ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
875 subscribers
3.46K photos
103 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
#ኒቆዲሞስ

(የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት)

ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ በነበረው በኒቆዲሞስ የተሰየመ ሰንበት ነው፡፡ የአይሁድ አለቆች አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ምልክት አሳየን” እያሉ ይፈታተኑት ነበር፡፡ ስለሞቱና ትንሣኤው በምሳሌ ቢነግራቸው አልገባቸውም፡፡ ሲያስተምር ብዙዎች ያምኑ ነበር፡፡ ለአይሁድ አለቆች ግን ጭንቅ ነበር፤ የታመሙ ሲፈወሱ ሕጋችን ተሻረ ይሉ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ተአምራትና ትምህርት የአይሁድ አለቆች ክርስቶስን ለመክሰስ በሚፈልጉበት ወቅት ከአይሁድ አለቆች አንዱ ኒቆዲሞስ በቀን እንዳያደርገው አይሁድን ፈርቶ አንድም ጊዜ አላደርሰው ብሎ እንደ አይሁድ አለቆች ኢየሱስን መቃወሙን ትቶ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሄደ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነፍስ የታመሙትን በቃሉ በሥጋ የታመሙትን በተአምራቱ ሲፈውስ፤ ኒቆዲሞስ ሰምቶና ተመልክቶ “መምህር ነኝ” ብሎ በመምህርነቱ ሳይኮራ አለቅነቱን መመኪያ ሳያደርግ፡፡ በልቦናው የተሳለውን እውነትን የመፈለግ ስሜት አንግቦ ጌታው መምህሩ ዘንድ በሌሊት ገሠገሠ ዮሐ.3÷1ደርሶም ምስክርነቱን እንዲህ ሲል መስጠት ጀመረ “መምህር ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል የለምና” ዮሐ.9÷24፣ የሐዋ.ሥራ 10÷38 በማለት መመስከር ሲጀምር ጎዶሎን የሚሞላ፡፡ አላዋቂነት በአዋቂነት የሚለውጥ፡፡ ከምድራዊ እውቀት ወደ ሰማያዊ ምስጢር የሚያሸጋግር አምላክ፡፡ “ዳግመኛ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” ዮሐ.3÷6 ,1ጴጥ.1÷23 በማለት የአይሁድ መምህር ለሆነው ኒቆዲሞስ ቢያስተምረው ስለዳግመኛ መወለድ ከመጽሐፍ ቢያገኘውም ምስጢሩ አልተገለጠለትምና “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይቻላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?” በማለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

“እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዝአበሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ኤፌ.5÷26 ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና፡፡ በማለት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢያስረዳው ምስጢሩ ከአቅሙ በላይ የሆነበት ኒቆዲሞስ እንደምን ይቻላል? በማለት ጠይቋል፡፡ አበ ብዙኀን አብርሃም ከአምላኩ ሞገስን አግኝቶ፤ የሰዶምና ገሞራ ጥፋት እንዳይደርስ እያማለደ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር እንደ ነበረ፤ ኒቆዲሞስም አላዋቂነቱን አምኖ ያልገባውን ምስጢር አምላኩን የመጠየቅ ዕድል በማግኘቱ ሲጠይቅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ ግን ይህን ነገር አታውቅምን? በምድር ያለውን ስንነግራቸው ካላመናችሁ በሰማይ ያለውን ብንነግራችሁ እንደምን ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፡፡ ሙሴ ምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለ የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀላል፡፡

ያመኑበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዲጠፉ አይደለም…..” ዮሐ.3÷14፡፡ እያለ ለድኅነተ ዓለም እንደ መጣ ሰው በመብል፣ አምላኩን ከድቶ ልጅነቱን ትቶ ከእግዚአብሔር ቢለይም የሰው ልጅ ያጣውን ልጅነት ለመመለስ ስመ ግብርና ሀብተ ወልድን ለመስጠት መምጣቱን አስረዳው። “ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፡፡ አመከርከኒ ወኢተረከ በዓመፃ በላዕሌየ፡፡ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ እጓለ እመሕያው፡፡ ልቤን ፈተንከው በሌሊትም ጎበኘኸኝ ፈተንከኝም ምንም አላገኘህብኝም፡፡ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው” መዝ.16÷3 እንዳለ ቅዱስ ዳዊት ምስጢረ ሥጋዌን የድኅነት ምስጢር ገልጾለታል፡፡

በሌሊት ከአምላኩ ተምሮ ምስጢሩ የተገለጸለት ኒቆዲሞስ ፍርሃት ርቆለት ቀድሞ በአደባባይ ሄዶ መማርን የፈራ ምስጢሩ ሲገለጽለት አይሁድ በሰቀሉት ዕለት ሳይፈራ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ቅዱስ ሥጋውን ገንዞ ለመቅበር በቃ “ወአልቦ ፍርሃት ውስተ ተፋቅሮትነ፡፡ ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል ማቴ.27÷58፣ 1ዮሐ.4÷18 እንዲል፡፡ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ ያልተጠመቀ ይፈረድበታል ማር.16÷16፡፡ ባለው አማናዊ ቃል ኪዳን መሠረት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አምላክነቱ አምነን ለመንግሥቱ ዜጋ እንድንሆን ለኒቆዲሞስ ምስጢሩን ጥበቡን የገለጸ አምላክ ለኛም ይግለጽልን፡፡

#የዕለቱ_የሰንበት_መዝሙር_እና_ግጻዌ

#መዝሙር
ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ ነአምን ብከ ከመ እምኃበ አብ መጻእከ ከመ ትኩን መምህረ፤ ዕጓለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምከ አንሥአኒ በትንሣኤከ፡፡ (ስሙ ኒቆዲሞስ የተባለው ሰው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄደ፤ መምህር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ እንደመጣህ እናምንብሃለን አለው። የአንበሳ ደቦል ተኛህ፣ አንቀላፋህም፤ በትንሣኤህ አንሣኝ።)

#መልዕክታት
ሮሜ 7÷1-12
"ወንድሞች ሆይ፥ ሕግን ለሚያውቁ እናገራለሁና ሰው ባለበት ዘመን ሁሉ ሕግ እንዲገዛው አታውቁምን? ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት ሲኖር ከእርሱ ጋር በሕግ ታስራለችና፤ ባልዋ ቢሞት ግን ስለ ባል ከሆነው ሕግ ተፈትታለች።...

1ኛ ዮሐ. 4 ÷18 - ፍጻሜ
ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። .....

የሐዋ.ሥራ 5÷34 - ፍጻሜ
በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ......

#ምስባክ
መዝ.16፥3
ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፡፡
አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመፃ በላዕሌየ፡፡
ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ እጓለ እመ ሕያው፡፡
ትርጉም፦
በሌሊትም ጐበኘኸኝ፤ ልቤንም ፈተንኸው÷
ፈተንኸኝ÷ ዐመፅም አልተገኘብኝም፡፡
የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር

#ወንጌል
ዮሐንስ 3፥1-12
"ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ። መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ
የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው።....

#ቅዳሴ - ዘእግዝእትነ ማርያም [ጎሥዐ]

(#ማኅበረ_ቅዱሳን_ድረ_ገጽ እና #ግጻዌ)