መዝገበ ቅዱሳን
20.7K subscribers
1.92K photos
9 videos
6 files
24 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
#ጥቅምት_7

#አባ_ባውላ

ጥቅምት ሰባት በዚች ቀን ጠመው ከሚባል አገር የሆነ የከበረ አባት አባ ባውላ አረፈ።

ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ መስተጋድል መነኲሴ ሆነ የሚኖረውም በላይኛው ግብጽ በአለ በእንጽና ገዳም ነው ስሙ ሕዝቅኤል የሚባል ረድእ አለው። እርሱም ስለ ትሩፋቱና ስለ ተጋድሎው ምስክር ሆነ ይህ አባ ባውላ ስለ ክርስቶስ ፍቅር ራሱን ሰባት ጊዜ ገድሏልና።

#መጀመሪያው ራሱን በዕንጨት ላይ ዘቅዝቆ በመስቀል አርባ መዓልት አርባ ሌሊት እንደ ተሰቀለ ኖረ። ደሙም በአፍንጫው ፈሰሰ ነፍሱንም አሳለፈ እግዚአብሔርም ከሞት አነሣው።

#ሁለተኛው ዓሣዎችና ዓንበሪዎች እንዲበሉት ራሱን ከባሕር ጨመረ እነርሱ ግን አልነኩትም በባሕርም ሠጥሞ ብዙ ወራት ኑሮ ሞተ። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዳግመኛ ከሞት አስነሣው።

#ሦስተኛም ጊዜ ራሱን በአሸዋ ውስጥ ደፍኖ ሞተ ጌታችንም አስነሣው።

#አራተኛም በውስጡ ስለታሞች ድንጋዮች ካሉት ረጅም ተራራ ላይ ወጥቶ ራሱን ከተራራው ላይ ወደ ታች ወርውሮ ተንከባለለ የተሳሉ ደንጊያዎችም በሥጋው ሁሉ ገብተውበት ሞተ። ረድኡም ያለቅስለት ነበረ ጌታችንም መጥቶ ከሞት አሥነሣው አጽናናውም ።

#አምስተኛ ከረጅም ዛፍ ላይ ወጥቶ ከስለታም ደንጊያ ላይ ራሱን ወረወረ ከሁለትም ተከፈለና ሞተ ያን ጊዜም ጌታችን አስነሣው።

#ስድስተኛ ራሱን በእግሮቹ ውስጥ አሥሮ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት እንዲህ ሁኖ ሞተ እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ ከሞት አነሣው አጽናናውም።

#ሰባተኛ ከውኃ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ እጆቹን ዘርግቶ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት በመቆም ሞተ ክብር ይግባውና ጌታችንም አስነሣው እንዲህም ብሎ አጽናናው ወዳጄ ባውላ ሆይ ራስህን ሰባት ጊዜ እስከምትገድል ድረስ ሰውነትህን አደከምክ እንግዲህ ድካምህ ይብቃህ።

አባ ባውላም ለመድኃኒታችን እንዲህ ብሎ መለሰለት ጌታዬ ሆይ ስለ ከበረው ስምህ እደክም ዘንድ ተወኝ አንተ አምላክ ስትሆን ስለኛ በመከራ ደክመህ ስለ ሰው ወገን ሞትክ ለእኛ ይህ አይገባንም ነበር በቸርነትህ ይህን የማዳንህን ሥራ ሠራህልን እንጂ። ጌታችንም ከአጽናናው በኋላ ከእርሱ ወደ ሰማይ ወጣ።

ከዚህም በኋላ አባ ብሶይ ወደ እንጽና ገዳም ሒዶ ከአባ ባውላ ጋር ተገናኘ ጌታችንም ለአባ ባውላ ተገልጾለት ሥጋህ ከአባ ብሶይ ሥጋ ጋር በአንድነት ይኑር አለው ሁለቱም በአረፉ ጊዜ ሥጋቸውን በአንድነት አኖሩ።

ወገኖቹም የአባ ብሶይን ሥጋ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሊወስዱ በወደዱ ጊዜ በመርከብ ጫኑት መርከቢቱ ግን መንቀሳቀስን እምቢ አለች። ከዚህም በኋላ ተመልሰው የአባ ባውላን ሥጋ አምጥተው በመርከብ ላይ ጫኑት ያን ጊዜ መርከቢቱ ተጓዘች። እንዲህም የቅዱሳኑን ሥጋቸውን ወደ አስቄጥስ ገዳም አድርሰው በአባ ብሶይ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአንድነት አኖሩ እስከ ዛሬም በዚያ ይኖራሉ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት)