ሰንፔር ሚዲያ Sapphire Media
433 subscribers
297 photos
4 videos
8 files
109 links
መንፈሳዊ መጣጥፎችን ግጥሞችን ወጎችን አጫጭር ልቦለዶች አስደናቂ ታሪኮችን ትምህርታዊ ፅሁፎችን ለማግኘት ይቀላቀሉን።

"ትውልድ ሆይ ወደ እግዚአብሔር ቃልና ወደ ተሰቀለው ክርስቶስ ተመልከቱ!!!"


https://youtu.be/KRKo3x7iYNw

http://Instagram.com/sapphiremedia4god

tiktok.com/@sapphiremedia1
Download Telegram
ነገ እንገናኝ 🙏
"እኔ ላይ የተላከው ሰይጣን ረቂቁ ሳይሆን መሃይሙና ጨቋኙ ይመስለኛል"
                           * * *

ከጉራጌ ገጠር የተገኘ ነው።  ቤተሰቦቹ የተፈሩ ባለውቃቢ ነበሩ። ይህ ብቻ ሳይሆን ገና የሰባት አመት ልጅ ሳለ የወደፊቱ ታላቅ ባለውቃቢ እንደሚሆን ተነግሮለታል። 

"የትልቁ ውቃቢ ተሸካሚ የሆኑት ባለውቃቢ  ሲሞቱ መንፈሱ እርሱ ላይ ያርፍና ታላቅ ባለውቃቢ ይሆናል" ተብሎለታል። በዚህም ሰበብ ገና ጨቅላ ሳለ ጀምሮ 'ወሰድ መለስ' የሚያደርገው 'ወፈፌ' ሊሆን ችሏል።

ህፃን ሳለ በባዕድ አምልኮ የታሰሩ ወደ ባዕድ አምልኮ ስፍራ ሲመጡ እርሱ ብርቱ አገልጋይ ሆኖ ይሰለፋል። እንጨት ይፈልጣል፥ ወንዝ ወርዶ ውሃ ይቀዳል፥ በማምለኪያ ግቢው ከሚገገኘው የጫት ዛፍ ጫት ቀንጥሶ ያቀርባል፥ በርከክ ብሎ 'የአምላኪዎቹን' እግር ያጥባል፥ ቡና አፍልቶ ለተሳታፊው በማደል ስራ ይሰማራል።

በብርቱ መታተር ውቃቢውን ቢያገልግም በውቃቢው የሚመሰገን አይደለም። ሲመሻሽ የጭንቅ ለሊት ይጀምራል። በብዙ  ይሰቃያል፥ ያውጓል፥ ደግሞም ይቃዣል።
"ታዛዥ አገልጋይ ሆኖ ሳለ እንዲህ መሰቃየቱ ለምን ሆነ?" የሚል ጥያቄ በቤተሰቡ አእምሮ ቢፈጠርም ልጃቸውን ለማፅናናት የሚሆን ቃል አያጡም። "ትልቅ ሰው እየሆንክ ስለሆነ ውቃቢው ሊዋረስህ ነው፥ ስቃይህ በዚህ የተነሳ ነውና ታገስ" ይሉታል።

ከቀናት በአንዱ ፥ እንደማንኛውም አዳጊ ልጅ አጎቶቹ ዘንድ ተልኮ  ሲሄድ ለየት ያለች ሴት ተመለከተ።

ሴቲቱ ጭንቅላቷ አነስተኛ፥ አንገቷ አጭርና ወፍራም ፥ከትከሻ እስከዳሌዋ ወፍራምና ቅርፅ አልባ ነች። ከቀኝ ትኬሻዋ ወደ ግራ ዳሌዋ አሮጌ ጨርቅን አሸርጣለች። ማንኛውም ሰው ሲራመድ በእጆቹ አየር ይቀዝፋል። ይቺ ግን እጆቿ አይንቀሳቀሱም። መላ ነገሯ ያልተለመደ ነው። ታዳጊው ሴትየዋን በአስተውሎ ከተመከተ በኋላ ተሸበረ። በፍርሃት ወደመጣበት ሊመለስ እያሰበ ሳለ ሴቲቱ ድንገት ተሰወረች።

ደግሞ ሌላ ቀን፥

ከእኩያ ጓደኞቹ ጋር ከብት ሊያግድ ተሰማራ። ይሄኔ ለሱ ብቻ አንድ ሰው ታየው።
ሰውዬው ለመግለፅ በሚከብድ ልክ ቀጫጫ ሲሆን ወንዝ መሃል ሹል  ድንጋይ ላይ ተቀምጦ ሰውነቱን እያከከ ይታጠባል። በነገሩ ግራ የተጋባው ብላቴና የተመለከተውን ለጓደኞቹ ሊያሳይ ዘወር ከማለቱ  ሰውዬው ተሰወረ።

በተደጋጋሚ የሚሆነው ክስተት ቤተሰቡን በማስጨነቁ መፍትሔ ተፈለገ። መላ ለማበጀትም በአባቱ መኖሪያ ካለ ወንዝ እንዲወሰድ ተወሰነ።

ዘወትር ረቡዕ ከለሊቱ 11 ሰኣት ሲሆን ማንም ወንዙን ሳይሻገር ወደ ወንዙ ይደርሳሉ።
ታዳጊው ልጅ አንዴ ወደ ወንዙ ከተነከረ በኋላ ወደ ዳር ይወጣና በአሻዋ ሰውነቱ ይታሻል። ከአሸዋ መታሸት ቀጥሎ ድጋሚ ይነከራል፥ መልሶም  በአሸዋ ይታሻል። ለሦስት ዙሮች በውሃው እየተነከረ በአሸዋ ከታሸ በኋላ በውሃ ይለቀለቃል። ይህ ሲሆን ከአሸዋው ጋር የሚቀላቀሉ ጥቃቅን ሹል ድንጋዮች የታዳጊውን ገላ እየሸነታተሩ ቁስል የሚፈጥሩ ሲሆን ወደ ውሃው በተነከረ ቁጥር ለከፍተኛ ስቃይ ይዳረጋል።

ድርጊቱ የአንድ ጊዜ ወይም ለተወሰነ ጊዜ የሚደረግ አይደለም!  ለ 49 ተካታታይ  ሳምንታት ሳይታጎል ይቀጥላል።
49 ሳምንታት በውሃ መነከርና በአሸዋ መታሸቱ ከተከወነ በኋላ በ50ኛው ሳምንት የመደምደሚያ ስርኣት ተከወነ።

በ50ኛው ረቡዕ ዥንጉርጉር ነብር መሳይ ፍየል ተፈልጎ ከተገኘ በኋላ የ10 አመቱ ብላቴና ፍየሉን ተሸክሞ ወደ ወንዝ ወረደ። ቀጥሎ የፍየሉን ደም ስር በጥሶ እንዲያደማ ታዘዘ። የፍሉን ደም ስር ለመበጠስ ስለት መጠቀም አይፈቀድለትም፥  መበጠስ ያለበት ጥርሱ ነው።

በበርቱ ትግል ፍየሉን ማድማት ተሳካለት።

ፍየሉ እንዲታረድ ከተደረገ በኋላ በአሸዋ የመታጠብና በውሃ የመነከር  ትርዒቱ ቀጠለ። ከአሸዋና ውሃ መነከር ድርጊት ቀጥሎ በፍየሉ ደምና ፈርስ ታጠበ።

ከጠቦቱ ስጋ አንዳች አልቀመስም። የዚህ ሰበቡ መናፍስታዊ እምነት ነበር። ፍየሉ የብላቴናውን ልክፍት ስለወሰደለት ስጋዋን ቢበላ ልክፍቱ ዳግመኛ ያገኘዋል በሚል እምነት ነበር ከመብል የተከለከለው።

ታዳጊው ልጅ ከገደል ራሱን ወርውሮ ስለመግደል ያሰበበት ወቅት ነበር። ሆኖም ከገደሉ ከወደቀ በኋላ ሳይሞት ቢቀር ለዘመናት በአካል ጉዳተኝነት ሊሰቃይ እንደሚችል በማመን ሃሳቡን ሰርዞታል።

ከሐገር ቤት ወደ አዲስ አበባ ካቀና በኋላ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፏል። በሰው ቤት በአሽከርነት በሚሰራበት ወቅት ተደብድቧል፥ ደግሞም የላቡን ውጤት ተከልክሎ ያውቃል።

ይህ ብላቴና ከአመታት በኋላ ይህን ሁሉ  ውጣ ውረድ አልፎ ታላቅ የወንጌላውያን አገልጋይ ሆኗል። ያለፈ ስቃዩን ሲያስታውስ "ልጅ ሳለሁ ለኔ የተመደበው ሰይጣን ረቂቁ ሳይሆን ጨቋኙና አምባገነኑ ይመስለኛል" እያለ ይቀልዳል።

ይህ ታሪክ የስመ ጥሩው አገልጋይ ፓስተር ታምራት ሃይሌ የልጅነት ህይወት ነው!

ማጣቀሻ መፅሐፍ ፥ ፓስተር ታምራት ሃይሌ "የታምራት አምላክ ታምረኛ"


© ተስፈኣብ ተሾመ
<<ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?>>

<<ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ።>> ዩሐ.13፥12-17

~~~~
[ትህትና ሊያስተምረኝ ወዶ
እግር አጠበ ባሪያውን ወርዶ
እራሱን አዋርዶ]
~~~

በአቧራማዋ እስራኤል በነጠላ ጫማ (Sandals) መንቀሳቀስ የተለመደ ነበር። የጋራ ምግብ ከመቅረቡ በፊት ደግሞ ሰው እግሩን ታጥቦ ነው የሚቀመጠው፣ እጅ መታጠብ በኛ ዘንድ እንደተለመደው። ምክንያቱ ደግሞ ጠረጴዛው ዝቅ ያለ (low table) ስለሆነ ነው። ኢየሱስ ተነስቶ እግራቸውን ሲያጥብ የመጨረሻው ተራ ሎሌ ባሪያ የሚያደርገውን እየከወነ ነበር። ደቀመዛሙርቱም ራሱን 'በማዋረዱ' ሳይገረሙ አይቀሩም። የነፍሳችን ጌታና መሲህ፣ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ፣ የአለምን ኅጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ... ሲሉት የከረሙት ሰዎች እግሩን ማጠብ ሲጠበቅባቸው እሱ ቀድሞ እግራቸውን ለማጠብ ማበሻ ማንሳቱ ባያስደንቃቸው ነው የሚገርመው። ምንም እንኳን እንደ ምድራዊ ንጉስና ነፃ አውጪ መጠበቃቸው የሚያደርጋቸውን እያንዳንዱን ድርጊቶቹን በአግባቡ ለመገንዘብ ቢከብዳቸውም፤ እንደ ስቅዩ-ሎሌ (suffering Servant) መምጣቱን አርፍደው ነው የተገነዘቡት (ኢሳ. 53)።

~~~~~~~
[ደቀመዛሙርቱ እግራቸው ቆሸሸ
አደፈ ጎደፈ ፍጹም ተበላሸ
ሁሉን የፈጠረ ሰውን የወደደ
ጭቃውን ሊያስወግድ ወደ ታች ወረደ]
~~~~~~

ምጡቅ የሆነ፣ ሁሉን የሚገዛና ሁሉ በሁሉ የሆነ አምላክ እግር ሊያጥብ ዝቅ አለ፣ ከአቧራማ እግሮች ስር ተገኘ። "ፍጹም የቆሸሸን" ሰው ለማንፃት ፍጹም ንፁህ የሆነው ወልድ ራሱን ባዶ በማድረግ ወደ ታች ወረደ (ፊል. 2፥6-11)። ቃል መገለጡና በውርደት መንቀሳቀሱ አስደናቂ ነበር። የእግዚአብሔር ልጅ የህማም ሰው በመሆን፣ ቤት አልበኛ በመሆን፣ የድኻ ወዳጅ በመሆን፣ የኅጢአተኛ ወዳጅ በመሆን የተሰበረውን አለም ራሱን በመስቀል ለመስበር ተገኘለት። እንዴት ያለ የትህትናና የፍቅር ጥግ አሳየን!

የእግራቸውን ቁሻሻቸውን ሲያፀዳ፣ አደፋቸውን ሲያጠራ ፈለጉን እንድንከተል ይመስላል "ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?" ብሎ የጠየቀን። አለሙ በኅጢአቱ ሲዳሽቅ ራሱን ለመላ አለሙ የቆረሰው ጌታ፣ ከአለሙ ድካምና ደዌ ራሱን ሳይሸሽግ የተገመሰለት አምላክ በድርጊቱ የምንቆርሰው እውነትን ችሮናል።

~~~
[እሱ ያላጠበው ከእርሱ ጋር አይኖርም
አይቆርስም ከአምላክ ጋር አንድነት የለውም
ጴጥሮስ ይህን አይቶ ሰውነቴን ደሞ
እጠበኝ ጌታ ሆይ አለውም ተማጽኖ]
~~~~~

ኢየሱስ ስለራሱ ከነበረው ግንዛቤ አንዱ የሚያደርገውን የሚያደርግበት ምክንያትን ጠንቅቆ ማወቁ ነው።በኢየሱስ ያደረገው ስለራሱ በማቴ. 20፥28 እንዳለው "ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።" ራሱን ዝቅ አድርጎ ሌሎችን ሊያገለግል ነው የመጣው። ከግዞት በኋላ እስራኤል ያጣችውን ፖለቲካዊ ነፃነትን ለእስራኤል ለመቸር ሳይሆን በኅጢአት ግሳንግስ የታፈነውን አለም ከህማሙ ለመፈወስ ነው የመጣው። እግዚአብሔር ለእስራኤል ብሎም ለአሕዛብ የሰጠውን ተስፋ በእርሱ የሚፈጸምበት እግዚአብሔር "ምርጤ፣ ባሪያዬ" ያለው መሆኑ በአግልግሎቱ ቁልጭ ብሎ ይታይ ነበር። ለዚህ ነው የገዛ የራሱን ዐለም ከውልደቱ ጀምሮ በትህትና፣ በዝቅታ፣ በመዋረድ፣ በመከራና ፍዳን በመቀበል ያናገረው። ብቸኛው ቋንቋ መስቀል የሆነው። ከማገልገሉም ባሻገር ሕይወቱ እንደሚነግረን በትህትና መሞላቱን ነው። ከአመጣጡ እስከ አሟሟቱ ድረስ ድንቅ በሆነ ትህትና የተሞላ ነው።

~~~~
[በሚደነቅ ብርሃን የሚኖር ፈጣሪ
አልፋና ኦሜጋ የፍጥታት ሰሪ
ማበሻ ጨርቅ ወስዶ እግር ሊያጥብ ወረደ
ዝቅ አ'ረገ ራሱን ለሰው ተዋረደ]
~~~~

የኢየሱስ ዝቅ ብሎ እግር ማጠቡ ዘማሪ ደረጄ ከበደ እንዳለው "ትህትናን ሊያስተምረኝ ወዶ" ነው። ያደረገልን ራሳችንን በትህትና ዝቅ አድርገን የባልንጀራችንን እግር እንድናጥብ ነው። ጉድፉን እንድናጠራ፣ ከክፉና እኩይ እንድንከላከለው እንዲሁም ራሳችን ለባልንጀራችን አሳልፈን እንድንሰጥ ነው። "በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ" በእኛ እንዲኖር ነው። እግር ጉድፍ ሲያነሳ እንድንጠርገው በዚያም ትህትናችን እንዲታይ ተጠርተናል።

~~~~~~~
[የሁሉ ማሰሪያ አላማ ያለው ነው
ጌታ ይህን አድርጎል እኔስ እንደምን ነው?
የወንድሜን እግር እስካጥብ ዝቅ ካልኩ
እውነትም 'የሱስን በእርግጥ ተከተልኩ]
~~~~~

ኢየሱስ የደቀመዛሙርቱን እግር አጥቦ ሲጨርስ "እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና" ብሏቸዋል። በሚደንቅ ብርሃን የሚኖር ምጡቅ አምላክ እግር ለማጠብ ማበሻ ጨርቅ ወስዶ የታናናሾችን ስራ ከሰራ እኛማ እንዴት ፈለጉን አንከተል?! እንደ ክርስቶስ ተከታይ እሱን በህይወቱ ልንመስል ይገባልና፣ ትሁት መሆን አለብን። የክርስቲያን መለኪያው ክርስቶስን መምሰል ነው። ዝቅ ማለት፣ ራሱን ማወረድ፣ ራሳችንን የሚጠቅመውን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሚጠቅመውንም ማድረግን ከጌታ ልንማር ይገባናል።የዝቅታን መንፈስ ይስጠን!

~~~~~~~
[ባሪያ ከሚያኖረው አይበልጥም አላቸው
መልክተኛም አይበልጥ ይልቁን ከላከው
እንግዲህ ጌታችሁ እኔ ይህን ስፈጽም
አድርጉት ለሁሉም ዛሬ ሁኑ እናንተም]
~~~~~~

ባሪያ ከጌታው እንደማይበልጥና እኩልም እንዳይደለ ሁሉ ጌታ የፈፀመው ድርጊት እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች ልንከተለው የተገባ ነው። እግር ማጠብ ግዴታ እግር ማጠብ አይደለም። ክብርን መተው፣ ራስን ዝቅ ማድረግ፣ ራስን ማዋረድ፣ ራስን ለሌሎች መቁረስ፣ ትህትና ነው። ጌታ ያደረገውን እርስ በእርስ እያንዳንዳችን እናደርገው ዘንድ የተገባ ነው። የክርስቲያን መለያው፣ የአማኝ መታወቂያው የክርስቶስን ፈለግ መከተሉ እስከሆነ ድረስ አንዳችን ለሌሎቻችን ራሳችንን ዝቅ በማድረግ ማገልገል ይገባናል።

Every good thing in the Christian life grows in the soil of humility. Without humility, every virtue and every grace withers. That's why Calvin said humility is first, second, and third in the Christian faith.
John Piper

እዚህ ጋር አንድ ዝማሬን እንዘምራለን፣ አብረን በፀሎት እንቃትታለን :-

[ከከበረው እንቁ ሰው ከሚሻማበት
እኔስ ትህትናን ባገኝ በዚ'ች ዕለት
ጥማቴም ፀሎቴም ዝቅ ዝቅ ማለት]
~~~~~

<<ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?>> ዩሐ. 13፥12

መልካም ፀሎተ ሐሙስ!
መልካም ቀን!

© አማኑኤል አሰግድ
እንደምን ጨካኝ ነው በልጁ ይሉኻል፣
ኃጢአትን ሰቅለው ወንበዴዎች መኻል!
.
ደካማ ነው አሉ ልጁን ካላዳነ፣
ሕዝብን ባንድ አድኖ ደም እየከደነ!
.
ይህ ተርታ ሕዝብ ኹሉ ተባብሮ ባንድ ቃል፣
"ራስህን አድን" ብሎ ይሣለቃል፣
ነገ በሱ ሊድን መኾኑን መች ያውቃል?

#ሰሙነ_ሕማማት

© Abere Ayalew
የዛሬ ሳምንት በሀዋሳ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን
እዩ ተመልከቱት ፤ የክርስቶስን መስቀል
ዛሬም ሲፈውስ ፤ የነፍስን ቁስል።

© ቢቶ
ኢየሱስ ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም አቅንቷል። ተከታዮቹ ፍርሃት እስኪገባቸው ድረስ ፍጥነቱ ጨምሯል “ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ኢየሱስ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ተገረሙ፣ ሌሎች የተከተሉት ደግሞ ፈርተው ነበር።” (ማር 10፥32)። በማርቆስ ወንጌል ትራኬ ውስጥ፥ ኢየሱስ አንድ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጣል፣ እርሱም ብዙ መከራ ይቀበላል፣ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት ይናቃል፣ ይገደላል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ ይነሣል። ማቴዎስም ኾነ ሉቃስ ይህንን የማርቆስን ትራኬያዊ አቅጣጫ በቅርበት ይከተሉታል። ነቢዩ ኢሳያስ “የጌታን መንገድ አዘጋጁ” እንደሚል፣ ይህ መንገድ ተጠርጓል፣ ጌታም እየተራመደበት ይገኛል። ይህ ሥጋ ለባሽ ኹሉ ወደ ሚመለከተው ክብር የሚወስደው መንገድ የሚያመራው ወደ ቀራንዮ ጎልጎታ ነው።

ታዲያ፣ኢየሱስ በዚህ መንገድ ላይ ሳለ ፦

  1. ሶስት ጊዜ ስለ መከራው፣ ሞቱና ትንሳኤው አስቀድሞ ይተነብያል (ማር 8፥31፣ 9፥31፣ 10፥33-34)።

  2. ሶስቱንም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ለዚህ ትንበያ ምላሽ ይሰጣሉ (8፥32፣ 9፥33-34፣ 10፥35-41)። ሆኖም ግን የሚሰጡት ምላሽ የእርሱን ተልዕኮ  እንዳልተገነዝቡ ያሳያል። ጴጥሮስ ኢየሱስን “ይገሥጸው ጀመር” (8፥32)፣ ሐዋርያት “ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው” እያሉ ይከራከራሉ (9፥34)፣ የተወሰኑትም “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ፣ ይህንን ያደመጡም በመቀደማቸው ይቆጣሉ (10፥37)።

  3. ሶስት ጊዜም ኢየሱስ እርሱን መከተል ምን ማለት እንደኾነ የደቀ መዝሙርነትን ምንነት እየገሰፀ ያስተምራቸዋል (8፥34-37፣9፥35-37፣ 10፥42-45)። ዐይነ ስውሩን ሁለት ጊዜ እደፈወሰው (8፥22-26) ደቀ-መዝሙርቱም እንዲኹ ሁለት ጊዜ መዳሰስ እስኪያስፈልጋቸው ድረስ ታውረዋል፣ ልባቸው ደንዝዟል። የኢየሱስ ተልእኮ አልገባቸውም ነበር።

1. “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (8፥34)

2. “መጀመሪያ ለመሆን የሚፈልግ፣ ከሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ ይሁን” አላቸው” (9፥35)

3. “ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን፤ "ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና።” (10፥43–45)

እንዳንዘነጋ፣ ይህ ቀን ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ቤዛ የኾነበት ቀን እንደኾነ ኹሉ፣ የእርሱን ፈለግ የምንከተልበትም ቀን ነው።

ኢየሱስ ሞቶ ከተነሣ በኋላ፣ እነዚህ ደቀ መዛሙርት የደቀ መዝሙርነት ትርጕም ገባቸው። ከራሳቸው በላይ ዝቅ ብለው ሌሎችን አገለገሉ። አልፎም እነርሱም እንደ ጌታቸው ለመሰቀል፣ ለመሠየፍና ለመወገር ፈቃደኞች እስኪሆኑ ለሌሎች ኖረው አለፉ።

የማርቆስ ጥያቄ አሁን ያነጣጠረው በእኛ ላይ ነው! ተልእኮው ገብቶናል? የደቀ-መዝሙርነት መንገዱ ገብቶናል? ግን ገብቶናል?

የማርቆስ ግሣጼ፣ ኢየሱስ ‘ተልእኮው ያልገባቸው ተከታዮች የሉትም’ የሚል ነው።

ሳምሶን ጥላሁን
በሀዋሳ አዲስ ከተማ ሙሉ ወንጌል የወጣቶች የድራማና የስነፅሁፍ ህብረት የተሰናዱ ሁለት ዝግጅቶች

#ብኤርለሃይሮኢ
ቀን: ነገ ማክሰኞ ሚያዚያ 29
ቦታ:በሀዋሳ አዲስ ከተማ ሙሉ ወንጌል
ሰዓት: 11:00

#ሎዶቅያዊት
ቀን: ግንቦት 02
ቦታ:በሀዋሳ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን
ሰዓት: 11:00
የመዝሙር ምህዳራችን ቢሰፋስ?
ዝማሬና መንፈሳዊ ቅኔ ለክርስቶስ ማሕበረሰብ ንዋየ ቅዱሳቱ ነው። የአምላኩን ትድግና፣ በክብር ከፍ ማለቱን፣ የመጥራቱንም ተስፋ፣ በቅዱሳንም መካካል ያለን የርስት ባለጠግነት እንዲዘምር በአምላኩ ተጠርቷልና። በዘመናት መኻልም በነበሩት የዜማ እቃዎች የክርስቶስ ማሕበር ይኼን ስርየት፣ ይኼን ተስፋ፣ ይኼን የምስራች ሲዘምር ከርሟል። ስለዚህም እግዚአብሔር ይመስገን።

እርሱ ከጨለማው ስልጣን ስላዳነን፣ የሞትንም ቀንበር ስለ ሰበረልን፣ ወደ ብርሃኑም ስለ መጣን እንዘምራለን። ዝማሬያችንም ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን ዳስሷል። ግላዊ በኾኑ ፈተናዎቻችንና ድሎቻችን ጉዳይ ዘምረናል። እንደ እምነት ማሕበረሰብ በሕብረት ስለኾነልንም ስለኾነብንም ምስጋናና ምልጃን አቅርበን እናውቃለን። ይኼም ልከኛ ነው ብዬ አምናለሁ። የዚህ ልጥፍ አላማ በዝማሬዎቻችን ሚዳሰሱት ርእስ ጉዳዮች ክበባቸው እንዲሰፋ መሞገት ነው።

ድነታችን ኹለንተናዊ ከኾነ፣ ወንጌላችንም ለኹለንተና የተሰበከ ከኾነ፣ እምነታችንም የማይነካው የኑረታችን ክፍል ከሌለ በዜማ ምናቀርበውም ዝማሬ መዳረሻው ሰፊ መኾን አለበት ብዬ አምናለሁ። ሃጢያት መልኩ ሰፊ ከኾነ( personal, corporate and structural) አልፎም sin of omission እና commission'ን ከጨመረ፤ በውጤቱም ኹለንተናችንን ካንኮታኮተ፤ አምላካችንም በቸርነቱ መድሃኒትን ከላከልን፣ መድኅናችንም በደሙ ከተቤዠንና ለአዲስና ህያው ተስፋ እንደ ምሕረቱ መጠን ዳግም ከወለደን የኑረትን ብዙ ገጾች በዜማችን ለመዳሰስ ምንገደድ ይመስለኛል። ለምሳሌ በሰማያት ያለ አባት አለን እያልን፣ አብ አባት ብለን ምንጣራበት የልጅነት መንፈስም ተቀብለን፣ ከእናትም በላይ አምላካችን ይራራልናል እያልን፣ በማደጎ ቤተሰብ እንድኾን ረድኤታችን ዋጅቶናል እያልን በዝማሬዎቻችን ውስጥ ቤተሰብን አለማንሳታችን ልክ አይመስለኝም። እናት አባትህን አክብር እድሜህ በምድር ይረዝማል የሚልን ግልጽ መመሪያን ይዘን ወላጆችን ስለ ማክበር በዜማ አለማቀንቀናችን ተገቢ መስሎ አይታየኝም። ድነት Ecclesial ብቻ ሳይሆን cosmological ነው እያልን ፍጥረተ ዓለሙ በጭንቅ ስለ መያዙ ደግሞም ስለ ማቃሰቱ ትንፍሽ አለማለታችን የጤና አይደለም። ሰማያት ክብሩን የሰማይም ጠፈር የእጆቹን ስራ በግልጥ ይለፍፋሉ እያልን መደነቂያችን ወደ ጫማ ዝቅ ማለቱ መንሻፈፍ ይመስለኛል። ስለ ብዙ ነገር ቀድመን መዘመር የነበረብን እኛ ነን ብዬ አምናለሁ። በጦርነት በምትታመስ ሀገር እየኖርን፤ ሚያስተራርቁም ብጹአን ናቸው የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ እያልን ለእርቅ ሚኾን በዜማ የቀረበ ተማጽኖ ከኛ አለመጀመሩ ልክ አይመስለኝም። አምላካችን ለተገፉ ተገን ነው፤ መጠለያ ለቸገራቸው መጠጊያ ነው እያልን በግፍ ለሚሰደዱና ከቀዬአቸው ለሚፈናቀሉ ማጽናኛ ዜማ ከኛ ከአማኞች አለመሰማቱ ጥፋት ነው። ባጭሩ የዝማሬ አድማሳችን ደግሞም ምህዳር ኹለንተናን ሚነካ እንዲኾን መስራት ያለብን ይመስለኛል። በአምላካችን ማዳን ያልተነካ የኑረት ክፍል ሊኖረን አይገባም! ነገ እግዚአብሔር ቢፈቅድና በሕይወት ብንኖር በዚህ ረገድ ፍር ቀዳጅ ናቸው የምላቸውን አንዳንድ ዝማሬዎች አንስቼ ጥዊት እላለሁ። ልኡል አምላክ ለአካሉ መታነጽ ደግሞም ለአደባባይ ምስክርነታችን ያመነውን ኹሉ የምንዘምርበትን፤ መልእክታችንም ሙሉ ሚኾንበትን ጸጋ ይስጠን!

ኢብሳ ቡርቃ
Our salvation is found only in one place. The person and work of Jesus Christ. That's Christianity.

Paul Washer