መዝገበ ቅዱሳን
25.5K subscribers
1.97K photos
9 videos
6 files
27 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
#ነሐሴ_12

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ #ቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #ቅዱስ_ቈስጠንጢኖስ ወደ ሮሜ ከተማ ገባ በሮሜ አገሮችም ሁሉ ላይ ነገሠ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሚካኤል_ሊቀ_መላእክት

ነሐሴ ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

በዚች ቀን እግዚአብሔር ወደ ዕሌኒ ልጅ ወደ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ልኮታልና ለእርሱም ጠላቶቹን እስከ አሸነፋቸው መንግሥቱም እስከ ጸናች ድረስ ኃይልን ሰጠው የጣዖታትንም ቤት አፍርሶ አብያተ ክርስቲያናትን ሠራ። በጌጥም ሁሉ አስጌጣቸው።

ስለዚህም አባቶቻችን የቤተክርስቲያን መምህራን የከበረ የመላእክት አለቃ የሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን እናደርግ ዘንድ አዘዙን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ታላቁ_ንጉሥ_ቅዱስ_ቆስጠንጢኖስ

በዚህችም ቀን ቈስጠንጢኖስ ወደ ሮሜ ከተማ ገባ በሮሜ አገሮችም ሁሉ ላይ ነገሠ።

(ዜናውም መጋቢት ሃያ ስምንት ቀን ላይ ተጽፏል።)
የዚህ ቅዱስ የአባቱ ስም ቍንስጣ የእናቱ ስም ዕሌኒ ነው ቊንስጣም በራንጥያ ለሚባል አገር ንጉሥ ነው መክስምያኖስም በሮሜ በአንጾኪያና በግብጽ ላይ ነግሦ ነበር።

ይህም ቍስጣ አረማዊ ነበር ግን በጎ ሥራ ያለው እውነትን የሚወድ በልቡናውም ይቅርታና ርኃራኄን የተመላ ክፋት የሌለበት ነው። ወደሮሐ ከተማ በሔደ ጊዜ ዕሌኒን አይቶ ሚስት ልትሆነው አገባት እርሷም ክርስቲያናዊት ናት። ንጉሥ ቈስጠንጢኖስንም ፀንሳ ወለደችው ስሙንም ቈስጠንጢኖስ ብላ ጠራቸው ይህም ዝንጉርጒር ማለት ነው።

ከዚህም በኋላ ንጉሥ ቊንስጣ ዕሌኒን በዚያው ትቷት ወደ በራንጥያ ከተማ ተመለሰ። እርሷም ልጇን እያሳደገች በዚያው ኖረች የክርስትናን ትምህርት አስተማረችው ይቅርታንና ርኅራኄን በክርስቲያን ወገኖች ላይ እንዲያደርግ በልቡናው ትዘራበት ነበር። እርሷ ክርስቲያን ስትሆን የክርስትና ጥምቀትን ታጠምቀው ዘንድ አልደፈረችም መንፈሳዊ ዕውቀትን ሁሉ በማስተማር አሳደገችው ዳግመኛም ለመንግሥት ልጆች የሚገባውንም ሁሉ።

ከዚያም በኋላ ወደ አባቱ ሰደደችው አባቱም በአየው ጊዜ ደስ ተሰኘበት ዕውቀትን የተመላ ሁኖ ፈረስ በመጋለብም ብርቱና የጸና ሆኖ አግኝቶታልና በበታቹም መስፍን አድርጎ ሹሞ በመንግሥቱ ሥራ ላይ ሁሉ ሥልጣን ሰጠው።

ከሁለት ዓመትም በኋላ አባቱ አረፈ ቈስጠንጢኖስም መንግሥቱን ሁሉ ተረከበ የቀና ፍርድንም የሚፈርድ ሆነ ከእርሱ በፊት የነበሩ ነገሥታት የጫኑባቸውን ጽኑ አገዛዝ ከሰዎች ላይ አስወገደ። አሕዛብም ሁሉ ታዘዙለት ወደዱትም የአገዛዙ ቅንነትና የፍርዱ ትክክለኛነት በአገሮች ሁሉ እስቲሰማ ተገዙለት።

የሮሜ ሰዎች ታላላቆች መልእክትን ወደርሱ ላኩ ከከሀዲ መክስምያኖስ ጽኑ አገዛዝ እንዲያድናቸው እየለመኑ እርሱ አሠቃይቷቸው ነበርና። ነመልእክታቸውንም በአነበቡ ጊዜ ስለ ደረሰባቸው መከራ እጅግ አዘነ ያድናቸውም ዘንድ ምን እደሚያደርግ በዐደባባይ ተቀምጦ እያሰበ ሲያዝን እነሆ ከቀኑ በስድስት ሰዓት በቀትር ጊዜ ኅብሩ እንደ ከዋክብት የሆነ መስቀል ታየው በላዩም በዮናኒ ቋንቋ ኒኮስጣጣን የሚል ጹሑፍ አለ ትርጓሜውም በዚህ ጠላትህን ድል ታደርጋለህ ማለት ነው።

የመስቀሉም ብርሃን የፀሐይን ብርሃን ሲሸፍነው በአየ ጊዜ አደነቀ። በላዩ ስለተጻፈውም አስቦ ለጭፍሮቹ አለቆችና ለመንግሥቱ ታላላቅ ባለሥልጣኖች አሳያቸው። እነርሱም ቢሆኑ ይህ መስቀል ስለምን እንደተገለጠ አላወቁም።

በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ለቈስጠንጢኖስ በራእይ ተገልጦ እንዲህ አለው በቀኑ እኩሌታ በቀትር በአየኸው በዚያ መስቀል አምሳል ላንተ ምልክት አድርግ በርሱም ጠላትህን ድል ታደርጋለህ አለው። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ልቡ ጸና የወርቅ መስቀልም አሠርቶ በነገሠበት ዘውድ ላይ አደረገው መኳንንቱንና ወታደሮቹን ጭፍሮቹን ሁሉ መስቀል ሠርተው በጦር መሣሪያቸው ላይ ያደርጉ ዘንድ አዘዛቸው እነርሱም እንዳዘዛቸው አደረጉ።

ይህም የሆነው በበራንጥያ በነገሠ በሰባተኛ ዓመቱ ነው። የሮሜን ሰዎች ከሥቃያቸው ሊያድናቸው ሠራዊቱን ሰብስቦ ተነሥቶ ወጣ። መክስምያኖስም ሰምቶ በታላቅ ወንዝ ላይም ታላቅ ድልድይ ሠርቶ ወደ ቈስጠንጢኖስም ተሻግሮ ከእርሱ ጋራ ተዋጋ።

የመስቀሉም ምልክት ቀድሞ በታየ ጊዜ የመክስምያኖስ ሠራዊት ድል ይሆኑ ነበር የቈስጠንጢኖስም ሠራዊት ከመክስምያኖስ ሰራዊት ብዙ ሰው ገደሉ። የቀሩትም ሸሽተው ሲሔዱ ከመክስምያኖስ ጋር ሊሻገሩና ወደ ሮሜ ሊገቡ ድልድይ ላይ ወጡ ድልድዩም ፈርሶ ፈርዖን ከሠራዊቱ ጋራ እንደ ሠጠመ እንዲሁ መክስምያኖስ ከሠራዊቱ ጋራ ሠጠመ።

ቈስጠንጢኖስም ወደ ሮሜ ከተማ ሲገባ የሮሜ ሰዎች ከካህናት ጋራ መብራቶች ይዘው በእንቍ የተሸለሙ አክሊሎችን ደፍተው እምቢልታ እየነፉ ተቀበሉት የተማሩ ሊቃውንትም የከበረ መስቀልን ሲያመሰግኑት የሀገራችን መዳኛ ይሉት ነበር ለከበረ መስቀልም ሰባት ቀን በዓል አደረጉ።

ቈስጠንጢኖስም ዳግመኛ በሮሜ ነገሠ ከሀዲዎች የሆኑ መክስምያኖስና ዲዮቅልጥያኖስ ስለ ክብር ባለቤት ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት ያሠሩአቸውን እሥረኞች ሁሉንም ፈታቸው ደግሞ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ ብሎ ዓዋጅ አስነገረ።

ዳግመኛም ክርስቲያኖችን እንዲአከብሩአቸው እንጂ እንዳያዋርዱአቸው የጣዖታቱንም ገንዘብና ምድራቸውን ለካህናት እንዲሰጧቸው አዘዘ ክርስቲያኖች በአረማውያን ላይ እንዲሾሙ አደረገ። ዳግመኛም አባቶቻችን ሐዋርያት እንዳዘዙ ማንም ሰው በሰሙነ ሕማማት ሥራ እንዳይሠራ አዘዘ።

በነገሠ በሥስራ አንድ ዓመት በሮሜ ሊቀ ጳጳሳት በሶል ጴጥሮስ እጅ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ። ሠራዊቱም ሁሉ። ይህም የከበረ መስቀል ከተገለጠለት በኋላ በአራት ዓመት ነው።

ከዚህ በኋላም በእርሱ ርዳታና ድል ያገኘበትን የሚያድን ስለ ሆነ ስለ ጌታችን መስቀል ትመረምር ዘንድ እናቱ ዕሌኒን ወደ ኢየሩሳሌም ላካት። እርሷም ዐመፀኞች አይሁድ ቀብረው ከደፈኑት ቦታ አወጣችው።

በዘመኑ ሃይማኖታቸው የቀና የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ጳጳሳት የአንድነት ስብሰባ በኒቅያ ስለ አርዮስ ተደረገ። ለክርስቲያኖች መመሪያ በበጎ አሠራር ክርስቲያናዊት ሥርዓት ተሰራች።

ከዚህም በኋላ በበራንጥያ ታላቅ ከተማ ሊሠራ አሰበ እንደ አሰበውም ታላቅ ከተማ ሠርቶ በስሙ ቍስጥንጥንያ ብሎ ጠራት። በውስጧም አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በአግያና በሶፍያም ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሠራ መንፈሳዊ በሆነ በመልካም ጌጥ ሁሉ አስጌጣት። በውስጥዋ ከሐዋርያት የብዙዎቹን ዓፅም ከሰማዕታትና ከቅዱሳን ጻድቃን ሥጋቸውን ስለሚሰበስብ።

የክብር ባለቤት ጌታችንን ደስ አሰኝቶ መልካም ተጋድሎውን ከፈጸመ በኋላ በኒቆምድያ ከተማ ጥቂት ታሞ መጋቢት ሃያ ስምንት አረፈ።

ገንዘውም በወርቅ ሣጥን አድርገው ተሸክመው ወደ ቊስጥንጥንያ አደረሱት የጳጳሳት አለቆችና ካህናቱ ከሁሉ ሕዝብ ጋር ወጥተው ተቀበሉት በብዙ ጸሎት በመዘመርና በማኅሌት በምስጋና ወደ ከበሩ ሐዋርያት ቤተ መቅደስ አስገብተው በክብር አኖሩት።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_እና_መጋቢት)
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5
#ነሐሴ_13

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ሦስት #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን #በደብረ_ታቦር የገለጠበት ዕለት ነው፣ #የቅዱስ_ሙሴ_ሊቀ_ነቢያት ልደቱ ነው፣ ተጋዳይ #አባ_ጋልዩን አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ደብረ_ታቦር

ነሐሴ ዐሥራ ሦስት በዚች ቀን ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅና ክቡር በዓል ነው።

በዚች ቀን መድኃኒታችን ሦስቱን ደቀ መዛሙርቶቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ላይ አወጣቸው። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ። ስለ እነርሱም ጌታችን የሰው ልጅ በጌትነቱ ሲመጣ እስከሚያዩት ድረስ በዚህ ከቆሙት መካከል ሞትን የማይቀምሱት አሉ አለ።

ሰዎች ሁሉ እርሱ ለሙሴ ጌታውና ከሞት ያስነሣው እንደሆነ ለኤልያስም ፈጣሪው እንደሆነና ካሳረገበትም ያወረደው እርሱ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ እነሆ ከጌታ ከኢየሱስ ጋራ እየተነጋገሩ ሙሴና ኤልያስ ወደርሱ መጡ።
ስለዚህም ጴጥሮስ ጌታችንን እንዲህ አለው አቤቱ በዚህ ትኖር ዘንድ ትወዳለህን ሦስት ሰቀላዎችንም አንድ ላንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ እንሠራ ዘንድ።

በዚህም ቃል የደካማነትና የትሕትና ምልክት አለበት። ደካማነት የተባለ ጴጥሮስ ጌታችን ከሰማይ የወረደበትን ሥራ ትቶ በተራራ ላይ ይኖር ዘንድና ራሱን የሚሠውርበትን ቤት ይሠራለት ዘንድ የተናገረው ነው። ትሕትና ያልነውም ጴጥሮስ ለራሱና ለባልንጀሮቹ ሐዋርያት ቤት ይሠራ ዘንድ ስለ አላሰበ ነው። ራሱንና ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን እንደ ባሮች ነቢያትን ደግሞ እንደ ጌቶች አድርጎ አስቧልና።

ሰለ ሐዋርያትም የእውቀት ማነስ አታድንቅ በዚያን ጊዜ ፍጹማን አልሆኑምና። እንዲህም በሚልበት ጊዜ ጌታችን በሰው እጅ የተሠራ ማደሪያን የማይሻ መሆኑን ለጴጥሮስ ያሳየው ዘንድ እነሆ ደመና ጋረዳቸው።

የጌታችንን ጌትነቱን የሚገልጽ በሐዋርያትም ልቡና እምነትን የሚያጸና እንዲህ የሚል ቃል ከደመና ውስጥ መጣ። ይህ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው እርሱንም ስሙት።

ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋራ ሲነጋገሩ ተሰሙ ስለ ርሱ መምጣት የተናገሩትን ትንቢታቸውንም በቸርነቱ አረጋገጠ። ወደ ተራራ ላይ በመውጣቱም ነቢያትና ሐዋርያት ደስ አላቸው።

ሁለተኛም የአብን ቃል በሰሙ ጊዜ ከእነርሱ ሥውር የነበረ የወልድ ዋሕድን በእውነት ሰው መሆን በዚያን ጊዜ ተረዱ ያን ጊዜ የጌትነቱ ክብር ተገልጦአልና። ሐዋርያትም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የሆነ እርሱ ሙሴን ከመቃብር ያስነሣው ኤልያስንም ያሳረገው አውርዶም ያመጣው እርሱ እንደሆነ አወቁ። ከእርሱ በቀር ማንም ማን የሙሴን መቃብር የሚያውቅ የለምና ከዐሳረገው ከእርሱ በቀር ማንም ማን ኤልያስ ያለበትን የሚያውቅ የለምና። በሰማይና በምድር ሥልጣን ካለው ከሁሉ ጌታ በቀር ሙታንን አድኖ ሊአስነሣቸው ማንም አይችልም።

ደብረ ታቦርም የቤተ ክርስቲያን አምሳል ሆነች ከብሉይና ከሐዲስ በውስጧ ሰብስባለችና። የአብንም ቃል በሰሙ ጊዜ በግምባራቸው ፍግም ብለው በምድር ላይ ወደቁ እንደ ሙታንም ሆኑ። ከዓለም አስቀድሞ ከእርሱ ጋራ በህልውና እንዳለ ለልጁ አብ ምስክርን ሆነ ወዲያውኑ ሙሴ ወደ መቃብሩ ኤልያስም ወደ ቦታው ተመለሱ።

ሐዋርያትንም በአነቃቸው ጊዜ ከብቻው ጌታችን በቀር ማንንም አላገኙም። ከባሕርያችን የተዋሐደና ሥጋችንን የለበሰ ፍጹም አምላክ እንደሆነ በዚህ ሐዋርያት አስተማሩ።

እንግዲህ እናስተውል ሰው ካልሆነ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታቸንን ድንግል ማርያምን በአበሠራት ጊዜ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው እንዴት አላት። አምላክ ካልሆነስ ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም እንዴት አላት። ሰው ካልሆነ በበረት እንዴት አስተኙት። አምላክስ ካልሆነ መላእክት ከሰማይ ወርደው ለእግዚአብሔር በሰማያት ምስጋና በምድርም ሰላም ለሰውም ግዕዛኑ ሊሰጠው እያሉ እንዴት አመሰገኑ።

ሰው ካልሆነ ዮሐንስ በውኃ እንዴት አጠመቀው አምላክስ ካልሆነ አልዓዛርን ከመቃብር እንዴት ሊያስነሣው ቻለ። ይህ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው እንድ ልጅ አካላዊ ቃል እግዚአብሔር እርሱ ያለ መለወጥ ያለ መለየት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው እንደሆነ እናምንበታለን። እርሱም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ሁል ጊዜ አንድ ህላዌ ነው ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሙሴ_ሊቀ_ነቢያት

በዚችም ቀን የቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት ልደቱ ነው።

ዓለም በተፈጠረ በ3,600 ዓመት እሥራኤል በረሃብ ምክንያት ያዕቆብ ወደ ምድረ ግብፅ ወረደ:: በዚያም ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ለ215 ዓመታት ተከብረው ለ215 ዓመታት ደግሞ በባርነት በድምሩ ለ430 ዓመታት በምድረ ግብፅ ኑረዋል። በባርነት ዘመናቸውም 'ራምሴና ጋምሴ' የሚባሉ 2 ከተሞችን (ዛሬ ፒራሚዶች የምንላቸውን) በደም ገንብተዋል። ግፋቸው እየበዛ ሲሔድ ግን ጩኸታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ። ያድናቸውም ዘንድ አንድ ቅዱስ ሰው እንዲወለድ አደረገ። ይኽም ሰው ሙሴ ይባላል።

ወላጆቹ መታመናቸውን በፈጣሪያቸው ያደረጉ ዮካብድና  እንበረም ሲሆኑ ከሌዊ ነገድ ናቸው፡፡ ከሙሴ ውጪም አሮንና ማርያምን ወልደዋል። ቅዱስ ሙሴ በተወለደበት ወራት ወንድ የእሥራኤል ሕጻናት ይገደሉ ነበር። ጌታ ግን በገዳዮቹ ልቡና ርሕራሔን አምጥቶ አትርፎታል።

በተወለደ በ3 ወሩ ወንዝ ላይ ጥለውት ተርሙት (የፈርኦን ልጅ) ወስዳ በቤተ መንግስት አሳድጋዋለች:: ሙሴ ያለችውም እርሷ ናት። 'ዕጓለ ማይ (ከውሃ የተገኘ) ለማለት ነው። ወላጆቹ ያወጡለት ስም ግን 'ምልክአም' ይባላል። ገና ሲወለድ ፊቱ እንደ መልአክ ያበራ ነበርና።

ቅዱስ ሙሴ 5 ዓመት በሆነው ጊዜ ፈርኦንን በጥፊ በመማታቱ ለፍርድ ቀርቦ እሳትን በመብላቱ አንደበቱ ኮልታፋ ሆኖ ቀርቷል። እናቱ ዮካብድ ሞግዚት ሆና ስላሳደገችው 40 ዓመት በሆነው ጊዜ የፈርኦንን ቤት ምቾትና የንጉሥ ልጅ መባልን ናቀ። ቅዱስ ዻውሎስ እንደሚለው በአሕዛብ ቤት ካለ ምቾት ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን ሊቀበል ወዷልና። (ዕብ. 11÷24)

አንድ ቀንም ለዕብራዊ ወገኑ ተበቅሎ ግብጻዊውን ገድሎት ወደ ምድያም ሸሸ። በዚያም ለ40 ዓመታት የካህኑን ዮቶርን በጐች እየጠበቀ ኢትዮዽያዊቱን ሲፓራን አግብቶ ኖረ። ልጆንም አፈራ። 80 ዓመት በሞላው ጊዜ እግዚአብሔር በደብረ ሲና ተናገረው። ሕዝቡንም ከባርነት ቀንበር እንዲታደግ ላከው፡፡ ሙሴም ከወንድሙ ጋር ግብጻውያንን በ9 መቅሰፍት በ10ኛ ሞተ በኩር መታ። እሥራኤልንም ነጻ አወጣ፡፡

ሊቀ ነቢያት የሠራቸው ሥራዎች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም፦ እርሱ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ ሕዝቡን በደረቅ አሻግሯል፣ ግብጻውያንን ከነሠረገሎቻቸው በባሕር ውስጥ አስጥሟል፣ ለሕዝቡ መና ከደመና አውርዷል፣ ውሃን ከጨንጫ (ከዓለት) ላይ አፍልቁዋል፣ በብርሃን ምሰሶ መርቷቸዋል፣ በ7 ደመና ጋርዷቸዋል፣ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ድል ነስቶላቸዋል፣ ቅዱስ ሙሴ ለ40 ዓመታት ሕዝቡን ሲመራ ከእግዚአብሔር ጋር ለ570 ጊዜ ተነጋግሯል።

ከጸጋው ብዛትም ፊቱ ብርሃን ስለ ነበር ሰዎች እርሱን ማየት አይችሉም ነበር። ታቦተ ጽዮንንና 10ሩ ቃላትን ተቀብሎ ጽላቱ ቢሰበሩ ራሱ ሠርቶ በጌታ እጅ ቃላቱ ተጽፈውለታል፡፡ ቅዱስ ክቡር ታላቅ ጻድቅ ነቢይና ደግ ሰው ቅዱስ ሙሴ በ120 ዓመቱ ዐርፎ በደብረ ናባው ሊቃነ መላእክት ቅዱሳን ሚካኤል ገብርኤልና ሳቁኤል ቀብረውታል። መቃብሩንም ሠውረዋል። (ይሁዳ 1÷9)

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ነሐሴ_14

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በእስክንድርያ ሀገር ድንቅ ተአምርን አደረገ፣ #የአባ_ስምዖንና የወዳጁ #የአባ_የዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ፣  #ቅዱስ_ባስሊቆስ በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መስቀለ_ክርስቶስ

ነሐሴ ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእስክንድርያ ሀገር ድንቅ ተአምርን አደረገ። ስለርሱም ከአይሁድ ብዙዎች አምነው በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአባ ቴዎፍሎስ እጅ ተጠመቁ እርሱም ለቅዱስ ቄርሎስ የእናቱ ወንድም ነው። ይህም እንዲህ ነው በእስክንድርያ አገር ስሙ ፈለስኪኖስ የሚባል አይሁዳዊ ባለጸጋ ሰው ይኖር ነበር እርሱም እንደ አባቶቹ የኦሪትን ሕግ የሚጠብቅና እግዚአብሔርን የሚፈራ ነው።

ዳግመኛም ሙያተኛዎች ሁለት ድኃዎች ክርስቲያኖች አሉ በአንደኛውም ላይ ሰይጣን የስድብ መንፈስ አሳድሮበት ጓደኛውን ወንድሜ ሆይ ክርስቶስን ለምን እናመልከዋለን እኛ ዶኆች ነን ይህ ክርስቶስን የማያመልክ አይሁዳዊ ፈለስኪኖስ ግን እጅግ ባለጸጋ ነው አለው።

ጓደኛውም እንዲህ ብሎ መለሰለት ዕወቅ አስተውል የዚህ ዓለም ገንዘብ ከእግዚአብሔር የሆነ አይደለም ምንም አይጠቅምም ጥቅም ቢኖረው ጣዖትን ለሚያመልኩ ለአመንዝራዎች ለነፍሰ ገዳዮች ለዐመፀኞች ሁሉ ባልሰጣቸውም ነበር።

አስተውል የከበሩ ነቢያት ድኆች ችግረኞችም እንደነበሩ ሐዋርያትም እንደርሳቸው ችግረኞች እንደነበሩ። ጌታችንም ድኆችን ወንድሞቼ ይላቸው እንደነበረ። ሰይጣን ግን የጓደኛውን ምክር እንዲቀበል ምንም ምን አልተወውም ሃይማኖቱን ምንም ምን አልተወውም ሃይማኖቱን ለውጦ ነፍሱን እስከማጥፋት ድረስ አነሣሣው ቀሰቀሰው እንጂ።

ከዚህም በኋላ ወደ ፈለስኪኖስ ሒዶ በአንተ ዘንድ እንዳገለግል ተቀበለኝ አለው። ፈለስኪኖስም እንዲህ ብሎ መለሰለት በሃይማኖቴ የማታምን አንተ ልታገለግለኝ አይገባም ከቤተ ሰቦቼም ጋራ የማትተባበር ልቀበልህ አይገባኝም። ሁለተኛም ይህ ጐስቋላ ወዳንተ ተቀበለኝ እኔም ወደ ሃይማኖትህ እገባለሁ ያዘዝከኝንም ሁሉ አደርጋለሁ አለው።

አይሁዳዊው ባለጸጋም ከመምህሬ ጋር እስከምማከር ጥቂት ታገሠኝ ብሎ ከዚያም ወደ መምህሩ ሒዶ ድኃው ክርስቲያናዊ ያለውን ሁሉ ነገረው መምህሩም ክርስቶስን የሚክድ ከሆነ ግረዘውና ተቀበለው አለው።

አይሁዳዊውም ተመልሶ መምህሩ የነገረውን ለዚያ ድኃ ነገረው ያም ምስኪን የምታዙኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ። ከዚህም በኋላ ወደ ምኵራባቸው ወሰደው የምኵራቡም አለቃ በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ጠየቀው። ንጉሥህ ክርስቶስን ክደህ አይሁዳዊ ትሆናለህን እርሱም አዎን እክደዋለሁ አለ።

የምኵራቡም አለቃ መስቀል ሠርተው በላዩ የክርስቶስን ሥዕል እንዲአደርጉ መጻጻንም የተመላች ሰፍነግ በዘንግ ላይ አሥረው ከጦር ጋራ እንዲሰጡት አዘዘ ከዚያም ከተሰቀለው ላይ ምራቅህን ትፋ መጻጻውንም አቅርብለት ክርስቶስ ሆይ ወጋሁህ እያልህ ውጋው አሉት።

ሁሉንም እንዳዘዙት አድርጎ በወጋው ጊዜ ብዙ ውኃና ደም ፈሰሰ ለረጂም ጊዜም በምድር እየፈሰሰ ነበር በዚያን ጊዜም ያ ከሀዲ ደርቆ እንደ ደንጊያ ሆነ። በአይሁድ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሀት ወደቀባቸው በእውነት የአብርሃም ፈጣሪ ስለእኛ ተሰቅሏል እኛም ዓለምን ለማዳን የመጣ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እርሱ እንደሆነ አመንበት እያሉ ጮኹ።

ከዚህም በኋላ አለቃቸው ከዚያ ደም ወስዶ የአንድ ዕውር ዐይኖችን አስነካው ወዲያውኑ አየ ሁሉም አመኑ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ ሒደው የሆነውን ሁሉ ነገሩት። ሊቀ ጳጳሳቱም ከካህናቱ ሁሉ ጋራ ተነሣ አባ ቄርሎስ ከእርሱ ጋራ አለ። ወደ አይሁድ ምኵራብም ሒዶ ውኃና ደም ከእርሱ ሲፈስ መስቀሉን አገኘው ከዚያም ደም ወስዶ በግንባሩ ላይ ቀብቶ በረከትን ተቀበለ ሕዝቡንም ሁሉ ግንባራቸውን በመቀባት ባረካቸው።

ያንንም መስቀል አክብረው ተሸክመው እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው ያኖሩት ዘንድ አዘዘ። ደም የፈሰሰበትንም ምድር አፈሩን አስጠርጎ ለበረከትና ለበሽተኞች ፈውስ ሊሆን በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኖረው።

ከዚህም በኋላ ፈለስኪኖስ ከቤተ ሰቦቹ ሁሉ ጋራ ሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስን ተከተለው ከአይሁድም ብዙዎቹ የቀደሙ አባቶቻቸው በሰቀሉት የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው ከእርሱ ጋራ አንድ አደረጋቸው ሥጋውንና ደሙንም አቀበላቸው። ከዚህም በኋላ ለዘላለሙ ክብር ምስጉን የሆነ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደየቤታቸው ገቡ። እኛንም ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን በመስቀሉ ኃይል ያድነን አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አባ_ስምዖንና_አባ_ዮሐንስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የአባ ስምዖንና የወዳጁ የዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ። እሊህ ቅዱሳንም በአማኒው ዮስጦንስ ዘመን መንግሥት የነበሩ ናቸው እሊህም ወንድሞች የከበሩ ክርስቲያን ናቸው።

ከዚህ በኋላ ለከበረ መስቀል በዓል ቅዱሳት መካናትን ሊሳለሙ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዱ ሥራቸውንም አከናውነው ወደ አገራቸው ሲመለሱ በፈረሶቻቸው ተቀምጠው ወደ ኢያሪኮ ቀረቡ።

ዮሐንስም በዮርዳኖስ በረሀ ያለውን የመነኰሳቱን ገዳም አይቶ ወንድሙ ስምፆንን ወንድሜ ሆይ ለእሊህ ገዳማት እኮ የእግዚአብሔር መላእክት ይኖራሉ አለው ዮሐንስም ከእርሳቸው ጋራ ከሆን አወን ልናያቸው እንችላለን አለው።

ከዚያም ከፈረሶቻቸውን ወርደው ለሰዎቻቸው ሰጥተው እስከምናገኛችሁ በየጥቂቱ ተጓዙ ብለው እንደሚጸዳዱ መስለው ወደ ዱር ገቡ።

የዮርዳኖስንም ጐዳና ተጒዘው ከሰዎቻቸው በራቁ ጊዜ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ ጸሎት እናድርግ ከእኛም አንዳንችን ወደ መነኰሳቱ ገዳም በምታደርስ ጐዳና ቁመን ዕጣ እንጣጣል እግዚአብሔር ከፈቀደ ዕጣችን ወደ ወጣበት እንሔዳለን።

ከዚህም በኋላ ስምፆን በዮርዳኖስ ጐዳና ቆመ ዮሐንስም ወደ ሀገራቸው በሚወስድ ጐዳና ላይ ቆመ ዕጣውንም በአወጡበት ጊዜ ዮርዳኖስ ጐዳና ላይ ወጣ እጅግም ደስ አላቸውና ስለ ደስታቸው ብዛት እርስ በእርሳቸው ተያይዘው ተሳሳሙ።

አንዱም አንዱ ወደኋላ እንዳይመለስ ስለጓደኛው ይጠራጠርና ይፈራ ነበር አንዱም ሁለተኛውን ይመክረውና ለበጎ ሥራ ያተጋው ነበር።

ዮሐንስ ስለ ስምፆን ይፈራ ነበር ስለ ወለላጆቹ ፍቅር አንዳይመለስ ስምፆንም ስለ ዮሐንስ ይፈራ ነበር እርሱ በዚያ ወራት መልከ መልካም የሆነች ሚስት አግብቶ ነበርና።

ከዚህም በኋላ ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ እንዲህም አሉ በውስጧ እንመነከኵስ ዘንድ ለኛ የተመረጠች ገዳም ደጃፍዋ ክፍት ሆኖ ብናገኝ ምለክት ይሆናል።

የገዳሙም አለቃ ኒቆን የሚሉት በተሩፋት ፍጽም የሆነ ድንቆች ተአምራትን የሚያደርግ ሀብተ ትንቢት የተሰጠጠው ሲሆን በዚያች ሌሊት በጎቼ ይገቡ ዘንድ የገዳሙን በር ክፈተት የሚለውን ራእይ አየ።

ወደርሱም በደረሱ ጊዜ የክርቶስ በጎች ሆይ መምጣታችሁ መልካም ነው አላቸውና ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ተላኩ ሰዎች አድርጎ ተቀበላቸው።

ከዚህም በኋላ አበ ምኔቱን የምንኵስናን ልብስ ያለብሳቸው ዘንድ ለመኑት እነርሱ በቆቡ ላይ የብርሃን አክሊል አድርጎ መላእክትም ከበውት አንዱን መነኰስ አይተዋልና ሰለዚህም ፈጥነው ይመነኵሱ ዘንድ ተጉ።
ከዚያም በማግስቱ አበ ምኔቱ የምንኲስናን ልብስ አለበሳቸው በቀን እንደሚተያዩ በሌሊትም እርስበርሳቸው የሚተያዩ እስቲሆኑ በፊታቸው ላይ የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን በራ ሁለተኛም በዚህ መነኵስ ላይ እንደሰዩ በራሶቻቸው ላይ የብርሃን አክሊል አዩ።

ከዚህም በኋላ ከመነኰሳቱ መካከል ተለይተው ወደ በረሀ ይገቡ ዘንድ ኀሳብ መጣባቸው። በዚያችም ሌሊት ብርሃንን የለበሰ ሰው ለአበ ምኔቱ ተገልጾ የክርስቶስ በጎች እንዲወጡ የገዳሙን በር ክፈት አለው በነቃም ጊዜ ወደ በሩ ሒዶ ተከፍቶ አግኝቶት እያዘነና እየተከዘ ሳለ ሊወጡ ፈለገው እሊህ ቅዱሳን መጡ በፊታቸውም በትረ መንግስትን አየ።

በአያቸውም ጊዜ ደስ ብሎት ተገናኛቸው እነርሱም በልባቸው ያሰቡትን ነግረውት እንዲጸልይላቸው ለመኑት ለረጅም ጊዜም አለቀሰ ከዚህም በኋላ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ በቀኙና በግራው አቆማቸው እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ ጸሎት አድርጎ ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቃቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር አደራ አስጠበቃቸው።ከዚያም በፍቅር አሰናበታቸው።

ከዚህም በኋላ አርጋኖን ወደ ምባል ወንዝ ሔዱ በዚያም አንድ ገዳማዊ በዚያን ወራት ያረፈ በውስጡ የኖረበትን በዓት አገኙ በውስጡም ያ ሽማግሌ ገዳማዊ ሲመገበው የነበረ ለምግባቸው የሚያስፈልጋቸውን የእህል ፍሬዎችን አገኙ ምግባቸውን በአዘጋጀላቸው በእግዚአብሔርም እጅግ ደስ አላቸው።

በድንግያ ውርወራ ርቀት መጠን አንዱ ከሁለተኛው የተራራቁ ሁነው ሰፊ በሆነ ተጋድሎ ቡዙ ዘመናት ኖሩ። ሰይጣንም ቡዙ ጊዜ ይፈታተናቸው ነበር ግን አባታቸው ቅዱስ ኒቅዮስ በራእይ ወደ እሳቸው መጥቶ ስለ እነርሱ ይጸልያል ተኝተውም ሳሉ የዳዊትን መዝሙር ያስተምራችዋል በነቁም ጊዜ ያስተማራቸውን ሁሉ በትክክል ያነቡታል እጅግም ደስ ይላቸዋል።

አምላካዊ ራእይም ተሰጣቸው ተአምራትንም ያደርጋሉ በዚያችም በረሀ የክብር ባለቤት በሆነ በክርስቶስ ኃይል ሰይጣንን ድል እስከ አደረጉት ድረስ የቀኑን ሐሩር የሌሊቱን ቊር ታግሠው ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነሩ።

ከዚህም በኋላ ስምዖን ወንድሙ ዮሐንስ እንዲህ አለው በዚህ በረሀ በመኖራችን ምን እንጠቃማለን ና ወደ አለም ወጥተን ሌሎችን እንጥቀማቸው እናድናቸውም ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አለው ወንድሜ ሆይ ይህ ኀሳብ ከሰይጣን ቅናት የተነሣ ይመስለኛል።

ስምዖን እንዲህ አለው ከሰይጣን አይደለም በዓለም ላይ እንድዘበትበት እግዚአብሔር አዞኛልና ነገር ግን ና እንጸልይ ያን ጊዜም በአንድነት ጸለዩ ልብሳቸውንም እስከ አራሱት ድረስ እርስበርሳቸው ተቃቅፈው አለቀሱ። ከዚህም በኋላ ስምዖን እስከሚሞትባት ቀን ሥራውን ይሠውርለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እየጸለየ ጎዳናውን ተጓዘ።

ወደ ዓለምም ገብቶ ራሱን እንደ እብድ አደረገ እብዶችንም የፈወሰበት ጊዜ አለ እሳትን በእጁ የሚጨብጥበትም ጊዜ አለ። ከዚህም በኋላ ከከተማው በር የሞተ ውሻ አግኝቶ በመታጠቂያውም አሥሮ እየጐተተ እንደሚጫወት ሆነ ሰዎች እስከሚሰድቡትና እስከሚጸፉት ድረስ።

በአንዲት ቀን እሑድ ከቅዳሴ በፊት የኮክ ፍሬ ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ መቅረዞችንም ሰበረ።ሴቶችንም መትቶ ከእርሳቸው ጋራ እንደሚተኛ ጐተታቸው ባሎቻቸውም ደበደቡት።

ዕረፍቱም ሲቀርብ የእግዚአብሔር መልአክ የእርሱንም የወንድሙ የዮሐንስንም የዕረፍታቸውን ጊዜ ነገረው ወደ ወይን ሐረግ ሥር ገብቶ ከወንድሙ ዮሐንስ ጋራ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ባስሊቆስ

በዚህችም ቀን ቅዱስ ባስሊቆስ በሰማዕትነት ሞተ። በእሥር ቤትም እርሱ ሳለ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦለት እንዲህ አለው የምስክርነትህ ፍጻሜ ደርሷልና ሒደህ ዘመዶችህን ተሰናበታቸው።

ከዚህም በኋላ ወታደሮችን ከእርሱ ጋራ ወደ ቤቱ ይሔዱ ዘንድ ለመናቸው ሒደውም ወደ ቤቱ ገቡ እናቱንና ዘመዶቹንም ተሰናበታቸው። በማግሥቱም የከበረ ባስሊቆስን ወደ ፍርድ ሸንጎ አቀረቡትና በሁለት ምሰሶዎች መካከልም አሥረው ሲደበድቡት ዋሉ በእግሮቹም ችንካሮችን አደረጉበት ደሙም በምድር ላይ ፈሰሰ ያየው ሁሉ አለቀሰለት።

ከዚህም በኋላ ከደረቀ ዕንጨት ላይ አሠሩት ዕንጨቱም በቀለና ቅርንጫፍና ቅጠሎችን አወጣ።ሰዎችም የልብሱን ጫፍ ለመንካት የሚጋፉ ሆኑ በበሽተኞችና በዚህ ዕንጨት ላይ ያደረገውን ተአምር አይተዋልና።

ከዚህም በኋላ ዋርሲኖስ ወደሚባል አገር በመርከብ ወሰዱት ወታደሮችም እንዳትሞት እህልን ብላ አሉት እርሱም እኔ ከሰማያዊ መብል የጠገብኩ ነኝ ምድራዊ መብልን አልመርጥም አላቸው።

ወደ መኰንኑም በአቀረቡት ጊዜ ለአማልክት መሥዋዕትን አቅርብ አለው የከበረ በስሊቆስም እኔ አንድ ለሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የምስጋና መሥዋዕትን አቀርባለሁ አለው።

ሁለተኛም ወደ ጣዖታቱ ቤት እንዲአስገቡት አዘዘ እርሱም ቁሞ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ያን ጊዜ እሳት ወርዶ ጣዖታቱን አቃጠላቸው መኰንኑም ፈርቶ ሸሽቶ ወደውጭ ወጣ። ቁጣንም ተመልቶ ይገድሉት ዘንድ ያ መኰንን አዘዘ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ባስሊቆስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ መከራውን ይሳተፍ ዘንድ ስለ አደለውም አመሰገነው።

ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት ብዙዎችም መላእክት ነፍሱን ሲያሳርጓት አዩዋት ጌታችን ኢየሱስም ወዳጄ ባስሊቆስ ወደ እኔ ና እኔ የምዋሽ አይደለሁም ተስፋ ያስደረግሁህን እፈጽምልሃለሁ ብሎ ጠራው። እንዲህም ተጋድሎውን ፈጸመ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ)
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5
#ነሐሴ_17

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን አሞራዊ #ቅዱስ_እንጣዎስ በሰማዕትነት ሞተ፣ ከደቡብ ግብጽ አቡስ ከሚባል አውራጃ መኑፍ ከሚባል ታናሽ መንደር #ቅዱስ_ያዕቆብ በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_እንጣዎስ_አሞራዊ

ነሐሴ ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን አሞራዊ ቅዱስ እንጣዎስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ክርስቶስን የካደ ነበር ገንዘብ ለማከማቸትም የሚተጋ ነበር።

በአንዲትም ዕለት ወደ ደማስቆ ከተማ ሔደ የበዓላቸው ቀን ነበርና ሕዝቡ ተሰብስበው ሳሉ ወደ ምሥራቃዊው ቅዱስ ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገባ ገብቶም ዕቃዎችን ማቃጠል ጀመረ መስቀልንም ሰበረ።

ከዚህም በኋላ በሰማይ ውስጥ የእሳት ፍላፃዎችን ይዘው ከሀዲዎችን ሲነድፏቸው አየ እርሱንም የቀኝ ጐኑን አንዲት ፍላፃ ነደፈችው። ያን ጊዜም ተጨንቆ ላቡ ተንጠፈጠፈ ከጥልቅ ልቡም እንዲህ ብሎ ጮኸ የቅዱስ ቴዎድሮስ አምላክ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አመንኩብህ ከእንግዲህ ዳግመኛ  ሌላ አምላክ እንዳያመልክ በልቡናው ቃል ገባ።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖችም በእርሱ ላይ የሆነውን አላወቁም ነገር ግን ጩኸቱንና የሚናገረውን ሰምተው አደነቁ እምነታቸውም ጠነከረ እጅግም ጸና። እንጣዎስም ኤልያስ ወደ ሚባል ጳጳስ ሒዶ በርሱ ላይ የሆነውን ሁሉ ነገረው የክርስትና ጥምቀትንም ያጠምቀው ዘንድ ለመነው።

ጳጳሱም በውኃው ላይ በጸለየ ጊዜ የብርሃን ምሰሶ እንደ ቀስተ ደመና ሁኖ ሕዝቡ ሁሉ እያዩት ወረደ ቅዱስ እንጣዎስም ተጠመቀ። ከእርሱም ጋራ ከአይሁድና ከአረሚ ዐሥር ሽህ ሰባት መቶ ዘጠና ስምንት ያህል ሰዎች ተጠመቁ። ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን ተቀበሉ።

ቅዱስ እንጣዎስም እንዲህ አለ እነሆ ይህን እያደነቅሁ ሳለ በእንቅልፌ ሕልምን አየሁ። ብርሃንን የለበሰች ሴት እጄን ያዘችኝ ወስዳም ወደ ኢየሩሳሌም አደረሰችኝ ወደ መሠዊያውም አቀረበችኝ እኔም ቅዱስ ቊርባንን ለመቀበል ተዘጋጀሁ በመሠዊያውም ውስጥ ነጭ በግን አየሁ ካህኑም በዕርፈ መስቀል በሠዋው ጊዜ ደሙ ጽዋው ውስጥ ተጨመረ ከእርሱም የክርስቶስን ሥጋና ደም በተቀበልሁ ጊዜ ሥጋው ንጹሕ ኅብስት ደሙም ጥሩ ወይን ሆነ።

ከዚህም በኋላ በደማስቆ ጐዳና ሲጓዝ አስቀድሞ የሚያውቁት ያዙት ወደ ንጉሡም ወሰዱት ንጉሡም ክርስቶስን በማመን እንደጸና አይቶ ጥርሶቹ እስቲበተኑ አፉን በበሎታ እንዲመቱት አዘዘ አፉም ደምን ተመላ። ከዚህም በኋላ እህል ውኃን ሳይሰጡ በተበሳ ግንድ ውስጥ ሰባት ቀን ያህል አሠሩት ከዚያም አውጥተው ዲን፣ ሙጫ፣ ዝፍት ከስብ ጋራ ባፈሉበት እሳት ውስጥ ጨመሩት ከእርሱም የመልካም መዓዛ ሽታ ወጣ።

ወታደሮችም ከእሳት ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ አገኙት። እሳቱም አልነካውም ወደ ንጉሥም ወሰዱት ንጉሡም የሥራይን ኃይል መቼ ተማርክ አለው ቅዱስ እንጣዎስም ንጉሡን እንዲህ አለው ሥራይንስ አላውቅም ነገር ግን ክብር ይግባውና በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል አሳፍርሃለሁ።

ንጉሡም ቁጣን ተመልቶ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። ከዚህም በኋላ ቅዱስ እንጣዎስ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ቆመ እጆቹንም ዘርግቶ ነፍሱን ወደ እግዚአብሔር አማፀነ ሲጸልይም ወደርሱ እንዲህ የሚል ቃል መጣ ከእስጢፋኖስና ከጊዮርጊስ ጋራ ታርፍ ዘንድ አገልጋዬ በሰላም ና። ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ራሱን ቆረጡት ምስክርነቱንም ፈጸመ ከሥጋውም ቁጥር የሌላቸው ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ያዕቆብ_ግብጻዊ

በዚህችም ቀን ከደቡብ ግብጽ አቡስ ከሚባል አውራጃ መኑፍ ከሚባል ታናሽ መንደር ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት ሞተ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ክርስቲያኖች ነበሩ ከእርሱ መወለድም በፊት ሦስት ሴቶች ልጆችን ወልደው ነበር።

ጥቂትም በአደጉ ጊዜ እንዲያስተምሩአቸውና በፈሪሀ እግዚአብሔር እንዲአሳድጓቸው በገዳም ለሚኖሩ ደናግል ሰጧቸው።  የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትንም ተማሩ። ወላጆቻቸውም ሊወስዷቸው በወደዱ ጊዜ እነርሱ ከደናግል ገዳም መውጣትን አልወደዱም። ነገር ግን ለድንግል ማርያምና ለልጅዋ ለክርስቶስ ሙሽሮች ይሆኑ ዘንድ መረጡ ወላጆቻቸውም ከእርሳቸው በመለየታቸው አዘኑ።

መሐሪ ይቅር ባይ እግዚአብሔርም በዚህ ቅዱስ  ያዕቆብ መወለድ አጽናናቸው። ሰባት ዓመትም በሆነው ጊዜ አባቱ ዐውሎ ወደ ሚባል አገር ጥበብን ይማር ዘንድ ላከው ትምህርትንም ተምሮ በትምህርት ሁሉ ፍጹም ሆነ።

አባቱም ለገንዘቡና ለጥሪቱ ለእንስሶቹም ሁሉ ተቈጣጣሪ አደረገው በዚያም አንድ በሥውር ብዙ ትሩፋትን የሚሠራ የበጎች ጠባቂ ነበረ በክረምትም በበጋም ብዙ ጊዜ ወደ ውኃ ጒድጓድ እየወረደ መላዋን ሌሊት ሲጸልይ ያድር ነበር።

ቅዱስ ያዕቆብም ሽማግሌው የበግ ጠባቂ በሚያደርገው አምሳል እያደረገ በዚህ ሥራ ብዙ ዘመን ኖረ። ከዚህም በኋላ ሰይጣን በክርስቲያን ወገኖች ላይ መከራን አስነሣ ብዙዎች ክርስቲያኖችም በሰማዕትነት ሞቱ።

በዚያንም ጊዜ ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት ይሞት ዘንድ ከዚያ ሽማግሌ ጋራ ተስማማ ቅዱስ ያዕቆብም ከሽማግሌው ጋራ ሒዶ ይመለስ ዘንድ አባቱን ፈቃድ ጠየቀ እርሱም ሒድ አለው።

በሔዱም ጊዜ በላይኛው ግብጽ የንጉሥ ልጅ ቅዱስ ዮስጦስን መኰንኑ ሲአሠቃየው አገኙት ሽማግሌውም ልጄ ሆይ ይህ የንጉሥ ልጅ መንግሥቱን ትቶ እውነተኛውን ንጉሥ ክርስቶስን እንደ ተከተለ ከሚስቱና ከልጆቹም እንደተለየ ተመልከት። እኛ ድኆች ስንሆን ለምን ችላ እንላለን ልጄ ሆይ እንግዲህ ተጽናና ከወላጆችህም በመለየትህ አትዘን አለው።

ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ቀርበው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ የረከሱ አማልክቶቹንም ረገሙ ያን ጊዜም መኰንኑ አስቀድሞ ሽማግሌውን ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው ራሱንም በሰይፍ ፈጥኖ አስቆረጠው ምስክርነቱንም ፈጸመ።

ቅዱስ ያዕቆብን ግን ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ከገመድ በተሠራ ጅራፍ ገረፈው ድንጋይም በእሳት አግለው በሆዱ ላይ አኖሩ። ዐይኖቹንም አቅንቶ ክብር ይግባውና ወደ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ጸለየ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከዚህ መከራ ርዳኝ አጽናኝም ያን ጊዜም ያለ ምንም ጉዳት አስነሣው።

ከዚህም በኋላ በማቅ ውስጥ አስጠቅልሎ በባሕር ውስጥ አስጣለው የእግዚአብሔርም መልአክ አውጥቶ ያለ ጉዳት በመኰንኑ ፊት አቆመው። መኰንኑንም አሳፈረው የረከሱ አማልክቶቹንም ረገመ።

ከዚህም በኋላ ፈርማ ወደሚባል አገር ላከው በዚያም የፈርማ መኰንን ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው ምላሱን ቆረጠው፣ ዐይኖቹንና ቅንድቦቹንም አወጣ፣ በመንኰራኩርም ውሰጥ አኬዱት፣ በመጋዝም መገዙት፣ ሕዋሳቱ ሁሉም ተሠነጣጠቁ።  ደሙም እንደ ውኃ ፈሰሰ የእግዚአብሔር መልአክ ሱርያል ወርዶ ቊስሎቹን አዳነለት።

መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በሠለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘና ቆረጡት የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበለ። ከገምኑዲ ሀገር የሆኑ አብርሃምና ዮሐንስም ከእርሱ ጋራ ሰማዕታት ሆነው ሞቱ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ)
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5
#ነሐሴ_23

ነሐሴ ሃያ ሦስት በዚች ቀን በእስክንድርያ አገር ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ሠላሳ ሺህ ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ፣ ሰማዕቱ #ቅዱስ_ድምያኖስ ዕረፍቱ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#የግብፅ_ሰማዕታት

ነሐሴ ሃያ ሦስት በዚች ቀን በእስክንድርያ አገር ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ሠላሳ ሺህ ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ።

ይህም እንዲህ ነው ንጉሥ መርትያኖስ አባታችን ዲዮስቆሮስን ወደ ደሴተ ጋግራ በአጋዘው ጊዜ ብዙ ዘመናት በእስክንድርያ አገር ሁከትና ብጥብጥ ሆነ።

መርትያኖስም በሞተ ጊዜ በርሱ ፈንታ ልዮን ነገሠ እርሱም አብሩታርዮስ የተባለውን መለካዊ ከሮማውያን ወገን ለእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ሾመ ይህም መለካዊ በኬልቄዶን ጉባዔ የሚያምን ነው ስለዚህም ከጥቂት ግብዞች ሰዎች በቀር የእስክንድርያ ሰዎች አልተቀበሉትም።

ያልተቀበሉትም ሰዎች አስቀድሞ አባታችን ዲዮስቆሮስ ከሾማቸው ቀሳውስት ሥጋውንና ደሙን የሚቀበሉ ሆኑ። ከዚህም በኋላ በቃሉ ለሚያምኑ ባልንጀሮቹ ጉባኤ አደረገላቸውና የክርስቶስ መለኮቱ ከትስብእቱ ተቀላቀለ የሚል አውጣኪን አወገዘው ።

አብሩታርዮስም ይህን ማድረጉ የእስክንድርያን ሰዎች ሸንግሎ ወደ ከፋች እምነቱ ሊስባቸው ወዶ ነው እንጂ ስለዚህ ነገር አባ ዲዮስቆሮስ አውጣኪን አስቀድሞ አውግዞታል። የአባታችን የዲዮስቆሮስ ሃይማኖት እንደ ባስልዮስና ጎርጎርዮስ እንደ ቅዱስ ቄርሎስ ቃል ከሥጋ ጋር ከተዋሐደ በኋላ አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ ብለው እንደሚያምኑ የሚያምን ነውና።

ከጉባኤውም በኋላ የሰበሰባቸው የአብሩታርዮስ ተባባሪዎቹ ወደየቦታቸው ተመለሱ። እርሱም ራሱ አብሩታርዮስ በቤቱ ውስጥ ተገድሎ ተገኘ ለባልንጀሮቹም የአባታችን ዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት ወይም የአውጣኪ ባልንጀሮች ወይም ሌቦች ገንዘቡን ለመውሰድ የገደሉት መሰላቸው ይህም እውነት ይመስላል።

የአብሩታርዮስም ባልንጀሮች ወደ ንጉሥ እንዲህ ብለው መልእክትን ላኩ እነሆ የዲዮስቆሮስ ወገኖች የንጉሥን ትእዛዝ በማቃለል ደፍረው የሾምከውን ሊቀ ጳጳሳት ገደሉት። በዚያንም ጊዜ ወንድሞቻችን የእስክንድርያ ሰዎች በላያቸው ጢሞቴዎስን ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።

እሊህ መናፍቃንም ከዚህ በኋላ ሁለተኛ እንዲህ ብለው ወደ ንጉሥ መልእክትን ላኩ። እነሆ አብሩታርዮስን የገደሉት ሰዎች አሁንም ያለ ንጉሥ ፈቃድ ደፍረው ሊቀ ጳጳሳት ሾሙ።

ንጉሡም በሰማ ጊዜ ከሁለቱ መልእክቶች የተነሣ እጅግ ተቆጣ። ሰይጣንም በልቡ አድሮ ጭፍሮቹን ልኮ ሃይማኖታቸው ከቀና ወንድሞቻችን ክርስቲያኖች ታላላቆችና ታናናሾች ሠላሳ ሺህ ሰዎች ተገደሉ ጢሞቴዎስንም ወደ ደሴተ ጋግራ አጋዘው በዚያም ሰባት ዓመት ኖረ።

ከአባታችን ዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት አንዱ የገደለውስ ቢሆን ስለ አንድ ሰው ፈንታ ሠላሳ ሺህ ሰው መግደል ይገባልን ስለዚህ ከሰይጣን ሥራ እንደሆነ ይታወቃል።

ከዚህ ከከፋ ዕልቂት በኋላም ወንድሞቻችን የሆኑ የዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት አብሩታርዮስን እንዳልገደሉት ንጉሡ ተረዳ እጅግም አዘነ ጢሞቴዎስንም ከተሰደደበት መልሶ በመንበረ ሢመቱ አኖረው ታላቅ ክብርንም አከበረው። መንጋውንም እያበረታ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ድምያኖስ

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሰማዕቱ ቅዱስ ድምያኖስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ የአንጾኪያ አገር መኮንን ይዞ ብዙ አሠቃየው፡፡

በኋላ ቅዱስ ድምያኖስ በእምነቱ መጽናቱን ሲያውቅና ማሠቃየትም በሰለቸው ጊዜ አንገቱን በሰይፍ ቆረጠውናሰማዕትነት ፍጻሜው ሆነ፡፡ የክብር አክሊንም ተቀዳጀ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ነሐሴ)
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5
#ነሐሴ_29

ነሐሴ ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን #የአባ_ዮሐንስ_ሐጺር ወደ አስቄጥስ ገዳም የሥጋው ፍልሰት ሆነ፣ #ቅዱስ_አትናቴዎስ #ገርሲሞስና_ቴዎዶጦስ ከሚባሉ ሁለት አገልጋዮቹ ጋር በሰማዕትነት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ዮሐንስ_ሐጺር

ነሐሴ ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን የአባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ አስቄጥስ ገዳም የሥጋው ፍልሰት ሆነ። ይህም የአባ እንጦንዮስ በሆነ በቊልዝም ገዳም ከአረፈ በኋላ ነው። ለእስክንድርያ አባ ዮሐንስ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ስምንተኛ የሆነ ነው። እርሱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ የከበሩ መነኰሳትም እንዲህ አሉት የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ በዚህ በቤተ ክርስቲያኑ ቢሆን እኛም ሥጋው በአለበት ለፈጣሪያችን እግዚአብሔር እንሰግድ ዘንድ እንሻ ነበር።

ያን ጊዜ የእግዚአብሔር ቸርነት አነሣሣችውና ስሙ ቆዝሞስ ለሚባል ለአንድ አበ ምኔት መልእክትን ጻፈ ከእርሱም ጋር የቊልዝም አገር የሆነ አረጋዊ አለ በደረሱም ጊዜ በዚያን ሰዓት ሥጋውን መውሰድ አልተቻላቸውም። የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ የኬልቄዶንን ጉባኤ በተቀበሉ መለካውያን ዘንድ ይጠበቅ ስለነበረ ነገር ግን ቦታውን አወቁ ተረዱ ወደ ቦታቸውም ተመልሰው ሃይማኖታቸው የቀና ምእመናን ሰዎችን አገኙ እነርሱም በዚያች አገር የሚኖሩ ናቸው ስለርሱ የመጡበትን ነገሩአቸው።

ከጥቂት ቀኖች በኋላም ከታላላቅ ዐረቦች ወገን ለቊልዝም አገር መኰንን ተሾመ እርሱም ለኤጲስቆጶስ አባ ሚካኤል ወዳጁ ነው ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስም ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ ወደ ኤጲስቆጶሱ መልእክትን ጻፈ። በመልእክቱም የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ ከከሐድያን መለካውያን እጅ እስከ አፈለሱት ድረስ መልእክተኞች አእሩግ መነኰሳትን ምክንያት ፈልጎ እንዲረዳቸው በማሳሰብ አዘዘው።

ኤጲስቆጶሱም በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለው ሒዶም ወዳጁ ለሆነ ለመኰንኑ ጸሐፊ ነገረው። ጸሐፊውም ለመኰንኑ ነገረው። እነሆ መኰንኑም ከመነኰሳቱ ጋራ ሔደ ጸሐፊውም መነኰሳቱ ወደዚያ ቦታ እንዲገቡ ምክንያት እንዴት እናገኛለን አለ።መኰንኑም በልብሶቻቸው ላይ የዓረቦችን ልብሶች ያልብሱአቸውና ከእኔ ጋራ ወደዚያ ቦታ ይምጡ አለ እንዲሁም እንዳላቸው አደረጉ።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ሔደ ከእርሱም ጋራ ብዙ ፈረሰኞች ሰዎች ብዙ ሕዝብም የአስቄጥስ ገዳም የከበሩ አረጋውያን አሉ ወደቊልዝም ገዳምም ደረሱ። መኰንኑም በዚያ የሚኖራውን የመለካውያን ኤጲስቆጶስ እንዲህ ብሎ አዘዘው ያንተን ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስወጣቸው በዚች ሌሊት እኔ በውስጧ አድራለሁና ያ መለካዊም መኰንኑ እንዳዘዘው አደረገ።

መነኰሳቱም እንስሶቻቸውን ከከተማ ውጭ አዘጋጅተው በሌሊት ወደዚያ ገብተው የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ ይዘው ወደ ምስር ደረሱ ከዚያም ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረሱ የአባ መቃርስ ገዳም መነኰሳትም መስቀሎችን፣ ወንጌሎችን፣ ማዕጠንቶችንና መብራቶችን በመያዝ እየዘመሩና እያመሰገኑ ተቀበሏቸው ወደ አባት መቃርስ ሥጋም አቀረቡትና ከእርሱ ተባረኩ በላዩም ብዙ ሽቱዎችን ነሰነሱ የቊርባን ቅዳሴንም ቀደሱ የከበረ ወንጌልም በሚነበብ ጊዜ ታላቅ ድንቅ ተአምር ተገለጠ ቤተ ክርስቲያኒቱ  ሁለመናዋ በሰማያዊ ብርሃን በራች። ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ በጎ መዓዛ ሸተተ ታላቅ ደስታም ሆነ በዚያም ቦታ ሰባት ቀን ኖረ።

ከዚህም በኋላ ወደ ራሱ ቤተ ክርስቲያን ተሸክመው ወሰዱት ዕብራውያንም በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እያሉ መድኃኒታችንን እንደተቀበሉት ልጆቹ መነኰሳት ተቀበሉትና ወደ ቦታው አኖሩት ከእርሱም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።

ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስ በወጣ ጊዜ ወደ አባ ዮሐንስ ሐጺር ቤተ ክርስቲያን ገባ። ከእርሱም ጋር ብዙዎች ኤጲስቆጶሳትና የእስክንድርያ አገር ታላላቆች ከግብጽ አገር ሁሉ አሉ። የአባ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ የተጠቀለለበትን ሰሌን ገልጦ ከእርሱ ተባረከ መሪር ልቅሶንም አለቀሰ ያን ጊዜ ሥጋው ሲገለጥ መብረቅና ነጐድጓድ ሆነ።በቤተ ክርስቲያኑም ውስጥ ያሉት ሁሉም ደንግጠው ወደቁ ሊቀ ጳጳሳቱም ሰሌኑን መልሶ በፍጥነት ሥጋውን ጠቀለለ በሽብሸባ እየዘመሩና እያመሰገኑ እንደቀድሞው ሸፈነው።

ከዚህም በኋላ ዳግመኛ እንዲህ እያሉ ሊያመሰግኑ ጀመሩ ፈጣን ደመና ሁነህ የመንፈስ ቅዱስን ዝናም የተሸከምክ ሠለስቱ ደቂቅ ወዳሉበት ወደ ባቢሎን የሔድክ በላይህ በአደረ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ እስከንድርያ አገር የተመለስክ ሁለተኛም ወደ ቊልዝም የሔድክ የጣዖታትን ቤቶች አፍርሰህ ሃይማኖትን የሰበክ በሽተኞችን የፈወስክ አጋንንትን ያስወጣህ ወደርስትህም የተመለስክ አንተ የበረከት ማደሪያ ነህና። የአባ ዮሐንስ ሐጺር የሥጋው ፍልሰት ከንጹሐን ሰማዕታት ዘመን በአምስት መቶ ሃያ ዓመት ሆነ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አትናቴዎስ_ሰማዕት

በዚህችም ቀን ኤጲስቆጶስ አትናቴዎስ በሰማዕትነት ሞተ ከእርሱም ጋር ስማቸው ገርሲሞስና ቴዎዶጦስ የሚባል ሁለት አገልጋዮች በሰማዕትነት አረፉ።

ይህንንም ቅዱስ አትናቴዎስን የእንጦኒቆስን የጭፍራ አለቃውን ልጅ እርሱ እንዳጠመቃት በንጉሥ ዘንድ ወነጀሉትና ንጉሥ አርስያኖስ ያዘው እርሱም ክርስቲያን እንደሆነ ታመነ ብዙ ሥቃይንም አሠቃየው።

በሃይማኖቱም ጸና እንጂ ሃይማኖቱን ባልካደ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ እንዲሁም እሊህን ሁለቱን አገልጋዮች ገርሲሞስንና ቴዎዶጦስን በግርፋትና በስቅላት ከቀጣቸው በኋላ ራሶቻቸውን በሰይፍ አስቆረጠ ሦስቱም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

አማንያን ሰዎችም መጡ ለወታደሮችም ገንዘብ ሰጥተው የቅዱሳኑን ሥጋቸውን ወሰዱ በአማሩ ልብሶችም ገንዘው በሣጥን ውስጥ አኖሩአቸው ከሥጋቸውም  ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ)
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5
#ጳጕሜን_3
#ሩፋኤል_ሊቀ_መላእክት_ወመልከጼዴቅ_ካህን
‹‹#ርኅወተ_ሰማይ_/ሰማይ የሚከፍትባት እለት››፤::

#እንኳን_ለቅዱስ_ሩፋኤል_በዓለ_ሢመትና_ለቅዳሴ_ቤቱ_በ4ኛው_መቶ_ክ_ዘመን_በቅዱስ_ቴዎፍሎስ_ዘእስክንድርያ_አማካኝነት_በሚደንቅ_ተዓምራት_በአሣ_አንበሪ_ጀርባ_ደሴት_ላይ_ለታነጸው_ቅዳሴ_ቤት

#እንዲሁም_ለካህኑ_መልከጼዴቅ_ዓመታዊ_ክብረ_በዓል_በሰላምና_በጤና_አደረሳችሁ_አደረሰን_፡፡

# ሩፋኤል ማለት “እግዚአብሔር ሐኪሜ ነው” ማለት ነው። ሣልሳይ ሊቀ መላእክት ነው። (“ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሩፋኤል እኔ ነኝ” እናዳለ /ጦቢ ፲፪፥፲፭/፡፡

✤ ሄኖክም “በሰው ቁስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” ይለዋል (መጽሐፈ ሄኖክ 6፥3)::
✤ ለሄኖክ ወልደ ያሬድ 6 ዓመት በእግረ ገነት ወድቆ ሳለ ኅበዓቱን ክሡታቱን አሳይቶታል። መ.ሄኖክ 8፡5
ቅዱስ ሩፋኤል ሰማያውያን መዛግብትን በእጁ የሚጠበቁ በመሆናቸው "ዐቃቤ ኖኅቱ ለአምላክ" ይባላል፡፡ እግዘአብሔር እንዳዘዘው የሚዘጋቸው የሚከፍታችው እርሱ ነው፡፡
✤✤✤ ቅዱስ ሩፋኤል ሰውን በመርዳት ሲኖር የነበረውን የጦቢትን ዓይን ያበራና፤ ሣራ ወለተ ራጕኤልን ተቆራኝቷት ከነበረው አስማንድዮስ ጋኔን (ያገባችውን ባል የሚገድል) አላቅቆ የጦቢት ልጅ ጦብያ እንዲያገባት ያደረገ በመኾኑ “ፈታሔ ማሕፀን (መወልድ/አዋላጅ፥ ምጥን የሚያቀል) ይባላል::
” ና ‹‹መልአከ ከብካብ›› ተብሏል (ዛሬም ድረስ የእናቶች ሐኪም ነው)፤ በኋላም ወደ ጦቢት በመኼድ ረዥም ዘመን የታወረ ዐይኑን አብርቶለት ቤቱንም በበረከት ሞልቶታል፤ በዚህም ፈዋሴ ቊስል (ድውያን)፥ ዐቃቤ ሥራይ (ባለ መድኃኒት ፈዋሽ) ተብሎ ይጠራል፡፡
#ጦቢት ልጁን ወደ ሜዶን ክፍል ወደ ምትሆነውና ራጌስ ወደ ምትባለው ሀገር ወደ ገባኤል ቤት ሲልከው መንገዱን የመራው አዛርያስ /ቅዱስ ሩፋኤል/ ነው፤ በዚህም ቅዱስ ሩፋኤል ‹መራኄ ፍኖት› /መንገድ መሪ/ ይባላል፡፡
#ቅዱስ ሩፋኤል በራማ ሰማይ ሁለተኛ ክፍል ላይ የሰፈሩትንና መናብርት በመባል የሚጠሩትን 10ሩን ነገደ መላእክት የሚመራቸው ነው፤ በዚህም ‹‹ሊቀ መናብርት›› ተብሎ ይጠራል፤ መናብርት የሚባሉት መላእክት ረቂቅ የኾነ የመብረቅ ጋሻ፥ የእሳት ጦር ይዘው፤ ከነፋስ ይልቅ የፈጠኑ ሲኾኑ፤ ከእነዚኽ 10ር ነገደ መላእክት 24ቱ ካህናተ ሰማይ ወጥተዋል፡፡


በኢትዮጵያ በቅዱስ #ሩፋኤል ስም ከተሰየሙት ቤተ ክርስቲያን መካከል፤
1,ጎንደር ደብረ ሣሕል ቅዱስ ሩፋኤል  ወአቡነ ሐራ ድንግል  ወቅዱስ ያሬድ  ቤተ ክርስቲያን (ጐንደር)፤ በአፄ በካፋ የተመሠረተና ዚቅ እንደተጀመረባቸው ከሚነገርላቸው ቦታዎች አንዱና ታላቁ ደብር፡፡
2,አዲስ አበባ ጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል፤ በ1878 ዓ.ም. በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተመሠረተና ባላ አንድ ጣሪያ ያለው ቀደምት የአዲስ አበባ ደብር፡፡
3,ደብረ ዘይት (አየር ኃይል) ቅዱስ ሩፋኤል ቤ.ክ.
4,ወላይታ ዳሞት ፑላስ ቅዱስ ሩፋኤል ቤ.ክ.



#በብዙኃን_ዘንድ_ለሚነሱ_ጥያቄዎች_መልስ_፡፡
#መልከ ጼዴቅ ማነው?
#አባትና እናትስ የሉትምን!?፤
#የሰው ዘር አይደለምን!!?፤
#እውን መልከ ጼዴቅ ክርስቶስ ነውን?!!!!

✤✤ #መልከ_ጼዴቅ_ማነው_?
መልከ ጼዴቅ በዘመነ አብርሃም የነበረ የሳሌም ንጉሥ እንዲሁም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነው /ዘፍጥ.14፤ ዕብ. 7/፡፡ ይህ ሰው አብርሃም ጠላቶቹን ነገሥተ ኮሎዶጎሞርን ድል አድርጎ ዮርዳኖስን ተሻግሮ በተመለሰ ጊዜ አብርሃምን ሊቀበለውና ሊባርከው ኅብስትና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ ባረከውም አብርሃምም ደግሞ ለመልከ ጼዴቅ ከምርኮው ዐሥራት አወጣ፡፡
(ኅብስትና ወይኑ የቅዱስ ቊርባን፣ መልከ ጼዴቅ የካህናት፣ አብርሃም የምእመናን፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌዎች ናቸው)፡፡
ካህኑ መልከ ጼዴቅን ‎ቅዱስ ዻውሎስ         "የትውልድ ቊጥር የለውም፤ ለዘመኑም ጥንትና ፍጻሜ የለውም" ብሎ ያስቀመጠው /ዕብ.7፥3/፤ ለወልደ እግዚአብሔር ምሳሌ ሲያደርገው እንጂ ትውልዱ ከነገደ  ‎ካም ነው፡፡ ወላጆቹም ‹‹#ሚልኪና #ሰሊማ  ›› ይባላሉ፡፡

በፋሬስ ደግሞ፤ ፋሬስ የኦሪት ዛራ ደግሞ የወንጌል ምሳሌዎች ናቸው፤ ዛራ እጁን አውጥቶ መመለሱ ወንጌል በመልከ ጼዴቅ ታይታ የመጥፋቷ ምሳሌ፤ ፋሬስ ጥሶ እንደወጣ በመሀል ኦሪት ተሠርታለች፤ ዛራ ሁለተኛ እንደመወለዱ ወንጌልም ቆይታ ተሠርታለች፡፡
   
#መልከ ጼዴቅ ክርስቶስን በአራት ነገሮች ይመስለዋል፤

#1. መልከ ጼዴቅ ማለት የጽድቅ ንጉሥ የሰላም ንጉሥ ማለት ነው፤ ክርስቶስም ደግሞ አምላከ ጽድቅ አምላከ ሰላም ነው፣
#2. መልከ ጼዴቅ በኅብስትና በወይን ያስታኵት /ያመሰግን/ ነበር፤ ክርስቶስም ሥጋና ደሙን በኅብስትና በወይን ሰጥቶናል፣
#3. መልከ ጼዴቅ በመጽሐፍ ቅዱስ እናቱና አባቱ አልተጠቀሱም ክርስቶስ ደግሞ ለሰማያዊ ልደቱ እናት ለምድራዊ ልደቱ አባት የለውም፣

በዓለማችን በመልከ ጼዴቅ ስም የተሰየመው ብቸኛው ቤተ ክርስቲያን፡፡ ደብረ ዘይት ሂዲ መልከጼዴቅ፡፡


‹‹#ርኅወተ_ሰማይ_/ሰማይ የሚከፍትባት እለት››፤
የሰዎች ሁሉ ጸሎት የሚያርግበት፥
አራተኛው መጋቤ ኮከብ (ሕልመልመሌክ) የሚያልፍባት፤
ለሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው ጸጋ በረከት የሚሰጥባት
ሰማይ የሚከፈትባት ቀን፤ በቅዱስ ሩፋኤል መሪነት ጸሎት የሚያርግባት፤ በዚህም ‹‹መዝገበ ጸሎት›› /የጸሎት መዝገብ መክፈቻ የተሰጠው/ ይባላል፡፡
የጌታችን ዳግም ምጽአት የሚታሰብባት ዕለት፤
በዚህም ምክንያ አባቶቻችን በዚህች እለት 365 አቡነ ዘበሰማያት ሲጸልዩ ያድራሉ፡፡

@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5
🌻 እንኩዋን ለታላቁ #ነቢይና_ሰማዕት_ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ 🌻

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ

=>ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: #ቅዱስ_ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "#ዘካርያስ ካህኑና #ቅድስት_ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

¤የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!

¤እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::

¤ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

¤ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል #እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

¤የአምላክ እናቱ ስትደርስና "#ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ #ሰብአ_ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

¤እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና #ስምዖን ወርደው ቀበሯት::

¤ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ #ድንግል_ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

¤ከዚህ በሁዋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::

¤ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ #መንፈስ_ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::

¤ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ:: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::

¤"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "#መጥምቀ_መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::

¤በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)

¤ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት #ደብረ_ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: #ቅዱሳን_ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት::

¤ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ሚያዚያ 15 ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::

<<¤ አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ (የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች) ¤>>
1.ነቢይ
2.ሐዋርያ
3.ሰማዕት
4.ጻድቅ
5.ካሕን
6.ባሕታዊ/ገዳማዊ
7.መጥምቀ መለኮት
8.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
9.ድንግል
10.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
11.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
12.መምሕር ወመገሥጽ
13.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

=>ጌታችን #መድኃኔ_ዓለም የመጥምቁ ዮሐንስን ምትረት አስቦ ይቅር ይበለን:: ጸጋውን: በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን::

=>መስከረም 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)
2.ቅዱስ ዳስያ ሰማዕት
3.ቅዱስ ዲዲሞስ ሰማዕት
4.ቅድስት መሪና

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

=>+"+ #ጌታ_ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ #ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ . . . ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችሁአለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን . . . እውነት እላቹሃለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም . . . ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ:: ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው #ኤልያስ ይሕ ነው::
የሚሰማ ጀሮ ያለው ይስማ:: +"+ (ማቴ. 11:7-15)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5
#መስከረም_6

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ስድስት በዚች ቀን ታላቅ ነቢይ የአሞጽ ልጅ #ቅዱስ_ኢሳይያስ አረፈ፣ #የአቡነ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ ዐፅማቸው ከዋልድባ አብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ዕለት ነው፣ #ቅድስት_ሰብልትንያ በዲዮቀልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ሞተች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ነቢዩ_ኢሳይያስ

መስከረም ስድስት በዚች ቀን ታላቅ ነቢይ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ አረፈ። ይህም ነቢይ ለይሁዳ በነገሡ በአምስቱ ነገሥታት ዘመን አስተማረ ትንቢትም ተናገረ እሊህም አዝያን ኢዮአታም አካዝ ሕዝቅያስና ምናሴ ናቸው።

በአካዝ ዘመንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ። እነሆ ስለዚህ እግዚአብሔር ምልክትን ይሰጣችኋል። እነሆ ድንግል ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች። ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ አንድ ሆነ ማለት ነው።

እርሱም በኃጢአታቸው ከሚመጣባቸው ፍዳ ወገኖቹን የሚያድናቸው ወደ ሃይማኖቱም የሚአስገባቸው እንደሆነ የእስራኤልንም ልጆች መሥዋዕታቸውንና ክህነታቸውን እንደሚሽር ከሐዲስ ወገኖችም የሚያመሰግኑት ካህናትን እንደሚሾም ተናገረ።

የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምም ኢየሩሳሌምን ከቦ የስድብ ቃልን በክብር ባለቤት በእግዚአብሔር ላይ በተናገረ ጊዜ የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምን ያጠፋው ዘንድ እግዚአብሔር እንዳለው ለሕዝቅያስ ትንቢትን ተናገረ።

በዚያች ሌሊትም እግዚአብሔር የላከው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ሠናክሬም ሰፈር መጥቶ ከፋርስ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ አርበኞችን ገደለ። የለኪሶ ሰዎች ሲነጋ በተነሡ ጊዜ የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ሁሉ አዩ።

ሕዝቅያስም ታሞ ለሞት በተቃረበ ጊዜ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደርሱ መጥቶ እግዚአብሔር ትሞታለህ እንጂ አትድንም ብሏልና ቤትህን አዘጋጅ አለው። ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ ወደ እግዚአብሔር ለመነ ፈጽሞ ጽኑ ልቅሶንም አለቀሰ።

ይህን ከነገረው በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኢሳይያስ መጣ ሒደህ ለሕዝቅያስ የአባትህ የዳዊት ፈጣሪ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰማሁ ዕንባህንም አየሁ። እነሆ በዘመንህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት ጨመርኩልህ አለ በለው።

ዳግመኛም ስለ እስራኤል መማረክና ከምርኮ ስለ መመለሳቸው ትንቢት ተናገረ የፈሳሽ ውኃን ምንጭ በማፍሰስ በእጆቹ ላይ እግዚአብሔር ምልክትን ገለጠ።

ክብር ይግባውና ስለ መድኃኒታችን ክርስቶስ መከራ ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ። እርሱም በመከራው ጊዜ ነገርን አልተናገረም እንደ በግ ይታረድ ዘንድ መጣ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንደ ማይናገር እንዲሁ በመከራው ጊዜ አልተናገረም።

ከዚህም በኋላ ደግሞ በሕዝቅያስ ልጅ በንጉሥ ምናሴ ላይ ትንቢት ተናገር ጣዖትን ስለማቆሙና ስለማምለኩ ገሠጸው። ስለዚህም ንጉሥ ምናሴ ተቆጥቶ በዕንጨት መሰንጠቂያ መጋዝ በራሱና በእግሮቹ መካከል ሠነጠቀው ምስክርነቱንም በዚህ ፈጸመ።

ትንቢት እየተናገረ የኖረበትም ዘመን ሰብዓ ዓመት ከዚያም በላይ ይሆናል። እርሱም ያስተማረው ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት በዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሦስት ዓመት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የዋልድባው የአቡነ ሳሙኤል ዐፅማቸው ከዋልድባ አብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ዕለት ነው፡፡ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ትውልዳቸው ከካህናቱ ወገን አክሱም ነው አባታቸው እስጢፋኖስ እናታቸው አመተ ማርያም ይባላሉ። ለመምህር ሰጥተዋቸው ሲማሩ አድገው በኋላም ወላጆቻቸው በሞት ሲለዩአቸው ደብረ በንኰል ገዳም ገብተው ሥርዓተ ምንኩስናን ከአበው እያጠኑ ለትልቁም ለትንሹም በትሕትና እየታዘዙ ውሃ እየቀዱ እንጨት እየሰበሩ በትኅርምት በጽሞና በጸሎት ይኖሩ ነበር።

ሰይጣን በውዳሴ ከንቱ ጾር ቢመጣባቸው ከማሕበረ መነኮሳቱ ተለይተው በተባሕትዎ ለመኖር ሽተው ወጥተው ሲሔዱ ተከዜ ደረሱ። ወንዙ ሞልቶ የማያሻግራቸው ቢሆን ውሃውን በትምህርተ መስቀል ባርከው በአንድ እጃቸው መጽሐፍ በአንድ እጃቸው መብራት እንደያዙ ገብተው መብራቱ ሳይጠፋ መጽሐፉ ሳይበላሽ ተሻግረዋል። ዋልድባ ሲደርሱ ጌታ እዚህ ተቀመጥ ስላላቸው ገዳም መሥርተው ሥርዓተ ምንኩስናን እያስተማሩ ተቀመጡ። ዛሬ በዋልድባ የሚያመሰግኑበት ውዳሴ ማርያም ቅዳሴ ማርያምን ከተከዜ ወዲህ ያመጡ እሳቸው ናቸው። ይህንን እየጸለዩ ሲሔዱ ክንድ ከስንዝር መሬት ለቀው ይታዩ ነበር። አንድ ቀንም ይህንን ጸሎት ደግመው ውኃውን ቢባርኩት ኅብስተ ሕይወት ሆነላቸው ከነደቀ መዛሙርቶቻቸው ተመግበውታል።

እመቤታችንም የፍቅር መግለጫ ዕጣን፣ ወርቅ፣ እንቁ ሰጥታቸዋለች። ውዳሴዬን ከቅዳሴዬ አንድ አድርጎ የደገመውን አንተ ከገባህበት መካነ ሕይወት አስገባዋለሁ ብላ ቃልኪዳን ሰጥታቸዋለች። ጊዜ እረፍታቸው ሲደርስ ጌታን በስብሐተ መላእክት ተገልጦ በስምህ የተማጸነውን በጎ የሰራውን፣ ዜና ገድልህን የጻፈውን፣ ያስጻፈውን፣ ያነበበ፣ የተማረ፣ ያስተማረ፣ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ምሬልሃለሁ። በዚህ ቦታ በዋልድባ የሚሰበሰቡ ልጆችህን ከእዳ ከፍዳ እሰውርልሃለሁ አላቸው። እንኪያስ ቦታዋን ባርክልኝ ብለው እንደ መሶብ አንስተው አስባርከዋታል ጌታችንም እህል አይብቀልብሽ ኃጢአት አይሻገርብሽ ብሎ ቃል ኪዳን ገባላት ለገዳመ ዋሊ። አባታችን አቡነ ሳሙኤል በበዓታቸው ውስጥ ጸንተው ሲኖሩ ታህሣሥ 12 ቀን ያረፉ ሲሆን ዛሬ መስከረም 6 ግን ፍልሰተ አጽማቸው የተከናወነበት እለት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሰብልትንያ

በዚህችም ቀን ቅድስት ሰብልትንያ በከ*ሀዲ ንጉሥ ዲዮቀልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ሞተች። ይችንም ቅድስት ዕድሜዋ ዘጠኝ ዓመት ሲሆን ከሀ*ድያን ያዙዋት እጆቿንና እግሮቿንም አሥረው ከሚነድ እሳት ውስጥ ጣሏት የክብር ንጉሥ በሆነ በእግዚአብሔርም ኃይል ከእሳት ዳነች።

ውኃን በተጠማች ጊዜ እግዚአብሔርን ለምናው ውኃን አፈለቀላትና ጠጣች ክብር ምስጉን የሆነ ጌታችንንም አመሰገነችው። ከዚህም በኋላ ነፍሷን በእግዚአብሔር እጅ አደራ ሰጥታ ራሷን ከእሳት ውስጥ ወረወረች ምስክርነቷንም ፈጸመች።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም እና #ከገድላት_አንደበት)
@petroswepawulos
@petroswepawulos
@petroswepawulos