መዝገበ ቅዱሳን
22.7K subscribers
1.93K photos
9 videos
6 files
26 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
#ታኅሣሥ_20

#ቅዱስ_ሐጌ_ነቢዩ

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ሃያ በዚህች ዕለት ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ፣ ከሌዊ ነገድ ከአሮን ትውልድ የሆነው ቅዱስ ሐጌ ዐረፈ። እርሱም ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነው። ናቡከደነጾርም የኢየሩሳሌምን ሕዝብ በማረከ ጊዜ የዚህ ጻድቅ ነቢይ ወላጆች ከእስራኤል ልጆች ጋር ወደ ባቢሎን አገር ተማርከው ሔዱ ዳርዮስ የተባለውም ኵርዝ በነገሠ ጊዜ በሁለተኛው ዘመነ መንግሥቱ ይህ ነቢይ ትንቢት ተናገረ።

የእስራኤልን ልጆች ወደ አገራቸው ይገቡ ዘንድ ኵርዝ ዳርዮስ በአሰናበታቸው ጊዜ እነርሱም ከገቡ በኋላ ቤተ መቅደስን ከመሥራት ቸለል በአሉ ጊዜ እነርሱ ግን በአማሩና በተሸለመ ቤቶች ውስጥ ይኖሩ ነበርና እንዲህ አላቸው። "ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር እንዲህ አለ የኔ ቤት ፈርሷል እናንተ ግን ሁላችሁም ቤታችሁን ታጸናላችሁ" አላቸው። "ስለዚህ ከምድር በላይ ያለች ሰማይ ዝናም ለዘር ትነሣለች ምድርም ፍሬዋን አትሰጥም" አላቸው።

ከሕዝቡም ደናጎቻቸው ሰምተው እጅግ ፈሩ የእግዚአብሔርንም መመስገኛ ቤት እንደሚገባ መሥራት ጀመሩ። ይህም ጻድቅ ነቢይ ሰባ ዓመት ያህል ኖረ የትንቢቱም ወራት ክብር ይግባውና ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት በአራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነው። ከዚህ በኋላም በሰላም በፍቅር ታኅሣሥ 20 ቀን ዐረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ ቅዱስ ሐጌ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ)
#ታኅሣሥ_21

ታኅሣሥ ሃያ አንድ ይህችን ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን #ኖላዊ_ሔር ብላ ታከብራለች፣ #የሐዋርያው_ቅዱስ_በርናባስ ዕረፍቱ ነው::

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ኖላዊ_ሔር

ታኅሣሥ ሃያ አንድ ይህችን ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን "ኖላዊ ሔር" ብላ ታከብራለች:: ይሕንንም ለሳምንት ያህል ታዘክራለች:: መሠረታዊ መነሻዋም (ዮሐ. 10፥1) ነው:: "ኖላዊ" ማለት በቁሙ "እረኛ" ማለት ሲሆን "ሔር" ደግሞ "ቸር፣ርሕሩሕ፣አዛኝ" እንደ ማለት ነው:: ገጥመን ብንተረጉመው ደግሞ "ቸር እረኛ" የሚል ትርጉምን ይሰጠናል:: ከአባታችን አዳም ስህተት በኋላ ተፈጥረው ከነበሩ ችግሮች አንዱ ቸር እረኛ ማጣት ነው። እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ: ቸር እረኛ ሆኖ በገነት አሰማርቶት ነበር።

ኤዶም ገነት የለመለመች: ፈሳሾች የሞሉባት መልካም መስክ ናትና:: አባታችን ቅዱስ አዳም ደግሞ እንደ አቅሙ የጸጋ እረኝነት ተሰጥቶት ነበር:: ድቀት ካገኘው በሁዋላ ግን ከነፍስ እረኛው ጋር ተጣልቶ ከመልካሟ መስክ ገነት ወጣ:: እርሷንና የነፍሱን እረኛ ሲሻም አለቀሰ:: ተስፋ ድኅነት ሲሰጠውም ለልጆቹ ነገራቸው:: ከዚያም በመንጋው ላይ በአዳም ሴት ተተካ:: ከሴት ኄኖስ፣ ከኄኖስ: ቃይናን . . . እያለ ከኖኅ ደረሰ።

ከኖኅም በሴም ከአብርሃም: ከአብርሃምም በይስሐቅና በያዕቆብ ወርዶ ከሙሴ ደረሰ:: ከሙሴም በኢያሱ አልፎ ከነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ደረሰ:: እነዚህ ሁሉ እረኞች ምንም እንኩዋ ለእግዚአብሔር ሕዝብ በትጋት ቢሠሩም ሕዝቡን ከሲዖል ማዳን አልቻሉም:: ከሲዖል የሚያድን የነፍስ እረኛ ነውና ያን ጊዜ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የራሱን: የአባቶቹንና የልጆቹን ጩኸት ባንድ አድርጐ ጮኸላቸው:: "ኖላዊሆሙ ለእሥራኤል አጽምዕ - የእሥራኤል እረኛ ሆይ ስማን!" አለ:: (መዝ. 79:1)

ጩኸቱም ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ:: ይህንን የሰማ ጌታም በጊዜው ከድንግል ማርያም ተወለደ:: በየጥቂቱ አድጐ ቸር እረኝነቱን ገለጠ:: መድኃኒታችን እንዳስተማረን እርሱ ቸር እረኛ ነው:: ከእርሱ በፊት የተነሱት ቴዎዳስ ዘግብጽና ይሁዳ ዘገሊላ (ሐዋ. 5:36, ዮሐ. 10:8) ሐሰተኛ እረኞች ነበሩ:: እርሱ ግን እውነተኛው የበጐች በር ነውና (ዮሐ. 10:7) በእርሱ የሚገቡ ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛሉ:: እርሱ እውነተኛ እረኛ ነውና (ዮሐ. 10:11) ለመንጋው ራሱን አሳልፎ ይሰጣል:: በእሥራኤል ባሕል እረኞች ከፊት: መንጋው (በጐቹ) ከሁዋላ ሆነው ይሔዳሉና ገዳይ ቢመጣ መጀመሪያ የሚገድለው እረኛውን ነው::

መድኃኒታችን ክርስቶስ በሞቱ ሕይወትን: በመራቆቱ የጸጋ ልብስን: በውርደቱ ክብርን: በድካሙ ኃይልን ይሰጠን ዘንድ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ ሰጠ:: የማይሞት ንጉሥ ስለ መንጋው ሞተ:: ሰማይን ከነግሡ ምድርንም ከነልብሱ የፈጠረ ጌታ (ዘፍ. 1:1, ዮሐ. 1:2) ስለ በጐቹ ይህንን ሁሉ ታግሦ ከሲዖል አዳነን:: በሚያርግ ጊዜም በእርሱ ፈንታ ባለ ሙሉ ስልጣን እረኞችን: ሐዋርያትን (ዮሐ. 21:15) ሊቃነ ዻዻሳትን (ሐዋ. 20:28) ካህናትን (ማቴ. 18:18) ሾመልን:: እነርሱን እረኞች አሰኝቶ እርሱ "ሊቀ ኖሎት-የእረኞች አለቃ" ተባለ:: እነርሱም እስከ ዓለም ፍጻም የክርስቶስን መንጋ ሊጠብቁ ስልጣኑም ኃላፊነቱም አለባቸው:: (ማቴ. 28:19)

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_በርባስ

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሐዋርያው ቅዱስ በርናባስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይህም ቅዱስ ሐዋርያ ከሊዊ ነገድ የሆነ አገሩ ቆጵሮስ ነው የቀድሞ ስሙ ዮሴፍ ነው ክብር ይግባውና ጌታችን ከመከራው በፊት ይሰብኩ ዘንድ ከላካቸው ከሰባ ሁለት አርድእት ጋር መረጠው ስሙንም በርናባስ ብሎ ጠራው። ከጌታ ዕርገትም በኋላ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ እርሱም ከሐዋርያት ጋር የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ተቀብሎ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አስተማረ። የእርሻ ቦታ ነበረውና ሽጦ ዋጋውን አምጥቶ ከሐዋርያት እግር በታች አኖረው።

ቅዱስ ጳውሎስም በጌታችን አምኖ ወደ ሐዋርያት በመጣ ጊዜ ክብር ይግባውና ለክርስቶስ እርሱ ደቀ መዝሙሩ እንደሆነ ሐዋርያት አላመኑትም ነበር። ይህ በርናባስ ጌታችን በመንገድ እንደ ተገለጸለትና እንደአነጋገረው እርሱም በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በደማስቆ እንደ አስተማረ ነገራቸው። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔርን ሥራ ሲሠሩ ሲጾሙ ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ "ሳውልና በርናባስን እኔ እነርሱን ለመረጥኩት ሥራ ለዩልኝ" አላቸው።

ከዚህም በኋላ ጹመው ጸልየው እጆቻቸውን በራሳቸው ላይ ጭነው ሾሟቸው። ከመንፈስ ቅዱስም ተሹመው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ ከዚያም ወደ ቆጵሮስ ሔዱ የእግዚአብሔርንም ቃል በአገሩ ሁሉ አስተማሩ። ልስጥራን በተባለ አገርም ልምሾ የነበረውን ሰው በአዳኑት ጊዜ የልስጥራን ሰዎች መሥዋዕትን ሊሠዉላቸው ወደዱ። ሐዋርያት ቅዱስ ጳውሎስና በርናባስም በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀድው ወደ ሕዝቡ ሔዱ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሏቸው "እናንት ሰዎች ይህ ነገር ምንድን ነው እኛማ እንደናንተ የምንሞት ሰዎች አይደለንምን ይህን ከንቱ ነገር ትታችሁ ሰማይና ምድርን ባሕርንም በውስጣቸው ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደሕያው እግዚአብሔር ትመለሱ ዘንድ እናስተምራችኋለን" አሏቸው እንዲህም ብለው መሠዋትን በጭንቅ አስተዋቸው።

ከዚያም ብዙ አገሮችን ከአስተማሩ በኋላ ቅዱስ በርናባስ ከቅዱስ ጳውሎስ ተለይቶ ቅዱስ ማርቆስን ይዞ ወደ ቆጵሮስ ሔደ በዚያም አስተማረ ብዙዎችን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማመን መለሳቸውና የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው።

በቆጵሮስ አገር የሚኖሩ አይሁድም ቀኑበት በመኳንንትም ዘንድ ወነጀሉት በእግር ብረትም አሥረው ጽኑ ግርፋትን ገረፉት ከዚህም በኋላ በደንጊያ ወገሩት ዳግመኛም ወስደው ከእሳት ጨመሩት ምስክርነቱንም ፈጸመ። ቅዱስ ማርቆስም ከርሱ ጋር አለ ግን እግዚአብሔር ጠብቆ አተረፈው። እርሱም ቅዱስ በርናባስን ከእሳት ውስጥ አወጣው ሥጋውንም እሳት ከቶ አልነካውም በአማሩ ልብሶችም ገንዘውና ተሸክሞ ወስዶ ከቆጵሮስ ከተማ ውጭ በዋሻ ውስጥ አኖረው።

የመድኃኔዓለም ቸርነቱ የድንግል እናቱ ምልጃዋ ከእኛ ጋር ይሁን፤ በሐዋርያ ቅዱስ በርናባስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ )
ይውላልና በዚህ ወቅት ደግሞ ፍጹም ሐዘን ልቅሶ ጾም ጸሎት ይያዛል እንጂ ደስታ ፌሽታ እልልታ ጭብጨባ የለም፡፡ ዓቢይ ጾም ፍጹም የሐዘን ወራት ነው፡፡ ታቦት አውጥቶ በዓል ማክበር ስህተት ነው፤ የአባቶችንም ሥርዓት ማፍረስ ነው፡፡ ምስጋና ይድርሳቸውና ቅዱሳን አባቶቻችን ሁሉንም ነገር በሥርዓት በሥርዓቱ አድርገው ሰፍረው ቆጥረው አስቀምጠውልናል፡፡ ከዓቢይ ጾም በኋላ ያሉትን 50 ቀናት ረቡዕና ዓርብንም ጭምር ሥጋ እንኳን እንድንበላ ነው ሥርዓት የሠሩልን፡፡ አባቶቻችን የሠሯት ሕግ ፍጽምት ናት፡፡ በዚህም መሠረት አባቶቻችን ሥርዓትን ሠሩልንና የመጋቢት 27 የጌታችንን የስቅለቱን በዓል ወደ ጥቅምት 27 ቀን አምጥተው እንዲሁም የመጋቢት 5 የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስን የዕረፍት በዓል ወደ ጥቅምት 5 ቀን አዙረው እንዲከበር አድርገዋል፡፡ የመጋቢት 29 የብሥራቱን በዓል ደግሞ ወደ ታኅሣሥ 22 ቀን አዙረውት በዚህ ዕለት እንዲከበር አድርገውታል፡፡ አንድም ነገረ ልደቱን ከማክበር አስቀድሞ ነገረ ፅንሰቱን ማዘከር ማክበር ተገቢና መሆንም ያለበት ነውና ነው፡፡ ይህንንም ያደረገው ታላቁ አባት ቅዱስ ደቅስዮስ ነው፡፡ በእመቤታችን ፍቅር ልቡ የነደደው ይህ ታላቅ አባት የእመቤታችንን ተአምራቶቿን የጻፈላትም እርሱ ነው፡፡ እርሱም ከፍቅሩ ጽናት የተነሣ የእመቤታችንን የተአምራቷን መጽሐፍ ሰብስቦ አዘጋጀ፡፡

አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናቸ ክብርት እመቤታችንም ተገለጸችለትና መጽሐፉን በእጇ አንሥታ ይዛ ‹‹ወዳጄ ደውስዮስ ሆይ! ይህን መጽሐፍ ስለጻፍክልኝ ባንተ ደስ አለኝ፣ አመሰገንኩህ፣ እንዳከበርከኝ እኔም አከብርሃለው›› አለችው፡፡ ከዚህም በኋላ ከእርሱ ተሠወረች፡፡ ደቅስዮስም እመቤታችንን ከመውዱ የተነሣ ፈጽሞ ደስ አለው፡፡ ፍቅሯም እንደ እሳት አቃጠለው፡፡ የእርሷን ክብር አብዝቶ ይጨምር ዘንድ ምን እንደሚያደርግ የሚሠራውን ያስብ ጀመር፡፡

ከዚህም በኋላ በዚያን ጊዜ ጾም ስለነበር ሰዎች አስቀድመው ሊያከብሩት ያልተቻላቸውን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ባበሠራት ቀን በዓሏን አከበረ፡፡ እርሱም የከበረ የሚሆን የልደትን በዓል ከማክበር አስቀድሞ በ8 ቀን አደረገ፡፡ ይኸውም ታኅሣሥ በባተ በ22ኛው ቀን ነው፡፡ ይኽችውም ሥርዓቱ እስካሁን ጸንታ ኖራለች፡፡ ሰዎቹም በዓሉን ባከበሩ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናቸ ክብርት እመቤታችን በእጇ የከበረ ልብስ ይዛ ዳግመኛ ለቅዱስ ደቅሲዮስ ተገለጸቸለትና ‹‹አገልጋዬ የሆንክ ወዳጄ ደቅስዮስ ሆይ! በዕውነት አመሰገንኩህ፣ በአንተ ደስ አለኝ፣ ሥራህንም ወደድኩ፡፡ በእኔም ደስ እንዳለህና የከበረ መልአክ ገብርኤል እኔን በአበሠረበት ቀን በዓሌን ስላከበርክ ሰውንም ሁሉ ስለእኔ ደስ ስላሰኘህ እኔም ዋጋህን ልሰጥህ መጥቻለሁ፤ አንተ በዚህ ዓለም እንዳከበርከኝ እኔም በሰው ሁሉ ፊት አከብርህ ዘንድ እወዳለሁ›› አለችው፡፡ ይህንንም ካለችው በኋላ ‹‹እርሷን ትለብስ ዘንድ ይህችን ልብስ እነሆ አመጣሁልህ፤ በላዩም ትቀመጥ ዘንድ ይህን ወንበር አመጣሁልህ ፡፡ ከሰው ወገን አንድ ስንኳ ይህችን ልብስ ሊለብሳት በዚህችም ወንበር ላይ ሊቀመጥ የሚቻለው የለም፡፡ ይህንን ነገሬን የሚተላለፍ ቢኖር እኔ እበቀለዋለሁ›› አለችውና ሰማያዊ ልብስና ሰማያዊ ወንበር ሰጠችው፡፡ እመቤታችንም ይህንን ተናግራ ከባረከችው በኋላ ከእርሱ ተሠወረች፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ደቅስዮስ በዚሁ በዓለ ብሥራትን ባከበረበት ዕለት ታኅሣሥ 22 ቀን ካረፈ በኋላ አንድ ሌላ ኤጲስቆጶስ በተሾመ ጊዜ እመቤታችን ለቅዱስ ደቅስዮስ የሰጠችውን ልብስ ለበሰ፣ በወንበሩም ላይ ተቀመጠ፡፡ ሰዎችም ይህን አይተው ‹‹እባክህ ይቅርብህ እመቤታችን እንዲህ ብላ ተናግራለችና›› ቢሉት በመታጀር ‹‹እርሱም (ደቅስዮስም) ሰው እኔም ሰው፣ እርሱም ኤጲስቆጶስ እኔም ኤጲስቆጶስ›› ብሎ በትዕቢት ተናገረ፡፡ በወንበሩም ላይ እንደተቀመጠ ወድቆ ሞተ፡፡ ይህንንም ያዩ ሁሉ ከእመቤታችን ተአምር የተነሣ አደነቁ፡፡ እጅግም ፈርተው እመቤታችንን አከበሯት፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ ለቅዱስ ደቅስዮስ የተለመነች ክብርን የተመላች ድንግል ወላዲተ አምላክ ለእኛም ትለመነን! አምላካችን ልጇ በምልጃዋ ይማረን!

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ እና #ከገድላት_አንደበት)
በዚህች ዕለት የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን አባ ሳሙኤል፣ አባ ስምዖንና አባ ገብርኤል ዕረፍታቸው ነው፡፡
አባ ሳሙኤል የተባለው ይኽም ቅዱስ ባሕታዊ ሆኖ ቀርጣሚን በምትባል አገር የሚኖር ነው፡፡ በዚያም አቅራፎስ የሚባል ሰማዕት ዐፅም ስለነበር ከእርሱ በረከትን እየተቀበለ እየተሳለመ ይኖር ነበር፡፡ ሰሊባ የሚባል አንድ መኮንን ነበር፡፡ እርሱም ስምዖን የሚባል ልጅ አለው፡፡ ልጁም ለሞት በሚያበቃ ጽኑ ሕማም ታመመ፡፡ መኮንኑ በልጁ ላይ ይጸልይ ዘንድ ወደ አባ ሳሜኤል ላከ፡፡ ነገር ግን አባ ሳሙኤል ሲደርስ ልጁ ሞቶ አገኘው፡፡ አባ ሳሙኤልም በጸሎቱ ከሞት አስነሣው፡፡ ልጁ ስምዖንም ከሞት ከተነሣ በኋላ የአባ ሳሙኤል ደቀመዝሙሩ ሆነ፡፡ ሁለቱም በጋራ በተጋድሎ አብረው ኖሩ፡፡

ቅዱስ ስምዖን ውኃ ሊቀዳ ሲሄድ ሰይጣን እንስራውን ሰበረበት፡፡ አባቱም ሌላ መቅጃ ቢሰጠው እርሱንም ሰበረበት፡፡ የታዘዘ መልአክ ተገለጠላቸውና ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ አዘዛቸው፡፡ ንጉሥ አንስጣስዮስም ቤተ ክርስቲያኑን ሠራላቸው፡፡ እነርሱም ለመነኮሳትና ለነዳያን መኖሪያ 500 መኖሪያ ቤቶችን ሠሩ፡፡ አባ ሳሙኤልም ባረፈ ጊዜ መነኮሳት ልጆቹን ለአባ ስምዖን አስረክቦ በሰላም ዐረፈ፡፡ መነኮሳቱም 12 ሺህ እስኪሆኑ ድረስ በዙ፡፡ አባ ስምዖንም በሚገባ ይመራቸው ነበር፡፡ በዘመኑም "ትንሣኤ ሙታን የለም" የሚል ሰይጣን በልቡ ያደረ አንድ መናፍቅ ተነሣ፡፡ አባ ስምዖንም ቢመክረውና ቢያስተምረው የማይለስ ሆነ፡፡ አባ ስምዖንም በሞተ ሰው ላይ ጸልዮ ያንን ሙት አስነሥቶ እንዲመሰክርለት ቢያደርገው አላምን አለው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ስምዖን ወደ እግዚአብሔር ቢጸልይ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያንን መናፍቅ አቃጠለውና ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡ አባ ስምዖንም አገልግሎቱን ፈጽሞ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡

ከአባ ስምዖንም በኋላ አባ ገብርኤል ተሹሞ መለኮሳቱን የሚጠብቅ እረኛ ሆነ፡፡ እርሱም ምግባሩ ያማረ ሃይማኖቱ የሰመረ በትሩፋት በተጋደሎ ያጌጠ ነው፡፡ ብዙ አስደናቂ ተአምራትንም የሚያደርግ ሆነ፡፡ ከዕለታም በአንደኛው ቀን መነኮሳቱ ለእንጀራ ማቡኪያ የሚሆን እጅግ ትልቅ የሆነ የድንጋይ ገንዳ ወደ ገዳሙ ሊያስገቡ ቢሉ ከክብደቱ የተነሣ እምቢ አላቸው፡፡ አባ ገብርኤልም በዚህ ጊዜ በገዳሙ ያሉት ሁሉ ወጥተው እንዲራዱ በቃላቸው ባዘዙ ጊዜ 10 ሺህ ሰዎች ከሙታን ተነሡ፡፡ አባ ገብርኤልም ይህን አይቶ "እናንተን ያልኩ አይደለም በሕይወት ያሉትን ነው እንጂ" አሏቸውና ወዲያው ወደ መቃብራቸው ተመለሱ፡፡

ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አንድ ሰው ብዙ የሆነ ወርቁን ከአንዱ መነኩሴ ዘንድ በአደራ አስቀምጦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፡፡ ሰውየውም በተመለሰ ጊዜ መነኩሴው ለማንም ሳይናገር በሞት ዐርፎ አገኘው፡፡ የመነኩሴውም ረድእ አባቱ ያስቀመጠበትን ቦታ እንዳልነገረው አስረዳ፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ገብርኤል ወደሟቹ መነኩሴ መቃብር ሄዶ መቃብሩን ስለዚያ ወርቅ ጠየቀው፡፡ ሟቹም መነኮሴ ወርቁን ያኖረበትን ቦታ ለአባ ገብርኤል ነገረውና ወስዶ ለባለቤቱ ሰጠው፡፡ ባለወርቁም እጅግ እያደነቀ ወርቁን ተቀብሎ በሰላም ሄደ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ጢሞቴዎስ_ገዳማዊ

ዳግመኛም በዚህች ዕለት አባጢሞቴዎስ ገዳማዊ ዐረፈ፡፡ ይኸውም ደጋግ የሆኑ ወላጆቹ የቤተ ክርስቲያንን ትምህት እያስተማሩ አሳደጉት፡፡ በደገም ጊዜ ዓለምን ንቆ መንሶ ገዳም በመግባት በተጋድሎ መኖር ጀመረ፡፡ መጻተኞችንና ጦም አዳሪዎችን ይመግባቸው ዘንድ ከገዳሙ አቅራቢያ መኖሪያን አበጀ፡፡ ነዳያንንም እየመገበ በመንፈሳዊ ተጋድሎው እየጸና 5 ዓመት ያህል ከኖረ በኋላ የበጎ ነገር ጠላት የሆነ ሰይጣን በቅናት ተነሣበትና የእጅ ሥራውን ትገዛ ዘንድ አንዲት ጋለሞታን ወደ እርሱ አመጣበት፡፡

እርሷም ወደ አባ ጢሞቴዎስ ከመመላለሷ የተነሣ የኃጢአት ፍቅር አድሮባቸው በመብል ጊዜ አብረው የሚመገቡ ሆኑ፡፡ ከዚህም በኋላ ከእርሷ ጋር በኃጢአት ወደቀና በኃጢአት ሥራ ውስጥ 7 ወር ያህል ኖረ፡፡ እግዚአብሔር ሁለቱንም አልጣላቸውምና በዕለተ ምፅዓት በፊቱ የሚቆሙ መሆናቸውን አሳሰባቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ጢሞቴዎስ ተነሥቶ ጥቅጥቅ ወዳለ ጫካ ገብቶ በዚያ እየታደለ ብዙ ዘመን ኖረ፡፡ እግዚአብሔርም ጣፋጭ የሆነች የውኃ ምንጭንና ቴምርን አዘጋጀለት፡፡ እርሷን እየተመገበ በተጋድሎ ሲኖር ሰይጣን ዳግመኛ በቅናት ተነሣበትና አስጨናቂ የሆድ ሕማም አመጣበት፡፡ አባ ጢሞቴዎስ ከሕማሙ ጽናት የተነሣ በግንባሩ ምድር ላይ የወደቀ ሆኖ ቀረ፡፡ በዚህም ጊዜ ነፍሱን ‹‹ነፍሴ ሆይ ይህ የሠራሽው የኃጢአትሽ ፍሬ ነውና በዚህ ደዌሽ ታገሺ›› ይላት ነበር፡፡ በዚህም አስጨናቂ ሕማም ውስጥ ሆኖ 4 ዓመት ኖረ፡፡

ከ4 ዓመትም በኋላ መሐሪና ይቅር ባይ የሆነ እግዚአብሔር ለአባ ጢሞቴዎስ መልአኩን ላከለት፡፡ መልአኩም የአባ ጢሞቴዎስን ሆድ በእጁ አሸው፡፡ ጎኑንም በጣቱ ሰነጠቀና ጨንጓራውንና አንጀቱን አፀዳለት፡፡ በኋላም ወደቦታው መልሶ እንደቀድሞው አያይዞ አዳነውና "እነሆ እንግዲህ ጤነኛ ሆንክ፣ ዳግመኛ አትበድል ከዚህ የከፋ እንዳይደርስብህ" አለው፡፡ አባ ጢሞቴዎስም በበረሃ እየተጋደለ 40 ዓመት ኖረ፡፡ ከዚያ በፊት በገዳም 17 ዓመት በዋሻ 10 ዓመት ኖሯል፡፡ በእነዚህም ዘመናቱ ከልብስ ተራቁቶ ኖረ፡፡ የራሱም ፀጉር ከፊትና ከኋላ ሸፍኖት ነበር፡፡ ስለ አገልግሎቱ፣ ስለ ተጋድሎውና ስለ አምልኮቱ የዱር አራዊት እስኪደግዱለትና የእግሩን ትቢያ እስኪልሱለት ድረስ እግዚአብሔር ትልቅ ጸጋን ሰጠው፡፡ አገልግሎቱንም ፈጽሞ ታኅሣሥ 23 በሰላም ዐረፈ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ)
አባ ጳውሊም ይህን ባየ ጊዜ ስለ ኃጢአታቸው በጣም አዝኖ "ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ?" ቢላቸው እነርሱም "አባቶቻችን ያዘዙን ትእዛዝና ባሕላችን ነው" አሉት፡፡ አባ ጳውሊም ወደዚያ ቤት ሲገቡ አይቶ እጅግ በማዘን ወደ ጌታችን ጸለየ፡፡ ጸሎቱንም እንደፈጸመ አንድ ጥቁር ሰው ከዝሙት ቤቱ ዕራቁቱን ሆኖ የእሳት ሰይፍ ተሸክሞ መጣ፡፡ አባ ጳውሊም ካማተበበት በኋላ "አንተ ማነህ? ማንንስ ትሻለህ?" አሉት፡፡ ጥቁሩም ሰው "እኔ ሰይጣን ነኝ፣ አንተ ወደ ጌታህ በለመንህ ጊዜ ላከኝ" አለው፡፡ አባ ጳውሊም "የምታስትበትን ነገር ሁሉ ትነግረኝ ዘንድ እጠይቅሃለሁ" አለው፡፡ ሰይጣንም "የምትሻውን ጠይቀኝ" አለው፡፡ አባም "ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ በሰው ላይ ታድር ዘንድ ምክንያት እንዴት ታገኛለህ?" አለው፡፡ ሰይጣንም "ሰው በእግዚአብሔር ሕግ ጸንቶ ሳለ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ስም በጠራ ጊዜና በንጽሕና ሆኖ የክርስቶስ ሥጋና ደምን በሚቀበል ሰው ላይ ለማደር ሥልጣን የለኝም" አለው፡፡ ከዚህም በኋላ የሚያስትበትን ሁሉ በዝርዝር ነገረው፡፡ ሊቀ ጳጳሳትን፣ ጳጳሳትን፣ መነኮሳትን፣ መእመናንን፣ ባለትዳሮችን፣ አዛውንቶችን፣ ወጣቶችና ሕፃናትን…ሁሉንም ነገር እያንዳንዱን በምን በምን እንደሚያስት ሁሉንም ነገር በዝርዝር ነገረው፡፡ ወዲያውም የሰይጣን መልኩ ተለውጦ እንደ እሳት ነበልባል ሲሆን አባ ጳውሊ ተመልክቶ እጅግ ደነገጠ፡፡ በዚያም ቅጽበት የታዘዘ መልአክ መጥቶ አባ ጳውሊን አበረታው፡፡

በዚያችም ሌሊት መቅሰፍት ወርዶ በዝሙት ቤት ያሉትን አጠፋቸው፡፡ ከ5 ወንዶችና ከ5 ሴቶች በቀር የተረፈ የለም፡፡ አባ ጳውሊም "ይህን ለምን ታደርጋላችሁ?" ቢላቸው "በየወሩ አንዲት ቀን ወደ ውሽባ ቤት እየገባን በሩን ዘግተን መብራት አጥፍተን ከእጃችን የገባችዋን ሴት ይዘን አንተኛለን" አሉት፡፡ "ከእናንተ ውስጥ እኅቱን ወይም ልጁን እንዴት ያውቃል?" አላቸው፡፡ "እንደ እንስሳ በመሆን እንጃ ማወቅ የለም" አሉት፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን የክርስቶስን ወንጌል ሰበከላቸውና አሳምኖ አጠመቃቸው፡፡ ሥጋ ወደሙንም አቀበላቸው፡፡ በሃይማኖት ካጸናቸው በኋላ ወደ በዓቱ ተመልሶ ገድሉን ፈጽሞ ታኅሣሥ 24 ቀን በሰላም ዐረፈ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_አስቴር

የአይሁድ ወገን የሚሆን ስሙ መርዶክዮስ የሚባል የኢያኤሩ ልጅ ከብንያም ወገን የተወለደ የቄስዩ ልጅ አንድ ሰው በሱሳ አገር ነበረ፡፡ ከኢሩሳሌምም በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነጾር እጅ የተማረከ ነው፡፡ ያሳደጋት ልጅ ነበረችው፡፡ እርሷም የአባቱ ወንድም የአሚናዳብ ልጅ አስቴር ናት፡፡ ከዘመዶቿ ተለይታ በወጣች ጊዜ ልጅ ትሆነው ዘንድ አሳደጋት፡፡ እርሷም እጅግ መልከ መልካም ነበረች፡፡ በአንዲትም ዕለት ንጉሥ አርጢክስስ ብዙ ተድላ ደስታ አድርጎ መኳንንቶቹን ሁሉ ጠራ፡፡ የመኳንንቶቹንም አለቃ አማሌቃዊውን ሐማንንም ጠራው፡፡ እርሱ ከሁሉም መኳንንት የከበረ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሥ 7ቱን ባለሟሎቹን ጠርቶ ንግሥቲቱን አስጢንን አምጥተው የእቴጌነት ዘውድ ያቀዳጇት ዘንድ እርሷ መልከ መልካም ናትና ለአሕዛብም አለቆች ሁሉ መልኳንና ውበቷን ያሳዩ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ ንግሥቲቱ አስጢን ግን የንጉሡን ትእዛዝ ባለመቀበል እምቢ አለች፡፡ ከባለሟሎቿም ጋር ትመጣ ዘንድ ባለወደደች ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተናዶ ከንግሥትነቷ ሻራት፡፡ ከዚህም በኋላ 127 ከሚሆኑ ከሚገዘቸው አገሮች አንድ ሺህ ቆነጃጅቶችን ይመርጡለት ዘንድ ንጉሡ አዘዘ፡፡ ከሺህ መቶ፣ ከመቶ ዓሥር፣ ከዓሥር ሦስት መረጡ፡፡ ከሁሉም በመልክ፣ በውበት፣ በደም ግባትም አንደኛ ሆና አስቴር ተመረጠች፡፡ ንጉሡም አስቴርን አነገሣት፡፡

ንጉሡም አስቴርን እጅግ አድርጎ ወደዳት፣ በሴቶቹም ሁሉ ላይ የበላይ አድርጎ ሾማት፡፡ ከዚህም አስቀድሞ መርዶክዮስ አገሩንና አደባባዩን ከሚጠብቁት ከንጉሡ ባለሟሎች ጋር በአደባባይ ኖረ፡፡ እነርሱም ስማቸው ታራ እና ገቦታ ይባላል፡፡ እርሱም እነዚህ ሁለቱ በንጉሡ ላይ ያሰቡትን ተንኮላቸውን ሰማ፡፡ ንጉሥ አርጤክስስን ይገድሉት ዘንድ ወንጀልን እንዳዘጋጁ ባወቀ ጊዜ መርዶክዮስ ሄዶ ለንጉሡ ነገረው፡፡ ንጉሡም ነገራቸውን መርምሮ ቀጣቸውና ይህን ነገር ታሪክና ወግ በሚጻፍበት ላይ ጻፈው፡፡ ሐማ ግን አማሌቃዊ ነበረና መርዶክዮስንና እስራኤላውያንን ይጠላቸው እጅግ ነበርና የአይሁድን ወገን ሁሉ ለማጥፋት ተነሣ፡፡ መርዶክዮስም ይህንን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀዶ ማቅ ለበሰ፡፡ መርዶክዮስም የሀዘኑን መርዶ ለአስቴር እንዲደርሳት አደረገ፡፡ አስቴርም "እስከ ሦስት ቀን ጹሙ ጸልዩ እኔም ደንገጡሮቼም እንጾማለን" ብላ ላከችለት፡፡ ሱባኤዋንም እንደጨረሰች የማቅ ልብሷን አውልቃ ጥላ ወደ ንጉሡ አዳራሽ በገባች ጊዜ "እስከ መንግሥቴም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሻለሁና የሆንሽውን ንገሪኝ" አላት፡፡ በዓልንም አደረገና ሐማንና መኳንንቱን ሁሉ ጠራ፡፡ በበዓሉም ላይ ድጋሚ "ላደርግልሽ ፈቅጂውን ንገሪኝ" አላት፡፡

ንጉሡም ለመርዶክዮስ ውለታ ያደረገለትን ሲያስብ ምንም እንዳላደረገለት ዐወቀ፡፡ ወዲያውም ሐማ መርዶክዮስን በመስቀል ላይ ሰቅሎ ሊገድለው እንደሆነ ተነገረ፡፡ ንጉሡም ሐማን "ንጉሥ የወደደውን ሰው ምን ያደርግለት ዘንድ ይገባል?" አለው፡፡ ሐማም "ይህስ ለእኔ ነው" ብሎ "በክብር ይሾም ዘንድ ሹመቱም አዋጅ ይነገርለት ዘንድ ይገባዋል" አለ፡፡ ንጉሡም ለሐማ ይህን ጊዜ "መልካም ተናግረሃል፣ ለመርዶክዮስ እንዲሁ ይደረግለታል" አለው፡፡ ሐማም የንጉሡን ትእዛዝ ተቀብሎ መርዶክዮስን በፈረስ አስቀምጦ በከተማው በማዞር በክብር መሾሙን በአዋጅ አስነገረለት፡፡

ከዚህም በኋላ ንጉሡና አስቴር ለማዕድ አብረው በተቀመጡ ጊዜ ንጉሡ "ጉዳይሽን የማትነግሪኝ ለምንድነው?" አላት፡፡ እሷም ይህን ጊዜ "ንጉሥ ሆይ ዝም ባልኩ በወደድኩ ነበር ነግር ግን ወገኖቼና እኔ ለሞት ተላልፈን ተሰጥተናል" በማለት ሐማ እስራኤላውያንን በአዋጅ ሊያጠፋ መሆኑን ነገረችው፡፡ ንጉሡም "ማነው ይህን በማድረግ የደፈረኝ?" አላት፡፡ እሷም ሐማ መሆኑን ነገረችው፡፡ ንጉሡም ሐማ መርዶክዮስን ለመስቀል ባዘጋጀው መስቀል ላይ ራሱ ሐማን እንዲሰቅሉት አዘዘ፡፡ ሐማም ተሰቅሎ ሞተ፡፡ የእስራኤል ወገኖችም ሁሉ በጻድቂቱ አስቴር መዳናቸው በእርሷ ተደርጓልና ሁሉም አመሰገኗት፡፡ ምስጉን የሆነ እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ የእስራኤል ወገኖች ሁሉ ድኅነታቸው በእርሷ ተደርጓል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ፊሎንጎስ

በዚህች ዕለት አባ ፊሎንጎስ ዐረፈ፡፡ ይኽም ቅዱስ አስቀድሞ ሚስት አግብቶ አንዲት ልጅ ወለደ፡፡ ከዚህም በኋላ ሚስቱ ሞተች፡፡ እርሱም ከዚህ በኋላ የምንኩስና ልብስ ለብሶ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ ኖረ፡፡ ስለ መልካም ተጋድሎውትና ስለ ትሩፋቱ በአገልግሎትም ስለመጠመዱ በአንጾኪያ አገር ላይ ሊቀ ጳጳሳት እንዲሆን እግዚአብሔር መረጠው፡፡ በተሾመም ጊዜ የክርስቶስን መንጋዮች ምእመናንን በመልካም አጠባበቅ ጠበቃቸው፡፡ ከአርዮሳውያን ከመቅዶንዮስና ከሰባልዮስ ነጣቂ ተኩላዎች በሚገባ ጠበቃቸው፡፡ በሊቀ ጵጵስናውም የሹመት ወቅት አኗኗሩን እንደ መላእክት አደረገ፡፡ መልካም የሆነ ገድሉንም ፈጽሞ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ እና #ከገድላት_አንደበት)
ትጠብቅ ዘንድ ላነገሠህ አንተ ቸለል ብለህ ለዘጋኸው ለእግዚአብሔር እንሰግዳለን እንጂ" ብለው መለሱለት።

ከዚህም በኋላ የተራቡ አራዊትን በላያቸው እንዲሰዱ አዘዘ እነዚያም ለቅዱሳን ሰግደው ተመልሰው ከከሀድያን ሰባ አምስት ሰዎችን ገደሉአቸው። እሊህንም ቅዱሳን ወደ ወህኒ ቤት ጨመሩአቸው ሌሎች ሁለት ወንድሞቻቸውም መጥተው ከእርሱ ጋር ተቀላቀሉ። ንጉሡም አምስቱን ወንድማማቾች አይቶ እጅግ ተቆጥቶ ከሚነድ እሳት ውስጥ ይጨምሩአቸው ዘንድ አዘዘ ነፍሳቸውንም በእግዚአብሔር እጅ አስረከቡ።

ከዚህም በኋላ የቅዱሳኑን ሥጋ አመድ እስከሚሆን ያቃጥሉ ዘንድ ዳግመኛ አዘዘ እሳቱም ከቶ አልነካቸውም ዳግመኛም ከባዶች ደንጊያዎችን ከሥጋቸው ጋር አሥረው ከባሕር ውስጥ ያሰጥሟቸው ዘንድ አዘዘ ባሕሩም አልዋጣቸውም ለዱር አራዊትና ለሰማይ ወፎች እንዲጥሏቸው አዘዘ አዕዋፍም ክንፎቻቸውን ጋርደውላቸው ዐሥራ አራት ቀኖች ኖሩ ሥጋቸውም እንደ ፀሐይ አበራ ከዚህ በኋላ ይቀብሩአቸው ዘንድ አዘዘ።

ከዚህም በኋላ ያንን የእግዚአብሔርን ሕግ የዘነጋ ንጉሥ ሌሊት በዐልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ እሊህ ቅዱሳን ተቆጥተው ሰይፋቸውን መዝዘው በፊቱ ቁመው ታዩት በነቃም ጊዜ የሚበቀሉት መስሎታልና ፈርቶ ተንቀጠቀጠ። እነዚያም የከበሩ ሰማዕታት "ክፉ ነገርን ስላደረግህብን እኛስ ክፉ ነገርን አንከፍልህም በነፍስ ፍዳ የሚያመጣ እግዚአብሔር ነውና ፍዳንስ የሚከፍልህ ፈጣሪያች እግዚአብሔር አለ። ነገር ግን ስለዕውቀትህ ማነስና ስለ ልቡናህ ድንቁርና እኛ ደኅነኞች እንደሆን ተገልጠን ታየንህ እኛንስ የገደልከን መስሎህ ድኅነትን አዘጋጀህልን። የጣዖቶችህ ካህናትና አንተ ግን ለዘላለሙ መውጫ ወደሌለባት ወደ ገሀነም ትወርዳላችሁ" አሉት ከዚህም በኋላ ከርሱ ተሠወሩ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ እና #ከገድላት_አንደበት)
#ታኅሣሥ_26

#ቅድስት_አንስጣስያ

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ሃያ ስድስት በዚህች ዕለት ከሮሜ አገር የከበረች ቅድስት አንስጣስያ በሰማዕትነት ዐረፈች፡፡ የዚችም ቅድስት አባቷ ጣዖትን የሚያመልክ ነው እናቷ ግን ክርስቲያን ናት ይቺንም ቅድስት በወለደቻት ጊዜ አባቷ ሳያውቅ የክርስትና ጥምቀትን በሥውር አጠመቀቻት አውቆ ቢሆን ማጥመቅ ባልተቻላትም ነበር። ከዚህም በኋላ በበጎ አስተዳደግ አሳደገቻት በቀናች ሃይማኖት እስከ አጸናቻት ድረስ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማረቻት ጠባይዋን መለወጥ ለማንም አልተቻለውም።

አድጋም አካለ መጠን በአደረሰችም ጊዜ አባቷ እንደርሱ ላለ ከሀዲ ሰው አጋባት እርሷ ግን እጅግ ጠላችው ልትገናኘውም አልፈለገችም በሴቶች ላይ በሚሆነው ግዳጅና አንዳንድ ጊዜም በደዌ የምታመካኝ ሆነች እንዲጠላትና ከእርሷ እንዲለይ ያደፈና የቆሸሸ የተጐሳቈለ ልብስ ትለብስ ነበር። ባሏም ወደ ሥራው ወጥቶ በተሰማራ ጊዜ እርሷም ስለ ቀናች ሃይማኖት የታሠሩ እስረኞችን ትጐበኝ ዘንድ ትሰማራለች ታገለግላቸውና የሚሹትን ትሰጣቸዋለች። ባሏም ይህን የምትሠራውን በአወቀ ጊዜ ወደ ውጭ እንዳትወጣ በቤት ውስጥ ዘጋባት እርሷም ከእጁ ያወጣት ዘንድ አዘውትራ በመረረ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር የምትለምን ሆነች ጌታችንም ልመናዋን ሰምቶ ያንን ሰው አጠፋው። እርሷም በሞቱ ደስ አላት ከዚህም በኋላ ለድኆችና ለምስኪኖች ስለ ቀናች ሃይማኖትም በመታመን ለታሠሩ እሥረኞች ገንዘቧን ሁሉ ሰጠች።

የሮሜ አገር ገዢም ዜናዋን በሰማ ጊዜ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣት ስለ ሃይማኖቷም ጠየቃት ክርስቲያን እንደሆነች በፊቱ ታመነች ቃል ኪዳን በመግባትም ተናገራት ከበጎ ምክርዋ አውጥቶ ወደ ክህደት ሊያዘነብላት አልቻለም። በዚያንም ጊዜ በብዙ በተለያየ ሥቃይ አሠቃያት።

ከዚህም በኋላ ወደ ባሕር ያሠጥሟት ዘንድ አዘዘ ባሕሩም በሕይወቷ ተፋት ዳግመኛም በአራት ካስማ መካከል አስተኝተው ዘርግተው አሥረው ታላቅና ጽኑዕ የሆነ ግርፋትን ይገርፋዋት ዘንድ አዘዘ መኰንኑም እንዳዘዘ አደረጉባት ግን ምንም ምን ጉዳት አልደረሰባትም። ከዚህም በኋላ ወደ አዘጋጁላት የእሳት ማንደጃ ውስጥ ይጨምርዋት ዘንድ አዘዘ በጨመርዋትም ጊዜ ነፍሷን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊል ተቀበለች።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት አንስጣስያ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ)
"አንተም ወንድሜ ሆይ ራስህን ዕወቅ፡፡ ምንም ተጋድሎን ብታደርግ ጾምኩ፣ ተራብኩ፣ ስለ እግዚአብሔርም ብዬ ራሴን አደከምኩ፣ እግዚአብሔርንም ስላገለገልኩ በሥራዬም እድናለሁ አትበል፡፡ መጨረሻህን አታውቅም፡፡ አንተ ግን ስለ እግዚአብሔር ብለህ ራስህን ኃጥእ አድርግ ያን ጊዜ እግዚአብሔር ያጸድቅሃልና፡፡ ወዳጄ ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ እንድትመሰገን ራስህን አታመስግን፤ ሌሎችም ያመሰግኑህ ዘንድ አትውደድ፡፡ ክብር ታገኝ ዘንድ ትሕትናን ገንዘብ አድርግ መጨረሻውን ሳታውቅ ሰው ሲበድል ብታይ አትጥላው አትናቀውም። አንተ ግን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር በጸሎትህ ይምረው ዘንድ ጸልይ። የእግዚአብሔር ምሕረት ብዙ ነውና ኃጥአንን ይምራቸዋል። ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረ ጳውሎስንም ሐዋርያ አደረገው። ቀራጭ የነበረውን ማቴዎስንም የወንጌል ጸሐፊ አደረገው። እግዚአብሔር ሽፍታ ሆኖ የሰውን ገንዘብ ሲዘርፍ የኖረ ለአባ በግዑ ምሕረት እንዳደረገለት አስተውል። እግዚአብሔር በቀኙ እንደተሰቀለው ሽፍታ በመጨረሻ ዘመኑ መረጠው የመንግሥተ ሰማያትም ወራሽ አደረገው"።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_አብሳዲ

ዳግመኛም በዚህች ዕለት የከበረ አባት ቅዱስ አባ አብሳዲ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ ከላይኛው ግብፅ የተገኙት ይህ ጻድቅ ምግባር ሃይማኖታቸው፣ ትሩፋት ተጋድሎአቸው ያማረ ነው፡፡ በዘመናቸው ከሃዲዎች የነገሡበት ዘመን ነበር፡፡ ያን ጊዜ ታላላቆች የሆኑ የላይኛው ግብጽ ኤጲስቆጶሳት አባ አብሳዲና አባ አላኒቆስ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሆነች በቀናች ሃይማኖት ሕዝቡን እንደሚያጸኑአቸው የአማልክትንም አምልኮ እንደሚሽሩ ዜናቸውን ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ መልክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጥቶ ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው። የከበረ አባ አብሳዲ ግን አንዲት ቀን እንዲታገሡት መልክተኞችን ለመናቸውና የቊርባን መሥዋዕትን አዘጋጅቶ ቅዳሴ ቀድሶ ለሕዝቡ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው። በቀናች ሃይማኖትም እንዲጸኑ አስተማራቸው ከዚህም በኋላ በሰላምታ ተሰናብቷቸው ከእርሳቸው ዘንድ ወጣ ሰውነቱንም በእግዚአብሔር ላይ ጥሎ ከመልክተኞች ጋር ሔደ ወደ እንዴናው ገዥ ወደ አርያኖስ ወሰዱት።

መኰንኑም አርያኖስም የአባ አብሳዲን ገጽ በአየ ጊዜ ከአርያውና ከግርማው የተነሣ አደነቀ ራራለትም እንዲህም አለው "አንተ የከበርክና የምታስፈራ ሰው ለነፍስህ እዘን የንጉሥንም ቃል ስማ"። አባ አብሳዲም እንዲህ ብሎ መለሰ "እኔ የንጉሥን ቃል ሰምቼ በዚህ በኃላፊው ዓለም ሕይወት መንግሥት ሰማያትን አልለውጥም" በመካከላቸውም ብዙ የነገር ምልልስ ሆነ ከበጎ ምክሪ ባተመለሰ ጊዜ በመንኰራኵር ያሠቃዩትና ከእሳት ማንደጃ ውስጥም ይጨምሩት ዘንድ መኰንኑ አዘዘ ይህን ሁሉ ታገሠ እግዚአብሔርም ያለ ጉዳት በጤና አስነሣው።

ከዚህም በኋላ ራሱን ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ አባ አብሳዲም ሰምቶ ደስ አለው ልብሰ ተክህኖ ለብሶ እጆቹንም ዘርግቶ አንገቱን ለሰይፍ ሰጠ የከበረች ራሱንም ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ እና #ከገድላት_አንደበት)
#ታኅሣሥ_28

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ሃያ ስምንት በህች ዕለት #የጌና_በዓል ሆነ። ይኸውም የልደት በዓል ነው፣ ከእንዴናው አገር ሰዎች መቶ ሃምሳ ወንዶች ሃያ አራት ሴቶች በሰማዕትነት ሞቱ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ዕለተ_ጌና

ታኅሣሥ ሃያ ስምንት በዚህች ዕለት የጌና በዓል ሆነ። ይኸውም የልደት በዓል ነው። ይህም እንዲህ ነው በአምላካችን በረቀቀ ጥበቡ ሰዎች ሁሉ ይቈጠሩ ዘንድ ስማቸውንም ይጻፋና ይመዘገቡ ዘንድ ከንጉሥ ቄሣር ትእዛዝ መጣ። ስለዚህም ከእመቤታችን ከከበረች ድንግል ማርያም ጋር ሊቆጠር ዮሴፍ ከናዝሬት ወደ ቤተልሔም የርሱንና የቡርክት ድንግል ማርያምን ስም ሊስመዘግብ ወጣ እርሱ ከይሁዳ ነገድ ከዳዊት ወገን ነውና ቤተልሔምም የዳዊት ቦታው ናትና።

የከበረ ወንጌል እንደተናገረ ከዚህም በኋላ ከዚያ ሳሉ የምትወልድበት ቀን ደረሰ የበኵር ልጇንም ወለደች አውራ ጣቱንም አሠረችው በጨርቅም ጠቅልላ በበረት አስተኛችው ለማደሪያቸውም ቦታ አልነበራቸውምና። በዚያ ሰፈር እረኞች ነበሩ ሌሊትም በየተራቸው ተግተው መንጋቸውን ይጠብቁ ነበር። እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ አጠገባቸው ቆመ የእግዚአብሔርም ብርሃን በላያቸው በራ ታላቅ ፍርሀትም ፈሩ መልአኩም "ለእናንተና ለመላው ዓለም ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ" አላቸው።

"እነሆ ዛሬ በዳዊት አገር መድኅን የሆነ ጌታ ክርስቶስ ተወልዶላችኋልና። ለእናንተም ምልክት እንዲህ ነው ሕፃኑ አውራ ጣቱን ታሥሮ በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ" አላቸው። ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ "በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም በሰው በጎ ፈቃድ እያለ መጡ።

ከዚህም በኋላ መላእክት ከእነርሱ ዘንድ ባረጉ ጊዜ እነዚህ እረኞች ሰዎች እርስበርሳቸው "ኑ ወደ ቤተ ልሔም ሔደን ይህን እግዚአብሔር የገለጠውንን ነገር እንወቅ" አሉ። ፈጥነውም ሔዱ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በበረት ውስጥ ተኝተ አገኟቸው። አይተውም የነገሩዋቸው ስለዚህ ሕፃን እንደሆነ አወቁ እረኞች የነገሩዋቸውን የሰሙ ሁሉ አደነቁ። እረኞችም ለሕፃኑ ሰግደው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደ ቦታቸውም ተመለሱ።

ከወገናችን ሰው ሁኖ ለጐበኘንና ይቅር ላለን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#174ቱ_ሰማዕታት (የቅዱስ ጳውሎስ ማኅበር)

በዚችም ዕለት ደግሞ ከእንዴናው አገር ሰዎች መቶ ሃምሳ ወንዶች ሃያ አራት ሴቶች በሰማዕትነት አረፉ።

እሊህም ቀድሞ ከሀ*ዲያን ነበሩ የእንዴናው መኰንን የከበረ ሶርያዊ ጳውሎስን በሚያሠቃየው ጊዜ ከዚያ ነበሩ ሲአሠቃየውም ይመለከቱ ነበር መኰንኑም ችንካሮችን በእሳት አግለው ዐይኖቹን እንዲአወልቁ አዘዘ ይህንንም ባደረጉበት ጊዜ ዐይኖቹ ወለቁ ከወህኒ ቤትም ጣሉት። በማግሥቱም እሊኒ ሰዎች ሊያዩት በሔዱ ጊዜ ያለ ምንም ጉዳት ድኖ ጤነኛ ሁኖ አገኙት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አድኖታልና።

ይህንንም ድንቅ ተአምር አይተው እጅግ አደነቁ ጣዖ*ቶቻ*ቸውም ምንም መሥራት እንደማይችሉ አስተዋሉ። የክርስቲያኖች አምላክ እርሱ እውነተኛ አምላክ እንደ ሆነ አወቁ ወደከበረ ጳውሎስ ሒደው ሰገዱለት እንዲጸልይላቸውም ለመኑት እርሱም ባረካቸው እግዚአብሔር እምነታችሁን ተቀብሎ ከሰማዕታት ጋር ይቊጠራችሁ አላቸው።

ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ቀርበው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ መኰንኑም ራሶቻቸውን ቊረ*ጡ ብሎ አዘዘና ቈረ*ጧቸው በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕታት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ)
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ)