻድቁ አባ ሙሴ እና አባ አንበስ ኢትዮዽያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ ሙሴ ዘሲሐት †††

††† #ገዳመ_ሲሐት የሚባሉ ብዙ ቦታዎች አሉ:: ቅድሚያውን የሚይዘው ግን የግብጹ ነውና ዛሬ የዚህን ገዳም አንድ ቅዱስ እናስባለን:: ሕይወታቸውም በእጅጉ አስተማሪ ነው:: ቅዱሱ አባ ሙሴ ይባላሉ:: የ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያን ናቸው::

እኒህ ጻድቅ አንድ ነገር ከሌሎች ቅዱሳን ይለያቸዋል:: ከምግባርና ትሩፋት በቀር አንድም የእግዚአብሔር ቃል አያውቁም:: ዝም ብለው በየዋሕነት ይኖሩ ነበር እንጂ:: ተወልደው ባደጉበት በምድረ ግብጽ በቅን ሕይወት ኑረው: በወጣትነታቸው ወደ ደብረ ሲሐት ገቡ::

በዚያም በብሕትውና ዘግተው በጾምና ጸሎት ተወስነው ለ45 ዓመታት ኖሩ:: እጅግ የዋሕ ሰው ናቸውና ከጸጋ (ከብቃት) ደረሱ:: ሰው በአካባቢው አልነበረምና አብረው የሚውሉት ከግሩማን አራዊት ጋር ነበር:: አራዊቱም ጻድቁን ያጫውቷቸው: ይታዘዙላቸውም ነበር:: በፈንታው ደግሞ አባ ሙሴ በተአምራት ዝናብ ያዘንቡላቸው: ምግብም ይሰጧቸው ነበር::

አባ ሙሴ ልብስ አልነበራቸውምና በቅጠል ይሸፈኑ ነበር:: የምግባቸው ነገርማ "በመጠነ ኦፍ" ይላል . . . ትንሽ ድንቢጥ የምትበላውን ያህል ቀምሰው: ጥርኝ ውሃም ተጐንጭተው ነበር የሚኖሩት:: በሁዋላ ግን እጅግ ከመብቃታቸው የተነሳ ዐይናቸውን ሲገልጡ 'ገነት' (የአትክልት ሥፍራ) ይታያቸው ነበር:: ከዚያም ለበረከት ቆርጠው ይበሉ ነበር::

ሰይጣን እርሳቸውን ይጥል ዘንድ እጅግ ቢጥርም አልተሳካለትም:: በስተ መጨረሻ ግን የሚጥልበት መንገድ ተከሰተለት:: ምንም ባለ መማራቸው ሊፈትናቸውም ተነሳ:: አንድ ቀን ከበአታቸው በር ላይ ከአራዊት ጋር ተቀምጠው ሳለ ሰይጣን ሽማግሌ መነኩሴ መስሎ እየተንገዳገደ መጣ::

አራዊቱ ደንግጠው ሲሸሹ እርሳቸው ግን ሳያማትቡ ሮጥ ብለው ደገፉት:: ወደ በዓታቸውም አስገቡት:: ማታ ላይ ሲጨዋወቱ "ማንነትዎን ይንገሩኝ" አላቸው:: ለአባ ሙሴ ሰይጣኑ የበቃ አባት መስሏቸዋልና የ45 ዓመታት ድንግልናዊ የተባሕትዎ ሕይወታቸውን ነገሩት::

እርሱም በፈንታው ሐሰቱን ቀጠለ:: "እኔ ግፍ እየሠራሁ በዓለም እኖር የነበርኩ ሰው ነኝ:: ነገር ግን ዓለምን ትቼ ላለፉት 40 ዓመታት በበርሃ በንስሃ ኑሬአለሁ:: ያም ሆኖ አንዲት ሴት ልጅ አለችኝና 'ማን ያገባታል' ብዬ ስጨነቅ አንተ እንደምታገባት ተገለጠልኝ" አላቸው::

አባ ሙሴ ደንግጠው "እንዴት ድንግልናዬንና ሕይወቴን ትቼ አገባለሁ?" ሲሉም ጠየቁ:: ሰይጣን ግን ቃለ እግዚአብሔር እንደማያውቁ ተረድቷልና "አንተ ከአብርሃም: ከያዕቆብ: ከዳዊት ትበልጣለህ? እነሱ አግብተው የለ!" ብሎ ቢገስጻቸው አንዳንዴ አለመማር ክፉ ነውና አባ ሙሴ ሸብረክ አሉ: ተረቱ::

ከዚያም ተያይዘው ጉዞ ወደ ዓለም ሆነ:: መንገድ ላይ ግን መነኩሴ ነኝ ያለው ሰይጣን ወደቀና የሞተ መሰለ:: አባ ሙሴ በእንባ ቀብረውት ሲሔዱ ተኖ ጠፋ:: አባ ሙሴ ቀና ሲሉ ሰይጣን በምትሐት የሠራውን ያማረ ግቢና ቆንጆ ሴት አዩ:: ወደ እሷ እቀርባለሁ ሲሉ አውሎ ንፋስ ማጅራታቸውን መትቶ ጣላቸው::

አባ ሙሴ ከወደቁበት ሲነሱ ያዩት ነገር ሁሉ ሰይጣናዊ ምትሐት መሆኑን አወቁ:: ወደ በአታቸው መጥተው ከገነት ፍሬ ቢቀምሱ ጸጋ እግዚአብሔር ተለይቷቸዋልና መራራ ሆነባቸው:: እያለቀሱ ከበዓታቸው ወጡ::

መንገድ ላይ ያው ሰይጣን ነጋዴ መስሎ: "መንገድ ልምራዎት" ብሎ ምንም ከሌለበት በርሃ ላይ ጥሏቸው ተሰወረ:: የሚያደርጉት ጠፋባቸው:: ረሃቡ: ጥሙ: ከፈጣሪ ጸጋ መለየቱ አቃጠላቸው:: አሁንም አንዲት ሴት መነኩሴ ድንገት መጥታ ወደ በዓቷ አስገባቻቸው::

የማይገባውን ድርጊት እናድርግ ብላ አባበለቻቸው:: ይባስ ብላ ወደ አይሁድ እምነት እንዲገቡ አሳመነቻቸው:: ወዲያውም ወደ ሌላ በርሃ ወስዳ "አወቅኸኝ?" አለቻቸው:: "የለም" አሏት:: እዚያው ላይ ተቀይራ ጋኔን መሆኗን አሳይታቸው ተሠወረች::

#አባ_ሙሴ በዚያው ሥፍራ በአንድ ጊዜ ሁሉንም አጡ:: አለቀሱ: ተንከባለሉ:: እንባቸው እንደ ዥረት ፈሰሰ:: ልቡናቸው ሊጠፋ ደረሰ:: ወደ ፊታቸው አፈር እየረጩ: "ወየው" እያሉ ሲያለቅሱ ጌታችን መልአኩን ላከላቸው::

እንደ ቀድሞውም ፊት ለፊት ታይቶ አጽናናቸው:: "አይዞህ! ፈጣሪ እንባህንና ንስሃህን ተቀብሏል" ብሎ ወደ ስውራን ከተማ ወሰዳቸው:: በዚያም ለ7 ቀናት ቆይተው በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: #አባ_ሳሙኤልም ቀብሯቸዋል::

††† አባ አንበስ ኢትዮዽያዊ †††

††† ጻድቁ የነበሩት በ13ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን የተወለዱት ትግራይ ውስጥ ነው:: ዛሬም ድረስ የብዙ ስውራን ቤት እንደ ሆነ የሚታወቀውን #ደብረ_ሐዘሎንም እርሳቸው እንደ መሠረቱት ይነገራል:: አባ አንበስ ከገዳማዊ ትሩፋታቸው ባሻገር በአንበሶቻቸው ይታወቁ ነበር::

የትም ቦታ ሲሔዱ በአንበሳ ጀርባ ላይ ነበር:: በእርግጥ አባቶቻችን ከዚህም በላይ ብዙ ድንቆችን ማድረግ ይችላሉ:: ምክንያቱም #እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነውና:: ጻድቁ የአቡነ #ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ: #የሳሙኤል_ዘዋልድባና #የአባ_ብንያሚን ባልንጀራ ናቸው:: ዛሬ ደግሞ ዕረፍታቸው ነው::

††† #አምላከ_ቅዱሳን የወዳጆቹን ፈተና አስቦ እኛን ከመከራ ይሰውረን:: በቃል ኪዳናቸው ይጠብቀን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

††† መስከረም 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ ሙሴ ዘደብረ ሲሐት
2.አባ አንበስ ኢትዮዽያዊ
3.አበው ኤዺስ ቆዾሳት
4.አባ ዲዮናስዮስ
5.አባ ዲዮስቆሮስ ሰማዕት
6.ቅዱስ በትንከል ዲያቆን

††† ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል
7.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)

††† "በመጠን ኑሩ: ንቁም:: ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጐ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና:: በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት::" †††
(1ዼጥ. 5:8)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

ምንጭ:- ዝክረ ቅዱሳን

🕊👉 @zekidanemeheret)
††† 🌻✝️መስከረም 4 ቀን የሚከበሩ የቅዱሳን በዓላት †††🌻✝️

†††🌻✝️ እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ እና ለቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††🌻✝️

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††🌻✝️ ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ ወመስፍን🌻✝️ †††

††† ቅዱሱ የተወለደው በምድረ ግብፅ በባርነት ከነበሩ እሥራኤላውያን ሲሆን የቀደመ ስሙ #አውሴ ይባላል:: ዘመኑ #እግዚአብሔር ሕዝቡን ከ215 ዓመታት ባርነት ሊያወጣ የተቃረበበት ነውና #ሊቀ_ነቢያት_ሙሴ ከምድያም ሲመለስ ከመረጣቸው ተከታዮቹ ዋነኛው ኢያሱ ነበር:: እሥራኤል ከባርነት ሲወጡ ሙሴ 80 ዓመቱ: ኢያሱ ደግሞ 40 ዓመቱ ነበር::

ሕዝቡ አንገተ ደንዳና ነበርና ለ40 ቀን የታሠበላቸውን መንገድ 40 ዓመት እንዲሆን አደረጉት:: በዚህ ጊዜ ኢያሱ ከመምህሩ ከሙሴና ከሕዝቡ አልተለየም:: አውሴን ኢያሱ ብሎ ስም የቀየረለት ሙሴ ሲሆን ይሔውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነው::

ኢያሱ ማለት " #መድኃኒት" ማለት ነው:: ለዚሕም ምክንያቶች አሉት:-
1.ለጊዜው አማሌቃውያንን ድል ነስቶ ሕዝቡን አድኗል: ምድረ ርስትን አውርሷል::
2.ለፍጻሜው ግን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ (ጥላ) እንዲሆን ነው::

ቅዱስ ኢያሱ በበርሃው ለዘመናት እግዚአብሔርን አምልኮታል:: ሊቀ ነቢያትን ታዞታል (አገልግሎታል): እሥራኤልንም የጦር አለቃ ሆኖ ከአሕዛብ እጅ አድኗቸዋል:: በዚህም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ዘንድ ሞገስን አግኝቷል:: ቅዱስ ሙሴ #ደብረ_ናባው ላይ ባረፈ ጊዜ ሕዝቡን: ካሕናቱንና ታቦተ ጽዮንን ተረከበ:: ይህን ጊዜ ዕድሜው 80 እየሆነ ነበር::

††† እግዚአብሔርም ኢያሱን "ከአንተ ጋር ነኝ" ብሎ በሕዝቡ ላይ ነቢይና መስፍን (አስተዳዳሪ) እንዲሆን ሾመው:: ቅዱሱም ሰላዮችን ልኮ አስገምግሞ:
¤ባሕረ ዮርዳኖስን ከፍሎ:
¤ሕዝቡን አሻግሮ:
¤የኢያሪኮን ቅጥር 7 ጊዜ ዙሮ:
¤በኃይለ እግዚአብሔር አፍርሶ:
¤የኢያሪኮን ነገሥታት አጥፍቶ:
¤ለሕዝቡ ምድረ ርስትን አወረሰ::

የገባዖን ሰዎች "አድነን" ብለው በላኩበት ጊዜ ነገሥተ አሞሬዎንን ይወጋ ዘንድ ኢያሱ ወጣ:: እነዛን ግሩማን ነገሥታት በፈጣሪው ኃይል: በጦርና በተአምራት ድል ነስቶ የእግዚአብሔር ስሙ ከፍ ከፍ አለ:: በዚሕች ዕለትም ለ12ቱ ነገደ እሥራኤል ርስትን ሲያካፍል ፀሐይን በገባዖን: ጨረቃን ደግሞ በቆላተ ኤሎም (በኤሎም ሸለቆ) አቆመ::

ሰባት #አሕጉራተ_ምስካይ(የመማጸኛ ከተሞችን) ለየ:: ነቢይና መስፍን ሆኖ ሕዝቡን ለ40 ዓመታት አገለገለ:: በመጨረሻም ለሕዝቡ:- "እኔና ቤቴ እግዚአብሔርን እናመልካለን:: (ኢያ. 24) እናንተስ?" አላቸው:: እነርሱም "እኛም እንዳንተ ነን" አሉት:: ለዚህም ምልክት ይሆን ዘንድ 3 ገጽ ያላት ሐውልትን በመካከላቸው አቆመ::

ይህችውም የቅድስት #ድንግል_ማርያም ምሳሌ ናት:: ሐውልቷ 3 ገጽ እንዳላት እመቤታችንም በ3 ወገን (በነፍስ: በሥጋ: በልቡና) ድንግል ናት:: አንድም በ3 ወገን (ከኃልዮ: ከነቢብ: ከገቢር ኃጢአት) ንጽሕት ናት:: ለዚህም ነው #አባ_ሕርያቆስ
"ሐውልተ ስምዕ ዘኢያሱ" (የኢያሱ የምስክር ሐውልት አንቺ ነሽ) ሲል ያመሰገናት::

ታላቁ ነቢይ ኢያሱ ግን ከግብጽ በወጡ በ80 ዓመት: በተወለደ በ120 ዓመቱ (ጥሬው መጽሐፍ ቅዱስ በ110 ዓመቱ ይላል) በወገኖቹ መካከል ዐርፎ በያዕቆብ መቃብር ተቀበረ:: እሥራኤልም ለ30 ቀናት አለቀሱለት::

†††🌻✝️ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ🌻✝️ †††

††† አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ እንደነገረን በመንግሥተ ሰማያት ታላቁ ሰው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ ከዘብዴዎስና ከማርያም ባውፍልያ ተወልዶ: በገሊላ አካባቢ አድጐ: ገና በወጣትነቱ መድኃኔ ዓለምን ተከትሎታል:: ቅዱስ ዮሐንስ ከሐዋርያት ቀድሞ ጌታን ከመከተሉ ባሻገር በምንም ምክንያት ከጐኑ አይጠፋም ነበር:: ስለ ንጽሕናውና በጐ የፍቅር ሕሊናው ሕጻን ሳለ በወንድሞቹ ሐዋርያት ዘንድ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው::

ጌታችንን እስከ እግረ #መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ድንግል እመቤታችንን ተቀብሏል:: ከእርሷ ጋር ለ15 ዓመታት ቢቀመጥ መዝገበ ምሥጢር ሆነ:: ስንኩዋን ከሰው ልጆች ይቅርና ከልዑላኑ መላዕክትም ማዕረጉ ከፍ አለ:: ሰው ቢበቃ መላእክትን ሊያይ ይቻለዋል:: ቅዱስ ዮሐንስን ግን መላእክት ሊያዩት ይከብዳቸዋል:: ከፍጥረት ወገን ከእመ ብርሃን ቀጥሎ ክቡር እርሱ ነው::

ቅዱሱ ከጌታችን ዕርገት በሁዋላ ለ70 ዓመታት በዚህ ምድር ሲኖር አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በኤፌሶን አካባቢ ነው:: ሕዝቡን ወደ ክርስትና ለማምጣት በአፍም በመጽሐፍም ደክሟል::

ሶስት መልዕክታት: ራዕዩንና ወንጌልን ጽፎላቸዋል:: ሕይወትን ስለ ሰበከላቸው በፈንታው ብዙ አሰቃይተውታል:: ከእሳት እስከ ስለት: እስከ መጋዝም በስተእርጅና ደርሶበታል:: እርሱ ግን በትእግስቱ ገንዘብ አድርጉዋቸዋል::

††† እናት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ስትጠራው እንዲሕ ነው:-
¤ወንጌላዊ
¤ሐዋርያ
¤ሰማዕት ዘእንበለ ደም
¤አቡቀለምሲስ (ምሥጢራትን ያየ)
¤ታኦሎጐስ (ነባቤ መለኮት)
¤ወልደ ነጐድጉዋድ
¤ደቀ መለኮት ወምሥጢር
¤ፍቁረ እግዚእ
¤ርዕሰ ደናግል (የደናግል አለቃ)
¤ቁጹረ ገጽ
¤ዘረፈቀ ውስተ ሕጽኑ ለኢየሱስ (ከጌታ ጎን የሚቀመጥ)
¤ንስር ሠራሪ
¤ልዑለ ስብከት
¤ምድራዊው መልዐክ
¤ዓምደ ብርሃን
¤ሐዋርያ ትንቢት
¤ቀርነ ቤተ ክርስቲያን
¤ኮከበ ከዋክብት

††† በዚህች ዕለት ቅዱሱ ሐዋርያ ከእናቱ #ማርያም_ባውፍልያ: ከአባቱ #ዘብዴዎስ መወለዱን ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች::

†††🌻✝️ አባ ሙሴ ዻዻስ🌻✝️ †††

እሥራኤላዊ ሲሆኑ ከአቡነ #ሰላማ ቀጥለው የመጡ የሃገራችን ዻዻስ ናቸው:: ፍጹም ገዳማዊና ትጉህ: ባለ ረዥም ዕድሜ ጻድቅም ናቸው::

ገዳማቸው #ወሎ ውስጥ ቢገኝም አስታዋሽ ያጣ ይመስላል:: መናንያኑ ለዕለት እንኩዋ የሚቀምሱት አጥተው ሲቸገሩ መመልከቱ እጅግ ያማል::

††† በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ያደረ የእመቤታችን ድንግል ማርያምና የአንድ ልጇ ፍቅር በእኛም ላይ ይደር:: ቸሩ ጌታ ስም አጠራራቸው ካማረና ከከበረ ወዳጆቹ በረከትን ያሳትፈን::

††† መስከረም 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ኢያሱ ወልደ ነዌ (ነቢይና መስፍን)
2.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ (ልደቱ)
3.ቅዱሳን ዘብዴዎስና ማርያም ባውፍልያ
4.አባ መቃርስ ሊቀ ዻዻሳት
5.አባ ሙሴ ዻዻስ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
2.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
3.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

††† "አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ:: በእውነተኛም ልብ አምልኩት . . . እግዚአብሔርን ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ . . . የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ: የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ:: እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን::" †††
(ኢያሱ. 24:14)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ዓመታዊ የተዓምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን†††

"በዛቲ ዕለት #እግዚአብሔር ገብረ: በእደ ባስልዮስ መንክረ::"
(በዚህች ዕለት
እግዚአብሔር በባስልዮስ እጅ ድንቅን አደረገ)

†   🕊   ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ    🕊   †

††† ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ባስልዮስ #አርእስተ_ሊቃውንት ከሚባሉ አባቶች አንዱ ነው:: አባቱ #ኤስድሮስ(ባስልዮስ የሚሉ አሉ): እናቱ ደግሞ #ኤሚሊያ ይባላሉ:: ባልና ሚስት ከተቀደሰ ትዳራቸው 5 ወንድና 1 ሴት ልጅን አፍርተዋል:: የሚገርመው ሴቷ ( #ቅድስት_ማቅሪና) ገዳማዊት ስትሆን 5ቱም ወንዶች ዻዻሳት መሆናቸው ነው::

የሁሉ የበላይ የሆነው ግን ቅዱስ ባስልዮስ ነው:: አባቶቻችን እንዳስተማሩን ቅዱሱ ሊቅ ከ318ቱ ሊቃውንት አንዱ ነው:: #ቅዱስ_ኤፍሬም ሶርያዊንም ያስተማረው እርሱ ነው:: ነገር ግን ቅርብ ጊዜ ከድረ ገጾች (websites) እየገለበጡ የሚጽፉ አንዳንድ ወንድሞች ይህንን የሚያፋልስ ነገር ጽፈው ተመልክተናል::

††† ቅዱስ ባስልዮስ
ገዳማዊ ጻድቅ:ባለ ብዙ ምሥጢር ሊቅ:
የብዙ ምዕመናን አባት: የቂሣርያ ሊቀ ዻዻሳት: ባለ ብዙ ተአምራትና ከከዊነ እሳት (ከፍጹምነት) የደረሰ አባት ነው::
ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳያንን ሆስፒታል በ4ኛው መቶ ክ/ዘ ያስገነባ እርሱ ነው::

እጅግ ብዙ ድርሰቶች አሉት:: መጽሐፈ ቅዳሴንም ዛሬ በምናውቀው መንገድ ያሰናሰለው እርሱ ነው:: ለምዕመናን የሚጠቅሙ ብዙ ሥርዓቶችን ሠርቶ: የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ታዲያ ይህ ሊቅ: ቅዱስና ጻድቅ ሰው ብዙ ድንቆችን ሠርቷል:: ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ዛሬ ይህኛውን ታስባለች::

በዘመኑ እዚያው #ቂሣርያ ውስጥ አንድ አገልጋይ (በዘመኑ አጠራር ባሪያ) ነበር:: የሚሠራው ደግሞ በሃገረ ገዥው ግቢ ውስጥ ነው:: ለሥራ ሲገባ የሰውየውን አንዲት ብቸኛ ልጅ ተመለከታት:: ቆንጆ ነበረችና በፍትወት ተለከፈ:: ጧት ማታ ሥራው እሷን ማየት ሆነ::

እንዳይጠይቃት ደረጃው አይመጥንምና ከባድ ፍርድ ይጠብቀዋል:: ነገሮች ከአቅሙ በላይ ሲሆኑበት በቀደመ ስሕተቱ ላይ ሌላ ከባድ ስሕተትን ጨመረ:: ወደ ጠንቅዋይ (መተተኛ) ቤት ሒዶ ሥራይ እንዲደረግለት ጠየቀ:: መተተኛው ግን "ይህንን ማድረግ የሚችል ሰይጣን ብቻ ስለሆነ ካልፈራህ ወደ እርሱ ልላክህ" አለው::

ያ ከንቱ ሰው "እሺ" አለ:: መተተኛው ቀጠለ "በል! ሌሊት 6 ሰዓት ሲሆን ወደ አሕዛብ መቃብር ሒድና ግራ እጅህን ወደ ላይ ዘርጋ:: ከዛ ይመጣልሃል" ብሎ ላከው:: አገልጋዩም የተባለውን ሲያደርግ ከአጋንንት አንዱ መጥቶ: ነጥቆ ወደ ጥልቁ: የሰይጣኖች አለቃ ወደ ሚገኝበት ወሰደው::

ጋኔኑ ሰውየውን አለው:- "አንተ የፈለከው እንዲፈጸም መጀመሪያ ክርስትናህን ካድ:: በክርታስም ላይ ክህደትህን ጽፈህ በፊርማህ ስጠኝ" አለው:: ያ ልቡ የታወረ ሰው እንደተባለው መጽሐፈ ክህደቱን ለሰይጣን ሰጠ:: ወዲያው ያ ያመጣው ወደ ቤቱ መለሰው::

በማግስቱ ጠዋት በሃገረ ገዥው ቤት ታላቅ ግርግር ሆነ:: ልጃቸው "ያን አገልጋይ ካላጋባችሁኝ ራሴን አጠፋለሁ" አለች:: ቢለምኗትም ልትሰማ አልቻለችም:: ወላጆቿ ግራ ስለተጋቡ ከምትሞት ብለው እያዘኑ ልጃቸውን ከአጋንንት ጋር ለተዛመደ ሰው ሰጡ::

እነርሱ ተጋብተው ኑሯቸውን ቀጠሉ:: ወላጆች ግን የአንድ ልጃቸውን ነገር እንዲህ በዋዛ ሊተውት አልወደዱምና ጾሙ: ጸለዩ: ተማለሉ:: በእንዲህ ሁኔታ ብዙ ዓመታት አለፉ:: ወላጆቿ ግን ተስፋ አልቆረጡምና እግዚአብሔር ሰይጣን የቀማትን ማስተዋል መለሰላት::

አንድ ቀንም ባሏን ጠርታ " #ቤተ_ክርስቲያን ተሳልመህ: ቆርበህ : ስመ እግዚአብሔር ጠርተህ: አማትበህስ ታውቃለህ?" አለችው:: እርሱም "በጭራሽ አላውቅም" አላት:: "ለምን?" ብትለው የሆነውን ነገር ሁሉ ዘርዝሮ ነገራት:: በጣም ከመደንገጧ የተነሳ ምድር ከዳት::

ለረዥም ሰዓት አለቀሰች:: ከሰይጣን ጋር ተጋብታ የኖረች ያህል ስታስበው አንገፈገፋት:: ሰውነቷ ተስፋ ቆረጠ:: ወዲያው ግን በህሊናዋ አንድ ሐሳብ መጣላት:: "ያ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ከሰይጣን ባርነት ሊገላግለኝ ይቻለዋል" አለች:: ፈጥናም ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ዘንድ ሒዳ ከእግሩ ሥር ወድቃ አለቀሰች::

እርሱም "ልጄ ሆይ! አይዞሽ: በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ቀላል ነው:: ሒጂና ባልሺን አምጪው" አላት:: ሒዳ አመጣችው:: ቅዱሱም ያን ሰው "መዳን ትፈልጋለህ?" አለው:: ሰውየው መልሶ "ያቺን ደብዳቤ መመለስ የሚቻል ቢሆንማ እፈልግ ነበር" አለው:: ቅዱስ ባስልዮስም ሴቷን "ሒጂና ጸልይ: ከ40 ቀን በሁዋላ ትመጫለሽ" ብሎ አሰናበታት::

በሰይጣን ባርነት የተያዘውን ያን ሰው ግን ወደ ራሱ በዓት ወስዶ አስገባውና በ4 አቅጣጫ በመስቀል አተመው:: ትንሽ ምግብ ሰጥቶት "ከ3 ቀን በሁዋላ እመጣለሁ" ብሎት ሔደ:: ቅዱሱ ያለ ዕረፍት ይጋደልም ጀመር:: በ3ኛው ቀን መጥቶ "እንዴት ነህ?" አለው:: "አባቴ! አጋንንት አሰቃዩኝ" አለው:: "አይዞህ!" ብሎት ወጣ::

በ6ኛው ቀን መጥቶ "አሁንስ?" አለው:: "አባ! ስቃዩ ቀረልኝ: ግን ደብዳቤዋን እያሳዩ ያስፈራሩኛል" አለው:: "በርታ" ብሎት ሔደ:: በ9ኛው ቀን ተመልሶ "ደግሞ አሁንሳ?" አለው:: "አባቴ! ምስጋና ለፈጣሪህ! ከአካባቢው እየራቁ ነው" አለው::

እንዲህ በ3: በ3 ቀናት እየተመላለሰ ለ13 ጊዜ ጠየቀው:: በ39ኛው ቀን መጥቶ "ዛሬ ምን አየህ" ቢለው "አባ! አጋንንትን ከእግርህ በታች ስትረግጣቸው አየሁ" አለው:: ቅዱስ ባስልዮስ በ40ኛው ቀን ደወል ደውሎ መነኮሳት: ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ: ያን ሰው ከመሃል አቁሞ: "እግዚኦ በሉ" አላቸው::

ሕዝቡ እግዚኦታውን ሲፈጽሙ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ:: ቀና ሲሉ ያቺ የክህደት ደብዳቤ ሁሉ እያዩአት ከመካከላቸው ወደቀች:: በዚያች ቦታም ታላቅ እልልታና ሐሴት ተደረገ:: ቅዱሱ በጸሎቱ ለ40 ቀናት ከእንቅልፍና ከምግብ ተከልክሎ ያቺን ነፍስ ማረከ::

የሕዝቡንም ሃይማኖት አጸና:: በዚያውም ቅዳሴ ቀድሶ ሕዝቡን አቁርቦ አሰናበታቸው:: ባልና ሚስቱንም ባርኮ በፍቅር ይኖሩ ዘንድ አሰናበታቸው:: ታላቁ ሊቅም ተጋድሎውን ፈጽሞ ጥር 6 ቀን ዐርፏል::

አምላከ ቅዱስ ባስልዮስ እኛንም ከኃጢአት ማሠሪያ ፈትቶ ከአጋንንት ሤራ ይሰውረን:: ከሊቁም በረከትን ያሳትፈን::

መስከረም 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
2.አባ ይስሐቅ ባሕታዊ

ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት
3."99ኙ" ነገደ መላዕክት
4.ቅዱስ አስከናፍር
5."13ቱ" ግኁሳን አባቶች
6.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
7.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

"እውነት እውነት እላቹሃለሁ:: በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል:: ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል:: እኔ ወደ አብ እሔዳለሁና:: አብም ስለ #ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ:: ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ::"
(ዮሐ. 14፥12)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ  ]
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ  አሜን ✞✞✞

መስከረም ፲፮ (16)

✞✞✞ እንኳን ለቅድስት ሃገር #ኢየሩሳሌም: ለቅዱስ #ጦቢት እና ለአባ #አጋቶን_ባሕታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

†   🕊   ሕንጸታ_ለኢየሩሳሌም    🕊   †

=>ኢየሩሳሌም በብሉይም: በሐዲስም ቅድስት ሃገረ
እግዚአብሔር ናት:: '#ኢየሩ' ማለት 'ሃገር' ማለት ሲሆን
'#ሳሌም' ደግሞ 'ሰላም' ማለት ነው:: ስለዚህ በቁሙ
'ሃገረ ሰላም': '#ሃገረ_ክርስቶስ' ማለት ነው::

+ኢየሩሳሌም የሚለው ቃል በቁሙ ቅድስት ሃገርን
ሲመለከት በምሥጢሩ ግን የቤተ ክርስቲያን: የመንግሥተ
ሰማያት እና የአማናዊት ሃገረ ሰላም #ድንግል_ማርያም
መጠሪያ ነው:: ኢየሩሳሌምን በከተማ ደረጃ የመሠረታት
ታላቁ ካህን #መልከ_ጼዴቅ ሲሆን 'ንጉሠ ሳሌም'
ተብሎም ኑሮባታል::

+ይህች ቅድስት ሃገር በብሉይ ዘመን እግዚአብሔር
በረድኤት ቢገለጥባት: ጻድቃነ ብሊት ቢኖሩባት
ተቀድሳለች:: በሐዲስ ኪዳን ግን አምላካችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ከሰማያት ወርዶ 33 ዓመት ከ3 ወር ያህል
የድኅነት ሥራውን ቢፈጽምባት: ለድንግል ማርያምና
ለብዙ ቅዱሳን ቤት ብትሆን የበለጠ ተቀድሳለች::

+ዛሬም ድረስ ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት በብዙ ድካምና
ወጪ ሊያዩዎት ይጉዋዛሉ:: የቀደመው ዘመን
አባቶቻችንም ይህችን ቅድስት ከተማ ለመሳለም እስከ
ደም ጠብታ ከፍለዋል::

+ወደ ዋናው ጉዳያችን እንለፍና የኢየሩሳሌምን መታነጽ
እንይ:: ኢየሩሳሌም በአሕዛብ እጅ ብዙ ጊዜ ፈርሳ
ታንጻለች:: እኛ ግን ዛሬ የምናከብረው የከተማዋን
መታነጽ ሳይሆን በከተማዋ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ
መንገድ በአንድ ጊዜ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት
መታነጻቸውን ነው:: ይሕስ እንደምን ነው ቢሉ:-

+ከክርስቶስ ዕርገት 300 ዓመታት በሁዋላ ለቤተ
ክርስቲያን የተነሳችው #ቅድስት_ዕሌኒ በጐ ሃሳብ
በሕሊናዋ ተመላልሷልና ተነሳች::

#ጉባኤ_ኒቅያ ከተጠናቀቀ በሁዋላ ልጇ ቆስጠንጢኖስ
በነገሠ በ20 ዓመቱ በ227 ዓ/ም አካባቢ ቅዱስ ዕጸ
መስቀሉን ትፈልግ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ አደረገች::

+መስቀሉን ፈልጋ ያገኘችበት ታሪክ ለነገ ይቆየንና
መስቀሉን ካገኘችው በሁዋላ በሙሉ ከተማዋ ላይ
አብያተ ክርስቲያናትን ለማነጽ ከልጇ ጋር ተስማማች::

+ለሕንጻው የሚሆን ብዙ ወርቅ: ብርና እንቁ ጭና
ማምጣቷን የተመለከቱት #አባ_መቃርስ (የኢየሩሳሌም
ሊቀ ዻዻስ ናቸው) "ልምከርሽ! ቤተ ክርስቲያኑን
በጠንካራ አለት ላይ ሥሪ:: ወርቅና ብሩን ግን ለነዳያን
በትኚ" ስላሏት በአካባቢው ላሉ ነዳያን ታላቅ ፌሽታ
ሆነ:: እጅግ ብዙ ሠራዊት: ብዙ ሺህ ሠራተኞች
ታጥቀው 80 አብያተ ክርስቲያናትን ያንጹ ጀመሩ::

+ሥራው ረቂቅና ብዙ ስለነበረ እጅግ አድካሚ ነበር::
ቅድስት ዕሌኒ ሃገሪቷን በቤተ መቅደሶች መሸፈን ስለ
ፈለገች እንዲታነጽ ያዘዘችው የቤተ ክርስቲያን ቁጥር 80
ደረሰ:: እነዚህም ጌታ ከጽንሰቱ እስከ ዕርገቱ
የረገጣቸውና #እመ_ብርሃን የረገጠቻቸው ቦታዎች
ናቸው::

+#ቤተ_ልሔም: #ዮርዳኖስ: #ደብረ_ሊባኖስ:
#ደብረ_ታቦር: #ደብረ_ዘይት: #ጐልጐታ: #ጌቴ_ሴማኒ:
#ቤተ_ሳይዳ: #ጽርሃ_ጽዮን ደግሞ ዋና ዋናዎቹ ናቸው::
በአካባቢው ያሉ ነዳያን ሳይርባቸው: ሠራተኞችም ደሞዝ
ሳይቸግራቸው: 80ው አብያተ ክርስቲያናት በፈጣሪ
ረዳትነት: በ10 ዓመታት ታነጹ::

+ቀጥሎም ንጉሡ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ በዓለም ያሉ
ታላላቅ ቅዱሳን ሊቃነ ዻዻሳትን ጠርቶ: ሁሉም እስከ
መስከረም 15 ቀን ወደ ኢየሩሳሌም በተሰበሰቡበት
የሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ቅዳሴ ቤት በአንድ ላይ
ሲከበር ከዝማሬው ብዛት: ከአምላክ ጸጋ የተነሳ
በከተማዋ ታይቶ የማይታወቅ ሐሴት ተደረገ::

*ኢየሩሳሌም ፍጹም አጊጣ እስከ መከራ ቀን (አሕዛብ እስከ ተነሱበት) ቆይታለች::

†   🕊   ቅዱስ_ጦቢት (ጻድቅ ነቢይ)    🕊   †

=>ከክርስቶስ ልደት በፊት እሥራኤላውያን ክፋትን
ሲያበዙ ጠላት መጥቶ ይማርካቸው: ንስሃ ሲገቡ ደግሞ
በድንቅ ተአምር ይወጡ ነበር:: ሕዝቡ ሲማረክ ነቢያት
እረኞች ናቸውና ያለ ጥፋታቸው አብረው ይማረኩ ነበር::
በዚያም ሕዝቡን ያስተምራሉ: ያጽናናሉ::

+በተመሳሳይ እሥራኤላውያን ተማርከው ወደ #ነነዌ
በወረዱበት ወራት ጦቢት የሚሉት ደግ ሰው
በመካከላቸው ነበር:: ይህ ደግ ሰው ከምርኮ በፊት
መልካም አምልኮት የነበረው: አሥራቱን በኩራቱን
የሚያወጣ: ለነዳያን የሚራራ ነበር::

+ከተማረኩ በሁዋላም ሕዝቡ ከአሕዛብ ጋራ ሲቀላቀሉ
እርሱ ንጽሕናውን ጠብቆ እግዚአብሔርን ያመልክ ነበር::
ቅዱስ ጦቢት በተለይ የሞተ ሰው ሲያገኝ ሳይቀብር
እህል አይቀምስም ነበር:: በዚህም ምክንያት የዘወትር
ጦመኛ ነበር::

+ይሕ ቅዱስ እድሜው 58 በሆነ ጊዜ ዓይኑ ጠፋ:: ብዙ
በመሰቃየቱም ሞቱን ለመነ:: በሌላ አቅጣጫ ደግሞ
#ሣራ 'አስማንድዮስ' የሚባል ጋኔን 7 ባሎቿን እየገደለ
አሳቅቁዋት ነበርና እርሷም ሞቷን ተመኘች::

+እግዚአብሔር ግን መልአኩን ልኮ: #ቅዱስ_ሩፋኤል
አዛርያን መስሎ የጦብያና የሣራን ጋብቻ ባርኩዋል::
ጋኔኑንም በጥልቁ አስጥሞታል:: በዓሣ ሐሞትም
የጦቢት ዓይኑ በርቶለት በእድሜው ላይ 100 ዓመታት
ተጨምረውለታል:: ቅዱስ ጦቢት ብዙ ሕብረ ትንቢቶችን
ተናግሮ በ158 ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፏል::

†   🕊   አባ_አጋቶን_ባሕታዊ    🕊   †

=>ይህንን ቅዱስ የማያውቅ የቤተ ክርስቲያን ሰው
ይኖራል ብዬ አልገምትም:: እርሱ ታላቅ ጻድቅ: ገዳማዊና
የእግዚአብሔር ሰው ሲሆን አንደበቱን ከክፋት ይከለክል
ዘንድ ለ30 ዓመታት ድንጋይ ጐርሶ ኖሯል::

+ይህንን ቅዱስ #ሊቃውንት ሲገልጹት "ክምረ ክምር
ጽድቁ እስከ አስተርአየ" ይሉታል:: ትእግስቱ: ደግነቱ:
አርምሞው: ትሩፋቱ ከመነገር በላይ ነው:: በነበረበት
በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም እንደ ኮከብ ያበራ ታላቅ አባት
ነው::

=>አምላከ ቅዱሳን የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያንን
ሰላምና ደስታ ያሳየን:: ከበዓላቱ ከሚገኘውም ጸጋ
በረከት አይለየን::


=>መስከረም 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=

1.ሕንጸታ ለኢየሩሳሌም
2.ቅድስት እሌኒ ንግሥት
3.ቅዱስ ጦቢት ነቢይ
4.ቅዱሳን ጦብያና ሣራ
5.አባ አጋቶን ባሕታዊ

=>ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ (የቅ/
ላሊበላ ወንድም)
4.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
5.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
6.አባ ዳንኤል ጻድቅ
7.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ)

+ ወደ #እግዚአብሔር ቤት እንሒድ ባሉኝ ጊዜ
ደስ አለኝ::
#ኢየሩሳሌም ሆይ እግሮቻችን በአደባባይሽ ቆሙ::
ኢየሩሳሌምስ እርስ በርሷ እንደ ተገለጠች ከተማ
ተሠርታለች . . .
ስለ ወንድሞቼ ስለ ባልንጀሮቼም በውስጥሽ ሰላም ይሁን
አልሁ::
ስለ አምላካችን ስለ
እግዚአብሔር ቤት ላንቺ
መልካምነትሽን ፈለግሁ:: + (መዝ. 121፥1-9)


† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ  ]


💚💛@sinkisar_gisawe_z_tewahedo
💚💛
    🇯 🇴 🇮 🇳 &🇸 🇭 🇦 🇷 🇪   
        ✥┈┈•◦●◈◎❖◎◈●◦•┈┈✥
  ✧━━━━━━━━━━━━━━━━━✧
      ❍ㅤ           ⎙ㅤ         ⌲ 
ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ         ˢᵃᵛᵉ          ˢʰᵃʳᵉ
††† እንኳን ለአበው ሰማዕታት #ቅዱስ_ዮልዮስና_ቅዱስ_ኮቶሎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††

†   🕊   ቅዱስ_ዮልዮስ_ሰማዕት    🕊   †

=>ከሁሉ አስቀድሞ ስለ ሰማዕታት ዜና ሲሰማ ለዚህ ቅዱስ አንክሮ (አድናቆት): ክብርና የጸጋ ውዳሴ ይገባዋል:: ምክንያቱም ገድለ ሰማዕታትን የጻፈልን እርሱ ነውና:: ነገር ግን መጻፍ ሲባል: ነገሮች እንዲህ እንደ እኛው ዘመን ቀላል እንዳይመስሏችሁ:: ቅዱሱ ዜና ሰማዕታትን ለማዘጋጀት ሃብቱን: ንብረቱን: ቤተሰቦቹንና ሕይወቱንም ሰውቷል::

+ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- በመጨረሻው ዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ ክ/ዘ) ዓለም በደመ ሰማዕታት ስትሞላ የሰማዕታቱን ዜና የሚጽፍ: ሥጋቸውን እንኩዋ የሚቀብር አልተገኘም:: "ወኃጥኡ ዘይቀብሮሙ-የሚቀብራቸውም አጡ" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት:: (መዝ. 78፥3)

+#እግዚአብሔር ግን ስለ ወዳጆቹ #ሰማዕታት ይህንን ቅዱስ አስነሳ:: ቅዱስ ዮልዮስ በዘመኑ ደግ ክርስቲያን: ትዳርና ልጆች ያሉት: እጅግ ባለ ጸጋና 300 አገልጋዮች ያሉት: ምጽዋትንም የሚወድ ሰው ነበር::

+በወቅቱ ክርስቲያኖች በየመንገዱ ወድቀው መታየታቸው ዕረፍት ቢነሳው ከቤተሰቦቹ ጋር መክሮ መልካም ግን ደግሞ ከባድ ውሳኔን አስተላለፈ:: ውሳኔውንም ታጥቆ ይተገብረው ጀመር:: ነገሩ እንዲህ ነው:-

1.የታሠሩ ክርስቲያኖችን ቁስላቸውን እያጠበ ያጐርሳቸዋል::

2.ቀን ቀን አገልጋዮቹን አስከትሎ የሰማዕታቱን ሥጋ እየሰበሰበ: ሽቱ ቀብቶ ይገንዛቸዋል:: አንዳንዶቹን ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲልክ ሌሎቹን ራሱ ይቀብራቸዋል::

3.ሌሊት ሌሊት በ300ው አገልጋዮቹ እየታገዘ የሰማዕታቱን ዜና: ቀለም በጥብጦ: ብራና ዳምጦ: ብርዕ ቀርጾ: ሲጽፍና ሲጠርዝ ያድራል:: በተረፈችው ጥቂት ሰዓት ደግሞ ይጸልያል:: ቅዱስ ዮልዮስ በእውነት ድንቅ ሰው ነው:: በምን እንመስለዋለን! እርሱን የፈጠረውን ጌታ "ዕጹብ ዕጹብ" ብለን ከማድነቅ በቀር::

+ሰማዕታቱም ስለ ደግነቱ የሚመልሱለት ቢያጡ ዝም ብለው ይመርቁት ነበር:: ምርቃታቸውም "ለሰማዕትነት ያብቃህ" የሚል ነው:: በእርግጥ ይህ ለዘመኑ ሰዎች ምርቃት ላይመስለን ይችል ይሆናል:: እርሱ ግን ይህንን ሲሰማ ሐሴትን ያደርግ: እጅም ይነሳቸው ነበር:: በዘመኑ ትልቁ ምርቃት ይሔው ነበርና::

+እንዲህ: እንዲህ እያለ ዘመነ ሰማዕታት ሊፈጸም ወራት ቀሩት:: በዚህ ጊዜ ለሰማዕትነት ከመነሳሳቱ የተነሳ ጌታችንን ተማጸነ:: ጌታችንም ተገልጾለት "ሒድና ሰማዕት ሁን: ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: እርሱም ደስ እያለው ዜና ሰማዕታቱን ለሁነኛ ሰው ሰጥቶ: ሃብት ንብረቱን ለነዳያን አካፈለ::

+ቀጥሎም ቤተሰቦቹንና አገልጋዮቹን ጨምሮ 500 ሰዎችን አስከትሎ ወደ ሃገረ #ገምኑዲ ሔደ:: በመኮንኑ ፊት የክርስቶስን አምላክነት ቢመሰክር ፈጽመው አሰቃዩት:: በማግስቱም ወታደሮቹ ለጣዖት ካልሰገድክ ሲሉት "ቆዩማ ላሳያችሁ" ብሎ በጸሎቱ ጣዖታትን ከነ ካህናቶቻቸው ምድር ተከፍታ እንድትውጣቸው አደረገ::

+በዚህ ተአምር የደነገጠው መኮንኑ #አርማንዮስ ከነ ሠራዊቱ በክርስቶስ አመነ:: ክብሩንም ትቶ ቅዱስ ዮልዮስን ተከተለው:: ቀጥሎም ጉዞ ወደ ሃገረ #አትሪብ ሆነ:: በዚያም ብዙ መከራን ተቀብሎ ጣዖታቱን አወደማቸው::

+እዚህም የአትሪብ መኮንን ደንግጦ ከነ ሠራዊቱ አምኖ ቅዱሱን ተከተለው:: በመጨረሻ ግን ሰማዕትነት እንዳይቀርበት ስለሰጋ ቅዱስ ዮልዮስ ተአምራት ማድረጉን ተወ:: በፍጻሜውም የ3ኛው ሃገር መኮንን ቅዱስ ዮልዮስ ከቤተሰቡና ከ1,500 ያህል ተከታዮቹ ጋር: 2ቱን የሃገረ ገዥዎች ጨምሮ አንገታቸውን አሰይፏቸዋል:: ቅዱሱም የክብር ክብርን አግኝቷል::

†   🕊   ቅዱስ_ኮቶሎስ_ሰማዕት    🕊   †

=>ይህ ቅዱስ በቀደመ ሕይወቱ አረማዊ ሲሆን የክርስቶስን ስም ሰምቶ አያውቅም:: በ4ኛው መቶ ክ/ዘ በፋርስ (አሁን #ኢራን) ሳቦር የሚባል ክፉ ንጉሥ ነግሦ ክርስቲያኖችን ያሰቃይ ነበር:: እርሱ የሚያመልከው ፀሐይና እሳት ነውና::

+የዚህ ንጉሥ ልጆቹ 'ልዑል ኮቶሎስና ልዕልት አክሱ' ይባላሉ:: በቤተ መንግሥት ውስጥ ስላደጉ የሚያመልኩት የአባታቸውን ጣዖት ነበር:: በፋርስ መንግሥት ውስጥ ከነበሩ የጦር አለቆችና ሃገረ ገዥዎች አንዱ #ጣጦስ ይባላል::

+ይህ ሰው እጅግ ብሩህ የሆነ ክርስቲያን ነበርና ዘወትር ከንጹሕ አገልግሎቱ ተሰነካክሎ አያውቅም:: ትንሽ ቆይቶ ግን ክርስቲያን መሆኑን ሳቦር ስለ ሰማ ሠራዊት ይልክበታል:: "ሒዱና ጣጦስን መርምሩት: ክርስቲያን ከሆነና አማልክትን እንቢ ካለ በእሳት አቃጥላችሁ ግደሉት" አላቸው::

+በአጋጣሚ የንጉሡ ልጅ ኮቶሎስና ጣጦስ በጣም የሚዋደዱ ባልንጀሮች ነበሩና ሊያስጥለው ወዶ ሔደ:: ኮቶሎስ ቅዱስ ጣጦስ ታስሮ በእሳት ሊቃጠል ሲል ደረሰ:: ወዲያውም ወደ እሳቱ ውስጥ ጨመሩት:: እነርሱ ፈጥኖ አመድ ይሆናል ብለው ጠብቀው ነበር:: ግን አልሆነም::

+ቅዱስ ጣጦስ በእሳት መካከል ቁሞ አላቃጠለውም:: እንዲያውም በትእምርተ መስቀል ቢያማትብበት እሳቱ ብትንትን ብሎ ጠፋ:: ኮቶሎስ ተገርሞ ቅዱሱን ባልንጀራውን "ወንድሜ! ሥራይ (መተት) መቼ ተማርክ ደግሞ?" ሲል ጠየቀው::

+እርሱ እስከዚያች ሰዓት ኃይለ እግዚአብሔርን አልተረዳምና:: ቅዱስ ጣጦስ ግን "ወንድሜ! አትሳሳት: እኛ ክርስቲያኖች መተትን አናውቅም:: በፈጣሪያችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ግን ሁሉን ማድረግ እንችላለን" ሲል መለሰለት::

+ኮቶሎስ ተገርሞ "አሁን እኔ በክርስቶስ ባምን እንዳንተ ማድረግ እችላለሁ?" ቢለው ቅዱሱ "አዎ ትችላለህ!" አለው:: ወዲያውም "እሳት አንድዱልኝ" አለና ጣቱን በመስቀል ምልክት አስተካክሎ ወደ እሳቱ ቢያመለክት እሳቱ 12 ክንድ ርቆ ተበትኖ ጠፋ::

+በዚያችው ሰዓት ቅዱስ ኮቶሎሰ በክርስቶስ አመነ:: ክብሩንና የአባቱን ቤተ መንግሥት አቃሎ ወደ እስር ቤት ገባ:: አባቱ ሳቦር ይህን ሲሰማ ተቆጥቶ "ምከሪው" ብሎ እህቱን አክሱን ላከበት::

+ቅዱስ ኮቶሎስ ልትመክረው የመጣችውን እህቱን አሳምኖ የክርስቶስ ወታደር አደረጋት:: አስቀድሞ #ቅዱስ_ጣጦስ: አስከትሎም #ቅድስት_አክሱ ተገደሉ:: በፍጻሜው ግን ቅዱስ ኮቶሎስን እግሩን አስረው በየመንገዱ ጐተቱት:: በጐዳናም አካሉ እየተቆራረጠ አለቀ:: ክርስቲያኖች በድብቅ መጥተው የ3ቱንም ሥጋ በክብር አኑረዋል::

=>አምላከ ቅዱሳን ሰማዕታትን ባጸናበት ጽናት ሁላችንም ያጽናን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

=>መስከረም 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=

1.ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት
2."1,500" ሰማዕታት (የቅዱስ ዮልዮስ ማሕበር)
3.ቅዱስ ኮቶሎስ ሰማዕት
4.ቅድስት አክሱ ሰማዕት
5.ቅዱስ ጣጦስ ሰማዕት
6.ቅዱስ ባላን ሰማዕት

=>ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
4.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
5.አባ ዻውሊ የዋህ

=>+"+ ሰውን ከአባቱ: ሴት ልጅንም ከእናቷ . . . እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና:: ለሰውም ቤተሰቦቹ ጠላቶች ይሆኑበታል:: ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም:: ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም:: መስቀሉን የማይዝ በሁዋላየም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም:: +"+ (ማቴ. 10፥35)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ  ]
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ መስከረም ፳፫ (23) ❖

✞✞✞ እንኳን ለቅዱሳን
#ጻድቃን_ወሰማዕት
#አውናብዮስና_እንድርያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

†  🕊  ቅዱሳን_አበው_አውናብዮስ_ወእንድርያስ    🕊   †

=>4ኛው መቶ ክ/ዘ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዘመነ ከዋክብት ይባላል:: ምናልባትም በዓለም ላይ ላለፉት
1,500 ዓመታት ያንን ዘመን መልሶ ማየት አልተቻለም::

*ያ ዘመን ብዙ #ሰማዕታት ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #ሊቃውንት ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #ጻድቃን ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #ደናግል ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #መነኮሳት ነበሩበት::
*ያ ዘመን ብዙ #ባህታውያን (ግኁሳን) ነበሩበት::

+ዘመኑ #ዘመነ_ብርሃን ነው:: እልፍ አእላፍ ቅዱሳን በዚህ ዘመን አብርተዋልና:: ጠላት ሰይጣንን ከቦታው
አሳድደው አስጨንቀውታል:: በዚህ ዘመነ ብርሃን ከወደ ምሥራቅ ካበሩ ከዋክብት መካከል ደግሞ በዚህ ዕለት
አባቶቻችን ቅዱሳን አውናብዮስና እንድርያስን እናዘክራለን::

+ቅዱሳኑ ባለ ብዙ ሃብት ነበሩ:: ከሰማዕታት: ከጻድቃን:
ከደናግል: ከሊቃውንቱም አሉበት:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

¤በተጠቀሰው ዘመን በቅዱስ #ጊዮርጊስ ሃገር በልዳ ከከበሩ ወገኖች ተወልደዋል::

+የቅዱሳኑ ወላጆች ክርስቲያኖች: በዚያውም ላይ ባለ ሥልጣኖችና ሃብታሞች ነበር:: ልጆቻቸውን
(አውናብዮስንና እንድርያስን) ሥጋዊውንም:መንፈሳዊውንም ትምህርት አስተምረዋቸዋል:: ወጣት በሆኑ ጊዜ ወላጆቻቸው የዚህን ዓለም ነገር
ሲያስቡላቸው: እነሱ ግን የተሻለውን እድል ያስቡ ነበር::

+ዘወትር ገድላተ ቅዱሳንን ያነቡ: ዜና አበውን ይሰሙ ነበርና ይመንኑ ዘንድ ልቡናቸው አወካቸው:: በአንዲት
ሌሊት ግን በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ወስነው:ከሃገራቸው #ልዳ ወጥተው ወደ ገዳም ሔዱ::

+ክብር ለቅዱሳኑ #አባ_ሮማኖስና #አባ_በርሶማ ይሁንና በወቅቱ በሶርያ ምድር ገዳማዊ ሕይወት ተስፋፍቶ: ብዙ
አድባራት በበርሃ ውስጥ ነበሩ:: 2ቱ ቅዱሳንም በአንዱ ገዳም ውስጥ ገብተው አገለገሉ::

+ተጋድሏቸውን እያበረቱ እስከ ምንኩስና ደረጃም ደረሱ::ተጋድሏቸው በጾም: በጸሎትና በትእግስት ብቻ
አይደለም:: በትሕትና በፍቅር በደግነትና በመታዘዝም ጭምር ነበር እንጂ::

+የምንኩስናና የገዳማዊ ሕይወት ጠላት 'ፍቅረ ዓለምና ፍትወት እንስሳዊት' ናቸው:: አንድ ሰው ከዚህ ዓለም
ቁሳቁስ ሳይርቅ መናኝ መሆን አይችልም:: ቅዱሳኑ ግን በመንኖ ጥሪት ይህችን ዓለም ከነኮተቷ ናቁዋት:አቃለሏት::

+የሥጋ ፈቃዳቸውን ያጠፉ ዘንድ ሰውነታቸውን በጾምና በጸሎት: ዕረፍትም በማሳጣት ቀጧት:: #እግዚአብሔር
ደግሞ ስለዚህ ፈንታ ጸጋውን አበዛላቸው:: ቅዱሳኑ በሶርያ ገዳማት ለዘመናት ከተጋደሉ በሁዋላ ወደ ግብጽ
ለመውረድ ወሰኑ:: ምክንያታቸው ደግሞ:-

1ኛ.ከውዳሴ ከንቱ ለመራቅ
2ኛ.ከቅዱሳን አበው ለመባረክ እና
3ኛ.ለተሻለ ተጋድሎ ለመብቃት ነበር:: እየጸለዩ እያመሰገኑም ግብጽ: ቀጥሎም ገዳመ አስቄጥስ ደረሱ::

+ታላቁ #ርዕሰ_መነኮሳት_አባ_መቃርስን ፊት ለፊት ቢያገኙት ደስ አላቸው፤ ሐሴትንም አደረጉ:: እግዚአብሔርን በማደሪያዎቹ ማግኘት ይቻላልና:: የታላቁ
ቅዱስ ደቀ መዝሙር ሆነው: በድንግልና ተጠብቀው:በተጋድሎ በርትተው በቦታው ለ3 ዓመታት ቆዩ::

+እግዚአብሔር ደግሞ ለሌላ አገልግሎት ፈልጐአቸው ነበርና በዚያ ሰሞን በከተማ የነበሩ ሊቃውንት ወደ ገዳም መጡ:: ገዳማውያንንም ዻዻስ ስላረፈብን "የምንሾመው መልካም እረኛን ስጡን" አሏቸው::

+ገዳማውያኑ ሱባኤ ገብተው ቢጠይቁ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ አውናብዮስን መረጠ:: አበውም ቅዱሱን ዽዽስና
ሲሾሙት ወንድሙን እንድርያስን ረዳት አደረጉት:: 2ቱ ቅዱሳን ከበርሃ ወደ
ከተማ መውጣታቸውን ተከትሎ ተጋድሏቸውን ለማበርታት ወሰኑ::

+ምክንያቱም ለአንድ ገዳማዊ ከተማ ውስጥ ከመኖር በላይ ፈተና የለምና:: ቅዱሳኑ ቀን ቀን ድውያንን
ሲጠይቁ: ሙታንን ሲቀብሩ: ሕዝቡን ሲያስተምሩ: ሥጋውን ደሙን ሲያቀብሉ ውለው ሌሊት ይጋደላሉ::

+ለፈቃደ ሥጋቸው ሳያደሉ እንዲህ ባለ ቅድስና ኖረው ደግሞ ሌላ ፈተና መጣ:: የከተማው ሃገረ ገዢ አረማዊ
በመሆኑ "ለጣዖት ስገዱ: ክርስቶስን ካዱ" ይል ጀመር:: ቅዱሳኑ ሕዝቡን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ሊያስተምሩ ወደዋልና መኮንኑን "ተው! ተሳስተሃል"
አሉት::

+በዚህ ምክንያትም ብዙ ስቃይ ገጠማቸው:: በመጨረሻም በዚህች ዕለት ሰማዕት ሆነዋል:: ጌታም ስለ ድንግልናዊ ሕይወታቸው: ስለ ወንጌል አገልግሎታቸውና ስለ ሰማዕትነታቸው 3 አክሊላትን አቀዳጅቷቸዋል::

=>አምላከ አበው ቸርነቱን ይላክልን፤ የቅዱሳኑን በረከትም ያሳድርብን::

=>መስከረም 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=

1.ቅዱሳን ጻድቃን አውናብዮስ ወእንድርያስ (ሰማዕታት)
2.ቅዱስ ጐርጐርዮስ መንክራዊ
3.ቅድስት ቴክላ ድንግል
4.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሰማዕት

=>ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እሥራኤል)
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
6.አባ ሳሙኤል
7.አባ ስምዖን
8.አባ ገብርኤል

=>+"+ በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ #ጽድቅ እንኩዋ መከራን ብትቀበሉ #ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ: አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት:: +"+ (1ዼጥ.3፥13)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ  ]


💚💛@sinkisar_gisawe_z_tewahedo
💚💛
    🇯 🇴 🇮 🇳 &🇸 🇭 🇦 🇷 🇪   
        ✥┈┈•◦●◈◎❖◎◈●◦•┈┈✥
  ✧━━━━━━━━━━━━━━━━━✧
      ❍ㅤ           ⎙ㅤ         ⌲ 
ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ         ˢᵃᵛᵉ          ˢʰᵃʳᵉ
††† እንኳን ከዘመነ ክረምት ወደ ዘመነ መጸው አሸጋግሮ ለቅዱስ ዮናስ ነቢይ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††


††† ስንዱ #እመቤት #ቤተ_ክርስቲያን (ሃገራችን) ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ትጠቀማለች:: እሊሕም ዘመናት #መጸው (ጽጌ): #ሐጋይ (በጋ): #ጸደይ (በልግ) ና ክረምት ናቸው:: ዘመናቱ ወቅቶችን ከመለየትና ማሳወቅ ባሻገር የእኛ ሕይወትም ምሳሌዎች ናቸውና ልብ ልንላቸው ይገባል::

#ዘመነ_መጸው / #ወርኀ_ጽጌ/ #ጥቢ እየተባለም ይጠራል:: በዚህ ወቅት ምድር በአበባ የምታጌጥበት: ክረምት የተለፋበት አዝመራ የሚደርስበት በመሆኑ ደስ ያሰኛል:: በጊዜውም:-
1.የእመቤታችን የቅድስት #ድንግል_ማርያም ስደቷ ይታሠባል:: እርሷ ስለ እኛ:-
*የሕይወት እንጀራን ተሸክማ መራቧን::
*የሕይወት መጠጥን ይዛ መጠማቷን::
*የሕይወት ልብስን አዝላ መራቆቷን::
*ሙቀተ መንፈስ ቅዱስን የሚያድለውን ተሸክማ ብርድ መመታቷን እናስባለን::
*ዘመኑ የበረከት ነው::

2.በሌላ በኩል ጊዜው ወርኀ ትፍሥሕት (የደስታ ወቅት) ነው:: በክረምት የደከመ ዋጋውን አግኝቶ: በልቶ: ጠጥቶ ደስ ይለዋልና:: ያልሠራው ግን ከማዘን በቀር ሌላ እድል የለውም:: ይኼውም ምሳሌ ነው::

ዘመነ ክረምት የዚህ ዓለም ምሳሌ: ዘመነ መጸው ደግሞ የመንግሥተ ሰማያት:: በዚህ ዓለም ምግባር ትሩፋትን የሠራ በወዲያኛው ዓለም ተድላን ሲያደርግ ሰነፎች ኃጥአን ግን እድል ፈንታቸው: ጽዋ ተርታቸው ከግብዞች ጋር የመሆኑ ምሳሌ ነው::

በወርኀ ትፍሥሕት እንደ ሊቃውንቱ እንዲህ ብለን ልንጸልይ ይገባል::
"ድኅረ ኀለፈ ክረምት ወገብአ ዝናም: ዘአስተርአይከ እግዚኦ ጽጌያተ ገዳም:
አፈወ ሃይማኖት ነአልድ ወፍሬ ምግባር ጥዑም:
አትግሃነ ለስብሐቲከ ከመ ትጋሆሙ አዳም:
ለጽብስት ንሕብ ወነአስ ቃሕም::"

††† የዘመናት ባለቤት ዘመነ መጸውን #ወርኀ_ትፍሥሕት ያድርግልን::

†   🕊   ቅዱስ ዮናስ ነቢይ    🕊   †

††† ዮናስ ማለት 'ርግብ: የዋህ' ማለት ሲሆን ከ12ቱ #ደቂቀ_ነቢያት አንዱ ነው:: በሰራፕታ ተወልዶ ያደገው ነቢዩ በልጅነቱ ታሞ ሙቶ ነበር:: ታላቁ ነቢይ #ኤልያስ ግን 7 ጊዜ ጸሎት አድርጐ ከሞት አስነስቶታል:: (1ነገ. 17፥17) እናቱ የሰራፕታዋ መበለትም ደግ ሴት ነበረች::

ቅዱስ ዮናስ በእድሜው ከፍ ሲል የቅዱስ ኤልያስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: የነ ኤልሳዕና አብድዩም ባልንጀራ ነበረ:: ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ካረገ በኋላ: ቅ.ል.ክርስቶስ በ800 ዓመት አካባቢ የነነዌ ሰዎች ኃጢአት ከመሥፈርቱ በማለፉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ መጣ::

"ሒድና ለነነዌ ሰዎች ንስሃን ስበክላቸው" አለው:: ከነቢያት ወገን ከሙሴና ከዳዊት ቀጥሎ የዮናስን ያህል የዋህ (ገራገር) የለምና እንቢ አለ (ሰምቶ ዝም አለ):: #እግዚአብሔር እየደጋገመ ሲናገረው ግን "እንዲህ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል!" ብሎ ወደ #ተርሴስ ኮበለለ::

ወገኖቼ አንድ ነገርን ልብ እንበል:: እንኳን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዮናስ እኛ ክፉዎችም ከጌታ ፊት መሸሽ እንደማይቻል ጠንቅቀን እናውቃለን:: ታዲያ ለምን ሸሸ ቢሉ:- ጥበበ እግዚአብሔር በውስጡ ስለ ነበረበት ነው::

ምክንያቱም ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ 3 ቀን እና ሌሊት ኖሮ: ሙስና (ጥፋት) ሳያገኘው መውጣቱ ለጌታ ትንሣኤ ጥላ (ምሳሌ) ነው:: ለዚህም ምስክሩ ራሱ ጌታችን ነው::
"ወበከመ ነበረ #ዮናስ ውስተ ከርሠ አንበሪ ሠሉሰ ዕለተ ወሠሉሰ ለያልየ: ከማሁ ይነብር ወልደ እጉዋለ እመ ሕያው ውስተ ልበ ምድር ሠሉሰ ዕለተ: ወሠሉሰ ለያልየ" እንዲል:: (ማቴ. 12፥39)

ቅዱስ ዮናስ በገንዘቡ ዋጅቶ ወደ መርከብ በገባ ጊዜ ታላቅ ማዕበል ሆነ:: የእምነት ሰው ነውና እንዲያ እየተናወጡ እርሱ በእርጋታ ተኝቷል:: እነርሱ ግን ቀስቅሰው ቢጠይቁት (እጣ ወድቆበታልና) "የእኔ ጥፋት ስለ ሆነ ወደ ማዕበሉ ጣሉኝ" አላቸው::

እያዘኑ ቢጥሉት ታላቅ ጸጥታ ሆነ:: እነዚያ አሕዛብም እግዚአብሔርን በመስዋዕትና በስዕለት አከበሩ:: ዮናስ ግን በማዕበልና በአሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ለ3 ቀናት ጸለየ:: አሣ አንበሪው በ3ኛው ቀን ወደ ነነዌ ተፋው::

ቅዱሱም "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ #ነነዌ ዐባይ ሃገር" እያለ ንስሃን ሰበከ:: የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸውን አምነው ቢጸጸቱ ከሰማይ ወርዶ ከደመና ደርሶ የነበረው የእሳት ማዕበል ተመልሶላቸዋል::

የነቢዩ ትንቢት ግን አልቀረምና ታላቋ ነነዌ ከ300 ዓመታት በኋላ ጠፍታለች:: ቅዱስ ዮናስ ግን በቀሪ ዘመኑ ፈጣሪውን እያገለገለ ኑሯል:: ጠቅላላ እድሜውም 170 ዓመት ነው::

††† አምላከ ቅዱስ ዮናስ እድሜ ለንስሃ: ዘመን ለፍስሃ አይንሳን:: ከበረከቱም ይክፈለን::

††† መስከረም 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ጸአተ ክረምት (የክረምት መውጫ)
2.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ
3.ቅዱስ እንጦንዮስ
4.ቅድስት በርባራ
5.ሐዋርያት ዼጥሮስ ወዻውሎስ
6.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

††† ወርሐዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
7.ታላቁ አባ ቢጻርዮን ገዳማዊ

††† "ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ: እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ::" †††
(ማቴ. 12፥39)


† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ  ]


💚💛@sinkisar_gisawe_z_tewahedo
💚💛
    🇯 🇴 🇮 🇳 &🇸 🇭 🇦 🇷 🇪   
        ✥┈┈•◦●◈◎❖◎◈●◦•┈┈✥
  ✧━━━━━━━━━━━━━━━━━✧
      ❍ㅤ           ⎙ㅤ         ⌲ 
ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ         ˢᵃᵛᵉ          ˢʰᵃʳᵉ
††† እንኳን ለቅዱሳኑ ኤዎስጣቴዎስ: አንጢላርዮስ: ጤቅላ እና አባ ዮሐንስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †††


†   🕊   ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስና ቤተሰቡ    🕊   †

††† ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ በቀድሞዋ #ሮሜ ግዛት ውስጥ የጦር አለቃ: የከተማዋ መኮንን እና እጅግ ባለጸጋ የነበረ ሰው ነው:: ግን በእምነቱ አረማዊ: በስሙም ' #ቂዶስ' ተብሎ የሚጠራ ነበር:: ምክንያቱ ባይገባውም እጅግ ቅን: ደግና ለምጽዋት የሚፋጠን ነበር::

#እግዚአብሔር ታዲያ ይህን ሰው ወደ ቀናው ጐዳና (ወደ ክርስትና) ሊመራው ወደደና ተገለጠለት:: ቂዶስ ለአደን ወጥቶ #ዋሊያ ሲያድን (ያኔ ዋሊያ ከዓለም አልጠፋም ነበር:: ዛሬ ግን ያለ #ኢትዮዽያ ውስጥ ብቻ ነው) መድኃኒታችን በዋሊያው ራስ ላይ የብርሃን መስቀልን ገልጦ ተነጋገረው::

ክርስቲያን እንዲሆንና መከራንም እንዲታገሥ አዘዘው:: ቂዶስም ወደ ቤቱ ተመልሶ ለሚስቱና ለ2 ልጆቹ የሆነውን ነገራቸው:: ክርስትናን ተምረው ሲጠመቁ አበው ቂዶስን 'ኤዎስጣቴዎስ' አሉት::

ከዚህ በኋላ ክርስቶስን እያመለኩ ቆይተው ረሃብ በሃገሪቱ መጣ:: ቅዱሱ ምንም መኮንንና ሃብታም ቢሆንም ገንዘቡ በምጽዋት በማለቁ ባሮቹ ተበትነው ደሃ ሆነ:: የሚበላውንም አጣ:: ከሥጋዊ ሥልጣኑም ተሻረ:: እርሱ ግን ይህንን ስለ ክርስቶስ ፍቅር ታገሠ::

ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ረሃቡ ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ሚስቱንና 2 ልጆቹን ይዞ ስደት ተነሳ:: ለጉዞ በተሳፈረበት መርከብ የሚከፍለው ገንዘብ ስላልነበረው ሚስቱን ቀሙት:: ልጆቹን ይዞ እያለቀሰ ከሌላ ወንዝ ደረሰ::

እንዳይሳፈር መርከበኞቹ ልጆቹን ሊቀሙት ስለሆነ ለመዋኘት ወሰነ:: አንዱን ልጁን ተሸክሞ አሻግሮት ሲመለስ ትቶት የሔደውን ልጁን አንበሳ ወስዶት አገኘው:: እያለቀሰና እየቸኮለ ወደ 2ኛው ቢመለስ ደግሞ ይህኛውንም ተኩላ ወስዶት ነበር::

ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ አንጀቱ በሃዘን ተቃጠለ:: በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ መራራ ለቅሶን አለቀሰ:: ነገር ግን ኢዮባዊ ሰው ነውና "እግዚአብሔር ሰጠ: እርሱም ነሣ" ብሎ በእንባ ተጉዋዘ:: በአንዲት ሃገርም ባርነት ተቀጥሮ ፈጣሪውን ሲያመሰግን ኖረ::

ከብዙ ዓመታት በኋላ የረሃቡ ዘመን አልፎ የቅዱሱ ወዳጅ የነበረ ሰው በሮም ላይ በመንገሱ ወታደሮችን "ወዳጄን ኤዎስጣቴዎስን ፈልጋችሁ አምጡ" ብሎ ላካቸው:: ከአድካሚ ፍለጋ በኋላ ያ ደግ ጌታቸው በባርነት ተቀጥሮ: ተጐሳቁሎ አገኙት::

ፈጥነው ወደ ሮም ከተማ ወስደው በቀደመ ክብሩ ላይ አኖሩት:: እርሱ ግን ሃዘንተኛ ነበር:: ከቀናት በሁዋላም አዳዲስ ወታደሮችን ከተለያየ ቦታ መለመለ:: ከእነዚያም መካከል መልካም የሆኑትን 2ቱን አለቆች አደረጋቸው:: ሁለቱ ደግ ወጣቶችም በጣም ይዋደዱ ነበር::

አንድ ቀን እኒህ 2 ወጣቶች ወይን ሊገዙ ሔደው ጠባቂዋን 'ስጭን' አሏት:: ሰጥታቸው እዚያው ያወራሉ:: አንደኛው "ታሪኬን ልንገርህ" ይለዋል:: "እሺ" ሲለው "እኔ ወላጆች የሉኝም:: ሕጻን እያለሁ በሃገራችን ረሃብ መጥቶ: ሃብታችን አልቆ ስንሰደድ እናታችንን መርከበኛ ወሰዳት:: አባቴ ወንድሜን ሲያሻግረው እኔን አንበሳ ወስዶ ከአንድ መንደር ጣለኝ" አለው::

ባልንጀራው ገርሞት "ታሪካችን ተመሳሳይ ነው:: እኔም እንዳንተ ሆኜ: አባቴ ሲያሻግረኝ ተኩላ ወስዶ አንድ መንደር ውስጥ ጣለኝ" አለው:: ይህንን ትሰማ የነበረችው ወይን ጠባቂ "ልጆቼ!" ብላ ጮሃ አለቀሰችና ደነገጡ:: እርሷም ቀርባ አቅፋቸው እያለቀሰች ነገሩን ሁሉ አስታወሰቻቸው::

ይህን ጊዜ ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሰምቶ ደረሰ:: ከረጅም ዓመታት በሁዋላ ሚስቱ አትክልት ጠባቂ ሁና ማንም ሳይነካት: 2 ልጆቹንም አገኘ:: እያለቀሱ ተቃቀፉ:: እግዚአብሔርንም ፈጽመው አመሰገኑት:: የሰማ ሁሉ "ዕጹብ! ዕጹብ!" አለ::
(እኛ የምናመልከው ጌታ እንዲህ ነው:: ክብር ለእርሱ: ለድንግል እናቱና ለወዳጆቹ)

ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስና ቤተሰቡ በቀሪ ዘመናቸው ቤተ ክርስቲያን አንጸው በምጽዋት ኑረዋል:: በመጨረሻም ዘመነ ሰማዕታት መጥቶ "ክርስቶስን አንክድም" በማለታቸው ብዙ ተሰቃይተው 4ቱም በዚህች ቀን ሰማዕት ሆነዋል::

†   🕊   ቅዱስ አንጢላርዮስ    🕊   †

††† ይህ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እጅግ የታወቀ ነው:: በቀደመ ሕይወቱ "ሊቀ መጸብሐን-የቀራጮች አለቃ" ይሉታል:: እጅግ ኃጢአተኛና ጨካኝ ሰው ነበር::

አንድ ቀን ግን አንድ የኔ ቢጤ ነዳይ ከመሰሎቹ ጋር ተወራርዶ " #በእንተ_ማርያም" ብሎ ቢለምነው በደረቅ ዳቦ ራሱን ገመሰው:: በሌሊትም ራዕይ አጋንንት ነፍሱን ሲናጠቁዋት: #መላእክት ደግሞ በዛች ደረቅ ዳቦ አመካኝተው ሊያድኑት ሲሞክሩ አየ::

በዚያች ቅጽበትም ፍጹም ተለወጠ:: መጀመሪያ ሃብት ንብረቱን በምጽዋት ጨረሰ:: ቀጥሎ የሚመጸውተው ቢያጣ ነዳያንን "ሽጣችሁ ተካፈሉኝ" አላቸውና ሸጡት:: በባርነት በተሸጠበት ሃገርም በጾምና በጸሎት ተጋደለ:: እረኛ ሲያደርጉትም በደረቅ በርሃ ላይ ውሃ እያፈለቀ: ለምለም ሳር እያበቀለ ይመግባቸው ነበር:: ዘወትርም መልአክ ያጽናናው ነበር::

በሁዋላ ግን ማን መሆኑ ሲታወቅበት ሸሸ:: በመንገድም የከተማዋ ዘበኛ መስማትና መናገር አይችልምና እፍ ቢልበት ከቅዱሱ አፍ እንደ እሳት ያለ ነገር ወጥቶ ቢነካው ዳነ:: ቅዱስ አንጢላርዮስም ቀሪ ዘመኑን በበርሃ ሲጋደል ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል::

†   🕊   ቅድስት ጤቅላ ሐዋርያዊት    🕊   †

††† ይህቺ ቅድስት እናት በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ቅዱሳት አንስት አንዷ ናት:: #ቅዱስ_ዻውሎስ በእስያ የወንጌል ጉዞ ሲያደርግ ይህችን ቅድስት #መቄዶንያ ላይ አግኝቷል:: ቅድስት ጤቅላ ምንም ወላጆቿ አረማውያን ቢሆኑ: እርሷ እስከ 3 ቀናት ድረስ ያለ ምንም ምግብ ቃለ እግዚአብሔርን ትሰማ ነበር::

የብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ተከታይ ሁና በእስያ ወንጌልን ሰብካለች:: በብዙ ስቃይ ውስጥ ስታልፍም በኃይለ እግዚአብሔር እሳትን አጥፍታለች:: አንበሶችም ሰግደውላታል:: #ቅድስት_ጤቅላ ፈጣሪዋን አስደስታ በዚህ ቀን ዐርፋለች::

†   🕊   አባ ዮሐንስ ዘደብረ ጽጌ    🕊   †

††† እኒህ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ በገዳም ውስጥ ሲጋደሉ ሰውነታቸው አለቀ:: ቅዱሱ ከማረፉቸው በፊት የገዳሙ አባቶች ውሃ በጋን ሞልተው በላያቸው ላይ ቢያፈሱ አንድም ጠብታ ወደ መሬት ሳይወርድ ቀረ:: አካላቸው ከመድረቁ የተነሳ ጠጥቶት ነበርና:: ዛሬ ዕለተ ዕረፍታቸው ናት::

††† አምላከ ኤዎስጣቴዎስ ትእግስቱን:አምላከ አንጢላርዮስ ምጽዋቱን:አምላከ ቅድስት ጤቅላ አገልግሎቷን:አምላከ አባ ዮሐንስ ጽናታቸውን ያሳድርብን:: የሁሉም በረከታቸው ይብዛልን::

†††መስከረም 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስና ቤተሰቡ (ሰማዕታት)
2.ቅዱስ አንጢላርዮስ ጻድቅ
3.ቅድስት ጤቅላ ሐዋርያዊት
4.አባ ዮሐንስ ዘደብረ ጽጌ

††† ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

1.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
2.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
4.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
5.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
6.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
7.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
🕊#እግዚአብሔር_ይመስገን የሚሉ 5 ሰዎች ሲገኙ ወደ ጥያቄው የምናልፍ ይሆናል!!!
መጋቢት 4 (ድርሳነ መስቀል)

✞✞✞ እንኳን ለታላቁ ነቢይ : ጠቢብና የእሥራኤል ንጉሥ "ቅዱስ ሰሎሞን" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*"
#ቅዱስ_ሰሎሞን_ንጉሠ_እሥራኤል "*+

=>መፍቀሬ ጥበብ::
¤ጠቢበ ጠቢባን::
¤ንጉሠ እሥራኤል::
¤ነቢየ ጽድቅ::
¤መስተሣልም (ሰላማዊ) . . . እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ሰሎሞን የታላቁ ነቢይና ንጉሥ ልበ አምላክ #ቅዱስ_ዳዊት እና የቅድስት #ቤርሳቤህ (#ቤትስባ) ልጅ ነው:: ከ3ሺ ዓመታት በፊት የተወለደው ቅዱስ ሰሎሞን እስከ 12 ዓመቱ ድረስ በቤተ መንግሥት ከአባቱ ጋር አድጉዋል::

+ቅዱስ ዳዊት 70 ዘመን በሞላው ጊዜ የአካሉን መድከም አይቶ : አዶንያስ በጉልበት እነግሣለሁ ቢልም አልተሳካለትም:: #እግዚአብሔር ሰሎሞንን መርጧልና ገና በ12 ዓመቱ ነገሠ:: ልበ አምላክ አባቱ ዳዊት ነፍሱ ከሥጋው ከመለየቷ በፊት መከረው:: "ልጄ ሆይ! ልብህን ስጠኝ:: ፈጣሪህንም አምልክ" አለው::

+ቅዱስ ሰሎሞን እንደ ነገሠ በገባዖን ለእግዚአብሔር መስዋዕትን አቀረበ:: ጌታም ተገልጾ "ምን ትፈልጋለህ?" አለው:: ሰሎሞንም ልክ እንደ አባቱ ማስተዋልን : ልቡናን ለመነ:: በዚህም ጌታ ደስ ስለተሰኘ "አልቦ እምቅድሜከ : ወአልቦ እምድኅሬከ - ከአንተም በፊት : ከአንተም በሁዋላ እንዳንተ ያለ ጠቢብና ባለጠጋ ሰው የለም : አይኖርም" ብሎት ተሠወረ:: ቅዱስ ሰሎሞን ለ40 ዓመታት በእሥራኤል ላይ ነገሠ::

+ግሩም በሆነ ፍትሑ : በልዩ ጥበቡ ዓለም ተገዛለት:: እግዚአብሔር የመረጣት የእኛዋ #ንግስተ_ሳባ / #አዜብ / #ማክዳም ትፈትነው ዘንድ ሒዳ ምኒልክን (#እብነ_መለክን) ጸነሰች:: በሁዋላም #ታቦተ_ጽዮንና #ሥርዓተ_ኦሪት መጣልን:: ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን #ድንግል_ማርያም ከእነሱ ዘር እንደምትወለድ ነግሮት ነበርና ያበጀ መስሎት ሴቶችን አብዝቶ ነበር::

+ነገር ግን:-
¤አንደኛ ሰው (ሥጋ ለባሽ) ነውና::
¤ሁለተኛ ደግሞ ከብዙ ሴቶች መካከል ከአንዷ #እመ_ብርሃን የምትገኝ መስሎት ነበር:: ነገሩ መንገድ ስቶበት ከአሕዛብ (ከፈርዖን ልጅ) ጋር በመወዳጀቱ ለጣዖት አሰገደችው:: እግዚአብሔር እጅግ አዘነ::

+በራዕይ ተገልጦ "ስለ ወዳጄ ስለ #ዳዊት ስል በአንተ ላይ ክፉን አላደርግም" አለው:: ታላቁ ነቢይ ሰሎሞን ይህንን ሲሰማ ወደ ልቡ ተመለሰ:: ማቅ ለብሶ : አመድ ነስንሶ በፍጹም ልቡ አለቀሰ:: ንስሃ ገባ:: መፍቀሬ ንስሃ ጌታችንም ንስሃውን ተቀበለው::

+የይቅርታው መገለጫም ተወዳዳሪ የሌላቸውን 5 መጻሕፍት ገለጠለት:: ተናገራቸው:: ጻፋቸው:: እሊሕም:-

1.መጽሐፈ ጥበብ
2.መጽሐፈ ተግሣጽ
3.መጽሐፈ መክብብ
4.መጽሐፈ ምሳሌ
5.መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ናቸው::

+ቅዱስ ሰሎሞን ልዩ የሆነውን #ቤተ_መቅደስ በመስራቱም ይደነቃል:: ደጉ ንጉሥ : ጠቢብና ነቢይ ሰሎሞን በዚህች ዕለት በ52 ዓመቱ ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሔዷል:: (እንደ ድርሳነ መስቀል ኢትዮጵያዊ ትውፊት)

=>ከመፍቀሬ ጥበብ ቅዱስ ሰሎሞን በረከት ይክፈለን፡፡

=>መጋቢት 4 የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት

1.መፍቀሬ ጥበብ ቅዱስ ሰሎሞን

=>ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጉዋድ (ወንጌላዊው)
2.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
3.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

=>+"+ የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ:: ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ : ፀሐይ : ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ . . . አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ : ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ::
ሰባኪው:- "ከንቱ : ከንቱ : ሁሉ ከንቱ ነው" ይላል:: +"+ (መክ. 12፥1-9)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>