መዝገበ ቅዱሳን
25.5K subscribers
1.97K photos
9 videos
6 files
27 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለነቢዩ #ቅዱስ_ዮናስ እና ለእናታችን #ቅድስት_አውፎምያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ ቅዱስ ዮናስ ነቢይ ✞✞✞

=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከ12ቱ #ደቂቀ_ነቢያት አንዱ የሆነው #ቅዱስ_ዮናስ ከክርስቶስ ልደት 800 ዓመታት በፊት እንደ ነበረ ይታመናል:: #ሊቃውንት እንዳስተማሩን ደግሞ እናቱ #ቅዱስ_ኤልያስን የመገበችው የሰራፕታዋ መበለት ናት:: ቅዱስ ዮናስ ገና ሕጻን ሳለ በእሥራኤል ምድር ዝናብ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ተከልክሎ ነበር::

+ይሕንንም ያደረገው ደጉ ነቢይ ኤልያስ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀንቶ ነው:: በወቅቱ ኤልያስ በሰራፕታ ሳለ ሕጻኑ ዮናስ ታሞ ሞተ:: ልጇ የሞተባት መበለትም ኤልያስን ለመነችው:: ኤልያስም ወደ ፈጣሪው ማልዶ ሕጻኑን ዮናስን ከሞት አስነስቶታል:: ትንሽ ከፍ ባለ ጊዜም ከጉዋደኞቹ (ከነቢያቱ) #አብድዩና #ኤልሳዕ ጋር ሆነው ታላቁን ነቢይ ኤልያስን ተከትለውታል::

+ኤልያስ ካረገ በሁዋላ ሁሉም በየተሰጣቸው አገልግሎት ተሠማርተዋል:: ቅዱስ ዮናስን #እግዚአብሔር "ወደ ነነዌ ሒደሕ ንስሃን ስበክ" አለው:: ዮናስ ግን የፈጣሪውን መሐሪነት ጠንቅቆ ያውቃልና አልሔድም አለ:: (ተመልከቱ የየዋሕነት ብዛት)

+እግዚአብሔር እየደጋገመ እንዲሔድ ሲነግረው ነቢዩ "እንዲሕ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል" ብሎ ሊኮበልል ወጣ:: ነገር ግን አልቀናውም:: በእርሱ ምክንያት ማዕበል ተነሳ:: ሕዝቡም ሊያልቁ ሆነ:: ከእንቅልፉ የነቃው ዮናስ ከመርከቡ ላሉት አሕዛብ አምልኮተ እግዚአብሔርን ሰብኮላቸው: በእርሱ ጠያቂነት ሐምሌ 15 ቀን ወደ ባሕር ጥለውታል::

+አሣ አንበሪም ተቀብሎታል:: በግዙፉ አሣ ውስጥም ያለ እንቅልፍ በጾም: በጸሎትና በምስጋና 3 ለቀን ቆይቷል::
ሙስና ሳያገኘውም በዚህች ቀን አሣ አንበሪው #ነነዌ ዳር ላይ ተፍቶታል:: ቅዱስ ዮናስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ ነነዌ ዓባይ ሃገር" /እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትገለበጣለች (ዮናስ 3:4)/ ብሎ አሰምቶ ሰበከ::

+የነነዌ ሰዎችም በስብከተ ዮናስ አምነው: ንስሃም ገብተው ድነዋል:: በዚህም ጌታችን በወንጌል ላይ አመስግኗቸዋል:: ቅዱስ ዮናስ መኮብለሉ #በሐዲስ_ኪዳን ለሚደረገው ምስጢረ ትንሳኤ ጥላ (ምሳሌ) ነውና ይደነቃል:: (ማቴ. 12:38) ነቢዩ ግን በተረፈ ሕይወቱ ሕዝቡን ሲያስተምር: ፈጣሪውን ሲያገለግል ኑሮ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::

+"+ ቅድስት አውፎምያ ሰማዕት +"+

=>እናታችን #ቅድስት_አውፎምያ (ስሟ አፎምያ አይደለም:: በስሕተት "ው" መካከል ላይ የገባች እንዳይመስልዎ:: እስመ ከመዝ ስማ-ስሟ እንዲሁ ነው የሚጠራው) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ወጣት ክርስቲያኖች አንዷ ናት:: ገና ከልጅነቷ ልቧ በፍቅረ ክርስቶስ የተነደፈ ነበር::

+በዚህም ምክንያት ራሷን በጾምና በጸሎት ወስና ትኖር ነበር:: እድሜዋ ገና በአሥራዎቹ ቢሆንም በመንኖ ጥሪት መኖር ምርጫዋ ነበር:: ሊቃውንት አበው ከሰማዕትነቷ ደርበው "ጻድቅት አውፎምያ" እያሉም ይጠሯታል::

+አንድ ቀን ግን መንገድ ወጥታ ነበርና ክርስቲያኖች ሲሰቃዩ ተመለከተች:: ምንም ጥፋት ሳይገኝባቸው ክርስቶስን ስላመለኩ ብቻ ይሙት በቃ ተፈርዶባቸው ሊገደሉ እየተወሰዱ ነበር:: አሕዛብ ግብራቸው የአውሬ ነውና ርሕራሔ የላቸውም:: ሰማዕታቱ ደማቸው በየመንገዱ እየፈሰሰ ጥቁር ሰንሰለት በአንገታቸው: በእጃቸውና በእግራቸው ላይ አድርገው ይጐትቷቸው ነበር::

+ቅድስት አውፎምያ የተደረገውን ሁሉ ተመልክታ አምርራ አለቀሰች:: ፈጠን ብላም ወደ መኮንኑ ቀርባ ገሰጸችው::
"አንተ አእምሮ የጎደለህ! እንዴት ክርስቲያኖችን እንዲህ ታሰቃያለህ? አምላካቸው #ጌታ_ክርስቶስ ታጋሽ ባይሆን ኑሮ በቅጽበት ከገጸ ምድር ባጠፋህ ነበር" አለችው::

+በድፍረቷ የተገረመው መኮንኑ "አንቺስ ማንን ታመልኪያለሽ?" ሲል ጠየቃት:: እርሷም "ሰማይና ምድርን የፈጠረውን: ስለ እኛ ሲል በቀራንዮ አንባ የተሠዋውን #ኢየሱስ ክርስቶስን አመልካለሁ" ስትል መለሰችለት:: በዚያች ሰዓት የመኮንኑ ቁጣ በቅድስቷ ላይ ነደደ::

+ነገር ግን ቁጣውን ከቁም ነገር አልቆጠረችውምና እንዲያሰቃዩዋት አዘዘ:: ወታደሮቹ ሥጋዋን በብዙ አሰቃዩ:: ብላቴናዋ አውፎምያ ግን ጽንዕት ናትና አልቻሏትም:: በመጨረሻ በእሳት ተቃጥላ ትሞት ዘንድ ተፈረደባት::

+እሳቱ ከመሬት ከፍ ባለ ጊዜ ወደ ውስጥ ወረወሯት:: በእሳቱ መካከል ቁማ ለረዥም ጊዜ ጸለየች:: ከዚያም ነፍሷን አሳልፋ ሰጠች:: ምዕመናን በክብር ገንዘው ቀብረዋታል::

=>አምላካችን ከነቢዩና ከሰማዕቷ ወዳጆቹ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ (ከአሣ አንበሪ ሆድ የወጣበት)
2.ቅድስት አውፎምያ (ጻድቅትና ሰማዕት)
3.ቅዱስ ዮስጦስ ሰማዕት (ታላቁ)
4.ቅዱስ ዘካርያስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)

=>+"+ በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና:- 'መምሕር ሆይ! ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን' አሉት:: እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው:- 'ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ:: +"+ (ማቴ. 12:38)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
@petroswepawulos
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ መስከረም ፲፮ (16) ❖

✞✞✞ እንኩዋን ለቅድስት ሃገር #ኢየሩሳሌም: ለቅዱስ #ጦቢት እና ለአባ #አጋቶን_ባሕታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ #ሕንጸታ_ለኢየሩሳሌም +"+

=>ኢየሩሳሌም በብሉይም: በሐዲስም ቅድስት ሃገረ
እግዚአብሔር ናት:: '#ኢየሩ' ማለት 'ሃገር' ማለት ሲሆን
'#ሳሌም' ደግሞ 'ሰላም' ማለት ነው:: ስለዚህ በቁሙ
'ሃገረ ሰላም': '#ሃገረ_ክርስቶስ' ማለት ነው::

+ኢየሩሳሌም የሚለው ቃል በቁሙ ቅድስት ሃገርን
ሲመለከት በምሥጢሩ ግን የቤተ ክርስቲያን: የመንግስተ
ሰማያት እና የአማናዊት ሃገረ ሰላም #ድንግል_ማርያም
መጠሪያ ነው:: ኢየሩሳሌምን በከተማ ደረጃ የመሠረታት
ታላቁ ካህን #መልከ_ጼዴቅ ሲሆን 'ንጉሠ ሳሌም'
ተብሎም ኑሮባታል::

+ይህች ቅድስት ሃገር በብሉይ ዘመን እግዚአብሔር
በረድኤት ቢገለጥባት: ጻድቃነ ብሊት ቢኖሩባት
ተቀድሳለች:: በሐዲስ ኪዳን ግን አምላካችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ከሰማያት ወርዶ 33 ዓመት ከ3 ወር ያህል
የድኅነ ትሥራውን ቢፈጽምባት: ለድንግል ማርያምና
ለብዙ ቅዱሳን ቤት ብትሆን የበለጠ ተቀድሳለች::

+ዛሬም ድረስ ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት በብዙ ድካምና
ወጪ ሊያዩዎት ይጉዋዛሉ:: የቀደመው ዘመን
አባቶቻችንም ይህችን ቅድስት ከተማ ለመሳለም እስከ
ደም ጠብታ ከፍለዋል::

+ወደ ዋናው ጉዳያችን እንለፍና የኢየሩሳሌምን መታነጽ
እንይ:: ኢየሩሳሌም በአሕዛብ እጅ ብዙ ጊዜ ፈርሳ
ታንጻለች:: እኛ ግን ዛሬ የምናከብረው የከተማዋን
መታነጽ ሳይሆን በከተማዋ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ
መንገድ በአንድ ጊዜ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት
መታነጻቸውን ነው:: ይሕስ እንደምን ነው ቢሉ:-

+ከክርስቶስ ዕርገት 300 ዓመታት በሁዋላ ለቤተ
ክርስቲያን የተነሳችው #ቅድስት_ዕሌኒ በጐ ሃሳብ
በሕሊናዋ ተመላልሷልና ተነሳች::

#ጉባኤ_ኒቅያ ከተጠናቀቀ በሁዋላ ልጇ ቆስጠንጢኖስ
በነገሠ በ20 ዓመቱ በ227 ዓ/ም አካባቢ ቅዱስ ዕጸ
መስቀሉን ትፈልግ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ አደረገች::

+መስቀሉን ፈልጋ ያገኘችበት ታሪክ ለነገ ይቆየንና
መስቀሉን ካገኘችው በሁዋላ በሙሉ ከተማዋ ላይ
አብያተ ክርስቲያናትን ለማነጽ ከልጇ ጋር ተስማማች::

+ለሕንጻው የሚሆን ብዙ ወርቅ: ብርና እንቁ ጭና
ማምጣቷን የተመለከቱት #አባ_መቃርስ (የኢየሩሳሌም
ሊቀ ዻዻስ ናቸው) "ልምከርሽ! ቤተ ክርስቲያኑን
በጠንካራ አለት ላይ ሥሪ:: ወርቅና ብሩን ግን ለነዳያን
በትኚ" ስላሏት በአካባቢው ላሉ ነዳያን ታላቅ ፌሽታ
ሆነ:: እጅግ ብዙ ሠራዊት: ብዙ ሺህ ሠራተኞች
ታጥቀው 80 አብያተ ክርስቲያናትን ያንጹ ጀመሩ::

+ሥራው ረቂቅና ብዙ ሥለ ነበረ እጅግ አድካሚ ነበር::
ቅድስት ዕሌኒ ሃገሪቷን በቤተ መቅደሶች መሸፈን ስለ
ፈለገች እንዲታነጽ ያዘዘችው የቤተ ክርስቲያን ቁጥር 80
ደረሰ:: እነዚህም ጌታ ከጽንሰቱ እስከ ዕርገቱ
የረገጣቸውና #እመ_ብርሃን የረገጠቻቸው ቦታዎች
ናቸው::

+#ቤተ_ልሔም: #ዮርዳኖስ: #ደብረ_ሊባኖስ:
#ደብረ_ታቦር: #ደብረ_ዘይት: #ጐልጐታ: #ጌቴ_ሴማኒ:
#ቤተ_ሳይዳ: #ጽርሃ_ጽዮን ደግሞ ዋና ዋናዎቹ ናቸው::
በአካባቢው ያሉ ነዳያን ሳይርባቸው: ሠራተኞችም ደሞዝ
ሳይቸግራቸው: 80ው አብያተ ክርስቲያናት በፈጣሪ
ረዳትነት: በ10 ዓመታት ታነጹ::

+ቀጥሎም ንጉሡ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ በዓለም ያሉ
ታላላቅ ቅዱሳን ሊቃነ ዻዻሳትን ጠርቶ: ሁሉም እስከ
መስከረም 15 ቀን ወደ ኢየሩሳሌም በተሰበሰቡበት
የሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ቅዳሴ ቤት በአንድ ላይ
ሲከበር ከዝማሬው ብዛት: ከአምላክ ጸጋ የተነሳ
በከተማዋ ታይቶ የማይታወቅ ሐሴት ተደረገ::

*ኢየሩሳሌም ፍጹም አጊጣ እስከ መከራ ቀን (አሕዛብ እስከ ተነሱበት) ቆይታለች::

+"+ #ቅዱስ_ጦቢት (ጻድቅ ነቢይ) "+

=>ከክርስቶስ ልደት በፊት እሥራኤላውያን ክፋትን
ሲያበዙ ጠላት መጥቶ ይማርካቸው: ንስሃ ሲገቡ ደግሞ
በድንቅ ተአምር ይወጡ ነበር:: ሕዝቡ ሲማረክ ነቢያት
እረኞች ናቸውና ያለ ጥፋታቸው አብረው ይማረኩ ነበር::
በዚያም ሕዝቡን ያስተምራሉ: ያጽናናሉ::

+በተመሳሳይ እሥራኤላውያን ተማርከው ወደ #ነነዌ
በወረዱበት ወራት ጦቢት የሚሉት ደግ ሰው
በመካከላቸው ነበር:: ይህ ደግ ሰው ከምርኮ በፊት
መልካም አምልኮት የነበረው: አሥራቱን በኩራቱን
የሚያወጣ: ለነዳያን የሚራራ ነበር::

+ከተማረኩ በሁዋላም ሕዝቡ ከአሕዛብ ጋራ ሲቀላቀሉ
እርሱ ንጽሕናውን ጠብቆ እግዚአብሔርን ያመልክ ነበር::
ቅዱስ ጦቢት በተለይ የሞተ ሰው ሲያገኝ ሳይቀብር
እህል አይቀምስም ነበር:: በዚህም ምክንያት የዘወትር
ጦመኛ ነበር::

+ይሕ ቅዱስ እድሜው 58 በሆነ ጊዜ ዓይኑ ጠፋ:: ብዙ
በመሰቃየቱም ሞቱን ለመነ:: በሌላ አቅጣጫ ደግሞ
#ሣራ 'አስማንድዮስ' የሚባል ጋኔን 7 ባሎቿን እየገደለ
አሳቅቁዋት ነበርና እርሷም ሞቷን ተመኘች::

+እግዚአብሔር ግን መልአኩን ልኮ: #ቅዱስ_ሩፋኤል
አዛርያን መስሎ የጦብያና የሣራን ጋብቻ ባርኩዋል::
ጋኔኑንም በጥልቁ አስጥሞታል:: በዓሣ ሐሞትም
የጦቢት ዓይኑ በርቶለት በእድሜው ላይ 100 ዓመታት
ተጨምረውለታል:: ቅዱስ ጦቢት ብዙ ሕብረ ትንቢቶችን
ተናግሮ በ158 ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፏል::

+"+ #አባ_አጋቶን_ባሕታዊ +"+

=>ይህንን ቅዱስ የማያውቅ የቤተ ክርስቲያን ሰው
ይኖራል ብየ አልገምትም:: እርሱ ታላቅ ጻድቅ: ገዳማዊና
የእግዚአብሔር ሰው ሲሆን አንደበቱን ከክፋት ይከለክል
ዘንድ ለ30 ዓመታት ድንጋይ ጐርሶ ኖሯል::

+ይህንን ቅዱስ #ሊቃውንት ሲገልጹት "ክምረ ክምር
ጽድቁ እስከ አስተርአየ" ይሉታል:: ትእግስቱ: ደግነቱ:
አርምሞው: ትሩፋቱ ከመነገር በላይ ነው:: በነበረበት
በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም እንደ ኮከብ ያበራ ታላቅ አባት
ነው::

=>አምላከ ቅዱሳን የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያንን
ሰላምና ደስታ ያሳየን:: ከበዓላቱ ከሚገኘውም ጸጋ
በረከት አይለየን::

=>መስከረም 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን
በዓላት=
1.ሕንጸታ ለኢየሩሳሌም
2.ቅድስት እሌኒ ንግሥት
3.ቅዱስ ጦቢት ነቢይ
4.ቅዱሳን ጦብያና ሣራ
5.አባ አጋቶን ባሕታዊ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ (የቅ/
ላሊበላ ወንድም)
4.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
5.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
6.አባ ዳንኤል ጻድቅ
7.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ)

=>+"+ ወደ #እግዚአብሔር ቤት እንሒድ ባሉኝ ጊዜ
ደስ አለኝ::
#ኢየሩሳሌም ሆይ እግሮቻችን በአደባባይሽ ቆሙ::
ኢየሩሳሌምስ እርስ በርሷ እንደ ተገለጠች ከተማ
ተሠርታለች . . .
ስለ ወንድሞቼ ስለ ባልንጀሮቼም በውስጥሽ ሰላም ይሁን
አልሁ::
ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ቤት ላንቺ
መልካምነትሽን ፈለግሁ:: +"+ (መዝ. 121:1-9)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
@petroswepawulos
††† እንኳን ከዘመነ ክረምት ወደ ዘመነ መጸው አሸጋግሮ ለቅዱስ ዮናስ ነቢይ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ስንዱ #እመቤት #ቤተ_ክርስቲያን (ሃገራችን) ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ትጠቀማለች:: እሊሕም ዘመናት #መጸው (ጽጌ): #ሐጋይ (በጋ): #ጸደይ (በልግ) ና ክረምት ናቸው:: ዘመናቱ ወቅቶችን ከመለየትና ማሳወቅ ባሻገር የእኛ ሕይወትም ምሳሌዎች ናቸውና ልብ ልንላቸው ይገባል::

#ዘመነ_መጸው / #ወርኀ_ጽጌ/ #ጥቢ እየተባለም ይጠራል:: በዚህ ወቅት ምድር በአበባ የምታጌጥበት: ክረምት የተለፋበት አዝመራ የሚደርስበት በመሆኑ ደስ ያሰኛል:: በጊዜውም:-
1.የእመቤታችን የቅድስት #ድንግል_ማርያም ስደቷ ይታሠባል:: እርሷ ስለ እኛ:-
*የሕይወት እንጀራን ተሸክማ መራቧን::
*የሕይወት መጠጥን ይዛ መጠማቷን::
*የሕይወት ልብስን አዝላ መራቆቷን::
*ሙቀተ መንፈስ ቅዱስን የሚያድለውን ተሸክማ ብርድ መመታቷን እናስባለን::
*ዘመኑ የበረከት ነው::

2.በሌላ በኩል ጊዜው ወርኀ ትፍሥሕት (የደስታ ወቅት) ነው:: በክረምት የደከመ ዋጋውን አግኝቶ: በልቶ: ጠጥቶ ደስ ይለዋልና:: ያልሠራው ግን ከማዘን በቀር ሌላ እድል የለውም:: ይኼውም ምሳሌ ነው::

ዘመነ ክረምት የዚህ ዓለም ምሳሌ: ዘመነ መጸው ደግሞ የመንግስተ ሰማያት:: በዚህ ዓለም ምግባር ትሩፋትን የሠራ በወዲያኛው ዓለም ተድላን ሲያደርግ ሰነፎች ኃጥአን ግን እድል ፈንታቸው: ጽዋ ተርታቸው ከግብዞች ጋር የመሆኑ ምሳሌ ነው::

በወርኀ ትፍስሕት እንደ ሊቃውንቱ እንዲህ ብለን ልንጸልይ ይገባል::
"ድኅረ ኀለፈ ክረምት ወገብአ ዝናም: ዘአስተርአይከ እግዚኦ ጽጌያተ ገዳም:
አፈወ ሃይማኖት ነአልድ ወፍሬ ምግባር ጥዑም:
አትግሃነ ለስብሐቲከ ከመ ትጋሆሙ አዳም:
ለጽብስት ንሕብ ወነአስ ቃሕም::"

††† የዘመናት ባለቤት ዘመነ መጸውን #ወርኀ_ትፍስሕት ያድርግልን::

††† ቅዱስ ዮናስ ነቢይ †††

††† ዮናስ ማለት 'ርግብ: የዋህ' ማለት ሲሆን ከ12ቱ #ደቂቀ_ነቢያት አንዱ ነው:: በሰራፕታ ተወልዶ ያደገው ነቢዩ በልጅነቱ ታሞ ሙቶ ነበር:: ታላቁ ነቢይ #ኤልያስ ግን 7 ጊዜ ጸሎት አድርጐ ከሞት አስነስቶታል:: (1ነገ. 17:17) እናቱ የሰራፕታዋ መበለትም ደግ ሴት ነበረች::

ቅዱስ ዮናስ በእድሜው ከፍ ሲል የቅዱስ ኤልያስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: የነ ኤልሳዕና አብድዩም ባልንጀራ ነበረ:: ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ካረገ በሁዋላ: ቅ.ል.ክርስቶስ በ800 ዓመት አካባቢ የነነዌ ሰዎች ኃጢአት ከመሥፈርቱ በማለፉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ መጣ::

"ሒድና ለነነዌ ሰዎች ንስሃን ስበክላቸው" አለው:: ከነቢያት ወገን ከሙሴና ከዳዊት ቀጥሎ የዮናስን ያህል የዋህ (ገራገር) የለምና እንቢ አለ (ሰምቶ ዝም አለ):: #እግዚአብሔር እየደጋገመ ሲናገረው ግን "እንዲህ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል!" ብሎ ወደ #ተርሴስ ኮበለለ::

ወገኖቼ አንድ ነገርን ልብ እንበል:: እንኩዋን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዮናስ እኛ ክፉዎችም ከጌታ ፊት መሸሸት እንደማይቻል ጠንቅቀን እናውቃለን:: ታዲያ ለምን ሸሸ ቢሉ:- ጥበበ እግዚአብሔር በውስጡ ስለ ነበረበት ነው::

ምክንያቱም ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ 3 ቀን እና ሌሊት ኖሮ: ሙስና (ጥፋት) ሳያገኘው መውጣቱ ለጌታ ትንሳኤ ጥላ (ምሳሌ) ነው:: ለዚህም ምስክሩ ራሱ ጌታችን ነው::
"ወበከመ ነበረ #ዮናስ ውስተ ከርሠ አንበሪ ሠሉሰ ዕለተ ወሠሉሰ ለያልየ: ከማሁ ይነብር ወልደ እጉዋለ እመ ሕያው ውስተ ልበ ምድር ሠሉሰ ዕለተ: ወሠሉሰ ለያልየ" እንዲል:: (ማቴ. 12:39)

ቅዱስ ዮናስ በገንዘቡ ዋጅቶ ወደ መርከብ በገባ ጊዜ ታላቅ ማዕበል ሆነ:: የእምነት ሰው ነውና እንዲያ እየተናወጡ እርሱ በእርጋታ ተኝቷል:: እነርሱ ግን ቀስቅሰው ቢጠይቁት (እጣ ወድቆበታልና) "የእኔ ጥፋት ስለ ሆነ ወደ ማዕበሉ ጣሉኝ" አላቸው::

እያዘኑ ቢጥሉት ታላቅ ጸጥታ ሆነ:: እነዚያ አሕዛብም እግዚአብሔርን በመስዋዕትና በስዕለት አከበሩ:: ዮናስ ግን በማዕበልና በአሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ለ3 ቀናት ጸለየ:: አሣ አንበሪው በ3ኛው ቀን ወደ ነነዌ ተፋው::

ቅዱሱም "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ #ነነዌ ዐባይ ሃገር" እያለ ንስሃን ሰበከ:: የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸውን አምነው ቢጸጸቱ ከሰማይ ወርዶ ከደመና ደርሶ የነበረው የእሳት ማዕበል ተመልሶላቸዋል::

የነቢዩ ትንቢት ግን አልቀረምና ታላቋ ነነዌ ከ300 ዓመታት በሁዋላ ጠፍታለች:: ቅዱስ ዮናስ ግን በቀሪ ዘመኑ ፈጣሪውን እያገለገለ ኑሯል:: ጠቅላላ እድሜውም 170 ዓመት ነው::

††† አምላከ ቅዱስ ዮናስ እድሜ ለንስሃ: ዘመን ለፍስሃ አይንሳን:: ከበረከቱም ይክፈለን::

††† መስከረም 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ጸአተ ክረምት (የክረምት መውጫ)
2.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ
3.ቅዱስ እንጦንዮስ
4.ቅድስት በርባራ
5.ሐዋርያት ዼጥሮስ ወዻውሎስ
6.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
7.ታላቁ አባ ቢጻርዮን ገዳማዊ

††† "ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ: እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ::" †††
(ማቴ. 12:39)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
@petroswepawulos
✞✞✞✝️ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ✝️ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✝️ሐምሌ ፲፪✝️

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱስ "ሚካኤል ሊቀ መላእክት"
የተአምር በዓልና ለሰማዕቱ "አባ ሖር" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" ተአምረ ቅዱስ ሚካኤል "*+

=>ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን በዚህች ዕለት የመላእክት
ሁሉ አለቃቸው: የቅዱሳንም ረዳታቸው የሆነው ደጉ
መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ንጉሡን ሕዝቅያስን ግሩም
በሆነ ተአምር ከከተማው #ኢየሩሳሌም ጋር ታድጐታል::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ከመድኃኒታችን #ክርስቶስ ልደት 700 ዓመታት በፊት
#ሕዝቅያስ የሚባል ንጉሥ በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር::
ደጋጉ #ዳዊትና #ሰሎሞን ካረፉ በሁዋላ የሕዝቅያስን
ያክል ቅን እና የእግዚአብሔር ሰው በእሥራኤል ላይ
አልነገሰም:: ንጉሡ ጣዖት አምልኮን ነቃቅሎ አጥፍቶ
ሕዝቡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ አድርጐም
ነበር::

+ነገር ግን ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት
የአሕዛብ (የአሦር) ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት::
ወደ አካባቢውም መጥቶ: ከቦ አስጨነቀው:: ሰናክሬም
በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር:: በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ
ከ185,000 በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ
እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት::

+"እገብርልሃለሁ:: የፈለግከውንም እሰጥሃለሁ:: ሃገሬን
ግን አታጥፋ:: ኢየሩሳሌምን አታቃጥል:: ሕዝቤንም
አትግደል" በሚል ለመነው:: እጅ መንሻ ግብሩንም
ከከተማዋ የተገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ ጭኖ ላከለት::

+ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን
ልመና ወደ ጐን ብሎ የእሥራኤልን አምላክ : ቅዱስ
ስሙንም ተገዳደረ:: ለሕዝቅያስም "ከእኔ እጅ የሚያድንህ
ማነው? ሕዝቡንም #እግዚአብሔር ያድናል ብለህ
አታታልላቸው" ሲል ላከበት:: ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ
የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ::

+መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ #ቅዱስ_ኢሳይያስ ልኮ እርሱ
ወደ ቤተ መቅደስ ገባ:: በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን
ቀድዶ ማቅ ለበሰ:: ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ
አለቀሰ:: በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰናክሬምን
መገዳደርና የሕዝቅያስን ልመና ሰምቷልና በኢሳይያስ
አንደበት እንዲሕ አለ:- "ስለ ባሪያየ ስለ #ዳዊት
ከተማዋን አድናታለሁ::"

+በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል
ከሰማያት በግርማ ወረደ:: ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር
ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው
ከአሕዛብ ሠራዊት 185 ሺ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ::
በለኪሶ የነበረው ሰናክሬም በጧት ቢነሳ ሠራዊቱ ሁሉ
ወደ አስከሬን ክምር ተቀይሯል::

+በድንጋጤ ወደ #ነነዌ ሒዶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሲገባ የራሱ
ልጆች (አድራማሌክና ሳራሳር) ገደሉት:: ትዕቢተኛው
ሰናክሬም ለአሕዛብ ሁሉ መዘባበቻ ሆነ:: ቅዱስ ሕዝቅያስ
ግን በፈጣሪው ታምኗልና ቅዱስ ሚካኤል ሞገስ ሆኖ
የዓለም ነገሥታት ሁሉ ፈሩት:: (1ነገ. 18:13, 19:1)

+*" ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት "*+

=>ዳግመኛ በዚህ ቀን #አባ_ሖር ሰማዕቱ ይታሠባል::

+ቅዱሱ:-

¤ስርያቆስ በምትባል የግብጽ አውራጃ ተወልዶ ያደገ:
¤ገና በልጅነቱ መንኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ:
¤ዘመነ ሰማዕታት በመጣ ጊዜም በመኮንኑ ፊት ቀርቦ
በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያመነ:
¤ከመኮንኑም ብዙ ስቃይ የደረሰበት:
¤ብዙ ተአምራትን በመስራቱ ያሰቃየው የነበረውን መኮንን
ወደ ክርስትና መልሶ ለሰማዕትነት ያበቃ አባት ነው::

+እርሱም የሰማዕትነትን ክብር በእጅጉ ሽቷታልና ወደ ሌላ
ሃገር ሒዶ በዚህች ቀን አንገቱን ተሰይፎ የክብርን አክሊል
ተቀዳጅቷል:: በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ያሳመናቸው 127
ወንዶችና 20 ሴቶችም አብረውት ተሰይፈዋል::

=>እግዚአብሔር በሊቀ መላእክት ክንፍ ሃገራችንን
ከአሕዛብ ስውር ጦር ይጠብቅልን:: ከሰማዕቱም በረከት
ያሳትፈን::

=>ሐምሌ 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሕዝቅያስ ንጉሥ
2.ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
3.ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት
4."147" ሰማዕታት (የአባ ሖር ማሕበር)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
3.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ድሜጥሮስ
5.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
6.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
7.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
8.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

=>+"+ እግዚአብሔር ይላል:- ስለ እኔም ስለ ባሪያየም
#ስለ_ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ::
በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ::
ከአሦራውያንም ሠፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ::
ማለዳም በተነሱ ጊዜ እነሆ ሁሉ በድኖች ነበሩ:: +"+
(1ነገ. 19:34)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>