መዝገበ ቅዱሳን
24.2K subscribers
1.97K photos
9 videos
6 files
26 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለነቢዩ #ቅዱስ_ዮናስ እና ለእናታችን #ቅድስት_አውፎምያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ ቅዱስ ዮናስ ነቢይ ✞✞✞

=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከ12ቱ #ደቂቀ_ነቢያት አንዱ የሆነው #ቅዱስ_ዮናስ ከክርስቶስ ልደት 800 ዓመታት በፊት እንደ ነበረ ይታመናል:: #ሊቃውንት እንዳስተማሩን ደግሞ እናቱ #ቅዱስ_ኤልያስን የመገበችው የሰራፕታዋ መበለት ናት:: ቅዱስ ዮናስ ገና ሕጻን ሳለ በእሥራኤል ምድር ዝናብ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ተከልክሎ ነበር::

+ይሕንንም ያደረገው ደጉ ነቢይ ኤልያስ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀንቶ ነው:: በወቅቱ ኤልያስ በሰራፕታ ሳለ ሕጻኑ ዮናስ ታሞ ሞተ:: ልጇ የሞተባት መበለትም ኤልያስን ለመነችው:: ኤልያስም ወደ ፈጣሪው ማልዶ ሕጻኑን ዮናስን ከሞት አስነስቶታል:: ትንሽ ከፍ ባለ ጊዜም ከጉዋደኞቹ (ከነቢያቱ) #አብድዩና #ኤልሳዕ ጋር ሆነው ታላቁን ነቢይ ኤልያስን ተከትለውታል::

+ኤልያስ ካረገ በሁዋላ ሁሉም በየተሰጣቸው አገልግሎት ተሠማርተዋል:: ቅዱስ ዮናስን #እግዚአብሔር "ወደ ነነዌ ሒደሕ ንስሃን ስበክ" አለው:: ዮናስ ግን የፈጣሪውን መሐሪነት ጠንቅቆ ያውቃልና አልሔድም አለ:: (ተመልከቱ የየዋሕነት ብዛት)

+እግዚአብሔር እየደጋገመ እንዲሔድ ሲነግረው ነቢዩ "እንዲሕ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል" ብሎ ሊኮበልል ወጣ:: ነገር ግን አልቀናውም:: በእርሱ ምክንያት ማዕበል ተነሳ:: ሕዝቡም ሊያልቁ ሆነ:: ከእንቅልፉ የነቃው ዮናስ ከመርከቡ ላሉት አሕዛብ አምልኮተ እግዚአብሔርን ሰብኮላቸው: በእርሱ ጠያቂነት ሐምሌ 15 ቀን ወደ ባሕር ጥለውታል::

+አሣ አንበሪም ተቀብሎታል:: በግዙፉ አሣ ውስጥም ያለ እንቅልፍ በጾም: በጸሎትና በምስጋና 3 ለቀን ቆይቷል::
ሙስና ሳያገኘውም በዚህች ቀን አሣ አንበሪው #ነነዌ ዳር ላይ ተፍቶታል:: ቅዱስ ዮናስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ ነነዌ ዓባይ ሃገር" /እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትገለበጣለች (ዮናስ 3:4)/ ብሎ አሰምቶ ሰበከ::

+የነነዌ ሰዎችም በስብከተ ዮናስ አምነው: ንስሃም ገብተው ድነዋል:: በዚህም ጌታችን በወንጌል ላይ አመስግኗቸዋል:: ቅዱስ ዮናስ መኮብለሉ #በሐዲስ_ኪዳን ለሚደረገው ምስጢረ ትንሳኤ ጥላ (ምሳሌ) ነውና ይደነቃል:: (ማቴ. 12:38) ነቢዩ ግን በተረፈ ሕይወቱ ሕዝቡን ሲያስተምር: ፈጣሪውን ሲያገለግል ኑሮ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::

+"+ ቅድስት አውፎምያ ሰማዕት +"+

=>እናታችን #ቅድስት_አውፎምያ (ስሟ አፎምያ አይደለም:: በስሕተት "ው" መካከል ላይ የገባች እንዳይመስልዎ:: እስመ ከመዝ ስማ-ስሟ እንዲሁ ነው የሚጠራው) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ወጣት ክርስቲያኖች አንዷ ናት:: ገና ከልጅነቷ ልቧ በፍቅረ ክርስቶስ የተነደፈ ነበር::

+በዚህም ምክንያት ራሷን በጾምና በጸሎት ወስና ትኖር ነበር:: እድሜዋ ገና በአሥራዎቹ ቢሆንም በመንኖ ጥሪት መኖር ምርጫዋ ነበር:: ሊቃውንት አበው ከሰማዕትነቷ ደርበው "ጻድቅት አውፎምያ" እያሉም ይጠሯታል::

+አንድ ቀን ግን መንገድ ወጥታ ነበርና ክርስቲያኖች ሲሰቃዩ ተመለከተች:: ምንም ጥፋት ሳይገኝባቸው ክርስቶስን ስላመለኩ ብቻ ይሙት በቃ ተፈርዶባቸው ሊገደሉ እየተወሰዱ ነበር:: አሕዛብ ግብራቸው የአውሬ ነውና ርሕራሔ የላቸውም:: ሰማዕታቱ ደማቸው በየመንገዱ እየፈሰሰ ጥቁር ሰንሰለት በአንገታቸው: በእጃቸውና በእግራቸው ላይ አድርገው ይጐትቷቸው ነበር::

+ቅድስት አውፎምያ የተደረገውን ሁሉ ተመልክታ አምርራ አለቀሰች:: ፈጠን ብላም ወደ መኮንኑ ቀርባ ገሰጸችው::
"አንተ አእምሮ የጎደለህ! እንዴት ክርስቲያኖችን እንዲህ ታሰቃያለህ? አምላካቸው #ጌታ_ክርስቶስ ታጋሽ ባይሆን ኑሮ በቅጽበት ከገጸ ምድር ባጠፋህ ነበር" አለችው::

+በድፍረቷ የተገረመው መኮንኑ "አንቺስ ማንን ታመልኪያለሽ?" ሲል ጠየቃት:: እርሷም "ሰማይና ምድርን የፈጠረውን: ስለ እኛ ሲል በቀራንዮ አንባ የተሠዋውን #ኢየሱስ ክርስቶስን አመልካለሁ" ስትል መለሰችለት:: በዚያች ሰዓት የመኮንኑ ቁጣ በቅድስቷ ላይ ነደደ::

+ነገር ግን ቁጣውን ከቁም ነገር አልቆጠረችውምና እንዲያሰቃዩዋት አዘዘ:: ወታደሮቹ ሥጋዋን በብዙ አሰቃዩ:: ብላቴናዋ አውፎምያ ግን ጽንዕት ናትና አልቻሏትም:: በመጨረሻ በእሳት ተቃጥላ ትሞት ዘንድ ተፈረደባት::

+እሳቱ ከመሬት ከፍ ባለ ጊዜ ወደ ውስጥ ወረወሯት:: በእሳቱ መካከል ቁማ ለረዥም ጊዜ ጸለየች:: ከዚያም ነፍሷን አሳልፋ ሰጠች:: ምዕመናን በክብር ገንዘው ቀብረዋታል::

=>አምላካችን ከነቢዩና ከሰማዕቷ ወዳጆቹ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ (ከአሣ አንበሪ ሆድ የወጣበት)
2.ቅድስት አውፎምያ (ጻድቅትና ሰማዕት)
3.ቅዱስ ዮስጦስ ሰማዕት (ታላቁ)
4.ቅዱስ ዘካርያስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)

=>+"+ በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና:- 'መምሕር ሆይ! ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን' አሉት:: እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው:- 'ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ:: +"+ (ማቴ. 12:38)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
@petroswepawulos
††† እንኳን ከዘመነ ክረምት ወደ ዘመነ መጸው አሸጋግሮ ለቅዱስ ዮናስ ነቢይ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ስንዱ #እመቤት #ቤተ_ክርስቲያን (ሃገራችን) ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ትጠቀማለች:: እሊሕም ዘመናት #መጸው (ጽጌ): #ሐጋይ (በጋ): #ጸደይ (በልግ) ና ክረምት ናቸው:: ዘመናቱ ወቅቶችን ከመለየትና ማሳወቅ ባሻገር የእኛ ሕይወትም ምሳሌዎች ናቸውና ልብ ልንላቸው ይገባል::

#ዘመነ_መጸው / #ወርኀ_ጽጌ/ #ጥቢ እየተባለም ይጠራል:: በዚህ ወቅት ምድር በአበባ የምታጌጥበት: ክረምት የተለፋበት አዝመራ የሚደርስበት በመሆኑ ደስ ያሰኛል:: በጊዜውም:-
1.የእመቤታችን የቅድስት #ድንግል_ማርያም ስደቷ ይታሠባል:: እርሷ ስለ እኛ:-
*የሕይወት እንጀራን ተሸክማ መራቧን::
*የሕይወት መጠጥን ይዛ መጠማቷን::
*የሕይወት ልብስን አዝላ መራቆቷን::
*ሙቀተ መንፈስ ቅዱስን የሚያድለውን ተሸክማ ብርድ መመታቷን እናስባለን::
*ዘመኑ የበረከት ነው::

2.በሌላ በኩል ጊዜው ወርኀ ትፍሥሕት (የደስታ ወቅት) ነው:: በክረምት የደከመ ዋጋውን አግኝቶ: በልቶ: ጠጥቶ ደስ ይለዋልና:: ያልሠራው ግን ከማዘን በቀር ሌላ እድል የለውም:: ይኼውም ምሳሌ ነው::

ዘመነ ክረምት የዚህ ዓለም ምሳሌ: ዘመነ መጸው ደግሞ የመንግስተ ሰማያት:: በዚህ ዓለም ምግባር ትሩፋትን የሠራ በወዲያኛው ዓለም ተድላን ሲያደርግ ሰነፎች ኃጥአን ግን እድል ፈንታቸው: ጽዋ ተርታቸው ከግብዞች ጋር የመሆኑ ምሳሌ ነው::

በወርኀ ትፍስሕት እንደ ሊቃውንቱ እንዲህ ብለን ልንጸልይ ይገባል::
"ድኅረ ኀለፈ ክረምት ወገብአ ዝናም: ዘአስተርአይከ እግዚኦ ጽጌያተ ገዳም:
አፈወ ሃይማኖት ነአልድ ወፍሬ ምግባር ጥዑም:
አትግሃነ ለስብሐቲከ ከመ ትጋሆሙ አዳም:
ለጽብስት ንሕብ ወነአስ ቃሕም::"

††† የዘመናት ባለቤት ዘመነ መጸውን #ወርኀ_ትፍስሕት ያድርግልን::

††† ቅዱስ ዮናስ ነቢይ †††

††† ዮናስ ማለት 'ርግብ: የዋህ' ማለት ሲሆን ከ12ቱ #ደቂቀ_ነቢያት አንዱ ነው:: በሰራፕታ ተወልዶ ያደገው ነቢዩ በልጅነቱ ታሞ ሙቶ ነበር:: ታላቁ ነቢይ #ኤልያስ ግን 7 ጊዜ ጸሎት አድርጐ ከሞት አስነስቶታል:: (1ነገ. 17:17) እናቱ የሰራፕታዋ መበለትም ደግ ሴት ነበረች::

ቅዱስ ዮናስ በእድሜው ከፍ ሲል የቅዱስ ኤልያስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: የነ ኤልሳዕና አብድዩም ባልንጀራ ነበረ:: ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ካረገ በሁዋላ: ቅ.ል.ክርስቶስ በ800 ዓመት አካባቢ የነነዌ ሰዎች ኃጢአት ከመሥፈርቱ በማለፉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ መጣ::

"ሒድና ለነነዌ ሰዎች ንስሃን ስበክላቸው" አለው:: ከነቢያት ወገን ከሙሴና ከዳዊት ቀጥሎ የዮናስን ያህል የዋህ (ገራገር) የለምና እንቢ አለ (ሰምቶ ዝም አለ):: #እግዚአብሔር እየደጋገመ ሲናገረው ግን "እንዲህ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል!" ብሎ ወደ #ተርሴስ ኮበለለ::

ወገኖቼ አንድ ነገርን ልብ እንበል:: እንኩዋን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዮናስ እኛ ክፉዎችም ከጌታ ፊት መሸሸት እንደማይቻል ጠንቅቀን እናውቃለን:: ታዲያ ለምን ሸሸ ቢሉ:- ጥበበ እግዚአብሔር በውስጡ ስለ ነበረበት ነው::

ምክንያቱም ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ 3 ቀን እና ሌሊት ኖሮ: ሙስና (ጥፋት) ሳያገኘው መውጣቱ ለጌታ ትንሳኤ ጥላ (ምሳሌ) ነው:: ለዚህም ምስክሩ ራሱ ጌታችን ነው::
"ወበከመ ነበረ #ዮናስ ውስተ ከርሠ አንበሪ ሠሉሰ ዕለተ ወሠሉሰ ለያልየ: ከማሁ ይነብር ወልደ እጉዋለ እመ ሕያው ውስተ ልበ ምድር ሠሉሰ ዕለተ: ወሠሉሰ ለያልየ" እንዲል:: (ማቴ. 12:39)

ቅዱስ ዮናስ በገንዘቡ ዋጅቶ ወደ መርከብ በገባ ጊዜ ታላቅ ማዕበል ሆነ:: የእምነት ሰው ነውና እንዲያ እየተናወጡ እርሱ በእርጋታ ተኝቷል:: እነርሱ ግን ቀስቅሰው ቢጠይቁት (እጣ ወድቆበታልና) "የእኔ ጥፋት ስለ ሆነ ወደ ማዕበሉ ጣሉኝ" አላቸው::

እያዘኑ ቢጥሉት ታላቅ ጸጥታ ሆነ:: እነዚያ አሕዛብም እግዚአብሔርን በመስዋዕትና በስዕለት አከበሩ:: ዮናስ ግን በማዕበልና በአሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ለ3 ቀናት ጸለየ:: አሣ አንበሪው በ3ኛው ቀን ወደ ነነዌ ተፋው::

ቅዱሱም "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ #ነነዌ ዐባይ ሃገር" እያለ ንስሃን ሰበከ:: የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸውን አምነው ቢጸጸቱ ከሰማይ ወርዶ ከደመና ደርሶ የነበረው የእሳት ማዕበል ተመልሶላቸዋል::

የነቢዩ ትንቢት ግን አልቀረምና ታላቋ ነነዌ ከ300 ዓመታት በሁዋላ ጠፍታለች:: ቅዱስ ዮናስ ግን በቀሪ ዘመኑ ፈጣሪውን እያገለገለ ኑሯል:: ጠቅላላ እድሜውም 170 ዓመት ነው::

††† አምላከ ቅዱስ ዮናስ እድሜ ለንስሃ: ዘመን ለፍስሃ አይንሳን:: ከበረከቱም ይክፈለን::

††† መስከረም 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ጸአተ ክረምት (የክረምት መውጫ)
2.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ
3.ቅዱስ እንጦንዮስ
4.ቅድስት በርባራ
5.ሐዋርያት ዼጥሮስ ወዻውሎስ
6.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
7.ታላቁ አባ ቢጻርዮን ገዳማዊ

††† "ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ: እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ::" †††
(ማቴ. 12:39)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
@petroswepawulos
#ሐምሌ_4

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሐምሌ አራት በዚህች ቀን #የቅዱሳን_አቡቂርና_ ዮሐንስ የሥጋቸው ፍልሰት ሆነ፣ #የነቢዩ_ሶፎንያስ እረፍት ነው፣ የዐሥራ ሁለቱ #ደቂቀ_ነቢያት መታሰቢያቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አቡቂርና_ዮሐንስ

ሐምሌ አራት በዚች ቀን የቅዱሳን አቡቂርና ዮሐንስ የሥጋቸው ፍልሰት ሆነ። ይህም እንዲህ ነው እሊህ ቅዱሳን የካቲት ስድስት ቀን ሰማዕታት ሆነው በሞቱ ጊዜ ምእመናን ሥጋቸውን ተሸክመው ወስደው በእስክንድርያ ከተማ በስተሰሜን ባለች በቅዱስ ወንጌላዊ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሥውር አኖሩዋቸው እስከ ሊቀ ጳጳሳት ቄርሎስ ዘመንም በዚያ ኖሩ።

የእግዚአብሔር መልአክም ለቅዱስ ቄርሎስ ተገለጸለት ወደ ወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያንም ሔዶ የቅዱሳን የአቡቂርንና የዮሐንስን ሥጋቸውን አውጥቶ እንዲሸከም አዘዘው። እርሱም ተነሥቶ ሔደ ከእርሱም ጋራ ብዙ ሕዝቦች ነበሩ በደረሱም ጊዜ ጸለዩ ምድሩንም ሲቆፍሩ ሥጋቸው በውስጡ ያለበት ቦታ ተገለጠላቸው በባሕር ዳርቻ ወደ አለች ወደ ሌላዪቱም የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ክብር የቅዱሳኑን ሥጋቸውን ተሸክመው አድርሰው በዚያ አኖሩ።

በዚያም ቤተ ክርስቲያን ሠሩላቸው በዚችም ቀን ታላቅ በዓል አደረጉ ከሥጋዎቻቸውም ድንቆች ተአምራት ተገለጡ አረማውያንም ተሰበሰቡ ይህንንም ድንቅ ተአምር በአዩ ጊዜ ጣዖቶቻቸውን ትተው ክርስቲያኖች ሆኑ። በዚያቺም የጣዖቶች ቤት አሸዋ በላይዋ ተከመረባት ታላቅ ኮረብታም ሆነ። የቅዱሳንም ሥጋቸው ታምራትንና ለበሽተኞች ታላቅ ፈውስን ያደርጋል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ነቢዩ_ሶፎንያስ

በዚህችም ቀን ደግሞ የአማርያ ልጅ፣ የሴዴቅያስ ልጅ፣ የጎዶልያ ልጅ፣ የኩሲ ልጅ የሶፎንያስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። እርሱም በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ዘመን ትንቢት ተናገረ። እንዲህም አለ እግዚአብሔር ከዚህ ዓለም ፈጽመው ይጠፋሉ አለ ከብቶችና ሰዎች ያልቃሉ። የባሕር ዓሣዎችና በሰማይ የሚበሩ አዕዋፍም ያልቃሉ።

ዳግመኛም ስለሞአብ እንዲህ አለ ስለዚህ ሞአብ እንደ ሰዶም ትሆናለች የአሞንም ልጆች እንደ ገሞራ ልጆች ይሆናሉ ደማስቆም እንደ እህል ታልቃለች። እርሱ እንደ ተነበየው እነዚያ አገሮች በናቡከደነጾር ምርኮ ይጠፋሉና።

ዳግመኛም ስለ ፋርስና ስለ ነነዌ ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ የፋርስን ሰዎች አጠፋቸዋለሁ ነነዌንም ፍርስራሽና ውኃ እንደሌለባት ምድረ በዳ አድርጋታለሁ መንጋዎችም በመካከሏ ይሠማሩባታል። ይህቺም ከተማ በመቄዶናዊው እስክንድር እጅ ጠፍታለች።

ዳግመኛም ስለ ክርስቶስ መምጣት እንዲህ ተናገረ። ያን ጊዜም ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ይጠራ ዘንድ በአንድ ሕግም ይገዙልኝ ዘንድ የአሕዛብን ሁሉ አንደበት ወደ ሕግ እመልሳለሁ። ደግሞም እንዲህ አለ ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ መሥዋዕቴን ያመጡልኛል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ደቂቀ_ነቢያት

ዳግመኛም በዚች ቀን ስለ ክርስቶስ ትንቢታቸውን እንደ ፈሳሽ ውኃ ያጐረፉ የዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት መታሰቢያቸው ነው።

ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነው፡፡ 12ቱ ቅዱሳን ደቂቀ ነቢያት የሚባሉት፡- ሆሴዕ፣ አሞጽ፣ ሚክያስ፣ ኢዩኤል፣ አብድዩ፣ ዮናስ፣ ናሆም፣ እንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ዘካርያስ እና ሚልክያስ ናቸው፡፡

ሌሎቹ ዋና (ዓበይት) ነቢያት የሚባሉት አራት ሲሆኑ እነርሱም ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ናቸው፡፡ ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ድረስ ያሉት ነቢያት ‹‹ደቂቀ ነቢያት›› የተባሉት ምክንያት አንድም የነቢያት ልጆች በመሆናቸው ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የጻፏቸው ትንቢቶቻቸው ዓበይት ነቢያቱ ከጻፏቸው ጋር በንፅፅር ሲታይ አነሥተኛ ስለሆነ ነው፡፡

'ነቢይ' ማለት እግዚአብሔር የመረጠውና የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ የሚያስተላልፍ ብሎም የተሠወረውንና የሚመጣውን ሁሉ በግልጽ የሚመለከት ማለት ነው፡፡ ነቢያት ሲባሉ በአጠቃላይ ምግባር ሃይማኖታቸው ያማረ፣ ትሩፋት ተጋድሎአቸው የሰመረ ነውና አካሄዳቸው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ነው፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ እና #ከገድላት_አንደበት)