ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
875 subscribers
3.46K photos
103 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
☆•• ☆ #ቅዳሴ ☆•• ☆

በቅዳሴ ጊዜ 5ቱ ምሥዋዕቶች ምን ምን ናቸው?

14ቱ ፍሬ ቅዳሴያት እነማን ይሆኑ?

ካህናት በቅዳሴ ወቅት 2: 3: 4: 5: 7: 12: ወይም 24: ሆነው ከቀደሱ ምሳሌነቱ ምን ምን ይሆን?

እኛ ክርስቲያኖች ቅዳሴን ባስቀደስን ቁጥር 4 ነገሮች እናገኛለን ምን ይሆኑ?

አምስቱ የስሜት ሕዋሳት በፀሎተ ቅዳሴ ጊዜ ያስቀድሳሉ እንዴት?
አውቀነው እንጠቀምበት ዘንድ ይነበብ.....ለሌሎች ሰማያዊ ምሥጢርን አካፍለን የተሰጠንን መክሊት እናተርፍበት ዘንድ እንትጋ +

☆•• ☆ #ቅዳሴ ☆•• ☆

ቅዳሴ በሥርዓተ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት በኅብረት የሚጸለይ የኅብረት ጸሎት ነው፡፡ ከፀሎቶች ሁሉ የላቀ የፀሎት ክፍል ነው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ ፭ቱ ምሥዋዕቶች ተሞልተው ይገኙበታል እዚህንም ፭ቱን መሥዋዕቶች ማንኛውም ክርስተያን ለፈጣሪው የሚያቀርበው ነው፡፡

፩. የቁርባን መስዋዕት፡-
+
በፀሎተ ቅዳሴ ጊዜ ውስጥ ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት ወይኑ ተለውጦ ደመ መለኮት የሚሆነው በቅዳሴው ፀሎት ነው ሳናስቀድስ አንቆርብምና የቁርባን መስዋዕት የሚፈጸመው በሥርዓተ ቅዳሴ ብቻ ነው፡፡ መስዋዕቱም በቤተልሔም ይዘጋጃል በቤተክርስቲያን ውስጥ በቤተ-መቅደስ ውስጥ ደግሞ ይቀርባል ወይም ይታደላል፡፡ ጌታችን ሲወለደ በቤተልሔም ተወልዶ ቀራንዮ ለዓለም ሁሉ መስዋዕት ሆኗልና ቀራንዮ በተባለች በቤተክርስቲያን ቅዱሱ መስዋዕት ለሕዝብ ይታደላል፡፡

፪. የከንፈር መስዋዕት፡- +

ካህኑ፣ ዲያቆኑና ሕዝቡ በመቀባበል በአንድነት ምስጋና ለፈጣሪያቸው የሚያቀርቡበት የከንፈራችን ፍሬ የሚሰዋበት የፀሎት ክፍል ፀሎተ ቅዳሴ ነው፡፡

፫. የመብራት መስዋዕት፡- +

በቅዳሴ ጊዜ የሚበራው ጦፍ ለእግዚአብሔር
የሚቀርብ የሚሰጥ የመብራት መስዋዕት ነው፡፡ ምሳሌነቱም የጌታችን
የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው ይህውም ጌታችን ጨላመ ለሆነ ዓለም
ብርሃን ሆኖ ብርሃንን ሊያበራ ወደ ዓለም መቷልና ነው፡፡

፬. የዕጣን መስዋዕት፡- +

የዕጣን ፀሎት ካህኑ ብቻ የሚያጥነው ሲሆን ይህውም በማዕጠንቱ አማካኝነት ቅዱሱን እጣን በመንበሩ፣ በቅዱሳን ስዕላቱ፣ በሕዝቡ መካከል ያጥናል ይህውም የሕዝቡን ፀሎት ወደላይ በደሥላሴ መንበር ይዞ ይወጣል በሰማይም ያሉ ቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሥላሴን መንበር እንደሚያጥኑ ሁሉ በምድርም ያለው ካህን የሰማያዊው ምሳሌ ነውና በምድር ያውን መንበር በማጠን ለእግዚአብሔር የዕጣን መስዋዕት ያቀርባል፡፡

፭. የሰውነት መስዋዕትነት፡- +

በቅዳሴ ጊዜ አብዛኛውን ሰዓት ሙሉውን ማለት ይቻላል በመቆም የሚፀለይ የፀሎት ክፍል ነው፡፡ በመሐል 2 ጊዜያት ብቻ የስገዱ ትዕዛዝ ሲተላለፍ ሕዝቡ ሁሉ ፊቱን ወደ ፈጣሪው አዞሮ እራሱን አዋርዶ ይሰግዳል በእግዚአብሔር ፊት መቆምም ሆነ መስገድ ለእግዚአብሔር የሚሰጥ የሰውነት መሥዋዕት ነው፡፡

☆•• ☆ •• ☆•• ☆

ይህ የፀሎት ክፍል (ቅዳሴ) በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላ
፩. የዝግጅት ክፍል
፪. የንባብና የትምህርት ክፍል
፫. ፍሬ ቅዳሴ
እዚህ ፍሬ ቅዳሴያት እንደየበዓሉ ይለዋወጣተሉ ብዛታቸውም ፲፬ (14) ናቸው እነዚህም፡-

፫.፩. ሥርዓተ ቅዳሴ
፫.፪. ቅዳሴ ዘሐዋርያት
፫.፫. ቅዳሴ እግዚእ
፫.፬. ቅዳሴ ማርያም
፫.፭. ቅዳሴ ዘዮሐንስ ወልደ ነጓድጓድ
፫.፮. ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምዕት
፫.፯. ቅዳሴ ዘአትናቴዎስ
፫.፰. ቅዳሴ ባስልዮስ
፫.፱. ቅዳሴ ጎርጎርዮስ
፫.፲. ቅዳሴ ዘኤጲፋንዮስ
፫.፲፩. ቅዳሴ ዘዮሐንስ አፈወርቅ
፫.፲፪. ቅዳሴ ዘቄርሎስ
፫.፲፫. ቅዳሴ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ
፫.፲፬. ቅዳሴ ዘዲዮስቆሮስ
-የጌታችን በዓል ከሆነ … (ቅዳሴ እግዚእ)
-የጌታችን ምጽአት፣ ጶጉሜ እሁድ ቀን ከዋለች ሰንበት … (ቅዳሴ አትናቴዎስ)
-የእመቤታችን በዓል ከሆነ ቅዳሴ ማርያም … (ጎሳ ልብየ ቃለ ሰናየ)
-የመላእክትና የሐዋርያት በዓል ከሆነ … (ቅዳሴ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ)
-ከዘመነ ልደት እስከ ዘመነ ግዝረት … (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ካልዕ)

☆•• ☆ •• ☆•• ☆

ቅዳሴን ለመቀደስ ብዙ ጊዜ ፭ሆነው ይቀድሳሉ ይህው የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሣሌ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከዚያም በሚያንስም ሆነ በሚበዛ ሰው ቅዳሴን መቀደስ ይቻላል ለምሳሌ ፯ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ይመስላሉ ፲፫ በ12ቱ ሐዋርያት እና በጌታችን ምሳሌ ሆነው ይቀድሳሉ፤ 24 በሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ይህ የሚሆነው እንደ ካህናቱ ብዛት ነው ጭራሽ ካህን ከጠፋ ደግሞ 1 ቄስና 1 ዲያቆን ሆነው መቀደስ ይችላሉ ሁለትነታቸው የመለኮትና የትስብዕት (የሥጋ) ምሳሌ ሆነው ይቀድሳሉ በሦስት ከሆነ በሦስቱ ሥላሴዎች አራት ከሆኑ በ4ቱ ወንጌላውያን ይመሰላሉ ከሁለት ባነሰ ግን 1 ሆኖ ግን ቅዳሴ አይቀደስም ቀኖናው የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዓት ይከለክላል፡፡

☆•• ☆ •• ☆•• ☆

“ጸልዩ” ይህ የቅዳሴው የፀሎት ዓይነት ሲሆን ለ13 ጊዜያት ይባላል፡፡
በሦስተኛው ክፍለ ቅዳሴ 4 ጊዜ ይባላል ፀልዩን ዲያቆኑ ሲያውጅ ፊቱን ወደ ህዝቡ ይመልስና እንዲጸልዩ ያውጃል፡፡ በዚህ ጊዜ ተሰጥዖ ካለ ተሰጥዖ ይመለሳል ከሌለ ግን “አቡነ ዘበሰማያት” ሕዝቡ እንዲደግሙ ያውጃል፡፡+
ለምሳሌ፡-
ንፍቁ ዲያቆን “ፀልዩ በእንተ እለያበዕኡ መባዕ … መባን ስለሚያገቡ
ሰዎች ፀልዩ” ሲል በዚህ ጊዜ አቡነ ዘበሰማያት አይደገምም ምክንያቱም
የራሱ ተሰጥዖ ስላለው “ተወከፍ መባዖሙ ለአሃው ወተወከፍ መባዖን…”
ይህ አቡነ ዘበሰማያት የሚተካ ፀሎት ነው፡፡
ድርገት ሲወርዱ “ፀልዩ በእንቲአነ” በሚባልበት ጊዜ እንድንጸልየው
የሚያዘው የዳዊትን መዝሙር 150ኛውን መዝሙር ነው፡፡ ፀልዩ ብሎ
ያዘዘው በዚህ ክፍል ያለ የዳዊትን 150ኛውን የመዝሙር ክፍል ነው
ማለት ነው፡፡

☆•• ☆ •• ☆•• ☆

እኛ ክርስቲያኖች ቅዳሴን ባስቀደስን ቁጥር
1ኛ የኃጢአት ሥርየት ይገኛል ምክንያቱም በአንቃዕዶ ሕሊና ይቅርታን ስለሚጠይቅ፣
2ኛ በነፍስም በስጋም በረከትን ያገኛል፣
3ኛ ጸሎቱም ይደመጣል፣
4ኛ የመላእክትን በረከት በቀጥታ እንሳተፋልን ቅዳሴን አስቀድሶ ሥጋ ወደሙ ሲቀበል የዘለዓለምን በረከት ያገኛል፡፡ +
በተጨማሪም ቅዳሴ በማስቀደስ
4 ነገሮች ይገኛሉ እነዚህም፡-

፩. ትምህርት+
የቤተክርስቲያኒቱን ዶግማ እና የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ትምህርት በቅዳሴ ገዚ ያገኛል፡፡ ለምሳሌ የማርያምን ቅዳሴ አባ ሕርያቆስ የደረሰውን ይህን ቅዳሴ ሲቀደስ በውስጡ ምሥጢረ ሥላሴ፣ እና ምሥጢረ ሥጋዊ እና ነገረ ማርያምን አምልቶ ይነግራል፡፡

፪. ታሪክ+
14ቱንም ቅዳሴ የሚያስቀድስ ሰው የቤተክርስቲያንን ታሪክ በቅዳሴ ውስጥ እንማራለን፡፡

፫. ምክር+
በቅዳሴ ውስጥ ተፋቀሩ፣ መጽውቱ፣ ተስማሙ፣ ጹሙ፣ ጸልዩ እየተባለ በቅዳሴ ውስጥ ሰፋ ባለመልኩ ምክር ይሰጣል ስለዚህ ቅዳሴን በማስቀደስ ምክርን ማግኝት ይቻላል ማለት ነው፡፡

፬. ተግሣጽ+
ቅዳሴ ውስጡ ተግሣጽን ይዞ እናገኝዋለን ለምሳሌ በቅዳሴ እግዚእ ላይ ከወንድሙ ጋር የተጣለ ቢኖር ይተውለት ይላል በዚህ የቅዳሴ ክፍል ውስጥ ራሳችንን ምን ላይ እንደቆምን ከሰዎች ጋር ያለንን ኅብረት ስምምነት ለፈጣሪ ራሳችንን ማስገዛታችንን እየገሠፀ ይነግረናል፡፡ እነዚህን መሠረታዊ የሆኑትን ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ቅዳሴ በማስቀደስ እናገኛቸዋለን፡፡
-ቅዳሴ ንባብም ዜማም የሚቀርብበት የፀሎት ክፍል ነው፡፡ ሁላችንም የምንሳተፍበት ቄሱም ዲያቆኑም ምእመኑም የሚሳተፉበት ነው፡፡
ፍኖተ መንግስተ ሰማያት
ይህ ቻናል ብሂለ አበው፣እራሳችንን እንድንፈትሽ የሚያደርጉ ጽሑፎች
መጋቢት 27 (በዓለ ስቅለቱ ለኢየሱስ ክርስቶስ)

በዚህ ቀን መጋቢት 27 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከወደቀበት የኃጢያት አዘቅት ሊያወጣው ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ስጋን ነስቶ ሳይገባው በበረት ተወልዶ፤ ስደታችንን ሊያስቀር ሳይገባው ተሰዶ፤ በክፉዎች አይሁድ ምክር ተከሶ በባህርይው መንገላታት የማይገባው አምላክ ለኛ ሲል የተንገላታና የተደበደበ፣ በጥፊ የተመታ፣ የተዘባበቱበት፣ ምራቅ የተተፋበት፣ እርጥብ መስቀል ተሸክሞ ከሄሮድስ ወደ ጲላጦስ እየተመላለሰ ከዚያም በቀራንዮ የራስ ቅል በምትባል ሥፍራ ተሰቅሎ ለኛ ሲል ሞታችንን በሞቱ ሽሮ በዋጋ ገዝቶናል። /ማቴ. 27፥1፣ ማር.15 ፥1፣ ሉቃ. 23፥1፣ ዮሐ.19፥ 1/

#የጌታ_ስቅለት_በአበው

"አደምን የፈጠሩ እጆቹ በመስቀል ቀኖች ተቸነከሩ ወዮ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ቀኖች ተቸነከሩ ወዮ የማይሞተው ሞተ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ የምትወዱት ሰዎች ፈጽሞ አልቅሱለት፡፡" #ቅዳሴ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

“እጆቹን እግሮቹን በተቸነከረባቸው ችንካሮች መወጋቱንም እናምናለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ እኛን ለማዳን ኃጢአታችንንም ለማሥተሥረይ መከራ ተቀበለ እንዳለ፣ በባሕርዩ ሕማም የሌለበት ሲሆን በሥጋ የታመመ ነው፤ በእርሱ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ድነናል አለ፡፡ በተገረፈና በተቸነከረም ጊዜ በመከራው ሁሉ መለኮትን ሕማም ተሰማው የሚል ሰው ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይሁን፡፡” #ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ሊቀ_ጳጳስ

‹‹የሚሠዋ በግ እርሱ ነው፤ የሚሠዋ ካህን እርሱ ነው፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ መከራንም ሁሉ የታገሠ እርሱ ነው፡፡ እንደ በግ ሊሠዋ መጣ፤ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንዳይናገር አልተናገረም፤ በአንደበቱ ሐሰት አልተገኘበትም፡፡›› #ጎርጎርዮስ1ዘኑሲስ

‹‹ታመመ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ለሥጋውያን ሞተ፤ ባሕርየ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማኅፀን ካደረ ጀምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደመሆኑ በሥጋ ይኸንን ሥርዐት ፈጸመ፡፡ ለማይመረመር ለመለኮቱ ባሕርይ እንደሚገባ ደግሞ እርሱ ኅብስት አበርክቶ ሁሉን ያጠግባል፤ አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤ አያንቀላፋም፤ አይታመምም፤ አይሞትም፤ ሕይወትን ለሁሉ ይሰጣል፡፡ ዳግመኛ በዛ በሲኦል ተገዝተው ያሉ ነፍሳትን ያድን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ በመለኮቱም ሲኦልን በዘበዘ›› #ቅዱስ_ቄርሎስ_ዘእስክንድርያ

‹‹ሙሴም ሞትን ያጠፋ ዘንድ አልቻለም፤ እርሱንም ይዞ ገዛው እንጂ፤ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ነቢያትንም ሁሉ ሞት ገዛቸው እንጂ፡፡ ክርስቶስ ግን በቸርነቱ ለሁሉ ሕይወትን ሰጠ›› #ቅዱስ_አቡሊዲስ_ዘሮም

‹‹ምትሐት ያይደለ በእውነት ተራበ፣ ተጠማ እንጂ፡፡ ዳግመኛም ከኃጥአን ከመጸብሐን ጋር በላ ጠጣ፤ ያቀረቡለትንም በላ፡፡ ራሱን አሳልፎ ለመስቀል ሰጠ፤ እጁን እግሩን ተቸነከረ፤ ጎኑን በጦር ተወጋ፤ ከእርሱም ቅዱስ ምሥጢር የተገለጠበት ደምና ውኃ ፈሰሰ /ወጣ/፡፡›› #ቅዱስ ባስልዮስ_ዘቂሳሪያ

@zekidanemeheret
#ዕለተ_ምጽአት (ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ)

አቤቱ የሚያረጅ የሚጠፋ ይህ የተስፋ ዓለም ለእኛ ለክርስቲያን ወገኖችህ አይደለም የሚመጣውን ተስፋ እናደርጋለን ደጅም እንጸናለን እንጂ። አንተ ሰማይና ምድር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም ብለሃልና።

በእለተ ምጽአት አምላክ ሲመጣ ሦስት ጊዜ ታላቅ የሆነ የመለከት መነፋት ይሆናል። ይህ የመለከት ድምጽም ሙታንን ሁሉ የሚያነቃ ነው።

በመጀመሪያው አዋጅ መለከት ሲነፋ በዓለም ዳርቻ ሁሉ የተበተነ የሥጋ ትቢያ ይሰበሰባል። በላይ ያለውና በታች ያለው በባሕር ያለውና በየብስ ያለው በአራዊትም ሆድ ያለው በልዩ ልዩ ሞት ፈጽሞ ያረጀና የጠፋ በምድር ላይ የወደቀ የሥጋ ቅርፍትም ሁሉ ወደ ቀደመ መገናኛው ይሰበሰባል።

በሁለተኛው አዋጅ መለከት ሲነፋ አጥንቶች ከሥጋና ከደም ጋር ይያያዛሉ ያለመንቀሳቀስ ያለመናወጥም እስከ ጊዜው ድረስ ፍጹም በድን ይሆናል።

በሦስተኛው አዋጅ መለከት ሲነፋ ሙታን እንደ ዓይን ጥቅሻ ፈጥነው ይነሳሉ ጻጽቃንና ኃጥአን ክፉም ቢሆን በጎም ቢሆን በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ የሠሩትን ከምድር የተከተላቸውን ሥራቸውን ተሸክመው ይነሣሉ ጻድቃንን በቀኝ ኃጥአንንም በግራህ ታቆማለህ። ለመረጥካቸውም በምሥጋና ቃል ትናገራቸዋለህ እንዲህ ብለህ፥-

እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥተ ሰማያት ትወርሱ ዘንድ ወደ እኔ ኑ ብራብ አብልታችሁኛልና፣ ብጠማ አጠጥታችሁኛልና፣ እንግዳ ብሆን አሳድራችሁኛልና፣ ብታረዝ አልብሳችሁኛልና፣ ብታመም ጎብኝታችሁኛልና፣ ብታሠር መጥታችሁ ጠይቃችሁኛልና በማለት (ማቴ. 25፥34-36) እንደተነገር ሁሉ ዳግመኛም ወደ ግራው ተመልሰህ በወቀሳ ቃል እንዲህ ትላቸዋለህ ብራብ አላበላችሁኝምና፣ ብጠማ አላጠጣችሁኝምና፣ እንግዳ ብሆን አላሳደራችሁኝምና፣ ብራቆት አላለበሳችሁኝምና፣ ብታመም አልጎበኛችሁኝምና፣ ብታሠር አልጠየቃችሁኝምና በማለት (ማቴ 25፥ 42-23) ያን ጊዜ ዓመጽና ሽንገላን ይናገር የነበረ አፍና አንደበት ሁሉ ይዘጋል። ያንጊዜ ኃዘን ይደረጋል፡ የማይጠቅም ኃዘን ነው።  ያንጊዜ ጩኸት ይደረጋል የማይጠቅም ጩኸት ነው። ያንጊዜ ፍጅት ይሆናል የማይጠቅም ፍጅት ነው። ያንጊዜ ለቅሶ ይሆናል የማይጠቅም ለቅሶ ነው። የሚያስደነግጥ የነጐድጓድ ቃል የሚቆርጥና የሚከፍል የሚለይ ብርቱ ብልጭልጭታም ወደእነርሱ ይላካል ይኸውም የኃጥአን ዕድላቸው ነው።

ያን ጊዜም ምድር አደራዋን ትመልሳለች እናትም የሴት ልጅዋን ጩኸት አትሰማም። ያን ጊዜ በሕይወትዋ ዘመን የሰራችው የነፍስ ሥራዋ ይገለጻል።

ልዑል እግዚአብሔር ሆይ ያን ጊዜ ትምረን ዘንድ ይቅርም ትለን ዘንድ በበላነው በቅዱስ ሥጋ በጠጣነው በክቡር ደምህ እንማጸንሃለን። ስለ እናትህ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብለህ ስለ ሁሉ ቅዱሳን መላእክት ጻድቃን ሰማዕታት ነቢያት ሐዋርያት እንዲሁም ደናግላን መነኮሳት እንማጸንሃለን። አምላክ ሆይ ያን ጊዜ ማረን ራራልንም ይቅርም በለን።
    
(#ቅዳሴ_ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘስሩግ)

https://t.me/zekidanemeheret
#ኒቆዲሞስ

(የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት)

ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ በነበረው በኒቆዲሞስ የተሰየመ ሰንበት ነው፡፡ የአይሁድ አለቆች አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ምልክት አሳየን” እያሉ ይፈታተኑት ነበር፡፡ ስለሞቱና ትንሣኤው በምሳሌ ቢነግራቸው አልገባቸውም፡፡ ሲያስተምር ብዙዎች ያምኑ ነበር፡፡ ለአይሁድ አለቆች ግን ጭንቅ ነበር፤ የታመሙ ሲፈወሱ ሕጋችን ተሻረ ይሉ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ተአምራትና ትምህርት የአይሁድ አለቆች ክርስቶስን ለመክሰስ በሚፈልጉበት ወቅት ከአይሁድ አለቆች አንዱ ኒቆዲሞስ በቀን እንዳያደርገው አይሁድን ፈርቶ አንድም ጊዜ አላደርሰው ብሎ እንደ አይሁድ አለቆች ኢየሱስን መቃወሙን ትቶ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሄደ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነፍስ የታመሙትን በቃሉ በሥጋ የታመሙትን በተአምራቱ ሲፈውስ፤ ኒቆዲሞስ ሰምቶና ተመልክቶ “መምህር ነኝ” ብሎ በመምህርነቱ ሳይኮራ አለቅነቱን መመኪያ ሳያደርግ፡፡ በልቦናው የተሳለውን እውነትን የመፈለግ ስሜት አንግቦ ጌታው መምህሩ ዘንድ በሌሊት ገሠገሠ ዮሐ.3÷1ደርሶም ምስክርነቱን እንዲህ ሲል መስጠት ጀመረ “መምህር ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል የለምና” ዮሐ.9÷24፣ የሐዋ.ሥራ 10÷38 በማለት መመስከር ሲጀምር ጎዶሎን የሚሞላ፡፡ አላዋቂነት በአዋቂነት የሚለውጥ፡፡ ከምድራዊ እውቀት ወደ ሰማያዊ ምስጢር የሚያሸጋግር አምላክ፡፡ “ዳግመኛ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” ዮሐ.3÷6 ,1ጴጥ.1÷23 በማለት የአይሁድ መምህር ለሆነው ኒቆዲሞስ ቢያስተምረው ስለዳግመኛ መወለድ ከመጽሐፍ ቢያገኘውም ምስጢሩ አልተገለጠለትምና “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይቻላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?” በማለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

“እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዝአበሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ኤፌ.5÷26 ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና፡፡ በማለት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢያስረዳው ምስጢሩ ከአቅሙ በላይ የሆነበት ኒቆዲሞስ እንደምን ይቻላል? በማለት ጠይቋል፡፡ አበ ብዙኀን አብርሃም ከአምላኩ ሞገስን አግኝቶ፤ የሰዶምና ገሞራ ጥፋት እንዳይደርስ እያማለደ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር እንደ ነበረ፤ ኒቆዲሞስም አላዋቂነቱን አምኖ ያልገባውን ምስጢር አምላኩን የመጠየቅ ዕድል በማግኘቱ ሲጠይቅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ ግን ይህን ነገር አታውቅምን? በምድር ያለውን ስንነግራቸው ካላመናችሁ በሰማይ ያለውን ብንነግራችሁ እንደምን ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፡፡ ሙሴ ምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለ የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀላል፡፡

ያመኑበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዲጠፉ አይደለም…..” ዮሐ.3÷14፡፡ እያለ ለድኅነተ ዓለም እንደ መጣ ሰው በመብል፣ አምላኩን ከድቶ ልጅነቱን ትቶ ከእግዚአብሔር ቢለይም የሰው ልጅ ያጣውን ልጅነት ለመመለስ ስመ ግብርና ሀብተ ወልድን ለመስጠት መምጣቱን አስረዳው። “ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፡፡ አመከርከኒ ወኢተረከ በዓመፃ በላዕሌየ፡፡ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ እጓለ እመሕያው፡፡ ልቤን ፈተንከው በሌሊትም ጎበኘኸኝ ፈተንከኝም ምንም አላገኘህብኝም፡፡ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው” መዝ.16÷3 እንዳለ ቅዱስ ዳዊት ምስጢረ ሥጋዌን የድኅነት ምስጢር ገልጾለታል፡፡

በሌሊት ከአምላኩ ተምሮ ምስጢሩ የተገለጸለት ኒቆዲሞስ ፍርሃት ርቆለት ቀድሞ በአደባባይ ሄዶ መማርን የፈራ ምስጢሩ ሲገለጽለት አይሁድ በሰቀሉት ዕለት ሳይፈራ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ቅዱስ ሥጋውን ገንዞ ለመቅበር በቃ “ወአልቦ ፍርሃት ውስተ ተፋቅሮትነ፡፡ ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል ማቴ.27÷58፣ 1ዮሐ.4÷18 እንዲል፡፡ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ ያልተጠመቀ ይፈረድበታል ማር.16÷16፡፡ ባለው አማናዊ ቃል ኪዳን መሠረት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አምላክነቱ አምነን ለመንግሥቱ ዜጋ እንድንሆን ለኒቆዲሞስ ምስጢሩን ጥበቡን የገለጸ አምላክ ለኛም ይግለጽልን፡፡

#የዕለቱ_የሰንበት_መዝሙር_እና_ግጻዌ

#መዝሙር
ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ ነአምን ብከ ከመ እምኃበ አብ መጻእከ ከመ ትኩን መምህረ፤ ዕጓለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምከ አንሥአኒ በትንሣኤከ፡፡ (ስሙ ኒቆዲሞስ የተባለው ሰው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄደ፤ መምህር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ እንደመጣህ እናምንብሃለን አለው። የአንበሳ ደቦል ተኛህ፣ አንቀላፋህም፤ በትንሣኤህ አንሣኝ።)

#መልዕክታት
ሮሜ 7÷1-12
"ወንድሞች ሆይ፥ ሕግን ለሚያውቁ እናገራለሁና ሰው ባለበት ዘመን ሁሉ ሕግ እንዲገዛው አታውቁምን? ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት ሲኖር ከእርሱ ጋር በሕግ ታስራለችና፤ ባልዋ ቢሞት ግን ስለ ባል ከሆነው ሕግ ተፈትታለች።...

1ኛ ዮሐ. 4 ÷18 - ፍጻሜ
ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። .....

የሐዋ.ሥራ 5÷34 - ፍጻሜ
በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ......

#ምስባክ
መዝ.16፥3
ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፡፡
አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመፃ በላዕሌየ፡፡
ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ እጓለ እመ ሕያው፡፡
ትርጉም፦
በሌሊትም ጐበኘኸኝ፤ ልቤንም ፈተንኸው÷
ፈተንኸኝ÷ ዐመፅም አልተገኘብኝም፡፡
የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር

#ወንጌል
ዮሐንስ 3፥1-12
"ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ። መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ
የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው።....

#ቅዳሴ - ዘእግዝእትነ ማርያም [ጎሥዐ]

(#ማኅበረ_ቅዱሳን_ድረ_ገጽ እና #ግጻዌ)