መዝገበ ቅዱሳን
25.5K subscribers
1.97K photos
9 videos
6 files
27 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
#ጥቅምት_15

ጥቅምት ዐሥራ አምስት በዚች ቀን #ቅዱሳን_ሐዋርያት ዓለምን በእጣ ለ12 የተካፋፈሉበት እና ከኒቆምድያ አገር #ቅዱስ_ቢላሞን በሰማዕትነት ያረፈበት ቀን ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#12ቱ_ቅዱሳን_ሐዋርያት

ጥቅምት ዐሥራ አምስት በዚች ቀን ቅዱሳን ሐዋርያት ዓለምን በእጣ ለ12 የተካፋፈሉበት ዕለት ነው። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከእመቤታችን በቀር ከቅዱሳን ሐዋርያት የሚበልጥ አልተነሳም። "ሐዋርያ" ማለት "ፍንው፣ ልዑክ፣ የተላከ፣ የጽድቅ መንገደኛ" እንደ ማለት ነው። በምሥጢሩ ግን "ባለሟል" ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል።

ይህስ እንደምን ነው ቢሉ:-

የፍጥረታት ሁሉ ጌታ የክብር ባለቤት መድኃኔዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ አድጐ፣ ተጠምቆ፣ ጾሞ ከገዳመ ቆረንቶስ ሲመለስ ቀዳሚ ሥራው ያደረገው ደቀ መዛሙርቱን መጥራት ነበር::

ከተከተሉት የ5 ገበያ ሕዝብ መካከል "ወሐረየ እምሰብአ ዚአሁ አሠርተ ወክልኤተ ሐዋርያተ" እንዲል በመጀመሪያ 12ቱን ሐዋርያት መረጠ። እሊህም:- #ዼጥሮስ የተባለ ስምኦን፣ #እንድርያስ (ወንድሙ)፣ #ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ፣ #ዮሐንስ (ወንድሙ)፣ #ፊልዾስ#በርተሎሜዎስ#ቶማስ#ማቴዎስ#ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ፣ #ታዴዎስ (ልብድዮስ)፣ #ናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን) እና #ማትያስ (በይሁዳ የተተካው) ናቸው። (ማቴ. 10፥1)

እነዚህን 12 አርድእቱን ከጠራ በሁዋላ ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ከዋለበት ሲማሩ ይውሉ ነበር። ሌሊት ደግሞ ምሥጢር ሲያስተረጉሙ ያድሩ ነበር።

ጌታ እንደሚገባ ካስተማራቸው በሁዋላ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ሾማቸው። ለዓለም እረኞች የእርሱም ባለሟሎች ሆኑ። እጅግ ብዙ መከራ እንደሚገጥማቸው ነገራቸው። (ማቴ.10፥16, ዮሐ.16፥33) በዚያው ልክ ክብራቸውንም አከለላቸው። (ማቴ. 19፥28) ሥልጣንም "በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል።" (ማቴ. 18፥18) "ይቅር ያላችኋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል፤ ያላላችኋቸው ግን አይቀርላቸውም።" (ዮሐ.20፥23) ብሎ ሰጣቸው።

የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ (ማቴ. 16፥19)፣ እረኝነትን (ዮሐ. 21፥15) ተቀበሉ። ጌታ በንጹሕ አንደበቱ ሐዋርያቱን እጅግ ሲያከብራቸው "ጨው፣ የዓለም ብርሃናት" (ማቴ. 5፥13) አላቸው። ወንድሞቹም ተባሉ። (ዮሐ.7፥5) ከዚህም በሚበልጥ በሌላ ክብር አከበራቸው።

ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ በጌታ ሕማማት ጊዜ ገና ነበሩና አንዳንዶቹ ፈርተው ተበተኑ። ተመልሰው ግን በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩ ሰንብተው የጌታን ትንሳኤ ተመለከቱ። እጆቹን፣ እግሮቹንም ዳስሰው ሐሴትን አደረጉ።

ለ40 ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትምሕርተ ኅቡዓት፣ ሌላም በፍጡር አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢራትን ተምረው ጌታ ሊቀ ጵጵስናን ሹሟቸው ዐረገ።

ለ10 ቀናት በእመብርሃን ሥር ተጠልለው ሲጸልዩና በአንድ ልብ ሲተጉ ሰንብተው መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው። በአንዴም ከፍርሃት ወደ ድፍረት ተመልሰው ፍጹማን ብርሃናውያን ሆኑ። 71 ልሳናትን ነስተው በአንዲት ስብከት ብቻ 3ሺ ነፍሳትን ማረኩ። (ሐዋ.2፥41)

ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እየተመላለሱ አስተምረው ብዙ እሥራኤላውያንን ወደ ክርስትና ማርከዋል። ከዚህ በኋላ ግን እንደ ትውፊቱ በዚህች ቀን ዓለምን በእጣ ለ12 ተካፈሏት።

ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው ነበርና ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው አሕጉረ ስብከቶች ደረሷቸው። እነርሱም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አስከትለው ለታላቁ መንፈሳዊ ዘመቻ ወረዱ።

በሔዱበት ቦታም ከተኩላ፣ ከአንበሳና ከነምር ጋር ታገሉ። በጸጋቸውም አራዊትን (ክፉ ሰዎችን) ወደ በግነት መልሰው ለክርስቶስ አስረከቡ። በየሃገሩ እየሰበኩ ድውያንን ፈወሱ፣ ለምጻሞችን አነጹ፣ እውራንን አበሩ፣ አንካሶችን አረቱ፣ ጐባጦችን አቀኑ፣ ሙታንንም አስነሱ፣ እልፍ አእላፍ አሕዛብንም ወደ መንጋው ቀላቀሉ።

ስለዚህ ፈንታም ብዙዎቹ በእሳት ተቃጠሉ፣ ቆዳቸው ተገፈፈ፣ በምጣድ ተጠበሱ፣ ደማቸው በምድር ላይ ፈሰሰ፣ ከአንድ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር ሁሉም ይህችን ዓለም በሰማዕትነት ተሰናበቱ። ጨው ሆነው አጣፍጠዋልና ብርሃንም ሆነው አብርተዋልና እናከብራቸዋለን። "አባቶቻችን፣ መምሕሮቻችን፣ ጌቶቻችንና ሊቆቻችን" እንላቸዋለን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቢላሞን

ዳግመኛም በዚች ቀን ከኒቆምድያ አገር ቅዱስ ቢላሞን በሰማዕትነት አረፈ።

የዚህም ቅዱስ አባቱ ጣዖት አምላኪ ነው እናቱ ግን ክርስቲያን ናት ጥበብንም አስተማሩት ከዚህም በኋላ ስሙ አርማላስ ከሚባል ቄስ ጋር ተገናኘ። እርሱም ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የቀናች ሃይማኖት አስተማረው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቀው ታላቅ የሆኑ ድንቆች ታምራትን የማድረግ ሀብትን እግዚአብሔር እስከ ሰጠው ድረስ በጾም በጸሎት ታላቅ ገድልን ተጋደለ።

በአንዲት ቀንም ለዓይኖቹ መድኃኒትን እንዲአደርግለት አንድ ዕውር ሰው ወደርሱ መጣ ቅዱስ ቢላሞንም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያለ በዕውሩ ዐይኖች ላይ የመስቀልን ምልክት አደረገ ያን ጊዜ ዐይኖቹ ድነው አየባቸው ጤነኛም ሆነ።

ንጉሥም ዐይኖቹ የተገለጡለትን የዚያን ዕውር ዜና በሰማ ጊዜ ወደርሱ አስቀረበውና ዐይኖችህን ማን አዳነህ ብሎ ጠየቀው እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት ቅዱስ ቢላሞን ፈወሰኝ እርሱ እጁን በዐይኖቼ ላይ አድርጎ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እያለ በመስቀል ምልክት አማተበብኝ ያን ጊዜ አየሁ ይህንንም ብሎ እኔ ክርስቲያን ነኝ እያለ በንጉሡ ፊት በግልጽ ጮኸ።ንጉሡም ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡት የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ከዚህም በኋላ ወታደር ልኮ ቅዱስ ቢላሞንን አስቀረበው ስለ ሃይማኖቱም በጠየቀው ጊዜ እርሱም ክርስቲያን ነኝ ብሎ በፊቱ ታመነ ንጉሡም ብዙ ሽንገላን በመሸንገል አባበለው። ብዙ ቃል ኪዳንም ገባለት ባልሰማውም ጊዜ በእርሱ ላይ ተቆጥቶ ድምፁን ከፍ አድርጎ ካልሰማኸኝ እኔ ጽኑ ሥቃይን አሠቃይሃለሁ አለው። ቅዱስ ቢላሞንም እኔ ከሥቃይህ የተነሣ ፈርቼ ሃይማኖቴን ለውጬ ፈጣሪዬን አልክድም አለው።

ከዚያችም ቀን ጀምሮ በብዙ አይነት ሥቃይ በብዙ ቀኖች ውስጥ ማሠቃየትን ጀመረ። በግርፋት በስቃላትም በባሕር ስጥመትም ወደ እሳት በመወርወርም የሚያሠቃይበት ጊዜ አለ።

በዚህም ሥቃይ ውስጥ ሳለ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጠመቀው ቄስ በአርሜላዎስ አምሳል ተገልጾለት እንዲህ የሚል የደስታ ቃል አሰማው። የመረጥኩህ ቢላሞን ሆይ ደስ ይበልህ እኔ ሰማያዊ መንግሥትን አዘጋጅቼልሃለሁና።

የንጉሡ ጭፍሮችም ይህን የደስታ ቃል ሰሙ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አምነው እነርሱ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የአመኑ መሆናቸውን በንጉሡ ፊት ገለጡ በዚያንም ጊዜ ራሳቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ ንጉሡ አዘዘ። ቅዱስ ቢላሞንንም እንዲቆርጡት አዘዘ ከእሊህ ጭፍሮች ጋርም እንዲህ ገድሉን ፈጸመ ቁጥራቸውም መቶ ኀምሣ ስምንት ነው የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)