መዝገበ ቅዱሳን
20.7K subscribers
1.92K photos
9 videos
6 files
24 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
#መስከረም_12

መስከረም ዐሥራ ሁለት መላእክት አለቃ #የቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #ጉባኤ_ኤፌሶን የቅዱሳን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ ሆነ

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሚካኤል

መስከረም ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

በዚችም ቀን ክብር ይግባውና እግዚአብሔር ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢይ ኢሳይያስ ላከው ይቅርም ብሎት ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስ ሒዶ እግዚአብሔር ይቅር እንዳለውና ከደዌው እንዳዳነው በዕድሜውም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እንደ ጨመረለት ይነግረው ዘንድ አዘዘው። ንጉሱም ሚስት አግብቶ ምናሴን እስከወለደው ድረስ እንዲሁ ሆነ።

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ለንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገለት ተአምር፡-

ከጻድቁ ንጉሥ ከቅዱስ ዳዊት በኋላ በእስራኤል እንደ ሕዝቅያስ ያለ ሌላ ጻድቅ ንጉሥ አልተነሣም፡፡ ከሕዝቅያስ በኋላ የተነሡት ሁሉም ጣዖትን አምልከዋል፣ ለጣዖታቱም የሚሆን መሠዊያ ሠርተዋል፡፡ ንጉሡ ሕዝቅያስ በነገሠ ጊዜ ግን ጣዖታትን ሰባብሯቸዋል፣ የእስራኤል ልጆች ያመልኩት የነበረውን የነሐስ እባብ ቆራርጦታል፡፡ እግዚአብሔርንም በማመኑ መንግሥቱ እጅግ ሰምሮለታል፡፡ እግዚአብሔርም ያሳጣው በጎ ነገርም የለም፡፡

ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዘመን የፋርሱ ነጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ኢየሩሳሌምን ከበባት፡፡ ይህም ሰናክሬም በወቅቱ እንደ እርሱ ያለ ኃይለኛ የለም ነበርና ሁሉም የምድር ነገሥታት ይፈሩትና ይገዙለት ነበር፡፡ ሕዝቅያስም ከሰናክሬም ግርማና የጦሩ ብዛት የተነሣ ፈርቶ ኢየሩሳሌምን እንዳያጠፋት ብዙ ወርቅና ብር እጅ መንሻ ቢልክለትም ሰናክሬም ግን እጅ መንሻውን አልቀበልም ብሎ ኢየሩሳሌምን ያጠፋ ዘንድ ተነሣ፡፡ ለሕዝቅያስም ‹‹አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእኔ እጅ ሊያደናችሁ ከቶ አይችልም›› የሚል የስድብን ቃል ላከለት፡፡

ሁለተኛም በልዑል እግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል ጽፎ ደብዳቤ ላከለት፡፡ ሕዝቅያስም ይህን ሲሰማ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ አለቀሰ፡፡ ልብሱንም ቀዶ ማቅ በመልበስ የሰናክሬምን ድፍረትና በኢየሩሳሌምና በሕዝቧ ላይ ሊያደርስ ያሰበውንም ጥፋት ወደ እግዚአብሔር አሳሰበ፡፡ ቀጥሎም ሕዝቅያስ ሰናክሬም የተናገረውን ይነግሩት ዘንድ ስለ ሕዝቡም እንዲጸልይ ለነቢዩ ኢሳይያስ መልእክት ላከበት፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ እግዚአብሔር አመለከተ፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ስለ ንጉሡ ለነቢዩ መልእክትን አመጣለት፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም የመጣለትን መልስ እንዲህ ብሎ ለሕዝቅያስ ላከለት፡- ‹‹ልብህን አጽና፣ አትፍራ፡፡ በዓለሙ ሁሉ እንደ እርሱ ያለ ያልተሰማ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥራ በሰናክሬም ላይ እግዚአብሔር ይሠራል›› አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ መጥቶ 185,000 (መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ) የፋርስ ሠራዊቶችን በአንድ ሌሊት ገደላቸው፡፡ 2ኛ ነገ 17፣19፡፡ የለኪሶ ሰዎችም ሲነጋ በተነሡ ጊዜ ምድሪቱን በእሬሳ ተሞልታ ስላገኟት በድንጋጤና በፍርሃት ከንጉሣ ጋር ሸሽተው ነነዌ አገር ገቡ፡፡

ንጉሡ ሰናክሬምም ወደ አምላኩ ወደ ጣዖቱ ቤት ገብቶ ሲጸልይ የገዛ ልጆቹ በሰይፍ መትተው ገደሉትና ወደ አራራት ኩበለሉ፡፡2ኛ ነገ ምዕራፍ 19፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስም ከሰናክሬም እጅ ያዳነውን እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡

ከዚህም በኋላ ሕዝቅያስ ታሞ ለሞት በደረሰ ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ ‹‹እግዚአብሔር ‹ትሞታለህ እንጂ አትድንም› ብሎሃል›› አለው፡፡ ነገር ግን ሕዝቅያስ አሁንም ልብሱንም ቀዶ ማቅ በመልበስ ጸሎቱን ወደ እግዚአብሔር አቀረበ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ቅዱስ ሚካኤል እግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ መጥቶ ነቢዩ ኢሳይያስን ወደ ንጉሡ ሕዝቅያስ ሄዶ በዕድሜው ላይ 15 ዓመት እንደተጨመረለት እንዲነግረው ያዘዘው፡፡

መልአኩ እንዳዘዘው ነቢዩ ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስን "እግዚአብሔር የአባትህ የዳዊት አምላክ ጸሎትህን ሰማሁ፣ ዕንባህንም አየሁ፣ እነሆ እኔ አድንሃለሁ፡፡ በዘመኖችህም 15 ዓመት ጨምሬልሃለሁ፡፡ ከፋርስ ንጉሥ እጅም አድንሃለሁ፡፡ ይህችን አገር ስለ እኔና ስለ ባለሟሌ ዳዊት አጽንቼ እጠብቃታለሁ›› ብሎሃል ብሎ የተላከውን ነገረው፡፡ ከዚህም በኃላ ንጉሥ ሕዝቅያስ የእግዚአብሔር ኃይል ስላደረበት የምድር ነገሥታት ሁሉ ፈርተውት እየተገዙለት እጅ መንሻን ያገቡለት ጀመር፡፡ ንጉሡም ዕድሜው ከተጨመረለት በኃላ ሚስት አግብቶ ምናሴን እስኪወልድ ድረስ ቆየ፡፡ በመንበረ መንግሥቱም 29 ዓመት ነግሦ ከኖረ በኋላ እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም ዐረፈ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጉባኤ_ኤፌሶን

በዚችም ቀን ደግሞ በኤፌሶን ከተማ የቅዱሳን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ ሆነ ይህም ለታላላቆች ጉባኤያት ሦስተኛ ነው።

ስብሰባቸውም የተደረገው የታላቁ ቴዎዶስዮስ ልጅ አርቃድዮስ የወለደው ታናሹ ቴዎዶስዮስ በነገሠ በሃያ ዓመት ነው። የስብሰባቸውም ምክንያት የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በንስጡር ነው ። እርሱ ስቶ እንዲህ ብሏልና እመቤታችን ድንግል ማርያም አምላክን በሥጋ አልወለደችውም እርሷ ዕሩቅ ሰውን ወልዳ ከዚህ በኋላ በውስጡ የእግዚአብሔር ልጅ አደረበት ከሥጋ ጋር በመዋሐድ አንድ አልሆነም በፈቃድ አደረበት እንጂ። ስለዚህም ክርስቶስ ሁለት ጠባይ ሁለት ባህርይ አሉት የተረገመ የከሐዲ ንስጡር የከፋች ሃይማኖቱ ይቺ ናት።

ስለ እርሱም የተሰበሰቡ እሊህ አባቶች ከእርሱ ጋር ተከራከሩ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው አምላክ እንደሆነ ገብርኤል መልአክ በአበሠራት ጊዜ ከተናገረው ቃል ምስክር አመጡ ። እንዲህ የሚል እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው ከአንቺ የሚወለደውም ጽኑዕ ከሀሊ ነው የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል ።

ዳግመኛም እነሆ ድንግል በድንግልና ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች ብሎ በትንቢቱ ከተናገረው ከኢሳይያስ ቃል ሁለተኛም ከእሴይ ዘር ይተካል ከእርሱም ለአሕዛብ ተስፋቸው ይሆናል።

ዳግመኛም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ ገሠጸው መከረው ስለዚህም እንዲህ ሲል አስረዳው ክብር ይግባውና የክርስቶስ የመለኮቱና የትስብእቱ ባሕርያት በመዋሐድ አንድ ከሆኑ በኋላ አይለያዩም አንድ ባሕርይ በመሆን ጸንተው ይኖራሉ እንዲህም አምነን ሰው የሆነ እግዚአብሔር ቃል አንዲት ባሕርይ ነው እንላለን።

ከሀዲ ንስጥሮስ ግን ከክፉ ሐሳቡ አልተመለሰም ከሹመቱም ሽረው እንደሚአሳድዱትም ነገሩት። እርሱ ግን የጉባኤውን አንድነት አልሰማም ስለዚህም ከሹመቱ ሽረው ረግመው ከቤተ ክርስቲያን ለይተው አሳደዱት ወደ ላይኛውም ግብጽ ሒዶ በዚያ ምላሱ ተጎልጒሎ እንደ ውሻ እያለከለከ በክፉ አሟሟት ሞተ።

እሊህም ሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት አባቶች ሃይማኖትን አጸኑዋት በዚህም ጉባኤ ውስጥ እንዲህ ብለው ጻፉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእርሷ ሰው የሆነውን የእግዚአብሔርን አካላዊ ቃል በሥጋ ወለደችው።

ከዚህም በኋላ ሥርዓትን ሠርተው ሕግንም አግገው በእጆቻቸው ጽፈው ለምእመናን ሰጡ። እኛም የሕይወትንና የድኅነትን መንገድ ይመራን ዘንድ እግዚአብሔርን እንለምነው። ለእርሱም ክብር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረ መልአክ በቅዱስ ሚካኤል እንዲሁም በከበሩ ቅዱሳን አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም እና #ከገድላት_አንደበት)